
ከ 5 ሰአት በፊት
ዩክሬን ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ሩሲያ የኩርስክ ግዛት ዘልቃ በመግባት የፈጸመችውን ድንገተኛ ወረራ ተከትሎ ሁለቱ አገራት የገቡበት ከባድ ውጊያ አምስተኛውን ቀን ይዟል።
በዓለማችን ትልቁ የሚባለው የኒውክሌር ጣቢያ በሚገኝበት በኩርስክ ግዛቷ ያልተጠበቀ ጥቃት የገጠማት ሩሲያ የአስቸኳይ ጊዜ ከማወጅ በተጨማሪ ተጠባባቂ ጦሯንም ጠርታለች።
ሁለቱ አገራት በድንበራቸው ላይ እያደረጉት ያለው ውጊያ የተፋፋመ ሲሆን፣ ሩሲያ ይህንን ለመመከት ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ስፍራው እየላከች ትገኛለች።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር “የሩሲያን ግዛት ለመውረር የሞከሩ የዩክሬን ታጣቂ ኃይሎችን” እየተፋለመ መሆኑን አስታውቋል።
ሩሲያ ጠላት ባለችው ኃይል የተፈጸመባትን የወረራ ሙከራ ለማክሸፍም የአየር እና የመሬት ኃይሏን አቀናጅታ እየተጠቀመች መሆኑንም ገልጻለች።
የሁለቱ አገራት ጦርነት ከተጀመረበት ወቅት በተለየ ከፍተኛ እና ያልተጠበቀ ነው የተባለው የማክሰኞ፣ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. የዩክሬን ጥቃት ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች የተሳተፉበት ነው።
የዩክሬን ምንጮች ጥቃቱ ከኩርስክ ጋር በሚዋሰነው ሰሜናዊ የዩክሬኗ ግዛት ሰሚ ላይ ሩሲያ ካቀደችው የወረራ ጥቃት በፊት የተፈጸመ “ቀዳሚ መብረቃዊ ጥቃት” ነው ማለታቸው ተዘግቧል።
የዩክሬን ወታደሮች ወደ ምዕራብ ሩሲያ ዘልቀው መግባታቸው ሞስኮን ከማስደንገጥ በተጨማሪ፣ የድንበር መከላከያዋ ደካማ መሆኑን ያሳየ እንዲሁም ወደ አውሮፓ በሚቀርበው የተፈጥሮ ጋዝ መስመር ላይ አደጋ የደቀነ ተብሏል።
ኪዬቭ ማክሰኞ ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በማሰማራት፣ በታጠቁ ተሽካርካሪዎች፣ በከባድ መሳሪያዎች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በመታገዝ ነበር ወደ ሩሲያዋ ኩርስክ ዘልቃ የገባችው።
ባለፈው ዓመት እንዲሁ የኩርስክን ግዛት እና አጎራባችዋን ቤልጎሮድን ለዩክሬን ወግነው እየተዋጉ ያሉ ሩሲያውያን አጠር ላለ ጊዜ ወረራ ፈጽመውባት ነበር።
ማክሰኞ ማለዳ የዩክሬን ኃይሎች የሩሲያን ድንበር አቋርጠው 5 ሺህ ነዋሪዎች ወዳሉባት ሱድዛ ከተማ ገቡ።
ሱድዛ የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ በዩክሬን በኩል ወደ አውሮፓ የሚደርስባት ብቸኛዋ የመተላለፊያ ጣቢያ እና ቁልፍ የምትባል ስፍራ ናት።
- ለ100 ዓመት የሌኒን አስክሬን እንዴት ተጠብቆ ቆየ? 5 ነጥቦች ስለሌኒን የመታሰቢያ ስፍራ4 ነሐሴ 2024
- ቫግነር ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ማሊ ከዩክሬን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች5 ነሐሴ 2024
- ዩክሬን ወደ ሩሲያ ዘልቃ ጥቃት በመፈጸሟ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ8 ነሐሴ 2024

ሁለቱ አገራት ደም አፋሳሽ ጦርነት ላይ ቢሆኑም ዩክሬን በሶቪየት ዘመን የነበረውን የጋዝ ቧንቧ ለሩሲያው ጋዝፕሮም በዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር ክፍያ እንዳከራየችው ነው።
