አልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኔ ኸሊፍ

ከ 4 ሰአት በፊት

በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ ከፍተኛ ውዝግብን ያስተናገደችው አልጄሪያዊቷ ቦክሰኛ ኢማኔ ኸሊፍ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነች።

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የሴቶች የዓለም ቦክስ ሻምፒዮና ላይ የጾታ ብቃት መመዘኛ ፈተናዎች አላለፉም በሚል ከታይዋኗ ቦክሰኛ ሊን ዩ ቲንግ ጋር በውድድሩ እንዲታገዱ ከመደረጋቸው ጋር ተያይዞ በፓሪስ ኦሎምፒክስ መወዛገቢያ ሆነው ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ዘረኛ እና ጾተኛ የሆኑ ዘለፋዎችን ያስተናገደችው ኢማኔ ኸሊፍ ቻይናዊቷን የዓለም ሻምፒዮን ያንግ ሊዪን በ66 ኪሎግራም ክብደት ምድብ በመርታት አሸናፊ ሆናለች።

የ25 ዓመቷ ኢማኔ በፍልሚያው የበላይነትን ካሳየች በኋላ አልጄሪያውያን ደጋፊዎች አረንጓዴ፣ ነጭ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማቸውን እያውለበለቡ በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

ኢማኔ ማሸነፏን ስታውቅ የቦክስ መድረኩ ላይ በመደነስ ደስታዋን ስትገልጽ የታየች ሲሆን ከተፋላሚዋ ጋርም ሞቅ ባለ ሁኔታ ነው ተቃቅፈው የተለያዩት።

“ማሸነፍ ሕልሜ ነው። በጣም ደስተኛ ነኝ። በጣም አስገራሚ ነው እንዲሁም አስደናቂ” ስትል ኢማኔ ኸሊፍ ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“የስምንት ዓመታት ትግል፣ እንቅልፍ አልነበረኝም። የአልጄሪያ ህዝብን በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ” ብላለች።

“ባሳየሁት ብቃት በጣም ደስተኛ ነኝ። ጠንካራ ሴት ነኝ” ስትልም ገልጻለች።

የማሸነፍ ውጤቷ ሲረጋገጥ ተፋላሚዋ ያንግ የኢማኔን እጅ አየር ላይ ከፍ አድርጋም የታየች ሲሆን አሰልጣኝዋ ትከሻ ላይ ታዝላ በደስታ በተሞላው መድረክ ስትዞር ነበር።

ከኢማኔ ኸሊፍ ጋር በኦሊምፒክስ መክፈቻው የቦክስ ፍልሚያ በ46 ሰኮንዶች ውስጥ ግጥሚያውን አቋርጣ የወጣችው እና የተረታችው ጣሊያናዊቷ ካሪኒ የኢማኔን እጅ አልጨብጥም ማለቷ ይታወሳል።

ኢማኔ ሜዳሊያዋን ስታጠልቅ በርካቶች ያጨበጨቡላት ሲሆን የአልጄሪያ ብሔራዊ መዝሙር ሲጫወትም እንባዋን ስታነባም ታይቷል።

በዓለም የዓለም ቦክስ ሻምፒዮና ባለፈው ዓመት ታግዳ የነበረችው ሌላኛዋ ቦክሰኛ ሊን ዩ ቲንግ ዛሬ፣ ነሐሴ 4/ 2016 ዓ.ም በፍጻሜ የቦክስ ውድድር ትፋለማለች።