
ከ 4 ሰአት በፊት
በብራዚል፣ ሳዎ ፖሎ ግዛት በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ሳቢያ 61 ሰዎች ሞቱ።
ካስካቫል ከተባለ አካባቢ ወደ ሳዎ ፖሎ ጉአርሎስ አውሮፕላን ማረፊያ እየተጓዘ ነበር።
የተከሰከሰው ቪንሄዶ የተባለ ከተማ ውስጥ እንደሆነ አየር መንገዱ አስታውቋል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አውሮፕላኑ ወደ መሬት ሲምዘገዘግ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ወጥተዋል።
ኤቲአር 72-500 አውሮፕላኑ 57 ተሳፋሪዎችና 4 የበረራ ሠራተኞች ይዞ ነበር። በሕይወት የተረፈ ሰው የለም።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ለሟቾች ወዳጆችና ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸዋል።
የሳዎ ፖሎ አገረ ገዢ ታራሲሶ ጎሜዝ ደ ፍሬቲያስ ለሦስት ቀናት ሐዘን አውጀዋል።
የአውሮፕላኑን ጉዞ የሚመዘግበው መሣሪያ መገኘቱ ተገልጿል። አውሮፕላኑን የሠራው የፈረንሳይና ጣልያን ጥምር ተቋም ኤቲአር በምርመራው እንደሚሳተፍ አስታውቋል።
አውሮፕላኑ የወደቀው መኖሪያ ሰፈር ቢሆንም በአካባቢው የተጎዳ ሰው የለም። ከኮንዶሚንየም ሕንጻ አንድ ቤት ብቻ ጉዳት ደርሶበታል።
አውሮፕላኑ ሲቀጣጠል በቪድዮ ታይቷል። ፖሊሶችና እሳት አደጋ ተከላካዮች በቦታው ደርሰዋል።
ፍላይትራዳር24 የተባለው በረራዎችን የሚከታተለው በይነ መረብ እንዳለው አውሮፕላኑ ከካስቫካል ከተነሳ በኋላ ያለበትን ማወቅ የተቻለው ከአንድ ሰዓት ተኩል በኋላ ነው።
የብራዚል ሲቪል አቭየሽን ባለሥልጣን፣ እአአ በ2010 የተገነባው አውሮፕላን “በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝና ተገቢው ሰርተፍኬት ያለው” እንደሆነ ገልጿል።
- ከ5500 በላይ ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፤ አብዛኞቹ በአማራ ክልል ያሉ ናቸውከ 5 ሰአት በፊት
- ዩክሬን በሩሲያ ላይ የፈጸመችው ያልታሰበ ወረራ የፈጠረው ድንጋጤከ 5 ሰአት በፊት
- ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገብ እንጂ የቀድሞው ህልውናው እንደማይመለስለት ምርጫ ቦርድ አስታወቀ9 ነሐሴ 2024
አራቱ የበረራ ሠራተኞችም በሙያቸው ብቁ እንደሆኑ አክሏል።
የዩፔካን ካንሰር ሆስፒታል ለቢቢሲ እንደገለጸው ከሞቱት መካከል ሁለቱ የተቋሙ ሠልጣኝ ሐኪሞች ናቸው።
አውሮፕላኑ ሲከሰከስ በመስኮቱ የተመለከተው ፊሊፔ ማጋሊስ ለሮይተርስ “ሲከሰከስ ከቤቴ መስኮት አይቻለሁ። በጣም ነው የደነገጥኩት” ብሏል።
ናላቲ ሲያሪ የተባለች ሌላ ነዋሪ ለሲኤንኤን እንደተናገረችው ምሳ እየበላች ሳለ ከፍተኛ ደምጽ ሰምታለች።
“በረንዳ ላይ ስወጣ አውሮፕላኑ እየተሽከረከረ ነበር። ያልተለመደ መሆኑን ወዲያው አወቅኩ ” ብላለች።
በብራዚል በ2007 ከደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በኋላ ይህ አደጋ የከፋው ነው።
በወቅቱ 199 ሰዎች ነበሩ በሳዎ ፖሎ የሞቱት።
ፕሬዝዳንት ሉላ አደጋው የደረሰበትን አካባቢ ሲጎበኙ “መጥፎ ዜና በመናገሬ አዝናለሁ። ሁላችንም የሕሊና ፀሎት እናድርግላቸው” ብለዋል።
በአደጋው “በጣም ማዘናቸውን” ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጽፈዋል።
በአቅራቢያው ካው ቫሊሆንስ ከተማ 20 የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ተልከዋል።
ኤቲአር ከአደጋው በኋላ ባወጣው መግለጫ “መጀመሪያ በአደጋው ለተጎዱ ሰዎች ሐዘናችንን መግለጽ እንፈልጋለን። በምርመራው ሙሉ በሙሉ እንሳተፋለን” ብሏል።