
Friday, 09 August 2024 16:41
Written by Administrator

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነት ተሰጥቶታል። ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት የተሰጠው በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓዋጅ መሰረት እንደሆነም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ህወሓት ሚያዚያ 13 እና 28 2015 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነቱ ወደነበረበት እንዲመለስ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር በማስታወስ፣ በዓዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የቀድሞውን የፓርቲ ሕልውና መመለስ እንደማይቻል የሚገልጽ ውሳኔውን ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ለፓርቲው ማሳወቁን አውስቷል፡፡
የተሻሻለው ዓዋጅ ቁጥር 1332/2016 በዓመጽ ተግባር ተሰማርቶ ለተሰረዘ ፓርቲ “የቀድሞ ሕልውናውን መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ” በመሆኑ በድጋሚ የቀረበለትን ጥያቄ አለመቀበሉንም ጠቅሷል።
በተሻሻለው ዓዋጅ አንቀጽ 2፣ ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ፣ ህወሓት ሃይልን መሰረት ያደረገ የአምጽ ተግባሩን በማቆም ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በመጥቀስ፣ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ለቦርዱ ማረጋገጫ መስጠቱን አንስቷል። ህወሓት በበኩሉ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ የፓርቲ ሃላፊዎች ስምና ፊርማ የያዘ ሰነድ ለቦርዱ አቅርቧል።
በሰነዶቹ መሰረት ቦርዱ፣ ህወሓት እንደፖለቲካ ፓርቲ እንዲመዘገብ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን፣ ለፓርቲው የሚሰጠው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ “በልዩ ሁኔታ” የሚል ቃል ያለበት እንደሚሆንም ነው ያመለከተው። ህወሓት በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሳኔን የያዘው ደብዳቤ በደረሰው በስድስት ወራት ውስጥ ታዛቢዎች በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርግ፣ የመተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጸድቅና አመራሮቹን እንዲያስመርጥ ወስኗል።