ሩቫራሺ ታካማሃንያ
የምስሉ መግለጫ,ሩቫራሺ ታካማሃንያ

ከ 4 ሰአት በፊት

የ11 ዓመት ልጃቸውን በመኪና የገጨው አሜሪካዊ ዲፕሎማት ይቅርታ እንዲጠይቃቸው ቤተሰቦቿ ተማፀኑ።

ልጃቸውን አሜሪካዊው ዲፕሎማት እንደገጨ ይታመናል። ቤተሰቦቿም ዲፕሎማቱ ወደ ዚምባብዌ ተመልሶ በአካል ይቅርታ እንዲላቸው ጠይቀዋል።

ዲፕሎማቱ ያለመከሰስ መብት እንዳለው ቢያውቁም ቤተሰቡን ይቅርታ ማለት እንዳለበት ተናግረዋል።

ሩቫራሺ ታካማሃንያ የተባለችው ታዳጊ በዲማ ከተማ ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ሳለ ዲፕሎማቱ እየነዳው በነበረ መኪና መገጨቷ ይታመናል።

ዲፕሎማቱ ይቅርታ ቢጠይቅ በልጃቸው ሞት ከደረሰባቸው ሐዘንና ስብራት ለማገገም እንደሚረዳቸው ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

በሀራሬ የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ “ለቤተሰቦቹ መጽናናትን እንመኛለን” ብለዋል።

ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር እየተባበሩ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኤምባሲው “አደጋው የፈጠረውን ሐዘን እንገነዘባለን” ብሏል።

ሩቫራሺ ታካማሃንያ ከጓደኛዋ ጋር ሰኞ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት እየሄደች ነበር። አስፋልት ስትሻገር ነበር በመኪናው የተገጨችው።

እናቷ ጁሊያና ቪቶ ስለ አደጋው የሰማችው ከጎረቤቶቿ ነበር። እየሮጠች ወደ ቦታው ደርሳለች።

“ትነቃለች ብዬ እየጠበቅኩ ነበር። አሁንም ድረስ ሕልም ነው የሚመስለኝ። በጣም ነው የተጎዳሁት” ብላለች የ24 ዓመቷ እናት።

አደጋው የደረሰበት ቦታ ስትደርስ አሽከርካሪው እንዳልነበር ተናግራለች። እስካሁን ለቤተሰቡ ምንም እንዳላለም ገልጻለች።

የሥራ ባልደረቦቹ በሱ ስም ይቅርታ እንደጠየቁና አካባቢውን ጥሎ የሄደው በአደጋው “በደረሰበት ጫና” እንደሆነ መግለጻቸውን እናትየው ተናግራለች።

“ፀፀት የተሰማው አልመሰለኝም። እኔ ጋር ቀጥታ መጥቶ የልቤን ብነግረው እመርጣለሁ” ብላለች።

የታዳጊዋ አባት ሲልቨስተር ታካሀማያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለቀብር ማስፈፀሚያ 2,000 ዶላር እንደሰጣቸው ተናግረዋል።

የኤምባሲው ቃል አቀባይ እንዳሉት “የልጅቷን ቤተሰብ እየደገፉ” ሲሆን፣ የኤምባሲው ተወካይ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ።

ሆኖም ግን ቤተሰቡ በሐዘናቸው ወቅት ችላ እንደተባሉ ይሰማቸዋል።

“ጠንካራ ለመሆን እየሞከርን ነው” ብለዋል አባትየው።

የታዳጊዋ ስም ትርጓሜ ‘የፈጣሪ አበባ’ ማለት ነው። ልጃቸው ልክ እንደ ስሟ እንደነበረች ቤተሰቦቿ ተናግረዋል።

ደግ፣ ጎበዝና ተወዳጅ ልጅ እንደነበረች ገልጸዋል።

“ሰዎች ሁሌም ይደነቁባት ነበር” ስትል እናቷ በኩራት ተናግራለች።

ታዳጊዋን የገጨው ዲፕሎማት አሁን ማረፍ እንደሚፈልግና ከመርማሪዎቹ ጋር እንደሚገናኝ እንደገለጸ የፖሊስ ቃል አቀባይ ፖል ኒያቲ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ዲፕሎማቱ ዚምባብዌን ለቆ በመውጣቱ ምርመራው እንደቆመ ተናግረዋል።

የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ጆርጅ ቻራምባ በክስተቱ ቁጣቸውን ግለጸዋል።

“ዲፕሎማት ሕይወት የቀጠፈ የመኪና አደጋ አድርሶ በሱ አገር ብቻ የሚገኝ የሚመስለውን የሥነ ልቦና ድጋፍ ለማግኘት በሚል ከፖሊስ ሲሸሽ ዲፕሎማት ሳይሆን ወንጀለኛ ይባላል” ብለዋል።

ሩቫራሺ ታካማሃንያ

የመንግሥት ቃል አቀባይ ኒክ ምናንግዋና በበኩላቸው የዲፕሎማት ያለመከሰስ መብት “መብትም ግዴታም ያለው ነው” ብለዋል።

“የተከሰተው አሳዛኝ አደጋ ቢሆንም ኃላፊነት ወስዶ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ፣ ከቤተሰቡ ጎን መቆምና የአገሪቱን ሕግ ማክበር ግዴታ ነው” በማለት አክለዋል።

“ይህ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማሻከር የለበትም። ዲፕሎማቱ ዜጋችንን ለመግደል አቅዶ ነበር አንልም። የተከሰተው አደጋ ነው” ሲሉም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ምርመራው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ከፖሊስ ጋር እንደሚተባበሩ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቋል።

የታዳጊዋ እናት እና አባት ለልጃቸው ትልቅ ተስፋ ነበራቸው።

“ትምህርት በጣም ትወድ ነበር። የበረራ አስተናጋጅ መሆን ነበር ሕልሟ” ብለዋል አባትየው።

እናቷም በልጃቸው ሕልም ደስተኛ ነበረች።

“አሁንም መሞቷን አላመንኩም። ብቸኛ ልጄ ነበረች። አንድ ቀን ትጦረኛለች ብዬ አስብ ነበር። ዝም ብዬ እየኖርኩ ነው እንጂ ሕይወቴም ተስፋዬም ተቀጥፏል። በእያንዳንዱ ቀን እየሞትኩ ነው” ብላለች።

ልጇን እንደ ቅርብ ጓደኛዋ ታያት እንደነበር ተናግራለች። ጤናዋ እየደከመ ስለመጣ ልጇ ታግዛት ነበር።

የገንዘብ ካሳ ኑሯቸውን ቢደግፍም የታዳጊዋ ወላጆች ከምንም በላይ የሚፈልጉት ልጃቸውን የገደለው ሰው በአካል ምን እንደተፈጠረ ቢያስረዳቸው ነው።

“ተመልሶ መጥቶ ይቅርታ ማለት አለበት” ብለዋል አባትየው።