ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና

ከ 4 ሰአት በፊት

በህዝባዊ ተቃውሞ ከአገር የኮበለሉት የባንግላዴሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሃሲና ምርጫ ሲታወጅ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ልጃቸው ሳጂብ ዋዜድ ጆይ ተናገረ።

አድሏዊ በተባለ የመንግሥት የስራ ቅጥር ኮታ ጋር ተያይዞ በተነሳው የተማሪዎች ተቃውሞን ተከትሎ በተነሳው ከፍተኛ ሁከት የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ስልጣን ለቀው ወደ ህንድ ኮብልለዋል።

ለሳምንታት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ከ500 በላይ ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን የባንግላዴሽ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ባንግላዴሽ ነጻነቷን ለማረጋገጥ ከአውሮፓውያኑ 1971 ካደረገችው ጦርነት በኋላ ያጋጠማት ነው በተባለው በዚህ ተቃውሞ እና ሁከት ከተገደሉት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።

“እርግጥ ነው ወደ ባንግላዴሽ ትመለሳለች” ሲል ልጃቸው የተናገረ ሲሆን እናታቸው ስልጣኑን የተረከበው ጊዜያዊ መንግሥት ምርጫውን ለማድረግ ከወሰነ በኋላ እንደሚመለሱ ተናግሯል።

በጦሩ የሚደገፈው ጊዜያዊ መንግሥትን የኖቤል ተሸላሚው መሐመድ ዩኑስ የሚመሩት ሲሆን ከ16 አማካሪዎች ጋር ሐሙስ ዕለት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል።

ሁለት የተማሪ ተቃዋሚ አመራሪዎች ከአማካሪዎቹ መካከል ይገኙበታል።

በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ባለሙያ የሆኑት ልጃቸው ዋዜድ እናታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት አስራ አምስት ዓመታትም የአይቲ አማካሪ ሆኖ ሰርቷል።

“በእርግጥ ወደ አገሯ ትመለሳለች። ወደ ፓለቲካ ተመልሳ ትገባለች ወይ የሚለው አልተወሰነም። ህዝቡ ባደረገባት ነገር ተሰላችታለች” ብሏል።

ለሳምንታት የዘለቀው የተማሪዎች ተቃውሞ ሕዝባዊ ገጽታን ይዞ ከአድሏዊ አሠራር ባለፈ መልኩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን እንዲለቁ የሚጠይቅ ሆኖ ነበር።

ምርጫ ሲካሄድ የሼክ ሃሲና ፖለቲካ ፓርቲ የሆነው አዋሚ አሸናፊ እንደሚሆን ልጃቸው እርግጠኛ ነው።

“ዛሬ በባንግላዴሽ ነጻ፣ ፍትሃዊ እና አሳታፊ ምርጫ ቢደረግ አዋሚ ሊግ ፓርቲ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ነኝ” ብሏል።

የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዘንድሮው ዓመት ጥር ወር በተደረገው አወዛጋቢ ምርጫ ለአራተኛ የስልጣን ዘመን አሸናፊ ሆነው ነበር።