የጋዝ ማጓጓዙ ስምምነት የአሁኑ የዩክሬን ወረራ ካላቆመው በመጪው ጥር ወር ይጠናቀቃል።
በዓለማችን እጅግ ዕድሜ ጠገብ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የኑክሌር የኃይል ማመመንጫ ጣቢያ ከሱድዛ በ70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኩርቻቶቭ ከተማ ወረራ በተፈጸመባት ኩርስክ ግዛት ነው የሚገኘው።
የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) በኩርቻቶቭ የታዩ ሲሆን፣ አንዳንድ ተንታኞች ሩሲያ የዩክሬን የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠረችበትን መንገድ በመከተል ኪዬቭም የሩሲያን የኃይል አቅርቦት መምታት ትፈልጋለች ብለዋል።
ረቡዕ ከሰዓት በኋላ የዩክሬን ወታደሮች ሱድዛን በመክበብ ሦስት መንደሮችን መያዛቸውን እና በአስር መንደሮች መታየታቸውን የሩሲያ ባለሥልጣናት እንዲሁም ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በዚህም ቢያንስ ሦስት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም 24 ሰዎች መቁሰላቸውን የጤና ባለሙያዎች መናገራቸው ተዘግቧል።
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወረራውን “በኪዬቭ አገዛዝ የተደረገ ፍጹም ትንኮሳ” ሲሉ የጠሩት ሲሆን፣ የዩክሬን ወታደሮች መኖሪያ አካባቢዎች እና ሰላማዊ ሰዎችን ባልለየ መልኩ ጥቃት ፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል።
የሞስኮ መከላከያ ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት 260 የዩክሬን ወታደሮች እንደተገደሉ፣ እንዲሁም ሰባት ታንኮች፣ 42 የታጠቁ ተሽከርካሪዎች፣ ሁለት የአየር መከላከያዎች እንዲሁም የሬድዮ ሳተላይት መቃወሚያ ማውደሙን አስታውቋል።
ዩክሬን በበኩሏ ከሩሲያ በኩል የተቃጡባትን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ማክሸፏን አስታውቃለች።
የዩክሬን አየር ኃይል አዛዥ እንዳሉት ሐሙስ ሌሊቱን 27 ያህል የድሮኖች ጥቃት በሩሲያ እንደተሰነዘረባቸው አስታውቀው ሁሉንም ተኩሰን ጥለናቸዋል ብለዋል።
ዩክሬን የአየር መቃወሚያ፣ ፀረ ሚሳኤል እና የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎችን በመጠቀም በኪዬቭ ፖልታሳ፣ ዶኔትስክ እና ሌሎች ግዛቶች ላይ የተደረገውን የሩሲያ የድሮን ጥቃት ተኩሰው መጣላቸውን አዛዡ አስረድተዋል።
በዚህ የሩሲያ የድሮን ጥቃትም ጥቅም ላይ የዋሉት የኢራን ስሪት የሆኑት ሻሂድ 136 እና 131 ሞዴሎች መሆናቸውንም አክለዋል።
አርብ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የዩክሬንን ጥቃት ለመከላከል ተጨማሪ ወታደሮች እና የጦር መሳሪያዎች ወደ ኩርስክ ግዛት እያጓጓዘ መሆኑን ገልጿል።
ሩሲያ “ቢኤም-21 ግራድ” የተሰኙ ባለ ብዙ ሮኬት ማስወንጨፊያዎች፣ ከባድ የአየር መከላከያ መሳሪያዎች፣ ታንኮችን ጨምሮ በርካታ ወታደሮችን ወደ ኩርስክ ግዛት እያሰማራች ነው ሲል የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ መንግሥታዊው ሚዲያ ታስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
