
9 ነሐሴ 2024
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ እና በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መወሰኑን ገለጸ።
ምርጫ ቦርዱ ለፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት በልዩ ሁኔታ መስጠቱን ዛሬ አርብ ነሐሴ 3/ 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫው የተሰጠው በኃይል እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሳተፉ ለነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ሕጋዊ ዕውቅና መስጠትን አስመልክቶ በዚህ ዓመት ግንቦት መጨረሻ በጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሠረት መሆኑንም ቦርዱ አመልክቷል።
ህወሓት በፖለቲካዊ ውሳኔ የነበረው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስለት እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ህወሓት የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ለቦርዱ አመልክቶ የነበረ ቢሆንም፣ በጸደቀው ማሻሻያ መሠረት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነትን መመለስ የሚል ባለመኖሩ ጥያቄው ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጿል።
የተሻሻለው አዋጅ “በአመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ በመሆኑ ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበለውም” ብሏል።
አቶ አማኑኤል “ሕጋዊ ሰውነት እንዴት እንደሚመለስ በምርጫ ሕጉ ግልጽ ስላልሆነ ተጨማሪ [የሕግ] ማዕቀፍ በማዘጋጀት የተሰረዘው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ይደረጋል የሚል ንግግር ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ከዚህ ቀደም ተናግረው ነበር።
ይህ የአዋጅ ማሻሻያ፤ “የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል ሳይሆን እንደ አዲስ ለመመዝገብ የሚያስችል” መሆኑን አቶ አማኑኤል ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን ጠቁመው ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀው ይህ አዋጅ፤ ኃይልን መሠረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ተሳትፎ የነበረ የፖለቲካ ቡድን በልዩ ሁኔታ በፓርቲነት የሚመዘገብበትን ሂደት በዝርዝር ያስቀመጠ ነው።
የአዋጅ ማሻሻያው፤ የፖለቲካ ቡድኑ “ሕገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ይደነግጋል።
- ህወሓት የቀደመ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ አንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ እንደማይፈልግ አስታወቀ23 ሀምሌ 2024
- ‘በኃይል እና በአመጽ የተሳተፉ’ የፖለቲካ ቡድኖች በፓርቲነት እንዲመዘገቡ የሚያስችለው የሕግ ማሻሻያ ጸደቀ4 ሰኔ 2024
- አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት ሊያደርግ ካሰበው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ9 ነሐሴ 2024
ማሻሻያው ከጸደቀ በኋላ የፍትህ ሚኒስቴር ለምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ “ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባሩን በማቆም ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የተስማማ መሆኑን በመጥቀስ” በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ እንዲችል በደብዳቤ መጠየቁ ተጠቅሷል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሰጠውን ማረጋገጫ እና ህወሓት ያቀረበውን ማመልከቻ እና ሰነዶች መሠረት በማድረግም ፓርቲው በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ቦርዱ መወሰኑ ተገልጿል።
የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ መሰረዙ ይታወሳል።
የትግራዩን ጦርነት ያስቆመው ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተፈረመ በኋላ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከፌደራል መንግሥት ጋር ንግግር መጀመሩን አቶ አማኑኤል አስታውሰው ነበር።
አቶ አማኑኤል “ወደ ምርጫ ቦርድ አመልክተን በዚያ አዋጅ መሠረት እንድንስተናገድ ነው የሚፈልጉት። እኛ ወደ ምርጫ ቦርድ ቴክኒካል ወደ ሆነው ጉዳይ እንደ አዲስ ለመመዝገብ ማመልከት ሳይሆን ፖለቲካሊ የተሰረዘውን ሕጋዊ ሰውነት ለማስመለስ የሚያስችል ፖለቲካዊ ውሳኔ በሚመለከተው የመንግሥት አካል እንዲሰጠን ነው የምንፈልገው” ሲሉ የፓርቲያቸው ውሳኔ አስረድተው ነበር።
አቶ አማኑኤል ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ሁለተኛ ዙር ግምገማ በተካሄደበት ጊዜ ይኸው የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ መነሳቱን ጠቅሰዋል።
በዚህ ግምገማ ላይ፤ “ህወሓት እንደ አዲስ መመዝገብ ሳይሆነ የነበረው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለሰት ነው መደረግ ያለበት” የሚል ሃሳብ መነሳቱን ጠቁመው ነበር።
ህወሓት በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሳኔን የያዘው ደብዳቤ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ የቦርዱ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ፣ የመተዳደሪያ ደንቡን በጉባዔው እንዲያጸድቅ እና አመራሮቹን እንዲያጸድቅ መወሰኑ ተገልጿል።
ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ከማካሄዱ ከ21 ቀናት በፊት የጉባዔውን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት ብሏል።
ቦርዱ በቀሪዎቹ ጊዜያት የፖለቲካ ፓርቲው “ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” ክትትል የማድረግ እና ግብረ መልስ የመስጠት ኃላፊነት አለበት።
ቦርዱ ይህንን ቢልም ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ከዚህም ጋር ተያይዞ በአመራሮቹ እና በአባላቱ መካከል ስምምነት አለመኖሩ እና ጉባኤው እንዲዘገይ የሚጠይቁ እንዳሉ ተገልጿል።
በተመሳሳይ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፓርቲው ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ዛሬ አርብ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. ማስታወቃቸው ተዘግቧል።