August 10, 2024 – Konjit Sitotaw 

° “ የደመወዝና የቤት ችግርን በተመለከተ የተገባልን ቃል አልተፈጸመም ” – የዩኒቨርሲቲ መምህራን

° “ ተደራጅተው መጠየቅ ነው ጠቃሚ የሚሆነው ” – የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር

የመኖሪያ ቤት ግንባታ እና የደመወዝ ጭማሪን በተመለከተ ተገብቶልን የነበረው ቃል እስካሁን አልተፈጸመልንም ሲሉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቅሬታቸውን አሰሙ።

” ምንም እንኳን በይፋም ባይሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ፤ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መምህራን በተገኙበት ስብሰባ ቃል ገብተው ነበር ” ያሉት መምህራኑ ሆኖም ጭማሪ እንዳልተደረገላቸው ገልጸዋል፡፡

ከጭማሪው ጋር በተያያዘ ካሁን በፊት በጠቅላይ ሚንስትሩ ትዕዛዝ  ከመምህራን ማህበር ፥ ከትምህርት ሚንስትር እና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተዉጣጣ ኮሚቴ ተሰይሞና ተጠንቶ ተግባራዊ ሊደረግ የነበረ ባለ ሶስት አማራጭ የደሞዝ ስኬል አማራጭ እንደነበር አንስተዋል።

” የገንዘብ ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ይህ ጥናት ከሐምሌ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ለተወካዮቻችን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አልተደረገም ” ብለዋል።

” ከዛ በኋላ ህዳር 26 ጀምሮ አድማ ተደረገ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ጥር 2015 ዓ.ም ላይ ሐምሌ 1/2015 ጀምሮ ጭማሪ ይደረጋል ያሉ ቢሆንም እስካሁን የተደረገ ጭማሪ የለም ” ሲሉ ገልጸዋል።

” በሀገራችን ከፍተኛ ወጭ ወጥቶበት ለዩኒቨርሲቲ መምህራን የተጠና ደመወዝ ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል። ” ያሉት መምህራኑ ተግባራዊ እንደማይደረግ ከታወቀ ፦
° ጥናቱን ለምን አጠኑት ?
° ለምንስ ከፍተኛ ወጭ ወጥቶ እንዲጠና ተደረገ ?
° ከተጠና በኋላስ ለምን ተግባራዊ ሳይደረግ ቀረ ?
° ከአሁን በፊት የተጠናውን ጥናት ተትቶ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከመጡ ጀምሮ ባለሙያ መድቤ እያስጠናሁ ነው ያለሁት ጥናት በሚቀጥለው ህዳር 2017 ይጠናቀቃል ማለት ምን ማለት ነው ? ሲሉ ጠይቀዋል።

እንዲሁም ነሐሴ 30/2015 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር አመራሮች በተገኙበት ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዩኒቨርቲ መምህራን የቤት ችግር በአጭር ጊዜ እንደሚፈታ መግለጻቸውን ማኀበሩ በወቅቱ ማስረዳቱን አውስተዋል፡

ቃል ሲገባላቸው ቢቆይም እስካሁን በተግባር የተገለጸ ነገር እንደሌለ፣ በዚህም የኑሮ ውድነቱ መቋቋም እንዳልቻሉ አስረድተው፣ ” የደመወዝና የቤት ችግርን በተመለከተ የተገባልን ቃል አልተፈጸመም ” ሲሉ አማረዋል፡፡

ቲክቫህ ኢትዮጵያም መምህራኑ ላደረባቸው ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጥ ለመሆኑ መምህራኑ ተገብቶልን ነበር ያሉት ቃል በተግባር ከምን ደረሰ ? ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር (ኢመማ)ን ጠይቋል፡፡

የማኀበሩ ፕሬዚንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ምን ምላሽ ሰጡ ?

” ዩኒቨርሲቲ ላይ አንዳንድ ከእሳቸው (ከጠ/ሚ አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር ማለታቸው ነው) ጋር ያወራናቸው ገዳዮች ነበሩ፡፡

ከክልል ርዕሳነ መስተዳድር ጋር አውርቻለሁ እንሄድበታለን ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተደጋጋሚ ማግኘት አይቻልም፣ አገሪቷ ያለችበት ኮሚትመንትም ብዙ ነው፡፡

እንደዛም ሆኖ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከከተማ አስተዳደር ጋር ተመካክረን ችግሩን የፈቱበትን ሁኔታ ሼር እየተደራረጉ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡

ስለዚህ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ያለውን የመምህራን ቅሬታ ፈርዘር የምንሄድበት ነገር እንዳለ ይሰማኛል። ” ብለዋል።

ለቅሬታው መፍትሄ ለመስጠት የተኬደበት ነገር አለ ? የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጭራሽ ጥያቄያችን ተዘንግቷል የሚል ቅሬታ አላቸው ፤ ለሚለው ጥያቄያችን ፕሬዚዳንቱ ምላሽ ሰጥተዋል።

” እኛ መቼም ችግሩ እንዲፈታ ነው የምንፈልገው፡፡ ያ ደግሞ እንዲሆን የራሳችንን ክትትል ነው የምናደርገው፡፡ ወዲያው ደግሞ የሚፈለገው ሁሉ ላይሆን ይችላል።

እሳቸው (ጠ/ሚ አቢይ (ዶ/ር) ማለታቸው ነው) ያሉት ነገር አለ፡፡ እኛም ያልነው አለ፡፡ ከምን ደረሰ? እንዴት እንፍታ? ብለን መከታተላችን አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴርም የራሱን አስተዋጽዖ ቢያደርግ መልካም ነው።

ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያዋጣቸው በየራሳቸው ማኀበር በየኒቨርሲቲ ደረጃ እደረጀን ነው ባልተደራጁባቸው እንዲደራጁ፣ ተደራጅተው መጠየቅ ነው ጠቃሚ የሚሆነው ” ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲ በታች ባሉ የትምህርት ተቋማት የመምህራን የቤት ችግር እየተፈታ መሆኑን ማኀበሩ ያስረዳ ሲሆን፣ ከመምህራኑ ቅሬታ ጋር በቀጣይ ይቀርባል፡፡