መከላከያ ሚኒስቴሩ ባለፉት 24 ሰዓታት ከ280 በላይ የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የዩክሬን ወታደሮች ወደ ሩሲያ ድንበር 10 ኪሎሜትር ዘልቀው በመግባት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩክሬን የሩሲያን ድንበር ጥሳ ወደ ግዛቷ ዘልቃ መግባቷን በይፋ ባትናገርም፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በሐሙስ ነሐሴ 2 “ሞስኮ ወረራ የሚያስከትለው ህመም ሊሰማት ይገባል” ብለዋል።
በሌላ በኩል አርብ ነሐሴ 3/ 2016 ዓ.ም በዶኔትስክ ግዛት በጦር ግንባሩ አቅራቢያ በምትገኘው በዩክሬኗ ኮስትያንቲኒቭካ ከተማ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ ሩሲያ በፈጸመችው ጥቃት አስር ሰዎች ሲገደሉ፣ 35 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚህ ጥቃት የመኖሪያ ህንጻዎች፣ ሱቆች እና ከ12 በላይ መኪኖች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ሚኒስቴሩ አክሏል።
የጥቃቱ ዜና የተሰማው የዩክሬን ጦር በሩሲያ ውስጥ የሚገኝ የጦር አውሮፕላን ሰፈርን በመምታት በርካታ የጦር መሳሪያዎችን የያዘ መጋዘን ማውደሙ ከገለጸ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ከዩክሬን እና ሩሲያ ድንበር 350 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሊፔትስክ የጦር አውሮፕላን ሰፈር ላይ ኪዬቭ የፈጸመችው ጥቃት ለበርካታ ጊዜያት ስታልመው የነበረ ነው ተብሏል።
ሊፔትስክ የሩሲያ ሱ-34፣ ሱ-35 እንዲሁም ሚግ-31 የተሰኙ የጦር አውሮፕላኖችን የያዘ እንደሆነም የዩክሬን ጦር አስታውቋል።
የግዛቲቷ ባለሥልጣናት “በኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማት” ላይ ፍንዳታ ማጋጠሙን አረጋግጠው የአስቸኳይ ጊዜ አውጀዋል። እንዲሁም በአቅራቢያው ባሉ አራት መንደሮች የሚኖሩ ነዋሪዎች እንዲወጡ እየተደረጉ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት አራተኛ ቀኑን በተሻገረው የዩክሬንን ድንበር ዘለል ጥቃት እና ግስጋሴን ለመመመከት ሩሲያ የተጠባባቂ ወታደሮቿን ብታሰማራም ወረራውን ለማስቆም ቀላል እንዳልሆነ እየተነገረ ነው።
ላለፉት 18 ወራት ጦርነቱን በበላይነት ስትመራ ለነበረችው ሩሲያ ይህ ግዛቷን ዘልቆ የገባው ጥቃት ጦሯን እንዲሁም ክሬምሊን ያስደነገጠ ነው ተብሏል።
ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ጥቃቱን በመመከት እና ዘልቀው የገቡ የዩክሬንን ወታደሮችን ከማስወጣት በተጨማሪ ይህንን ጥቃት ባለመከላከል ከሕዝቡ የሚቀርብን ወቀሳ ለማረጋጋት መንግሥት መንገድ መቀየስ አለባት ተብሏል።
ምዕራባውያኑ የዩክሬን አጋሮች ጦርነቱ የበለጠ እንዳይጋጋል ቢሰጉም፣ በአሁኑ ወቅት ኪዬቭ እያደረገችው ያለውን ድንበር ዘለል ጥቃት ራሷን የመከላከል መብት እንደሆነ ነው የሚያዩት።
ምንም እንኳን ዩክሬን በሩሲያ ግዛት ውስጥ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ሞስኮን ያስደነገጠ ቢሆንም፣ ሩሲያ ካላት የሠራዊት እና የጦር ኃይል የበላይት ጋር ተያይዞ ብዙ ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ተገምቷል።