
ከ 2 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ ዛሬ በተደረገው የፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን የሩጫ ውድድር ክብረ ወሰን በመስበር ለአገሩ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ።
ታምራት ቶላ የ42 ኪሎሜትር ውድድር በአሸናፊነት ያጠናቀቀበት ሰዓት 2:06:26 ሲሆን በዚህም የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን አሻሽሏል።
ቶላ የተጎዳን አትሌት በመተካት ከሁለት ሳምንት በፊት በተጠባባቂነት የኦሊምፒክ ማራቶን ተሳታፊ ለመሆን እንደበቃም ተዘግቧል።
በዚህ ውድድር የቤልጂዬሙ በሺር አብዲ ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በዚህ ውድድር ላይ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደረሰ ገለታ 5ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ ከታምራት 5 ደቂቃ 58 ሰኮንዶች ዘግይቶ 39ኛ ሆኖ ጨርሷል።
የትራክ እና የጎዳና ላይ የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ የሆነው ታምራት ቶላ ከስምንት ዓመት በፊት በብራዚል ሪዮ በተደረገው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ሦስተኛ ሆኖ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቶ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2022 በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ታምራት በማራቶን የተወዳደረ ሲሆን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ላይ በተካሄደው የብር ሜዳሊያ፣ ዩጂን አሜሪካ በተደረገው ደግሞ የውድድሩን ክብረ ወሰን በማሻሻል ወርቅ አሸንፏል።
በተጨማሪም ታምራት በቶኪዮ እና በለንደን የማራቶን ውድድሮች ላይ ሦስተኛ በመሆን የጨረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት (2023 እአአ) የኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶንን ክብረ ወሰን በመስበር አሸናፊ ሆኗል።
- ታሪክ ሠሪዋ ጽጌ ዱጉማ6 ነሐሴ 2024
- የትግራዩ ጦርነት የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ተስፋ ጎድቶታል?7 ነሐሴ 2024
- የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ24 ሀምሌ 2024

ታማራት ቶላ በፓሪስ ኦሊምፒክ በማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስገኝ የእነ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴን እና ገዛኽኝ አበራን ታሪክ በመቀላቀል ስሙን ከታላላቆቹ አትሌቶች ጎን እንዲመዘገብ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በማራቶን ወርቅ ያገኘችው ከ24 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2000 በሲድኒ ኦሊምፒክ በገዛኽኝ አበራ መሆኑ ይታወሳል።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ለራቀው የኢትዮጵያ ቡድን የታምራት ቶላ የማራቶን ወርቅ ትልቅ ድል እንደሆነም ተነግሯል።
በነገው ዕለት ነሐሴ 5/ 2016 ዓ.ም በሚጠናቀቀው ውድድር የዛሬውን የወርቅ ሚዳሊያን ጨምሮ ኢትዮጵያ እስካሁን ያገኘቻቸው ሦስት ሜዳልያዎችን ነው።
አትሌት ጽጌ ድጉማ በ800 ሜትር እንዲሁም በሪሁ አረጋዊ በ10 ሺህ ሜትር የብር ሜዳሊያዎችን አግኘተዋል።
በሩጫ ውድድር በተለይም በአምስት ሺህ፣ በአስር ሺህ እና በማራቶን ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች ሜዳሊያዎችን በማግኘት የሚታወቁት ኢትዮጵያውያን ሯጮች በፓሪሱ ኦሊምፒክ የተጠበቀውን ያህል ድል አልቀናቸውም።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና በኦሊምፒክ ኮሚቴው ላይ ውጤት ሲጠብቁ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን በኩል ጠንካራ ትችት እየተሰነዘረ ይገኛል።