ተማሪዎች በትምሕርት ላይ

ከ 5 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ባሉ ግጭቶች እና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ ከ5500 በላይ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራቸውን ከማከናወን ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ የዜጎች የትምህርት መብት “በእጅጉ እየተጣሰ” መሆኑን ብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ኮሚሽን ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ ባጋጠሙ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ ትምህርት ቤቶች እተዘጉ እንዲሁም ለሌላ ዓላማ እየዋሉ ነው በማለት በኢትዮጵያ የትምህርት መብትን አሳሳቢ አድርጎታል በማለት ብሏል ኮሚሽኑ።

በዚህም ኢትዮጵያ ካሏት 12 ክልሎች መካከል በስምንት ክልሎች አምስት ሺህ 564 ትምህርት ቤቶች ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎላቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

ይህም በአገሪቱ ያለው የትምህርት መብት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የኢሰመኮ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገ/ሐዋሪያ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶች በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት እየተዘጉ መሆናቸውን የጠቀሱት ርግበ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በተለይ ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያነትነት መዋላቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም “በትጥቅ ግጭት ውስጥ ባሉ አካላት [የጦር] ካምፕ ሆነው ነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ከግጭት እያገገሙ ነው በሚባሉ እንደ ትግራይ ባሉ ክልሎች ውስጥ ደግሞ የመልሶ ግንባታ ሂደቱ በተቻለ ፍጥነት እየተካሄደ አይደለም” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ እና እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች መካከል ትምህርት ቤቶች የተፋላሚዎች የጥቃት ኢላማ ከመሆናቸው ባሻገር በተዋጊ ቡድኖች የጦር ካምፕ እንደሚደረጉ ኮሚሽነር ርግበ ለቢቢሲ ተናግዋል።

“በተለያዩ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በተዋጊዎች ኢላማ ይደረጋሉ፤ ወድመዋል፤ ፈርሰዋል። በተጨማሪም ለሌላ ዓላማ ወይም ለጦር ካምፕነት የሚውሉባቸው ቦታዎች አሉ” ብለዋል።

ባለፈው ግንቦት ወር በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ ተሬ ቀበሌ የሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የወላጅ መምህራን ኅብረት ስብሰባ ላይ የነበሩ ሠላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና መምህራን መቁሰላቸውን ቢቢሲ የዐይን እማኞች እና የተጎጂ ቤተሰቦችን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል።

ከዚህ ባሻገርም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የክልል መስተዳደሮች ለመምህራን ደሞዝ መክፈል ባለመቻላቸው የመማር ማስተማር ሂደት እየተስተጓጎለ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።

በተለይም አዲስ በተመሠረቱት ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ደሞዝ በአግባቡ እና በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከዚህ ቀደም በሠራው ዘገባ የዎላይታ ዞን መምህራን ደሞዝ በሚዘገይባቸው ቀናት ወደ ትምህርት ቤቶች እንደማይሄዱ እና ተማሪዎችም ከትምህርት ቤቶች እንደሚቀሩ ተናግረው ነበር።

“ሰው እየተራበ ማስተማር አይችልም። ደሞዝ ሳይከፍል ደግሞ ለምን አላስተማርክም ብሎ ማስገደድ አይቻልም” ብለዋል።

በመምህራኑ ሀሳብ የሚስማሙት ኮሚሽነር ርግበ “እነሱ [መምህራን] በትክክል ደሞዝ ተከፍሏቸው ባልኖሩበት ሁኔታ አገልግሎት ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም። . . . በበጀት በኩል መምህራን ደሞዛቸው በትክክል ባለመከፈሉ ምክንያት ትምህርት ላይ ሌላ ተጽዕኖ እየመጣ ነው” ብለዋል።

ግራፍ

ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንደራቁ ለማወቅ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚያወጧቸው የተጣረሱ መረጃዎች ትክክለኛውን አሃዝ ማወቅ አልቻልኩም ብሏል።

ሆኖም ኮሚሽኑ ሌሎች ተቋማት ያወጧቸውን መረጃዎች ዋቢ በማድረግ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ እንደሆኑ ጠቅሷል።

የትጥቅ ግጭት እየተደረገበት ያለው አማራ ክልል በ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን አስታውቋል።

ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው “ለድርብርብ የመብት ጥሰት” እንደሚያጋልጣቸው የተናገሩት ኮሚሽነሯ፤ አሳሳቢ ሲሉ ለገለጹት የመብት ጥሰት እየተዳረጉ ነው ብለዋል።

“ለምሳሌ ሴት ተማሪዎች ላለ እድሜ ጋብቻ እንዲዳረጉ ይሆናሉ። ህጻናት ለጉልበት ብዝበዛ እንዲሁም ለፍልሰት እየተዳረጉ ነው። ምክንያቱም ትምሕርት በማይኖርበት ሁኔታ፤ ቤተሰብም የገቢ ምንጭ በሚያጣበት ሁኔታ ያለ እድሜያቸው ሥራ ላይ እንዲሰማሩ፤ ጉልበታቸው እንዲበዘበዝ፤ መብታቸው እንዲጣስ እየሆኑ ነው” ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ትምህርት በመቋረጡ እና ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ በመሆናቸው እየደረሰ ያለውን ጉዳት የገለጹት ኮሚሽነር ርግበ “ጊዜ የለንም” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

“ለሦስት፤ አራት ዓመታት ትምህርት ቤት ያልገቡ ተማሪዎች አሉ። ከሕይወታቸው ላይ ይህን ያህል ዓመት እንደመስረቅ ነው። ይህንን ዓመት አንመልስላቸውም። በትውልድ ላይም እየሆነ ያለው ነገር ትክክል አይደለም። እንደ አገርም በጣም ትልቅ ነገር እያጣን ነው” ሲሉ ኪሳራውን አንስተዋል።

ኢሰመኮ አሳሳቢ ሆኗል ባለው የትምህርት መብት አደጋ ላይ መውደቅ እና መፍትሔዎቹ ዙሪያ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር ባለፈው ሐምሌ ወር መምከሩን ገልጿል።

በምክክሩ የሚመለከታቸው አካላት ለችግሩ ፈጣን እና የተቀናጀ የመፍትሔ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።