
ከ 41 ደቂቃዎች በፊት
የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የህወሓት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው መሆኑን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ትናንት አርብ ነሐሴ 3/2006 ዓ.ም. መስጠቱን ተከትሎ ለቦርዱ በጻፉት የቅሬታ ደብዳቤ ነው አቶ ጌታቸው ይህንን የገለጹት።
ምርጫ ቦርድ የህወሓት የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ እና በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገብ ውሳኔ ማሳለፉን መግለጹ ይታወቃል።
አቶ ጌታቸው “የምዝገባ ጥያቄው” የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው እንደሆነ ገልጸው “እኛ ለዚሁ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም ዓይነት ሰነድ ሳይኖር፣ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው ከድርጅቱ አሠራር ውጪ የፈፀሙት ያልተገባ ተግባር መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉ ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም. ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
ምርጫ ቦርድ ህወሓት ካስገባው ማመልከቻ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሠረት የፖለቲካ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲ ኃላፊዎች ስም እና ፊርማን የያዘ ሰነድ ማቅረቡን አስታውቋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም ምርጫ ቦርዱ የደረሰው ማመልከቻም ሆነ የፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና ፊርማ የያዘው ሰነድ “የምዝገባ ጥያቄ ግለሰቦቹ እኛን ሳያስፈቅዱ የፈፀሙት መሆኑን እየገለጽን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነዚህ ግለሰቦች የሰጠው ምዝገባ በተጭበረበረ ማስረጃ መሠረት በመሆኑ መልሶ እንዲመረምረው እንጠይቃለን” ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንን ቢሉም የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የፈረሙበት የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት ለመመለስ የሚጠይቅ ደብዳቤ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገብቷል።
ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ በተጠየቀበት በዚህ ደብዳቤ ላይ “የድርጅታችን ህወሓት ሕጋዊ ሰውነት መመለስ ከፕሪቶሪያው ስምምነት፣ ከሕግ እና ድርጅታችን እያደረገ ካለው ተጨባጭ እንቅስቃሴ አንፃር እስከ አሁንም መዘግየት ያልነበረበት መሆኑ በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የጋራ መግባባት ያለ በመሆኑን እና ሰላም እንዲዳብር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ ቦርዱ የድርጅታችንን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመልስልን” የሚል ይገኝበታል።
በዚህም ደብዳቤ ላይ የፓርቲው ፕሮግራም፣ ሕገ ደንብ እና የአመራሮች ዝርዝር በአባሪነት መያያዛቸው ተገልጿል።
- አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ህወሓት ሊያደርግ ካሰበው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ9 ነሐሴ 2024
- ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገብ እንጂ የቀድሞው ህልውናው እንደማይመለስለት ምርጫ ቦርድ አስታወቀ9 ነሐሴ 2024
- ህወሓት የክልሉን “መንግሥት የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመሃል” ሲል እንደወቀሳቸው አቶ ጌታቸው ተናገሩ30 ሀምሌ 2024
በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በሚመራው እና በምክትል ሊቀመንበሩ እንዲሁም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል ያለው ቅራኔ እና ሽኩቻ እየሰፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው አቶ ጌታቸው ይህንን ደብዳቤ የጻፉት።
አቶ ጌታቸው ፓርቲያቸው በቅርቡ ሊያደርግ ካቀደው ድርጅታዊ ጉባኤ ራሳቸውን ማግለላቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ ድርጅታዊ ጉባኤ ለማድረግ እየተካሄደ ያለውን ዝግጅት “በአንድ አካል እየተፈፀመ ያለ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ” ሲሉም ፈርጀውታል።
ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ለመቋጨት በተካሄደው የፕሪቶሪያ ድርድር የትግራይ ተወካይ የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን “መንግሥትን የሚያፈርስ ስምምነት ፈርመሃል” ሲል ህወሓት እንደወቀሳቸው ከሳምንት በፊት ተናግረው ነበር።
የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የመቋጨት ስምምነት የክልሉን መንግሥት እንዲያፈርስ እንዳደረገው እና ይሄንንም ተግባራዊ አድርገዋል ተብለው በፓርቲያቸው መተቸታቸውን ከድምጺ ወያነ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።
ህወሓት “የተደራጀ ስም የማጥፋት ሥራዎች” ሲያካሂድብኝ ቆይቷል ያሉት አቶ ጌታቸው “በውስጣዊ አለመግባባቶች፣ በፖለቲካዊ ሽኩቻዎች ምክንያት፣ አንዱ የጀመረውን እንቅስቀሴ ሌላው ስም ስለሚሰጠው” ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን መሥራት አልተቻለውም ብለዋል።
ከሰሞኑ ይህንን ሽኩቻ በማየትም “የትግራይ ሰላምና ፀጥታ የሚያውክ እና በትግራይ ፖለቲካ ከሚመለከተው የትግራይ ሕዝብ ውጪ በውጫዊ ኃይል የሚደረግ ጣልቃ ገብነት አጥብቀን እንቃወማለን። ከፌዴራል መንግሥት ጋር በሂደት እየተፈፀመ ያለው የፕሪቶሪያ ስምምነት በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር የበኩላችንን እንወጣለን” ሲሉ የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች ከሰሞኑ መግለጫ ሰጥተው ነበር።