Friday, 09 August 2024 16:39

Written by  በሚኪያስ ጥላሁን

የየኢዜማ ዋና ጸሐፊ ከሃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ

“ለአገሬ የምመኘው እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ዕውን
እስከሚሆን የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ”


የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ ከሃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታወቁ። አቶ አበበ ለኢዜማ ብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ እና ለምርጫ ወረዳ 28 በጻፉት ደብዳቤ፣ “ይስተዋላል” ባሉት የፓርቲው ዕንቅስቃሴ ውስጥ በአባልነትም ሆነ በሃላፊነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።

ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በጻፉት በዚህ ደብዳቤ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት የኢዜማ ዋና ጸሐፊ ሆነው መስራታቸውን በማስታወስ፣ “ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሄው የዜግነት ፖለቲካው ስለመሆኑ ዛሬም የጸና እምነት አለኝ።” ብሏል፡፡

ሆኖም ግን “ይስተዋላል” ባሉት የፓርቲው አቋምና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ውስጥ በሃላፊነትም ሆነ በአባልነት መቀጠል እንደማይፈልጉ አመልክተዋል። በመሆኑም ከሃምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢዜማ የዋና ጸሃፊነት ሃላፊነታቸው መልቀቃቸውን፣ የኢዜማ አባላትና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ “ይወቁልኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

“በቀጣይ ቀሪ የዕድሜ ዘመኔ፣ ለአገሬ የምመኘው ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዕውን እስከሚሆን የበኩሌን አስተዋጽኦ አደርጋለሁ።” ብለዋል።

አቶ አበበ አካሉ፤ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፣ በኋላም በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት ተሳትፎ ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው።