የአማራ ብሔርተኝነት እና የሀገረ-ኢትዮጵያ መስተጋብር 

ByAdmin

 መስከረም አበራ

መስከረም አበራ 
ሀምሌ 2016 

ይህ ሰነድ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ከፃፍኳቸዉ ሰነዶች አራተኛዉ ነዉ፡፡ ሰነዶቹ የሃሳብ ተያያዥነትና ተከታታይነት ስላላቸዉ አንባብያን በጉዳዩ ላይ የተሻለ መረዳት እንዲኖራቸዉ ይህን ሰነድ ከማንበባቸዉ በፊት ቀዳሚዎቹን ሶስቱን ሰነዶች ቢያነቡ የተሻለ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ሰነድ “የአማራ ህዝብ ትግል ዳራና ቀጣይ አቅጣጫዎች” የተፃፈ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ሰነድ “የአማራ ህዝብ ትግል እንዴት ይመራ?” የሚል ርዕስ ይዟል፡፡ ሶስተኛዉ “የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች” በሚል ርዕስ የተፃፈ ነዉ፡፡ 

(ሰነዶቹን አንባብያን እዚህ ላይ በመክፈት ማንበብ ይችላሉ) 
የአማራ ህዝብ ትግል ዳራና ቀጣይ አቅጣጫዎች
የአማራ ህዝብ ትግል እንዴት ይመራ?

የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች


ማውጫ እዚህ ላይ አለ

1-መንደርደሪያ 

በአማራ ህዝብ ላይ የታወጀዉ የጠላትነት ጥንስስ የተጀመረዉ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ቢሆንም አማራ ጠልነት ህገ-መንግስታዊና ተቋማዊ ቅርፅ ይዞ የሃገራችን ፖለቲካ ማጠንጠኛ የሆነዉ ግን ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ነዉ፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰዉና እየደረሰ ያለዉ ከ “ጄኖሳይድ” እስከ “አፓርታይድ” የሚደርሰዉ መንግስታዊ ወንጀል የአማራ ብሄርተኝነትን አይቀሬ አድርጎታል፡፡ ይህ የአማራ ብሄርተኝነት በፕ/ሮ አስራት ወልደየስና ጓዶቻቸዉ የተጀመረዉ ቀደምቱ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ ቀደምቱ የአማራ ብሄርተኝነት ታድያ በወቅቱ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ የነበረዉን እና ወደፊትም ሊፈፀም ያለዉን ግልፅ አደጋ በመረዳትና ለተረዳዉ እዉነት ፀንቶ በመቆም ረገድ እንከን የማይወጣለት ነበር፡፡ ሆኖም እንቅስቃሴዉ በዋናነት ከህወሓት በመጣበት ምህረት የለሽ ተግዳሮት ሳብያ መሪዉን በመነጠቁ የታሰበዉን ያህል ለመራመድ አልቻለም፡፡ ብሄርተኝነቱ በፈጠረዉ መላዉ አማራ ድርጅት(መአድ) በተባለዉ ቀደምት አታጋይ ፓርቲ ዉስጥ የተፈጠረዉ ዉስጣዊ ችግርም ተደማምሮ እንቅስቃሴዉን እሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ አድርጎታል፡፡ 

ከመአድ በኋላ እስከ ፋኖ ትግል ድረስ ያለዉ ዘመን የአማራ ህዝብ ያለሁነኛ አታጋይ ፓርቲ አዉላላ ሜዳ ላይ ተጋልጦ ሲሳደድ እና በጅምላ ሲገደል የኖረበት ዘመን ነዉ፡፡ በዚህ ዘመን ብቅ ብሎ የነበረዉ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የተባለዉ ፓርቲ መሪዎች በስተመጨረሻዉ የአማራ ጠሉ ጎራ ሰልፈኛ ከሆነዉ ከብዓዴን/የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መሪዎች የሚለዩበትን ገፅታ ፈልጎ ማግኘት በሚቸግር መልኩ ሩጫቸዉን በጅምሩ የጨረሱ የአጭር ርቀት ተጓዦች ሆነዉ ቀርተዋል፡፡ “ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት” የተባለዉ ድርጅትም የበኩሉን ለማበርከት የሞከረ ድርጅት ነዉ፡፡ እነዚህ እና የመሳሰሉ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች የተደረጉ ቢሆንም የአማራን ህዝብ በህይወት የመኖር መብት ጨምሮ ሌሎችን መብቶች ማስከበር አልተቻለም፡፡ በመሆኑም አሁን በተስፋ ሰጭ ጎዳና ላይ እየተራመደ ያለዉ ፋኖነት የሆነዉ የአማራ ብሄርተኝነት እንዲወለድ ሆኗል፡፡ 

ይህ ብሄርተኝነት ከቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች በእጅጉ በተለየ መንገድ ህዝባዊ መሰረትና የትግል ቁርጠኝነት ይዞ የተነሳ ነዉ፡፡ ትግሉ በትክክለኛ ምክንያት ላይ የቆመ፣ እጅግ አስቸኳይ የሆነዉን በህይዎት የመኖር መብትና ሌሎች ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ያለመ በመሆኑ አመርቂ ዉጤቶችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ እያስመዘገበ ያለ የህዝብ ትግል ነዉ፡፡ ሆኖም ፋኖነት የሆነዉን የአማራ ብሄርተኝነት ትግል በተመለከተ የትግሉ ወዳጅ ከሆኑም ካልሆኑም ጎራዎች በርካታ ጥያቄዎች እያነሱ ይገኛል፡፡ ከሚንሱ ጥያቄዎች ትልቁን ድርሻ የሚይዘዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር ያለዉ መስተጋብር እንዴት ያለ እንደሆነ የሚጠይቀዉ ነዉ፡፡ይህን ጥያቄ በተገቢ መንገድ መመለሱ ለአማራ ህዝብ ትግል ቁልፍ ሚና ያለዉ ስለሆነ ይህን ሰነድ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ ሆኖም ሰነዱ ይህን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጥያቄዉ ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች እሳቤዎችንም ለማንሳት ይሞክራል፡፡ በዚህ ሰነድ ላይ “አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት” በሚል ሃረግ የተጠቀሰዉ ሃሳብ ከመአድ፣ ከአብን እና ሌሎች የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ዉስንነቶች፣ ክፍተቶችና ስህተቶች ትምህርት ወስዶ በፋኖነት የተገለጠዉን የአማራ ብሄርተኝነት ለመግለፅ ነዉ፡፡ ሰነዱ እንደ መነሻ ሃሳብ ብቻ የሚወሰድ፣ በተከታታይ ፅሁፎችና ዉይይቶች ሊዳብር የሚገባዉ መሆኑን ከወዲሁ ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ 

— 

2. አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የቆመባቸዉ መርሆዎች 

2.1 የቀደሙ ስህተቶችን ማጤንና ማረም፡- በዚህ ሰነድ መግቢያ ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረዉ የአማራ ህዝብን ዘርፈ ብዙ የህልዉና አደጋዎች ለመቀልበስ ታሳቢ ተደርገዉ የተጀመሩ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሎች ከአደጋ መታደግ ሳይችሉ ቀርተዉ በተገላቢጦሹ የአማራ ህዝብ ወደ ሃገሩ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንዳይገባ የሚከለከልበት የአፓርታይድ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ የአማራ ህዝብ ለ30 በላይ አመታት በዘለቀ ጊዜ ማንነት ተኮር ግድያና መሳደድ የእለት ተዕለት ህይወቱ አካል እስከመምሰል ደረሰ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ህጋዊ መስለዉ በግልፅ ሲፈፀሙ በአማራዉ በኩል አደጋዉን የሚመጥን ትግል ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚያመለክተዉ ቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ስህተቶች የበዙባቸዉ፣ ክፍተቶች የበረከቱባቸዉ እንደነበሩ ነዉ፡፡ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን የጀመረዉ የቀደሙ ስህተቶችን በማረም፣ ክፍተቶቹን በመሙላትና ዉስንነቶቹን ለመመርመርና ለማሻሻል በማሰብ ነዉ፡፡ እነዚህ የቀደሙ ስህተቶች በርካታ ቢሆኑም ይህ ሰነድ ከተፃፈበት አላማ ላለመዉጣት ቀደምቶቹ የአማራ ብሄርተኝነቶች ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጋር በነበራቸዉ መስተጋብር አንፃር በታዩ ስህተቶችና ክፍተቶች ላይ ለማተኮር ይሞክራል፡፡ ከቀደምቱ መአድ ቢጀመር የአማራ ህዝብ ከአማራ ጠሉ ስርዓት የተጋረጠበትን አስከፊ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ለማስቆም የተቋቋመ ነበር፡፡ ሆኖም ፓርቲዉ የተፈጠረበትን በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣ ማንነት ተኮር ጥቃት በማንነት ተደራጅቶ የመመከት ተገቢ ጅማሬ ከግቡ ሳያደርስ ይልቁንም በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ የነበረዉ መከራ እተባባሰ በሄደበት ሁኔታ በርካታ መሪዎቹ እና አባላቱ መኢአድ የተባለዉን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲ ማቋቋማቸዉ መአድን ወደ ሞት አፋፍ ያጣደፈ ጉልህ ስህተት ነበር፡፡ 

ይህ መሰረታዊ ስህተት ሌላ ከሃገራችን ህገ-መንግስት ጋር የሚጋጭ ስህተት ወልዷል፡፡ የሃገራችን ህገ-መንግስት የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነዉ በሃገሪቱ በሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦች ስምምነትና በጎ ፍቃድ ላይ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ስለዚህ የአማራ ህዝብ ጥብቅ ፍላጎት የሆነዉን የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ለማረጋገጥም ቢሆን የአማራ ህዝብን በብሄር አደራጅቶ እንደማንኛዉም ሌላ ብሄረሰብ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት እጣ ፈንታ ላይ የሚወስንበትን ፖለቲካዊ አቋም እንዲይዝ የሚያደርግ አታጋይ ፓርቲ ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህን ሲያደርግ ብቻ ወቅቱ የሚጠይቀዉን የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ እየተናገረ፣ በብሄር ተደራጅቶ የራሱን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር ይችላል፡፡ መአድ ያለጊዜዉ ወደ መኢአድነት ሲቀየር የሰራዉ ስህተት የወቅቱን የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ ይዞ ሲጓዝበት የነበረዉን ተገቢ አካሄድ ትቶ ህገ-መንግስታዊም መሰረትም ሆነ የወቅቱ የፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ በሌለዉ የትግል ዘይቤ ለመሄድ መምረጡ ነዉ፡፡ መኢአድ በዚህ አካሄዱ ያለመርከብ በዉቅያኖስ ዉስጥ ተጉዞ አንድ ከተማ ለመድረስ የተመኘ ተጓዥ ይመስላል፡፡ 

በአሁኑ የሃገራችን የፖለቲካ ዘይቤ አንድ የፖለቲካ ተጓዥ ብሄረሰቡን መርከብ አድርጎ፣ የብሄረሰብ መብት ማስከበርን ቀዳሚ አላማዉ አድርጎ ነዉ ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ጋር መስተጋብር የሚፈጥረዉ፡፡ ስለ ሃገረ-ኢትዮጵያ ቀጣይነት 

መምከር ተገቢ የሚሆነዉ ደግሞ ከሌሎች አቻ የብሄር መርከበኞች ጋር በመታደም ብቻ ነዉ፡፡ ባጭሩ ወደ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚኬደዉ ተገቢ ጉዞ የሚባለዉ በብሄር በኩል ሲያዘግሙት ብቻ ነዉ፡፡ በመሆኑም ጥሩ ኢትዮጵያዊ ለመሆን በመጀመሪያ ጥሩ ትግሬ፣ጥሩ ኦሮሞ፣ጥሩ ሲዳማ፣ ጥሩ ኮንሶ፣ ጥሩ አማራ፣ ጥሩ ከምባታ ወዘተ… መሆን ያስፈልጋል ሲሉ የብሄር ፖለቲካዉ የዘመኑ ቀሳዉስት ሊያስረዱ ሞክረዋል፡፡ “l’m Oromo first” የሚለዉ ዝነኛ አባባል የተነገረዉ ይህንኑ ወቅታዊ የፖለቲካ መንፈስ እጥር ምጥን አድርጎ ለመግለፅ ነበር፡፡ 

በብሄርተኝነት መርከብ ተሳፍረዉ ከሚያደርጉት ጉዞ ዉጭ ወደ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚደረግ ጉዞ በትምክህተኝነት የሚያስፈርጅ፣ የራስን ብሄር ፍላጎት በኢትዮጵያ ስም በሌሎች ላይ በመጫን የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት ለመስጠት የመሞከር እብሪተኝነት ሲያስወርፍ የኖረ “ስሁት” አካሄድ ነዉ፡፡ ይህን ወቅታዊ ሁኔታ ባላገናዘበ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የሚፀና የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትም ሆነ የሚከበር የአማራ ህዝብ መብት የለም፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ሃገረ-መግስት ቀጣይነትም ሆነ የአማራ ህዝብ ህልዉና ጥያቄ ዉስጥ ይገኛል፡፡ 

የመአድ ያለጊዜዉ መኢአድ መሆን ያመጣዉ ሌላ ስህተት የአማራ ብሄርተኝነትን በአማራ ህዝብ ዘንድ የማስረፅና ህዝቡ በአማራ ጠሉ ስርአት የተጋረጠበትን በዉል ለማስረዳት የሚያስችል ፋታ ያሳጣ መሆኑ ነዉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የአማራ ህዝብ አማራ-ጠሉ ስርዓት የሰነቀለትን አደገኛ ስንቅ ቀምሶት ብቻ እንዲረዳዉ አስገድዷል፡፡ በአንጻሩ መአድ መዒአድ ለመሆን ሳይቸኩል ተገቢዉን ፋታ ወስዶ ቢሆን ኖሮ የአማራ ህዝብ በማንነቱ የተቃጣበትን አደጋ በተገቢዉ ሁኔታ መቀልበስ በሚያስችል የፖለቲካ አቋም ላይ ቆይቶ እራሱንም ኢትዮጵያንም ለመታደግ የሚያስችለዉን ትግል ቀደም ብሎ መታገል ይችል ነበር፡፡ 

ከመአድ መዳከም በኋላ የመጣዉ በአብን የሚመራዉ የአማራ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ አብን እንደተመሰረተ ሰሞን የአማራ ብሄርተኝነት እና የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መስተጋብር አስመልክቶ በዋነኛ አመራሮቹ በኩል በአደባባይ ይገልፀዉ የነበረዉ ንግግር ዉጤቱ በዉል ያልታሰበበት ስለነበረ ፓርቲዉ ገና በሁለት እግሩ ሳይቆም ከአማራ-ጠሉ ጎራ ከፍተኛ ትችትን እንዲያስተናግድ አድርጓል፡፡ ይህ ማስተዋል የጎደለዉ የአብን አመራሮች ንግግር ከአማራ ልሂቃን በኩል የሚሰማዉን ማንኛዉም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥርጣሬ እና ስጋት የሚያየዉ የአማራ-ጠሉ ጎራ አማራዉን ትምክህተኛ እያለ ለማብጠልጠል አዲስ የፕሮፓጋንዳ ግዳይ እንዲያገኝ ያደረገ ነበር፡፡ ሌላው በአብን በኩል ሲቀነቀን የነበረው የትግላችን መንታ ነው መርሁ፣ ማለትም የአማራ ብሔርተኝነት እና የሀገረ-ኢትዮጵያ ብሔርተኝነት በእኩል ትግል አሳካለሁ ማለቱ በሁለት ያጣ ውጤት እንዲደመደም አድርጎታል፡፡ 

በዚህ ስህተት ሳቢያ የአብን እንቅስቃሴ የአማራ ብሄርተኝነትን እንደጠላት ከሚያዩ ኢትዮጵያዉያን ጎራ ጭምር በጥርጣሬ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የአብንን ስህተት በማጤን የአማራ ህዝብ ትግል የአማራ-ጠሉ ጎራ የፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዳይሆን ጥንቃቄ የተሞላበት የህዝብ ግንኙነት ስራን ለመስራት ይሞክራል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ምንም አይነት ጠብ የሌለዉ መሆኑ አበክሮ ለማስረዳት ይሞክራል በይበልጥ ደግሞ በተግባር ለማሳየት ይሰራል፡፡ ይህ ትግል ከኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ጋር ጠብ ሊኖረዉ ቀርቶ የሚታገለዉ ሀገረ-ኢትዮጵያ የአማራን እና የሌሎች ወንድም እህት ህዝቦችን መብት አክብራ በጥንካሬ እንድትጓዝ ነዉ፡፡ በተጨማሪም የአማራ ህዝብ የፋኖነት ትግል በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ምንም አይነት የበላይነትና የበታችነት ግንኙነት እንዲኖር እንደማይፈቅድ፣ እየታገለ ያለዉም የእራሱንም ሆነ የሌሎች ወገን ህዝቦችን መብት የምታከብር ኢትዮጵያን እዉን ለማድረግ እንደሆነ ለማሳወቅ ይጥራል፡፡ 

2.2. ባልተሄደበት አዲስ የትግል ስልት የሚጓዝ 

ባለፉት ከሰላሳ በላይ አመታት የአማራ ህዝብ በከፍተኛ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች ዉስጥ የሚገኘዉ የወቅቱን የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በዉል አጢኖ ህዝቡን ከእልቂት የሚታደግ ጠንካራ የአማራ ብሄርተኛነት ማምጣት ስላልቻለ ነዉ፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ይህን የሽንፈት ታሪክ ለመቀየር አልሞ የተነሳ እንቅስቃሴ ነዉ፡፡ ስለሆነም ከዚህ ቀደም የተሞከሩ የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ዉጤት አልቦ ያደረጉ ስህተቶችን ላለመድገም በከፍተኛ ጥንቃቄ በአዲስ ስልት የሚጓዝ ነዉ፡፡ በአንድ አይነት የስህተት መንገድ እየተመላለሱ የተለየ ዉጤትና ድል መጠበቅ ስለማይቻል አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን በአዲስ መንገድና ስልት ለማስኬድ ወስኗል፡፡ 

እነዚህ አዲስ መንገዶች በርካታ ቢሆኑም በዚህ ሰነድ ሁኔታ ከአማራ ብሄርተኝነት እና ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት አንፃር የተተለሙ አዲስ የትግል ስልቶችን በመቃኘቱ ላይ አተኩራለሁ፡፡ 

ከዚህ አኳያ ቀዳሚ የተደረገዉ አዲስ የትግል ስልት መአድ ወደ መኢአድ ለመቀየር የፈጠነዉን ስሁት ፍጥነት ባለመድገም ይልቅስ ሙሉ ሃይልን የአማራ ብሄርተኝነትን በማጎልበት ላይ በማድረግ በቂ ጊዜን መዉሰድ ነዉ፡፡ በዚህ እጅግ አስፈላጊ የጊዜ ፋታ ዉስጥ በርካታ አስፈላጊ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ የመጀመሪያዉ የአማራ ህዝብ ከአማራ-ጠሉ ስርአት የተቃጡበትን አደጋዎች በዉል እንዲረዳ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ህዝቡ የተጋረጠበትን አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችሉ ማታገያ ጥያቄዎቹ በህዝቡ ዘንድ የሚታወቁ ቢሆንም በተቀራራቢ ሁኔታ መግባባት ላይ የተደረሰባቸዉ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ ይሰራል እየተሰራም ነዉ፡፡ ብሄርተኝነቱን በላቀ ግንዛቤና በጠንካራ የትግል ስነ-ምግባር መርተዉ ዳር ሊያደርሱ የሚችሉ መሪዎችን ማፍራትም ሶስተኛ አስፈላጊ ስራ ነዉ፡፡ ሌላዉና አራተኛ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችለዉ ስራ የአማራ ብሄርተኛነት ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋ እንጅ ስጋት እንዳልሆነ በተጨባጭ የማሳየት ስራ ነዉ፡፡ በአጠቃላይ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ሙሉ ትኩረቱን በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ለማድረግ የሚወስደዉ ጊዜ የራሱን ዉስጠብሄር የፖለቲካ የቤት ስራ ሰርቶ አጠናቆ ከሌሎች ወንድም እህት ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ስለ ኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይ እጣ ፈንታ ለመምከርና ለመወሰን የሚያስችል ጥንካሬን ይዞ ለመዉጣት የሚያስፈልግ አስፈላጊ ጊዜ ነዉ፡፡ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ይህን ያልተሄደበት አዲስ መንገድ ለመተግበር የወሰነዉ አማራ-ጠሉ ጎራ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የአማራ ብሄርተኝነት መደበቂያ ዋሻ አድርጎ የመቁጠርና ሁለቱንም በአንድ ድንጋይ በማጥቃት የማሽመድመድ የቆየና የተካነበት ዘዴ ስላለ ከዚህ በተቃራኒ በመጓዝ ሁለቱንም ብሄርተኝነቶች ለማዳን በማሰብ ነዉ፡፡ በሌላ አባባል የኢትዮጵያና የአማራ ብሄርተኝነትን በዉል ያልነጣጠለ የትግል ስልት ለአማራ-ጠሉ ጎራ ጥቃት ምቹ ሆኖ መቅረብ ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ቀላቅሎ የመጣን የአማራ ብሄርተኝነት አማራ-ጠሉ ስርዓት ከመቅፅበት በትምክህተኝነት፣ በጨፍላቂነት እና በጠቅላይነት ፈርጆ አማራዉን የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በትግላቸዉ ያመጡትን የብዝሃነት ፖለቲካ ለመቀልበስ የሚሞክር የብሄረሰቦች ብሄራዊ ጠላት አድርጎ ያቀርባል፡፡ 

ይህ አደገኛ ፍረጃ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በየብሄራቸዉ ጎራ ገብተዉ ስለ ብሄራቸዉ መብት መከበር ብቻ ሲሰሩ የኢትዮጵያን ሃገረ-መንግስት የማስቀጠሉ እዳ በአማራ ህዝብ ጫንቃ ላይ ብቻ የወደቀ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የራሱን ብሄርተኝነት ያላሳደገዉ የአማራ ልሂቅም ይህን አደገኛ ሃላፊነት የሚቀበለዉ የአማራን ህዝብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መስዋዕት በማድረግ ሆኖ ኖሯል፡፡ አማራዉም ለኢትዮጵያ ቀጣይነት የሰራ መስሎት ይሄን እጅግ አደገኛ ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነትም ቢሆን ያልጠቀመ ሃላፊነት በመቀበሉም የሚተርፈዉ ምስጋና እና ሽልማት ሳይሆን “ከሌሎች ብሄረሰቦች የበለጡ ኢትዮጵያዊነት አለኝ የሚል ትምክህተኛ” የሚል ማሸማቀቂያ ነዉ፡፡ ይህ አስጠቂ የትግል ስልት የመአድና የመኢአድን ጉልበት ያዛለ ብቻ ሳይሆን አንድነት እና ሰማያዊ በሚባሉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ፓርቲ ጥላ ስር ገብተዉ ይታገሉ የነበሩ የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞችን በግል ሳይቀር ግራ ሲያጋባ የኖረ፣ዳግመኛ ሊኬድበት የማይገባ የሽንፈት መንገድ ነዉ፡፡ 

በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ የአማራ ህዝብ ትግል ሩቅ መንገድ በመጓዝ እራሱንም ኢትዮጵያንም ለመታደግ ከፈለገ በትግሉ የመጀመሪያዉ ወሳኝ አመታት (Formative Years) ሙሉ ትኩረቱን ማድረግ ያለበት በአማራ ብሄርተኝነት ጉዳዮች ብቻ ነዉ፡፡ በእነዚህ ወሳኝ ጊዜያት ስለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት እጣ ፈንታ የሚበይን ሆነ የሚያወሳ የትግል ስልት ለመተለም መሞከር “እራስ ሳይጠና ጉተና” ከመሆኑም ባሻገር ከአማራ-ጠሉ ጎራ በኩል በተለመደዉ ዱላ ተደጋሞ ለመመታት በተለመደዉ የስህተት መንገድ መመላለስ ነዉ፡፡ ስለሆነም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት መነሻዉን በአማራ ህዝብ ጥያቄዎችና በደሎች ላይ አድርጎ፣ በዛዉ ላይ በቂ ጊዜ ወስዶ ቆይቶ ዉስጠ ብሄር የቤት ስራዉን በስኬታማ መንገድ ፈፅሞ መዳረሻዉን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ጋር በመመካከር የፀናች የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስትን እዉን በማድረግ ላይ ያደርጋል፡፡ ፋኖነት የሆነዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ትግሉን ከዚህ ቀደም ባልተኬደበት መንገድ ማድረጉ ገና ከጅምሩ በርካታ አበረታች ዉጤቶችን እያስገኘለት ይገኛል፡፡ 

ከላይ የተገኙት ዉጤቶች የመጀመሪያዉ አዲሱ የትግል ስልት የአማራ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ነጥሎ ማቅረቡ አማራ-ጠሉ ስርዓት እንደለመደዉ የአማራብሄርተኝነት እና የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን አዳብሎ ለማሽመድመድ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይልቅስ የአማራዉ የብቻ ሃላፊነት መስሎ የኖረዉ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን የማስቀጠል ሃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን እንዲታወቅ ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን በአማራ በኩል ሲጠላና የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን ሲያንቋሽሽና አፈርሳለሁ እያለ ሲገለገል የነበረዉ አማራ-ጠሉ ጎራ የኢትዮጵያ ቀጣይነት የሚያስጨንቀዉ ሃገር ወዳድ መስሎ ቀርቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አማራ-ጠሉ ጎራ ከዚህ ቀደም በትምክህተኝነትና ጨፍላቂነት ዘለፋ አድበስብሶ ሲያልፋቸዉ ከነበሩ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች እና ሲፈራዉ ከኖረዉ እዉነተኛዉ የአማራ ብሄርተኝነት ጋር በግላጭ ለመፋጠጥ ተገድዷል፡፡ ይህ አካሄድ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነትም ሆነ ለአማራ ህዝብ መብት መከበር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነዉ፡፡ ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ላይ ሙሉ ትኩረቱን ማድረጉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ቸል ማለቱ ወይም ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አደጋ መሆኑን ሳይሆን የኢትዮጵያንም የአማራንም ህልዉና ለመታደግ የሚያስችል የድል መንገድ መሆኑን ነዉ፡፡ 

2.3 ስህተት መሰራት የሌለበት ነዉ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ስህተት መስራት የለበትም የሚለዉ መርሆ ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጋር ካለዉ መስተጋብር አንጻር ሲታይ የሚሰጠዉ ትርጉም በኢትዮጵያ ብሄርተኝነትና በአማራ ብሄርተኝነት መካከል ሊኖር የሚገባዉን ጤናማ ሚዛናዊነት በትክክል አስጠብቆ መራመድ መቻል ነዉ፡፡ የአማራ ህዝብም ሆነ ልሂቅ በታሪኩ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነትን በእጅጉ የሚፈልግ ለዚሁም በአፍ ሳይሆን በተግባር በርካታ መስዋዕትነትን የከፈለ ነዉ፡፡ ይህ አካሄድ በራሱ ጥፋት ያለዉ ነገር ባይሆንም የወቅቱን የሃገሪቱን የብሄር ፖለቲካ የጨዋታ ህግ ተረድቶ የአማራ ህዝብ እንደ ብሄር ያሉበትን አደጋዎች በማጤን በሁለቱ ብሄርተኝነቶች መካከል ሊኖር የሚገባዉን ጤናማ ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ አለመሞከሩ ግን ዉድ ዋጋ ያስከፈለ ስህተት ነዉ፡፡ 

የቀደመዉ ያልተመጣጠነ አካሄድ ስህተት ስለነበረ ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝትን እርግፍ አድርጎ መተዉም ሌላ አዲስ ስህተት መፍጠርም ይሆናል፡፡ ይህ ስህተት ከሚሆንባቸዉ በርካታ ምክንያቶች ሁለቱ ዋነኞች ናቸዉ፡፡ የመጀመሪያዉ የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ስሪት ዉስጥ የማይተካ ሚና ያለዉና የፖለቲካ ስነልቦናዉም ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ በመሆኑ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በመላዉ ኢትዮጵያ ተበትነዉ የሚኖሩ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነትም እነዚህ የአማራ ተወላጆች በሃገራቸዉ ላይ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸዉ ተከብረዉላቸዉ እንዲኖሩ ማስቻልን አልሞ የተነሳ ነዉ፡፡ ይህ የሚሳካዉ ደግሞ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ሲኖረዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የኢትዮጵያ ሃገረ መንግስትን መቀጠል በእጅጉ የሚፈልገዉ ነገር ነዉ፡፡ 

2.4 ማሸነፍን ብቻ ታሳቢ አድርጎ የሚሰራ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ቀዳሚ አላማዉ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን በህይወት የመኖር መብት የማስከበር ነዉ፡፡ የሰዉ ልጆች በህይወት የመኖር መብትን ማክበርና ማስከበር የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት መግባቢያ ቋንቋ መሆን ያለበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ዜጎች በሃገራቸዉ እንደልባቸዉ ተንቀሳቅሰዉ እንደልባቸዉ የመስራት ሰብዓዊ መብታቸዉ መጠበቅ ብቻ የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስትን ህልዉና ቀጣይነትን ያረጋግጣል፡፡ ዜጎች በገዛ ሃገራቸዉ የሆነ ቦታ ላይ መገኘታቸዉ የወንጀል ወንጀል ሆኖ በጭካኔ ሞት የሚያስቀጣ ከሆነ ኢትዮጵያ አለች ማለት አይቻልም፡፡ የዘር ማጥፋትን ማቆምና ማስቆም ያልቻለ መንግስት ህገ-መንግስታዊ ነኝ ማለት ቀርቶ ሰብዓዊ ነኝ የማለት ብቃት የለዉም፡፡ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በዋናነት ለአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት የሚታገል ቢሆንም በአጠቃላይ እሳቤ ደረጃ ግን የሁሉም ኢትዮጵያዉያን ሰብዓዊ መብት ያለ ቅድመ ሁኔታ መከበር መቻሉ ያገሪቱ ፖለቲካ መግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን አጥብቆ ይሻል፡፡ 

ይህ አይነቱ የዜጎችን የሰብዓዊ መብት የማስከበር ትግል ደግሞ አሸናፊነትን ብቻ አንግቦ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ምክንያቱም ትግሉ አሸናፊ መሆን ካልቻለ ዘር ማጥፋትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሃገራችን መንግስታዊ አስተዳደር ዘይቤ ሆኖ መቀጠሉ ነዉ፡፡ ዘር ማጥፋትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደ አዘቦት ተግባር የሚቆጥር መንግስታዊ አስተዳደር ደግሞ ሃገረ-መንግስት ሊያስቀጥል ከቶ አይቻለዉም፡፡ ስለዚህ የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበርን ክቡር አላማ ይዞ የተነሳዉ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አሸናፊ ይሆን ዘንድ ግድ ነዉ፡፡ 

3 በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች 3.1 “ከሌሎች ንዑስ ብሄርተኝነቶች በምን ይለያል?” 

ይህ ጥያቄ በሁለት አበይት ምክንያቶች ይነሳል፡፡ የመጀመሪያዉ ብሄርን ፖለቲካ ማድረግ በሃገራችን ላይ ያስከተለዉን ዉድመት ከመገንዘብ የሚነሳ ስጋት አዘል አጠያየቅ ነዉ፡፡ ይህ በራሱ ችግር ያለበት ነገር ባይሆንም በዉስጡ ያዘለዉ ስህተት ግን አለ፡፡ ስህተቱም ሃገራችን በብሄር ፖለቲካ ምክንያት የተጋረጠባትን የመፍረስ አደጋ ለማስቀረት አማራዉ በብሄር መደራጀት የለበትም፤ አማራዉ በብሄር መደራጀት ከጀመረ ሃገሪቷ መፍረሷ ነዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ የዚህ እሳቤ ሌላዉ ገፅ ኢትዮጵያ የቆመችዉ ወይም ልትቆም የሚገባት በአማራ ትከሻ ላይ ብቻ ነዉ የሚል ከእዉነታ የተፋታ አመክንዮ ነዉ፡፡ አስተሳሰቡ አደገኛ ዉጤት ያለዉ ስህተት ያዘለ ቢሆንም በአብዛኛዉ የአማራ ልሂቅና የኢትዮጵያን መቀጠል በሚሹ የሌሎች ብሄሮች ልሂቃን ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ ለረዥም ዘመናት ገዥ ሃሳብ መስሎ የኖረ እሳቤ ነዉ፡፡ 

ይህ እሳቤ ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ መሆኑን በዚህ ሰነድ 2.1 እና 2.2 ላይ በአጭሩ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ሃሳቡን እጅግ በአጭሩ ለማስታወስ ያህል አማራ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ተደራጅቶ የብሄር ፖለቲካዉን ሊታገል የሞከረበት አደገኛ አካሄድ ለአማራ-ጠሉ የብሄር ፖለቲካ ቀሳዉስት የምቾት ከባቢ (Comfort Zone) ሆኖላቸዉ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እና የአማራ ህዝብ አዳብለዉ በመቀጥቀጥ ሁለቱንም ለማሽመድመድ ያስቻላቸዉ የተካበት መንገድ ነዉ፡፡ 

በተጨማሪም ይህ ስልት ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አይነተኛ ጉልበት የሆነዉ የአማራ ህዝብ እያለፈበት ያለዉን አሰቃቂ ጥቃት እና የህልዉና አደጋ እንደሌለ አድርጎ በመካድ እዉነተኛ ባልሆነ የደህንነት ስሜት ዉስጥ እራሱን እያታለለ ሲጓዝ የኖረ አካሄድ ነዉ፡፡ በመሆኑም የትግል ስልቱ ከእዉነት የተጣላ እና ፍሬ ቢስ ሆኖ ቀርቷል፡፡ 

ይህ የትግል ስልት በሃገራችን ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ፖለቲካ ዉስጥ እዚህ ግባ የሚባል ተጽኖ የሌለዉ ሆኗል፡፡ የዚህ የትግል ስልት መንገደኛ ከሆኑ ድርጅቶች ዋናዉ የሆነዉ ኢዜማ የተባለዉ ፓርቲ ደግሞ ስልጣን ላይ ያለዉ አማራ-ጠል ዘረኛ ስርአት ገባር ሆኖ ከመግባቱ ባሻገር በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለዉን ግልፅ ዘር ማጥፋት በአደባባይ ክዷል፡፡ የኢዜማ ለብሄር ፖለቲካዉ ግብር መግባት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነቱን ጎራ መጠጊያ አልባ ከማድረጉም በላይ ስልጣን ላይ ያለዉ ዘረኛ ስርዓት “ተፎካካሪ” ፓርቲን ስልጣን እስከማጋራት የደረሰ “ዲሞክራሲያዊነት” እንዳለዉ እያነሳሳ ሰሚን የሚያሰለችበት የፕሮፓጋንዳ ሲሳዩ ሆኗል፡፡ 

“የአማራ ብሄርተኝነት ከሌሎች ብሄርተኝነቶች በምን ይለያል?” የሚለዉ ጥያቄ የሚነሳበት ሁለተኛዉ ምክንያት ሸር የማያጣዉ፣ አዉቆ ማደናቆር እና ፍርደ-ገምድልነት የተጣመሩበት ነዉ፡፡ በዚህ ጥያቄ ዉስጥ ያደፈጠዉ የፖለቲካ ሸር በአማራ ህዝብ ላይ ዘር ማጥፋት ወንጀል እየሰራ ያለዉን አማራ-ጠል ስርአትና ይህንኑ ለመከላከል የተፈጠረዉን የአማራ ብሄርተኝነት በእኩል የጥፋተኝነት ወንበር የሚያስቀምጥ ነዉ፡፡ በሌላ አባባል ጥያቄዉ ገዳይና ሟችን በአንድ ላይ 

አዳብሎ፣ በዉስጠ ታዋቂ ለገዳይ የሚወግን ነዉ፡፡ ይህ እሳቤ የረሳዉ ነገር የአማራ ብሄርተኝነትን እና ሌሎች ንዑስ ብሄርተኞችን የፈጠረዉ ምክንያት ሰፊ ልዩነት ነዉ፡፡ በርግጥ ይህ እሳቤ እንደሚለዉ የአማራ ብሄርተኝነት ንዑስ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ ነገር ግን ዋናዉ ነጥብ አማራዉን ለንዑስ ብሄርተኝነት የጋበዘዉ የተደቀነበት የዘር ማጥፋን የሚያክል የሞት ሽረት ጉዳይ እንጂ እንደሌሎቹ በፋሽት ጣሊያን አማራ-ጠል ፕሮፓጋንዳ ላይ ተሸፍኖ በቀላሉ ስልጣን ላይ የመፈናጠጥ የስልጣን ጥም አይደለም፡፡ 

እነዚህ ጠያቂዎች ግን የመነሻዉን ልዩነት አዉቀዉ ትተዉ መጨረሻዉ ከብሄርተኝነት ስለሆነ የአማራም፣ የህወሃትም፣ የኦነግም ብሄርተኝነት ያዉ ብሄርተኝነት ነዉ ሲሉ ያደናቁራሉ፡፡ ይህን ሲሉም አማራዉ ንዑስ ብሄርተኛ ላለመባል ዝም ብሎ የማለቅን አማራጭ ብቻ ያቀርቡለታል፡፡ 

በአጠቃላይ ይህ ጥያቄ የመነጨበት እሳቤ አንድ ክፉ ድርጊት (Action) አፀፋዊ እራስን የመከላከል ድርጊት (Reaction) የማስከተሉን አይቀሬ ሃቅ የካደ የጠላት በለሃ ልበልሃ ነዉ፡፡ ይህን በማድረግ ወይ ዝም ብሎ እንዲሞት እታገላለሁ ካለ ደግሞ ግልፅ የሆነዉን የትግሉን ምክንያት አዉቆ ለተፃፈና ጆሮ በማስረዳት እንዲባዝን የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡ 

በአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች ምንጫቸዉ ምንም ይሁን ምን ጥያቄዉ እስከተነሳ ድረስ ቢያንስ አንድ ጊዜ ለዋነኛ ጥያቄዎች መልስ መስጠቱ ለአማራዉ ትግል ብርታት ይሆናል እንጅ ጉዳት ስለሌለዉ ወደዛዉ እንለፍ፡፡ የአማራዉ ብሄርተኝነት ከሌሎች ንዑስ ብሄርተኞች የሚለይበት በርካታ ሃቆች አሉ፡፡ 

የመጀመሪያ- የአማራ ብሄርተኝነት ግልፅ ከሆነ መንግስታዊ ዘር ማጥፋት ወንጀል የተነሳ የታለፈባቸዉ ተጨባጭ የህይወት ተሞክሮዎች (lived experiences) በመነሳት የተተለመ እራስን የመከላከል የአፀፋ ብሄርተኝነት መሆኑ ነዉ፡፡ ስልጣን የያዘዉ አማራ-ጠል ስርዓት የብሄረ-ኢትዮጵያ ርዕዮትን ከማበሻቀጥ አልፎ የብሄረ ኢትዮጵያ መድህን አድርጎ ሰፈዉን የአማራ ህዝብ በህይወት የመኖር መብት እስከመግፈፍ የደረሰ፣ግዴታን ያላገናዘበ የመብተኝነት አዉዳሚ ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ የአማራ ብሄርተኝነትን ወለዱ ይህ አዉዳሚ ጉዞ በመግታት እራስን የመከላከል ተገቢ ፍላጎት ነዉ፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ንዑስ ብሄርተኝነቶች በተለይ ህወሃትና ኦነግ በብሄር መደራጀት በቀላሉ የህዝብን ስሜት አገንፍሎ ለስልጣን ስለሚያበቃ የመረጡት መንገድ እንደሆነ መሪዎቻቸዉ በግልፅ የተናገሩት ሃቅ ነዉ፡፡ በአማራ ህዝብ አንፃር ህዝብን በብሄር ማደራጀት ቀላል እንዳልሆነ የአማራ ብሄርተኝነትን እዉን ለማድረግ የፈጀዉ ረጅም ዘመን ምስክር ነዉ፡፡ 

በአጠቃላይ የአማራ ብሄርተኝነት በግልፅ እየደረሰበት ያለዉን አደጋ ለማስቆም ሲባል በጣም ከረጅም ዘመን በኋላ የተጀመረ እንጂ እንደ ህወሃትና ኦነግ ንዑስ ብሄርተኝነቶች በፍጥነት የስልጣን ማማ ላይ ለመሰየም ቀላሉ መንገድ ነዉ ተብሎ ተመርጦ እዉነቱንም ዉሸቱንም እየተደበላለቀ የተሸመነ የሀሰት ሸማ አይደለም፡፡ 

ሁለተኛዉ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት መፈጠርም ሆነ መቀጠል ጋር ምንም ጠብ የሌለዉ መሆኑ ነዉ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት የብሄር-ኢትዮጵያ ርዕዮትን አንግቦ ለሃገረ-መንግስቱ ቀጣይነት በሙሉ ልቡ የሚሰራ ነዉ፡፡ የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ህዝብ ከብሄረ-ኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ጥብቅ የስነ-ልቦና ቁርኝት ስለሚያዉቅ ከህዝብ ስነ-ልቦና በተቃራኒ የመሄድ እብሪት ስለሌለዉ ነዉ፡፡ በተጨማሪም አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አንዱ አላማዉ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆችን መብት ማስከበር ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህን አላማ ለማሳካት የኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት ጥያቄ ዉስጥ የማይገባ ነገር ነዉ፡፡ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከብሄር ኢትዮጵያ ርዕዮት ጋር የማይጣላ ይልቅስ ተደጋግፎ የሚሄድ ነዉ ሲባል የሚነሳ ሌላ ጥያቄ አለ፡፡ ይኸዉም የንዑስ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ግራ ዘመም ስለሆኑ የአማራ ብሄርተኝነትም ግራ ዘመም መሆን አለበት፤ግራ ዘመም ሆኖ ደግሞ ስለ ሃገረ-መንግስት ቀጣይነት አስባለሁ ማለት አብሮ አይሄድም የሚል ነዉ፡፡ ይህን ጥያቄ የሚያነሱ አካላት በአመዛኙ የህወሃትና የኦነግ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ደጋፊዎችና ወዳጆቻቸዉ ናቸዉ፡፡ ኦነግና ህወሃት ትግላቸዉን የጀመሩት ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት በመክሰስ ነበር፡፡ ትግላቸዉን ሲያጣጡፉ የነበረዉም ኢትዮጵያን መፍረስ ያለባት የአማራ ስሪት እንደሆነች በመደስኮር ነዉ፡፡ 

ይህን ሲሉ በነበረበት አንደበታቸዉ ደግሞ ስልጣን ሲይዙ ኢትዮጵያ ተጠብቃ መኖር ያለባት ዉብ ሃገር እንደሆነች መለፈፍ ጀመሩ፡፡ ስልጣን ላይ ቁጭ ብለዉ ሲያዩዋት ብቻ የምታምራቸዉን ኢትዮጵያን በተመለከተ ትላንት ምን እያሉ ሲያበሻቅጥዋት እንደነበር የሚያስታዉቸዉ ሲገኝ ደግሞ ያንን የተናገሩት ብስለት በማጣት እንደሆነ ሲያስረዱ ይገኛሉ፡፡ 

ይህንን አቋም የለሽ የፖለቲካ ዘይቤያቸዉን ነዉ የግራ ፖለቲካ ተከታይነት አድርገዉ የሚያስቡት፡፡ የሆነዉ ሆኖ ስልጣን ከመያዛቸዉ በፊት በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ ሲያወርዱት የኖሩት የጥፋት ዉርጅብኝ የግራ ዘመምነት የፖለቲካ ዘይቤ ነዉ ከተባለ እንኳን ያንን አቋማቸዉን ይዘዉ አልዘለቁ፡፡ አሁን ላይ ከስልጣን ጥፍጥና የተነሳ የቀኝ ፖለቲካ መንገደኛ ነን እያሉ ጭራሽ አማራዉ ሃገር እዳያፈርስ እንሰጋለን እያሉ ነዉ፡፡ በአንፃሩ አማራዉ የእራሱን ብሄር-ተኮር ጥያቄ ለማስመለስ ኢትዮጵያን ማበሻቀጥ ግድ እንዳልሆነ ከበፊትም ጀምሮ ያዉቅ ነበር እና ዛሬም ድሮም ኢትዮጵያን ሳያዋርድ፣ ክፏን ሳያወራ በነበረበት ትክክለኛ መንገድ ላይ ቆሞ ከገዛ ሃገሩ ሊያገኘዉ የሚገባዉን መብቱን ብቻ እየጠየቀ ይገኛል፡፡ 

ሶስተኛዉ- የአማራ ብሄርተኝነት የትኛዉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ በጠላትነት ያልፈረጀ መሆኑ ነዉ፡፡ በህወሃት ኦነግ የተመሰረተዉና በሌሎች አማራ-ጠል ብሄርተኞች የተጠናከረዉ አማራ-ጠሉ ስርአት በአማራ ህዝብ ላይ የማይነገር በደል ቢያደርስም የአማራ ብሄርተኝነት በስርዓትና በህዝብ መካከል ያለዉን ልዩነት ከጅምሩ ያጤነ ስለሆነ ምንም አይነት የበቀልተኝነት ዝንባሌ የሌለዉ እንደሚሆን መግባባት የተያዘበት ነገር ነዉ፡፡ ከሁሉም በላይ አማራ-ጠሉ ስርዓት በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሰዉን ወንጀል ሁሉ እንዲያደርስ በብአዴን/አማራ ብልፅግና ፓርቲ ዉስጥ የተሰገሰጉ የአማራ ተወላጅ ፖለቲከኞች ያበረከቱት ሚና ከህወሃትና ኦነግ ፖለቲከኞች የማያንስ ነዉ፡፡ ይህ በመሆኑም የአማራ ብሄርተኝነት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ለመፈረጅ እንደማይችል ሁሉ ሌላዉ ኢትዮጵያ ህዝብም በጠላትነት ሊፈርጅ አይሞክርም፡፡ 

3.2 “የአማራ ብሄርተኝነት ጠመንጃ ያነሳ ስለሆነ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነዉ” 

ይህን ሃሳብ ለመሞገት ቀዳሚ ሆኖ መምጣት ያለበት ነገር አማራዉ ለምን ጠመንጃ አነሳ? ጠመንጃ ከማንሳቱ በፊት ለሩብ ምዕተ ዓመት መታገሱ ምንን ያሳያል? የሰዉ ልጅ ህይወቱን ከዘር ማጥፋት ስጋት ለማዳን እራሱን ባገኘዉ መንገድ ሁሉ መከላከል ሌላ ሊያደርገዉ የሚችለዉ ሌላ አማራጭ አለ ወይ? 

እራሱን ለመከላከል ጠመንጃ ካነሳዉ የአማራ ብሄርተኝነትና በሰላማዊ ሰዎች ላይ አማራ በመሆናቸዉ ብቻ ዘር ማጥፋን ከሚፈፅመዉ ስርኣት የትኛዉ ነዉ ቀድሞ ዲሞክራሲን የገደለዉ የሚሉ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት እራሱን ለመከላከል ጠመንጃ ማንሳቱ የማይካድ ሃቅ ነዉ፡፡ እራስ መከላከል ደግሞ ተፈጥሮአዊ መብት ነዉ፡፡ ዋናዉ ጥያቄ መሆን ያለበት ጠመንጃ የተነሳበት ምክንያት ነዉ፡፡ በአንድ ዘወትራዊ ተጠያቂነትና በአንድ ስርዓት የሁልጊዜ አጥቂነት መስተጋብር የሚፈጠር ዲሞክራሲ የለም፡፡ ስለዚህ አማራዉ ያነሳዉ ጠመንጃ ዲሞክራሲን ለመግደል ሳይሆን እራስን ለመከላከል መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ 

3.3 “የአማራ ብሄርተኝነት በአዉራጃዊነት የተከፋፈለ ነዉ” 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ዋነኛ ማንነቱ የፋኖ ትግል ነዉ፡፡ ፋኖነት የሆነዉ የአማራ ህዝብ ትግል የተፋፋመዉ አማራ-ጠሉ ስርዓት በአማራ ህዝብ ላይ ሲያደርስ የኖረዉ በደል እያደር ቅጡን አጥቶ፣ ሊታገሱት የማይቻል ደረጃ ላይ በመድረሱ ከዚህ በኋላ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ የሚያስከትለዉን በመረዳት ነዉ፡፡ አንገት ላይ በደረሰዉ ስርዓታዊ ግፍና በደል በአስቸኳይ መፍትሄ ለማምጣት ቆርጦ የተነሳዉ የፋኖ ታጋይ ትግሉን የጀመረዉ በየአካባቢዉ በመሰባሰብ ነበር፡፡ ይህ የፋኖ ትግል ለህወሃት የትግል ዘይቤ በእጅጉ የተለየ ያደርገዋል፡፡ 

በህወሃት ሁኔታ በመጀመሪያ የተወሰኑ የትግራይ ተወላጅ ልሂቃን ከየዩንቨርሲቲዉ አቋርጠዉ በመዉጣት የትግሉን አስኳል በመመስረት የመሪነቱን ሚናም አብረዉ ወሰዱ፡፡ ቀጥለዉም ለትግሉ ሰራዊት የሚሆኑ ታጋዮችን ከመላዉ ትግራይ መመልመል ጀመሩ፡፡ በመሆኑም ትግሉ በአንድ የእዝ ማዕከል የሚመራ፣ከሞላ ጎደል የእዝ ተዋረዱ የሚታወቅ ነበር፡፡ በአማራ ፋኖ ትግል ሁኔታ ግን ትግሉ እራሱ የተጀመረዉ ስርዓታዊዉ በደል አማራ በተባለዉ ህዝብ ቤት ሁሉ በነፍስ ወከፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመግባቱ ህዝቡ ባልተጠበቀ ሁኔታ በጅምላ የተነሳበት ነዉ፡፡ በመሆኑም እንደ ህወሃት በመጀመሪያ ሰባት ስምንት ሰዎች ጫካ ገብተዉ የሆነዉንም ያልሆነዉንም የሚያወሳ የማታገያ ማኒፌስቶ ፅፈዉ ህዝቡን ጎትተዉ ወደ ትግል ማስገባት አላስፈለገም፡፡ 

ይህ የሚያሳየዉ የአማራ ፋኖ ትግል ከፕሮፖጋንዳና ከልሂቃን ጉትጎታ የመነጨ ሳይሆን ከህዝብ እዉነተኛ ምሬት የተነሳ በራሱ በህዝቡ ተፈጥሮአዊ የነፃነት ፍላጎት እየተገፉ በስተመጨረሻ የማይቀለበስ ሙላት ላይ የደረሰ ፍትሃዊ ትግል እንደሆነ ነዉ፡፡ በመሆኑም የአማራ ፋኖ ትግል ከመላዉ አማራ ግዛት በተነሱ ታጋዮች የተጀመረና ቀስ በቀስ ወደ መያያዝ የሚመጣ የትግል አይነት ነዉ፡፡ 

የአማራ ፋኖ ትግል ከማእከላዊ እዝ የሚመራ አለመሆኑ ትግሉ ህዝባዊ እንጂ መንግስት እየለፈፈ እንዳለዉ የልሂቃን ብቻ እረብሻ እንዳልሆነ ያመለክታል፡፡ ትግሉ ከማእከላዊ እዝ የማይነሳ ይልቅስ ህዝቡ በየአካባቢዉ በመሰባሰብ ለህልዉና ለመታገል የወጣበትና መሪዎቹንም ከዚያዉ ከስብስቡ ቀስ እያለ እየመረጠ መሄዱ በአንዴ ማዕከላዊ አመራር ለማምጣት የማያስችለዉ መሆኑ አዉቆ ላልተኛ ሁሉ ግልፅና ቀላል ሃቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ የፋኖ ትግል ከአንድ ማእከላዊ ዕዝ የማይመራ መሆኑ ከትግሉ _ አጀማመር ተፈጥሮ የሚመነጭ እንጂ አማራ የተለየ የአዉራጃዊነት ፍቅር ያለበትና አንድ መሆን የማይችል ህዝብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ይህም ማለት የሰዉ ልጅ ከአካባቢዉ ጋር ያለዉ ጥብቅ ትስስር በአማራ ህዝብ ዘንድ የለም ማለት አይደለም፡፡ አካባቢያዊነት ድል አድርጎ ስልጣን ለመያዝ በቻለዉና ከዉጭ ሲያዩት ፍፁም አንድነት የሚያሳይ በሚመስለዉ፣ በትግል አጀማመር ዘይቤዉም በመጀመሪያ ማዕከላዊ እዙን አዘጋጅቶ ትግሉን በጀመረዉ ህወሃት ዉስጥም ይንፀባረቅ የነበረ የሰዉ ልጆች ሁሉ ዝንባሌ ነዉ፡፡ ዋናዉ ነገር አካባቢዊነት ዋናዉን የትግል አላማ ማስረሳት መቻል ያለመቻሉ ጉዳይ ነዉ፡፡ የአማራ ፋኖ ትግል ከዚህ አንፃር ሲገመገም መነሳት ያለበት ምክንያታዊዉ ግምገማ ትግሉ ከተጀመረበት እስከዛሬ ባለዉ በጣም አጭር የሚባል ጊዜ ትግሉን በመሪዎች ስር የማሰባሰቡ አኳያ እየተወሰደ ያለዉ እርምጃ ምን ያህል አበረታች ነዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ተስፋ ሰጭ እርቀቶችን የሄደ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ 

አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ከሚመራባቸዉ ጥብቅ መርሆዎች አንዱ የቀደመ ስህተትን መድገምም ሆነ አዲስ ስህተት መሰራት የለበትም የሚለዉ ነዉ፡፡ ከአማራ ብሄርተኝነት የቀደሙ ስህተቶች አንዱ ደግሞ የተሸከሙትን የህዝብ አደራ በጠንካራ ታማኝነትና ዲስፕሊን ዳር የማድረስ ሁለንተናዊ ብስለትና ጥንካሬን የተላበሱ መሪዎችን የማግኘት ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህ አደገኛ ስህተት ለማረም ትግሉ በሁነኛ መሪዎች እጅ እንዲገባ ጊዜ ወስዶ በከፍተኛ ጥንቃቄ መሰራት እንዳለበት መግባባት ላይ የተደረሰበት ጉዳይ ነዉ፡፡ ስለዚህ ትግሉ ማዕከላዊ አመራር አለዉ እንዲባል ብቻ ሲሮጡ የመታጠቅ ስራ ከመስራት መቆጠቡ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ ትግሉን ከቀደሙ ክሽፈቶች ለመታደግ ሲባል የሚደረግ የጥንቃቄ ጉዞ ብአዴን ስፖንሰር እያደረገ ሲያራግበዉ ከኖረዉ አላማ ቢስ መንደርተኝነት ለይቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡ 

አማራ-ጠሉ ስርዓት የአማራ ፋኖ ትግል የተበጣጠሰና መሪ የሌለዉ እንደሆነ እየለፈፈ እራሱን የሚያፅናናበት አካሄድ መሪዎቹን ካወቀ በኋላ ህወሃት በጀግናዉ ጎቤ መልኬ ላይ ያደረገዉን አይነት እና ሌሎች ሸሮች ተጠቅሞ መሪዎቹን በማጥፋት ለመበተን ካለዉ ፍላጎት አንፃርም መታየት አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ትግሉ መሪ እንኳን የሌለዉ ተራ ረብሻ ነዉ ብሎ ለማጣጣል ሲባል የሚደጋገም ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ለማንም ሊሰወር አይገባም፡፡ የሆነዉ ሆኖ የአማራ ፋኖ ትግል ከተጀመረበት ጊዜ ይልቅ ዛሬ በተሻለ የመሰባሰብና የመናበብ ፈለግ እያያዘ ያለ፣በቅርብ ጊዜም የህዝብን ትግል በምስር ወጥ የማይሸጡ ሁነኛ መሪዎችን ይዞ የመምጣት ጥንቃቄ የተሞላበት ስራ ላይ ያለ ተስፋ ሰጭ ትግል ነዉ፡፡ 

መቋጫ 

ለአንድ ህዝብ መብት መከበር ተብሎ የሚደረግ ትግል የሚታገልለትን ህዝብ ፖለቲካዊ ስነልቦና ባገናዘበ መንገድ በተነደፉ የትግል መርሆዎች መመራት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ትግሉ በልሂቃን ስሜት ተደምሮ የእነሱን የግል ጥቅም በማርካት ፍሬ-ቢስ መደምደሚያ ይጠቀማል፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ የተነሱት ትግል መሳይ ነገሮች መጨረሻ ከዚህ የራቀ አልነበረም፡፡ እነዚህ ትግሎች የህዝቡን ማህበረ-ፖለቲካዊ ስነ-ልቦና ያገናዘበ የሁኔታ ትንተና ሳይሰሩ ወደ ትግል የገቡ በመሆናቸዉ ብዙ ስህተቶችን ሰርተዋል፡፡ ከእነዚህ ስህተቶችን ዋነኛዉ በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ ይነገር የነበረዉ አደገኛ ማጣጣል፣ዉርጅብኝ እና በቀኝ ገዥነት እስከመፈረጅ የደረሰ አዕምሮ የጎደለዉ የአዉዳሚነት አካሄድ ነዉ፡፡ ይህን አደገኛ አካሄድ በማራመዱ ረገድ ህወሃትና ኦነግ ዋነኞቹ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ላይ የመዘዙት አዉዳሚ ፍላፃ ቀድሞ ያገኘዉ የአማራን ህዝብ ነዉ፡፡ እነዚህ በአማራ በኩል ኢትዮጵያን የሚጥሉ ንዑስ ብሄርተኞች ዋኖቻቸዉን ህወሃትና ኦነግን አስቀደመዉ በአጠቃላይ ግን እራሳቸዉን “የፌደራሊስት ሃይሎች” ብለዉ ይጠራሉ፡፡ 

እነዚህ ሃይሎች በአማራ ህዝብ ላይ ያደረሱት በደል ማቆሚያ ማጣቱ ነዉ አዲሱን የአማራ ብሄርተኝነት የፈጠረዉ፡፡ ሆኖም የአማራ ህዝብ አዲሱ የትግል ዘይቤ የእነዚህ ሃይሎች ስህተት መድገምን አልመረጠም፡፡ ይልቅስ ከዚህ አዉዳሚ ጎራ ስህተቶች ትምህርት በመዉሰድ ትግሉን በታሰበበትና በሰከነ መንገድ ማስኬድን መርጧል፡፡ በመሆኑም የሚታገልለት የአማራ ህዝብም ሆነ መላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ በረዥም ዘመን የሃገረ-መንግስት የታሪክ ዘመኑ ያዳበራቸዉ ሃይማኖታዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስነ-ልቦናዎች በማክበር እንጅ ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ ሃገርን በማጣጣል የህዝብን አብሮ የመኖር ፍላጎት በመናቅ የሚደረግ ትግል የትም እንደማያደርስ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት በዉል ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ያለዉን ጥብቅ ቁርኝት ማስቀጠል የአዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት መርህ ነዉ፡፡ 

ሆኖም ይህ ቁርጠኝነት ከዚህ ቀደም እንደነበረዉ የአማራን ህዝብ ብሄር-ተኮር ጥያቄዎች ለማዳፈንበአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሱ ግልፅ በደል ለማጥፋት የሚዉል የአማራ-ጠሉ ስዓት ዋሻ እንዲሆን አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት አይፈቅድም፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግም እንደ ዋነኛ የትግል ስልት የወሰደዉም የአማራ ብሄርተኝነትን ከኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ነጥሎ በማዉጣት የአማራን ህዝብ አንገብጋቢ የህልዉና ጥያቄዎችን ጥርት ባለ መንገድ ግልፅ ማድረግና ለጥያቄዎቹ መልስ ለማግኘት የሚያስችል ጠንከር ያለ የአማራ ብሄርተኝነት ትግል ማድረግ ነዉ፡፡ ይህ ሲደረግ የአማራ ብሄርተኝነትን በተገቢዉ መንገድ ማጠናከር የሚቻልበትን በቂ ትኩረትና ጊዜ መዉሰድ በምንም ሊተካ የማይገባዉ የትግሉ አንጓ መሆኑ ታምኖበት ነዉ፡፡ ይህ አዲስ የትግል ስልት በአማራ ልሂቃን ሲደረግ የተለመደ ስላልሆነ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ሙሉ ትኩረቱን አድርጎ መሰራቱ ኢትዮጵያን በመካድ ሊያስከስስ እና በፅንፈኝነት ሲያስፈርጅ መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህ ችላ ብሎ በዋናዉ አላማ ላይ ማተኮር ሊያነጋገር የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ ምክንያቱም አማራዉ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ፅናት ያለዉን ታማኝነት የደም ዋጋ እየከፈለ አሳይቷልና ዛሬ ገና እንደ አዲስ ኢትዮጵያን ምን ያህል እንደሚወድ ለማሳየት የተደቀነበትን የህልዉና ስጋት ለመቀልበስ የጀመረዉን ትግል መተዉ የለበትም፡፡ በምትኩ ለኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ፅናትና ቀጣይነት ያለዉን ታማኝነት ማሳየት ያለበት ኢትዮጵያን ሲያበሻቅጥ የኖረዉ አማራ-ጠሉ የፌደራሊስት ሃይል ነኝ የሚለዉ ጎራ ነዉ፡፡ ይህ ጎራ ኢትዮጵያን የዘረኝነቱ መሸፈኛ የማድረግ አደገኛ ዝንባሌ ያለዉ ከመሆኑም በተጨማሪ ኢትዮጵያን እወዳለሁ የሚለዉ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ሲዘርፋት ብቻ መሆኑን አስመስክሯል፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ ሃገረ-መንግስት ጋር ያለዉ መስታግብር ምን ያህል ጤነኛ እንደሆነ በተግባር ማስመስከር ያለበት ይህ የማይታመን ሃይል እንጅ የአማራ ህዝብ አይደለም፡፡ 

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የዲዛይን ችግር የሚያንገላታው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
መስከረም 9 2013 ዓ ም

ኢህአዴግ የሚባለው ህወሃትን የሶስት ዋነኛ፣የአምስት ምክትል ሎሌዎች ጌታ አድርጎ የኖረው ፓርቲ ፈርሶ ብልፅግና በሚባለው ፓርቲ ሲተካ የሃገራችን ፖለቲካ የተሻለ መስመር ይይዛል ብለው ተስፋ ካደረጉት ወገን ነበርኩ፡፡የተስፋየ ምክንያት በርካታ ነው፡፡አንደኛው የሃገራችን ፖለቲካ በቀላሉ እርምት ሊያገኝ የሚችለው እንዳይሆን አድርጎ ያበላሸው ኢህአዴግ ራሱ እንዳበላሸው አድርጎ ካስተካከለው  ነው በሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ ህዝባዊ ለውጡን ከውስጥ ሆነው ያገዙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ለውጥ የፈለጉት በአንድ ጌታ ስር ማደር ሰልችቷቸው፣በራስ እምነት የመኖር ክብሩ ተገልጦላቸው መስሎች ነበር፡፡ ሶስተኛው ምክንያቴ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እንሰራለን ሲሉ የኢህአዴግ ሰዎችንም ቢሆን እስከማመን የሚደርስ ተላላነት ስላለኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ ሃገራችንን ከህወሃት/ኢህአዴግ መዳፍ ማላቀቁ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ስላልሆነ ለውጥ ልናመጣ ነው ያሉ ሰዎችን ጊዜ ሰጥቶ ማየቱ ጥፋት አይደለም፡፡ 

ብልፅግና የተባለው ፓርቲ ሲመሰረት የሃገራችንን ሁለንተናዊ ችግር ይፈታል የሚል የጅል ተስፈኛ እንደማይኖር እሙን ነው፡፡ ተስፋው ቢያንስ እንደ ህወሃት ሰማይ የደረሰ ጌታ እና እንደ አጋር/አባል ፓርቲዎቹ ትቢያ ላይ ተንበርክኮ “አቤት ወዴት” የማለትን ያህል የተራራቀ የአዛዥ ታዛዥ ግንኙነት በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ አይደገምም የሚል ነበር፡፡ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ ተራርቆ የኖረውን የጌታ እና የሎሌ የፖለቲካ መስተጋብር ለማቀራረብ ይረዳል ብየ በግል አስበው የነበረው ከውጭ ሆነው ሲያዩት በኦህዴድ እና በብአዴን መኳንንት ዘንድ የመጣ የመሰለው የእሳቤ ለውጥ ነበር፡፡

ይህ ለውጥ ከኦህዴድ አኳያ የበለጠ ታግያለሁ ብሎ ለስድነት የሚዋሰን ጌትነት መሻት መጨረሻው እንደ ህወሃት መሆን እንደሆነ መረዳት አያዳግተውም የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ ከብአዴን አንፃር የድሮው ብአዴን ሆኖ በአማራ ህዝብ ትከሻ ላይ ለአንድ ተጨማሪ ወር እንኳን መኖር የማይታሰብ እንደሆነ እንደው በጥቂቱም ቢሆን መገንዘብ ተችሏል በሚል ነበር፡፡ሆኖም የኦሮሚያ ብልፅግና ሆኛለሁ ያለው ኦህዴድም  ሆነ የአማራ ብልፅግና ተብየ የአማራን ህዝብ እመራለሁ የሚለው ብአዴን ካድሬዎች ያሰብነውን ለውጥ በሚያመጣ መንገድ የተለወጡ አልሆኑም፡፡ 

አለመለወጡ የሚብሰው ግን በብአዴን ላይ ነው፡፡ ኦህዴድ ተቀይሮ የህወሃትን ቦታ ልያዝ እያለ እንደሆነ ሽመልስ አብዲሳ አይሰማም መስሏቸው ካወሩት ብቻ ሳይሆን እነ ታከለ ኡማ ከሚተገብሩት ሁሉ መረዳት ይቻላል፡፡በርግጥ መለወጥ ሁሉ መልካም አይደለም፤ወደ ህወሃትነት መለወጥ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

መለወጥ በፊቱ ዝር የሚል የማይመስለው የአማራ ብልፀግና ፓርቲ ነው፡፡ይህ ፓርቲ ከተለወጠም የሚለወጠው ወደ ብአዴንነት ወይም ኢህዴንነት ነው፡፡የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አለመለወጥ፣ከተለወጠም ወደ በጎ አለመለወጥ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋነኛው ምክንያት ግን ሲፈጠር ጀምሮ የተጠናወተው የዲዛይን ችግር ነው፡፡ይህ የብአዴን ዋነኛ ደዌ የሚመነጨው ብአዴንን ዲዛይን ካደረገው ህወሃት ሆኖ ተሰሪውን ብአዴንን ለማይድን በሽታ አሳልፎ ሰጥቶት ቀርቷል፡፡የብአዴን ነገር በእናቱ ሆድ ሲጠነሰስ ጀምሮ ለአንዳች አካላዊም ሆነ አእሯዊ ልምሻ ተጋልጦ መላ አካላቱ እንዳልሆነ ሆኖ የተወለደን ህፃን ልጅ ይመስላል፡፡ከእናቱ ሆድ ሲወጣ በተበላሸ የአካል ቅርፅ የተወለደ ልጅ የትኛውንም ህክምና ቢያገኝ ጤነኛ ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡ይህን አይነት ልጅ ጤነኛ ለማድረግ የሚደረገው ድካምም ከንቱ ድካም ነው፡፡   

ህወሃት ብአዴንን ሲሰራው የተሰራበትን አላማ እያመከነ እንዲኖር ነው፡፡ይህም ማለት  ብአዴን የተፈጠረው ለሰፊው የአማራ ህዝብ መብት መከበር ነው የሚል የይስሙላ ፕሮፖጋንዳ ነገር ነበረ፡፡ ሆኖም በእውነታው ዓለም ብአዴን የቆመው ይህን አላማ ለማምከን፣አማራውን ያለ እውነተኛ መሪ ለማስቀረት ነው፡፡ከአላማ በተቃራኒ መቆም ማለት ይህ ነው፡፡ይህን ደግሞ ከብአዴን በላይ የቻለበት ፓርቲ የለም፡፡ 

ህወሃት ብአዴንን ሲፈጥረው አማራ ሁሉ ጨቁኖኛል፣አማራ ሁሉ ጠላቴ ነው የሚለውን እሳቤውን ከልቡ ሳይፍቀው ግን ለአፉ ጭቁኑ አማራ ምንም አላደረገኝም ጠላቴ የአማራ ገዥ መደብ ነው ማለት የጀመረ ሰሞን ነው፡፡ህወሃት የሆዱን በሆዱ አድርጎ ድንገት ጭቁን ነህ ላለው ሰፊው የአማራ ህዝብ  ወኪል ይሆን ዘንድም ኢህዴንን “ብአዴን” ሲል ጠራው፡፡”ከዛሬ ጀምሮ ብአዴን ትባላላችሁ” የተባሉት መኳንንትም ከማኒፌስቶ 68 ጀምሮ እስከ ሽግግር ቻርተር ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ መርገም ሁሉ ምክንያቱ አማራ ነው የሚለውን የጌታ ህወሃትን የፖለቲካ ዘፍጥረት ያነበነቡ ጀመር፡፡

ድርጅቱን እንዲመሩ የተሰየሙት መሪዎችም የሚታየውን የአማራ ህዝብ ድህነት ይገነዘቡ ዘንድ የሰው ልጅ ልቦና ያልፈጠረባቸው፣ከአማራ ህዝብ ጋር የመንፈስ ቁርኝት የሌላቸው፣ምናልባትም አማራ ወደሚባለው  ክልል የሚወስደው መንገድ በየት በኩል  ወዴት እንደሆነ ለማወቅ መሪ የሚያስፈልጋቸው  የህወሃት ግዙዎች ናቸው፡፡የነዚህ ሰዎች ራስ ደግሞ ኤርትራዊው በረከት ስምኦን ነበር፡፡ከፅንሰቱ በዚህ መንገድ የተፈጠረበትን አላማ እያመከነ እንዲኖር ዲዛይን የተደረገው ብአዴን ስም ቢቀይር፣መዋቅር አስተካከልኩ ቢል ከተሰራበት ግብሩ ፈቅ ነቅነቅ ሊል አልቻለም፡፡ 

ብአዴን የተሰራበት የራስን አላማ አፈር የማልበስ፣በገዛ ህዝቡ ላይ ጦር ነቅንቆ ማቁሰል፣ቢለዋ ስሎ በጀርባ የማረድ  ግብር በራሱ ትልቅ ችግር ሆኖ ሳለ ሌላ ችግርን ወዷል፡፡ ይህ ችግር የህወሃት እና የኦህዴድ የጥንካሬ ምንጭ የሆነው የክርስትና አባት(God father) አልቦ ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ እንደ እኛ ሃገር ተቋማዊነት ባልበረታበት፣ፖለቲካውም የቤተሰብ መልክ ባለው የዘውግ እሳቤ በሚደወርበት ኋላቀር የፖለቲካ አውድ የክርስትና አባት ፖለቲካ የአንድ ፓርቲ የጥንካሬ ምንጭ ነው፡፡ህወሃት ከጫካ ጀምሮ ስብሃት ነጋ፣ስዩም መስፍን፣አባይ ፀሃይየ የሚባሉ በርከት ያሉ ክርስትና አባቶች ያለው ድርጅት ነው፡፡በመሆኑም የፓርቲው አባላት በጥቃቅን ነገሮች ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም የትግራይን  ህዝብ ጥቅም በተመለከተ ግን በጋራ የሚያዩት ራዕይ አላቸው፡፡ 

ከዚህ ራዕይ ፈቀቅ ሲሉ እነዚህ የክርስትና አባቶች ከመስመር የወጣውን በውግዝም ሆነ በእርግማን ወደ መስመር አንዲገባ ያደርጋሉ፡፡በተመሳሳይ ኦህዴድም አባዱላ ገመዳ የሚባል ክርስትና አባት አለው፡፡ኦህዴድ እንደሰው፣ አባዱላ እንደ ድርጅት ደግሞ ኦነግ የሚባል የክርስትና አባት ስላለው የተቋቋመበትን የኦሮሞ ብሄርተኝትን ዋነኛ ዓላማዎች ለሰኮንድ ችላ ሳይል ያለ ይሉኝታ ያስፈፅማል፡፡ኦህዴድን በህወሃት ወንበር ለመቀመጥ ያበቃውም መንገዱን የሚመራው ክርስትና አባት ያለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡

የኦህዴድ የፓርቲ ክርስትና አባት ኦነግ ለኦሮሞ ቆምኩ የሚሉ አካላት ሁሉ ሊያሟሉ የሚገባቸውን ስትራቴጂያዊ ግቦች  ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦለታል፡፡ ይህን ስትራቴጅ እንደ ኦህዴድ ለማስፈፀም ደግሞ አባ ዱላ የተባለው ክርስትና አባት ቅድመ-ሁኔታዎችን ያስተካክላል፡፡ ከነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ህወሃት በመንበሩ ላይ እያለ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ስጋት እንዳይሆንበት ሲል በፓርቲው ላይ የሚያሳርፈውን ጡጫ በመከላከል ይልቅም ከለላ በመስጠት ወጣት የኦሮሞብሄርተኞች ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ያላሰለሰ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይህ ሚናውም እንደ ዶ/ር አብይ፣አቶ ለማ፣አቶ አዲስ አረጋ፣አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የመሳሰሉ የሃገርን በትረ ስልጣን የሚመኙ የኦሮሞ ብሄርተኞች ብቅ እንዲሉ ረድቷል፡፡እነዚህ አዲስ ኦሮሞ ብሄርተኞች ራሳቸው አንደተናገሩት “አደናግረው”፣”አሳምነው” እና “ቆምረው” የፌደራል ስልጣን ላይ ወጥተው በኦነግ ልብ ታስቦ በስልጣን እጥረት ምክንያት ገቢራዊ ያልሆኑ የኦሮሞ  ብሄርተኝት ዋነኛ ህልሞችን ወደ እውንነት ለመቀየር እየሞከሩ ነው፡፡ 

በአንፃሩ ብአዴን ለራሱ ከእናቱ ሆድ ሲወጣ ይዞት በወጣው የዲዛይን ችግር ወለድ ደዌ በመሰቃየት ላይ ሲገኝ እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ደግሞ ለስለት እና ለድንጋይ ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ፈዞ ቀርቷል፡፡ብአዴን የተፀነሰው በእንጀራ እናት ማህፀን ውስጥ በመሆኑ ምንም አይነት የፖለቲካ ዓላማ እየተመገበ ያደገ ፓርቲ አይደለም፡፡ሰው በእናቱ ተወልዶ በእንጀራ እናት ቢያድግ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ከጅምሩ ለልጇ እድገትን ሳይሆን መቀጨጭን በምትመግብ እንጀራ እናት ሆድ ውስጥ ተፀንሶ መወለድ ግን በምድር ላይ ታይቶ የማይታቅ ነገር ነው፡፡

የብአዴን የእንጀራ እናቶቹ በረከት ስምዖን ፣አዲሱ ለገሰ አና ተፈራ ዋልዋ የሚባሉ በየደረሱበት አማራውን የሚያንቋሽሹ እንጅ ለአማራው ህዝብ ጥቅም የሚሆን አንዳች ስትራቴጅያዊ ዓላማ የማያስቀምጡ ሰዎች ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ከኢህዴን ወደ ብአዴን የተቀየረው ጉደኛ ፓርቲ መስራቾች ቢሆኑም የአማራን ህዝብ በእውነት የሚመራበትን ስትራቴጅ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያቀብሉ፣መንገድ የሚያቀኑ አባዱላ ለኦህዴድ የሆነውን አይነት የክርስትና አባቶች ሊሆኑ አይችሉም፡፡የዚህ ጉዳይ መዘዝ የአማራ ህዝብን ለሰላሳ አመት በማይታጠፍ ሰይፍ እንዲታረድ ምክንያት ሆኗል፡፡ 

እንጀራ አባት እንጅ ክርስትና አባት የሌለው ብአዴን በዚሁ አስገራሚ አፈጣጠሩ ሳቢያ በድርጅቱ ውስጥ ምንም አይነት ወደ በጎ የመለወጥ ክስተት እንዳይኖር እግድ ሆኖበታል፡፡መቀየር ካለም ወደ ባሰ አሽከርነት፣ወደ ተባባሰ ዓላማ የለሽነትና ወደ ሚያስገርም ለህዝብ መከራ ስሜት አልቦነት ነው፡፡ይህ ብአዴን ከተፈጠረበት እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ የሚከተለው እውነተኛ መልኩ ነው፡፡ይህን አስቀያሚ መልኩን ለራሱ ይዞ ቢቀመጥ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር ባልነበረው፡፡ ችግር የሆነው ብአዴን የሚናቅበትን መናቅ ወደ አማራ ህዝብ ማስተላለፉ ነው፡፡

ከህወሃት/ኢህአዴግ  እስከ ኦህዴድ/ብልፅግና ሃገሪቱን የሚመሩ ዘውገኛ መሪዎች ብአዴንን በሚያዩበት የንቀት ዓይን የአማራን ህዝብ ያያሉ፡፡ህወሃት በብአዴን የተነሳ የአማራን ህዝብ የመናቁነገር ተወርቶ አያልቅም፡፡ ከሁሉ የሚብሰው ግን የወልቃይት ጠገዴን መሬት ወስዶ ህዝቡን በገዛ መሬቱ ላይ ግዞተኛ ማድረጉ ነው፡፡በጦር ሜዳ ጀብዶ ስልጣ የያዘው ህወሃት ቀርቶ ራሱ ብአዴን እሽኮኮ ብሎ ስልጣ ላይ ያስቀመጠው ጠ/ሚ አብይ ለአንድ ክልል ህዝብ ብለን ህገ-መንግስት አንቀይርም ሲሉ ንቀታቸውን ጠቆም አድርገዋል ሲቀጥልም የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር እና የልማት እንጅ የማንነት አይደለም ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው የብአዴን ለንጉስ ማጎንበስ የአማራ ህዝብ ማጎንበስ ተደርጎ በመቆጠሩ ነው፡፡      

ብአዴን ወደ በጎ እንዳይቀየር ዋነኛ ደንቃራ የሆነበት የቆየ ምክንያት  በረከት ስምኦን የሚባል የህወሃት ዋርድያ በቁራኛነት ስለታሰረበት ነው፡፡ይህ ሰውየ ከጅምር እስከፍፃሜ ፓርቲውን ሲያሾር የኖረ ሰው ነው፡፡በረከት ስምኦንን የብአዴን ዋርድያ አድርጎ ያሰረውን የህወሃትን ገመድ መበጠስ ዘጠኝ ሱሪ መታጠቅን ይፈልግ ይሆናል እንጅ የማይቻል ነገር ግን አልነበረም፡፡ብአዴን ደግሞ እንኳ ዘጠኙ አንዱም ሱሪ እየሰፋ የሚወርድበት ካድሬ የተጠራቀመበት እንደሆነ ማሳያው ዛሬም ድረስ “ህዝቤን ያስገደልክልኝ ሆይ ካባ ይገባሃል” ባዩ ሰውየ ከሰው ተመርጦ ክልሉን እየመራ መሆኑ ነው፡፡ 

የሆነው ሆኖ በኦህዴድ ውስጥ አባዱላን የመሰለ ክርስትና አባት ያመጣው አጋጣሚ ለብአዴንም ሊሆን የሚችልበት የመጀመሪያው አጋጣሚ አማራ የሆነ ሰው ክልሉን እንዲመራ የሆነበት አቶ አያሌው ጎበዜ የተባሉ ሰው ወደ ስልጣን የመጡበት ዘመን ነበር፡፡ሆኖም ሰውየው ራስ ደህና ባይ ነገር ሆነው ኖሮ በኢህአዴግ ቤት የአማራ ክልልን ለመምራት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ የተቀመጠውን የአማራን ህዝብ ስቃይ እንደ አስደሳች ዶክመንተሪ ፊልም ቁጭ ብሎ ከማየት ያለፈ አንዳችም የሚታወሱበት ስራ ሳይሰሩ ወደ ሚሄዱበት ሄደዋል፡፡

ቀጥለው የመጡት አመራሮችም ቢሆኑ የዚህን ሰውየ ፈለግ ከመከተል ያለፈ የሰሩት ስራ የለም፡፡በጋራ ተናበው ትርጉም ያለው ስራ መስራት ቀርቶ በጋራ የሚያልሙት ህዝባዊ ዓላማ የለም፡፡ ሁሉም የሚያልመው የራሱ ኑሮ የደቀነበትን ፈተና የሚያቀለበትን የራሱን ዓላማ ነው፡፡አንዱ V8 ላይ ለመውጣት ሲያልም ሌላው ከ V8 ላለመውረድ ያልማል፣ሌላው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ዶክተር የሚባልበትን ጥበብ ሲያሰላ ሌላው እዴት በንጉስ ፊት አጎንብሶ የፌደራል ባለስልጣን አንደሚሆን ይተልማል ሌላው እንዴት የፌስቡክ አክቲቪስት ቀጥሮ የራሱን ፖለቲካዊ ኪሎ እንደሚጨምሮ ያልማል፡፡በፓርቲው ውስጥ ያለው የአመራር ፍዘት ከዚህ ዝብርቅርቅ ዓላማ የሚነሳ ነው፡፡ አንድ አላማ የሌለው ሰው ፈር ያለው አመራር ሊሰጥ አይችልም፤በራሱ ግላዊ ዓላማ ፍቅር የናወዘ ሰው ለህዝብ ሊቆም ከቶም አይቻለውም፡፡      

እንዲህ ባለ ልሙጥ የታዛዥነት ምግባር ዘመናቸውን ያሳለፉት በአዴኖች ህወሃትን በመጣሉ ከቆየ ማንነታቸው ጋር የማይጣጣም ስራ ሰሩ በሚል አማራጭ የሌለው ህዝብ በእነሱው ላይ ተስፋ አደረገ፡፡በዚህ ሰዓት የክልሉ መሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልልን የሚመራው ፓርቲያቸው ከሚታወቅበት የአቤት ወዴት ባይነት አባዜ የራሱ ነፍስ ያለው ሰው እንደሚያደርገው ያለ ፖለቲካ እንዲያራምድ ያደርጋሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡ ምክትል ጠቅላይ  ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በባህርዳር ከተማ ተገኝነተው “እስካሁን አንሰማችሁም ነበር አሁን ግን ፈጥነን እንሰማችኋለን” ሲሉ በመናገራቸው ተስፋው የበለጠ አድጎ ነበር፡፡ሆኖም ችግሩ ከፅንሰት ውልደት የመጣ የዲዛይን ችግር ስለሆነ ፈቅ ነቅነቅ ማለት አልተቻለም፡፡ጭራሽ የክልሉን ባለስልጣናት ሽጉጥ ያማዘዘ ልዩነት ተፈጥሮ ቁጭ አለ፡፡ 

የሽጉጥ መማዘዙ ምክንያት ምን እንደሆነ አጥግቦ የሚነግር አንድስ አንኳን ከእውነት የወገነ ሰው ጠፍቷል፡፡እስከ ዛሬ ከተነገረው ሁሉ በበኩሌ ፍንጭ የሰጠኝ የፖለቲካ አመራሩ እና የፀጥታ ክፍሉ ተስማምቶ መስራት አለመቻል እንደሆነ ጀነራል ተፈራ ማሞ የፃፉት ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ የሰጠው ፍንጭ የፖለቲካ አመራሩ የተባለው አካል አሁን አሁን ከሚሰራው ከበፊቱ አንኳን የባሰ የአጎብዳጅነት ስራ ጋር ሲነፃፀር ከፀጥታ አካሉ ጋር ያልተስማማበትን ምክንያት ለመገመት አያዳግት፡፡የሆነው ሆኖ አሁን በፖለቲካ አመራሩ ላይ የሚሰነዘረው ፍላፃ የሚነሳው ከፀጥታ ሃይሉ አንዳይሆን በደንብ ታስቦበት የተሰራ ይመስላል፡፡

ሆኖም ከዚህ በኋላ የሚነሳው ተግዳሮት ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው የማያድበሰብሱት፣እከሌ ብለው ከሚረግሙት አንድ አካል ሳይሆን ሉዓላዊ ከሆነው ህዝብ የሚነሳ የፊቱን የትቂቶች የጠመንጃ ሞት ቅንጦት የሚያደርግ፣ለወሬ ነጋሪ የማያስተርፍ የዲን እሳትም ሊሆን ይችላል፡፡ሲወለድ የታመመ ሲሞት ብቻ ይፈወሳል!      

መሪዎቿን የምትመስለው ኦሮሚያ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

(በመስከረም አበራ)
ነሐሴ 2, 2012

በሃገራችን በሁለት የከተማ አስተዳደሮች እና በአስር ክልሎች ተከፋፍላ ትተዳደራለች፡፡ከአስሩ ክልሎች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል በቀር ዘጠኙ ክልሎች ከሞላ ጎደል አንፃራዊ ሰላም ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ሆኖም እነዚህ ዘጠኝ ክልሎችም አለፍ አለፍ ብሎ የፀጥታ መደፍረስ፣ዘውግ ተኮር ግጭት፣የባለስልጣናትን ሞት የጨመረ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ ገብተው ያውቃሉ፤ወደፊትም እንዲህ ያለ ነገር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ክልሎቹ የገጠማቸውን ፈተና ጠቅልሎ ማጥፋት አይቻልምና በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩ እንዲቃለል ግን አደርገዋል፡፡ ይህ የሆነው በዋናነት በክልሎቹ አመራሮች ኢትዮጵያን የማዳን ቁርጠኝነት ነው፡፡እነዚህ ክልሎች ኢትዮጵያን ለማዳን የሚሰሩት የዘውጋቸው ሰው “ስልጣን በቃኝ” እስከሚል ዙፋን ላይ ተቀምጦ ስለኖረ ወይም የህዝባቸው ጥያቄም ሙሉ በሙሉ ስለተመለሰ አለያም በክልላቸው ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ስለሆነ አይደለም፤’ከሁሉም የሃገር ህልውና ይቅደም’ በማለት እንጅ!

በሃገራችን ካሉ ክልሎች የኦሮሚያ ክልል በልዩ ሁኔታ መረጋጋት የሌለባት፣ሰላም የራቃት በግዛቷ ለመኖር ቀርቶ በትራንስፖርት አልፎ ለመሄድ የምታሰጋ ሆናለች፡፡በኦሮሚያ ክልል የሚታየው አለመረጋጋት እያደር እየተባባሰ  ክልሉን አስፈሪ ቀጠና እያደረገው መጥቷል፡፡ኦሮሚያ ክልል በተለይ መጤ ለተባለው የህብረተሰብ ክፍል እጅግ አስጊና አስፈሪ ክልል ነው፡፡ይህ ምን ቢሸፋፍኑት ሽፋን ገልጦ የሚከሰት ሃቅ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሰው እንደ ዶሮ ታርዶ ተበልቷል፡፡እናት አምጣ የወለደችው የሰው ፍጡር የዘጠኝ ወር እርጉዝ ላይ መጨከን ሆኖለት ድርስ እርጉዝ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወቷ አልፏል፤ ወልዶ ሊስም የጓጓው አባት እርጉዝ ሚስቱን አጥቶ፣ወላጅ የሌላቸው ህፃናትን ታቅፎ ቀርቷል፡፡በኦሮሚያ የተደረገው ዘግናኝ ድርጊት ተወርቶ አያልቅም፡፡  የዚህ ፅሁፍ ዓላማም በኦሮሚያ የሆነውን መዘርዘር አይደለም፡፡ የፅሁፉ ዓላማ ይህን ሁሉ መዓት በኦሮሚያ ያመጣው ምንድን ነው የሚለውን ከአመራሩ አንፃር መመርመር ነው፡፡ 

ህግ የማያከብሩ “ህግ አስከባሪዎች”

የኦሮሞ ዘውገኝነት ፖለቲካ በትክክል ማንሳት ያለበትን ጥያቄ አንግቦ ከመታገሉ ጎን ለጎን እውነቱንም እውሸቱንም እያደባለቀ ቂምን ለወጣቱ ሲመግብ የኖረ ነው፡፡በጉልምስና እድሜያቸው ለወጣቱ እልህን፣ቂምን እና ጥላቻን ሲሰብኩ የኖሩ የኦሮሞ ብሄርተኝት ፖለቲከኞች በስተርጅ ለዘብ ያለ ፖለቲካን እናራምድ ቢሉም ሰሚ አላገኙም፡፡የተዘራ ነገር ይበቅል ዘንድ ግድ ነው፡፡መጠንቀቅ ሲዘሩ ነው፤የዘሩት እንክርዳድ በቅሎ ማዘርዘር ሲጀምር ‘ስንዴ ሁን’ ቢሉት አይሆንም፡፡በኦሮሚያ እየሆነ ያለው ይህ ነው! 

የኦሮሞ ብሄርተኝት ፖለቲካ ግንዱ ኦነግ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ኦፌኮ ይባል ኦህዴድ፣ኦዴግ ይባል ኦህኮ ተሸምኖ የተሰራው በኦነግ እሳቤ ነው፡፡ሆኖም በህወሃት ቤት ያደገው ኦህዴድ የዋናውን የኦነግን አስተምሮ ጨርሶ ባይረሳም ኦነግን እድሜ ብቻ ያደረገውን ስህተቱን አርሞ ስልጣን ላይ ለመውጣት ችሏል፡፡ኦህዴድ ስሙን ቀያይሮ ከኦዴፓ እስከ ኦሮሚያ ብልፅግና የደረሰ ቢሆንም ሁሉንም አይነት የኦሮሞ ብሄርተኝት መንፈሶች የያዘ ነው፡፡በኦሮሚያ ብልፅግና ውስጥ ኦነግን በልቡ፣ ኦሮሚያ ብልፅግናን በልብሱ ይዞ የሚጓዘው ብዙ እንደሆነ በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡ሆኖም የሚያዛልቀው መንገድ ሁሉንም እኩል የምታደርግ ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን መስራት እንደሆነ ከልባቸው አጥብቀው የሚያምኑ፣ በዚሁም የተነሳ ብዙ ዋጋ የከፈሉ የኦሮሚያ ብልፅግና መሪዎች እንዳሉ የታወቀ ነገር ነው፡፡

ሃገራችን አሁን ያለችበት ተስፋ ሰጭ ጉዞ እውን እንዲሆን የእነዚህ አስተዋይ የኦሮሞ አመራሮች ሚና ጉልህ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ጉልበታቸው ደርጅቶ የተመኟት ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን፣ድካማቸው ስምረት እንዲያገኝ ምኞቴ ቢሆንም የእነዚህ እውነተኛ የእኩልነት ታጋዮች ቁጥር ምንያህል በቂ ነው የሚለው እጅጉን የሚያሳስብ ነገር ነው፡፡ወረድ ብየ የማነሳው የኦሮሚያ ብልፅግና መሪዎች ህፀፅም እነዚህን መሪዎች የማይመለከት እንደሆነ ላሳውቅ እወዳለሁ፡፡ለነዚህኞቹ እንደውም አድናቆት አለኝ፤የከረረውን የኦሮሞ ፖለቲካ ለማለዘብ በሚደክሙት ድካም ውስጥ ህይወት ጭምር ሊያስከፍል የሚችል አደጋ አዝለው እንደሚንቀሳቀሱ በደንብ እረዳለሁ፡፡  

አንድ ድርጅት ስሙን ሲቀይር መንፈሱን ለመቀየሩ ጅማሬ ሊሆን ይችላል እንጅ አብሮት የጎለመሰ መንፈሱን በስም ቅያሬ አለቅልቆ እንደማይደፋው ግልፅ ነው፡፡ይህ በኦሮሚያ ብልፅግና መሪዎች ዘንድ በእጅጉ ይስተዋላል፡፡ከስማቸው ጋር ያልተቀየረው መንፈሳቸው የሚያናገራቸውን እና የሚያሰራቸውን ለተከታተለ እየተመላለሱ የሚደሰኩሩትን የህግ የበላይነት የማስከበር መሃላ የጎሪጥ እንዲያየው የሚያስገድድ ነው፡፡የህግ የበላይነትን ለማስከበር መጀመሪያ የህግ የበላይነትን ፅንሰ-ሃሳብ በትክክክለ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡የህግ የበላይነት ከአላዋቂነት፣ከድንፋታ፣ከፕሮፖጋንዳ ፣ከርካሽ ተወዳጅነት ጋር ህብረት የለውም፡፡የህግ የበላይነት ለማስከበር ሚዛናዊ ጭንቅላት፣በአቋም መፅናት ከሁሉም በላይ ህግ አላከበረም ከሚባለው ተራው የህብረተሰብ ክፍል የተሻለ ማንነት ያስፈልጋል፡፡የህግ የበላይነትን ለማስከበር ውስጥን እና ውጭን፣አፍንና ልብን አንድ ማድረግ ያሻል፡፡ ሞገደኛ ሆኖ ሞገደኛን በህግ ማረቅ አይቻልም፡፡ በOBN መደንፋት በOMN ከመደንፋት የተለየ አለመሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሚታየው ምስቅልቅል መነሻው ከአክራሪው የኦሮሞ ብሄርተኝት ክንፍ የሚነሳ ጥፋት ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ ለዘብተኛ ነኝ የሚለው የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መሪዎችም ከንግግር እስከ ድርጊታቸው ለዚህ ምስቅልቅል ያልተናነሰ ሚና አላቸው፡፡እነዚህ መሪዎች ስልጣንን የመሰለ ስክነት የሚፈልግ ክቡር ነገር በእጃቸው ይዘው አክራሪነቱ ከስልጣን ደጀሰላም ካራቀው የኦሮሞ ብሄርተኝት ክንፍ ጋር የአክራሪነት ውድድር ውስጥ ይገባሉ፤አንዳንዴም ከዚሁ ቡድን ጋር ማህበር መጠጣት ያሰኛቸዋል፡፡ከዚሁ አክራሪ ቡድን ጋር ያላቸው አንድነት ልዩነትም ግር እስከሚል ድረስ  “በአንድ ቅል እንጠጣ” የሚሉበት ጊዜም አለ፡፡አክራሪነቱ እነሱ ያገኙትን ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሃገር የመምራት እድል ያሳጣውን አክራሪ ቡድን የዓይናችን ብሌን ነው እስከማለት ደርሰዋል፡፡

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ መሪዎች ከፅንፈኛው የኦሮሞ ክንፍ ጋር ያላቸው መስተጋብር፣አንዳንዴ የሚናገሩት ንግግር፣የሚያደርጉት ድርጊት ለታዛቢ እውነተኛ አቋማቸው እውን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የምትሆን ኢትዮጵያን መመስረት ነው ወይ የሚለውን ጥርጣሬ ላይ የሚከት ነው፡፡በግሌ የኦህዴድ ባለስልጣናት ኢህአዴግን በብልፅግና ፓርቲ ለመተካት በተኬደው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ያሳዩትን ሃገር የማዳን ቁርጠኝነት በአድናቆት ካየሁ በኋላ የሃገራችን ፖለቲካ የተሻለ መስመር እንደሚይዝ ትልቅ ተስፋ አድርጌ ነበር፡፡ ሆኖም የኦሮሚያ ክልልን የሚመሩ የኦሮሚያ ብልፅግና መሪዎች ከዛ ወዲህ የሚያደርጓቸውን አንድንድ ነገሮች ሳጤን አካሄዳቸውን  በጥርጣሬ ለማየት ተደድጃለሁ፤የሚያወሩትን የህግ የበላይነት ማስከበርስ የሚችሉ ናቸው ወይ የሚለውም  ሌላው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡የኦሮሚያ ክልልን የሚመሩ የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች የሚሉትን የህግ የበላይነት ለማስፈን የሚበቁ ናቸው ወይ የሚለውን ጉዳይ እጅግ በጥያቄ ውስጥ እንዲከት ያደረጉኝን መሪዎቹ በተለያየ ሰዓት በየሚዲያው የሚያንፀባርቋቸውን ከህግ የበላይነት ጋር በእጅጉ የሚጣሉ ነጥቦች ላንሳ፡፡ 

“ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም”

“ከዚህ በኋላ ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም” የሚለውን ንግግር በሃገራችን የህወሃትን አድራጊ ፈጣሪነት ያስወገደው ለውጥ ከመጣበት ዘመን ጀምሮ ኦሮሚያን በሚያስተዳድሩ ባልስልጣናት አፍ በየሚዲያው  የሚደጋገም መፈክር ነው፡፡ይህ ንግግር ከህግ የበላይነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነትና ከሰብዓዊ መብት እሳቤዎች ጋር የተጣላ እጅግ ኋላ ቀር አባባል ነው፡፡ህጋዊነት እና የህግ የበላይነት እሳቤዎች የሚደነግጉት ማንም ሰው ሰውን መግደል እንደማይችልም እንደሌለበትም ነው፡፡በነዚህ ባለስልጣናት ንግግር መሰረት ግን ነውር የሚሆነው ኦሮሞ ኦሮሞን ሲገድል ነው፡፡ይህ ጥንቃቄ የጎደለው፣በዘውገኝት ላይ የቆመ ስሜታዊ ንግግር በርካታ ክፍተቶችን የሚተው ነው፡፡ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም ሲባል የሰማ የክልሉ ፀጥታ አስከባሪ ኦሮሞ ሌላውን ሲገድል ምን ማድረግ እንዳለበት እጅግም አይጨነቅም፡፡ጭራሽም በኦሮሚያ ክልል ሌላ የተባለውን መግደል ችግር ላይመስለውም ይችላል፡፡ ግፋ ካለም መለዮውን አውልቆ ከገዳዮች አንዱ እስከመሆን ሊደርስ ይችላል፡፡ ይሄው የፀጥታ አስከባሪ በሌላ ወገን ደግሞ ኦሮሞ እና እስልምና አይነጣጠሉም ሲባልም የሚሰማ ነው፡፡ስለዚህ በኦሮሚያ ክልል ያለ ክርስቲያን  መገደሉ ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም የሚለውን መርህ የጣሰ ስለማይመስለው እያየ እየሰማ ዝም ሊል ይችላል፡፡ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም የሚለው የፀጥታ አስከባሪው ጋር ሲደርስ ኦሮሞ ኦሮሞን ወንጀል ሲሰራ አይቶም ወደ ህግ ቦታ አይወስድም ገመና ይሸፍናል እንጅ የሚል ትርጉም ሊሰጥም ይችላል፡፡የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ከሰሞኑ በኦሮሚያ በማታ ቀርቶ በቀን በብርሃን የሰው ልጅ በግፍ ሲገደል፣ተወልዶ ባደገበት ሃገር በማንነቱ ዘር ማጥፋት ሲደረግበት የህግ አካላት ዝም ብለው ማየታቸው ነው፡፡ ተጎጅዎቹ መንግስት አለወይ? ብለው የሚጠይቁትም ይህንኑ መጠቆማቸው ነው፡፡የህግ አካላት ለገዳች መንገድ መርተው ዞር ሲሉ፣የሰው ልጅ እንደ ከብት ሲታረድ ቆመው እያዩ ዝም እንዳሉ የመሰከሩ ተጎጅዎችም አሉ፡፡ 

“ነፍጠኛን ሰብረናል…..”

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል የታየው የዘር ማጥፋት መሪ ቃል “ዲና ነፍጠኛ”(ጠላት ነፍጠኛ እንደማለት)  የሚለው ነው፡፡ሰው በቢለዋ ሲታረድ፣ድንጋይ ተንተርሶ አይኑ ተጎልጉሎ ሲወጣ፣የሰው ልጅ ሰውነት እንደ ቲማቲም እስኪፈራርስ ድረስ በአጣና ተቀጥቅቶ ሲገደል ከገዳዮች አፍ በህብረት የሚወጣው ቃል “ዲና ነፍጠኛ”  የሚለው ነው፡፡ይህ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊት በኦሮሚያ ክልል ከመከሰቱ ጥቂት ወራት በፊት ክልሉን የሚመሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ስንት ሽህ ህዝብ በተሰበሰበበት የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ “ሲያዋርደን የኖረውን ነፍጠኛን ሰብረናል” ሲሉ በባለስልጣን አዋቂነትና ብስለት ሳይሆን በመደዴ ድንፋታ፣እጅግ ግዴለሽነትና አላዋቂነት በተጫነው እብሪት ተናግረዋል፡፡ አንድ ወንጀል ያዘለ ንግግር በንግግርነቱ ባያስጠይቅ እንኳን ንግግሩን ተከትሎ፣በንግግሩ ምክንያት ተጨማጭ ጥፋት ከመጣ ግን ተናጋሪው መጠየቁ ግድ ነው፡፡

በኦሮሚያ ከሰሞኑ የተደረገው የዘር ማጥፋት ማጀቢያ ሙዚቃ “ዲና ነፍጠኛ”  የሚል ነው፡፡ገዳዮቹ ይህን እያሉ ሰው ሲገድሉ ክልላቸውን በሚመራው ሰውየ አንደበት “ትናንት ሲሰብራችሁ ነበር” የተባሉትን ነፍጠኛን በሜንጫ፣በአጣና፣በድንጋይ እየሰባበሩ ነው:: ይህ ወንጀል  ከአቶ ሽመልስ ንግግር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በሃገራችን  ህግ ኖሮ ፣ሰዎች ሁሉ በህግ ፊት እኩል ቢሆኑ ኖሮ ሰውየው በOMN አደገኛ ቅስቀሳ አደረጉ ከተባሉ ሌሎች ሰዎች እኩል መጠየቅ ነበረቸው፡፡እሳቸው ግን ጭራሽ የሕግ የበላይነት ጠበቃ ሆነው ትዕግስትም ልክ እንዳለው፣አሁን የህግ የበላይነት ዘመን እንደሆነ በቴሌቭዝን ሊደሰኩሩ መጡ! ዋል አደር ብለው ደግሞ፣በዚህ ሳምንት OBN በተባለ ሚድያ ሌላ ህገ-ወጥነት ሊዘሩ፣ሌላ መተላለቅ ሊቆሰቁሱ ብቅ አሉ፡፡የፈለጉትን ተናግረው ስልጣን ላይ ጉብ ማለቱን ለምደውታል-ንጉስ እንደሆነ አይከሰስ! 

አሁን ሃገራችን በምትመራበት ህገ-መንግስት ከኦሮሚያ ክልል ውጭ በሆነ በራሷ ካውንስል የምትተዳደርበት፣የራሷ አስተዳደር ያላትን አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንደ አንዷ ለምሳሌ እንደ አዳማ እንደሆነች በOBN በግልፅ ተናግረዋል፡፡ይህ ንግግር ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡ተወደደም ተጠላ ህገመንግስቱ በስራ ላይ እስካለ ድረስ መከበር አለበት፡፡ህገ-መንግስትን ያላከበረ መሪ የትኛውን ህግ ያከብራል? ከህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ-መግስት በሚዲያ የደረመሰ መሪ ተብየ የትኛውን የህግ የበላይነት ነው የሚያስከብረው?እንዲህ አይነት ስሜታዊ ሰው የሚመራው ክልል እንዴት ሆኖ ነው የህግ የበላይነት፣የሰው ልጆች የሰብዓዊ መብት የሚከበርበት?የክልሉ የፀጥታ አስከባሪ ማንን አይቶ ነው ህግ አክባሪና አስከባሪ እንዲሆን የሚጠበቀው?ከአናቱ፣ከቁንጮው የታመመ የመንግስት መዋቅር እንዴት ሆኖ እጅ እግሩ ጤነኛ ይሆናል?

ኦሮሚያ ክልልን የሚመሩት አቶ ሽመልስ በOBN ቆይታቸው አሁንም ሌላ የዘር ማጥፋት ሊቆሰቁስ የሚችል ንግግር ተናግረዋል፡፡ይኽውም ኦሮሞ በአዲስ አበባ ዝንጀሮ እንኳን የሚሰጠውን ቦታ ተነፍጎ እንደኖረ አሁን ግን ለሟንም፣ወተቷንም አይብ ቅቤውንም ኦሮሞ እንደተቆጣጠረ ተናግረዋል፡፡በዚህ ንግግር ለኦሮሞው ሌላ የተንቄ ኖሬያለሁ ቁጭት የሚያሳድር መርዝ ለሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ሁለመናውን ተቆጣጥሮ የበይ ተመልካች አድርጎት የኖረው ህወሃት በሌላ ካርድ መጣብን የሚል ክፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ሰውየው አውቀው ከሆነ ይህን የሚያደርጉት በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡ በበኩሌ ነገሩ ሆን ተብሎ የተደረገ ሳይሆን የለመደ የተበድየ ተረክን ያለመተው አባዜ ውጤት፣ንግግር የሚያመጣውን ችግር የማስተዋል ብልሃት እጥረት አለያም አክራሪውን የኦሮሞ ወጣት ልብ ለማግኘት የሚደረግ ከንቱ መዋለል መስሎ ይሰማኛል፡፡የችግሩ ምንጭ እኔ የገመትኩት ከሆነ ሰውየው ከዋኛ የስልጣን መንበር አለያም ከሚዲያ ዘወር የሚሉበት መላ ቢመታ ደግ ነው፡፡የእውነት የህግ የበላይነትን የማስከበር ቁርጠኝነት ካለ ደግሞ አቶ ሽመልስ ህግ ፊት መቅረብም ያለባቸው ሰው ናቸው፡፡ 

ዘር ማጥፋትን መካድ

ሌላው አሮሚያን የሚመሩ ባለስልጣናት ችግር በኦሮሚያ የሚፈጠረውን የፖለቲካ ችግር አሳንሶ ማቅረብ ነው፡፡ይህ አባዜያቸው ሲበረታ ሃገር ያወቀውን ፀሃይ የሞቀውን በክልሉ የተፈፀመውን ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራት ይልቅ “ፖለቲካዊ አላማ ያለው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት” ሲሉ ሁለት ሰዎች ሰክረው በጥፊ ስለተመታቱበት ትዕይነት የሚያወሩ በሚመስል ሁኔታ መግለፅ ይዘዋል፡፡ይህ ወንጀል ነው!በኦሮሚያ የተደረገው ወንጀል በተባበሩት መንግስታት በ1946ዓም ለዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰጠውን ትርጉም መስፈርቶች ሁሉ ያሟላ ነው፡፡ ይህን መካድ ኢሰብዓዊነት ብቻ ሳይሆን መሪዎቹ በክልሉ ሌላ ዙር የዘር ማጥፋት እንዳይከሰት ለመስራት ፍላጎቱ እንደሌላቸው አመላካች ነው፡፡

የኦሮሚያ ብልፅግና መሪዎች በክልላቸው የተከናወነውን  የዘር ማጥፋት ወንጀል  የሚክዱት በሶስት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ አንደኛውና ዋነኛው በዘር ማጥፋቱ ሂደት ክርስቲያን ኦሮሞዎችም አብረው ስለተገደሉ በኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ውስጥ ሙስሊም- ክርስቲያን የሚል ክፍፍል እንዳይመጣ በመስጋት ነው፡፡ሁለተኛው የክልሉ ስም ዘር ማጥፋትን በመሰለ መጥፎ ወንጀል እንዳይነሳ ገመና ለመክተት ነው፡፡ክልሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእጅጉ የሚወገዘው የዘር ማጥፋት የተከናወነበት ነው ከተባለ ቱሪስቱም፣ኢንቨስተሩም ይሸሻልና ገመና መክተቱ ተመራጭ ነው፡፡ ሶስተኛው ምክንያት ድርጊቱ የዘር ማጥፋት ከሆነ መንግስት ይህን ባለመከላከል መጠየቁ ስለማይቀር ከተጠያቂነት ለመሸሽ ነው፡፡

 ሲጠቃለል በኦሮሚያ ክልል የሚከሰተው አለመረጋጋት ክልሉን የሚመሩ አብዛኛዎቹ መሪዎች የኖሩበትን በተበድየ ተረክ፣በመጤ ጠልነትየበለፀገ አክራሪ ዘውገኝነት ትተው በህግ የበላይነት እና በዲሞክራሲያዊ መርሆች ለመምራት ቁርጠኝነቱም ፣ ፍላጎቱም ፣ ችሎታውም የሚያጥራቸው በመሆኑ ነው፡፡በዚህ ላይ የሚደረበው ችግር ደግሞ እውነተኛውን የአክራሪ ዘውገኝነት፣መጤ ጠልነታቸውን በአዲስ የአብሮነት አስተሳሰብ የተኩ እንደሆኑ ለማስመሰል መሞከራቸው ነው፡፡ማስመሰሉ ያስፈለገው ስልጣን ላይ ለመሰንበት ነው፡፡ስልጣን በኢትዮጵያ የሁሉ ነገር ምንጭ ነው፡፡ የኑሮን እንቆቅልሽ ለመፍታት፣ ከሰው በላይ ሆኖ ለመኖር፣አዋቂ ለመምሰል፣ክብር ለማግኘት ሁሉ ስልጣን ወሳኝ ነገር ነውና እንደዋዛ የሚተውት አይደለም፡፡ስለዚህ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ረባሽም አረጋጊም ለመሆን ይሞከራል፡፡ በዚህ መሃል የደሃ ደም ይፈሳል፤ሃገርም ደም ታለቅሳለች!            

የብ/ጄ ተፈራ ማሞ ምስክርነት ሲመረመር (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ሰኔ 14 2012 ዓ. ም .

የሰኔ 15ቱን ግድያ በተመለከተ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ “ያየሁት የሰማሁት” ብለው የፃፉትን ጦማር በዘ-ሃበሻ ድረ-ገፅ ሲነበብ ሰማሁት፡፡እውነት ለመናገር የሰኔ 15ቱ ድርጊቱ “ባይደረግ ደግ ነበር፤ ከሆነ ደግሞ የሞቱትን ሁሉ ነፍስ ይማር” ተብሎ ቢታለፍ እመርጣለሁ፡፡ሆኖም ነገሩ ከተፈፀመ ዕለት አንስቶ ከወደ መንግስት በኩል የሚነገሩ መረጃዎች(ያን ቅጠቢስ ዶክመንተሪ ጨምሮ)፣የዓይን ምስክር ነን ከሚሉ የአማራ መኳንንት የሚሰጠው ምስክርነት ሚዛናዊነት ማጣት “ነፍስ ይማር” ብሎ ብቻ ነገሩን መተው የሚፈልግን ሰው ላልፈለገው ምርምር የሚጋብዙ ናቸው፡፡የዛሬው የብ/ጄ ተፈራ ማሞ ምስክርነትም ከዚህ በፊት ከሰማኋቸው ወደ አንድ አቅጣጫ ካጋደሉ የመንግስት ፕሮፖጋንዳዎችም ሆነ የካድሬ ግለሰቦች ምስክርነቶች  ብዙም የማይርቅ ሆኖ አግቸዋለሁ፡፡ 

“የሞተን ሁሉ ነፍስ ይማር” ብለን እንዳንቀመጥ ምስክር ነን ባዮች ከመጡ ዘንዳ ሚዛናዊ የሆኑ፣ለእውነቱ የሚቀርቡ ምስክርነታቸውን ቢያቀርቡ መጭው ትውልድ ከሰኔ 15ቱ ስህተት እንዲማር ያግዙ ነበር፡፡በተቀረ መንግስት ራሱ በዶክመንተሪ ፣የአማራ ክልል ባለስልጣናትን አማራ መገናኛ ብዙሃን ድረስ እያመላለሰ በማናዘዝ ያደነቆረንን የአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ ይዞ መምጣት አስተዛዛቢ እንጅ አስተማሪ ሊሆን አይችልም፡፡የዚህ የተንጋደደ አካሄድ ሌላው ጉዳት “የሁሉንም ነፍስ ይማር” ብሎ የተቀመጠውን ህዝብ ለሌላ ምርምር፣ለባሰ መከፋፈል የሚጋብዝ ነገር መሆኑ ነው፡፡

ከሰኔ 15 ማግስት ስለ ግድያው የሚሰጡ ምስክርነቶች ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ ሟቾች ላይ የሚሰጡ በመሆናቸው ከአድሎ የፀዱ፣በተቻለ መጠን የግራ ቀኙን እውነት ያካተቱ  ቢሆኑ ለምስክሮቹም ልዕልና፣ ለእኛ ለአድማጮችም ይህን ስህተት ላለመድገም ትምህርት የምንወስድበት በጎ አጋጣሚ ይሆን ነበር፡፡ብ/ጄ ተፈራ የፃፉት የምስክርነት ጦማር እነዚህን ልዕልናዎች ካሉት በሚል በጥንቃቄ እና በተደጋጋሚ ነበር ያዳመጥኩት፡፡ ሆኖም የጠበቅኩትን ያህል አዲስ መረጃ የያዘም ያሰብኩትን ያህል ሚዛናዊ ሆኖም አላገኘሁትም፡፡ በነገራችን ላይ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ እና ኮሎኔል አለበል የዛሬ አመት የሰኔ 15ቱ ግድያ ተፈፀመ እንደተባለ በአማራ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ነበር፡፡ እናም ኮሎኔል አለበል በንግግራቸው ውስጥ ብ/ጄ አሳምነው ግድያውን በመፈፀም ተጠርጥረው እየተፈለጉ እንደሆነ ሲገልፁ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ ግን አሳምነው ገዳይ እንደሆነ ባስረገጠ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡በዚህ ንግግራቸቸው እንኳን ጓደኛ አንድ ህግ አክባሪ ሰው ለአንድ ለማያውቀው ሰው የሚሰጠውን ከፍርድ በፊት ነፃ ተደርጎ የመቆጠር መብት ሲነፍጉ አስተውያለሁ፡፡

ስለሆነም የብ/ጄ ተፈራን ምስክርነት ሚዛናዊነት ጥርጣሬ ውስጥ መክተት የጀመርኩት ከያኔ ጀምሮ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ በብ/ጄ አሳምነው እና በብ/ጄነራል ተፈራ ማሞ መካከል ያለው ግንኙነት ራሱ እሳቸው ዛሬ እንደሚያወሩት የወዳጅነት ብቻ መሆኑ አጠራጣሪ ነው፡፡ይህን የምልበት ምክንያት በግድያው ማግስት በአማራ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው የተናገሩት ንግግር የፖለቲካ ካድሬዎቹ እየተመላለሱ ከሚነግሩን የአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ የተለየ አለመሆኑን ስላስተዋልኩ ነው፡፡ይልቅስ ዝም ባሉት ኮሎኔል አለበል ላይ የተሻለ የገለልተኝነት እና ከፍርድቤት ቀድሞ  ያለመፍረድ ህጋዊነት አስተውያለሁ፡፡ መሆን ያለበትም ይኽው ነው፡፡ በሰኔ 15ቱ ግድያ ያጣናቸው ሰዎች ሁሉም ይበጃል ያሉትን ለመስራት የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከሁሉም በላይ አሁን ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በመሆናቸው ስለ እነሱ ማውራታችን ግድ ከሆነ እንኳን ማውራት ያለብን እውነቱን እና የምናውቀውን ሁሉ በምሉዕ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡በከፊል የምንናገረው እውነት፣አድበስብሰን የምናልፈው ሃቅ፣አንጋደን የምናቀርበው ምስክርነት ጉዳት እንጅ ጥቅም ስለሌለው በብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ላይ ያየኋቸውን እንከኖች ወደ መዳሰሱ ልለፍ፡፡          

ከመነሻው ጥያቄ ሆኖ የሚመጣው የአማራ ክልል የፖሊቲካ እና ወትድርና ባለስልጣናት ለግምገማ ለምን  አዲስ አበባ ድረስ ተጓጓዙ የሚለው ነው?ግምገማው አዲስ አበባ በሚኖሩት አቶ ደመቀ መሪነት እንደተደረገ ተነግሮናል፡፡ቢሆንም ይህ ሁሉ ባለስልጣን ተንጋግቶ አዲስ አበባ ከሚሄድ ሰብሳቢው አቶ ደመቀ አንድ ግለሰብ ናቸውና ባህርዳር ቢመጡ የተሻለ ነበር፡፡በአሁኑ ወቅት ባህርዳር ለአማራ ባለስልጣናት እጅግ አስፈሪ ቦታ እንደ ሆነች በሰፊው ይወራል፡፡ይህ መሆን የጀመረው ከመቼ ወዲህ እና ለምንድን ነው? የሚለው መመርመር ያለበት ነገር ነው፡፡የተገምጋሚ ባለስልጣናት ወደ አዲስ አበባ ማምራትም ከባህርዳር አስፈሪ መሆን መጀመር ጋር የተያያዘ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው? የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡አስፈሪነቱስ ለነአቶ ደመቀ ነው ወይስ ለክልሉ ባለስልጣናትም ጭምር ነበር?ማን ማንን ነው የሚፈራው?በምን ምክንያት? የሚለው በውል መጤን አለበት፡፡ ሁሉም ለአማራ ህዝብ ጥቅም በመስራት ላይ ልዩነት የላቸውም ከተባለ የሚያስተዳድሩት ክልል ዋና ከተማን እንደጦር የሚፈሩት ለምንድን ነው? የሚለው ነገር በጥብቅ መመርመር ያለበት ነገር ነው፡፡ይህንን የምለው በአማራ ብልፅግና አመራሮች እና የአማራ ህዝብ የልብ መራራቅ ሳቢያ የአማራ ክልል ለባለስልጣናቱ ወደማይታዘዝ የለየለት የብጥብጥ ቀጠና እንዳይቀየር ከፍተኛ ስጋት ያለኝ በመሆኑ ነው፡፡ይህ ደግሞ ከሰኔ 15ቱ አሰቃቂ ትዝታ ሳንወጣ ሌላ አሰቃቂ ነገር የሚያመጣ አደጋ አዝሎ ስለሚታየኝ ነው፡፡   

ወደ ብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ስንመለስ ምስክርነታቸውን የሚጀምሩት አስራ ሶስት ሰዓት ፈጀ በተባለው ግምገማ ነው፡፡ በዚህ ግምገማ  ብ/ጄ አሳምነው የሁሉም ባለስልጣናት  ትኩረት ተደርጎባቸው እንደነበረ ነግረውናል፡፡በገምጋሚዎቹ የሚነሳው ዋናው የብ/ጄ አሳምነው ችግር ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተግባብተው መስራት የተሳናቸው ሰው መሆናቸው ነው፡፡(ይህን መስካሪው ብ/ጄ ተፈራም የሚያምኑበት ይመስላል)፡፡ የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ ያለው በዚህ አለመግባባት ተብሎ በታለፈው ጉዳይ ላይ  ይመስለኛልና ብ/ጄ አሳምነውን ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸው ምክንያት ምን እንደሆነ በብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ጦማር ውስጥ በደምብ ተፍተታቶ መቅረብ ነበረበት፡፡ ሆኖም ብ/ጄ ተፈራ ያለመግባባቱን  ምክንያት በጨረፍታ እንኳን አይነግሩንም፡፡ያልነገሩን ግን ስለማያውቁት አይመስለኝም፡፡

ብ/ጄ ተፈራ በፅሁፋቸው መሃል መሃል ከብ/ጄ አሳምነው ጋር የረዥም ዘመን ጓደኛሞች/ወንድማማቾች እንደሆኑ እስከነገሩን ድረስ ብ/ጄ  አሳምነው ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸውን ነገር ለጓዳቸው ተፈራ ማማከራቸው የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡መስካሪው በፅሁፋቸው አብረን ተቀምጠን ታደምን ባሉት ግምገማ ላይ ብ/ጄ አሳምነው ያጋጠማቸውን ነገር እንደ አዲስ  ስልክ ደወለው “ሁሉም እኔ ላይ ተረባረቡ” በማለት ደግመው እንደ ነገሯቸውና  እሳቸውም ደግመው እንደሰሟቸው መናገራቸው ሁለቱ ሰዎች በመከፋት መደሰታቸው ዙሪያ የማውራት ልምድ እንዳላቸው አመላካች ነው፡፡ይህ አይሆንም ብንል እንኳን ራሳቸው ፀሃፊውም ቢሆኑ የክልሉ የልዩ ሃይል አዛዥ የነበሩ በመሆኑ ከመስተጋብሩ የራቁ ሰው አይደሉምና ብ/ጄ አሳምነው ከፖለቲካ አመራሩ ጋር የማያግባባቸውን ምክንያት በተመለከተ የራሳቸው መረዳት ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ይህን በምስክርነታቸው ላይ ጨምረው ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ 

ሆኖም ብ/ጀነራል ተፈራ ማሞ ጓዳቸው ብ/ጄ አሳምነው ከፖለቲከኞች ጋር መግባባት የማይችሉ ሰው መሆናቸውን ብቻ ነግረውን አልፈዋል፡፡ጭራሽ የፖለቲካ አመራሮች ቅኖች ሆነው ሳለ ጓዴ የሚሏቸው አሳምነው ይህን ቅንነት መረዳት የማይችሉ ሰው እንደሆኑ በምክር መልክ እንደነገሯቸው ፅፈዋል፡፡አክለውም አሳምነው የሚገመገሙበትን ጭብጥ መረዳት የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ፤ለሚመጣባቸው ግምገማም የግምገማውን ጭብጥ ያማከለ መልስ መስጠት የማይችሉ፣ስለ ባሌ ሲወራ ስለ ቦሌ የሚዘባርቁ ሰው እንደሆኑ አስቀምጠዋል፡፡ይህ በግሌ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ሚዲያዎች(በOMN፣ቪኦኤ፣በአማራ መገናኛ ብዙሃን )ከሰማሁት የብ/ጄነራል አሳምው  ንግግር አዋቂነት ጋር የሚጣረስ ምስክርነት ነው፡፡እዚህ ላይ ብ/ጄ ተፈራ ማሞ ሟቹን ጓዳቸውን ተራ ዘባራቂ አድርገው በማቅረብ  ሟች ብ/ጄ አሳምነው እና የአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች ሊግባቡ ያልቻሉበትን እውነተኛ ምክንያት ሊደብቁን ፈልገዋል፡፡ 

ብ/ጄ ተፈራ የነገሩን ተጨማሪ የብ/ጄ አሳምነው ጥፋት የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ምግባሩ ከበደ እና ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር አምባቸው ስብሰባ ሲጠሯቸው የማይገኙ መሆናቸውን ነው፡፡ሆኖም ዶ/ር አምባቸው እና ብ/ጄ አሳምነው የሚግባቡ ወዳጆች እንደነበሩ፣ጭራሽ አቶ ገዱ በዶ/ር አምባቸው እንዲተኩ ዋነኛው ጎትጓች ብ/ጄ አሳምነው እንደ ነበሩ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር የሆኑ ሰው አጫውተውኛል፡፡የሁለቱ ሟቾች ወዳጅነት መቼ፣ለምን እና እንዴት አብቅቶ ስብሰባ ላይ አብሮ ለመቀመጥ እስከ መቸገር እንደ ደረሱ ለብ/ጄ አሳምነው ቅርብ ነኝ ያሉት ብ/ጄ ተፈራ የማያውቁት ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ነገር ግን ጓዳዊ ምስክርነት ሲፅፉ ይህን ሳይነግሩን እንዲሁ ብ/ጄ አሳምነው ስብሰባ መግባት አሻፈረኝ የሚሉ እምቢተኛ እንደሆኑ ብቻ ነግረውን አልፈዋል፡፡የሚያውቁትን ሁሉ እውነት  የማይናገሩበት ምስክርነት ችግሩ አንባቢን አለማጥገቡ ብቻ ሳይሆን ቅንነቱም አጠራጣሪ መሆኑ ነው፡፡

ብ/ጄ ተፈራ አዲስ አበባ ላይ የተደረገውን የሰኔ 12ቱን ግምገማ በተመለከተ የነበራቸውን ምስክርነት  ጨርሰው ወደ ባህርዳሩ ትዕይንት ሲመለሱ ምስክርነታቸውን የሚጀምሩት ሟች አሳምነው ስብሰባ ጠርተዋቸው በነበረበት ቦታ “መጣሁ” ብለው እንደሄዱ፣ከዛም ከግማሽ ሰዓት በኋላ በተደወለ ስልክ አሳምነው ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ መች ቡድን አሰማርተው ዶ/ር አምባቸውን እንደገደሉ እንደተነገራቸው ነው፡፡ይህ ደዋይ ብ/ጄ ተፈራ የሚመሩት የክልሉ ልዩ ሃይል ትስንቅ እና ትጥቅ(Logistic) መምሪያ ሃላፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በግማሽ ሰዓት ውስጥ አሳምነው ያሰማራውን የገዳይ ቡድን ቁጥር ሳይቀር አውቀው ቅልብጭ ያለ መረጃ ለብ/ጄ ተፈራ በስልክክ ያሳወቁት የትሆነው አይተው/ማን ነግሯቸው ነው? የአይን ምስክር ናቸው? ወይስ የስሚ ስሚ የሰሙትን ለአለቃቸው ማስተላለፈቸው ነው? “በኋላ ሳጣራ ብዙ ነገር አወቅኩ” የሚሉት ብ/ጄ ተፈራ ይህን ሁሉ አብራርተው  ሊነግሩን ይገባ ነበር፡፡ 

ሌላው ምስክርነት ብ/ጄ አሳምነው በሶስት ቡድን የተከፋፈለ መች ቡድን አሰማርተው እንደ ነበር የተነገረበት ነው፡፡ አንዱ ገዳይ ቡድን በራሳቸው በብ/ጄ አሳምነው የሚመራው ወደ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ሄዶ አሰቃዊውን ግድያ ያደረገው ቡድን ሲሆን፤ ሁለተኛው  ሃገር ሰላም ብሎ የብ/ጄ አሳምነውን ወደ ስብሰባ መመለስ ሲጠባበቅ የነበረውን መስካሪው ብ/ጄ ተፈራ ጭምር ያሉበትን ቡድን እንዲገድልየተላከው ነው፡፡ ሶስተኛው ቤታቸው የተቀመጡ የክልሉን አመራሮች በየቤታቸው እንዲገድል የተላከው ነው ተብሏል፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ ብ/ጄ አሳምነው ሶስት ገዳይ ቡድኖችን እንዳሰማሩ በርካታ የአማራ ክልል የመኳንንት እየተመላለሱ የነገሩን ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ርዕሰ መስዳድር ቢሮ ከተደሉት እነ ዶ/ር አምባቸው በቀር ሌሎቹ ሁለት ገዳይ ቡኖች ተሰማሩ በተባለበት ቦታ ሰው አልገደሉም፤ለምን? ብ/ጄ ተፈራም ሲመሰክሩ እነሱ ለስብሰባ በተቀመጡበት በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ ሊገድላቸው የመጣ መች ቡድን ከእርሳቸው ጠባቂዎች ጋር “ቁም ቁም” ሲባባሉ መስማታቸውን ነግረውናል፡፡ ያልነገሩን ነገር ብ/ጄ አሳምነው እነ እነ ብ/ጄ ተፈራን እንዲገድል ላኩት የሚሉት ሁለተኛው ገዳይ ቡድን የኮሚሽኑ ህንፃ መግቢያ በር ላይ ያሉ ዋርድያዎችን ብቻ ገድለው፣እነ ብ/ጄ ተፈራ ያሉበት ህንፃ ድረስ ደርሰው ማንንም ሳይገድሉ የተመለሱበትን ምክንያት ነው፡፡ 

ብ/ጄ ተፈራ የሚሉት  ገዳዮቹ የመሰብሰቢያው ህንጻ አካባቢ ደረሰው ከእርሳቸው ጠባቂዎች ጋር “ቁም ቁም” ከተባባሉ በኋላ “ማነው ያለው?” ብለው ሲጠይቁ  “ተፈራ ነው” ሲሉዋቸው ተመለሱ ነው፤አክለውም “ገዳዮቹ ማንን እንደሚገድሉ እንኳን አያውቁም” ይላሉ፡፡ይህ እጅግ አደናጋሪ የሆነው የብ/ጄ ተፈራ ምስክርነት ነው፡፡ 

የነገሩን ነገር እውነት ከሆነ ሰዎቹ የሚገድሉትን ስለሚያውቁ ነው ስለማያውቁ የእርሳቸውን መኖር ሲያውቁ ማንንም ሳይገድሉ የተመለሱት? ደግሞስ አለቃው ሄደህ ግደል ብሎ ወታደራዊ ትእዛል ያዘዘው ሰው  እንትናንማ አልገድልም የማለት ስልጣን አለው? የሚገድለውን የማያውቅ ሰው የጠባቂዎቹን ተኩስ መቋቋምና ጥሶ መግባት ከቻለ ጥሶ ገብቶ ውስጥ ያለው ማንም ይሁን ማን በታዘዘው መሰረት ይገድላል እንጅ ያለው እንትና ነው ሲባል አለቃው ያዘዘውን የመከለስ ስልጣን አለው? ሌላው ጥያቄ የክልሉ አመራሮችን በየቤታቸው እንዲገድል የተላከው ቡድን ከአቶ ደስየ በተጨማሪ ማን ማን ቤት ሄደ? አቶ ደስየን ጨምሮ ሌሎች ቤታቸው ገዳይ የተላከባቸው የክልሉ አመራሮች እንዴት ከሞት ተረፉ? በገስት ሃውስ እገታ ተደረገባቸው የተባሉት እነ ኮሎኔል አለበልስ ሁሉን ለመግደል ከቆረጠው የብ/ጄ አሳምነው እርምጃ እንዴት ተረፉ? ብ/ጄ አሳምነው እነ ብ/ጄ ተፈራን እና አበረን ጨምሮ ጠሩት በተባለው  ስብሰባ ላይ ምክትላቸው ኮሎኔል አለበል እንዴት/ለምን ሳይገኙ ቀሩ? 

ሌላው አደናጋሪ ነገር ብ/ጄ ተፈራ ከእዝ ሰንሰለታቸው ውጭ፣በብ/ጄ አሳምነው ግዳጅ ተቀበሉ የተባሉ ሰዎችን እያዘዝኩ የአሳምነው ያስነሳው ብጥብጥ እንዳይዛመት አደረግኩ ያሉት ነገር ነው፡፡ይህ ከወታደራዊ የዕዝ ባህል እጅግ ያፈነገጠ አካሄድ በምን አስማት ለእሳቸው ተሳክቶ በብ/ጄ አሳምነው ዕዝ ሰንሰለት ያሉ፣ጭራሽ ግዳጅ የተቀበሉ ሰዎችን በስልክ ትዕዛዝ ብቻ ወደሚፈልጉት አቅጣጫ እንዳመጧቸው ተዓምር መሰል ነገር ነው፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ብ/ጄ ተፈራ ጓዳቸው ብ/ጄ አሳምነው ያሰማሯቸውን ሰዎች በስልክ እያዘዙ ከአለቃቸው ትዕዛዝ ውጭ እንዲሰሩ በሚያደርጉበት ሰዓት ብ/ጄ አሳምነው ምን ይሰሩ እንደነበር ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡በብ/ጄ አሳምነው ታዘው ግዳጅ ላይ የተሰማሩ ቡድኖች አለቃቸው አሳምነው በህይወት እያሉ የእዝ ሰንሰለታቸውን በቀላሉ ወደ ብ/ጄ ተፈራ ቀይረው፣ ወዲያውኑ ተፈራ በሚሏቸው መንገድ መሄድ የጀመሩበት ምትሃት ምንድን ነው? በወቅቱ አሳምነው በህይወት ስላልነበሩ ያሰማሩትን ቡድን መሪዎች ማዘዝ አልቻሉም እንዳይባል አሳምነው ህይወታቸው ያለፈው ከሁለት ቀን በኋላ እንደሆነ ነው የተነገረን፡፡

ራሳቸው ተፈራም አሳምነው ከኋላው ኤፍሴስ አር ሙሉ ወታደር አስከትለው ከፊት በፒክአፕ መኪናሆነው  ከባህርዳር እንደወጡ፣ከኋላ ያሉት ወታደሮች ሲያዙ አሳምነው እንዳመለጡ ጠቆም አድርገውናል፡፡ከሁሉ ግራ የሆነው ስለ ሰኔ 15ቱ ግድያ ሊነግሩን የተነሱት ብ/ጄ ተፈራ በዚሁ ክስተት የሞቱትን፣ ጓዴ የሚሏቸውን የብ/ጄ አሳምነውን አሟሟት ከዓመት በኋላ ተመልሰው ሲመጡም ሳይነግሩን መቅረታቸው ነው፡፡የሃገር መከላከያ ሰራዊት ረብሻውን  በመቆጣጠሩ ረገድ ምንም ሚና አልነበረውም፤ሙሉ በሙሉ ነገሩን የተቆጣጠረው የአማራ ልዩ ሃይል እንደሆነ አድርገው ያቀረቡት ነገርም የዛሬ አመት በመንግስት ሚዲያዎች ከተዘገበው ጋር የሚጋጭ በመሆኑ እጅግም አሳማኝ ነገር አይደለም፡፡ በወቅቱ የመንግስት ሚዲያዎች የዘገቡት ግርግሩ በቁጥጥር ስር የዋለው በመከላከያ ሰራዊት እና በክልሉ ልዩ ሃይል ጥምር ጉልበት እንደሆነ ነው፡፡ሌላው ምስጢር ከሞት ከተረፉት የአማራ መኳንንት ሁሉ ተለይተው ብ/ጄ ተፈራ እና ኮ/ሎ አለበል ብቻ በአሳምነው ግብረ አበርነት  ተጠርጥረው የታሰሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ መስካሪው ተፈራ ሳይናገሩ መቅረታቸው ነው፡፡የፀጥታው ክንፍ አባላት ስለሆኑ ተጠረጠሩ ከተባለም የፖሊስ ኮሚሽነሩ አበረ አዳሙ አልታሰሩም፡፡ 

በስተመጨረሻም ብ/ጄ ተፈራ ምስክርነታቸውን ሲጨርሱ ሁለት ቀልቤን የሳቡ ነገሮችን አስቀምጠዋል፡፡ አንደኛው ለውጡ ፈጣሪዎቹን የበላው እንዴት ነው ሲሉ የጠየቁት ነገር ነው፡፡ይህ መልስ ሊሰጠው የሚገባው ጥያቄ ነው፡፡ሁለተኛው ከላይ ብ/ጄ አሳምነውን የተቹት በቅንነት እንደሆነ የመሰከሩላቸውን የክልሉን የፖለቲካ አመራሮች በአራሙቻነት የከሰሱበት ነው፡፡”አራሙቻ” የሚለው አገላለፅ ከምን አንፃር የተባለ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ሆኖም መስካሪው ተፈራ ያሉትን ተከትለን ነገሩን ብናየው የአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች “አራሙቻ” ከሆኑ ብ/ጄ  አሳምነው ከአራሙቻዎቹ የፖለቲካ አመራሮች ጋር እንዴት ብለው ተግባብተው እንዲሰሩ ነው ብ/ጄ ተፈራ “ከአሳምነው ጋር ባደረግኩት የመጨረሻ ስንብት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር ተግባብተህ ስራ ብየ መከርኩት” የሚሉት? ከአራሙቻ ጋር መግባባት የሚቻለው እንዴት ነው?        

አቶ ስዩም መስፍንስ ስለ ዲፕሎማሲ የማውራት የሞራል ብቃት አላቸው? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ግንቦት 23 ፤ 2012 ዓ ም

የሰው ልጅ ስላጠፋው ጥፋት ካልተጠየቀ ጭራሽ ተበዳይነት እንደሚሰማው የታወቀ ነው፡፡ህወሃቶች እየተሰማቸው ያለው እንዲያ ነው፡፡ስላደረሱት ዘረፋ፣የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ስላወደሙት የሃገር እሴት ስላልተጠየቁ ዘረፋን ህጋዊ ያደረጉበትን፣የኢትዮጵያን ህዝብ ደም እምባ ያስለቀሱበትን ስልጣን የያዙበት ቀን ግንቦት ሃያ አሁንም እንደ ድሮው ደምቆ ካልተከበረ ብለው እንደተበደለ እያማረሩ ነው፡፡የግንቦት ሃያ ዕለት ማታ በትግራይ ቲቪ ቀርበው የዶ/ር አብይን መንግስት እንዳይበላ እንዳይዘራ አድርገው ሲያራክሱ አምሽተዋል፡፡ሌላው ቀርቶ የእነሱ ልብስ በሆነው ዘረፋ፣ሃገር ክህደት ሳይቀር ዶ/ር አብይን ሲያብጠለጥሉ አምሽተዋል፡፡ “የባንክ አካውንታችን ከዶ/ር አብይ የባንክ አካውንት ከበለጠ እንቀጣ” አይነት የተለመደ ሰሚን የመናቅ ለበጣቸውን ያለምንም ሃፍረት አዝንበዋል፡፡ በጣም የሚገርመው አቶ ስዩም መስፍን የዲፕሎማዊ ልሂቅ ሆነው የቀረቡበት ድፍረት ነው፡፡

አቶ ስዩም መስፍን በትጥቅ ትግሉ ዘመን በምን ተመርጠው እንደሆነ በማይታወቅ መንገድ ከሃገር ሃገር እየዞሩ የሸማቂውን ፓርቲያቸው የውጭ ጉዳይ ሲያስተናብሩ ኖረዋል፡፡ በህወሃት ቤት በጫካ ቆይታ የተደረገ ነገር ሁሉ በየትኛውም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ከመማር የበለጠ እውቀት እና ድፍረት የሚሰጥ ነገር ከመሆኑም ባሻገር የትዕቢትም ምንጭ ነው፡፡በመሆኑም የጫካው ቆይታ አክትሞ ህወሃት ስልጣን ሲይዝ ስዩም መስፍን አስራ ዘጠኝ አመት ሙሉ ያለምንም ተቀናቃኝ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ኖረዋል፡፡

በዚህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የስልጣን ቆይታቸው ባድመ ለኢትዮጵያ ተፈርዳለች ብለው ህዝብን በነጭ ውሸት አስጨፍረዋል፡፡ዛሬ አቶ ስዩም ዶ/ር አብይን ግብፅን በአንዴ ባለመርታት የዲፕሎማሲ አላዋቂነት ይከሳሉ፡፡ግብጽ እንደ አንድ ዓይኗ በምታየው አባይ ዙሪያ ድርድር ሲደረግ ስንት ውጣ ውረድ እንደሚኖር ግልፅ ነው፡፡ይህን የሚያውቁት አቶ ስዩም መስፍን አብይን በአንዴ ግብፅን አሳምነው የአባይን ግድብ ሙሊት ያለ ምንም ሁከት ማድረግ ባለመቻላቸው የፍርደ-ገምድል ክስ ይከሳሉ፡፡ጭራሽ አብይ ግድቡን ለግብፅ መሸጣቸውን “ወላሂ አልነካችሁም” ብሎ ምሏል ብለው የህፃን ክርክር ያመጣሉ፡፡ 

አብይን በተወሳሰበው የአባይ እና የግብፅ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ ወዲያው እልባት ባለመስጠት የሚከሰው አቶ ስዩም መስፍን እርሱ የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያለ ሃገሪቱን ሲመራ የነበረው መንግስት አስራ ሰባት አመት በነበረው የጫካ ትግል በረባሶ እየተቀያየ፣ወታደር እየተለዋወጡ ደርግን ከተዋጉት፣ እንደ እጅ መዳፍ ከሚያውቁት  ባልንጀራቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር እንኳን ቁጭ ብለው ተደራድረው የሰባ ሽህ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት የበላውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማስቆም ያልቻሉ ሰዎች ናቸው፡፡

የሚብሰው ደግሞ እነ አቶ ስዩም የሚመሩት ዲፕሎማሲ በጦርነት ያሸነፈችውን ሃገራችን ተሸናፊ መንግስት እንደሚያደርገው ተሸቀዳድማ ‘ይግባኝ የሌለው ፍርድ እቀበላለሁ፣ያሻችሁን ጣሉብኝ’ ስትል የተሸናፊ በር እንድትይዝ ማድረጉ ነው፡፡ይግባኝ የሌለው ፍርዱ ደግሞ ሰባሽህ የሃገራችን ወጣት ያለበቀትን ግዛት ወደ ኤርትራ ማካለሉን እያወቁ ሃፍረተቢሱ አቶ ስዩም “ግዛቶቹ ለእኛ ተፈርደዋል” ብለው ያመናቸውን የሃገራችንን ቅን ህዝብ ሲያስጨፍሩ መሰንበታቸው ነው፡፡ ይህ የተረሳ መስሏቸው ዛሬ ፈርጥጠው በመሸጉበት በመቀሌ፣የኢትዮጵያን ህዝብ ዘርፈው ባከማቹት ገንዘብ ባቋቋሙት የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው “ከእኔ በላይ ዲፕሎማት ላሳር” ዓይነት መመጻደቅ ሲያሰሙ ሰሚን ያሳፍራሉ!

የአቶ ስዩም ጉዳይ በዚህ አያበቃም፡፡በተራዛሚው የ19 ዓመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው የዲፕሎማሲውን ዘርፍ ከእርሳቸው ዘውግ የመጡ ሰዎች መናኽሪያ አድርገው የኖሩ ሰው ናቸው፡፡በዘር ተቧድነው ከአታሼ እስከ አምባሳደር በዓለም ዳርቻ የተበተኑ የአንድ ዘውግ ሰዎች በተበተኑበት ሃገር ንግድ የሚያጧጡፉ፣ለዘመዶቻቸው የውጭ ንግድ በር የሚከፍቱ፣አለፍ ካለም በሃገር ውስጥ የተዘረጋው የዘረኝነት መንግስት አላስቀምጥ ብሎት ሃገር ጥሎ የሄደውን ኢትዮጵያዊ የሚሰልሉ ነበሩ እንጅ እንደ ዲፕሎማት ለሃገራቸው ሰዎች የሚቆሙ ጠበቆች አልነበሩም፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ወደ ውጭ ሃገር የሚሰደዱ ኢትጵያዊያንን ከሃገር የሚያስወጡ ኤጀንሲዎቸ ሳይቀሩ ከአንድ የአቶ ስዩም ዘውግ አባላት እንዲሆኑ ያደረጉ ፍፁም ዘረኛ ሰው ናቸው ዛሬ ከእኔ በላይ ላሳር እያሉ ፀጉር የሚሰነጥቁት-አቶ ስዩም፡፡እነዚህ ሰዎች ደግሞ በየተሰየሙበት ኢምባሲ ኢትዮጵያዊያን ላይ ጥይት እስከመተኮስ የሚደርስ ጥጋብ ያንገላታቸው  ነበሩ፡፡ በአረብ ሃገር ኢምበሲዎች የተሰየሙት ደግሞ ኢትዮጵያዊያን በዘይት ሲጠበሱ፣ከፎቅ ሲወረወሩ፣ህይወታቸውን ጠልተው በገመድ ተንጠልጥለው ሲሞቱ ኮሽ ያለ የማይስላቸው ልበ-ደንዳች ናቸው፡፡  

አቶ ስዩም መስፍን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው፣ፓርቲያቸው ህወሃትም ከአድራጊ ፈጣሪነቱ ላይመለስ ሊነሳ ጥቂት ወራት ሲቀሩት የአቶ ስዩም ጉድ ከቤት ወደ ውጭ የወጣበት ወቅት ነበር፡፡ ይኽውም በአቶ ስዩም የተመራው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በቤት የለመደውን ወገንተኝነት ተሸክሞ የደቡብ ሱዳን መሪዎችን (ሪክ ማቻርን እና ሳል ቫኪርን) ለማስታረቅ ሲሞክር ሳልቫኬር እንድም ሁለቴ ነገሩን ካዩ በኋላ ‘ስዩም በሚመራው የዲፕሎማሲ ቡድን ገለልተኝነት አለ ብየ ወደ አዲስ አበባ እግሬንም አላነሳ’ ብለው ነገር አለሙን ትተው ሃገራቸው ቁጭ ማለትን መርጠው እንደነበር የዜና አውታሩ ሁሉ የዘገበው የአቶ ስዩም ቅሌት ነው፡፡ይህ ቅሌት ነው እንግዲህ ከእኔ በላይ ላሳር በሚል የሚል እያኩራራ ያለው ! 

የአቶ ስዩም መኩራራት ምን ያህል ጭፍን እንደሆነ የሚያስታውቀው ከጫካ ጀምረን በውጭ ግንኙነታችን መርህ የተሞላን፣ከኢትዮጵያ ጥቅም ዘነፍ የማንል ነን ሲሉ ሲኩራሩ ነው፡፡አቶ መለስ ይቅርታ የጠየቁበትን ከዚያድ ባሬ ጋር ወግነው ሃገራቸውን የወጉበትን ጉዳይ ሳይቀር በተቃራኒው ገልብጠው ሊነግሩን ሞክረዋል፡፡ዛሬ አይናችሁን አያሳየኝ የሚለውን የአቶ ኢሳያስን ሻዕብያን ትርፍራፊ ለማግኘት ሲሉ ሃገራቸውን በቅኝ ገዥነት ማብጠልጠላቸውን የምንረሳ ይመስል እኛ ከትናት እስከ ዛሬ በመርህ የመርህ የተሞላን የሃቅ ሰዎች ነን ሲሉ መስማት ያሳቅቃል፡፡ሃገርን በውሸት ታሪክ ላይ ቆሞ የቅኝ ገዥነት ክፉ ስም መስጠት ለሃገር ጥቅም መቆም ነው ነው የሚሉት አቶ ስዩም ! 

ሃገር ጠቅልሎ ለመጉረስ የደረሰውን የዘረፋ አባዜ እንኳን እንደ አቶ ስዩም ያለውን የፊት ወንበር ሰልፈኛ ቀርቶ እሱን የተጠጋን ሳይቀር በአንድ ሌሊት ሚሊየነር ማድረጉ እየታወቀ እስከ ሰባት ጉልበታችን አንድ ስባሪ ሳንቲም ያልነካን ቅዱሳን ነንና አካውንታችን ከጠ/ሚ አብይ አካውንት ጋር ይነፃፀር፡፡ ተነፃጥሮ የእኛ በልጦ ከተገኘ እንቀጣ ያሉት ነገር ህወሃት በሞቱ ብቻ የሚፈወስ  ክፉ በሽታ እንደተጠናወተው አስረጅ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ አፅናኙ ነገር  የህወሃት የትዮጵያን ህዝብ በመንታ ጥርሱ የሚነክስበት ዘመን ማክተሙ ነው!      

የሌለው “ጭንብላችን” ቢገለጥ ምን ይመጣል? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ጥር 19, 2012 ዓ .ም.

ሃገራችን ሩብ ምዕተ-ዓመት በቆየችበት ህወሃት-መር የጎጠኝነት ፖለቲካ እንደ አማራው ግራ የተጋባ ህዝብ/ልሂቅ የለም፡፡አማራው ከጎጥ ፖለቲካው ጋር መላመዱ አልሆን ብሎት እስካሁን  በገዛ ሃገሩ እንደ መፃተኛ ሆኗል፡፡በጎጥ መደራጀቱ እንደ የማይገለጥ ምስጢር የሆነበት የአማራ ልሂቅ መገፋት ገፍቶት የመሰረተው መአድ የተባለው ፓርቲ ግማሽ ጎኑ  አፍታም ሳይቆይ ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲነት ሲቀየር መቀየሩን ያልወደደው ቅሪቱ መአድ እንደ ሲኒ ውሃ እያደር ተመናምኖ ወዳለመኖር የተጠጋ ሁኔታ ላይ  ነው፡፡ መአድ የተባለው ፓርቲ መኢአድ ወደሚባል ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ የተቀየረው መለስ ዜናዊ አማራውን የሚያሳድድበትን በትር፣የሚያሳርድበትን ቢለዋ ወደ ሰገባው ሳይመልስ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው አማራው በጎጥ መደራጀቱን ስለማያውቅበት ነው፡፡ይህ የዘመኑን ፋሽን ያለመከተል የአማራው ግርታ ያደረሰበት ጉዳት መጠነ ሰፊ ነው፡፡

አማራን ሁሉ ባላንጣ አድርገው የሚያስቡ ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች  የአማራ ልሂቃንን ለዘውግ ፖለቲካ ባይትዋርነት “አማራው የብሄር ፖለቲካው አልገባ ብሎት ሲደናገር ሩብ ምዕተ አመት ሞላው፤ይህ ለኦሮሞ መልም ነው” ሲሉ በመሳለቅ ይገልፁታል፡፡እነዚህ ቡድኖች አማራው ሲሞትም፣ሲፈናቀልም፣ሲንጓጠጥም ሲገደለም ዝም ማለቱ ብቻ ይስማማቸዋል፡፡አማራው መናገር ሲጀምር ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ህወሃታዊ ትግራዊያን  የሚናገረው ሁሉ ያስበረግጋቸዋል፡፡አማራው በዘውጉ የሚደርስበትን ሁሉ ችሎ የለመደውን ኢትዮጵያዊነት ሲያጠብቅ በኢትዮጵያዊነት ስም ፍላጎቱን በብሄረሰቦች ላይ የሚጭን ጨቋኝ ሲሉ ኢትዮጵያን በማለቱ በድንጋይ መወገር የሚገባው  ሃጢያተኛ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ እነሱው በየደረሱበት በሚሰኩት የአማራ ጥላቻ ሳቢያ በአማራነቱ መሞቱ ተሰምቶት ኢትዮጵያዊነቱን ሳይጥል አማራነቱ እያስገደለው እንደሆነ ከተናገረ ደግሞ በጭብላምነት ያብጠለጠሉታል፡፡ አማራውም ይጥለው ዘንድ የማይችለውን ኢትዮጵያዊነት በደሙ ውስጥ ይዞ የተጋረጠበትን የህልውና አደጋም ለመከላከል ቢጣጣርም አማራነቱን ማጠባበቁ ከኢትዮጵያዊነቱ የሚጋጭ እየመሰለው በፈራተባ ውስጥ ይኖራል፡፡        

የአማራው ዘመን አመጣሹን የጎጥ ፖለቲካ ፋሽን ተረድቶ ራሱን ከዘመኑ ጋር ማራመድ አለመቻሉ(በባላንጣዎቹ ንግግር “ግራ መጋባት”) ቋጥኝ የሚያክል ፈተና ያንዣበበትን የአማራውን ህዝብ ያለጠበቃ አስቀርቷል፡፡የጎጥ ፖለቲካውን መላመድ ድሮ ቀርቶ ዛሬ ያልሆነላቸው የአማራ ምሁራን በአማራ ብሄርተኝነት መስመር ተሰልፈው ሌሎች እንደሚያደርጉት ለህዝባቸው መሞገት አለመቻላቸው ለኦነግ ግርፍ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ህወሃት ቀመስ ትግራዊያን የአባት ገዳይን በግላጭ እንደማግኘት ያለ ሰርግ እና ምላሽ ነበር፡፡ሆኖም በአማራው ላይ የሚወርደው ዱላ የተኛ ቀርቶ ሙት የሚቀሰቅስ እየሆነ ሲመጣ ዛሬ ላይ የአማራ ምሁራንም ከእንቅልፋቸው መንቃት ጀመሩ፡፡ይህ ደግሞ ለኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና ለህወሃቶች መልካም አዝማሚያ አይደለም፡፡ ለእነሱ መልካም የሚሆነው ባፈው ሃያ ሰባት አመት እንደሆነው አማራው ከሞት በበረታ ዝምታ ውስጥ ሆኖ ግድያውንም፣መንጓጠጡንም፣መፈናቀሉንም፣መገደሉንም አጎንብሶ ሲቀበልነው፡፡

ይህ ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛው አማራው “በሰራው ታሪካዊ ወንጀል” የሚሸማቀቅ በደለኛ እንጅ ስልጣን የሚጋራ የፖለቲካ ሃይል አለመሆኑ ለኦሮሞ ብሄርተኛ ሁለተኛውን ግዙፍ ዘውግ ከስልጣን ተገዳዳሪነት ይቀንስለታል፡፡ ሁለተኛው ጥቅም በታሪክ በድሎናል የሚሉትን ህዝብ በማሸማቀቅ የሚያገኙት ስሜት በቀለኝነት የሚጋልበውን የስነ-ልቦና ቀውሳቸውን ተንፈስ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ አሁን አሁን ከበደል ብዛት የተነሳ እያቆጠቆጠ ያለውን የአማራ ብሄርተኝነት አይወዱትም፡፡ ምክንያቱም የአማራው ብሄርተኝነት ካቆጠቆጠ አማራው ያለ ስራው የተለጠፈበትን የበደለኝነት ተረክ የሚያፈርስ መልስ መስጠት ይጀምራል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ አማራውን ጭራቅ አድርገው የሚያቀርቡበትን ተረክ ብቻቸውን እያወሩ፣ያወሩትም እንደእውነት እየተቆጠረ ወደስልጣን ማዝም አይቻልም፡፡አማራውን የማይስተሰረይ ሃጢያት የሰራ በደለኛ አድርጎ ማሸማቀቅም አይቻልም፡፡ ስለዚህ አማራው በደሉ እንዲሰማው አይፈለግም! በአይን የሚታየውን በአማራ ህዝብ ላይ ያንዣበበ አደጋም ሆነ በዚህ ህዝብ ላይ በወያኔ እና ኦነግ  የተደረገውን ግፍ አንስቶ የሚሞግት አማራም ሆነ ሌላ የሰው ዘር አይፈለግም፡፡

ከወያኔ ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ በአማራ ህዝብ ላይ በርካታ በደል የተፈፀመ፣አሁንም ይህ ህዝብ በሃገሪቱ ባሉ የዘውግ ፖለቲከኞች ሁሉ በክፉ አይን የመታየት  ፈተና ውስጥ ያለ ቢሆንም የአማራ ምሁራን እና ልሂቃን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነታቸውን የሚቀማቸው የሚመስላቸውን የአማራ ብሄርተኝነት መልበስ አይፈልጉም፡፡በአንፃሩ የወጡበት ህዝብ ያለበት ፈተናም ያሳስባቸዋል፡፡ስለዚህ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነታቸውን ሳይጥሉ ስለ አማራው ህዝብ እንግልትም ይሟገታሉ፡፡የአማራ ህዝብ ሁሉ ባላንጋራቸው የሚመስላቸው ኦነጋዊ የኦሮሞ ብሄርተኞች ደግሞ መለስ ዜናዊ እንዳደረገው የአማራን ህዝብ ያለ አንዳች ጠበቃ መቅጣት ስለሚፈልጉ ይህን ነገር አምርረው ይጠላሉ፡፡ኢትዮጵያዊነትን ሳይጥል የአማራ ህዝብ ለምን በገዛ ሃገሩ እንዲህ ይደረጋል የሚል የሚል የአማራ ልሂቅ ሲገጥማቸው ሌባ እጅ ከፍንጅ እንደያዘ ሰው ባለድልነት ይሰማቸዋል፡፡

ለአማራ ልሂቃን/ምሁራን ኢትዮጵያዊነት የክብር ልብስ እንጅ ጭንብል አይደለም!ኢትዮጵያዊነት ጭንብላችን ቢሆን ኖሮ በአማራ ህዝብ ላይ ከመለስ ዜናዊ እስከ ጃዋር መሃመድ ነጋሪት ጎሳሚነት የደረሰው በደል ጭንብል ቀርቶ ቆዳ የሚያስወልቅ ክፉ  ነውና “ጭንብል”  ወርውሮ ጎጠኛ መሆን አስቸጋሪ ሆኖ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት በአማራ ህዝብ/ልሂቅ/ምሁር ዘንድ በደም ውስጥ የሚሮጥ ልክፍት እንጅ ጭንቅላት ላይ ለይምሰል ሸብ የሚደረግ ቡቱቶ ጨንብል አይደለም፡፡የአማራ ልሂቃንን በጭንብላምነት የሚከሱ የኦሮሞ ብሄርተኞች ኢትዮጵያ እንደኩንታል አናታቸው ላይ ተጭና የምትከብዳቸው ሸክማቸው እንደሆነች የፈረንጅ ጋዜጠኛ እጅ እየመቱ የሚምሉ፣ ኦሮሚያ የምትባል ሃገር ናፍቆተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሉም እንደነሱ ይመስላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማለት ትርጉም ስለማይሰጣቸው ሁሉም እንደእነሱ ኢትዮጵያን በጭንብሉ፤መንደሩን ሃገር አሳክሎ በልቡ ተሸክሞ የሚጓዝ የማነስ ልክፍተኛ ይመስላቸዋል፡፡ ስለዚህ የሌለ ጭንብል ይፈልጋሉ፡፡

ለማንኛውም እነሱ ጭንብል የሚሉት ነገር ለአማራው ማን እንደጣለበት የማያውቀው፣በደሉን እንኳን እንዳይቆጥር የሚያደርግ ኢትዮጵያን የሚያስብለው ከደሙ ጋር በመላ ሰውነቱ የሚዞር ልክፍቱ እንጅ አናቱ ላይ የተንከረፈፈ ጭንብሉ አይደለም፡፡ይህ ልክፍቱ ነው ኢትዮጵያን ካለ ጋር ሁሉ የሚያዛምደው፡፡አማራው ኢትዮጵያን ይላል ማለት ግን ስሟ በተጠራበት ልገኝ በሚልላት ሃገሩ  አማራነቱ ወንጀል ሆኖ ሲያስገድለው ዘላለም የማይገባው ነፈዝ ነው ማለት አይደለም፡፡ኢትዮጵያዊ ሆኖም በአማራነቴ አትግደሉኝ ማለትን የሚከለክል ፍርደ-ገምድል ህግ የለም! “ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልክ አማራ ነህ ብየ ስገድልህ አመጣጤ አይግባህ” የሚባል አካሄድ ድሮ ቀርቷል፡፡ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ሰው አማራ ነህ ብሎ ገድሎ ያስገደለህን ምክንያት ስሙን አትጥራ ማለት የሞኝ ብልጠት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውን ሰው አማራ ነህ ብሎ የሚያስገድለው አባዜ ሁለቱንም የመጥላቱ በሽታ መሆኑን ማን ያጣዋል?

ለማንኛውም አማራው አጠለቀው የተባለው የኢትዮጵያዊነት ጭንብል የኢትዮጵያዊነቱን ከፍታም ሳይለቅ በአማራነቱ ሚመጣበትን ፍላፃም ለመከላከልም የመሞከሩ  የሚዛናዊነቱ ምልክት ነው፡፡አማራውን ኢትዮጵያዊ ነኝ በል እያሉ ግን በአማራነቱ የሚገድሉት አዳኞች ደግሞ ይህን አይወዱምና ኢትዮጵያዊነት ከአማራው ላይ እንደማይወልቅም፣ጭምብል እንዳልሆነም እያወቁ “ጭንብልህን አውልቅ” ይላሉ፡፡አይሆንም እንጅ አማራው ችሎ ኢትዮጵያዊነቱን  እንደተንከረፈፈ ጭንብል ቢያወልቅ ለኢትዮጵያ መልካም አይሆንም፡፡ አማራው ኢትዮጵያዊነቱን አወለቀ ማለት ትልቁ የኢትዮጵያ አእማድ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ ይሄኔ ኢትዮጵያዊነት በአማራነት ይተካል፤ከተተካ ደግሞ የጎጥ ፖለቲካ መለያ የሆነው “ሁሉ ኬኛ” የሚባለው አባዜ አማራውንም ይዋሃደውና የቱ የአማራ የቱ የኦሮሞ ግዛት እንደሆነ የመነጋገሪያ ፋታ የለም! ያኔ መናጋገሪያው ጡጫ ይሆናል፡፡አንዴ ወደ ቁልቁለት ከተወረደ ደግሞ ጡጫ የማይጨብጥ እጅ ያለው የለም፤በአንድ እጅ አስር ጡጫ የሚጨብጥ ባለ ዘጠኝ ሱሪም የለም!  

የአማራ ክልል ፈተናዎች እና “ጭምት” አመራሩ – ክፍል ሁለት (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin


(በመስከረም አበራ)
ጥር 12 , 2012 ዓ.ም.

በሃገራችን ሩብ ምዕተ-ዓመት ያስቆጠረውን የህወሃት የበላይነት ያስወገደውን ለውጥ ተከትሎ የአማራ ክልል አዳዲስ ፈተናዎች እንደተጋረጡበት ባለፈው ሳምንት ባስነበብኩት ፅሁፍ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡እነዚህ ፈተናዎች በህወሃት የበላይነት ዘመን ለአማራ ህዝብ ላይ ተጋርጠው በነበሩት ፈተናዎች ላይ የተደረቡ መሆናቸው ፈተናውን ድርብርብ እና ውስብስብ ያደርገዋል፡፡የመጣው ለውጥ የአማራን ህዝብ የቆዩ ፈተናዎች በማቃለል ረገድ ያመጣው ተጨባጭ ነገር አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡በአማራ ህዝብ ላይ የተቃጣው ጥቃት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተወረወረው ፋላፃ አካል ነው፡፡በአማራ ክልል ላይ የፈተና ዶፍ የሚያወርዱ አካላት ኢትዮጵያን እና አፈጣጠሯን የማይወዱ የፖለቲካ ሃይሎች ናቸው፡፡ይህን የደደረ ፈተና ለማቃለል ደግሞ የፈተናውን  ክብደት የሚመጥን ንቁ፣ቆራጥ፣ጥንቁቅ እና የተሰጠ አመራር ያስፈልጋል፡፡ሆኖም አማራ ክልልን የሚመሩ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር አቋም ይዘው ስለመገኘታቸው አፍ ሞልቶ የሚያስወራ ምልክት ያለ አይመስልም፡፡

የአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች በህዝባቸው ልብ የሚጣልባቸው እንዳይሆኑ ያደረገ በርካታ ምክንያት አለ፡፡የመጀመሪያው የጥራዝ ነጠቁ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ትግል የአማራን ህዝብ በጨቋኝት የፈረጀበት ደመ-ነፍሳዊ አካሄድ የወለደው አማራውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መርገም ሁሉ ምንጭ አድርጎ የማየቱ ትንተና ያመጣው ነገር ነው፡፡ይህ አማራውን ጨቋኝ አድርጎ የማየቱ ነገር ህወሃት የተባለው የባሰበት ጥራዝ ነጠቅ ደደቢት ከመሸገበት፣ አዲስ አበባ እስከ ገባበት፣ ከዛም ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ግማሽ ምዕተ አመት ስልጣን ላይ በተወዘተበት ዘመን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ህወሃት ጌታ ሆኖ ኢትዮጵያን ሲያሾር በኖረበት ዘመን ካሰማራቸው ሶስት የእህት አምስት የአጋር ድርጅት ሎሌዎች መሃል አንዱ የአማራ ክልልን የሚያስተዳደርው ብአዴን ነበር፡፡

ሁሉም የአባል/አጋር ፓርቲ ሎሌዎች በአሳዛኝ ራስን የማከራየት ጎስቋላ ህይወት ውስጥ የነበሩ ቢሆኑም የብአዴንን ለየት የሚያደርገው በራሱ ህዝብ ላይ የተቃጣውን ጦርነት ሊያጋፍር የወጣ ሎሌ መሆኑ ነው፡፡ይህ ቡድን ከሎሌነቱ የባሰ ሌላ ፈተና ነበረበት፡፡ ይኽውም “እንደ ወጣበት ህዝብ ትምክህተኛ አለመሆኑን” ለጌታ ህወሃት የማስመስከር የማያልቅ ስራ ነበር፡፡ይህን ለማስመከር ደግሞ ህወሃት በአማራ ህዝብ ላይ የሚያወርደውን ሁለንተናዊ መከራ ዝቅ ሲል ባላየ ማለፍ ከፍ ሲል ደግሞ ከህወሃት ጋር ተደርቦ የራስን ህዝብ ልብስ አስወልቆ በእሾህ ለበቅ መለብለብ ያስፈልግ ነበር፡፡ይህን በማድረግ የብዴን ሹማንነት “አማራ በመሆናቸው ምክንያት ከዘር የወረሱትን  የትምክህተኝነት ሃጢያት” የማራገፋቸውን ለጌታ ህወሃት ያስመሰክሩ ነበር፡፡ይህ ከሩብ ምዕተ-ዓመት በላይ ከብአዴን ሹማምንት ጋር አብሮ የኖረ አባዜ እንዲህ  በቀላሉ ትቷቸው ሊሄድ አይችልምና ዛሬም ለህዝባቸው ለመቆም ወገባቸውን ሳይዘው አልቀረም፡፡

ይህ ድክመት ከብአዴን ሹማንምንት ያለፈ ታሪክ ብቻ የሚቀዳ አይደለም፡፡ይልቅስ ከላይ ከፍ ብሎ እንደተቀመጠው ከነጥቆ በረሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ንፋስ ውስጥ አማራውን ጨቋኝ አድርጎ የመሳሉ ነገር ዛሬ ድረስ ተሻግሮ ክልሉን የሚመሩ ባለስልጣናት ለህዝባቸው እንዳይሰሩ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ሳያስከትል አልቀረም፡፡ይህም ማለት የአማራ ክልልን የሚመሩ ባለስልጣናት ለህዝባቸው የመቆርቆር ነገር ካሳዩ “የቆየ ትምክህታቸውን ሊመልሱ፣የቀድሞውን ስርዓት ሊያመጡ” የሚል ዜማ ይከተላቸዋል፡፡ ይህ ነገር የአማራ ክልል አመራሮች ከሌላው በተለየ “ጭምት” እንዲሆኑ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ይህን ነገር ለመስበር ደግሞ የክልሉ አመራሮች በህወሃት ዘመን በከፍተኛ የስነልቦና ስልበት ውስጥ የቆዩ በመሆናቸው ዛሬ ብድግ ብለው በራሱ የሚተማመን፣የሚቆምለት መርህ ያለው፣የፖለቲካ ተደራዳሪነትን ካርዶችን አሰላስሎ ሰብስቦ አጀንዳ አስቀማጭ ሊሆኑ አይችሉም-በጥብቅ ሰንሰለት ታስሮ የኖረ ምርኮኛ ሰንሰለቱ ቢፈታለትም ቶሎ እጁን ማዘዝ እንደማይችል ሁሉ!

ይህ ልማድ ግን ለአማራ ህዝብ ደህንነትም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል ነገ ዛሬ ሳይባል መወገድ ያለበት ልማድ ነው፡፡አማራ ክልልን የሚመሩ መሪዎች “ጭምትነታቸውን” ማቆም አለባቸው፡፡በክልሉ ላይ የተደቀነው ፈተና በትናንቱ የፖለቲካ ልማድ የሚወጡት አይደለም፤ለአፍታም የሚያስተኛ አይደለምና ወገብ ጠበቅ አድርጎ መስራት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ “የሚሰራው ስራ ምንድን ነው?” የሚል ተገቢ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡የሚሰራው በርካታ ስራ ቢሆንም እኔ የታየኝን ላስቀምጥ፡፡                         

   ነቀፌታን ማስወገድ

ለውጥ መጣ ከተባለ ወዲህ በተለይ ወያኔ እንኳን ወደመረሻው አካባቢ ረስቶት የነበረውን የአማራን ህዝብ የማብጠልጠል ነገር በተለይ በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ በግልፅ በአደባባይ እየተቀነቀነ ይገኛል፡፡ይህ የአማራን ህዝብ የማብጠልጠያው መግቢያ በር “ነፍጠኛ” የሚለው አማራው ሊያፍርበት የማይችለው፣ይልቅስ የሚኮራበት ስም ነው፡፡ሆኖም ዋናው ጉዳይ ያለው አማራው “ነፍጠኛ” ለሚለው ስም  የሚሰጠው ትርጉም ላይ አይደለም፡፡ዋናው ጉዳይ ያለው ሌሎች ለዚህ ስም የሚሰጡት ትርጉም ላይ ነው፡፡ የመከፋፈል ካህኑ መለስ ዜናዊ “ነፍጠኛ” የሚለውን ቃል አማራው ከሚያውቀው በተለየ ሁኔታ ለካድሬዎቹ ሲያሰለጥን ኖሯል፡፡አማራውን ከኢትዮጵያ እኩል የሚጠሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችም ሆኑ የሌላ ዘውግ ፖለቲከኞች “ነፍጠኛ” ለሚለው ስም ያላቸው ትርጓሜ ከመለስ ዜናዊ ጥራዝ ነጠቅ ካድሬዎች የተለየ አይደለም፡፡

በነዚህ አካላት ትርጉም “ነፍጠኛ” ማለት ቅኝ ገዥ፣የሰው ባህል ጨፍላቂ፣የሰው መሬት ቀማኛ፣በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች ላይ የዘር ማጥፋት ያደረገ ጨካኝ ማለት ነው፡፡በዚህ እሳቤ መሰረት አሁን በህይወት ያሉ፣ የዚህ ነፍጠኛ የተባለው “ጭራቅ” ልጆች ደግሞ አሁን ላይ የአባቶቻቸውን ሃጢያት ደሞዝ ማግኘት አለባቸው የሚል የማይናወጥ አቋም አለ፡፡ይህ እሳቤ ነው በኢትዮጵያ ዳርቻ ላሉ አማሮች በህይወት የመኖር ስጋት፣ይህ እሳቤ ነው አማራ ክልልን በየአጋጣሚው የማሳቀል ምክንያት፣ይህ እይታ ነው ጊዜ እና ቦታ ሳያስመርጥ ከባስልጣን እስከ መደዴ የፖለቲካ ንግግር ማሳመሪያው አማራን ማንጓጠጥ አድርጎ እንዲታሰብ ያደረገው፡፡ችግሩ አማራውን በማንጓጠጥ የሚቆም ቢሆን ኖሮ በአመዛኙ  የአማራ ህዝብ ካለው ጠንካራ የስነልቦና ውቅር አንፃር አሳሳቢ አይሆንም ነበር፡፡ ዋናው ችግር ይህ እሳቤ ወደ ተግባር ተቀይሮ እጅ እና እግር፣ጥፍር እና ጥርስ አውጥቶ አማራውን እና የአማራ የተባለን ነገር ሁሉ ሊውጥ መንደርደሩ ነው፡፡ይህ አደጋ በቀጥተኛ ቋንቋ ሲገለፅ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው አማራ በተለይ በከፍተኛ የእልቂት ስጋት ውስጥ መገኘቱ ነው፡፡

ይህን ችግር ለማቃለል ክልሉን ከሚመሩት መኳንንት የቀረበ ሰው የለም፡፡ችግሩን ለማቃለል በክልሉ ሹማንት ሊደረግ የሚገባው ቀዳሚው ነገር ከክልሉ ውጭ ለሚኖረው አማራ ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን መረዳት ነው፡፡ይህን ከተረዱ በኋላ በመጀመሪያ ከእራሳቸው ፓርቲ ጓዶች የሚመጣውን እልቂት የሚጠራ የአደባባይ ንግግር በአንክሮ ተመልክቶ በጠንካራ ወገብ መፋለም ነው፡፡ይህ ማለት አንድ ሁለት ቀን ተደርጎ የሚረሳ የሁለት ካድሬዎች የፌስ ቡክ ንትርክ ማለት አይደለም፡፡ከዛ ያለፈ ነገር ያስፈልጋል፡፡ባለቤት ካልናቁ አጥር አይነቀነቅምና “በአንድ ፓርቲ ጥላስር ያለ አጋር ተዝናንትቶ በአደባባይ የምመራውን ህዝብ የሚወርፈው እኔን እንዴት ቢያየኝ ነው?” ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፤በግማሽ አይን መታየት ጥሩ ነገር አለመሆኑን ለራስ መንገር ያስፈልጋል፣መከባበር የሌለበት የሽንፈት ህብረት ወንዝ እንደማያሸግር አምኖ ለዚሁ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ በፓርቲ ስብሰባዎች፣በፖለቲካዊ ግንኙነቶች ወቅት አጥንት ለብሶ መቆምን ይጠይቃል፡፡

የቤትን እርግጫ አደብ ካስያዙ በኋላ የሚቀጥለው ከወጭ የሚመጣውን ውረፋ መቋቋም ነው፡፡ከውጭ የሚመጣው ውረፋ ከዘውግ ብሄርተኞች የሚሰነዘር የአማራውን ህዝብ ህይወት እጅግ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ፣የማምለክ መብቱን የሚጥስ በአጠቃላይ አማራነትን የሞት ምልክት የሚያደርግ እጅግ አደገኛ ነገር እየሆነ መጥቷል፡፡ይህን ነገር ዝም ብሎ ማየት የአማራ ህዝብ ፍትህን ከእጁ እንዲያገኝ መገፋፋት፣ሃገራችንንም ወደ አላስፈላጊ ትርምስ መክተት ነው፡፡ቤኒሻንጉል ላይ የአማራ ህፃናት ሳይቀሩ በቀስት ሲሰነጠቁ ክልሉን የሚመራው አመራር ችላ በማለቱ የሆነው ነገር የሚታወቅ ነው፡፡ያን መሰል ድርጊት አሁንም እንዳይደገም መፍትሄውን ማምጣት የሚችለው መራሩ ነው፡፡መፍትሔ ማምጣት ማለት ደግሞ ህፃን ልጅን እንኳን የማያሳምን “እየተከታተልን ነው፣ጎጅ ባህል ስለሆነ ነው፣እልባት ለመስጠት አቅጣጫ ተቀምጧል” የሚል አሰልች ፕሮፖጋንዳ መደርደር አይደለም፡፡የአማራ ህዝብ በሚገደልበት ክልል ሁሉ ክልሉን የሚመሩ ባለስልጣናት ችልታ ወይ እገዛ አብሮ አለ፡፡ይህ ቅድም ከላይ የተነሳው መለስ ዜናዊ በካድሬዎቹ ውስጥ አስርጎት የሄደው ስልጠና ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ አማራው በሚታረድበት ጥጋጥግ ያሉ አመራሮች ሁሉ ሃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው የሚጠየቁበትን መንገድ ጠንከር ብሎ መጠየቅ የአማራ መኳንንት ፋንታ ነው፡፡በየሚያስተዳድሩት ክልል  አማሮች ሲታረዱ፣ቤታቸው ሲቃጠል፣እምነት ቦታቸው ዶግ አመድ ሲሆን ዝም የሚሉ በብልፅግና ፓርቲ ስር ያሉ አመራሮች አማራ የክልልን ከሚመሩ ጓዶቻቸው ይልቅ ለነጃዋር የሚቀርብ ስነ-ልቦና ያላቸው እንደማይጠፉ ግልፅ ነው፡፡እነዚህን አመራሮች ተከታትሎ መገዳደር የአማራ መኳንንት ስራ ነው፡፡በአጠቃላይ የአማራ ህዝብ ስቃይ ነፍጠኛ የሚለውን ስም እና ተከትሎት የሚመጣውን እሳቤ ተንተርሶ የሚመጣ ነውና ይህን የነቀፌታ እሳቤ በአደባባይ ማፀባረቅ ቀለል ተብሎ የሚነገር መሆኑን ማስቆም ግድ ነው፡፡ሌሎች ብሄረሰቦች ሊባሉ የማይፈልጉትን ስም ማስወገድ የቻሉት ወከልናችሁ የሚሏቸው ልጆቻቸው ተግተው ስለሰሩ ነው፡፡ “ለሌሎች ህዝቦች የሚደረገው ጥንቃቄ ለእኔ ህዝብ የማይደረገው እኔ ምን ቢጎድለኝ ነው?” ብሎ ማሰብ ከባድ ነገር አይደለም!

ራስን በትክክል መግለፅ

የዘውግ ፖለቲከኞች የአማራን ክልልን በውስጡ ያሉ ብሄረሰቦችን መብት ካለማክበር እስከ ዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀም ድረስ በደረሰ የበሬ ወለደ ክስ እንደሚያብጠለጥሉ የሚታወቅ ነው፡፡ የክልሉ መንግስት ለዚህ ዘመቻ ምንም የሚመልሰው ነገር ስለሌለ የሃሰት ክሱ የብቸኛ እውነትነትን ማማ ተቆናጦ ቁጭ ብሏል፡፡ ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው የቅማንት ህዝብ በህገመግስቱ በተደነገገው መሰረት  ብሄረሰብ የሚያስብለው የተለየ ቋንቋ ሳይናገር፣ አማርኛ እየተናገረ የልዩ ብሄረሰብ አስተዳደር የተሰጠው ብቸኛ ህዝብ መሆኑን ሳይሆን ጥያቄው ታፍኖ በአማራ ልዩ ሃይል የዘር ማጥፋት እየተደረገበት እንደሆነ ነው፡፡ይህን የሚያራግበውን ሚዲያ በህግ ተጠያቂ ማድረግ ቀርቶ የተለያዩ ሚዲያዎችን ተጠቅሞ የአማራ ክልል ለቅማነት ህዝብ ያደረገውን እላፊ መብት የማክበር ፈለግ የማስተዋወቅ ስራ እንኳን መስራት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ ሃሰቱ እውነት አክሎ በአማራ ህዝብ ጠላቶች የፕሮፖጋንዳ ከበሮ ይመታበታል፡፡

የአማራ ክልል የሚብጠለጠልበትን የብሄረሰቦች መብት የመደፍጠጥ የሃሰት ወሬ ውድቅ የሚያደርገው የቅማንት ጥያቄ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ለኦሮሞ፣ለአገው ህዝቦች የተሰጠው የራስን በራስ የማስተዳደር መብትም ሌላው ምስክር ነው፡፡ የአማራ ክልልን በብሄረሰቦች መብት ጨፍላቂነት የሚከሱ ሰዎች የእኛ በሚሉት ክልል በአማራው፣በጋሞው፣በጉራጌው ወላይታው፣ጌዲኦው ላይ  በአደባባይ በማይክራፎን ግልፅ የዘር ማጥፋት አዋጅ የሚታወጅበት ነው፡፡ይህን ጠቅሶ ታገሱ የሚል እውነታውን የሚያሳይ ያልተጋነነ፣ፕሮፖጋንዳ ያልሆነ፣ህዝብን ከህዝብ የማያጋጭ ግን ደግሞ እውነቱን የሚያሳይ የሚዲያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ነገር ካልተሰራ እነዚህን አካላት ከአማራው ህዝብ አናት ላይ ማውረድ አይቻልም፡፡ይህን ለማድረግ ደግሞ የአማራን ክልል የሚመሩት አመራሮች ቀዳሚ መሆን አለባቸው፡፡ በተግባር ሲታይ ግን ይህን በማድረጉ ረገድ አንድ የፌስቡክ ገፅ ያለው ግለሰብ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ ይመስላል፡፡ ይህ የግለሰቦች የማህበራዊ ደረ-ገፅ እንቅስቃሴ ደግሞ ደምፍላት ያለው፣ሙሉ እውነታውን ሊያቀርብም የማይችል፣ጭራሽ ግጭቱን የሚያካርር በመሆኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚበልጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የክልሉ መንግስት ነገ ዛሬ ሳይል የክልሉን ተጨባጭ እውነታ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ሃሰትን ቦታ ማስለቀቅ ይጠበቅበታል፡፡

ያደረ አጀንዳን የመግለጥ ስራ

በአሁኑ ወቅት እየተጋጋለ የመጣው አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጎራ ከህወሃት ውድቀት ወዲህ የታየው ለውጥ በኦሮሞ ልጆች ትግል የመጣ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ስለሆነም ህወሃት ያደርግ እንደነበረው የትግል ጀብዷቸውን እየተረኩ የህወሃት የበላይነትን በኦሮሞ ሊሂቃን የበላይነት ለመተካት ይሻሉ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃት ከዚህ አልፎ በመሄዱ ምኞታቸው ስጋ ሊለብስ አልቻለም፡፡ይልቅስ ኦሮሞ ብቻ ታግሎ እንዳመጣው የሚያምኑት ለውጥ የዘረጋው ፖለቲካዊ ዘይቤ እያሳካ ያለው  ነፍጠኛ/አሃዳዊ እያሉ በተለያየ ስም የሚጠሩትን የአማራን ህዝብ ፖለቲካዊ እሳቤ እንደሆነ ያምናሉ፤አምነውም ይብሰለሰላሉ፡፡በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ጎራ እሳቤ መሰረት ኢትዮጵያ የተሰራችበትን እውነት ተቀብሎ፣የሚታረመውን አርሞ፣አንድነቷ ተጠብቆ ወደ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ የምትሄድበትን መንገድ መተለም የአማራ ብቻ ናፍቆት ነው፡፡ለዚህ ነው ከኦሮሞ  ህዝብ የወጣውን ጠቅላይ ሚንስትር አብይን አፄ ምኒልክን በሚጠሉበት ጥላቻ አምርረው የሚጠሉት፣በአማራ ጉዳይ አስፈፃሚነት የሚከሱት፡፡ይህን ሁሉ ያመጣው አሁን የመጣው ለውጥ የመጣው በኦሮሞ ልጆች ትግል ሆኖ ሳለ የጠቀመው ግን አማራን ነው ብሎ ከማሰብ ነው፡፡

ይህን የተንሸዋረረ እሳቤ ማስተካከል አሁንም በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ የአማራ መኳንንት ተቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት፡፡የማስተካከያ ስራው መጀመር ያለበት ደግሞ የመጣው ለውጥ አክራሪ ብሄርተኞች እንደሚያስቡት ለአማራው የተለየ ያመጣው ነገር እንደሌለ ነው፤ይልቅስ የአማራህዝብ ሃገሩ በለውጥ ምጥ እንዳትሞት ፣ለውጡ እስኪረጋ ድረስ ጊዜ በመስጠት፣ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደሙ ብቻ በይደር ያስቀመጣቸው በርካታ አጀንዳዎች እንዳሉት ማሳወቅ ነው፡፡በይደር የተቀመጡ አጀንዳዎችን ወደማሳቱ ከማለፌ በፊት ግን ሌላ አበይት ነጥብ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ይኽውም ጠ/ሚ አብይን ወደ ስልጣን ያመጣው ለውጥ ሲረገዝም ሆነ ሲወለድ አማራው በአቶ ደመቀ መኮንን በኩል ከማንም በላይ ለስልጣን ቅርብ ሆኖ ሳለ ለስልጣን ልሙት ሳይል ሃገር የሚያረጋጋው መንገድ ስልጣን መያዙ ስላልመሰለው ስልጣኑ ወደ ኦሮሞ ተወላጁ ዶ/ር አብይ እንዲዞር አድርጓል፡፡ እዚህ ውስጥ ብዙ ትርጉም አለ!

ይህን ትርጉም ለማወቅ የሃገር አጀንዳ ከዘውግ አጀንዳ ዘለግ እንደሚል መረዳትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ያደረገ ሰው ናፍቆቱ ገዘፍ ያለው ሃገር የማዳን ተግባር እንጅ የመንደር ልፊያ እንዳልሆነ የሚገባው የሃገርን ትርጉም የሚያውቅ ብቻ ነው፡፡ጠ/ሚ አብይ ከገዛ የዘውጉ ሰዎች ሰባት ጦር የሚወረወርበት ይህ የገባው ሰው ስለሆነ ነው፡፡ጠ/ሚው የሚጠበቅበትን ያህል ሃገር የማረጋጋት ስራ እንዳይሰራ እግር ተወርች የታሰረውም በዚሁ እሳቤ ተሸካሚ የዘውጉም፣የፓርቲውም መካከለኛ እና ዝቅተኛ  ሹመኞች፣የህግ /የፀጥታ አካላት ህቡዕ ስራ ነው፡፡

ስልጣን ላይ ልሙት ሳይል ስልጣን አሳልፎ የሰጠው የአማራው ናፍቆት ሃገር ማዳን ነበር፡፡ የዚህ ስራ ትክክለኛ ትርጉም የሚገባው ግን ለሃገር ግድ የሚለው ብቻ ስለሆነ ክልል እና ሃገር የተሳከረባቸው ሰዎች የሰጡት ትርጉም ሌላ ሆነ፡፡ ስልጣንን አሳልፎ መስጠት ማጉድል መሆኑ ቀርቶ ማትረፍ ተደርጎ ተተረጎመ፡፡በታሪክ ለኢትዮጵያ ሲሞቱ የነበሩ ኦሮሞ አርበኞችን ለአማራ ንጉስ ብለው ነው ወደ ጦርሜዳ ሄደው ቀኝ ገዥን የተፋለሙት ሲሉ የኖሩት የኦሮሞ ብሄርተኞች አሁን የሃገሪቱን የመጨረሻ ስልጣን የያዘው ኦሮሞው አብይ ሲሆንም ኢትዮጵያን የሚለው በስሩ ላሉ አማሮች ተገዝቶ እንደሆነ ሲናገሩ አያፍሩም፡፡ስለዚህ የአማራ መኳንንት በመጣው ለውጥ ሃገር ያሰነበቱ መስሏቸው ሳይከራከሩ ስልጣን አሳልፈው እንደሰጡ፣በዚህም መላው አማራ ከማንም በላይ ደስ እንዳለው ማሳሰብ ሳይስፈልጋቸው አልቀረም፡፡ለዚህ ለውጥ መምጣት የብአዴን ባለስለጣናት ከህወሃት ጋር ያደረጉትን ትንቅንቅ መግለፅ ቢቻልም በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ እየበዛ የመጣውን የብቸኛ ጀግንነት አጉል ቀንድ ሊሞርደው ይችላል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው የአማራ ፖለቲከኞችም ሆነ ህዝቡ ኢትዮጵያ ከለውጥ ነውጥ እስክትድን በእናት ሃገራቸው ህመም ላይ ሌላ ራስ ምታት ላለመጨመር ሲሉ ያሳደሯቸው አጀንዳዎች እንዳሉ ማሳወቅ ነው፡፡ይህን ማድረጉ ለውጡ ለአማራ የተለየ ቱርፋ ያመጣ ለሚመስላቸው አካላት እንዲረጋጉ በማድረግ በኩል ጥቅም ይኖረዋል፡፡ከነዚህ አጀንዳዎች አንዱ ወልቃይትን ጨምሮ ሌሎች ከጎንደር ግዛት ላይ በህወሃት ተዘርፈው የተወሰዱ ለም መሬቶች፣እነዚህን ለም መሬቶች ለመወሰድ ሲል ህወሃት በአማራ ህዝብ ላየ የፈፀማቸው ዘር ማጥፋቶች፣ሰው ሰራሽ የዲሞግራፊ ለውጦች፣የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጉዳይ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ ከዚሀ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከጎንደር ግዛቶች እየታፈኑ ተወስደው ትግራይ እስርቤት ስለታሰሩ እስረኞች ቢነሳ ብዙ ጉድ አለ!

እንደሚታወቀው በደቡብ ክልል ያለው የሲዳማ ዞን ልሂቃን  ወደ ክልል ለማደግ የሚያደርጉትን ትግል አጧጡፈው ያነሱት ህወሃትን ባስወገደው ለውጥ ማግስት ነው፡፡ ይህን ትግል ሲያደርጉ ዛሬውኑ ጥያቄያችን ይመለስ የሚል ፋታ የሌለው ትግል አድርገው፣በርካታ ነዋይ ፈሰስ ተደርጎ ሪፈረንደም አስደርገው ጥያቄያቸው አንድም ሳይሸረፍ መቶ በመቶ መልስ አግኝቷል፡፡ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄም በአማራ ህዝብ ዘንድ ከዚህ ያነሰ አንገብጋቢነት ያለው ነገር አይደለም፡፡ነገር ግን ከህወሃት ጋር ጠመንጃ እስከመማዘዝ ደርሶ የነበረው የወልቃይትማንነት ኮሚቴ ለውጡን ተከትሎ የመረጋጋት ዝንባሌ አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው የምንወዳት ሃገራችን ባለባት ህመም ላይ ሌላ ህመም ጨምሮ ሞቷን ላለማፋጠን ሲባል እንጅ አማራው በወልቃይት ጉዳይ ላይ የደረሰበት መከራ ቀላል ሆኖ ወይም ለወጡ ጥያቄውን መልሶለት አይደለም፡፡

ሌላው አጀንዳ በአማራው ህዝብ ቁጥር ላይ ያለው ጥያቄ ነው፡፡እንደሚታወቀው ህወሃት አማራውን ለማሳነስ ካለው አምሮት የተነሳ 2.8 ሚሊዮን አማራ የገባበት ጠፋ ሲል በአደባባ ተናግሯል፡፡ይህ የቁጥር መቀነስ ስትራቴጅ አማራው በፓርላማ ያለውን ወንበር ለማሳነስ፣ለክልሉ የሚመደበውን በጀት ለመቁረጥ፣የህዝቡን የፖለቲካ ተደራዳሪነት ግዝፈት ለመቀነስ የተደረገ የህወሃት የዝቅተኝት ስነልቦና የወለደው አካሄድ ነው፡፡ይህ የህዝብ ቁጥር ጉድለት አማራው ሁሉ ይሁን ብሎ የተቀበለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ይልቅስ ሃገርን በማስቀደም የተተወ ነገር እንጅ! ሐገርን ባያስቀድም ኖሮ ይህ ሁሉ ህዝብ የገባበት ጠፋ የተባለው የአማራ ህዝብ የህዝብ ቆጠራ ተደርጎ ሎች እንደሚሉት “በቁመናየ ልክ ወንበር ካልተደለደለልኝ ምርጫ ውስጥ አልገባም” በማለት ሃገር የማመሱን ረብሻ መቀላቀል ይችል ነበር፡፡ህዝብ ቆጠራው ቢቀር እንኳን ጠፋ የተባለው ህዝብ ተደምሮ አሁን ባለኝ ህዝብ ቁጥር ላይ ይደመርልኝ ማለት ይቻላል፡፡ግን አልተደረገም፤አልተደረገም ማለት ግን ጥያቄ የለም፤እንደሚታሰበውም ለውጡ ለአማራዊ ፍላጎት የቆመ ስለሆነ አማራው ደስ ብሎት ዝም አለ ማለት አይደለም፡፡ይልቅስ አማራው ኢትዮጵያን የሚለው ከጉድለቱ ጋር ጭምር በመሆኑ ነው፡፡ይህን አስረግጦ ማስረዳት ደግሞ የአማራ መኳንንት ስራ ነው፡፡ ካልሆነ ሃገር ባልሆነ ተረክ ስትታመስ መክረሟ ነው፡፡

እያዚም ቤት እሳት እንዳለ ማሳሰብ

የአማራን ክልል በእጅ አዙር እያመሰ ያለው የቅማንትን ጥያቄ ተገን አድርጎ ከዘውግ ፖለቲከኞች የሚነሳው ተግዳሮት ነው፡፡ የዚህ ተግዳሮት ፊት አውራሪ ህወሃት ስትሆን ቀጣዩ ደግሞ ህወሃት የእስትራቴጅክ አጋሩ እንደሆነ በአደባባይ የመሰከረው የጃዋር ካምፕ ነው፡፡በተለይ ህወሃት የቅማንትን ጉዳይ ያለ ይሉኝታ የገባበት ከመሆኑ ብዛት የቅማንት ኮሚቴ እያለ ለሚጠራቸው ስብስቦች መቀሌ ቢሮ እስከመስጠት ደርሷል፡፡ በዚሁ ኮሚቴ ስም ታጣቂ እያስገባ የአማራ ክልልን የሚያምሰው ነገርም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ህወሃት ይህን የሚያደርገው የቅማንት ህዝብ የትግሬ ማንነት አለኝ ባላለበት ሁኔታ ነው፡፡በአንፃሩ የትግራይ ክልል አማራ ነኝ የሚሉ የወልቃይት ህዝቦች እና ወደ አማራ ክልል መካለል እንፈልጋለን የሚሉ የራያ ህዝቦች  ያሉበትን መሬት በጉልበት ዘርፎ ወስዶ፣ሰዎቹን መብታቸውን ረግቶ በግዞት እያኖረ ነው፡፡

ይህን ህወሃት መራሹ የትግራይ ክልል አስተዳደር የሚያደርገውን ግፍ ለመታገል የወጡ የወልቃይት ማንነት እና የራያ ማንነት ኮሚቴዎች ግን ወደ ግዛቱ እንካለል ከሚሉለት የአማራ ክልል አስተዳደር ይህ ነው የሚባል እርዳታ አግኝተው አያውቁም፡፡የትግራይ ክልል አስተዳደር ምንም በማይመለከተው የቅማንት ማንነት ኮሚቴ ውስጥ ይህን ያህል የወሳኝነት ሚና ሲወስድ የአማራ ክልል አማራ ነኝ ለሚሉ ግን ደግሞ በህወሃት ከባድ ቀንበር ስር ላሉ ህዝቦች ይህ ነው የሚባል እርዳታ ያለማድረጉ የመፋዘዙ እንጅ የብልህነቱ ምልክት ሆኖ አይታየኝም፡፡በርግጥ ህወሃት በአማራ ክልል ላይ እንደሚያደርገው የአማራ ክልል ሹማምንትም ወደ ትግራይ ክልል ታጣቂ እያሰረጉ ማተራመስ ልክ መንገድ አይደለም፡፡ከዚህ በመለስ ግን አማራ ነን በማለታቸው አበሳ ለሚያዩ ህዝቦች ድጋፍ ማሳየት ተገቢ ነገር ነው፡፡ይህ ዋናው ነገር ሆኖ እግረ መንገዱን ለህወሃትም እዚያም ቤት እሳት አለ የሚል መልዕክት መስጠቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ የትግራይ ክልል አስተዳደር የራሱ መታወቂያ የሆነውን የህዝቦች መብት መደፍጠጥ ወደ አማራ ክልል የማላከክ ፕሮፖጋንዳውንም ሆነ ወደ አማራ ክልል የሚልከውን ፈተና ለመቀነስ ይረዳል፡፡  

የአቶ ለማ መገርሳ “ልዩነት” ሰምና ወርቅ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ታህሳስ 10 , 2012 ዓ. ም.

“የለማ ቡድን” የሚባለው ስብስብ የህወሃትን የበላይነት የማስወገዱ ታላቅ ትግል በሚዘከርበት ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይዞ ሲወሳ የሚኖር ቡድን ነው፡፡ይህ ቡድን ሃገራችን በለውጥ ወሊድ እንዳትሞት ያደረገ ባለውለታ ነው፡፡የለማ ቡድን በስተመጨረሻው የህዝብን ትግል ባይቀላቀል ኖሮ የሃገራችን እጣ ፋንታ እንደ ሊቢያ ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡የዚህ ቡድን መጠሪያ በስማቸው የተሰየመላቸው አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊነትን አንግበው ለውጥ እንደሻቱ ሲናገሩ የብዙውን ኢትዮጵያዊ ልብ በሃሴት ሞልተዋል፡፡ ኢትዮጵያን አጀንዳ አድርጎ መነሳቱ ከወደ ኦሮሞ ብሄርተኝት ፖለቲከኞች መንደር እምብዛም የተለመደ ስላልሆነ ነበር ደስታው፡፡

የሆነ ሆኖ የአቶ ለማ የድንገቴ ኢትዮጰያዊነት መንፈስ እና ይህን ጉዳይ ከሱስ ጋር አናፅረው ያቀረቡበት መንገድ እኔን ጨምሮ አንዳንዶቻችንን ጥርጣሬ ላይ ጥሎን ነበር፡፡ባህር ዳር ላይ “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ያሉት አቶ ለማ ከባህርዳር ሲመለሱ አዲስ አበባ ላይ ከአራቱ ፓርቲዎች ሊቃነመናብርት ጋር መግለጫ ለመስጠት በተቀመጡበት ደግሞ “ኢትዮጵያዊነት በግድ የተጫነብን ስለሆነ ለመለማመድ ጊዜ ያስፈልገናል”ሲሉ መሰማታቸው በግሌ ግራ አጋብቶኝ “በለማ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው?” በሚል ርዕስ በከተብኩት ፅሁፍ ነገሩን በጥንቃቄ ማየት እንደሚገባ በገባኝ መጠን ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡አቶ ለማ ከዚች ቀን ንግግራቸው ሌላ ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ንግግር አለመድገማቸው ኢትዮጵያን የሚለው ሰው እያደር እንዲያምናቸው ሆነ፡፡    

ለውጡ ከተዋለደ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት የመጡት አቶ ለማ ታዲያ ከህወሃት መባረር በኋላ ስለኢትዮጵያ ቀድሞ በሚናገሩበት ሁኔታ ሲናገሩ የተደመጡት ሚኖሶታ ላይ ከዶ/ር አብይ ጋር ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ብቻ ነው፡፡ኋላ ላይ “የከተማ ፖለቲካን መቆጣጠር ወሳኝ ነገር በመሆኑ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን አዲስ አበባ መሃል እና ዳር ዳር ማስፈር ይዣለሁ” ሲሉ የሚናገሩበት ቪዲዮ በዶ/ር አብረሃም አለሙ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ተመልሶ መውጣቱ፣በዚህ ቪዲዮ የሚናገሩት ደግሞ ዶ/ር አብይም ጭምር መሆናቸው “ያለን ኢትዮጵያዊ አጀንዳ ነው” ሲሉ እጅግ አምኗቸው ለነበረው ህዝብ ትልቅ ግራ መጋባትን የፈጠረ ነበር፡፡

ከዛ ወዲህ ለማ ከአደባባይ ጠፉ!ከዕይታ በመጥፋታቸው ብቻ ሳይሆን ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድርነት መነሳታቸውን እና በአደባባይ መታየት በመቀነሳቸው “እስከ ሞት እከተለዋለሁ” ካሉት ባልንጀራቸው ዶ/ር አብይ ጋር እንደ ወትሮው እንዳልሆኑ መወራት ያዘ፡፡በሌላ በኩል አብይ እና ለማ እጅ እና ጓንት ሆነው በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ስም ለኦሮሞ የበላይነት የሚሰሩ ተደርጎም ይወሰድ ነበር፡፡

እውነት እና ንጋት እያደር ጠርቶ የዶ/ር አብይ እና የአቶ ለማ የሃሳብ ልዩነት በራሳቸው በአቶ ለማ አንደበት ይፋ ሆነ፡፡ ይህ ልዩነት መከሰቱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ልዩነቱ የተከሰተበትን ምክንያት መመርመሩም አስፈላጊ ነው፡፡ሃገራችን ተቋማዊ ዲሞክራሲን ያልገነባች በመሆኗ የፖለቲካዋ እጣ ፋንታ ስልጣን በተቆናጠጡ ሰዎች ፍላጎት፣ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ፣የግል ማንነት በእጅጉ የሚላጋ ነውና የአቶ ለማ ልዩነት ዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ልዩነት ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ሳይሆን በትኩረት መተንተን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

አቶ ለማ ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ያስቀመጧቸው ሃሳቦች ለልዩነታቸው ዋነኛ የሆኑ ምክንያቶችን ያስረዳሉ፡፡በዚህ ቃለ ምልልሱ አቶ ለማ ያነሱት አንደኛው ነጥብ “ከሆነ ጊዜ ወዲህ ተሰሚነቴ ቀንሷል” የሚል ነው፡፡ይህ ተሰሚነቴ ቀንሷል የሚለው ነገር ህወሃትን ለመጣል በሚደረገው ትግል አቶ ለማ ዶ/ር አብይ የኦህዴድ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የፈለጉበትን ምክንያት የሚጠቁም ጭላንጭል አለው፡፡አቶ ለማ ለዶ/ር አብይ የኦህዴድ ሊቀመንበርነታቸውን የለቀቁላቸው እርሳቸው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መቀመጫ ወንበር ስለሌላቸው ነበር እንጅ ይህ ቅድመ ሁኔታ ቢሟላላቸው ኖሮ ወንበራቸውን አሳልፈው ለሌላ ይሰጡ ነበር ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡አብይ በወቅቱ የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር መሆናቸው ደግሞ አቶ ለማ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ለሌላ የኦህዴድ ሰው የመስጠታቸውን ሁኔታ ሩቅ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር ደግሞ አቶ ለማ እና ዶ/ር አብይ ጓደኝነት ነው፡፡አቶ ለማ ዶ/ር አብይን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያበቃውን የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ወንበር የመልቀቃቸው “ውለታ”፣ሁለቱ ሰዎች ያላቸው ጓደኝነት እና የዶ/ር አብይ የፓርቲ ጓዶቻቸውን በተቻለ መጠን እንደፀባያቸው አባብሎ ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት(የለማ ልብ መሻከር ከገፃቸው ላይ እየተነበበም አብይ “የኖቤል ሽልማቴን ለድህነት ጓዴ ለለማ ሰጥቻለሁ” ማለታቸውን ልብ ይሏል) ወዘተ ለለማ የሚሰጠው መልዕክት ይኖራል፡፡ይህ መልዕክት ጠ/ሚ አብይ የለማ ሌላኛው እጃቸው እንደሚሆኑ፣ለማ አድርግ የሚሏቸውን የሚያደርጉ እሽ ባይ እንደሚሆኑ የማሰብ ሳይሆን አልቀረም፡፡አቶ ለማ የጠ/ሚነቱን መንገድ መጥረጊያ የሆነውን የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ለአብይ አመቻችተው የማቅረባቸው ውለታም በለማ በኩል ለተጠበቀው የአብይ እሽ ባይነት እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

“ተሰሚነቴ ቀንሷል” የሚለው አባባል አቶ ለማ ባሰቡት ልክ አብይን መዘወር ያለመቻልን ቅሬታ ያዘለ ነገር አለው፡፡ነገሩ የመዘወር ፍላጎት ባይሆን ኖሮ አቶ ለማ አለኝ የሚሉት የሃሳብ ልዩነት በአብላጫ ድምፅ ከተሸነፈ ማድረግ የነበረባቸው በዲሞክራሲያዊ አካሄድ ሃሳባቸው ብዙሃኑን ማሳመን ስላልቻለ በድምፅ መበለጣቸውን ተቀብለው መቀጠል እንጅ “ተሰሚነት አጣሁ” ብሎ ለክስ መነሳት አልነበረም፤በዲሞክራሲያዊ የድምፅ ብልጫ መሸነፍ ማለት ተደማጭነት ማጣት አይደለምና፡፡በዲሞክራሲያዊ የድምፅ ብልጫ የተሸነፈ ሃሳብ ገዥ ያልሆነው የእኔ ተደማጭነት ስለቀነሰ ነው ማለት “ህግ መሆን ያለበት የኔ ሃሳብ ነው” የማለት የመዘወር ፍላጎት የማያጣው ዝንባሌ ነው፡፡  

ለማ በምን መልኩ ነው አብይን ሊዘውሩ የሚፈልጉት የሚለው ተገቢ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡የዚህጥያቄ መልስ የሚገኘው ደግሞ “የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ ያስረከበንን ጥየቄ ሳንመልስ ቀረን” የሚለው የአቶ ለማ ንግግር ውስጥ ነው፡፡ 

የኦሮሞ ልሂቃን “ስም አይጠሩ” ጥያቄዎች

የኦሮሞ ህዝብ እንደሰው የሰው ልጆች ሁሉ የሚጠይቁት የሰብዓዊ መብት፣የዲሞክራሲ፣የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ይኖሩታል፡፡በታዳጊ ሃገር እንደሚኖር፣ መብቱ ተረግጦ አንደኖረ ህዝብ ደግሞ ከማኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር የሚጋራው በርካታ ጥያቄ ይኖረዋል፡፡እንደ ኦሮሞነቱ ደግሞ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡የኦሮሞ ህዝብ እንደ ሰውነቱም፣እንደ ኢትዮጵያዊነቱም ሆነ እንደ ኦሮሞነቱ  የሚያነሳቸው ጥያቄዎችን አንግቦ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ ታግሏል፡፡

በህዝባዊ ትግሉ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ግልፅ ነበረ፡፡ከቀየው ያለመፈናቀል፣ያለመታሰር ፣ያለመሳደድ፣በማንነቱ የመከበር፣በክልሉ ሃብት ተጠቃሚ የመሆን ጥያቄዎች ናቸው የኦሮሞን ህዝብ ለትግል ያሰለፉት፡፡ከዚህ በተጓዳኝ ሲነሳ የሚሰማው ኦሮምኛን የኢትዮጵያ የስራ ቋንቋ የማድረግ ጥያቄ ነው፡፡ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ህዝብ ከሰው ፍጥረት፣ከኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ የተለየ ረቂቅ ጥያቄ ሊኖረው አይችልም፡፡ሆኖም በግልፅ እንዳይናገሩት አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት ደረጃ የማይፈቅድላቸው በኦሮሞ ህዝብ ስም የራሳቸውን ረቂቅ ጥያቄ አንግበው የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ልሂቃን አይጠፉም፡፡በየደረሱበት “የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ” እያሉ የሚያመሳጥሩትም የራሳቸው ልቦና የሚጠይቃቸውን ጥያቄ ነው፡፡ይህን ጥያቄ መመርመር የፖለቲካችንን ፈር የሚያሳይ ነውና ወደዛው ልለፍ፡፡

ጥያቄ አንድ

እነዚህ የኦሮሞ ልሂቃን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታ ናቸው፡፡የመጀመሪያው ማንኛውም የበለጠ ታግያለሁ ባይ የሚያነሳው ይበልጥ በመታገሌ በሃገሩ ፖለቲካ ላይ በለጥ ብየ ልታይ የሚል የውለታ አስቆጣሪነት፣የልብለጣችሁ ባይነት ጥያቄ ነው፡፡በርካታ የኦሮሞ ልሂቃን አሁን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ እንዲመጣ የታገለው ኦሮሞ ነው ብለው ያስባሉ፡፡አስበውም ህወሃት ያደርገው እንደነበረው የኦሮሞ የበላይነት በሃገሪቱ እንደሚጣ አጥብቀው ይሻሉ፡፡ይህ ፍላጎት ኦሮሞ ከዚህ በፊት ስልጣን ላይ እንዳይወጣ ተደርጎ ሲናቅ፣ሲጨቆን ኖሯል የሚል ከስነ-ልቦናዊ ነገር ጋርም ተያያዥነት አለው፡፡አሁን ተጠራርቶ ስልጣን ላይ መቀመጡ የሚፈለገውም ሲንቀኝ፣ሲጨቁነኝ ነበር ተብሎ የሚታሰበውን አካል ከዋነኛ የፖለቲካ ጨዋታ ውጭ አድርጎ ለመበቀል ያለመ ህወሃት ሲጓዝበት በነበረው መንገድ ለመጓዝ የመፈለግ ዝንባሌ ነው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰኑ የኦሮሞ ብሄርተኞች ወደ ህወሃቶች መለስ ቀለስ ማለታቸው፣በግልፅ ህወሃት ስትራቴጃዊ አጋራችን ነው ሲሉ መደመጣቸው የዚህ ዝንባሌ ምልክት ነው፡፡

ሆኖም ከአዘቦታዊው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትርክት ከፍ ብለው የመጡት ዶ/ር አብይ እና በጣም ጥቂት የኦህዴድ ጓዶቻቸው ይህ አካሄድ እንደማያዋጣ፣ለኦሮሞ ህዝብም የሚጠቅመው በእኩልነት እንጅ በመብለጥ መኖር እንዳልሆነ ተረድተው በልጦ ለመታየት ከሚሹ የኦሮሞ ብሄርተኞች የተለየ መንገድ ያዙ፡፡በግልፅ የማይነገረው ግን ደግሞ ቀላል የማይባሉ የኦሮሞ ልሂቃን የሚጋሩት በህወሃት መንገድ የመጓዝ እሳቤ ነው በኦህዴድ ውስጥ ያሉትንም ሆኑ የሌሉትን አክራሪ ኦሮሞ ልሂቃን ከዶ/ር አብይ ጋር ሆድ እና ጀርባ ያደረጋቸው፡፡ሌሎች ምክንያቶች ከዚሁ ምክንያት የሚመዘዙ ዘለላዎች ናቸው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን አቶ ለማ መገርሳም የዚህ እሳቤ ተጋሪ መሆናቸው ነው፡፡”የኦሮሞ ህዝብ ቆጥሮ ያስረከበኝ ጥያቄ አለ” ሲሉ በኦሮሞ ህዝብ ስም ያነሱት ስም አይጠሩ ጥያቄ ይሄው ጎላ ብሎ የመታየት ምኞት ካልሆነ እንደ ጀመሩት ወደ ሚዲያ ቀርበው ተሰጠኝ ያሉትን ጥያቄ ቢያስረዱ ለመስማት የሚጓጓው ብዙ ነው፡፡

ጥያቄ ሁለት

ሌላው ስም አይጠሩ የኦሮሞ ልሂቃን ጥያቄ እነሱ “አባ ቢዩማ” የሚሉት ወደ አማርኛው ሲመለስ “የሃገር ባለቤት” የመሆን ጥያቄ ነው፡፡ይህ ጥያቄ ሳይድበሰበስ እንቅጩን ሲቀመጥ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ከኦሮሚያ ነቅሎ የማስወጣት ፍላጎት ነው፡፡የጥያቄው ዋነኛ አቀንቃኝ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የአክራሪው የኦሮሞ ብሄርተኝነት መሪው አቶ ጃዋር መሃመድ  ነው፡፡ጃዋርና ሰልፈኞቹ የኦሮሞ ህዝብ ዋነኛ ችግር ኦሮሞ ያልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በኦሮሚያ ክልል መኖሩ ይመስላቸዋል፡፡

በጃዋር እና በሰልፈኞቹ እሳቤ ኦሮሚያ ክልል የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ አማራ ከሆነ ለጭቆና የሄደ ነው፤አማራ ካልሆነ ደግሞ የኦሮሚያን ተፈጥሮ ሃብት ሊቀራመት፣ሊያራቁት የሄደ ጥገኛ እንጅ ለኦሮሚያ ማደግም የሚያዋጣው እውቀት፣ሙያ፣ገንዘብ እና ጉልበት ይዞ የሚሄድ አይደለም፡፡ስለዚህ ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ኦሮሚያን መልቀቅ አለበት፡፡በቅርቡ በባሌ በግልጽ በአደባባይ የሌሎች ብሄረሰቦች ስም እየተጠራ ከእነሱ ጋር የሚደረግ ግንኑነት እንዲቋረጥ እንዳለበት፣ ከኦሮሚያም ለቀው እንዲወጡ የሚያስፈራራ ስማበለው ሲለፈፍ መሰማቱ አንድ አስረጅ ነው፡፡በቡራዩ የተደረገው ግድያ እና ሌሎች በርካታ አጋጣሚዎች ሁሉ የዚህ እሳቤን ስር መስደድ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ይህ መጤ የማስለቀቁ ስራ ሲተገበርና ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖረው፣የሚነግደው፣ተቀጥሮ  የሚሰራው  ሁሉ ኦሮሞ ብቻ የማድረጉን አካሄድ ነው በነጃዋር የፖለቲካዊ መዝገበ ቃላት “አባ ቢዩማ”፤በአማርኛው ሲመለስ ደግሞ “የሃገር ባለቤት” የሚባለው፡፡ጃዋር ከለማ ወግኖ አብይን የሚያብጠለጥለው አብይ ይህ እሳቤ ሃገር የማዳን መንገድ እንዳልሆነ ስለተረዱ፤ሃሳቡንም ሃሳባቸው ስላላደረጉ ነው፡፡በአንፃሩ ጃዋር እና አቶ ለማ በዚህ ጉዳይ ላይ ተቀራራቢ እሳቤ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ባይሆን ኖሮ ጃዋር የለማን ስም እንደ ማስቲካ ከአፉ የማይነጥልበት ምክንያት አይኖርም፡፡

አቶ ጃዋር መሃመድ ከዛሬ ስንት አመት በፊት “Ethiopia out of Oromiya” ወደ አማርኛው ሲመለስ “ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ትውጣ” የሚለው ስሜታዊ የቪዲዮ ንግግሩን የዚህ እሳቤ ተሸካሚነቱ ምስክር ነው፡፡”ያ የቆየ ንግግሩ ነው፤ ዛሬ የእሳቤ ለውጥ አምጥቶ ይሆናል” የሚል አንባቢ ካለ ደግሞ ጃዋር ከዛሬ አምስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ወደ ሲዳማ ዞን ተጉዞ፣በሲዳማ ኮበሌዎች ተከቦ “ክልላችሁን በህግም በጉልበትም የራሳችሁ ካደረጋችሁ የክልላችሁ ሃብት ባለቤቶች ትሆናላችሁ፤የክልላችሁ ሃብት የትምክህተኞች እና የዘራፊዎች መፈንጫ መሆኑ ያበቃል፤ኦሮሚያም የኦሮሞ፣ሲዳማም የሲዳማ ብሄረሰብ ትሆናለች” ሲል የተናገረውን ማድመጥ ይቻላል፡፡በዚህ ንግግር ውስጥ ጃዋር “ዘራፊ” እና “ትምክህተኛ” ሲል የሚገልፀው በሲዳማ ዞን የሚኖር ሲዳማ ያልሆነን ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ክርክር ያለው ነገር አይደለም፡፡                           

ይህን የሚለው አቶ ጃዋር ደግሞ ገና ከመነሻው ዶ/ር አብይን ስሙን ለመጥራት ሳይቀር ሲቸገር የነበረ በአንፃሩ ደግሞ አቶ ለማን ለማሞገስ ጊዜ የማይበቃው፣በአቶ ለማ ጠ/ሚ መሆን አለመቻል ሲብሰለሰል የኖረ ሰው መሆኑ የአቶ ለማ ዘመም ዘመም ወደ አቶ ጃዋር ጎራ ለመሆኑ ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡አቶ ጃዋር ከዶ/ር አብይ ጋር አይን እና ናጫ፣ ከአቶ ለማ ጋር ደግሞ ወዳጅ እንደሆነ የሚጠቁሙ ዝንባሌዎችን በተደጋጋሚ ማሳየቱ ሳያንስ አቶ ለማ ከዶ/ር አብይ ጎራ ጋር ያላቸውን ልዩነት በቪኦኤ ወጥተው የተናገሩበት ንግግር ሳይታገድ ጭምር “ታግዷል” እያለ ደረት ሲመታ መሰንበቱ የአብይን እና የለማን፣እንዲሁም የአብይን እና የጃዋርን አሰላለፍ ልዩነት ሲጠራጠር ለነበረ ሁሉ ውዥንብሩን የገፈፈ ነበር፡፡ዋናው ጉዳይ ግን ጃዋር የለማ ልዩነት ታማኝ ምንጭ በሆነው ቪኦኤ ይፋ እንዲሆን ለምን ፋታ አጥቶ ሰራ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡

ጃዋር ይህን ያደረገው በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ የለማ ሚዛን ከአብይ ሚዛን ከብዶ የሚታይ መስሎት፣በለማ በኩል የራሱን የጃዋርን ሚዛንም በማከል የአብይን ፖለቲካዊ ሚዛን ለማቅለል ነበር፡፡ይህ ቢሳካ ኖሮ በተዋሃደው ፓርቲ ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ብሄርተኞች በውህደቱ ማግስት ንትርክ አንስተው አንድ አንድ እያሉ  በለማ ጎራ ተሰልፈው ‘የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሞ ህልውና የሌለው የነፍጠኞች ፓርቲ ነው’ የሚለውን ዘፈን ጮክ አድርጎ ለማዘፈን ነበር፤አልተሳካም፡፡ይህ የጃዋር እሳቤ ቢሰምር ኖሮ ሃገራችን ከወደ ኦሮሚያ በሚነሳ ፖለቲካዊ ድብልቅልቅ ተመትታ በቋፍ ላይ ያለው መረጋጋቷ አደጋ ላይ በወደቀ ነበር፡፡ይህ እንዳይሆን አብይ ያደረጉትን መለኛነት፣ብስለት፣ አስገራሚ ብልሃት የተሞላበት፣ እጅግ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ አለማድነቅ አይቻልም፡፡

አብይ ለማን እና ጃዋርን የመሰሉ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ እጅግ ግዙፍ ቦታ ያላቸውን ሰዎች አሸንፈው፣ኦህዴድን ሙሉ በሙሉ ይዘው ወደ ብልፅግና ፓርቲ መጓዛቸው በግሌ ተዓምር የሚመስለኝ ድል ነው፡፡እዚህ ላይ ላስመዘገቡት ባለድልነታቸው ለዶ/ር አብይ ትልቅ አድናቆት አለኝ! አድናቆቴ የሚመነጨው ደግሞ ከውስጥ አቶ ለማን የመሰሉ ምርኩዝ ባፈነገጡበት፣ከውጭ ጃዋርን የመሰለ አጯጯሂ በር ላይ ባለበት ሁኔታ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ወደ ሲቪክ ፖለቲካ ጎትቶ ማምጣት ምን ያህል አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ሙከራ መሆኑን ስለምረዳ ጭምር ነው፡፡ነገሩን ተዓምር የሚያስመስለው ሌላ ጉዳይ በብዙ ያመንናቸውን አቶ ለማን ሳይቀር የፈተነውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት እድገት ደረጃ ምን ላይ እንደደረሰ ስለምገነዘብ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ በውስጥ ውስጥ ጉም ጉም ሲባልበት የሰነበተው የአብይ እና ለማ ልዩነት በጃዋር አጋፋሪነት በቪኦኤ እንዲለቀቅ የተፈለገበት የአብይን ሚዛን የማቅለል ዘመቻ ጃዋር እንዳሰበው አብይን አቅልሎ በለማ ላይ ሞገስ ደርቧል ወይ? የሚለው ሲመረመር ነገሩ አቶ ጃዋር ካሰበው በተቃራኒ ነው፡፡እንደውም ለአብይ ከሁለት በኩል ድል ሲያስመዘግብለት አቶ ለማን ደግሞ ወደ ጃዋር ቀጠና በመውረዱ የቁልቁሊት ጉዞ እንዲያዘግሙ አድርጓል፡፡

አብይ ከሁለት ጎራ የሰበሰቡት የፖለቲካ ትርፍ ከየት እና ከየት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ስለሚችል ግልፅ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡አንዱ ጎራ በተለያዩ ጊዜያት በታዩ ምልክቶች (ለምሳሌ የአዲስ አበባ የኦሮሞ ባለቤትነት ላይ ፓርቲያቸው ባወጣው መግለጫ፣ከአቶ ለማ ጋር ስለ ዲሞግራፊ ለውጥ ሲያወሩ በታዩበት ቪዲዮ፣አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ መከልከላቸውን፣ከባላደራው ጋር በገቡበት እሰጣ ገባ ሳቢያ)የተነሳ ከለማ እና ጃዋር ያልተለዩ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኛ አድርጎ ያያቸው የነበረውን እና የቀደመ ፍቅሩን እየቀነሰ የመጣውን የኢትዮጵያ ብሄርተኛውን ጎራ ልብ በተወሰነ ደረጃ ለመመለስ መቻላቸው ነው፡፡የለማ ማፈንገጥ እና ይህን ተከትሎ ጃዋር በግልፅ ከለማ ጎን መቆሙን የሚያሳዩ ዲስኩሮች ማድረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው አብይ  ከላይ የተጠቀሱትን በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት የሚያስጠረጥሩትን ነገሮች ሲያደርግ የነበረው በለማ መሪነት ከፓርቲው በሚመጣበት ጫና እንደነበረ ለመገንዘብ የቻለበት ነገር በተወሰነ ደረጃ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ይህ ለአብይ ቡድን እጅግ ጉልበት ሰጭ ነገር ሲሆን ለለማ እና ለጃዋር ጎራ የሚጎዳው እንጅ የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡

ሁለተኛው አብይ የፖለቲካ ትርፍ የሰበሰቡበት ጎራ ከሌለው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር በእኩልነት እና በሰላም መኖርን እንጅ የህወሃትን መንገድ የማይደግፈውን ሰከን ያለውን ኦሮሞ ህዝብ ከፍል ነው፡፡ለኦሮሞ ህዝብ ይበልጥ ተቆርቋሪ እንደሆነ የሚያወሳው የአቶ ለማ/ጃዋር ቡድን ኦህዴድ ውስጥ ጉልበት እንደሌለው፣ ማንንም የኦህዴድ አባል የብልፅግና ፓርቲ አባል ከመሆን ማስቀረት አለመቻሉን ያሳጣ ነው ይህ አጋጣሚ፡፡ይህ ደግሞ ቢያንስ በኦህዴድ ውስጥ ቢበዛ ሰከን ባለው የኦሮሞ ፖለቲከኛ ዘንድ የአብይ ፖለቲካዊ ሚዛን ከለማ/ጃዋር ከበድ እንደሚል ያመላክታል፡፡ የአብይ ለዘብተኛ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን የማስኬድ መንገድ  ከጃዋር/ለማ መንገድ በተሻለ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድም ተቀባይነት እንዳለው በአንፃሩ የጃዋር/ለማ ቡድን “የአባ ቢዩማ” እሳቤ እምብዛም ሩቅ የሚያስኬድ እንዳልሆነ ግልፅ ምስክር ነው፡፡የአብይ መንገድ ከኦሮሙማ ጠባብ እሳቤ አለፍ ብሎ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከገባችበት ቅርቃር የመታደግ ሰፊ እሳቤ በመሆኑ በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ዘንድም የሃገር አዳኝነትን የከፍታ ስነ-ልቦና የሚያሰርፅ ትልቅ ምዕራፍ ነው፡፡

ጥያቄ ሶስት

 ሶስተኛው የጃዋር/ለማ ሰልፈኞች ጥያቄ በልዩ ጥቅም ጥያቄ የተጠቀለለው አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር የማስተዳደር ፋታ አልቦ አምሮት ነው፡፡ይህ ህገ-መግስታዊ ካለመሆኑ ባሻገር የአዲስ አበባን ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የሚቀማ የጉልበተኝት ጥያቄ ሃገራችን ለምትሻው የህገ-መንግስታዊነትነት እና ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ዘይቤ ትልቅ ተግዳሮት የሚደቅን ፈተና ነው፡፡ሆኖም ከዲሞክራሲም ሆነ ከህግ የበላይነት ጋር ትውውቅ የሌላቸው ግን ደግሞ ዲሞክራሲንም ሆነ የህግ የበላይነትን በማነሳሳቱ ማስመሰል ወደር የሌላቸው የዘውግ ፖለቲካው ጎራ ቀሳውስት ጥያቄው ተገፍቶበታል፡፡አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ለአዲስ አበባ የራሷን መቀመጫ የሰጠ መሆኑ ለአዲስ አበባ ህዝብ ጥሩ ምልክት ቢሆንም የኦሮሞ ብሄርተኞች በአዲሱ ፓርቲ ላይ ዋገምት የሚተክሉበት አቅጣጫ መሆኑም መረሳት የለበትም፡፡

አቶ ለማ አዲስ አበባን የኦሮሚያ የማድረጉ የማይሆን ጉዞ መንገደኛ መሆናቸውን ያኔ የዲሞግራፊ ለውጥ ለማምጣት እየሰራሁ ነው ያሉበትን ንግግር አስተባበልኩ ብለው በተናገሩት ንግግር ውስጥ “ኦሮሞ አዲስ አበባ አምጥቼ ባሰፍርስ እኔ የኦሮሚያ አስተዳዳሪ አይደለሁም እንዴ?ይህን ማድረግ መብቴ አይደለም እንዴ?” ባሉት ንግግር ውስጥ ፍንጭ ማግኘት ይቻላል፡፡ለማ “የኦሮሞ ህዝብ የሰጠንን ጥያቄ ሳንመልስ ወደ ውህደት መሄድ የለብንም” ሲሉ እንደ ማኛውም አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኛ  በግልፅ የማይናገሯቸው ግን ከላይ የተነሱ ሶስት ጥያቄዎችን ሳንመልስ ከብሄርተኝነታችን ፈቀቅ ማለት የለብንም ማለታቸው ነው፡፡

ይህን ሲሉ የረሱት መሰረታዊ ነገር ግን እነሱ አሉን የሚሏቸው ጥያቄዎች ኦሮሞ ላልሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ማለት ናቸው የሚለውን ነው፡፡ይህን መሰረታዊ ነገር ጨርሰው እንዳልረሱ የሚያሳየው ደግሞ ጥያቄዎቹን በግልፅ ሲያስቀምጡ አለመታየቱ ነው፡፡ይልቅስ እነዚህን ልባቸውን የሞሉ ጥያቄዎች ሌላ ስም ሰጥተው ነው የሚያቀርቧቸው፡፡”ኦሮሞ የበለጠ ስለታገለ የበለጠ ይግዛ” የሚለውን የልባቸውን ጥያቄ “የኦሮሞ ህዝብ ትግል ተካደ” የሚል የኮድ ስም ሰጥተውታል፡፡በኦሮሚያ ክልል ኦሮሞ ማየት ያለመፈለግ መጤ ጠል ጥያቄያቸውን “የኦሮሞ ህዝብ የሃገር ባለቤትነት ጥያቄ” በሚል የአደባባይ ስም ይጠሩታል፡፡አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር የማስገባቱን ኢ-ህገመግስታዊ፣ኢዲሞክራሲያዊ የጉልበተኝት ጥያቄያቸውን “በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም አለን” የሚል የዳቦ ስም ሰጥተውታል፡፡ስሙን ለመጥራት ራሳቸውም የሚሽኮረመሙበት ጥያቄ እንዴት ሆኖ እውን እንደሚሆን ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ 

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።                                       

ግልፅ ወቀሳ ለኦሮሞ መኳንንት (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ህዳር 12 2012 ዓ ም

ይህን ጦማር ፈቃዳችሁ ሆኖ እንድታነቡ ስፅፍ አስቀድማችሁ፣ምናልባትም ርዕሱን ብቻ አይታችሁ “ይህች ነፍጠኛ የኦሮሞ ጥላቻዋ ተነሳባት” የምትሉ አትጠፉም፡፡ይህ ቅድመ-ፍርዳችሁ ጊዜየን ወስጄ የምፅፈውን ፅሁፍ እንዳታነቡ እንዳይከለክል ስል ብቻ  ማንነቴ እናንተ እንደምታስቡት እንዳልሆነ ለመግለፅ እገደዳለሁ፡፡እኔ ከኦሮሞ እናት እና ከአማራ አባት የተወለድኩ ጎጃም ውስጥ ያደግኩ ሰው ነኝ፡፡ ስለዚህ ኦሮሞ እጠላለሁ ማለት እናቴን እጠላለሁ ማለት ነው፡፡ እናንተም ኦሮሞ እንደምጠላ የምታስቡት እናንተ የምትጠሉት “ነፍጠኝነት” ሁለመናየን የሞላ ነጠላ ማንነቴ ስለሚመስላችሁ ነው፡፡የምትጠሉትን ማንነት ይዤ በመገኘቴ ሳቢያ የእናንተው ችኩል ጥላቻ እኔም ኦሮሞ እንደምጠላ እርግጠኛ ያደርጋችኋል፡፡

ከኦሮሞ እናት እንደተወለድኩ እየነገርኳችሁም ኦሮሞ እንደምጠላ በማስባችሁ የምትቀጥሉ ሳትበዙ አትቀሩም፡፡ የዚህም ምክንያት ያለው እናንተው ጋር ነው፡፡በእናንተ ጎራ የፖለቲካ ባህል የእናቱ አማራ መሆን የአማራ ጥላቻውን የማያስተነፍስለት፣አማራ እስከሆነች ድረስ እናቱን ለመጥላትም የማያመነታ አስፈሪ እሳቤ የያዘ ሰው እንዳለ ከአማራ እናት ተወልዳችሁም በሚዲያ ወጥታችሁ ስለዚሁ መከረኛ የአማራ ህዝብ ከምታወሩት ነገር እንደማስተውል፤እንደምታዘባችሁም መካድ አልፈልግም፡፡የሆነ ሆኖ እኔ ኦሮሞ የማልጠላው ኦሮሞ እናት ስለወለደችኝ ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ ማመልከቻ አስገብቼ፣በብቃቴ ተወዳድሬ ከኦሮሞ እናት/ከአማራ አባት አለመወለዴን ስለማውቅ ደክሜ ባላመጣሁት ማንነቴ ላይ ተመርኩዤ መውደድ መጥላቱ ልክ ስለማይመስለኝ ነው፡፡ይልቅስ ታላቅ ዕድል እና ክብር የሚመስለኝ ሰው ሆኜ መፈጠሬ ነው፡፡

ሰውነት ክቡርነት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ ሰው ሁሉ እንደእኔው ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ክቡርነት ይሰማዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡እኔ ሰውነቴ ክቡር ስለሆነ መከበር አለብኝ ብየ እንደማስበው ሌላውም ስለራሱ እንዲሁ ይሰማዋል ስል በጥብቅ አምናለሁ፡፡ስለዚህ በሰው ልጆች ላይ ክብር እንዲጓደል፣እኩልነት ድርድር ውስጥ እንዲቀርብ አልሻም፡፡ሰዎች ሁሉ የሚጋሩት ድንቅ ማንነት ሰውነት ነው ብየ አጥብቄ አምናለሁ፡፡የሰብዓዊ መብት የመብቶች ሁሉ ቁንጮ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ሌላው ማንነት ብዙና ተለዋዋጭ ነውና የፖለቲካ ዕምነት ይሆን ዘንድ አቅም የለውም፡፡ይህን የምለው እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ዓለም እያሳደደ የሚያነባቸው፣እየተደመመ የሚያደምጣቸው ምሁራን ጭምር እንጅ!       

ማንነት አንድ አይደለም፡፡ ይልቅስ እጅግ በርካታ፣በጣም ውስብስብ፣አንዱ ካንዱ የማይበልጥ፣ቋሚነት የሌለው ነገር ነው ይላሉ  እኔ መፅሃፎቻቻን ለማግኘት የቻልኳቸው ታዋቂዎቹ ምሁራን ፍራሲስ ፎኩያማ እና አማር ቲያሲን በመፅሃፎቻው፡፡እናንተም በዘውግ ክር ብቻ የሰፋችሁት ፖለቲካ ሃገሪቱን ወደ ገሃነም ይዞ ሲምዘገዘግ ስታዩ ይህ ሚስጥር ዘግየት ብሎም ቢሆን ምን ያህል እንደገባችሁ እርግጠኛ ባልሆንም  የገባችሁ ይመስላል፡፡መገለጫው ደግሞ በዘር ግንባር ተቀናጅቶ በየግንባሩ እንደ ፍየል ሊዋጋ ትንሽ የቀረውን ግንባራችሁን ቀይራችሁ ውህድ ልታደርጉ እየሞከራችሁ መሆኑ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ የኦሮሞ ፖለቲከኞችም ሚና ስላላችሁ ለመለወጥ መንገድ ለመጀመራችሁ አንድ ምልክት ተደርጎ ለመውሰድ ይቻላል፡፡ ግን ደግሞ ቃል በተግባር ይመዘናል፡፡ወደ ተግባር ሚዛን ሲመጣ እናንተ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በተግባር የምታደርጉት ድርጊት እና ሌሎች ወደ ውህደት እየተንደረደሩ ያሉ የግንባሩ አባል/አጋር ፓርቲዎች የሚያደርጉት ድርጊት የትየለሌ የተራራቀ ነው፡፡አሁን እንደምታደርጉት ድርጊት ከሆነ ውህዱ ፓርቲ እመራበታሁ የሚለውን የሲቪክ ፖለቲካ ለመተግበር ቀርቶ ከፅንሰሃሳቡ ጋር ለመላመድ ራሱ ቀላል የሚሆንላችሁ አይመስልም፡፡  

ከእናንተ ጋር ሲወዳደሩ የግንባራችሁ አባል/አጋር የሆኑ ሹማምንት የሲቪክ ፖለቲካን ለመልድ የሚያሳዩት ዝንባሌ እጅግ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል በፊውዳል ዘመን ቀርቶ አሁን ብሄረሰቦች ከእስርቤተ ተፈቱ በተባለበት የህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን እንኳን የሶማሌን ክልል የሚመራው ፓርቲ በሃገሩ ዋነኛ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ድምፁን ለማሰማት ከእናነተ እኩል ሲሰየም እንዳልኖረ እኔ ለእናንተ አልነግርም፡፡እናንተ ከዘውጋችሁ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሾም እንቅልፍ አጥታችሁ ስታሰሉ፣ የፓርቲያችሁ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ስላልሆነ ይህ እንቅፋት እንዳይሆን ዶ/ር አብይን ሊቀመንበር አድርጋችሁ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ወንበር እንቅልፍ አጥታችሁ ስታማትሩ የሱማሌ ክልል ተወላጅ ግን ቀለል ያለ የፌደራል ሚኒስትር መስሪያቤት ሚኒስትር ለመሆንም እንዳይችል ሆኖ ኖሯል፡፡

ይህ የሆነው እናንተም በተቀበላችሁት፣አካል ሆናችሁ ስትሰሩበት በኖረው አግላይ አሰራር በመሆኑ በዚህ ህወሃት ብቻ አይወቀስም፡፡ከሁሉ የሚገርመኝ “ዲሞክራሲያዊ” የሚለውን ስም ባንጠለጠለው ግንባራችሁ ውስጥ አባል ሆናችሁ፣ በዚህ የሰለጠነ ዘመን የምትኖሩ እናንተ ይህ መሆኑ ሳይጎረብጣችሁ ራስ ደህና ብላችሁ እየኖራችሁ ፊውዳሉ ሚኒሊክ በፊውዳል ዘመን ሰብዓዊ መብት አላከበረም ብላችሁ መውቀስ ከጀመራችሁ ቀን የማይበቃችሁ፣ሰሚ ይሰለቻል ብላችሁ የማታስቡ መሆኑ ነው፡፡ምኒሊክ በኦሮሚያ ያደረገውን ሁሉ በሶማሊ ክልል አድርጓል፡፡ ብሄረሰብ ከእስር ቤት ተፈታ ሲባል ግን የሶማሌ ኢትዮጵያዊያን እኩል ኢትዮጵያዊ የመሆኑ መብት እንደ ታስሮ ቀርቷል፡፡ ከአሳሪዎቹ አንዱ እናንተው ናችሁ! የሶማሌ ኢሊቶች ይህን ስለማያውቁ አይደለም አሁን ሃገር አዲስ የጉዞ ምዕራፍ ትያዝ ሲባል እጃቸውን ሰብስበው፣ ራመድ የማለት ፖለቲካን ለመስራት ግንባር ቀደም ሆነው የተሰለፉት፡፡በዚህ የትየለሌ በልጠዋችኋል! 

እናንተ ቤተ-መንግስት የገባችሁበትን ሩጫ ስትሮጡ እግራቸውን ታስረው የኖሩ፣ይህንንም አሳምረው የሚያውቁ የሶማሌ ልሂቃን ትናንትን ትተው በዛሬ ውስጥ ነገን ለመስራት ደፋ ቀና የማለቱን ስራ ክልላቸውን ሰላማዊ በማድረግ ጀምረዋል፡፡ህዝባቸው ቀስት እና ጦርን ጥሎ፣ያለፈውን ችላ ብሎ ወደፊት እንዲራመድ አስተምረዋል፡፡ከዚህ ያፈነገጠውን(ሄጎ የሚባለውን ገዳይ ቡድን) ዘር ከልጓም ሳይስባቸው አደብ አስገዝተው የሃገር ሰውን ሁሉ አጃኢብ አስብለዋል!ምሬት አብርሯቸው ጦር ያነሱ ብረት አንጋች የሶማሌ ሸማቂዎች ዛሬ መናኝ የሚያስንቁ የሰላም ሰባኪዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ ከተባለ ዋናወን ወረታ የሚወስደው ክልሉን የሚመሩ መሪዎች እሳቤ መዋጀት ነው፡፡

እሳቤያቸው በመዋጀቱ “በክልላችን የጠፋው ጥፋት እኛኑ እንጅ ማንንም አይወክልም” ሲሉ የመታረም መጀመሪያ የሆነውን ፀፀት በህዝባቸው ዘንድ አሰረፁ፡፡በጎሳ ተከፋፍሎ የኖረ ህዝባቸውን አንድ አድርገው  ጭራሽ በሱማሌነታቸው ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸውን እንዲያስቡ መምራት ጀመሩ፡፡ተሳካላቸው! በሚያስተዳድሩት ክልል በማንነቱ የሞተን ሰው ቤተ-ዘመድ ካሱ፣የእምነት ቦታው የተቃጠለበትን ስንት እጥፍ አብልጠው ሰርተው፣በኢትዮጵያ ባንዲራ አሸብርቀው “እነሆ መፅናኛህ!” አሉ፡፡ይህን ሁሉ ሲሰሩ ተግዳሮት ሳይኖርባቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ግን ከልብ አልቅሰዋልና እንባ አልገደዳቸውም፡፡ ራሳቸው ተለውጠዋልና ለህዝባቸው አዋጩን መንገድ መጠቆም አላቃታቸውም!  

እናንተስ?ወገባችሁን ጠበቅ አድርጋችሁ ህዝባችሁን ከፅንፈኛ አክቲቪሰቶች እና ምሁራን ተብየዎች አስተምሮ ከመዋጀት ይልቅ ከፅንፈኞች የባሰ ፅንፈኛ የመሆን ውድድር ውስጥ ተዘፍቃችሀዋል፡፡የቱ እውነተኛ ቀለማችሁ የቱ ማስመሰላችሁ እንደሆነ ለማወቅ ከመላዕክት ጋር ስብሰባ መቀመጥ ይጠይቃል፡፡ራስን ሆኖ መውጣትን የመሰለ የድል በር የለም! ራሳችሁን ሁኑ፡፡ በአንድ ጊዜ እኛ ኢትዮጵያን በምንል ሰዎች ዘንድ አማላይ ለመሆምን፤ኢትዮጵያን የማይፈልጉ ፅንፈኞች በሚሰብኩት የኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የበለጠ ፅንፈኛ ሆኖ ለመቆጠርም  የምታደርጉት መሰባበር መነኩሴም ኮማሪትም ለመሆን የምትፈልግን ሴት ያስመስላችኋል! በስተመጨረሻም ከሁለት ያጣ እንደሚያደርጋችሁ እወቁት፡፡ ይህ ነገር አሁንም ጀምሯችኋል፡፡ 

ስልጣን ስትይዙ ዘሩን ሳይቆጥር ራሳችሁን እንኳን  እሲኪገርማችሁ ድረስ በደስታ የሰከረው ኢትዮጵያን የሚወደው ህዝብ ዛሬ ላይ የእግዜር እንግዳ ብሎ ገብቶ ሰርቆ እንደሄደ እንግዳ እየቆጠራችሁ ነው፡፡ያልሆኑትን በመምሰል መልቲነት እየጠረጠራችሁ ነው፡፡ሁለተኛ ላይምናችሁ እየተማማለባችሁ ነው፡፡መታመን መወደድ የማይከብዳችሁ አድርጎ እየቆጠራችሁ ነው፡፡ይህን ሁሉ ያመጣው ልባችሁ የሚላችሁ እውነተኛ ነገር ምን እንደሆነ ቃል ከተግባር ፈትኖ ለማረጋጋገጥ እጅግ የምታዳግቱ፣ለመደገፍም ለመንቀፍም የማትመቹ በመሆናችሁ ነው፡፡ እባካችሁ የሆናችሁትን ሆናችሁ ኑ! ራስን መሆንን የመሰለ ውበት የለም፡፡ 

አፋችሁ ኢትዮጵያዊነትን እየሰበከ ተግባራችሁ ግን ሌላ ነው፡፡ ኦሮሞ ሳይሆን ኦሮሚያ ክልል የሚኖር ኢትዮጵያዊ አሰቃቂ ሞት፣እንግልት፣ስደት፣የንብረት መቃጠልን በተመለከተ ትንፍሽ አትሉም፡፡ትንፍሽ ካላችሁም የመምሰል እና የመሆን ርቀታችሁ ከገመትነው በላይ በእጅጉ የተራራቀ መሆኑን ብቻ አስመስክራችሁ ከመድረክ ትወርዳላችሁ፡፡ የምትመሩት ክልል የህግ አስከባሪ አካል ግፍን በማስቀረት ፋንታ ዘውጉን አጥንቶ ግፈኛው የዘውጉ ሰው እስከሆነ ድረስ በግፍ ለመተባበር የማያመነታ መሆኑን እያወቃችሁ ባላየ ታልፋላችሁ፡፡በል ሲላችሁም ገዳይ አስገዳይን የዘውጋችሁ ሰው ስለሆነ ብቻ “ወንድማችን፣የአይን ብሌናችን” ትላላችሁ፡፡የስለት እና የድንጋይ ሞት አንሶባችሁ፣ የመንግስት ሃላፊነት ላይ ቁጭ ማለታችሁም እዳ ሳይመስላችሁ በአደባባይ “ለገዳይ መሳሪያ እናከፋፍላል” ስትሉ በኩራት ነው፡፡ይህን ስትሉ አድማጭ ትናንት “ከኢትዮጵያ አልፈን አፍሪካን አንድ የማድረግ ህልም ታይቶን የሃገር አስተዳዳሪነት ተመኘን” ማለታችሁን የማመሳከር ችሎታውን ትዘነጋላችሁ፡፡እንዲህ በመሆን እና በመምሰል መሃከል የሚያላጋችሁ መሆናችሁ ከመምሰላችሁ ስለሚበረታ ነው፡፡መሆናችሁ ክፉኛ የዘለቃችሁ ዘውገኝነታችሁ ነው፤መምሰላችሁ ደግሞ ሌላ! 

መሆናችሁን የተቆጣጠረው ዘውገኝነታችሁ የኦሮሞን ህዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብርቱ ማስጠላት ውስጥ መክተቱ እንደ ዜጋ የሚያሳዝነኝ ነገር ነው፡፡መብለጥን ኢላማ የሚያደርገው እናንተም ከህወሃት የቀዳችሁት የእበልጣለሁ ባይነት፣የማግበስበስ  ክፉ አባዜ የኦሮሞ ህዝብ ማንነትም፣ ፍላጎትም፣ የትግል ግብም፣ አይመስለኝም፡፡ በህወሃት ቤት ያዳበራችሁትን ይህን ክፉ እሳቤ በህወሃት እልፍኝ ዝር ያላለው በደሳሳ ጎጆው ቁጭ ብሎ ግፍ ሲጎጭ የኖረው የኦሮሞ ህዝብ እሳቤ እንዴት ሊሆን ይችላል?እናንተ በህወሃት እልፍኝ የተማራችሁት በጤናማ መንገድ የስራ እድል አግኝቶ ከትንሽ ተነስቶ፣ሰርቶ ጥሮ ግሮ የሚያድግበትን የመልካም አስተዳደር በር ብቻ ከመንግስት ከሚፈልገው አብዛኛ  የትግራይ ወጣት ውስጥ የትግራይ መኳንንት ቤተ-ዘመድ የሆነውን ጥቂቱን ቆንጠር አድርጎ እርሱ አስቦት በማያውቅ ሁኔታ በአንድ ሌሊት ቱጃር ማድረግን ነው፡፡ይህን ዕድል ያላገኘን ቤተ-ዘመድ ከትግራይ ጠርቶ አዲስ አበባ ውስጥ ኮንዶሚኒየም በገፍ ማደል እናንተም “ለኔ ባረገው” ስትሉት የኖራችሁት የህወሃት ፈሊጥ ነው፡፡ይህ ያልሆነለት ደግሞ ያለ ይሉኝታ የነበረው እየተነቀለለት በየመንግስት መስሪያ ቤቱ ይሰገሰጋል፡፡ 

በህወሃት ቀንበር ስር የነበራችሁ፤አሁን ደግሞ የህዋትን የፌደራል ስልጣን የተካው የእኛ ዘውግ ነው ብላችሁ የምታስቡ የኦሮሞ መኳንንት አብዛኞቻችሁ ትምህርት ቤታችሁ ህወሃት ስለሆነ ለህዝብ መስራት ማለት ከላይ የተጠቀሰውን የህወሃት ተግባር መድገም ይመስላችኋል፡፡ህወሃትን እያያችሁም እያደነቃችሁም ስለኖራችሁ ስልጣን የፍርደ-ገምድልነት የይለፍ ይመስላችኋል፡፡ህወሃትን ለመጣል ስትታገሉም የኦህዴድ ባለስልጣናት ሁሉ ተመሳሳይ አላማ ያላችሁ አልመሰለኝም፡፡የህወሃትን  ስልጣን ወለድ እብሪት ጠልተው ይንን ላለመድገም ስልጣን የተመኙ በጣም ጥቂት የኦህዴድ መኳንንት እንዳሉ መካድ ባይቻልም ብዙዎቻችሁ ግን ህወሃትን የታገላችሁት “የባለስልጣንነት እብሪቱ እኛ ላይምን ይመስላል?” ብላችሁ ለመሞከር ይመስላል፡፡ከህወሃት ጋር ያጣላችሁም “ግፍ ለመስራት እኔ ምን ያንሰኛል?” ማለት እንጅ “ለምን ግፍ ይሰራል?” የማለት ልህቀት አይመስለኝም፡፡ በመሆኑም በህወሃት መንገድ እየነጎዳችሁ ነው፡፡ 

ሰው ስንት አመት ቆጥቦ የሰራውን ቤት በድብቅ ለተፈናቃይ የኦሮሞ አርሶ አደር ሰጠን ብላችሁ ለዘውጋችሁ ዲያስፖራ ጭምር የማከፋፈል ማናለብኝነት ላይ የደረሳችሁት ህወሃት እዚህ ጥጋብ ላይ ለመድረስ የፈጀበትን የሃያ አመት እድሜ ሳትጠብቁ ገና በስድስት ወራችሁ ነው! ታዛቢያችሁ ብዙ ነው፡፡ከመሬቱ በግፍ ለተፈናቀለ ኦሮሞ ምንም ቢደረግ ማንም የሚደግፈው ሰናይ ተግባር ነው፡፡በድብቅ መስጠትን ያመጣው በአርሶ አደሩ ስም የምትሰሩትን አድሏዊ አሰራር ለመሸፈን ነው፡፡በግፍ የተፈናቀለ አርሶ አደር አንድ አባወራ ሆኖ ሳለ ነገ ጥረው ግረው ህይወታቸውን መግፋት ላለባቸው ልጆቹ ጭምር ሰው ቆጥቦ የሰራውን ቤት ማደል የግፍ ግፍ ነው፡፡

የተነሽው አርሶ አደር ልጆች እንዲህ ያለ ዛብ የለቀቀ ካሳ ይገባቸዋል ከተባለ እንኳን አዛኝ ቅቤ አንጓች ነኝ ያለ ሁሉ አዲስ ቤት ገንብቶ መስጠት እንጅ ስንት ዘመን ቤት አገኛለሁ ብሎ፣ካልተረፈው ቆጥቦ የሰራን ህዝብ ቤት ማደል ነገ ወድቀህ ተነሳ የሚል ማጣትን  የሚያመጣ የህወሃት አይነት የኪሳራ ጉዞ ነው፡፡ዛሬ ህወሃትን ወድቀህ ተነሳ የሚለው የጠፋው እንዲህ ያለው ግፉ ተጠራቅሞ ከፅዋ በመምፍሰሱ ነው፡፡

እውነት ለመናገር ተነሽ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ራሳቸው እንዲህ ያለ ዛብ የለቀቀ ካሳ እንዲካሱ የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ይህ የማግበስበስ፣አንዱን መቶ በመቶ አሸናፊ ሌላውን በዜሮ የቀረ ከሳሪ የማድረግ ስነ-ልቦና የኢህአዴግ ካድሬ ስነ-ልቦና እንጅ ዋናውን አጥቶ እንኳን ተመስገን የሚለው የኢትዮጵያ ደሃ ህዝብ መለያ አይደለም፡፡የኦሮሞ ህዝብም ከዚህ የተለየ ስነልቦና ያለው አይደለም፡፡ተነሽ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ያጡትን የሚመጥን ካሳ ካገኙ እንደ ኢህአዴግ ካድሬ እኔ ብቻ በልቼ ልሙት የሚሉ አይደሉም፡፡የኦህዴድ መኳንንትም ይህን የምታደርጉት ለአርሶ አደሮቹ አስባችሁ አይመስለኝም፤ይልቅስ በህወሃት ስትቀኑበት  የነበረው ስልጣን ወለድ እብሪት እጃችሁ መግባቱን የኔ ለማትሉት ዘውግ ማስመሰከራችሁ፣ የስነልቦና ቀወሳችሁን ማስተካከላችሁ እንጅ! በዚህ መሃል የኦሮሞን ህዝብ እያስጠላችሁት እንደሆነ እወቁ፡፡በጣም ጥቂት ለሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች በምታደርጉት አድሎ መላውን የኦሮሞ ህዝብ ክፉኛ እያስጠላችሁ እንደሆነ ማየት ያቃታችሁ የስልጣን ሰገነት ስለጋረዳችሁ ነውና እኔ መሬት ያለሁ ወገናችሁ ልንገራችሁ፡፡

ሌላ በስተመጨረሻ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር በምትመሩት የኦሮሚያ ክልል የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቤተ-ክርስቲያን ለማጥቃት የሚደረገውን ፋታ አልቦ ጉዞ መግታት ሲገባችሁ ዝም ብላችሁ የምታዩት ነገር፣አንዳንዴም በተለይ የበታች ሹማምንቶቻችሁ ተባባሪ ሆነው የሚገኙበት አካሄድ፣እናንተ አውራዎቹም የበታች ሹማምንታችሁን አድሏዊ ስራ ለማስቀየስ የምታደርጉት አስተዛዛቢ መጣጣር መጥፎ ነገር ይዞ እንደሚመጣ እንድታውቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገዥዎቹ ሁሉ የሚውሉበትን ግፍ የሚያቃልለው በየዕምነት ቦታው ሄዶ ለፈጣሪው በመንገር ነው፡፡ ከነገስታት የሚመጣበትን ዘመናትን ያስቆጠረ ግፍ ችሎ የኖረው  በየዕምነት ቦታው ሄዶ በሚያገኘው መለኮታዊ መፅናናት ነው፡፡ይህ ብቸኛ የመፅናኛ አለት ከፈረሰበት መጽናናት የለውምና ቁጣው ይነድባችኋል፡፡ የህዝብ ቁጣ ምን እንደሚያደርግ ህወሃትን ጠይቁ! አደብ ግዙ …..በክልላችሁ የተፈጠረውን ከፍተኛ ስርዓት አልበኝነት አንድ በሉ፡፡

የዘውጋችሁ ሃይለኝነት መገለጫ፣አንዳዴም የፖለቲካ ጉልበታችሁ ምንጭ  አድርጋችሁ የምታስቡት የዘውጋችሁ ጎረምሶች የሚያነሱት ትርምስ ኦሮሚያ ክልል በሌላው ኢትዮጵያዊ ዘንድ እንደሞት ሃገር እንድትቆጠር እያደረገ እንደሆነ እወቁ፡፡ለዚህ ትርምስ ባለድርሻውም ሆነ ተጠያቂው ሜንጫ እና አጣና ይዞ የሚወጣው ጎረምሳ ብቻ እንዳልሆነ ራሳችሁ በአደባባይ የምታወሩት ጠብ አጫሪ ንግግር ምስክር ነው፡፡ኦሮሚያ የሞት ቀጠና ተደርጋ ስትወሰድ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብም ከሞት እና ገዳይነት ጋር አብሮ እንደሚነሳ እወቁት!ጠባጫሪነትን በተፋው በዛው አፋችሁ እንደገና “የኦሮሞ አቃፊ ህዝብ ነው” የምትሉት ነገር አሁን አሁን ለኦሮሚያ ክልል እየተሰጠ ያለውን ጥሩ ያልሆነ መልክ አይቀይረውም፡፡ሰው የሚያምነው የሚያየውን እንጅ የእናንትን ፕሮፖጋንዳ አይደለም፡፡ወደዳችሁም ጠላችሁም በሃገራችን ካሉ ክልሎች ውስጥ እናንተ እንደምታስተዳድሩት ክልል እለት ዕለት የሚታመስ፤ለሃገር ቀጣይነትም ስጋት እየሆነ ያለ ክልል የለም!ሌሎች ክልሎች የፀጥታ ችግር ቢገጥማቸው እንኳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ፈትተው ወደ ሰላማዊ የማስተዳደር ስራ ሲገቡ ይታያል፡፡እናንተ ክልል ግን ሁከት ደምብ እየሆነ ነው፡፡እናንተ ራሳችሁ የችግሩ ምንጭ ከሆነው የብሄር(ሃይማኖት)ፅንፈኝነት የተዋጃችሁ ብትሆኑ ኖሮ በክልላችሁ የሚታየው ችግር ከአቅማችሁ በላይ ሆኖ የሚያስቸግር ከቶውንም አይሆንም፡፡በክልላችሁ የሰማኒያ ምናምን ሰው ሬሳ ሲታፈስ ብዙም ያልገረማችሁ ሰዎች ሌላ ቦታ ሁለት የኦሮሞ ተማሪ ሞተ ብላችሁ ለመግለጫ ስትጠራሩ ተስፋ ታስቆርጣላችሁ…..   

ዛሬ ለውህደት እየተንደረደራችሁ ባለበት ወቅት፣እኔን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊ ከውህደታችሁ አንዳች የተሻለ ነገር ጠብ ይላል ብሎ በሚጠብቅበት ወቅት እዛው የምትረግጡት ነገር በእናንተ ተስፋ ማድረጋችንን ያጨነግፈዋል፡፡የእናንት ዘውግ ሞት ከሌላው ሞት በልጦ ከተሰማችሁ ስንኖርም ከሌላው ዘውግ እንበልጣለን እያላችሁ እንደምትኖሩ ክርክር የለውም፡፡ከዛሬው ያልታየ የመለወጥ ዝንባሌ ውህደቱ ሲመጣ ተብቆ እንደመንፈስ እንደማይወርድባችሁ የታወቀ ነው፡፡ስዚህ ለውጣችሁን በተግባር እንየው፤በጥቂት እንኳን ተለወጡ፣ያመናችሁበትን ብቻ ስሩ፣ሰውን ለማስደሰት ብላችሁ የምትሰሩት ስራ የፖለቲካ ህመማችንን አክፍቶ አሟሟታችንን መጥፎ ያደርግ ይሆናል እንጅ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡እውነተኛ ቀለማችሁን እንየው፤ለእውነተኛው እምነታችሁ ብቻ ስሩ! ያኔ ባይሳካላችሁ እንኳን ለለውጥ ስትሰሩ የሆነ እንደሆነ ቢያንስ ታሪክ ይመዘግብላችኋል፡፡ለእምነታችሁ ድፈሩ፣ፖለቲካ ማመቻመች እንዳለውም አውቃለሁ ግን ማስመሰል ከበዛው ደግ አይደለም፡፡አንድ በማስመሰል፤አንድ በመሆን ሁለት ለመያዝ ስትሮጡ አንዷን ሃገራችንን እንዳታሳጡን!  

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።                         

ወደ ህወሃት ሽማግሌ የሚልክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይልካል? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ
ጥቅምት 12, 2012 ዓ. ም.

በተለያየ አጋጣሚ ከሚያጋጥሙኝ አስተያየቶች አንዱ አቶ ጃዋር መሃመድን መነጋገሪያችን ማድረጉን እንተው፤ግለሰቡ የሚሰጠንን አጀንዳ አንስተን በመተንተን ሰውየው የሚፈልገውን ክብር በመስጠት ተፅኖ ፈጣሪነት እንዲሰማው አናድርግ የሚል ነው፡፡በግሌ ስራየ ብሎ ሰውን ማጉላትንም ሆነ ሆን ብሎ ሰውን ማሳነስን ብቻ አላማ አድርጎ መጓዙ የብልህ መንገድ አይመስለኝም፡፡ጠቃሚው ነገር የሰው ስራ የሚያመጣው ተፅዕኖ ላይ ትኩረት አድርጎ መነጋገሩ ይመስለኛል፡፡በዚህ ሁኔታ ግባችን ግለሰቦች ሳይሆኑ የግለሰቦች ሃሳብ እና አካሄድ የሚያመጣው በጎ ወይ መጥፎ ተፅዕኖ ነው፡፡በጎ ወይም መጥፎ ተፀዕኖ ያመጣውን የሰዎችን ስራ በተመለከተ ስንነጋገር የሰዎችን ስም ማንሳታችን ደግሞ አይቀርም፡፡በጎውን ስራ ስናወድስ፤መጥፎው ስራ ወደ ባሰ መጥፎ እንዳያድግ ልንነጋገርበት ስናነሳሳው ከግለሰቦች ጋር የተለየ ፀብ ወይም ፍቅር ስላለን አይደለም፡፡

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ዝም ብሎ ለማለፍ ሞክሬ ያልቻልኩት የአቶ ጃዋር ንግግር ነው፡፡ንግግሩን ሰምቼ ዝም ብሎ ማለፉ ያቃተኝ ደግሞ ግለሰቡ በርካታ ስሜታዊነት የበዛው ተከታይ ያለው ሰው በመሆኑ ንግግሩ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጎ ስላልመሰለኝ ነው፡፡የዚህ ንግግር አንድ በጎ ጎን አቶ ጃዋር መስመሩ ከህወሃት ጋር መሆኑን በግልፅ ማሳወቁ ብቻ ነው፡፡ለዛሬው ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ የግለሰቡ ንግግር የተደረገው  በኦሮምኛ ቋንቋ “OMN” በተባለው ሚዲያ ላይ ነው፡፡ንግግሩ ከኦሮምኛ ወደ አማርኛ ሲተረጎም ይህን ይመስላል፤

“በደቡብም በምስራቅም ሄጃለሁ፡፡ብዙ ሰዎች ፈርተው አይናሩትም እንጅ አቋማቸው ከህወሃት የተለየ አይደለም፡፡ፖለቲካ ያስተማሩኝም የብዙ ፓርቲዎች አመራር፣ምሁራን፣ወጣቶችም ጭምር በተለያየ ዘዴ አዋርቻቸዋለሁኝ፡፡ በይዘት ህወሃት የሚያራምደውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋሉ፡፡ እኛም አሁን ከህወሃት ጋር የሚያጣላን የታክቲክም ሆነ የእስትራቴጅ ልዩነት የለም፡፡ ህወሃቶች ፌደራሊስቶች መሆናቸውን በተደጋጋሚ በተግባርም በአቋምም አሳይተዋል፡፡ድሮ ብዙ ተባብለናል፡፡ያለፈው አልፏል፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ግን በአብይ ዙሪያ ካሉት ሰዎች መካከል አብይን ከልብ የሚደግፉ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው፡፡በስም ሁሉ ልጠራቸው እችልላለሁ፡፡አሁን ኦሮሞ ማድረግ ያለበት ለእስትራቴጅክ  አጋሮቹ አጋርነቱን ማሳየት ነው፡፡ ሽማግሌም ቢሆን ልከን  ዋናውን እስትራቴጅያዊ ወዳጅ አብሮን እንዲሰራ እንሞክር፡፡ አብይ ብቻውን ነው እየሄደ ያለው፡፡እንደተናገርት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው አጠገቡ ያሉት፡፡” (መስመር የእኔ)

ይህን ንግግር በፍጥነት ወደ አማርኛ መልሰው ለህዝብ ይፋ ያደረጉት የተለያዩ የትግራይ ሚዲያዎች ናቸው፡፡ተናጋሪው ወደ  ምስራቅ እና ምዕራብ መጓዙን ሲናገር የተጓዘው ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኦሮሚያ ይሁን ወደ ደቡብ/ምስራቅ ኢትዮጵያ ግልፅ አይደለም፡፡ከተናጋሪው የቆየ በሚዲያ ለሚደረግ ንግግር ጥንቃቄ ያለማድረግ፣ተረጋግቶ እና አስቦ ያለማውራት ባህሪ ተነስቶ ለገመገመ ደግሞ ደቡብ/ምስራቅ የሚለው አባባል ደቡብ/ምስራቅ የሚለውን አቅጣጫ ለመጠቆም ሳይሆን  ወደ ብዙ ቦታ ተዘዋውሬ ሰዎች አነጋግሬያለሁ ለማት ሲሆን ይችላል፡፡

ተናጋሪው ኦሮሚያ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፖለቲከኛ በመሆኑ እያወራ ያለው በኦሮሚያ ስላነጋገራቸው ሰዎች ነው ብለን ብንነሳ እየተባለ ያለው በኦሮሚያ ውስጥ ህወሃት ያራምደው የነበረው የፌደራሊዝም ፖለቲካ በእጅጉ ይወደዳል ነው፡፡ይህ ማለት ኦሮሚያ ክልል በህወሃት ምርጫ ይሰየም የነበረ ርዕሰ መስተዳደር በመናፈቅ እየዋተተች ነው ማለት ነው፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኦሮሚያ ክልል ህወሃት በሚያሰማራቸው ህወሃታዊ ዘራፊዎች መዘረፉ ስለቀረበት አዝናነው ሊሞቱ ነው ማለት ነው፡፡    

ምስራቅ የተባለው በምስራቅ ኢትዮጵያ ነው ከተባለ ደግሞ የሶማሌ ክልል ምሁር፣ፖለቲከኛ ወጣት ህወሃት ያደርገው የነበረውን ፌደራላዊ ፖለቲካ ይደግፋል ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል የሶማሌ ምሁር፣ፖለቲከኛ እና ወጣት አብዲ ኢሌ እና ህወሃት እጅ ለእጅ ተያይዘው ያነበሩትን የፌደራሊዝም ፖለቲካ የሚደግፍ ነው ማለት ነው፡፡ይህ ማለት የሶማሌ ፖለቲከኛ፣ወጣት እና ምሁር የጄል ኦጋዴንን ሲኦል በመናፈቅ መዋተት ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡የሶማሌ ህዝብ በህወሃት ጀነራሎች የኮንትሮባንድ ንግድ ዘረፋ ናፍቆት እየተቸገረ ነው ማለት ነው፡፡የሶማሌ ሴቶች በቀን በብርሃን በመሃል ከተማ መደፈርን የመሰለን “አክብሮት”ያመጣላቸውን ፌደራሊዝም እየናፈቁ ነው ማለት ነው፡፡

ሕወሃት ያነበረው ፌደራላዊ ፖለቲካ ተናጋሪው እንደሚያስበው የደቡብ/ምስራቅ ጉዳይ ስላልሆነ ሰፋ አድርገን ስናየው በጋንቤላ በህወሃት ጀነራል እና ደራሽ ኢንቨስተር መሬትን መዘረፍ፣የሲጋራ መግዣ የማያክል ገንዘብ ከፍሎ ለሚመጣ የውጭ ኢንቨስተር መሬትን አስረክቦ መፈናቀል፣ህወሃት በሾመው አሻንጉሊት አስተዳዳሪ መተዳደር ባጠቃላይ የህወሃት የገንዘብ ሳጥን መሆን ነው፡፡ለጋንቤላዎች ህወሃት ያነበረው የፌደራል ፖለቲካ ለኑዌር ወግኖ አኙዋክን መቸፍጨፈ፤አለያም ኑዌር እና አኙዋክ ወንድማማችነቱን ረስቶ ለደመኝነት እንዲፈላለግ ማድረግ ነው፡፡

የህወሃት የፌራሊዝም ፖለቲካ በአማራ ክልል ሁኔታ እንየው ከተባለ ለምለም መሬትን ለህወሃት አስረክቦ፣የማልቀሻ እና መዝፈኛ ቋንቋን ሳይቀር ህወሃት የሚመርጥበት የባርነት አለም ውስጥ ቋንጃን ተቆርጦ መንፏቀቅ ነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለአማራ ህዝብ በረከት ስምኦን በተባለ ኤርትራዊ ገዥ እግር ስር ተደፍቶ ውርደት መጋት አለያም አለምነው መኮንን በተባለ የአሽከር አሽከር አሻንጉሊት አስተዳዳሪ ያልተገራ አፍ መሰደብ ነው፡፡የህወሃት ፌደራሊዝም በአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ከተማ ህወሃት በቀለሰው እስርቤት በህወሃት ገራፊ በፌሮ መገረፍ ነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ በአማራ ክልል በተቀለሰ እስርቤት አማራ ሱሪውን አወልቆ ራቁቱን እንደቀረ፣አከርካሪው የተሰበሰ ሽባ እንደሆነ እየተነገረው የበላው በአፉ እስኪመጣ በህወሃት መኳንንት ተዘቅዝቆ የሚሰቀልበት ማለትነው፡፡የህወሃት ፌደራላዊ ፖለቲካ ለደቡብ ክልል ፖለቲከኛ በአንድ ህወሃት ቀላጤ ደብዳቤ መሾር፤የህወሃት ባስልጣናትን ዘመድ አዝማድ በአንድ ሌሊት ከበርቴ የሚሆንበትን መንገድ ከፍቶ ዳርቆሞ ማየት ነው፡፡

የህወሃት ፌደራሊዝም ዘጠኙም ክልል ጀግናው ህወሃት በትግርኛ ፅፎ ያሰናዳውን መመሪያ በየቋንቋው ተርጉሞ ህወሃት እንደወደደ ለማስፈፀም ሽር ጉድ ማለት፤ለባርነት መታጠቅ ነው!የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት የሶስት አባል እና የአምስት አጋር ፓርቲዎች  ካድሬዎች የህወሃትን መንበር ተሸክመው “አሜን አሜን” ሲሉ ማለት ነው፡፡የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት መለስ ዜናዊ የእግዜር ታናሽ ተደርጎ ተቆጥሮ የተናገረው ቃል በዘጠኙም ክልል ካድሬዎች እንደወረደ ሲነገር ማለት ነው፡፡ የህወሃት ፌደራሊዝም ማለት ህወሃት የጠላውን ዜጋ በሌሊት ይሁን በቀን፣በእግር ይሁን በፈረስ ከፈለገው ክልል አምጥቶ ማዕከላዊ አስገብቶ ጥፍሩን ሲነቅል፣በፌሮ ጀርባውን ሲተለትል፣ዘር እንዳይተካ ሲያኮላሽ፣ግብረ ሰዶም ሲፈፅም፣ሴት በርብርብ ስትደፈር ማለት ነው፡፡ህወሃት ፌደራሊስትነቱን በተግባር አስመስክሯል ሲባል “ይህ አረመኔያዊ ተግባር ስሙ የፌደራሊዝም ፖለቲካ ይባላል” ብሎ መናገር ነው፤ይህ ደግሞ ለእብደት መዋሰን ነው! ከህወሃት ጋር ስትራቴጃዊ አጋር ነኝ ማለት የዘረፋ፣የአይን አውጣነት፣የሰብዓ መብት ጥሰት አጋር ነኝ ማለት ነው፡፡

በርግጥ የህዋትን አረመኔነት ለመገንዘብ ከኢትዮጵያ ህዝብ አጠገብ ተቀምጦ ህወሃት ባሳረረው ማሳረረር ሳቢያ ከእትንፋሱ የሚወጣውን የምሬት ጭስ ማየት ይጠይቃል፡፡በህወሃት ዘመን ወደ ኢትዮጵያ ዝር ለማለት ቀርቶ ለማሰብ የማይደፍር ራሱን ጠባቂ “ታጋይ” ህወሃት በኢትዮጵያ ህዝብ አካል እና አእምሮ ውስጥ ስላስቀመጠው የማይሽር ጠባሳ ሊያውቅ አይችልም፡፡እንዲህ ያለው “ታጋይ” ትናንት ህወሃትን ሲታገል የነበረው ከአትላንቲክ ማዶ ነፍሱን በጨርቅ ቋጥሮ በተቀመጠ፣መራራ በደል ባልቀመሰ ማንነቱ ስለነበረ ያለፈውን እንደዋዛ ለመተው አይቸገርም፡፡

በመሆኑም አቶ ጃዋር በምድረ-አሜሪካ ሆኖ ህወሃትን ታገልኩ ባለበት ዘመን ስለ ህወሃት ስላለው ነገር ሁሉ እንደ መፀፀት በሚቃጣው መልኩ እንደ አለፈ ውሃ እንዲተለው ይፈልጋል፡፡እኛ የህወሃትን አረመኔያዊ ገፅታ ሁሉ እዚችው ቁጭ ብለን ያየን ኢትዮጵያዊያን ግን ህወሃትን መታገላችን ከበቂ በላይ በሆነ ምክንያት የተነሳ የተደረገ ነበርና የሚያፀፅተን፣እንደ አለፈ ውሃ እንዲረሳልን የምንፈልገው ታሪክ አይደለም፡፡ይልቅስ ባሰብነው ቁጥር የምንኮራበት የታሪካችን ገፅ ነው! ወደፊትም ህወሃታዊነት የሚያንሰራራ በመሰለን ጊዜ ሁሉ ከቀድሞ በበረታ ጥንካሬ ለመታገል እጅ ለእጅ የምንያያዝ ባለምክንያት እምቢ ባዮች  ነን እንጅ “የትናንቱን እርሱልን እና እንታረቅ” የምንል አጥነተ-ቢስ ልፋጭ ስጋዎች አይደለንም፡፡ትላንት ያለ ምክንያት የጮኽ ብቻ “የትናነትቱን እርሱልኝ” ይላል፤ትናንት በበቂ ምክንያት የታገለ ባለ አእምሮ በታገለው ባላጋራው ፊት አይሽረከረክም፡፡

ከሁሉም በላይ የባላጋራችንን የህዋትን ማንነት አሳምረን  እናውቃለን፡፡ህወሃት ስልጣኑን ካስቀማው ባለጋራው  ጋር  አይደለም አንድ አጭር  የትችት አርቲክል ከፃፈበት ሰው ጋር የእውነት እርቅ አይታረቅም፡፡በህወሃት እልፍኝ የእውነት እርቅ የለም! ህወሃት ከነገሩ ሁሉ አጥንት አለው! ጠላቱ እንታረቅ ባለው ሰዓት ሁሉ የሚታረቅ ደጅ ወጥቶ የተቀመጠ ልብ የለውም፡፡የሆነ ሆኖ የህወሃት እግር ስር ተንከባሎ ማሩኝ ማለት፣አመድ ነስንሶ ማቅ ለብሶ፣ድንጋይም ተሸክሞ  ለእርቅ የህወሃትን ደጅ ማንኳኳት ይቻላል፡፡ መታወቅ ያለበት አበይት ጉዳይ ግን ህወሃት ጥፋቱን አምኖ ለመስተካከል ባልሞከረበት፣ጭራሽ ሃገሪቱን ለባሰ ብጥብጥ ለመዳረግ ታጥቆ በሚሰራበት በዚህ ወቅት  “ሽማግሌ ልኬም ቢሆን ከህወሃት ጋር እታረቃለሁ” ማለት ለኢትዮጵያ ህዝብ የጠብ ደብዳቤ መፃፍ ነው!

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የኦሮሞ ብሄርተኞች ትምክህት ምንድን ነው? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ጥቅምት 4, 2012 ዓ. ም.

ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል ሁሉንም ነዋሪቿን በሚያሳስብና በሚያሰጋ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፡፡የዚህ ስጋት ዋነኛ ምንጭ ማን ነው?የሚለው ግን በውል የተመረመረ አይመስልም፡፡ይህን የስጋት ምንጭ መመርመር በሞት እና ህይወት መሃል የምትገኘውን ሃገራችንን ለማዳን ይጠቅማል፡፡ሃገራችን አሁን የምትገኝበት ፖለቲካዊ ስጋት ዋነኛ  ምንጭ መለዘብም መብሰልም ያልቻለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ነው፡፡እንደሚታወቀው ሃገራችን የብሔር ፖለቲከኞች መናኸሪያ ከሆነች ከረምረም ብላለች፡፡ሆኖም በሃገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ብሄርተኞች ከህወሃት መውደቅ በኋላ የቀደመ አክራሪነታቸውን ለዘብ አድርገዋል፡፡የመለዘባቸው ምክንያት ሃገሪቱ አሁን በምትገኝበት ፖለቲካዊ ሁኔታ የአንድ ብሄርን ዳርቻ አልቦ ጥቅም ለማስከበር የሚሽቀዳደሙበት ሳይሆን ሃገሪቱ ራሷ የምትቀጥልበትን መንገድ የሚተለምበት ወሳኝ ወቅት እንደሆነ በማሰብ ነው፡፡

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ‘ሃገር ከመገንጠል ሌላ ዓላማ የለውም’ እየተባለ በአፍራሽነት ስሙ ሲብጠለጠጠል እና ሲፈራ የኖረው ኦብነግ ነው፡፡ሆኖም ኦብነግን የሚመሩ የሶማሌ ልሂቃን ለውጥ መጥቶ ወደ ሃገርቤት ሲገቡ ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ኦብነጎች እነሱ ራሳቸው የሃገር ህልውና ፈተና ሊሆኑ ቀርቶ በህወሃት ዘመን በጎሳ ተከትፎ የነበረውን የሶማሌ ክልል አንድ የማድረጉን አስቸጋሪ ስራ ወደማገዙ ገብተው ለመልካም መስራት ጀመሩ፡፡ከክልላቸው አልፈው ለሃገር ሰላም ስፍነት አጋዥ እስከመሆን፣ብሄርተኝነታቸውን አብስለው ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ለመሆን እስከማቀድ ድረስ ደርሰዋል፡፡ በሃገር አጥፊነት ሲከሳቸው የነበረውን ቡድን አሳፍረዋል፡፡ኦብነግ ይህን ሁሉ ፖለቲካዊ ብስለት ያመጣው እንደ ኦሮሞ ብሄርተኞች የፌደራል ስልጣን ላይ የመቀመጥ መደለያ ሳይጠይቅ ነው፡፡

ኦብነግ በታሪክ ላይ ላላዝን ቢልም የኦሮሞ ብሄርኞች ከሚያላዝኑበት የሚበልጥ ምክንያት ያለው ድርጅት ነው፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች እዬዬ የሚሉበት የፊውዳሉ ዘመን የኢትዮጵያ አመሰራረት ቀርቶ ‘ብሄረሰቦችን ከእስር ቤት ፈትቼ ለቀቅኩ’ በሚለው ህወሃት የስልጣን ዘመን የሶማሌ ህዝብ ትልቅ በደል ደርሶበታል፡፡በህወሃት ዘመን የሶማሌ ህዝብ ወደ ዋነኛ የፌደራል መንግስት የስልጣን እርከኖች እንዳይወጣ በአጋር ድርጅትነት ስም ተሸብቦ ሁለተኛ ዜጋ ተደርጎ ኖሯል፡፡በክልሉ ሲፈፀም የኖረው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ራስ የሚያስይዝ እንደ ነበረ ዓለም ያወቀው ገመናችን ነው፡፡የሶማሌ ፖለቲከኞች ይህን እያነሱ ወደኋላ እያዩ ማልቀስ ሲችሉ ይህን አልመረጡም፤ሃገር ለዲሞክራሲያዊ መዳረሻ ለምታደርገው ጉዞ እንቅፋት መሆንን አልፈለጉም፤የሃገርን ህልውና በሚፈታተን መንገድ አልነጎዱም፡፡ይልቅስ የሃገራቸውን ህልውና የማፅናቱን ስራ ካገዙ በኋላ በመሃል ሃገር ፖለቲካ ተዋናይ መሆንን ያለመ የባለ አእምሮ እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

እንዲህ ያለውን የሱማሌ ብሄርተኝነትን ፖለቲካ የማብሰሉን ስራ የሚመሩት አቶ ሙስጠፌ ሌላው ቀርቶ በቤተሰብ ደረጃ ግፍ የተሰራባቸው ሰው ናቸው፡፡እንደ ክልል ላስብ ካሉም በጎጣቸው ሰዎች ላይ የሚሰቀጥጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈፀም ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ሆኖም እንደ ልጅ ወደኋላ እያዩ ከማልቀስ ይልቅ ወደፊት መራመዱ የተሻለ መሆኑን ተረድተው በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ቀጣይነት ከሚጠቀሱ ጠንካራ ዋልታዎች አንዱ ሆነው የሚቆጠሩ ሰው ሆነዋል፤የክልላቸው ህዝብም እንደዛው፡፡ዛሬ በሱማሌ ክልል አጣና ይዞ፣ጎራዴ ስሎ፣ድንጋይ ተሸክሞ ጎዳና የሚወጣ ጎረምሳ የለም፡፡ከዚህ የምንረዳው የጎራዴ እና አጣና ትርዒት በዘረኛ ፖለቲከኞች ልቦና ውስጥ ካልተጠነሰሰ የማንኛውም ጎጥ ጎረምሳ መግደያ ይዞ አደባባይ እንደማይወጣ ነው፡፡ስለዚህ የመጋደሉ ትርዒት ንድፈ ሃሳብ የሚያልቀው በጎጥ ፖለቲከኞች አእምሮ ጓዳ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ጉልበታቸውን የጎጣቸውን ጎረምሳ ይዞ በሚወጣው የመግደያ ቁሳቁስ ላይ በማስደገፉ የቀጠሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ብቻ ናቸው፡፡ይህ ደግሞ የኦሮሞ ብሄርተኞችን ዋነኛ የሃገር ህልውና ስጋት አድርጓቸዋል፡፡    

የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች የሃገር ህልውና/ሰላም ስጋት ምንጭ ሆነው እንዲቀጥሉ ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡እነዚህን ምክንያቶች መርምሮ አካሄዳቸውን ማወቅ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን የሚፈልገውን አብዛኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሃገሩን ለማዳን በየት በኩል መሰለፍ እና  እንዴት መስራት እንዳለበት የሚጠቁም ይሆናል፡፡

ምክንያት አንድ፡የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና

እንደሚታወቀው በሃገራችን ከሁለት አመት በፊት የመጣውን ለውጥ ለማምጣት ትግል የተጀመረው ህወሃት ከጫካ ከተመልሶ ሃገራችንን የሚጎዱ የውጭ እና የውስጥ ወንጀሎች መስራት ከጀመረበት ዘመን አንስቶ ነው፡፡ይህ በተግባር ሲገለፅ ደግሞ ህወሃት ሃገራችንን አንድ አይሉ ሁለት ወደቧን አስረክቦ ወደብ አልቦ ክርችም ቤት ካደረጋት እና በውስጥ አስተዳደሩም ዘረፋውን እና ማባላቱን አጠናክሮ ከቀጠለበት ዘመን አንስቶ በትቂትም በብዙም የተደረጉ ትግሎችን ያካትታል፡፡ከዚህ ዘመን ጀምሮ የሚደረገው ማንኛውም ትግል ህወሃትን ከስልጣን የማውረዱን ትግል ውሃ ያሞቀ ነው፡፡በዚህ ረዥም የትግል ዘመን ውስጥ ህወሃትን ለመጣል ፈርጀ ብዙ የማዳከም ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ህወሃትን በማዳከሙ ትግል ውስጥ የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተደረጉትን ትግሎች የሚስተካለል የለም፡፡ ይህ ትግል የህወሃት ገበና በአለም ፊት ግልፅ ብሎ እንዲወጣ ያስቻለ፣በሃገር ውስጥም በህወሃት መራሹ አስተዳደር ስር ዲሞክራሲ እንደማይታሰብ ያስመሰከረ ትግል ነው፡፡ይህ እውነት ይገለፅ ዘንድ እስርቤት የገቡ፣ህይወታቸውን ያጡ፣የተሰደዱ፣የተገረፉ ሁሉ ህወሃነትን የመጣሉ ትግል እንዲበስል እንጨት ሆነው የነደዱ አርበኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች “ከአንድ ጀግና ዘር” የመነጩ የአንድ ጎጥ ሰዎች ሳይሆኑ ከመላ ሃገሪቱ የተውጣጡ ዜጎች ናቸው፡፡

የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ በሃገርቤት ከአምባገነን መንግስት ጋር የተደረገውን ትንቅንቅ ለማገዝ በውጭ ሃገር ብድር እና እርዳታ የማስከልከል ዲፕሎማሲያዊ ፍልሚያም ተደርጓል፡፡ይህ ነገር አቶ መለስ እስከ ዕለተ ሞታቸው ሲያስቡት ቱግ የሚያደርጋቸው “በሃገራች ሰዎች የተሰራብን የኢኮኖሚ አሻጥር” ሲሉ ንዴታቸውን መቆጣጠር እስኪያቅታቸው በግነው የሚገልፁት አመርቂ ትግል ነበር፡፡ በዛ አስፈሪ ወቅት በሃገር ቤት ውስጥ መንግስትን የሚተቹ ጋዜጣ እና መፅሄቶች መስርተው በነፍሳቸው ቆርጠው ህዝብን ሲያነቁ የነበሩ ዜጎች ሁሉ ህወሃትን የጣለው ትግል እንዲፈላ እሳት ያነደዱ ታጋዮች ናቸው፡፡

ይሄ ሁሉ እሳት ነዶበት የፈላው ህወሃትን የመጣሉ ትግል ላይ የመጨረሻውን ማገዶ የጨመረው የዛሬ ሁለት አመት በኦሮሚያ ክልል፣በአማራ እና በደቡብ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ የታየው ትግል ነው፡፡እነዚህ ትግሎች የፈላ ውሃ እንዲገነፍል የሚረዳውን የመጨረሻ ማገዶ አስገቡ እንጅ በረዶ የነበረውን ትግል አቅልጦ ውሃ አድርጎ፣ውሃውን አፍልቶ ያገነፈለ ትግል ያደረጉ አይደሉም፡፡ይህ የመጨረሻውን ማገዶ የማስገባት ስራም ቢሆን የተሰራው ኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች በየደረሱበት እንደሚናገሩት በኦሮሞ ወጣቶች ብቻ አይደለም፡፡የአንድ ወገን የአንድ ሰሞን ትግል ለብቻው ህወሃትን የመሰለ ስር የሰደደ መንግስት ሊገለብጥ ከቶውን አይቻለውም፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዛሬ እንደሚያወሩት ህወሃትን ከውጭ የተገዳደረው የኦሮሞ ወጣት ፣ከውስጥ ደግሞ ኦህዴድ ብቻ ቢሆን ኖሮ ሁለቱንም ድባቅ መትቶ መልሶ በመንበሩ ለመቀመጥ የሚከለክለው አንዳች ነገር አይኖርም ነበር፡፡ 

ህወሃትን ግራ ያጋባት በአጠቃላይ በሃገሪቱ የረበበውን ህወሃት በቃኝ የማለት አስፈሪ ሁኔታ ነው፡፡ይህ እንቅስቃሴ ስጋ ለብሶ መታየት የጀመረው የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን የመተግበር እንቅስቃሴን ተከትሎ በመጣው የኦሮሚያ ወጣቶች የተቃውሞ ትግል ቢሆንም ህወሃት በሃገሪቱ ምድር ውስጥ የቀድሞ አድራጊ ፈጣሪነቷ አብሯት እንደሌለ ያወቀችው ግን ጎንደር ተሻግራ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን እጁን ይዛ አምጥታ ማዕከላዊ መደብደብ እንደማትችል ከእውነቱ ጋር የተፋጠጠች ዕለት ነው፡፡

ይህ የህወሃት ስንፈተ-ጉልበት እውን የሆነው በብአዴንም ትብብር በመሆኑ ህወሃት በኢህአዴግ ላይ የነበራት የኖረ ጌትነት እንዳበቃ የመጀመሪያውን ፊሽካ የሰማችውም ከወደ ብአዴን ነበር፡፡ስለዚህ በትግሉ ወቅት አጓጉል ጀግንነቱ ሲወራለት የነበረው ኦህዴድ እምቢ ማለትን የለመደው ከብአዴን ነበር ማለት ነው፡፡ብአዴን ህወሃትን እምቢ ብሎ ምንም አለመሆኑን ያየው ኦህዴድም ተደፋፍሮ የውስጥ ትግል ጀመረ፡፡የኦህዴድ የውስጥ ትግል ጀማሪዎች የብአዴንን አጋርነት ብቻ ሳይሆን መከታነት ባያገኙ ኖሮ በህወሃት ጎራዴ ከመከተፍ እንደማይድኑ ዛሬ አደባባይ ወጥተው ሌላ የሚያወሩት የኦህዴድ ካድሬዎች ሳይቀሩ የማይክዱት ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ከተለያየ ወገን በተሰባሰበ ጉልበት የበሰለው ትግል ነው እንግዲህ ህወሃትን ጥሎ ዛሬ ላለንበት ቀን ያበቃን፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የኦሮሞ ብሄርተኞች ግን ህወሃትን ታግሎ የጣለው የእነሱ ዘር ወጣት  ብቻውን ትግሉን ጀምሮ እና ጨርሶ ያመጣው ጀግንነት አስመስለው ሲያወሩ የዕሩብ ምዕተ-ዓመቱን ህወሃትን የመጣሉን ትግል ወደ ስምንት ወር ትግል አሳንሰው ያቀርቡታል፡፡ የስምንቱ ወር ትግልም ቢሆን በኦሮሞ ወጣቶች ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ትግሉም እነሱ እንደሚያስቡት ከወደ ኦሮሞ ወጣቶች ብቻ በተወርውሮ ህወሃት የመሰለ ስር ሰደድ ክፉ ስርዓት ለመጣል የቻለ አይደለም፡፡

እውነተኛው ነገር ህወሃትን የመጣሉ ትግል ስኬቱን ያገኘው ከውስጠ-ፓርቲም ከፓርቲ ውጭ በህዝብ ትግልም ስለታገዘ ነው፡፡በሁለቱም የትግል መስመሮች የኦሮሞ ተወላጅ ብቻውን ታግሎ ያመጣው ድል የለም፡፡ለትግሉ ስኬት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሲያደርግ ሩብ ምዕተ አመት አሳልፏል፣በስተመጨረሻ የህወሃት የበላይነት ፍፃሜውን እንዲያገኝ ያደረገው ትግልም ቢሆን በኦሮሞዎች ብቻ የተደረገ አይደለም በሚለው ላይ ስምምነት ከተደረሰ ቀጣዩ ንግግር ማን የበለጠ ታግሏል የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚያዘወትሩት ነገር ይሆናል፡፡

ህወሃትን በመጣሉ ትግል ላይ አዘውትረው እና አበክረው ጎዳና ላይ በመውጣት ሲታገሉ የነበሩት የኦሮሞ ወጣቶች መሆናቸው የታመነ ቢሆንም ትግሉን ለፍሬ በማብቃቱ ረገድ የአማራ ወጣቶች በባህርዳር እና በጎንደር ጎዳናዎች ደማቸውን ማፍሰሳቸው መረሳት የለበትም፡፡ከህወሃት ስልጡን ወታደር ጋር ሊጋጠም ከአማራ ገጠራማ ቦታዎች  ጠመንጃውን አንግቶ ከመጣው የአማራ ገበሬ የህወሃትን ጉልበት በማራድ በኩል የነበረው ሚና ከኦሮሞ ወጣቶች ያነሰ ይሁን የበለጠ ወንበሯላይ የተቀመጠው ኦሮሞ ሆኖ ሳለ አማራን አምርራ የምትረግመው ህወሃት ታውቃለች፡፡በውስጠ-ፓርቲው ትግልም ቢሆን ከኦዴፓ እና ከአዴፓ የህወሃትን ግበዓተ መሬት ማን እንዳፋጠነው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ከሁለቱ ፓርቲዎች ማንን አምርራ እንደምትጠላ በማጤን የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ማንን አምርራ እንደምትጠላ ለማወቅ ደግሞ ሌላው ቀርቶ የአማራ ክልሉን ግድያ አስከትላ በማያገባት ገብታ ህወሃት ለአዴፓ የፃፈችውን ደብዳቤ ማንበብ በቂ ነው፡፡ 

ሲጠቃለል ዛሬ የመጣውን ለውጥ ለማምጣት የታገለው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ሲሆን የትግሉ ዘመንም የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንደሚያስቡት ስምንት ወር ብቻ አይደለም፡፡ የስምንት ወሩ ትግል የፈላውን ትግል  የሚያገነፍል  አስተዋፅኦ አደረገ እንጅ ትግል አሙቆ፣አፍልቶ፣አገንፍሎ ህወሃትን የሚያስወግድ ማዕበል አላመጣም፡፡ይህ በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ይህ የስምንት ወሩ ትግልም ቢሆን በኦሮሞ ወጣቶች እና ፖለቲከኞች ብቻ የተደረገ አይደለም፡፡ዛሬ ያለ እነሱ ጀግና ያለ የማይመስላቸው፣አድራጊ ፈጣሪ የሆኑት የአትላንቲክ ማዶ የወንጭፍ ታጋይ የኦሮሞ ብሄርተኞች የኪቦርድ ጀግንነት ማዕከላዊ ገብቶ ከወጣ ዛሬ ስሙ ከማይነሳ አንድ ታጋይ ጀግንነት ይብለጥ ይነስ ማወዳደር የሚወዱት እነሱው እንዲበይኑት ልተወው፡፡ 

 ስለዚህ ህወሃትን በመጣሉ ትግል ውስጥ የኦሮሞ ብሄረተኞች እና ወጣቶች ሚና እነሱ የሚያገዝፉትን ያህል እንደ ዝሆን የገዘፈ የሌላው ደግሞ እንደ አይጥ ያነሰ አይደለም፡፡በውስጠ ፓርቲው ትግል ውስጥ እንደውም የብአዴን ትግል እንደሚልቅ ግልፅ ነው፡፡አልተወራም ማለት የለም ማለት አይደለም፡፡ ለኦህዴዶች ህወሃትን እምቢ ማለትን ያስተማራቸው ብአዴን ነው፡፡ለዚህ ማመሳከሪያው ደግሞ የጎንደሩ የኮሎኔል ደመቀ ክስተት ነው፡፡ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የኦሮሞ ብሄርተኞች ለራሳቸው እና ለጎሳቸው ወጣቶች ትግል የሚሰጡት የተጋነነ ጀግንነት እና የበለጠ የድል ባለቤትነት በራሱ ስህተት ከመሆኑ ባሻገር ብዙ ስህተቶችን እየወለደ ሃገራችንን ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየመራት ይገኛል፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች ስለጀግንነታቸው ደጋግመው የሚያወሩት ጎበዝ ተብለው እንዲጨበጨብላቸው፤ወይ የገዳይነት ሎቲ ጆሯቸው ላይ አንጠልጥለው የመሄድ ፈቃድ ብቻ እየጠየቁ አይደለም፡፡እንደዛ ቢሆን ኖሮ ለማንም አይከብድም ነበር፡፡

ነጋጠባ ጀግንነታቸውን የሚዘምሩብን፣በሃገሪቱ የተደረገው መልካም ነገር ምክንያቶች እነሱ እና የዘራቸው ወጣቶች እንደሆኑ የሚነግሩን ለበላይነታቸው እያመቻቹን ነው፡፡ ለጀግና እንደሚገባ ፈሪዎችን ቀጥቅጦ የመግዛት፣በልጦ የመኖር፣ተፈርቶ የመግዛት የይለፍ እንዳላቸው እየነገሩን ነው፡፡እሳቤያቸው በስሙ ሲጠራ ‘እኔ ጀግና ስለሆንኩ ከሌላው ጋር እኩል እኖር ዘንድ አይገባም፤ የበላይ እሆን ዘንድ ጀግነንነቴ ያዛል’ አይነት መልዕክት ነው፡፡ይህ ደግሞ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ከደረሰበት የፖለቲካ ንቃት ደረጃ በእጅጉ ወደኋላ የቀረ፣ሃገራችንን አብረን የምንኖርባት የሰላም ሃገር ሳይሆን የምንተላለቅባት የደም መሬት የሚያደርግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡

ምክንያት ሁለት፡ የብዙ ቁጥር ነኝ ዕብሪት

የኦሮሞ ብሄርተኞች ሌላው መመኪያ የኦሮሞ ቁጥር በሃገሪቱ ካሉ ብሄረሰቦች ላቅ ማለቱ የበለጠ ጉልበተኛ ያደርገናል ብለው ማመናቸው ነው፡፡የዘር ፖለቲካ ባረበባት እና ህወሃትን በመሰለ ለምንም ማይታመን አስተዳዳሪ ስር በቆየችው ሃገራችን ውስጥ በህዝብ ቆጠራ ተደረሰበት የሚባለው የብሄረሰቦች ቁጥር ራሱ አጠያያቂ ነው፡፡ የሆነው  ሆኖ የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ከሌሎቹ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ላቅ ማለቱ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ላቅ ማለቱ የሚያስማማ ሆኖ የማያስማማው ግን ከተከታዩ የአማራ ህዝብም ሆነ ከሌሎች ብሄረሰቦች በምን ያህል ቁጥር ይልቃል የሚለው ነው፡፡በህወሃት ዘንድ ማነሱ እንጅ መጉላቱ የማይፈለገው የአማራ ህዝብ ሌላው በሚጨምርበት ሁኔታ ለብቻው ተለይቶ በሚሊዮኖች በሚቆጠር ቁጥር እንደቀነሰ የተነገረውን ቁጥር ተቀብለን ብንሄድ እንኳን በኦሮሞ እና በአማራ ህዝብ መሃል ያለው የቁጥር መበላጥ የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚያወሩት አንዱን ጌታ ሌላውን ባሪያ ለማድረግ በሚደርስ ርቀት ላይ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ የህዝብ ብዛት አለመሆኑ ላይ መግባባት ቢቻል ደግሞ ይህ ሁሉ ባልመጣ ነበር፡፡

የህዝብ ብዛት ዋነኛ ነገር አለመሆኑን ለመረዳት በአፍሪካ በህዝብ ብዛቷ አንደኛ የሆነችው ናይጀሪያ እና በህዝብ ቁጥሯ አናሳ የሆነችው ሞሪሽየስ ያሉበትን የዲሞክራሲ እና የሰላም ሰማይ እና ምድር ማጤን ነው፡፡ከሃገር ቤት ልምዳችን እናውሳ ካልንም ዋናው ነገር የህዝብ ብዛት ቢሆን ኖሮ ባለ ብዙ ቁጥሩ ኦነግ ያላሳካውን የትጥቅ ትግል ድል ንዑሱ ህወሃት በአስራ ሰባት አመት ትግል ማሳካቱ ነው፡፡የኦሮሞ ናሽናሊስቶች ከዚህ ከቁጥራቸው መላቅ ጋር የሚያነሱት ክርክር ብዙ ችግሮችን ያዘለ ነው፡፡የመጀመሪያው ችግር በቁጥር ስለምንልቅ ኢትዮጵያን ዘለዓም መግዛት ያለብን እኛ ነን ሲሉ የኦሮሞ ስርወ-መንግስት መመስረት እንደሚገባ በአደባባይ የሚያወሩት እስከ ሶስተኛ ዲግሪ የዘለቁ የኦሮሞ ምሁራን ናቸው፡፡እነዚሁ ምሁራንም ሆኑ አውቃለሁ ባይ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ይህን ክርክር ይዘው ወደ ዲሞክራሲ መንደር ያቀናሉ፡፡በዚህ አካሄዳቸው የዲሞክራሲ መርሆ የሆነውን የሃሳብ ብዝሃነትን ከብሄር ብዝሃነት ጋር አዋቅተው ጥያቄያቸውን ከህገመንግስቱ፣ከፌደራሊዝሙ እና ከብሄር ፖለቲካው ጋር ፈትለው ያቀርቡታል፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች አሁን ያለው ህገ-መንግስትም ሆነ የብሄር ፌደራሊዝም አይነካብን ሲሉ ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡በህወሃት ዘመን የነበረው ችግርም ህገ-መንግስቱን ስራ ላይ ያለማዋል እና ፌደራሊዝምን ዲሞክራሲያዊ ያለማድረግ ችግር እንጅ ሌላ ስላልሆነ ህገ-መንግስቱ በስራ ላይ ይዋል፤ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን፤ይህ ከሆነ ሰላም ነው ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ይህ ክርክር የራሳቸውን ምቾት ብቻ የሚያስጠብቅ አብሮ ለመኖር ቅንጣት ያህል ግድ የሌለው ነው፡፡ህገ-መንግስቱ በስራ ላይ ይዋል፣ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን ሲሉ ህገ-መግስቱ በስራ ላይ ከዋለ በፓርላማ ብዙ ወንበር መያዝ የሚችለው ኦሮሞ ሁልጊዜ ከስልጣን አይጥፋ ማለታቸው  ነው፡፡ፌደራሊዝሙ ዲሞክራሲያዊ ይሁን እንጂ አይነካ ሲሉም እንደዛው ኦሮሚያን አለቅጥ አስፍቶ የመተረው አከላለል ለእነርሱ የሚመች ሆኖ ስላገኙት ነው፡፡ፌደራሊዝሙ ዲሞክራሲያዊ ይሁን የሚሉት ደግሞ የሃሳብ ብዝሃነት ያሸንፋል የሚለውን የዲሞክራሲ መርሆ ባለማወቅ ሳይሆን ሆን ብለው የብሄር ብዝሃነት ያሸንፋል በሚለው ትርጉም ተክተው የኦሮሞ ገዥነትን እና የበላይነት ዘላለማዊ ለማድረግ የሄዱበት የትም የማያደርስ መንገድ ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኞች ህገ-መንግሰቱ በስራ ላይ ይዋል እንጅ አይከለስ፣ፌደራሊዝሙም ዲሞክራሲያዊ ይሁን እንጅ አይነካካ የሚሉት በሁለቱም በኩል እነሱ በሚጠቀሙበት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ስለሚያውቁ ነው፡፡ከህወሃት ጋር ለቆ የማይለቅ ፍቅር የያዛቸውም ለወደፊቱ ስንገዛ የምንኖርበትን ሰፊ ግዛት የሸለመን፣ሽልማቱንም በህገ-መንግስት ያፀናልን እርሱ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ስለሆንም የማታ ማታ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከህወሃት ጋር ገጥመው ሃገር ለማጥፋት የማይመለሱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ህወሃት በበኩሉ እርሱ ከስልጣን ከወረደ ሃገር ከምትኖር ባትኖር የሚመርጥ፣ስልጣን የማጣት እልህ ምላጭ ሊያስውጠው የደረሰ ስብስብ ነው፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞችም የኢትዮጵያ መኖር አለመኖር እንቅልፍ አሳጥቶ የሚያሳስባቸው ነገር አይደለም፡፡እነሱን የሚወዘውዛቸው ኦሮሚያ አሁን በተንሰራፋችበት ስፋት እና ግዝፈቷ ላይ ከአማራ ክልል ቆረስ አድርጋ ወሎን፣ከወደ ምስራቅ ሃረርን፣በላዩ ላይ አዲስ አበባን፣ከዘም ራያን ጨምረው ከልለው ግዙፏን ኦሮሚያን መመስረት መቻል አለመቻላቸው ላይ ነው፡፡                

ምክንያት ሶስት፡ የኦሮሚያ መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ

ካላይ እንደተጠቀሰው የኦሮሞ ብሄርተኞች አሁን ያለው ህገ-መንግስት እንዳይነካ የሚያስጠነቅቁት ህገ-መንግስቱ የሰፊ ክልል ባለቤት ስላደረጋቸው ነው፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞችን የሚያረካቸው የክልላቸው ስፋት ብቻ ሳይሆን ክልሉ የተቀመጠበትን ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ ስትራቴጅካዊ አድርገው ሲለሚቆጥሩት ነው፡፡በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ የኦሮሚያ ክልል ከሌላው ክልል የበለጠ ስትራቴጅካዊ ቦታ ላይ እንዳለ የሚያስቡበት አንዱ ምክንያት የሃገሪቱን መዲና አዲስ አበባን ከቦ በመዘርጋቱ እኛ ከተቆጣን ከተማዋን በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በአራት መዕዘን ዘግተን እንዳትተናፈስ ማድረግ እንችላለን የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ተመሳሳይ ምክንያታቸው ደግሞ ኦሮሚያ በሃገሪቱ መሃል ላይ ያለች በመሆኗ እኛ ከፈለግን የሃገሪቱ ሌሎች ክልሎች እንዳይገናኙ አድርገን መንገዶችን መዝጋት እንችላለን የሚል ነው፡፡

እነዚህ ክርክሮች እውነት መሆናቸው አያነጋግርም፡፡ የሚያነጋግረው ይህን ማድረግ የሚፈይደው ነገር ካለ የሚፈይደው የሌላው ኢትዮጵያዊ ትዕግስት እስካላለቀ ድረስ፣ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሃገርም እንደ ሃገር እስካለችና የኦሮሞ ፖለቲከኞች አበክረው የሚያነሱት ህገ-መንግስትም በስራ ላይ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ከፈረሰች በሃገሪቱ የሚነሳው ብጥብጥ ይህ ህገ-መንግስት የከለላትን ኦሮሚያን ሳይነካ በጎን በጎኗ እያለፈ የሚሄድ አይሆንምና ኦሮሚያ ቀርታ የግለሰብ መኖሪያ ቤትም የግል መሆኑ ያበቃል፡፡ በዚህ ሰዓት አዲስ አበባን እከባለሁ የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች ራሳቸውን የሚያኙት በሌላው የኢትዮጵያ ክልል ተከበው ነው፡፡ በሰላሙ ጊዜ መሃል በመሆናቸው የኮሩበት አቀማመጥ ክፉ ቀን ሲመጣ መውጫው በጨነቀ እሳት መከበብ ማለት እንደሆነ አላሰቡትም፡፡አሁን ኦሮሚያ የሚባለውክልል መለኮት የከለለው ስላልሆነ ክፉቀን የመጣ ዕለት ያለው እንዳለ እንደማይቀጥል ማወቅ ከባድ ነገር ባይሆንም እየታሰበ ያለው ግን እንደዛ ነው፡፡  

የኦሮሚያ መሃልነት የሚያኮራው ኢትዮጵያ በሰላም ውላ እስካደረች ድረስ ነው፡፡አዲስ አበባን መክበብ ማስፈራሪ የሚሆነው ኦሮሞ ተቆጭ ሌላው ታጋሽ መሆኑ እስኪያከትም ብቻ ነው፡፡ሌላውም የሰውልጅ ነውና ትዕግስቱ ያለቀ ዕለት አዲስ አበባን በመክበቡ የሚመፃደቀው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ራሱን በመላው የተቆጣ ኢትዮጵያዊ መሃል ያገኘዋል፡፡ ያኔ ህገ-መንግስቱ ይከበር ማለት የሚቻል ከሆነ ደርሰን እናየዋለን! ህገ-መንግስት በዋስትና የማይጠራበት፣ብዙ ቁጥርነት የማያመፃድቅበት ወቅት የመጣ ዕለት ማን የበለጠ እንደሚጎዳ ደርሰን እንየው ማለት አልፈልግም፡፡ስላልተፈለገ እንደማይቀርም ግልፅ ነው፡፡ሳይነገር መቅረት የሌለበት ነገር ግን አሁን የኦሮሞ ብሄርተኞች በያዙት አያያዝ ከቀጠሉ የጥፋቱ ዘመን ሩቅ እንደማይሆን ነው፡፡ ያየጥፋት ዘመን የመጣ ጊዜ ብዙ ቁጥር ያለው ዘር በገዳይ፣ትቂት ቁጥር ያለው ዘር በሟች መስመር እንደማይሰለፍ፤ሁሉም ለጥፋት እንደማያንስ በተግባር የምናይበት ይሆናል፡፡ያኔ ሁሉም እየገደለ የሚሞትበት እንጅ ብዝሃነት ያለውን ኦሮሞን ፈርቶ የሚንቀጠቀጥበት ወቅት እንደማይሆን እድሜም ሆነ ትምህርት ላላስተማረው ሁሉ ተግባር ያስተምረዋል፡፡

ምክንያት አራት፡የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጉልበት መመናመን

የኢትዮጵያ ብሄርተኝት ሰልፍ የተመናመነው ህወሃት ስልጣን ይዞ የዘውግ ፖለቲካን ህገ-መንግስታዊ እና መዋቅራዊ ካደረገ ወዲህ ነው፡፡ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት ፈርጆ የፖለቲካ ጥርሱን የነቀለው ህወሃት ኢትዮጵያ እንድትኖር የሚፈልግው እርሱ መንበረ ስልጣኗ ላይ ሆኖ መዝረፍ እስከቻለ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ለመዝረፍ እንዲመቸው ደግሞ ህዝቦቿን በዘር ከፋፍሎ ማባላት ነበረበት፡፡ ያሰበውን በደምብ ለማሳካት ደግሞ ለኢትዮጵያ የማሰቡን በጎ እድል ተሳስቶ በደግ አንስቶት ለማያውቀው የአማራ ህዝብ አሸከመው፡፡ ስዚህ ኢትዮጵያን ማለት አማራ መሆን ማለት እስኪመስል ድረስ የታላቋ ሃገር የመኖር አለመኖር እጣ ህወሃት ሊያጠፋው ከቆረጠው የአማራ ህዝብ ጋር ተፈተለ፡፡ ህወሃት የአማራን አከርካሪ ሰበርኩ ሲል ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ሽባ አደረግኩ ማለቱ ነበር፡፡

ኢትዮጵያን ማለቱ ያስጠቃው አማራም መዳን የሚችለው በሚያሳድነው አማራነቱ መደራጀት እንጅ የሞቱ መንስኤ በሆነው ኢትዮጵያዊነት አለመሆኑን ውሎ አድሮ በመረዳቱ ሳይወድ በግድ ወደ አማራነቱ መደብ ገባ፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትም በሞት ጥላ ስር ሆነ፡፡ይሄኔ የዘውግ ብሄርተኝነት በህገ-መንግስት ተደግፎ እናቱቤት እንዳለ ህፃን ሲዝናና ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሰልፈኛ እንደ እንጀራ እናት ሆነች፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ቅሪት ያለው በኢትዮጵያ ከተሞች ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሃገሪቱ ከተሞች ከገጠር በመጡ የዘውግ ብሄርተኝነት ምልምሎች ቁም ስቅላቸውም ያያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተሞች ያለ ስጋት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ያለበትን “የእልም ስልም” ኑሮ ያሳያል፡፡

እንዲህ ያለውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመጥፋት የተቃረበ መዳከም እንደ ድል የሚያየው ኢትዮጵያ በግድ እንደተጫነችበት የሚተርከው  የኦሮሞ ብሄርተኝነት ነው፡፡ከአክሱምጀምራ ስትሰፋ ሞያሌ የደረሰችውን ኢትዮጵያ “ነይልኝ” ብሎ ጋብዞ የተቀላቀለ ያለ ይመስል “ኢትዮጵያ መጥታ ተጭናብኛለች” በሚል የጫኝ ተጫኝ ተረክ የተገነባው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንደ ህወሃት ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ለአማራ ለመሸለም ይቃጣዋል፡፡ ስዚህ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ሰማይ ምድር የሚደፋበት አማራው ብቻ እንደሆነ ያስባል፡፡ አማራውን ግራ ማጋባት ካስቻለ ደግሞ ኢትዮጵያ ብትፈራርስም ለኦሮሞ ብሄርተኞች ችግር አይደለም፡፡

የኦሮሞ ብሄረተኞች ኢትዮጵያ ስትፈርስ  ኦሮሚያን እንዳትነካ ተጠንቅቃ ይመስላቸዋልና ኢትዮጵያ ብትፈርስም ኦሮሚያ በፍፁም ሰላም ውስጥ የምትኖር አድርገው ያስባሉ፡፡ኢትዮጵያ ስትፈርስ ትልቁ ስባሪ ኦሮሚያ ስለሆነ፣ትልቁን ድርሻውን ይዞ ለመሄድ ያሰፈሰፈው የኦሮሞ ብሄርተኛ በርካታ ነው፡፡ እዚህ ላይ የተረሳው ነገር ሃገር ሲፈርስ የሃገር ስብርባሪ ለመካፈልም ጊዜ እንደሌለ ብቻ ሳይሆን በመፋረስ ሁኔታ ውስጥ ሁሉም ለራሱ ብዙ ለመውሰድ የሚሮጥ፣ መግደል የሚገባውን የሚገድል፣ማጥፋት የሚገባውን የሚያጠፋ ጉልበታም እንደሚሆን ነው፡፡ 

ምክንያት አምስት፡የኦሮሞ ብሄርተኝነት ንረት

የኦሮሞ ብሄረተኝነት ስኬት ባያጅበውም የኖረበት እድሜ ከሁሉም በሃገራች የሚንቀሳቀሱ የዘውግ ብሄርተኞች የሚልቅ ነው፡፡ይህ የኖረበት ረዥም እድሜ ስኬት ቢርቀውም የተበድየ ፖለቲካን በህዝብ ዘንድ ለማስረፅ ግን ጥሩ ግብዓት ነው፡፡ በመሆኑን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከማደግ አልፎ ወደ አክራሪነት ተመንድጓል፡፡ይህ ዝንባሌ ከሁለት አመት ወዲህ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ለስልጣን የማብቃቱ ድል የእኔ ነው ከሚለው የድል አድርጊነት ስሜት ጋር ሲደመር የብሄርተኝነቱ ንረት ወደ አደገኝነት እንዲነጉድ አድርጎታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከማንኛውም ብሄረተኝነት በሚልቅ መልኩ እንደ አንድ ሰው የሚነጋገር እና የሚግባባ፣ተነስ ሲባል አፍታም ሳይቆይ የሚነሳ ሆኗል፡፡ይበልጥ አሳሳቢው ነገር ደግሞ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ቁጭ ብድግ የሚያደርገው ጃዋር የተባለ ግለሰብ መረጋጋት ያልጎበኘው፣ሃላፊነት የማይሰማው፣የሚፈልገው ነገር ገደብ የለሽ  መሆኑ ነው፡፡በዚህ ሰው የሚመራው አደገኛው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ትክክለኛው የኦሮሞ ህዝብ ትግል ትርጉም ተደርጎ እየተወሰደ  ነው፡፡ በዚህ ትግል እሳቤ መሰረት ደግሞ ኦሮሚያ ወሎንም፣ሃረርንም፣ድሬዳዋንም፣አዲስ አበባንም ጠቅልላ መግዛት አለባት፡፡በነዚህ ግዛቶች የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በኦሮሞ ገዥ ፀጥ ለጥ ብለው፣እንዳች የፖለቲካ ጥያቄ ሳያነሱ ለመገዛት ካልፈለጉ ወደ መሄጃቸው መሄድ እንዳለባቸው ያምናል፡፡ አልፎ ተርፎ ኦሮሞ ያልሆኑ ብሎ ያሰባቸው የሃገራች ዜጎች ወደ ሃገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ መግባት አለመግባታቸውን በሰላሌ ኦሮሞ ጎረምሶች በኩል መቆጣጠር ይፈልጋል፡፡ይህ እሳቤ ሃገሪቱን እየመራ ያለውን ኦዴፓ የተባለ ፓርቲ ከሞላ ጎል አዳርሶ፣ይህ ፓርቲ የሚመራውን የመንግስት ክንፍ በአመዛኙ በቁጥጥሩ ስር ከማስገባቱ የተነሳ ህግ አስከባሪ አካላት ሳይቀሩ በጃዋር ከሚታዘዙ ጎረምሶች ጋር መንገድ በድንጋይ ዘግተው በዘጉት መንገድ ላይ ጠመንጃቸውን ወድረው መታየት ጀምረዋል፡፡    

የኦሮሞ ብሄርተኝነት እያደር መክረሩ ሳያንስ በአንድ ሃላፊነት የማይሰማው ሰው እጅ ተጠቃሎ እየገባ መሆኑ ነገሩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡የሚብሰው አደገኛ ነገር ይህ ብሄርተኝነት የሚያመጣው እልቂት የሚጎዳው ራሱን ኦሮሞውን ጭምር መሆኑን የብሄርተኝነቱ መሪ የተረዳው አለመሆኑ ነው፡፡ ከላይ እንደተቀመጠው የኦሮሞ ብሄርተኝነት በዚህ አናናሩ ቀጥሎ እኔ ብቻ ነኝ ነፃነት የሚገባኝ፣እኔ ብቻ ነኝ የመብት ያለኝ፣እኔ ብቻ የፈለግኩት እና ያልኩት ነው በሃገሪቱ መሆን ያለበት በሚለው አካሄዱ ከቀጠለ ሃገሪቱ ወደ ተሟላ ውድቀት ማዝገሟ አይቀርም፡፡ ይህ ውድቀት በሚያስከትለው እልቂት ጃዋር  የእልቂቱ አሰናጅ እንጅ የመራራው ፅዋ ተካከፋይ እንደማይሆን ግልፅ ነገር ነው፡፡

የኦሮሞ ብሄርተኝነት መዘውር በአንድ ሃላፊነት የማይሰማው ሰው እጅ ተጠቃሎ መግባቱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ ብሄርተኞቹ ግን የአደገኛው እንቅስቃሴ በአንድ ሰው የሚከፈት የሚዘጋ መሆኑን እንደ ትምክህት ወስደውታል፡፡ሃገሪቱን በአንድ ቀን ቀጥ ማድረግ እንደሚችሉ ያስፈራራሉ፡፡በአንድ የማህበራዊ ድረ-ገጸ መልዕክት የጎጡን ጎረምሳ ለጥፋት መሰለፍ መቻሉን እንጅ ይህ ጥፋት ትእግስቱን አስጨርሶ ለሌላ ጥፋት የሚያስነሳው የሌላ ጎጥ ጎረምሳ እንዳ ለጊዜው ዘንግቶታል፡፡ለጥፋት መታጠቁ ሌላ ጥፋት አምጥቶ ሃገር ሲነድ እሱ ባህር ማዶ ቁጭ ብሎ የእኛን እውነታ እንደ ፊልም እስካላየ ድረስ ሌላም ቤት እሳት እንዳለ መረዳት አልቻለም፡፡

ምክንያት ስድስት፡የኦዴፓ ወቅታዊ አቋም

በአሁኑ ወቅት በሃራችን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የማይተነበይ፣በምን ሰዓት ምን አይነት ችግር ይዞ እንደሚመጣ የማይታወቅ ነው፡፡ችግሩን የሚያብሰው ደግሞ ሃገሪቱን የሚመራው ኦዴፓ የተባለው ፓርቲ ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ ከውጭ ሆኖ ለሚያስተውለው እጅግ ግራ የሚያጋባ መሆኑ ነው፡፡የሃገሪቱን የአመራር መንበር በአመዛኙ የያዘው ኦዴፓ ዋና ባለስልጣናቶቹ ሳይቀሩ ሃገር እግር በራስ የሚያደርግ ንግግር በአደባባይ የሚናገሩ፣በማህበራዊ ድረገፅ የሚፅፉ ናቸው፡፡ይህ ንግግራቸው ኦዴፓ የተባለው ፓርቲ እስከ ሞት አብረን እንዘልቃለን ካሉት አዴፓ ጋር ጭምር ወደ ለየለለት ግብግብ ውስጥ ሊነክራቸው የሚችል ነው፡፡ይህ ማለት የሃገር ህልውና አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡በዋናነት እነዚህን ሁለት ፓርቲዎች (አዴፓ እና ኦዴፓን) ተማምኖ ሃገር ይድናል ብሎ ያሰበው ህዝብ የኦዴፓ ባለስልጣናት ጃዋርን እየመሰሉት ሲሄዱ ቢመለከት “የምንመራው በጃዋር ነው” እስከማለት ደርሷል፡፡በጃዋር መመራት ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ አይነገርም፡፡

አደባባይ ወጥተው እንደ ጃዋር የሚያወሩ የኦዴፓ ባለስልጣናት ለሃገር መኖር አለመኖር ግድ የሌላቸው፣በኦዴፓ ውስጠ የመሸጉ የጃዋር ሰልፈኞች እንደሆኑ ህዝብ መጠርጠሩ አይቀርም፡፡ያውም እጅግ አደገኛ በሆነ ፈታኝ ወቅት ሃገር የማስተዳደር ትልቅ እምነት የተጣለበት ኦዴፓ አብዛኛው ባለስልጣናት መታመን የማይከብዳቸው መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡የሃገር ህልውና ከኦሮሙማ ህልም የበለጠ የሚያሳስበው የኦዴፓባለስልጣን ምን ያህሉ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን አይቻለም፡፡ሌላው ቀርቶ ለውጡ ሲመጣ በሰፊው ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ ወደ ስልጣን ለመቅረብ ከተላበሱት ገፀ-ባህሪ ጋር አብረው ይኑሩ ከገፀ ባህሪ ይውጡ ለማወቅ በሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ናቸው፤በኦህዴድ ውስጥ የጃዋር ሰልፈኛ ላለመሆናቸውም አፍ ሞልቶ መናገር ያዳግታል፡፡

የፌደራል መንበረ ስልጣን በያዘው ኦዴፓ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አቋም ዝብርቅርቅ ሃገሪቱን ወደመቀመቅ ይዞ እንዳይወርድ ያሰጋል፡፡ስልጣን ወደ እጃቸው ስትቀርብ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ያሉት ኦህዴዶች ውለው አድረው የሃገር ፈተና እየሆኑ ነው፡፡ሃገር በሚመራው ኦህዴድ ውስጥ ሃገር ለማዳን ሲባል የሚወሰድ አንድ የፖለቲካ አቋም በሌለበት ሁኔታ፣ጭራሽ ከመሃከላቸው ኢትዮጵያን ለማዳን የሚሰራ አንድስ እንኳን ሰው ሲገኝ በአማራ አሽከርነት ተፈርጆ ከየ አቅጣጫው ጦር የሚመዘዝበት ከሆነ ሃገሪቱ ያለችበትን ችግር መገመት አያዳግትም፡፡በግሌ ኦህዴድ ወደ ስልጣን ሲቃረብ አእምሮየን ሞልቶት  የነበረው ጥያቄ “እውን ኦህዴድ ኢትዮጵያን መምራት የሚፈልገውን ስፋት ሰፍቶ ሃገር ማዳን ይችላል ወይ? በኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ ስር የሰደደው የኦሮሙማ መንፈስስ እንዲህ በቀላሉ የሚነቀል ነው ወይ?” የሚለው ነገር ነበር፡፡ኦሮሙማ የሚለውን ጠባብ ጥብቆ የለመደ ቡድን ሃገር የሚያክል ስፋትን ከመቅፅበት ሊያመጣው አይችልም፡፡ ቢያመጣው እንኳን ሁሉም በኦዴፓ ውስጥ ያለ ፖለቲከኛ በአንዴ ሊያመጣው አይችልም፡፡ በዚህ መሃል ቀድሞ በኢትዮጵያ ልክ የሰፋ አስተሳሰብ ማምጣት የቻለው ጥቂት ቡድን ከየአቅጣጫው በሚወረወር ጦር መቁሰሉ አይቀርም፡፡ቁስለቱ ይህን ቡድን በሚገድለው ደረጃ ከበረታ የሃገራችን እጣ ፋንታም አሳሳቢ ይሆናል፡፡

በገልፅ ለማስቀመት በአሁኑ ወቅት በኦህዴድ ውስጥ ብዙ አይነት  የፖለቲካ ሰልፈኛ አለ፡፡አንደኛው ሃገር እግር በራስ ብትሆን ግድ የማይሰጠው ሲሆን ሁለተኛው ሃገር እጁ ላይ እንዳትፈርስ የሚቸገረው ቡድን ነው፡፡ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ መሆኑም የሚያምረው ኦሮሙማንም ለመተው የሚቸግረው ወላዋይ ነው፡፡ሶስስተኛው የኦሮሞ የበላይነትን ያሰፈነች ኢትዮጵያን መገንባት የሚፈልግ ነው፡፡ኦህዴድ እንዲህ ባለው ድብልቅልቅ ሰልፈኛ መከፈሉ ለአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሌላው ትምክህታቸው ነው፡፡ሃገር በሚመራው ኦህዴድ ውስጥ ቀላል የማይባል ሰልፈኛ ማሰለፋቸው የመንግስትን ስልጣን እንደ መቆጣጠር ሳይወስዱት አልቀሩምና በሃገሪቱ ውስጥ ሁሉን ማድረግ የመቻል እብሪት እየተሰማቸው ነው፡፡

አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከላይ የተጠቀሱትን ዋነኛ ሁኔታዎች እንደ መመኪያ ወስደው የሃገራችንን ፖለቲካ ወደ ፈለጉበት አቅጣጫ ለመውሰድ በማናለብኝት ሲንቀሳቀሱ ሌላው ኢትዮጵያዊ መታገስን መርጧል፡፡ይህ መልካም ውሳኔ ቢሆንም የኦሮሞ ብሄርተኞችን እንቅስቃሴን በማጤን እና አካሄዳቸው ሃገርን እንዳያጠፋ ለመግታት የሚያስችል መስመር ላይ መቆም ያስፈልጋል፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት በኦዴፓ ውስጥ ያለውን የሃይል አሰላለፍ አንድ ወጥ አለመሆኑን ተረድቶ በጅምላ ከመውቀስ መቆጠብ ነው፡፡ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ማንም ከማን የማይበልጥባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር  የሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች ተሰባስበው ተጨባጭ የሆነ ህብረት መፍጠር ነው፡፡ይህ ህብረት የዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ጎራ ሆኖ ሲፈጠር የኦሮሞ ብሄርተኞች ትምክህት የሆነው የብዙ ቁጥር ትርክት ውድቅ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን የሚፈልገው ኢትዮጵያዊ አለመመሰባሰቡ እንጅ ኦሮሞ የገነነባት ኢትዮጵያ እውን ትሁን ይሁን ከሚለው ቡድን እንደሚበልጥ እርግጥ ስለሆነ ነው፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች ኢትዮጵያን የሚፈልግ ኦሮሞም በርካታ ስለለሚሆን የልብለጥ ባይ ኦሮሞዎችን ግማሽ እውነት ከሆነው ትርክታቸው ጋር ለብቻቸው እንዲቀሩ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ካልሆነ የሚከሰተው ነገር ሃገራችንን እንድናጣ የሚያደርግ አደገኛ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ይህ አደገኛ ነገር እውን የሚሆነው በሃገሪቱ ለእኩልነት የሚሰራ አካል የለም ተብሎ ተስፋ መቁረጥ ላይ ከተደረሰ ነው፡፡እንዲህ ያለው ተስፋ ማጣት በሃገራችን የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች የኦሮሞ ብሄርተኝነት አሁን እየሄደበት ባለው መንገድ ተጉዘው የየዘውጋቸውን ደህንነት ከኦሮሞ ብሄረተኞች የበላይነት ለማዳን በተናጠል መንቀሳቀስ እንዲጀምሩ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እልህን አዝሎ የሚመጣ የመጨረሻ እንቅስቃሴ ስለሚሆን ከዚህ ውስጥ ሃገር በሰላም ትወጣለች ብሎ ማሰብ ዩጎላቪያ ተመልሳ ሃገር ትሆናለች ማለት ነው፡፡ከዚህ ለመዳን በአሁኑ ወቅት ያለውን የሃገራችንን የፖለቲካ ሃይች አሰላላፍ በእርጋታ ማጤን፣በተለይ የኦሮሞ ብሄርተኘነትን አደገኛ ጉዞዎች ለመግታት በተናጠል ከመሮጥ ይልቅ መተባበር ያስፈልጋል፡፡   

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።  

የአማራ ብሄርተኝነት ስንክሳር እና ያዘለው አደጋ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ
መስከረም 14 2012 ዓ ም

በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተፀንሶ የተወለደው የሃገራችን የፓርቲ ፖለቲካ ታሪክ መሰረቱን ያደረገበት ስታሊናዊ ርዕዮተ-ዓለም የዘመኑን ታጋዮች ቀልብ ከሃገራቸው የፖለቲካ አድባር አፋትቶ ከሩሲያ እና ቻይና ጋር ያዋደደ ነበር፡፡ይህ ወደ ራስ ልዩ ሁኔታ በጥልቅ ለመመልከት ፋታ ያልተወሰደበት የፖለቲካ ግልቢያ ነው እስከዛሬ ያላባራ የመከራ ዶፍ በሃገራችን ሰማይ ላይ አዳምኖብን የሄደው፡፡መሰረቱ የተበላሸ ቤት አይፀናምና ከጅምሩ በተንሸዋረረ ትንታኔ ላይ የቆመው የፓርቲ ፖለቲካችን ሁለመና ዛሬ ላይ ሃገራችንን ራሷን ይዟት ሊሄድ በሚችል ህመም ውስጥ ከቷታል፡፡

በዚህ ዘመን ያለን እኛ የፖለቲካችንን ዋነኛ ችግር ተረድተን ለመጭው ትውልድ የምናስረዳበትን ሸውራራ እሳቤ የተረከብነው ከቀደምቶቻችን የፖለቲካ እሳቤ ነው፡፡ሸውራራው የፖለቲካ እሳቤ ከጅምሩ የተቀዳበት ምንጭ  ደግሞ ሰከን ብሎ የታሰበበት፣ሃገራዊ እውነታን ያገናዘበ፣ሙሉ አካል ያለው ትንታኔ አልነበረም፡፡ይልቅስ አንድ አቅጣጫን ይዞ በሚግለበለብ፣ነጥቆ በረርነቱ በበዛ፣ጥራዝ ነጠቅ እውቀት ላይ የቆመ ነበር፡፡ይህ እሳቤ ከወቅቱ ስታሊናዊ የፖለቲካ ፋሽን መምጣት ጋር ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የቆየ ነበር፡፡ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ነፍስ ዘርቶ ስጋ ለብሶ ብቅ ያለው ከአምስት ገፅ በማይበልጥ የዋለልኝ መኮንን ተንታኔ ነው፡፡

ይህ ትንታኔ በኢብሳ ጉተማ “ኢትዮጵያዊው ማን ነው?” በሚል ግጥም ታጅበ፡፡የሩሲያ ቻይና  ማርኪሲስት ድርሳናትን ከማነብነቡ ጋር ተደማመረና ወደ የ1968ቱ የህወሃት ማኒፌስቶነት አደገ፡፡ ትግሉንም ወደ ደደቢት መራው፡፡ይህ ሲባል የዛ ዘመን ትግል ህወሃት ያደረገው የደደቢት ትግል ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ደደቢት ላይ ማተኮር ያስፈለገው ስሁትነቱ ከስኬት ያላገደው አንድያ ትግል እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡በተጨማሪም አሁን ያለንበትን የፖለቲካ መስመር የመቃኘቱን መልካም ዕድል ያገኘውም ይሄው ስሁት መስመር በመሆኑ ነው፡፡በ1968 የተፃፈው ማኒፌስቶ ውስጥ የተቀመጠው፣ህወሃትን እስከ ዛሬ እየዘወረው ያለው ስሁት መስመር የጀርባ አጥንት ከዋለልኝ መኮንን ጥራዝ ነጠቅ ትንታኔ የሚቀዳ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የአንድ ብሄር(የአማራ) የበላይነት አለ ሲል ያቀረበው ሙሉ አካል የሌለው ስንኩል ትንታኔ ለአንድ ማህበረሰብ ዋና በሆነው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ረገድ አማራ ሲባል በጅምላ የተጠራው ማህበረሰብ ከበላይነቱ አንፃር የመጠቀሙን ምልክቶች አያሳይም፡፡ፖለቲካዊ አድሎ በሚለው ነገር ላይም ከማለት ባለፈ አማራ መሆን የሚያስኬድበትን እና አማራ አለመሆን የማያስኬድበትን መንገድ አያሳየንም፡፡ከሁሉ በላይ ዘውግ ፖለቲካዊ ህልውና እና ትርጉም ባላገኘበት የሃገራችን የፊውዳል ስርዓት ውስጥ ዘውግን ብቸኛ የትንታኔ መሽከርከሪያ ማድረጉ የዋለልኝ ትንታኔ ዋና ሳንካ ነው፡፡ጡንቻውን ያፈረጠመ ሁሉ ወደ ስልጣን በሚጠጋበት፣ዋናው ጉልበት በሆነበት የፊውዳል ስርዓት ውስጥ ዋናውን (የጉልበተኝነትን ጉዳይ) ግምት ውስጥ ሳያስገባ የሚደረግ ትንታኔ ሙሉ አካል የሌለው ድኩም ሃተታ መሆኑ አይቀርም፡፡ይህን ድኩም ሃተታ ማኒፌስቶው አድርጎ ተጠራርቶ ደደቢት የገባው የአንድ መንደር ጎረምሶች ቡድን ደግሞ የባሰው ድኩም፣ስህተት ደጋሚ፣የሃገር መከራ አስረዛሚ መሆኑ ሳያንስ በለስ ቀንቶት ቤተ-መንግስት መግባቱ የሃገር መከራ እንዳያባራ አድርጓል፡፡ 

የዋለልኝን ድርሳን በልባቸው ፅላት የፃፉት ህዋቶች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ሁሉም የዘውግ ፖለቲከኞች ከህወሃት ባላነሰ ሁኔታ የሚመሩበት ነው፡፡ ህወሃትን እና ሌሎቹን የዘውግ ፖለቲከኞች የሚለያቸው ህወሃቶች ጥርሳቸውን ነክሰው መዋጋት ያስቻለ ብርታታቸው ለቤተ-መንግስት ያበቃቸው ሃሞተ ኮስታሮች መሆናቸው ነው፡፡ይህ ኋለኛው እድፋም ታሪካቸው ሊጋርደው የማይገባው የህወሃት ታጋዮች ውበት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ኮስታራው ትግላቸውም ሆነ ቅምጥል የስልጣን ዘመናቸው ለኢትዮጵያ የፈየደው በጎ ነገር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም-የሃሪቷን መፀኢ እድል ካለፈችበት የባሰ አስፈሪ ድርጎት ሄደ እንጅ!

የዛሬዋን ኢትዮጵያ በስሁት መንገድ እየነዳ አምጥቶ ገሃነም በር ላይ አስቀምጦ የሄደው የህወሃት ዋና ፈሊጥ አማራ የሚባለውን የኢትዮጵያ ህዝብ በሆነውም ባልሆነውም መክሰስ፣ማክፋፋት፣ቅስም መስበር ነው፡፡ ህገ-መንግስት ሲፅፍ የአማራውን ትምክህት ለመስበር እንደሆነ ለተላላ ሰሚዎቹ ይነግራል፡፡በዘር የተሸነሸነ የአስተዳደር ክልለ ሲመትር አማራው ከተንሰራፋበት የኢትዮጵያ ክልል ተነስቶ ወደጎሬው እንዲገባ፣ከለመደው መግዛት መንዳት እንዲጎድል እንደሆነ ይሰብካል፡፡የመሬትን ባለቤትነት ለብሄር ብሄርሰቦች ሰጠሁ ሲል መሬቱን አማራ እንዳይገዛው እየጠበቅኩላችሁ ነው ሲል እየሰበከ ነው፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ አማራው ንጉስ የጠላው ፍጡር የሚያየውን መከራ ሁሉ አይቷል፡፡የህወሃት የስልጣን ዘመን የተሟሸው አማራው በበደኖ እና አርባጉጉ ባሰማው የሲቃ ድምፅ  ነው፡፡ይህ የሲቃ ድምፅ ለህወሃት የድል ማህተም ነው፤የአማራ አከርካሪ መሰበር፣ላይመለስ ሞቶ ርቆ መቀበር ምልክት ነው፡፡የሰው ልጅ አሰቃቂ ሞት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ የዝቅተኝነት ስሜት ማርገቢያ ሙዚቃ ሆነ፡፡ የአማራው መፈናቀል፣በአንድ ሌሊት ሃብት ንብረት አራግፎ ነፍስ ብቻ ይዞ እግር ወደመራው መትመም አጀብ የማያሰኝ አዘቦታዊ ነገር፣ጆሮ ዳባ ልበስ የሚባል ተገቢ ነገር መሰለ፡፡ ይህ የሆነው ለአጭር ጊዜ አይደለም-ለሩብ ምዕተዓመት እንጅ! 

በሃገራችን መፈናቀል ብርቅ ሆኖ ማነጋገር የጀመረው ከሁለት አመት ወዲህ፣የዘር ፖለቲካው ከአማራው ሌላ ብሄረሰቦችን ቤት ማንኳኳት ሲጀምር ነው፡፡የዘውግ ፖለቲካው ከጨቋኙ የአማር ብሄር በስተቀር ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን አስተቃቅፎ የሚያኖር፣ ከአማራ ጭቆና የሚታደግ ድንቅ እድል ተደርጎ ሲሰበክ ኖሯል፡፡የዘውግ ፌደራሊዝሙ ለአማራው ያልተመቸው ደግሞ ሊጨቁን በሃገር ዳርቻ ስለተበተነ ነው የሚል ተረክ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሲተረክ ኖሯል፡፡ይህ ተረክ እውነት አለመሆኑ እየታየ የመጣው በጨቋኝነት የማይታወቁት እንደ ጌዲኦ፣ኦሮሞ ከሶማሌ ክልል፣ከምባታ ከከፋ፣ወላይታ ከሲዳማ በገፍ መፈናቀል ሲጀምሩ ነው፡፡የሆነ ሆኖ ይህ እውነታ የታወቀው እጅግ ዘግይቶ በመሆኑ አማራው ከብዙ አቅጣጫ በሚወረወር ጦር እንዲዋከብ አድርጎት ኖሯል፡፡የዚህ ድምር ውጤት ዛሬ በአስፈሪ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የአማራ ብሄርተኝነት ወልዷል፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ጅማሬ?

ባለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት አማራ መሆን ራሱን የቻለ ችግር ሆኖ ኖሯል፡፡በዚህ ዘመን ባለችው ኢትዮጵያ በተለይ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው የአማራ ተወላጅ ሰው ቤት እንዳለ ሰው አሳቃቂ ተቆጭው በዝቶ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ሆኖም የዚህ ህዝብ እንግልት አደጋውን  በሚመጥን ደረጃ የሚታገልለትነት የአማራ ብሄርተኝነትን ሳይወልድ ቆይቷል፡፡በዚህ ምክንያት የአማራ ህዝብ ብርቱ ጠበቃ በሚያስፈልገው የህወሃት የስልጣን ዘመን ሁነኛ ተሟጋች ሳያገኝ መራራ ፍዳውን በየግሉ ሲጎነጭ ኖሯል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ  ዋነኛው መልስ የህወሃት ጫና ነው፡፡ባለስልጣኑ ህወሃት ከጫካ ጀምሮ የተዋጋለት ዓላማ የአማራውን ቅስም መስበር ነው፡፡ በኋላ ጠቤ ከገዥ እና ነጅው አማራ ጋር ነው እንጅ ከህዝቡ ጋር አይደለም የሚለውን ኢህአዴጋዊ መቀላመድ አምጥቷል፡፡ሆኖም ህወሃት አማራን እንደ ህዝብ እንደ ባለጋራ የሚያይበት ልክፍት እንዳልለቀቀው ማሳያው ብዙ ነው፡፡ ከብዙው አንዱ አፈር ገፊውን አማራ ለዘር ያስቀመጠውን እህል ሳይቀር በቀበሌ ካድሬ እንዲቃጠልበት እያደረገ ሲያፈናቅል፣ይህ ደግሞ ትክክል መሆኑን በፓርላማ ሳይቀር ሊያስረዳ ሲነሳ ነው፡፡

ህወሃት በአንድ በኩል አማራውን በእሾህ ለበቅ እየገረፈም የተበድየ ተረክም ሆነ ተጨባጭ በደል የሚወልደው የዘውግ ብሄርተኝነት በአማራው ዘንድ ብቻ ሲሆን እንዳይበቅልም ወገቡን አስሮ ይሰራ ነበር፡፡ለምን ቢባል የአማራው ብሄርተኝነት ከተወለደና ካደገ አማራን እንደ ጭራቅ እየሳሉ ማስፈራራት አይቻልም፡፡ ይህ ካልሆነ ግንዛቤ የጎደለውን የዘር ፖለቲከኛ በዚሁ አማራ በተባለው ጭራቅ ተፃራሪ አሰልፎ ‘እኔ አማራ ከተባለ ከጭራቅ የማድናችሁ ታዳጊያችሁ ህወሃት እባላለሁ’ እያሉ ስልጣን ማስረዘም አይቻልም፡፡በበኩሌ ህወሃት አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ አውርዶ ብሄርተኛ አድርጎ ለማሳነስ ሲሰራ ኖሯል በሚለው ሙግት አልስማማም፡፡ይልቅስ ተቃራኒውን አምናለሁ፡፡ ህወሃት የአማራው ብሄርተኝነት አድጎ በህዝቡ ላይ የሚወርደውን በደል ባያስቀር እንኳን በደሉ ስለመድረሱ ሰብዓዊነት ለሚሰማው ሁሉ ክስ እንዳያቀርብ ተግቶ ሲሰራ መኖሩ ትክክለኛ ትንታኔ ሆኖ ይታየኛል፡፡ 

በነገራችን ላይ የማንኛውም ዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ የትኛውንም ዘውግ ከመበደል አያድነውም፡፡ለምሳሌ በኢትዮጵያ በአንጋፋቱ ከህወሃትም የሚቀድመው የኦሮሞ ብሄርተኝነት የኦሮሞን ህዝብ ከእስር፣እንግልት፣መፈናቀል መሰደድ፣መሞት ፣መታሰር አላዳነውም፡፡ ያደረገለት ነገር ቢኖር ይህ መከራው ለሰሚ እንዲታወቅ ሪፖርት ማድረግ፣ህዝቡን ለተቀናጀ ትግል ማነሳሳት ነው፡፡ ህዝብን ከፖለቲካዊ በደል የሚታደገው የዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ ሳይሆን የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ብቻ ነው! 

ወደ ቀደመ ጉዳያችን ስንመለስ የአማራ ብሄርተኝነት እንዳያድግ እንቅፋት የሆነው የህወሃት ክርን ነው፡፡ይህ የህወሃት ክርን ለምን አስፈለገ ስንል ሁለት ምክንያት ይኖረዋል፡፡የመጀመሪያውና ዋነኛው የአማራ ብሄርተኝነት ካደገ ህወሃት መወጣጫ አድርጎት ወደ ስልጣን የመጣበትን መሰላል ስለሚያነሳ ነው፡፡ያ መሰላል አማራን እየወቀሱ፣እንዳይመለስባችሁ የምጠብቃችሁ እኔ ነኝ እያሉ ከሌሎች ብሄርሰቦችን የታዳጊነት እምነት አግኝቶ  ስልጣን ላይ መቀመጥ ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ የአማራ ብሄርተኝነት ካደገ በአማራው ላይ እየተደፈደፈ ያለውን ለሁሉም የሃገሪቱ ችግር መነሾ የመደረግ የጥፋተኝነት ዳፋ ሃሰትነት ለማስረዳት መነሳቱ፣በሃሪቱ ዳርቻ በአማራው ላይ የሚደረገወውን ግፍ ነቅሶ አውጥቶ ማሳወቁ አይቀርም፡፡

ይህ ሲደረግ ደግሞ በአማራ ክልል ያለው (በመረጃ እጥረት ምክንያት ከክልሉ ውጭ ባሉ ወገኖቹ ላይ የሚደርሰውን በደል ከተባራሪ ወሬ በቀር በተገቢው ሁኔታ ሳያውቅ የኖረው) የአማራ ህዝብ ከሆነበት በደል የተነሳ አዲሱ ወደሆነው የአማራ ማንነት ህብረት መሄዱ አይቀርም፡፡ንዴት የሚቀናው የዘውግ ህብረት ደግሞ ከአማራ ህዝብ  ብረት የማንገት ባህል ጋር ተዳምሮ አማራን ከረዥም ዝምታው ሊያነቃው ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የአማራውን ነፍስ እንዳለው አካል መንቀሳቀስ የማይወደወን “ገድየ ቀበርኩ” ባዩን ህወሃትን ማስበርገጉ አይቀርም፡፡ስለዚህ ህወሃት የአማራውን መደራጀት በተለየ ትዕግስት ማጣት እንዲያየውና እየተከተለ እንዲያጠፋው አድርጓል፡፡የፕሮፌሰር አስራትን ነፍስ በመብላት ያልተመለሰው የመአድ እና የህወሃት ግብግብ ለዚህ ሁነኛ ምስክር ነው፡፡ መአድ የተደረገበትን ያህል ኦብኮ/ኦፌኮ ያሉ ሌሎች የዘውግ ፓርቲዎች ገና ዳዴ ከማለታቸው የህወሃትን መራራ በቀል አለመቅመሳቸው መአድ በልዩ ሁኔታ ይታይበት የነበረውን የህወሃት ክፉ አይን ለማወቅ ይረዳል፡፡

እንደ መአድ ተወልዶ እንደ መኢአድ ያደገው ፓርቲ ከመነሻው የዘውግ ፓርቲ መሆኑ የግድ እንጅ የውድ እንዳልነበር ማሳያው ብዙ ነው፡፡ አሁንም በየ ድረገፁ የሚገኘው ፕሮፌሰር አስራት በወቅቱ ያደርጉት የነበረው ንግግር ይዘት አንዱ ነው፡፡መሪው የተናገሯቸው የቪዲዮ መዘክሮችም ሆኑ በህይወት ታሪካቸው ዙሪያ የተፃፉ መፅሃፎች የሚያስረዱት የአማራው ብሄርተኝነት መነሻው ከህወሃት የመጣው ክፉ ለበቅ እንደሆ ነው፡፡ የአማራው ትግል መነሻ በአማራው ህዝብ ላይ ያንዣበበውን የህልውና አደጋ መመከት ሲሆን መዳረሻው ደግሞ እኩልነት በሰፈነባት ኢትዮጵያ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በሰላም መኖር ነው፡፡የዚህ ምልክቱ ደግሞ ፓርቲው የአማራን ህዝብ ያንዣበበትን የሞት ጥላ ታግሎ ካስወገደ በኋላ ፓርቲያቸው መኢአድ ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲ እንደሚቀየር በግልፅ ያስቀጡበት መንገድ ነው፡፡ ሆኖም ፕሮፌሰር አስራት የመሰረቱት እና ህይወታቸውን ያጠቱለት መአድ ወደ መኢአድ የተቀየረው አማራውን ከህልውና ስጋት በተግባር መታደግ ችሎ ነው ወይ የሚለው ነገር አጠያያቂ ቢሆንም መአድ ወደ መኢአድ ተቀይሮ አማራውም ሁነኛ ጠበቃ በሚያስፈልገው ጊዜ ምትክ አልቦውን ጠበቃውን ፕሮፌሰር አስራትን ተነጥቆ ክፉውን ጊዜ በየግሉ እንዲጋፈጥ ሆኗል፡፡

ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ

መአድ በህወሃት ክርን ተደቁሶ ወደ መኢአድ ከተቀየረበት ዘመን ጀምሮ እስከ ህወሃት ለመውደቅ ዘመም ዘመም ማለት ድረስ ባለው ረዥም ዘመን ከየአቅጣጫው እንደ እንጀራ ልጅ ለሚዋከበው የአማራ ህዝብ ጥብቅና የሚቆም ፓርቲም ሆነ ሌላ አይነት ድርጅት በሃገር ውስጥ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት አማራው ከአርባጉጉ በደኖ በኋላ ለተከሰተ መንግስት መራሽ ሁለተኛ ዙር ሞት እና መፈናቀል ተዳረገ፡፡ይህ መንግስት መራሽ መፈናቀል በህወሃት መራሹ የአዲስ አበባው መንግስት ቀጭን ትዕዛዝ እንደ ሽፈራው ሽጉጤ እና ያረጋል አይሸሹም ባሉ ተላላኪ አሽከሮቻቸው አጋፋሪነት በጉራ ፈርዳ እና በቤኒሻንጉል የተከወነ ነበር፡፡ህወሃት በአፉ በአልጠላውም የሚለውን የአማራ አርሶ አደር ከገጠር ሲያፈናቅል፣ እንደማይወደው በግልፅ የሚናገረውን የአማራ ምሁር እና የከተማ ልሂቅ ደግሞ ወደ እስርቤት እያጋዘ አስሮ ይገርፍ ነበር፡፡

የሚሰራውን ሲሰራ እንቅፋቱን ሁሉ ቀድሞ ማስወገዱ ላይ የማይሰንፈው ህወሃት የአማራ ብሄርተኝነት እንዳይፀነስ ታጥቆ ይሰራ የነበረው ይህ ሁሉ ግፍ ሲሰራ ለአማራ ህዝብ የሚጮህ እንዳይኖር፣ጠላቴ ያለውን ቤት ዘግቶ ለመደብደብ ነው፡፡ይህ ደግሞ በደምብ ተሳክቶለታል፡፡ማሳያው የአማራን ህዝብ መፈናቀል በተመለከተ ትርጉም ባለው ተቋማዊ መንገድ የሚሞግት አካል አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች በግላቸው በተለያየ ሚዲያ ነገሩን ለማሳወቅ የሚያደርጉት ጥረት ከጋዜጣ አዘጋጆች ጀምሮ በሚደቀን እንቅፋት ስኬታማ አለመሆኑ ነው፡፡

ሆኖም ተጨባጭ በደል ቀርቶ እውነት እና ውሸትን በዘነቀ ተረክ ለመወለድ የማይቸግረው የዘውግ ብሄርተኝነት ለአማራ ህዝብ ብቻ ሲሆን ከመምጣት አይቀርምና ቢዘገይም የአማራ ብሄርተኝነትም የማታ ማታ መከሰቱ አልቀረም፡፡ይህ ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ከቀድሞው(ፕሮፌሰር አስራት ይመሩት ከነበረው) የአማራ ብሄርተኝነትነት በብዙ መንገዶች በሚለይ ሁኔታ የተከሰተ ነው፡፡ የመጀመሪያው ልዩነቱ የኋለኛው የአማራ ብሄርተኝነት ያቆጠቆጠው የህወሃት ፈርጣማ ክንድ መዛል በጀመረበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአማራው ብሄርተኝነት የሁነኛ ባለጋራውን የህወሃትን የቀደመ ክርን ሳይቀምስ በሙሉ አቅሙ እንዲጓዝ  ወለል ያለ መንገድ የሚጠርግ ነውና የብሔርተኝነቱን እድገት ፈጣን አድርጎታል፡፡

ሁለተኛው ልዩነቱ የአሁኑ የአማራ ብሄርተኝነት የተጠነሰሰው ወጣቱ እንደልቡ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ተገናኝቶ ከዚህ ቀደም በህወሃት አዝማችነት ከ1968ቱ ማኒፌስቶ ጀምሮ አማራው ላይ የተደረገውን በደል ለማሰላሰል መቻሉ ነው፡፡ይህ ደግሞ ወጣቱ የተበድየ ስነልቦናን በልቡ ማህደር መፃፍ  በቻለበት ሁኔታ ፈጠረ፡፡ለዘውግ ብሄርተኝነት ማደግ ዋና የሆነውን የተበድየ ስነልቦና በተለይ በወጣቱ ዘንድ ማስረፀ መቻሉ ሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ከቀዳሚው በተለየ መልኩ እንዲያብብ አድርጎታል፡፡

በሶስተኝነት ደረጃ የሚጠቀሰው ልዩነት የሁነኛ መሪ ጉዳይ ነው፡፡ቀዳሚው የአማራ ብሄርተኝነት ፕሮፌሰር አስራትን የመሰሉ የሚሞቱለትም የሚቆሙለትም አላማ ያላቸው፣ በቀለም ትምህርት ግንዛቤቸውም አንቱ የተባሉ ሰው የሚመሩት ስብስብ ነበር፡፡ይህ ቀዳሚው የአማራ ብሄርተኝነት ከሁለተኛው ዙር ብሄርተኝነት እጅግ በጣም የሚልቅበትም የሚለይበትም ሁነኛ ልዩነት ነው፡፡ፕ/ሮ አስራት ለአማራው መብት ለመታገል ያበቃቸውን የትግል ምክንያት ጠንቅቀው አውቀው መስህብ ባለው የጨዋ አቀራረብ ማስረዳት የሚችሉ ብቻ ሳይሆኑ ትግላቸው ወደፊት ባሉት አመታት ወዴት እንደሚያመራ ሳይቀር ማስረዳት የሚችሉ ባለግርማ መሪ ነበሩ፡፡በዚህ በእርሳቸው በሳል  ባለ መስህብ መሪነት እና የትግላቸውን ምክንያትን ጠንቅቆ አውቆ እጅግ ጭዋ በሆነ መንገድ ለሌሎች የማስረዳት ፀዳል ሳቢያ ሰብዓዊነት የሚሰማውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የፓርቲያቸው አባል ካልሆነም ደጋፊ ለማድረግ ችለው ነበር፡፡

በተቃራኒው የሁለተኛው ዙር የአማራ ብሄርተኝነት ባለግርማ መሪ ማግኘቱ ያልሆነለት፣ተረጋግቶ የትግሉን ምክንያት ማስረዳት የተሳነው፣ሊናገር ሲነሳ ቁጣ የሚቀድመው፣ከዘውጉ ውጭ ያሉ ሰብዓዊነት የሚሰማቸውን ሰዎች መሳብ ቀርቶ የትግሉን ምክንያት የሚደግፉ የራሱን ብሄረሰብ ምሁራን ማስጠጋት የተሳነው፣ፖለቲካዊ ብልሃት የጎደለው ደም ፍላታም ንግግር የሚቀድመው፣ወዳጅ ከማበጀት ይልቅ ጠላት የሚያበዛ፣ነጋዴው ከታጋዩ የተደባለቀበት፣አማራነት ሰፍቶበት ገና ከጅምሩ በወሎየ ጎጃሜ፣በተጉለት በቡልጋ፣በደባርቅ ጃናሞራ፣በቆላ በደጋ የሚከፋፈል ሊቀርቡት ቀርቶ ሊሰሙት መስህብ በሌለው ፖለቲካዊ መስተጋብር የተዘፈቀ፣በእርስበርስ ሊፊያ የተመታ፣በመቧካት ፖለቲካ የተጠቃ፣ በአራስ ቤት እንሚሞት ልጅ የመሰለ ነው፡፡     

የመጀመሪውም ሆነ ሁለተኛው የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ዋነኛ መነሾ የህወሃት አማራን አይቼ ልጥፋ የሚል ፖለቲካዊ ስሪት መሆኑ ደግሞ ሁለቱን እንቅስቃሴዎች የሚያመሳስላቸው ነገር ነው፡፡የአማራ ብሄርተኛነት መነሾው ይህ የህወሃት ተፈጥሮ ቢሆንም የአማራ የብሄርተኝት ስጋት ግን ህወሃት ብቻ ነው ማለት አይቻልም፡፡እውነት ለመናገር በሃገሪቱ የሚገኙ የዘውግ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ አማራን ሳይወቅሱ እና ሳይረግሙ የፖለቲካ ትግላቸውን መነሾ ሊያስረዱ ይችላሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ስለዚህ የአማራ ብሄርተኝነት ስጋት ሁሉም በሃገሪቱ ያሉት የዘውግ ፓርቲዎች ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ከህወሃት ባላነሰ መጠን ለአማራ ብሄርተኝነት ስጋት ሆኖ ብቅ ያለው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ነው፡፡ 

እንደ ህወሃት አማራውን ኢላማ አድርጎ ማኒፌስቶ ባይፅፍም የትኛውም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ውድድር ውዝግቡ አማራ ከተባለው አካል ጋር ነው፡፡በኢህአዴግ ወገን የኖረው የኦሮሞ ብሄርተኝነት በኦህዴድ በኩል ስልጣን መያዙ መላውን የኦሮሞ ብሄርተኛ ያስደሰተ ቢሆንም ከኦሮሞ ቀጥሎ በመንግስታዊ ስልጣኑ ላይ በሁለተኝነት የሚታየው አማራ መሆኑ፣ኦሮሞ በያዘው ቤተመንግስት ውስጥ የአማራ አጋፋሪ መታየቱ የሚረብሸው የኦሮሞ ብሄርተኛ ቀላል ቁጥር ያለው አይደለም፡፡በአንፃሩ ኦሮሞ ስልጣን ስለያዘ አማራን ህወሃት ባደረገው መንገድ ይጎዳል ብሎ የሚያስብ የአማራ ብሄርተኛ ቀላል አይደለም፡፡ይህ የጥርጥር እና የፍራቻ እሳቤ መሬት ላይ ካለው የኦሮሞ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ወደ ልቅነት የሚጠጋ እንደልቡ የሆነ ንግግር እና አካሄድ ጋር ሲዳመር አማራው የቀደመ ኢትዮጵያዊ ብሄርኝነቱን ባይተወው እንኳን ችላ ብሎት በአማራነቱ ላይ እንዲያተኩር እያደረገው ይገኛል፡፡

ይህ እያደር እየበረታ የመጣው የአማራ ብሄርተኝነት ታዲያ በቅርቡ የተጀመረውን በዋናነት በአብን በሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት ዙሪያ ለመሰባሰብ ሲያመነታ የሚታይበት አጋጣሚ ይበዛል፡፡አብን የሚመራው የአማራ ብሄረተኝነት በዋናነት የሚደገፈው በወጣት አማሮች ሲሆን በእድሜም ሆነ በትምህረት የገፋው አማራ ግን በብሄርተኝነቱ የትግል ምክንያት ላይ ልዩነት ባይኖረውም አብንን ለመቀላቀል ግን ሲያመነታ ይስተዋላል፡፡ ይህ የሆነበት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም ከላይ ከፍብለው የተጠቀሱት አዲሱን የአማራ ብሄርተኝነት ተብትበው የያዙ ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ የአብን የአማራ ብሄርተኝነት ከጅምሩ በዋነኛ መሪዎቹ ሳይቀር የሚነገሩ ፖለቲካዊ ብስለት የሚጎድላቸው ንግግሮች፣ መሪዎቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው ሲናገሩ የትግላቸውን ምክንያት ጠብሰቅ አድርገው ማስረዳቱ ላይ ላይ  የሚቀራቸው መሆኑ የአማራ ምሁራንን ቀልብ መሳቡ እንዳይሳካላቸው አድርጓል፡፡

በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት የራሱን ልዩ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነቅሶ አውጥቶ በራሱ ቀለም ከመታገል ይልቅ እምብዛም መስህብ የሌለውን የኦሮሞ ብሄርተኞች የትግል ስልት በመድገሙ ላይ የተጠመደ ነው፡፡በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝንት ኦነግ ቀመሱን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ለመምሰል የሚያደርገው ጉዞዞ ትልቅ ድክመት ያበት ነው፡፡ ይኸውም አምባየ ነው የሚለው የአማራ ህዝብ አንደኛ ከሚያደርገው የኢትዮጵያ ህልውና ጋር የሚላተምበት አጋጠሚም መታየቱ ነው፡፡በማንኛውም ስም የሚጠራ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ኦነግ ወለድ ነው፡፡የኦነግ አንደኛ ደግሞ ኦሮሚያ እንጅ ኢትዮጵያ አለመሆኗን “መጀመሪያ ኦሮሞ ነኝ” በሚለው የትግሉ ዋነኛ መፈክር መረዳት ይቻላል፡፡ይህ ኢትዮጵያዊነቱን አንደኛ አድርጎ ለኖረው እና ቢቸግረው ብቻ አማራነቱን በመለማመድ ላይ ላለው የአማራ ህዝብ ትርጉም ሰጭ አይደለም፡፡በአብን የሚመራው የአማራ ብሄርተኝነት ደግሞ አይኑን የተከለው አርዓያ ባደረገው ኦሮሞ ብሄርተኝነት ላይ እንጅ የአማራን ህዝብ ስነልቦና አገናዝቦ ቆምኩልህ በሚለው ህዝብ ስነልቦና አንፃር አይመስልም፡፡ በዚህ ሳቢያ አብን የአማራ ምሁራንን እና ነፍስ ያወቀውን የዘውጉን ህዝቦች መማረኩ አልሰምር ብሎታል፡፡   

የአማራ ምሁራን እና አዋቂ የዘውጉ ህዝቦች ከህወሃት መሄድ በኋላ ህወሃትን ሊተካ የሚፋትረው የኦሮሞ ብሄርተኝነት አይጠረቄ አካሄድ “ወሎ የእኔ ነው” እስከማለት እንዳደረሰው የሚገነዘቡ ናቸውና እንዲህ ያለውን አካሄድ ለመመከት እንደ አብን ያለ ቁጠኛ የአማራ ብሄርተኝነት መኖሩን ላይጠሉ ይችላሉ፡፡ሆኖም በአብን ስም ለመጠራት የሚወደው የአማራ ምሁር ቁጥር እስከዚህም ነው፡፡የዚህ ምክንያቱ ለአማራ ህዝብ ያለአባት በሆነ መንገድ አብን የሚያሳየው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን እንደመዋጋትም፣ እንደማጠየቅም የሚቃጣው ኦነግ ቀመስ አካሄድ ነው፡፡ይህ ሄዶ ሄዶ አብንን ከባህር የወጣ አሳ የሚያደርግ ብልሃት አልቦ ጉዞ ነው፡፡የአብን በአማራ ምሁራን ዘንድ ሞገስ ማጣት የኦሮሞ ምሁራንን አግበስብሶ ከያዘው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር ለሚያደርገው ውድድር ሚዛን እንዳይመታ ማድረጉ አይቀርም፡፡በዚህ መሃል ከኦሮሞ ብሄርተኝነት መጦዝ የተነሳ የአማራ ብሄርተኝነት እንዲኖር የሚፈልገው የተማረውን ጨምሮ በርካታው የአማራ ብሄር ተወላጅ ወደ አዴፓ እንዲያዘነብል እያደረገ ነው ፡፡

የኢህአዴግ አባል የሆነው አዴፓ ደግሞ በቅርቡ ከእህት ድርጅቶች ጋር ተዋህጄ የሲቪክ ፖለቲካ አራማጅ ፓርቲ እሆናለሁ እያለ ይገኛል፡፡ይህ ውህድ ፓርቲ አማራውን በእጅጉ የሚያስጨንቀውን የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአግላይነቱ ህወሃትን የሚያስመኝ፣ለሰብዓዊ መብቶችም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ እና ህጋዊ ድንጋጌዎች ቁብ የማይሰጠውን የኬኛ ፖለቲካ ሃይ ማለት መቻል አለበት፡፡ውህዱ ፓርቲ ይህን ማድረግ ከቻለ አማራው ለመልበስም ለማውለቅም የተቸገረበትን የአማራ ብሄርተኝነት ካባ አውልቆ ጥሎ የለመደውን እና የሚያምርበትን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመልበስ የሚያመነታ ህዝብ አይደለም፡፡ ይህ ገቢራዊ ከሆነ በቁጡነቱ ስሙ በክፉ የሚነሳውን አብንንም ሆነ ኮበሌ ደጋፊዎቹን ሳይቀር ማሳመን የሚችል የኢትዮጵያ የመዳኛ መንገድ መሆን ይቻለዋል፡፡ 

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ውህዱ ፓርቲ በሲቪክ ፖለቲካ ስም ለተረኛ ነኝ ባዩ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሸብረክ የሚል ከሆነ የአማራ ምሁራንም ሆኑ ሌላው አብንን ለመቀላቀል እየተሸኮረመመ ያለው አማራ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ አክራሪ ብሄርተኝነት መንጎዱ አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ የአማራ ክልልን ምናልባትም ታጣቂ ሸማቂዎች ጭምር የሚንቀሳቀሱበት ግልፅ የአመፅ ቀጠና ሊያደርገው ይችላል፡፡የዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያን ከማለት የመነጨው የአማራ ህዝብ ትዕግስት ተሟጦ “ስንት ጊዜ እከዳለሁ?” ወደሚል ቁጭት ሊቀየር መቻሉ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ጫካ እያለም ሆነ ስልጣን ላይ በወጣ ማግስት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሲንቀሳቀስ የነበረውን ህወሃትን አብልቶ አጠጥቶ፣ደጀን ሆኖ አዲስ አበባ ያስገባው የአማራ ህዝብ ነው፡፡የህወሃት መልስ ግን ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

ህወሃትን ከአድራጊ ፈጣሪነቱ ያነሳው የአሁኑ ለውጥ እንዲመጣም በውስጠ ፓርቲ ትግሉ ወቅት የአማራው ወኪል ነኝ የሚለው ብአዴን ያደረገው አስተዋፅኦ ከተወራው በላይ ነው፡፡አሁን የመጣው ለውጥም ህወሃት እንዳደረገው የአማራውን አስተዋፅኦ ገደል ወርውሮ የተረኝነት ልግዛ ልንዳ ባይነትን መልሶ ሊያመጣ ከዳዳው የአማራ ብሄርተኝነት ተቀጣጥሎ የሚያመጣው ወላፈን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ክፉኛ ሊጎዳ የሚችል ግፋ ካለም የሃገሪቱን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞ የሚመጣ ይሆናል፡፡ስለዚህ ኢትዮጵያን ለማዳን የሚሰራ ስራ ሁሉ መጨረሻው እኩልነትን ከማስፈን፣ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም ከመገንባት ውጭ በሌላ መንገድ መሄድ ከጀመረ ሃገር ላይ እሳት ለኩሶ መልቀቅ እንደሆነ ሊረዳ ይገባል፡፡ትክክለኛውን የእኩልነት ጉዞ ለመጓዝ፣ሃገርንም እንደጧፍ ከመንደደ ለመታደግ ምን መደረግ አለበት፣ሃገራችን ወደ ዲሞክራሲያዊ የእኩልንት መንገድ እንዳትሄድ ዋነኛ አደጋ የጋረጠውስ ማን ነው? የሚለውን ለመዳሰስ ሳምንት ልመለስ፡፡       

ማስታወሻበዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ሰኔ 29 ፤ 2011 ዓ.ም.

ጠንካራ ነኝ ማለቱ ለበጎ ያልሆነው ህወሃት የማዕከላዊ መንግስቱን መዘወሩን ካቆመ ወዲህ የመጣው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከባት ኢትዮጵያ በጉያ በጀርባዋ፣በእጅ በእግሯ፣በአፍ በሆዷ ውስብስብ ችግር አዝላ የምትጎተት ነች፡፡ይህ ችግር በድንገት በመጣው የዶ/ር አብይ መንግስት ቀርቶ በማኛውም እኔ ነኝ ባይ የምድር ጠቢብብ በአንድ አመት ውስጥ ሊፈታ አይችልም፡፡ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት እና ውዝፍነት የተነሳም ሆነ ከእርሳቸው ሰዋዊ ድክመት የተነሳ ችግር መፍታት ቢያቅታቸው እንኳን እሳቸው የሚያመጡት ተጨማሪ ችግር እንዳይኖር ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂነት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በመንግስታቸው አሰራር ላይ ጥያቄ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አላማው እሳቸውን ማጣጣል፣የጀመሩትን ጉዞ ማጨናገፍ፣ይበጃል ብለው እየሰሩ ያለውን ነገር ዋጋ ለማሳጣት ሊሆን አይችልም፡፡ይልቅስ ሃገራችን በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደመሆኗ መንግስታቸው በችግሩ አሳሳቢነት መጠን ያልተራመደ የሚመስለው ዜጋ ሊተቻቸው ይችላል፡፡ይህ አይነቱ ትችት የእሳቸውን ልፋት ገደል ለመክተት የተደረገ ክፉ ነገር አይደለም፡፡

እሳቸው ግን የሚቀርብባቸውን ትችት በበጎ ጎኑ የሚረዱት አልመሰለኝም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው ካሳዩት ሁኔታ የተረዳሁት የሃሳብ ልዩነትን እና የመንግስት ተጠያቂነትን እምብዛም እንደማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚፈትናቸው ነው፡፡የእርሳቸው ስሜታዊ መሆን ደግሞ የሚያጠፋው ብዙ ነው፡፡ወጣት መሪ መሆናቸው፣ሃገሪቱ ራስ አዟሪ ውስብስብ ችግር ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ወደስልጣን መምጣታቸው ተደማምሮ ብስጭታቸውን ሊያብሰው ይችላል፡፡ሆኖም መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ማሰቡ ለእራሳቸውም ለሃገራችንም በጎ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በግሌ ዶ/ር አብይ ውስብስብ ችግር ያዘለችውን ሃገር ሊመሩ መንበር ከጨበጡ ወዲህ ኢህአዴግ ውስጥም ኢትዮጵያ ትታየኛለች፡፡ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ በምጠረጥርበት ሃገር የማፍረስ ሴራ የዶ/ር አብይን ኢህአዴግ አልጠራጠውም፡፡ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ፡፡ህወሃት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ሲል ግን ስልጣኑን አጥብቆ እያሰረ እንደሆነ ብቻ እረዳ ነበር!ስለዚህ እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ከዶ/ር አብይ ጋር የሚያስማማው አንድ ጉዳይ አለ-የኢትዮጵያ ህልውና!

በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡ይህ መሰረታዊ አንድነት ሳይረሳ ጥፋት የጠፋ ሲመስለው የተቸ ቢያንስ ኢትዮጵያን በማለቱ ላይ ያለው ተመሳሳይ ምኞት ተረስቶ ለጥፋት የቆመ፣መተቸት ብቻ የሚያስደስተው፣የአሉባታ ሱስ ብቻ የሚያናገረው ተደርጎ በመንግስት ዘንድ የሚታሰብ ከሆነ ቀጣዩ ትዕይንት ጋዜጠኛን እና ተችን እያሳደዱ መሰር ነው የሚሆነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ በሰሞኑ የፓርላማ ውሏቸው ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ገሚሶቹ ስሜታዊ አድርገዋቸው ተችዎችን “እኛ የያዝነው እውነት ነውና ማሸነፋችን አይቀርም፤እናንተ ግን እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡ይህን ንግግራቸውን ስሰማ ዶ/ር አብይ ለትችት ያላቸውን ስስ ስሜት በደንብ ተረድቻለሁ፤ብዙ ነገርም ወደ ህሊናየ መጥቷል-ጭንቀት ጭምር! ዶ/ር አብይ የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲያገኛቸው ለፈጣሪ አሳልፈው የሰጧቸው ሚዲያዎች በውጭ ሃገር የሚገኙ፣በዩቱብ የሚሰራጩ እንደሆኑ አብረው ገልፀዋል፡፡ “ባህር ማዶ ስላላችሁ እኔ ምንም ላደርጋችሁ አልችልም” ሲሉም አክለዋል፡፡

አብይ በተችዎቻቸው ላይ የመለኮት ፍርድ እንድትመጣ የፈለጉት እነዚህ ሚዲያዎች ከእርሳቸው ግዛት ውጭ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡ይህ ንግግራቸው እና ብስጭታቸው ሚዲያዎቹ በአብይ ግዛት ቢሆኑስ ኖሮ ማስባሉ አይቀርም፡፡ከዚህመረዳት የሚቻለው ነገር በዶ/ር አብይ ግዛት ሆኖ መንግስታቸውን መተቸት እምብዛም እድሜ ያለው ፈለግ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡

ጠ/ሚው እያደር ስሜታዊነት እየታየባቸው መምጣቱ ሁለት አደጋ አዝሎ ይታየኛል፡፡ አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ ሁለተኛው በዶ/ር አብይ ዘንድ እየተተከለ የመጣ የተጠልቻለሁ ስጋት፡፡ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብይ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ሁለተኛው ችግር ሰውየው የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ያደርጋል፣ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ይቀንሳል፣በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ይህም ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ሊመራ የሚችል ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡

በበኩሌ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘቸው ሃገሬ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ ያለባት ተሰባሪ እቃ እየመሰለችኝ ከመጣች ዋል አደር ብያለሁ፡፡አሁን የቀድሞዋ የምትባለው ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ አንድ አመት በፊት የመፍረስ ምልክት ያልነበረባት መሆኗን የሰማሁ ነኝና “እንዴትም አድርገን ብንይዛት ኢትዮጵያ አትፈራርስም” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ ይልቅስ “ከአያያዝ ይቀደዳል” ባይ ነኝ! በተለይ የዘር ፖለቲካ የበላት ሃገር አትፈርስም ብሎ ከመተማመን ይልቅ ተቃራኒውን አስቦ አያያዙ ላይ ጠንክሮ መስራቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡አያያዙን ማሳመሩ የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም መንግስትን የሚዘውሩት ዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ አቋቋም ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
አብይ በቋፍ ያለችውን ሃገሬን በመሃል እጃቸው ይዘው የቆሙ ሰው ይመስሉኛል፤ሃገርን ያህክል ውድ ነገር እጃቸው ላይ ያስቀመጥንባቸውን ሰው በከንቱ ሊያስመርር ትችት ይዞ የሚመጣ አለመኖሩን ቢረዱ መልካም ነው፡፡እንዲህ ያለ ሰው አይጠፋም ከተባለም ነገሩን ንቆ የተሻለ ነገር ወደመስራቱ ማዘንበሉ ይመረጣል፡፡የጠሚው ስነ-ልቦናዊ ብርታት፣ የአስተሳሰብ ከፍታ፣እንደሚያወሩት የይቅርታ ሰውነት፣በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ነገር፣ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ቁርጠኝነት፣አለማዳላት፣የሚናገሩትን ሆኖ መገኘት በሃገሬ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነ አስባለሁ፡፡የተሳሳቱ ሲመስለኝ አካሄዳቸውን ብተችም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም እረዳለሁ፡፡በአንፃሩ ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይከለክላቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት፣ አለማድረግ ሲገባቸው ያደረጉት ነገር እንዳለም ይሰማኛል፡፡

ባፈው አንድ አመት የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚዲያቸውም ሆነ በጠመንጃቸው ያጠፉትን ጥፋት ሃይ አለማለታቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ ካድሬዎች የምስኪኖችን ቤት ያውም በክረምት እያፈረሱ ማባረራቸው እና እሳቸውም አልሰማሁም ማለታቸው ባያደርጉት ምንም የማይጎዳቸው ግን ወገባቸውን ታጥቀው የሰሩት ጥፋት ይመስለኛል፡፡ይህን ከባድ ጥፋት በሪፖርታቸው በአብዛኛው ሳይነኩት ከነኩትም አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡

በሰፊው እያነጋጋረ ያለው የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብሎ መሾምን በተመለከተ ሳይጠየቁ ራሳቸው አንስተውት “ኦሮሞ ያለአግባብ፣በማይገባው ሁኔታ ስልጣን ይዞ ከሆነ ከእኔ ጀምሮ ተጠያቂ እንደረግ” ብለዋል::መልሳቸው ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ኦሮሞ በዛ ብሎ ተሹሞ ከሆነም የሚገባውን ቦታ ነው የያዘው አይነት ሲሆን ሁለተኛው ኦሮሞ በዝቷል እየተባለ የሚባለው ነገር ከነአካቴው ውሸት ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡ አባባላቸው ኦሮሞ ብዙ ሆኖ መሾሙ ያለ አግባብ አይደለም ሲለሚገባው ነው የሚል ከሆነ የህወሃትን መጨረሻ እንዲያስቡ ከመምከር ውጭ ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡

ኦሮሞ ስልጣን ላይ በርከት ብሎ ተሹሟል የሚለው ነገር እውነት አይደለም የሚሉ ከሆነም በንግድ ባንክ የተሰገሰጉት፣በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ የበዙት፣በውትድርናው መስክም ቢሆን በስመ ምክትል ኢታማጆር ሹምነት ይዝ መምሪያዎችን ሁሉ ለጠቅልሎ መያዙን አየር ሃይሉን፣የመከላከያ ሚኒስትርነቱን፣የሃገር ውስጥ ደህንነቱን፣የጠቅላይ አቃቤህግነቱን ኦሮሞ የያዘ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምንም ችግር የለውም ብየ ስናገር መታመንን አገኛለሁ ብለው ከሆነ ይህ ከህዝብ የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ ነገር አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑትን አቶ ታከለ ዑማን የሾሙበት መንገድ ኦሮሞን ያለ አግባብ የመሾሙ ምልክት አይደለም ተብሎ ከሆነ የነገውን መፍራት ሊኖርብን ነው፡፡

በመንግስታዊ መዋቅሩ ላይ የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብለው ከመታየታቸው ባሻገር በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው እንደ ጃዋር ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚናገሩት፣የባሰባቸው ደግሞ በቪዲዮ ምስላቸውን እያሳዩ የሰው ህይወት እንሚያጠፉ የሚዝቱት እና ደግሞ ምንም የማይደረጉት፣ወደ ሃያ የሚጠጉ በንኮችን የዘረፈው የኦሮሞ ድርጅት ምንም አለመባሉ ኦሮሞ ያለ አግባብ መብት እያገኘ ስላልሆነ ከሆነ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

የህገ-መንግስት መሻሻልን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱበት መንገድ አንድም ቅንነት በጎደለው ሁለትም የችግሩን አንገብጋቢነት በማይመጥን መልኩ የተመለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ጠ/ሚ አብይ መልሳቸውን የጀመሩት “ህገ-መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሰዎች ህገ-መንግስቱ ከሚሰጣቸው መብት መጠቀማቸውን አልተውም” በሚል ንግግር ነው፡፡

በመጀመሪያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላ ህግ እንዲቀየርለት የሚጠይቅ አካል ጥያቄው ተሰምቶ ህጉ እስኪቀየር ድረስ ባለው ህግ የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ የማይፈልጉትን ህገ-መንግስት አክብረው መብቱንም የሚጠቀሙ ግዴታውንም የሚያደርጉ ሰዎች ሊመሰገኑ እንጅ ሊወቀሱ አይገባም፡፡አብይም መብትን ይጠቀማሉ ብለው ከሰሷቸው እንጅ ጠያቂዎቹ ህገመንግስቱ የጣለባቸውን ግዴታም እየተወጡ ነው፡፡ሁለተኛው እና ዋናው ነገር ህገመንግስቱ እንዲቀየር የሚጠይቁ ሰዎች ህገ-መንግሰቱ ሲረቀቅ አብረው ያላረቀቁ፣ባልተስማሙበት ህግ እንዲገዙ የተፈረደባቸው የዘር ፖለቲካው ባይትዋሮች ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት አብይ እንደሚያስቡት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ከአማራ ክልል ህዝብ በተጨማሪ ህገ-መንግስቱ የማያውቃቸው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው፣ከሁለት እና በላይ ብሄሮች የሚወለዱ ሰዎች በአጠቃላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልተስማሙበት ህግ ይገዙ ዘንድ የሚጣልባቸው ዕዳ ከየት እንደመጣ ህገ-‘መንግስቱ ጫፉ አይነካ’ የሚሉ አካላት እንዲያስረዷቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው፡፡በተረፈ ‘ህገ-መንግስቱ እኔን እና ቤቴን ስለሚያረካ አናንተ እና ቤታችሁ እኛ ባወጣነው ህገ-መንግስት ትገዙ ዘንድ የተገባ ነው’ የሚሉ አካላትን እና ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ውስጥ በአንዱ ንዑስ አንቀፅ ውስጥ እንኳን ፍላጎታቸውን እንዳያካትቱ የተፈረደባቸውን ዜጎች እኩል “ዋልታ ረገጥ” ብሎ መሰየም ቅንነት አይደለም፤ሚዛንንም ሰባራ ያደርጋል፡፡

ከሰሞኑ የሞት አጀብ አስከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ ጠ/ሚው ስሜታዊነታቸው በርትቶ፣እርግማናቸው በዝቶ አንድ ወገንን መልኣክ ሌላውን ሰይጣን የማድረግ መዛመም ታይቶባቸዋል፡፡ ወደ መልዓክት ወገን ሊያስጠጓቸው የከጀላቸውን፣በስም የጠሯቸውን ሟቾች(ዶ/ር አምባቸው እና ጀነራል ሰዓረን) የገደለውን አካል እስከመግደል ያደረሰውን ምክንያት ሁሉ በፓርላማ ውሏቸው እንዲነግሩን አይጠበቅባቸውም፡፡ሆኖም ቢያንስ ገዳዮቹን ለዚህ እርምጃ ያበቃቸው አብይ የሚሉት ክፋት፣እርኩስነት፣ፍልቅልቅ ሰው ላይ የመጨከን እርኩሰት፣ያጎረሰ እጅን የመንከስ ውለታ ቢስነት ብቻ እንደማይሆን አውቆ ላልተኛ ሁሉ የሚሰወር ነገር አይደለም፡፡በአዴፓ መሪዎች መሃል ለተከሰተው መጋደል የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ማለትም የኢህአዴግን የፓርቲ ባህል አለማወቅ ነው፡፡

በተለይ አሁን አዴፓ ሆኛለሁ ያለው ብአዴን ለንጉስ የማጎንበስን የረዥም ዘመን ታሪክን ለሚያውቅ የገዳይ እውነት አብይ ከሚሉት እጅግ የተለየ ሌላ ሊሆን እንሚችል፤ፅድቃቸው በፌደራል መንግስት በጣም የተወራላቸው ሟቾችም መታዘዛቸው ፅድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር አይከፋም፡፡በተረፈ ገዳይ ተብሎ የተብጠለጠለው ቡድንም የራሱ ቤተሰብ፣ደጋፊ ያለው ለሃገርም ይበጃል ያለውን ሊሰራ የሞከረ በመሆኑ ቢያንስ ቀብሩ መዘገብ እንደነበረበት ለፍቅር እና ይቅርታ ሰባኪው ጠ/ሚ አብይ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
በአንፃሩ በዓብይ መንግስት ድርጎ የሚሰፈርላቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሆኑ የአብይ መንግስት ፍቅር ያነሆለላቸው ወዶ ገባ የባሕር ማዶ ሚዲያዎች አስር ሰኮንድ ወስደው አብይ አምርረው የጠሏቸውን የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ቀብር መዘገብ አልፈለጉም፡፡ይህ የመረረ ጥላቻ አብይንም ሆነ ለአብይ መንግስት የሚያሸበሽቡ ሚዲያዎችን ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ድራማው ላይ ግድያውን የጀመረው ማን ነው? በዚህ ውስጥ የፌደራሉ መንግስት እጅስ የለበትም ወይ?የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል፡፡
____

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ሰኔ 29 ፤ 2011 ዓ.ም.

ጠንካራ ነኝ ማለቱ ለበጎ ያልሆነው ህወሃት የማዕከላዊ መንግስቱን መዘወሩን ካቆመ ወዲህ የመጣው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከባት ኢትዮጵያ በጉያ በጀርባዋ፣በእጅ በእግሯ፣በአፍ በሆዷ ውስብስብ ችግር አዝላ የምትጎተት ነች፡፡ይህ ችግር በድንገት በመጣው የዶ/ር አብይ መንግስት ቀርቶ በማኛውም እኔ ነኝ ባይ የምድር ጠቢብብ በአንድ አመት ውስጥ ሊፈታ አይችልም፡፡ዶ/ር አብይን እንደ መልስ ሳጥን ቆጥሮ ሁሉን በአንድ ቀን ፍታ የሚል ጤነኛ ኢትዮጵያዊም የለም፡፡

ሆኖም ከችግሩ ውስብስብነት እና ውዝፍነት የተነሳም ሆነ ከእርሳቸው ሰዋዊ ድክመት የተነሳ ችግር መፍታት ቢያቅታቸው እንኳን እሳቸው የሚያመጡት ተጨማሪ ችግር እንዳይኖር ለሚሰሩት ስራ ሁሉ ተጠያቂነት ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በመንግስታቸው አሰራር ላይ ጥያቄ የሚያነሳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አላማው እሳቸውን ማጣጣል፣የጀመሩትን ጉዞ ማጨናገፍ፣ይበጃል ብለው እየሰሩ ያለውን ነገር ዋጋ ለማሳጣት ሊሆን አይችልም፡፡ይልቅስ ሃገራችን በጣም አሳሳቢ ችግር ውስጥ እንደመሆኗ መንግስታቸው በችግሩ አሳሳቢነት መጠን ያልተራመደ የሚመስለው ዜጋ ሊተቻቸው ይችላል፡፡ይህ አይነቱ ትችት የእሳቸውን ልፋት ገደል ለመክተት የተደረገ ክፉ ነገር አይደለም፡፡

እሳቸው ግን የሚቀርብባቸውን ትችት በበጎ ጎኑ የሚረዱት አልመሰለኝም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ የፓርላማ ውሏቸው ካሳዩት ሁኔታ የተረዳሁት የሃሳብ ልዩነትን እና የመንግስት ተጠያቂነትን እምብዛም እንደማይፈልጉ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚፈትናቸው ነው፡፡የእርሳቸው ስሜታዊ መሆን ደግሞ የሚያጠፋው ብዙ ነው፡፡ወጣት መሪ መሆናቸው፣ሃገሪቱ ራስ አዟሪ ውስብስብ ችግር ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ወደስልጣን መምጣታቸው ተደማምሮ ብስጭታቸውን ሊያብሰው ይችላል፡፡ሆኖም መንግስትነት ሆደ-ሰፊነት መሆኑን ማሰቡ ለእራሳቸውም ለሃገራችንም በጎ ውጤት ይኖረዋል፡፡

በግሌ ዶ/ር አብይ ውስብስብ ችግር ያዘለችውን ሃገር ሊመሩ መንበር ከጨበጡ ወዲህ ኢህአዴግ ውስጥም ኢትዮጵያ ትታየኛለች፡፡ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ በምጠረጥርበት ሃገር የማፍረስ ሴራ የዶ/ር አብይን ኢህአዴግ አልጠራጠውም፡፡ዶ/ር አብይ “በኢትዮጵያ ህልውና ላይ አንደራደርም” ሲሉ እኔም ስለምሳሳላት ኢትዮጵያ እኔ በሚሰማኝ መጠን እየተሰማቸው እንደሚያወሩ አምናለሁ፡፡ህወሃት ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ሲል ግን ስልጣኑን አጥብቆ እያሰረ እንደሆነ ብቻ እረዳ ነበር!ስለዚህ እኔን ጨምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያን የሚወድ ዜጋ ከዶ/ር አብይ ጋር የሚያስማማው አንድ ጉዳይ አለ-የኢትዮጵያ ህልውና!

በዚህ መሰረታዊ ነገር የተስማማን ሁሉ ግን ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያን ለማዳን እርሳቸው ትክክል ነው ብለው አምነውበት በሚሄዱበት አካሄድ ሁሉ እንስማማለን ማለት አይደለም፡፡ይህ መሰረታዊ አንድነት ሳይረሳ ጥፋት የጠፋ ሲመስለው የተቸ ቢያንስ ኢትዮጵያን በማለቱ ላይ ያለው ተመሳሳይ ምኞት ተረስቶ ለጥፋት የቆመ፣መተቸት ብቻ የሚያስደስተው፣የአሉባታ ሱስ ብቻ የሚያናገረው ተደርጎ በመንግስት ዘንድ የሚታሰብ ከሆነ ቀጣዩ ትዕይንት ጋዜጠኛን እና ተችን እያሳደዱ መሰር ነው የሚሆነው፡፡

ጠ/ሚ አብይ በሰሞኑ የፓርላማ ውሏቸው ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ ገሚሶቹ ስሜታዊ አድርገዋቸው ተችዎችን “እኛ የያዝነው እውነት ነውና ማሸነፋችን አይቀርም፤እናንተ ግን እግዚአብሄር ይፍረድባችሁ” እስከማለት አድርሷቸዋል፡፡ይህን ንግግራቸውን ስሰማ ዶ/ር አብይ ለትችት ያላቸውን ስስ ስሜት በደንብ ተረድቻለሁ፤ብዙ ነገርም ወደ ህሊናየ መጥቷል-ጭንቀት ጭምር! ዶ/ር አብይ የእግዚአብሄር ፍርድ እንዲያገኛቸው ለፈጣሪ አሳልፈው የሰጧቸው ሚዲያዎች በውጭ ሃገር የሚገኙ፣በዩቱብ የሚሰራጩ እንደሆኑ አብረው ገልፀዋል፡፡ “ባህር ማዶ ስላላችሁ እኔ ምንም ላደርጋችሁ አልችልም” ሲሉም አክለዋል፡፡

አብይ በተችዎቻቸው ላይ የመለኮት ፍርድ እንድትመጣ የፈለጉት እነዚህ ሚዲያዎች ከእርሳቸው ግዛት ውጭ ስለሆኑም ጭምር ነው፡፡ይህ ንግግራቸው እና ብስጭታቸው ሚዲያዎቹ በአብይ ግዛት ቢሆኑስ ኖሮ ማስባሉ አይቀርም፡፡ከዚህመረዳት የሚቻለው ነገር በዶ/ር አብይ ግዛት ሆኖ መንግስታቸውን መተቸት እምብዛም እድሜ ያለው ፈለግ ላይሆን እንደሚችል ነው፡፡

ጠ/ሚው እያደር ስሜታዊነት እየታየባቸው መምጣቱ ሁለት አደጋ አዝሎ ይታየኛል፡፡ አንደኛው የአምባገነንነት ዋዜማ ሁለተኛው በዶ/ር አብይ ዘንድ እየተተከለ የመጣ የተጠልቻለሁ ስጋት፡፡ሁለቱም አሳሳቢ ናቸው፡፡አብይ ወደ አምባገነንነት እያዘነበሉ ከሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ አምባገነንነትን የመሸከም ትዕግስቱ ስለተመናመነ ሃገርን ክፉ ችግር ውስጥ የሚከት፣የመንን እና ሶሪያን የሚመስል የመንግስት እና የህዝብ አምባጓሮ ሊመጣ ይችላል፡፡ አብይ የተቻቸው ሁሉ የጠላቸው አድርገው የማሰባቸው ሁለተኛው ችግር ሰውየው የስነልቦና መረጋጋት እንዳይኖራቸውና የሃገሪቱን ችግር ሰከን ባለ ልቦና እንዳይፈቱ ያደርጋል፣ለህዝብ የመስራት ተነሳሽነታቸውንም ይቀንሳል፣በስነልቦና አለመረጋጋት እና ግራ መጋባት ውስጥም ሊከታቸው ይችላል፡፡ይህም ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ሊመራ የሚችል ነገር ነው፡፡ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው፡፡

በበኩሌ በብዙ ችግር ተቀስፋ የተያዘቸው ሃገሬ በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ ያለባት ተሰባሪ እቃ እየመሰለችኝ ከመጣች ዋል አደር ብያለሁ፡፡አሁን የቀድሞዋ የምትባለው ይጎዝላቪያ ከመፈራረሷ አንድ አመት በፊት የመፍረስ ምልክት ያልነበረባት መሆኗን የሰማሁ ነኝና “እንዴትም አድርገን ብንይዛት ኢትዮጵያ አትፈራርስም” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ ይልቅስ “ከአያያዝ ይቀደዳል” ባይ ነኝ! በተለይ የዘር ፖለቲካ የበላት ሃገር አትፈርስም ብሎ ከመተማመን ይልቅ ተቃራኒውን አስቦ አያያዙ ላይ ጠንክሮ መስራቱ የበለጠ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡አያያዙን ማሳመሩ የሁላችንም ሃላፊነት ቢሆንም መንግስትን የሚዘውሩት ዶ/ር አብይ ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ አቋቋም ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
አብይ በቋፍ ያለችውን ሃገሬን በመሃል እጃቸው ይዘው የቆሙ ሰው ይመስሉኛል፤ሃገርን ያህክል ውድ ነገር እጃቸው ላይ ያስቀመጥንባቸውን ሰው በከንቱ ሊያስመርር ትችት ይዞ የሚመጣ አለመኖሩን ቢረዱ መልካም ነው፡፡እንዲህ ያለ ሰው አይጠፋም ከተባለም ነገሩን ንቆ የተሻለ ነገር ወደመስራቱ ማዘንበሉ ይመረጣል፡፡የጠሚው ስነ-ልቦናዊ ብርታት፣ የአስተሳሰብ ከፍታ፣እንደሚያወሩት የይቅርታ ሰውነት፣በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ነገር፣ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ቁርጠኝነት፣አለማዳላት፣የሚናገሩትን ሆኖ መገኘት በሃገሬ ፖለቲካዊ እጣ ፋንታ ላይ የማይተካ ሚና ያለው እንደሆነ አስባለሁ፡፡የተሳሳቱ ሲመስለኝ አካሄዳቸውን ብተችም ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታም እረዳለሁ፡፡በአንፃሩ ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ የማይከለክላቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት፣ አለማድረግ ሲገባቸው ያደረጉት ነገር እንዳለም ይሰማኛል፡፡

ባፈው አንድ አመት የኦሮሞ ብሄርተኞች በሚዲያቸውም ሆነ በጠመንጃቸው ያጠፉትን ጥፋት ሃይ አለማለታቸው ሊያደርጉ ሲገባ ያላደረጉት ነገር ነው ብየ አስባለሁ፡፡የሚመሩት ፓርቲ ኦዴፓ ካድሬዎች የምስኪኖችን ቤት ያውም በክረምት እያፈረሱ ማባረራቸው እና እሳቸውም አልሰማሁም ማለታቸው ባያደርጉት ምንም የማይጎዳቸው ግን ወገባቸውን ታጥቀው የሰሩት ጥፋት ይመስለኛል፡፡ይህን ከባድ ጥፋት በሪፖርታቸው በአብዛኛው ሳይነኩት ከነኩትም አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡

በሰፊው እያነጋጋረ ያለው የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብሎ መሾምን በተመለከተ ሳይጠየቁ ራሳቸው አንስተውት “ኦሮሞ ያለአግባብ፣በማይገባው ሁኔታ ስልጣን ይዞ ከሆነ ከእኔ ጀምሮ ተጠያቂ እንደረግ” ብለዋል::መልሳቸው ሁለት ትርጉም አለው፡፡ አንደኛው ኦሮሞ በዛ ብሎ ተሹሞ ከሆነም የሚገባውን ቦታ ነው የያዘው አይነት ሲሆን ሁለተኛው ኦሮሞ በዝቷል እየተባለ የሚባለው ነገር ከነአካቴው ውሸት ነው የሚል አንድምታ አለው፡፡ አባባላቸው ኦሮሞ ብዙ ሆኖ መሾሙ ያለ አግባብ አይደለም ሲለሚገባው ነው የሚል ከሆነ የህወሃትን መጨረሻ እንዲያስቡ ከመምከር ውጭ ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡

ኦሮሞ ስልጣን ላይ በርከት ብሎ ተሹሟል የሚለው ነገር እውነት አይደለም የሚሉ ከሆነም በንግድ ባንክ የተሰገሰጉት፣በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን ላይ የበዙት፣በውትድርናው መስክም ቢሆን በስመ ምክትል ኢታማጆር ሹምነት ይዝ መምሪያዎችን ሁሉ ለጠቅልሎ መያዙን አየር ሃይሉን፣የመከላከያ ሚኒስትርነቱን፣የሃገር ውስጥ ደህንነቱን፣የጠቅላይ አቃቤህግነቱን ኦሮሞ የያዘ መሆኑ እየታወቀ ይህ ምንም ችግር የለውም ብየ ስናገር መታመንን አገኛለሁ ብለው ከሆነ ይህ ከህዝብ የሚያርቅ እንጅ የሚያቀርብ ነገር አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑትን አቶ ታከለ ዑማን የሾሙበት መንገድ ኦሮሞን ያለ አግባብ የመሾሙ ምልክት አይደለም ተብሎ ከሆነ የነገውን መፍራት ሊኖርብን ነው፡፡

በመንግስታዊ መዋቅሩ ላይ የኦሮሞ ባለስልጣናት በርከት ብለው ከመታየታቸው ባሻገር በመደበኛው የመንግስት መዋቅር ላይ ምንም ስልጣን የሌላቸው እንደ ጃዋር ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ የሚናገሩት፣የባሰባቸው ደግሞ በቪዲዮ ምስላቸውን እያሳዩ የሰው ህይወት እንሚያጠፉ የሚዝቱት እና ደግሞ ምንም የማይደረጉት፣ወደ ሃያ የሚጠጉ በንኮችን የዘረፈው የኦሮሞ ድርጅት ምንም አለመባሉ ኦሮሞ ያለ አግባብ መብት እያገኘ ስላልሆነ ከሆነ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል?

የህገ-መንግስት መሻሻልን በተመለከተ የተነሳውን ጥያቄ የመለሱበት መንገድ አንድም ቅንነት በጎደለው ሁለትም የችግሩን አንገብጋቢነት በማይመጥን መልኩ የተመለሰ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ጠ/ሚ አብይ መልሳቸውን የጀመሩት “ህገ-መንግስቱ አይወክለንም የሚሉ ሰዎች ህገ-መንግስቱ ከሚሰጣቸው መብት መጠቀማቸውን አልተውም” በሚል ንግግር ነው፡፡

በመጀመሪያ ህገ-መንግስትም ሆነ ሌላ ህግ እንዲቀየርለት የሚጠይቅ አካል ጥያቄው ተሰምቶ ህጉ እስኪቀየር ድረስ ባለው ህግ የመገዛት ግዴታ አለበት፡፡ የማይፈልጉትን ህገ-መንግስት አክብረው መብቱንም የሚጠቀሙ ግዴታውንም የሚያደርጉ ሰዎች ሊመሰገኑ እንጅ ሊወቀሱ አይገባም፡፡አብይም መብትን ይጠቀማሉ ብለው ከሰሷቸው እንጅ ጠያቂዎቹ ህገመንግስቱ የጣለባቸውን ግዴታም እየተወጡ ነው፡፡ሁለተኛው እና ዋናው ነገር ህገመንግስቱ እንዲቀየር የሚጠይቁ ሰዎች ህገ-መንግሰቱ ሲረቀቅ አብረው ያላረቀቁ፣ባልተስማሙበት ህግ እንዲገዙ የተፈረደባቸው የዘር ፖለቲካው ባይትዋሮች ናቸው፡፡

እነዚህ አካላት አብይ እንደሚያስቡት የአማራ ክልል ነዋሪዎች ብቻ አይደሉም፡፡ይልቅስ ከአማራ ክልል ህዝብ በተጨማሪ ህገ-መንግስቱ የማያውቃቸው የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች በአብዛኛው፣ከሁለት እና በላይ ብሄሮች የሚወለዱ ሰዎች በአጠቃላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልተስማሙበት ህግ ይገዙ ዘንድ የሚጣልባቸው ዕዳ ከየት እንደመጣ ህገ-‘መንግስቱ ጫፉ አይነካ’ የሚሉ አካላት እንዲያስረዷቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት የአብይ መንግስት ሃላፊነት ነው፡፡በተረፈ ‘ህገ-መንግስቱ እኔን እና ቤቴን ስለሚያረካ አናንተ እና ቤታችሁ እኛ ባወጣነው ህገ-መንግስት ትገዙ ዘንድ የተገባ ነው’ የሚሉ አካላትን እና ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ውስጥ በአንዱ ንዑስ አንቀፅ ውስጥ እንኳን ፍላጎታቸውን እንዳያካትቱ የተፈረደባቸውን ዜጎች እኩል “ዋልታ ረገጥ” ብሎ መሰየም ቅንነት አይደለም፤ሚዛንንም ሰባራ ያደርጋል፡፡

ከሰሞኑ የሞት አጀብ አስከትሎ የመጣውን ፖለቲካዊ ቀውስ አስመልክቶ የተነሳውን ጥያቄ ሲመልሱ ጠ/ሚው ስሜታዊነታቸው በርትቶ፣እርግማናቸው በዝቶ አንድ ወገንን መልኣክ ሌላውን ሰይጣን የማድረግ መዛመም ታይቶባቸዋል፡፡ ወደ መልዓክት ወገን ሊያስጠጓቸው የከጀላቸውን፣በስም የጠሯቸውን ሟቾች(ዶ/ር አምባቸው እና ጀነራል ሰዓረን) የገደለውን አካል እስከመግደል ያደረሰውን ምክንያት ሁሉ በፓርላማ ውሏቸው እንዲነግሩን አይጠበቅባቸውም፡፡ሆኖም ቢያንስ ገዳዮቹን ለዚህ እርምጃ ያበቃቸው አብይ የሚሉት ክፋት፣እርኩስነት፣ፍልቅልቅ ሰው ላይ የመጨከን እርኩሰት፣ያጎረሰ እጅን የመንከስ ውለታ ቢስነት ብቻ እንደማይሆን አውቆ ላልተኛ ሁሉ የሚሰወር ነገር አይደለም፡፡በአዴፓ መሪዎች መሃል ለተከሰተው መጋደል የፌደራል መንግስቱ እጅ የለበትም ማለትም የኢህአዴግን የፓርቲ ባህል አለማወቅ ነው፡፡

በተለይ አሁን አዴፓ ሆኛለሁ ያለው ብአዴን ለንጉስ የማጎንበስን የረዥም ዘመን ታሪክን ለሚያውቅ የገዳይ እውነት አብይ ከሚሉት እጅግ የተለየ ሌላ ሊሆን እንሚችል፤ፅድቃቸው በፌደራል መንግስት በጣም የተወራላቸው ሟቾችም መታዘዛቸው ፅድቅ ሆኖ የተቆጠረላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር አይከፋም፡፡በተረፈ ገዳይ ተብሎ የተብጠለጠለው ቡድንም የራሱ ቤተሰብ፣ደጋፊ ያለው ለሃገርም ይበጃል ያለውን ሊሰራ የሞከረ በመሆኑ ቢያንስ ቀብሩ መዘገብ እንደነበረበት ለፍቅር እና ይቅርታ ሰባኪው ጠ/ሚ አብይ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
በአንፃሩ በዓብይ መንግስት ድርጎ የሚሰፈርላቸው የሃገር ውስጥ ሚዲያዎችም ሆኑ የአብይ መንግስት ፍቅር ያነሆለላቸው ወዶ ገባ የባሕር ማዶ ሚዲያዎች አስር ሰኮንድ ወስደው አብይ አምርረው የጠሏቸውን የብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ቀብር መዘገብ አልፈለጉም፡፡ይህ የመረረ ጥላቻ አብይንም ሆነ ለአብይ መንግስት የሚያሸበሽቡ ሚዲያዎችን ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ ድራማው ላይ ግድያውን የጀመረው ማን ነው? በዚህ ውስጥ የፌደራሉ መንግስት እጅስ የለበትም ወይ?የሚለውን ጥያቄ ያጠናክራል፡፡
____

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን የሚያፍነው መንግስት ብቻ ነው?(በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ግንቦት 5 2011 ዓ.ም.

ሃገራችን ለረዥም ዘመናት በተፈራራቂ አምባገነኖች ክርን ስትደቆስ በመኖሯ ሳቢያ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት እጅጉን ተጎድቶ ኖሯል፡፡ በነዚህ አምባገነን መንግስታት ዘመን መናገር ከተቻለም የሚቻለው እነሱኑ ከነአፋኝ ማንነታቸው ለማወደስ ነው፡፡ በተቀረ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ሃሳብን መግለፅ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል፡፡አምባገነኖቹ ገዥዎቻችን አፈናን የሚያስኬዱበት መጠን፣ተችዋቻቸውን ለማሳደድ የሚሄዱበት ርቀት ብዙ ሲባልበት የኖረ ስለሆነ ያንን መደጋገም የዚህ ፅሁፍ አላማ አይደለም፡፡የዚህ ፅሁፍ አላማ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግዳሮት የሚመጣው ከመንግስት ብቻ እንዳልሆነ ከየሁት እና ካጋጠመኝ ተነስቼ ማሳየት ነው፡፡

በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከመንግስት ብቻ የሚመጣ ተግዳሮት እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡ይህ የሆነው መንግስት እስርቤት ስላለው የማይፈልገውን ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎችን ወደእስር ቤት ሲያጉር ስለሚታይ ነው፡፡ነገር ግን እስርቤት የሌላቸው፣እንደ አምባገነኑ መንግስት የፖለቲካ ስልጣን ያልያዙ አፋኞች በሃገራችን ሞልተዋል፡፡ እነዚህ አፋኞች ምናልባትም ከእነሱ የበለጠ ጉልበት ባለው አምባገነን መንግስት “ሃሳብን ስለመግለፅ መብት ሲታገሉ” ሲታሰሩ ሲፈቱ የምናያቸው፣መንግስትን በአፋኝነቱ ሲያብለጠለጥሉ የኖሩ የሚዲያ ሰዎች፣የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሃሳቡን በመግለፁ፣ጋዜጣ በማሳተሙ መንግስት ያሰረው ሁሉ ሃሳብን የመግለፅ መብት የሚያከብር፣ከአፋኙ መንግስት የሚሻል ነው ማለት አይደለም፡፡በኢትዮጵያ ፕሬስ ውስጥ በአምደኝነት በተሳተፍኩባቸው ዘመናት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት አፋኙ ህወሃት መራሹ መንግስት ብቻ እንዳልሆነ በደምብ ተረድቻለሁ፡፡ስለዚህ በሃገራችን ሃሳብን በነፃነት ስለመግለፅ መብት መከበር ምክክሮች እና ውይይቶች ሲደረጉ ራሱ ታፈንኩ የሚለው የግሉ ሚዲያ የታቀፋቸው የአፋኝነት ዝንባሌዎቹን በተመለከ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ይህ ሲደረግ ግን አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡

ከሰሞኑ በሃገራችን UNISCO ባዘጋጀው በዓል ላይም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በማፈኑ ረገድ ከመንግስት ባሻገር ድርሻ ያላቸው አካላት ጉዳይም ተነስቶ እንደተመከረበት እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ብቸኛው አፋኝ መንግስትን ብቻ አድርጎ ማቅረቡ ደግሞ ግማሽ እውነት ስለሆነ ለችግሩ ምሉዕ መፍትሄ አያመጣምና በሁሉም የአፋኝነት ድርሻ፣ዝንባሌ እና ጉልበት ባላቸው አካላት ዙሪያ መነጋገሩ ጠቃሚ ነው፡፡ስለሆነም እኔ በግሌ ያስተዋልኳቸውን፣ሃሳብን በነፃነት ከመግፅ አኳያ ከግሉ ሚዲያ ተዋናዮች በኩል የሚመጡ ተዳሮቶች ናቸው ብየ ያሰብኳቸውን ላንሳ፡፡የማነሳቸው ሃሳቦች በሁሉም የግል ሚዲያዎች ይታያሉ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡

በግለሰቦች ባለቤትንት በሚታተሙ ህትመቶች ሁኔታ የጋዜጣው ባለቤት ህወሃት በሃገሪቱ ላይ ነግሶ የሚያደርገውን አፈና ለማድረግ የሚሞክረው፣በጋዜጣው/መፅሄቱ ገፆች ላይ ይገዛ ይነዳ ዘንድ የሰሌን ዘውድ በእጆቹ ሰርቶ ለራሱ የደፋ አምባገነን ሲሆን በጋዜጣው ኤዲትርነት ወይም በሌላ ስም የተቀጠሩ ሰራተኞቹ ደግሞ የኑሮ ነገር ሆኖባቸው፣ባለቤቱ የጠላውን ሰውም ሆነ ሃሳብ የሚጠሉ፣ባለቤቱ የወደደወን ብቻ የሚወዱ “በእርስዎ መጀን” የሚሉ ሲሆኑ ያጋጥማል፡፡እነዚህ የጋዜጣ ባለቤቶች ከእነርሱ የባሰው የህወሃት መንግስት አንድ ሁለት ጊዜ እስር ቤት ስለወሰዳቸው ብቻ በቅኑ የሃገራችን ህዝብ ዘንድ የሃሳብን መግለፅ ነፃነት አርበኛ ተብለው ቁጭ ብለዋል፡፡ በተግባር ግን እስር ቤት እና ጠመንጃ ስላለው “የወርቅ” ዘውድ የደፋው አምባገነን የሚያሳድዳቸው “ባለሰሌን ዘውድ” አምባገነኖች የሆኑም አሉበት፡፡

እነዚህ ባለ ግል ፕሬስ ጋዜጠኞች አምባገነንነታቸው በምን ይገለፃል ከተባለ የመጀመሪያ ሆኖ የሚመጣው በገዛ ጋዜጣቸው ስማቸው ተጠቅሶ እንዲተቹ ፈፅሞ የማይፈቅዱ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የእነሱ ወዳጅ የሆነ ሰው ጭምር በጋዜጣቸው እንዲተች የማይፈልጉ፣ ይህንንም በግልፅ የሚናገሩ መሆናቸው ነው፡፡የጋዜጣውን ባለቤት ስም ጠቅሶ በእግረ መንገድም እንኳን ቢሆን መተቸት ንጉስ እንደ መድፈር ተቆጥሮ “ከባለ ሰሌን ዘውዱ” አምባገነን ጋር ወደ መረረ ጠብ የሚከት ነገር ሆኖ “የተደነገገባቸው” የግል የፕሬስ ውጤቶች አሉ፡፡
ከጋዜጣው ባለቤት በመቀጠል አይተቹም የሚባሉት የጋዜጣው ባለቤት ወዳጆች ደግሞ ለጋዜጣው/መፅሄቱ መቸብቸብ ላቅ ያለ አስተዋፅኦ አላቸው ተብለው የሚገመቱ፣ወይ አንዳች እርጥብ ነገር ይዘው ከጋዜጣው/መፅሄቱ ባለቤት ጋር አንድ ምንጣፍ ላይ አብረው የሚውሉ ስለሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ በግሌ ያጋጠመኝን ባነሳ በአንድ የፕሬስ ውጤት ላይ ልክ ያልመሰለኝን ነገር የፃፈ አምደኛን ለመተቸት ፅሁፍ አዘጋጅቼ ስልክ “በዚህ ጋዜጣ ላይ እንቶኔን መተቸት አይቻልም” ተብየ አውቃለሁ፡፡ እኔም ነገሩ በጣም ስላስደነገጠኝ “እንዲህ ከሆነ እናንተ ግለሰቡ አይተችም እንዳላችሁኝ ጠቅሼ ለሌላ ጋዜጣ እልከዋለሁ” ብየ ፈርጠም በማለቴ “የመጀመሪያውን ክፍል ብቻ እናስተናግዳን” ተብየ በዚሁ ወደእዛ ሚዲያ ሳልመለስ ቀርቻለሁ፡፡ ነገሩ በጣም ስለከነከኝ፣የአንድ ጋዜጣው ሰራተኛ ሰው ሃሳብ ሊሆንም ይችላል በሚል ለጋዜጣው ባለቤት ጉዳዩን አስመልክቼ ለላኩት መልዕክት መልስ ላገኝ አልቻልኩም፡፡
ሌላው በጣም የገረመኝ አጋጣሚ ደግሞ ራሳቸው ባለቤት ባልሆኑበት ጋዜጣ ላይ ጭምር ለመተቸት የማይደፈሩ፣እጅግ አስፈሪ አምባገነን የጋዜጣ ባለቤቶች እንዳሉ ያወቅኩበት አጋጣሚ ነው፡፡ይህ አጋጣሚ በአንድ መለስተኛ ስርጭት ባላት ጋዜጣ አምደኛ ሆኜ በምፅፍበት ወቅት የተከሰተ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከብዙው ፅሁፌ ውስጥ በአንድ አንቀፅ ላይ አንድ የሌላ ጋዜጣ ባለቤት በጋዜጣው ከፃፈው እና በወቅቱ ብዙ ሰው እውነት ብሎ ከወሰደው ነገር ጋር ያለኝን ልዩነት ገለፅኩ፡፡ፅሁፌን ያነበበው የጋዜጣው ባለቤት ፅሁፉን ወደማተሚያ ቤት ከመላኩ በፊት ደወለልኝ፡፡

ሃሳቤን በመግለፅ ነፃነቴ ላይ ያለኝን ጠንካራ አቋም በደንብ ስለሚያውቅ “እባክሽ ይቅርታ አድርጊልኝ፤ ከፅሁፍሽ አንድ አንቀፅ ላወጣ ነው” አለኝ፡፡”ምን ክፋት አገኘህበት? የተሳሳትኩት ነገር አለ? ማለቴ ከጥሬ ሃቅ አንፃር ልክ ያልሆነ ነገር አገኘህበት?” አልኩት፡፡ “አይደለም እንቶኔን ስሙን አንስተሽ ሃሳቡን አልቀበልም ብለሽ ያቀረብሽው ማስረጃ ስህተት ባይሆንም ለእኔ ግን ጥሩ አይደለም፤ለጋዜጣውም ህልውና ላይ ችግር ይመጣብኛል” አለኝ፡፡ “እኔ የምትለው ነገር ምንም አልገባኝም፤ እንዲህ ስለተፃፈ ከጋዜጣው ህልውና ጋር ምን አገናኘው? አንተስ እሱን ይህን ያህል የምትፈራው ለምንድን ነው? የሚያሳትምልህ እሱ ነው እንዴ?” አልኩት፡፡ “አያሳትምልኝም፤ ግን ነገሩ ብዙ ነው፣በስልክ የሚሆን አይደለም ስንገናኝ እነግርሻለሁ አሁን ቅር ሳይልሽ ሃሳቡን እንዳወጣው ፍቀጅልኝ” አለኝ፡፡ “አሁን እየጠየቅከኝ ለያው ነገር ልክ እንዳለሆነ ግን ታምናለህ? እሽ ብልህ እንኳን ይሄን አምነህ መሆን አለበት” አልኩኝ የልጁ አቀራረብ ቢያሸንፈኝም ነገሩ እያስቆጣኝ፡፡ “አዎ! ልክ አለመሆኑ ምንም አያጠያይቅ፡፡አንች አስተማሪ ስለሆንሽ እንዲህ ያለውን ነገር ላታውቂ ትችያለሽ:: እኛ አለቃችን ብዙ ነው፤ፕሬሱ ላይ ያለው ችግር መንግስት በፕሬሱ ላይ ከሚያደርገው አይተናነስም፤ሁሉንም ስትመጭ እናወራለን” ብሎኝ ስልኩን ዘጋ፡፡

ስንገናኝ የነገረኝ ነገር የግሉ ፕሬስ ተግዳሮት የመለስ ዜናዊ ክንድ ብቻ እንዳልሆነ ያረጋገጠልኝ ነገር ነው፡፡ እንደነገረኝ ከሆነ በሃገሪቱ የግል ፕሬስ ሽያጭ እና ስርጭት ላይ ሰፊ እጅ ያላቸው የተወሰኑ ስመጥር የጋዜጣ/መፅሄት ባለቤቶት የሆኑ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጋዜጣ/መፅሄት አከፋፋዮችን በእጃቸው አድርገው ከእነሱ ጋዜጣ እና መፅሄት ቀጥሎ የማንን መፅሄት ስርጭት እንደሚያሳልጡ እና የነማንን ጋዜጣ ስርጭት እንደሚያከስሙ ይነግሯቸዋል፡፡ ስለዚህ የእነሱ ስም ተጠርቶ የተተቸበትን ጋዜጣ፣ከእነርሱ ጋር በሆነ ጉዳይ የተቀያየመ ሰው የሚያሳትመውን የህትመት ውጤት ወይም ከእነርሱ ጋዜጣ በይዘቱ የተሻለ እና ውሎ አድሮ የእነርሱን ጋዜጣ ሽያጭ የሚገዳደር የመሰላቸውን የህትመት ውጤት ስርጭት አዳክመው ከገበያ እንዲወጣ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በተለይ አዳዲስ የህትመት ውጤቶችን ለመጀመር ከነዚህ ጋዜጠኞች እና አከፋፋዮች ጋር መልካም ግንኙነት መመስረት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ለዚህ ነው እንደማትወጅ ባውቅም ፅሁፍሽን ቆርጬ እንዳወጣ እንድትፈቅጅልኝ በጣም ያስቸገርኩሽ” ሲል ያስጨነቀውን ነገር አጫወተኝ፡፡

በጣም ገረመኝ፣መቀበልም አቃተኝ፡፡በተለይ ይህን ያደርጋል የተባለው ጋዜጠኛ ከሩቁ ያለው ምስል እንዲህ የወረደ ስላልሆነ፣ እኔም ከሩቅ ከሚያውቁት መሃል ስለሆንኩ የተነገረኝን እንደወረደ መቀበል አቃተኝ፡፡ የሚነግረኝ ሰው በአንድ በኩል የኔን ፅሁፍ ቆርጦ ለማውጣት በሌላ በኩል እኔንም ላለማስቆጣት የተጨነቀውን መጨነቅ አይሉት መርበትበት ሳስብ ደግሞ ነገሩ እውነትነት አያጣውም የሚል ነገር አስቤ በዝምታ መገረም ጀመርኩ፡፡በሃሳቤ መሃል አንድ ጥያቄ መጣልኝ፡፡ “አከፋፋዮቹ ግን ከያንዳንዱ ጋዜጣ ገንዘብ ያገኛሉ አይደል?” አልኩት “አዎ” አለኝ፡፡”ታዲያ በነዚህ አምባገነን ጋዜጠኞች ታዘው የጋዜጦችን ስርጭት ሲያግዱ ራሳቸውስ አይጎዱም ወይ?” አልኩት፡፡

“ይህ እንደ አፈናው አላማ ይወሰናል፡፡አታሰራጩ የሚሏቸው ጋዜጠኞች ስርጭቱ እንዲገታ የሚፈልጉት ጋዜጣ ከእነሱ ጋዜጣ የሚበልጥ ይዘት ያለው ስለመሰላቸው ከሆነ ጋዜጣው ተዳክሞ ከገበያ ሲወጣ የእነርሱ ጋዜጣ ኮፒ ይጨምራል፡፡ስለዚህ አከፋፋዮቹ ዞሮ ዞሮ ከከልካቹ ጋዜጠኞች ጋዜጦች ኮፒ ማደግ ገንዘቡን ያገኙታል፡፡የአፈናው አላማ ስለነሱ መጥፎ የፃፈን ወይም ሲፃፍ ዝም ብሎ ያሳተመ የጋዜጣ ባለቤትን ለመጉዳት ከሆነ ደግሞ እነዚህ ጋዜጠኞች የተሻለ ስርጭት ያለው ጋዜጣ/መፅሄት ስለሚኖራቸው ኪሳራውን እስከመሸፈን ሊሄዱ ይችላሉ፡፡” ሲል በጣም ያስደነገጠኝን ነገር አጫወተኝ፡፡

ይህን ጉዳይ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ነገሩ ምናልባት የአንድ ጋዜጠኛ መረዳት ሊሆን ይችላል ወይስ በእውነት ያለ ነገር ነው የሚለውን ለማጣራት በግሉ ፕሬስ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በምገናኝበት ጊዜ ጉዳዩን ማንሳቴ አልቀረም፡፡ የጠየቅኳቸው ሁሉ ሰዎች ያረጋገጡልኝ ነገር የህትመት ውጤቶች ስርጭት ጉዳይ ከአከፋፋዮች እና በመስኩ ስም ካገኙ የጋዜጣ ባለቤት ጋዜጠኞች በጎ ፈቃድ ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለው ነው፡፡ስለዚህ ስለ መናገር ነፃነት መብት መከበር ሲታሰብ ከመንግስት አንባገነንነት በተጨማሪ የነዚህ እና ሌሎች እኔ ያላነሳኋቸው ተግዳሮቶች አንፃርም ማየቱ ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በዚህ ከመንግስት እጅ ውጭ ባለው ተግዳሮት ዙሪያ ሳይንሳዊ ጥናት ቢደረግ ተጨማሪ ግኝትም አይጠፉም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ጥናቶችን አድርጎ መፍትሄ ማስቀመጡ ለመናገር ነፃነት መብት መከበር አስፈላጊ ነገር ነው፡፡

ከህትመት ሚዲያው አለፍ ስንል ሃሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት አስመልክቶ ተግዳሮት የማያጣው የብሮድካስት ሚዲያው ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ ስለብሮድካስት ሚዲያው የማነሳው ሃሳብ በሃገራችን መንግስት የሚተዳደሩ እና በሌላ ሃገር መንግስት ስር ያሉ እንደ ቪኦኤ እና የጀርመን ድምፅ (DW) ያሉ ሚዲያዎችን አይጨምርም፡፡ከነዚህ ሚዲያዎች ውጭ ያሉ በቦርድ የሚተዳደሩም ሆኑ በሌላ መንገድ የሚሰሩ የብሮድካስት ሚዲያዎች እንደ ፕሬሱ ሁሉ የግለሰቦች ረዥም እጅ ጫና ሚኖርባቸው ሚዲያዎች ቢኖሩም በእኔ ግላዊ ግምገማ የተሻለ የሃሳብ ብዝሃነት የሚያቀርቡ እና በገለልተኝነቱም ጥሩ የሚባል አቋም ያላቸው ሚዲያዎችም አይጠፉም፡፡ በግሌ ዋዜማ ራዲዮ የሃሳብ ብዝሃነት በማቅረብ፣ተዓማኒ ዜናዎችን በመስራት፣የፖለቲከዊ ሁኔታዎችን እና የግለሰብ ጋዜጠኞችን ግላዊ የአቋም ለውጥ እየተከተሉ የማይዋልሉ ጠንካራ ትንታኔዎችን በማቅረብም ሆነ በገለልተኝነቱ በኩል ጥሩ የሚባል ሚዲያ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ይህ ሚዲያ ወደ ቴሌቭዝን/ሬዲዮ አድጎ አብዛኛው ህዝብ የሚከታተለው ቢሆን መልካም ነበር፡፡

ሌላው የብሮካስት ሚዲያ ኢሳት ነው፡፡ኢሳት ህወሃትን በመታገሉ በኩል ጉልህ አስተዋፅኦ ያደረገ ሚዲያ ቢሆንም ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የፓርቲ ንብረትንነትም ስለማያጣው በገለልተኝነቱ በኩል አፍ ሞልቶ የሚያናገር ነገር የለውም፡፡ይህ ገለልተኝነት የሚያንሰው የኢሳት ተፈጥሮ አምባገነኖችን ለመታገል አማራጭ ያልነበረው ነገር ነው ቢባል እንኳን አሁን ህወሃት ከወረደ በኋላ አንፃራዊ የመናገር ነፃነት እየታየ ነው በሚባልበት ወቅት ሊቀር የሚገባው ነገር ነው፡፡ከገለልተኝነቱ በተጓዳኝ የሃሳብ ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድም ኢሳት የሚያንሰው ነገር ብዙ ነው፡፡ኢሳት ሲመሰረት የህወሃትን አምባገነንነት ለመታገል ተብሎ መመስረቱ ህወሃትን የተካን ሁሉ ብፁዕ አድርጎ ማቅረብ ማለት እንዳልሆነ ሁሉም የሚዲያው አባላት አና አካላት የተረዱ አይመስልም፡፡በመሆኑም ህወሃትን ለተካው የዶ/ር አብይ መንግስት ሆደ ቡቡነት ከማሳየት አልፎ ጥብቅና የሚሞክረው ነገር የሚያሳዩ ጋዜጠኞቹን ወደ መስመር ማስገባቱ አልሆን ብሎታል፡፡

እነዚህ በአብይ መንግስት ላይ የማጠና ሆድ ያላቸው የኢሳት ጋዜጠኞች በተለያዩ ቦታዎች ሃላፊነት ላይ የተቀመጡ ወይም ሚዲያው ሲመሰረት ጀምሮ የቆዩ በመሆናቸው ከበድ ያለ እጅ ሳይኖራቸው አልቀረም፡፡ይህ ደግሞ የሃሳብ ብዝሃነትን ለማፈን ለፈለገ ሰው አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነገሩን ለማስተካከል መስራት የሚችለው ጣቢያው ይመራበታል የሚባለው ቦርድ እና የጣቢያው ማኔጅመንት ነው፡፡እነዚህ አካላት ኢሳት ብዙ ሃሳብ የሚስተናገድበት፣የኤዲቶሪያል ነፃነነት ያለው ሚዲያ እንጅ ማንም በለጥ እና ከበድ ያለ እጅ እንዳይኖረው የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው፡፡የኤዲቶሪያል ነፃነት ባለበት ሚዲያ ደግሞ ጋዜጠኞች የኤዲቶሪያል ሃፊዎቻቸውን ሳይፈሩ፣ሳይሸማቀቁ የሃሳብ ብዝሃነት ያለውን ፕሮግራም ሰርተው ያቀርባሉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ለአድማጭ ገዝፎ የሚታይ ሚዲያውን የሚገዛው አንድ ሃሳብ አይኖርም ማለት ነው፡፡ኢሳት ግን ቀደም ካሉ ዘመናት ጀምሮ እስከ ዛሬ አንድ ገዝፎ የሚታይ ሃሳብ አንግቦ የሚራመድ ሚዲያ ነው- በፊት ህወሃትን መቃወም አሁን ደግሞ የአብይ መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ መቆም አይነት ነገር፡፡
የአብይን መንግስት በትችት እንዳይደናቀፍ ዘብ የመቆሙ የኢሳት አካሄድ በሁሉም የኢሳት ጋዜጠኞች የሚቀነቀን ባይሆንም በጣቢያው ላይ ከበድ ያለ እጅ እና ሻል ያለ ስልጣን ባላቸው ጋዜጠኞች የሚዘመር መሆኑ የጣቢያውን ገለልተኝነት ከመጉዳቱም በላይ ከህዝብ ጋርም ሊያራርቀው እየሞከረ ነው፡፡ይህ ነገር ህወሃት “ልማታዊ ጋዜጠኛ” ከሚለው ጋር መሳ የሚሆን “የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች” የሚባል ዘይቤ እንዳያመጣብን ያሰጋል፡፡የኢሳት የቲም ለማ ለውጥ ጥበቃ ጋዜጠኞች ዝንባሌ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን መጋፋቱም አልቀረም፡፡

በቅርቡ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ከጋዜጠኛ ቴድሮስ ፀጋየ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ እንዳታቀርብ በኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ መወሰኑ እና የኢሳት ቦርድም ሆነ ማኔጅመንት ከህዝብ በሰፊው ተቃውሞ የገጠመውን ይህንን ውሳኔ ማፅናቱ ህዝብ የማክበር ምልክት አይደለም፡፡የህዝብን ድምፅ ችላ ማለት የአምባገነንነት ጅማሬ ነው፡፡በተጨማሪም ይህ ነገር የኢሳት ቦርድም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ለመናገር ነፃነት ያለውን አቋም ያስገመገመበት፣ትዝብት ላይም የወደቀበት ክስተት ነው፡፡ ሁለቱ ጋዜጠኞች ያደረጉት ውይይት እንዳይቀርብ የተደረገበትን ምክንያት ለጋዜጠኛ ርዕዮት አሳውቀናል ከማለት በዘለለ ምንም አሳማኝ ነገር ለህዝብ ማቅረብ ያልቻለው የኢሳት የኢዲቶሪያል ቦርድ እቃወመዋሁ እያለ ሲያብጠለጥለው የኖረውን የአፋኙን የህወሃት መልክ እንደማያጣ ለህዝብ አሳይቷል፡፡

ፕሮግራሙ ለህዝብ እንዳይቀርብ የተደረገበት ምክንያት በግልፅ ለህዝብ እስካልተነገረ ድረስ ጉዳዩ ጋዜጠኛ ቴድሮስ የጠ/ሚ አብይን መንግስት ከመተቸቱ ጋር ተያይዞ የመጣ ጉዳይም ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ቴድሮስ አብይን ሲተች እንደ ሲሳይ አጌና ያሉ የኢሳት ጋዜጠኞችንም አብሮ መተቸቱ በኢሳት ሚዲያ ላለመስተናገዱ ምክንያት እንዳልሆነስ አጋጁ የኢዲቶሪያል ቦርድ እንዴት ማሳመን ይችላል? “ኢሳት አፈና አያውቅም” ብሎ መግለጫ ማውጣት እና አፋኝ አለመሆንን በተግባር አንድ ሁለት ብሎ ማስረዳት ይለያያሉ፡፡በበኩሌ የኢሳት ኤዲቶሪያል ቦርድ ያገደውን ፕሮግራም ያገደበትን ምክንያት ዘርዝሮ እስካላሳመነኝ ድረስ ነገሩን ከአፈና ሌላ ስም ልሰጠው አልችልም፡፡
ይህ ማለት ደግሞ ኢሳት ውስጥ በስመ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ለራሳቸው የዳንቴል ዘውድ ሰርተው የደፉ ጥቃቅን እና አነስተኛ አምባገነኖች አሉ ማለት ነው ወደሚል ጥርጣሬ ይመራል፡፡ይህን የአምባገነንነት ዝንባሌ ሃይ ማለት ያልቻለው የኢሳት ማኔጅመነትም ሆነ ቦርድ የአምባገነንነቱ ተጋሪ ነው፡፡ኢሳትን ከሚመሩ የቦርድ አባላትም ሆነ የኤዲቶሪያል ቦርድ አባላት ከሆኑ ግለሰቦች ውስጥ ለወትሮው አፈና ሊያደርጉ ቀርቶ እነሱ በተገኙበት መድረክ አፈና ይኖራል ተብሎ የማይሰቡ ሰዎች መኖራቸው አምባገነንን የተቃወመ ሁሉ ራሱ አፋኝ አይሆንም ማለት እንዳልሆነ፤አፋኙም መንግስት ብቻ እንዳልሆነ አሳይቷል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ለኦህዴድ ልጓም ከወዴት ይምጣ? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ሚያዚያ 8 ቀን 2011 ዓ .ም.

በሃገራችን ፖለቲካ ልማድ ስልጣን የያዘ አካል ያሻውን ለማድረግ የሚያግደው ነገር የለም፡፡የዚህ ምክንያቱ ስልጣንን ሊገሩ ሚችሉ የዲሞክራሲ ተቋማት አቅም አለመዳበር ነው፡፡ደርግ ያሻውን ሲገድል የኖረው፣ህወሃት እጁ የቻለውን ሁሉ ሲዘርፍ የከረመው፣አሁን ደግሞ ባለተራው ኦህዴድ ለዚሁ ልማድ እየተንደረደረ ያለው ስልጣን እንዳያባልግ ልጓም ማስገባት ስላልተቻለ ነው፡፡ስልጣንን ያለገደብ የልብን ለመስራት የመጠቀሙ ፖለቲካዊ ልምድ እንዲቀር ካልተደረገ አምባገነን እየቀያየርን በመኖሩ እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ይህ ደግሞ የምንፈልገው ነገር ስላልሆነ እንዲቀር መስራት አለብን፡፡

የስልጣን ገደብ አልቦ አድራጊ ፈጣሪነት እንዲቀር ለመስራት በመጀመሪያ በስልጣን አለመገራት የሚመጣውን ችግር ማጤን ያስፈልጋል፡፡ስልጣን ባለመገራቱ ሃገራችን ቀይሽብርን የመሰለ ዘግናኝ ሁነት አሳልፋለች፣ህወሃት በእስርቤቶች ያደረገውን ክፉ ጭካኔ፣ጆሮ የሚያስይዝ ዘረፋ፣ሃገር እስከማፍረስ የደረሰ ዘረኘነት ወለድ ብልሹ ፖለቲካ አስተናግዳለች፡፡ህወሃትን ተክቶ ስልጣን ላይ ተሰየመው ኦህዴድም በዚሁ መንገድ ለመጓዝ መንገድ ጀምሯል፡፡

ይህ ዝንባሌው በብዙ መንገድ ይገለፃል- ስልጣን ጠቅልሎ ለጎሳው ሰዎች በመስጠት፣የጎሳውን የፖለቲካ ጥቅም ለማስከበር ሃገሪቱን እንደ ሃገር መቆም ጭምር የሚጎዱ መግለጫዎች በማውጣት፣ ስለተናገረው እና ስላደረገው ድርጊት መጠየቅን በመሸሽ አንዳንዴም ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ፣የጎጡ ታጣቂዎች/ጎረምሶቸ/አክቲቪስቶች/ፖለቲከኞች ለሚያጠፉት ጥፋት ተመጣጣኝ የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ጥፋቱን ማለባበስ፣በተቃራኒው ከጎጡ ውጭ ያሉ ሰዎች ህግን ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ችኩል እና አፋኝ እርምጃዎች መውሰድ ኦህዴድ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እያዘገመ እንደሆነ ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ነገሩን አደገኛ የሚያደርገው ደግሞ ኦህዴድ እንዲህ ወደ ልጓም አልቦ ስልጣን እተየጓዘ ባለበት ወቅት ሰፊውን ህዝብ ጨምሮ በሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድ የኦህዴድ አካሄድ ወዴት እንደሆነ ለመረዳት አለመቻሉ ነው፡፡ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኦህዴድ በሚያሳየው እጅግ ተለዋዋጭ ፖለቲካዊ ሁኔታ ነው፡፡ፓርቲው ወደስልጣን ሲመጣ የጎሳ ፓርቲ መሆኑን እሰኪረሳ ድረስ ሊብራል የሚያስመስለውን ዲሞክራሲያዊነት እና እኩልነት እየደጋገመ ሲሰብክ ሰነበተ፡፡ይህን የሚያመሳክሩ ጥሩ የሚባሉ እርምጃዎችንም ወሰደ፤ለምሳሌ የሚዲያዎች መከፈት እና የእስኞች መፈታት፡፡

ይህ በመጠነኛ ተግባራዊ እርምጃ የታጀበው ብዙ ስብከቱ ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚፈልገው ሰፊውን ኢትዮጵያዊ ሃሳቡን ጥሎ ኦህዴድ/ኦዴፓን ተስፋ እንዲያደርግ አደረገው፡፡ሃገሩ ወደ ተሻለ የፖለቲካ ልማድ እልፍ እንድትል የሚፈልገው ይህ ተስፈኛ ቡድን ኦህዴድ በአደባባይ ሌላ በጓዳ ሌላ (በአማርኛ ሌላ በኦሮምኛ ሌላ)እያወራ የሚያደርገውን እጅግ አደገኛ አካሄድ ለመረዳት እና አንድ አቋም ለመያዝ ተቸግሯል፡፡በበኩሌ ይህ የሚያስቸግር ነገር መሆኑ ማብቃት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በኋላ ኦህዴድ መመዘን ያለበት በሚያደርገው ድርጊት መሆን አለበት፡፡የሚያወራው ነገርም ቢሆን ወጥነቱ መፈተሸ አለበት፡፡የንግግር ወጥ አለመሆን አፍ እና ልብ ልዩነት እንዳላቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ኦህዴድ ሰላም እና ፍቅርን በሰበከበት አፉ ድብልቅልቅ ያለ ጦርነት ሊያነሳ የሚችል ኮማንዶ መሆኑንም የሚናገር የንግግር ወጥነት የሌለው ፓርቲ ነው፡፡በዚህ ላይ የማይሰማ መስሎት በር ዘግቶ ያወራውን ወዲህ ወዲያ የማያስብል ሃቅ ሊክድ የሚፋትር ሰሚን ለመናቅም የሚሞክረው ፓርቲ ነው፡፡የተናገረውን ሊል እንዳልተናገረ ሲያስረዳን ለማመን ሞኘነት ተዘጋጅቶ መቀመጣችን ሊያበቃ ይገባል፡፡ይህን ያቆምን ጊዜ ኦህዴድ/ኦዴፓም የስልጣን ፈረሱ ላይ ልጓም እንዳለ ያስብና የሚሰራ የሚያወራውን አስቦ ይሰራል፡፡ይህ ደግሞ ለእርሱም ለእኛም የሚበጅ ነገር ነው፡፡

በኦህዴድ/ኦዴፓ የስልጣን ፈረስ ላይ ልጓም ለማስገባት እና እየሆነ ላለው የማንስማማበት የፖለቲካ አኳኋኑ ጠንከር ያለ አቋም መያዝ ያልተቻለው አብይ እና ለማ ከኦህዴድ የተለየ ለኢትዮጵያ ብሄርተኛው የሚቀርብ አቋም አላቸው ተብሎ ለእርግጠኝነት በደረሰ ሁኔታ በሰፊው በመታሰቡ ነው፡፡ይህ እሳቤ አብይ እና ለማ በተዘጋ በር ውስጥ ሆነው አንሰማም ብለው ያወሩትን ነገር ሁሉ ያወሩት፣ያወሩት ነገር ሲሰማባቸው ደግሞ ሸምጥጠው የካዱት፣አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚል መግለጫ ፈርመው የሚያወጡት፣አዲስ አበባ የህዝቦቿ መሆን አለባት በሚሉ ሃይላት ላይ ጦርነት የሚያውጁት፣አይን ያየውን በአዲስ አበባ የሚደረገውን ህገ-ወጥ የመታወቂያ እደላ ሸምጥጠው የካዱት ሁሉ በኦህዴድ/ኦዴፓ አክራሪዎች ተገደው ነው እስከማለት የሚደርስ “ለጋስ” እሳቤ ነው፡፡እሳቤው ሲቀጥል አብይ እና ለማን ከኦህዴድ ውጭ ባለው ሰው ከተደገፉ ይህን ሁሉ እንዲያደርጉ የሚያስገዱዷቸውን የኦህዴድ/ኦዴፓ አክራሪዎች አሸንፈው እነሱ የሚያምኑበትን እኛም የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ሊያመጡ ይችላሉ፤ስለዚህ ዝምብለን እንደግፋቸው ወይም በብርቱ አንተቻቸው የሚል ነው፡፡

በግሌ ይህን እሳቤ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡የመጀመሪያው ምክንያቴ አብይ እና ለማ የኬኛ ፖለቲካን ከሚያራምዱ አክራሪ ከሚባሉት ሌሎች የኦህዴድ አባላት እምብዛም የተለየ ፍላጎት ያላቸው ስለማይመስለኝ ነው፡፡ይህን የማመሳክረው ደግሞ ሁለቱ ግለሰቦች በንግግራቸው ወጥ ያለመሆናቸው፣ማድበስበስ እና ማስቀየስ የሚያበዙ፣አንዳንዴም ሰሚን ሞኝ አድረገው የሚመለከቱባቸውን ነገሮች ስለማስተውል ነው፡፡ከሁሉም በላይ ተስፈኛው ህዝብ አክራሪው ኦህዴድ አስገድዷቸው እንዳደረጉት በሚያወራላቸው ድርጊቶች ዙሪያ ጥያቄ ሲቀርብልቸው ማድረጋቸው ትክክል መሆኑን የሚናገሩበት ፈርጣማነት(ለምሳሌ ከሶማሌ ክልል የመጡ ተፈናቃዮችን አዲስ አበባ ማስፈር ስህተት እንደሌለው፣እንደውም ገጠሬን ከተሜ ለማድረግ ጥሩ እንደሆነ ጠሚው የተናገሩበት ፈርጣማነት) ወይ ደግሞ ጉዳዩን ለማድበስበስ እና ለማስቀየስ የሚጥሩት ጥረት(ለምሳሌ ጠ/ሚው የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚያሳዩት ሙልጭልጭነት፣በጌዲኦ ህዝቦች ላይ ኦነግ ያደረገውን ጥፋት ለማድበስበስ የሚያደርጉት መተጣጠፍ፣አቶ ለማ ዲሞግራፊክ ለውጥ ለማምጣት መስራታቸውን የተናገሩበትን ንግግር ያድበሰበሱበት መንገድ) ከትዝብቶቸ ውስጥ ዋነኞቹ ናቸው፡፡

የእኔ ትዝብት ስህተት ቢሆን እና አብይ እና ለማ ሁሉንም ነገር የሚያደርጉት ተገደው ነው የሚለው እሳቤ ትክክል ነው አንበል፡፡እዚህ ሰዎች ተገደው አክራሪዎቹ የሚሏቸውን ነገር እያደረጉ ሄደው ሄደው የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት እስከ ማድረግ ድረስ የደረሰ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ይህ ሁሉ ከእነሱ ፍላጎት ውጭ የሆነ፣ ተገደው ያደረጉት ነገር ነው ከተባለ የአክራሪ ተብየውን እሳቤ ተገዳድረው እነሱ በእውነት ያምኑበታል የሚባለውን የሚያደርጉት መቼ እና እንዴት ነው? ወደውም ይሁን ተገደው አክራሪው የሚላቸውን እየፈፀሙ ህጋዊ ባልሆነ ሁኔታ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ንብረት እስከማድረግ ከደረሱ ምን ቀርቶን ነው በመደገፋችን የምንቀጥለው? እንደሚባለው አብይ እና ለማ የተለየ ሃሳብ ያላቸው የዲሞክራሲ ሰዎች ቢሆኑ እንኳን ሁለት ብቻ ሆነው አእላፉን በኦሮሙማ የደቆነ የኦህዴድ ካድሬ መርታት እንዴት ይሆንላቸዋል?

የአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች የመጨረሻው ስኬት አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት ማድረግ ነው፡፡ይህን ደግሞ አብይን እና ለማ ስልጠን ላይ በሰየሙበት ሁኔታ ሊያስፈፀሙት ጠንክረው እየሰሩ ነው፡፡ከዚህ በኋላ አብይን እና ለማን የምንደግፈው አክራሪ የተባሉት አብይን እና ለማን ተክተው የሃገሪቱ መሪዎች እንዳይሆኑ ነው?አክራሪ ተብየዎቹ ስልጣን ላይ ቢዎጡስ አዲስ አበባ የእኔ ናት ከማለት በላይ፣ኦነግ በሃገር ዳርቻ እተየዟዟረ ሃገር እንዲያምስ ከመፍቀድ፣ኦሮሞ ያልሆነ ሰው በኦሮሚያ መኖሩ ጭንቅ እንዲሆንበት ከማድረግ በላይ ምን ያደርጋሉ?ምናልባት እንደ ለማ እና አብይ ሳይሆን እንደ በቀለ ገርባ ይናገሩ ይሆናል እንጅ በድርጊታቸው ብዙ ልዩነት ያለው ነገር የሚያመጡ አይመስለኝም፡፡
ዝም ብለን አብይን እና ለማን በመደገፋችን እንቀጥል፣ከረር ያለ ትችትም አንተቻቸው የሚለው አካሄድ በአብይ እና ለማ ለስላሳ አንደበት ተከልለው የልባቸውን ለሚሰሩ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ያሻቸውን እንዲያደርጉ መልካም እድል መስጠት ይመስለኛል፡፡አብይ እና ለማ የእኛ ድጋፍ ካልተለያቸውና ጊዜ በተሰጣቸው ቁጥር አሉ የሚባሉትን አክራሪዎች ሊያሸንፉ ይችላሉ የሚለው አካሄድ ለዜግነት ፖለቲካ ፈላጊው ዜጋ ከሰጥቶ መቀበል ይልቅ መሸነፍን የደገሰ መንገድ ነው፡፡ሰጥቶ መቀበል ማለት መሰረታዊ ፍላጎትን አስጠብቆ መለስተኛ ፍላጎትን ለሰላም ሲባል ትቶ ሁሉንም አሸናፊ በሚደርግ መንገድ መጓዝ ነው፡፡ መረታት ማለት ደግሞ ተገዳዳሪን ለማባበል ሲባል ዋና ፍላጎትን ሁሉ እንደዋዛ አስረክቦ ተሸንፎ መግባት ነው፡፡

አሁን የያዝነው አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችን በለማ እና አብይ በኩል እናባብል የሚለው አካሄድ የሚቀርበው ለሽንፈት እንጅ ለሰጥቶ መቀበል አይደለም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ማስረጃው አብይ እና ለማ አዲስ አበባን እስከመስጠት ድረስ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞችን ፍላጎት ለማርካት ሲሰሩ በአንፃሩ ለዜግነት ፖለቲከኛው መልካም ንግግርን ከመናገር የዘለለ ያስመዘገቡለት ድል አለመኖሩ ነው፡፡የኦሮሞ ብሄርተኞች ከፍተኛው ድል እኛ ለፍላጎታችን ይቆማሉ ባልናቸው አብይ ፊርማ አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚል መግለጫ ማስወጣታቸው ነው፡፡ በአንፃሩ የፖለቲካው የማዕዘን ራስ የሆነችውን አዲስ አበባን ቢያንስ በመግለጫ ያስረከበው የዜግነት ፖለቲካ አቀነቃኙ ጎራ የአብይ/ለማን ለጆሮው እንዲስማማ አድርገው የሚደሰኩሩትን ዲስኩር በፍላሽ ቀድቶ ከማዳመጥ የዘለለ ያገኘው ጥቅም የለም፡፡ሰርክ የሚወራለት አብይ ያደረጉት እስረኛ መፍታት እና ሚዲያ እንዲናገር የመፍቀዱ ነገር ለሁለቱም ጎራ የመጣ ቱርፋት እንጅ ለዜግነት ፖለቲካው ብቻ የወረደ በረከት አይደለም፡፡ስለዚህ የፖለቲካ ትርፍ ዲሳራ ሲሰላ የነአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ጎራው ተጨባጭ ድል ሲያስመዘግብ ለዜግነት ፖለቲካው ይህ ነው የሚባል ተግባራዊ ድል ያላመጣ ነው፡፡

የአብይ/ማን ወደስልጣ መምጣት ተከትሎ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ያስመዘገበው ድል ከህግ በላይ ሆኖ በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት ለመሆን መንደርደር ብቻ አይደለም፡፡የሃገሪቱን ዋነኛ ስልጣ በኦሮሞ መኳንንት እጅ ማስገባት፣የዜግነት ፖለቲከኛውን እግር አስሮ ለኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች እንደልባቸው እንዲሆኑ መፍቀድ(ለምሳሌ መንግስት ለሃሮምሳ ፊንፊኔ እና ለባላደራ ምክር ቤት ያለው የተለያየ እይታ፤ለኢሳት ዘገባዎች ያለው ቁጠኝነት እና ለOMN ለሚያስተላልፋቸው ፕሮግራሞች ያለው ለዘብተኝነት)፣የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች አፍራሽ ንገግሮችን ለመናገር እንኳን የሚሰማቸው የመዝናናት ስሜት እና ሌላው ላይ ሲሆን መንግስት ያለው ተቆጭነት ሁሉ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከነ አብይ/ለማ ወደስልጣን መምጣት ያተረፋቸው ትርፎቹ ናቸው፡፡

ይህ ሁሉ የማባበል ስራ መሰራቱ ሃገሪቱ ንዳትበታተን ለማድረግ ሲባል መደረግ ያለበት ትክክለኛ አካሄድ ነው የሚል በሰፊው የሚነገር ግን ደግሞ ልክ የማይመስለኝ ክርክር አለ፡፡የዚህ ክርክር ትልቁ ስህተት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፓለቲከኞችንም ሆነ ሌላ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችን እያባበሉ መኖር ይቻላል ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ይህ እሳቤ ልክ ቢሆን ኖሮ ሁለተኛው የአለም ጦርነት አይካሄድም ነበር፡፡ ልክ ስላልሆነ ሂትለር የፈለገውን ሲሰጡ የኖሩት እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የማታ ማታ ወደ ፈሩት ጦርነት መግባታቸው አልቀረም፡፡የማባበል ፖለቲካቸውም የሂትለርን ጡንቻ ማፈርጠሚያ ጊዜ ሰጥቶ ባለጋራቸውን የማይጋፉት ተራራ አደረገባችው እንጅ የረዳቸው ነገር የለም፡፡

የዘር ፖለቲካ በተፈጥሮው የማይጠረቃ ፍላጎት ያለው እሳቤ ነው፡፡የዘር ፖለቲከኛ የጠየቀውን እየሰጡ በማባበል ለመኖር መንገዱ ሲጀመር በስተመጨረሻው የራስን ፖለቲካዊ ፍላጎትም አስረክቦ በዘር ፖለቲከኛ ስር ለማደር ለመስማማት መወሰን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡መጠየቅ የማይታክተው የዘር ፖለቲከኛ የራሴ የሚውን ሁሉ ጠይቆ ካበቃ በኋላ የሌላውንም የኔ ነው ማለቱ አይቀርም፡፡በጀመርነው የኦሮሞ ብሄርተኞችን የማባበል አካሄድ አዲስ አበባ የእኔ ናት ከማለት አልፈው ወደ ወሎም፣ጎንደርም፣ራያም እያማተሩ ያሉት ለዚህ ነው፡፡በማባበል፣አብይን እና ለማን መድህን በማድረግ ይህን ማስቀረት፣ የምፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ማምጣት አንችልም፡፡

የምንፈልገውን የሰለጠነ፣እኩልነት እና ዲሞክራሲ የሰፈነበት ፖለቲካ ማምጣት የምንችለው በስልጣን ላይ ያለውን ህዴድ/አዴፓን ስልጣን በመግራት ነው፡፡ የኦዴፓን/አዴፓን ስልጣን ለመግራት ስናስብ የሚያስቸግረን አብይ/ለማ የልዩ ናቸው የሚለው ስህተት የማያጣው ስሜት ነው፡፡ይህን እሳቤ ለመቋቋም እነዚሀ ሰዎች ልዩ ቢሆኑ እንኳን ሁለት ብቻ መሆናቸውን፣ለእኛ የሚስማማንን የእኩልነት ፖለቲካ ለማራመድ ሃሳባቸውን የሚጋራ ሌላ በርከት ያለ አጋር የሌላቸው በመሆኑ ስልጣን ላይ ያለው ኦህዴድ የሚይዘው የአብዛኛውን አባል መልክ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ኦህዴድ እኛ የምንፈልገውን መልክ የያዘ ድርጅት አለመሆኑን ደግሞ ማመሳከሪያው ብዙ ነው፡፡ስለዚህ የምንፈልገውን የእኩልነት ፖለቲካ ለማምጣት ኦህዴድ ከህወሃት ከተማረውን የእበልጣለሁ ባይነት መንገድ እንዲመለስ ልጓም ሊገባለት ይገባል፡፡

ኦህዴድ ከተያያዘበት የማያዋጣ አካሄድ እንዲመለስ ልጓም የማስገባቱ ስራ በመጀመሪያ ደረጃ መምጣት ያለበት ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ነው፡፡ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ስልጣን በመነጠቁ ያኮረፈው እና ከሌላው እህት ድርጅት ኦዴፓ ጋር ክፉኛ ባለጋራነት የሚሰማው ህወሃት ለዚህ ስራ የሚሆን ተፈጥሮ ያለው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድን የመግራቱ ሃላፊነት በቀዳሚነት የመወድቀው ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ላይ ነው የሚሆነው፡፡እነዚህ ፓርቲዎች ኦህዴድን አደብ ለማስገዛት የመጀመሪያው እርምጃቸው መሆን ያለበት አጋር ፓርቲዎች ወደ አባልነት እንዲያድጉ መስራት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ፓርቲያቸው ኢህአዴግ አስቸኳይ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ጠርቶ ሃገሪቱ ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ በአራት ፓርቲዎች ብቻ የማይቻል ይልቅስ የአጋር ድርጅቶችንም ተሳትፎ የሚፈልግ ስለሆነ እነዚህ ፓርቲዎች ከአባል ፓርቲዎች እኩል ድምፅ ኖሯቸው በሃገራቸው ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጡ ማስወሰን አለባቸው፡፡ ይህን ለማድረግ የኢህአዴግ ምክርቤት (ማዕለላዊ ኮሚቴ) ጉባኤ መጠራት ካለበትም ተጠርቶ አጋር ፓርቲዎች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ የማድረጉ እንቅስቃሴ መጠናከር አለበት፡፡

የአጋር ፓርቲዎች በሙሉ ድምፅ እና ውሳኔ ሰጭነት በተገኙበት ሁኔታ የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ማዕከላዊ ኮሚቴዎች በሃገሪቱ ፀጥታ እና ደህንነት፣የህግ የበላይነት፣ታጣቂ ፓርቲዎችን አደብ በማስገዛት ጉዳይ፣በኦህዴድ በተለይ በአዲስ አበባ ላይ በሚያሳየው የአፈና አካሄድ ዙሪያ በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ አማካይነት ሂሳዊ ምክከር መደረግ አለበት፡፡ አሁን ኦህዴድ እያሳየ ያለውን አይነት በገዥነት ላይ የተቀመጠን ፓርቲ ጥፋቶች ለማረም የሚደረግ የውስጠ ፓርቲ እንቅስቃሴ መመራት ያለበት በፓርቲው ቁጥጥር ኮሚቴ እንጅ በራሱ በታራሚው ባለስልጣን ፓርቲ አይደለም፡፡

እንዲህ ያለውን መደበኛ የፓርቲ ቁጥጥር ከማካሄዱ ባሻገር የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች(አጋር የሚለው መጥፋት አለበት) ኦህዴድ እያሳየ ያለውን ህወሃትን የመተካት አምባገነናዊ አካሄድ ለመቆጣጠር የእርስበርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡የሃገር አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከተውን የኦህዴድ ኦነጋዊ ዝንባሌ በመድፈቅ ረገድ በጋራም ሆነ በተናጠል ጠንካራ አቋም መሊኖራቸው ይገባል፡፡

በዚህ ረገድ ኦዴፓ የአዲስ አበባ የእኔ ናት የሚል መግለጫውን ተከትሎ ብአዴን/አዴፓ እና ደኢህዴን ያወጡት ጠንከር ያለ መግለጫ በጥሩ ጅማሬነቱ የሚያዝ ቢሆንም በቂ ግን አይደለም፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች በሃገሪቱ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ከኦህዴድ ጋር ሆነው የህወሃትን የበላይነት ለማስወገድ የታገሉ እንደመሆናቸው አሁን እያኮበኮበ ያለውን የኦህዴድ የበላይነት ለመዋጋትም ቀዳሚዎቹ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህ የሚሆናቸውን ጉልበት ለማግኘት ሁለቱ አባል ፓርቲዎች እርስበርስ ተናበው ከመስራት ባለፈ አጋር ድርጅቶችንም ከጎናቸው አሰልፈው ሃገርን ከአስፈሪ ውድቀት፣ከእርስበርስ መተላለቅ የማዳን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ያስፈልጋል፡፡ይህን ለማድረግ የሚመሩትን ህዝብ አስተባብረው ሰላማዊ ትግሎችን በማድረግ ተገዳዳሪ ጉልበት እንዳላቸው ማሳየት ይችላሉ፡፡

ኦህዴድ/ኦዴፓ የበላይነቱን ለማስተማመን እየሰራ ያለው፣የኦሮሞ ብሄርተኞችም የፖለቲካ ጥቅማቸውን እጅግ በተለጠጠ መንገድ ለማስከበር እተራወጡ ያሉት የሃገሪቱ ብዙ ቁጥር ያለውን የኦሮሞ ህዝብን ውክለናል በማለት ነው፡፡ይህን የብዙ ነኝ ትምክህትን ለመገዳደር እና ሃገርን ከውድቀት ለማዳን ሲነጣጠሉ ንዑስ የሆኑት ሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲ ድርጅቶች በአንድ መቆም አለባቸው፡፡ እነሱ በአንድ ሲቆሙ የኦሮሞ ብሄርተኞች የብዝሃነት ትምክህት ያበቃል፡፡የኢህአደግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ይህን ማድረግ ተስኗቸው አሁን እያደረጉ እንዳሉት ኦህዴድ የሚሰራውን ዝም ብለው በማየቱ ከቀጠሉ ሃገራችን ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ ትርምስ መግባቷ አይቀርም፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች የኦህዴድን አካሄድ መግራት ከቻሉ እና በውይይት ከስህተቱ እንዲታረም ማድረግ ከቻሉ እዳ ቀለለ ማለት ነው፡፡ ካልሆነና ኦህዴድ በተያያዘው የአምባገነንነት እና የሃገርን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል ቸልተኝነት የሚቀጥል ከሆነ ሃገሪቱ የሽግግር መንግስት ወደማቋቋም እንድትሄድ ፓርቲው ፍላጎት እንዲያሳይ ግፊት የማድረግ ህጋዊ ሰውነትም አላቸው እነዚህ ፓርቲዎች፡፡እነሱ ተጠናክረው የአንድ ፓርቲውን አምባገነንነት ለመገዳደር ከሞከሩ የሃገሪቱ ህዝብም ከጎናቸው መሰለፉ አይቀርም፡፡

ከኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች በመቀጠል ኦህዴድን የማረቅ ሃላፊነት ያለው ህገ-መንግስትን የመተርጎምን ጨምሮ በርካታ የህግ ማስከበር ስልጣን ያላቸው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ፕሬዚደንት የወ/ሮ መዓዛ መስሪያ ቤት እና የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ናቸው፡፡ ኦህዴድ መራሹ መንግስት እንደ ፓርቲ የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ የሚያራምደው አቋም ህገ-መንግስቱን የሚጥስ መሆኑን ጠቅሶ ወደመስመር እንዲገባ ለማድረግ ከፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ፕሬዚደንት እና ከፌደሬሽን ምክርቤት የሚቀድም ሃላፊነት ያለው አካል የለም፡፡እነዚህ አካላት ከመነሻው ሃላፊነታቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ አዲስ አበባ የንትርክ መነሾ ሆና ቀጥላለች፡፡ይህ ንትርክ አድጎ እና ቀጥሎ ለሚያመጣው ጥፋት የወ/ሮ መዓዛ መስሪያቤትም ሆነ የፌደሬሽን ምክርቤት ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡

የኦህዴድን ስልጣን በመግራቱ ረገድ ሶስተኛው ባለድርሻ የሃገሪቱን የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በመሃል እጁ የያዘው የዲያስፖራው ማህበረሰብ ነው፡፡ሃገራችን የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ የምትልክ ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቷን ለማሟላት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የምትደገፈው በዲያስፖራው መሆኑ የማያነጋግር ሃቅ ነው፡፡ዲያስፖራው የውጭ ምንዛሬውን በመከልከልም ሆነ ተከታታይ ሰልፎችን በማድረግ በህወሃት ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ኦህዴድ የማያውቅ ስላልሆነ ዲያስፖራው ኦህዴድ እየሄደበት ያለውን አላስፈላጊ የአምባገነንነት መንገድ እንዲያቆም በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ አለበት፡፡ኦህዴድ ከህወሃት በተሻለ የህዝብ ድምፅ ሰምቶ የመስተካከል ነገር ካለው መልካም፤ ካልሆነ ግን የውጭ ምንዛሬን እስከማገድ በደረሰ ጫና ዲያስፖራው ኦህዴድ መራሹን መንግስት ማስገደድ አለበት፡

የኦህዴድን አላስፈላጊ አካሄድ በመግራት ረገድ ከሁሉም በላይ ጉልበታም የሆነው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ኦህዴድ መራሹ መንግስት የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በአንክሮ ተከታትሎ ከፍላጎቱ እና ጥቅሙ ውጭ የሆኑ፣ወደመተላለቅ ሊመሩ የሚችሉ አካሄዶቹን እንዲያርም በተለያዩ የሰላማዊ ትግል መንገዶች ትግሉን መቀጠል አለበት፡፡ ከህዝቡ ጎን ለጎን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር የሚኖሩ ታዋቂ ግለሰቦች፣ምሁራን እና የሲቪክ ማህበራትም እያደገ ያለውን የአንድ ፓርቲ የበላይነት እና ተያያዝ ጥፋቶች ለማስወገድ መንግስትን ታገስ ተመለስ ማለት አለባቸው፡፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይህን ነገር ለመስራት ተቀዳሚዎቹ ባለድርሻዎች ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ይህ ሃላፊነትም እምነትም የሚጣልበት ፓርቲ ስላልታየኝ ስለ እነሱ ምንም ማለት አልችልም፡፡

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ልጓም አልቦው የኬኛ ፖለቲካ ወዴት ያደርሰናል? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
መጋቢት 23 ቀን 2011 ዓ .ም.

ህወሃት በአምሳሉ ጠፍጥፎ ሰርቶ እስትንፋስ “እፍ” ያለባቸው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ካድሬዎች የእውቀት ራስ ህወሃት ብቻ ይመስላቸዋል፤እርሱ ከሄደበት መንገድ ውጭም ፖለቲካ የሚዘወር አይመስላቸውም፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ወዝውዞ ወዝውዞ ያዛለውን ፈጣሪ ጌታቸውን ህወሃትን ገፍትረው ለመጣል የደፈሩት የህዝብን ክንድ ተማምነው ነበር፡፡ህወሃት ከወደቀ በኋላ ስልጣን ላይ የተሰየመው ኦዴፓ ጌታው ህወሃት አይንህ ላፈር የተባለበትን ነገር ሁሉ እየደገመ ያለው ከህወሃት ውጭ አስተማሪ፣ከመለስ ዜናዊ ጥራዞች ውጭ ንባብ፣እንደው ባጠቃላይ ከህወሃት ውጭ “ትምህርት ቤት” ስለማያውቅ ነው፡፡

ብዙ ህዝብ እንወክላለን የሚሉትን የኦህዴድ ካድሬዎችን ጨምሮ ሁሉንም የኢህደዴግ ድርጅት ሰዎችን ሲዘውር የኖረው ህወሃት እንደ እውቀት ጥግ ሲያዩት ለኖሩት ለአገልጋዮቹ ሲያስተምር የኖረው አንዴ ስልጣን ላይ ከተቀመጡ እንዴት ይሉኝታ ቢስ ብልሹ ዘረኛ መሆን እንደሚቻል ነው፡፡በእህወሃት እግር ስር ቁጭ ብለው ዘረኝነት፣እብሪት፣ሃሰት፣ሼር እና ዘረፋ ሲማሩ ከነበሩ አንዱ(ኦዴፓ) በለስ ቀንቶት ስልጣን ላይ ሲወጣ እየደገመ ያለው ብቸኛው መምህሩ ህወሃት ሲያደርግ የኖረውን ነው፡፡

የተለየ ነገር ቢኖር ኦዴፓ የእበልጣለሁ ባይነቱን ስሜት እንደ ህወሃት ጊዜ ወስዶ ረጋ ባለመንገድ ማስኬድ አለመቻሉ ነው፡፡የአዴፓ ለበላይነት መራወጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ መንቀዥቀዥ የታየበት፣በይሉኝታ ቢስነቱም ህወሃትን ሊያስናፍቅ የሚቃጣው ነው፡፡ይህ ኦዴፓን በአራስ ቤት እንደሚሞት ህፃን እድሜውን ሊያሳጥር የሚችለው አካሄድ ሁሉን ነገር ለእኔ በሚለው በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ “የኬኛ ፖለቲካ” እያልኩ በምገልፀው እጅግ ብልሃት በጎደለው አካሄዱ ይታጀባል፡፡እየጎመራ የመጣው የኬኛ ፖለቲካ አዝማሚያ ለሁሉም ዜጋ እጅግ አደገኛ ነገር ይዞ ስለሚመጣ መገለጫዎቹን መመርመሩ አስፈላጊ ነውና ወደዛው ልለፍ፡፡

የ”ባንክ እና ታንክ” ቁጥጥር

የኦህዴድ መምህር ከህወሃት ለ27ዓታት የኢትዮጵያን ሁለመና በመሀል እጁ ይዞ የኖረው በክላሹ እና ከህዝብ በሚዘርፈው ገንዘብ ነበር፡፡ከህወሃት ውጭ ዓለምም፣ አስተማሪም፣ንባብም የሌላቸው የኦህዴድ ካድሬዎችም በለስላሳ ምላሳቸው የሚሉትን ብለው ህዝቡን ወከክ ካደረጉ በኋላ መንግስታቸው የፀና ሲመስላቸው ያደረጉት ባንኩን እና ታንኩን መቆጣጠር ነው፡፡ህወሃት ኢፈርትን የመሰለ የዘረፋ ኢምፓየር የገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እየዘረፈ ነበር፡፡የአሁኑ ንጉስ ኦዴፓም ተመሳሳዩን ለማድረግ የጎጡን ሰዎች ከአዋሽ ባንክ አምጥቶ በንግድ ባንክ ቁንጮ የአስፈፃሚነት ቦታዎች ከኮለኮለ እነሆ አንድ ወር ተጠጋው፡፡

ባንኩን መቆጣጠር የገዥውን ጎጥ ሰዎች እየመረጡ ቱጃር ለማድረግ አመች ነገር ነው፡፡ዘመድ ሰብሰብ ብሎ ባለስልጣን በሆነበት ባንክ ያለማስያዣም ቢሆን የብድር አግልግሎት ይቀላጠፋል፣በንግድ መሃል ኪሳራ ከመጣም “ክፈሉ” የሚል ግዳጅ የለም “የተበላሸ ብድር” ተብሎ እዳው ወደኢትዮጵያ ህዝብ ይዞራል፡፡የዘመድ በየባንኩ መኮልኮል የሚበጀው የራስን ጎጥ ለመጥቀም ብቻ አይደለም “የትምክህተኛን” ወይም የሌላን ዘር አድጋለሁ ባይ ነጋዴ ለማቀጨጭም ነው፡፡ሁሌም በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ካለ በልዩ ሁኔታ ተጎጅ አለ፡፡የራስን ጎጥ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ እና ሌሎችን የበይ ተመልካች ማድረግ ደግሞ ለጎጥ ፖለቲከኛ ትልቁ ስኬቱ ነው!

ኦዴፓ እንደ ዝንጀሮ ልጅ(የዝንጀሮ ጎረምሳ ማደጉን የሚያረጋግጠው እግሩን ከአባቱ እግር ጋር እለካ ነው ከሚባለው አባባል ጋር በሚዛመድ መልኩ) እድገቱን የሚለካው እግሩን በህወሃት ዱካ እየለካ ለመሆኑ ማስረጃው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የጎጡን ሰዎች የሰገሰገበት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡በህዝብ ሞኝነት እርግጠኛ የሆኑት ጠ/ሚኒስትሩም ይህንኑ የጎጣቸውን ሰዎች ማህበር ከሁሉም አብልጠው የሚመኩበት ኢትዮጵያዊ ተቋም እንዳደረጉት ደንቀፍ ሳያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡አርአያው ህወሃት የሆነ ሰው ሲዋሽ በምቾት ነው!ዋናው ጥያቄ ግን መከላከያን የአንድ ጎጥ ጎሬ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው የሚለው ነገር ነው፡፡መልሱም ቀላል ነው-አፈንጋጭን በሰደፍ እየነረቱ መንግስትን ለማፅናት፡፡

በዚህ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ዋና ማዘዣ አዲስ አበባ እንዲከትም አዲሱ ጌታ ኦህዴድ አዟል፡፡ይህን ተከትሎ ሶስት ሽህ አዳዲስ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊሶችም አዲስ አበባ እንዲከትሙ ተደርጓል፡፡ይህ የአንድ ዘር የወታደር ጉልበት መጠናከር የኦህዴድን አንደበት ቀይሮታል፡፡ ሰላምን በመስበክ የሰነበቱት ጠ/ሚ አብይ የኬኛ ነገር የተነካካባቸው ሲመስላቸው ቅልጥ ያለ ጦርነት ውስጥ እንደሚገቡ ከሰሞኑ ቆጣ ብለው እየተናገሩ ነው፡፡ይህ የአንደበት ለውጥ የመጣው ጦርነቱን የሚመራው ቤተ-ዘመድ መሆኑን ጠ/ሚው የሰሩትን ሰርተው ስላስተማመኑ ነው፡፡

ከዚህ የምንረዳው የኬኛ ፖለቲካ የተንተራሰው የፈጠራ ታሪክን እና የህገ-መንግስትን ተረክ ብቻ ሳይሆን የወታደር ጉልበትንም ደጀን እንዳደረገ፣በታንክም እንደሚታገዝ ነው፡፡ጠ/ሚው ከጦርነት ማስፈራሪያቸው አስከትለው የሱሉልታን እና ሆለታን ስም የጠሩት አዲስ አበባን የከበበውን ባለ ሜንጫ ቄሮ እንደ ተጨማሪ ማስፈራሪያ መጠቀማቸው ነው፡፡እነዚህን አካባቢዎች የሚመሩት ደግሞ የለውጥ አመራር የተባሉ ልሙጥ ዘረኞች መሆናቸው መረሳት የለበትም፡፡

የለውጥ አመራሮች- የንቅል ካድሬዎች ምትክ

ኦህዴድ ከህወሃት የተለየ ለመምሰል በሚሞክርበት ዘመን ፓርቲው “የለማ ቡድን” የተባሉ የለውጥ አመራሮችን መፍጠሩን ሲያወራ ከርሟል፡፡እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ሲገልጡ ደግሞ የለገጣፎዋ አረመኔ አፈናቃይ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅን፣ግራ የገባቸውን ተፈናቃዮች ሰብስባ ስትመፃደቅ የሰነበተችዋን የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ጠይባ አህመድን፣ከጎኗ ተሰይሞ በሰው ቁስል እንጨት ሲሰድ የከረመውን አቶ አዲሱ አረጋን አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ሌላዋ ግልፅ ዘረኛ እና እብሪተኛ የለውጥ አመራር ተብየ ደግሞ “በአርባ ሽዎች የሚቆጠሩ ሰዎን ባላፈናቅል ጣቴ ነው አንገቴ ይቆረጥ” ስትል በአደባባይ የምትናገር ወ/ሮ ሮዛ የተባለችው የሱሉልታ ከንቲባ ነች፡፡ ይህች ሴትዮ ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸው ሰማይ ምድር የዞረባቸውን ሰዎች ሰብስባ የኦሮሞ ቤት ተቀባ ማለት ይፈርሳል ማለት እንዳልሆነ እና ኦሮሞዎች የባዕዳንን ጦርነት መዋጋታቸውን እንዲያቆሙ ኮራ ብላ በአደባባይ የምትናገር ናዚ ነች፡፡እነዚህ የለውጥ አመራር የተባሉ ሰዎች የሚያስፈፅሙት አብይ እና ለማ በሌሉበት ብቻቸውን ያቀዱትን ዕቅድ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡
ዕቅዱ እስከ ክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ድረስ እውቅና እንዳለው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወ/ሮ ጠይባ እና አቶ አዲሱ ተፈናቃዮችን ሰብስበው የሚናገሩት እብሪት የተሞለ ንግግር ምስክር ነው፡፡ ለማ እና አብይም የእቅዱ አካል እንደሆኑ የሚጠራጠር ካለ እነዚህ የለውጥ አመራር ተብየ ዘረኞች የተሾሙት በማን ነው? የስራ ሪፖርታቸውን የሚያቀርቡትስ ለማን ነው? ብሎ ራሱን ይጠይቅ፡፡ከሁሉም በላይ አብይ እና ለማ በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚደረጉ የግፍ መፈናቀሎች ያሳዩት አልሰማሁም የሚል የፌዝ መልስ እና የምንግዴ ዝምታ፣አፈናቃይ ባለስልጣናቱም እስካሁን በስልጣናቸው ላይ መቀመጣቸው የለማ ቡድን የሚያስፈፅመው ለማ ያቀደውን እንደሆነ ምስክር ናቸው፡፡
እነዚህ አደገኛ የዘረኝነት አዝማሚያ የተሸከሙ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየዎች ህወሃት ከትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች አምጥቶ አዲስ አበባ ይሰገስጋቸው የነበሩ፣ህወሃት ካዘዛቸው ምንም ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ በተለምዶ ንቅል ካድሬ የሚባሉትን አይነት ናቸው፡፡ እንደ ህወሃት ንቅል ካድሬዎች ሁሉ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየዎች ከሚመሩት እና ከሚያፈናቀሉት ህዝብ ጋር አንዳች የቆየ ትስስር የሌላቸው ከኦሮሚያ ክልል ሌላ አካባቢዎች መጥተው የተሾሙ እንደሆኑ ነው ተጎጅዎች የሚነገሩት፡፡

እነዚህ ንቅል የለውጥ አመራሮች ከሌላ የኦሮሚያ ቦታ(ምናልባትም ገጠራማ ቦታዎች) መጥተው አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን እንዲመሩ የተደረገው የከተሜን ከዘር ትስስር የራቀ አኗኗር ስለማይረዱ በማፈናቀሉ ላይ ወደ ኋላየማይሉ መሆናቸው በለማ ቡድን ስለተፈለገ ነው፡፡ለዚህ ማስረጃው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን አቶ አዲሱ አረጋን አስከትላ ለገጣፎ ተገኝታ ወ/ሮ ሃቢባ ያደረገችው አረመኔያዊ ማፈናቀል እንዴት ህጋዊ እንደሆነ ለተጎጅዎቹ ለራሳቸው ልታስረዳ የተሟሟተችበት መንገድ ነው፡፡

እንደዚህ ከላይኛው አመራር ጥብቅና የሚቆምላቸው ንቅል የለውጥ አመራሮች የከተማ ሰው እንዴት እንደሚኖር የማያውቁ፣ጥሩ ፖለቲከኛ ማለት ጭፍን ዘረኛ የሚመስላቸው፣ብልጣብልጦቹ አለቆቻቸው የኬኛ ፖለቲካን የመሰለ አደገኛ መርዝ ጭነው ፈተው የለቀቋቸው የእውቀት ድሆች ናቸው፡፡ብልጦቹ የላይኞቹ አመራሮች ደግሞ የሚያምን ሞኝ ካገኙ ይህን የሚያደርጉት ከነሱ ቁጥጥር ውጭ የወጡ አክራሪ ዘረኞች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡በዚህ መንገድ ከኦሮሙማ አላማቸውም ሳይናጠቡ ከህዝብ ድጋፍም ሳይጎድሉ ለመጓዝ ይሞክራሉ፡፡ ይህ እስከየት እንደሚያስኬዳቸው የሚታይ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ ማስወጣት፤ኦሮሚያን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት

የኦህዴድ ንቅል የለውጥ አመራሮች የኦሮሙማ አጀንዳቸውን የሚያሳኩበት የኬኛ ፖለቲካ ዋናው አላማው ኦሮሚያን የኦሮሞዎች ብቻ ማድረግ ነው፡፡ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ የምትሆነው ደግሞ በለገጣፎ እና በሱሉልታ እንደተደረገው ዘር እየለዩ ኦሮሞ ያልሆነውን ህዝብ አፈናቅሎ ከኦሮሚያ ምድር በማስወጣት ነው፡፡ መፈናቀሉ ዘር የለየ እንደሆነ የለገጣፎዋ ወ/ሮ ሃቢባም ሆነች የሱሉልታዋ ወ/ሮ ሮዛ በገዛ አንደበታቸው የተናገሩት ነው፡፡አሁን በዚህ ሰዓት ደግሞ በአርሲ እና በባሌ የተለያዩ ቦታዎች ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በተለይ አማሮች ሃገራቸውን ለቀውላቸው እንዲወጡ የሚያሳስብ እና የሚያስፈራራ ወረቀት በየ”ባዕዳኑ” በር ላይ እየተለጠፈ እንደሆነ እማኞች እየተናገሩ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ከአርሲ እና ባሌ እንዲወጡ የተጠየቁት እንደ ሱሉልታ እና ለገጠፎዎች ህገወጥ ቤት ሰርታችኋል የሚል አስመሳይ ምክንያት እንኳን ሳይነገራቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የኬኛ ፖለቲካ መዳረሻው ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ማፅዳት እንደሆነ ነው፡፡

ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች ብሎ ሰፊ እና ለም ክልልን ለኬኛ ፖለቲከኞች ብቻ የሸለመው የህወሃት ህገ-መንግስት ይህ ክልል ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመፍለሱ በፊት ህዝብ እንደነበረበት ለኬኛ ፖለቲከኞች አላስረዳቸውም፡፡ከህወሃት የሚያልፍ እውቀት ያለ የማይመስላቸው የኬኛ ፖለቲከኞች ደግሞ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች የሚለውን የህወሃት ተረክ ንጥር ሃቅ፣የማይጠየቅ እውነት አድርገው ተቀብለው ሃገርን እግር በራስ የሚያደርግ ስህተት እየሰሩ ነው፡፡

አሮሚያን ለኦሮሞ ብቻ የሚሉት የኬኛ ፖለቲከኞች በአንድ በኩል ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ እሰከማስወጣት የደረሰ የቂል ሙከራ ሲያደርጉ በሌላ በኩል ኦሮሚያን ኢትዮጵያ ላይ ለማንሰራፋት የፌደራል ስልጣኑን ወረውታል፡፡ከሲቪል እስከ ወታደራዊ ስልጣን፤ከሚዲያ እስከ የፍትህ አካላት የፌደራል መንግስቱ ስልጣን በእጃቸው ነው፡፡የመንግስት ሚዲያው ኦህዴዶች ለኦሮሙማ አላማቸው የማይፈልጉትን አጀንዳ የሚያራምድ ሁነት አይዘግብም፤ለምሳሌ የአዲስ አበባ ህዝብ በባልደራስ ተሰብስቦ ዘረኝነት እና ስልጣን ተጋግዘው ካመጡበት አደጋ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ትግል መንግስት የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች በስህተት አልዘገቡም፡፡ ኦህዴድ ህገ-መንግስቱን ጥሶ በማያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ያለችው አዲስ አበባ ከተማ “የግል ንብረቴ ነች” የሚል ህገ-ወጥ መግለጫ ሲያወጣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በወንጀል ያልጠየቀው መስሪያ ቤቱ በኦህዴድ ስለሚዘወር ነው፡፡አዲስ አበባ ነዋሪዎቿ ላልሆኑ ሰዎች በገፍ መታወቂ ስታድል የአዲስ አበባ ምክር ቤት ድምፁን ያጠፋው ተጠሪነቱ (ስለ አዲስ አበባ የሚጠይቅ ጦርነት ይነሳበታል እያሉ ማስፈራራት ለጀመሩት) ለኦህዴዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነ ነው፡፡

የኬኛ ፖለቲካ መዘዘዞች

ከላይ የተጠቀሱ እና ባለፈው ሳምንት ለመጠቆም የሞከርኳቸውን አስቻይ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ ክፉኛ እየሰገረ ያለው የኬኛ ፖለቲካ ፈረስ ልጓም ካልገባለት በርካታ መዘዞችን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው፡፡ እነዚህ መዘዞች የወዲያው(Immediate) እና የረዥም ጊዜ(Long t erm)ተብለው በሰፊው ለሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፡፡ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ጥፋቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ከነዚህ ጥፋቶች አንዱ የህዝቦች መሞት፣መፈናቀል፣ መዘረፍ፣ፍትህ ማጣት ነው፡፡

የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝቦች ስቃይ፣የለገጣፎ ተፈናቃዮች፣በሱሉልታ መፈናቀል የተደገሰላቸው በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮች፣በአርሲ እና ባሌ በስጋት የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ስጋት እና እንግልት አንዱ የኬኛ ፖለቲካ መዘዝ ነው፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ብዙ ያልተነገረለት ግፍ የተከሰተው በቡርጅ እና በኮይራ ህዝቦች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የደቡብ ህዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚጎራበቱ በአገረማርያ(ቡሌ ሆራ) እና አጎራባች የኦሮሚያ መሬቶችም ይኖራሉ፡፡በተለይ በጤፍ አምራችነታቸው በአጠቃላይ በጠንካራ አራሽነታቸው ይታወቃሉ፡፡

በዚህ ምክንያት “መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ” እየተባሉ መንገላታት ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል፡፡ ከአንድ አመት በላይ መንገድ ተዘግቶባቸው ለቅንጦት ቀርቶ ቢታመሙ፣ወላድ ምጥ ቢይዛት ሆስፒታል የሚደርሱበት መንገድ የላቸውም፡፡በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ቡርጅ እና ኮይራዎች “ባለመሬት ነኝ” ባዮቹ ካድሬዎች የፈለጉትን ቢያደርጓቸው አቤት የሚሉበት አካል የለም፡፡አንድ ከአካባቢው የመጣ ኦሮሞ እንደሆነ ግን በድርጊቱ በጣም እንደሚያዝን የነገረኝ ልጅ ይህን ግፍ አጫውቶኛል፡፡አራት ጌዲኦዎች ታርደው ተጥለው በአይኑ እንዳየ እየዘገነነው ነግሮኛል፡፡የሃገር ባለቤት ነን ያሉ የኦሮሞ ጎረምሶች በቀን በብርሃን የቡርጅዎች ቤት ጣራ ላይ ወጥተው ቆርቆሮ ነቅለው ሲወስዱ ባለቤቶቹ ቡርጅዎች ቆመው ከማየት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው፤ይህንንም ሲያደርጉ እንዳየ እያዘነ ነግሮኛል፡፡”ይሄ ቡርጅ፣ኮይራ፣ጌዲኦ ላይ ለምን ተደረገ?”ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ በቡርጅ ፣ኮይራ እና ጌዲኦ ተወስኖ ይቀራል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው፡፡ዝም ከተባለ ነገ አዲስ አበባ ይመጣል፤እየመጣም ነው፡፡

ይህ የህዝቦች መፈናቀል፣የባለ ጊዜ ነኝ ባዮች ስርዓት አልበኝነት በራሱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ ለሌሎች ክልሎች ጎረምሶችም አርአያነትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ይህ ደግሞ በተጨባጭ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ፣በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የታየ ነው፡፡ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ስርዓት አልበኛ ምንም ሲደረግ ያላየ የሌላ ክልል ጎረምሳም ዘሩን የበላይ ለማድረግ “ሌሎች” በሚላቸው ላይ ተመሳሳዩን እያደረገ ሲሄድ ሃገራችንን መልሰን ላናገኛት እንችላለን፡፡
ነገሩን ከሃገር መፍረስ በመለስ እንየው ከተባለም ሃገሪቱን ለከፋ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋትል፡፡ሲንፏቅ የኖረው ኢኮኖሚያችን ጨርሶ እንዲሞት ያደርጋል፡፡የኢኮኖሚ ችግር ደግሞ ዘረኝነት የለኮሰውን የፖለቲካ እሳት ይብስ ያነደዋል፤ስርዓት አልበኝነቱን ያጎነዋል፡፡ይህ ሁሉ ተደማምሮ በሃገር ተስፋ መቁረጡን ያባብሳል፡፡ስደት መፍትሄ ይሆናል፤ የባህር ራት መሆኑ ከነበረው ብሶ ይቀጥላል፡፡ኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነም እንደ ውሻ በየቦታው ወድቆ ከመቅረት፣በየባዕድ ሃገር በረሃ ከማለቅ ውርደት ጋር ተጋምዶ ይቀጥላል፡፡

በኬኛ ፖለቲካ ምክንያት በህዝብ እና በመንግስት መሃል ወርዶ የነበረው እርቅ ይከስማል፤ጠብ እና ክርክር ከአንድ አመት እረፍት በኋላ ወደቦታው ይመለሳል፤እየተመለሰም ነው፡፡በዚህ ሳቢያ ከዲያስፖራው ይመጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ይመናመናል፤እንደ ቀድሞው በዘመቻ የሚታገድበት ጊዜም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ሃገር ውስጥ ያለው ዜጋ ስራውን እንዳያከናውን የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እግር ብረት ሆኖ ይቀይደዋል፡፡የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ያገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጥ ወደ ማጥ ይከተዋል፡፡ይህ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ተፅዕኖ የሚያመጣው ተራዛሚ ውጤት ይሆናል፡፡ ይህ ተራዛሚ ውጤት ሃገሪቱን መልሶ ወደ አለመተማመን ፖለቲካ፣ ወደተስፋ መቁረጥ እና በኋላቀር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ወደመመራት ልማዷ ይከታታል፡፡ተከባብሮ ተማምኖ መኖር ይጠፋል፡፡መብለጥን እንጅ እኩልነትን እንደ መፍትሄ የማያየው የዘር ፖለቲካ መጨረሻው ሃገር ማፍረስ ነው፡፡ በሰለጠነ ዘመን፣በነቃ ህዝብ ላይ የበላይ ሆኖ መኖርን ማሰብ፣በልብ ሌላ ይዞ በአፍ ሌላ እያወሩ ሰውን ለማመሞኘት የሚደረግ ሩጫ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን እንደይጎዝላቪያ “ነበረች” ወደ ምትባልበት ተረት ሊቀይራት ይችላል፡፡

የኬኛ ፖለቲከኞች ሁሉን ለእኔ በማለታቸው የገፉት ይህን ሁሉ ስለማያውቁ አይደለም፡፡ይልቅስ የያዛቸው የዘረኝነት አባዜ ኢትዮጵያ ፈርሳ ኦሮሚያ ልታብብ እንደምትችል ስለሚነግራቸው ነው፡፡ይህ እጅግ ስህተት ቢሆንም ተገፍቶበታል፡፡ልጓም ያልገባለት ምኞታቸው የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የአንድ ጎጥ ንብረት ለማድረግ እስከመሞከር ሄዷል፡፡ይህ ሳይታፈርበት በመግለጫ እስከመነገር ደርሷል፡፡ይህን ህገ-ወጥ እና ዘረኛ መግለጫ ፈርመው ያፀደቁት ባለ ብዙ መልኩ ጠ/ሚ አብይ ሳምንት ቆይተው ደግሞ “አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊ ሁሉነች” ማለት ጀምረዋል፡፡ይህ ኢህአዴጋዊ ተንኮል ያለበት ንግግር ነው፡፡አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው እውቅና እየሰጡ ያሉት ከኬኛ ፖለቲካቸው ጋር የማይጋጨውን የአዲስ አበባን የፌደራል ከተማ የመሆን ነጠላ ማንነት ብቻ ነው፡፡ሁለተኛውን እና እያጨቃጨቀ ያለውን፣ለኬኛ ፖለቲካቸውም ጋሬጣ የሚሆነውን አዲስ አበባ የኗሪዎቿ የመሆኗን ሃቅ ሊናገሩት አልደፈሩም፡፡

አዲስ አበባን በትክክል እና በተሟላ ሁኔታ የሚገልፃት ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብት ያላት ከተማ እንዲሁም የሁሉም ኢትዮጵያዊ መዲና የመሆኗ መንታ ማንነት ነው፡፡ራሷን በራሷ የምታስተዳድር የኗሪዎቿ ከተማ መሆኗን መግለፅ ከተማዋን በማስተዳደሩ በኩል ለኦሮሞ ከፈጣሪ የተሰጠችነች ከሚለው የኬኛ ፖለቲካ ጋር ስለሚጣረስ አብይ በዘዴ አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ይህ ማደናገሪያ ነው፡፡እውነተኛው በመግለጫ ተነግሮናል፡፡መግለጫውን ተረድቶ ሃገርን ከጥፋት ለማዳን የሚደረገውን ማድረግ ወይም የማደናገሪያውን ማደንዘዣ ተወግቶ ሃገር ሲጠፋ ማየት የሰሚው ምርጫ ነው፡፡

የኬኛ ፖለቲካ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን አላማ እንዲያሳካ እና ከተማዋን እንዲቆጣጠር መፍቀድ ለማንም ኢትዮጵያዊ የሚሆንለት ነገር አይደለም፡፡በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለውም አብይ እንዳት የሱሉልታ እና የሆለታ ኦሮሞ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርብ ርቀት ደብረብርሃን እና ቡታጅራም አሉ፡፡አዲስ አበባን የመሰለች የኢትዮጵያዊነት ምልክት ለመታደግ ሰመራም፣ጅጅጋም፣ባህርዳርም፣ድሬዳዋም፣አርባምንጭም፣ሆሳዕናም፣ወላይታ ሶዶም፣ዱረሜም፣አሶሳም፣ደብረማርቆስም ሩቅ አይደሉም፡፡በሰለጠነ ዘመን የሃገር ሩቅ የለም! በቅርብ ያለሁ እኔነኝና አርፋችሁ ተቀመጡ የሚለው ቂልነት የማያጣው ሃሳብ ይልቅስ ከተማዋን የእልቂት አምባ ያደርጋታል፡፡

አዲስ አበባ ስትታመስ የምናጣው ብዙ ነው፡፡አዲስ አበባችን ከኒውዮርክ እና ጄኔብ ቀጥላ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መዲና በመሆን ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ ከተማ ነች፡፡ይህ ክብራችን ነበር! ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፤ ይህ የሆነው እኛ በዘር መባላቱ አዳርሶን በሰራነው ስራ አይደለም- በነጋ በጠባ የምንረግማቸው አባቶቻችን ሞተው ባመጡልን ክብር የተገኘ እንጅ!የኬኛ ፖለቲካ ዝቅታ እንዲህ ላለው ለአዲስ አበባ ዓለማቀፋዊ ግዝፈት የማይመጥን የኦሮሙማ ጠባብ ጥብቆ ሊያለብስ የሚንገታገት ነው፡፡ግዙፏ፣አለማቀፏ አዲስ አበባ በዚህ ጠባብ ጥብቆ ለመግባት ትልቅነቷ አይፈቅድላትም፡፡

በጠባቡ ጥብቆው እንድትገባ የሚደረገው አሽቆልቋይ ትግል አዲስ አበባን እጅግ ያዉካታል፤መረጋቷን ይነጥቃታል፡፡ባልተረጋጋ ከተማ ለመኖር የሚፈቅድ ዓለም ዓቀፍ ተቋም ደግሞ አይኖርም፡፡ሁሉም አንዳንድ እያለ በኬኛ ፖለቲካ የምትታመሰውን አዲስ አበበን እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ይሄኔ የአፍሪካ መዲናነት ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ይህን ክብር ለማግኘት ሌት ተቀን ሲሰሩ የኖሩ የአፍሪካ ሃገራት መባላታችንን ጠቅሰው የአፍሪካ መዲናነት ወደሚመጥነው ከተማ እንዲያቀና ይከራከራሉ፡፡ያኔ ምን እንደምናወራ አላውቅም!የሜንጫ እና የዱላ ትርኢት በሚታይበት፣በገዛ ጠ/ሚኒስትር ጦርነት በሚታወጅበት ከተማ መኖር አለባችሁ ብሎ ማስገደድ ይቻላል? ላስገድድ ቢባልስ ማን ይሰማል? ስለዚህ የኬኛ ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችንን ሊነጥቀን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪካዊ፣ዲፕሎማሲያዊ፣ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ውርደት ያመጣል፡፡ከዚህ ውርደት ለመዳን ኦህዴድ ሃይ መባል አለበት፡፡እንዴት? ለሚለው ሌላ ቀጠሮ ልያዝ::
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የ”ኬኛ” ፖለቲካ እንዴት ያሰልፋል? (በመስከረም አበራ)

ByAdmi

በመስከረም አበራ
መጋቢት 15 2011 ዓ.ም.

ኦህዴድ ወደ ስለጣን በመጣ ማግስት የሚያደርጋቸው ድርጊቶች “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው”ያስባለው የስልጣን ጥም አላማው የኦሮሞ የበላይነትን ማስፈን እንደሆነ የሚያስረዱ ናቸው፡፡የኦሮሞ የበላይነት ፖለቲካ ደግሞ ሊያሳካቸው ከሚፈልጋቸው ዋና ነገሮች አንዱ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት እና የጨፌ ኦሮሚያ ግዙ ማድረግ ነው፡፡በህገ-መንግስቱ የኦሮሚያ ግዛት አካልም ሆነ የጨፌ ኦሮሚያ ተዳዳሪ ያልሆነችውን አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት የማድረጉ የኦነግ/ኦዴፓ ህልም የሚታለመው ህገ-መንግስቱ አንድም አረፍተነገሩ እንዳይነካ በሜንጫ በሚያስፈራሩ ወገኖች መሆኑ ነገሩን ግራ ያደርገዋል፡፡

የህገ-መንግስቱ አንድም መስመር ሳይነካ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ግዛት፣ የጨፌ ኦሮሚያ ተገዥ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ ኦዴፓ/ኦህዴድ አስቻይ አድርጎ የያዘው መንገድ የፌደራል ስልጣን የመጨበጡን መልካም እድል፣የቆየውን የተበድየ ተረክ ፣የኢህአዴግን የፓርቲ አወቃቀር እና አሰራር (የአጋር/አባል ፓርቲ ነገር) ሊሆን ይችላል፡፡ህወሃት ሊወድቅ ሲንገዳገድ ኦህዴድን አባይ ማዶ ድረስ ያበረረው የስልጣን አምሮት ምንጩ ስልጣን መያዝ የልብን ለመስራት ቁልፍ ነገር እንደሆነ በአቶ መለስ ህወሃት ስለተማረ ሳይሆን አልቀረም፡፡

አቶ መለስ ስልጣን ላይ መቀመጣቸው በዘረፋ ሳይቀር የወገንን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዳስቻላቸው ኦህዴድ በደንብ ተገንዝቧል፡፡ስለዚህ አይገቡ ገብቶ፣አያወሩ አውርቶ፣የማይከበር ቃል ገብቶ ስልጣን ላይ ተሰየመ፡፡ከዛ በኋላ ኦነግ ሲያምረው የቀረውን ነገር ሁሉ በአንድ ጀምበር ለማከወን በከፍተኛ መራወጥ ላይ ይገኛል፡፡ይህ ነገር ይሰምራል ወይ? የዛሬዋ ኢትዮጵያም ሆነች የዛሬው ኢህአዴግ አቶ መለስ እንደነበሩባቸው ዘመናት ያሉ ናቸው ወይ? የሚለውን ነገር ኦህዴድ በቅጡ የመረመረ አልመሰለኝም፡፡የሆነ ሆኖ ኦዴፓ/ኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካውን ለማሳካት ሲንቀሳቀስ የሚያግዙትም ሆኑ የሚያደናቅፉት እውነታዎች አይጠፉም፡፡ አነዚህን እውነታዎች መመርመሩ አስፈላጊ ነውና ለለኬኛ ፖለቲካ አስቻይ መሰረቶችን በማየቱ እንጀምር፡፡

የተበድየ ተረክ

በሃገራችን የተንሰራፋው የዘውግ ፖለቲካ የትግሉ መነሻ በደልን መተረክ ሲሆን መዳረሻው ደግሞ አይኑ የወደደውን ሁሉ “የእኔ ነው” የማለት አካሄድ ነው፡፡አይን የወደደውን የራስ ለማድረግ ደግሞ የተበድየ ፖለቲካን መተረክ ዋነኛው የስኬት መንገድ ተደርጎ ተወስዷል፡፡እያጋነኑም እየፈጠሩም በደልን ማውራት ሁለት ጥቅም አለው፡፡አንደኛ የዘውግ መሰሎችን በቁጭት ለማነሳሳት ይረዳል፡፡በዘውጉ ምክንያት ብቻ እንደተጨቆነ የሚተርክ የበደል ተረክ የተጋተ ወጣት ቀረቶ ማንኛውም ሰው ግራቀኝ ሳያይ በቀላሉ ወደመሩት ይሄዳል፡፡ ሁለተኛው ጥቅም በበዳይነት የሚከሰሰው አካል አንገቱን እንዲደፋ እና ነገሮች ሁሉ ተበዳይ ነን ባዮች እንደፈለጉ እንዲሆን ይረዳል፡፡

በእኛ ሃገር ሁኔታ የተበድየ ፖለቲካን በማቀንቀን የኦሮሞ እና የትግሬ ልሂቃንን የሚወዳደር የለም፡፡እነዚህ ልሂቃን በደለን የሚሉት ደግሞ የአማራ ብሄርን ነው፡፡ይህ ምስስሎሽ የትግሬን እና የኦሮሞ ልሂቃንን ከልብ የሚያስተሳስር እውነተኛ እምነታቸው ነው፡፡የኦሮሞ ልሂቃን የራባቸውን ስልጣን ለማግኘት በለማ ቡድን በኩል ከአማራው ብአዴን ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ይህን ተረክ ቀየር አድርገውት የነበረ ቢሆንም ነገሩ ከልብ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡አማራን በዳይ አድርጎ የሚያቀርቡ የሁለቱ ብሄሮች ልሂቃን አማራ ወደ ስልጣን እንዳይመጣ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ይጠብቃሉ፡፡አማራው ተጠናክሮ ወደ ስልጣን የመጣ ከመሰላቸው የተጣሉ የሚመስሉት የትግሬ እና የኦሮሞ ልሂቃን ተመልሰው ግንባር ፈጠረው አማራውን ወደ ከረመበት ድብታ ለመክተት እንደሚተባበሩ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡ይህን ለማድረግ ደግሞ የአማራን ጭራቅነት ሲሰብኳቸው የኖሩትን የሌሎችን ብሄረሰቦች ካድሬዎች በተከታይነት መጥራታቸው የማይቀር ጉዳይ ነው፡፡

ህወሃት ሲመራው በኖረው የሃያ ሰባት አመት አስተዳደር አማራው አንገቱን ደፍቶ የኖረው ሲተረክ በኖረው የተበድየ ተረክ ነው፡፡ይህን ተረክ የበአዴን አመራሮችም ተቀብለውት ኖረዋል፡፡የዚህ ምክንያቱ አማራው ጊዜው ያለፈበት በዳይ ተደርጎ ይቆጠር ስለነበረ የብአዴን መኳንንትም ሆኑ ተራው አማራ በበዳይነት ሃፍረት ተሸማቀው ኖረዋል፡፡ይህ ተረክ አማራውን ወክለናል የሚሉት የብአዴን ባለስልጣናት የህዝባቸውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሙግት አንስተው እንዳይከራከሩ ከልክሏል፡፡

በሃሰት የበዳይነት ተረክ ጨቋኝ ተደርጎ ፕሮፖጋንዳ ሲደለቅበት የኖረው የአማራ ህዝብን በህይወት የመኖር መብትን ጨምሮ ሌሎች መብትን የማስከበር ጥያቄ ሲያነሳ ድሮ በለመደው ጨቋኝነት፣ጨፍላቂነት፣አሃዳዊነት ለመግዛት ፈልጎ የሚንቀሳቀስ እንጅ የእውነት ተቸግሮ መብቱን/ህልውናውን ለማስከበር ያነሳው ጥያቄ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ይህ ነገር አሁንም እንዳልቀረ ሰሞኑን ኦዴፓ/ኦህዴድ የአዲስ አበባ ባለቤትነቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ “ድሮ በለመዱት አካሄድ ….” በሚለው ሃረግ ላይ በግልፅ ይታያል፡፡

ይህ መግለጫ የተፃፈው አዴፓ/ብአዴን ትቂት ቀናት ቀደም ብሎ አዲስ አበባን አስመልክቶ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች ሲል ላወጣው መግለጫ መልስ እንደሆነ ከመንፈሱ መረዳት ይቻላል፡፡ሁለቱም ፓርተዎች ያወጡት መግለጫ በፓርቲዎቹ መሃከል ያለው መደማመጥ ነፋስ እየገባው እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ከሁሉም በላይ እነዚህ ፓርቲዎች ህወሃትን ለመጣል ዳርዳር ሲሉ ለሁሉም ዜጋ የምትበቃ፣የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት እንደቆረጡ ሲቀላምዱ የነበረው ቅጥፈት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ለቃኪዳኑ መፍረስ ሰበቡ ደግሞ ገበያ እንደወጣ ህፃን ሁሉን ለእኔ የሚለው ኦዴፓ/ኦህዴድ ነው፡፡

በኦነግ አስተምሮ ተፀንሶ ያደገው ኦዴፓ ስለኢትዮጵያ ሃገር ሆኖ መቆም እና በዲሞክራሲ መራመድ ግድ ይለኛል ሲል የባጀው ክፉኛ የተጠማውን ስልጣን በእጁ አድርጎ በአቶ መለስ በክርን ሲደሰቅ የኖረውን ገደብ አልባ ኦነጋዊ አምሮቱን ለማርካት ነበር፡፡ይህን በወቅቱ መጠርጠሩ አስቸጋሪ ስላልነበረ ብዙዎች በዚህ ዙሪያ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያስጠነቅቁ ነበር፡፡ሆኖም የለማ ቡድን “ጤፍ የሚቆላ” ምላስ አዋቂ፣ጠርጣራውን ሁሉ አደንዝዞት ከረመ፡፡ይህ አፈ ቂቤ ቡድን በመረጃ ዘመን ህዝቡን በምላሱ አደንዝዞ በሆዱ የያዘውን ጬቤ አውጥቶ የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል ማሰቡ ትልቁ ሞኝነቱ ነው፡፡ሆኖም የለማ ቡድን ይህን ያሳሰበው ሌሎችን ጅል አድርጎ የማሰቡ ኢህአዴጋዊ ዝንባሌ ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ ይህን ለማድረግ ያስችለኛል ብሎ እንዲያስብ ያደረገው እና ያስተማመነው አንደኛው ምክንያት የበኦነግ እና ህወሃት ተደርሶ በሁሉም የዘውግ ፖለቲከኛ ሲቀነቀን የኖረው የተበድየ ተረክ ነው፡፡

የተበድየው ተረክ አማራ ያልሆነውን የኢህአዴግ ካድሬ አማራውን ሊፈራ እንደሚገባው ጭራቅ እንዲያይ አድርጎታል፡፡ዛሬ ግንባር ፈጥረው ሃገር እንምራ ሊሉ የሞከራቸው ብአዴን እና ኦህዴድም በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር ነን እያሉም ለዘመናት የጎሪጥ ሲተያዩ የኖሩ አንደሆኑ በውስጣቸው የኖሩ ሰዎች የሚናገሩት ነው፡፡የኢህአዴግ ፓርቲዎች አማራውን እንዲጠሉ በመለስ ዜናዊ ሲጋቱ የኖሩት የጥላቻ መጠጥ በአማራው ላይ ብቻ አይወሰንም፡፡ተረኩ የኢትዮጵያን አመሰራረት ጭምር ከፈጠራው የአማራ ጨቋኘነት ጋር የሚፈተል ነው፡፡ስለሆነ እነዚህ ካድሬዎች የአማራ ጥላቻ ኢትዮጵያን ጭምር ወደ ማፍረስ ጥፋት ለመንጎድ እንዳያመነቱ አድርጓቸዋል፡፡ ህወሃት ከስልጣን ሲነሳ የአዴፓ/ብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ስልጣን ለመምጣት የአቶ ለማን ያህል ጉብ ቂጥ ያላሉት አማራው ወደ ስልጣን ከመጣ ቀሪው የኢህአዴግ ካድሬ ሀገር እስከማፍረስ የሚደርስ መሆኑን ከኖሩበት ሃቅ ስለተረዱ ነበር፡፡በዚህ ምክንያት ኦህዴድ ወደስልጣን መጥቶ ሃገር ብትተርፍ የተሻለ እንደሆነ ብአዴን ራቅ አድርጎ በማሰቡ የሆነው ሆነ፡፡

ነባሩ የኢህአዴግ የሃይል አሰላለፍ

እንደዚህ ባለ መንገድ በብዙ እልልታ ወደስልጣን የመጣው ኦዴፓ/ኦህዴድ በተግባር ሲፈተሽ የሆነው ሌላ ነው፡፡ኦዴፓ/ኦህዴድ ስላወራው ቃል ግድ ሳይለው ካወራው በተቃራኒ የኦሮሙማን አላማ ይዞ የነጎደበት ሁለተኛው ምክንያት በኢህአዴግ ውስጥ በአቶ መለስ የተበጃጀው የፖለቲካ አሰላለፍ ስልጣን ለያዘ አካል የፈለገውን ለማድረግ የሚመች መሆኑን ስለሚረዳ ነው፡፡ ይህ የሃይል አሰላለፍ በሃገሪቱ ያሉ ዜጎችን እጅግ በሚያሳፍር ሁኔታ “አባል” እና “አጋር” በሚል፣መስፈሪያው በማይታወቅ አካሄድ የአንድ ሃገር ሰዎችን አንደኛ እና ሁለተኛ ዜጋ የሚደርግ አካሄድ ነው፡፡አባል የተባሉት አራቱ ፓርቲዎች በህወሃት አዛዥነት የሃገሪቱን ፖለቲካ ሲያሾሩ ሌሎቹ አጋር ተብለው ከዋና የስልጣን ቦታዎችም ሆነ የሃገራቸውን ህልውና ከሚወስኑ ፖለቲካዊ ምክክሮች ተገልለው ኖረዋል፡፡

በእኛ ሃገር ፓርቲ መንግስትን ይመራል፡፡ፓርቲ ደግሞ በአራት አባል ፓርቲ ካድሬዎች ስራ አስፈፃሚ ውሳኔ ይዘወራል፡፡የአራቱ ፓርቲ ካድሬዎች ደግሞ ለወትሮው በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ያድራሉ፡፡በዚህ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ አጋር ፓርቲ ተብለው በየክልላቸው የኢህአዴግን ፍላጎት የሚያስፈፅሙ ሶማሌን፣ የጋምቤላን፣ የቤኒሻንልን፣ የሃራሪን፣አፋርን የሚመሩ ፓርቲዎች አይሳተፉም፡፡ይህን ድልድል ያመጣው “ብሄረሰቦችን ከአማራ እስርቤት ፈትቼ ለቀቅኩ” የሚለው የአቶ መለስ ህወሃት መራሽ አስተዳደር ነው፡፡ይህ አካሄድ ለውጥ መጣ በተባለ ማግስት የሚቀየር ነገር መስሎኝ ነበር፤ተቀጥሎበታል፡፡

የለውጥ መሪነኝ ባዩ ብልጣብልጥነት እየሞከራቸው ያለው ጠ/ሚ አብይ ያደረጉት ነገር ቢኖር በቅርቡ በተደረገ አንድ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርት ብቻ እንዲገኙ ማድረግ ነው፡፡ይህ ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡የተገኙት ሊቀመናብርትም በገዛ ሃገራቸው ጉዳይ ላይ ታዛቢ ብቻ ሆነው እንዲቀመጡ ለብቻቸው ወደተጠሩበት ስብሰባ ምን ሊሆኑ እንደሄዱ አይገባኝም፡፡ እስከዛሬ ድረስ ሁለተኝነታቸውን ተቀብለው፣በሃገራቸው አንኳር የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ሳይሳተፉ ሰው በወሰነላቸው የኖሩ የአጋር ድርጅቶች ካድሬዎችም ሁሌ የሚደንቁኝ ጉዶች ናቸው፡፡

ጠ/ሚ አብይ እነዚህን የአጋር ፓርቲዎች ሊቀመናብርተ ብቻ ወደ ስራ አስፈፃሚ የጋበዙበት ምክንያት “ይህንንም ያደረግኩላችሁ እኔ ነኝ” የሚል ውለታ ለማስቆጠር ነው፡፡ለዚህ ማስረጃው ጠ/ሚው በቅርቡ ወደ አፋር እና ሶማሌ ክልል ባመሩበት ወቅት ስንት ሚኒስትር ከአፋር እና ሱማሌ እንደሾሙ እየቆጠሩ “ተመስገን በሉ” አይነት ነገር ማውራታቸው ነው፡፡ይህስ ለምን አስገለገ ከተባለ አጭሩ መልስ በውለታ ተይዘው ለኦዴፓ/ኦነግ የኬኛ ፖለቲካ ስምረት የሚሰሩ አዳዲስ ሰራዊቶች ለመሰብሰብ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኬኛ ፖለቲካ ሳቢያ ኦዴፓ/ኦህዴድ ከአዴፓ/ብአዴን ጋር የገባበት ፍጥጫ የሚካረር ከሆነ እነዚህን አጋር ድርጅቶች ለኦሮሙማ ጥቅም በኦዴፓ/ኦህዴድ ሰልፍ ለማሰለፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ወደ አጋር ድርጅቶች መሄድ ለምን አስፈለገ የሚለውን ተገቢ ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አጋር ድርጅቶች ያስፈለጉበት ምክንያት ለወትሮው ግንባር ፈጥረው አጋር ድርጅቶችን እንምራ ሲሉ የኖሩት አራቱ አባል ድርጅቶች ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ የተወናከረ፣የድሮው አዛዥ ታዛዥ ድራማ የጠፋበት እና ግንባሩ ራሱ አለወይ በሚያስብል ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡

ኢህአዴግ የወትሮው ነው?

የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ህወሃት፣ደኢህዴን፣አዴፓ እና ኦዴፓ ናቸው፡፡ከነዚህ ውስጥ ህወሃት በስልጣን መነጠቁ ሳቢያ ያኮረፈ እና ከሚወደው ስልጣኑ የመገፍተሩ ዋነኛ ምክንያት ወትሮም የማይወደው የአማራ ልሂቃን መራሹ ብአዴን እንደሆነ ያስባል፡፡በዚህ ምክንያት ከአዴፓ/ኦዴፓ ጋር ለተቃረነ ሁሉ አላማውን ሳይጠይቅ ጭምር መወገኑ አይቀርም፡፡ስለዚህ አሁን ከአዴፓ ጋር ሽርክናውን ጨርሶ ወደ መሸካከር የሄደው ኦዴፓ/ኦህዴድ ያየውን ሁሉ የእኔ ለሚለው የልጅ አካሄዱ ጭምር ከህወሃት ጊዜያዊም ቢሆን ድጋፍ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ሆኖም ከህወሃት ጋር አጋርነት መፍጠር በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በህወሃት ዓይን የመታየት አደገኛ ውጤት ይዞ የሚመጣ መሆኑ ለኦዴፓ አይጠፋውም፡፡በዚህ ላይ የበላይ ካልሆነ የኖረ ከማይመስለው ህወሃት ጋር የሚደረግ ህብረት መጨረሻው ለኦሮሙማ የሚበጅ ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ከዚህ በፊት በኦሮሙማ ጉዳይ ላይ የነበረው የህወሃት እና የኦህዴድ ግንኙነት የሚያሳየው ነገሩ እንደማይበጅ ነው፡፡

በመቀጠል የሚመጣው የደኢህዴን ጉዳይ ነው፡፡ኦዴፓ ለሚያሳየው የኬኛ ፖለቲካ ደኢህዴን ሊመልሰው የሚችለውን መልስ መገመት አስቸጋሪ የሚያደርገው ደኢህዴን የሚመራው የደቡብ ክልል በአሁን ወቅት ያለበት ቀውስ ነው፡፡ደኢህዴን የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ ደግፎ አዲስ አበባን በጨፌ ኦሮሚያ ስር ለማድረግ ለሚያደርገው ሩጫ አጋርነቱን ካሳየ በክልሉ አዋሳ የእኔ ናት ለሚሉት የሲዳማ ፖለቲከኞች ተመሳሳዩን ማድረግ አለበት፡፡በተመሳሳይ አዲስ አበባ የእኔ ነች እያሉ መግለጫ የሚያግተለትሉት ባለጊዜ ነን ባዮቹ ኦዴፓዎች የሲዳማ ፖለቲከኞች የሚያነሱትን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ መግፋት አይችሉም፡፡አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች የሚለው ልክ ነው ብሎ መግለጫ የሚያወጣ አካል አዋሳም የሲዳማ ነች የሚለውን የሲዳማ ልሂቃ ጥያቄ የሚገፋበት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ አይችልም፡፡የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የሲዳማ ልሂቃንን የአዋሳ ባለቤትነት ጥያቄ አምርረው የሚደግፉት በዚሁ ተመሳሳይነት ሳቢያ ነው፡፡

አዋሳን የራሳቸው ለማድረግ አጥብቀው የሚሹት አቶ ሚሊዮን ማቲወስን እና አቶ ደሴ ዳልኬን የመሰሉ የሲዳማ ልሂቃ የአድራጊ ፈጠሪው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ስራ አስፈፃሚ አባላት ናቸው፡፡በሌላ በኩል ደኢህዴንን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት በጠ/ሚው ዘንድ ሞገስ ከማግኘታቸው የተነሳ የዶ/ር አብይን መንግስት 2/3ኛ ስልጣን እና ሃላፊነት የተሸከሙ ሴት ናቸው፡፡በዚህ ምክንያት የኦዴፓ/ኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ ከወደ ደቡብ በሶስቱ ሰዎች ሊደገፍ ይችላል፡፡ሌሎቹ የደኢህዴን ካድሬዎች በጉዳዩ ላይ ሊኖራቸው የሚችለው አቋም እምብዛም ወደ ኦዴፓ ያጋደለ ላይሆን ይችላል፡፡

ቀጥሎ የሚመጣው በኦዴፓ የኬኛ ፖለቲካ ላይ ጋሬጣ መሆኑን በግልፅ መግለጫ አቋሙን የገለፀው አዴፓ/ብአዴን ነው፡፡አዴፓ/ብአዴን ከሌሎች አባልም ሆነ አጋር ፓርቲዎች በተለየ የአዲስ አበባን ጉዳይ አስመልክቶ መግለጫ ያወጣውም ሆነ የኦዴፓን የኬኛ ፖለቲካ በአንክሮ የሚከታተለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ዋነኛው ምክንያት ኦዴፓ መራሹ የለውጥ መንገድ ሲጀመር ከኦዴፓ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያዊን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የማድረጉን ሃላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ ቃል መግባቱ ነው፡፡በዚህ ቃል ሳቢያ የህዝብ ተስፋ አብቦ ነበር፡፡ይህን ያበበ ተስፋ ኦዴፓ የፈለገው ፈልጎ፣የበለጠው በልጦበት ገደል ስለከተተው አዴፓም ተከትሎ የህዝብን ተስፋ ማጨለም የለበትም፡፡ኦዴፓን እና አዴፓን ሁለት እግር አድርጎ የቆመው ኢትየጵያዊያን በእኩል የመኖር ተስፋ በኦዴፓ መንሸራተት ምክንያት አንድ እግሩ ተሰብሮ ያነክስ ይዟል፡፡በዚህ ወሳኝ ወቅት አዴፓ/ብአዴን ቃሉን ጠብቆ የህዝብን ተስፋ ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን የተሰበረውን አንድ እግር በበርካታ ጠንካራ እግሮች ተክቶ የኢትዮጵያንን ተስፋ የማደስ ታሪካዊ ሃላፊነት አለበት፡፡

ይህን ከባድ ሃላፊነት እንዳለበት ኦዴፓም እንደተረዳ አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያዊ እርስት እና የፌደራሉ መንግስት መዲና እንጅ የአንድ ወገን ንብረት እንዳልሆነች ከገለፀበት መግለጫው ያስታውቃል፡፡ይህ አባባል ደግሞ ከህገ-መንግስቱ ድንጋጌም፣ከአዲስ አበባ ህዝብፍላጎት ጋርም፣ከኦህዴድ/አነግ በቀር ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ጋርም አዴፓን የሚያስማማው አቋም ነው፡፡የኬኛ ፖለቲካ በአሁኗ ቅፅበት እንኳ በጌዲኦ፣ወለጋ፣በለገጣፎ፣በሱሉልታ እና ሰበታ እያመረተ ያለውን የህዝብ ሰቆቃ እና እንግልት ያየ ኢትዮጵያዊ ሁሉ አዲስ አበባን ለኦዴፓ አስረክቦ የኢትዮጵያዊነቱን ምልክት ማጣትን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡

የኬኛ ፖለቲካ ወዳጅ አለው?

አቶ መለስ በስልጣናቸው ላይ ዘመናቸው የፈቀደላቸውን የመርገጥ እድል ተጠቅመው የዘውጋቸውን ልሂቃ ሁለንተናዊ የበላይነት እውን አድርገው ኖረዋል፡፡ይህን እያየ ተመሳሳዩን ለመድገም ሲጎመዥ የኖረው አዴፓ የአሳዳጊውን አካሄድ እየተከተለ ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ የረሳው ነገር ግን ትናንት ዛሬ እንዳልሆነ ነው፡፡ትናንት ዛሬ አለመሆኑ ኢህአዴግን ጭምር ቀይሮታል፡፡ትናንት ለአቶ መለስ ሲያደገድግ የኖረው የአባል ፓርቲ ካድሬ ዛሬ አለቃ ላወጣው መግለጫ ሌላ መግለጫ በሚሰጡ ሰዎች ተቀይሯል፡፡የአማራን ጭራቅነት አንስቶ ማስፈራራቱም ቢሆን ብዙም የሚያስኬድ አይደለም፡፡የኦሮሞ ስልጣን መያዝም ለሌላው ኢትዮጵያዊ ምን እንዳመጣ በአጭር ጊዜ ብዙ ትምህርት እየተገኘ ነው፡፡ስለዚህ ዋናው ጭራቅ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ስለአሮጌው ጭራቅ ማውራቱ ሞኝ ሊያስመስል ይችላል፡፡

ኦዴፓ በፍጥነት እውነተኛ ምግባሩን መግለፁ በኢትዮጵያዊነቱ በኢትዮጵያ ምድር እኩል ሆኖ የመኖር አምሮት ያለው ዜጋ ሁሉ ፊቱን እንዲያዞርበት አድርጓል፡፡ይህ ከኦዴፓ በቀር በሃገሪቱ ብቅ እያሉ ያሉ አዳዲስ አመራሮችን ሁሉ የሚጨምር ይመስላል፡፡ኦዴፓ በኬኛ ፖለቲካ በኩል የኦነግ አምሮት ወደሆነው ኦሮሙማ በፍጥነት በሚምዘገዘግበት ወቅት በሃገሪቱ አዲስ የሆነ የዲሞክራሲ እና የእኩልነት ፖለቲካን የመሻቱ ነገር እያየለ መጥቷል፡፡የህወሃትን የበላይነት አዝሎ ጀርባው የዛለው የኢትዮጵያ ህዝብ የማንንም የበላይነት የሚያስተናግድበት የጠጠር መጣያ ቦታ አልቀረለትም፡፡ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከኦህዴድ የኬኛ ፖለቲካ በተቃራኒው ያቆመዋል፣ኦህዴድን ጠላተ ብዙ አድርጎ መሞቻውን ጊዜ ያፋጥናል፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ ሚናውን ያልለየው፣ድምፁን ያጠፋው የተቃውሞ ጎራ አሰላለፉ ከወዴት እንደሆነ ማወቅ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡የተቃውሞ ጎራው ሃገሪቱ እንዲህ አቅጣጫ በጠፋት ጊዜ ብቅ ብሎ ህዝቡን ካላረጋጋ ህልውናው ለመቼ እንደሚያስፈልግ ግልፅ አይደለም፡፡

ኦህዴድ አሁን የያዘው መንገድ በሃገርቤት ብቅ ካሉ አዲስ የለወጥ አመራሮች እስከ አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ፣ከተራው ዜጋ እስከ ሲቪክ ማህበራት ድረስ ወዳጅ የሚያሳጣው ነው፡፡የምዕራቡ ሚዲያ የሚቀባበለው የጌድኦ ስደተኞች ጉዳይ ጠ/ሚውንም ሆነ እናት ፓርቲያቸውን አይንህ ላፈር የሚስብል እንጅ አበጀህ የሚያስብላቸው ነገር አይደለም፡፡ትናንት በወለጋ ነጆ አካባቢ ሰብዓዊ ፍጡራንን መግደሉ አንሶ በላያቸው ላይ እሳት መልቀቁ የኬኛ ፖለቲካ ቱርፋት ነው፡፡ይህ ሁሉ ነገር ጠ/ሚ አብይን በሁለት እጃቸው የጨበጧቸው የምዕራብ ሃገራት ባለስልጣናት ፊታቸውን እንዲያዞሩባቸው የሚያደርግ ነው፡፡የምዕራቡ ሃገራት የወደዷቸውም የኢትዮጵያን ህዝብ ተከትለው ነውና ህዝቡ ፊቱን ሲያዞርባቸው እነሱም ሙገሳውን እንደሚተው ግልፅ ነገር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኦህዴድ መራሹን መንግስት ክፉኛ ማዳከሙ አይቀርም፡፡ ስለዚህ ኦህዴድ አዝማሚውን ተረድቶ የኬኛ ፖለቲካውን ልጓም ሊያበጅለት ይገባል፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ልጓማ ካልገባለት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እና ጉዳቱን ለመቀነስ ሌላው ኢትየጵያዊ ምን ማድረግ አለበት የሚለውን ለማየት ለሳምንት ላሳድረው፡፡

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ሲደጋገሙ እውነት የመሰሉ አዲስ አበባ ተኮር ተረኮች (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ
መጋቢት 8 2011 ዓ.ም.

አዲስ አበባ የወቅታዊ ፖለቲካችን የልብ ትርታ እየሆነች ነው፡፡ለወትሮው የሃገራችን ፖለቲካዊ አሰላለፍ የዜግነት ፖለቲካ እና የዘውግ ፖለቲካ የሚራመድበት ተብሎ በሰፊው ለሁለት የሚከፈል ነበር፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ሰልፈኞች አዲስ አበባን መዲናቸው አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡ከዘውግ ፖለቲከኞች ውስጥ ‘ትልቅ ነን፣ሰፊ ነን፣ፍላጎታችንን ለማስጠበቅ የምችል ክንደ ብርቱ ነን’ ባዮቹ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ደግሞ በአዲስ አበባ ላይ በለጥ ያለ ባለቤትንት አለን ይላሉ፡፡ይህንንም በገልፅ ሲያስቀምጡት “አዲስ አበባ ንብረትነቷ የኦሮሞ ሆና ሌላው ሰውም በከተማዋ መኖር ይችላል” ይላሉ፡፡

መኖር ሁሉ መኖር ነው?

እዚህ ላይ ዋናው ጥያቄ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት በሆነችበት ከባቢ ውስጥ መኖር ትችላለህ የተባለው ኦሮሞ ያልሆነው ኢትዮያዊ የሚኖረው እንዴት ነው?” የሚለው ነው፡፡መኖርማ ኢትዮጵያዊ የትም ይኖራል::መኖር ከተባለ በየመንም፣በሊቢያ፣በደቡብ አፍሪካ፣በአፍጋኒስታን፣በቤሩትም ከፖሊስ ጋር አባሮሽ እየገጠመ ይኖራል፡፡መኖር ሁሉ ግን መኖር አይደለም!የሆነ ምድር ባለቤት ነኝ ያለ፤”በችሮታው” እንዲኖሩ የፈቀደላቸውን ህዝቦች እንዴት ሊያኖር እንደሚችል የሚጠፋው የለም፡፡በሰው ቤት ሲኖሩ ሁሉን እሽ ብሎ፣አጎንብሶ፣ከክብርና መብት ጎድሎ ነው፡፡ለዛውም ባለቤት ነኝ ባዩ የፈለገ እለት አጎንቦሶ ተለማምጦ መኖርም ላይቻል ይችላልና በሰው ግዛት ዋስትና የለውም፡፡

“ሌላው ኢትዮጵያዊ መኖር ይችላል እኛ ግን ባለቤት ነን” የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች የተመኙት ሰምሮ ባለቤት ቢሆኑ ሰውን እንዴት እንደሚያኖሩት ዶ/ር አብይ ስልጣን እንደያዙ መንግስታቸው በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ያደረገው እና የሰሞኑ ይዞታቸው ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡ሰሞኑን የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲችል ለመምከር ተሰብስቦ ሲመለሰ ተኩስ ተከፍቶበት የታሰረ ሰው ነበረ፡፡ይህ የወደፊቱ የሚብስ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ዛሬ ባለቤትነቱ ሳይረጋገጥ፣ምኞቱን ተከትሎ ብቻ እንዲህ ያደረገ አካል ነገ የተመኘውን ባለቤትነት ቢያገኝ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡ ነገሩን በሰፊው እንየው ከተባለ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች እየገጠማቸው ያለውን ችግር ብናስተውል የኦሮሞ ብሄርተኞች “ሌላው መኖር ይችላል” ሲሉ በምን መንገድ ሊያኖሩ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

በታሪክ ገፅ የተመዘቡት በኦሮሚያ ክልል በሌሎች ህዝቦች ላይ የተደረጉ በደለሎችን ሳናነሳ በዚች ቅፅበት የሚደረገውን ብቻ ብናነሳ እንኳን በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጌዲኦዎች በቄሮ እና በታጣቂው ኦነግ “ከሃገራችን ውጡ” ተብለው መከራ እያዩ ነው፡፡ይህ ዓለም ሁሉ የዘገበው፣በባዕዳን ሁሉ ዘንድ ትዝብት ላይ የወደቅንበት ገበናችን ነው፡፡በገዛ የሃገራቸው ሰዎች በጭካኔ ከቀያቸው ተባረው፣ምግብ አጥተው፣ የከሳ ሰውነታቸውን እያሳዩ ስለ ጌዲኦ ተፈናቃዮች የሚዘግቡ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን የሚነዙት ገበና የሚያሳየው የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች “የእኛ” ባሉት ምድር ኦሮሞ ሳይሆኑ መኖር ምን እንደሚመስል፣ምንያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ነው፡፡

በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በቄለም ወለጋ በ1977 ዓ.ም (ምናልባትም ዛሬ ባለ ሃገር ነን ብለው የሚያፈናቅሉት ቄሮዎች ሳይወለዱ) ወደ ስፍራው ያቀኑ የአማራ ክልል ተወላጆች እና የልጅ ልጆቻቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ እተገደዱ ነው፡፡በዚህ ማስገደድ ውስጥ ቄሮ፣የክልሉን መንግስት የሚመራው የኦዴፓ ባለስልጣናት እና የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች በትብብር እንደሚሰሩ ተጎጅቹ ተናግረዋል፡፡በነዚህ የአገር ባለቤት ነን የሚሉ ሃይሎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ሴቶች ይደፈራሉ፣ወንዶች እግራቸው ወደመራቸው ጫካ እየገቡ እንደሆነ ነው እማኞች ለኢሳት የተናገሩት፡፡ክልሉን የሚያስተዳድረው “የለውጥ ሃይል ነኝ” ባዩ ኦዴፓ ታዲያ በቦታው ደርሶ ሰዎቹን ከመታደግ ይልቅ ችግሩን ሽምጥጥ አድርጎ መካድን መርጧል፡፡ጭራሽ ነገሩን የዘገበውን ጣቢያ ኢሳትን እከሳለሁ እያለ ነው፡፡

በጉጂ ዞን የሚኖሩ ጌዲወችን እና በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮችን ጉዳይ ወቅታዊ ስለሆነም አነሳሁት እንጅ ኦሮሞ ሳይሆኑ በኦሮሚያ ክልል መኖር ያለው ፈተና ብዙ ነው፡፡ሌላው ቀርቶ በየቀኑ የሚንቆለጳጰሰው ወያኔን የጣለው ትግል አካል በሆነው የቄሮ እንቅስቃሴ ወቅት በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ወገኖች በትልቅ ችግር ውስጥ እንደነበሩ የሚናገሩ በርካቶች ናቸው፡፡ስለዚህ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ከሆነች በኋላ መኖርን አንከለክልም የሚለው የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ስብከት አጓጉል ማስመሰል እንደሆነ ለገጣፎን፣ሰበታን እና ቡራዩን ያየ ሁሉ መረዳት የሚችለው ነገር ነው፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ስትሆን አዲስ አበባን ሊያስተዳድሩ የሚመጡት እንደ ለገጣፎዋ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅ ያሉ በግፍ የተፈናቀሉ ሰዎች ቤተክርስቲያን እንኳን እንዳይጠለሉ የሚያደርጉ “ግፍ ልብሱ” የሆኑ፣ ህወሃትን የሚያስከነዱ ዘረኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰብዓዊነት በዞረበት ያልዞሩ ሰዎች የሾሙት መለዓክ ናቸው በሚባሉት አቶ ለማ እና ሙሴ የተባሉት ዶ/ር አብይ በሚመሩት ኦዴፓ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች በፊት በስህተት ተሹመው ይሆናል ከተባለም ይህን ሁሉ ግፍ ከሰሩ በኋላም እዛው ስልጣን ላይ መቀመጣቸው አዲስ አበባን ንብረቴ ላድርግ የሚለው ኦዴፓ ለሰለጠነ የከተሜ ፓለቲካም ሆነ ለአዲስ አበባ እንደማይመጥን ነው፡፡አዲስ አበባን የሚመጥናት በማህፃኗ ተወልዶ ያደገ/የኖረ፣ችግሯን በውል የሚረዳ፣የሰለጠነው ዘመን ውስብስቦሽ ሰውን በዘሩ ብቻ ለተመን እንደማያስችል የሚያውቅ፣ከሁሉም በላይ የከተማውን ህዝብ ይሁንታ ያገኘ ሰው ነው፡፡መሆን ያለበት ይህ ሆኖ ሳለ “አዲስ አበባ ለኦሮሞ ከፈጣሪ የተሰጠችን እርስት ነች” እንደማለት የሚሞክረው ነገር ከኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ዘንድ እየተደመጠ ይገኛል፡፡

አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ እነዚህ ሃይሎች አዲስ አበባ ለእነሱ እንደምትገባ ሲከራከሩ በዋናነት የሚጠቅሱት ታሪካዊ እና ህገ-መንግስታዊ ማስረጃዎችን ነው፡፡ከሁለቱም ማስረጃዎች የሚበረታው ግን የደመነፍስ ለእኔ ብቻ የሚያስብል ጉጉታቸው እና ሌላውን ገፍትሮ ራስን ብቻ የማስቀደም አስገማች አካሄዳቸው ነው፡፡ ከታሪክ አንፃር አዲስ አበባ የኦሮሞ የግል ንብረት የምትሆነው አለም የተፈጠረው፣ታሪክ የተቆጠረው ከአስራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ቢሆን ነበር፡፡በህገ-መንግስቱም ቢሆን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ እና ራሷን የምታስተዳድርበት ምክርቤት ያላት ከተማ እንጅ በጨፌ ኦሮሚያ ስር የምትተዳደር ከተማ ነች አልተባለም፡፡አዲስ አበባን ለመውሰድ የሚቋምጠው የኦሮሞ ብሄርተኛ ሁሉ ይህን አይክደውም፤ ያምታታዋል እንጅ!

ማምታቻ አንድ ፡ የመቀመጫ እና የመዲና ተረክ

የኦሮሞ ብሄረተኝነት ልሂቃን አዲስ አበባ የኦሮሞ ለመሆኗ ታሪክ እና ህገ-መንግስት ምስክራችን ነው ይበሉ እንጅ ታሪክንም ሆነ ህገ-መንግሰቱን ተንተርሰው ጠበቅ አድርገው የሚያስረዱት ብርቱ ክርክር አያመጡም፡፡ ምክንያቱም ታሪክም ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ያልፋል፤ ህገ-መንግስቱም አዲስ አበባ ባለቤቷ ጨፌ ኦሮሚያ ነው አይልምና ነው፡፡ይህ ነገር ሩቅ እንደማያስኬዳቸው ያወቁት ለአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ሲሆን ብቻ የሚስማሙት የኦሮሞ ብሄርተኛ ልሂቃን ሌላ አዳዲስ ግማሽ እውነቶች እያመጡ ጥያቄያቸውን ትክክለኛ ለመምሰል እየሞከሩ ነው፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መዲና እንደሆነች ስሜት ውስጥ ገብቶ ማውራት ሰሞኑን ከመጡ ማምታቻዎች ዋነኛው ነው፡፡ይህ ቅጥፈት በዚህ አያበቃም፡፡ጭራሽ አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫ፣የኦሮሚያ ክልል ደግሞ መዲና እንደሆነች መላልሶ በማውራት እውነትን ከታች ወደላይ ገልብጦ በሃሰት የመተካት ሃፍረተ-ቢስ አካሄድ ተይዟል፡፡የባሰው ሲመጣ ደግሞ አዲስ አበባ የኦሚሮያ መዲና መሆኗ የማያከራክር፤ መቀሌ የትግራይ፣ባህርዳር የአማራ ክልል ዋና ከተማ ከመሆኗ ጋር እያወዳደሩ ምሳሌ ማድረግ ነገሬ ተብሎ ተይዟል፡፡እውነቱ ግን ተቃራኒው ነው፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሚያ መዲና ነች የሚል ህግ ሆኖ የወጣ ብሄራዊም(ፌደራላዊ) ሆነ ክልላዊ ህገመንግስት የለም፡፡የፌደራሉ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49/1 አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ እንደሆነች በግልፅ ያስቀምጣል፡፡በ1994 የተሻሻለው የኦሮሚያ ህገ-መንግስት አንቀፅ 6 ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መዲና አዳማ እንደሆነች በግልፅ ይደነግጋል፡፡ይህ የተሻሻለው ህገ-መንግስት የፀደቀው ራሱ በአዳማ ከተማ እንደሆነ በመጀመሪያዎቹ ገፆች ላይ አስቀምጧል፡፡ይህ የሆነው አሁን ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ጌታ እንደሆነች ታሪክም ህገ-መንግስም ምስክር ነው የሚለው የአቶ ለማ ኦዴፓ/ኦህዴድ በሌለበት አይደለም፡፡አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ እንደሆነች የሚደነግገው አቶ ለማ በምስክርነት የሚጠሩት ህገ-መንግስት የቱ እንደሆነ የት ተገኝተው ይጠየቃሉ?

ይህ ከሃቅ ጋር የማይመሳከር የግፋኝ ክርክር ለደምፍላት ፖለቲከኞች መንደርደሪያ ሆኖ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዘዝ የምትለው የአማራ ክልል በባህርዳር ላይ ልዘዝ እንደሚለው ወይም የትግራይ ክልል በመቀሌ ላይ ልዘዝ እንደሚለው ነው ተብሎ ቁጭ አለ፡፡ይሉኝታቢስነት፣ቅጥፈት፣ግማሽ እውነት በአደባባይ ሲናገሩት የማያሳፍርበት፤አይነ-ደረቅነት እና የአደባባይ ውሸታምነት ቅሌት እንደ ጉብዝና የሚታይበት ዘመን ስለሆነ ይህ ነገር እንደ እውነተኛ ነገር ተቀጥሎበታል፡፡እውነቱን ተናግሮ ለማለፍ ግን አዲስ አበባ የፌደራል መንግስቱ ዋና ከተማ፤የኦሮሚያ ክልል ደግሞ መቀመጫ ነች፡፡መቀመጫ እና መዲና ይለያያል፡፡መቀመጫ ማለት ተቀማጩ (በዚህ ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል መንግስት) በከፊል መስሪያ ቤቶቹን አዲስ አበባ አድርጎ ስራውን ይሰራል ማለት ነው፡፡

በዚህ መሰረት የኦሮሚያ ክልል መስሪያቤቶች በአብዛኛው አዲስ አበባ ሲሆኑ የክልሉ ምክርቤት አዳማ ከትሟል፡፡የገልማ አባገዳ የተንጣለለ አዳራሽ በአዳማ ከተማ የተገነባው ለዚህ ነው፡፡የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የማንኛውም መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ህግ አውጭው የመንግስት ክንፍ/ፓርላማው ነው፡፡የኦሮሚያ ክልልን የሚመራው ኦዴፓ(የቀድሞው ኦህዴድ) የፓርላማ መቀመጫውን ያደረገው አዳማ ላይ በተገነባው ገልማ አባገዳ ነው፡፡አሁን ክልሉ የሚመራበት በ1994 የተሸሻለው ህገ-መንግስት የፀደቀው በራሱ በህገ-መንግስቱ የክልሉ መዲና ተብላ በተጠቀሰችው አዳማ ላይ በተደረገ ስብሰባ እንደሆነ እዛው ህገ-መንግስቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ዛሬ አዲስ አበባ ንብረቴ ነች የሚለው ኦዴፓ በአንድ ወቅት በአቶ መለስ ትዕዛዝ ጓዙን ጠቅልሎ አዳማ ገብቶ አንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጓዙን ጠቅለሎ ወደ አዳማ ከትሞ የነበረውም ሆነ ዛሬም ቢሆን በከፊል መስሪያቤቶቹን አዳማላይ ያደረገው ያለምክንያት አይደለም-አዳማ የኦሮሚያ ክልል ህጋዊ (ህገ-መንግሰታዊ) መዲናዋ ስለሆነች እንጅ፡፡

ባህርዳር የአማራ ክልል፤መቀሌ የትግራይ ክልል መዲና እንደሆነችው እንደሆነችው ባለ የህጋዊነት መጠን አዲስ አበባም የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ነች የሚለው የኦሮሞ ልሂቃ ክርክር ልክ ቢሆን ኖሮ አዲስ አበባ የምትመራው በጬፌ ኦሮሚያ በሚወጡ ህጎች ሆኖ ማየት ነበረብን፡፡ ምክንያቱም ባህርዳር የምትመራው በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክርቤት በሚወጡ ህጎች እና ደምቦች ነው፡፡ መቀሌም እናደዛው በትግራይ ክልላዊ መንግስት ፓርላማ በሚደነገጉ ህጎች ትተዳደራለች፡፡አዲስ አበባ ግን የራሷ ፓርላማ ያላት፣በራሷ ምክርቤት የምትተዳደር ከተማ እንጅ በኦሮሚያ ክልል የተመረጡ አንደራሴዎች በሚወጡ ህጎች አትመራም፡፡ይህን ቁሮም ሆነ አለቃው፤ኦህዴድም ሆነ ኦነግ የአዲስ አበባ ባለቤትነት አምሮት ከቁጥጥራቸው ውጭ ሆኖ ስላዋተታቸው የማይቀይሩት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ነው፡፡ህገ-መንግስቱ አይቀየር የማለቱ ጥብቅና የሚበረታው ደግሞ በእነርሱው ስለሆነ ሲመችም ሳይመችም ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎቸን ማክበር ግድ ይላቸዋል፡፡

አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል…..

ኦሮሚያ ክልል የሚመራበት ህገ-መንግስት በግልፅ የክልሉ መዲና አዳማ ነች ሲል በደነገገበት ሁኔታ የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባን መቀመጫው ያደረገው በምን የህግ መሰረት እንደሆነ ኦህዴድም ሆነ እውቀት ከእኔ በላይ ላሳር የሚሉ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ሲያስረዱ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ በርግጥ እነሱ የማያስረዱት ጠያቂ ስለጠፋም ይሆናል፡፡የኦሮሚያ ዋና ከተማ አዳማ መሆኗ በህግ ተደንግጎ ሳለ የክልሉ መንግስት አዲስ አበባ የተቀመጠው፣ደግሞ ወደ አዳማ የሄደው ከ1997 ወዲህ ደግሞ መልሶ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በአቶ መለስ ትዕዛዝ እንደሆነ ግልፅ ነገር ነው፡፡

አቶ መለስ ለምን ይህን አደረጉ ለሚለው ጥያቄ ደግሞ መልሱ በ1997 ምርጫ በአዲስ አበባ ህወሃት መራሹ መንግስት በደረሰበት ሽንፈት ሳቢያ በመበሳጨቱ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ የውዝግብ ችግኝ መትከሉ ነው፡፡ ይሄው ችግኝ አድጎ ነው ዛሬ እያነታረከን ያለው፡፡በተጨማሪም “ህወሃት እኔ ስልጣን ከለቀቅኩ ሃገሪቱን ለኦነግ አስረክቤነው የምሄደው” ባለው መሰረት ወዶ ስልጣኑን በግልፅ ኦነግ ነኝ ለሚል አካል ባያስረክብም እየሆነ ያው ግን ህወሃት በተመኘው መንገድ ነው፡፡የሃገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠረው ኦዴፓ ውስጥ ገዥው ሃሳብ የኢትዮጵያ መኖር ያለመኖር ግድ የማይሰጠው የኦነግ ሃሳብ ነው፡፡ዛሬ ሃገሪቱንም ሆነ አዲስ አበባን የሚያሰጋት በተለያየ ስም በሚጠሩ የኦሮሞ ፓርቲዎች እና ግለሰብ አክቲቪስቶች ያደረው የኦነግ መንፈስ ነው፡፡

ሲጠቃለል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እንደ ዘሃ ዘጊ ከአዲስ አበባ አዳማ የሚያደርገው ምልልስ ደራሲው የእኩይ ፖለቲካ ሊቁ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡በሌላ ህግም ሆነ አዋጅ ሳይደገፍ በአቶ መለስ ቀጭን ትዕዛዝ ብቻ አዲስ አበባ የከተመው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው እንግዲህ የአዲስ አበባ ባለቤት ነኝ የሚለው፡፡ስለዚህ አዲስ አበበ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር የሚታገል አዲስ አበቤ ሁሉ “ካልገዛኋችሁ ሞቼ እገኛለሁ” ለሚለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሰት ማንሳት ያለበት ጥያቄ “የአዲስ አበባ ባለቤትነቱ ቀርቶ መቀመጫነቱን የደነገገው ህግ የቱ ነው?” የሚል ነው፡፡የመለስ ተንኮል ህግ ሆኖ ተጠቅሶ አያከራክር መቼም! ዘመኑ እፍረት የጠፋበት ነውና የአዲስ አበባ ብቸኛ ባለቤት ያደረገን መለስ ነው ከተባለም መለስ ጌትነቱ ለአሽከር ፓርቲዎች እንጅ ለአዲስ አበባ ህዝብ አይደለምና ነገሩ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡

ሌላ ነገር እንበርብር ከተባለም በሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ ሯሷን የቻለች ክልል 14 እንጅ አሁን እንደሚወራው በዘመን መካከል ሁሉ ከኦሮሚያ ጋር የተሰፋች ርስት አይደለችም፡፡ ነገሩ አሁን እንደሚወራው ቢሆን ኖሮ ኦነግ አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት የሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ እንዴት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ሆና ሳትደለደል ቀረች?የሽግግሩ ወቅት የታሪክ አካል ነው፡፡አቶ ለማ የታሪክ እና የህግ ምስክር ጠርተው አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት መሆኗን ሲያስረዱ የሽግግር ዘመኑ የታሪክ እውነታ የሚቆመው ግን በተቃራኒቸው አንጅ በጎናቸው አይለም፡፡ ከዛ በፊት ያለው ታሪክም ቢሆን ክርክራቸውን አይደግፍም፡፡ከዚህ አይነት የክህደት ክርክር የሚገኘው ትርፍም ትዝብት ብቻ ነው፡፡

ማምታቻ ሁለት፡ ተበታተንኖ እና ተሰባስቦ የመኖር ነገር

የኦሮሚያ ክልል በውስጡ የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን መብት አያከብርም የሚል በተግባር ማሳያ ያለው ትችት ይቀርብበታል፡፡ ሌሎች ክልሎች ለምሳሌ የአማራ እና የደቡብ ክልል በውስጣቸው ለሚኖሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች የልዩ ዞን እና ልዩ ወረዳ የአስተዳደር መልክ ሰጥተው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ይፈቅዳሉ፡፡የኦሮሚያ ክልል ይህን ለምን እንደማያደርግ የሚጠየቁ የኦሮሞ ምሁራን ኦሮሚያ ይህን የማያደርገው በክልሉ የሚኖሩ ሌሎች ህዝቦች የራሳቸውን ልዩ አስተዳደር ለመከለል እንዲመች ሆነው በአንድ ቦታ የማይኖሩ ይልቅስ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተሰባጥረው የሚኖሩ ስለሆኑ ክልሉ ልዩ ወረዳ እና ዞን ለመስጠት ተቸግሮ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ይህን ባሉበት አፋቸው ደግሞ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ተሰባስበው በአንድነት የሚኖሩበትን፣በህገ-መንግስት የኦሮሚያ ክልል አካል ያልሆነውን የአዲስ አበባ ከተማን ካላስተዳደርን፣በግዛቱም ላይ ባለቤት ካልሆንን ብለው የህዝቡን ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት በዱላ ጭምር ለመጋፋት ይሞክራሉ፡፡

በክልላቸው ውስጥ ያልሆነውን፣በአንድ ውስን አካባቢ የሚኖር ህዝብ የግል ንብረቱ ለማድረግ የሚያንቧትረው የኦሮሚያ ክልል በክልሉ ውስጥ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች በአንድ ላይ ቢኖሩም ልዩ ዞን ወይም ወረዳ ሰጥቶ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ያደርጋል ማለት የማይታመን ነገር ነው፡፡ክልሉ ይህን አድረጋለሁ ካለ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ደራ በምትባለው የኦሮሚያ ክልል ምድር ላይ የሚኖሩ አማሮች የሚያነሱትን የልዩ ዞንነት ጥያቄ መልሶ ያሳይ፡፡

ማምታቻ ሶስት፡ የማዕከልነት ጥያቄ

ሌላው የኦሮሞ ልሂቃን ክርክር አዲስ አበባ ለእኛ ትገባናለች የምንለው ዙሪያዋን በኦሮሚያ ተከባ በመሃል የምትገኝ ስለሆነች ነው ይላሉ፡፡በዚህ ላይ አዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ነበሩ፣ከተማዋ ስትቆረቆር በግድ ተፈናቅለው ነው የሚል ክርክር ይደርባሉ፡፡ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ነበሩ የሚለውን ልብ አውላቂ ክርክር አይረቤነት ከዚህ ቀደም በሰፊው ስላነሳሁ ለአሁኑ ከ15ኛው ክፍለዘመን በፊትም ዘመን ነበረ፣ሰው ነበረ በሚለው ብቻ ልለፈው፡፡ወደ ፊተኛው ክርክር ማለትም አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ ስለምትገኝ ለእኛ ትገባለች ወደ ሚለው ክርክር ስንመለስ አጭሩ መልስ የአንድን ግዛት ዙሪያውን መክበብ ብቻ ባለ እርስት እንደማያደርግ የሌሴቶን እና የደቡብ አፍሪካን ካርታ አፈላልጎ ማየት ነው፡፡ ሌሴቶ በደቡበ አፍሪካ ግዛት መሃል ላይ የምትገኝ ግን ራሷን ያለች ሃገር ሆና የምትኖር ሉዓላዊት ሃገር ነች፤ደቡብ አፍሪካም “ስለከበብኩሸ ልዋጥሽ” ሳትላት እስከዛሬ በጉርብትና ይኖራሉ፡፡ ዙሪያዋን በጣሊያን ግዛት ተከባ ግን በመንፈሳዊ መሪ የምትመራዋ የቫቲካን ግዛትም እንዲሁ የጣሊያን መንግስት “ንብረቴ ነሽ” ብሏት አይውቅም፡፡

በአጠቃላይ የኦሮሞ ብሄርተኞች በአዲስ አበባ ላይም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሚያሳዩት እንደ ልጅ ሁሉም ለእኔ ይገባኛል የሚለው አካሄድ ጠላት ያበዛባቸው ይሆናል እንጅ የሚያሳኩት ምኞት አይመስልም፡፡እንዲህ ያለ የፖለቲካ እሳቤ የሚንጠው፣የራሱን ምኞት እንኳን መግራት ያልቻለ ቡድን ፌደራላዊ ስልጣን ላይ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ሃገራዊ ስፋት ይሰጠዋል፡፡በዚህ ምክንያት የሃገሪቱን የፖለቲካ አሰላለፍ ያመሳቅለዋል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ሁሉን ለእኔ የሚል አካሄድ የሃገሪቱን ፖለቲካአሰለለፍ እንዴት ያደርገዋል የሚለውን ጉዳይ ለማንሳት ሳምንት ልመለስ፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የአቶ ገዱ እና የዶ/ር አምባቸው ሹም ሽር የጉልቻ መለዋወጥ ነው? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
መጋቢት 5 2011 ዓ.ም.

የለውጥ አመራር የሚባለው የኢህአዴግ ክፋይ ቡድን በዋናነት ከብአዴን አቶ ገዱ፣ ከኦህዴድ አቶ ለማ እንደሚመሩት ሲነገር ቆይቷል፡፡ይህ ቡድን ተባብሮ የህወሃትን የበላይነት እንዳስወገደው ሁሉ በከባድ ችግር ውስጥ ያለችውን ሃገር እጣ ፋንታም እንደዛው ተባብሮ መልክ ያስይዛል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡በዚህ ረገድ ከፍ ያለ ተስፋ የተጣለባቸው አቶ ለማ መገርሳ ነበሩ፡፡ምክንያቱም ህወሃት ሊወድቅ ገደድ ገደድ ሲል ባህር ዳር ድረስ ተጉዘው ያለ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደማይሆንላቸው ሲወተውቱ ስለነበር ነው፡፡ከባህርዳሩ ጉዞ መልስም ቢሆን እኩልነት የሰፈነባት ሃገር ለሚፈልገው አብዛኛው ዜጋ ጆሮ የሚጥሙ የዘመናዊ ፖለቲካ ቅመሞችን የያዙ ንግግሮች ሲናገሩ ሰንብተዋል፡፡ቃል በተግባር ሲፈተሽ ግን አቶ ለማ ሌላ ሰው ሆነው ተገኙ፡፡በአደባባይ የተናገሩለት የኢትዮጵያዊነት ሱስ ተገዳዳሪን አደንዝዘው የኦሮሞ የበላይነትን ወደ ማስፈኛው መንገድ የሚያዘግሙበት ብልሃት እንደሆነ እየተገለጠ መጣ፡፡

በሃገሪቱ ዋነኛ ስልጣናት ላይ ኦሮሞን በመኮልኮል የተጀመረው የበላይነት አምሮት ዝንባሌ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ያለምክንያት ለቃቅሞ በማሰር ተፋፋመ፡፡በአንፃሩ ቄሮ ከነፍስ ማጥፋት እስከ ሌላ የሚደርስ ህገወጥነት ሲያሳይ ዝምታን በመምረጥ የለማ ቡድን ወዴት ዘመም ዘመም እያለ እንደሆነ አስመሰከረ፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ቸኩሎ ያመነው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ እነ ለማን መውቀስም ሆነ ቃላቸውን በማጠፍ መጠርጠሩን አልፈለገም ነበር፡፡ከዚህ ይልቅ አንዳች አክራሪ ሃይል አስቸግሯቸው ይህን ሁሉ እያስደረጋቸው እንሆነ ነበር የታሰበው፡፡ሆኖም እውነት እና ንጋት እያደር ጠርቶ በብዙ የታመኑት አቶ ለማ እና ዶ/ር አብይ የኦሮሞ ተወላጆችን ሰብስበው፣በተዘጋ በር ውስጥ ጎን ለጎን ተቀምጠው የተናገሩት ንግግር ቪዲዮው ወጥቶ ሲታይ ለወደፊቱ ጭምር መተማመንን የሚፈታተን ነገር ተከሰተ፡፡የአቶ ለማ እውነተኛ ፍላጎት ታየ፣ተሰማ፡፡በዚህ ያዘነው አማኙ ህዝብ ከኦዴፓ ላይ አይኑን አንስቶ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች ለዚህ የኦዴፓ የበላይነት አምሮት የሰጡትን ምላሽ፣ይህን አደገኛ አካሄድ ለመግታት ያደረጉትን ጥረት ማጤን ጀመረ፡፡ከነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች አንዱ ለውጥ ለማምጣት ከአቶ ለማ ኦዴፓ ጋር አብሬ ሰርቻለሁ የሚለው በአቶ ገዱ የሚመራው አዴፓ ነው፡፡

አዴፓ በቀድሞወ ስሙ ብአዴን ስልጣን ላይ ለወጣ ቡድን በማደግደግ የሚታወቅ ታሪክ አለው፡፡የለውጥ አመራር መሪ የተባሉት አቶ ገዱም የዚህ ችግር አንደኛ ተወቃሽ ነበሩ፡፡ህወሃትን በአዴፓ የሚተካው ትግል ሲደረግም የተደረገው ለውጥ የትግሬ መኳንንትን የበላይነት ስልጣን በተራቡ የኦሮሞ መኳንንት የበላይነት እንዳይተካ ስጋት ነበር፡፡”ይህን ስጋት የማስወገዱ የፖለቲካ ጨዋታ አዋቂነት አቶ ገዱ በሚመሩት አዴፓ ዘንድ አለ ወይ?” የሚለው ዋና ጥያቄ ነበር፡፡ለዚህ ጥያቄ አወንታዊ መልስ ማግኘት የሚሻው ዜጋ ሁሉ የአደፓን ብልህ እና ጠንካራ የፖለቲካ ሃይልነት አጥብቆ ይሻ ነበር፡፡ሆኖም የአቶ ለማ ኦዴፓ ህወሃት ለሃያ ሰባት አመት ሰርቶ ያመጣውን ፍፁም የበላይነት በሁለት ወር ውስጥ እውን ሊያደርግ ሲራወጥ የአቶ ገዱ አዴፓ እንደ ገራም የቤት እንስሳ ዝም ብሎ ከማየት ውጭ ያደረገው ነገር ቢኖር አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ መሆኗን የሚናገር ቀላጤ መፃፍ ብቻ ነው፡፡ይህ የኦዴፓ ዝግተኛ ፖለቲካዊ አካሄድ ሁሉን ነገር በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ እየሰገረ ያለውን የኦዴፓን ሽምጥ ግልቢያ መከተል የማይችል እጅግ በጣም ቀርፋፋ አካሄድ ነው፡፡

የአቶ ገዱ ኦዴፓ በፍዘት በሚያስተውለው የፖለቲካ ሜዳ ኦዴፓ “ነገ የለም” የተባለ ይመስል ሁሉን ነገር ዛሬውኑ የራሱ ለማድረግ ትንፋሽ እስኪያጥረው እየተራወጠበት ይገኛል፡፡አዲስ አበባን ጠቅልሎ ወስዶ የጨፌ ኦሮሚያ ገባር ሊያደርግ ይፈልጋል፣ይህ እስኪረጋገጥ ደግሞ አዲስ አበባ አንድ ኢንች መሬት እንኳን ከኦሮሚያ ወስዳ ቤት እንዳትገነባ ይከላከላል፣ከስንት አመት በፊት በራሱ ጭምር ስምምትን የተሰራን የጋራ መኖሪያ ቤት የኦሮሞ መሆን አለበት ሲል ይሟገታል፣ወዲያው ደግሞ ወደ ክልሌ እንዳትሰፋ እያለ የሚከለክላትን አዲስ አበባን መምራት ያለበት ኦሮሞ ነው ሲል የትንሽ ከተማ ከንቲባ ስቦ አምጥቶ እላዋ ላይ ይሾማል፡፡በአዲስ አበባ የሚደረገው ነገር ሁሉ የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ያገናዘበ መሆን አለበት ሲል ይፎክራል፡፡ከጭናግሰን ቆላ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን በብርዳማው አዲስ አበባ አምጥቼ አሰፍራለለሁ ይላል፡፡

ኦሮሞ አዲስ አበባን ያስተዳድር፣ከየትም ዳርቻ ያለ ኦሮሞ ተፈጥሯዊ ባልሆነ የገጠር-ከተማ ፍልሰት አዲስ አበባ መጥቶ ይግባ፣በአዲስ አበባ የሚደረገው ነገር ሁሉ የኦሮሞን ፍላጎት ያገናዝብ እያለ ሲል የአዲስ አበባ ባለቤት የኦሮሚያ ነች ማለቱ ነው፡፡ይህን ባለበት አፉ ደግሞ አዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ መስፋት የለባትም ሲል በተቃራኒው ቆሞ ይገኛል፡፡አዲስ አበባ የኦሮሞ ከሆነች ከተማዋ ወደ ኦሮሚያ አንድ ኢንች መስፋት የለባትም ብሎ መሞገት እጅግ ግራ አጋቢ ፍላጎት ነው፡፡

ሳያስበው ስልጣን እጁ ላይ የወደቀው የኦቶ ለማ/አብይ ኦዴፓ እንዲህ የሚያቅበጠብጠው ምኞቱን ከስር ከስር የሚያቃልልበት ስልጣን አግኝቶ ስለማያውቅ አሁን ድንገት ስልጣን ሲያገኝ የቱን ዕለቱን አድርጎ የቱን እንደሚያሳድር እንኳን ስለጠፋው ነው፡፡ይህን ፖለቲካዊ መንቀዥቀዥ አደብ የሚያስይዝ ከበድ ያለ የፖለቲካ ሚዛን ያለው አካል ያስፈልጋል -ይሄውም አዴፓ ሊሆን ይችላል፡፡ይህን የአዴፓ አመራሮች ቆይተውም ቢሆን ተረድተዋል፡፡ በመሆኑም አቶ ገዱ ይህን ሚና እንዲጫወቱ ከአዴፓ ካድሬዎች ግፊት ሳይበረታባቸው አልቀረም፡፡ለዚህ ምስክሩ ከሰሞኑ በአቶ እንዳወቅ አብጤ ሰብሳቢነት የአዴፓ ምሁራ ስብሰባ ሲካሄድ መሰንበቱ ነው፡፡

የግፊቱ መበርታት የአቶ ገዱን ፍዝ የፖለቲካ እርምጃ ከመውቀስ ጋር የተዳበለም ሊሆን ይችላል፡፡የአቶ ገዱ ዝግተኛ አካሄድ በኦህዴድ በኩል እንደሚወደድ ትናንት ዶ/ር አብይ አህመድ ባህርዳር ላይ ድንገት ተከስተው የተናገሩት ንግግር ያሳብቃል፡፡ከኦህዴድ ጋር በአንድ ልሳን እያወራ ያለው አቶ ጃዋር መሃመድም ዶ/ር አብይን ተከትሎ ያለወትሮው አቶ ገዱን እያሞካሸ ይፅፍ ይዟል፡፡ዶ/ር አብይ እንደውም ለአቶ ገዱ የፌደራል ስልጣን እንዳዘጋጁላቸው ጠቆም የሚያደርግ ንግግር አክለዋል፡፡የበላይነታቸውን ለማፅናት እንደ መንግስትም እንደ አክቲቪስትም ተባብረው እየሰሩ ያሉት የኦሮሞ ልሂቃን አቶ ገዱን የሚያሞካሹት አቶ ገዱ የሚባለውን ያህል የፖለቲካ አዋቂ ሆኖ ላይሆን ይችላል፡፡ይልቅስ የአቶ ገዱ ፍዝ አካሄድ ለተጣደፈው የበላይነት ጉዟቸው እንቅፋት ያልደቀነ ስለሆነ ነው፡፡

“በፈቃዳቸው ስልጣን አስረከቡ” የተባሉት አቶ ገዱ ስልጣን ለመልቀቅ ያስገደዳቸው ድጋሜ የማንንም የበላይነት ተሸክሞ መኖር የማይሻበት የብስለት ደረጃ ላይ የደረሰው የአዴፓ ካድሬ ግፊት መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ኦህዴድ ወደ የበላይነት እና አምባገነንነት የሚደርገውን ጉዞ፣የትግራይ ክልል የሚያደርገውን ድንፋታ እና የጦር ቱማታ ዝም ብሎ የሚያየው የአቶ ገዱ ዳተኛ አካሄድ ለአዴፓም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አደገኛ ነገር ይዞ የሚመጣ ውጤት ይኖረዋል፡፡ይህን አደገኛ አካሄድ ልጓም የሚያስይዝ አዲስ አመራር ማስፈለጉም ሳይሆን አይቀርም ዶ/ር አምባቸውን ወደ ስልጣን ያመጣቸው፡፡ዶ/ር አምባቸው ለዚህ ብልሃት ያለው ፖለቲካዊ አካሄድ ትክክለኛው ሰው ናቸው አይደሉም? የሚለውን በእርግጠኝነት ለመናገር አሁን ጊዜው ባይሆንም አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት ግን ይቻላል፡፡

የለማ/አብይ መንግስት ስልጣን በተረከበት ሰዓት ዶ/ር አምባቸው የንግድ እና እንዱስትሪ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ግን ከዚህ ወንበር እንዲነሱ ሆኗል፡፡ዶ/ር አምባቸው በተነሱበት ወንበር የተቀመጡት ደግሞ ተጋዳሊት ፈትለወርቅ ገ/እግዚብሄር(ሞንጆሪኖ)ናቸው፡፡ሰው በሰው ሲተካ አንድም ተተኪው ከቀዳሚው ይሻላል ተብሎ፤ ሁለትም ለፓርቲያዊ የስልጣን ቅርምት ነው፡፡ ሞንጆሪኖ ከዶ/ር አምባቸው የተሻሉ ሰው ሆነው በወንበሩ ተቀምጠው ከሆነ ደግ ቢሆንም በኢህአዴግ ቤት ይህን መጠበቅ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡

የሆነ ሆኖ ዶ/ር አምባቸው ከሚኒስትርነት ተነስተው ብዙም ፖለቲካዊ ጉልበት በሌለው የአማካሪነት ቦታ ላይ መቀመጣቸው በአዴፓ ካድሬዎች እና ደጋፊዎች ዘንድ ጉም ጉም ፈጥሮ ነበር፡፡በዚህ ላይ ዶ/ር አምባቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርገው ሊሾሙ እንደሆነ ከተወራ በኋላ ቀረ፡፡ይባስ ብሎደግሞ ብአዴኗን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ከምክትል ከንቲባነት ተነስተው እምብዛም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማምጣት በማያስችለው የትራንስፖርት ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ተመደቡ፡፡ይህ ሁሉ ነገር ሲያያዝ ኦዴፓ መራሹ መንግስት ሆን ብሎ የአዴፓ ጠንካራ ሰዎችን ከመሃል እያሸሸ እንደሆነ በአዴፓ ካድሬዎች ዘንድ ቁጭት የጨመረ መረዳትን አመጣ፡፡

ይህን ሁሉ አዲስ አበባ ተቀምጠው የሚያጤኑት ዶ/ር አምባቸው የዶ/ር አብይን ኦዴፓ የበላይነት ጉዞ መረዳታቸው አይቀርም፡፡ እንደ ግለሰብም ከስልጣን ማዕድ መገፋታቸው ጥሩ ስሜት የለውም፡፡በዚህ ላይ በኢህአዴግ ቤት ስልጣን ዋና ነገር ነው፡፡ከዚህ ሁሉ በላይ ዶ/ር አምባቸው ከአቶ ገዱ በጣም በተለየ ሁኔታ የአማራ ክልል ህዝብ የተጋረጠበት አደጋም ሆነ ኦዴፓ የገባበት አጣብቂኝ የሚሰማቸው ሰው እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ፤በአደባባይ የሚያደርጓቸው ንግግሮችም ምልክት ናቸው፡፡

ይህ የዶ/ር አምባቸው ቁጭት በተለይ የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር ለገባው ፍጥጫ ችኩል ውሳኔ እንዳያስወስናቸው ሰፊ ስጋት አለ፡፡ይህን ስጋት ዶ/ር አብይም እንደሚጋሩት በትናንቱ የባህርዳር ንግግራቸው “ዶ/ር አምባቸው ወደ መቀሌም ወደ አምቦም ጎራ በል” በሚል አይነት ንግግራቸው ጠቆም አድርገዋል፡፡የሆነ ሆኖ ዶ/ር አምባቸው የአቶ ገዱን ያህል ለአብይ/ለማ መራሹ መንግስት የሚመቹ አይመስልም፡፡የዶ/ር አምባቸው ሹመት ዶ/ር አብይ ቀድመው የማያውቁት እና ድንጋጤን ጭምር የፈጠረባቸው የሚመስል ነገር ከሁኔታቸው ይነበብ ነበር፡፡ከዚህ የምንረዳው ኦዴፓ እና አዴፓ እየተነጋገሩ መስራታቸው እንደ ቀድሞው እንዳልሆነ ነው፡፡በርግጥ ተደጋግፎ መስራቱን ቀድሞ ጥያቄ ውስጥ የከተተው ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ቢያስቸግርም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት እንደሆነች የለፈፈው ኦዴፓ ነገሩን እንዳበላሸ መገመት ይቻላል፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የስቃይ ገፈት የሚጋተው የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝብ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ

የካቲት 30 2011 ዓ.ም.

ቋንቋን መሰረት ያደረገው የጎሳ ፌደራሊዝም አስከፊ ገፆቹ ብዙ ናቸው፡፡በመሰረታዊነት የሰውን ልጅ በጎሳው ከልሎ ማስተዳደር ከሰውልጆች ተፈጥሯዊ መስተጋብር የማይገጥም አካሄድ ነው፡፡የሰው ልጅ መሬት ጠበበኝ ብሎ ሽቅብ ወደ ጠፈር በሚምዘገዘግበት በዚህ የሰለጠነ ዘመን ቋንቋን መሰረት ያደረገ ክልል ከልሎ አንዱን የክልል ባለቤት ሌላውን ባይተዋር የሚያደርግ አስተዳደር መዘርጋት ከዘመን መጣላት ነው፡፡አሁን ዓለማችን ያለችበት ሁለንተናዊ እድገት እትብት በተቀበረበት አካባቢ ብቻ የሚያስቀምጥ ያህል ቀላል አይደለም፡፡የእኛ ሃገር ፖለቲካ ደግሞ እትብቱ የተቀበረበትን መሬት እያየ እዛው ላልተቀመጠ ሰው የመከራ ገፈት የሚግት ነው፡፡ ዕትብቱ በተቀበረበት ሃገር እየኖረ ያለውም ቢሆን የወላጆቹ፣የሰባት ጉልበቱ እትብት የተቀበረበት ቦታ ሌላ ከሆነ የጎሳ ፖለቲካ ወለድ ስቃዩ አያልፈውም፡፡

እንዲህ ያለው ለወሬ የማይመች ህሙም ፖለቲካዊ መስተጋብር አጀማመሩ ጨቋኝ እየተባለ ባልበላው የሚብጠለጠለውን የአማራ ህዝብ ከሃገሪቱ ዳርቻ ለማሳደድ ተብሎ የተቀመረ የህወሃት፣የሻዕብያ እና የኦነግ ቀመር ነበር፡፡ይህ ደማቅ ውሸት እውነት ተደርገ በመለስ ዜናዊ እና አሽከሮቹ አፍ ሲነዛ ስለኖረ ተቀባይነት አግኝቶ ኖሯል፡፡ የጎሳ ፖለቲካው እና ፌደራሊዝሙ ሲፈጠር የታቀደለትን አማራውን እያደኑ የማሳደዱ ስራ ለረዥም ዘመን በተሳካ ሁኔታ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ሆኖም እሳትን ሃላፊነት በማይሰማው ሁኔታ ካያያዙት በኋላ አካሄዱን የሚወስነው ራሱ እሳቱ ነውና ከባለቤቱ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ያገኘውን ሊበላ ይችላል፡፡የሃገራችን የዘር ፖለቲካም እንዲያ ነው!አማራውን ለመብላት ተብሎ ነደደ ውሎ አድሮ ግን ‘አማራው በአንድ ላይ ሲጨቁናቸው የኖሩ ናቸው’ የተባሉ ዘሮችምን እርስ በርስ እያናከሰ ይገኛል፡፡የጌዲኦ እና የጉጅ ህዝቦች ለሌላ የነደደው የጎሳ ፖለቲካ እሳት እየለበለባቸው ያሉ ህዝቦች ናቸው፡፡

የጌዲኦ እና የጉጅ ህዝቦች ለረዥም ዘመን አብረው የኖሩ፣ እኩል በእኩል በሆነ ሁኔታ ኦሮምኛም ኤዲኦኛም የሚናገሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ሁለቱን ህዝቦች በሚናገሩት ቋንቋ “ጉዲኦ” እና “ጉጅ” ብሎ መለየት አስቸጋሪ እንደሆነ በህዝቦቹ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ፅፈዋል፡፡በተለይ በጉጅ እና በጌዲኦ ድንበር አካባቢ “ጌዲኦ” በሚል የሚጠራ ሰው “የጉጅ ኦሮሞ” ከሚባለው ሰው ባልተናነሰ ኦሮምኛን የሚያቀላጥፍ ነው፤ጉጅውም እንደዛው ጌዲኦኛን አቀላጥፎ ያወራል፡፡በዚህ ምክንያት ህዝቦቹን ለይቶ በአንድ ክልል መከለል አስቸጋሪ ነው፡፡ በታሪክም ቢሆን ጦር አዋቂዎች እና ሃይለኞች ተደርው የሚወሰዱት የጉጅ ኦሮሞዎች እንደነሱው ኦሮሞ ከሆኑት ቦረናዎች፣አርሲዎች እና ሲዳማዎች ጋር በተለያየ ምክንያት የመጋጨት ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ ከጌዲኦዎች ጋር ግን የስምምነት እና የትብብር ታሪክ እንዳላቸው ነው ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡

የጦር አዋቂነታቸው የሚነገርላቸው ጉጅዎች ከጌዲኦ ጋር የስምምነት ታሪክ ሊኖራቸው የቻለው አንድም ጌዲኦዎች እህል አምራች፣ጉጅዎች ደግሞ ከብት አርቢ በመሆናቸው በምርት ልውውጥ ተደጋግፈው የሚኖሩ በመሆኑ፣ሁለትም ጌዲኦዎች እምብዛም የጦረኝነት ባህል ስለሌላቸው በግብርና ላይ የሚያተኩሩ ህዝቦች በመሆናቸው ጌዲኦዎችን መውጋት በጉጅዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተግባር ስላልሆነ፣ ሶስትም ‘በጌዲኦ እና በጉጅ ቀደምት አባቶች ዘንድ በሁለቱ ህዝቦች መሃል መጋደል እንዳይኖር የተደረገ መሃላ አለ፤ይህን መተላለፍ እርግማን ያመጣል’ ተብሎ የሚታመን እምነት ስላለ እንደሆነ አሰበ ረጋሳ “Ethnicity and Inter-ethnic Relations: the ‘Ethiopian Experiment’ and the case of the Guji and Gedeo” በሚል ርዕስ የሰራው ጥናት ያመለክታል፡፡እነዚህን ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ እሳቤዎች ተላልፎ አንዳንዴ በሁለቱ ህዝቦች መሃከል ግጭት ቢከሰት እንኳን “ጎንዶሮ” በሚባው በሁለቱም ህዝቦች እኩል በሚሰራበት የይቅርታ እና እርቅ ባህል አማካይነት ሰላም ሲወርድ እንደኖረ ይሄው ጥናት ያስረዳል፡፡

እንደዚህ በሰላም የኖሩ ህዝቦች ዛሬ ለመጋደል እና ለመፈናቀል/ማፈናቀል ያበቃቸው ምንድን ነው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡የአሁኑ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ፌደራሊዝም ስራ ላይ ከመዋሉ በፊት የጌዲኦ እና ጉጅ ህዝቦች የሲዳሞ ክፍለሃገር በሚባለው አከላለል ውስጥ አብረው ተከልለው ይተዳደሩ ነበር፡፡ሆኖም የጎሳ ፌደራሊዝም ስራ ላይ ሲውል ጉጅዎቹ ወደ ኦሮሚያ ክልል፣ጌዲኦዎቹ ደግሞ በደቡብ ክልል ውስጥ እንዲተዳደሩ ሆነ፡፡እነዚህ ህዝቦች ግን እንደማንኛውም አብሮ እንደኖረ ህዝብ የተቀላቀሉ ስለሆኑ በጌዲኦ እና ጉጅ መሃከል መስመር አውጥቶ፣ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ማካለሉ እጅግ አስቸጋሪ ነገር ፈጠረ፡፡በዚህ ምክንያት ብዙ ጉጅዎች በደቡብ ክልል ወደሚገኘው ወደ ጌዲኦ ዞን ፣በርካታ ጌዲኦዎች ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ወደሚገኘው ምዕራብ ጉጅ ዞን እንዲካለሉ ሆነ፡፡

በዚህ አከላለል ጉጅዎች በተለይ ‘በርካታ መሬቶች ወደ ጌዲኦ ተካለውብናልና ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችንን ተነፍገናል፤ያለ አግባብ በጌዲኦ ዞን ስር እንድንተዳደር በመደረጋችን ማንነታችን ተጨፍልቋል፣የትምህርት፣የስራ እና የስልጣን እድል ከጌዲኦዎች እኩል እያገኘን አይደለም’ የሚል ቅሬታ ለመንግስት ያቀርባሉ፡፡ጌዲኦዎች በበኩላቸው በርካታ መሬታችን ያለ አግባብ ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ተካሏል፣እስከ ቡሌ ሆራ(ሃገረ ማርያም) ድረስ ያለው መሬት ይባናል የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ይሄው ንትርክ ወደ ግጭት አድጎ በ1987 ዓም ላይ በሁለቱ ብሄረሰቦች መሃከል2000-3000 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ትልቅ መጋደል አስከትሎ ነበር ይላል ከላይ የተጠቀሰው የአሰበ ረጋሳ ጥናት፡፡

ይህን መጋደል ለማስቆም በኦህዴድ የሚመራው ኦሮሚያ ክልል እና በደኢህዴን የሚመራው ደቡብ ክልል ከፌደራሉ መንግስት ጋር በመተባበር በአከራካሪዎቹ ስድስት ወረዳዎች ላይ ህዝበ-ውሳኔ እንዲደረግ ሆነ፡፡በህዝበ ውሳኔው መሰረት አራት ወረዳዎች እዛው ጌዲኦ ዞን ውስጥ እንዲረጉ ሲሆን ቀሪዎቹ ሁለቱ ወረዳዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን እንዲካለሉ ተደረገ፡፡ ሆኖም መፍትሄ ያመጣል የተባለው ሪፈረንደም ጌዲኦዎቹንም ሆነ ጉጅዎቹን ሊያስደስት የሚችል አልሆነም፡፡’የፌደራሉ መንግስት በብሄር ፌደራሊዝሙ ብዙ ግዛታችንን ለጌዲኦዎች ሰጥቶብናል’ ብለው የሚያስቡት ጉጅዎቹ ‘ሪፈረንደሙን የመራው መንግስት ለጌዲኦዎች ያደላል’ ብለው ያስባሉ፡፡በዚህ ላይ ከስድስቱ አራቱ ተመልሰው ወደ ጌዲኦ ዞን መካለላቸው ቅሬታቸውን አባብሶታል፡፡ጌዲኦዎች በበኩላቸው ‘በሪፈረንደሙ ለጉጅዎች የተሰጠው ሁለት ወረዳ መሬት ያለአግባብ የሄደ ለእኛ የሚገባ ነው’ ብለው ያስባሉ፡፡

በዚህምክንያት ሪፈረንደሙ የታሰበውን ሰላም ሳያመጣ ቀረ፡፡አካባቢውም በሁለቱ ብሄረሰቦች በሚነሳ ግጭት ውጥረት እንዲቀጥል ሆነ፡፡ውጥረቱ ተባብሶ በ1990 የበርካታ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ላይ ሌላ ግጭት ተቀሰቀሰ፤የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡የፌደራል መንግስቱ ተከታታይ ስብሰባዎችን እና ባህላዊ የእርቅ ስነ-ስርዓቶችን ቢያከናውንም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የቀደመ ሰላማቸውን መመለስ አልተቻለም፡፡ከሪፈረንደም እስከ ጎንዶሮ ድረስ የሚያደርገው ሙከራ ሁሉ ያልተሳካለት ህወሃት መራሹ ፌደራል መንግስት መላ ሲጠፋው እንደሚያደርገው የጉጅዎች እንቅስቃሴ በኦነግ የሚደገፍ ነው እያለ ሰዎችን ማሰር ጀመረ፡፡እስሩ በጉጅ ኦሮሞዎች ዘንድ የሃይማኖት መሪ ተደርጎ የሚታመንበትን አባ ቃሉ እስከማሰር ደረሰ፡፡የታሰሩት አባ ቃሉ እስርቤት ህይወታቸው ማለፉ የጉጅ ኦሮሞዎችን ቁጣ አባባሰው፡፡መንግስትም በመላ-ቢስ እስሩ እና የጉልበት አካሄዱ ቀጠለበ፡፡

የመንግስት ጉልበት የበረታባቸው ጉጅዎች መንግስት የሚያንገላታቸው ለጌዲኦዎች አግዞ እንደሆነ መገንዘብ ጀመሩ፡፡መንግስትም የጉጅዎቹን እንቅስቃሴ ከኦነግ ጋር አያይዞ በጭካኔው ቀጠለበት፡፡ይህ የመንግስት ብስልት የጎደለው አካሄድ በጌዲኦ እና ጉጅ ታጋዮች መካከል ያለውን መቃቃር እያባባሰው ሄደ፡፡በዚህ መሃከል በሁለቱም ዞኖች ውስጥ የሚኖረው የጉዲኦም ሆነ የጉጅ ህዝብ እንግልት ውስጥ ወደቀ፡፡በተለይ በጉጅ ዞን የሚኖሩ ጌዲኦዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መጥፎ ሁኔታ ውስጥ መኖር ጀመሩ፡፡

ነገሮችን ከማሻሻል ይልቅ በማባሱ የጉልበተኝነት አካሄድ ሲሄድ የኖረው ህወሃት ከማዕከላዊ ስልጣ ወርዶ ኦዴፓ ስልጣን ሲይዝ፣ኦነግ ደግሞ በአካባቢው መንቀሳቀስ ሲጀምር በጉጅዎቹ በኩል እንቅስቃሴው እየተፋፋመ ሄደ፡፡ኦነግ በአካባቢው የሚንቀሳቀስ መሆኑ ደግሞ በጉጅ ዞን ለሚኖሩ ጌዲኦዎች እጅግ አደገኛ ሁኔታ ፈጠረ፡፡አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ስምንት መቶ ሽህ የሚደርሱ ጌዲኦዎች ጉጅ ዞንን ለቀው ወደጌዲኦ ዞን እንዲፈናቀሉ ሆነ፡፡የተፈናቃዩ ብዛት የረድኤት ድርጅቶችን ጉልበት ፈተነ፡፡ህፃናት በክረምት ከቤታቸው ወጥተው በአሳዛኝ ሁኔታ ሜዳ ላይ ፈሰሱ፣ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቀሉ፣ሴቶች፣አዛውንቶች በማያውቁት ሰበብ ከቤታቸው ወጥተው ሜዳላይ ወደቁ፡፡የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ባለፈው የህዝብ ቆጠራ መሰረት በምዕራብ ጉጅ ዞን 14% የሚሆነው ሰው ጌዲኦ ሆኖ በመገኘቱ ውለው አድረው ከተባዙ መሬቱ የእኛ ነው የሚል ጥያቄ ያመጣሉ የሚል እሳቤ ከጉጅዎቹ ዘንድ በመነሳቱ ነው፡፡ይህ ከጎሳ ፌደራሊዝሙ ያገኘነው አስከፊ ቱርፋት ነው ንፁሃንን ከቤታቸው አውጥቶ እያንገላታ ያለው!

መፈናቀሉ ከአንድ አመት በፊት ሲጀመር ስምንት መቶ ሽህ የሚደርሰው የጌዲኦ ተፈናቃዮች ቁጥር አሁን ወደ 1.4 ሚሊዮን እየተጠጋ እንደሆነ “irinnews.org” የተባለው ድረ-ገፅ “Etheiopia’s Neglected Crisis: No easy way home for doubly displaced Gedeos” በሚል ርዕስ ከቀናት በፊት ባወጣው ፅሁፍ አስነብቧል፡፡ ይህ ቁጥር ሃገራችንን በሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከዓለም አንደኛ ያደርጋታል፡፡የድረ-ገፁ ዘገባ ተፈናቃዮቹ ከአንድ አመት ለዘለለ ጊዜ ከቤታቸው ወጥተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሊያዙበት ይገባል ብሎ ካወጣው መስፈርት እጅግ በወረደ ሁኔታ እየኖሩ፣ህፃናት በምግብ እጥረት እና በሽታ እየተሰቃዩ እንደሆነ ያትታል፡፡

እንደ ዘገባው አራት በአራት በሆነች ድንኳ ውስጥ የአራት አባወራ ወደ ሰላሳ የሚጠጉ በተሰቦች ተፋፍገው ይኖራሉ፡፡በዚህ ላይ የረድኤት ድርጅቶች ገብተው እነዚህን ወገኖች እንዳይታደጉ መንግስት በምዕራብ ጉጅ ዞን አድርጎ ወደ ተፈናቃዮቹ የሚወስደውን መንገድ ጠርቅሞ ዘግቷል፡፡በዚህ ምክንያት ህፃናት፣አረጋዊያን ሴቶች እና ሌሎች ተፈናቃዮች ኮሌራን በመሰለ ተላላፊ በሽታዎች፣በምግብ እጥረት፣በውሃ እጦት እየተሰቃዩ እና ማንም ሳያውቅላቸው እያለቁ እንደሆነ ጋዜጠኛው ያነጋጋራቸው የዓለም አቀፍ ረድኤት ድርጅት ሰራተኞች ተናግረዋል፡፡መንግስት ወደ ተፈናቃዮቹ የሚወስደውን መንገድ ለረድኤት ድርጅቶች የዘጋው ተፈናቃዮቹን ወደ ነበሩበት ወደ ምዕራብ ጉጅ ዞን እንዲመለሱ ለማስገደድ ነው ይላሉ የረድኤት ሰራተኞቹ፡፡ተፈናቃዮቹ ደግሞ ከአንድም አራት ጊዜ በኦሮሚያ ክልል ጉጅ ዞን ወደሚገኘው ቀያቸው ለመመለስ ሞክረው በታጣቂ ቡድኖች እና ዘረኛ ጎረምሶች በደረሰባቸው ህይወትን አደጋላይ የሚጥል ማስፈራራት እና ዘረፋ ምክንያት ወደ ጌዲኦ ዞን መልሰው መላልሰው ለመፍለስ ተገደዋል፡፡

ጋዜጠኛው ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች እንደሚሉት የመንግስትን ቃል አምነው እና አክብረው ተወልደው አድገው ወደኖሩበት የጉጅ ዞን ቀያቸው ሲመለሱ በተመለሱበት ቀን ማግስት ማታ በቡድን ሆነው የሚመጡ ታጣቂዎች እና ስለታማ ነገር የያዙ ጎረምሶች ይዘውት የመጡትን ነገር ሁሉ ተዘርፈው፣ቀየውን ለቀው እንዲሄዱ ጥብቅ ማስፈራሪያ እንደተነገራቸው ይገልፃሉ፡፡በዚህ ሁኔታ ከአንድም አራት ጊዜ ስለተመላለሱ ጉጅ ዞን መሄድ እንደሚያፈራቸው እና እንደማይፈልጉ አበክረው ገልፀዋል፡፡ ሆኖም መንግስት የተፈናቃዮቹን ደህንነት በአስተማማኝ ደረጃ ባላስጠበቀበት ሁኔታም ሰዎቹ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል ብቻ ሳይሆን ያስገድዳል፡፡መንግስት የተፈናቃዮቹን መመለስ የሚፈልገው በቅርቡ አደርገዋለሁ ለሚለው ህዝብ ቆጠራ በቀያቸው እንዲገኙ ነው፡፡በተጨማሪም “ተፈናቃዮቹ አሁን ተመልሰው ሚያመርቱትን መሬት ለመጭው ክረምት ለእርሻ ካላዘጋጁ በሚቀጥለው አመት ተረጅ እንዳይሆኑ ስጋት ስላለን ነው” ይላሉ የአደጋ መከላከል ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ካሳ ለድረ-ገፁ በሰጡት መልስ፡፡በሞት ሰቀቀን እና በከፍተኛ የስነልቦና አለመረጋጋት ላይ የቆየ ህዝብ እንዴት አምራች ሊሆን እንደሚችል ተናጋሪው ባለስልጣ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡

ይህ የመንግስት ምክንያት እጅግ አሳዛኝም ሰብዓዊነት የጎደለውም ነው፡፡በመጀመሪያ ነገር እነዚህ ተፈናቃዮች አንድ አመት ሙሉ ሲንገላቱ እንደ መንግስት ስቃያቸውን በሚመጥን ሁኔታ ትኩረት አልተሰጣቸውም፡፡ አንድ የተደረገ ነገር ቢኖር የሰላም ሚኒስትር የተባሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል አምና ተፈናቃዮቹን መጎብኘታቸው ነበር፡፡የሚኒስትሯ ጉብኝት “ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 90%ን ወደቀያቸው መልሰን እያቋቋምን ነው” የሚል የውሸት ሪፖርት ከማዥጎድጎድ ውጭ ያመጣው ነገር የለም፡፡እንዴውም ወ/ሮ ሙፈሪያት ራሳቸው ተፈናቃዮቹ ወደቀያቸው እስካልተመለሱ ድረስ የረድዔት እርዳታ እንዳይደርሳቸው መንገድ መዘጋት እንዳለበት ማዘዛቸውን ነው ከላይ የተጠቀሰው ድረ-ገፅ ያስነበበው፡፡

ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ከተመለሱ ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑን ከአንድም ሶስት አራት ጊዜ በተግባር ተመላሰው አረጋግጠው እየተናገሩ በግድ ካልተመለሱ የረድኤት አቅርቦት እንዳይደረግላቸው የማዘዝ ጭካኔ መንግስትነትን ቀርቶ ተራ ሰውነትን አይመጥንም፡፡ችግር ባይሆንበት ማንም ከቤቱ ወጥቶ ሜዳላይ የመሰጣት እና በረሃብ የማለቅ ፍላጎት የለውም፡፡ ሰዎቹ የኖሩበትን መንደር የፈሩት ያዩትን አይተው ነው፡፡በጉጅ ዞን ኦነግ ከነጠመንጃው እንደሚንጎራደድ እየታወቀ፣መንግስት ራሱ በቴሌቭዥኑ “ይህን ያህል ወረዳ በኦነግ ቁጥጥር ስር ነው” እያለ እየተናገረ ምስኪን ሰዎችን ወደሞት ሂዱ ካልሆነ እዚህ በረሃብ ሌላ ሞት ይጠብቃችኋል ማለት በጣም አሳዛኝ አረመኔነት ነው፡፡

የሰው ልጅ ተፈናቃይም ቢሆን ክብር ያለው፣በምርጫው መኖር ያለበት ፍጡር ነው፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ሲመለሱ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋት ሳይኖራቸው፣በግድ ሳይሆን ወደው፣መመለሳቸው ሌላ መፈናቀል እንደማያስከትል ተረጋግጦ፣ሰብዓዊ ክብራቸውን ባስጠበቀ ሁኔታ መሆን እንዳለበት ደነግጋል፡፡ይህ ቀርቶ ባዕዳን ረጅዎች ለሰዎቹ የእለት ጉርስ ሚደርስበትን ነገር ሲጠይቁ የራስን ወገን በረሃብ ለመግደል መጨከን በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡

ከመንግስት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብም ከሱማሌ ክልል ለተፈናቀሉ፣ከአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚፈናቀሉ ወገኖቹ የሚያሳየውን የወገንተኝነት መቆርቆር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት የጌዲኦ ተፈናቃዮችም ማሳየት አለበት፡፡ችግራቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ማንሳት አለበት፤በፍጥነት ወደተረጋጋ ኑሯቸው የሚመለሱበት መንገድም የሚገኘው ለነገሩ ትኩረት ሰጥቶ በመነጋገር ነው፡፡እነዚህ ሰዎች በየማህበራዊ ድረ-ገፁ ብቅ እያለ ወደቀ ሲባል ተሰበረ የሚል ዘረኛ አክቲቪስት ስለሌላቸው ሰማይ ሙሉ ችግራቸው እንደቀላል ነገር መቆጠር የለበትም፡፡እነዚህ ተፈናቃዮች ለሁላችንም ወገን የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ናቸውና ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ብሶታቸውን ሊያስተጋባላቸው ያስፈልጋል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የኦዴፓ ክንብንብ ሲወርድ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
የካቲት 24 2011 ዓ.ም.

ሃገራችን ኢትዮጵያ ከህወሃት አረመኔያዊ አገዛዝ ለመላቀቅ ባደረገችው የትግል ምጥ “የለማ ቡድን” የተባለ የድንገቴ ልጅ ታቀፈች፡፡ይህ ቡድን አለ ወይስ የለም የሚለው ራሱ ሲያጠራጥር ነበረ፡፡መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ከህወሃት ባርነት ነፃ የመሆን አለመሆኑ ነገር ብዙ ሲያከራክር ቆየ፡፡ከህወሃት ነፃ መሆኑን ፈጣሪ ጌታውን ራሱን ህወሃትን ከስልጣን ገፍትሮ ጥሎ አሳየ፡፡በስተመጨረሻው እንደ አውሬ አድርጎት የነበረውን ህወሃትን ገፍትሮ በጣለ ቅፅበት ኦዴፓ የኢትዮጵያን ህዝብም በአደንዛዥ ፍቅር ጣለ፡፡የፍቅር ብዛት ትንታግ ተቃዋሚውን ገራም ባለሟል፣አዋቂውን አላዋቂ፣ተጠራጣሪውን አማኝ አደረገለት፡፡የወዳጅ ጠላቱ በፍቅር ሰመመን ውስጥ መውደቅ ኦዴፓ የሚሰራው ሁሉ በመላዕክት ጉባኤ የተወሰነ ቅዱስ ሃሳብ ተደርጎ እንዲወሰድ አደረገ፡፡ብዙው ሰው በፅኑ ፍቅር መመታቱን ያጤነው ኦዴፓ ከአባቱ ኦነግ፣ከጌታው ህወሃት የወረሰውን ዘረኝነቱን ፈራ ተባ ሳይል ያስኬደው ጀመር፡፡

የመጀመሪያው የኦዴፓ እውነተኛ ማንነት የተገለጠው ስልጣን በያዘ ማግስት ህግ ጠረማምሶ የአዲስ አበባ ምክርቤት አባል ያልሆነ ሰው የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሲሾም ነው፡፡ ኦዴፓ የፌደራል ስልጣን ላይ ተስተካክሎ ሳይቀመጥ ገና እንዲ ያለ ህግ የመጣስ ድፍረት ያሳየው በአዲስ አበባ ላይ የነበረውን አላማ ለማስፈፀም ካለው ጉጉት አንፃር ነው፡፡ታከለ ዑማ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርጎ የተሾመው ሰውየው ከኦሮሞነቱ በተጨማሪ የሰፈረበት የኦነግ መንፈስ ብርታት ስለተፈለገ ጭምር ነው እንጅ በአዲስ አበባ ካውንስል ውስጥ ኦሮሞ ፈልጎ ማግኘት አስቸግሮ አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ ግራ አጋቢው አዲስ አበባን መምራት ያለበት ኦሮሞ ብቻ ነው የሚለው ህግ ከየት እንደመጣ ነው፡፡

የኦዴፓ ክንብንብ የወረደበት ሌላው አጋጣሚ የኦነግ ሼኔ አመራሮችን ወደ አዲስ አበባ መግባት ተከትሎ በቡራዩ የተደረውን አሳዛኝ ጭፍጨፋ ማዳን ሲችል አለማዳኑ፣ነገሩ ከተከሰተ በኋላም ገዳዩን በጥብቅ የህግ ክትትል ስር ለማድረግ ወገቤን ማለቱ ነው፡፡ይህ ሳያንስ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለቃቅሞ ከሃገር ዳር አውጥቶ ሁለትም ወር ሙሉ በበረሃ እስርቤት ማጎሩ ነው፡፡በበኩሌ የኦዴፓ ነገር የበቃኝ የዚህ ጊዜ ነው፡፡ ኦዴፓ መራሹ መንግስት ያንን ሁሉ የአዲስ አበባ ወጣት ያለምክንያት ሲያስር ለመታሰራቸው በቂ ምክንያት ያላቸውን የቡራዩ ነፍሰ-ገዳዮች በብር ዋስ እየፈታ ነበር፡፡በዚህ ላይ የአዲስ አበባ ልጆች መታሰራቸው ትክክል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኦዴፓ ዋና ዋና ባለስልጣናት እየተፈራረቁ ያስረዱን ነበር፡፡የአዲስ አበባ ወጣቶች እስር ደግሞ ማንን ለማስደሰት እንደሆነ ግልፅ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ ኦዴፓ ከህወሃት ባላነሰ ስልጣን እና ዘረኝነት የሚያመጡትን ብልግና የመድገም “ብቃት” እንዳለው መገመት ከባድ አልነበረም፡፡ አሁን እያደረገ ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡

በሶስተኝነት የማስቀምጠው በግሌ ኦዴፓን የመረመርኩበት አጋጣሚ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተ-መንግስት መግባታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩት ንግግር ነው፡፡ጠ/ሚ አብይ በፓርላማ ተገኝተው “የወታደሮቹን ቤተ-መንግት ሰተት ብሎ መግባት እንደቀላል ነገር በቴሌቭዥን ያወራሁት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ኦሮሞዎች መንግስታችን ወደቀ ብለው በፈረስ እንዳይደርሱ ፈርቼ ነው” ብለዋል፡፡ፍቅር አይኑን ላልሸበበው ሰው ይህ ንግግር ብዙ ትርጉም አለው፡፡ከሁሉም በላይ ግን አብይ “የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ” ሲሉ የባጁትን ንግግር ልባዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡አብይ ቦምብ ሲወረወርባቸው በእጁ የተከላከለላቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ቢሆንም ለእርሳቸው የክፉቀን ደራሽ፣የዙፋናቸው ደጀን ሆኖ የሚታያቸው የሆሎታ እና የሱሉሉታ ፈረሰኛ ኦሮሞ ነው፡፡ከዚህ መረዳት የሚቻለው የዘር ፖለቲከኛ የአንገት እና የአንጀት ወዳጅ እንዳለው ነው፡፡የዘር ፖለቲከኛ ከዘሩ ህዝብ ጋር እኩል ያየኛል፣የእኩልነት ፖለቲካ ያመጣልኛል ብሎ መድከምም ለቂልነት የሚዋሰን ነገር ነው፡፡

አራተኛው እና ዋናው ክንብን አውራጅ ስራ የተሰራው ህግን እና ደምብን ባልተከተለ መንገድ ከኦሮሚያ ክልል ለመጡ ሰዎች የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ በገፍ መታደል ሲጀምር ነው፡፡ነገሩን በጣም አሳፋሪ የሚያደረገው ነገር ደግሞ መታወቂያው የተሰጠው ከንቲባው በገዛ አንደበታቸው “በአዲስ አበባ ማንኛውንም አይነት መታወቂያ መስጠት አቁመናል” እያሉ በሚያወሩበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ከዚህ የባሰው አስገማች ነገር ደግሞ ይህን የእብሪት እና ማንአለብኝነት ህገወጥ አሰራር ያጋለጠችን ወ/ሮ ሰናይት የተባለች የእውነት ሴት ከስራ ማባረሩ ነው፡፡ከስራ መባረሯ ተሰምቶ በህዝብ ዘንድ ጉም ጉም ሲያስነሳ ሴትዮዋን ወደ ስራዋ ለመመለስ ተብሎ የተፃፈው ደብዳቤ አስተዛዛቢ ነው፡፡የደብዳቤው ይዘት ኦዴፓ በህወሃት ቤት በአሽከርነት ሲያድግ እንዴት ጌታውን መስሎ እንዳደገ አመላካች ነው፡፡የህወሃትን መልክ ጠልቶ ቢቸግረው ኦዴፓን ያመነው ህዝብ ደግሞ በማንም ውስጥ መልሶ የህወሃትን መልክ የማየት ፍላጎትም ትዕግስትም የለውም፡፡ይህን አለመረዳት የውርደት ሞት ይገድላል!

ቀድሞ ከተገለፁት በልጦ በኦዴፓ እውነተኛ ማንነት ላይ ግልፅ ምስክር የሆነው የለገጣፎ ቤት የማፍረስ ክስተት ነው፡፡ይህ በምላስ ሊጋርዱት የማይችሉት ያፈጠጠ ገበና ነው፡፡የለገጣፎው ነገር ኢህአዴግን የመሰለ ዘረኛ ድርጅት ዙፋን ላይ አስቀምጦ ስለ ሰብዓዊ መብት ማውራት ለቅሶቤት እንደመዝፈን ያለ ዕብደት እንደሆነ ያስመሰከረ ሃቅ ነው፡፡የለገጣፎው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ኢ-ሰብአዊነት ብዙ የተባለለት ስለሆነ ወደዛ መግባቱ ላያስፈልገኝ ይችላል፡፡ይልቅስ ጉዳዩን አስመልክቶ የኦዴፓ መራሮች የሚናገሯቸውን ንግግሮች ተንተርሰን የፓርቲውን ማንነት ወደመመርመሩ ማለፉ የተሻለ ይሆናል፡፡

የለገጣፎው ቤት የማፍረስ አካሄድ እንዴት ትክክል እንደሆነ የሚያስረዱ የኦዴፓ ባለስልጣናት በተለይ ከንቲባዋ ወ/ሮ ሃቢባ ነገራቸውን የሚጀምሩት የለውጥ/የተሃድሶ አመራር መሆናቸውን በመጥቀስ ነው፡፡የለውጥ አመራር ነኝ ባይዋ ሴትዮዋ ወ/ሮ አዜብ እንዳደረጉት በኢሳቷ ጋዜጠኛ ኢየሩሳሌም ተክለፃዲቅ ጆሮ ላይ ስልክ ጠርቅመው ዘግተዋል፡፡ስልክ መዝጋቱን ያመጣው ጋዜጠኛዋ የማያፈናፍን ጥያቄ በማቅረቧ ነው፡፡ ወ/ሮ ሃቢባ ስልክ ከመዝጋታቸው በፊት ምንም አይነት ሰው እንዳላፈናቀሉ፣የመፈናቀሉን ወሬ የሰሙት በኢሳት እንደሆነ ተናግረው ሳይጨረርሱ ደግሞየፈረሰው ቤት ሁለት መቶ ሆኖ ሳለ ኢሳት አራትመቶ ብሎ ማውራቱ ልክ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ሁለት መቶ ቤት ፈርሶ ምንም ሰው የማይፈናቀለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እንጓጓሁ ስልኩን ጠርቅመው ዘግተው አረፉት፡፡

ከኢሳት እንዲህ የተሰናበቱት የለገጣፎ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ የቡራዩውን ከንቲባ አስክለው “OMN” በተባለው ቴሌቭዥን ላይ በአካል ቀርበው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ቤት ማፍረሱ እንዴት ትክክል እንደሆነ ለማስረዳት ሁለቱም ከንቲባዎች ከ2004 በፊት እና በኋላ የሚል ነገር ያስቀምጣሉ፡፡ከ2004 በፊት ግንባታ ያደረጉ ሰዎች ህጋዊ ካርታ እንዳገኙ ጠቅሰው ከ2004 በኋላ የሰፈሩቱ እና ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር ግጭት ያለው አሰፋፈር የሰፈሩ (ለምሳሌ በማስተር ፕላኑ የኦሮሞን ባህል ለማሳደግ ሲባል የፈረስ መጋለቢያ፣የአረንጓዴ መናፈሻ ቦታዎች ተደርገው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የገነቡ) ሰዎች ቤታቸው መፍረሱ ህግን የማስከበር ስራ እንደሆነ ደጋግመው አስረድተዋል፡፡

ቤት የፈረሰባቸውን ሰዎች ገበሬውን አታለው በትንሽ ዋጋ መሬቱን ገዝተው የሰፈሩ መሬት ወራሪዎች እንደሆኑ ሁለቱም ከንቲባዎች ያስረዳሉ፡፡ይህ የዘር ፖለቲካ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡መሬት የብሄር ብሄረሰቦች ነው በሚለው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት ገንዘብ ሲፈልግ መሬቱን መጤ ለተባለ ሰው የሸጠ ብሄር ብሄረሰብ ገንዘቡ ሲያልቅበት መሬቱንም የመከጀል መብት ያለው ይመስለዋል፡፡ይሄን አስቂኝ ክርክር ከገበሬው እሻላላሁ ብሎ ስልጣን ላይ የተወዘፈ የዘር ፖለቲካ ባለስልጣንም እንደሚጋራው የለገጣፎዋ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ እና ቢጤዋ የቡራዩው ከንቲባ ምስክር ናቸው፡፡ወ/ሮ ሃቢባ ህዝብን ማፈናቀላቸው፣ከቤት ጋር ህይወት ማፍረሳቸው ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የመስራታቸው መገለጫ እንደሆነ፣ከዚህ በፊትም እንዲሁ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ሲታገሉ እንደኖሩ፣ወደፊትም በዚህ እንደሚቀጥሉ ኮራ ብለው ተናረዋል፡፡ከዚህ የምንረዳው የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየው በዘረኝነቱ ህወሃትን የሚያስንቅ እንደሆነ ነው፡፡

“ገበሬው ተታሎ በዝቅተኛ ዋጋ መሬት ሸጠ” የሚለው ከእውቀት ነፃ የሆኑ ዘረኛ ባለስልጣናት ክርክር አስቂኝም አስገራሚም ነው፡፡ ገበሬው ተታሎ በትንሽ ዋጋ የሚሸጠው መሬቱን ብቻ የሆነው እንዴት ነው?ገበሬው ምነው ተታሎ ኩንታል ጤፉን በአምስት መቶ ብር ሸጦ አያውቅ? ምነው ተታሎ ሰንጋ በሬውን በአንድ ሽህ ብር ሲሸጥ አልታየ?ይህ ከአዝጋሚ ጭንቅላት የሚመነጭ ክርክር አላማው “ወገንን” አድኖ “መጤን” ለማጥቃት ነው፡፡ገበሬው ተታለለ የሚለው መሬት መሸጥ ህገወጥ መሆኑንም ሳያውቅ ነው የሸጠው፣ተታሎ በትንሽ ዋጋ ስለሸጠ የሚገባውንም ጥቅም አላገኘም በሚል መሬቱን ሼጦ የበላውን “ወገን” አርሶ አደር ነፃ በማድረግ “መጤው” ላይ እርምጃ ለመውስድ ያለመ አካሄድ ነው፡፡እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ገበሬው መሬቱን የሚሸጠው ግራቀኝ አስቦ፣የሚጠቅመውን አውቆ ነው፡፡በተለይ ከ1997 ወዲህ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የአዲስ አበባ ዙሪያ መሬቶችን በኢንቨስትመንት ስም እየቀማ፣ለገበሬው የአይብ መግዣ የማይሆን ካሳ ከፍሎ ማፈናቀል ጀምሮ ነበር፡፡ይሄኔ ገበሬው መንግስት መጥቶ በማይረባ ገንዘብ ሳያፈናቅለው በፊት መሬቱን በጣም በተሻለ ዋጋ ለግለሰቦች መሼጡን አማራጭ አድርጎ ወስዶ ነበር፡፡እንዲህ ጥቅም ጉዳቱን አመዛዝኖ የሸጠው ገበሬ ነው እንግዲህ ተታሎ በርካሽ ሸጠ የሚባለው፡፡

ከገበሬው ቀጥሎ ማዳን የተፈለገው ደላላም፣ባለስልጣንም ሆኖ መሬቱን ሲቸበችብ የነበረውን የኦህዴድ ባለስልጣን ነው፡፡ከገዥም ከሻጭም የበለጠው ጥፋተኝነት ያለው በነዚህ ካድሬዎች ላይ ሆኖ ሳለ የእነሱ ጥፋተኝነት በለሆሳስ ይታለፍና ጦሱ ሁሉ የሚወድቀው ኦደፓ ከቆመለት የኦሮሞ ህዝብ ውጭ የተወለዱ፣”ያለግዛታቸው መጥተው ቤት የሰሩ ሰዎች” ላይ ነው፡፡ይህ የኢህአዴግ ዘረኝነት አይነተኛ መለያ ነው፡፡እነዚህ በበስልጣናቸው ላይ ደላላነት እና ሌብነት የደረቡ ባለስልጣናት ላይ የማይጨከነው አሁን ደግሞ ተገልብጠው “የለውጥ አመራር” ተብለው የአብይን እና የለማን ዙፋን የሚሸከሙ ስለማይጠፉ ነው፡፡

ከለገጣፎ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ በ”OMN” ማብራሪያ ከሰጡት የቡራዩ ከንቲባ ንግግር ደግሞ ጉዳዩ ህገ-ወጥ ያሉትን ግንባታ ከማፍረስ አለፍ ያለ አላማ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ከንቲባው ስለጉዳዩ ሲያስረዱ መሬት ወራሪዎቹ አንድ ቤት ከገዙ በኋላ ብዙ ዘመድ አዝማዳቸውን እየጎተቱ እንደሚያመጡ፣በአንድ መሬት ግዥ ሰበብ በተገዛው ጊቢ ውስጥ ብዙ ሰው እንደሚሰፍር በምሬት ገልፀዋል፡፡ይህ ንግግራቸው የፓርቲው ጠብ ከቤቱ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በቤቱ ውስጥ ከሚኖሩ ግለሰቦች ማንነት እና ብዛት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሳያውቁት ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ ሃቢባ ከተል ብለው እነዚህ ሰዎች እዚህ አካባቢ መጥተው የሰፈሩት የሆነ ድብቅ ዓላማ ይዘው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በሴትዮዋ አስተሳሰብ ሰዎቹን ለገጣፎ የወሰዳቸው የቤት ችግር ሳይሆን ኦሮሞ ሳይሆኑ ኦሮሚያን የመውረስ “እኩይ” ሃሳብ ነው፡፡በዚህ ያልበቃቸው ሃቢባ የሰዎቹ መፈናቀል ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው(በሃቢባ አነጋገር ጫጫታ ያስከተለው) ተፈናቃዮቹ ሚዲያ ከሚጮህት ሁለት ክልል የመጡ በመሆኑ እንደሆነ ንዴት እየተናነቃቸው ተናገሩ፡፡አሁንም ሳያውቁት ማፈናቀሉ ዘር የለየ እንደነበር በገዛ አንደበታቸው አወጁ! ስልጣን ለመያዝ የዘረኝነት ልክፍት እንጅ እውቀት እና ማገናዘብ ከማይጠየቅበት ከኢህአዴግ ቤት እንዲህ ያለ ኩርማን ሃሳብ ያው ሰው ከንቲባ ሆኖ ቢገኝ ገራሚ ነገር የለውም፡፡

የሃገሪቱን ህዝብ በሰፊው ሲያነጋግር፣የኦዴፓን ማንነትም በገሃድ ሲያሳይ የሰነበተውን የለገጣፎውን የቤት ማፍረስ ተግባር አስመልክቶ ገዥውን ኦዴፓን የሚመሩት ዶ/ር አብይም ሆኑ ክልሉን ኦሮሚያን የሚመሩት የነወ/ሮ ሃቢባ አለቃ አቶ ለማ መገርሳ ትንፍሽ ሳይሉ መሰንበታቸው የሚያሳየው ከግፉ ተቃራኒ መቆማቸውን ሊሆን አይችልም፡፡ሳምንት ቆይተው ስለጉዳዩ ሲናገሩም ጠ/ሚንስትሩጭራሽ አልሰማሁም ሲሉ አቶ ለማ በዝምታቸው ቀጥለዋል፡፡ ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉ ፓርቲዎች ዝምታ ነው፡፡ይህ ነገር የዜግነት ፖለቲካ ሁነኛ ጠበቃ የሌለው የፖለቲካ አሰላላፍ ለመሆኑ ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡
__

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

“የዶሮ ሻኛ አምጣ” የሚባለው ኤርሚያስ አመልጋ(በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
የካቲት 19ቀን 2011 ዓ.ም.

ኢትዮጵያችን በፖለቲካ ጣሯ ላይ የኢኮኖሚ ደዌ የደረበች ጎስቋላ ሃገር ነች፡፡”አፍርሻት ልፍረስ” የሚለው የፖለቲካ ዛሯ ተሻለው ሲባል የሚብስበት መሆኑ ብቻ አይደለም ክፋቱ-ኢኮኖሚዋንም ይዤ ልሙት ማለቱ እንጅ፡፡ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲጠፉም ሲለሙም አብረው የሆኑ መንትያዎች በመሆናቸው አንዱን ለይቶ ጤናማ ማድረግ አይቻልም፡፡ፖለቲካው ካለመፈወሱ የተነሳ ኢኮኖሚውም እንዲሁ በህመም ላይ ይገኛል፡፡ፖለቲካውን የተጣባው ዘረኝነት ፣ኢፍትሃዊነት፣ሴረኝነት ፣ማስሰመሰል፣እውቀት አልቦነት ሁሉ በኢኮኖሚው ላይም ይንፀባረቃል፡፡ነግዶ ለማትረፍ፣ተናግሮ ለመሰማት፣ወጥቶ ለመመግባት ወሳኙ ነገር መርጠን ያልተገኘንበት ዘር፣መቼ መናገር እንደ ጀመርን እንኳን የማናውቀው ቋንቋ ሆኗል፡፡

እንዲህ ባለው እጅግ ኋላቀር የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት ከማምጣት ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል፡፡በውስብስቡ ድህረ-ዘመናዊ ዘመን እየኖርን በቅድመ-የድንጋይ ዘመን ነጠላ የኑሮ ዘይቤ መኖር መርጠናል፤የሰው ነጠላ ማንነቱ የሚናገረው ቋንቋ ብቻ ይመስለናል፡፡ስለዚህ አሁን ያለንበትን ውስብስብ ዘመን የሚመጥን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እንዲኖር የሚፈልጉ ሰዎችን እስከ አድማስ ዳርቻ እናሳድዳለን፡፡ህልማቸውን፣አበርክቷቸውን፣ወደፊት ደግሞ ሊጠቅሙ የሚችሉትን አስበን መንገዳቸውን ከማቅናት ይልቅ ትንሳኤ የሌለው ሞት እንዲሞቱ እንሰራለን፡፡ይህን ለማድረግ ደምባደምቦችን፣መመሪያዎችን እንደገፋለን፡፡ፖሊሲዎቻችን፣ህጎቻችን እንዴት እንደሚሳካ ሳይሆን እንዴት እንደማይሳካ ይደነግጋሉ፡፡አለማስቻልን በህግ ደንግገን እንኖራለን፡፡ይህን ጉዳይ በተግባር የሚያሳይ አንድ ገጠመኜን ላጋራ፡፡

በቅርቡ ቪዥን ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ባዘጋጀው የጥናት መድረክ ተገኝቼ ነበር፡፡የአዲስ አበባን የትራንስፖርት ችግር የማቃለል ስራ ለመስራት ከአሜሪካን ሃገር የመጣ አንድ ወጣት በዚሁ ጉዳይ ላይ ስላሉ ችግሮች ጥናት ሊያቀርብ ተገኝቶ ነበር፡፡ስራውን ለመስራት ወደ ተግባር ሲገባ የገጠመውን በመመሪያ እና ደምባደምብ የተጠቀለለ መሰናክል ሲያቀርብ መስማት ራሱ ራስ ያዞራል፡፡ልጁ በጥናቱ የሃገራችንን በህግ፣መመሪያ እና ምባደምብ የተደገፈ ያለማስቻል ከባቢ ከሌሎች ሃገሮች ጋር እያወዳደረ ሲያቀርብ ሁለት ውስጤ የቀሩ ለአንባቢም ላጋራ የምወደውን ምሳሌዎችን አመጣ-የፌስ ቡክን እና የማይክሮ ሶፍትን ጉዳይ፡፡

ፌስቡክን እና ማይክሮ ሶፍትን የፈጠሩ ስራ ፈጣሪዎች (ማክዙከምበርግ እና ቢልጌትስ) ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ቢሆኑ ኖሮ አንድ እርምጃ ሳይራመዱ በደምባደምብ ዱላ እግራቸውን ተቀልጥመው እንደሚቀሩ አስረዳን፡፡ነገሩ እንዲህ ነው የኢትዮጵያ ህግ አንድ ሰው የሆነ ሥራ ለመስራት ፈቃድ ለማግኘት በሚሰራበት ስራ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው ያስፈልጋል ይላል፡፡በተጨማሪ በድሃዋ ሃገራችን ኢትዮጵያ አንድ ስራ ለመጀመር መንግስት እንዲፈቅድለት ስራ ፈጣሪው ምን የመሰለ ቢሮ፣ከነ ሙሉ ቁሳቁሱ ማሳየት ግድ ይለዋል፡፡ማክከምበርግ አና ቢልጌትስ ደግሞ ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሳይመረቁ አቋርጠው የወጡ፣ሥራ ሲጀምሩ ቢሮ የሚባል ነገር ያልነበራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ስለዚህ የፌስቡክንም ሆነ የማይክሮ ሶፍትን ሃሳብ ያመጣው ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ቢሆን ኖሮ ፌስቡክ እና ማይክሮ ሶፍት የሚባሉ ካምፓኒዎች በዓም ላይ አይኖሩም ነበር ሲል ጥናት አቅራቢው በቀላል ምሳሌ የሃገራችንን ከድህነት ጋር በህግ መተሳሰር በደምብ አስረዳን፡፡

በሃገራችን የሚወጡ ህጎች፣መመሪያዎች እና ደምቦች ሃገሪቱን በሚመራው ካድሬ የእውቀት ልክ የተሰፉ ናቸው፡፡ከካድሬ እውቀት አድማስ ሻገር ያለ ነገር ያመጣ ሰው ሃሳብህ ከህግ ማዕቀፍ ውጭ ስለሆነ የምናስተናግድበት ህግ፣መመሪያ እና ደምብ የለንም እና ሃሳብህን ይዘህ ቁጭ በል ወይ ወደ መሄጃህ ሂድ ይባላል፡፡በዚህ ላይ ሃሳቡን ያመነጨው ሰው የተወለደው “ከትምክህተኛ” ይሁን “ከጠባብ” ዘር መሆኑ ደግሞ ዋናው ነገር ነው!በዚህ ምክንያት ሃገራችን ሃሳብ ያለው ሁሉ መጥቶ አይቷት ላይመለስ ጥቁር ድንጋይ ወርውሮባት የሚሄድ ሃገር ሆናለች፡፡የሆላንድ ካርስ ባለቤት፣የኢትዮጵያ አማልጋሜትድ ሊሚትድ ባለቤት አቶ ገብረየስ ቤኛ ሃገራችን ካስመረረቻቸው ባለሃብቶች እና ስራ ፈጣሪዎች መካከል ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ሃገራችን የታሰረችበት ለእድገት የመይመች ትብታብ አላላውስ ሲላቸው ነገር አለሙን ትተው ስደትን የመረጡ ሰዎች ናቸው፡፡የልብ ሃኪሙ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም ሌላ ተጠቃሽ ሰው ናቸው፡፡

ሌላው የካድሬ ፖለቲካ መረብ እጅግ ካወካቸው ሰዎች ውስጥ ተጠቃሹ ታዋቂው ስራ ፈጣሪ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡አቶ ኤርሚያስ ከዓመታት በፊት ወደ ሃገራቸው በመጡበት ወቅት ያዩት የሃገሪቱ ኋላቀርነት እዚሁ ቀርተው እውቀት ልምዳቸው በሚችለው አቅም የሃገር እድገት ለማገዝ በድንገት እንደወሰኑ ተናግረዋል፡፡በሃገር ውስጥ ቆይታቸው የሰሯቸው የስራ ፈጠራዎች በሃገሪቱ ተሰርተው የማያውቁ አዳዲስ ሃሳቦችን የያዙ ችግር ፈቺ ስራዎች ናቸው፡፡ስራ ፈጠራ ከችርቻሮ ንግድ የሚለይ መሆኑን በተግባር ያስመሰከሩ ሰው አቶ ኤርሚያስ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡በሃገሪቱ ለዘመናት ሲፈስ የኖረውን የምንጭ ውሃ አሽጎ ለአገልግሎት የማዋልን ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጡት አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡አሁን ከሰማኒያ የሚልቁ ውሃ አሽጎ ሻጭ ነጋዴዎች በሃገራችን ችርቻሯቸውን ሲያጧጡፉ የስራው ጀማሪ አቶ ኤርሚያስ ከስራው እጣ ፋንታ እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ስም ማጥፋቶች እና ቢሮክራሲያዊ ጦርነቶች ተደርጎባቸዋል፡፡

በግላቸው በቢዝነሱ ዓለም ያላቸውን እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ሲንቀሳቀሱ በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ ያስተዋሉትን እጅግ የተንቀራፈፈ ኋላ-ቀር አሰራር ተመልክተው ዝም ብሎ ከማማረር ይልቅ ዘርፉን ለማዘመን የበኩላቸውን ለማበርከት በመወሰን ዘመን ባንክን መሰረቱ፡፡ዘመን ባንክን ሲመሰርቱ በአንድ ቅርንጫፍ ተገልጋይ ያለበት ድረስ በመሄድ አገልግሎት የመስጠት እና ሌሎች ዘመናዊ የባንክ አሰራሮችን ለማስተዋወቅ ነበር ህልማቸው፡፡አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ዘመን ባንክን በመመስረታቸው ብዙ ግፍ የደረሰባቸው ቢሆንም ሰውየው ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ፊታቸውን በማዞራቸው ብቻ በሚገርም ሁኔታ የሃገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ እንዲዘምን ረድተዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ከመግባታቸው በፊት የሃገራችን ባንኮች ምሳ ሰዓት ላይ ይዘጋሉ፣ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ የውስጥ ስራ ስለምንሰራ ለደምበኛ አገልግሎት አንሰጥም ብለው መስኮት በራቸውን ጠርቅመው ይቀመጡ ነበር፡፡ቅዳሜ አይሰሩም፣ማታ መስራት አይታሰብም፡፡የመክፈያ መንገዳቸው በቢሯቸው መስኮት ላይ ሰው አሰልፎ ገንዘብ ማደል፣ቢበዛ ቼክ ፅፎ መስጠት ነበር፡፡ቅዳሜን ጨምሮ በምሳ ሰዓት መስራትን፣በመስኮት አስልፎ ከመክፈል ባለፈ ደምበኛው ድረስ ወርደው የሚደረጉ የተለያዩ ቀልጣፋ የክፍያ አይነቶችን(ለምሳሌ እነ ኤም ብር አይነት) በስራ ላይ የማዋልን ሃሳብ ያመጡት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ናቸው፡፡ዘጠኝ ሰዓት ላይ የውስጥ ስራ ለመስራት በሚል ለደምበኛ ይከረቸሙ የነበሩት የባንክ ቤት በሮች የተከፈቱት አቶ ኤርሚያስ ለዘመን ባንክ አሰራር ካመጡት ዝመና ጋር አብሮ ለመራመድ ነው፡፡አሁን የእስር ድግስ እየተገሰላቸው በነበረበት ሰሞን ደግሞ አቶ ኤርሚያስ አሊባባ ከተባለው ታዋቂ ኩባንያ ጋር በመተባበር ማንም ያላሰበውን የኢ-ፋይናንስ አሰራርን በሃገራችን ለማስተዋወቅ እየጣሩ ነበር፡፡ይህን ህልማቸውን እንዳረገዙ ነው እስርቤት የተወረወረሩት፡፡

በሪል ስቴት ኢንዱስትሪው በኩልም ቢሆን አቶ ኤርሚያስ ያበረከተው አዲስ ነገር አለ፡፡ከከተማ ዳር ወጥቶ ቪላ ቤት አንጣሎ መኖርን የሚችል አቅም ለሌላቸው፣ከሃገር ሳይወጡ መሃል ከተማ ላይ አፓርትመንቶችን ሰርቶ ለተጠቃሚ በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብን ሃሳብ አመንጭተው ስራ የጀመሩ የመጀመሪያው ሰው አቶ ኤርሚያስ ናቸው፡፡ሥራ ፈጣሪው ይህን ሲያስቡ ለራሳቸው መኖሪያቤት የሌላቸው በኪራይ ቤት የሚኖሩ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡የቸርቻሪ ነጋዴ እና እንደ አቶ ኤርሚያስ ንግድን በእውቀት የሚያስኬድ ስራ ፈጣሪ ልዩነታቸው ይህ ነው፡፡ቸርቻሪ ነጋዴዎች ለደምበኛ የመኖሪያ ቤት የሚያቀርብ ንግድ ውስጥ የሚገቡት ለራሳቸው እና ለልጅ ልጆቻቸው አንድ ቀበሌ የሚያክል ግዛት ላይ ቤተ-መንግስት የሚመስል ቤት ከደረደሩ በኋላ ነው፡፡እንዲህ ያሉት “ራስ ደህና” ባይ ነጋዴዎች እስርም፣ክስም አጠገባቸው አይደርስም፡፡በአንፃሩ ስራ ፈጣሪው አቶ ኤርሚያስ የዶሮ ሻኛ አምጣ እየተባለ ፍርድቤት ይመላለሳል፡፡የመንግስት ቢሮክራሲ አዝግሞ እስኪደርስ ድረስ ቀድሞ ስራውን አጠናቆ መጠበቅም ኤርሚያስ ጋር ሲደርስ ወንጀል ሆኖ ያስከስሰዋል፡፡ሰውየውን ከዘመን ባንክ እጣፋንታ ያጎደለው ባንኩን ለመመስረት የተያዘው ገንዘብ ሁለት አመት በመንግስት ቤት ተዘግቶበት እስኪቀመጥ ድረስ እሱ ስራ ከመፍታት ብሎ የራሱን ገንዘብ አውጥቶ የሰራተኛ ቅጥርን ጨምሮ ለባንኩ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ቀድሞ በማሟላቱ ነበር፡፡

ብዙ ብዙ ያየበት፣እጅግ ስሙ የተነሳበት የአክሰስ ሪል ስቴት ግንባታ መዘግየት መነሻ ሰበቡ የመንግስት ብድግ ብሎ ግንባታ ማገድ ነው፡፡ግንባታው ሲታገድ ለደምበኛ ሰርቶ ለማስረከብ የተገባውን ቃል በቀነ ቀጠሮው ማድረስ የማይቻል ነገር እንደሆነ ግልፅ ነገር ነው፡፡ከዚህ በኋላ ችግር ችግርን እየወለደ፣የአንድ ወገን ብቻ እውነት እየተሰማ ስለቀጠለ ኤርሚያስ ከጥፋቱ በላይ ጥፋተኛ ሆኖ ብዙ ችግር ደረሰበት፡፡በዚህ ሁኔታ የኤርሚያስ ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል አንድ ነጥብ ግንባታው ሲታገድ የገንዘብ ዲፕሪሽየሽንን ለመቀነስ ሲል የመሬት ግዥ ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ይህ እጁ ላይ ያለው ገንዘብ እንዲያልቅና ገንዘብ ይመለስልን ለሚሉ ደምበኞቹ ቃል በገባው መሰረት ገንዘቡን መመለስ እንዳይችል አደረገው፡፡ይህ ራሱ ጥፋት ነው ለማለት አስቸጋሪ የሚሆነው ደግሞ አንድም የቻለውን ያህል ለደምበኞቹ ገንዘባቸውን ለመመለስ መሞከሩ፣ ሁለትም ወደ መሬት ግዥ የገባው ግንባታው ሳይካሄድ በቆየ መጠን ሊመጣ የሚችለውን የገንዘብ ዲፕሪሽየሽኑን ለመከላከል ነበር፡፡እንዲህ ያለ የዕቅድ መዛባት ሲገጥመው ሌላው የሃገራችን ነጋዴ ሪስኩን ሁሉ ጠቅልሎ የሚጭነው ደምበኛ ላይ ነው፡፡ ኤርሚያስ ግን ይህን ማድረግ ስላልፈለገ ነበር መሬት ግዥ ውስጥ የገባው፡፡

ሌላው የኤርሚያስ ጥፋት ተብሎ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ በመጀመሪያ ወደ ገበያው ሲገባ አለቅጥ ለደምበኞቹ ያደላ ቃል በመግባቱ ነው፡፡ከደምበኞቹ ጋር ውል ሲገባ አንደኛ ደምበኞች በማንኛውም ሰዓት ቤቱን አንፈልግም ብራችን ይመለስ ካሉ ብራቸውን እንደሚመልስ ቃል ገብቷል፡፡ሁለተኛ ቤቱን ሰርቶ ለማስረከብ ቃል በገባው ጊዜ ገደብ ሰርቶ ማስረከብ ካልቻለ የደምበኞችን ብር ከነወለዱ እንደሚመልስ ቃል ገብቷል፡፡እነዚህ ሁለት አለቅጥ ለደምበኛ ያደሉ ሁኔታዎችን ማድረግ ያስፈለገው ያለምንም ማዛባት ቤቶቹን ሰርቼ አስረክባለሁ የሚል መተማመን በኤርሚያስ ጋር ስለነበረ ሁለትም የቤት ሽያጩ ዋጋ ለገዥ እጅግ አጓጊ በመሆኑ ገዥ ገንዘቤን መልስልኝ ሊል አይችልም ከሚል መተማመን ሊሆን ይችላል፡፡ትልቁ ስህተት ያለው እዚህ ጋ ነው፡፡

ህወሃትን የመሰለ ዘረኛ እና አምባገነን ቡድን በሚመራት ሃገር ሁሉም ነገር ሙሉ እና ዝግጁ ሆኖ ስራየን እሰራለሁ ብሎ ማሰብ ኢትዮጵያን አለማወቅ ነው፡፡ኤርሚያስ ያየው የራሱን ስራውን ዳር የማድረስ ጉጉት እና እሱ ሊቆጣጠራቸው የሚችላቸውን ጉዳዮች መሰናዳት ነው፡፡ዋናው ነገር ያለው ግን ከሱም ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብም አቅም በላይ በሆነው ህወሃት እጅ ነበርና የሆነው ሆነ፡፡በዚህ ላይ የራሳቸው ርካሽ አጀንዳ ያላቸው የሚዲያ ባለቤቶች አዛኝ መስለው ቀርበው በኤርሚያስ እና በደምበኞቹ መሃከል ያለውን ግንኙነት አበለሻሹት፡፡መደማመጥ ጠፋ!ፍረጃው በረከተ፡፡ ይሄኔ ድሮም ይፈልገው የነበረው ህወሃት ቢለዋዉን ስሎ መጣ፡፡

ህወሃቶች ኤርሚያስን የሚያሳድዱት የሚሰራው ነገር ሁሉ ከአቅማቸው እና ግንዛቤቸው በላይ ስለነበረ ነው፡፡በዚህ ላይ የጎጣቸው ሰው ስላልሆነ ይፈሩታል፡፡የሚሰራውን ነገር ሁሉ ከጭንቅላታቸው በላይ ስለሆነ በዚህ ላይ ብዙ አመት ከሃገር ውጭ ያውም በወልስትሪት ሲሰራ የኖረ ሰው በመሆኑ በሆነ እነሱ በማይደርሱበት መንገድ የተቃውሞውን ፖለቲካ የገንዘብ ዝውውር የሚረዳ መስሎ ሳይሰማቸው አይቀርም፡፡ስለዚህ እያንዳንዱን እንቅስቃሴውን በእውቀት አልቦ ፍርሃት ይከታተላሉ፡፡በተለይ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ እንዳይገባ የፈለጉት ለዚህ ነው፡፡ለዚህ ማመሳከሪያው አንድን የብሄራዊ ባንክ ሰው ለምን እንዲህ እንደሚያንገላቱት ሲጠይቅ በግልፅ “ኤርሚያስ እኛኮ አንተ የምትሰራውን ነገር በደምብ ስለማናውቀው በጣም እንፈራሃለን አሉኝ” ሲል ራሱ ኤርሚያስ አመልጋ ለJTV የተናገረው ነው፡፡ለሃገር የሚያስብ መንግስት ቢኖር ኖሮ ኤርሚያስ የሚያመጣቸውን ነገሮች ባለማወቁ የሰውየውን እግር አልነበረም የሚያስረው፡፡ይልቅስ ከኤርሚያስ ጋር በእውቀት የሚተካከሉ አዋቂዎችን አማካሪ አድርጎ ጉዳዩን መከታተል ይቻል ነበር፡፡

ግራም ነፈሰ ቀኝ የኤርሚያስ አመልጋ ጥፋት ኢትዮጵያን አለማወቁ ነው፡፡ኢትዮጵያ በድህነቷ ሃብታም መሆን የሚፈልጉ፣ከእውቀት የተጣሉ ሰዎችን በላይዋ ላይ ሾማ የምትንፏቀቅ ሃገር ነች፡፡እነዚህ ሰዎች እንደ ኤርሚያስ አይነት ስራ ፈጣሪዎችን የሚፈልጉት ሃሳባቸውን ዘርፎ እነሱን እስርቤት ለመወርወር እንጅ ህልማቸውን እንዲኖሩ አይደለም፡፡ለእነዚህ ሰዎች ህልም መሳካት የሚሰራው የገንዘባቸው እና የክላሻቸው ምርኮኛ ደግሞ ብዙ ነው፡፡ኤርሚያስ በበኩሉ እዚህ ሃገር በተለይ በአገልግሎቱ ዘርፍ ያለውን ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ ህልሙን ብቻ ተከትሎ የሚነጉድ ህልመኛ ሰው ነው፡፡ህልም ደግሞ ህልም ብቻ ነው-እውን የሚያደርገው ስርዓት ካልተዘረጋ በቀር፡፡

ኢትዮጵያን ሳያውቅ ህልሙን ብቻ ተከትሎ የተጓዘው ኤርሚያስ ጥፋት ካጠፋም የጥፋቱ ስር መሰረት መበለጥን የማይፈልገው የኢህአዴግ መንግስት አሰራር ነው፡፡ኢህዴግን አይነት እንቅፋት ባይገጥመው ኖሮ ኤርሚያስ ሊያጠፋ የሚችለው ማንኛውም የሚሰራ ሰው ሊሰራቸው የሚችሉ ውስን ጥፋቶችን ነበር፡፡በግሌ የሚገርመኝ ነገር ኤርሚያስ ኢህአዴግን የመሰለ እንቅፋት ተቋቁሞ ለመኖር እንጅ ተመልሶ ወደ መጣበት ለመሄድ አለማሰቡ ነው፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ ኤርሚያስ ከበደለው የተበደለው ይበልጣል፡፡አምጦ ከወለደው ዘመን ባንክ እንደዋዛ ተባሯል፣የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን አስቦ የሞከረው በጎ ምኞቱ ከዘራፊ አስቆጥሮታል፡፡የእርሱ እውነት ታፍኖ የአንድ ወገን የሸር ጩኽት ብቻ ሲሰማ በመኖሩ “በአጭበርባሪነቱ” ስምምነት ተደርጓል፡፡ይህ ትልቅ የሞራል ስብራት ያመጣል፡፡የኤርሚያስ ፈተና ህወሃት ከስልጣን ሲነሳም አለማብቃቱ በጣም አሳዛኝ ነገር ነው፡፡

የህወሃትን ከስልጣን መነሳት ተከትሎ የዶ/ር አብይ መንግስት መልካም ዘመን ለመምጣጡ ምልክት ይሆነን ዘንድ እስረኞችን ፈትቷል፣ከስራ ተባርረው የነበሩ ምሁራን ወደ ሥራቸው መልሷል፣ማዕረጋቸው የተወሰደባቸውን ውትድርና ባለሙያዎች ማዕረጋቸውን መልሷል፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ ምርኮው ያልተመለሰለት ኤርሚያስ አመልጋ ነው፡፡ከዘመን ባንክ ጀምሮ ቢወራ የማያልቅ ግፍ ተሰራበትን ሰው ጉዳዩን በአግባቡ መርምሮ የሚገባውን እንዲያገኝ እርሱም ያጠፋውን እንዲያስተካክል ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሲገባ ለሌላ ዙር እስር ተዳርጓል፡፡አሁን የታሰረው ደግሞ “ሆቴልህን ለምን በውድ ዋጋ ለሜቴክ ሸጥክ” በሚል የዶሮ ሻኛ አምጣ አይነት አስገራሚም፣አሳዛኝም ነገር ተከስሶ ነው፡፡

ለዚህ አቶ ኤርሚያስ ለፍርድቤት መልስ ሲሰጥ ኢምፔሪያል ሆቴልን የገዛው በ18 ወር ተከፍሎ በሚያልቅ 47 ሚልዮን ጥሬ ብር ሊከፍል እና ሆቴሉ ያለበትን 23 ሚሊዮን ባንክ እዳ ሊከፍል ተስማምቶ እንደነበር፡፡በመሃል ሜቴክ ሆቴሉን መግዛት ሲፈልግ ኤርሚያስ የተስማማበትን የሆቴሉን እዳም ሆነ ጥሬ ገንዘብ ከፍሎ ስላልጨረሰ የሆቴሉ ስመ-ሃብት በኤርሚያስ ስም አልዞረም ነበርና ግዥ እና ሽያጩ የተፈፀመው በመጀመሪያው የሆቴሉ ባለቤት እና በሜቴክ መሃከል ነበር፡፡አሁን አቶ ኤርሚያስ እስርቤት የተወረወረው በሌለበት ግዥ እና ሽያጭ ሁኔታ ነው፡፡በዚህ ላይ አስወድደህ ሸጠሃል የተባለው ሆቴሉ የነበረበት የባንክ እዳ ግንዛቤ ውስጥ ሳይገባ ነው፡፡ከዚህ የምንረዳው ህወሃት ከስልጣን ቢወርድም አዋቂን የማይወደው የፓርቲው ባህል አሁንም በተግባር ላይ እንዳለ ነው፡፡ሁለትም ኤርሚየስ የታሰረው የታሳሪ ሙሰኞችን የብሄር ተዋስኦ ለማብዛት እና ከወደ ትግራይ የሚመጣውን “የብቻችንን ታሰርን” ጩኽት ለማርገብ ነው እንጅ ኤርሚያስ ሰባ ሳባት ቢሊዮን ብር አመድ ካደረጉ ባለስልጣናት የበለጠ ጥፋት ስላጠፋ አይደለም፡፡በዚህ ላይ ኤርሚያስ በመታሰሩ ግር ብሎ ወጥቶ መንገድ የሚዘጋለት የዘሩን ጎረምሳ ቀድሞ ያላደራጀ የስራ ሰው ስለሆነ ነው እስሩ እምብዛም የማያስፈራው፡፡

እንደ ኤርሚያስ ያሉ ከጥፋታቸው ልማታቸው የሚበልጥ ስራ ፈጣሪዎችን እስርቤት እየዶለ ያለው መንግስት እድገት ማምጣትም የሚያምረው መሆኑ ነው አስቂኙ ነገር፡፡ብናውቅበት ኤርሚያስ ሃገሩ ብትመቼው ብዙ ደረጃ የሚደርስ አቅም እና እውቀት ያለው ሰው ነበር፡፡ኑልን እያልን የምንለምናቸው አፍሪካዊ ኢንቨስተሮችን እነ ዳንጎቴን እና ሞኢብራሂምን አይነት ባለሃብት ሊወጣው የሚችል ሰው ነበር ኤርሚያስ አመልጋ አያያዙን ብናውቅበት፡፡የሆነ ሆኖ ገና የምንመራበት ስርዓት ከዘር ቆጠራ የኋሊት ጉዞ ያልተፈወሰ ነውና ማር እንደማይጥማት እንስሳ ደህና ነገር አይወድለትም፡፡ሰው የደረሰበት መድረስ የሚፈልግ ዘመኑን የሚመጥን የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ዜጋ ሁሉ ግን ይህን የመንግስት አካሄድ ሃይ ማለት አለበት፡፡በውሃ ቀጠነ የሚታሰረው ኤርሚያስ አመልጋ ለሃገር የሚጠቅመው ከእስርቤት ውጭ ሆኖ በመሆኑ በአስቸኳይ መፈታት እንዳለበት አጥብቆ መጠየቅ መራመድ የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ የሞራልግዴታ ነው፡፡

__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ኢህአዴግ እና የሰብዓዊ መብት ነገር (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
የካቲት 6 2011 ዓ.ም.

አሮጌው ህወሃት መራሽ ኢህአዴግ ከአዕላፍ ነቀፌታዎቹ አንዱ በሰብዓዊ መብት ላይ ያለው እንደ ዱር አውሬ የሚቃጣው አቋሙ ነበር፡፡ኢህአዴግ በራሱ ህዝብ ላይ ያደረሰው አረመኔያዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓለም ላይ በእርኩስነታቸው ከሚታወቁ መንግስታት መደዳ ቀዳሚው ሳያደርገው አይቀርም፡፡ቀዳሚ የሚሆንበት አበይት ምክንያት በዓለም ታሪክ ብቅ ብለው የነበሩ እንደ ናዚ ያሉ ጨካኝ መንግስታት የጭካኔ በትራቸው ያረፈው በራሳቸው ህዝብ ላይ ሳይሆን “ሌላ” በሚሉት ህዝብ ላይ ስለነበረ ነው፡፡ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ግን ለመናገር እንኳን በሚያሳቅቅ የመከራ ድስት ውስጥ ከድኖ ሲቀቅል የኖረው የራሱን ህዝብ ነበር፡፡

“በአምባገነኑ ደርግ በመጨቆኑ አዝኜ ጫካ ገብቼ፣ተራራ ቧጥጨ ታገልኩለት” የሚለውን ህዝብ መፈጠርን በሚያስረግም ግርፋት፣ቁም-ስቅል፣እስራት፣ስደት እና መከራ ያሳለፈ ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ህወሃት/ኢህዴግ ብቻ ነው፡፡በኢህዴግ እስር ቤቶች የአጋንንት ሰራዊት እንኳን ተመካክረው ሊፈጥሩት የማይችሉት የጭካኔ ትዕይንት በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ ተፈፅሟል፡፡የሰው ልጅ ጀርባ በኤሌክትሪክ ገመድ ተተልትሏል፣ሰው ከነነፍሱ እባብ ባለበት በጉርጓድ ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጓል፣ሴት ወንዱ ተገዶ ተደፍሯል፡፡ ባጠቃላይ በነፃ አውጭ ነኝ ባዩ አሮጌው ኢህአዴግ ዘመን ስልጣን፣ድንቁርና እና ብልግና ሲቆራኙ የሚፈጠረው ጥፋት ሁሉ ደርሷል፡፡የሰው ልጅ ክቡርነት ተረስቶ፣ ሰው ምናምንቴ፣ ስልጣን ደግሞ ክቡር ሆኖ ኖሯል፡፡

ከእስር ቤት ውጭ ያለው ዜጋም ቢሆን በመፍራት በመንቀጥቀጥ የኖረ፣ካድሬ ደስ ባለው ቀን ያሰረበትን ዘመዱን መጠየቅ እንደ ሰማይ ርቆት፣ጭቆናው ገላጋይ የሌለው መርገም መስሎት፣እስር ቤት ባይገባም ቤቱን እስርቤት አድርጎ በስነልቦና መረበሽ የሚማቅቅ ነበር፡፡ኢህአዴግ ያሰረውን አስሮ ያላሰረውን የታሳሪ ቤተሰብ ስልጣኑ በፈቀደለት መጠን ሁሉ የሚያንገላታ፣መንግስትነትን የማይመጥን እኩይ ማንነት ባለቤት ነበር፡፡አረመኔው ኢህአዴግ በጭቃ ጅራፉ ገርፎ፣ስሙን አክፍቶ ላሰረው ዜጋ ስንቅ እንዲያቀብል የሚፈቅደው ከቤተሰቡ በእድሜው የገፋውን ሰው መርጦ ነበር፡፡

ይሄኔ በልጆቻቸው መጦር የሚገባቸው፣ለራሳቸው ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችሉ አቅመ ደካማ አዛውንት የታሳሪ ወላጆች ስንቅ ተሸክመው ከከተማ ዳር ባሉ እስርቤቶች ይንከራተታሉ፡፡እነዚህ አዛውንቶች በዚህ መንከራተታቸው ጊዜ ሁሉ ከእብሪተኞቹ ነገስታት አልፈው እነዚህን እርኩሶች በላይዋ ላይ የሾመችውን ሃገር ጭምር የሚረግሙ ይመስለኛል!በህይወቴ የኢህአዴግ እርኩሰት ጎልቶ እንዲታየኝ ካደረጉኝ ምክንያቶች አንዱ ይህ አዛውንቶችን በማንከራተቱ ራሱን ጎበዝ አድርጎ የማየቱ ነገር ነው፡፡በዚህ የተነሳ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ተስማምቶ አመታትን ያስቆጠረ ሰው ሁሉ እስከዛሬ ይቀፈኛል፡፡የኢህአዴግ ካድሬነት ከመሰረታዊ የሰውነት ባህሪ ጋር የሚጋጭ የሚመስለኝም ለዚህ ነው፡፡

መሰረታዊ የሰብዓዊነትን መርህን ችላ ብሎ ለስልጣን መደራደር ኢህአዴግን ኢህአዴግ ያደረግው ዋና ማንነቱ ነው፡፡ተለወጥኩም ተለነቀጥኩም ቢል ኢህአዴግ ከዚህ ማንነቱ ፈቅ ነቅነቅ አይልም፡፡ተለወጥኩ ያለው የዶ/ር አብይ ኢህአዴግ በሰብዓዊመብት ላይ አለቅጥ ሲያሾፍ የኖረውን ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄርን አምባሳደር አድርጎ ሾሞ ሸልሞ አሳይቷል፡፡አዲሱ ገ/እግዚብሄር ለሰብዓዊ መብት የቆመ ተቋምን እመራለሁ ብለው ወንበር ላይ ተቀምጠው በዛው መስሪያቤት ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ሽፋን ሲሰጡ የነበሩ ተራ ዋሾ ሰው ነበሩ፡፡ሰባ ሰባት ሽህ አማሮችን ስንት አመት ከኖሩበት ጉራፈርዳ ወረዳ በአንድ ሌሊት ነቅሎ ከህፃን እሰከ አዋቂ ዜጎችን ለመከራ የዳረገውን፣በዚሁ ዝናው ባዕዳን እንኳን አምባሳደርነቱን አንቀበልም ያሉትን ሽፈራው ሽጉጤን ሃገር እየቀያየረ የሚሾመው አወዳሹ የበዛው የዶ/ር አብይ መንግስት ስለ ሰብዓዊነት ግድ ይለዋል ብሎ ምክንያታዊ ሰሚን ሊያሳምን የሚችል ሰው የለም፡፡በሱማሌ ክልል ከአብዲ ኢሌ ጋር ያደረጉት እኩይ ስራ አልበቃ ብሏቸው አቶ ሙስጠፋን አላሰራ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ በተለይ በኋለኛው ሙከራቸው የተነሳ በፊት ላደረጉት በሱማሌ ክልል ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሁሉ ተጠየቂ ሊሆኑ ሲገባ አሁንም በንጉስ እልፍኝ ይሽሞነሞናሉ፡፡ወርቅነህ ገበየሁ የተባለውን የ1997 ባለዝና ገዳይ አስገዳይ እንደ ደህና ጌጥ በየምዕራቡ ሃገር ይዞ የሚዞሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓርላማ ተገኝተው “እኛ ጥፍር ነቃዮች ህገ-ወጦች ነን” ያሉት ከአንጀት ነው ካንገት አጠያያቂ ነው፡፡

መቼም ለዶ/ር አብይ መንግስት ጠበቃው ብዙ ነውና እነዚህን በሰብዓዊ መብት ላይ ጉልህ ወንጀል የሰሩ ሰዎች መሾሙ ሃገር ለማረጋጋት ብሎ ነው፣ሁሉም በአንዴ አይሆንም፣አንዳንዱን ጥፋት መተው ነው የሚል አይጠፋም፡፡ በበኩሌ በሰው ልጅ ክቡርነት አጥብቄ የማምን ነኝና ገንዘብ ከዘረፈው ይልቅ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት የረገጠው ሰው ይበልጥ ወንጀለኛ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ስለዚህ አንድ ቀን እንኳን ከተጠያቂነት ነፃ ሆኖ ሲንጎራደድ ማየት አልሻም፡፡ሲቀጥል በኢህአዴግ እልፍኝ የሰብዓዊ መብት ነገር እጣ ፋንታ የሌለው ጉዳይ ስለሆነ መጠየቁ ቀርቶባቸው እነዚህ ሰዎች ከነክፉ ወንጀላቸው እንደማንኛወም ሰው እየወጡ እየገቡ መኖሩ አንሷቸው ስለ መሾማቸው ሿሚው አብይ ራሳቸው ከተራ ካድሬያዊ ሽኩቻ ባለፈ ሰው ፊት የሚያቀርቡት ምክንያት ያላቸው አይመስለኝም፡፡

ምናልባት ሃገራችን ካለችበት ክፉ የዘረኝነት ፖለቲካዊ አየር የተነሳ እነዚህን ሰዎች ተጠያቂ ማድረጉ የመጡበትን ዘር የሚያስቆጣ ሆኖ የሚያመጣው ችግር እንዳይኖር ተፈርቶ ነው የተሾሙት የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ይህ በነዚህ ሰዎች ሁኔታ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ህወሃት ከሌላው ፓርቲ በተለየ ሁኔታ ወከልኩት በሚለው ህዝብ ዘንድ ጥብቅና የሚቆምለት ስለሆነ በአቶ አዲሱ ገ/እግዚአብሄር ተጠያቂነት ምክንያት የሚነሳ ዘረኝነት ወለድ ጉም ጉም ባይጠፋም ሌሎቹ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው ባደረጉበት ማስመረር ምክንያት የወጡበት ህዝብ ራሱ ለፍርድ የሚፈልጋቸው ናቸው፡፡የጄል ኡጋዴን መከራ ናፍቆት ለአህመድ ሽዴ ጥብቅና የሚቆም ሱማሌ አይገኝም፡፡ሽፈራው ሽጉጤም ቢሆን በወጣበት ህዝብ ዘንድ ወድቀህ ተነሳ ያማይባል ስመ-ክፉ ሰው ነው፡፡የመለስ ዜናዊ የግድያ አጋፋሪው ወርቅነህ ገበየሁም ቢሆን ወዳጅነቱ ለዶ/ር አብይ ይሆናል እንጅ ለማንም ጎጥ ሰው አይደለም!

የሰብዓዊ መብትን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር አብይም እንደማንኛውም ኢህአዴግ ቅም የማይላቸው ሰው እንደሆኑ ማሳያው ከላይ የተጠቀሰው ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ የ1997 ዓም ምርጫን ተከትሎ በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ በዳኛ ፍሬ ህይወት ሳሙኤል ሰብሳቢነት በተቋቋመ ገለልተኛ ኮሚሽን የተደረገውን ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ሪፖርት ተቀብለው በሃሰተኛው ቦታ እንዲተኩ በተደጋጋሚ ከኮሚሽኑ አባላት የሚቀርብላቸውን ጉትጎታ ችላ ማለታቸው ነው፡፡እነዚህ የኮሚሽኑ አባላት አሁን የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው የነዶ/ር አብይ ቡድን አንገቱን ደፍቶ፣ከግፈኛው መለስ ዜናዊ ጋር አብሮ፣ ግፍን ሁሉ አሜን አሜን በሚልበት በዛ አስፈሪ ዘመን አንገታቸው ላይ የተሳለ ቢለዋ ሊያርፍ እንደሚችል እያወቁ ከእውነት ጋር ብቻ ያበሩ፣በሞራል ልዕልና የለውጥ ሃይል የተባለውን ጭምር የሚያስከነዱ ሰዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ያለጊዜው ጭምር የፀኑ ሰዎች የኢህአዴግ ካድሬ ሁሉ ምስል ቀርፆ ሊያመልከው የደረሰው መለስ ዜናዊ በመንበሩ ቁጭ ብሎ እያለ ነው ነፍሳቸውን ሸጠው የህዝብን አደራ ብቻ አንግበው ከሞት ጋር የሚፋጠጡበትን አስፈሪ መንገድ የተጓዙት፡፡በዚህ ጉዟቸው ውስጥ የተረጋጋው ኑሯቸው ተናግቷል፣ለዱብዳ ስደት በመዳረጋቸው ቤተሰባቸው ተበትኗል፣ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡ለህዝብ ሲሉ ይህን ሁሉ ስላደረጉ ሊመሰገኑ ሲገባ ሊሞቱለት የቆረጡትን፣ብዙ የለፉበትን ነገር ተራ ጥቆማ አድርጎ ማቃለል ራስን ማስገመት ነው፡፡በርግጥ በሃሰት ፖለቲካ፣ በጌታ ፈቃድ እያደረ የኖረ የኢህአዴግ ባለስልጣን ለእውነት ሲባል የሚከፈልን መሰዕዋትነት ለመረዳት እና ተገቢውን ክብር ለመስጠት ሊቸግረው ይችላል፡፡ይህን መሰረታዊ ኢህአዴጋዊ ባህሪ እንደተሸከሙ የለውጥ መሪ ነኝ ማለቱ ግን የሚገጥም ነገር አይደለም፡፡

የኮሚሽኑ አባላት መለስ ዜናዊ ያቀረበላቸውን፣የኢህአዴግ ካድሬ የእለት ተዕለት ኑሮው አካል የሆነውን የሃሰት ግብዣ እምቢ ብለው ከሃገር የወጡበት መንገድ እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ነገሩ የሰዎቹን የእውነት ሰውነት የሚያሳይ፣ሌላ ሃገር ቢሆን ትልቅ ሽልማት የሚያሰጣቸ፣ለትውልድ ትምህርት የሚሆን ስራ ነው፡፡የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዳኛ ፍሬ ህይወት በተበደለው ህዝባቸው ላይ ሌላ ሃሰት ጨምሮ በህዝብ ቁስል እንጨት ላለመስደድ ሲሉ በቦሌ በኩል የወጡበትን መንገድ ለኢሳት ቀርበው ሲያስረዱ በበኩሌ ነገሩ ማለፉን ሁሉ ረስቼ በትልቅ ጭንቀት ተወጥሬ ነበር ያዳመጥኳቸው፡፡በዛች ቅፅበት ያቀዱት አንዱ ነገር ውልፊት ብሎ በመንግስት ውስጥ እጅ ቢወድቁ ሊደርስባቸው የሚችልውን ነገር ማሰቡ የሰውየውን የፍትህ ሰውነት ለመረዳት ያግዛል፡፡ምድረ ካድሬ እንደ አምላኩ የሚያረግድለትን፣ በቀለኛውን መለስ ዜናዊን እምቢ የማለታቸው ድፍረት ሳያንስ ኮሚሽኑ በማጣራቱ ወቅት በጥንቃቄ ያደራጃቸውን መረጃዎች ሁሉ ሰብስበው ይዘው ለመውጣት በሚገርም ድፍረት ማሰባቸው እና ማሳካታቸው ሁሌ የሚገርመኝ ነገር ነው፡፡ከዚህ የምንረዳው ለዳኛ ፍሬህይወት ፍትህ በደማቸው ውስጥ የሚዞር ነገር እንጅ ለእንጀራ ሲሉ ብቻ የያዙት ጉዳይ እንዳልሆነ ነው፡፡እስከ ዛሬ ለፍትህ የሚሞግቱት ሌሎቹ የኮሚሽኑ አባላት እነ አቶ ምትኩ ተሾመ፣ዳኛ ወ/ሚካኤል መሸሻ፣አባ ቲዎፍሊዎስ ሁሉ የህዝብን አደራ ከመብላት ራሳቸውን ለመስዕዋት ያቀረቡ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡

በጣም የሚያሳዝነው እና የሚገርመው ተለውጫለሁ የሚለው መንግስት እነዚህን ሰዎች በክብር ጠርቶ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ሲገባው በህይወታቸው የተደራደሩበትን ሪፖርት እያቃለለ መሆኑ ነው፡፡ይህ የሚያሳየው ለዶ/ር አብይ መንግስት ከየአቅጣጫው እየወረደ ያለው የበዛ የውዳሴው ድቤ አቅሉን እንዲስት እንዳደረገው ነው፡፡ይህ ደግሞ ለማም አይበጅም! ይብስ የሚገርመው ደግሞ ለወትሮው ለፍትህ እቆማለሁ የሚለው ተቃዋሚ ሃይልም ሆነ ህወሃትን ለማብጠልጠል ምክንያት የማይፈልገው ጋዜጠኛ ሁሉ ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ አለማለቱ ነው፡፡ጭራሽ ለፍትህ እሟገታለሁ ሲል የኖረው ጋዜጠኛ እና ፖለቲከኛ የዶ/ር አብይ መንግስት በስራው ሁሉ ትክክል ነው እንደ ማለት የሚሞክረው የፖለቲካ አዝማሪነት ውስጥ እየገባ ነው፡፡ይህ አካሄድ ስለማያዋጣ የአጣሪ ኮሚሽኑን ተገቢ ጥያቄ ዳር ለማድረስ ሰብዓዊነት ይሰማኛል ባይ ሁሉ በሃቅ ላይ ፊቱን ባዞሮው የዶ/ር አብይ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር አለበት፡፡ይህን ስለተባለ የአብይ መንግስት አይሟሟም!

አሁን የለውጥ ሃይል የሚባለው የኢህአዴግ ቡድን በ1997 ለደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢያንስ በዝምታ ድጋፍ የሰጠ ነው፡፡በአንፃሩ ዛሬ ስለ እውነት የሚማፀኑት የኮሚሽኑ አባላት በህዝብ ላይ የደረሰውን በደል ለማጋለጥ በነፍሳቸው የተደራደሩ ሰዎች መሆናቸው ሊሰመርበት ይገባል፡፡ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የህዝብን ትግል ተተግነው የለውጥ አራማጅ ነን ያሉትን የዛሬዎችን ገዥዎች ሳይቀር የሚልቅ የሞራል ልዕልና ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡በመሆኑም ዛሬ ስልጣን ላይ የወጣው ቡድን የኮሚሽኑን ሪፖርት በመቀበል የትናንት ጥፋቱን የማረም ግዴታ አለበት፡፡ካልሆነ ስለትናንቱ መጠየቅም እንደሚኖር ማሰብ ደግ ነው፡፡የኮሚሽኑ አባላት የተመሰከረለት ለእውነት የመቆም ፅናት ደግሞ ጉዳዩን የትም ድረስ የመውሰድ ብርታት እንዳለው ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ነገሩ ተጓትቶ ባዕዳን ደጃፍ ከመድረሱ በፊት የለውጥ አመራር ነኝ ባዩ የሃገራችን መንግስት ህይወት የተገበረበትን፣ቤተሰብ የተበተነበተን ትልቅ ጉዳይ ማቃለሉን ትቶ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ባይወድም ግዴታው እንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡

የምንግዴው ኢህአዴግ ስንጣቂ መሆኑ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ብልጭ የሚለው የለውጥ አመራር የኮሚሽኑን ሪፖርት ተቀብሎ በሃሰተኛው ቦታ ለመተካት የተቸገረው ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡የዚህ ዋነኛው ምክንያት ሃሰት ላይ ተመቻችቶ ተኝቶ ለእንቅልፍ ያለመቸገር ለቆ የማይለቅ ኢህአዴጋዊ የክህደት ተፈጥሮው ነው፡፡በመቀጠል የዶ/ር አብይ መንግስት በአደባባይ ከሚያወራው የለውጥ ማንነት ጋር ልዩነት ያለው ውስጣዊ ማንነት ስላለው ሳይሆን አይቀርም፡፡ይህ ደግሞ ትርጉሙ አስመሳይነት ነው፡፡በሰው ደም ላይ ተመቻችቶ ተቀምጦ የስልጣንን ማረፊያ ማመቻቸት ተቀየርን ብለውም እንኳን የኢህአዴ ካድሬዎችን የማይለቃቸው ልዩ ተፈጥሮ ነው፡፡ይህ ክፉ አመል ነው የሰብዓዊነትን ጉዳይ ችላ የሚያስብላቸው፡፡በተቀረ ሰዎች ለፍተው ደክመው፣መለስ ዜናዊ ከሚባል ጨካኝ አምባገነን ጋር አባሮሽ እየተጫወቱ ያጣሩትን የህዝብ እውነት ማድበስበስ ያከስር ይሆናል እንጅ የፖለቲካ ትርፍ አያመጣም፡፡አሁን በዶ/ር አብይ አመራር የተያዘው እውነትን ማድበስ ሁነኛ ምክንያቱ እንደ ወርቅነህ ገበየሁ ያሉ የ1997ቱ ግድያ መሪ ተዋናዮችን (የአሁን ዘመን ደግሞ የለውጥ አመራር አጋፋሪዎች) ተጠያቂ ላለማድረግ ነው፡፡በደሉን ረስቶ፣ጥፋትን ሁሉ ይቅር ብሎ ወንበር ላይ ላስቀመጠ ህዝብ ከመቆም እና ለወንጀለኛ ባለስልጣናት ሽፋን ከመስጠት የሚያዋጣው የቱ እንደሆነ ውሎ አድሮ ይለያል!
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ኦነግ ሼኔ- “የንጉስ ልጅ” (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ጥር 27 2011 ዓ.ም.

የተቀየረውን ኢህአዴግ ከከራሚው ኢህአዴግ የሚለየው አንድ ቁም-ነገር ለተቀናቃኞቹ የሚያሳየው ሆደ-ሰፊነቱ ነው፡፡ይህ አካሄዱ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የሚሰበስብበት አዋጭ መንገድ ነው፡፡ አዲሱ ኢህአዴግ ሊመሰርተው የሚሞክረው አካታች ፖለቲካዊ ንፍቀ-ክበብ አማራጭ ፖሊሲ ይዞ መጥቶ፣ ሰርቶ ለማሸነፍ ለተፈጠረ የፖለቲካ ሃይል ብቻ የሚመች ነው፡፡የወትሮው ኢህአዴግ ችኩል እና ጠላት ያለመናቅ አባዜ ትንሽንም ትልቁንም ጠላቱን ሲያስር ሲፈታ ሳያውቀው ለትንንሽ ጠላቶቹ የፖለቲካ ኪሎ ሲጨምር፣ የራሱን ኪሎ ደግሞ ሲያመናምን ኖሯል፡፡ራቅ አድርጎ የማያየው የአቶ መለስ ኢህአዴግ ዶሮም ነብርም የሚያክለውን ጠላቱን እኩል ሲያሳድድ እራሱን ግምት ውስጥ ከማስገባት አልፎ አይንህ ላፈር የሚያስብል ጥላቻን አትርፏል፡፡

ይህን ብልሃት እና ብስለት አልቦ፣በአመዛኙ ጫካ ቀመስ የአቶ መለስን ኢህአዴግ አጓጉል የፖለቲካ ጉዞ ሲያጤን የኖረው በለማ/ገዱ/ደመቀ/አብይ የሚመራው አዲሱ የለውጥ ሃይል የጠላትን ስም በመቀየር አዋጭ ጉዞውን ጀምሯል፡፡የአቶ መለስ/በረከት ኢህአዴግ ጠላት የሚላቸውን አካላት አዲሱ የለውጥ ሃይል ግን “ተፎካካሪ” በማለት በመሃከላቸው የነበረውን ውጥረት ስም በመቀየር ብቻ ማለዘብ ችለዋል፡፡የስም ለውጡን በተግባር ለማስመስከር የፖለቲካ ምህዳሩን በመክፈት፣ሚዲያዎችን ነፃ እንዲንቀሳቀሱ ትቷል፡፡ይህ ሁኔታ ለኢህአዴግ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡አንደኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስለድክመታቸው ኢህአዴግን ተወቃሽ የማድረግ አካሄዳቸውን ያስቀርና ለድክመታቸው ተጠያቂነቱ/ሃላፊነቱ የራሳቸው እንዲሆን ያደርጋል፡፡ይህ የተቃውሞ ፖለቲካውን መንደር ለስራ እንዲነሳ ያስገድደዋል፤የእውነት ለሃገር የሚያስበው እና ለስልጣን ብቻ የሚቋምጠው፣በብቃት/በእውቀት የሚታገለው እና ተቃራኒው፣ምርት እና ግሩዱ ይለያል፡፡

እባብ ያየው ኦነግ ሼኔ

በዶ/ር አብይ የሚመራው የኢህአዴግ የለውጥ ቡድን ሆደ-ሰፊነት መጋረጃቸውን ቀዶ ገበናቸውን አደባባይ ካወጣባቸው ፓርቲዎች አንዱ በምዕራብ ወለጋ እንቀሳቀሳለሁ የሚለው የኦነግ ሼኔ ቡድን ነው፡፡በለውጡ ሃይል የበዛ ትዕግስት የተገለጠው የኦነግ ሼኔ አንዱ ገበና እድሜውን በሚመጥን መንገድ በሃገሪቱ እያታዩ ያሉ ፖለቲካዊ ለውጦችን ተረድቶ በዛው መንገድ ለመሄድ ያለመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡እንደሚታወቀው ኦነግ በሽግግሩ ወቅት በተራ ፖለቲካ ሻምፒወኑ መለስ ዜናዊ መጥፎ በሆነ ሁኔታ የፖለቲካ ቁማር የተበላ ፓርቲ ነው፡፡

ይህ የፖለቲካ ቁማር ሽንፈት ምሬት ለዳኦድ ኢብሳ ትናንት የተደረገ ያህል የሚያንገበግብ ቁጭት ውስጥ የከተታቸው ይመስላል፡፡ ዳኦድ ኢብሳ መለስ ብለው ሲያስቡት የፖለቲካ ቁማሩ ሽንፈት የተጀመረውም የተጨረሰውም ኦነግ ወታደሮቹን ካምፕ እንዲያስገባ የተስማማ ቀን እንደሆነ ገብቷቸዋል፡፡ሊረዱ ያቻሉት ትናንት ዛሬ አለመሆኑን፣መለስ ዜናዊ የሚባል የተራ ፖለቲካ ቁማርተኛም ከአፈር በታች እንደሆነ ነው፡፡ዳኦድ የሽግግር ዘመኑ ላይ ቆመው ከመቅረታቸው የተነሳ ሌላው ቀርቶ አሁን በኢትዮጵያ መንበረ ስልጣን ላይ ያለው ኦሮሞ መራሹ ኦዴፓ መሆኑን እንኳን ያሰላሰሉት አይመስልም፡፡ሌላው የዘነጉት ትልቅ ጉዳይ የአቶ መለስ ቁማር አሳዛኝ ተሸናፊ ያደረጋቸው ወታደሮቻውን ካምፕ የማስገባት ያለማስገበት ጉዳይ በወቅቱ የሃገሪቱን ብሄራዊ ጦር ከማደራጀት ጋር የተያያዘ ግጥምጥሞሽ ዛሬ እንደሌለ ነው፡፡

እንደሚታወቀው ህወሃት/ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ለዘመናት የተገነባውን፣በስብጥርነቱ ሃገራዊ መልክ የነበረውን የሃገር ብሄራዊ ጦር ሰራዊት “የደርግ ወታደር ነው” በሚል ምክንያት በትኗል፡፡በተበተነው ጦር ምትክ ሃገራዊ ጦር ሰራዊት መገንባት የሃገሪቱን የሽግግር መንግስት የሚመሩ ዋነኛ የፖለቲካ ሃይሎች ፋንታ ሆኖ ነበር፡፡በሽግግር መንግስቱ አባልነት የተሰየሙ ቡድኖች ብዙ ቢሆኑም በጦር ታጅበው የመጡቱ ህወሃት/ኢህአዴግ እና ኦነግ ነበሩ፡፡ከድሮ እስከ ዘንድሮ ጦር ያነገበ በሚፈታት ሃገራችን ህወሃት እና ኦነግ ባለ ጦር በመሆናቸው ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በእጃቸው ሆኖ ነበር፡፡እነዚህ ሁለት ሃይሎች የሃገሪቱን ብሄራዊ ጦር በማደራጀቱ ስራ ላይ ያላቸው ሚና የሃገሪቱ መፃኢ ፖለቲካ ለመዘወር ላለመዘወር ዋናው የይለፍ ነበር፡፡ብልጣብልጡ አቶ መለስ ኦነግን ያሸነፉት እና ለቀጣዮቹ ረዥም ዘመናት የፖለቲካ ሜዳውን ብቻቸውን ሊፈነጩበት የሚችሉበትን መላ የመቱት የህወሃት/ኢህአዴግ ጦር ላቅ ያለ ልምድ እና ብቃት ያለው በመሆኑ የሃገሪቱ ብሄራዊ መከላከያ ሰራዊት እንዲሆን፣በአንፃሩ የኦነግ ወታደር ትጥቁን ፈቶ ወደ ትንንሽ ወታደራዊ ካምፕ እንዲገባ ሲያደርጉ፣ኦነግም በዚህ ሲስማማ ነው፡፡

አቶ መለስ ይህን ያደረጉት በቀጣዮቹ አመታት ሃገሪቱን በሚያወሩለት ዲሞክራሲ ሳይሆን በጠመንጃ ጉልበት እንደሚመሯት አሳምረው ስለሚያውቁ ነው፡፡ለዚሁ እንዲመች ወታደራዊ አመራሩን ከላይ ታች በወንዛቸው ልጆች ሞሉት፡፡ወታደሩ “በለው!” ሲባል ያገኘውን በጥይት የሚደፋው ከደደቢት ጀምሮ በተፈተለ ጥብቅ ገመድ ከመለስ መንግስት ጋር ስለታሰረ ነው፡፡ከዚህ በኋላ አስቀድሞ በአቶ መለስ አእምሮ የተፃፈው የኦነግ አገልግሎት ስላበቃ የኦነግ አመራሮች በቦሌ እንዲሸኙ ተደረገ፡፡ይህን አቶ መለስን ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰገነት ከፍታ ኦነግን ወደ ስደት የዳረገ መበለጥ የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ በተለይ ሊረሳው አልቻለም፡፡ሽግግር፣ድርድር፣ትጥቅ መፍታት የተባሉ ነገሮች በተከሰቱ ጊዜ ሁሉ ይሄው ሽንፈቱ ውል እያለበት ሳይቸገር አልቀረም፡፡ቁስሉ ያልዳነለት ሰው ያየው ሰው ሁሉ አቁሳዩ ይመስለዋል፣ማንም በተጠጋው ቁጥር ቁስሉ ይመረቅዛል፡፡ኦነግ እየሆነ ያለው እንዲያ ነው፡፡ስህተት ላለመድገም መጠንቀቄ ብሎት ሞቱን የሚያፋጥን ትልቅ ስህተት ውስጥ እየወደቀ ያለው ለዚህ ነው፡፡

ያ ሌላ ይሄ ሌላ

ከሃያ ሰባት አመት በፊት መለስ ዜናዊን ለመሰለ ሰው ያሳየው ፖለቲካዊ ገራምነቱ ያስበላው ኦነግ(ሼኔ) ዛሬ በገራሙ ዶ/ር አብይ/ አቶ ለማ መገርሳ ፊት ያለ ወቅቱ የአቶ መለስን መሰሪነት ወርሶ አጓጉል ብልጥ ለመሆን እየሞከረ ይገኛል፡፡ብልጥነቴ ብሎ የተያያዘውን ጉዞ አንድ ያለው ኤርትራ ድረስ ሄደው ለተደራደራቸው የአቶ ለማ መገርሳ ቡድን ህወሃትን ለመውጋት በምዕራብ ወለጋ የሰማራውን ሸማቂ ቡድን ደብቆ ኤርትራ ባለው ጦሩ ብቻ ለመደራደር ሲሞክር ነው፡፡ብረት አስቀምጨ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ብሎ ሲደራደር ኤርትራ ያለውን ጦሩን ትጥቅ ለማስፈታት ተስማምቶ ነው፡፡

ሆኖም ኦነግ ከድሮም በወለጋ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ኖሯል፡፡ይህ ሃይል ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ ለመጣል በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ራሱን በወታራዊ ሃይልም ሆነ በፋይናንስ ለማሳደግ ችሏል፡፡በአሁኑ ሰዓት በኦሮሚያ፣በቤኒሻንጉል፣በደቡብ ክልል የተለያዩ ቦታዎች(አማሮ፣ቡርጅ፣ጌዲኦ፣ሰገን ዞኖች) አካባቢዎች እየተዘዋወረ ሰላም የሚነሳው፣በኦሮሚያ ባንክ የሚዘርፈው የኦነግ ሼኔ ቡድን ይሄው በሃገር ቤት በተለይ ደግሞ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ሲንቀሳቀስ የነበረው የኦነግ ሼኔ ቡድን አካል ነው፡፡ኦነግ ሼኔ ከነ አቶ ለማ ጋር በኤርትራ ባደረገው የሰላም ስምምነት በወለጋ ስለሚያንቀሳቅሰው ታጣቂ ቡድን ምንም እንዳላነሳ ነው የሚነገረው፡፡

ስለዚህ ድርድር ከአቶ ለማ መንግስት በኩል ግልፅ ነገር ያልተነገረ መሆኑ ነገሩን ይበልጥ እንቆቅልሽ ከማድረጉም በላይ ኦነግን ለብጥበጣ ሳይረዳው አልቀረም፡፡የድርድሩ ሁኔታዎች ለህዝብ ግልፅ አለመደረጉ አቶ ለማን (በግሌ ለመጠርጠር በሚቸግረኝ) የኦነግ ወገንተኝነት ጭምር ያስጠረጠራቸው ነገር ነው፡፡በርግጥ ኦነግ(ሼኔ) ከመስመር ወጥቶ ሰው መግደል፣ባንክ መዝረፍ የመሰሉ ተራ የውንብድና ተግባራት ላይ ጥልቅ ብሎ ከገባ በኋላ የአቶ ለማ ኦዴፓ ከኦነግ ሼኔ ጋር ያደረገው ድርድር ከሌሎች ብረት አንጋች ተቃዋሚወች ጋር ከተደረገው የተለየ እንዳልሆነ ደጋግሞ እየተናገረ ነው፡፡ሆኖም ይህ ነገር የአቶ ለማ ኦዴፓ ከኦነግ ጋር ሲደራደር ያደረገውንም ሆነ የፌደራል መንግስቱ ከታጠቁ ሃይሎች ሁሉ ጋር ሲደራደር ያደረገውን ግልፅነት የጎደለው አካሄድ ስህተትነት አይሸፍነውም፡፡

የታጠቁ ተቃዋሚ ሃይሎች ወደ ሃገር ቤት ሲጋበዙ የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩን ለፓርላማ ውይይት አቅርቦ የድርድር ሁኔታዎችን ማስወሰን፣እግረ-መንገዱንም ሁኔታዎቹን ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ነበረበት፡፡ይህ ባለመሆኑ ሳቢያ ነው በኦነግ ሼኔ በኩል ብዙ ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት፡፡የድርድሩ ሁኔታ ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ ኦብነግ እና አርበኞች ግንቦት ሰባት ወደ ትክክለኛው መስመር ገብተው የሃገር ማረጋጋቱን ስራ በማገዝ ላይ ባሉበት ሁኔታ ኦነግ ሼኔ ለማረጋጋት መስራቱ ቀርቶ መበጥበጡን በመተው ሊተባበር አልቻለም፡፡ይህን የኦነግ ሁኔታ ዝም ብሎ በማየት ላይ ያለው የዶ/ር አብይ መንግስት አዝማሚያ ለሌላው ሰው ግራ አጋቢ ሲሆን ለኦነግ ሼኔ ደግሞ የሰፈሩ ሰዎች የሃገሪቱን ስልጣን በመቆጣጠራቸው የፈለገውን ለመሆን የተፈቀደለት የንጉስ ልጅ አድርጎ ራሱን እንዲቆጥር ሳያደርገው አልቀረም፡፡

ኦነግ ሼኔ አሁን እያደረገ ያለውን ብጥበጣ የሚያደርገው የሃገሪቱ መንግስት በትግራይ መኳንንት በሚዘወርበት ዘመን እንደ ቂል ተሸናፊ ተቆጥሮ መናቁ ልክ እንዳልሆነ፣ ይልቅስ አስፈሪ፣ጉልበታም፣ጦረኛ መሆኑን ለማሳየትና ስም ለመቀየር ነው፡፡ ኦነግ ሼኔ የረሳው ነገር የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ዘመን ከተኳሽነት ይልቅ ታጋሽነት ጀግና የሚያስብልበት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እንደ ኦነግ ሼኔ ከዘመን ጋር የሚተላለፍ አሳዛኝ ፓርቲ ያለ አይመስለኝም፡፡ ጦር ዋና በሆነበት ዘመን ጦሩን ለመለስ ዜናዊ አስረክቦ፤ዛሬ የሰላም ያለህ በሚባልበት ጊዜ “ተኳሽ ነኝ!” ማለት ከዘመን ጋር ክፉኛ መተላለፍ ነው፡፡

ማለባበስ ይቅር

የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ (ሼኔ) በሰላም ለመታገልተስማምቼ መጣሁ ብሎ አዲስ አበባን ከረገጠበት ሰሞን ጀምሮ በችግር ፈጣሪነት ስሙ እየተነሳ ነው፡፡ከቡራዩው አሰቃቂ፣አስከፊ እና አሳዛኝ ግድያ እስከ ዛሬው የሰገን ግድያ ድረስ የኦነግ ስም ይነሳል፡፡የኦነግ “መሳሪያየን እንዳዘልኩ ለሰላማዊ ምርጫ ልወዳደር” እንደ ማለት የሚቃጣው ክርክር ሰሚን ሁሉ ሲያስቅ የሰነበተ ነገር ነው፡፡ዋል አደር ብሎ በባንክ ዘረፋ ላይ እንደተሰማራም እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ኢሳት እና ዋዜማ እንደዘገቡት ኦነግ አስር ቀን ባልሞላ ጊዜ አስራ ሰባት ባንኮችን ዘርፈፏል፡፡

ሌላው የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ አስቂኝ ነገር “ከዛሬ ሃያ ምናምን አመት በፊት በሃገሪቱ ምርጫ ቦርድ ባህር መዝገብ ውስጥ የታወቅኩ ፓርቲ ስለሆንኩ ድጋሜ በምርጫ ቦርድ መመዝገብ አያስፈልገኝም” ያለው ነገር ነው፡፡አንድ ፓርቲ በሃገሪቱ ምርጫዎች በተከታታይነት ካልተሳተፈ እንደሌለ የሚቆጠር ሆኖ እንደገና መመዝገብ እንዳለበት ማወቁ የአንድ አዛውንት አመት በትግል ላይ ለኖረው ኦነግ ቀርቶ ለሌላውም ቀላል ነገር ነው፡፡በተጨማሪ የዛሬ ሃያ ምናምን አመት የነበረው ኦነግ በትንሹ ወደ አምስት ክልፋዮች ተቀይሯል፡፡እንዲህ ግዙፍ ለውጥ በላዩ ላይ የተካሄደበት ኦነግ አንዱ ስንጣሪ ታዲያ በድሮው ኦነግ ስም መመዝገቤ ከእሩብ ምዕተ አመት በኋላ ለብዙ ተሰነጣጥቄ ስመለስም የሚሰራ ነገር ነው ብሎ ማሰቡ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡

የኦነግ መቅበጥበጥ እና የመንግስት የበዛ ትዕግስት በተለይ ኦሮሞ ባልሆነው ሰው ዘንድ ጥርጣሬ እየፈጠረ ይገኛል፡፡በሃገሪቱ ዳርቻ ታጥቆ እየተንጎማለለ ልቡ በል ባለው ሰዓት የሚተኩሰውን ኦነግ ሼኔን እመራለሁ የሚሉትን አቶ ዳኦድ ኢብሳን አዲስ አበባ ላይ ቁጭ አድርጎ ማኖሩ በተለይ ኦዴፓ መራሹን መንግስት ለትዝብትም ለጥርጣሬም ዳርጎታል፡፡የሚብሰው ደግሞ ከሰሞኑ ፍሪዳ ተጥሎ ከኦነግ ሼኔ ጋር ኦዴፓ አደረገው የተባለው እርቅ ነገር ነው፡፡አስታራቂዎቹ ኦነግ ባንክ ሲዘርፍ፣እየተዟዟረ ሰው ሲገድል አንዳች ማለት ያልቻሉት አባገዳዎች እና የኦሮሞ ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ሽማግሌዎቹ ኦነግ በብዙ ሲያጠፋ ዝም ብለው ከኦዴፓ ጋር እናስታርቅ ባሉበት መድረክ ኦሮሞ ለኦሮሞ መጣላት እንደሌለበት ሲማፀኑ ተደምጠዋል፡፡ኦነግ ሼኔ ከኦሮሚያ ክልል ወጥቶ ኦሮሞ ያልሆኑ ዜጎችን በጥይት መቁላቱ ለሸምጋዮቹ የሚሰጠውን ትርጉም ያወቀ የለም!ከሁሉም በላይ አሁን ኦነግ ሼኔ እያጠፋ ያለውን ጥፋት አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ኦብነግ ቢያደርጉት ኖሮ ከመንግስት ተመሳሳዩ ትዕግስት ይኖር ነበር የሚለውን መጠየቅ እሻለሁ፡፡የአዲስ አበባ ወጣቶችን ያለ ጥፋታቸው እያፈሰ ያሰረው የዶ/ር አብይ መንግስት በባለ ብዙ ጥፋቱ በኦነግ ላይ ተመሳሳዩን ለማድረግ ለምን እንደተቸገረ ግልፅ አይደለም፡፡

አጥፊውን ኦነግ ሼኔን አርዶ ጋርዶ የታረቀው የአቶ ለማ ኦዴፓም ቢሆን ከዚህ ቀደም ሲሸማገል የቆየ እና “አሁን ትዕግስቴ ስላለቀ የሃይል እርምጃ ወስጄ የኦነግ ሼኔን የወለጋ አምባ እያፈራረስኩ ነው” ሲል የሰነበተ ነበር፡፡”ትግስቴ ስላለቀ ወታደራዊ እርምጃ ጀምሬያለሁ” ያለው ኦዴፓ በመሃል ደግሞ “ልታረቅ” ማለቱ ክፉ ነገር ባይሆንም ለእርቅ ሲቀመጥ እርቁ የሚፈታው ነገር ምንድን ነው የሚለውን ትልቅ ጥያቄ አለመመለሱ አጠያያቂ መሆኑ አይቀርም፡፡እርቅ የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ሆኖም ከኦነግ ጋር የሚደረግ እርቅ መልክ ሊያስይዛቸው የሚገባ ጉዳዮች አሉ፡፡

አንደኛው በምዕራብ ወለጋ ያሰማራቸው ታጣቂዎች በአነግ ሼኔ ሰላማዊ ትግል ላይ ያላቸው ሚና ምን እንደሆነ ቁርጥ አድርጎ ማሳወቅ አለበት፡፡ከቁጥራቸው ጀምሮ፣ትጥቅ አውርደው ካምፕ የሚገቡበትንም ሆነ ሌላ ሁኔታ ካለ የዚህን የጊዜ ገደብ በውል ማሳወቅ አለበት፡፡በተጨማሪም ከባንክ ዘረፈ የተባለውን ገንዘብ መጠን ተገልፆ፣ በአስቸኳይ ይቅርታ ጠይቆ እንዲመልስ መደረግ አለበት፡፡ካልሆነ ነገ ኦነግ ሼኔም እንደ ህወሃት “ስታገል የቋጠርኩት የግል ጥሪቴ ነው” ብሎ ከሃገሪቱ ባንኮች በዘረፈው ገንዘብ ኦሮሟዊ ኢፈርት ልመስርት ሊል ይችላል፡፡ከሁሉም በላይ መንግስት ሆኖ ሃገር የሚመራ አካል ባንክ ከዘረፈ ብድን ጋር በድፍኑ ታርቄያለሁ ማለቱ የሚያስተላልፈው መልዕክት ሌብነትን ማውገዝ ሊሆን አይችልም፡፡ይህ ነገር ተጨማሪ የባንክ ዘራፊወችን ሊፈጥር እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡የድሃን ሃገር ገንዘብ የወንበዴ ሲሳይ እያደረጉ በየምዕራብ ሃገሩ ምፅዋት መለመኑ ምን ትርጉም አለው?
ሁለተኛው ነገር ከኦነግ ጋር የተደረገው እርቅ ፓርቲው ነውጠኝነቱን በሰላማዊነት ተክቶ፣ከሃያ ሰባት አመት በኋላ በላዩ ላይ የተከሰተውን ለውጥ አጢኖ በአዲስ መልክ በምርጫ ቦርድ ለመመዝገብ ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ወይ የሚለው ነው፡፡”ማን ትጥቅ ፈቺ ማን አስፈቺ ሊሆን ነው” ያለው ኦነግ ሼኔ “እኔን ልመዝግብህ የሚል ደፋር ምርጫ ቦርድ ማን ነው” እንደማይል እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

ሌላው እና ዋነኛው ነገር የኦነግ ነገር የኦሮሚያ ጉዳይ ብቻ ባለመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከተው ተደራዳሪ ኦዴፓ ብቻ መሆን የለበትም የሚለው ነው፡፡ኦሮሞን ነፃ ለማውጣት እታገላለሁ የሚው ኦነግ ሼኔ ውጅግራውን አንግቦ የሚንቀሳቀሰው በኦሮሚያ ምድር ብቻ አይደለም፡፡ይልቅስ ኦሮሚያን በሚያጎራብቱ ክልሎች እየዘለቀ የንፁሃንን ሰዎች ህይወት እያጠፋ ይገኛል፡፡በዚህ ምክንያት የአጎራባች ክልሎች መንግስታትም በኦነግ አደብ መግዛት ዙሪያ ሊነጋገሩ እርቅ ካስፈለገም ሊታረቁ ያስፈልጋል፡፡ኦነግ ከኦሮሚያ በተጨማሪ የደቡብ ክልልን እና ቤኒሻንጉል ክልሎችን እያመሰ ይገኛል፡፡ይህ ማለት ደግሞ የፌደራል መንግስቱም በእርቅ ድርድሩ ውስጥ ሊወከል ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ለእርቅ ሲቀመጡ እንዲህ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ሳይነካኩ በየወሩ ፍሪዳ እያረዱ መታረቅ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ለዚህ ምስክሩ ኦነግ እና ኦዴፓ ታረቁ በተባለ ማግስት ኦነግ ሼኔ በደቡብ ክልል ሰገን ዞን ዘልቆ ሃገር ሰላም ብለው የሚጓዙ አራት የኮሬ እና አማሮ ወጣቶችን ከመኪና ላይ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን መቅጠፉ ነው፡፡

____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የጅጅጋ ፖለቲካ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ
ጥር 20 2011 ዓ.ም.

ለሃያ ሰባት አመት የኖረው ኋላቀር ፖለቲካችን የሃገራችንን ክልሎች ሁሉ ሲያንገላታ የኖረ ቢሆንም የሱማሌ ክልል ደግሞ ከሚብሱት በባሰ ችግር ውስጥ የቆየ፣በሁለት ሶስት ለበቅ ሲገረፍ የኖረ ክልል ነው፡፡የዚህ ክልል ህዝብ ከሌላው ህዝብ በተለየ መከራው እንዲብስ ያደረገው በሁለት በኩል እሳት የሚነድበት መሆኑ ነው፡፡በአንድ በኩል የመለስ ዜናዊ ምልምል የሆነው አብዲ ኢሌ “ኦብነግን ትደግፋላችሁ” እያለ ህዝቡን ወደ እስር ቤት አጉሮ ሊያልፉበት ቀርቶ ሊያደምጡት በሚያስቸግር መከራ ውስጥ ይዶላል፡፡በስሙ ጦስ ህዝብ በአብዲ ኢሌ ለበቅ የሚገረፍለት ኦብነግ በበኩሉ አብዲ ኢሌን ፈርተው ይሁን አላማውን ተቃውመው ያልተባበሩትን የክልሉ ነዋሪዎች “አብዲ/የመለስ መንግስት ደጋፊዎች ናችሁ” እያለ ያንገላታል፡፡በዚህ ላይ ክልሉ እምብዛም ያልለማ ከመሆኑ በላይ ያለው የፀጥታ ችግር ተደምሮ ህዝቡ በሶስተኛው ለበቅ(በኢኮኖሚ ችግር) እንዲገረፍ አድርጓል፡፡

የአብዲ ኢሌ አረመኔነት በህዝቡ ላይ ያደረስ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እኛን የሃገራቸውን ሰዎች ቀርቶ ምዕራባዊንን ያሳሰበ ነበር፡፡በስተመጨረሻው እንደውም አሜሪካ አብዲ ኢሌን ከተፈላጊ ወንጀለኞች አንዱ አድርጋ ታድነው ሁሉ ነበር፡፡የህወሃት/ኢህአዴግን ገመና ለመክተት ተብሎ የተቋቋው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዓለምን ጉድ ያስባለ እርኩሰት ወደሚሰራበት ወደ ሶማሌ ክልል ትውር ብሎ አያውቅም፡፡ቱሪስትም መናኝም መስለው ገብተው በክቡሩ የሰው ልጅ ላይ አብዲ ኢሌ እና መለስ ዜናዊ ይሰሩት የነበረውን ግፍ የሚያጋልጡት ባዕዳኑ ምዕራባዊን ነበሩ፡፡የመልቲው አዲሱ ገብረእግዚአብሄር መስሪያቤት በፈረንጆቹ ስለ ጉዳዩ ሲጠየቅ “ወደዛ ክልል ሄጄ አላውቅም” ሲል በምቾት ነበር፡፡

ታዛቢ በሌለበት ተከድኖበት ሲንተከተክ የኖረው የሶማሌ ህዝብ አምላክ በቃህ ብሎት አብዲ ኢሌ የተባለው ሰውየ ከትከሻው ተነስቷል፡፡አብዲ ሲነሳ የተተኩት አቶ ሙስጠፋ ኡመር ደግሞ ለበደሉ በካሳነት የተቀመጡ የሚመስሉ ሰው ናቸው፡፡ አቶ ሙስጠፋ ጥሩ በሚከፍሉ ዓለም ዓቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ተቀጥረው ባህርማዶ የሚኖሩ ሰው ነበሩ፡፡የተመቼ ኑሯቸውን ጥለው በአመፅ ስትታመስ የኖረችውን የሱማሌን ክልል ለማቅናት በጄ ማለታቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡የተረከቡትን ሃላፊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገርም ቅንጅት አመርቂ በሆነ ሁኔታ ለመወጣት እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ ያስመሰግናቸዋል፤በብዙዎች ዘንድም ተወዳጅነትን አትርፈውበታል፡፡

አቶ ሙስጠፋ በኢህአዴግ ፖለቲካ ውስጥ የኖሩ ሰው አይደሉም፣ክልሉን የሚመራው ሶህዴፓ አባልም አይደሉም፡፡ይልቅስ የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ፍርስራሽነት የቀየራቸውን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትን ህዝቦች በረድኤት ለመታደግ በሚሰሩ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ ሲሰሩ የኖሩ የተግባር ሰው ናቸው፡፡በስራቸው ምክንያት የእነዚህን ሃገራት አሳዛኝ እጣፋንታ ያዩት አቶ ሙስጠፋ ኢትዮጵያም እንደ ሃገር እስካልቆመች ድረስ የሶሪያ እና የየመን እጣ እንደሚጠብቃት ተረድተው ይህ እንዳይከሰት ለመስራት እንደሚፈልጉ ለአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መልልስ ገልፀዋል፡፡

ሙስጠፋ የኢህአዴግ ካድሬነት ታሪክ ስለሌላቸው የሰሩትን የመዘከሩ የፕሮፖጋንዳ ጥማት አይፈትናቸውም፣በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ችግር መጠኑን በሚወክል ሁኔታ ተረድተው በአፋጣኝነቱ መጠን ይሰራሉ እንጅ እንደ ሌሎቹ የክልል ባስልጣናት በችግሩ ዙሪያ አይዞሩም፡፡ስልጣን ላይ ከተቀመጡ ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ክልሉ ያልለመደውን የሰላም አየር እንዲስብ አድርገዋል፡፡የዘር ፖለቲካ ሃገሪቱንም ሆነ ሱማሌ ክልልን እንደማይጠቅም በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያው የሃገራችን ባለስልጣን ሙስጠፋ ኡመር ናቸው፡፡ቋንቋ መግባቢያ እንጅ ማግለያ እንዳልሆነ ለማስመስከር ዘር ሳይቆጠር ሶማሊኛ የሚናገር ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሱማሌ ክልሉ እንዲያገለግል አድርገዋል፡፡በአብዲ ኢሌ የመጨረሻ የስልጣን ቀናት የክልሉ ነዋሪዎች ዘር፣ሃይማኖት ቆጥረው የተጋደሉ ለማስመሰል የተደረገውን ክፉ ስራ ለማርከስ የክልሉ ተወላጆች ባያጠፉ እንኳን “ጥፋቱ የተደረገው በእኛው ስም ስለሆነ ወንድሞቻችንን ይቅርታ መጠየቅ፣የጠፋባቸውን ንብረት ምትክ እንዲያገኙ ማድረግ፣በስነ-ልቦና በማፅናናት ወገንተኝነታችንን ማሳየት አለብን” የሚል በጎ አካሄድ እንዲፈጠር የሙስጠፋ አመራር ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

በጎሳ ተሸንሽኖ ለመባላት አንድ ሃሙስ ቀርቶት የነበረውን የሶማሌ ክልል በጎሳዎች መካከል ያለውን ፍጥጫ ሳይቀንሱ ስለሱማሌ ክልልም ሆነ ስለኢትዮጵያዊነት ማውራት አይቻልም በሚል እሳቤ በጎሳዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር የሃገሩን ባህላዊ የእርቅ መንገድ ተጠቅሞ በጣም ባጭር ጊዜ አመርቂ ስራ ሰርቷል-አቶ ሙስጠፋ፡፡ከክልሉ መጠሪያ ጀምሮ እስከ ባንዲራው ድረስ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን ቅሬታ አዳምጦ ህዝብ በሚፈልገው መንገድ መፍትሄ ሰጥቷል፡፡አቶ ሙስጠፋ እንዲህ ባለው ብቁ አመራሩ በበኩሌ እጅግ ያሰጋኝ የነበረውን የሶማሌ ክልል ፀጥታ አረጋግቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በትርምስ ይታወቅ የነበረውን ክልል በአሁኑ ወቅት ምናልባትም ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሰላም ላይ የሚገኝ ክልል አድርጎታል፡፡ሃገራችን እንዲህ ያሉ ወደ ስራው ያመዘኑ፣ ስራቸው ራሱ አፍ አውጥቶ የሚያወራላቸው እንጅ የፕሮፖጋንዳ አጀብ የማይጠሩ ሰዎች ያስፈልጓታል፡፡

የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር በሱማሌ ክልል ሰላም አና መረጋጋት ላይ ላስመዘገቡት ስኬት የኦብነግ ድርሻም ላቅ ያለ ነው፡፡ኦብነግ በትጥቅ ትግል የህወሃት/ኢህአዴግን የግፍ አገዛዝ ከመንበሩ ለማውረድ ከሚታገሉ ብረት አንጋች ታጋዮች መካከል በአቶ መለስ በጥብቅ ይፈራ የነበረው ነው፡፡አቶ መለስ ኦብነግን ላቅ አድርገው ይፈሩት እንደነበር የክልሉን ልዩ ሃይል ለማቋቋም ያፈሰሱት በጀት፣በኦብነግ አጋርነት በተጠረጠሩ ሰዎችላይ ይፈፀም የነበረው ለየት ጭካኔ፣አብዲ ኢሌን ይዘውበት የነበረው የወዳጅነት ትስስር ጥብቀት ማስረጃ ነው፡፡በተጨማሪም ኦብነግን ወደ ሌላ ፍጥረት በሚጠጋ አረመኔነት እና ሰላም ያለመፈለግ አመፀኝነት የመፈረጁ የፕሮፖጋንዳ ናዳ ኦነግን በጥብቅ ከመፍራት የመጣ ነገር ነው፡፡

በህወሃት/ኢህአዴግ በኦብነግ ላይ በተነዛው ፕሮፖጋንዳ ሳቢያ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ መደመር ለሚለው ፍልስፍናቸው ትልቅ ፈተና ሊጋርጥ የሚችለው ኦብነግ ሊሆን ይችላል የሚል ፍርሃት ነበር፡፡የሆነው ግን ሌላ ነው፡፡ምናልባትም ኦብነግ ከአብዛኛዎቹ የኦዴፓ አመራሮች በተሻለ የዶ/ር አብይ የመደመር ፍልስፍና አጋር ሳይሆን አልቀረም፡፡ጭራሽ የአቶ ሙስጠፋን መንግስት ለመበጥበጥ በአቶ አህመድ ሽዴ እየተመራ ያለውን የሶህዴፓ እና የኦዴፓ ጥቂት አመራቶች ቡድን አደብ እንዲገዙ፣በክልሉ ሰላም ላይ ያነጣጠረ እኩይ ስራቸውን እንዲያቆሙ እያስጠነቀቀ ያለው ኦብነግ መሆኑ የሃገራችን ፖለቲካ እንዴት ባለ የግልምቢት ዘመን ላይ እንዳለ ወለል አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

የአቶ መለስ ዘመን ኢህአዴግ የቀኝ እጅ የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ የአቶ ሙስጠፋ አስተዳደር ላይ ታች ብሎ ፈር ያስያዘውን የሶማሌ ክልል ሰላም ለማደፍረስ፣የአቶ አብዲ ኢሌን ዘመን አስተዳደር ትንሳኤ ለማምጣጥ እየሰሩ እንደሆነ የክልሉ የህግ እና ሰብዓዊ መብት አማካሪ የሆኑት አቶ ጀማል ድርየ ቀጥ ባለ ግልፅ ቋንቋ ለኢሳት ተናግረዋል፡፡ይህ ግልፅነት ፌደራል መንግስቱን ጨምሮ ሌሎችም የክልል አስተዳደሮች ሊከተሉት የሚገባ አካሄድ ነው፡፡የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደ ብልህነት የሚያዩት የበዛ ማስመሰል እና መሸነጋገል ለተገዳዳሪ የመፈርጠሚያ ጊዜ ይሰጥ ይሆናል፣የችግሩንም ጥልቀት ይጨምር ይሆናል እንጅ የትም አያደርስም፡፡ይህ የተገለፀላቸው የሱማሌ ክልል ባለስልጣናት የአረመኔውን አብዲ ኢሌን አገዛዝ ትንሳኤ ለማምጣት ላይ ታች የሚሉ የሶህዴፓ ሹማምንትን (በዋናነት አቶ አህመድ ሽዴን) በስም ጠቅሰው፣ከድሮ እስከ ዘንድሮ ቅንጣት ያህል የህዝብ ወገንተኝነት የሌላቸው ስልጣን እና ጥቅም አምላኪ ተላላኪዎች እንደሆኑ አቶ ጀማል ድርየ አስረግጠው ለኢሳት ተናግረዋል፡፡

ዛሬ ለምን ሰላም ወረደ ብለው በጥባጭ የሆኑት አቶ አህመድ ሽዴ አመት ካልሞላ ጊዜ በፊት ኦብነግን በበጥባጭነት ሲከሱ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ዛሬ ደግሞ ሸሽተው ቱርክ ኢስታምቡል ከገቡ የአብዲ ኢሌ ግብራበሮች ጋር ግንባር በመፍጠር ክልሉን ለማረጋጋት ደፋ ቀና የሚሉ ሰዎችን ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው፡፡አሁን የማን ምንነት አየለየ ነው፡፡አሁን በሹመት ላይ ሆነውም በመከራ የተረጋጋውን ክልል ለማመስ እየሞከሩ ያሉት አቶ አህመድ ሽዴ ድሮም አሁንም የሶማሌ ክልል ሰላም እና የህዝቡ እጣ ፋንታ የሚያስጨንቃቸው ሰው እንዳልነበሩ ነው ከሰሞኑ ስራቸው መገንዘብ የሚቻለው፡፡በአንፃሩ ትናንት በአመፀኝነት ሲከሱት የነበረው አብነግ ሳይሾም ሳይሸለም፣አመራሮቼ በክልሉ አስተዳደር ላይ ይሾሙልኝ ሳይል ለህዝብ ሰላም ስለሆነ ብቻ በቂ ነው ብሎ አደብ ገዝቶ መቀመጡ ሳያንስ እነሱኑ እንዲታገሱ እየመከረ ነው፡፡አልፎ ተርፎም በሃገራችን የዘር ፖለቲካ አብቅቶ የዲሞክራሲ ዘመን እንዲመጣ ለመስራት ስለሚፈልግ ለዚሁ እንዲመቸው ራሱን ወደ ህብረብሄራዊ ፓርቲነት ሊቀይር እንደሆነ በይፋ ተናግሯል፡፡ይህ ያልገረመው አይገኘም መቼም!

የኦብነግ ጨዋነት ትናንት ትጥቅ ያስነሳው በህዝብ ላይ ሲደረግ የነበረው ግፍ ብቻ እንደሆነ አስመስካሪ ነው፡፡ይህ የኦብነግ ብስለት የተሞላበት ፖለቲካዊ ጨዋነት ለሶማሌ ክልልም ሆነ ለሃገራችን መረጋጋት እጅግ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡በአራቱም ማዕዘን በሰላም ውላ በማታድረው ሃገራችን ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ኦብነግም እንደ ኦነግ ለጠብም ለፍቅርም የማይመች ቢሆን ኖሮ ፈተናችን ይከብድ ነበር፡፡አብዲ ኢሌን ሲወጋ የነበረው ኦብነግ አቶ ሙስጠፋንም ለመውጋት አልተነሳም፤ በአንፃሩ ብዙ አመት ታገልኩ የሚለው ኦነግ አቶ አባዱላን/አቶ ሙክታርን ለመውጋት አልሆንልህ ባለው ጦሩ አቶ ለማ መገርሳን የመሰሉ ሰው ሊወጋ ይገለገላል፡፡

የኦብነግ የአዋቂ እርምጃ፣የአቶ ሙስጠፋ ድንቅ አመራር ከሱማሌ ህዝብ የሚበጀውን አዋቂነት ጋር ተደማምሮ የጅጅጋ ፖለቲካ ሙክክ ብሎ እንዲበስል አድርጎታል፡፡አሁን በነእ አቶ አህመድ ሽዴ ቆስቋሽነት የተነሳው የለውጥ ቅልበሳ ሴራ የሚናቅ ባይሆንም ህዝባዊ ድጋፍ ስለማይኖረው እምብዛም ሩቅ የማይሄድ ግን ደግሞ በአንክሮ ሊታይ እና መላ ሊባል የሚገባው ችግር ይሆናል፡፡አቶ አህመድ ሽዴ ከዚህ በኋላም በዶ/ር አብይ እልፍኝ እንዲሽሞነሞኑ ሊፈቀድላቸው አይገባም፡፡ሌላ ሰው የማይገባው የኢህአዴግ ካድሬዎች ጠላትን አጠገብ በማድረግ የሚከናወን የፖለቲካ ጨዋታም ቢሆን እንዲህ ነገሮች ፍርጥ ብለው ከወጡ በኋላ የሚያመጣው ጥቅም ያለ አይመስለኝም፡፡

ይልቅስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የወዳጅ ጠላትን ማጥፋቱ የተሻለ ይሆናል፡፡አደገኛ ጠላትን አጠገብ አድርጎ መሾም መሸለሙ፣በክልሉ የተጠላ ካድሬን ፌደራል ወንበር ላይ ቂብ አድርጎ ረዥም እጁን ወደ ተወለደበት ክልል ፖለቲካ እንዲሰድ የመልቀቁ የኢህአዴግ ካድሬዎች ዘይቤ ኢህአዴግ ላልሆኑት አቶ ሙስጠፋ ግርታን መፍጠሩ አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ አቶ ሙስጠፋ ዑመር ድምፃቸውን አጥፍተው፣በአጭር ጊዜ ላስመዘገቡት ድንቅ አስተዳደራዊ ብልጫ ምስጋና የሚገባቸ፣ያለንበትን ዘመን የሚመጥን ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሊደግፋቸው የሚገባ፣በሃገር ደረጃ ሳይቀር ትልቅ ስራ የመስራት ችሎታ ያላቸው ብስል እና የተግባር ሰው ናቸው፡፡

___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የአዴፓ እና ህወሃት”እርቅ” ይሰምራል? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ጥር 15 2011 ዓ. ም.

ህወሃት አንጉቶ የጋገረው ኢህዴን ፈጣሪው ህወሃት ሁን ያውን ሁሉ እየሆነ ሰላሳ አምስት የታዛዥነት ዘመናትን አሳልፏል፡፡ኢህዴን መነሻው የወቅቱን የሃገራችንን ፖለቲካ ቀልብ ስቦ ከነበረው ኢህኣፓ ነው፡፡ኢህአፓ ደግሞ ህወሃቶች ማኒፌስቶ እንኳን ሳይፅፉ ታጋይ ነን የሚሉ ልሙጥ ፖለቲካኞች መሆናቸውን እየጠቀሰ ከመናቅ አልፎ ሲዘባበትባቸው የነበረው ፓርቲ ነው፡፡ነገሮች ተገለባብጠው የተናቀው ህወሃት በሃገራችን ፖለቲካ ላይ ጌታ መሆኑን አስረግጦ ጭራሽ አሽከር የሚያምረው ኋላቀር ጌታ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ህወሃት በሃገራችን የሰፈነው የዘር ፖለቲካ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቁጭ ሲል አሽከሮቹ ደግሞ የየክልላቸውን የዘር ቆጠራ ፖለቲካ የሚያስተናብሩ፣ጆሯቸውን ከጌታቸው ከህወሃት ንግግር ለአፍታ አንስተው ለህዝባቸው የማያውሱ ከፊል መስማት ተሳነው ሆነው ብዙ ዘመን ኖረዋል፡፡በዚህ አሽከርነቱ እንከን የማይወጣለት የቀድሞው ኢህዴን፣የትናንቱ ብአዴን ነው፡፡

ኢህዴን ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሆኖ ሳለ ለአንድ ዘር ቆሜያለሁ ለሚለው ህወሃት አሽከር ሆኖ መታዘዙ ነውር መስሎት የሚያውቅ አይደለም፡፡ጭራሽ እንደ ጌታ ለማጎንበስ ሲል ከኢህዴንነቱ ተኮማትሮ “ብአዴን ነኝ” ሲል ለአንድ ዘር በመቆሙ ጌታውን መስሎ ቁጭ አለ፡፡በብአዴንነት ዘመኑ ታዲያ ጌታው ህወሃት ጥርስ የነከሰበትን የአማራ ሕዝብ በእሾህ ለበቅ ሲገርፍ አንገቱን ደፍቶ የኖረ ወገንተኝነቱ ለጌታው ህወሃት ብቻ የሆነ ስብስብ ነበር፡፡ይህን ጠንቅቆ የሚያውቀው የአማራ ክልል ህዝብም ብአዴንን እና ህወሃትን አንድ እና ያው ብሎ መድቧቸው ራሱን ነፃ የማውጣቱ ትግል ከሁለቱም ጋር እንደሆነ አምኖ ትግሉን በዚሁ መሰረት አስኬደ፡፡ሆኖም በመለወጡ ተስፋ የተቆረጠበት ብአዴን እንደ አላዛር ባለ ሁኔታ ከፖለቲካ ሞቱ ተነስቶ፣የህዝብን ትግል ተገን አድርጎ ጌታውን ማንጓጠጥ ጀመረ፡፡

ብአዴን እና ሌላው የረዥም ዘመን አሽከር ኦህዴድ እንደ ሰው እምቢ ማለት በጀመሩ አፍታም ሳይቆይ የጌታ ጉልበት መብረክረክ ጀመረ፡፡ጌትነቱም አከተመ፤ወንበሩም በትናንት አገልጋዮች ተያዘ፡፡የአገልጋች ስም ተቀየረ፡፡ዛሬ የህወሃትን መንበር የሚሸከሙት ብአዴን እና ኦህዴድ የሉም፤ህወሃትም ከዙፋኑ ውርዶ መለስተኛ አስተዳዳሪ ሆኖ መቀሌ ከትሟል፡፡ሆኖም ህወሃት እግሩ ከወንበር ይውረድ እንጅ ልቡ ዛሬም ጌትነቱን እንጅ መለስተኛ አስተዳዳሪነቱን የተቀበለው አይመስልም፣ራሱን አግዝፎ የሚያይበት መነፅርም፣የቀድሞው እበልጣለሁ እና ከኔ በላይ ብልጥ ላሳር ባይ ስነልቦናውም የተቀየረ አይመስልም፡፡ዛሬም በአድራጊ ፈጣሪነቱ ዘመን በሰፊ እጁ ያፈሰውን ሁሉ እንደልቡ መቆርጠም ይፈልጋል፡፡

ጠመንጃውን ተመርኩዞ ከአማራ ክልል ያፈሰውን ለም መሬት ዛሬም ተዝናንቶ አርሶ፣ ምርት ማፈስ ይፈልጋል፡፡ይህን ፍላጎቱን አደባባይ ወጥቶ ሲናገር “የአማራ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ ጠብ የለውም፣እኔም ከገዱ ጠብ የለኝም እንደውም ጓዶች ነን” ይላል በርዕስ መተዳድሩ በዶ/ር ደብረፅዮን አፍ፡፡ከትናንት በስቲያ በሽማግሌዎች ፊት ይቅር ለእግዜር እንባባል ብለው የተሰየሙት የአማራ ክልል እና የትግራይ ክልል መሪዎች ጋዜጣዊ መግለጫ ባሉት ዲስኩራቸው ብዙ ማድበስበስ እና እልፍ ማስመለሎችን ሲያዘንቡ አምሽተዋል፡፡ትልቅ ችግር መደንቀሩ ሳይጠፋቸው ምንም ችግር እንደሌለ ሲቀላምዱ ሰሚን ያሰለቻሉ፡፡የተለመደውን መፍትሄ አልቦ፣እውቀት አልቦ፣መስህብ የለሽ የካድሬ ንግግራቸውን ግተውን ወርደዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ እና የአማራ ህዝብ አልተጣላም የሚለው ከካድሬዎቹ አልፎ የሌሎቻችንም የንግግር ማሳመሪያ እየሆነ የመጣው የማድበስበስ ፈሊጥ በሁለቱ ክልሎች ላይ ላንዣበበው ትልቅ ችግር መፍትሄ ቢሆን ኖሮ እሰየው ነበር፡፡ ለመሆኑ ሁለቱ ባለስልጣናት እስኪያቅረን እንደነገሩን የትግራይ እና የአማራ ህዝብ ካልጣላ፣ክልሉን የሚመሩት ሰዎችም ጓዶች ከሆኑ ሽምግልናውን ምን አመጣው ሊባል ነው? ነው ወይስ ዶ/ር ደብረፅዮን መቀለዴ ብለው እንደ ተናገሩት ሽማግሌዎቹ እና ደብረፅዮን ስለተዋደዱ ነው እየተገናኙ የሚሸማገሉት?ማድበስበስ ምን ያህል ያስኬዳል? የቱን ችግር ይፈታል?

ሽማግሌ ተብየዎቹስ በምን አላማ ሊያሸማግሉ እንደተነሱ፣ከሽምግልናው ምን መፍትሄ እንደሚጠበቅ ወይም የተሳካ ነገር ካለ ከመቀሌ ባህርዳር፣ ከባህርዳር አዲስ አበባ የሚንከራተተው ሽምግልናቸው ትርፍ ምን እንደሆነ ለህዝብ ግልፅ የማያደርጉበት ሽምግልና ለማን ምን ትርጉም ይኖረዋል ብለው ነው የሚደክሙት?ከዚህ በፊት የሽምግልናቸው ልዕልና የት ድረስ ቁልቁል እንደሚምዘገዘግ የታዩ ሰዎች እንዲህ በሽፍንፍን የሚያደርጉት ቀርቶ በግልፅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴም በህዝብ ዘንድ እንዴት በአጥርጣሬ እንደሚታይ አለማወቃቸው ትልቁ ችግራቸው ነው፡፡

በፖለቲከኞቹ በኩል ያለው ማድበስበስ እና ማስመሰል ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ከእውነት ጋር ክፉኛ የተጣላ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ሁለቱም መሪዎች ነገ ዛሬ ሳይባል ተፍረጥርጦ ውይይት ሊደረግበት የሚገባ አንገብጋቢ ችግር ታቅፈው የሚመሩትን ህዝብ እየጠቀሱ ጥርስ ያበቀለ ህፃን ሳይቀር የሚያውቀውን ጠቅላላ እውነት ሲደጋግሙ መዋላቸው ለዚህ ምስክር ነው፡፡አንዱ ተደራዳሪ “የእንትን ህዝብ ከሰላም ስለሚጠቀም አጥብቆ ሰላም ይፈልጋል እና ቀድሞ ጥይት አይተኩስም”ሲል፤ሌላው በኦሪት ዘመን የተደረገውን እያነሳ “የኔ አካባቢ ህዝብ እነ እንቶኔ ከእንትን ሃገር ሲመጡ አስጠልሎ ነበር አሁን ግን ተፈናቀለ ይህም ሆኖ ችግሩን ይሸከማል እንጅ ጥይት አይተኩስም” ይላል፡፡ቀድሞ ነገር ከሰላም የማይጠቀም ህዝብ የለም፡፡ሲቀጥል የአመፅ ልብ ይዞ፣በእበልጣለሁ ባይነት ታጅሎ በኦሪት ዘመን አንድ ደግ ንጉስ ያደረጉት እንግዳ ተቀባይነት ደጋግመው ቢያወሩት ለዚህ ዘመን ችግር መፍትሄ አይሆንም፡፡የደጉ ንጉስ ስራ የሚወክለው ራሳቸውን እንጅ ዘራፊውን እና ገራፊውን ህወሃትን አይደለም፡፡የህወሃት ተጨባጭ ማንነት ሌላ ነው፡፡

ህወሃት ህዝብን በጊንጥ የሚገርፍ፣በዘረፋው እና በግፉ ሃገር ከመመረሩ የተነሳ “ሆ!” ብሎ ወጥቶ ከወንበሩ የፈጠፈጠው የአረመኔዎች ስብስብ ነው፡፡ህወሃትነትን የመሰለ ደም የተነከረ ሸማ የለበሰ ሰው የደጉን ንጉስ ስራ እየጠራ ሌላውን ህዝብን ባፈናቃይነት መክሰስ ትልቅ ግብዝነት ነው፡፡ማን በማን ላይ እንዴት ያለ አሰቃቂ ወንጀል እንደሰራ፣ማን አቡክቶ የጋገረውእብሪት እና ዘረኝነት ወለድ ችግር በአጎራባች ህዝቦች መሃከል የእልቂት ዳመና እንዲያንዣብብ እንዳደረገ፣መሬቱን እና ማንነቱን ተቀምቶ በመፈናቀሉ፣በመገደሉ፣በመሳደዱ፣በስውር እና ግልፅ እስርቤት አሳር መከራ በማየቱ በኩል ማን የሚብስ ብሶት እንዳለው የሁሉም ሆድ ያውቀዋል-ሽማግሌ ተብየዎቹም ጭምር፡፡ሆዳቸው ሲያውቅ እንሸማገል ብለው የተሰየሙት ሹማምንትም ጉዳያቸው ከቄስ መነኩሴ ሽምግልና አለፍ ያለ የህግ የበላይነት፣የተጠያቂነት፣የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የመሳለሉ ስልጣን፣እብሪት እና ጠመንጃ መራሽ ችግሮች ጥርቅም እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል፡፡

ፖለቲከኞቹም ሆኑ ሽማግሌዎቹ ሆዳቸው ሲያውቅ ሽምግልና ያስቀመጣቸው ምንድን ነው የሚለውን ነገር መመርመር ያስፈልጋል፡፡እንደሚታወቀው ሽምግልናው የተደረገው የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ሊደረግ ቀናት ሲቀረው ነው፡፡በዚህ ስብሰባ ላይ ደግሞ በተካረረ መነቋቆር የቆዩት የአዴፓ እና ህወሃት ሹማምንት ሊገኙ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች የችግሩን ስር በማይነቅለው የቄስ መነኩሴ ሽምግልና መሸማገላቸው ምናልባትም ለስብሰባው ሲገናኙ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሚያስቸግር አምባጓሮ ውስጥ እንዳይገቡ ለማለሳለስ ይሆናል እንጅ ውስብስቡ የአማራ እና ትግራይ ክልል ችግር በምናውቃቸው በነፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ ሽምግልና እልባት ያገኛል ተብሎ አይደለም፡፡የጋዜጣዊ መግለጫው ፍሬ ከርስኪነት ለዚህ እሳቤ ምስክር ነው፡፡

በተረፈ ሽምግልናን ለምን እንደሚጠቀም ከሚታወቀው ህወሃት ጋር በቄስ መነኩሴ ተሸማግዩ ፖለቲካዊ ችግሮችን በቤተ-ዘመድ “አንተም ተው አንተም ተው” እፈታለሁ ማለት የችግሩን መጠንም ሆነ ችግሩን ማድበስበሱ የሚያስከትለውን አደጋ አለመረዳት ነው፡፡ህወሃት ሽምግልናን የሚጠቀመው ለብልጣብልጥ አላማው ማስፈፃሚ ብቻ እንደሆነ ካለፈው መማር ያስፈልጋል፡፡ይህ የሚሆነው ደግሞ ህወሃት በቀድሞው የአዛዥ ናዛዥነቱ ወንበር ላይ ቢሆን ነበር፡፡አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ስለዚህ ለህወሃት ሽምግልና እንደወትሮው የልቡን የሚያደርስለት፣አዘናግቶ የሚመታበት የጊዜ መግዣ፣ጣላትን ማደንዘዣ በስተመጨረሻም እንዳይነሳ አድርጎ መቅበሪያ መሰሪ ትዕንት አይደለም፡፡

ዶ/ር ደብረፅዮን ችግሮችን በሽምግልና ከመፍታት ይልቅ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ይመርጡ እንደ ነበር ቁጭት ባዘለ የተሸናፊነት ድምፀት በንግግራቸው መጀመሪያ በገደምዳሜ ተናግረዋል፡፡ሽምግልና የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ቡራኬ ቢሆን ነበር የህወሃት ፍላጎት፡፡ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በተባለው ህወሃትን የአሸናፊነት ማዕከል ላይ በሚያስቀምጠው ፈረስ ላይ ተጭኖ ያልመጣ መፍትሄ ሁሉ ለህወሃት አይጥመውም ብቻ ሳይሆን ያሳዝነዋል፡፡ዶ/ር ደብረፅዮን ለሽማግሌዎቹ “ሳመሰግናችሁ እያዘንኩ ነው” ያሉትም ለዚህ ነው፡፡ደብረፅዮንን ያሳዘናቸው “የፓርቲ እሴት መሸርሸር” ሲሉ የገለፁት የብአዴን ወደ አዴፓ መቀየር፣የታዛዥን ወደ እኩልነት ተርታ መምጣት የሚወክለውን የፓለቲካ መናወጥ ነው፡፡
ብአዴን ወደ አዴፓ የመቀየሩ ነገር የስም ለውጥ ብቻ አይደለም፡፡ወትሮ ህወሃት ያለውን ነጥቆ እየበረረ፣በህዝቡ ኪሳራ የአዛዡን ፍላጎት ያስጠብቅ የነበረው ብአዴን ዛሬ ስም ከምግባር ተቀይሯል፡፡ጌታ ቀይሯል-ህወሃትን በሚያስተዳድረው ህዝብ፡፡አቶ ገዱ በሽምግልናው ፍፃሜ ከዶ/ር ደብረፅዮን ጋር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በተደጋጋሚ”እኔ እዚህም እዛም ስሄድ የማወራው ተመሳሳይ ነገር ነው….ከዚህ ውጭ ብሄድ ህዝብ አይፈቅድልኝም” ያሉት ነገር ትርጉሙ የድሮው አይደለሁም፤ጌታየም ተቀይሯል ማለት ነው፡፡

ይህን መራራ እውነት መቀበል የማይፈልገው ህወሃት ታዲያ የአዴፓን ከህዝብ የመወገን ወደ በጎ የመለወጥ ነገር “የድርጅታችን እሴት መሸርሸር” እና “የእኛ ስራችንን አለመስራት” ሲሉ በቁጭት ይጠቅሱታል፡፡ሁልጊዜ አሸናፊነትን እና እበልጣለሁ ባይነትን ሰንቆ የሚነሳው ህወሃት የሚያስበው እንዲህ ነው፡፡ህወሃት ሲያሾረው በኖረው ኢህአዴግ የድርጅት እሴት ተከበረ የሚባለው የግንባሩ አባል እና አጋር ድርጅትቶች ሹማምንት በየተሾሙበት ክልልላቸው ህወሃት ሊኖረው የሚችለውን አምሮት ማሳካት ነው-መሬት ካማረው መሬት፣ንግድ ካማረው ገበያ፣ዝርፊያም ካማረው ህጋዊ፣አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ሽፋን መስጠት፡፡

አሁን ይህ ነባር የቤታቤት ደምብ የለም፡፡ህወሃት ማዘዝ አቁሟል፡፡የቀድሞ ታዛዦቹም ማሸብሸብ ትተው የቀድሞ አዘዣቸውን በትከሻቸው ከማየት አልፈው ወንበር ነጥቀው፤ከማእከል አባረው ጠረፍ አስይዘውታል፡፡የቀድሞው የህወሃት ማዘዝ እና የአጋር/አባል ፓርቲዎች መታዘዝ እንደወትሮው አለመቀጠሉ ነው በዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር ውስጥ”…እኛ ስራችንን መስራት ባለመቻላችን ነው ይህ ሁሉ የመጣው” ተብሎ የተገለፀው፡፡

በሽታውን የደበቀ መድሃኒት ከወዴት ይማስለታል?

በአጠቃላይ የሽምግልናው ማሳረጊ ተብሎ በተሰጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከህወሃትም ሆነ ከአዴፓ በኩል በችግሩ ዙሪያ ከመዞር እና ከማድበስበስ በቀር በችግሩ ላይ የቆመ ሃሳብ አልተሰነዘረም፡፡እንደውም ንግግራቸው ሲጠቃለል በአማራ እና በትግራይ ሕዝብ ዘንድም ሆነ በህወሃት እና በአዴፓ መሃከል ምንም አይነት ችግር እንደሌለ ነው የተገለፀው፡፡ይህን የሚለው መቀሌ ላይ ሰልፍ ጠርቶ በትግራይ ሕዝብ ላይ ትልቅ ስጋት እንዳለ ለህዝብ የሚናገረው ህወሃት ነው፡፡መቀሌ ላይ የትግራይ ህዝብ በትልቅ አደጋ ውስጥ በመሆኑ የተነሳ ለማንኛውም ነገር መዘጋጀት እንዳለበት ያወሩት ዶ/ር ደብረፅዮን ሂልተን ሆቴል ላይ “ጓዴ” ካሏቸው አቶ ገዱ አጠገብ ተምጠው የሚያወሩት ደግሞ ገብስ ገብሱን ነው፡፡
እንደውም በተለመደው ህወሃታዊ ብልጣብልጥነት የጎንደር ህዝብ ሲሞት፣ሲሰደድ፣ሲገረፍ፣ሲፈናቀል የኖረለትን የድንበር ጥያቄ፣ማንነት የመነጠቅ ጉዳይ በምድር ላይ የሌለ ጉዳይ እንደሆነ፣አቶ ገዱ እና እሳቸውም እንደ አጋጣሚ በሽማግሌዎች ፊት ተገኙ እንጅ በሁለቱ ክልሎች መካከል ኮሽታም እንደማይሰማ እንዲህ ሲሉ ገለፁ “ሁለታችን ስለተጠራን እንጅ የተለየ ግጭት የለንም፤ሊያበጣብጡን የሚፈልጉ አሉ፤የወሰን ችግር የለብንም ፣የመሬት ነገር አጀንዳችን መሆን የለበትም፤በቦታ የምንጋጭ አይሆንም;አልተጋጨንም…”፡፡የዚህ አባባል ትርጉም፣አላማ እና ፖለቲካዊ ጥቅም የኢህአዴግ ካድሬ ሆኖ ለማያውቅ ሰው ሊገባው አይችልም፡፡

እንዲህ በሽታውን ሽምጥጥ አድርጎ የሚክድ ሰው ከነበሽታው አፈር ከመግባት በቀር ምን መፍትሄ ይፈለግለታል፡፡የሽምግልናውም ሆነ የጋዜጣዊ መግለጫው ያስፈለገበትን ዋና ጉዳይ፣እሳቸው ራሳቸው በዛች ቅፅበት እዛ ቦታ ተገኝተው እንዲያወሩ ያደረጋቸውን ዋና ነገር የለም ሲሉ ከካዱ ሰውየ ጋር ተነጋግሮ ለመግባባት፣መፍትሄም ለማምጣት የመላዕክት ቋንቋ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ፖለቲካ እና ሰላም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ተደርገው የቀረቡበት የዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር ነው፡፡”ፖለቲካውን ለብቻ ሰላሙን ለብቻ … ፖለቲካው ሊቆይ ይችላል ሰላሙ ግን ጊዜ አይሰጥም ፤ይቆይ ፖለቲካው ሰላም ይቅደም…..” ይላሉ ፖለቲካ አዋቂ ነኝ ብለው ሃያ ሰባት አመት በሃገሪቱ ፖለቲካ ዋና ዋና ቦታ ላይ የኖሩት ዶ/ር ደብረፅዮን፡፡ፖለቲካው ባልተረጋጋበት ሃገር እንዴት ያለ ሰላም እንደሚጠበቅ የሚያውቁት ደብረፅዮን ብቻ ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር ይህን የሰውየውን ንግግር ስሰማ በሁነኛ እጅ ላይ ወድቆ በማያውቀው የሃገሬ ፖለቲካ አዝኛለሁ፡፡ኢህአዴግ በከፍተኛ የአሳቢ ጭንቅላት ድርቅ የተመታ ፓርቲ መሆኑ ድሮም የሚታወቅ ቢሆንም ይህ ንግግር ደግሞ ይህንኑ የሚያጠናክር ነገር ነው፡፡የሃገራችን ችግር በኢህአዴግ ካድሬዎች የመፈታቱ ነገር አጠያያቂ የሚሆነውም በዚሁ በፓርቲው ሰዎች የእውቀት ጠብ ነው፡፡ ከእውቀትም ከእውነትም ተጣልቶ ምን መፍትሄ ሊመጣ እንደሚችል ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የህወሃት መኳንንት ነገር…. (በመስከረም አበራ)

(በመስከረም አበራ)
ጥር 8 2011 ዓ.ም.

በሃያ ሰባት አመታት የህወሃት/ኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርዓት የኖረው የሃገራችን ህዝብ በትግሉ የህወሃትን የበላይነት ከኢትዮጵያም ከኢህአዴግም ትከሻ ማሽቀንጠርን ችሏል፡፡ስልጣን ሲጥመው የቀረበት ህወሃት ታዲያ እሱ የማይዘውራት ኢትዮጵያ በሰላም ውላ ማደሯን የሚወድ አይመስልም፡፡ በስልጣን ዘመኑ “እኔ ከሌለሁ ሃገር ይፈርሳል” እያለ ሲያስፈራራ ስለኖረ እሱ በሌለበት ሃገር ሰላም ውላ ማደር እንደማትችል ማስመስከር ይፈልጋል፡፡ህዝብ ለውጡን ለመደገፍ ነቅሎ በወጣበት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር፣በሃገሪቱ አራቱም አቅጣጫ የሚከሰቱ ብጥብጦችን በመቆስቆስ፣እንደ ኦነግ ያለውን ወዳጅ ጠላት የማይለይን የፖለቲካ ቡድን አይዞህ እያለ በማበጣበጥ ይጠረጠራል -ስልጣን ወዳዱ ህወሃት፡፡

ሳይፈልግ ብቻ ሳይሆን ሳያስብ የለውጥ ማዕበል ያጣለመው ህወሃት ለውጡ ይዞት የመጣውን አመራር ለመቀበል እንደተቸገረ ያስታውቅበታል፡፡አሁን የለውጥ ሃይል ሆኖ ስልጣን የተቆናጡት አካላት(በዋናነት ኦዴፓ እና አዴፓ) ቀድሞ የህወሃት ታማኝ ታዛዥ አገልጋዮቹ የነበሩ መሆናቸው ህወሃት ለራሱ ከሚሰጠው የተጋነነ እና የተሳሳተ ግምት ጋር ሲደመር ያፈጠጠውን እውነት ለመቀበል እንዲቸገር ሳያደርገው አልቀረም፡፡

ህወሃት ሊወድቅ ዘመም ዘመም ሲል ወደ ጀርመን ተጉዘው የህወሃት ደጋፊዎችን ያነጋገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ “ህወሃት በሌላ ይታዘዝ ማለት ነውር ነው” ሲሉ የተናገሩት ንግግር ህወሃቶች ንዑስነታቸውን በማይመጠን ሁኔታ ለራሳቸው የሰጡትን ትልቅ ግምት አመላካች ነው፡፡እንዲህ ባለ አለቅጥ በተጋነነ የትልቅነት ስነ-ልቦና ውስጥ የቆየው ህወሃት በራሱ አገልጋዮች ተባርሮ መቀሌ መግባቱ ሊቀበለው የማይፈልገው ሃቅ ነው፡፡ሃቅን መቀበል ባለመቻሉ ሳቢያ በስነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ያለው ህወሃት የራሱን ቀውስ ሃገራዊ ቀውስ ለማስመሰል ታጥቆ እየሰራ ነው፡፡በዚህ ምክንያት በሃገራችን የታየውን የለውጥ ጭላንጭል በማጨለሙ በኩል ህወሃት ቀዳሚው ስጋት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ህወሃት የለውጡ ስጋት መሆኑን የሚያስመሰክርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡የመጀመሪያው እና ዋነኛው በወንበሩ ላይ የተቀመጠውን የለውጥ አመራር እንደመንግስት ለመቀበል መቸገር ነው፡፡ይህ ዝንባሌ ከሚገለፅባቸው ሃቆች አንዱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር በወንጀል የሚፈልጋቸውን ግለሰቦች ትግራይ ሰብስቦ ማስቀመጡ ነው፡፡ጌታቸው አሰፋን የመሰለ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ በጉያው የያዘው ህወሃት “ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ይዤ ለማእከላዊው መንግስት የሰጠሁት እኔ ነኝ” ሲልም ይደመጣል፡፡ ጀነራል ክንፈ ዳኘው በተያዙ ሰሞን ወንጀለኞችን ለመያዝ የትግራይ ክልላዊ መንግሰስት ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ የክልሉ መሪ ዶ/ር ደብረፅዮን ተናግርው ነበር፡፡ ይህን ብለው አፍታም ሳይቆዩ ደግሞ “ወንጀለኞችን ተጠያቂ የሚያደርገው የመንግት አካሄድ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ያለመ ነው” ሲሉ ነገሩን ሁሉ እግር በራስ አድርገውት ቁጭ አሉ፡፡ይህ አደገኛ አስተሳሰብ የሚመሩት ክልል ህዝብም የሚጋራው እንደሆነ በተግባር ለማሳየት ሰላማዊ ሰልፍ በማታውቀው ትግራይ ክልል ሰው በቤቱ የቀረ የማይመስልበት ሰልፍ አሰለፉ፡፡

ህግ የሚፈልጋቸውን ተጠርጣሪ ወንጀለኞች የደበቀ ክልል ህገ-መንግስት ይከበር ሲል የዋለበት ሰልፍ የትግራይ ክልል መንግስት ለዶ/ር አብይ አስተዳደር ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆኑን ያስመሰከረበት ነው፡፡ ይህን በመሰለው ለተጠረጠረ ወንጀለኛ ጥብቅና የመቆም ሰልፍ ያሁሉ የትግራይ ህዝብ መገኘቱ ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ በጣም የተራራቁ ናቸው ብሎ የሚያስበውን ከትግራይ ውጭ ያለ ሌላው ኢትዮጵያዊ በከፍተኛ ግርምት ውስጥ የከተተ ነበር፡፡

በሰልፉ ሰዓት ከተደረገው የዶ/ር ደብረፅዮን ንግግር በተጨማሪ እንደ አቶ አስመላሽ ገ/ስላሴ፣አቶ ስብሃት ነጋ ያሉ የህወሃት አባላትም በትግራይ ቲቪ ብቅ እያሉ የሚናገሩት ንግግር ኢትዮጵያ ከህወሃት ውጭ በሌላ መተዳደሯ እንደማይዋጥላቸው የሚያሳብቅ ነው፡፡አልዋጥ ያላቸው ሃቅ ደግሞ ህዝብን አግተልትሎ ሰልፍ ከማስወጣት አልፎ በመላ ሃገሪቱ የሚደረጉ ብጥብጦችን እስከ ማጋፈር የደረሰ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ከመንግስት በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተገለፀ ነው፡፡

የትግራይ ክልላዊ መንግስት ለፌደራሉ መንግስት አልታዘዝም ከማለት አልፎ ራሱን እንደ ሉዓላዊ ግዛት በማሰብ በህገመንግስቱ ያልተፈቀደለትን አካሄድ እንደ መብት በመቁጠር ለኤርትራ መንግስት ደብዳቤዎችን በመፃፍ ግንኙነት ለማድረግ ሲሞክር ታይቷል፡፡ የሃገር መከላከያ ሰራዊት በፌደራል መንግስቱ ታዞ ከዛላምበሳ በሚነሳበት ወቅት ያካባቢው ነዋሪ ያለመብቱ ገብቶ ለማዘዝ ሞክሯል፡፡ የክልሉ መንግስት በማዕከላዊ መንግስት ትዕዛዝ ለስራ ጉዳይ ወደ ትግራይ የሚገቡ ወታደራዊ መኮንኖችን እና ተሸከርካሪዎቻቸውን አግቶ ለወራት በትግራይ አስቀምጧል፡፡ዶ/ር ደብረፅዮንን፣አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴን፣አቶ ጌታቸው ረዳን፣አቶ አባይ ፀሃይየን ጨምሮ አብዛኞቹ የህወሃት አባል የፓርላማ ተመራጮች ሌላው ቀርቶ ዶ/ር አብይ ፓርላማ በሚገኙባቸው ቀናት እንኳን የፓርላማ ወንበራቸው ላይ አይታዩም፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ፓርላማው ከፍተኛው የስልጣን ባለቤት ነው፡፡የፓርላማ አባላት የተባሉ ሰዎች በመርህ ደረጃ ይህን ከፍተኛ ስልጣን የተሸከሙ ግለሰቦች ናቸው፡፡ስልጣን ደግሞ ሃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው ነገር ነው፡፡ የፓርላማ አባልነትን የመሰለ ክብር ያለው ሃላፊነት የተሸከሙ ሰዎች ከኔ ቢጤው ተራ ህዝብ ላቅ ያለ ህግ የማክበር ስብዕና ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡በእኛ ሃገር በተለይ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የፓርላማ አባላት ላይ እየታየ ያለው ፈለግ ግን ህግ አክባሪነትን የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡ የህዝብ ድምፅ ይሆናሉ ተብለው በክቡሩ የፓርላማ ወንበር የተሰየሙ አባላት አዘውትረው በፓርላማ ስፍራቸው ሲገኙ አይታይም፡፡

ይህ ነገር በህወሃት ባለስልጣናት በተለይ ባስ ይላል፡፡ ከላይ በስም የተጠቀሱት የህወሃት ባለስልጣናት የዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በፓርላማ አዘውተረው ሲገኙ አይታይም፡፡ በተመሳሳይ የቀድሞው ጠ/ሚ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ ባላቸው አቶ መለስ ካረፉ ጀምሮ ወደ ፓርላማ ትውር ብለው አያውቁም፡፡ይብስ የሚገርመው ደግሞ ህግ-ይከበር ብለው ሰልፍ የሚወጡት/የሚያስወጡት እነሱው መሆናቸው ነው፡፡ከዚህ የምንረዳው ለነዚህ የህወሃት ባለስልጣናት ፓርላ የሚያስቀምጣቸው፣ሃላፊነቱ የሚጥማቸው፣ህግ አክባሪ ከእኔ በላይ ላሳር የሚያስብላቸው ሁሉ የተቆራኛቸው የስልጣን ጥም እንጅ ሌላ እንዳልሆነ ነው፡፡ባይሆን ኖሮ የአዲስ አበባውን ስልጣን ተነጥቀው ወደ መቀሌ በኮበለሉ ማግስት ስለ ህግ አክባሪነታቸው ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ሲመፃደቁ መኖራቸውን ረስተው የፓርላማ ወንበራቸው ላይ እንኳን ያለመገኘት ተራ አመፀኛነት ውስጥ አይገቡም ነበር፡፡

እነዚህ ባለስልጣናት ፓርላማ አለመገኘታቸውን አስመልክቶ ሃይ የሚላቸው አካል የሌለ መሆኑ ደግሞ ኢህአዴግ መሪ በሆነበት መንግስት ህግ ምን ያህል መቀለጃ እንደሆነ ያሳያል፡፡መቼም የፓርላማ አባላት ስነ-ምግባር ከፓርላማ ስንት ቀን መቅረት እንደሚያስቀጣ ሳያስቀምጥ አይቀርም፡፡ፓርላማ ቀርቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ተማሪ ምን ያህሉን የትምህርት ቀን በክፍል ውስጥ መገኘት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ራሳቸውን እንደ ህግ አክባሪ በመቁጠር አትዝረፉ ያላቸውን ሁሉ በህገ-ወጥነት እየከሰሱ የሞት ፍርድ ሲፈርዱ የነበሩ ግብዝ የህወሃት ባለስልጣናትም ከፓርላማ መቅረት ህጋዊ እንዳልሆነ አያጡትም፡፡ከፓርላማው የሚያስቀራቸው ጉዳይ ሌላ ነው-የአዲስ አበባውን ወንበራቸውን የማጣት እብድ የሚያደርግ ቁጭት፡፡

ሕወሃት ተበድሏል?

ሳያስቡት ከአዲስ አበባ ተባረው መቀሌ የከተሙት አዛውንት የህወሃት ባለስልጣናት ቁጭታቸውን ተንፈስ ሚያደርግላቸው እጃቸው ላይ የቀረ ነገር ቢኖር ስልጣናቸውን ለቀማቸው አካል ባለመታዘዝ ንቀታቸውን ማሳየት፣የወንበር ነጣቂያቸውን ሰላም ከሚያደፈርስ ጋር ሁሉ ማህበር መጠጣት ነው፡፡ከኦነግ ጋር ማዕድ ያስቆረሳቸው ይሄው ነው፡፡ ኦነግ በበኩሉ በኦዴፓ በሚመራው አዲሱ የለውጥ አመራር ላይ ቅሬታ አለበት፡፡

የዳኦድ ኢብሳ ኦነግ ዛሬ በኦዴፓ የኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ ተደርገው የሾሙትን ጀነራል ከማል ገልቹን በኤርትራ በረሃ ደማቸውን ሊያፈስ አጥብቆ ይፈልጋቸው የነበረ ደመኛው ናቸው፡፡በዚህ ላይ ለውጡን የሚመራው ኦዴፓ “በታሪክ አማራ ኦሮሞን ሲበድል ኖሯል” የሚለውን የዳኦድን ኦነግ ፓርቲ ፕሮግራም የማዕዘን ድንጋይ አናግቶበት የሚያላዝንበት ሙሾ አሳጥቶታል፡፡በኦዴፓ አዲስ እይታ ሳቢያ የአማራ እና ኦሮሞ የጠላትነት ታሪክ ግርግዳ መፍረስ ምናልባትም ከኦነግ በላይ ህወሃትን እብድ በሚያደርግ የፖለቲካ ኪሳራ ላይ የጣለው ነው፡፡የአብይ/ለማ/ደመቀ/ገዱ ቡድን በህወሃት ላይ ያስመዘገበው አብረቅራቂ ስኬት ጅማሬም ፍፃሜም ይሄው ስልት ነው፡፡ይህ የለውጡ አመራር ስኬት ደግሞ የዳኦድን ኦነግ እና ህወሃትን እኩል ያከሰረ ስልት ስለሆነ ነው ሁለቱ ከሳሪዎች ግንባር መፍጠራቸው፡፡ በተመሳሳይ የጀነራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ መደረግ የዳኦድን ኦነግ እንዳናደደ ሁሉ የጀነራል አሳምነው ፅጌ የአማራ ክልል የፀጥታ እና ደህንነት ሃላፊ መሆን ደግሞ ህወሃትን ብግን የሚያደርግ የእግር እሳቷ ነው፡፡

ሌላው ህወሃት ተከፋሁበት የሚለው ነገር ሃገር ቆማ እንዳትሄድ አድርጎ ሲዘርፍ የኖረውን ሜቴክን ሲያጋፍሩ የኖሩት ጀነራል ክንፈ ዳኜው ሲያዙ በሃገሪቱ ቴሌቭዥን ቀጥታ መተላፉ፣እጃቸው ላይ ካቴና ገብቶ መታየቱ፣ሰውየው ይመሩት የነበረውን ሜቴክን ሁለንተናዊ ሌብነት የሚያሳይ ዲክመንተሪ ፊልም መሰራቱ ነው፡፡ክንፈ ዳኘው ሊያመልጡ ሲሉ የተያዙበት ሁኔታ ከቦታው በቀጥታ መተለላለፉም ሆነ ሰውየው ሲያዙ እጃቸው ውስጥ ካቴና መግባቱ ምንም ነውር ያለበት ነገር አይደለም፡፡ ይልቅስ ማንም ሰው ከህግ ስለማያመልጥ የፍርድቤት ጥሪ ሲደርሰው አክብሮ ህግን መጋፈጥ እንዳለበት፣ መሸሽ እንደማያዋጣ ትምህርት ይሰጣል፡፡የጀነራል ክንፈ ጉዳይ በፍርድ ቤት ተይዞ ሳለ ጉዳዩን አስመልክቶ ዶክመንተሪ ፊልም መስራቱ ይልቅ ጥፋት ነው፡፡ ኢህአዴግ ይህን አባዜውን ሊያቆም ይገባዋል፡፡

በተረፈ ተጠርጣሪ ወንጀለኛው እጅ ላይ ለምን ካቴና ገባ የሚለው ነገር ከህወሃት ሲመጣ የሚያስመሰክረው የህወሃትን ድልብ ዘረኝነት ነው፡፡ምክንያቱም ይህን ወንጀል አድርጎ የሚያወራው ህወሃት ራሱ ክስ ፈብርኮ በከሰሳቸው መናኝ መነኮሳት ሰላላ እጅ ውስጥ ካቴና አስገብቶ፣ እንደ በግ አቆራኝቶ አስሮ ሲያንገላታ የኖረ፣እነ ኡስታዝ አቡበክርን፣እነ አንዱአለም አራጌን፣እነ ዶ/ር መረራ ጉዲናን በካቴና ጠፍንጎ አስሮ በቴሌቭዥን ሲያሳይ የነበረ ግፈኛ መሆኑ ነው፡፡ አሁን የክንፈ ዳኘው ልዩ ሆኖ የታየው ክንፈ ዳኘው “ወርቅ ነው” እያለ ከሚያወራለት ዘር የተገኙ የወንዙ ሰው ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ህወሃት ይሄ እበልጣለሁ ባይነቱ ከዙፋኑ ባፍጢሙ እንደደፋው እስከ ዛሬ እንኳን አለመገንዘቡ ነው፡፡

ሌላው የህወሃት ትልቅ በደል እንደደረሰበት አድርጎ የሚያቀርበው ነገር ፓርቲው ሲያጋፍረው በኖረው የደህንነት መስሪያቤት አዛዥነት በሰው ልጆች ላይ ሲደረግ የኖረው አረመኔያዊ የሰብዐዊ መብት ጥሰት በሃገሪቱ ቴሌቭዥን መጋለጡ፣ ሲጋለጥ ደግሞ ተጎጅዎቹ “የገረፉን ትግርኛ የሚናገሩ ሰዎች ናቸው” ማለታቸውን ነው፡፡ይህን የሚለው ህወሃት ሃገሪቱን በሚዘውርበት ዘመን የህወሃቱ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ተገኝተው የካቢኔ ሹመት ሲያፀድቁ ከእጩዎቹ ስም ቀጥለው የሚጠሩት ዘራቸውን እንደነበር ማንም አያጣውም፡፡ህወሃት ባዋቀራት ኢትዮጵያ ለመሾም ለመሻር፣ለመግረፍ ለመገረፍ፣ነግዶ ለማትረፍ ለመክሰር፣ለመውጣት ለመግባት ሁሉ ዘር ሳይጠራ አይሆንም፡፡ ስዚህ የገራፊ ዘር ሲጠራ ሰማይ እና ምድር ቦታ የተቀያየሩ ማስመሰሉ ቅን ነገር አይደለም፡፡ የገራፊ እና የተገራፊ ድልድል ለማድረግ ዘር መስፈርት መሆኑም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ገራፊ ለመሆን ወንበር ላይ የተቀመጠውን ባለጊዜ የልብ የሚያደርስ ዘር ባይፈለግ ኖሮ ገራፊው እና አሳሪው ሁሉ ከአንድ ዘር በልሆነ ነበር፡፡በአጠቃላይ ዘር ሳይጠራ ምንም የማይደረግበት ሃገር በራስ እጅ ካበጃጁ በኋላ ለምን የገራፊ ዘር ተጠረራ ብሎ ተበደልኩ ማለት ትርጉም የለውም፡፡

የአማራ ክልል እና የራያ ወጣቶች ወደ ትግራይ የሚሄደውን መንገድ ሲዘጉብን የዶ/ር አብይ መንግስት ዝም ማለቱም አስከፍቶናል ባዮች ናቸው ህወሃታዊያኑ፡፡መንገድ መዘጋቱን ብቻ ሳይሆን ለምን ተዘጋ ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡የራያ ህዝብ መንገድ የዘጋው ማንነቴ ትግሬ አይደለም በማለቱ ሳቢያ የትግራይ ልዩ ሃይል በጥይት ስለቆላው ነው፡፡በአማራ ክልል በኩል ያለውን መንገድም እንዲሁ የአማራ ህዝብ በህወሃት ተዘቅዝቆ ሲገረፍ የኖረ በመሆኑ በመሰለው መንገድ ቅሬታውን ማሳየቱ ነው፡፡

በፌሮ ሲገረፍ የኖረ፣በማንነት ጥያቄው ላይ ሲሾፍበት የኖረ ህዝብ ለተወሰነ ቀን መንገድ መዝጋቱ እሪ ሊያስብል አይገባም፡፡ የሚያዋጣው ስህተትን አምኖ ለበደል ይቅርታ መጠየቅ እንጅ ስገርፍ የኖርኩት ህዝብ ዘንባባ ያንጥፍልኝ የሚል ትዕቢት አይደለም፡፡ በዚህ ላይ የቆየውን ያህል ቆይቶም መንገዱን ያስከፈተው የዶ/ር አብይ መንግስት መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ የዶ/ር አብይ መንግስትም ቢሆን ህዝብ ቅሬታውን ማቅረብ ያለበት መንገድ በመዝጋት እንዳልሆነ ህዝብን ቀርቦ እስኪያስረዳ ቀናት እንደሚያልፉ መገንዘብ ከባድ ነገር አይደለም፡፡አብይ መንገዱ የተዘጋ የዕለቱ ዕለት ከዙፋኑ ወርዶ ሲገሰግስ አድሮ ለምን በማግስቱ አላስከፈተልንም የሚለውም እበልጣለሁ ባይነትን የተሸከመ ትዕቢት ያለበት ክርክር ስሆነ የሚያስኬድ ነገር አይደለም፡፡

ከሁሉም በላይ ህወሃት መንገድ ተዘጋብኝ ብሎ በሚጮህበት ወቅት ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ እሪ የማይሉ ግን ለወራት መንገድ ተዘግቶባቸው ያሉ ወገኖች ነበሩ፤ወለጋ ላይ በጥይት የሚቆሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ወቅቱ የሽግግር እንደመሆኑ፣ህወሃት ደግሞ ደህና በመስራት የማይታወቅ ፓርቲ እንደመሆኑ ጥፋቱን አምኖ ይቅርታ ባልጠየቀበት ሁኔታም ሁልቀን ፋሲካ መጠበቅ የለበትም፡፡ህወሃት ራሱ በሰጣት የቤት ስራ ምክንያት እየታመሰች ባለች ሃገር ለምን የኔሰፈር ብቻውን በቸር ውሎ አላደረም ማለት፣ይህንንም አምርሮ ማራገብ ክፉ ራስ ወዳድነት ነው፡፡

በሙስና እና በሰብዐዊ መብት ጥሰት የተጠየቁ አመራሮች ሁሉ ህወሃቶች ብቻ ናቸው፤ይህ የሆነው ደግሞ የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ነው የሚለው ሌላው ህወሃቶች ተለይተን ተጠቃን የሚሉበት ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነገር የመጀመሪያው ክርክር በወንጀል መጥሪያ የተቆረጠባቸው ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ህወሃቶች ብቻ አይደሉም፡፡ህወሃቶች ብቻ የሆኑት የፍርድቤት መጥሪያ ተቆርጦባቸው ሳለ ለህግ አንታዘዝም ብለው በትውልድ ቦታቸው የከተሙት ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ናቸው፡፡ ለተጠርጣሪ ወንጀለኛ የወንዙ ልጆች ዘር ቆጥሮ መጠለያ እየሰጠ ያለውም የትግራይ ክልላዊ መንግት ብቻ ነው፡፡ እነ ያሬድ ዘሪሁን፣ተስፋየ ኡርጊ፣ጠና ቁርንዲ ወዘተ ትግሬዎች ያልሆኑ፣የክልላቸው መንግስትም ዘር ቆጥሮ ያልደበቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ በተረፈ ወደፊትም በተጠያቂነቱ ዝርዝር የህወሃት ሰዎች በርከት ብለው ሊታዩ ይችላሉ፡፡ይህ ህወሃት ከመባረሩ በፊት መስርቶት የነበረው ስርዓት የወንዝ ልጆች ተጠራርተው፣ፍትሃዊ ባልሆነ ሁኔታ የሃገሪቱን ሁለመና የመዘወራቸው ነፀብራቅ እንጅ እንደሚያወሩት ትግራይን የማጥቃት ሃራራ ያለበት መንግስት ስለመጣ አይደለም፡፡ የሃገራችን መንግስት ህወሃትን የማንበርከክ ጥማት አለው ቢባል እንኳን ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ጌታቸው አሰፋን የምትፈልገው ትግራይ ተንበርክካ ለማየት ካላት ክፉ ምኞት ሊሆን አይችልም፡፡ ማገናዘብ ደግ ነው!

ህወሃት እንዴት አደብ ይግዛ?

ወንጀለኛ ሰብስቦ የያዘው፣የፌደራሉን መንግስቱን በግልፅ ሃገር ማስተዳደር የማይችል ነው የሚለው የትግራይ ክልልን የሚመራው የህወሃት አዛውንቶች ስብስብ በሃገር ላይ ሌላ ሃገር መስርቶ የመኖሩ ነገር ሊያበቃ ይገባል፤በክልሉ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም ከህግ በላይ አለመሆናቸው ግልፅ ሊሆን ይገባል፡፡ካልሆነ ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ለውጥ ውስጥ ነኝ ብላ መናገር አትችልም፡፡ትዕግስት የህግ የበላይነትን ተፈታትኖ፣አለቃ እና ምንዝር የማይታወቅበት ስድ ፖለቲካ እስኪያመጣ ድረስ ልቅ መሆን የለበትም፡፡

የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ስር እንደመሆኑ መጠን በክልሉ ያሉ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን እንዲሰጥ መለመን ሳይሆን መታዘዝ ነው ያለበት፡፡ለወራት ወንጀለኛን ደብቆ ያስቀመጠው የትግራይ ክልል መንግስት ውንጀል ሰርቷልና ከደበቃቸው ወንጀለኞች እኩል መጠየቅ አለበት፡፡ ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማይደግሙት የክልሉ ፕሬዚደንት ዶ/ር ደብረፅዮን በተለይ በግምባር ቀደምነት መጠየቅ አለባቸው፡፡ይህን ለማድረግ እንደ መንግስትም እንደፓርቲም እርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል፡፡

እንደ መንግስት የትግራይ ክልል መንግስት ተጠርጣሪ ወንጀለኞቹን ለፌደራሉ መንግስት የሚያስረክቡበት የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ በጊዜ ገደቡ የማያቀርቡ ከሆነ በሚኒስትሮች ምክርቤት አስወስኖ የዶ/ር ደብረፀዮንን ያለመከሰስ መብት ለማንሳት በፓርላማ ማስወሰን፡፡ወንጀለኛ የደበቀ ወንጀለኛ ነውና ደብረፅዮንም ከተፈላጊ ወንጀለኖች ዝርዝር ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ክልሉ ደግሞ በታዳኝ ወንጀለኛ መመራት ስለሌለበት የፌደራል መንግስቱ በደብረፅዮን ለሚመራው የክልሉ መንግስት እውቅና መንፈግ አለበት፡፡እንደ መንግስት ይህን ካደረጉ በኋላ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ተሰብስቦ ህገ-ደንቡን በተከተለ ሁኔታ በህወሃት ላይ ቅጣት መጣል አለበት፡፡ይህ ሁሉ ሆኖ ካልሆነ መንግስት ለክልሉ የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ እስከ ማቆም የሚሄድ እርምጃ ሊወስድ ይችላል፡፡
_____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ሃገራችን “ምርጫ አሁኑኑ” የሚባልባት ነች? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ጥር 1 2011 ዓ ም

ሃገራችን ለፖለቲካ ህመመሟ ፈውስ በምታገኝበት ወይም ጨርሳ የአልጋ ቁራኛ በምትሆንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ዋነኛ ህመሟ የዘር ፖለቲካ አመጣሽ ደዌ ነው፡፡የዘር ፖለቲካ በደም ሥሯ ገብቶ መላ አካሏን የሚያናውጣት ይህች ደሃ ሃገር ሲባል የሰማችው እንዳይቀባት ስታደርግ የኖረችው ሃገራዊ ምርጫም ቀነቀጠሮው ደርሷል፡፡ እንደ ፅዋ ማኅበር ወራቱን ጠብቆ ምርጫ ማድረግ እና ተመልሶ በዘር ፖለቲካ ኋላ ቀር ዘይቤ መመላለስ ከዲሞክራሲዊ ምርጫ ትርጉም ጋር የማይዛመድ ልማዳችን ነው፡፡ይህ ልማዳችን የፖለቲካችንን ጉልበት ለዝለት ዳርጎ እንዳንራመድ ሲያንፏቅቀን የኖረ ክፉ ቁራኛችን ሆኖ አለ፡፡

ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ነው ቢባልም ሁሉም ምርጫ የዲሞክራሲ እምብርት ሊሆን አይችልም፡፡ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጋር የሚዛመደው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ ነው፡፡ እንደ ሰንበቴ ወር እየጠቁ ምርጫ ማድረግ ለሃገር ዲሞክራሲን አያመጣም፡፡ በአፍሪካ አህጉር የሚደረጉ እንደ ትጥቅ ትግልም የሚሞክራቸው ምርጫዎች ለአምባገነኖች የተመርጫለሁ ሽንገላ ይረዱ ይሆናል እንጅ ለሃገር እና ለህዝብ ዲሞክራሲን ሊያመጡ አይችሉም፡፡

ሃገራችንን ጨምሮ ከምርጫ ማግስት ደም መፋሰስን እና በፍርድ ቤት መካሰስን አስከትሎ የሚመጣው የአፍሪካ ሃገራት ምርጫ ለህዝብ ጭንቅን እንጅ ደስታን ይዞ አይመጣም፡፡በቅርቡ በኬንያ የተደረገው(የምርጫ ኮሚሽነሩን መሰዋት ያደረገው) ምርጫ ሲቃረብ የሃገሪቱ ህዝብ ምርጫው በሰላም እንዲያልፍ በየእምነት ተቋሙ ሱባኤ መግባት ጀምሮ ነበር፡፡ጎረቤት ሩዋንዳ፣ብሩንዲ፣ዩጋንዳ በተመራጭ አምባገነኖች የሚንገላቱ፣ የእኛ ቢጤ “የምርጫ ሰለቦች” ናቸው፡፡

በሃገራችን የተደረጉ ምርጫዎች ታሪካዊ ዳራ ቢጠና የህወሃትን በተለይ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊን ጉልበት ከቀን ቀን እያበረቱ በስተመጨረሻው ወደ ተሟላ ተመራጭ አምባገነንነት ያደረሱ ሃዲዶች ናቸው፡፡በኢህአዴግ ስር የተደረጉ ምርጫዎች የእድገት ጫፍ በፓርላማው መቀመጫ ሁሉ የአንድ ፓርቲን ካድሬዎችን መኮልኮል ነው፡፡ተገዳዳሪ ለማይወደው ኢህአዴግ ይህ ብቻ ድል ሆኖ አሳርፎ አያስቀምጥም፡፡ይልቅስ የድሉ ማህተም ከፓርላማ ወንበር ርቀው በቆሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጓዳ ገብቶ ህብረታቸውን ማፈራረስ፣ስማቸውን ከህይወት መዝገብ መሰረዝ ነው፡፡

ይህን ካደረጉ በኋላ ደግሞ ተቃዋሚ ጠፋ እንዳይባል ነፍስ ያላቸውን ተቃዋሚዎች ለማፍረስ የተጠቀመባቸውን የፖለቲካ ወንጀለኞች ተቃዋሚ ብሎ ደሞዝ ሳይቀር እየከፈለ የፈለገውን ያናግራቸው ነበር፡፡የሚወደውን ወንበሩን ለመጠበቅ የራሱን ተቃዋሚ ፈጥሮ ደሞዝ መክፈል ድረስ ርቆ ወደታች የሚምዘገዘገው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ጠላት ከሩቅ ሲጠብቅ አቤት ወዴት ሲያስብላቸው የኖሩ የራሱ ሎሌዎች ባላሰበው መንገድ ገፍተር አድረጉት፡፡ የገዛ አቤት ባዮቹ በፅኑ ፍቅር የጣለውን ወንበሩን ሲይዙ ራሱን አግዝፎ የሚያየው ህወሃት ዕብድ የሚያደርገውን ንዴቱን ብቻ ይዞ ቀረ፡፡

ህወሃት ቀርቶ እኛም ባላመንነው መንገድ የፖለቲካችን/የኢኮኖሚያችን መዥገር የሆነው የህወሃት አገዛዝ ቢወገድም ዲሞክራሲን አርቆ ለመቅበር ሳይታክት ሲሰራው የኖረው ስራው ግን ለሃገራችን ዲሞክራሲ ትልቅ ፈተና ደቅኗል፡፡ህወሃት ዘረፋውን ለሚጋርድለት ስልጣኑ ሲል ያጠፋው ጥፋት የትየለሌ ቢሆንም በሃገራችን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ባህል ስር እንዳይይዝ ያደረገው ድርጊት ይቅር ለማለት አስቸጋሪው ጥፋቱ ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በመሰረታዊነት የሃሳብ ውድድር ነው፡፡የሃሳብ ውድድሩ መሰረት የሚያደርገው ተወዳዳሪዎቹ የሚያመጡት የፖሊሲ ሃሳብ እንጅ የሚናጉትን ቋንቋ አይደለም፡፡ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ሃሳብ የሰማው ህዝብ በምርጫ ካርዱ ለሚቀጥሉት አራት ወይም አምስት ዓመት ማን ፖሊሲ ያውጣልኝ የሚለውን ይወስናል፡፡ ህዝብ የተገዳዳሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ ለመስማት፣ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የፖሊሲ ብልጫቸውን ለህዝብ ለማቅረብ ህዝብ እና ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ያለገደብ መገናኘት አለባቸ፡፡የውድድሩ ሜዳ ለማንም ያላዳላ ፍትሃዊ መሆን አለበት፡፡እድሜው ለመምረጥ መመረጥ የደረሰ ሰው ሁሉ መምረጥም መመረጥም መቻል አለበት፡፡ህዝቡም ሆነ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድን ጨምሮ በምርጫው አስፈፃሚዎች ላይ እምነት መጣል አለበት፡፡ይህ በስተመጨረሻም በሃገሪቱ ባሉ የፖለቲካ ሃይሎች ዘንድም ሆነ በህዝቡ ዘንድ የምርጫ ውጤቱን አምኖ ለመቀበል ያስችላል፡፡

ወቅታዊ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንቅፋቶች

አሁን ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ ከላይ የተቀመጠውን የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መሰረታዊ ይዘት ባሟላ ሁኔታ ማድረግ የሚያስችል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ምርጫው ጊዜውን ጠብቆ ይደረግ አይደረግ ከመባሉ ቀደም ብሎ መነሳት ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በግሌ ምርጫውን በታቀደለት ጊዜ ማድረግ የማይቻል ብቻ ሳይሆን አደገኛ መስሎም ይሰማኛል፡፡ምርጫውን በቀጠሮው ለማድረግ የማያስችሉትን ምክንያቶች በሶስት መክፈል ይቻላል፡፡

1. ህወሃት/ኢህአዴግ ሰራሽ እንቅፋቶች

የመጀመሪያው እና መሰረታዊው ችግር ከፍ ብሎ የተጠቀሰው ህወሃት ለስልጣኑ እና ዘረፋው ሲል ተገዳዳሪን ድምጥማጥ ለማጥፋት ያደረገው (ደደቢት ላይ ካደረገው ያላነሰ) ተጋድሎ ነው፡፡በዚህ እጅግ አሳዛኝ ስራው አንድነትን የመሰለ ጠንካራ ፓርቲ አጥፍቷል፡፡ በትንግርት የተረፈው ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን መሪዎቹን ለእስርቤት ገብሮ በመኖር እና ባለመኖር መሃል ብቅ ጥልቅ ሲል የኖረ ነው፡፡መኢአድም ገና ከጠዋቱ ያለ ርህራሄ በህወሃት ሰደፍ ሲደቆስ ፣ሰላማዊ ተቃዋሚ ሆኖ ሳለ እንደ ታጣዊ ቡድን በእጅጉ ሲታደን የኖረ፣እስከዛሬ መኖሩም የሚገርመኝ ፓርቲ ነው፡፡ኢዴፓም ቢሆን በተመሳሳይ እንግልት የኖረ ከመሆኑም ባሻገር በቅርቡ ቤቱን ከማጥራቱ በፊት ከአንዳንድ መሪዎቹ ሁኔታ አንፃር ከህወሃት ጋር ያለው ግንኑነት በህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነበር፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲህ ባለ የህወሃት/ኢህአዴግ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሰፈር ጉልበተኛ አይነት ስራ በከፍተኛ መገለል እና የመጥፋት አደጋ ውስጥ በኖሩበት ዘመን አሁን እንደ ፓርቲ ይወዳደር የሚባለው ኢህአዴግ ደግሞ በፖለቲካው መስክ ሃገር ምድሩን በግድም በውድም አባል አድርጎ ኖሯል፡፡በኢኮኖሚው መስክ ፓርቲ መሆኑ ሳያግደው ሲነግድ ኖሯል፡፡ብቻውን ተቆጣጥሮ ልማታዊነቱን ሲነዛበት የኖረው የህዝብ ሚዲያ አሁንም በእጁ ነው፡፡በንፃሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ሊያነቁበት፣ከህዝብ ጋር ሊገናኙበት የሚችሉት የግሉ ሚዲያ በህወሃት/ኢህአዴግ ሰደፍ ተገዶ ተዘግቶ ኖሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በአመዛኙ ህዝብ ታግሎ ያመጣው ለውጥ ወሮታ በተለምዶ የለማ/ገዱ ቡድን ለሚባለው ለኢህአዴግ ፓርቲ አፈንጋጮች እየተሰጠ ነው፡፡ይህ የቅድመ ለውጥ ምክንያት በድህረ ለውጥ ከተባባሰው የዘር ፖለቲካው ጋር ሲደመር ወደ ሁለተኛው የምርጫ እንቅፋት ያደርሰናል ፡፡

2. ከለውጡ ጋር የሚዛመዱ እንቅፋቶች

ህወሃት/ኢህአዴግ ተደላድሎ ተቀምጦ ሃገርን አሳር መከራ ሲያሳይ የኖረበትን አገዛዝ ያስወገደው ህዝባዊ ትግል ተስፋንም ስጋትንም ያዘለ ድባብ አለው፡፡ተስፋው አዲሱ የለውጥ አመራር ሃገሪቱን ሊያጠፋት ደርሶ የነበረውን መከፋፈል በማጠየቅ የጋራ ሃገርን ለመገንባት የሚያደርገው ጉዞ ሊያደርሰን የሚችለው ሃገራዊ ብልጽግና ሲሆን ስጋቱ ደግሞ ይህን ጉዞ ሊያደናቅፍ የሚችለው የዘር ፖለቲካ ወለድ መተላለቅ ነው፡፡ ለውጡ ብዙ ጥሩ ብስራቶች ቢኖሩትም እጅግ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ መርገሞችንም ያመጣ፣ ወደፊትም የባሰውን ሊያመጣ የሚያስችል አዝማሚያ ያለው ነው፡፡

ይህ አስፈሪ የዘር ፖለቲካ ተዘርቶ የበቀለው እና እንዲህ ለውድመት ብቁ የሆነው ለውጡ በቆየበት የስምንት ወር እድሜ አይደለም፡፡ዘረኝነት በእንክብካቤ አድጎ ያሸተው ህወሃት/ኢህአዴግ በኖረበት ረዥም ዘመን ነው፡፡ህወሃት አስሮ ያሳደገው ዘረኝነት የሚባል አውሬ ጎልምሶ፣ ከጎሬው ወጥቶ አሳዳጊውን ቦጫጭቆ መግደሉ ደግ ቢሆንም ህወሃትን አጠፋሁ ብሎ ዝም ብሎ የማይተኛ መሆኑ ነው ጭንቁ፡፡ህወሃትም ቢሆን ራሱ ተንከባክቦ ያሳደገው ዘረኝነት ራሱንም እንዳጠፋው ቢያውቅም ከእርሱ መጥፋት በኋላ ሃገሪቱ በዘረኝነት ጦስ ስትታመስ እሱ ስለሌለ የመጣ ችግር እንጅ እሱ ያልፈጠረው ችግር አድርጎ ለማውራት አይሰንፍም፡፡ይህን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ በስልጣኑ ወራት ዘቅዝቆ ሲገርፋቸው ከነበሩ አክራሪ የዘር ድርጅቶች ጋር እየተገናኘ የሃገርን ጣር ለማብዛት እንደሚሰራ የታወቀ ነው፡፡

ህወሃት እና የቀድሞ ጠላቶቹ የአሁን ወዳጆቹ አክራሪ የዘር ፖለቲከኞች ገንዘብ ጠመንጃቸውን አዋህደው በስልጣን ላይ ያለውን ቡድን እያስጨነቁ፣ሃገር ወደ ገሃነም በር የምትደርስበትን መንገድ እየተለሙ ይገኛሉ፡፡ከዚህ ስራቸው አንዱ የሃገሪቱ ምርጫ በተያዘለት ፕሮግራም ይደረግ የሚለው ህጋዊ መሰል ጥያቄያቸው ነው፡፡ይህን ጥያቄ በዋናነት የሚያቀነቅኑት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፓርቲዎች ሲሆኑ ህወሃትም እንደሚፈልገው ጥናት አቀርባለሁ ብለው መቀሌ የነጎዱት አቶ በረከት ጠቆም አድርገዋል፡፡ምርጫው በሰዓቱ ይደረግ የሚሉት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ መሪዎች አክራሪዎቹ ብቻ አይደሉም፡፡ ይልቅስ መሃል መንገድን እንደሚሹ አጥብቀው ሲናገሩ የኖሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሳይቀሩ “ምርጫው ነገ ቢደረግ እኛ ደስታችነ ነው” ሲሉ ስሙን በማላስታውሰው ቴሌቭዥን ቀርበው ሲያወሩ ሰምቻለሁ፡፡

የዘር ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ምርጫው በሰዓቱ እንዲደረግ የሚፈልጉበት ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ከድሮ እስከ ዘንድሮ ሲመረጡ የኖሩት እትብታቸው በተቀበረበት መንደር እየሄዱ ነው፡፡ዕትብታቸው በተቀበረበት መንደር እስከሄዱ ድረስ እንደሚመረጡ እርግጠኛ ናቸው፡፡ በዚህ መሃል ይህን ጉዳይ በተመለከተ ዶ/ር መረራ በአንድ ወቅት ከኢሳቱ አቶ ግዛው ለገሰ እና ሟቹ አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ጋር ባደረጉት ቆይታ “ግፈቃደ አንተም አምቦ የተወለድክ(ያደግክ?) ቢሆንም አሁን አንተ እና እኔ ለምርጫ ልንወዳደር አምቦ ብንሄድ የምመረጠው እኔ እንደሆንኩ ጥርጥር የለኝም” ብለው ነበር፡፡

ከዚህ የምንረዳው በሰፈሩ የምርጫ ጣቢያ ብቻ ለመመረጥ የተሰየመ የዘር ፖለቲከኛ በምርጫ ለማሸነፍ የሚሰራው አንዳች ነገር የለም፡፡ አሸናፊነቱን የሚያፀናው ስራ ተሰርቶ ያለቀው በተፈጥሮ አደራጅነት፣ ከዛች መንደር፣ የዛን አካባቢ ቋንቋ ከምትናገር እናት የተወለደ ቀን ነው፡፡ እንዲህ ባለው በተፈጥሮ አጋፋሪነት በሚያልቅ መምረጥ መመረጥ ውስጥ የሃሳብ ውድድርን ገበያ አንደኛ የሚያደርገው የዘመናዊ ዲሞክራሲ ምርጫ እጣ ፋንታ የለውም፡፡ ምርጫ ይኖራል ዲሞክራሲያዊ ግን አይደለም፡፡ምርጫው የሚኖረውም እዛው ሰፈር እትብቱ የተቀበረ ሌላ ተገዳዳሪ ከመጣ ነው እንደጂ የሌላ ሰፈር ሰው ድርሽ እንዳይል የእትብት መማዘዙ ፖለቲካ ያግዳል፡፡እንዲህ ባለው ውድድር ለማሸነፍ ደግሞ ክርክሩ የእናት የአባት የዘር ንጥረት ይሆን ይሆናል እንጅ የሃሳብ ሙግት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ውስጥ ዲሞክራሲን መፈለግ ላምም ሳርም በሌለበት ኩበት መልቀም ነው!

በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ ተፈጥሮን ሳይሆን ተመክሮን እና ሃሳብን መሰረት ስለሚያደርግ ትልልቅ ስራዎች የጠብቁታልና ምርጫ ነገ ይሁን ለማለት አይደፍርም፡፡አንደኛው ትልቅ ፈተና የዘር ፖለቲካ አለቅጥ እጅ እግሩን ዘርግቶ ተንሰራፍቶ በኖረበት ሃገር የፖሊሲ ሃሳብን ይዞ የወንዙ ልጆች ባልሆኑ ሰዎች ፊት መቅረቡ ነው፡፡ የሰፈሩን ሰው ብቻ እንዲያምን ሲነገረው የኖረ ህዝብ የሌላ ሃሳብ መስማት ቀርቶ በሰፈሩ መርገጡ ራሱ ሊያስቆጣው እንደሚችል አዝማሚያዎች እያየን ነው፡፡እድል ቀንቶት፣ሃሳብ የሚሰሙ ዜጎች አግኝቶ፣በፖሊሲው መስህብ ማርኮ የመመረጥ እድል ቢያገኝ እንኳን የምርጫውን ውጤት የሚቀበለው ሰው ምን ያህሉ ነው የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው፡፡

3. ህገ-መንግስት ወለድ እንቅፋቶች

በሃሳብ የበላይነት ላይ የሚቆመው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተፈጥሮን አጋፋሪነት ብቻ ተማምኖ ከሚቀመጠው የዘር ፖለቲካ ምርጫ ጋር ዝምድና የለውም፡፡አሁን ሃገራችን የምትመራበት ህገ-መንግስት ደግሞ የዘር ፖለቲካን በህግ ያነበረ፤ የአዋቂዎች አካታች የመምረጥ መመረጥ (Adult Universal Suffrage)መብትን በተዘዋዋሪ የሚነፍግ ነው ፡፡ ይህ ህገ-መንግስት ዘር ቆጥሮ በከለለው ክልል ሰባት ጉልበቱ ያልተወለደ ሰው መራጭ ይሆናል እንጅ የመመረጥ መብት የለውም፡፡ ጭራሽ እሱ መጤ/ሰፋሪ/ወራሪ እየተባለ በሚኖርበት መሬት በወቅቱ የማይኖሩ ግን ከሃምሳ ስልሳ አመት በፊት እዛ ሃገር እንደ ተወለዱ የሚታመንባቸው፣ሰባት ጉልበታቸው ተቆጥሮ ሃገሬነታቸው የተረጋገጠ ሰዎች ተመራጭ ሆነው ይመጣሉ፡፡በዚህ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ምርጫ መስፈርት የሆነው በአካባቢው ከሁለት አመት በላይ መኖር እና እድሜ ለመመረጥ መድረስ ዋጋ የላቸውም፡፡

እንዲህ ያለው ህገ-መንግስት አንድ ዓረፍተ-ነገሩ ሳይነካ፣የምርጫው ቀን አንድ ሰኮንድ ሳያልፍ ምርጫው ይደረግ የሚሉ የዘር ፖለቲካ መሪዎች ፍላጎት የሃሳብ ዘመን ሳይመጣ ፣በግርግር ስልጣን ላይ መቀመጥ እና በጥፋቱ ብዛት እየተጠላ ያለውን፣የህልውናቸው መሰረት የሆነውን የዘር ፖለቲካ ከመጥፋት ታድጎ ማስቀጠል ይመስላል፡፡የዘር ፖለቲካ የሚመቸው ዘራቸውን ጠርተው ብቻ ያለ ልፋት ስልጣን ላይ ለሚቆናጠጡ ልሂቃን እና ቅዝምዝምን ዝቅ ብለው የሚያሳልፉበት ትርፍ ሃገር ላላቸው አክቲቪስቶች ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ግላዊ ጥቅማቸውን እና ዝናቸውን ለለማጣት ሲሉ ብቻ የዘር ፖለቲካ ወለዱ የዘር ፌደራሊዝም እጅግ ድንቅ እንደሆነ ቢሰብኩም በተግባር የሚታየው ተቃራኒው ነው፡፡

ከሁለት አመት በፊት በዘር ፖለቲካው ምክንያት የሚሞተው የሚፈናቀለው አማራው ብቻ ነበር፡፡አማራው ደግሞ ለመጨቆን በሃገሪቱ ዳርቻ የተበተነ የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ጠላት ተደርጎ ይወሰድ ስለነበረ ዘርን መሰረት ያደረገው ፖለቲካ ችግር ፈጣሪ ተደርጎ ሳይታይ፣ጭራሽ አማራውን የቀጣ ጥሩ ለበቅ ተደርጎ ሲወሰድ ኖሯል፡፡ሆኖም ዘመኑ ሲደርስ ኦሮሞው፣ጌዲኦው፣ሱማሌው፣አማሮው፣ጋሞው፣ወላይታው፣ጉራጌው፣ከንባታው፣ማረቆው፣መስቃኑ፣ቀቤናው ሁሉ የችግሩ ሰለባ ሲሆን የዘር ፖለቲካው አዋጭ እንዳልሆነ በተግባር እየታየ ነው፡፡በዚህ ምክንያት የዘር ፖለቲካው ችግር ወስጥ እንዳለ የዘር ፖለቲካ መሪዎች አጢነዋል፡፡በአኖሌ ሃውልት ዙሪያ ሲሰበሰብ ነበረው የአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ “ኢትዮጵያ ቅደሚ” ማለቱ በዘር ፖለቲካው ላይ ለመምሸቱ አይነተኛ ምልክትም፣ከባድ ስጋትም ሆኖ ሳይቆጠር አልቀረም-በዘር ፖለቲከኞች ዘንድ፡፡

አብልቶ አልብሶ የሚያኖራቸውን የዘር ፖለቲካ ክፉ የማይወዱ የፖለቲካው ልሂቃን ታዲያ የህልውናቸውን ዋስትና ለመታደግ በመራወጥ ላይ ይገኛሉ፡፡ምርጫ ሳይውል ሳያድር ይደረግ የሚሉት መዋል ማደር ከመጣ የሃሳብ እና የምክንያታዊነት ፖለቲካ መድረኩን ሊረከብ ይችላል፤ይህ ደግሞ ተከታይ ያሳጣናል ከሚል ስጋት ነው ምርጫ አሁኑኑ እተባለ ያለው፡፡ በአንፃሩ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ ፓርቲዎች ህብረት እየፈጠሩ መሄዳቸው፣ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ከማዘንበሉ ጋር ሲደመር የጎሳ ፖለቲከኞችን ጭንቅ ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡”ምርጫው አሁኑኑ ይደረግ፣የሽግግር መንግስት የሚል ድምፅ እንዳንሰማ” ባሉበት አፋቸው ድንገት ብድግ ብለው “እንደውም ብሄራዊ የአንድነት እና የሽግግር መንግስት ይመስረትልን” እያሉ ያሉት ልብስ ጉርሳቸው የዘር ፖለቲካ ሊወድቅ ዘመም ዘመም ያለ ቢመስላቸው ነው፡፡
__
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ያለሽግግር መንግስት ሃገር ማሻገር (ለቪዥን ኢትዮጵያ የቀረበ) – በመስከረም

በመስከረም አበራ
ለቪዥን ኢትዮጵያ የቀረበ ታህሣስ 18-19 , 2011 ዓ.ም.

የጥናቱ ጨመቅ(Abstract)

ሃገራችን አሁን የምትገኝበት ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን የሚከለክል ስላልሆነ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሳያስፈልግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል የሽግግር ስራ መስራት ይቻላል፡፡ ይህን ሽግግር ለማድረግ ሃገሪቱ ለረዥም ዘመን ዲሞክራሲን እንዳታሰፍን ያደረጉ ችግሮችን በሽግግሩ ወቅት አቃሎ በምርጫ ለሚመጣው መንግስት ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚመች ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ፅሁፍ አላማ እነዚህን ችግሮች ለይቶ የሚፈቱበትን መንገድ መጠቆም ነው፡፡ ይህን ለማድረግ የተለያዩ መፅሃፍት፣ጥናታዊ ፅሁፎች እና ተመሳሳይ ለውጥ ያደረጉ የአለም ሃገራት ልምድ ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የፅሁፉ አቅራቢ እይታዎች ግብዓት ተደርገዋል፡፡ ከተዳሰሱ መዛግብት በተገኙ መረጃዎች መሰረት ሃገራችን ዲሞክራሲን እንዳታሳድግ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያላቸው እንደ የዘውግ ፖለቲካ/ፌደራሊዝም፣የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ፣ፓርላመንታዊ የመንግስ ስርዓት እና ኢህአዴግ የመሰረተው የፓርቲ ፖለቲካ ዘይቤ ዋነኞቹ ናቸው፡፡እነዚህ ችግሮች በታሪክ እየተጠራቀሙ የመጡ በመሆናቸው በሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በተሳተፉበት ሰፊ ስራ እና በህዝብ ውይይት በሽግግሩ ወቅት መፈታት አለባቸው፡፡ ችግሮቹ በሽግግሩ ወቅት ሳይፈቱ በምርጫ ወደ ሚመረጠው መንግት ከተላለፉ የሚመረጠውን መንግስትም ሆነ የሃገሪቱን ህልውና አደጋላይ ሊጥሉ ይችላሉ፡፡በተቃራኒው ታሪካዊ ችግሯን የፈታች(ያቃለለች) ሃገር ለተመራጩ መንግስት ማስተላለፍ ከተቻለ ተመራጩ መንግስት ታሪካዊ ችግሮችን የመፍታት አስቸጋሪ ስራ ውስጥ ሳይገባ ሃገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ መስመር የሚያስገቡ ስራዎችን ወደ መስራቱ እንዲገባ ይረዳዋል፡፡ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ታሪካዊ ችግሮችን መርምሮ፣የእልባት መንገድ አፈላልጎ፣ሽግግሩን/ለውጡን የሚያፀኑ ስራዎችን በመስራት ሃገር የሚያሻግር፣ ይህን ለማድረግ በቂ ስልጣን የተሰጠው ተቋም መዋቀር አለበት፡፡

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ነገረ-ወልቃይት – ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

ByAdmi

(በመስከረም አበራ)
ኅዳር 21 ፤ 2018 ዓ.ም.

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

የሃገራችን የፖለቲካ ችግር መሰረቱ የብሄረሰቦች ጭቆና እንደሆነ የሚያምነው ኢህአዴግ ለዚህ መፍትሄ ብሎ ያቀረበው ሃገሪቱን በዘውግ ፌደራሊዝም ከፍሎ ማስተዳደርን ነው፡፡እስከ መገንጠል የደረሰ የብሄረሰቦች መብት የሰጠው ህገ-መንግስት የዘውግ ፌደራሊዝምን ምርጫው አድርጓል፡፡ይህ የሆነው የሃገሪቱን ብሄረሰቦች ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል ስለሆነ ለሃገሪቱ ህልውና ሁነኛ መፍትሄ ነው በሚል እሳቤ ነው፡፡ ሆኖም ውጤቱ እንደ ታሰበው ሃገር ያረጋጋ፣በዘውጎች መካከል የታሰበውን ያህል ሰላም ያመጣ አይደለም፡፡ምናልባትም ውጤቱ በተቃራኒው ሳይሆን አይቀርም፡፡በሃገራችን ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት፣መፈናቀል፣ዘር ማጥፋት፣ደም መፋሰስን ያስከተለ የማንነት ጥያቄ የተከሰተው ይሄው ሃገር ያረጋጋል የተባለው የዘውግ ፌደራሊዝም በስራ ላይ ከዋለ በኋላ ነው፡፡

የዘውግ ፌደራሊዝሙን ተከትሎ ከሚነሱ ጥያቄዎች አንዱ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ነው፡፡የወልቃይት ጉዳይ ከማንነት ጥያቄ ባለፈ ከኢኮኖሚያዊ እስከ ስነ-ልቦናዊ ጉዳዮችን የያዘ ውስብስብ ጥያቄ ነው፡፡ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እርምጃ ሁሉ የጉዳዩን ክብደት እና ውስብስቦሽ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ህወሃት የወልቃይትን ችግር ሲቀምም መፍትሄ እንዳይኖረው አድርጎ ነው፡፡ስለዚህ የወልቃይትን ችግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ችግር ፈጣሪው ህወሃት ጉዳዩ እንዲሄድ በሚፈልግበት መንገድ ተኪዶ ሊሆን አይችልም፡፡የወልቃይትን ጉዳይ ለመፍታት ሃይል እና መጠፋፋት አማራጭ ሆነው መቅረብ የለባቸውም፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የችግሩ እንጅ የመፍትሄው አካል አይሆንም፡፡

ሁነኛ መፍትሄ ለመፈለግ የወልቃይት ችግር መቼ?እንዴት?በማን? እና ለምን? ተፈጠረ የሚለውን ነገር በመፈተሽ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች በመመርመር የሚነሳ ሁነኛ የመፍትሄ እርምጃ በቀጥታ የሚያመራው የወልቃይት ነገር ተወሳስቦ ወደታሰረበት ወደ ሽግግሩ ዘመን ወቅት ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ስለወልቃይር ችግር ጥብቀት ባነሳሁበት ፅሁፍ የሽግግር ዘመኑ እንዴት ለወልቃይት ችግር መነሻ እንደሆነ እና ይህ ችግር እንዴት ከህገ-መንግስቱ ጋር በጥብቅ እንደታሰረ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ በሽግግሩ ወቅት ህወሃት በወልቃይት ላይ ጤናማ ያልሆነ የስነ-ህዝብ ለውጥ አድርጓል፡፡እጅግ የተጣደፈ እና ሰውሰራሽ የህዝብ ስብጥር ለውጡን ያደረገው የፈለገውን ሰው በቦታው በማስፈር ብቻ አልነበረም፡፡ ይልቅስ በአካባቢው ነባር ሰዎች ላይ ዘር እየለየ የመግደል፣የማፈናቀል እና ማንነትን የማስካድ ጉልበታዊ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

ህወሃት ይህን ያደረገው ከጫካ ጀምሮ በነበረው ትግራይን ከሱዳን ጋር ጎረቤት የመድረግ እቅድ እንደነበረ የድርጅቱ መስራች ዶ/ር አረጋይ በርሄ ተናግረዋል፡፡ ሌላው ተጨማሪ ጉዳይ ልምላሜ ለሚያጥራት ትግራይ ለም መሬት የማምጣት ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ሲሆን ስነልቦናዊ ነገርም አያጣውም፡፡በሽግግር ወቅቱ ደርግን የጣለው ህወሃት በከፍተኛ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰክሮ ነበር፡፡እንደ አንድ ዘረኛ ድርጅት አሸናፊነት ቦታ ላይ ቆሞ መጀመሪያ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ደግሞ ታገልኩላት ለሚለው የትግራይ ብሄር ይጠቅማል የተባለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ከዚህ አንዱ የትግራይን ንዑስ ግዛት በመስፋፋት ወደ ግዙፍነት መቀየር ነው፡፡ጨቋኝ እና ትምክህተኛ እያለ ሲያክፋፋው ከነበረው የአማራ ግዛት ላይ መሬት ወስዶ ለትግራይ መስጠት ደግሞ የአሸናፊነቱን ስሜት ጣፋጭ ከማድረጉም በላይ ለአማራው ሞቶ መቀበር ምልክት ተደርጎ ታይቷል፡፡የህወሃት ሰዎች “አማራውን ገድለን ቀብረነዋል” ሲሉ የኖሩበት አንዱ ምክንያት(ብቸኛው ባይሆንም) ወልቃይት ላይ ያደረጉትን ሲያደርጉ “ሃይ” የሚል ስለጠፋ ነው፡፡

ከዚህ የምንረዳው የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል፣የዲሞግራፊ፣የኢኮኖሚ፣የህግ የበላይት(የተጠያቂነት) እና የስነ-ልቦና ጉዳዮችን ሁሉ ሰብስቦ የያዘ መሆኑን ነው፡፡ስለዚህ የማንነትን ጉዳይ ብቻ አጉልቶ የሚያወጣው የወልቃይትን ጉዳይ የሚከታተለው ኮሚቴም ሆነ ነገሩ ያመለከተኛል ባይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ከዚሁ አንፃር መሆን አለበት፡፡ እናም ከስሙ ጀምሮ “የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ” የሚለውን አጠራር መቀየር አለበት፡፡ ኮሚቴው በዚህ መጠሪያ መቀጠሉ “ሪፈረንደም ይደረግና የህዝቦቹ ትግሬ/አማራነት ይለይ” የሚለውን የህወሃት ክርክር የማጠናከር አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ የወልቃይትን ፈርጀ-ብዙ ችግር ደፍጥጦ ከችግሩ አንዱ ብቻ በሆነው የማንነት ጥያቄ ላይ ብቻ ያንጠለጥለዋል፡፡ ይህ የሚበጀው ደግሞ ያደረገውን እያወቀ “ነገሩ በሪፈረንደም ይለቅ” ለሚለው ህወሃት ብቻ ነው፡፡

የወልቃይት ጉዳይ ከላይ በተጠቀሱት ፈርጀ ብዙ ጥያቄዎች አንፃር ከታየ ቀዳሚ ሆኖ የሚመጣው የህወሃት ባለስልጣናት ከጫካ ጀምሮ ያቀዱትን ከሱዳን ጋር የመዋሰን፣አማራን የማንበርከክ ፣ትግራይን ታላቅ የማድረግ ዕቅድ ለማሳካት በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብት ላይ ያደረጉትን ወንጀል በተጨባጭ ማስረጃ አጠናቅሮ ለሃገር አቀፍም ሆነ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ማቅረብ እና ነገሩን በነሱ ደረጃ እንዲከታተሉት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡የሰብዓዊ መብት ጥሰት በህግ ይርጋ የሌለው ወንጀለ ስለሆነ የተፈፀመበት ዘመን ቢርቅም ወንጀለኞቹ ለህግ መቅረባቸውን የሚያግድ ነገር የለም፡፡ይህ በዋናነት የኮሚቴው ስራ ቢሆንም የሁሉም ሰብዓዊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ድርሻ መሆን አለበት፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱን የማጣራቱ ስራ ለጉዳዩ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የሚረዳ ነገር ይዞ ይመጣል፡፡ ይኸውም “ህወሃቶች በሽግግር ወቅቱም ሆነ ከዛ ወዲህ በወልቃይት ህዝብ ላይ ያደረጉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያደርጉ ምን አስገደዳቸው?” የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጥ እውነተኛ መልስ የችግሩ ራስ፣ የመፍትሄውም ጭራ ነው፡፡ መልሱ የሚሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ የተካሄደው ህወሃት ትግሬ እንድትሆን የፈለጋት ወልቃይት ከሽግግሩ ወቅት በፊት በነበራት ተፈጥሯዊ የህዝብ ስብጥር ትግሬ ሆና ወደትግራይ ለመካለል የሚያስችል ትግሬነት ስላልነበራት ነበር፡፡ስለዚህ ወልቃይትን ትግሬ ለማድረግ ትግሬን በጥድፊያ ከተከዜ ማዶ እያመጡ ከማስፈሩ በተጨማሪ ለወልቃይት ቀደምት አማራነት ምልክት የሆኑ አማሮችን ከአካባቢው በእስር፣በግድያ ፣በማፈናቀል መቀነስ ወይ ማጥፋት አስፈልጓል፡፡

ከክቡሩ የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት የበለጠ ምንም ነገር የለምና በወልቃይት ጉዳይ ከሚነሳው ኢኮኖሚያዊ እና የድንበር ጉዳይ በፊት መመርመር ያለበት በቦታው የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ለማጣራት ገለልተኝን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ በስራው ብዙ ልምድ ያካበቱ እንደ “Genocide watch”, “Human rights watch” ያሉ ድርጅቶችም መጋበዝ አለባቸው፡፡የነዚህ ድርጅቶች ሪፖርት ብቻውን ወንጀለኞችን ፍርድቤት ለማቅረብ በቂ ስለማይሆን መንግስትም የራሱን ኮሚሽን አቋቁሞ ነገሩን ማጣራት አለበት፡፡ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ የሚችለው እንዲህ ካለው ከስር ከመሰረት ችግሩን ከመመርመር በሚነሳ እርምጃ እንጅ ከችግሩ ወገብ ተነስቶ፣ህወሃት ችግሩን ሲፈጥር በጓዘበት መንገድ ተጉዞ “በህገ-መንግስታዊ መንገድ ይፈታ” በሚለው ፍርደ-ገምድል መንገድ አይመስለኝም፡፡

“የወልቃይት ጉዳይ በህገ-መግስታዊ መንገድ ካልተፈታ እንዴት ይፈታ?” የሚል ጥያቄ መከተሉ አይቀርም፡፡ ይህን ጥያቄ በተመለከተ የማቀርበው ነገር እኔ በግል ይበጃል ብየ የማስበውን እይታየን ለማጋራት እንጅ የመጨረሻ መልስ ለመስጠት አይደለም፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ችግሩን ለመፍታት የሚደረገው እርምጃ መጀመር ያለበት በቦታው ለረዥም ዘመን የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መርምሮ ወንጀለኛን ተጠያቂ በማድረግ ላይ መሆን አለበት፡፡ሌሎቹ ቀጥየ የማነሳቸው የቢሆን መፍትሄዎች የሚሰሩት ይህ ከተደረገ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም በደሉ ተገልጦ ሳይወራ/ሳይካስ፣እውነት ሳይወጣ ተሸፋፍኖ ከቀረ ሁለት አደገኛ መዘዞች ይኖሩታል፡፡አንደኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰጥን የመሰለ ክፉ ወንጀል የሰራን ሰው ዝም ብሎ ማለፍ የተጠያቂነትን እና የህግ የበላይነትን ጉዳይ ድርድር ውስጥ ማስገባት ከመሆኑም በላይ ወንጀለኛን ማበረታታት ነው፡፡ ለዚህ ነው በወልቃይት ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳደረጉ በሃገሬው ህዝብ ዘንድ የሚወራላቸው የህወሃት ባለስልጣናት ያለ ምንም መሸማቀቅ የወልቃት ህዝብ ጉዳይ ለማዳፈን የሚሰሩት፡፡ ሁለተኛው መዘዝ ተበዳዩ ህዝብ ቂሙን እንዳይረሳ ስለሚያደርግ ዋናውን ችግር በመሸፋፋን የተፈለገውን የሰላም መፍትሄ ማምጣት ፈፅሞ አይቻልም፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ጉዳይ ተበዳዮችን በሚያረካ ሁኔታ በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ታይቶ እልባት ከተሰጠው በኃላ ወደ ፖለቲካዊ መፍትሄዎቹ መምጣት ይቻላል፡፡ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ደግሞ የትግራይ እና የአማራ ህዝብ/ልሂቃን ዘንድ ከእልኽኝነት ይልቅ የሚዛናዊነት እና ሆደ ሰፊነት አካሄድን መምረጥ አለባቸው፡፡በመንግስት በኩልም ከችግሩን ውስብስብነት የተነሳ እውነትን ከመሸሽ ይልች የችግሩን ብልት አውጥቶ መለሃኛ ውሳኔ ማሳለፍ አለበት፡፡ቀድሞ የሰብዓዊ መብት ወንጀሎችን ማጣራቱ እና ተጠያቂነትን ማረጋገጡ ለዚህ ጉልበት የሚሰጥ እርምጃ ነው፡፡ፖለቲካዊ መፍትሄ ሲሰጥ ከላይ እንደተጠቀሰው ችግሩ ከማንነት አልፎ የዲሞግራፊ ጉዳይ እንደሆነም በአማራም ሆነ በትግራይ ህዝቦች ዘንድ መረዳት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ የችግሩ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ የዘውግ ፌደራሊዝምን መቀየር ነው፡፡ ይህ ግን በአጭር ጊዜ ሊሆን የሚችል አይደለም፡፡ አሁን በወልቃይት ምክንያት በትግራይ እና አማራ ልሂቃን መሃከል የተፈጠረውን እያደር የሚካረር ፍጥጫ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሄ ያሻዋል፡፡ ይህን መፍትሄ ለማዋለድ በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ ማስተዋል የተሞላበት አካሄድ ያስፈልጋል፡፡

ህወሃት ስልጣ እንደያዘ በመኪና እያጫነ ወደ ወልቃይት ያመጣቸው ትጥቅ-ሰቀል ወታደሮቹም ሆኑ ሲቪል የትግራይ ተወላጆች በአሁኑ ወቅት ሲመጡ በነበሩበት ቁጥር ላይ የሚገኙ አይደሉም፤እጅግ ተባዝተዋል፡፡ ወልደው እዛው ምድር ላይ ያሳደጉ ሰዎች ናቸው፡፡ እዛው ምድር ላይ ተወልዶ ያደገን ሰው ደግሞ “ዛሬ ተነስና ወደ መድረሻህ ድረስ” ማለት ከህወሃት አለመሻል ነው፡፡ እዚህ ላይ አብሮ መታየት ያለበት አንድ ህዝብ ነቅሎ ሌላውን የመትከሉ ሴራ ተጀምሮ እስኪጨረስ የተከወነው በህወሃት እንጅ “የተሻለ ህይወት ላመጣላችሁ ነው” ሲባሉ በመኪናተሳፍረው በመጡ እንጀራ ፈላጊ ግለሰቦች እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በአካባቢው የሰፈሩ ሰዎች ህወሃትን እንደ አጉራሽ አይተው በወልቃይት ህዝብ ላይ በሚያደርገው ግፍ ላይ የመተባበር አዝማሚያ አሳይተው ከሆነም አካሄዳቸው ስህተት እንደነበረ አሁን እየሆነ ካለው ነገር መረዳታቸው አይቀርም፡፡ህወሃት የሃገሪቱን ህዝቦች ድህነት እና እንጀራ ፈላጊነት ተጠቅሞ ሲያባላ እንደኖረ ማስተዋል አለብን፡፡ ይህን ያደረጉ የህወሃት ሰዎች በህግ ቅጣት እስካገኙ ድረስ ነገሩን አርግቦ በአንድ ሃገር ልጅነት መንፈስ መተያየት ያስፈልጋል፡፡

“አብሮ መኖሩ የመሆነውስ እንዴት ባለ መዋቅር ውስጥ ነው?” የሚለውም ሌላ አስቸጋሪ ጥያቄ ነው፡፡የወልቃይትን ህዝብ ሲገድለው፣ ሲያሳድደው፣ማንነቱን ጨፍልቆ “በትግርኛ አልቅስ” ሲለው በኖረው የትግራይ ክልል መስተዳድር ስር ተዳደር ማለት እየፈጩ ጥሬ መሆን ነው፡፡በአንፃሩ ወልቃይትን እንኳን ትግሬ ለማስመሰል ከትግራይ ተነቅሎ የመጣን ህዝብ በአማራ ክልል ስር ተዳደር ማለትም አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጉዳይ ሌላ መሃለኛ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በግሌ አንድ መፍትሄ የሚመስለኝ አካባቢውን በፌደራ መንግስት ስር የሚተዳደር ልዩ ዞን አድርጎ በህወሃት እና አዴፓ ጥምር አስተዳደር እንዲተዳደር ማድረግ ነው፡፡ የሃረሬን ክልል ኦዴፓ እና ሃብሊ እያስተዳደሩት ስለሚገኙ ይህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የአዴፓ እና የህወሃት ባለስልጣናት ከገቡበት የውድድር፣የንትርክ እና እልኸኝነት መንፈስ ወጥተው ለሁለቱ ክልል ህዝቦች የተረጋጋ መፍትሄ የማምጣት ስክነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡

ሰላማዊ መፍትሄ ይምጣ ከተባለ እልኽኝነቱ ባስ የሚልበት ህወሃት አዴፓ በወልቃይትም ሆነ በራያ ጉዳይ ትንፍሽ እንዳይል የሚፈልገውን ነገር መተው አለበት፡፡በነዚህ ህዝቦች ላይ የቀድሞውን ብአዴንን በጠመንጃው አስገድዶ የሰራውን ሆዱ እያወቀ አዴፓ “አማራነንና በስርህ እንተዳደር” የሚሉ ሰዎችን ጉዳይ እየሰማ ዝም ይበል ማለት ብአዴን ተቀይሮ አዴፓ እንደሆነ፤ህወሃትም የቀድሞው ህወሃት እንዳልሆነ መረዳት አለመፈለግ ነው፡፡ ብአዴን አዴፓ ሆነ ሲባል የፓርቲውን መጠሪያ ሆሄያት ቀያየረ ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ በብአዴንነቱ ዘመን ለህወሃት በማደግደጉ ሳቢያ ‘አይንህ ላፈር’ የሚለው የአማራ ህዝብ አሁን በተለይ በወልቃይት ጉዳይ ከሞላ ጎደል አብሮት እንደሆነ ህወሃት ማወቅ አለበት፡፡ ህዝብን የያዘ እንደሚያሸንፍ ደግሞ ለህወሃት ዛሬ ካልገባው መቼም አይገባውም፡፡ ሰላማዊ መፍትሄ የማይወደው ህወሃት ‘እኔም ህዝብን ይዣለሁና ይዋጣልን’ የሚል ከሆነ “ይሞክረው” ባይባልም እንደማያስኬደው ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

አዴፓ እና ህወሃት ተስማምተው አካባቢውን ለማስተዳደር መጣጣሙ ካልሆነላቸው ሁለተኛው አማራጭ የሚሆነው የፌደራሉ መንግስት ልዩ ዞን የሆነውን የአካባቢውን አስተዳደር እንዲረከብ ማድረግ ነው፡፡ የፌደራሉ መንግስት አስተዳደሩን ከተረከበ በኋላ በአካባቢው ዘልቆ ከህወሃትም ከአዴፓም ያልሆኑ ነገር ግን ከሁለቱም ብሄሮች የተውጣጡ ብቃት ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በህዝቡ ተመርጠው እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ የተለየ እና የተሻለ ሁለቱን ህዝቦች በሰላም የሚያኖር ውጥረቱንም የሚያረግብ ሃሳብ ያለው ዜጋ ሁሉ የታየውን ቢሰነዝር ደግሞ የተሸለ አማራጭ ላይ ለመድረስ ይቻላል፡፡
___
ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ወልቃይት ፡ አጥብቆ ያሰረ ዘቅዝቆ ይሸከማል…..(በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ጥቅምት 3 ፤ 2011 ዓ.ም

በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባን የተቆጣጠረው ህወሃት ቀጣይ ሥራ ያደረገው የትግራይን ግዛት ማስፋፋት ነበር፡፡ይህ የረዥም አመት ፕሮጀክት የተጀመረው ከጎንደር ወልቃይትን የመሰሉ፣ከወሎ ራያን የመሰሉ ለም መሬቶችን ልምላሜ ወደ ሚያጥራት ትግራይ ክልል በማካለል ነው፡፡ይህ ህወሃት በአማራው ህዝብ ላይ ከሰራቸው በርካታ ግፎች ውስጥ በከፍተኛ በጥንቃቄ የተሰራው ነው፡፡ቀን እንደዞረለት የተረዳው ህወሃት ግዛቶቹን ወደ ትግራይ የማካለሉን ስራ ሲሰራ ተገን ያደረገው መሳሪያውን ብቻ አልነበረም፡፡ይልቅስ የኢትዮጵያ ጌታ መሆኑ የሰጠውን ቱርፋት ሁሉ ተጠቅሞ ጉዳዩን በተለያዩ ገመዶች አትብቆ ሲያስር ኖሯል፡፡

ህወሃት ኮስተር ብሎ የያዘው ከአማራ ክልል ግዛቶችን እየወሰዱ ትግራይን ለም፣ግዙፍ እና ሃያል ግዛት የማድረጉን ነገር አጥብቆ ከማሰሩ የተነሳ ይህን በተመለከተ ጥያቄ ሲነሳበት ፈርጠም ብሎ “ሪፈረንደም ይደረግ” እስከ ማለት አድርሶታል፡፡

በአንፃሩ የመሬቱ እውነተኛ ባለቤት የአማራ ክልል እንደሆነ፣ እነሱም አማራ እንደሆኑ የሚያነሱ ወገኖች ሪፈረንደሙን አጥብቀው የሚቃወሙት ብቻ ሳይሆን በሰላም ለመኖር ያለመፈለግ ዝንባሌ አድርገውም ያዩታል፡፡ለመሆኑ ህወሃት ሪፈረንደም እስከመጠየቅ ድረስ ያስደፈረው፣ጉዳዩ ወደራሱ ፍላጎት እንዲያዘነብል አድርጎ አጥብቆ ያሰረበት ገመድ ምንድን ነው? ብዛቱ እና ጥብቀቱስ እንዴት ነው? የሚለውን መመርመሩ አስፈላጊ ነው፡፡

ገመድ አንድ- የጎሳ ፖለቲካ ተረክ

ህወሃት የተፈጠረለት አላማ ትግራይን ከአማራ አገዛዝ ነፃ ማድረግ ነበር፡፡በተፈጥሮ ሃብት ድህነቷ ሳይቀር የመጣውን የትግራይ ጉስቁልና ምክንያቱ አማራ ነው ሲል ኖሯል-ህወሃት በማኒፌስቶው፡፡ የትግራይ ችግር ሁሉ በአማራ ምክንያት የመጣ እንደሆነ በደመ-ነፍስ ሲያስብ የኖረው ህወሃት የትግራይ ጉስቁልና የሚከላውም የአማራውን ሃብት በመዝረፍ፣ግዛቱን በመቀማት፣አከርካሪውን በመስበር እንደሆነ አምኖ ታጥቆ ሰርቶበታል፡፡የዚሁን ቅጅ ለሌሎች ብሄረሰቦች ሲያዛምት፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ችግሮች ሁሉ ባለቤት አማራው እንደሆነ ሃፍረቱን ጥሎ በአደባባይ ሲሰብክ ኖሯል፡፡

ይህንኑ ዕምነቱን በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ለማስረፅ ብዙ አልተቸገረም ነበር፡፡በዚህ ላይ በአማራው ላይ የተጋረጠውን ትልቅ አደጋ በሚመጥን ቅንብር እና ፍጥነት የአማራው ብሄርተኝነት መብቀል አለመቻሉ ህወሃትን ከልካይ አልቦ የአማራው ቀጭ አድርጎታል፡፡አማራው መተንፈስ ያለበት ትምክህተኛ፣መቀጣት ያለበት ወንጀለኛ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ይህ እሳቤ በሃገሪቱ አለቅጥ የገዘፈው የጎሳ ፖለቲካ የሚሽከረከርበት ሃዲድ ሆኖ ኖሯል፡፡የአማራው መበደል፣መሸማቀቅ የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት መረጋገጥ ምልክት መስሏል፡፡አማራውን መግደል፣ማሳደድ፣በአደባባይ ማሸማቀቅ፣ማክፋፋት ለታሪክ ስህተቶች የሚሰጥ እርምት ሆኖ ተቆጠረ፡፡የአማራ መሞት፣መብት መገፈፍ ለጆሮ የማያስደነግጥ፣ ለዘገባም የማያስቸኩል፣ቢዘገብም ጉድ የማያስብል ነገር ሆነ፡፡

በዚህ መሃል ህወሃት ገበያው ደራለት! በአንድ በኩል አማራውን የመግደል የማሳደዱን ነገር በመላ ሃገሪቱ ከተነሱ በአማራ ተበደልኩ ባይ የጎሳ ፖለቲከኞች ጋር እየተጋገዘ እየከወነ በሌላ በኩል የአማራውን መሬት ወደ እናት ምድሩ ትግራይ የማዳበሉን ነገር ለብቻው ተያዘው፡፡ተጠንቅቆ ያበጃጀው የጎሳ ፖለቲካ ከባቢ አማራውን ያለጠያቂ እንደፈለገ እንዲያደርግ የፈቀደለት ህወሃት ገመዶቹን እያነባባረ የመሬት ዘረፋወን አጥብቆ ማሰሩን ቀጠለ፡፡

ገመድ ሁለት- ረዥሙ የሽግግር ወቅት

ህወሃት አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ያወጀው አራት ዓመት የሽግግር ወቅት በሽግግር መንግስት እድሜ ከተሰላ ረዥም የሚባል ነው፡፡እውነተኛ አላማው እንደስሙ ለመሸጋገር ከሆነ ሁለት አመት ለሽግግር በቂ ጊዜ ነበር፡፡በእያንዳንዱ ጉዞው ላይ የራሱ የሆነ ድብቅ አጀንዳ ለማያጣው ህወሃት ግን የሽግግር ወቅቱ የሃገሪቱን የፖለቲካ ልጓም በህዝብ ወደተመረጠ መንግስት እጅ ማሸጋገር ብቻ አልነበረም፡፡ይልቅስ የሽግግሩ ጊዜ ለህወሃት የሃገር ጌትነት ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ባላነሰ እጅግ አስፈላጊ ወቅት ነበር፡፡ ስለዚህ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶ ለወደፊት የገዥ ነጅነት ዘመኑ ስምረት መሰረት የሚጥሉ ስራዎችን መከወን ነበረበት፡፡

ከነዚህ ጉዳዮች አንዱ ከአማራው ግዛት ላይ እጁ የቻለለትን፣ልቡ የወደደውን ያህል መሬት መቦጨቅ የሚያስችለውን ቅድመ-ሁኔታ ማመቻቸት ነበር፡፡ይህ ስራ ወደፊት(የሽግግሩ ወቅት ሲያልቅ) በህገ-መንግስት ሊፀና የታሰበው የጎሳ ፌደራሊዝም ህወሃት የሊበላቸው ያሰባቸውን ወልቃይት፣ጠገዴ፣ጠለምት፣ራያ የተባሉ አሞሮች ጅግራ የሚያደርግ መሆን ነበረበት፡፡ስለዚህ በነዚህ ቦታዎች እጅግ ፈጣን በሆነ ሁኔታ በጠመንጃ የታገዘ የህዝብ ስብጥር ለውጥ (Artificial Demographic Reengineering) መደረግ ነበረበት፡፡

ይህ ፈጣን እርምጃ አሃዱ የተባለው መለስ ዜናዊን ቤተ-መንግስት ያስገቡ በሽዎች ሚቆጠሩ የህወሃት እግረኛ ወታደሮችን መሳሪያቸውን አስፈትቶ ወልቃይት ላይ በማስፈር ከሸማቂነት ወደ ዘመናዊ ገበሬነት በማሸጋገር ነበር፡፡ከዚህ በተጨማሪ ከህወሃት የጌትነት ወራት በፊት በተፈጥሯዊው የጎረቤት ህዝቦች የመሄድ መምጣት መስተጋብር ከትግራይ ወደ ወልቃይት ካቀኑ ትግሬዎችም በተጨማሪ ሲቪል ትግሬዎችን በፍጥነት ወደ ወልቃይት ማስፈሩ ለነገ የማይባል አልቸኳይ ስራ ሆነ፡፡

ይህን ለማድረግ ሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎችን ማቋቋሙ ወደፊት ሊመጣ ያለውን ለማያውቀው አማራ አፍዝ አደንግዝ ነበር፡፡ የተደገሰለትን የማያውቀው የአካባቢው ህዝብ ህወሃት በሽግግሩ ወቅት ከተከዜ ማዶ ህዝብ በገፍ እያመጣ የማስፈሩን ነገር ለእርሻ ሥራው ሰራተኛ ከማምጣት ያለፈ አድርጎ ለማሰብ እንደ ህወሃት ከተንኮል መቦካትን ይጠይቃል፡፡
ጥድፍ ያለው ሰፈራ ህወሃት የወልቃይትን ጉዳይ አጥብቆ ካሰረባቸው ገመዶች እጅግ ጠባቃው ነው፡፡ህወሃት በዚህ ስራው መሬት ከመቀማቱ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት ሳይቀር በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቁትን ከባድ ወንጀሎች በወልቃይት ህዝብ ላይ ሰርቷል፡፡ከገብሩ አስራት ጀምሮ በዚህ ወንጄል የማይጠየቅ የህወሃት አመራር ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፡፡

ወልቃይትን በግድ ትግሬ ለማድረግ የሽግግሩ ወቅት ሳያልቅ በሚል እሽቅድምድም በሚመስል ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ በምድሯ የበቀለው አማራ በጅምላ ተገድሏል፣ ታስሯል፣ ተፈናቅሏም፡፡በምትኩ የባለጊዜ በአንድ ሌሊት እንደ ጅብ ጥላ በቅሎ እንዲያድር ተደርጓል፡፡

ይህ ግልጥልጥ ብሎ ሳይመረመር፣ለተሰራውን አሰቃቂ የኢ-ሰብዓዊነትና የመብት ረገጣ ግዙፍ ወንጀል ተጠያቂነት ሳይመጣ የወልቃይትን ነገር በአራት ዓመት ውስጥ በተፈበረኩ አርቲፊሻል ብቃዮች የሪፈረንደም ድምፀ-ውሳኔ ልፍታ ማለት ሲበደል በኖረው ህዝብ ላይ መቀለድ፣ሰሜን ኢትዮጵያንም የሁከት ምድር ማድረግ ነው፡፡

ገመድ ሶስት- ህገ-መንግስቱ እና አሰራሩ

ህወሃት በ1987 ያወጣው ህገ-መንግስት በረዥሙ የሽግግር ወቅት በጠመንጃ ታግዞ ለጀመረው ትግራይን በአማራው ኪሳራ ማስፋፋት ፕሮጄክት ህጋዊ ሽፋን የሰጠበት ነው፡፡ወልቃይትን በተጣደፈ፣ጤናማ ያልሆነ ሰፈራ በትግሬ የመሙላቱን ስራ አማራውን አሳዶ ከመግደል ማሰሩ ጋር አሰናስሎ ወልቃይትን “አፍላ ትግሬ” ማድረጉን ከ1987 በፊት አስረገጠ፡፡አሁን ተራው ህገ-ወጡን ብቻ ሳይሆን ወንጀሉን ህጋዊ ለማድረግ ህገ-መንግስቱን በስራ ላይ የማዋል ነው፡፡

ፅንሰት ውልደቱ ከህወሃት መሃል እጅ የማይወጣው የሃገራችን ህገ-መንግስት ያዋቀረው ዘጠኝ ክልል ቋንቋቸው ተመሳሳይ የሆኑ ህዝቦችን በአንድ ግዛት ያዋስናል፡፡ “አፍላዋ ትግሬ” ወልቃይትም ቀድሞ በህወሃት የልብ ፅላት ወደ ተፃፈላት ወደ ትግራይ ክልል ከመካለል ውጭ አማራጭ አልነበራትም፡፡

ማራጭ የለኝም ብላ ግን ዝም ብላ ወደ ነዷት አልነጎደችም፡፡ከግድያ፣ከባዶ ስድስት ሲኦል የተረፉት ሰላላ ድምፆቿን ሰብስባ፣መፈናቀል የበታተናቸውን ጉልበቶቿን እንደምንም አቀናጅታ አማራነቷን እያወጀች ትገኛለች፡፡ጩኽቱ የሚጎርፈው ግን ህወሃት እንዲመቼው አድርጎ በሰራው ቦይ ስለሆነ ጠመንጃ ይገላግለኝ ከሚለው የቢቸግር መፍትሄ የተለየ ጠብ የሚል ሁነኛ መፍትሄ ሊገኝ አልቻልም፡፡

የሽግግር መንግስቱ የጀማመረውን የጎሳ አከላላል ያፀናው ህገ-መንግስት ወልቃይትን ከነጩኽቷ ለትግራይ ክልል ምክርቤት በመሸለም የግፍ ጉዞዋን እንድትቀጥል አደረገ፡፡ ወልቃይትን በተመለከተ ህገ-መንግስቱ ያደረገው ነገር ቢኖር በሽግግሩ ወቅት የተደረገውን ወንጄል፣የተሰራውን ደባ ህጋዊ ማድረግን ነው፡፡ህጋዊ የሆነ ነገር ሁሉ ተገቢ ነው ማለት አይቻልም፡፡

ለዚህ ከወልቃይት ጉዳይ በላይ ማሳያ የለም፡፡ከአራት አመት በኋላ የሚፃፈው ህገ-መንግስት ትግሬ ብሎ እንዲጠራው በተፈለገ የአማራ መሬት ላይ የሚኖርን ህዝብ በፍጥነት ገድሎ፣አስሮ፣አሰድዶ፣የገባበትን አጥፍቶ፣የቀረውን ደግሞ ማንነቱን አስክዶ በምትኩ ከአንድ ዘር ብቻ የተቀዳን ህዝብ በመኪና እየሞሉ በገፍ ማስፈር ሃገሩ ኢትዮጵያ ባይሆን ብዙ አመት ፍርድ ቤት የሚያመላልስ ወንጀል እንጅ ሆድ ሲያውቅ በሆነ ሁኔታ ህገ-መንግስቱን እየጠሩ የሚመፃደቁበት፤ጭራሽ ለሪፈረንደም የሚጋበዙበት ሰው ፊት የሚያቆም ሥራ አልነበረም፡፡

ህገ-መንግስቱን ለገደብ የለሽ ምኞቱ ማስፈፀሚያ እና ለይሉኝታ ቢስ ክርክሩ ማገር ብቻ የሚጠቀመው ህወሃት ታዲያ ፍትህ ተነፍገው፣ሳይወዱ በግድ በግፍ ወደ ትግራይ የተካለሉ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ቦታዎችን የትግራይ ህጋዊ ግዛቶች ናቸው ሲል በእማኝነት የሚጠራው ራሱ በጠመንጃው የከተበውን ህገ-መንግስት ነው፡፡

ከእርሱ ህልውና በፊት በወልቃት አካባቢ በጉልበተኛው ህወሃት እጅ የተደረጉ ወንጀሎችን ያይ ዘንድ አፈጣጠሩ የማይፈቅድለት ህገ-መንግስትም የተፈጠረለትን አላማ ከማስፈፀም በቀር ፍትህ ርትዕ ሳያሰፍን የህወሃት ማኒፌስቶ ቅጅ ሆኖ ብቻ ሃያ ሰባት አመት ዘልቋል፡፡በህወሃት ሳቢያ በጥንድ አይኑ የሚያለቅሰውን የወልቃይት ህዝብ የሚያስለቅሰውን ጉዳይ ይዞ ወደ ችግሩ አባት ወደ ወህወሃት ፓርላማ እንዲሄድ ያዛል፡፡ይህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ህገ-መንግስቱን ራሱን ህወሃት የወልቃይትን ነገር አጥብቆ ያሰረበት ሶስተኛ ገመድ ያደርገዋል፡፡

ገመድ አራት- የህወሃት “ሁለት-ነፍስ”

ወልቃት በፍጥነት ትግሬ ሆና ህገ-መንግስቱን እንድትጠብቅ ወንጀል ሲሰራ የኖረው ህወሃት ምንም እንዳልሰራ ሰው የወልቃይት ነገር መታየት ያለበት በህገ-ንግስቱ እንደሆነ ይወተውታል፡፡ከብዙ አመት በኋላ የወልቃየትን ጉዳይ በአደባባይ ይዘው መከራከር የጀመሩት አባላትም ይህንኑ በደባ የተሞላ መንገድም ቢሆን እንሞክረው ብለው ሲደክሙ ኖረዋል፡፡እነዚህ ሰዎች ለደከሙት ድካም እና ላሳዩት ቆራጠነት ትልቅ ክብርም አድናቆትም ያለኝ ቢሆንም በመንገዱ አዋጭነት ላይ ግን ወደተስፋቢስነት የተጠጋ ትልቅ ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡

የወልቃይት ማንነት ጥያቄ ኮሚቴ ሲሄድበት የነበረው መንገድ የሚያመራው ህወሃት ነገሩ እንዲሄድ ፈልጎ ባስተካከለው ፣እሱን ከነወንጀሉ እውነተኛም፣ህጋዊም፣በስተመጨረሻም በስመ-ሪፈረንደም አሸናፊ በሚያደርገው አቅጣጫ በመሆኑ ነው፡፡በዚህ አካሄድ መጀመሪያው አቤቱታ የሚቀርበው ምናልባትም የወልቃትን ህዝብ በአራት አመት ውስጥ በማጥፋቱ ላይ ተግተው የሰሩ የህወሃት ወንጀለኛ ባለስልጣናት በሞሉት የክልላቸው ምክርቤት ነው፡፡ይህ ምክርቤት ነገሩን በፈለገው የጊዜ ርቀት ሲያሸው ኖሮ ከላከው የሚልከው ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት ነው፡፡

ህወሃት በሃገሪቱ የፖለቲካ አየር ሞልቶ እንደመኖሩ ጉዳዩ ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ በሚያደርገው ሽግግር ላይ ባለ ሁለት ነፍስ ሆኖ በየደረጃው ጥቅሙን የሚያስከብር ስራ ሲሰራ ኖሯል፡፡በፌደሬሽን ምክርቤት ውሳኔ ጉዳዩ በትግራይ ክልል ፓርላማ ብቻ እልባት ይሰጥበት የሚል አስቂኝ ይሉኝታ ቢስ ውሳኔ ተወስኖ የነበረው በህወሃት ሁለት ነፍስ ምክንያት ነበር፡፡

ምስጋና ለጊዜ ይግባውና ህወሃት ሁለት ነፍስ መሆን ቀርቶ አንዱን ይዞ መኖሩ አጠራጣሪ መሆኑን ሲያውቅ፣በሞት አፋፉ ላይ ሆኖም ወ/ሮ ኬሪያ የተባሉ ህወሃት የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ እንዲሆኑ ያደረገው የወልቃይት ጉዳይ እንቅልፍ የማይሰጥ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡

አምስተኛው ገመድ-የገለልተኛ ወገን ዜማ

ውሉ ሲወሳሰብ የኖረው የወልቃት ችግር አሁን አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ይህ የገባው የዶ/ር አብይ ኢህአዴግ ቢቸግረው ነገሩን የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄ ሲል እውነትን መሸሽን ሲመርጥ ተስተውሏል፡፡ህወሃትም በበኩሉ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ እልባት አግኝቷል ሲል እሳትን በጋቢ ሊያዳፍን ሲሞክር ኖሯል፡፡የሆነ ሆኖ ዛሬ ላይ የወልቃይት ጉዳይ ቢሸሹት የማይሆን ጉዳይ በመሆኑ መንግስትም የማንነት ጥያቄ መሆኑን ተቀብሏል፡፡ሆኖም ችግሩን ሊፈታ የተነሳበት መንገድ ፍቱንነት አሁንም አጠራጣሪ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት የማንነትን ጥያቄ ለመፍታት ቆርጠናል ሲሉ በቴሌቭዥን ብቅ ብለው ተናግረዋል- የፌደሬሽን ምክርቤት አፈጉባኤዋ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፡፡ ለችግሩ መፍትሄ ያመጣል ያሉትን አካሄድ ሲያስረዱም ገለልተኛ ቡድን አዋቅረን ወደ ህዝቡ ወርደን ችግሩን እንፈታለን የሚል የተለመደውን የህወሃት ዘይቤ ነው ይዘው የመጡት፡፡ገለልተኛ የተባለው ደግሞ ብዙ የማንነት ጥያቄን የፈታው ደቡብ ክልል ነው ሲሉ አክለው ከዩኒቨርሲቲም ሰዎችን ጨምረው ጉዳዩን እንደሚያዩት ተናግረዋል ወይዘሮዋ፡፡

ይህ አካሄድ ከላይ የተጠቀሱትን የህወሃት ገመዶች ይመግብ ይሆናል እንጅ አዲስ እና ሁነኛ መፍትሄ የሚያመጣ አይመስልም፡፡ቀድሞ ነገር ይቋቋማል የተባለው አካልም ሆነ የራሳቸው የወይዘሮ ኬሪያ ገለልተኝነት ማንን ያስማማል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ በመቀጠል የማንነት ጥያቄን የመመለስ ብዙ ልምድ ስላለው ተመረጠ የተባለው የደቡብ ክልል በወልቃይት ደረጃ የተወሳሰበ ችግር ገጥሞት ፈቶያውቃል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

በዚህ ላይ ህወሃት በጌትነት ዘመኑ የደቡብ ክልልን ካድሬዎችን እንደ ሁለተኛ ነፍሱ የሚቆጥራቸው መሆኑ ግልፅ በመሆኑ ከደቡብ ይመጣሉ ለተባሉት ሰዎች ገለልተኝነት ጥብቅ ጥያቄ የሚያስቀምጥ ነው፡፡በዚህ ላይ ህወሃት አማራውን የሌሎች ብሄሮች ሁሉ ጨቋኝ አድርጎ ሲያቀርብ እንደመኖሩ የአማራውን የማንነት ጥያቄ በሌሎች ብሄረሰቦች ዘንድ በገለልተኝነት የመስተናገዱ ነገር ምንያህል አስተማማኝ ነው የሚለው ሁሉ ያጠያይቃል፡፡

በአጠቃላይ የወልቃይት ጉዳይ ሁሉም ሰው ወደ ማይፈልገው የአመፅ መፍትሄ እንዳይገባ ከተፈለገ የችግሩ አቀራረብም ሆነ የአፈታት መንገድ ከዚህ ቀደም ከታየበት እይታ በተለየ መታየት አለበት፡፡ እንዴት መታየት አለበት በሚለው ላይ የታየኝን ለማለት ሳምንት ልመለስ፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

በፍርሻ አደጋ ውስጥ ያለው የደቡብ ክልል (በመስከረም አበራ)

ByAdmi

በመስከረም አበራ
ኅዳር 25, 2011 ዓ.ም.

የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ሃገሪቱ ካሏት ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ብሄረሰቦች ውስጥ ከሁለት ሶስተኛ በላይ የሚሆነውን የያዘ ነው፡፡ በክልሉ ከሃምሳ ስድስት በላይ ብሄረሰቦች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡የዚህ ክልል አከላለል ከሌሎች ስምንት ክልሎች የተለየ ነው፡፡ ሌሎቹ የሃገሪቱ ክልሎች በቋንቋቸው ስም የወጣላቸው ናቸው፡፡የክልሉ ዋነኛ ባለቤቶችም ክልሉ የተሰየመበትን ቋንቋ የሚናገሩ ብሄረሰቦች እንሆኑ አንዳንዶቹ በየህገመንግስታቸው አውጀውዋል፡፡ያላወጁትም ቢሆኑ በተግባር ይህንን ካወጁት በተመሳሳይ የክልሉ አንደኛ ደረጃ ባለቤት የሆነ ዘውግ ያላቸው ናቸው፡፡ሁለተኛው እና ዋነኛው ልዩነት ግን ከሃምሳ በላይ የሚሆኑ ዘውጎች በአንድ ክልል ተደርገው መከለላቸው ነው፡፡ በተጨማሪም እነዚህ በርካታ ብሄረሰቦች ደኢህዴን በሚባል አንድ ፓርቲ ስር እንዲተዳደሩ ሆኗል፡፡ይህ ሲደረግ ደኢህዴን በሚባለው እምቅ ፓርቲ ውስጥ ከሃምሳ በላይ የሚሆኑት ብሄረሰቦች እንዴት ባለ ሁኔታ በፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል እንደሚወከሉ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡አለ ከተባለም ሲሰራበት አልታየም፡፡

‘ሌላው በየብሄረሰቡ ክልል ተሰይሞለት እኛ በአቅጣጫ በተሰየመ ክልል ውስጥ የምንኖረው እንዴት ነው?’ የሚለው ነገር በክልሉ ውስጥ በሰፊው ሲብላላ የኖረ ነገር ነው፡፡ሆኖም ከሲዳማ ብሄር ልሂቃን በቀር በሌሎች የክልልሉ ነዋሪ ብሄረሰቦች ዘንድ የራስን ክልል የመመስረቱ ነገር ብዙ ጎልቶ የሚነሳ ነገር ሳይሆን ኖሯል፡፡የዚህ ምክንያቱ በክልሉ ያሉ ልሂቃን እና ምሁራን በአመዛኙ የብሄር ማንነትን ከማጉላት ይልቅ በኢትዮጵያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ሃገራዊ ነገርን የማስቀደም ዝንባሌ ያላቸው በመሆናቸው ነው፡፡የደቡብ ክልል ልሂቃን የፖለቲካ ትግል ውስጥ ሲገቡም ከዘውግ ፓርቲ ይልቅ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲን ወደ መቀላቀሉ ያደላሉ፡፡ይህ በአክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ዘንድ የማይወደድ የደቡብ ክልል ሊሂቃን/ምሁራን ዝንባሌ ነው፡፡

አፄ ምኒልክ ደቡብ ምዕራባዊ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ገዝተዋል በሚል ተረክ ላይ ትግላቸውን የመሰረቱት አክራሪ የኦሮሞ ልሂቃን እና ምሁራን የደቡብ አቻዎቻቸው ፈለጋቸውን ተከትለው ምኒልክን የመርገሙን ፖለቲካ እንዲያፋፍሙ ይከጅላሉ፡፡የደቡብ ልሂቃ በአንፃሩ የነፍጠኛው ብቻ ጉዳይ ተደርጎ የሚቀርበውን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አንደኛ አድርገው የዘውግ ፖለቲካን ችላ ይላሉ፡፡ እንደውም ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ዘበኛ ተደርጎ ከሚቆጠረው የአማራ ክልል እኩል አንዳንዴም በሚልቅ ሁኔታ በደቡብ ክልል ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ይቀነቀናል፣ከዘውግ ማንነቶች ይልቅ የሃገር ምልክቶች ይጎላሉ፡፡በዚህ ምክንያት ከደቡብ የማይወለደው ኢትዮያዊ ወደ ሌላ ክልል ከማምራት ይልቅ የዘውግ ነገር ዋና ጉዳይ ወዳልሆነበት ደቡብ ክልል መኖርን ይመርጥ ነበር፡፡ይህ ለክልሉ ማደግ ያበረከተው አስተዋፅኦ አለው፡፡ክልሉ ለህብረ-ብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱበት ዋነኛ መሰረታቸው ነው፡፡

የደቡብ ህዝቦች፣ ልሂቃን እና ምሁራን ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት እንዲያዘነብሉ ያደረጓቸው ብዙ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ኢኮኖሚያዊውን ምክንያት ብናይ አካባቢው እንደ ቡና፣ፍራፍሬ፣ቅመማቅመም ያሉ የገበያ ምርቶች(Cash Crop) በአብዛኛው የሚያመርት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከዘውግ ቀርቶ ከሃገርም ሰፋ ያለ የገበያ መስተጋብር ይፈልጋል፡፡ ሰፋ ያለ የገበያ መስተጋብር ለመፍጠር ደግሞ ወደ ክልሉ/ዞኑ/ወረዳው የሚመጣው የሌላ አካባቢ ህዝብ የመግዛት አቅም ይዞ እንደሚመጣ መገንዘብን ይፈልጋል፡፡ ከክልሉ ውጭ ላለ ገበያ ደግሞ ሃገር የሚባል ሰፊ መስተጋብር መኖር አለበት፡፡ሃገር የሚባለው ሁለንተናዊ ሰፊ ገበያ መኖሩ ሸቀጥ የሌለው እንኳን ጉልበቱን ሼጦ የሚኖርበት የስራ እድል ይፈጥራል፡፡ ዘውግ በሚባል ጠባብ ጥብቆ መወሰን ይህን ሁሉ የዘመናዊ ካፒታሊስት ማህበረሰብ አቋም ማጣት ነው፡፡

የገበያ ምርቶችን በማምረት የሚተዳደረው የደቡብ አብዛኛ ማህበረሰብ በመላ ሃገሪቱ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ካፒታል ያለው ነግዶ፣የሌለው ጉልበቱን ሼጦ የሚኖር ነው፡፡ ጋሞ፣የወላይታ፣የጉራጌ፣የከምባታ፣የሃድያ፣ስልጤ፣ከፋ ህዝቦች ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚህ ላይ በደቡብ ክልል በተለይ በወላይታ፣ከንባታ እና ሃድያ ዞኖች ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የማይጣጣም የመሬት ጥበት አለ፡፡ በዚህ ምክንያት እነዚህ ህዝቦች የሥራ ዕድል ፍለጋ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የጉራጌ ህዝብ ማብራሪያ የማያስፈልገው ነው፡፡የወላይታ ህዝብም ከኦሮሚያ እስከ ቤኒሻንጉል፣ከአዋሳ እስከ አዲስ አበባ ስራ ባለበት ሁሉ ለፍቶ ለማደር የሚጓዝ ህዝብ ነው፡፡ የከንባታ እና ሃድያ ህዝብ እንደ ወንጅ/መረሃራ/አፋር ባሉ ፋብሪካ ባለባቸው ቦታዎች ሄዶ ከመስራት አልፎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ድረስ ያመራል፡፡ የተማረ የሰው ሃይል በኩልም ደቡብ ክልል በሃገሪቱ ዳርቻ የሚሰሩ በርካታ ምሁራንን አበርክቷል፡፡ እነዚህ ለአብነት ተነሱ እንጅ ሌሎችም የክልሉ ህዝቦች ተንቀሳቅሰው የሚሰሩ ናቸው፡፡ይህ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት ልምድ ክልሉ ካለው የገበያ ምርት አምራችነት ጋር ተደምሮ ህዝቡ ከዘውግ ማንነት ይልቅ ዘመኑን የሚመጥነውን መደባዊ ማንነቱን እንዲያስቀድም ሳያደርገው አልቀረም፡፡ የዚህ ሁሉ ድምር ውጤቱ የዘውግ ፖለቲካ በደቡብ ክልል ስር እንዳይሰድ አድርጎ ኖሯል፡፡

አዲሱ ዘፈን

የሃገራችን ህገ-መንግስት ለመገነጣጠል ህጋዊ ድጋፍ የሚሰጥ የዓለማችን ብቸኛው ህገ-መንግስት ነው፡፡ ሆኖም በደቡብ ክልል የሚኖሩ በርካታ ዘውጎች መነጣጠሉ ላይ ትኩረት አያደርጉም ነበር፡፡እንዴት እንደተመሰረተ በማይታወቅ ክልል ውስጥ ኢትዮጵያዊነታቸውን እያሰቡ ለሃያ ሰባት አመት ኖረዋል፡፡ አሁን ከሰሞኑ ግን በክልሉ ባልተለመደ ሁኔታ በየዘውጉ ተከፋፍሎ ክልል ለመሆን የመፈለግ ተከታታይ ጥያቄዎች እየተደመጡ ነው፡፡የሲዳማ፣የጉራጌ፣የወላይታዬከፋ፣የከንባታ፣የሃዲያ ዞኖች በተጨባጭ ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረቡ ዞኖች ናቸው፡፡ የነዚህ ዞኖች ጥያቄ ለደቡብ ክልል በተለይ ተብሎ የተዘጋጀ የሚመስል ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌን የተመረኮዘ ነው፡፡

ደቡብ ክልል ከሌሎች ክልሎች በተለየ የብሄረሰቦች ምክር ቤት የሚባል አወቃቀር አለው፡፡ ይህ ምክር ቤት ክልሉ ውስጥ የብዙ ዘውግ አባላት በአንድ ክልል ስለሚኖሩ እነዚህ ክልል የተነፈጋቸው ዘውጎች ጉዳያቸውን የሚመክሩበት የየዘውጉ ምክርቤት ይኑራቸው የሚል እንደ ማፅናኛ ያለ ነገር ነው፡፡ይህ የብሄረሰቦች ምክርቤት የሚባለው ነገር ሌላ ዋና ነገር አዝሏል፡፡ደቡብ የሚባለው ክልል ብዙ ብሄረሰቦችን አጭቆ የያዘ፣ እንዴት እንደተፈጠረ ለመታሪው ኢህአዴግ ብቻ በሚገባ መስፈርት የተፈጠረ ክልል ነው፡፡ ይህን የሚረዳው የብልጣብልጡ አቶ መለስ ዘመን ኢህአዴግ እነዚህ ብሄረሰቦች የተከለሉበት አከላለል ትርጉም ግልፅ አይደለምና አንድ ቀን በየዘውጋችን ክልል ይኑረን የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው እንደማይቀር አስቧል፡፡ ነገር ግን ይህ እርሱ በስልጣን ላይ እያለ እንዳይነሳ “ክልል ባይኖራችሁም የየዘውጋችሁን ጉዳይ የምትመክሩበት የብሄረሰቦች ምክርቤት ለእናንተ ብቻ አዘጋጅተን ሰጥተናል” በማለት የክልል ጥያቄን ሲከላከል ኖሯል፡፡ ከዚህ አልፎ ለሚሄድ በጠመንጃው መልስ ይሰጥ ነበር፡፡”የሎቄው ግድያ” በሚባል የሚታወቀው በ1995 የተደረገው ወደ አርባ የሚጠጉ የሲዳማ ተወላጆች ያለቁበት እርምጃ ተጠቃሽ ነው፡፡

በአንፃሩ ለህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን የክልል ጥያቄን መከላከያ ተደርጎ የተቀመጠው የብሄረሰቦች ምክርቤት የሚባል አካል ህወሃት ከስልጣን የሚወገድ ከሆነ ደግሞ “ህወሃት የሚዘውረው ኢህአዴግ ከሌለ ሃገር ትፈራርሳለች” ለሚለው ፕሮፖጋንዳው ማመሳከሪያ የሚሆን ፈንጅ ተደርጎ ቀብሯል፡፡የህገመንግስቱ አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3 ስር ከሀ-ሠ በተዘረዘሩ ቅድመ ሁኔታዎች ‘ማንኛውም ብሄረሰብ በፈለገው ሰዓት፣በብሄረሰቦች ምክርቤት በሚቀርብ ጥያቄ እና በጠያቂው ብሄረሰብ አባላት በሚደረግ ሪፈረንደም ዙሪያ በሚዞር ውሳኔ (የማዕከላዊው መንግስትም ሆነ ሌላ አካል እውቅና ሳያስፈልገ) ክልል መሆን ይችላል’ ይላል፡፡

ከኢትዮጵያ በቀር እንደዚህ ያለ አዲስ ክልል ወይም አስተዳደር የሚፈቅድ አንቀፅ ያላቸው ሃገራት ጉዳዩን ከመነሻው እስከ መድረሻው በአካባቢያዊ ምክርቤቶች ወሳኔ እንዲያልቁ የሚተው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የጀርመን ህገ-መንግስት ተመሳሳይ የአዲስ አስተዳደር መመስረትን በሚፈቅድበት አንቀፁ(አንቀፅ 29 ንዑስ ቁጥር 1 እና 2) ጉዳዩ ከመነሻው በማዕከላዊ መንግስቱ የሚታዩ ቅድመ-ሁኔታዎች ታይተው የሚያስችሉ ሆነው ሲገኙ ነው ጉዳዩ እንዲቀጥል ለአካባቢያዊ ምክርቤቶች የሚላከው፡፡በማዕከላዊው መንግስት ጥናት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል አዲስ አስተዳደር የሚጠይቀው አካባቢ በራሱ ለመቆም የሚያስፈልጉትን ኢኮኖሚያዊ፣የሰው ሃይል፣የመሰረተ-ልማት፣መልከዓምድራዊ ቅድመ-ሁኔታዎችን ያሟላ ስለመሆኑ ነው፡፡
በእኛ ሃገር ህገ-መንግስት ሁኔታ ግን የማዕከላዊው (የፌደራሉ) መንግስት ክልሎች በራሳቸው የብሄረሰቦች ምክርቤት እና የክልል ምክር ቤት ዙሪያ በሚዞር ውሳኔ ብቻ ስንት ቦታ እንደተሸነሸኑ እየቆጠረ በጀት ከመመደብ ያለፈ ስልጣን እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ይህ ድንጋጌ መቼም አቶ መለስ በሚመሩት ሃገር ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የተደረገ አይደለም፡፡ ይልቅስ በህወሃት/ኢህአዴግ የምትዘወረዋ ሃገር በህወሃት ዋናነት መዘወሯን እምቢ ያለች ቀን የሚፈነዳ ህገ-መንግስታዊ ቦምብ ነው፡፡ መንገድም ህይወትም እኔ ነኝ የሚለው ህወሃት አጋፋሪዎች ደፍሮ ስልጣናቸውን ለሚመኝ ትልቅ ፈተና አስቀምጠው ለመሄድ እንደማያመነቱ ግልፅ ነው፡፡በተግባር የሆነውም ይሄው ነው፡፡በደቡብ ክልል የመጀመሪያው የክልልነት ጥያቄ የተነሳው ዶ/ር አብይ ተስተካክለው ወንበራቸው ላይ ሳይቀመጡ ነበር፡፡ይህን ተከትሎ “እኔስ ምን እጠብቃለሁ?” የሚሉ ሌሎች ዞኖች የክልል ልሁን ጥያቄያቸውን ፋታ በሌለው ሁኔታ እያከታከተሉ ነው፡፡

ከህገ-መንግስታዊው የሽንሸና ማበረታቻ አንቀፅ በተጨማሪ የጎሳ ፌደራሊዝሙ የፈጠረው አለመተማመን የክልል ጥያቄዎች እንዲጧጧፉ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ እንደሚታወቀው የደቡብ ክልል ለሃያ ሁለት አመት ያህል ዋና ከተማውን ያደረገው በሃዋሳ ከተማ ላይ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ከተማዋ በሁሉም የክልሉ ብሄረሰቦች አስተዋፅኦ አድጋ አሁን የደረሰችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡አሁን የሲዳማ ዞን የክልል ጥያቄ ሲያነሳ ሃዋሳ ከተማን የአዲሱ የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ የማድረግ ጥያቄ አብሮ እየተነሳ ነው፡፡ ሃዋሳ ከተማ የሲዳማ ክልል ዋና ከተማ ስትሆን የቀረው የደቡብ ክልል አንድ ላይ ሆኖ ሌላ አዲስ ዋና ከተማ ከክልሉ በአንድ ቦታ ላይ እንዲመሰርት ነው እሳቤው፡፡ ዋናው ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡
እንበልና የተቀሩት የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች አንድ ላይ ሆነው አርባምንጭ ወይም ሆሳዕና አለያም አንዱ የደቡብ ክልልለ ከተማ ላይ አዲስ ዋና ከተማ ለመመስረት ይስማሙ፡፡የተመረጠችው አዲስ ዋና ከተማ ሆሳዕና ብትሆንና ከተማዋ የደቡብ ክልል ዋና ከተማ ሆና ማደግ ስትጀምር ያረፈችበት ሃዲያ ዞን ደግሞ “ሆሳዕና ከተማን ይዤ የሃድያ ክልልን እመሰርታለሁ” ቢል በደቡብ ክልል ውስጥ ያሉት የተቀሩት ብሄረሰቦች እጣ ምን ይሆናል? ደሞ ሌላ ዞን ፈልገው፣ ዋና ከተማ ከትመው፣ ማደግ ስትጀምር ከተማዋ ያለችበት ዘውግ “ከተማየን ይዤ ክልል መሆን እፈልጋለሁ” ሲል አስረክበው፣ደሞ ሌላ የሚያቀኑት ከተማ ፍላጋ ሊሄዱ ነው? ይህ መተማመኛ ማጣት ነው በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖችን የራሳቸው አካባቢ ላይ ክልል ስለመመስረት አጥብቀው እንዲጠይቁ ያደረጋቸው፡፡ ይህ የአለመተማመን ፖለቲካ ስሩን የተከለው ደግሞ በሃገሪቱ ህገመንግስት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ ነው፡፡የመሸንሸን ፖለቲካውን ችግር ለመፍታት ከተፈለገ መፍትሄው መሰራት ያለበት መበታተንን የሚያበረታቱ የህገ-መንግስቱን አንቀፆችን በማሻሻል ነው፡፡

ጥያቄው ምን ጉዳት አለው?

የክልልነት ጥያቄ እያዥጎደጎዱ ያሉ የደቡብ ክልል ዞኖች ክልል እንዲሆኑ ቢፈቀድ ሚመጣው የመጀመሪያው ጉዳት ከክልሉ አልፎ ወደ ሃገሪቱ የሚሻገር ኢኮኖሚያዊ እክል ነው፡፡ከመበታተን ይልቅ አንድ መሆኑ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ያለው በጎ አስተዋፅኦ የሚያነጋግር አይደለም፡፡አሁን ክልሉን ስንት ላይ ሲደርስ እንደሚያቆም በማይታወቅ አዳዲስ ክልሎች መከፋፈሉ በአዲሶቹ ክልሎች ውስጥ አፍላ የዘውግ ብሄርተኝነትን ስለሚቀሰቅስ ክልሉ እንደ ወትሮው ሳቢ ከመሆን ይልቅ ገፊ የመሆኑ ነገር ያደላል፡፡ ይህ ኢኮኖሚውንም ምርታማነቱንም ማዳከሙ አይቀሬ ነው፡፡ሁለተኛው ችግር ፖለቲካዊ ነው፡፡ እነዚህ ዞኖች ተሳክቶላቸው ክልል መመስረት ቢችሉ ደኢህዴን የሚባለው ፓርቲ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ይህ ማለት አሁን እየተቃረበ ባለው ምርጫ ኢህአዴግ በደቡብ ክልል እንዴት እንደሚወከል ግራ ያጋባል፡፡ ደኢህዴንን ጥለው አዲስ ክልል የመሰረቱ ክልሎችስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓርቲ መስርተው በሃገራዊ ምርጫ የሚወክላቸውን ፓርቲ የሚያገኙት እንዴት ነው፡፡በዚህ ላይ የደቡብ ክልል ምሁራን እና ልሂቃ ለብሄር ፖለቲካው ባትዋር የመሆናቸው ነገር ፓርቲዎቹን በአጭር ጊዜ መስርቶ በሃገራዊ ምርጫ የመሳተፉን ነገር ዳገት ያደርገዋል፡፡ሌላው ችግር የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ጠንካራ መሰረት የነበረው የደቡብ ክልል በዘውግ የመሸንሸኑ ነገር በኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ላይ የሚደቅነው ከባድ አደጋ ነው፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ነገረ-ሸገር (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ጥቅምት 3 ፤ 2011 ዓ.ም

በኦነግ የሚመሩት የአዲስ አበባ ባለቤትነት ይገባኛል ባይ የፖለቲካ ሃይሎች ባለቤትነትታቸውን ለማስረገጥ የሚያቀርቡት ማስረጃ የሚመዘዘው ከታሪክ እና ከህገ-መንግስቱ አንቀፅ ነው፡፡እነዚህ ወገኖች ታሪክን የሚጠቅሱት ጥያቄያችንን እውነተኛ ያደርግልናል ብለው ከሚያስቡበት የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ህገ-መንግስቱንም ቢሆን የሚያነቡት ልባቸውን በሞላው የባለቤትነት መንፈስ ስለሆነ ክርክራቸው ህገ-መንግስቱን ራሱን የሚጣላ ነው፡፡

ታሪክን ከወገቡ ጎምዶ፣ህገ-መንግስታዊ አንቀጾችን “ለራስ ለመቁረስ” በሚመስል መንገድ እየተረዱ መሄዱ ብዙ አዋጭ አይደለም፡፡ታሪክ ከወገቡ ሳይሆን ከስሩ ሲታይ ሸገር ንብረትነቷ የማን መሆን እንዳለበት ከአመት በፊት በሰፊው አስነብቤ ስለነበር ዛሬ ወደዛ ሰፊ ሃተታ አልገባም፡፡በዚህ ፅሁፍ መዳሰስ የፈለግኩት የሸገር ጉዳይ ማወዛገቡ እንዲቀጥል ያደረጉ ምክንያቶችን እና ሌሎች በጥያቄው ዙሪያ ያሉ መገለጥ ያለባቸውን ሃሳቦች ነው፡፡

አዲስ አበባ የኔ ነች የሚለው ኦነግ ይህ ጥያቄው ምክንያታዊ እና ተገቢ ቢሆን ኖሮ ለጥያቄው የማያዳግም መልስ የሚያገኘው በ1983 ከህወሃት ጋር በፍቅር በከነፈበት ዘመን ነበር፡፡ በዛ ዘመን ህወሃት ኦነግን ለማባባል ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበር አቶ መለስ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለምልልስ መግለፃቸውን “World Peace Foundation” የሚባል የጥናት ድርጅት Augest 20,2018 ላይ ባወጣው መጣጥፍ ላይ ተገልጧል፡፡ አቶ መለስ በአንደበታቸው ያሉትን ለመግለፅ ያህል እንጅ እንደ ሃገራችን አቆጣጠር በ1980ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ኦነግ የሃገራችንን እጣ ፋንታ ከሚዘውሩ ዋነኛ የፖለቲካ ሃይሎች አንዱ እንደ ነበረ፣ህወሃትም መቀመጫውን እስኪያስተካክል ይለማመጠው እንደነበረ ግልፅ ነው፡፡

ኦነግ እንዲህ ባለው አድራጊ ፈጣሪነት ላይ በተሳተፈበት፣ህወሃትም እጅግ ሲያባብለው በነበረበት ዘመን አጥብቆ የሚፈልጋትን አዲስ አበባን በተመለከተ ማድረግ የቻለው ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ጥቅም በተመለከተ በህገ-መንግስት ላይ ማስፈርን ብቻ ነው፡፡ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ጋር ባለው ጉርብትና ምክንያት በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ልዩ ጥቅም ይኖረዋል ማለት ባለቤት ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ነገር ሲፃፍ ኦነግ እዛው ቤተ-መንግስቱ አካባቢ ባለሟል ነበር፡፡

ህገመ-ንግስቱ ከላይ ወደታች በህዝብላይ የተጫነ እንጅ በትክክል የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የተሳተፈበት ባለመሆኑ ኦነግ ከቅርበቱ የተነሳ “ልዩ ጥቅም” የሚለውን ዛሬ በሚለው “የአዲስ አበባ ባለቤት ኦሮሚያ ነው፤ መኖርግን ለሁሉም የተፈቀደ ነው” በሚለው ማስቀየር ያልሆነለት ለምንድን ነው?ሲባል ይህ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ነች ሌላው ህዝብ የሚችለው ዝምብሎ መኖር ነው የሚለው ጥያቄ ለሌላው ሰው ቀርቶ ለወንበሩ ሲል ሁሉን ሸጦ ለማረፍ በማያመነታው ህወሃት ዘንድ እንኳን ተቀባይነት በማጣቱ ነው፡፡ጥያቄው ለምን ተቀባይነት አጣ ለሚለው መልስ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ጥቄው ተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር ተጨባጭም ስላልሆነ ነው፡፡

“አዲስ አበባ ባለቤትነቷ የኦሮሚያ ሆኖ ሌላው ሰውም ግን መኖር ይችላል” የሚለው ሃሳብ ጭብጥ አልቦ፣ለተፈፃሚነትም አስቸጋሪ፣ከህገ-መንግስቱም ጋር የማይጣጣም ነው፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሶስቱም የመንግስት ክንፎቹ የሚያስተዳድረው ውስን ግዛት ያለው አካል ነው፡፡ ይህ አካል በህገ-መንግስቱ የተሰጠው መብት ኦሮሚያ የሚባለውን ግዛት የማስተዳደር መብት ብቻ ነው እንጅ “በአቅራቢያህ ባለው ግዛት ላይ ሁሉ ጌታ ነህ” አልተባለም፡፡

በዚህ ምክንያት በክልሉ የማይኖሩ ኦሮሞዎች በስፋት የሰፈሩባቸውን ግዛቶች እንኳን ማስተዳደር አይችልምና ነው የኦሮሚያ ዞን የሚባለው የከሚሴ ልዩ ዞን በአማራ ክልል ስር የሚተዳደረው፡፡ በአንፃሩ ኦነግ የኦሮሚያ ንብረት ነች የሚላት ሸገር በግዛቷ የሰፈሩ አንድ ወጥ ቋንቋ የማይናገሩ ህዝቦች ራሳቸውን በሚመስል፣ስብጥርነታቸውን በሚወክል መንገድ ያቋቋሙት የራሳቸው መስተዳደር አላቸው፡፡

እንዴት/በምን የሚገለፅ ባለቤትነት?

እንዲህ ባለ ነባራዊ ፖለቲካዊ ቅርፅ ኦነግ እና ሌሎች የኦሮሞ ብሄረኞች የሚሉት ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ባለቤት መሆኗ የሚገለጠው እንዴት ነው?ባለቤትነት ከሚገለፅበት ነገር አንዱ ማስተዳደር ነው፡፡አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ሆኖ ሌላው ዝም ብሎ ይኑር ከተባለ አዲስ አበባ ፓርላማዋ ፈርሶ፣መስተዳድሯ ታጥፎ በጨፌ ኦሮሚያ ስር ትተዳደራለች ማለት ነው፡፡ይህ ደግሞ በህገ-መንግስቱ ከተቀመጠው ጋር ይጋጫል፡፡

ህገመንግስቱ አዲስ አበባ ራሷን እንደምታስተዳድር ቁልጭ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ታዲያ የኦሮሚያን የአዲስ አበባ ባለቤትነት ማጣቀሻው የህግ ማዕቀፍ ከወዴት ነው?ሃገሩ የሕግ ሃገር ቢሆን ኖሮ ለኦሮሚያም ለራሷ ለአዲስ አበባም ለራሷ እንዴት እንደሚተዳደሩ ያስቀመጠን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ጥሶ አዲስ አበባ የኔ ነች ማለት በህግ የሚያስጠይቅ ነገር ነበር፡፡ ወይስ በአስተዳደራዊ፣ፖለቲካዊ እና ህጋዊ ማዕቀፍ የማይገለፅ በስነ-ልቦና ብቻ የኔ ነው ለማለት የሚያስችል የባለቤትነት ፅንሰ-ሃሳብ አለ?

የህግ ማህበረሰብ የምንሆንበት ጊዜ ገና ስለሆነ የህጋዊነቱን ነገር ለጊዜው እናቆየውና አምስቱ የኦሮሞ ፓርቲዎች ስሜታቸው እንዳቀበላቸው ያሉትን ተቀብለን ብንሄድ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ሆና ሌላውም ሰው ግን መኖር ይችላል የሚለው ነገር ተግባራዊነቱ እንዴት እንደሚሆን ተናጋሪዎቹ ራሳቸው አውቀውት በተጨባጭ አመክንዮ ለሚያስብ ሌላ ዜጋ የሚያስረዱት ነገር አይመስለኝም፡፡

የራሱ መስተዳድር ያለው ህዝብ ሌላ ባለቤት እንዳለበት እያሰበ የሚኖረው እንዴት ነው? በተባለው መሰረት ቦረና የሚኖር አንድ አርሶ አደር ቦሌ ተወልዶ ካደገ የአዲስ አበባ ነዋሪ ይልቅ የአዲስ አበባ ባለቤት ነው ማለት ነው፡፡የቦሌው ነዋሪ የአዲስ አበባ ባለቤት ለሆነው የቦረና ወይ የባሌ ኦሮሞ ስለባለቤትነቱ የሚሰዋለት ነገር ምንድን ነው? ምናልባት የቦረናው አርሶ አደር ቦሌ መኖር ያማረው ቀን ቦሌን ለቆ መድረሻውን መፈለግ ወይስ እርሱ ያልመረጠው ከባሌ የመጣ ኦሮሞ አስተዳዳሪህ ነው ሲባል ዝም ብሎ መቀበል?ይህን ነገር ራስን በራስ ከማስተዳደር ዲሞክራሲያዊ መብት ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

በመንግስት ደረጃ ስናየው የነገሩ ጭብጥ አልቦነት ይብሳል፡፡ኦሮሚያ የአዲስ አበባ ባለቤት ከሆነች አዲስ አበባ መስተዳድር ህልውና ምን ይሰራል?ወይስ የአዲስ አበባ መስተዳድርም አዲስ አበባ ላይ መኖር ይችላል የአዲስ አበባ ባለቤት ግን ጬፌ ኦሮሚያ ነው ሊባል ነው?ይሄ ራሱ ትርጉሙ ምንድን ነው? ጨፌ ኦሮሚያ በትርፍ ጊዜው የሸገርን ነገር ሊያይ ሊቀመጥ ነው?አዲስ አበባ ሰው ሳይጠፋ ህግ ተጠረማምሶ ከንቲባ ከአጎራባች ሚጢጢ ከተማ መምጣቱ የዚህ ምልክት ይሆን? ይሄ የአዲስ አበባ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳድር የሚያደርግ ትልቅ የመብት ጥሰት ነው፡፡ በእሳት ላይ ቤንዚን ላለመጨመር ተብሎ ዝም ስለተባለ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡

መሰረታዊው ችግር

ከስሜት ወጥተን ነባራዊ ሃቆችን ያገናዘበ ነገር ስናነሳ በሃገራችን ህገ-መንግስት ድንጋጌ መሰረት ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች በአንድ ክልል ውስጥ ያድራሉ፤ ኦሮሚያ ክልልም ኦሮምኛ የሚናገሩ ህዝቦችን በአንድ ሸክፎ ያስተዳድራል፡፡ሸገር ደግሞ አንድ ቋንቋ አትናገርምና በቋንቋ በተከለለ ክልል ውስጥ መከለል አልቻለችም፡፡በመሆኑም ኦሮሚያ ቢያጎራብታትም፣ ቢከባትም፣ ቢዞራትም ኦሮሚያ በሚለው ክልል ውስጥ ልትካለል አልቻልችም፤አትችልምም፡፡ህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውም ይህንኑ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከህገ-መንግስታዊም ሆነ ከነባራዊ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ሃቆች ባፈነገጠ ሁኔታ ራሷን እንዳታስተዳድር ጭራሽ የእንቶኔ ነች የእከሌ ነች ወደሚለው ንጥቂያ የገባችው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ሸገርን ለንትርክ ምን ዳረጋት? ሲባል የነገሩ ስር መሰረት የውክልና አልቦነት ችግር ነው፡፡

1. በገዥው ፓርቲ ውስጥ ውክልና አልቦነት

በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ፓርቲ መንግስትን ይመራል፡፡ ይህ ማለት ኢህአዴግ መንግስትን ይመራል ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ የአራት ድርጅቶች ጥምረት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በየሁለት አመቱ አንዴ፣እንዳስፈላጊነቱ በሚደረግ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት ስብሰባ በሚወስኑት ውሳኔ ሃገር ይመራል፡፡እነዚህን አራት ፓርቲዎች የሚወክሉ አባላት ጎሳቸውን ወክለው ነው ውሳኔውን የሚያሳልፉት፡፡ጎሳ አልቦዋ ሸገር በዚህ ውስጥ ውክልና የላትም፡፡ ይህ ማለት ግን የሸገር ጉዳይ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አይነሳም ማለት አይደለም፡፡ ሲነሳ የሚነሳው ግን ኦሮሚያን፣አማራን ወይም ደቡብን አለያም ትግራይ ክልልን ወክለው በመጡ፣በዋናነት ሸገር ለእናት ክልላቸው መጠቀሚያነት እንዴት እንደምትመቻች በሚያሰሉ ሰዎች እንጅ የሸገርን ጉዳይ ለራሷጥቅም እና እድገት ሲሉ በሚያነሱ ሰዎች አይደለም፡፡

ታከለ ዑማ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚነት ወንበር ቁጭ ብሎ ስለሸገር ሲያወራ ሸገር እንዴት የኦሮሚያ ንብረት ትሆናለች የሚለውን ነገር ተመርኩዞ ነው፡፡የቦሌ ወጣቶችን ሰበሰብኩ ብሎ ከነማን ጋር ስብሰባ እንደተቀመጠ ግልፅ ነው፡፡ አርከበ እቁባይ ከንቲባ እያለ የአዲስ አበባን መሬት ለማን እንዴት አድርጎ እንዳደለ የሚታወቅ ነው፡፡እንዲህ ባለው ጉባኤ የሚነሳው ነገር ሸገር የኔ ነች የኔ ነች በሚል ጥቅመኝነት እና ዘረኝነት ተባብረው በተጫኑት ዝንባሌ እንጅ አዲስ አበባ ከተማ ራሷን በማስተዳደሯ የምታገኘውን ጥቅም ለማስረገጥ ሊሆን አይችልም፡፡

2. ህገ-መንግስታዊ ክፍተት

የኢትዮጵያን ህዝቦች በጎሳቸው መትሮ ክልል ያደለው የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ሸገርን ራሷን ታስተዳድራለች ቢልም ተጠሪነቷ ለፌደራል መንግስት እንደሆነ በመደንገግ ከሞላ ጎደል ለፌደራሉ መንግስት ክርን አመቻችቶ ትቷታል፡፡ በምርጫ 1997 ማግስት አቶ መለስ የገቢ ምንጮቿን ሁሉ በአንድ ጀንበር በፌደራሉ ክልል ስር አዙረው ያሸነፋቸውን ፓርቲ ቅንጅትን ከተማዋን ለመረከብም ለመተውም እንዳይወስን ግራ ያጋቡት ይህንኑ ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ነበር፡፡ሰውየው ከዚህ አለፍ ብለው በቅንጅት ስም የተመረጡ የከተማዋን አስተዳዳሪዎች እንደ ቁም እስረኛ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል መመሪያ ሁሉ ሊያወጡ እንደ ከጀላቸው ኤርሚያስ ለገሰ “ባለቤትአልባ ከተማ” ባለው መፅሃፉ አስቀምጦታል፡፡

የክልሎችን በጄት በሚወስነው የፌደሬሽን ምክርቤት ውስጥ ሸገር ህገ-መንግስታዊ ውክልና የላትም፡፡በዚሁ ምክርቤት ባለመወከሏ ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚኖራትን ውዝግብ በህገ-መንግስታዊ ማእቀፍ ለመፍታት ድምጿን ማሰማት አትችልም፡፡በአንፃሩ ለኔ ትገባለች የሚለው ኦሮሚያ ክልል በፌደሬሽን ምክርቤት ውስጥ ሰፋ ያለ ወንበር አለው፡፡

አንዳንዴ በፌደሬሽን ምክርቤት የተወከሉትስ ምን ተጠቀሙ የሚል ሃሳብ እሰማለሁ፡፡ይሄ የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ ለውጥ ኖረም አልኖረም ካልተወከለ አካል ይልቅ የተወከለ አካል ድምፁን ማሰማት ይችላል፡፡የወልቃይትን ጉዳይ የሚከታተሉ ቡድኖች አማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር ያለውን ጉዳይ አስመልክቶ አቤቱታቸውን ያሰሙት ውክልናው ስላለ ነው፡፡አቤቱታን ሰምቶ በተገቢው መንገድ የመመለስ አለመመለስ ነገር የመልካም አስተዳደር እጦት ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከነአካቴው አለመወከል ላመጣው ችግር መፅናኛ ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው ህገ-መንግስታዊ ክፍተት ሃገሪቱ የብሄር ብሄርሰቦች ናት የሚለው ነው፡፡ ሃገሪቱን ለብሄር ብሄረሰቦች የሰጠው ህገ-መንግስት የአዲስ አበባን ህዝብ “ነዋሪ” ይለዋል፡፡ለብሄር ብሄረሰቦች በባለቤትነትን የተሰጠችው ሃገር ከዚህ የተለየ ማንነት ያላቸው ግን ደግሞ ኢትዮጵያ ሃገራቸው የሆነች ሰዎች(ከሁለት ብሄር የተወለዱ፣ራሳቸውን በብሄር የማይገልፁ…) የሃገራቸው ባለቤት የሚሆኑበትን መንገድ ጥርት ባለ መንገድ መግለጽ ነበረበት፡፡ይህ ክፍተት ነው ለአዲስ አበባ ትልቅ ፈተና የደቀነው፡፡

ወደ መፍትሄው ስንመጣ እነዚህን እና ሌሎችን ክፍተቶችን ባገናዘበ መልኩ ህገ-መንግስታዊ መሻሻል መደረግ አለበት፡፡ህገ-መንግስቱ እንዲነካ አንፈልግም የሚሉ አካላት ይህን እርምጃ እንዳይደረግ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡አሁን ሃገራችን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንዲህ ያለ ንትርክ ውስጥ መግባት አስቸጋሪ ስለሚሆን ለአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚሆነው አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት አክብሮ መንቀሳቀሱ ነው፡፡

አሁን ያለው ህገመንግስት ደግሞ አዲስ አበባ በጥብቅ የፌደራል ቁጥጥር ውስጥ እንዳለች ቢደነግግም ከተማዋን ለማንኛውም ክልላዊ መንግስት በንብረትነት አልሰጠም፡፡ስለዚህ ከከተማዋ መጠሪያ ጀምሮ ህገመንግስቱ ካስቀመጠው ውጭ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት ይባስ ብሎም ይህንኑ መግለጫ አድርጎ ማንበብ ኢ-ህገመንግስታዊ ህነው፡፡ህገ-መንግስቱ መቀየር የለበትም የሚል አካል እሱው ራሱ ህገ-መንግስታዊ ድጋፍ ሌለው ሁኔታ ስሜትን ብቻ ተመርኩዞ ያዩትን ሁሉ የኔነው ማለት ትርፉ ትዝብት ላይ መውደቅ ብቻ ነው፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ጃዋር መሀመድም ግንቦት 7 ነው እንዴ!!!? (መስከረም በቀለ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

መስከረም በቀለ
ነሃሴ 30 2-10 ዓ.ም.

ሰሞኑን በከተማው በታክሲ ስጓዝ ለግንቦት 7ቶች አቀባበል በአዲስ አበባ ላይ ዝግጅቱ ደምቋል።

የዚህ የአቀባበል ዝግጅት አካል ሆነው አደባባዮች እና ጎዳናዎች በባነር እና በልሙጡ ባንዲራ አሸብርቀዋል:: ታዲያ ይህ አይደለም ግርምትን የጫረብኝ የግንቦት 7 አመራሮች እና አባላት ተብሎ በተዘጋጁት ባነሮች ላይ የሰፈሩቱ የአንዳንድ ግለሰቦች ምስሎች እንጂ::

በባነሮቹ ላይ ካልተሳሳትኩ ኔልሰን ማንዴላን አላየሁም። አሁንም ካልተሳሳትኩ የሀቀኝነት እና ለህሊና የመኖር ምሳሌ በመሆን ዛሬ ሳይሆን ገና በጠዋቱ የህ.ወ.ሀ.ትን ሴራ በማጋለጥ ሲታገል የኖረው ገብረ መድህን አርአያ የእሱንም ምስል በግንቦት 7ቶች ባነር ላይ አላየሁም። ይሁን እንጂ አሉ የተባሉ የወቅቱ የሀገራችን የነፃነት ታጋዮች እና በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የገቡ የትልቅ ስብእና ባለቤት ተደርገው የተወሰዱ ግለሰቦች ምስል አይቻለሁ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ፣ለማ መገርሳ፣ ቴዲ አፍሮ፣ እስክንድር ነጋ፣ አንዱአለም አራጌ፣ታማኝ በየነ፣ በቀለ ገርባ….ወዘተ ተካተዋል::

ልክ እንዳየሁት “እንዴ…!በቀለ ገርባ…ቴዲ አፍሮ……ግንቦት 7 ናቸው እንዴ!?” ብዬ እየተገረምኩኝ ስጓዝ በሌላ ቦታ ባለ ሌላ ባነር ላይ ደግሞ የጃዋር መሀመድን ምስል ተካቶበት አየሁ?!!!

የኔ የግንዛቤ ችግር ከሆነ ይቅርታ እጠይቃለሁ። የግንቦት 7 አመራርም አባልም ያልሆኑ ግለሰቦችን ማድነቅ ይቻላል። ማመስገንም ይቻላል። በባነሮቹ ላይ ማካተት ግን ለግንቦት 7ቶች ለምን እንዳስፈለጋቸው አልገባኝም።ተገቢም ነው ብዬ አላምንም።
ይሄ የፖለቲካ ንግድ እና የህዝብን ግንዝዛቤ መናቅም ጭምር አድርጌ እወስደዋለሁ።

ግንቦት 7ቶችን ውስጤ አያምናቸውም። ህልማቸው ህዝብን ማገልገል ሳይሆን በማንኛውም መንገድ ስልጣን መጨበጥ ይመስለኛል። እናም የወደፊቱ ወያኔ ይመስሉኛል። ይሄ የግል አመለካከቴ ነው። እንዴት ለሚለው በተለያየ አጋጣሚ የግንቦት 7ቶችን ሴረኛነታቸውን እና ውሸታምነታቸውን ታዝቢያለሁ።

1. የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋይ የነበረው ታጋይ መሳፍንት(ገብርዬ) ተገድሎ ተጥሎ የቆየ እሬሳውን እርቃኑን አድርገው በኢሳት ላይ ዜናውን ሲያስተላልፉ በህዝብ ላይ እንዲሁም በአማራው ህዝብ ላይ በተለይም በቤተሰቦቹ ላይ የተፈጠረውን የልብ መሰበር እንደ ሰው ማንም አይረሳውም። ከዛም በኋላ የዚህ ጀግና አሟሟት? የት አካባቢ? ማን እንደገደለው? እና ለምን? ለሚሉት ጥያቄዎች ግንቦት 7ቶች ተቀባይነት ያለው እና በቂ የሆነ ማብራሪያ አልሰጡም።

2. ግንቦት 7ቶች በተለይ የአማራውን ገበሬ ትግል ለመንጠቅ በሚያደርጉት እሩጫ ወያኔ በአማራው ህዝብ ላይ ሲያካሂድ ለነበረው ጭፍጨፋ ሽፋን ሆነው ወያኔን አገልግለዋል።ጭቁኑን የአማራ ህዝብ ትግል ለማንኳሰስ ሲሰሩት የነበረውም ደባ ይገርመኝ ነበር። በ ዛ በጨለማ ወቅት የአማራ ገበሬ ከወያኔ ጋር ታግሎ ድል አደረገ ሲባል ብርሀኑ ነጋ በኢ ሳት መስኮት ብቅ ይልና “አይዟችሁ መጥተናል እኛ ነን፣ አገር ውስጥ ገብተናል ” እያለ ህዝብ ላይ ሲያላግጥ የነበረውም አይረሳኝም።

በኋላ ላይ የግንቦት 7 አመራር አንዳርጋቸው ፅጌ ቢቢሲ ሀርድ ቶክ ላይ ለዘይነብ በዳዊ “ግንቦት 7 አንዲትም ጥይት ተኩሶ አያውቅም!” ሲላት ስሰማ በጣም አዘንኩ።

እና ግንቦት 7 ለምንድነው ብቃት እና ተቀባይነት ያለው የፖለቲካ ፖርቲ ለመሆን ከመስራት ከመታገል ይልቅ በአቋራጭ በመቅደም በጀብደኞች ላይ ተንጠላጥሎ ባለድል ለመሆን የሚሞክረው?
ለምንድነው ሴረኛ የሚሆነውስ? ለምንድነው ከአማራውስ ትግል በተፃራሪ የቆመውስ?
ግልፅ ነው አማራው የሚወክለው ብሄርተኛ ድርጅት ካለው ለግንቦት 7 ድምፅ መስጠቱ ይቀራል። ታዲያ እኮ የአማራውን ድምፅ ለመግዛት የአማራውን ጥያቄ የሚመልስ ሀሳብ ይዞ መምጣት እንጂ አማራው የቆመለትን ትግል ለማኮላሸት መሞከር ወዳጅነት ሳይሆን ጠላትነት ነው ብዬ ነው የማምነው።

እኔ አንድ እትዮጵያዊ ግለሰብ እንጂ የማንኛውም ድርጅት አባል አይደለሁም። ለማንኛውም ወገን ጥብቅና የመቆም አላማ ይዤም አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት። በመጨረሻም አንድ ነገር ማለት ግን እፈልጋለሁ። ይህም አንድ ለአማራ ክልል ወጣቶች ሁለት ለአዲስ አበባ ወጣቶች ነው።
የአማራ ወጣቶች የኖራችሁበትን እና እየኖራችሁበት ያለውን የሰቆቃ እና የመከራ ዘመን አስቡ፤ ከማን ጋር ለትግል አብሮ መሰለፍ ከማን ጋር መጓዝ እንዳለባችሁ ከመምረጣችሁ በፊት “ማን ምንድነው አላማው?” ብላችሁ ፈትሹ። ይህ ካልሆነ ግን ከወያኔ ለከፋው ዳቢሎስ የመጋለቢያ ፈረስ ለመሆን እራሳችሁን እያቀረባችሁ እንደሆነ እወቁት።

በተመሳሳይም የአዲስ አበባ ወጣቶች በስሜታዊነት የግለስቦችን ዱካ እየተከተላችሁ አጃቢ ከመሆናችሁ በፊት ትንሽ ጊዜ ወስዳችሁ “ማን ምንድነው አላማው፣ግለሰቡን ነው ወይስ ሀሳቡን ነው የደገፍኩት፣በስሜት ነው ወይስ በምክንያት የደገፍኩት፣ የምደግፈውንስ የፖለቲካ ድርጅት ማኒፌስቶውን አንብቢያለሁ ተረድቻለሁ ወይስ ዝም ብዬ ነው?” ብላችሁ ብትጠይቁ ካለፈው ለመማር ይረዳል እላለሁ።

ጸሃፊውን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል : legessemetasebiya@gmail.com
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ምን እያሉ ነው? (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)
ነሃሴ 19 ፤ 2010 ዓ.ም.

የህወሃት ነባር ታጋይ የሆኑት ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ገ/ተንሳይ ከህወሃት ተለየሁ ካሉ በኋላም መለስ ቀለስ እያሉ ኢቲቪን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፡፡ ህወሃት አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት ዘመን ሁሉ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሃሳብ ልዩነት ተለይተው ከወጡ በኋላ የጦር አማካሪ መሆን፣እየነገዱ መኖር፣ደርሶ የዩኒቨርሲቲ መምህር መሆን፣በሚዲያ ብቅ እያሉ አስተያየት መስጠት የሚቻለው ህወሃት የሆኑ እንደሆን ነው፡፡

ህወሃት ያልሆኑቱ የኢህአዴግ የቀድሞ ባለስልጣናት ከቀናቸው እንደ እነ ኤርሚያስ ለገሰ፣ጁነዲን ሳዶ፣ኡሞድ ኦቦንግ ሃገር ጥለው ይሰደዳሉ፡፡እንደ ታምራት ላይኔ ያሉት ደግሞ ሁለት ዲጅት ቁጥር አመት እስር ቤት እንዲያሳልፉ ይሆናል፣ ሌ/ጄ አሳምነው ፅጌን፣ጄ/ል ተፈራ ማሞን ያገኘ ያገኛቸዋል፡፡ህወሃት ሆነው እስር ቤት የገቡት ስየ አብርሃ እና ወልደስላሴ የተባሉ ሰዎች እስራቸው የሌሎቹን የኢህዴግ አባላት ታሳሪዎች ያህል የልረዘመ ካለመሆኑም ባሻገር ከእስር ሲወጡ የገጠማቸው እድል እንደ ሌሎቹ ጡረታ ተከልክሎ፣ከመኖሪያቤት ተፈናቅሎ በመዋጮ የመኖር እጣ አይደለም፡፡ ትክክለኛው ለህወሃቶቹ የተደረገው ነው፡፡አንድ ወቅት በመንግስተዊ አስተዳደር መሰላ ውስጥ ሆኖ ሲያገለግል የኖረ ሰው በሃሳብ ተለየ ተብሎ ልጆቹን የሚያበላው እህል ውሃ፣ ጎኑን የሚያሳርፍበት ቤት እስከሚያጣ ድረስ መበቀል መንግስትነትን አይመጥንም፡፡

በጎ ባልሆነው ህወሃት ዘመን ሳይቀር በጎ የሆነላቸው ጄ/ል ፃድቃን በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ የሚሰጧቸውን አስተያየቶች እከታተላለሁ፡፡ብዙ ጊዜ በሚሰጧቸው ሃሳቦች ላይ ልዩነቶች አሉኝ፡፡በሃሳቦቻቸው ውስጥ የህይወት ልምዳቸውን የሚመጥን ሚዛናዊነት አጣለሁ፡፡ ሚዛናዊ ለመምሰል የሚወረውሯቸው አንዳንድ ሃሳቦች ቢኖሩም አፍታም ሳይቆዩ ወደ ህወሃት ዘመም ዘመም ሲሉ ይገጥመኛል፡፡የትግራይን ህዝብ ከሰው የተለየ ፍላጎት ያለው፣ከህግ በላይ የመሆን መብት የተሰጠው፣የተለየ እንክብካቤ የሚገባው ልዩ ፍጡር አድርገው የያቀርቡት ነገር አይዋጥልኝም፡፡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ 15/12/2010 በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በወጣው ቃለ ምልልሳቸው የተናገሩት ይህንኑ ነው፡፡

በቃለ ምልልሱ ላይ እርስበርስ የሚጋጩ ብዙ ሃሳቦችን አስተውያለሁ፡፡ይህ የሆነው ፃድቃን በእውነት በሚያምኑት እና መስለው መታየት በሚፈልጉት ነገር መሃል ባለ መጋጨት ነው፡፡ አስተውሎ ለተከታተለው ግን ፃድቃንም ሆኑ ባልንጀራቸው ጄ/ል አበበ ተክለሃይማኖት የህወሃትን የበላይነት አይጠሉትም፡፡የትግራይን ህዝብ የተለየ ህዝብ አድርጎ ከማየቱን ዘረኝነት ወለድ እበልጣለሁ ባይነት የተዋጁ ሰዎችም አይደሉም፡፡ ይህን ያስባለኝ ምክንያቴ በብዙ ቦታዎች ካደረጓቸው ቃለምልልሶች፣ ከፃፏቸው ፅሁፎች የታዘብኩ ቢሆንም ለዛሬ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከተናገሩት ብቻ እያነሳሁ ላስረዳ፡፡

አሁን ለመጣው ለውጥ መፅናት መንግስት በሰላማዊ ተፎካካሪዎች እና ህዝብን በሚያናውጡ ታጣቂዎች መሃል ልዩነት አስምሮ በበጥባጮች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያስቀመጡትን ሃሳብ እጋራለሁ፡፡ያለውን ስጋት ሲያስቀምጡ “….የዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብታቸው አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ይገደላሉ…..” ያሉት ነገር ግን በተለይ ለአማራው ህዝብ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ለሌ/ጄ/ል ፃድቃንም አዲስ ነገር አይመስለኝም፡፡

ወላድ፣እርጉዝ፣ህፃን፣አዋቂ ሳይል ሰባ ምናምን ሽህ ህዝብ አማራነቱ ብቻ ጥፋት ሆኖ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሽፈራው ሽጉጤ በተባለ ባለስልጣን ፊርማ ከጉራፈርዳ ሲባረሩ ፃድቃን ያልሰሙት ጉዳይ አይደለም፡፡የፃድቃን የትግል ጓድ አቶ መለስ ስለዚሁ ጉዳይ ፓርላማ ቀርበው ሲጠየቁ “ደግ አደረግን” አይነት መለስ ሲሰጡ የህዝብ በማንነቱ ብቻ መፈናቀል ስጋት ሆኖባቸው ፃድቃንም ወደ አዲስ አድማስም ሆነ ወደ ማንኛውም ሚዲያ ቀርበው ዛሬ የሚናገሩትን አልተናገሩም፡፡ በዚሁ መከረኛ ህዝብ ላይ በበደኖ እና በአርባ ጉጉ የሆነው ሲሆን ፃድቃን አድራጊ ፈጠሪ የመንግስት ባለስልጣን ነበሩ፤ እኔ በወቅቱ ሚዲያ መከታተል የምችል ሰው ባልሆንም ነገሩን ሲያወግዙ ሰማሁ የሚል ገጥኝ አያውቅም፡፡

በአንፃሩ አብይ በሚመሩት መንግስት ውስጥ የሚደረገውን ማንኛውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያወግዛሉ፡፡የድርጊቱን ፈፃሚዎች ያወግዛሉ፡ይህ ነገር ሲደረግ ዝም ብለው ያዩ የመንግስት አካላትንም ራሳቸውን ከስልጣን እንዲያገሉ እያደረጉ ነው፡፡ የጠፋው የሰው ነፍስ የሚያሳዝን ቢሆንም አብይ ለነገሩ እልባት ለመስጠት ያላቸው ዝንሌ እና ቁርጠኝነት ደግሞ የነገሩ ማብቂያ እንደ ደረሰ ተስፋ የሚያጭር እንጅ ፃድቃን ዛሬ የተጀመረ አድርገው እንደሚያወሩት “እግዚኦ” የሚያስብል ነገር አይመስለኝም፡፡

ሌ/ጄ/ል ፃድቃን ነገሩን አተኩረው እንዲያዩት፣በሚዲያም መጥተው አፅኖት እንዲሰጡት ያደረጋቸውም ምናልባት ህወሃት እሳቸውም አባል በነበሩበት ወቅት ማኒፌስቶ ፅፎ ጠላቴ ነው ላለው የአማራ ህዝብ የደገሰው የማፈናቀል፣የማሳደድ፣መገደል ክፉ ድግስ ዛሬ ህወሃት ጠመንጃውን ታቅፎ ከኖረበት መንበሩ ሲጠፋ “ህዝቤ” ለሚለው የትግራይ ህዝብም የተረፈ ስለመሰላቸው ይሆናል፡፡ለዚህ ማስረጃው ፃድቃን ስጋታቸውን ሲያስረግጡ ጣና በለስ ላይ ስለሞቱ ሁለት ሰዎች (እነዚህ ሰዎች ትግሬዎች ናቸው የሚል ወሬ ሲናፈስ ሰንብቷል) ማንሳታቸው፣በተደጋጋሚ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንደሚያሳስባቸው መናገራቸው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ማንነትን ማዕከል አድርጎ መሞት የተጀመረው ዛሬ አይደለም፡፡ የሰው በማንነቱ መሞት የሚያሳስበው፣በሰው ሁሉ እኩልነት የሚያምን ሰው እሪ የሚለው ድርጊቱ የተጀመረ እለት እንጅ ሄዶ ሄዶ የእሱን ሰፈር ሰዎች ሲያሰጋ መሆን የለበትም፡፡ ጣና በለስ ላይ ሁለት ትግሬዎች ሞቱ ተብሎ ሞት ብርቅ በሆነበት ሃገር የሞቱ ያህል ብዙ ሲባል ሰንብቷል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ነገር አለ፡፡አንደኛ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ምንም አይነት ሰራተኞች እንዳልሞቱበት ለዋዜማ ሬዲዩ ተናግሯል፡፡ሁለተኛ ሰዎቹ ሞቱ በሚባልበት ጊዜ በትግሬነታቸው ብቻ እንደሞቱ ፃድቃንም ሆነ ሌሎቹ አራጋቢ የትግሬ አክቲቪስቶች መረጃቸውን ሲያቀርቡ አልታየም፡፡

በጣም የሚገርመው ፃድቃን በዚሁ በማንነት ምክንያት የመሞትን እና ሌሎች በሃገሪቱ አልፎ አልፎ የሚታዩ ግርግሮችን በተመለከተ የዶ/ር አብይን መንግስት ሊወቅሱ መነሳታቸው ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ ፃድቃን “በአሁኑ ወቅት ህዝብ ብሶቱን እየገለፀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጉዳቱን የሚያመጣው የብሶት አገላለፁ ነው፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ ደግሞ ሁኔታውን ተረድቶ ብሶቱን ከማባባስና ሂደቱን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ ከመግፋት ይልቅ ሁኔታውን ማርገብ ይገባው ነበር፡፡….ቀደም ሲል በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ተሰርቶ ነበር፡፡ የበደሉ፣ የብሶቱ ሁሉ ምንጭ፣ እሱ ነው ተብሎ፣ ውስጥ ለውስጥ በርካታ የፕሮፓጋንዳ ስራ ተሰርቷል። በአንፃሩ፤ ይሄን ፕሮፓጋንዳ የመመከት ስራ አልተሰራም፡፡ ቀደም ሲል የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣንን ይቆጣጠራል ተብሎ የነበረው ኃይል ከቦታው ሲወጣ፣ ለዘመናት የነበሩ ጥላቻዎች ፊት ለፊት እየወጡ ነው ያሉት። ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የጥላቻ ፖለቲካ ደግሞ ለወደፊት በሃገራችን ውስጥ ልንፈጥር የምናስበውን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም የሚበርዝ ነው፡፡ አንደኛውን ወገን ተስፋ የሚያስቆርጡ፣ ጠባሳም ጥለው የሚያልፉ ናቸው፡፡.” (የአፅኖት መስመር የእኔ)፡፡

በፃድቃን አስተሳሰብ የዶ/ር አብይ መንግስት የህዝብን ብሶት እያባባሰ እና ሁኔታውን ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እየመራ ነው፡፡አድማጭ እስኪሰለቻቸው ድረስ በየደረሱበት ሁሉ “የትግራይ ህዝብ እና ህወሃትን ለዩ” እያሉ የሚወተውቱት ጠ/ሚ/ር አብይ የትግራይ ህዝብ ራሱብሎት የማያውቀውን “የትግራይ ህዝብ በህወሃት እንደ ሁላችሁም የተበደለ ነው፣እኔን ከወደዳችሁኝ በዚህ ህዝብ ላይ አንዳች ክፉ እንዳታስቡ” እስከ ማለት የደረሱ ሰው ናቸው፡፡

ይህ ሰው በጠ/ሚነት የሚመሩት ማዕከላዊ መንግስት የህዝብ ብሶት እያባባሰ ነው ባይ ናቸው ፃድቃን ደግሞ፡፡ ሌላው ሌላው ይቅርና አብይን/መንግስታቸውን እንዲህ ብሎ ለመውቀስ ፃድቃን ማኒፌስቶ ፅፎ በአንድ ህዝብ ላይ የሞት አዋጅ ያወጀው ህወሃት አባል ያልሆኑ፣ ለዚሁ ያልሰሩ ሰው መሆን ነበረባቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት በየደረሱበት ስራየ ብሎ “የትግራይን ህዝብ እባካችሁ አትጥሉት፣ ምስኪን ደሃ ህዝብ ነው፣ ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ አይደለም” እያሉ በሃገር ውስጥ ሆነ በውጭ መድረክ ፣በአደባባይ ሰልፍ ሆነ በቤት ውስጥ ውይይት ሁሉ መወትወት ፃድቃን “በትግራይ ህዝብ ላይ ተነጣጥሮ ተሰራ” የሚሉትን ፕሮፖጋንዳ የመመከት ስራ አይደለም፡፡ዶ/ር አብይንም ሆነ መንግስታቸውን በዚህ መውቀስ አንድም ትልቅ ፍርደ ገምድልነት፤ሁለትም “ዘር ማንዘሬን ሰብስባችሁ በአንቀልባ እዘሉልኝ” አይነት ነገር ነው፡፡

በበኩሌ አንድም ሁለትም ትግሬ ‘እንዲህ በተባለ ሃገር ሞተ’ የሚለው ነገር በማስረጃ ተረጋግጦ ቢያንስ ሞቱ የተባሉት ሰዎች ፎቶ በማህበራዊ ድህረገፅ ሲቀርብ፣ ዘመዳችን ሞተብን የሚሉ ሰዎች በገለልተኛ ሚዲያ ቀርበው ስለ ሁኔታው ሲያወሩ ሰምቼ አላውቅም፡፡በአንፃሩ ህወሃት በማንነታቸው ሲያስር ሲገድል ሲያፈናቅላቸው የነበሩ ሰዎች በየሚዲያው ሲቀርቡ ከራሳቸው አንደበት ብሶታቸውን እንሰማለን፡፡ የትግሬዎቹ ተጎጅዎች ነገር እንዲህ ጥርት ባለ መረጃ ቢቀርብ እኛም ነገሩን የምናወግዘው፣ሃዘኑም የሚሰማን ሰዎች ነን፡፡

ለትግሬ ለማዘን የግድ ትግሬ መሆን አያስፈልግም፡፡ነገር ግን ባልተረጋገጠ ወሬ፣ ሞቱ የተባሉ ሰዎች ይሰሩበት ነበር የተባለው መስሪያቤት ለሚዲያ “የሞተብኝ ሰው የለም” እያለ እየተናገረ ባለበት ሁኔታ፣ የሞተው ሰው ስም ማን ይባላል? ቢባል እንኳን መጥራት በማይቻልበት ነገር ፃድቃንን የሚያክል የእድሜ ዘመን ፖለቲከኛ የትግራይ ህዝብ ሞት ታወጀበት ብሎ ማውራት በማንነቱ ሲሞት በኖረው ህዝብላይ መቀለድ ነው፡፡

እንደማንኛውም የትግሬ ፖለቲከኛ ፃድቃን የመሃል ሃገር ሰው ትግሬ ወገኖቹን ለማጥፋት ዘመቻ እንደ ጀመረ አፋቸውን ሞልተው ያወራሉ፡፡ይሄ መዓት መጥራት በትግሬ ፖለቲከኞች ዘንድ የተለመደ፣ይበልጥ የተበደሉ አስመስሎ አስቀድሞ በመጮህ የህወሃትን በደል ለመሸፈን የሚሞከርበት አስቀያሚ አካሄድ ነው፡፡ በተረፈ የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በሚያወሩት መጠን በትግራይ ወንድሞቹ ላይ ሴራ አሲሮ አንዳች ክፉ ነገር ለማድረግ የሚያስብ ሆኖ አይደለም፡፡

ፃድቃን ግን ያለምንም የሃላፊነት ስሜት እንዲህ ይላሉ “አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በመሃል ሀገር የሚደረገው ፀረ-ትግራይ እንቅስቃሴ፣ በነበረው ይቀጥል የሚሉትን ኃይሎች የሚያጠናክርና ድጋፍ የሚያስገኝላቸው ነው የሚሆነው፤ ግን በግልፅ በህወሓት ውስጥ ሁለት ኃይሎች ፍትጊያ እያደረጉ ነው……በኋላ ግን በጅምላ የሚፈርጀውና ትግራይ ላይ ያነጣጠረው እንቅስቃሴ ሲመጣ፣ ህዝቡ ለውጡን በስጋትና በጥርጣሬ ለማየት ተገድዷል፡፡…….በየሄድንበት እየተሸማቀቅን ልንኖር ነው ወይ? በሀገራችን ተዘዋውረን ሃብት አፍርተን፣ እንደ ማንም ሰው መብታችን ተጠብቆ በስርአት መኖር ልንከለከል ነው ወይ? የሚል ስጋት አለው፡፡ ለዚህ ስጋት ደግሞ ዋናው ምክንያት በየአካባቢው የትግራይ ህዝብ ዒላማ እየተደረገ፣ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት የመንጋ ፖለቲካ ነው።” መሃል ሃገር የት ቦታ የተጀመረ፣ ምን በሚባል ስም ስለሚጠራ፣በነማን ስለሚመራ ፀረ-ትግራይ እንደቅስቃሴ እንደሆነ የሚያወሩት አልገባኝም፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ምክንያት ሰለባ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ስንት እንደሆኑ፣የት ቦታ ምን እንደደረሰባቸው በተጨባጭ ያስረዱን ይሆን? ይህ ጥያቄ በቃለ ምልልሱ ወቅት ቢነሳ መልካም ነበር፡፡

እውነት እንዲህ ያለ በመሃል ሃገር ሰዎች የሚደረግ እንቅስቃሴ ካለ ለምን ወደ ህግ አልወሰዱትም? ምን እስኪሆን ነው የሚጠበቀው? አሁን በተጨባጭ በደልን አቅርቦ ተበደልኩ ማለት የሚቻልበት ዘመን ነው፡፡ መለስ እና ፃድቃን ይመሩት እንደነበረበት ዘመን ሰው በማንነቱ ምክንያት በገደል ተወርውሮ፣ ሆዱ በጦር ተቀዶ፣ወለል በሌለው ጥልቅ ውስጥ ከነነፍሱ ተጥሎ ዝም የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡ በተጨባጭ በደል ካለ ማስረጃ ይዞ መቅረብ ነው፡፡የማይጨበጥ ነገር እያነሱ ማውራት ግን ዘር ማንዘሬ ለምን ከስልጣን ሰገነት ጠፋ የምትል አደባባይ የማትወጣ ምክንያት የምትገፋው ማላዘን ነው የሚሆነው፡፡

በህወሃት መንደር የደረሰ ሰው መቼም እፍረት የለውምና ፃድቃን ወደ አንድ ህዝብ ላይ ያተኮረ ጥላቻ ለወደፊቱ ሃገራዊ አንድነት ችግር እንዳለው ኮራ ብለው ይናገራሉ፡፡በመጀመሪያ ወደ አንድ ህዝብ ያተኮረ የሚሉት ጥላቻ የትኛው ነው? ይሄኔ እኔም በዚህ ፅሁፍ እሳቸው የተናገሩትን በመሞገቴ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥላቻ እንደምሰብክ እያሰቡ ይሆናል፤በዚህ የሚስማማ የወንዝ ልጅም አይጠፋም፡፡

“የትግራይ ህዝብ እውነት ህወሃት እንደ በደለው ካሰበ ለምን ተቃውሞውን አይገልፅም፣ለምን በስሙ ሲነገድ ዝም ይላል፣ ለምን እኛን ወገኖቹን አግዞን ሁላችንም ከህወሃት ግፈኛ አገዛዝ ነፃ እንድንወጣ አይሆንም?” ማለት በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የጥቃት ፕሮፖጋንዳ ከሆነ ማኒፌስቶ ፅፎ አንድን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ ሃያ ሰባት አመት ሲያስገድሉ መኖር ምን ሊባል ነው? ወይስ የትግሬ ነፍስ ልዩ፤ ሞቱም እጥፍ ነው? የትግራይን ህዝብ አትንኩት እያሉ በየደረሱበት በሚማልዱት አብይ ዘመን ቀርቶ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪም ያለ አንዳች እፍረት በአንድ ህዝብ ላይ ሞት ሲያውጅ፣ገድሎ ሲያስገድል፣ሰድቦ ሲያሰድብ በነበረው መለስ ዜናዊ ዘመንም ተኑሯል፡፡

ዛሬ ደርሰው የሰብአዊነት ዘበኛ ሊሆኑ የሚቃጣቸው ፃድቃንም ጠመንጃቸውን አንግበው ይህንኑ የሞት አዋጅ ሲያስፈፅሙ የኖሩ ሰው መሆናቸውን ሌላው ቢረሳ የውሻ ሞት ሲሞት ከኖረው የአማራ ህዝብ የወጣን እኛ አንረሳውም! ጅብ እንኳን ቁርበት አንጥፉልኝ የሚለው በማያውቁት ሃገር ሄዶ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በሚታወቅበት ሃገር ቁጭ ብሎ ደርሶ ሩህሩህ፣ብድግ ብሎ የሰብዓዊነት ዘብ ሲሆን የሚስገምተው ራሱን ነው፡፡

አንድን ህዝብ ነጥሎ ማጥቃት ተጎጅውን ህዝብ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ያሉት ፃድቃን ይህ ዛሬ ለምን እንደገባቸው ግልፅ ቢሆንም ሃሳቡ እውነት ነው፡፡በማንነቱ ብቻ እንደውሻ በየሜዳው ሲገድሉት፣በየእስርቤቱ ሰውነቱን ሲተለትሉት፣አእምሮውን በርካሽ አንደበታቸው ሲያደሙት የኖረው አማራ የሚወደውን ኢትዮጵያዊነቱን ድርድር ውስጥ አሰገብቶ በማያውቀው የጎጥ ከረጢት ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ፃድቃን ጭምር ታጥቀው የሰሩበት ዘር ተኮር ጥቃት ተስፋ አስቆርጦት ነው፡፡ በዘር ማንነት ምክንያት የመገለል፣ከሰው ተለይቶ የመክፋፋት፣በሃገር ዳርቻ የመሳደድ ጠባሳውም በሁላችንም አእምሮ ውስጥ አለ፡፡አሁን በወንበሩ ላይ ያሉት መለስ ሳይሆኑ አብይ መሆናቸው ነው ተስፋን የሚያሰንቀው መልካሙ ዜና!
ሌ/ጄ ፃድቃን ስለ ትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ስሜት የተናገሩት ካሉት ነገር ሁሉ ይበልጥ ያደናገረኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፃድቃን ስንቱን ትግሬ አናግረው ምን ያለ ጥናት አድርገው እንዲህ የአንድ ክልልን ሰው ሁሉ ስሜት ማውራት እንደቻሉ ጥያቄ ነው፡፡ሲቀጥል ስብሰባ ለማድረግ ስሄድ ካየሁት ትዝብቴ ተነስቼ የተገነዘብኩት እያሉ የሚያወሩት ነገር እውነት የትግራይን ህዝብ ስሜት የሚወክል ከሆነ አሳሳቢ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ቁጣው ነዷል የሚሉት ፃድቃን የቁጣውን ምክንያት እንዲህ ያስረዳሉ “ቁጣው ምንድን ነው? ከተባለ፣ መሪዎች አጥፍተው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከትግራይ የወጡ መሪዎችን ጥፋት መነሻ በማድረግ፣ የህዝቡን መስዋዕትነት ማራከስ፣ እንደ እላፊ ተጠቃሚ መቆጠር ህዝቡ ውስጥ ቁጣ እየፈጠረ ነው፡፡ የዲሞክራሲ እጦትና የመልካም አስተዳደር ችግር ከየትኛውም የሀገሪቱ ክልል በትግራይ የባሰ ሆኖ ሳለ፣ እላፊ የስርአቱ ተጠቃሚ ተደርገን በጅምላ መፈረጃችንና የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ መሆናችን ተገቢ አይደለም ከሚል የመነጨ ቁጣ ህዝቡ ውስጥ እንዳለ መረዳት ይቻላል። ለውለታችን ምላሽ ይሄ ነው ወይ የሚል ቁጣ አለ፡፡”

ይህ አባባል እንደተባለው የትግራይ ህዝብ ስሜት ከሆነ የሚያስነሳው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡ ከትግራይ የወጡ ሰዎች ባጠፉት ጥፋት የህዝብን መስዕዋትነት ማራከስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ማን ነው መስዕዋትነታቸውን ያራከሰው? የትግራይን ህዝብ መስዕዋትነት ማክበር ማለት እንደ አቶ ኃ/ማርያም ሶስት ገበያ ህዝብ አስከትሎ፣ኩሽሽ አንገት ላይ ጠምጥሞ ደደቢት በረሃ ወርዶ የጥንቱን የህወሃት የዋሻ ቢሮ መሳለም ነው? የተፈለገው ይህ ከሆነ አብይ አሁን ያሉበት ሃገራዊ ፈተና ይሄን ለማድረግ ጊዜ የሚሰጣቸው አይደለም፡፡በተቀረ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ መቀሌ በሄዱበት ወቅት የሰማዕታት ሃውልት በተባለው ስፍራ ተገኝተው የሚደረገውን አድርገው ነው የተመለሱት፡፡

ከዚህ በላይ ምን መደረግ ነበረበት? እውነት እንነጋገር ከተባለ ልጅ ያልሞተበት ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የትግራይ ህዝብስ ለሞቱት ልጆቹ ሃውልት አቁሞ የመጣው ሁሉ ለቅሶ እደረሰ ነው፡፡ እነዚህ የትግራይ ሰማዕታት የገደሏቸው የሌላው ኢትዮጵያዊ ልጆች ግን መታሰቢያ እንኳን የቆመላቸው አይደሉም፡፡ የሞቱለት አላማ ቢመረመር ደግሞ የማናቸውም ሞት ለኢትዮጵያ የተሻለ ቀን አላመጣም፡፡ስንሞትም ስንቆምም እንበልጣለን ካልተባለ በቀር!

የዲሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር እጦቱ በትግራይ ይብሳል ለሚለው የባሰው ሰው ተነስቶ ታግሎ ቀንበሩን ያሽቀነጥራል፡፡የትግራይ ህዝብ ደግሞ ለዚህ የታወቀ ነው፡፡ደርግን ለመታገል አንድ አመት አልጠበቀም፡፡ደርግ ተስተካክሎ ወንበሩ ላይ ሳይቀመጥ ነው ህወሃት ወደ ጫካ የገባው፣የትግራይ ህዝብም ትግሉን የተቀላቀለው፡፡አሁን ህወሃት በደለኛ ነው ከተባለም ተመሳሳዩን ለማድረግ አፈናው ከለከለ የሚለው ለኔ በግሌ አይዋጥልኝም፡፡ ኦሮሞ የመታገያው ሜዳ እነሆ ተብሎ ተሰጥቶት አይደለም “ሆ!” ብሎ ወጥቶ የሞተው ሞቶ የተረፈው የተሻለ ስርዓት ለማየት የበቃው፡፡ አማራ የልጁ ደም ጣናን ሲያቀላ እያየ ነው ሲታገል የነበረው፣ኮንሶው፣ጉራጌው፣አፋሩ ወዘተ መንግስት እየደጎመው አይደለም በቻለው ሁሉ ሲታገል የነበረው፡፡

ሰው ተበድያለሁ ብሎ ያሰበውን ያህል ይታገላል፡፡እውነቱ ያ ነው! መበደል ብቻውን ቁምነገር አይደለም፤ለትግል እኩል አስፈላጊው ነገር ተበዳዩ በደልን የመቁጠር ጭካኔ ላይ ደርሷል ወይ የሚለው ነው፡፡ ህወሃት የትግይራን ህዝብ እንደሚበድል ይታወቃል፡፡ ጥያቄው የትግራይ ህዝብ የደርግን በደል ይቆጥር በነበረበት መንገድ የህወሃትን በደል ይቆጥራል ወይ? የሚለው ነው፡፡ይህን በተመለከተ ፃድቃን ራሳቸው በዚሁ ቃለመጠይቃቸው”የትግራይ ህዝብ ከፈለገ ህወሓትን ያጎለብታል፤ ካስፈለገው ደግሞ ይገድለዋል” ሲሉ ጨርሰውታል፡፡
የትግራይ ህዝብ ለሌላው ህዝብ ውለታ ውያለሁ፤የውለታየ ምላሽስ ይህ ነው ወይ እያለ ያዝናል ይቆጣል የተባለው ነገር ግራ አጋቢ ነው፡፡ውለታ የተባለው እነዚሁ ዘወትር የሚነሱት ስልሳ ምናምን የትግራይ ሰዎች ህወሃትን ወግነው ደርግን ሲታገሉ መሞታቸው መሰለኝ፡፡ ህወሃት ትግራይን እገነጥላለሁ እያለ በነበረበት ዘመን ትግራይን ለመገንጠል የሞቱት ሰዎች ውለታቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የሆነበት መንገድ አልገባኝም፡፡ህወሃት ብድግ ብሎ “ትግራይን መገንጠሉን ትቼዋለሁ” ሲል ደግሞ “ታዲያ ለምን እንዋጋለን?” እስከማለት ተደርሶ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ፤ አቶ መለስም በዚህ ጉዳይ ተቸግረው እንደሆነ በራሳቸው በአንደበት ተናግረዋል፡፡መለስ እንደምንም ብለው አሳምነዋቸው ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ የሞቱት ደግሞ የሞቱለት ስርዓት ሲዘርፈን፣ሲገድለን፣ሲያሰድደን ኖረ እንጅ ውለታቸውን እንቆጥር ዘንድ ዲሞክራሲን አላመጣልንም፡፡በአጭሩ የማንም ውለታ የለብንም!

“[ኢትዮ-ሶማሌ ክልል] ሶማሌ ውስጥ የተደረገው ነገር ትግራይ ውስጥ ሊመጣ እንደሚችል ወጣቱ ይነገረዋል፤ በዚህም ይሰጋል።የትግራይ ህዝብ በትግሉና በመስዋዕትነቱ ያገኘውን መብት ማንም ሰው መጥቶ እንዲድጠው አይፈልግም።ከውስጡ የወጡት አጥፊ ኃይሎችንም ቢሆን ራሱ ሊቀጣቸው ይፈልጋል እንጂ በሌላ ኃይል ተድጠው፣ አንተ የትም አትደርስም የሚል መልዕክት እንዲተላለፍለት አይፈልግም፡፡ጥፋት ያጠፉ ካሉ በህገ መንግሥቱ መሰረት ይስተካከል እንጂ ኃይል ያለው ሁሉ በዘፈቀደ ከህግ ውጪ፣ እኛን ወደ ጎን ትቶ ለውጥ አመጣለሁ የሚል ከሆነ፣ የኛን ክብርና ማንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” የሚል ነገር ይፈጠራል፡፡” ይላሉ ፃድቃን በሌላ ንግግራቸው፡፡

ኢትዮ-ሶማሌ ክልል ውስጥ ምን ሆነ? ህወሃት ቀብቶ በህዝብ ላይ የጫነው፣አንድ ሚሊዮን ህዝብ ሲያፈናቅል ቅር የማይለው፣የራሱን ህዝብ እስርቤት ከቶ መከራ የሚያሳይ፣ሃገር ያስመረረ አብዲ ኢሌ የሚባል ወንበዴ የኢትዮ-ሱማሌ ህዝብ አዲስ አበባ ድረስ ተጉዞ አቤት በማለቱ ሳቢያ ከስልጣን እንዲነሳ ህጋዊ መንገድ እንዲጀመር ሲጠየቅ አሻፈረኝ ብሎ ህዝብ አስጨረሰ፣ የእምነት ቦታዎችን በተላላኪዎቹ አወደመ በስተመጨረሻው ተያዘ፡፡ይሄ እንዴት ነው በትግራይ የሚደገመው? በማዕከላዊ መንግስቱ የሚፈለጉ የትግራይ ተወላጅ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ ባለስልጣናት ትግራይ መሽገው የክልሉ መንግስት ደግሞ ለወንጀለኛ ከለላ የሰጠ እንደሆን ነው፡፡

ስለዚህ ይህ እንዳይሆን ማድረግ የሚችለው የትግራይ ህዝብ እና የክልሉ መንግስት ነው፡፡ቀላሉ መንገድ ትግራይ የከተሙ ተጠርጣሪ ወንጀለኛ የቀድሞ ባለስልጣናት የፍርድቤት ጥሪ አክብረው በህግ ፊት እንዲቀርቡ ማድረግ ነው፡፡እነዚህ ሰዎች ጥፋተኛ መሆን አለመሆናቸውን የሚመረምረው የወጡበት ጎሳ የቤተ-ዘመድ ጉባኤ አይደለምና ፃድቃን እንደሚሉት የትግራይ ህዝብ “ተጠርጣሪዎቹ ካጠፉም እኔ ልቅጣቸው” የማለት መብት ፈፅሞ የለውም! ፍርድቤት ችሎት ላይ ተቀምጦ የጎሳውን ሰው የክስ መዝገብ የመረመረ ህዝብ በዓለም ላይ ታይቶ ስለማይታወቅ የትግራይን ህዝብ ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም፡፡

ትግሬ የሆነ የቀድሞ ባለስልጣን የኢትዮጵያ ፍርድቤት ቀርቦ በመጠየቁ የሚጎድል የትግራይ ህዝብ ክብር የለም፡፡እንዲህ መታሰቡ ራሱ ስህተት ነው፡፡ ‘እኛን ወደጎን ትቶ ለውጥ ማምጣት አይቻለም’ ማለትስ ምን ማለት ነው? የትኛው ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ስልጣን ላይ እንደወጣ ነው የትግራይ ህዝብ ሁሉ ተሰብስቦ ወንበር ላይ የሚወጣው? ወይስ የትግራይ ህዝብ አልተገለለም እንዲባል የኢትዮጵያ ህዝብ ዘላለሙን በህወሃት ጊንጥ ሲገረፍ መኖር አለበት? ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት እኛን ያልጨመረ፣ግልፅ ያልሆነ ነው ማለትስ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሁለት ሃገሮች በሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ ድርድር የትኛው ጎሳ ነው መሃላቸው ቁጭ ብሎ የድርድር አካል የሆነው? መለስ ዜናዊ “ይባኝ ሳልል የምትሉትን እቀበላለሁ” ብሎ መሬቱን ሲያስረክብ “እኛን አላማከርክም” ተብሎ ነበር?

የህወሃት ማኒፌስቶ ግልባጭ የሆነው ህገ-መንግስትም በትግራይ ህዝብ ዘንድ አለው ስለተባለው ትልቅ ቦታ እንዲህ ብለዋል ፃድቃን “የትግራይ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ህገ-መንግስት እንደ ዋስትና ያየዋል፡፡አንቀፅ 39ን እንደ ዋስትና ነው የሚመለከተው፡፡ ይህ ሲባል በኢትዮጵያዊነት ይደራደራል ማለት አይደለም። ራሱን ከኢትዮጵያዊነት ነው የሚያስተሳስረው። ኢትዮጵያዊነት ከደሙና ከአጥንቱ ጋር የተዋሃደ፣ ታሪኩም ነው፡፡ የመነጠል ፍላጎት ትግራይ ውስጥ የለም፡፡ ነገር ግን አንቀፁ ዋስትና ይሰጣል፣ መብትን ለማስከበር ይረዳል ብሎ ያምናል፡፡ የትግራይ ህዝብ፣ ህገ መንግስቱ ይከበር ሲል ከዚህ አንፃር ነው፡፡”

ህወሃት ጠላቴ የሚለውን የአማራ ህዝብ አግልሎ፣በአመዛኙ እንደ እሱው የአማራን ህዝብ በመጥላት በሽታ የታወሩ የጎሳ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ ያወጣው ህገ-መንግስት ለትግራይ ህዝብ እንደክታብ አንገት ላይ የሚታሰር በስስት የሚታይ ክቡር ነገር ነው- እንደ ፃድቃን ገለፃ፡፡ህወሃት በሌሎች ላይ ላይ ያልተገበረው ምናልባት ስልጣኑን ያጣ እለት ኤርትራ ፊት ከሰጠቸው ትግራይን ገንጥሎ በሚወደው የገዥነት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ሲል ያስቀመጠው አንቀፅ 39 ለትግራይ ህዝብ ዋስትና መሆኑ እውነት ከሆነ፤ ስለትግራይ ህዝብ እና ህወሃት ልዩነት ፃድቃን ሲያወሩ የዋሉት ሁሉ ማሞ ቂሎ ብቻ የሚያምነው ተረት ነው የሚሆነው፡፡ ለማንኛውም የትግራይ ህዝብ የሚሰስትለት ህገ-መንግስት የአማራ ህዝብን እንደ ዘውግ ያገለለ፣ ከሁለት ዘውግ ለተወለዱ ኢትዮጵያዊያን ቦታ የሌለው እና ራሳቸውን እንደ ኢትጵያዊ ዜጋ ብቻ የሚገልፁ ሰዎችን የማያውቅ በመሆኑ ሌላው ህዝብ እንደ ትግራይ ህዝብ በእንስፍሳፌ ሊወደው እንደማይችል ሌላው ሌላው ቢጠፋው ፖለቲካ አዋቂ ነኝ የሚሉት ፃድቃን አይጠፋቸውምና ለወገኖቻቸው ማስረዳት ይኖርባቸዋል፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena.com ይላኩልን።

የፀጥታ ፈተናችን አንድ መፍትሄ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

(በመስከረም አበራ)

ሐምሌ 30 ፤ 2010 ዓ.ም.

ሃገራችን አሁን ያለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ህወሃት በሌለበት ብቻ ሊከሰቱ የሚችል በጎ ነገሮችን እያስተናገደ ነው፡፡ይህ ሁሉ በጎ ነገር ህወሃት ከአድራጊ ፈጣሪነቱ እውነትም ገሸሽ እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ዶ/ር አብይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያመጣውን የኢህአዴግ ውስጠ-ፖርቲ ንጠት ከኋላ ሆነው መንዳት የሚወዱት ህወሃቶች ስንጣሪ አካል ይኖርበት ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ስለዚህ የለውጥ እንቅስቃሴው የህዝብን እውነተኛ ፍላጎት ያነገቡ ሰዎች የሚመሩት ነው ብሎ ለመቀበል ወሳኝ ፖለቲካዊ እርምጃዎች እስኪወሰዱ መጠበቅ ግድ ነበር፡፡አሁን ላይ ያለው ፖለቲካዊ ድባብ ከሞላ ጎደል የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ፣ይሆናል ብለን ካሰብነው በላይ መሪዎች የሃገርን ፈተና ለማቅለል እየጣሩ ያለበት ነው፡፡

የሃገራችንን ፖለቲካዊ ታሪክ ሲፈትን የነበረው፣መጋደልን ብቻ መፍትሄ አድርጎ የኖረው በተፃራሪ ፖለቲካ ሃይሎች መሃከል የነበረው ግንኙነት ዶ/ር አብይ/ቲም ለማ ምስጋና ይግባቸውና ወደ ሰለጠነ ቁጭ ብሎ የመነጋገር ዘይቤ ተሸሽሏል፡፡ይህ ራመድ ያለ ጅማሬ በጣም አስደሳች እና ተስፋ ሰጭ ነው፡፡በተፃራሪ የፖለቲካ ቡድኖች መሃከል የኖረው ያልሰለጠነ መስተጋብር የሃገራችን ፖለቲካ ውስብስቦሽ ትልቁ ምንጭ ነበር፡፡ የሃገራችንን የፖለቲካ ለሌሊት ያስረዘመውም እሱው ነበር፡፡ ይህን ክፉ ምዕራፍ ለመዝጋት ፍላጎት ያሳየው የዶ/ር አብይ/ቲም ለማ ስብስብ በሃገሪቱ ፖለቲካዊ ታሪክ መዝገብ ላይ ድንቅ አሻራ አስቀምጧል፡፡

የሃገራችን ሁለንተናዊ ችግር መንስኤው የደደረው ፖለቲካዊ ችግራችን በመሆኑ ፖለቲካዊ ችግሩን ሊፈታ ላይ ታች የሚለው የዶ/ር አብይ ቡድን በኢኮኖሚው፣በማህበራዊ ዘርፉ፣በውጭ ግንኑነቱ ሁሉ ከቀደምቶቹ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተስፋ ተጥሎበታል፤አያያዙም መልካም ነው፡፡ በህዝብ ዘንድ ያተረፈው አመኔታ ለስኬት ተስፋው ስንቅ ነው፡፡ሁሉን እኔ ልፍጄው ከሚለው የቀደምት መሪዎች ዘይቤ ወጥተው “መምራት እንጅ መንዳት አልፈልግም” ያሉት ዶ/ር አብይ ዘመኑን የሚመጥኑ መሪ ናቸው፡፡መምራትን እንጅ መንዳትን ያልመረጡት አብይ መልካምን እድል መርጠዋል፡፡

መንዳትን የሚመርጡት ቀደምቶቻቸው ሁሉን አውቃለሁ ባዮች ናቸውና በህዝብ ላይ በር ዘግተው ሁሉን ያደርጋሉ፡፡ስለዚህ ለሚመጣው ጥፋትም ሆነ ልማት ሃላፊዎቹም ራሳቸው ናቸው፡፡ መንዳት ያልወደዱት ዘመናዊው አብይ ግን በእድሜም በእውቀትም የሚልቋቸው ታላላቆች መኖራቸውን ያምናሉ፡፡ሁሉም ለሃገሩ የሚመበጅ ስንቅ ቋጥሮ ሳለ አሰባሳቢ ፖለቲካዊ ምህዳር በመጥፋቱ ብቻ ሃገር ብዙ እንደ ከሰረች ይገነዘባሉ፤ይህንኑ በየደረሱበት ይሰብካሉ፡፡ከመቅፅበት ታዳሚወቻቸውን ሁሉ ደቀ-መዘሙር የሚያደርግ የመሪነት ብልሃት አላቸው፡፡አድማጭን ያከብራሉ፡፡ከህዝብ እንደ አንዱ ያወራሉ፡፡ይህ መሰለኝ “መሪ እንጅ ነጅ አይደለሁም” ያሉለት ማንነታቸው፡፡መሪ ደግሞ ችግሩንም ቱርፋተንም ለተከታዮቹ አቅርቦ ‘ምን እናድርግ?’ ይላልና እንደ ነጅው በር ዘግቶ ብቻውን ሲፋትር ከችግር ጋር ሞቶ አይገኝም፡፡የመሪ ጉዳይ ሁሉ የተከታየቹም ጉዳይ ነው፡፡

መሪ የመሆንን መልም እድል የመረጡት ዶ/ር አብይ ወቅታዊ ችግር የሃገር ፀጥታ እና ደህንነት ነው፡፡ የሃገራችን ፀጥታ እና ደህንነት ደግሞ በህወሃት የቤተ-ዘመድ ገመድ እጅጉን ተተብትቦ የነበረ ዘርፍ ነው፡፡በዚሁ ዘይቤ ለሃምሳ አመት ሊገዛ ሲያሰላ የኖረው ህወሃት ያላሰበውን ለውጥ ተከትሎ ከዋነኛው እርስቱ በመነሳቱ ጥርስ የሚያፋጭ ነው፡፡ ሃገር ሰላም ውሎ ቢያድር የሚመኝም አይመስልም፡፡ ጭራሽ በተቃራኒው ሊሰራም ይችላል፡፡

ለዚህ የተመቼው ደግሞ የሃገር ባለቤት ሆኖ የፀጥታ እና ደህንነት መስኩን በሚዘውረበት ዘመን ከእርሱ ዘውግ ያልሆኑ የውትድርና ሳይንስ ልሂቃን እና ሃገር ወዳዶችን ክብር በሚነካ መንገድ ሞራላቸውን ሰብሮ፣ማዕረጋቸውን ነጥቆ፣ እስር ቤት ወርውሮ፣ከሃገር አባሮ የእለት ጉርስ እስኪያጡ ድረስ ያጎሳቆላቸው በርካታ መሆናቸው ነው፡፡ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ለተወሰኑት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ቢያንስ ጡረታቸውን እና ማዕረጋቸውን መልሰው እንዲያገኙ በማድረግ በጎነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡

እንደሚታወቀው ህወሃት ሃገሪቱን በሚዘውርበት ዘመን በሰለጠነ የሰው ሃይል ድርቅ ካስመታቸው የሃገሪቱ መስኮች አንዱ የውትድርናው እና ፀጥታው መስክ ነው፡፡ዘራቸው እንጅ እውቀታቸው ከቁብ ሳይገባ በሚያሳዝን ሁኔታ ከሙያ ገበታቸው እንዲገለሉ የተደረጉ በርካታ የውትድርናው ሳይንስ ምሁራን ሃገርቤትም በውጭ ሃገርም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አንድም በጡረታ ሁለትም በሽብር ወይ በሌላ ስም ተለጥፎባቸው ነው ሃገራቸውን በሙያቸው እንዳያገለግሉ የተደረጉት፡፡ በውጭም ሆነ በሃገርቤት ያሉ እነዚህ ወታደራዊ መኮንኖች ለሃገራቸው በጣም የሚያስፈልጉበት ሰዓት አሁን ነው፡፡

የዶ/ር አብይ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ለገባበት የሃገር ፀጥታ እና ደህንነት የማስከበር ፈተና እነዚህ ሰዎች ሁነኛ መፍትሄ ይመስሉኛል፡፡ ስለዚህ አብይ ለፖለቲካዊው ፈውስ ጉምቱ ፖለቲከኞች ሃገራቸው ገብተው እንዲሰሩ በጋበዙበት ሁኔታ ለተሰዳጅ ወታደራዊ ሳይንስ ምሁራንን እና ባለሙያዎችንም ተመሳሳይ ጥሪ ማድረግ አለባቸው፡፡የቀድሞው ዘረኛና አግላይ አስተዳደር ያለ አግባብ ተገፍትረው ለስደት የተዳረጉ የውትድርናው መስክ ምሁራን ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ውጥንቅጡ እዳይወጣ የሚያስፈራውን የሃገራችንን የፀጥታ ሁኔታ መልክ እንዲያስይዙ ሊጋበዙ ያስፈልጋል፡፡

ይህ ግብዣ በደርግ ስርዓት ለሃገራቸው ሲያገለግሉ የነበሩ የጤናቸው እና የእድሜያቸው ሁኔታ ለአሁኑ የሃገር ጥሪ መልስ በሚያሰጥ ሁኔታ ያሉትንም የሚጨምር መሆን አለበት፡፡ ይህን ጥሪ ማድረጉን ቀላል የሚያደርገው ደግሞ አብዛኞቹ ተሰዳጅ ወታደራዊ ምሁራን በየዘርፋቸው ማህበር ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ዶ/ር አብይ እነዚህን መኮንኖች በመጥራቱ ካመኑበት በማህበራቸው በኩል ማናገሩ አካሄዱን ቀላልም መደበኛም ያደርግላቸዋል፡፡

በተመሳሳይ እንደ ጀነራል ሳሞራ ያሉ አዛውንቶች ስልጣን በስልጣን ላይ ማዕረግ በማዕረግ ላይ ሲጨመርላቸው በእድሜም ሆነ በአካላዊ ብቃት ከእነርሱ ወጣት የሚሆኑት ሰዎች ዘራቸው እድሜ ሆኖ ተቆጥሮ በጡረታ እንዲገለሉ ተደርገው ሃገርቤት በችግር እና በቁጭት እንደሚኖሩ ከዶ/ር አብይ የተሰወረ አይደለም፡፡እነዚህ ወታደሮች ይህ ሁሉ የደረሰባቸው ለቀድሞው አስተዳደር የማይመች ነገር ስለተገኘባቸው፣ከግፍ ጋር አናብርም ስላሉ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎችን ለመልሶ አገልግሎት ቢጠሩ የቀደመው ከፋፋይ ስርዓት እንዳያንሰራራ በቁጭት እና በትጋት ያገለግላሉ ብየ አስባለሁ፡፡

በወጭ ሃገር ያሉቱ በያሉበት ሃገር ቤተሰብ የመሰረቱ፣ጠለቅ ያለ የኑሮ ስር ያላቸው ሊሆኑ ስለሚችሉ በዚህ ወሳኝ እና አስቸኳይ ሰዓት ጓዝ ጠቅልሎ ወደ ሃገርቤት መምጣቱ የሚያስቸግራቸው ቢሆን እንኳን ቤተሰባቸውን በሚመቻቸው ቦታ አድርገው እነርሱ ለተወሰነ ጊዜ ሃገራቸውን የሚያገለግሉበት ከዛም ተመልሰው ወደመጡበት ሃገር መሄድ ከፈለጉ ይህንኑ እነስከ ማመቻቸት መሄድ ይቻላል፡፡

ይህ በጣም አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ህወሃቶች ስር ሰደውበት የኖሩበት የፀጥታው ክበብ አልፎ አልፎ በዋነኛ ቦታዎች እንኳን በሌላ ካልተተካ ስልጣን መነጠቃቸው ሞት ለሚመስላቸው አኩራፊዎች ቀዳዳ ማስገኘቱ አይቀርምና የሃገሪትን ፀጥታ የማስከበሩን ፈተና ያወሳስበዋል፡፡
የሃገር ፀጥታ ባልተከበረበት ሁኔታ ደግሞ በህወሃቶች እና ጀሌዎቻቸው እንደ ደመኛ ጠላት የሚታዩ የእውነተኛ ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ወደ ሃገርቤት በሚገቡበት ሰዓት እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመስራት የደህንነት ስጋት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ይህ ስጋት ለዶ/ር አብይም የሚቀር አይመስለኝም፡፡የፖለቲካው ፈውስ የሚፀናው ፀጥታ እና ደህንነቱ አስተማማኝ ሲሆን ስለሆነ በዚህ ረገድ ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ በቀድሞው አስተዳደር ገለል የተደረጉ በሳል ወታደራዊ ምሁራንን መጋበዙ አስፈላጊም አንገብጋቢም ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የደህንነት እና ውትድርናው መስክ የተሰገሰጉ ሰዎች እንከናቸው ብዙ ነው፡፡ አንደኛ ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ ትምህርት የቀሰሙ ሳይሆኑ ህወሃትን ሳያሰልሱ በማገልገላቸው ወይ ጎሳቸው ከገዥ ጎሳ ስለሆነ ብቻ በማዕረግ ላይ ማዕረግ የተደረበላቸው ናቸው፡፡ የአስራ ሰባት አመቱ የገበሬ ጦር ሽምቅ ውጊያው ስለሰመረላቸው ብቻ ይሄው የውትድርና ሳይንስ እንደመቅሰም ተቆጥሮ ሰማይ የደረሰ ማዕረግ የተሸከሙ ብዙ ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ከእውቀት ውስንነት ባሻገር አሁን ላለው ለውጥ ታማኝነታቸውም አጠራጣሪ ነው፡፡

የመለስ ዜናዊን ደንነት ለማስጠበቅ የሰው ቆዳ ውስጥ ገብተው መፈተሸ የሚቀራቸው የፀጥታ አካላት ገዳይ በመኪና ቦምብ ጭኖ በህዝብ መሃል አልፎ በመሪ ላይ ሲወረውር አላወቁም ብቻ ሳይሆን ለስኬቱ አልሰሩም ማለት ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ እንዲህ የእውቀትም የታማኝነትም ድርብ እንከን ያለበትን የፀጥታ ዘርፍ ቀደም ሲል ተገፍትረው በወጡ ወታደራዊ ባለሙያዎች መበረዝ ችግሩን በአንዴ ባያጠፋው እንኳን ሊያቃልለው ይችላልና በመንግስት በኩል ቢታሰብበት፡፡
____
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

የ“ሲርት” ፖለቲከኞች (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
ሃምሌ 22 2010 ዓ.ም.

አስራ ሰባት አመት በዱር በገደል የታገሉት ህወሃቶች ደርግን የጣለው የእነሱ ጠመንጃ ብቻውን ይመስላቸዋል፡፡ይሄው ግማሽ እውነት ደግሞ ራሳቸውን ሁሌ ስልጣን ላይ መኖር የተገባቸው፣ አሸናፊነት ብቻ እጣ ፋንታቸው የሆነ ብቸኛ ሃያላን አድርገው እንዲያስቡ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ይህ ስህተት ስህተትን እየወለደ ሄዶ ከስልጣን መውረድ፣ከአድራጊ ፈጣሪነት መጉደል ሊመጣ እንደሚችል እንዳያስቡ እና አሁን ላሉበት ሁኔታ የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዳያደርጉ ከልክሏል፡፡ ጠመንጃ ወደ ስልጣን መምጣት ያስችል ይሆናል እንጅ ስልጣን ላይ እንደማያኖር መረዳት አልሆን ያላቸው ህወሃቶች ባላሰቡት ብቻ ሳይሆን ባላሰብነው መንገድ ብቻቸውን ሃገር ከመዘወሩ ገለል ብለዋል፡፡እውነቱን የተቀበሉት ግን አይመስልም፡፡

እንደ ህወሃት ያለ ሁሉበእጁ ሁሉ በደጁ የሆነ፣ስልጣን ላይ ተወዝቶ ስር የሰደደ ፓርቲ እንዲህ በቀላሉ እንደጉም ብን ብሎ ከመንበር ይታጣል ብሎ መገመቱ ራሱ ከባድ ነበርና ህወሃትም ይህን መቀበል ቢያስቸግረው አይፈረድበትም፡፡ በዚህ ላይ የኢህአዴግን ስጋ ለብሶ ሁሉን የሚያደርገው ህወሃት አጥብቆ ይመካ የነበረው አለቅነቱን በግድ በጫነበት ኢህአዴግ ውስጠ- ፓርቲ አንድነት ነበር፡፡

በህወሃት የበላይነት ሳይነጋገር ተስማምቶ ለጥ ሰጥ ብሎ በሚገዛው የአጋር እና አባል ፓርቲ ካድሬ አስተማማኝ ባርነት አጥብቆ የሚመካው ህወሃት ነግ በእኔ ሳይል በተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደ አክርማ መሰንጠቅ ይስቅ ነበር፡፡በጌታ-ሎሌ ግንኙነቱ የቆመውን ‘ውስጡን ለቄስ’ የነበረውን የፓርቲውን አንድነት የፓርቲ ዲስፕሊን በማጎልበት ይተረጉመው ነበር፡፡ ህወሃት ያለ አባል ፓርቲዎች እኩልነት አንድነት አመጣለሁ ብሎ ማመኑ ድንገት ሞቶ መገኘትን አመጣበት፡፡ ይህን ማመን ህወሃትን ሆነው ሲያስቡት ከባድ ነው፡፡

ህወሃትን የመሰለ ሁሉን በጉልበት ማድረግ የሚቀናው፣ፈርጣማ ፓርቲ ገፍትሮ ለመጣል ከህዝብ የተፋፋመ ትግል ጋር የወገኑት አዲሶቹ የኢህዴድ አመራሮች ድፍረታቸው የሚደነቅ ነው፡፡ በህወሃት ቤት ማደጋቸው የፓርቲውን የቤታቤት ደባ፣ሼር እና ተንኮል በደንብ መረዳት ስላስቻላቸው የህዝብ ትግል ወዝውዞ ወዝውዞ ባደከመው ህወሃት ላይ የመጨረሻውን ሃይለኛ ምት ሰንዝረዋል፡፡ ውድቀቱ ከወደ ብረት አንጋች ተገዳዳሪዎቹ መንደር(በተለይ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት) ብቻ እንደሚመጣ ይጠብቅ የነበረው ህወሃት ይህን ድንገቴ የማንጅራት ምት መቋቋም አቅቶት ተሽመድምዷል፡፡

ህወሃት የመጨረሻ የውድቀት ደወሉን የደወለው አቶ ኃ/ማርያምን ተለማምጦ ስልጣን ላይ ለማቆየት ኩራቱ በጄ ያላለው ጊዜ ነው፡፡በህወሃት ነቃፊዎች ዘንድ የዓለምን ውርጅብኝ እያስተናገዱም ቢሆን ‘አቤት ወዴት’ ሲሉ የኖሩትን አቶ ኃ/ማርያምን ክፉኛ ያስከፋው ህወሃት ሰውየው በእጁ እያሉ ለሚፈልገው በሰው ክንድ የአዞ ጉድጓድ የመለካት ፖለቲካ የሰጡት ጥቅም አልታየውም ነበር፡፡

ባልጠበቀው ሁኔታ፣ኦህዴድ ክፉኛ ባንጓጠጠበት ወቅት፣በሃገር ዳርቻ በተነሳ ተቃውሞ ወንበሩ እንደወተት እየተናጠ ባለበት ወቅት በአደገኛ መገጣጠም ስልጣን በቃኝ ያሉትን አቶ ኃ/ማርያምን በግማሽ ቀን ሲያሰናብት የሚመጣውን አላመዛዘነም፣ያንዣበበት አደጋ አቶ ኃ/ማርያምን ከመለመን የበለጠ መዘዝ እንደሚያመጣበት አላሰበም ነበር፡፡ የአቶ ኃ/ማርያምን መነሳት ተከትሎ በመጣው ውስጠ-ፓርቲ ጉሽሚያ ባለጠመንጃው ህወሃት በባለ ብዙ ህዝቡ ኦህዴድ መሸነፉ ለሽንፈት ተዘጋጅቶ ለማያውቀው ህወሃት ሊዋጥ የማይችል እንደ ህልም ያለ ነገር ነው፡፡

ህወሃት ባላሰበው አቅጣጫ የመጣበት ምት ስልጣኑን እንዳሳጣው ለመረዳት ብቻ ሳይሆን ሽንፈቱን ለመቀበልም ያስቸገረው ይመስላል፡፡ በፍጥነት እየተቀያየረ ያለውን የሃገራችን ፖለቲካ ጭራ ለመያዝም ግር እንዳለው ያስታውቃል፡፡ ፈጣኑ የፖለቲካ ሁነት በመንገዱ ሁሉ የህወሃትን ስር እየነቀለ የሚሄድ መሆኑ ግርታውን አብሶታል፣የሚይዝ የሚጨብጠውን አሳጥቶታል፡፡ለወትሮው ሲያሾረው የነበረው ኦህዴድ የማይጋፉት ባለጋራ ሆኖበታል፡፡ ብአዴንም የድሮው አይደለም፡፡ቀን ከዞረበት ጋር ጉዳይ የሌለው የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም ከአሸናፊው ጋር ሽው እልም እያለ ነው፡፡

ልክ ባልሆነ ከመጠን ያለፈ የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ሰክሮ የኖረው ህወሃት ሽንፈትን መቀበል በራሱ ችግር እንደሚሆንበት ባያጠራጥርም እንደ ባዶ እቃ እየሞላ የፈለገውን ሲያደርጋቸው ከነበሩት ገባር ፓርቲዎች የመጣበትን ሽንፈት እንዲህ በቀላል ተቀብሎ እኛ እንደምናስበው ሟሽሾ እንደማይቀር መገመት ደግ ነው፡፡ገሃድ የሆነውን የፖለቲካ ስልጣን ቢያጣም በስልጣን ላይ ስር ሰዶ እንደ መኖሩ የልቡን ባያደርስለትም፣የንዴቱን ያህል ባይሆንም አንዳንድ ከፀጥታ እና ደህንነት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍጠር የሚያስችል ጉልበት አያጣም፡፡
ይህ ከህወሃት የአልሸነፍ ባይ እልኽኝነት፣ስር ለስር ሄዶ የጨለማ ስራ የመስራት ልምድ እና በአመዛኙ ወታደራዊ ማንነት ውቅር ጋር ሲዳመር የሃገራችን መከራ በምናስበው ፍጥነት እንደማያበቃ ያመላክታል፡፡በሌላ በኩል ቁጣው በነደደው ህወሃት ተቃራኒ የቆመው የጠ/ሚ/ር አብይ አስተዳደር ህወሃት በማያውቀው የሲቪል እና ይቅር የመባባል ቋንቋ ብቻ አነጋግሬ ህወሃትን ገራም አደርጋለሁ ባይ ነው፡፡

ይህ ነገር ሁለት ቋንቋቸው የማይመሳሰል ሰዎች በየቋንቋቸው ሲያወሩ የሚፈጠረውን ነገር ይመስላል፡፡ ለህወሃት አይሆኑ ሆኖ ያኖረውን ወንበሩን የቀማው ሰው በምንም ቋንቋ ቢያናግረው ለበጎ መስሎ አይሰማውም፡፡ ለህወሃት መልካም የሆነችው አብሮነት እሱ ወንበሩ ላይ ሆኖ ሌሎች ወረድ ብለው ቆመው የምትደረገዋ ነች፡፡ያለ እንደዚህ ያለች አብሮነት ሃገርም ብትሆን በህወሃት ልቦና ትርጉም የላትም፡፡ አብይ ደግሞ “ሊያስሩኝ ይፈልጉ ነበር” ያሏቸውን ህወሃቶችን ዝም ብሎ በመተው ብቻ ፍቅርን ለህወሃት ማስተማር ይቃጣቸዋል፤ህወሃትን ህወሃት ያደረገውን የውድድር፣የበቀል እና ሁሌ የማሸነፍ ማንነት እንዲህ ባለ መንገድ የሚቀይሩ ይመስላቸዋል፡፡የትግራይን ህዝብ ደህንነት ማንም እንዳይጋፋ በማሳሰብ ብቻ በግድም በውድም ህወሃት በትግራይ ምድር የገነባውን ተቀባይነት ሊገዳደሩ ይሞክራሉ፡፡

በህወሃት ባህል ይህ ሁሉ ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡ ህወሃት የሚያውቀው ሁለት ተቃራኒ ነገሮችን ነው-ማሸነፍ ወይ መሸነፍ፡፡ ማሸነፍ የእሱ ነው መሸነፍ ደግሞ የሌላ! ስለዚህ ጠ/ሚ አብይ ዛሬ ያሸነፉት ለህወሃት ብቻ የተሰጠውን ማሸነፍ ሰርቀው ነው፡፡ በተሰረቀ የማሸነፍ ሜዳ ላይ ቆመው የሚያናግሯቸው ዶ/ር አብይ የመደመር ሆነ የፍቅር፤ ሃገር ማዳን ሆነ የፍትሃዊነት ቋንቋ ለህወሃቶች እንደ ሚንሿሿ ፀናፅል ትርጉም አልቦ ነው፡፡ ማሸነፋቸውን ከሰረቃቸው ሰው ጋር መደማመጥ ለዘመናት ሲገነቡት የመጡትን፣ደርግን በማሸነፍ ደግሞ “ያረጋገጡትን” መሰረታዊ የአሸናፊነት ስነ-ልቦናቸውን የሚገዳደር አካሄድ ነው፡፡በህወሃቶች እሳቤ አሸናፊ ማለት እነሱ በአሸናፊነታቸው ዘመን እንደሚያደርጉት ባለጋራውን ለቃቅሞ የሚያስር፣የሚገድል፣የሚገርፍ፣የሚሳደብ፣የሚያሰድድ ነው፡፡

ይህን ያላደረጉት አብይ በህወሃቶች ዘንድ አሸናፊ ናቸው ተብለው ይቆጠሩ ዘንድ የሚሆን አይመስለኝም፡፡ አሸናፊ፣ጉልበታም ማሰር እየቻለ ነገር ግን መንግስትነቱን በሚመጥን ማስተዋል አስተውሎ፣ የቂም በቀልን፣ የጥርስ መናከስ ፖለቲካዊ ባህላችንን የሆነቦታ ለመስበር ሲል ብቻ ማሰር የሚገባውን ላያስር እንደሚችል በህወሃቶች ዘንድ ግንዛቤው ያለ አይመስለኝም፡፡ አዲስ ባህል ሊያመጡ የሚቸገሩት ጠ/ሚ/ር አብይ የገጠማቸው ትልቅ ፈተና ቋጠሮው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ አብይም የህወሃትን ነገራ ነገር አይተው የመደመር ፍልስፍናቸው በተደማሪው ሁሉ ዘንድ እሳቸው የሚሰጡትን (ከነተበው ፖለቲካችን የመውጣት መንገድ አይነት) ትርጉም ብቻ ሊይዝ እንደማይችል የተረዱ አልመሰለኝም፡፡በሁለት አካላት ዘንድ የሚደረግ የመስተጋብር ዘይቤ አንደኛው አካል የተረዳበት አረዳድ መልካም ስለሆነ ብቻ መልካም ፍፃሜ ላይኖረው ይችላል፡፡

የጠ/ሚር አብይ የመደመር ፍልስፍና የ “ኑ ተደመሩ ግብዣ” ለቀረበለት ህወሃት የሚሰጠው ትርጉም ፍፃሜውንም ሆነ ሂደቱን በመወሰን ረገድ ከፍ ያለ ሚና አለው፡፡ ህወሃት የፖለቲካ ስልጣን ላይ ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ተንሰራፍቶ የኖረ ሥረ-ብዙ ፓርቲ እንደመሆኑ ስልጣንን አጥቶ ለመደመር ያለው ዝንባሌ ለወደፊቱ የፖለቲካችን ጉዞ የማይናቅ ሚና አለው፡፡ በተመሳሳይ ጠ/ሚር አብይ ህወሃትን ጨምሮ የመደመር ፍልስፍናቸው ለማይዋጥላቸው አካላት ተለዋጭ መላ መዘየዱን መርሳት የለባቸውም፡፡ እንጂ እሳቸው ያመጡት (ብዙዎችም የወደዱላቸው) የመደመር ፍልስፍና እንደ አየር ሁሉም ደስ እያለው ይስበዋል ብለው ማሰብ የለባቸውም፡፡ በጎ ነገርን ለመቀበል በጎ ማንነት ያስፈልጋል፡፡ በጎነት ሁሉ ስልጣን ላይ መውጣት ብቻ የሚመስለው ህወሃት ደግሞ ስልጣኑን ጥሎ የሚያነሳው ምንም ምድራዊ ስጦታ የለም፡፡ስለዚህ የከዳውን የስልጣን ገድ ለመፈለግ የሚማሰውን ሁሉ ይምሳል፤የሚጎነጎነውን ሁሉ ይጎነጉናል፤ ሚሴረውን ሁሉ ያሴራል፤ ለዚሁ ይረዳኛል ያለውን የክፉ ቀን ወዳጅ ሁሉ ይጠራል፡፡

በድንገት የቆመበት መሬት እየተናደበት ያለው ህወሃት እንደፈለገ ሲያደርጋት የኖረውን ሸገርን ለባለ ጊዜ ሰጥቶ መቀሌ መሽጓል፡፡ በመቀሌው የድንጋጤ ቁዘማ የተሰየመው ግን ህወሃት ብቻውን አይደለም፡፡ ለወትሮው ህወሃትን በሰብዓዊ መብት ረጋጭነቱ፣በአምባገነንነቱ፣ በሙስናው ህዝብን በማስመረር ሲከሱት የነበሩት የቀድሞ አባሎቹ አይተ ግደይ ዘርዓፅዮን እና ዶ/ር አረጋይ በርሄ፣ተቃዋሚ ነን ብለው አረና ትግራይን የመሰረቱ አመራሮች፣አቶ መለስ አፈር ሳይጫናቸው ከህወሃት ተሰነጠርን ያሉ ግለሰቦች እና ሌሎች ትግራዊያን ሁሉ ከህወሃት ጋር ለስብሰባ ተሰይመዋል፡፡

እነዚህ በህወሃት ጭንቅ ጊዜ ከበውት ስብሰባ የተቀመጡ ሰዎች ከትግሬነታቸው በቀር ከህወሃት ጋር የሚያዛምዳቸው ነገር ግልፅ አይደለም፡፡ ሁሉም በሚባል ሁኔታ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ህወሃትን በዘረፋ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በማስፈን የሚከሱት ነበሩ፡፡አብሮ ስብሰባ ለመቀመጥ የሚያስችል የቀደመ ይፋዊ ውይይት አድርገው እንደሁ ግልፅ ያደረጉት ነገር የለም፡፡አሁን የሚያደርጉትም ህወሃት የቀድሞ ስህተቱን አምኖ ወደፊት አብሮ ለመስራት የሚያስችል ድርድር ለማድረግ እንደሆነ የተነገረ ነገር የለም፡፡ከዚህ ይልቅ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የህወሃት የወንጀለኝነት ምልክት ተደርጎ በሚወሰደው ኢፈርት እጣ ፋንታ ላይ መምከር አንዱ የስብሰባቸው አላማ እንደሆነ ነው ከገለልተኛ ምንጮች እየተዘገበ ያለው፡፡

በግል ትዝብቴ ከአቶ ገብረመድህን አርአያ በቀር የኢፈርትን ወንጀል-ወለድ ድርጅትነት እና የህወሃት የአድሎ ምልክትነት አንስቶ ሲያወግዝ የሰማሁት የትግሬ ፖለቲካኛ፣አክቲቪስትም ሆነ ልሂቅ አላጋጠመኝም፡፡በተቃራኒው በሌላ ጉዳይ ህወሃትን የሚያብጠለጥሉ የትግሬ ፖለቲከኞችም ሆኑ አክቲቪስቶች በኢፈርት ጉዳይ ላይ ወይ የትግራይ ህዝብ አንጡራ ሃብት እንደሆነ ፈርጠም ብለው ይናገራሉ አለያም፤ ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን ለህወሃት በመጥቀሙ ይቆጫሉ፤ ካልሆነም ኢፈርትን መንካት የትግራይን ህዝብ የሚያስቆጣ መዳፈር እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ፡፡የአሁኑ ከምድር ዳርቻ መቀሌ ላይ ከትሞ የኢፈርትን እጣ ፋንታ ለመወሰን መሟሟቱ የኢፈርትን አፈጣጠር ጤናማነት በወል የመቀበሉ ቅጥያ ነው፡፡

ኢፈርት የተፈጠረው በዘረፋ፣ ቆሞ የሚሄደውም የኢትዮጵያ ህዝብ ለፍቶ ወይ በስሙ ተለምኖ በሚመጣ ዶላር በሚንቀሳቀሱ ባንኮች ላይ በሚደረግ ደባ እንደሆነ ህወሃት ላልሆኑት ዛሬ ህወሃትን ከበው መቀሌ ለከተሙት ምሁራን፣ታላላቅ ሰዎችም ሆነ ወጣት ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች የሚጠፋቸው ጉዳይ አይደለም፡፡ትክክል መስሎ የተሰማቸው በወንዛቸው ልጆች በእነሱ ቀየ የተደረገ ነገር ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ ተመሳሳዩ በሌላ ቦታ ቢደረግ ኖሮ ለእሪታው የሚቀድማቸው እንደማይኖር የመንደራቸው ጥቅም የተነካ ሲመስላቸው በሚያሰሙት ሮሮ አንፃር መገመት አይቸግርም፡፡

በሃገራዊ ደረጃ ተደመሩ በሚለው የዶ/ር አብይ ብሄራዊ ጥሪ ሰበብ መጥተው ከህወሃት ጋር ለመደመር መቀሌ ያቀኑት የትግራይ ተወላጅ ጉምቱ ፖለቲከኞች ስብሰባ የተቀመጡት እንደፓርቲ ወንጀለኝነትን ከጠገበው ህወሃት ጋር ነው፡፡በግል ደግሞ ማዕከላዊው መንግስት በወንጄል ሲፈልጋቸው አሻፈረኝ ብለው ወደ ትውልድ ቀያቸው ከኮበለሉት እስከ ህወሃት ከወረደ ስልጣን ላይ አልቀመጥም ብለው ስልጣን ካስረከቡት የህወሃት አባላት ጋር ነው፡፡ ግፋ ሲልም በትግራይ ቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው ጥፋቱ ምን እንደሆነ ግልፅ ባልሆነው ጠ/ሚ አብይ ላይ ውግዝ የሚያወርድም አለ፡፡ አብይ ቢያጠፉ ቢያጠፉ ከህወሃት የበለጠ ያጠፉት ነገር አይኖርም፡፡ለዲሞክራሲ፣ለህግ የበላይነት እና ነፃነት እንታገላለን ይሉ የነበሩት ስደተኛ ፖለቲከኞች የህግን ጥሪ አሻፈረኝ ካለ ሰው ጋር ምን እንጋራን ብለው እንደተቀመጡ ብቻ ሳይሆን ቀድሞስ ከህወሃት ጋር ተጣላን የሚሉት ለምን እንደሆነ ግር ያሰኛል፡፡
በመደመር ስም ወደሃገር ቤት የመጡ ስደተኛ ፖለቲከኞች ምን እየሰሩ እንደሆነ ነገሬ ብሎ የማይከታተለው የዶ/ር አብይ መንግስትም እኩል ግር ያሰኛል፡፡ኢትዮጵያን ሁሉ የሚያስተዳድረው የዶ/ር አብይ መንግስት መቀሌ ወርዶ በወንጄል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ማምጣት ካልቻለ እንዴት በብዙ ሊታመን ይችላል? በዚህ ሁኔታ ህወሃት ከስጣን ገለል በማለቱ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የተፈጠረው ተስፋስ እንዴት ሊፀና ይችላል?

ከፅንሰት ውልደቱ ጀምሮ ትግራይን እስከመገንጠል በደረሰ አክራሪ የትግራይ ብሄርተኝነት የሚታወቀው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ ሁሉ የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት አንድ ነው ሲል ኖሯል፡፡ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ለዚህ ያለውን መልስ በገሃድ ወጥቶ ተናግሮ አያውቀምና ‘አንድ ነው አይደለም?’ የሚለው ክርክር የሚደራው በትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እና አክትቪስቶች እንዲሁም ትግሬ ባልሆኑ የሃገራችን ፖለቲከኞች እና በህወሃት መሃል ነው፡፡ ህወሃት ‘የትግራይ ህዝብ እና እኔ አንድ ነን’ ሲል ቀደም ብለው የተጠቀሱት ፖለቲከኞች ደግሞ የለም የትግራይ ህዝብ እና ህወሃት አይገናኙም ይላሉ፡፡ ከባለቤት የወጣ ነገር በሌለበት የትኛው ክርክር እውነታውን ወካይ እንደሆነ ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ህወሃት የስልጣኑ መሰረት ሲያረገርግ ወደ ትግራይ መንጎዱ ቀድሞም ‘እኔ ህዝብ ነኝ ህዝቤም እኔ ነው’ ሲል ከኖረው ነገር ጋር በደንብ ይገጥማል፡፡

ይህ ነገር የማይረታውን የህዝብ ትግል ለማሸነፍ ሲንተፋተፍ ኖሮ በስተመጨረሻው ተስፋውን ወደ ትውልድ መንደሩ ወደ ሲርት ያደረገውን አምባገነኑን የሙአምር ጋዳፊን መጨረሻ ያስታውሳል፡፡ ጋዳፈ ተስፋ ያደረጉበት የሲርት ህዝብም ባለው አቅም የለውጥ ሃይሉን በመፋለም ለሰውየው የስልጣን እድሜ መራዘም አጋርነቱን አሳቷል፡፡ዝምታው የበዛው እና ከስንት ዘመን በሀኋላ አደናጋሪ ሰልፍ እያደረገ ያለው የትግራይ ህዝብ መቼ ምን እንደሚያደርግ ማወቅ ባይቻልም ህወሃት ግን ጨራረሱን እንደ አጀማመሩ ወደ ትውልድ መንደሩ በማድረግ እስትንፋሱን ለማቆየት ያሰበ ይመስላል፤በትውልድ ቀየው ከወንዙ ልጆች ጋር መክሮ ሞቱን በህይወት ለመቀየር፣ዳግም ለማንሰራራት ማሰቡም የማይጠበቅ አይደለም፡፡ህወሃት ሲዳከም ህወሃትን ተክቶ የትግራይን ህዝብ ከመጣው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ጋር ማላመድ፣የትግራይ ህዝብንም (እንደሚባለው ከህወሃት የሚለይ ከሆነ) ከኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ጋር ማሰለፍ ይገባው የነበረው አረና ትግራይ የተባለው ፓርቲም ፀሃይ ከጠለቀችበት ህወሃት ጋር በር ዘግቶ መቆዘሙን መርጧል፡፡

የዶ/ር አብይ መንግስትም ለህግ እምቢኝ ባይ የህወሃት ባለስልጣናትን ትግራይ ዘልቆ ከህግ በላይ አለመሆናቸውን ለማሳየት አቅም ይጠረው፣ ፍላጎት አይኑረው፣ በይደር ያቆየው በውል የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ዶ/ር አብይ እነዚህን አሻፈረኝ ባይ ባለስለጣናት ከመቀሌ አምጥቶ በሚፈልጋቸው ህግ ፊት ለማቆም የትግራይን ህዝብ ቅዋሜ እንደፈራ ከሰሞኑ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቆም አድርገዋል፡፡ይህ ነገር ዶ/ር አብይ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵዊ የትግራይ ህዝብ የህወሃቶችን ክፉ እንደማይወድ እንሚያስቡ ያመላክታል፡፡

ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ ህወሃት ጥፋተኝነቱ እየታወቀ ሳይቀር ቆምኩለት ባለው ህዝብ ዘንድ ግዙፍ ተቀባይነት ያለው ፓርቲ ከመሆኑ አንፃር የዶ/ር አብይ ንግግር ስህተት የለውም፡፡ይህ ንግግራቸው ዶ/ር አብይ ለአብሮነት ሲባል የሚያደርጉትን እላፊ መጠንቀቅ ቢያሳይም ስህተት ግን አለው፡፡የትግራይ ህዝብ በህግ የሚፈለግ ሰው እንደማናቸውም ሰዎች ዝም ብሎ ካልተንጎራደደ ብሎ የመቀየም መብት የለውም፡፡ የትግራይ ህዝብ እውን በዚህ ጉዳይ ይቀየማል ወይ በሚለው ጉዳይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም የሚቀየም ከሆነ ቅያሜው ህጋዊነትም አግባብነትም ያለው ነገር አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት መቀሌ የሰፈሩ ከስልጣን ተነሽ የህወሃት የቀድሞ ባለስልጣናት አንዳንዶቹ ቢሮ ለማስረከብም አሻፈረኝ እንዳሉ ነው የሚነገረው፡፡ይህን የልብ ልብ የሰጣቸው ምንድን ነው? ብሎ መመርመሩ አይከፋም፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ህወሃት ወንበር ላይ ተወዝቶ ብዙ በመኖሩ በቀላሉ እፍ ብለው የማያጠፉት ቅሪት ተፅዕኖ ሃያልነት ነው፡፡ህወሃቶች የተካኑበት በድለው እንኳን የተበደሉ ያህል ገርፎ የመጮህ ልማድ እውነትን የያዘን ሰው ሳይቀር የተሳሳተ መስሎት ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ጠ/ሚር አብይ በዚህ ነገር ሳይቸገሩ አይቀሩም፡፡
አብይ እንደ መንግስት በሚያደርጓቸው የህወሃትን ጥግ የነካ የጥቅመኝነት ዝንባሌ የሚነኩ ውሳኔዎች ሳቢያ በህወሃት እና ጋሻ ጃግሬ እህት ድርጅቶቹ ካድሬዎች የድርጅት ግምገማ እና ስብሰባ ወቅት መብጠልጠላቸው አይቀርም፤አልፎ ተርፎ የድርጅት ኪዳን በመብላት ሊከሰሱ ይችላሉ፡፡መንግስትን ይመራል የሚባለው የፓርቲያቸው ዘይቤ ደግሞ ለዚህ ይረዳል፡፡ ይህ ደግሞ አብይ ከድርጅት መንፈስ ውጭ እንደ መንግስት በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ላይ እንደልባቸው እንዳይሆኑ ማድረጉ አይቀርም፡፡በዚህ ምክንያት ህዝብ እንደሚጠብቀውም ዶ/ር አብይ ራሳቸው እንደሚመኙትም ለመራመድ ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ህወሃት በትግራይ ክልል ሰፊ ተቀባይነት ያለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡በዚህ ምክንያት የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች የፌደራል መንግስት ተፈላጊ የህወሃት ባለስልጣናትን ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት ከልባቸው ላያግዙ ይችላሉ፡፡ አልፈው ተርፈውም ለመከላከል ሊሞክሩ ይችላሉ፡፡ኤፍ.ቢ.አይ ባጣራው መረጃ መሰረት ደግሞ አዲስ አበባ ያሉ ባለስልጣናትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡እነዚህን ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ህጋዊ በሆነ መንገድ በፍትህ ፊት እንዲቆሙ ለማድረግ የአብይ የፀጥታ ሃይሉን የማዘዝ ጉልበት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ቀስ በቀስ ጉልበቱን እያበረታ እንደሆነ ከሚደረጉ ሹም ሽሮች መረዳት ቻላል፡፡

ሆኖም ህወሃት ለረዥም ዘመን የፀጥታ ሃይሉን ቀፍድዶ የመቆየቱ ነገር ከገሃዱ ስልጣን ወርዶ እንኳን ለረብሻ የሚሆን ጉልበት እንዳያጣ ሊረዳው ይችላል፡፡ በዚህ ላይ የሰሜን ዕዝ እና የማዕከላዊ እዝ ሰራዊት ትግራይ መከተማቸው፣የእዝ አዛዦቹም ከህወሃት ሊወግኑ የሚችሉ ሰዎች መሆናቸው፣የደብረዘይቱ የአየር ሃይልም በከፊል ወደ መቀሌ እንደተጓዘ ከሚነገረው ጋር ተደምሮ አብዝተው በወታደራዊ ጉልበት ለሚያምኑት ህወሃቶች የልብ ልብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡

ሶስተኛው ምክንያት ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ኦሮሚያ ክልል በአልገዛም ባይነት ሲያስቸግረው እንደነበረ፤ኦህዴድም በሌሎቹ እህት ድርጅቶች መጠን ገራም ሎሌ እንዳልነበረ (መለስ ሳይሞቱ ጭምር አንዳዴ ሲያስቸግር እንደነበረ ይታወቃል) እና ይሄው እርሾ አድጎ እነ ለማ/አብይን እንደወለደ ስልጣን ለማይጠግቡት ህወሃቶች በቁጭት እና በቂም የሚታሰብ ሃቅ ነው፡፡ስለዚህ ዛሬ ቀን ተቀይሮ ኦህዴድ ባለ ወንበር ሲሆን ህወሃቶች ደግሞ ወደ ትውልድ ቀያቸው አቅንተው ትግራይ ክልል ደግሞ በተራው ለኦህዴድ ዙፋን የማይመች ሁከተኛ ቀጠና(Restive political zone) ሊያደርጉት ሊመኙ ይችላሉ፡፡

ኦህዴድ ወደስልጣን ሳይወጣ በኦሮሚያ ካለው ተቀባይነት ይልቅ ህወሃት ከስልጣን ወርዶም ሆነ ስልጣን ላይ እያለ ትግራይ ውስጥ ያለው ተቀባይነት ላቅ የሚል መሆኑ ለዚህ እሳቤው ማገር ሊሆን ይችላል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ እንደሚደረግ የሚታሰበው የድንበር መካለል በኢሮብ ህዝቦች ላይ ሊያመጣ የሚችው ተፅዕኖ ደግሞ ህወሃት ስልጣኑን በማጣቱ የሚያደርገውን የማጯጯህ አካሄድ ለህዝብ የማሰብ መጋረጃ ሊሰጥለት ይችላል፡፡ህወሃት ብቻ ሳይሆን የህወሃትን ስልጣን ላይ መቆየት ለማይጠላው ዘረኝነት ሽው ያለበት ሁሉ የድንበር ማካለሉ ነገር ሰም ሆኖ ለወርቁ (የህወሃት ከስልጣን መታጣት ሃዘን) ጮክ ብሎ እንዲያለቅስ ያግዘዋል፡፡

ከዚሀ በተጨማሪ ዋነኛ መነጋገሪ ነጥብ የሚሆነው የዶ/ር አብይ የመደመር እና የይቅርታ ፍልስፍና የህግ የበላይነትን ከማስከበር እና ወንጀለኞችን በህግ ፊት ከማቅረብ ጋር ያለው ፍቅር እና ጠብ እንዴትነት አለመታወቁ ነው፡፡ወንጀል የሰራ ሰው በህግ ፊት ቀርቦ ህጋዊ የእርምት እርምጃ ሊወሰድበት ግድ ነው፡፡ይህ ካልሆነ ወንጀለኞች ቀድመው በሰሩት ወንጀል አለመጠየቃቸው አንድ ጥፋት ሆኖ በህግ ጥላ ስር አለመሆናቸው ተጨማሪ ጥፋት እንዲስከተሉ ያግዛቸዋል፡፡በጉጉት የምናየውን የለውጥ ሂደት እስከማደናቀፍም ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ‘እኔ ከሌለሁ ትፈራርሳላችሁ’ እያለ ሲያስፈራራ የኖረው ህወሃት እሱ ሳይኖር ሃገር በተቀበለችው መሪ ተሰትራ ስትመራ ማየት ደስ ላይለው ይችላል፡፡

አብሮነት በመዝራቱ፣ከዘረኝነት ጋር በመፋለሙ፣ህዝብን በማክበሩ፣ስልጡን ፖለቲካ ለማምጣት በመድከሙ ጠ/ሚ አብይ አጠገብ ለመድረስ የሚያስችል ማንነት እንደሌለው ህወሃት አሳምሮ ቢያውቅም በተካነበት የመተኮስ ጥበብ ፀጥታ በማስጠበቁ ረገድ አብይን እንደሚበልጣቸው ማሳየት ሳይፈልግ አይቀርም፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን ብጥብጥ አይጠላውም፤ሊያነሳሳው፣እየቆሰቆሰ ሊያባብሰውምይችላል፡፡

ይህን ለማስታገስ አብይ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር የቀደመ የፖለቲካ ባህላችንን የገመገሙበትን እና አስቀያሚውን የመበላላት ፖለቲካዊ ዘያችንን ሊያስቀሩ ያሰቡበት መንገድ እንደገና ማጤን ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንስማማው እና ዶ/ር አብይም አጥብቀው እንደሚያምኑት የቀደመ የመግደል መጋደል፣የማገት መታገት፣የማመቅ መታመቅ ፖለቲካዊ ባላህችን መቀየር አለበት፡፡ ይህን ማድረጊያው ጥሩ ሰዓትም አሁን ነው፡፡

ለምን ቢባል የከረመው የፖለቲካ ባህላችን እግር ከወርች ቀፍድዶ አላራምድ ያለ የችግራችን ሁሉ ራስ መሆኑን ለመረዳት የቻሉ ጠ/ሚ ወንበር ላይ በመሆናቸው ነው፡፡ለዚሁ መልካም ነገር ልባቸውን ማስነሳታቸው ዶ/ር አብይን በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ሆኖ የከረመውን ልማድ በአንዴ ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን እላፊ ሄደው “ማሰር ያለፈበት ነው አናስርም” በሚል እሳቤ ወንጀለኞችን ሳይቀር ህግ እንደሚያዘው በህግ ጥላ ስር ለማድረግ ዳተኛ መሆናቸው የሚያስኬድ አልመሰለኝም፡፡አልፎ ተርፎ ለራሳቸው ህይወት እስከማስጋት፣ የተጀመረውንም የለውጥ ጭላንጭል እስከማዳፈንም ሊደርስ ይችላል፡፡ ከሁሉ በላይ የህግ የበላይነትን የሚጋፋ ይመስለኛል፡፡

መሆን ያለበት “አላስርም” ሳይሆን “ቀዳሚዎቼ በደምፍላት ያደርጉት እንደነበረው ያለ በቂ ምክንያት አላስርም፣አስሬም አልደበድብም፣ደብድቤ ያልሰሩትን እንዲናገሩ አላደርግም፣ባላደረጉት ሃጢያት ስማቸውን ጭቃ አልቀባም” ነው፡፡ ‘አስበው አልመው ባጠፉት፣ማስረጃ በተገኘበት ጥፋትም ቢሆን ጭርሱኑ አላስርም’ ማለት ግን ወደተፈለገው ስልጡን ፖለቲካ የሚወስደንን መንገድ ለአሰናካይ አሳልፎ መስጠት እንዳይሆን ስጋት አለኝ፡፡ ነገሩ ለወንጀለኛ ተጨማሪ በደል እንዲያደርስ፤ስልጣኑ ሲያምረው ለቀረው ቢሆንለትም ባይሆንለትም ለማንሰራረት እንዲፋትር እጣ ፋንታ ዕድል ተርታ መስጠት ነው፡፡
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን/የጸሃፊዋን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ታላቁ እስክንድር (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
ሃምሌ 14 2010 ዓ.ም.

ሰው እንዳደገበት የህይወት ዘውግ ማንነቱ ይቃኛል፡፡ በልስላሴ ያደጉ የባለጠጋ ልጆች በአብዛኛው ለስላሳውን መንገድ እንጅ ሌላውን አይመርጡም፡፡በተቃራኒው ደሃ አደጎቹም ቢሆኑ ለፍተው ጥረው የህይወትን መንገድ ለማለሳለስ መድከማቸው ሰዋዊ ደምብ ነው፡፡ መነሻው ምንም ሆነ ምን መድረሻውን ለስጋዊ ህይወቱ ምቹ ለማድረግ መትጋቱ የአዳም ዘር አንዱ ተመሳስሎሽ ነው፡፡ ሆኖም የስብዕናቸው ውቅር እንዲህ በቀላሉ ለመረዳት የሚያስቸግር ሰዎችም አሉ፡፡ እንዴት ቢያድጉ፣እንዴት ያለ ንባብ ቢያነቡ፣እንደ ምን ጠልቀው ቢያስቡ እንዲህ ያለውን ረቂቅ ማንነት ታደሉ የሚያሰኙኝ ጥቂት ሰዎች አሉ፡፡ እስክንድር ነጋ ከነዚህ ጥቂት አስገራሚዎቼ አንዱ ነው! እስክንድር ህይወትን ለስላሳ አድርጎ የአዘቦት ኑሮ ለመኖር ቢፈልግ ኖሮ ከደህና በመወለዱ ለዚሁ ቀድሞ መንገድ የተጠረገለት ሰው ነበር፡፡ ሆኖም እስክንድር ህይወትን በአዘቦት እይታ የማያይ በመሆኑ ብዙዎቻችን የምናይበትን የድሎት መነፀር አሽቀንጠሮ ጣለ፡፡የብቻውን ድሎት ሳይሆን የብዙሃኑን ፍዳ ለመቋደስ ትልቅ ነፍሱ የነገረችውን ሰንቆ አስቸጋሪውን ብቻ ሳይሆን አስፈሪውን ፅዋ መረጠ፡፡

የእስክንድር ነጋ ነፍስ በብዙ ጌጦች የተዋበች ነች፡፡ ትህትናው ሲባል እውቀቱ፤ እውቀቱ ሲባል ቆራጥነቱ፤ ይህ ሲባል ብሶት እየቆጠረ ጥርስ የማያፋጭ የይቅርታ ሰው መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ብዙዎቻችን ትልቅ ቦታ የምንሰጠውን ስጋዊ ምቾት ችላ ማለቱ ድንቅ ነው፡፡ ሳር ቅጠሉ ስደት በሚያልምበት ዘመን የሰው ወርቅ እንደማያደምቅ አውቆ ለስደት ያለንን አመለካከት የቀየረ ሰው ነው እስክንድር፡፡ በነገራችን ላይ ለእስክንድር መሰደድ የመኖር አለመኖር ጥያቄም ነበር፡፡ እዚሁ ሃገሩ ላይ ሆኖ የሚሆነውን ለመቀበል ሲቆርጥ ከማንም በላይ ህይወቱ አደጋ ላይ የነበረች ሰው ነው፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ አለመሰደድን ከብረት የጠነከረ ብቸኛ አማራጭ አድርጎ እስከመጨረሻው መፅናት እስክንድርነትን ይጠይቃል፡፡ በዋነኝነት የሚገርመኝ የእስክንድር ልዩነት ይህ ነው፡፡ ላመኑበት መኖር ሁልጊዜም የማይገኝ ቢሆንም እንደ እስክንድር ላመኑበት እስከ መሞት ድረስ መጨከን ግን ሌልኛ ነው! ረቂቅ ነው! ዛሬ ላየነው የለውጥ ጭላንጭል እስክንድር ነጋ የከፈለው ዋጋ ውድ፣ረቂቅ እና ብዙ ገፅ ያለው ነው፡፡

እስክንድር የሚዲያ ነፃነት ፅኑ አርበኛ ነው፡፡ራሱን መሃለኛ አድርጎ ማውራት የማይወድ አዋቂ፣እዩኝ እዩኝ የማይል፣ራሱን ተራ ማድረግ የሚወድ የሃሳብ ሰው፣ ትዕቢት የማይነካካው ትሁት ስለሆነ እንጂ ቢተረክ ብዙ ገድል የሰራ ሰው ነው፡፡ አጥንቱ እስኪሰበር ተቀጥቅጧል፡፡ “አጥንቴን ተሰብሬላችሁ” ብሎ ግን ውለታ አያስቆጥርም፡፡ ይህን ግፍ በሰው ጎትጓችነት ቢያወራ እንኳን ይቅርታውን አስቀድሞ፣ ሌሎች ደግሞ ከዚህ የበለጠ የህይወት ዋጋ እንደከፈሉ አጥብቆ ተናግሮ፣ የእሱ እና የሙያ አጋሮቹ መስዕዋትነት የተከፈለው ዲሞክራሲ ለሚባል ውድ ነገር ስለሆነ ወደዛው እስኪደረስ ሁሉም መታገል እንዳለበት ለማስመር እንጅ የራሱን ገድል ለማውራት አይደለም፡፡

እስክንድር በጣም ብዙ ከሚገርሙኝ ማንነቶቹ አንዱ ይህ በነፃው ፕሬስ ብዙ ያልተለመደ ለሙያ አጋሮች እውቅና የመስጠት ቅንነቱ ነው፡፡ የእስክንድር መልካምነት እውቅና ከመስጠት አልፎ ሽልማቶቹን ለማጋራትም ይሞክረዋል፡፡ እስርቤት በነበረበት ጊዜ አንድ ቀን ሞልቶልኝ ልጠይቀው ሄጄ ይህንኑ አስተውያለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ማንነት በነፃው ፕሬስ ባህል አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ገርሞኝ ነው ያየሁት፡፡ የሄድኩት እሱ በደምብ ከሚያውቃቸው ሁለት ሰዎች ጋር ነበር፡፡ ስሙ ተጠርቶ ሲመጣ ፀሃያማ ፈገግታው የእስረኛ አይመስልም፡፡

እኛ የሄድንበት ሰሞን ባለቤቱ እና ልጁ ባህርማዶ የሄዱ ሰሞን ነበር፡፡ ይህ ለእሱ ቀላል ፈተና እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ “እስኬ ለምን ሰርኬን እንድትሄድ አደረክ? አንተ እዚህ ማን አለህ? ልክ አላደረክም!” አለ አብሮኝ የነበረው ጠያቂ፡፡ “አይ አይ ለእኔ የሚሻለኝ ይሄ ነው፡፡ ናፍቆት እዚህ ሲመጣ የሚሰማው ስሜት ጥሩ አይደለም፣በማንም ላይ ቂም እንዲያዝ አልፈልግም እና መሄዱ ይሻላል” አለውና የእሱ የግል ወሬ ላይ ያተኮረ መስሎት አጀንዳ ቀየረ፡፡ ስለጤናችን አጥብቆ ጠየቀ፡፡ እኔን ስለማያውቀኝ ፊቱ ላይ ትንሽ ግርታ ያየው ወዳጄ “እሷ ካልጠየኩት ብላ ነው የመጣችው:: አንተ ባታውቃትም እሷ ታውቅሃለች” ብሎ ስሜን እና ከእሱ ጋር የሚያገናኘኝ የመሰለውን አንዳንድ ማንነቶቸን ሊያስተዋውቅ ሞከረ፡፡ “ጥሩ ነው! እኛ ምናልባት ስራ ሰራን ከተባለ እንደ እሷ ያሉ ተተኪዎችን “Inspire” አድርገን ስለሃገራቸው እንዲያነቡ እንዲፀፉ ማድረግ ከቻልን ነው” አለ፡፡ “አይ እስኬ አንተማ በከተማዋ አራት ማዕዘን ሃውልት ሊሰራልህ የሚገባ ሰው ነህኮ!” ሲለው “አይ እኔኮ የተለየ ነገር አላደረኩም፤ ከሃገር ውጭም ሃገር ውስጥም ብዙ ጓደኞች ስላሉኝ ነው ሽልማት የበዛው፤ እንደው የተወሰነ ደግሞ ለሌሎች ታሳሪዎች ቢሰጥ ጥሩ ነበር፤ እነሱም ብዙ ዋጋ ከፍለዋል…. “ይላል፡፡

እንደታዘብኩት እሱን ማዕከል አድርጎ የሚወራ የጎበዝነህ ገድል ብዙ ምቾት አይሰጠውም፤ወሬውን ቶሎ ያስቀይርና ስለሌሎች ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች ተመሳሳይ አበርክቶ ያወራል፤ ለእሱ የሆነው በዝቶ ይሰማዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ለሌሎች ባልደረቦች እውቅና እና ምስጋና መስጠት በግሉ ፕሬስ በኩል አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ እስክንድር ሰውነቱም ጋዜጠኝነቱም ለየት ይላል! የማወቅ እና የአስተዳደገ መልካምነት መለያ የሆነውን ትህትና ተሸክሟል፡፡ እንደ ህፃን ልጅ ያለ ቅንነቱን ለማየት ከአስር ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ በአንፃሩ በራሱ እስከ መጨከን ድረስ ላመነበት ይፀናል፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያው ከማውቃቸው ሁሉ ገዝፎ ይታየኛል፡፡በማንኛውም ደረጃ ቢያቀርቡት የሚያኮራ መረዳት አለው፡፡ እውቀቱ የወለደው ትንታኔው እንደ ትንቢት ይቃጣዋል፡፡

እስክንድር ዛፍ ሲጠፋ አድባር የሆነ እምባጮ አይደለም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እኔ ነኝ ካለ ተንታኝ ጋር ቢሰለፍ የሚያኮራ መረዳት ያለው ሰው ነው፡፡ ለውይይት ይሁን ለመፃፍ ሲቀመጥ ቁንፅል ነገር ይዞ አይደለም፡፡ ይልቅስ ስለሚጽፍ የሚናገረው ነገር በደንብ ያውቃል፡፡ ክርክሩን በዓለም ጠርዝ የትኛውም ቦታ ላይ ከተከናወነ ፖለቲካዊም ሆነ ታሪካዊ ሁነት ጋር እያሰናሰለ ያስረዳል፡፡ የንባቡን ስፋት በፅሁፎቹ ውስጥ ማየት ይቻላል፡፡ አንብቦ የሚፅፍ እየጠፋ ባለበት ሃገር እስክንድር ለምልክት የቆመ ይመስላል፡፡ሆኖም እኔነት በእርሱ ዘንድ የለም፡፡ ሃሳቡን ሲያስረዳ በአውቃለሁ ባይነት ትዕቢት አይደለም፤በማራኪ ትህትና እንጅ!

እስክንድር ሃሳብን በነፃነት ለመግለፅ መብት መከበር ቃላት የማይወክሉት መስዕዋትነት የከፈለ ሰው ነው፡፡ሰውነቱ ደቆ ፣ቤተሰቡን በትኖ ፣ወልዶ ዕለቱኑ መሳም አለመቻልን ያህል ህመም ጥርሱን ነክሶ ችሏል፡፡ ለእስክንድር ጋዜጠኝነት ሰንደል ማስቲካ እንደመሸጥ ያለ ኪስ የማድለቢያ የችርቻሮ ስራ አይደለም፡፡ በኪሳራ ሳይቀር ጋዜጣ ሲያሳትም እንደኖረ የሚያውቁት ሁሉ የሚናገሩት ነው፡፡ እስክንድር በታሰረ ሰዓት በሆነ አጋጣሚ ያገኘሁት ጋዜጣ አዟሪ ለእስክንድር ገንዘብ ምንም እንዳልሆነ፣ ለጋዜጣ አዟሪዎች የነበረው ክብር እና ያልሰሩበትን እስከ መስጠት እና ለእርሱ የሚገባውን ሁሉ ለእነሱ እስከመተው በደረሰ ደግነት እንደሚያውቁት አጫውቶኛል፡፡ እስክንድር የሚያወራውን ሆኖ የሚያሳይ እንጅ በአደባባይ ሌላ በጓዳ ሌላ የሆነ ግብዝ አይደለም፡፡የሰላማዊ ትግል ሃዋርያ ነው፡፡ እሱኑ በየደረሰበት ይሰብካል፡፡ እየሞተ መታገልን የሚመርጥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ እስክንድር ይገርማል -ነግረውት የማያልቅ ግዙፍ!

በጣም የሚገርመው ደግሞ የተሸከመውን መከራ ከምንም የማይቆጥር በሁሉም ስፍራ አንድ አይነት አቋም ያለው ሰው ነው፡፡ እስርቤት ያገኘሁት ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያክል ስለ ሰላማዊ ትግል ማስታወሻ ይዘው የሚማሩበት ቁም-ነገር አጫውቶናል፡፡ እያጫወተን እያለ አንድ ስርዓት የሌለው አይነት እስረኛ እላዩላይ የመውጣት ያህል ተጠግቶት የሚነግረንን ሁሉ ያጠነጥናል፡፡ ሰላይ መሆኑ ነው፡፡ ስጋት የገባው ወዳጄ እስክንድር ንግግሩን እንዲገታ በምልክት ያሳየዋል፡፡ እስክንድር እስከዛሬ የሚገርመኝን መልስ ሰጠ “ተወው እኔ ያልኩትን ሳይጨምር ሳይቀንስ ፅፎ ካመጣ እኔ መናገሬን እፈርምለታለሁ”አለ:: ሳላስበው አይኔን አፍጥጨ አየሁት፡፡ ምን አይነት ሰው ነው? ገረመኝ!

ከኢህአዴግ ጋር የማይታረቀው ማንነቱ ይህ ነው፡፡ መከራ የማያስጎነብሰው፤የብረት ጉልበት አንሶ የሚታየው ደፋር! የሆነበት ሁሉ የማይሰብረው ከነፍሱ ታላቅነት፣ ከህልሙ ግዝፈት ፣ከፍላጎቱ ርቀት የተነሳ ይመስለኛል፡፡በማይመጥናቸው ወንበር ላይ ቁጢት ያሉ ገዥዎች ደግሞ ይህ አይገባቸውምና ሰላማዊው፣ጨዋው፣ትሁቱ እስክንድር ለነሱ ሞገደኛ ሽብርተኛ ነው፡፡ ቀንድ እንዳለው አውሬ ይፈሩታል፡፡ ከአእምሯቸው በላይ የሆነው ግንዛቤው የሆነ ተዓምር ፈጥሮ ከስልጣናቸው እንዳይመነግላቸው ይሰጋሉ፡፡

በእርግጥ ዕውቀት ከፅናት ያሟላው ባለ ሙሉ ስብዕናው እስክንድር ከእስርቤት ውጭ ቢሆን፣ብዕሩንም ባይነጥቁት ኖሮ ወንበራቸው ላይ መደላደሉ ቀላል አይሆንላቸውም ነበር፡፡ኢትዮጵያ ያዋለደቻቸው ሃገራት ዲሞክራሲን ሲተገብሩ የሃገሩ ከዲሞክራሲ እድል ፋንታ መጉደሏ ይቆጨዋል፣ ያሳፍረዋል፣የተደራጀ ዘረፋው የሚያስከትለው የሙስና ጣጣ በደንብ ይገባዋል፤በጣም ያሳስበዋል፡፡ የነፃ-ሚዲያ ያለመኖር ሙስናን ለመዋጋት ያለማስቻሉ ጉዳይ አጥብቆ ያስጨንቀዋል፡፡ነገ ምን ይመጣብኛል ሳይል ፣በአውሬዎች መዳፍ እንዳለ ሳያጣው ባገኘው አጋጣሚ በወንዝ ልጆች የሚደረገውን የተደራጀ ዘረፋ እና ገፈፋውን ያጋልጣል፡፡ ሞትን ንቆ፣ወፌ ላላ ግርፋትን ያላየ፣አጥንቱ ተሰብሮ በሸክም ያልወጣ ያልገባ ይመስል፣ያልወለደ፣ የልጅ ናፍቆት ያላዋተተው ያህል ላመነበት ጉዳይ ይተጋል፡፡ይሄ ፅናቱ ከማከብረው እና ከማደንቀው ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ እንደ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ እስክንድር የራሱ ገላ ምቾት አያስጨንቀውም፡፡ከሰው በላይ ሆኖ ለመታየት የሚያደርገው ነገር የለም፡፡ አልባሌ ሳይሆን እንደ አልባሌ ይኖራል፡፡ የነፍሱ ረሃብ ስጋውን አክስቶታል፡፡ በቀጭን ስጋው ውስጥ ግን ትልቅ ነፍስ መሽጋለች! በነፃነት ጉዟችንም ሆነ ስኬታቸን ውስጥ ይህችን ነፍስ ልናከብር ይገባል፡፡ እስክንድር ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት አርበኛችን ብቻ ሳይሆን የትም ብናሰልፈው የሚያኮራን ድምጻችን ነው!
___
ማስታወሻ:በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም።
ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ሆድ ያባውን ሰልፍ ያወጣዋል (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ሃምሌ 3 ፤ 2010 ዓ.ም

ሃገር እንድትኖረው ሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የዶ/ር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ወዶታል ብቻ ብሎ ማለፍ ያስቸግራል፡፡ሰውየው ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሊታደግ የተጠቀመበት መለኮታዊ ወኪል አድርጎ የሚወስድም አይጠፋም፡፡የቀድሞ ካድሬነቱም ሆነ የመጣበት ዘውግ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ አይደለም፡፡ጉዳዩ ያለው ይዞት ከመጣው ሃገራዊ አንድነትን የማጉላት ወቅታዊ፣ሁነኛ፣አሸናፊ እና ብዙ ርቀት ተጓዥ ሃሳብ ጋር ነው፡፡ይህ ሃሳብ ራሱ ሰውየው በኦሮሞነታቸው በኩል አልፈው የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ከመሆናቸው ጋር ግጭት እንዳለው ተረስቶ አይደለም፡፡ወጣም ወረደ የዶ/ር አብይ መምጣት ብዙ ኢትዮጵያዊን አስደስቷል፡፡በዚህም ሰበብ የድጋፍ ሰልፎች እየተደረጉ ነው፡፡ በድጋፍ ሰልፎቹ መራሄ የአዲስ አበባው ሰልፍ ላይ የተወረወረው ቦምብ ያመጣው ህዝባዊ ቁጣ በሌሎች ከተሞችም የድጋፍ ሰልፉ እንዲጧጧፍ ሳያደርግ አልቀረም፡፡እየተመናመነ ከመጣው አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ካምፕ ዘንድ ውግዝ የበዛበት የባህርዳሩ ሰልፍ የዚሁ የድጋፍ ሰልፍ አካል ነው፡፡

የባህርዳሩን ሰልፍ በትዊተር ገፁ ለመተቼት የፈጠነው ዶ/ር አወል ቃሲም ነው፡፡ “Today’s Bahir Dar rally, healed to support the PM Abiye ‘s reform is more rejection of plurality and diversity than anything else. If this is a really peoples idea of “Medemer”, we have a good problem. There is no glorious past to return to. We have to imagine a new future”. ይህን መፃፉን ተከትሎ የተሰጡትን አስተያየቶች ተከትሎ ደግሞ በፌስ ቡክ ገፁ “Bahir Dar’s Rally,Abiye Ahmed’s Medemer and the Endless Fascination by the past” በሚል ርዕስ ስር ሰፋ ያለ ሃተታ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አስፍሯል፡፡ ከዚህኛው ፅሁፉ ውስጥ ለወደፊቱ የሃገራዊ አብሮነታችን ሲባል መፍታታት አለባቸው ብየ የማስባቸውን ክርክሮች እንዲህ ለይቼ አውጥቻቸዋለሁ፡፡

“When Abiye Ahmed comes up with the now famous notion of “medemer”, I thought and hoped that this would be …. an opportunity for us to build a new political community that is not hostage to the historically and culturally defended ideologically ….I thought this would be a moment of to break out of the old ways of being together , to build egalitarian consensuses underpinned by democratic values of equality and liberty. …I hoped a new vision of being together, caring for each other, of solidarity, and inter-ethnic and inter religious coexistence is on horizon. I was wrong…. “Isrilites built Egyptian pyramids, God is the same as Allah, Repeated citation of Jesus Christ, Noha” and more that characterized the some of the speeches and the general environment [of the Bahir Dar Rally]. That is not pluralism. ……..The massive display of the flag, beyond being a total in difference to the effects it has on those marginalized under it; it takes on a form of contempt to this whole idea of change and “medemer”. Many of us do not simply recognize ourselves in this symbol. I am not sure that to what extent those in the unity camp are aware of the views and conversations in other political circles, especially in ethno-national political spheres especially such as of the oromo, Somali, Gambella,Afar, and sidama”

“ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መደመር የሚለውን ሃሳብ ይዘው ሲመጡ በታሪካዊው እና ባህላዊው አንድ ወጥ እሳቤ ያልታገተ አዲስ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጥሩ አጋጣሚን ይዞ ይመጣል የሚል ግምት እና ተስፋ ነበረኝ…….ይህ ከአሮጌው የአብሮነት ዘይቤ ሰብረን የምንወጣበት አፍታ እንደ ነፃነት እና እኩልነት ባሉ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ የቆመ እና የፀና አብሮነት የሚመጣበት መስሎኝ ነበር……..የአብሮነት፣የመተሳሰብ፣የወንድማማችነት፣በሃይማኖቶች/ብሄረሰቦች አብሮ የመኖር አዲስ እይታ እንደሚመጣ ተስፋ አድርጌ ነበር…..ተሳስቼ ነበር!….. የግብፅን ፒራሚድ የሰሩት እስራኤላዊያን ናቸው፣እግዚአብሄር እና አላህ ተመሳሳይ ናቸው የሚለው እና በተደጋጋሚ የኢየሱስን እና የኖህን ስም የሚጠራው የተናጋሪዎች ንግግር እና በአጠቃላይ የሰልፉ [ባህርዳሩ] ከባቢ ብዝሃነትን የሚያሳይ አልነበረም…… ረዥም ሰንደቅ አላማ ማሳየቱ በባንዲረው ምልክትነት የተገለሉ ሰዎች ለሚሰማቸው ስሜት ግዴለሽ መሆን ፤መደመር ለሚለው ሃሳብም ንቀት ነው….. ብዙዎቻችን በዚህ ሰንደቅ የመወከል ስሜት የለንም፡፡ የአንድነት አቀንቃኞች በኦሮሞ፣ሶማሌ፣ጋምቤላ፣አፋር ሲዳማ እና ሌሎች የብሄር ፖለቲካ አራማጆች ዘንድ ስላለው ፖለቲካዊ አመለካከት ምን ያህል ትክክለኛ መረዳት እንዳላቸው እርግጠኛ አይደለሁም”::
በእነዚህ ሃሳቦች ላይ የተሰማኝን ለማለት ጊዜ የወሰድኩት ሃሳቡ በዶ/ር አወል ቃሲም በኩል ቢነሳም ሌላ ተጋሪም የማያጣ፣ብንነጋገርበት ብዙ የሚፈቱ ሃሳቦችን የያዘ፣ከመነጋገራችን ደግሞ የምንጠቀምበት መስሎ ስለተሰማኝ ነው፡፡ ከላይ ያስቀመጥኩት ወንድሜ ዶ/ር አወል ቃሲም በትዊተር ገፁ ያስቀመጣት አጭር ሃሳብ በኋላ በፌስ ቡክ ገፁ ሰፋ አድርጎ ያስቀመጠውን ሃሳብ ጨመቅ አድርጋ የያዘች ሃሳብ ነች፡፡ የሁለቱም ሃሳቡ ሲጠቃለል ደግሞ የባህርዳሩ ሰልፍ ለዶ/ር አወል የሃይማኖትን እና የዘውግን ብዝሃነት ሊጨፈልቅ የተነሳ፣መደመር የሚለውን ሃሳብ በመጨፍለቅ በሚለው የተካ፣ ለወደፊቱ አብሮነት አደጋ አዝሎ የመጣ፣አሮጌውን የአብሮነት መልሶ ለማምጣት የታሰበ ሁነት ሆኖ ታይቶታል፡፡ በዚህም ምክንያት በዶ/ር አብይ የመደመር ፖለቲካዊ ላይ የነበረው ተስፋ ተሟጧል ብቻ ሳይሆን በፊት ተስፋ ማድረጉም ስህተት እንደነበር ከትቧል፡፡ለዚህ ከባድ ተስፋ መቁርጥ ያበቃው ደግሞ ወ/ሮ እማዋይሽ እና ጀነራል አሳምነው ፅጌ መፅሃፍ ቅዱሳዊ ሃሳቦች በንግግራቸው መሃል ማንሳታቸው እና አላህን ከኢየሱስ መሳ አድርገው መናገራቸው ነው፡፡ ይህ ነገር በባህርዳር ከተማ ከታየው የ500 ሜትር እርዝመት ካለው ባንዲራ ጋርም ተዛምዶ እንዳለው “ባንዲራው ሃገራዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ምልክትነት አያጣውም፤ነገር ግን እኔ ያዘው እስካልተባልኩ ድረስ ችግር የለብኝም” ሲል ረዘም ባለው የፌስቡክ ፅሁፉ ላይ ጠቅሷል፡፡ ወደኋላ ተመልሰን ልናመሰግነውም ሆነ ልንመልሰው የሚገባ ምንም በጎ ነገር እንደሌለ ነው ዶ/ር አወል የሚያስቀምጠው፡፡

ባህርዳርን ምን ልዩ አደረጋት?

ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው የባህርዳሩ የድጋፍ ሰልፍ የአዲስ አበባውን ሰልፍ የተከተለ ነው፡፡ በባህርዳር የተያዘው ባንዲራም አዲስ አበባ ከተያዘው ልሙጡ ባንዲራ የተለየ ነገር ያለው በእርዝመቱ ብቻ ነው፡፡እርዝመቱ ደግሞ ያን ያህል የሚያነጋግር ነገር ያለው አይመስለኝም፡፡ቁምነገሩ የወከለው ነገር ነው፡፡ ይህ ባንዲራ ዶ/ር አወል ሃይማኖታዊ እና ዘውጋዊ ብዝሃነትን የመጨፍለቅ ምልክት አለው ሲል ያልገቡኝ ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ይህ ባንዲራ የጭፍለቃ ምትሃቱ የሚወጣው ባህርዳር ላይ ሲውለበለብ ብቻ ነው ወይ? አዲስ አበባ ላይ ሲውለበለብ ዶ/ር አወል ለምን ተመሳሳይ ሃሳብ አላነሳም? ለሁለት ተመሳሳይ ነገሮች ተመሳሳይ ምላሽ ካልተሰጠ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ ችግሩ ያለው ደግሞ ባንዲራውን ይዞ ከወጣው ህዝብ እንጅ ከባዲራውም ሆነ ከምልክትነቱ ጋር አይደለም፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ ቢያስ ካህርዳር በፊት አዲስ አበባ ላይ ይህ ባንዲራ ሲታይ እንዲህ አይነት ትችቶችን መስማት ነበረብን፡፡ ከባህር ዳር በኋላ በደቡብ ከተሞች የአንበሳ ምልክት ያለው ባንዲራ ሳይቀር ተይዞ ታይቷል፤ ዶ/ር አወልም ሆነ ሌሎች መሰል ተችዎች ምንም አላሉም፡፡

አዲስ አበባ ሲታይ ምንም ያልተባለው ጉዳይ ባህርዳር ላይ ሲሆን ብዙ የማናገሩ ምንጩ ከወደ አማራ ክልል እና አማራ ህዝብ የሚመጣን ነገር ሁሉ የመጠራጠር፣የማጣጣል፣የመተቸት እና በክፉ የማየት ዝንባሌ ነው፡፡ ለምንጩ ምንጭ ስንፈልግ ደግሞ የአማራ ህዝብን እና የድሮውን ጨቋኝ ስርዓት አንድ እና ያው አድርጎ የማየቱ ሲደጋጋም እውነት የመሰለ ስሁት እሳቤ ነው፡፡ የገረመኝ ነገር ግን ይህ ሃሳብ የመጣው የትግራይ ህዝብን እና ህወሃትን ለዩ እያለ በተደጋጋሚ ሲናገር ከሰማሁት፣በምክንያታዊነቱ እንደምሳሌ ከምወስዳቸው ሰዎች አንዱ ከሆነው ከዶ/ር አወል ቃሲም መሆኑ ነው፡፡

ይህ ስሁት እሳቤ ጥቂት ምክንያታዊ በሚባሉ ምሁራን አእምሮ ጓዳ ውስጥም መሽጎ መገኘቱ የአማራ ህዝብ ፈተና ገና እንዳላበቃ አንድ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ህዝብን እና ስርዓትን ከመለየት አንፃር የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ተነጥሎ የመታየት ተገቢነት የሚሟገቱ ሰዎች የድሮውን የፊውዳል ስርዓት ከአማራ ህዝብ እና የአማራ እንደህዝብ የበላይነት ጋር አገናኝቶ ማየት፤የአማራ ህዝብ የቀድሞው ስርዓት የሚመቸው የታሪክ እስረኛ አድርጎ ማቅረብ እያቆጠቆጠ ያለውን የአማራ ብሄርተኝት ወደ ፅንፈኝት የመንዳት አደገኛ ውጤት ይኖረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራው ህዝብ የቀድሞው ስርዓት ወኪል አድርጎ ማየቱ ራሱ እንደገና ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡አማራው ኢትዮጵያ የምትባለዋ ሃገር ፀንታ እንድትኖር የሚፈልገው የቀድሞዋ ፊውዳል ኢትዮጵያ በአልጋ ላይ ስላስቀመጠችው አይደለም፡፡እንደሚታወቀው የፊውዳል ስርዓት ለሰፊው አርሶ አደር የመከራ ህይወትን የሚግት ስርዓት ነው፡፡አማራው ደግሞ አብዛኛው አፈር ገፊ ደሃ አርሶ አደር ነው፡፡በዚህ ስርዓት አማራው በተለይ የተጠቀመው፣የሚጓጓለትም ነገር የለውም፡፡አንድ የተለየ ያገኘው ነገር ቢኖር በቋንቋው የቤተ-መንግስት ስራ ተከውኗል፡፡ይህ ደግሞ ለአብዛኛው የቀለም ትምህርት አልቦ አርሶ አደር የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ በፊውዳሉ ሥርዓት ለቤተ-መንግስት ቀረብ ያለው አማራ ተመሳሳይ እድል የገጠመው ኦሮሞም ሆነ ሌላ የተጠቀመውን ያህል ተጠቅሞ ሊሆን ይችላል፡፡ክርስትና በሰሜን በኩል በመግባቱ የተነሳ አማራው የተሻለ የቤተ-ክህነት ትምህርት የመቅሰም እድል ስለነበረው አማርኛ ማንበብ መፃፍ በመቻሉ በመላ ሃገሪቱ ተበትኖ አነስተኛ ስራዎችን ለማግኘት እድል ነበረው፡፡ይህ ማለት ግን አማራው ሁሉ የቤተ-ክህነት ትምህርት የማግኘት እድል ነበረው ማለት አይደለም፡፡በፊውዳሏ ኢትዮጵያ ምንም ከመሆን በላይ የጦር አዋቂ መሆን ቤተ-መንግስት ጓሮ ለመታከክ ያስችላል፡፡ጦር አዋቂው ካሳ ሃይሉ፣አሉላ አባ ነጋ፣ሃብተጊዎርጊስ ዲነግዴ፣ራስ ጎበና ዳጨ ወዘተ የዚህ ማሳያዎች ናቸው፡፡

የአማራ ህዝብ ለፊውዳሉ ስርዓት ምልክትም ሆነ ጠበቃ የሚያደርገው የተለየ ጉዳይ የለም፡፡ የአማራውም ሆነ ሌላው ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን የሚወደው ኢትዮጵያዊ ከፊውዳሉ ስርዓት ጋር የሚጋራው ነገር የሃገሩን ህልውና አጥብቆ የሚወድ ስለሆነ ነው፡፡የፊውዳሉ ስርዓት ኢትዮጵያ ፀንታ እንድትኖር የሚፈልገው ከተፈጥሯዊው የሃገርፍቅር ባሻገር ግብር የመሰብሰብ ናፍቆቱም ነው፡፡ አማራው እና ሌላው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ደግሞ ሃገሩ ከሌለች እንደሌለ ስለሚያውቅ የሃገሩን ህልውና ይወዳል፡፡ ይህ የአማራ ህዝብ ብቻ ከኢትዮጵያ ህልውና ልዩ ተጠቃሚነት ስላለው የመጣ ሳይሆን አማራ ያልሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚጋራው ስሜት እንደሆነ የሰሞኑ ሰልፎች አስረጅ ናቸው፡፡

አጠያያቂው ጉዳይ ይህን ነባራዊ ሃቅ በካደ ሁኔታ ሃገራዊ ምልክቶች እና የአንድነት አምሮቶች የአማራው ብቻ ፍላጎት ተደርገው የሚታዩበት እሳቤ ነው፡፡ይህ እሳቤ አማራውን የቀድሞው ስርዓት ልዩ ተጠቃሚ አድርጎ ከማሰብ እስከ የስርዓቱ ባለቤት አድርጎ የደረሰ መጓተት አለው፡፡አማራው የቀድሞው ስርዓት ተጠቃሚ ነው አይደለም የሚለው ልብ አውላቂ ክርክር አንድ እውነት ቢኖረው አማርኛ የሃገሪቱ የስራ ቋንቋ ሆኖ ስለኖረ አማራው/አማርኛ ማንበብ መፃፍ የሚችል ሁሉ በተለያየ ቦታ ተዘዋውሮ ስራ የማግኘት እና የስነልቦና ጥቅም አግኝቶ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ምን ያህሉ አማራ ማበብ መፃፍ ችሎ የስራ እድሉ ተጠቃሚ ሆነ?ምን ያህሉስ አማራ ያልሆነ ሰው አማርኛ ማንበብ መፃፍ እየቻለ አማራ ባለመሆኑ ብቻ አማሮች ከሚያገኙት የስራ እድል ተገልሎ ኖረ የሚለው ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል አማራው ሃገሩን የሚወደው ባለፈው ስርዓት ተጠቃሚ ስለነበረ፣በደስታ በፍሰሃ ስለኖረ ነው ወይ የሚለው መጤን አለበት፡፡በሃገራችን ታሪክ ዋነኛ ክስተቶች አማራው የፊውዳሉን ስርዓት በመቃወም፣በመገዝገዝ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ቢበልጥ እንጅ የሚያንስ ሚና አልነበረውም፡፡የተመቸው ህዝብ ለምን ያምፃል? ማን ጤነኛ የሰው ልጅ ነው በመልኩ በአምሳሉ የተበጄን ስርዓት ለማፍረስ የሚታገል? የባሌ እና የጌዲኦ ገበሬዎች ሲያምፁ የጎጃም ገበሬ የፊውዳሉ ስርዓት ባለቤት ነኝ ብሎ ዝም አላለም፡፡በአፄው ስርዓት የአውሮፕላን ቦምብ የወረደው በጎጃም እና በትግራይ ህዝብ ላይ ነው፡፡ ትንሽ ወደፊት እንለፍ ከተባለም አትዮጵያን የማበጀቱ መስፋፋት አካል የነበረው የኢምባቦ ጦርነት የጎጃምን ህዝብ አጭዷል፤የአፄ ቴድሮስ ቢለዋ የወሎን፣ አጤ ዮሃንስ ቢለዋ የጎጃምን ህዝብ እጅ ቆርጦ አንገቱ ላይ አንጠልጥሏል፡፡ መለስ ዜናዊ በሥነ-ስርዓቱ ህገመንግስት ፅፎ አማራው ላይ እንደ ኦሪት ለምፃም የመገለል፣የመገደል እና የመጠላት አዋጅ አውጇል፡፡ በአማራ ህዝብ ላይ በር ዘግቶ አነሰም በዛ ሌላውን ህዝብ ወክያለሁ የሚሉ ሰዎችን ሰብስቦ ህገ-መንግስት ፅፎ ግን አማራውም እንዲተዳደርበት አድርጓል፡፡የነገሩ ደራሲ ወያኔ ቀርቶ ለዲሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ ተቃዋሚዎች የአማራ ፓርቲ ላለመባል አይሆኑ ሲሆኑ ኖረዋል፡፡ ወያኔ እና ኦነግ በሰለጠነ ዘመን አማራ የተባለን ፍጡር ወደገደል ወርውረዋል፡፡ ኦነግ አላደረግኩም ይላል፤የሚያምነው ካገኘ ቢያንስ ሲቃወም አላየንምና ከተጠያቂነት አይድንም፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመሩት ኦህዴዶች አማራውን የጎሪጥ የማየቱ በሽታ ያልነካካቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ አማራውም በዚህ በሽታ ተሸካሚዎች አልተጠቃም ወይም መጠቃቱን የሚረሳ ነፈዝ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሌላው ቀርቶ ዘረኝነትን የተውት ዶ/ር አብይ የጠ/ሚነት ስልጣን ላይ እያሉ፣ኦቦ ለማ ኦሮሚያን እያስተዳደሩ እንኳን አማራው በኦሮሚያ ይታረዳል፡፡ዶ/ር አብይን ሊደግፍ የወጣው አማራ ላላዝን ቢል የሚያላዝንበት የሌለው፣ከታሪክ ማር ብቻ እየዘነበለት የመጣ ህዝብ አይደለም፡፡አላላዘነም ማለት አልተበደለም ማለት አይደለም፡፡ ይልቅስ ወዳጅ ጠላቱን ለይቶ ስለሚያውቅ ነው፡፡ የሚበድለው ማን እንደሆነ፣ህግ ፅፎ ሊገድለው የተማማለው መሰረታዊ ጠላቱ ማን እንደሆነ ስለሚያውቅ ለማ እና አብይ ላይ መነሳት ሳይሆን መደገፍን መርጧል፡፡የአማራው ህዝብ ኦሮሞውን ዶ/ር አብይን ደግፎ መውጣቱ ዘር ባለመቁጠር፣በደልን በመተው ሊያስመሰግነው ሲገባ መወቀሱ የሚገርም ነው፡፡

የባህርዳር ሰልፍ እና የብዝሃነት ጭፍለቃ

የባህርዳሩ ሰልፍ ዶ/ር አወል በመደመር ፖለቲካ ላይ የነበራቸውን ተስፋ ያጨለመ ብቻ ሳይሆን ተስፋ ማድረጋቸው ራሱ ስህተት እንደ ነበረ እርግጠኛ እንዲሆኑ ድርጓል፡፡ተስፋ ማድረግም ተስፋ መቁረጥም የግለሰቡ መብት ቢሆንም ለዚህ ውሳኔ ያደረሰው ምክንያት በተለይ ዶ/ር አወል በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ምክንያታዊነታቸውን ላየ ሰው ግር ማሰኘቱ አይቀርም፡፡ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተስፋ ያደረጉበትን የመደመር ፖለቲካ ተስፋቢስ ያደረገባቸው ምክንያት በባህርዳር ከተማ በተደረገው ሰልፍ ተጋባዥ የክብር እንግዳ ተደርገው የተጠሩት ወ/ሮ እማዋይሽ እና ጄ/ል አሳምነው ፅጌ ያደረጉት ንግግር ነው፡፡ወደ ንግግሩ ይዘት ከመግባቴ በፊት እነዚህ ሰዎች እንግዳ ሆነው ተጋበዙ እንጅ የመደመር ፖለቲካውን የሚዘውሩ ባለስልጣናትም ሆነ የአማራ ህዝብ በአፋቸው የሚናገርባቸው ልሳነ-ህዝብ አይደሉም፡፡ ዶ/ር አወልም በመደመር ፖለቲካው ላይ ተስፋ ያደረጉት ወ/ሮ እማዋይሽ እና በጄ/ል አሳምነው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን እሳቤ ተመርኩዘው አይመስለኝም፡፡ ስዚህ የሁለቱን ሰዎች ንግግር እንደሰማሁ ወዲያው ተስፋ ቆረጥኩ ሲባል ተስፋ የመቁረጡ እውነተኛ ምክንያት ሌላ መሆን አለበት፡፡

ወደ ንግግሩ ይዘት ስገባ ሰዎች ነገራቸውን ለማጠናከር ከመፅሃፍ ቅዱስም ሆነ ከቁራን ከኦሾም ሆነ ከዳርዊን ንግግር ሊያጣቅሱ ይችላሉ፡፡ሰው እንደ ንባቡ ግንዛቤው ይቃኛል፡፡መንፈሳዊ መፅሃፍትን የሚያነቡ ሰዎች ከዛው ያጣቅሳሉ፡፡የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንዲህ ባለው ስብሰባ ላይ የነብዩ መሃመድን አባባሎች ሲጠቅሱ አጋጥሞኝ ያውቃል፡፡በአዲስ አበባው ሰልፍ “ዘረኝነት ጥንብ ናት ተዋት” የሚለው የነብዩ መሃመድን ጥቅስ በባነር አሰርተው ይዘው የወጡ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሰልፈኛ አይቻለሁ፡፡ይህን ያየ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሙሾ ሲያስወርድ አላጋጠመኝም፤ሌላ ተሸፋኝ ምክንያት ከሌለው ነገሩ ብቻውን ለዚህ የሚያደርስም አይመስለኝም፡፡ዶ/ር አወልም ንግግሩን ከአማራ ክልል ሌላ ቦታ፣አማራ ካልሆኑ ሰዎች አንደበት ቢሰማው ኖሮ እንዲህ የሚያሳስበው አይመስለኝም፡፡

ባንዲራው እና ምልክትነቱ

500ሜ የሚረዝም ባንዲራ ይዞ መውጣት በባንዲራው ምልክትነት ክፉ ለተደረገባቸውን ህዝባች ብሶት ግዴለሽነት ማሳየት፤ለመደመር ፖለቲካም ንቀት እንደሆነ የሚከሰው ዶ/ር አወል ክርክር በርካታ ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ባንዲራው እንዲህ ያለ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የተከሰተለት ባህርዳር ላይ ብቻ ሲያየው ነው? በዚህ ባንዲራ ሃገር ሲገዙ የነበሩ ነገስታት ለአማራ ህዝብ ገነትን ከሰማይ አውረደው ለብቻው ደሴት ላይ አስጠልለውት ነበር?በባንዲራ ምልክት ዙሪያ ከተነሳ ወለጋ ላይ የተውለበለበውን አረንጓዴ፣ቀይ ፣አረንጓዴ ባንዲራ ሲያይ እናት አባቱ፣አክስት አጎቱ፣ዘመድ አዝማዱ በገደል ሲወረወር የሚያሰማው የሲቃ ድምፅ በጆሮው የሚያቃጭልበት አማራ ይጠፋል? ባህርዳሮች የምኒልክ ዘመን ድረስ ርቀው ሄደው ለሰው ስሜት እንዲያስቡ የሚያሳስበው ዶ/ር አወል ትናንት፣በሰለጠነ ዘመን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ዘመዶቻቸውን ያጡ አማሮች የወለጋውን ባንዲራ ሲያዩ የሚሰማቸውን ስሜት አጢኖ ትዊት ማድረግ ያልቻለው እንዴት ነው?

በኦሪት ዘመን የሞቱትን አፄ ምኒልክን በጨፍጫፊነታው በመጥላት ባንዲራውንም አታሳዩን በሚባልበት ዘመን ከህወሃት ጋር ግንባር ገጥመው ትናት በደኖ ላይ አማሮችን ያስፈጁት ኦቦ ሌንቾ ለታ አዲስ አበባ ላይ እንደማንኛውም ሰው እየተንጎራደዱ ነው፡፡ በመደመር ዘይቤው ኦቦ ሌንቾ ለታ ሃገራቸው ገብተው እንዲታገሉ የጠራውን ዶ/ር አብይን ሊደግፉ የወጡት አማሮች ደግሞ ግራ ቀኝ ያገናዝባል በተባለው ዶ/ር አወል ሳይቀር እየተወቀሱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ነገርስ የት ያደርሳል? ጥቅሙስ ምንድን ነው? ምሁራን ያላመጡት አስተዋይነት ከየት ሊጠበቅ ይችላል? እንዲህ ያለው የዶ/ር አወል ያጋደለ ክርክር እሱ በባህርዳሮቹ ተናጋሪዎች ላይ ተስፋ እንደቆረጠው በሌላ ፅንፍ ለቆመ ችኩል ተስፋ ቆራጭ ደግሞ የእሱን ክርክር ተስፋ ለመቁረጥ ግብዓት ለመሆን ምን ያንሰዋል?

አይን የፈለገውን ያያል ….

በዶ/ር አወል ቃሲም እይታ የባህርዳሩ ሰልፍ አንዳች በጎ ነገር የሌለው አሮጌውን አብሮነት ለማምጣት ያለመ እና ብዝሃነትን የሚጨፈልቅ ፈንጠዝያ ነው፡፡እዚህ ላይ የረሳው ትልቅ ነገር የባህርዳር ሰው የሚፈነጥዘው የወንዙ ልጅ ደመቀ በኦሮሞው ዶ/ር አብይ ተሸንፎ አብይ ስልጣን ስለያዙ ነው፡፡ ይህ ቢያንስ የባህርዳር ሰልፈኛ ከዘረኝነት ጋር ጉዳይ የሌለው ሃገሩን ካለ ጋር ሁሉ የሚሰለፍ በመሆኑ የሚያስመሰግን ነበር፡፡በአንፀሩ አማራው ደመቀ ተመርጦ፣ከሰማይ ሰባት አክሊል በሚያወርድ መልካምነት ቢመራ እንኳን ተመሳሳዩን በኦሮሚያ ከተሞች ስለማየታችን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በተጨማሪም ብዝሃነትን በመጨፍለቅ የተከሰሰው የባህርዳር ህዝብ ከዋቆ ጉቱ እስከ አለማየሁ አቶምሳ፤ ከአቶ አሰፋ ጫቦ እስከ አማዳም አና ጎሜዝ የተወደሱበት ነበር ይህ ከብዝሃነት ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ከጥላቻ የፀዳ ሁሉ የሚመሰክረው ነው፡፡በመጨረሻም ዶ/ር አወል ካለፈው ታሪክ እናስተታውሰው ዘንድ አንዳች በጎ ነገር የለም ሲል ያስቀመጠው ነገር የምሁርነት ምክንያታዊነትን ቀርቶ የበጎ አሳቢ ተራ ሰውን ቅንነት የሚመጥን ሆኖ እንዳላገኘሁት ማንሳት ብቻ ይበቃኛል! .

አቶ በቀለ እውነት እልዎታለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም ! (በመስከረም አበራ )

ByAdmin

(በመስከረም አበራ )
ግንቦት 29 ፤ 2010 ዓ.ም.

በሃገራችን የዘውግ ፖለቲከኞች ልማድ የፖለቲከኞቻቸው ቁርጠኝት ጥግ የሚለካው ያለምንም ማገናዘብ ኢትዮጵያ መፈራረስ እንዳለባት በአደባባይ በመናገር ይመስላል፡፡ ታዋቂው የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ጠላት፣የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዝ ስብሃት ነጋ የእሱ ሰፈር ሰዎች ዘረፋ “ለምን?” በተባለ ቁጥር ኢትዮጵያ መፈራረስ እንዳለባት ይዘባርቅ ነበር፡፡ ስለ ሃገር መፍረስ ማውራት በህግ ሳይቀር የሚያስጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም የጎጥ ፖለቲከኞች ተጠራርተው የከተቡት ህገ-መንግስት ሃገር የማፍረስን ወንጀል እንደ መብት የፃፈ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም የጎጥ ፖለቲከኞች ሃገር የማፍረስን ወንጀል እንደ ደህና ነገር ተዝናንተው በየአደባባዩ የሚናገሩት፡፡

አንድ የጎጣቸው ሰው ባጠፋው ጥፋት ሲተች “ሆ..!” ብለው ለስድብ እና ለአምባጓሮ የሚጠራሩት የጎሳ ፖለቲካ ጄሌ ደጋፊዎችም መሪያቸው ስለ ሃገር መፍረስ መናገሩ አንዳች ስህተት ያለበት ነገር አይመስላቸውም፡፡ ይልቅስ ምጥቀቱ ይታያቸዋል፡፡ይሄ በብዙ መንገድ ስህተት አለው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሃገር የማፍረስ ጥሪ ወንጄል ከመሆኑም ባሻገር የሌላውን መብት መጋፋት ነው፡፡የጎጥ ፖለቲከኞች በክልላቸው፣በባህላቸው በአጠቃላይ የጎጣቸው ህልው እና ክብር ላይ አንዳች ክፉ ነገር የተነገረ ሲመስላቸው የሚሆኑት ነገር የሚታወቅ ነው፡፡ እነሱ በማንነታቸው ላይ አንዳች ክብረ-ነክ ነገር የተባለ ሲመስላቸው የሚናገሩትን እስከማያውቁ ድረስ ስሜት ውስጥ እንደሚነከሩት ሁሉ ህልውናውን ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የፈተለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው ወገንም የእናት ሃገሩን መፍረስ እንደ መልካም ሙዚቃ አንገቱን እየወዘወዘ የሚያዳምጥበት ምክንያት እንደሌለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለውን የደመ-ነፍስ ንግግር ከመናገር በፊት ግራ ቀኝ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በሚያክል ግዙፍ ተቋም የሚያስተምር እንደ አቶ በቀለ ገርባ አይነት ሰው መምህርነትን የመሰለ ሃላፊነት ተሸክሞም ይህን መሳት የለበትም፡፡ የራስን ሲያከበሩ እና ሲያስከብሩ የሰውንም ማክበር እንጅ እግር እጅ የሚችለውን ያህል ተንጠራርቶ የሌላውን መብት እየነኩ የእኔን ብቻ አክብሩልኝ ማለት እንደ ልጅ ያስቆጥራል፣ያስገምታል፣ያስንቃልም!

የኢትዮጵያ ብሄርተኝት ጎራው በደመ-ነፍስ የማይመራ፣ዝምብሎ እያጨበጨበ የሚከተላቸው የሰፈር ሰዎች ስለሌሉት መመሪያው ምክንያታዊነት፤መዳረሻው ለሁሉም የምትበቃና የምትመች ኢትዮጵያ ነች፡፡ መዳረሻውን ላፍርስ የሚል ሰው ደግሞ አይንህን ላጥፋ፣ድካምህን ሁሉ ከንቱ ላድርግ ባይ ባላጋራ ስለሆነ እንዲህ ያለውን አካል በትዕግስት መመልከቱ ማብቃት አለበት፡፡ እስከዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ማሟረት ቢበዛ ያስወግዝ ይሆናል እንጅ ምንም ችግር የሌለው ነገር ሆኖ ኖሯል፡፡ ይህ የሆነው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው በትንሽ ትልቁ የማያላዝን፣በራስ መተማመን ያለው፣ቶሎ የማይበረግግ ስለሆነ፣ነገሩ በጣም ከአቅም በታች ስለሆነ በንቀት ማየትን በመምረጡ ነበር፡፡

ሆኖም ሃገር ማለት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ስሜትም ጭምር ነውና ነገሩ ሲበዛ ሃይ መባል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ንቀው ዝም ሲሉት ልክ የሆነ የሚመስለው ሰው ስለማይጠፋ መሰለኝ ሃገር ትፈርሳለች የሚለው አስገማች ንግግር እንደ ደህና ነገር ተይዞ የቀጠለው፡፡ ስለዚህ በዝምታ መነጋገር ለማይችለው የህብረተሰብ ክፍል በንግግር እና በተግባር ማናገር ያስፈልጋል፡፡ በግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ተደራጅቶ ኦሮሚያን እገነጥላለሁ ብሎ መነሳት፣ ለዛም መታገል እድሜ ለህወሃት ህገ-መንግስታዊ መብት ነው፡፡ መብት ያልሆነው ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትፍረስ ማለት በሌላው ኢትዮጵያዊ እጣ ፋንታ ላይ ልወስን የማለት እብሪት ነው፡፡ አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ሊረዱት የሚገባው አንድ ሃቅ አለ፡፡ ስለ ኦሮሚያ አዛዥ ናዛዝ ነኝ ማለት እና የኦሮሞን ህዝብ ወቅታዊ ፍላጎት ማወቅ ለየቅል ናቸው፡፡ እንደምኞታቸው ሆኖ ኦሮሚያ ላይ የማዘዝ መብት አላቸው ብንል እንኳን ኢትዮጵያ ማለት ኦሮሚያ ብቻ አይደለችም፡፡ይህ ረገጥ ተደርጎ መታመን አለበት !

ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ለሚል ሰው ትዕግስቱ ቢበቃ ደግ ነው፡፡ በበኩሌ ሃገሬን ስለማፍረስ የሚናገር ሰው የትም ይወለድ የትም ስብሃት ነጋን እና መለስ ዜናዊን ይመስለኛል፡፡ ሩቅ ሲኬድ ደግሞ ከዚያድባሬ እና ሞሶሎኒ ለይቼ የማይበት ነገር አይታየኝም፡፡ እናም ሃገሬን ለመፍረስ መዘጋጄት እንዳለባት ኮራ ብሎ የሚያወራን ሰው እንደ ጠላት ፋሽስት እንጅ እንደ ሃገሬ ሰው ላየው እቼገራለሁ፡፡ በዚህ ላይ ራሱ ከሰፈሩ ሰዎች ውጭ ያሉትን ሁሉ “ሌሎች” ብሎ የጥላቻውን መንገድ እስከ ከፈተ ድረስ በግድ ውደደኝ፣ወገንህ አድርገህ ቁተረኝ ብየ በአንድ ወገን ፍቅር የምቸገርበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ይሁን ቢባል እንኳን የአንድ ወገን ፍቅር የትም አያደርስም!

“የእኛ ሰው” በቤተ-መንግስት፣በመስዋዕት ሜዳ….

አቶ በቀለ ገርባ ከሰሞኑ ለ“OMN” ቴሌቭዥን በኦሮምኛ ቋንቋ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ብዙ ብዙ አነጋጋሪ ጉዳይ የያዘ ንግግር ተናግረዋል፡፡ይህ የአቶ በቀለ ንግግር ለመማማርም ሆነ የሃገራችን ፖለቲካ የሚሄድበትን መንገድ ለማጤን ሲባል ተፍታቶ መታየት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ በንግግራቸው መሃል “…ከእኛ ወገን የሆነ ሰው ስልጣን ላይ መውጣቱን ጠልተን አይደለም…” የሚሉት አቶ በቀለ ገርባ የጠ/ሚ/ር አብይን ፓርቲ ኦህዴድን እቃዎማለሁ ብለው ተቃዋሚውን ኦፌኮ የተቀላቀሉ ሰው ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ጠ/ሚ/ር አብይ የአቶ በቀለ ገርባ ሰው የሆኑት ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ለአቶ በቀለ ኦሮሞ የሆነ ሁሉ የእርሳቸው ሰው ነው፤ኦሮሞ ያልሆነ ደግሞ በተቃራኒው፡፡

እንዲህ የሚያስቡት አቶ በቀለ ከኦህዴድ ጋር በተለያየ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ ያውም ተቃዋሚ ነኝ ብሎ ጉልበት መጨረሱ ለምን እንዳስፈለገ ግልፅ አይደለም፡፡በዚህ እሳቤ ጥምረት፣መድረክ እያሉ ከኦፌኮ ጋር ተጣምረው ኦህዴድ ያለበትን ኢህአዴግን እንታገላለን የሚሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ፓርቲዎች እንደ አቶ በቀለ ባሉ ሰዎች እንዴት እንደሚታዩ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ንግግር በወረቀት ላይ ያለ ጥምረት እና ህብረት ብቻ ጉልበት እየመሰላቸው በቅንነት ለሚታለሉ በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ለሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ትልቅ ትምህርት ሰጭ ንግግር ነው፡፡

ከተወልጄ የደመ-ነፍስ ስሜት ወጣ ብሎ፣ምክንያትን ተመርኩዞ ለማየት ፋታ ላገኘ ሰው ግን ኦሮሞነት ብቻ የህብረት መሰረት እንደማይሆን ኦፌኮን እና ኦህዴድን ጨምሮ አእላፍ የኦሮሞ ፓርቲዎችን ማስተዋሉ ብቻ በቂ ነው፡፡ በልብ እየተዋደዱ በፓርቲ መለያየት ከሆነም ነገሩ ያው ፍሬቢስ ከመሆን እንደማይዘል አቶ በቀለ ሊጨብጡት ሲጓጉ የነበረው የጠ/ሚ/ር አብይ እጅ አቶ አንዳርጋቸውን ቀድሞ መጨበጡ የተወልጄ ፖለቲካ እየመሸበት ይሁን እየነጋለት ለመገመቱ ቀላል ማስረጃ ነው፡፡ እኔ የሰፈር ሰው ሆኜ ሳለ ሳልጨበጥ እንዴት እንቶኔ የሩቁ ሰው ተጨበጠ ብሎ ከመብገን ሌላው ምን ቢይዝ ቀድሞ ተፈለገ እኔ ምን ብይዝ ልፈለግ አልቻልኩም ብሎ ማጤኑ ተሻይ ነው፡፡

አቶ በቀለ አጥብቀው እንደሚመኙት የሰፈሩን ሰዎች ሰብስቦ ቤተ-መንግስት ሲገባ ያልታየው ጠ/ሚ/ር አብይ የዘረ-መል ፖለቲካን አታሳዩኝ የሚል፣ ሰብዓዊነትን ብቻ አንግቦ በፖለቲካው አለም የተወለደ ሰው አይደለም፡፡ይልቅስ በጥላቻ ፖለቲካው ሻምፒዎን በመለስ ዜናዊ እግር ስር ተቀምጦ ሲሰለጥን ያደገ፤ የመምህራቸውን የከፋፍለህ ግዛ ወንጌል ሰንቀው በኦሮሚያ ዳርቻ ከሰበኩት ከነጁነዲን ሳዶ ጋር ሆኖም የሰራ ሰው ነው -ጠ/ሚ/ር አብይ፡፡

የአብይ ልዩነት ግን ዘግይቶም ቢሆን ከመለስ ዜናዊ ሌላ የእውቀት ምንጭ አለ ብሎ ማመኑ፣አርቆ የሚወስደውን መንገድ ማወቁ፤እንደ ተወለደ ለመሞት አለመፈለጉ፣ለፍቅር የተዘረጋ እጅን አለመገፍተሩ፣ የኦሮሞ ሰፊ ህዝብ(የጥቂት አክራሪ ብሄርተኞች የመለያየት አጀንዳ እንዳለ ሆኖ) ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በሰላም የመኖር እንጅ ተከፋፍሎ “እኛ” “እናንተ” እየተባባለ መናቆር እንደማይፈልግ ያሳየውን ምልክት መረዳቱ፣ ዛሬ የቆመበት ወንበር በማን የፍቅር መዳፍ ተደግፎ እንደቆመ ማወቁ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የአብይ/ለማ ቡድንን ምክንያታዊነት እየጎበኘው እንደሆነ ምልክት ነው፡፡ ምክንያታዊነት የጀመረ ሰው ደግሞ ከጎሳ ፖለቲካ ቅርፊት ለመውጣት መንገዱን ጀምሯል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደ አቶ በቀለ ገርባ ካሉ ሰዎች ጉሽሚያ የገጠመው፡፡

ጠ/ሚ/ር አብይ እና ኦቦ ለማ መገርሳ በኦነግ መንፈስ ደቁነው ኦህዴድን ቢቀላቀሉም በኦነግ ዘመን ደንቁረው በኦነግ ስም እየማሉ መኖርን ያልፈለጉ የአዲሱ ትውልድ አባላት ናቸው፡፡ባለ አዲስ ልቦና የአዲስ ትውልድ ሰው ደግሞ መምህሩን ኦነግን እድሜ ብቻ ያደረገውን የመነጣጠል ፖለቲካ ይዞ መንገታገትን አይፈቅድም፡፡ እንደ አብይ-ለማ ያለ ወጣት ፖለቲከኛ ገና ብዙ የመኖር ተስፋ አለውና ሃገር አፍርሼ ልፍረስ አይልም፡፡ ተስፋ የቆረጠ ብቻ ሃገር ለማፍረስ ይመኛል፡፡ ተስፋ ያለው ሰው በሃገሩ ላይ ወደፊት ስለሚኖረው ብሩህ ተስፋ ያልማል፤ ለዛው ይሰራል፤ ሃገር የሁሉም እንድትሆን የጎበጠውን ሊያቀና ይጥራል፡፡ በተቃራኒው በሰፊው ህዝብ ዘንድ የማሸጥ አርጀቶ ሃሳብ ያዘለ ብቻ የያዘውን ይዞ ወደ ሰፈሩ ሰዎች ጎሬ ያዘግማል፡፡ ሌላው ምን ቢለፋ ከመንደሩ ሰዎች አስተዋፅኦ በቀር አይታየውም፡፡

ደግነቱ ይህ አስተሳሰብ ጥቂት ለውጥ የማይዘልቃቸው አክራሪዎች እሳቤ እንጅ የመላው ኦሮሞ ህዝብ አቋም አለመሆኑ ነው፡፡ሰፊው የኦሮሞ ህዝብ እኩልነቱን የሚሻ እንጅ ሌላውን ረግጬ ልቁም የሚል እበልጣለሁ ባይ እንዳልሆነ የሚታወቅ ሃቅ ነው፡፡ ሆኖም በአብዛኛው በልሂቃን የሚዘወረው ፖለቲካችን ሰፊውን ህዝብ አዳምጦ አያውቅምና የህዝብ በጎነት ያለው አቋም ብቻውን ለሃገር እጣፋንታ መልካምነት ማስተማመኛ አይሆንም፡፡ስለዚህ የልሂቃን አንደበት ሲስት በጊዜ መገራት አለበት እንጅ “የአንድ ሰው ሃሳብ ነው”፣ “አነጋገሩ ተሳስቶ ተተርጉሞ ነው”፣”የጎሳ ፖለቲከኛ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ቢል ምን ክፋት አለው?” የሚለው ቂልነት አይሉት ማድበስበስ የሚጠቅመን ነገር የለም፡፡ አስቦ መናገር የሁሉም ሰው ግዴታ ነው፡፡ አስቦ ያልተናገረ ደግሞ ታገስ ተመለስ ሊባል ግድ ነው፡፡

ሃገራችን አሁን ያለችበት ለውጥ ባለቤቱ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ብዙ የሚወደሱት አቶ ለማ መገርሳ እና ጠ/ሚ/ር አብይ ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ህዝብ ኮስተር ያለ ትግል ውጤት ናቸው እንጅ እነሱ ታግለው ለውጥ ያመጡ ሰዎች አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ሙቀት እነሱን አበሰላቸው፣የህዝብ ጉልበት ህወሃት የሚባለውን ጣኦት እንዲያፈርሱ የልብ ልብ ሰጣቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን እያየው ያለው የለውጥ ጭላለንጭል የራሱ የትግል ውጤት እንጅ ለማ፣ገዱ ወይም አብይ በወርቅ ሰፌድ የሰጡት ገፀ-በረከት አይደለም፡፡በተቃራኒው ህዝብ ነው እነሱ ባርነት በቃኝ እንዲሉ ድፍረት የሰጣቸው፡፡ ይህ ሳይምታታ ነው መነጋገር ያለብን፡፡

አቶ በቀለ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ የሸለሙት ታግሎ ለውጥ የማምጣት ፀጋም ልክ አይደለም፡፡ህወሃትን መርዙን የተፋ እባብ ለማድረግ የሚደረገው ትግል ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ፣ብዙ ተዋናዮች ያሉበት እንጅ አቶ በቀለ እንዳሉት የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ታግሎ ያመጣው ነገር አይደለም፡፡“….እኛ የደከምንበትና የሞትንበትን ትግል ሌሎች ናቸው የተጠቀሙበት…..ልጆቻችን ደማቸውን ያፈሰሱበትና አጥንታቸውን የከሰከሱበት ትግል ሌሎች ባዕዳን ናቸው እየተጠቀሙበት ያለው፡፡ሞትንበት መስዕዋትነት ከፈልንበት እንጅ ፋይዳ አላገኘንበትም” የሚለው የአቶ በቀለ ገርባ ትልቅ ክህደት ያዘለ አስተዛዛቢ ንግግር ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሃት/ኢህአዴግ የባርነት እና አፓርታይድ አገዛዝ ለመላቀቅ ትግል የጀመረው አቶ በቀለ ገርባ እንደሚያስቡት በኦሮሞ ቄሮዎች እንቅስቃሴ አይደለም፡፡እንደ ህወሃት ያለ በኢኮኖሚውም፣በፖሊቲካውም፣
በውትድርናውም፣በዲፕሎማሲውም ስሩን የተከለ ከዛም የጎሳ ፖለቲካን የመሰለ ህዝቦች በአንድ ቆመው መብታቸውን እንዳያስከብሩ የሚደርግ መንፈስ ያሰረፀን መሰሪ ፓርቲ ለመታገል የአንድ ወገን ጡንቻ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የሆነውም እሱ አይደለም፡፡ ህወሃት ዛሬ የምስጋና ድቤ የሚመታላቸውን ገዱን፣ለማን፣አብይን አሽከር አድርጎ በአፋቸው እየተናገረ በሚገዛበት ዘመን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ላይ ነበር፡፡ እነ ለማ-አብይ፣ገዱ ይህን ረዥም የህዝብ ትግል እጅግ ዘግይተው የተቀላቀሉ የድል አጥቢያ አርበኞች ናቸው፡፡

እነ አብይ ራሳቸው ትልቅ ዓለም በሚመስላቸው የህወሃት እልፍኝ ውስጥ ባሮች እንደሆኑ ይገባቸው ዘንድ የሃገሪቱ የግል ፕሬስ ብዙ ብዙ ወትውቶ ነው የማታ ማታ የገባቸው፡፡ አውዳሚው የሲቪክ ማህበራት ህግ ከመምጣቱ በፊት ብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዲሞክራሲ ምፅኣት ደክመዋል፡፡ ቅንጅት፣ህብረት እና ሌሎች ፓርቲዎች ስልጣንን በህዝብ እጅ ለማድረግ ባይሰምርላቸውም ህዝብን ለማንቃት፣ህወሃት መራሹን መንግስት ለመገዳደር ብዙ አበርክተዋል፡፡የሙስሊሙ የሃገራችን ህዝብ ለሃይማኖቱ ነፃነት በአስደማሚ መናበብ፣ የማንንም ክብር ባልነካ ጨዋነት፣ ፅናት በተሞላበት መንገድ ረዘም ላለ ጊዜ መታገሉ አሁን ለታየው የለውጥ ጭላንጭል ትልቅ ግብዓት ነው፡፡

አቶ በቀለ በጣም የተመኩበት የቄሮዎች ቆራጥ እና ኮስተር ያለ ትግል ከፅናቱ መናበቡ፣ከመናበቡ ማስፈራቱ የገዥዎችን ጉልበት ያራደ ነበር፡፡ ጠመንጃ ያነገቡ ገዳዮች ግራ እስኪገባቸው ድረስ ኦሮሚያን መዝረፍ ተረት እንደሆነ ተነግሯቸዋል፡፡ብዙዎች በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡበት፣ እልፎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ዝናብ ፀሃይ የሚፈራረቅባቸው የሆኑበት፣ለሰው ይተርፍ የነበረ ንብረት ያፈሩ ወገኖቻችን ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ በማያውቁት ነገር የቂም በቀል መውጫ መሆናቸው እጅግ አሳዛኝ ቢሆንም የትግሉ አካል ሆኖ በታሪክ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ወጣቶች ከባለጠመንጃ ጋር በጠመንጃም ሆነ በባዶ እጅ ተናተንቀው መሰዕዋት ሆነዋል፡፡ አቶ በቀለን ከሚያስተምሩበት እየነዱ የወሰዱ የወያኔ ባለጠመንጃዎች በሌሊት ቤቱ የመለጡበት አልሞት ባይ ተጋዳዩ ደመቀ ዘውዱ ዘጠኙን ባለጠመንጃዎች ወደ ማይመጡበት ሸኝቶ እንደ ጥጃ እየጎተተ ማሰር የለመደውን ስርዓት የጀግና እጅ አሳይቷል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ ከመቶ በላይ የሆኑ የባህርዳር ወጣቶች ደም ከጣና ጋር ተቀላቅሎ ጣናን የደም ገበቴ አድርጎታል፡፡ በጎንደር ዘሎ ያልተገበ ወጣት አናት እንደበሰለ ድንች ተፈርክሶ አይተናል፣ ብዙ ወጣቶች በጥይት የሚያወርዳቸው ቅጥር ነፍሰገዳይ ፊት የሃገር ባንዲራ ሲሰቅሉ አልፈሩም፡፡ የሃገራቸውን ባንዲራ እንደያዙ እንደ አሞራ ከዛፍ ላይ በጥይት ወርደው መሬት ሆነዋል፡፡ይህን አቶ በቀለ ቢረሱት የሞተባቸው እናቶች፣ሰብዓዊነት የሚሰማው ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ አይረሳውም፡፡ ይህ የወንዝን ልጅ ብቻ ለማጀገን ሲባል የሚራከስ መስዕዋነት አይደለም፡፡

የኮንሶ ህዝብ መብቱን ለማስከበር ሆብሎ ወጥቶ ብዙ ቀናትን ጎዳና ላይ አሳልፏል፣ቤቱ ተቃጥሎበታል፣ልጆቹ ሞተዋል፣ታስረዋል፣ተሳደዋል፡፡ የጉራጌ ወጣቶች ዘርማ በሚል ስም ራሳቸውን አደራጅተው ተንቀሳቅሰዋል፣ የአፋር ህዝብ ምሬቱ ቢጠናበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ነገሬ ሳይል አደባባይ ወጥቶ ጩኽቱን እያሰማ ነው፡፡ በክረምት ቤታቸውን በጉልበተኛ ሊያጡ እንደሆነ የተነገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሁን ይህን ፅሁፍ ስፅፍ ወደ ቤተመንግስት እየተመሙ ነው፡፡የአብዲ ኢሌ አምባገንነት ያበረራቸው የኢትዮ-ሱማሌ ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ፈሰው አቤት እያሉ ነው፡፡ ይሀ ሁሉ ትግል ተጠራቅሞ ነው ሃያ ሰባት አመት የገነነውን አምባገነን አስተዳደር እያራደው ያለው፡፡ ይህን ማገናዘብ በጣም ከባድ ነገር አይመስለኝም፡፡
ኦሮሞ ብቻ ሞቶ ሌላው ዝም ብሎ በተቀመጠበት ቀን የወጣለት ማስመሰል አንድም ራስን ማስገመት ሁለትም የህወሃት ቅጅ የመሆን መንደርደሪያ ነው፡፡በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እኛ እና ሌሎች የሚባል ነገር የለም፡፡ በደል፣መረገጥ፣መዋረድ ሁሉን አንድ አድርጎታል፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው በሰላም እና በእኩልነት አብሮ መኖርን እንጅ ሃገሩን ሁሉ ተፈናቃይ ያደረገውን የ”እኛ” እና “እናንተ” ተረክ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት በህወሃት እግር ገብቶ “ዘሬ ሞቶ ዘርህን ስላዳነ መቶ አመት ናትህ ላይ ሰፍሬ እገዛህ ዘንድ የተገባነው” የሚለው፣ለሞቱ ሰማዕታቶቹ ሃውልት ሰርቶ እያሳለመ፣በቦታው ተገኝቶ ትንሽ እንባ እንዲያፈስ እያስገደደ፣ ከማይታገል “ፈሪ” ዘር በመገኘቱ የበታችነት እንዲሰማው የሚያደርግ ተቀያያሪ ዘረኛ ገዥን ማስተናገድ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ህዝብ ህወሃትን በኦህዴድ ለመቀየር የሰኮንድ ትዕግስት አልቀረለትም! በተፈጥሮው ጀግና ሆኖ የሚወለድ ዘርም የለም፤ይህን ሊነግረን ለሚመጣ “የተረት አባት” የሚተርፍ ሽራፊ ጊዜ የለንም፡፡ህዝብ እበልጣለሁ ባይን ላይመለስ የሚቀብርበት ትግል ላይ ነው፡፡ ዘመኑ የእኩልነት ነው!

“የሚዘፍኑ ሌሎች” እነማን ናቸው?

ጠ/ሚ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲወጡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ በደስታ ሰክሯል፡፡ እኔ በምኖርበት ደቡብ ክልል የሚኖረው ህዝብ የተደሰተው ከአብራኩ የወጡት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ወድቀው አብይ በመመረጣቸው ነው፡፡ የአማራ ህዝብ በአብይ መመረጥ ሲደሰት በአብይ የተሸነፉት አቶ ደመቀ መኮንን የክልሉ ሰው ስላልሆኑ አይደለም፡፡ ዛሬ በመላ ሃሪቱ በሚጓዙ ተሸከርካሪዎች ላይ የአቶ ለማ መገርሳ እና የጠ/ሚ/ር አብይ ውብ ፎቶዎች ተለጥፈው የሚታዩት የዚህ ሁሉ መኪና ሹፌር ኦሮሞ ስለሆነ አይደለም፡፡ የጎንደር ህዝብ ዛሬ “ሌሎች” እና “እኛ” እያሉ ያሉትን የአቶ በቀለ ገርባን ፎቶ ይዘው ይፈቱልን ሲሉ የጮሁት የታሰረ የወንዛቸው ልጅ ስላልነበረ አይደለም፡፡ነገሩ ሌላ ነው፡፡ ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ “የእኔ ሰው” ለማለት በኩታ ገጠም ቀበሌ መወለድ፣ አንድ አይነት ቋንቋ መናገር ወይም በአንድ የዘውግ ፓርቲ ውስጥ መስፈር ግዴታ መሆኑ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያን ያለ ሁሉ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ የሚነግስበት ዘመን ነው፡፡ አብይ የተረዱት አቶ በቀለ ግር እንዳላቸው የቀረው እውነት ይህ ነው፡፡

አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች ትቂት መሰሎቻቸው ለመረዳት ያዳገታቸው አዲስ እውነት ነው አብይን ጠ/ሚ/ር ያደረጋቸው፡፡ አብይ ለጠ/ሚ/ርነቱ ፍልሚያ ነፍስ ሲዋደቁ ብአዴን ደርሶ ባይደግፋቸው ኖሮ የሆነው ሁሉ አይሆንም ነበር፡፡የአብይ ጠ/ሚ/ርነት የሰመረው የእኛ ሰው የሚለው የትም የማያደርስ እሳቤ በመቅረቱ እንጅ ብአዴንም ደኢህዴንም የ”እኔ ሰው” በሚለው ጥበት ውስጥ ገረው ቢቀሩ ኖሮ ማን እንደሚጠቀም ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ “የእኛ ሰው” የተባለው አብይ ወደ ቤተ-መንግስት መምጣቱ ብቻ ሳይሆን አመጣጡም መጤን አለበት፡፡ ‘የእኛ ሰው በእኛ ሰዎች ትግል ብቻ ወደ ስልጣን መጣ ግን የእኛን እጅ ይዞ ቤተመንግስት አልገባም’ የሚለው ቅሬታ እውነት ላይ የቆመ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህን የተሳሳተ ቅሬት ማስወገድ አንድ ነገር ሆኖ አብይ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ያገዘውን ሁሉ እጅ ይዞ ቤተ-መንግስት መግባት እንደማይችል መገንዘብም አስፈላጊ ነው::ለአብይ ወደ ስልጣን መምጣት ያላበረከተ ስለሌለ “ሌሎች” የሚለው አበባል ራሱ ልክ አይደለም፡፡ ለአብይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወገን ነው፤ ይህን በደንብ የተረዳው አብይ ራሱም “የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ” ብሎ ነገሩን ጨርሶታ፡፡ከዚህ በሁዋላ የጎጡን ሰዎች ሰብስቦ በቤተ-መንግስት ሽው እልም እንዲል መመኘት ገድለ-ደደቢትን በገድለ-ቄሮ ተክቶ ሌላውን ህወሃት በሌላ ልብስ ለማምጣት መፋተር ነው፡፡ ይህ ደግሞ አብዛኛውን የኦሮሞ ህዝብ ጨምሮ በማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በጥብቅ የሚጠላ፤ዕለቱን የሚገድል ነገር ነው፡፡

“ጦር ይዞ ሲወጋቸው የነበረውን መሪ ፈትተው ቤተ-መንግስት አስገብተው ሲጨባበጡ ፎቶ ተነስተው ማየት በጣም የሚያሳዝን ነው…የኦሮሞ ልጆች እስርቤት አሸባሪ ተብለው እያሉ ከባድ ወንጄል የሰሩት ተፈተው ቤተ-መንግስት ፎቶ ይነሳሉ” የሚለው ንግግራቸው እጅግ በጣም ያሳዘነኝ ንግግር ነው፡፡ አቶ በቀለ ለብቻቸው የሚያውቁት አንዳርጋቸው የሰራው ከባድ ወንጄል ምንድን ነው? ወንጄል ከተባለ የእሱ ወንጄል አፈር ላይ እስከመተኛት፣ያለ እድገቱ እንጨት እስከመፍለጥ ድረስ ሃገሩን መውደዱ ብቻ ነው! ይህ ሰው በመታሰሩ ልጆቹ በጥንድ አይናቸው የሚያለቅሱለት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ነው፡፡ አቶ በቀለ ገርባም ልጆች አሏቸው፡፡አንዳርጋቸው ለምን እና እንዴት ጦር አንስቶ ወያኔን ለመውጋት እንደ ደረሰ ለሁሉም ሰው እኩል ግልፅ ላይሆን ይችላል እና ወደዛ አንሂድ፡፡ ዝም ብለን በስብዕና እናስበው፡፡ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት እና ቤተ-መንግስት ገብቶ ፎቶ መነሳት በጣም የሚያሳዝነው እንዴት ነው? በኦሮምኛ እና በOMN ይህን የሚሉት አቶ በቀለ ገርባ ከሳምንት በፊት በአማርኛ እና በVOA የተናገሩት ሌላ ነው፡፡ የወጣላቸው ክርስቲያን እግዚአብሄርን አማኝ ከመሆናቸው የተነሳ ልጆቻቸውን በእግዚአብሄር መንገድ የሚያሳድጉ፣በወያኔ ላይ ጭምር ቂም እንዳይዙ፣በአባታቸው አሳሪዎች ላይ ክፉ ስሜት እንዳያዳብሩ የሚመክሩ ሰው እንደሆኑ ሲናገሩ ጆሮየ ሰምቷል፡፡ ታዲያ የአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት፣የሌሎች መጨፈር ያሳዘናቸው እንዴት? ወይስ የአንዳርጋቸው ፅጌ ታስሮ መማቀቅ በአምላክ ወንጌልም የታዘዘ እና የሚደገፍ ነው?!

የማስተባበያው ይባስ

አቶ በቀለ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል ቀርበው ያስተባበሉበት ሁኔታም በበኩሌ ከመጀመሪያው ሃሳባቸው የራቀ ነገር አላየሁበትም፡፡ ማስተባበያ ባሉት ንግግር ላይ አቶ በቀለ ይህን ይላሉ “እንደሚታወቀው ከአራት ዓመታት ወዲህ ብዙ እንቅስቃሴዎች በሀገሪቱ ውስጥ ተካሄደዋል። እንቅስቃሴው በአብዛኛው የተከናወነው በአሮሚያ ክልል ውስጥ መሆኑን ማንም የሚያውቀው ነው። ብዙ ህይወት እና ንብረት የጠፋው፣ ሀገሪቱንም ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተው ሁኔታ በዚሁ ስፍራ የተከናወነ እንደሆነ ግልፅ ነው።ከፍተኛውን መሰዋዕትነት የከፈሉት፤ ለእስር እና ለቤተሰብ መበተን የተዳረጉት፣ አካላቸው የተጎዳው በአብዛኛው የኦሮሚያ ወጣቶች እንደነበሩ ማንም የሚክድ አይመስለኝም።”

የመስዕዋትነት ከፍተኛ እና ዝቅተኝነት መለኪያው ምንድን ነው? ህዝቦች ከጋራ ትግላቸው ውጤት ተጠቃሚ ለመሆን ዝቅተኛው እና ከፍተኛው የመስዕዋትነት ስፍር የት ላይ ያርፋል? ትግል አክሲዮን ይመስል ባዋጡት መጠን የሚጠቀሙበት ማህበር ነው? ይህ ህወሃት ከብአዴን እና ሌሎች እህት ድርጅቶች በበላይነት ቂጢጥ ብሎ “ከነዘር ማንዘሬ ለትግሉ ይበልጥ ስለሞትኩ ስለተሰነጠቅኩ የሁሉ ነገር እፍታ ይገባኛል” ከሚለው ክርክር ጋር ልዩነቱ አይታየኝም፡፡እንዲህ ያለው ውለታ የማስቆጠር እና ከፍ ብሎ ለመታየት መሞከር ደግሞ ከላይ እንደተገለፀው የህወሃት የበላይነት መንፈስ ጓደኛ ነውና በኢትዮጵያዊያን ዘንድ አይፈለግም፡፡

ሌላው አስገራሚ ማስተባበያ ይህን ይላል “ለምን እከሌ ተፈታ? እከሌ መፈታት አልነበረበትም? ማለቴ ሳይሆን፣ ተመሳሳይነት ወጥነት ያለው ስራ አልተሰራም፣ ትናንት ስንታገለው የነበረው ኢፍትሃዊነት አሁንም አለ፣ዛሬም በዐይናችን እያነው ነው ለማለት ነው።በተመሳሳይ ሁኔታ (ወደ ኢትዮጵያ) ከባዕድ ሀገር ታፍነው እና ተጠልፈው የመጡ አሉ፡፡ አንዱን ፈትቶ አንዱን ማስቀረት አለ። ከዚህ በላይ ኢፍትሃዊነት ለኛ የለም። ኢፍትሃዊነቱም በግልፅ በዘር መስመር የተፈጸመ ነው ”

ጦር ይዞ ሲወጋቸው የነበረው ሰው ተፈቶ ቤተመንግስት ገብቶ መጨባበጡ ያሳዝነኛል ያለ ሰው በዚህ ሃሳብ የቀደመ ንግግሩን ለማስተባበል እና ለመታመን ይችላል ወይ የሚለውን ለአንባቢ የህሊና ፍርድ ልተወው፡፡ ‘ፍቺው ወጥነት ስለሌለው ነው ቅር ያለኝ’ ወደሚለው በመጠኑ የተሻለ ወደሚመስለው ነገር ልለፍ፡፡ ይሄ ክርክር ራሱ ችግር አያጣውም፡፡ ሁሉም ሰው ይፈታ ማለት እና እከሌ ተፈቶ የእንቶኔን እጅ መጨበጡ በጣም ያሳዝነኛል ማለት በምንም አይገናኝም፡፡ “ኢፍትሃዊነቱ በግልፅ በዘር መስመር የተፈፀመ ነው” ማለት ምን ማለት ነው?ለየትኛው ጎሳ ምን ያህል የበለጠ ኮታ ተሰጥቶ ነው የእስረኛ ፍቺ የተደረገው? ለመሆኑ የምን ጎሳ ሰው ነው የኢትዮጵያን እስር ቤት ያረገጠው? ነገሩ የኦሮሞ ቁጥር ይበልጣል የሚል ሃሳብ ያለው ይመስላል፡፡ነገር ግን የሰብዓዊ መብትን ፅንሰ-ሃሳብ የሚያውቅ ሰው በታሳሪ/በተጎጅ ቁጥር ብዛት እና ማነስ የመብት ረገጣን አይለካም፡፡

meskiduye99@gmail.com
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በeditor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com ይላኩልን።

ህልም የመሰለኝ እምዬ አንዳርጋቸው ፅጌ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

ግንቦት 28 2010 ዓ.ም.

አንዳርጋቸው ፅጌ ከገዘፉት ገዝፎ የሚታየኝ ፖለቲከኛ ነው -በመፅሃፉ እያዳንዱ መስመር ሳልፍ አንድ ደረጃ ከፍ እያለብኝ እየራቀኝ የሚሄድ ምጡቅ፡፡ግጥም ልፃፍ ሲልም በእያንዳዱ ስንኝ ውስጥ ቢፈቱት የሚረዝም እምቅ እውቀት ለማስታቀፍ የሚያጥረው የለም፡፡ንባብ ገንዘቡ ነው፡፡ አንባቢነቱ በንግግሩም ሆነ በፅሁፉ ውስጥ ጎልቶ ይታያል፡፡የነፍሱ መስህብ ሃያል ነው፡፡ ከክርክሩ ማምለጫ ቀዳዳ የለም፡፡ ማለት የፈለገውን ሲል አንባቢን በምክንያት ገመድ ጎትቶ ወደ ራሱ ያስጠጋል፡፡ የፃፈ የተናገረውን እንደ ቡና ብደጋግም አይሰለቸኝም፡፡ደጋግሜ ባነበብኩት መፅሃፉ እና በማያልፉኝ ቃለ-ምልልሶቹ ውስጥ አሰላስለዋለሁ እንጅ በአይኔ አየዋለሁ ብየ አስቤ አላውቅም፡፡መታሰሩን ስሰማ ሃገር ኦና የቀረች መስሎ ተሰማኝ፡፡ እስር ቤት መከርቼሙ ብክነት መሰለኝ፡፡ ችግር መፍትሄን ሲያስር የሃገሬ ነገር እንደማይሆን ሆኖ እንደተተበተበ ታወቀኝ፡፡ ከሁሉ በላይ የተያዘበት መንገድ አንገበገበኝ፡፡

ክፉ ቀን እና ክፉ ሰዎች ገጥመው እስርቤት ከከረቼሙት ቀን በኋላ አንዳርጋቸው ፅጌን አየዋለሁ ብየ አስቤ አላውቅም፡፡የመፈታቱን ዜና ዋዜማ ሬዲዮ ከዘገበ ቀን ጀምሮ በመፈታቱ ላይ እምነት ጣልኩ-መቼ ይፈታል የሚለው ቀላል ጥያቄ እንዳ ሆኖ፡፡ ለእኔ ከባድ ምጥ የነበረው በጤና እና በስነ-ልቦና እንዴት ያለ አቋም ላይ ይሆን? የሚለው ነገር ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ከሆነበት መከራ የተነሳ “ትግል በቃኝ” እንዳይል የሚለው መጥፎ ስጋት ሽው ይለኝ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ የሌለበት ትግል ደግሞ መስህብ ይጎድለዋል፡፡ይህን እያሰላሰልኩ፣ ዋዜማ የዘገበው ዜና መላዕክት ፅፈው የላኩት እስኪመስለኝ አምኜው እሁድ በሌሊት ወደ አዲስ አባባ በረርኩ፡፡ እስከ ሰኞ የአቀባበሉ ሸብ ረብ ላይ ማተኮርን መረጥኩ፡፡

ሰኞ ግንቦት ሃያ እንደሚፈታ ለህወሃት ቅርብ የሆኑ አንድ አይሉ ሁለት ሰዎች ነግረውኛል፡፡ አንዱ ግን ማክሰኞም ሊሆን እንደሚችል ከእዛ ግን እንደማያልፍ አስረግጦ ሲነግረኝ የአንዳርጋቸው ፍች አሳስቦት ሳይሆን ለእኔ ብሎ እንደሆነ አበክሮ ነገረኝ፡፡ አመስግኜ ማክሰኞ ላይ አተኮርኩ፡፡ ነገር ግን ሰኞ ሌሊት ከመጣም በሚል ሌሊቱንም ስንጓጓ አደርን፤ምንም የለም፡፡ ማክሰኞ እየተጎተተ መጣ፤እየተጎተተ ረፈደ፤ እየተሳበ ሊመሻሽ ቃጣው፡፡ ዝናቡ መጣሁ መጣሁ ማለት ጀመረ፡፡ አንዲ ግን የለም! ብስጭት ጀመረን፡፡ ጩኽት ሁሉ የሞከረው ነበረ፡፡ ጀግናችን በዘገየ ቁጥር የጠባቂው ጉጉ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሄደ፡፡ያለፈ ያገደመው መኪና ላይ ሁሉ ማፍጠጥ ሆነ፡፡

በስተመጨረሻው አንድ አልባሌ አሮጌ አንቡላንስ በሚጎተት ፍጥነት መጣች፡፡በበኩሌ ህመምተኛ ቤቱ አድርሳ የምትለስ ነበር የመሰለኝ እንጅ የጥበቃችንን መልስ፣ የህመማችንን ፈውስ ይዛ የመጣች አድርጌ አላሰብኩም፡፡ከወደ ሁዋላየ ቆመ አንድ ሰው “ይሄ ይሆን እንዴ?” ከማለቱ መኪናዋ ፍጥነቷን ጨምራ ወደ አቶ ፅጌ ቤት ፈትለክ ስትል ሰው በሰው ላይ እየተነባበረ ተሯሯጠ፡፡ እኔ እግሬ ከዳኝ፡፡ እንደምንም እግሮቼን ሰብስቤ መኪናዋን ተከተልኩ፡፡ መኪናው ጋ ስደርስ ገቢና የተቀመጠው ነጭ ለባሽ ደህንነት እና ሾፌሩ ብቻ ናቸው፤አንዳርጋቸው ከኋላ ነው፡፡ መኪናውን የከበበውን ሰው ብዛት ሲያይ አመልጣለሁ ብሎ መፈትለኩ ከመወረር እንዳላተረፈው ሲያውቅ በድንጋጤ የሚጨብጠው ጠፋበት፡፡ አስሬ ስልክ ይደውላል፣በብስጭት እና በክርክር ሁኔታ ያወራል፣ስልኩን ዘግቶ ወደ ውጭ ሲያይ እያደር በሚጨምር ሰው ተወሯል፡፡ አንዳርጋቸውን ከመኪና ማውረድ ትልቅ ፈተና ሆነበት፡፡ አኛ ደግሞ አንዳርጋቸውን ለማየት ሰባት አመት እንደቆየው አይነስውር ትዕግስት አጣን፡፡ በስተኋላ በኩል የመኪናው መስታውት ላይ ያለውን ዝናብ ጠራርጌ ወደ ውስጥ ለማየት ተንጠራራሁ፡፡ መስታውቱ በጥቁር ቀለም ስለተደፈነ ከኋላ የተቀመጠውን ናፍቆታችንን ማየት አልቻኩም፡፡

የግፊያ እርግጫው ነገር አይወራ፡፡ ዝናቡ ትዕግስቱ አልቆ የያዘውን ውሃ እላያችን ላይ ዘረገፈው፡፡ አቶ ደህንነት በር ለመክፈት የሚሆን ቦታ እስኪያጣ ድረስ ፍቅር ብቻ ስቦ ባመጣው የአንዲ ሰራዊት ተከበበ፡፡ “አባቱን ጥሩልኝ ለአባቱ ነው የማስረክበው” አለ:: አቶ ፅጌ በዛ ሁሉ ህዝብ መሃል ቀጭን መንገድ ተከፍታላቸው መምጣት ጀመሩ፡፡ ሆኖም ግፊያው አስፈሪ ስለነበረ አንዲን በእጃቸው መስጠት አልተቻለም፡፡እሳቸው ከተመለሱ በኋላ የባሰ ግፊያ ሆነ፡፡ ግራ የገባው አድራሽ ደህንነት “በቃ እምቢ ካላችሁ ይዤው እመለሳለሁ” አለ፡፡ “ትመለሳለህ? ደም ይፈሳታላ!” አለ ከመሃላችን አንዱ አይኑን አፍጥጦ፡፡

እንደምንም ተገፍትረን የኋላ በር ተከፍቶ አንዳርጋቸው ብቅ ሲል እንደ ትንሽ ልጅ አፈፍ አድርጎ ትክሻው ላይ ያደረገው ልጅ ብቅ ሲል አይኔ የመገረም ፈገግታ ፈገግ ካለው አንዳርጋቸው ፅጌ ፊት ላይ ተሰካ፡፡ አይኔን በዙሪያው በሚራኮተው ሰው ከተከበበው ከአንዳርጋቸው ላይ ነቅየ ወደ ታላቁ አምላክ መንበር ወደ ሰማይ አነሳሁ!! የአንዳርጋቸው ፈገግታ ትርጉም ያለው፣አፍ አውጥቶ የሚናገር አይነት ነበር፡፡ በፈገግታው ውስጥ ህክምና አየሁ! ያችን ሰዓት በአይኔ ከማየት ስላልጎደልኩ ደስ አለኝ፡፡

አንዳርጋቸው ግርግር የሚወድ፣ጭብጨባ ሞተር ሆኖ የሚነዳው ሰው እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ከመኪና ሲወርድ፣አፈፍ ተደርጎ ትክሻ ላይ ሲደረግ በወገን መሃል የመሆን ፍቅር የሚያመጣው፣የአላማ ተጋሪ የማግኘት መፅናናት የወለደው ፈገግታ አየሁ! ማመን እና አለማመን በሚታገሏት ነፍሴ ውስጥ የአንዳርጋቸው መንፈስ ሲታከም አስተዋልኩ፡፡ ህልም መሰለኝ፡፡

ሆኖም የአንዳርጋቸው ስጋ ከስቶ ጎስቁሎ ሳይ የሆነ የሃገር መርገም ታየኝ፡፡ ይህንኑ መርገም አንዱአለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ ፊት ላይ አይቻለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች እጣ ወድቆባቸው የሃገር ምጥ ያምጣልሉ፡፡ ወደው ‘የሃገር መርገም በእኔ ላይ ይሁን’ ብለው የፖለቲካችንን ህማም ይቀበላሉ፡፡አንዳርጋቸውን ሳየው ልክ ባልሆነ ሁኔታ የሃገር መርገም በትቂቶች ላይ ብቻ ወድቆ ሌሎቻችን ለቅሶ ቤት የምንዘፍን ዓለመኞች እንደሆንን ተሰማኝ፡፡ ልስላሴያችን፣ምቾታችን ሁሉ የነሱን ያህል ትልቅ ነፍስ ከማጣታችን የመጣ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ከማየው አንዳርጋቸው ፅጌ በተጨማሪ፣አንዱዓለም አራጌ፣እስክንድር ነጋ ፊቴ ላይ ድቅን አሉ፡፡የበታችነት ተሰማኝ፡፡ታላቅነታቸው ጎላብኝ፡፡ በአንፃሩ ሸክም ያለመጋራት ሃፍረት ነገር ወረረኝ፡፡

የሆነ ሆኖ አንዳርጋቸውን ከእስር ተፈቶ ሳየው ሃገሬ የተፈታች መሰለኝ፡፡ ፅናቱ ገረመኝ፡፡ (በነገራን ላይ አንዳርጋቸውን ነፃ ያወጣው የራሱ ፅናት ነው፡፡ ከዚህ ላይ ሸርፈን ለራሳችን የምንወስደው ፀጋ የለም! ሲኦል ደርሶ እስኪመለስ የፀና ሰው ‘ያስፈታሁት እኔ ነኝ፣ የእኔ ዘር እንዲህ ስላደረገ ነው’ ማለት ይሉኝታ ቢስነት ነው፡፡)እንደምንም ተጋፍቼ፣ “የት አለች?” በሚሉ ወዳጆቼ ፍለጋ ታግዤ አጠገቡ ደረስኩ:: የማደርገው ጠፋኝ፤ደመ-ነፍሴ የመራኝን ካደረግኩ በኋላ አጠገቡ ተቀመጥኩ፡፡ የጤንነቱን ነገር ጠየቅኩት “ደህና ነኝ” አለኝ ፈገግ ብሎ፡፡ በፈገግታው አልፌ በከሳ ፊቱ ውስጥ ያለችውን የምንወዳትን ወፍራም ነፍሱን አየኋት፡፡ ደስ አለኝ!!!! አጠገቡ አንገቴን ደፍቼ እንደተቀመጥኩ አንድ አባት መጥተው “እንዴት ነው ሞራልህ? እሱ ነበር ያሳሰበን ገላ ይመለሳል” ሲሉት ፈገግ ብሎ እያያቸው “እንዲህ በቀላሉ” ሲል ልቤ በደስታ ዘለለች፤ አንዲ ያልተቀነሰበት የሃገሬ ፖለቲካ ውበቱ ታየኝ- ሰማይ ሙሉ ደስታ!!!!!! የአራት አመት የእግር እሳት በአንድ ቀን ደስታ ሲሸነፍ ሳይ የመልካም ነገር ጉልበቱ ታወቀኝ፡፡

እውነት ለመናገር የአንዳርጋቸው ፅጌ መታሰር የማልፈልገውን አይነት ማንነት እንዲቆራኘኝ አድርጓል፣ብዕሬን ቁጡ ስሜቴን ስስ አድርጎት ኖሯል፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ከመታሰሩ በፊት ወደ ሁለት አመት ገደማ በፕሬስ ሚዲያው ላይ በአምደኝነት እሳተፍ ነበር፡፡ በተቻለ መጠን የግል ስሜቴን ገትቼ የታየኝን እና ከስሜት ይልቅ ምክንያት የበዛበት የመሰለኝ ነገር ለመጠቆም እሞክር ነበር፡፡ገዥዎች የሚያደርጉት ነገር ከስሜታዊነትም በላይ የሚያሳብድ ነገር እንደማያጣው ባውቅም መሰዳደቡ፣ስሜታዊነቱ፣አለመከባበሩ፣እንደ ጠላት መተያየቱ፣ በምንጠላው የገዥዎች መንገድ መሄድ ነው፡፡ የሚያመጣልን ነገር አልታይ ስለሚለኝ በተለይ ብዕር ሳነሳ ንዴቴን ዋጥ አድርጌ ራሴን ለመግዛት እሞክር ነበር፡፡ይህ በገዥዎች ዘንድ ሳይቀር በበጎ ይታይ እንደነበር ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይነግሩኝ ነበር፡፡

አንዳርጋቸው ፅጌ መያዙን ከሰማሁባት እርጉም ቅፅበት ጀምሮ ግን ውስጤን ቂመኝነት ሞላው፡፡ የገዥዎችን ስህተት ከዚህ ቀደም ከምረዳው በተለየ መረዳት ጀመርኩ፡፡ ቀደም ሲል የገዥዎች ስህተት ሁሉ በብዛት ካለማወቅ፣ በትቂት ከራስ ወዳድነት እና የአለማወቅ ውላጅ ከሆነው ዘረኝነት የሚመነጭ በመሆኑ በጊዜ ሂደት ከልምድ እና ከእውቀት ሊስተካከል ይችላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ለዚሁም ነው የበኩሌን ለማለት ወደ ሚዲያው የወጣሁት፡፡ አንዳርጋቸውን ለመያዝ የተኬደውን ርቀት፣ የተከፈለውን ዋጋ ፣የተሴረውን ሴራ ትብትብ ሳይ ነገሩ ተራ አለማወቅ ሳይሆን አውቆ የሃገር አለኝታ የማጥፋት አደገኛ እና ክፉ አካሄድ እንደሆነ ገባኝ፡፡ሳልፈልግ ጥላቻ ቋጠርኩ፡፡ሳልወድ ንዴታም ሆንኩ፡፡ንዴትና ቁጭት አብሮኝ የሚጓዝ፣ከዚህ መንግስት ጋር የወገነ ሁሉ የሚያንገሸግሸኝ ፣ንግግራቸውን ባልሰማ፣አይናቸውን ባላይ የምመርጥ ፅንፈኛ ሆኘ ቁጭ አልኩ! ይህን ስሜቴን አልወደውም፤ አንዲ ሲፈታ እኔም ከዚህ ስሜት በመፈታቴ ደስ ብሎኛል፡፡

አጠገቡ እንደተቀመጥኩ ነኝ፡፡ ከአክብሮቴ ብዛት ቃላት ከአፌ መውጣት አቅቷቸዋል፡፡ ዝም ብየ እሱን መስማት አሰኘኝ፡፡አንድ ቤተሰብ የሆነ ሰው መጥቶ አባቱን በደንብ ማግኘት እንዳለበት ይነግረዋል እሱ ደግሞ ውጭ ያለውን ሰው ወጥቶ ሰላም ማለት እንዳለበት አጥብቆ ይወተውታል፡፡ቤት የገባው በትልቅ ግፊያ በሰው ሸክም ነው፡፡ ነገሩን የምናስተባብር ሰዎች ሁሉ ነገር ከቁጥጥራችን ውጭ ሲሆን ደህንነቱ በጣም አሳሰበንና ነገሩ እስኪረጋጋ ድረስ ቤት አስገብተን በሩን መዝጋቱን መረጥን፡፡ እሱ ግን አልፈለገም ወጥቶ ማናገር ፈለገ፤ “ለህዝብ አስቡ እንጅ ዝናብ ላይ ቆሞ እንዴት እኔ ቤት እቀመጣለሁ፤ አመስግኜ ልሸኝ አስወጡኝ” አለ፡፡ ይዘነው ስንዎጣ “ካልተረጋጋችሁ አይወጣም” ብለን አስፈራርትን ወደኋላ የመለስነው ህዝብ እሱን ይዘን እስክንወጣ በር ላይ ደርሶ ጠበቀን፡፡የጠጠር መጣያ የለም፡፡ ብቅ ሲል “እጅህን ብቻ” የሚል ድምፅ ሲሰማ በእኛ ላይ ተንጠራርቶ እጁን ሰደደ አንዱ ሲለቅ አንዱ እየያዘ ጎትተው መሃቸወ ሊከቱት ሲሆን በማንኛውም ሰዓት የሚያሳስበን ደህንነቱ ወደቤት መልሰን እንድንወስደው ግድ አለ፡፡ ተመልሶ መግባቱን ያየ ሰው ራሱ ወደኋላ ሆኖ መውጫውን አመቻቸልን፡፡ ወጥቶ አመሰገነ፣የማይሰበር መንፈሱን ያስመሰከረ ንግግር አደረገ፣ እንዲህ ያለ አቀባበል እንዳልጠበቀ ተናገረ፡፡ “ይገባሃል ያንስሃል እንወድሃለን አንዲ የእኛ” የሚል ጩኽት አቋረጠው፡፡ “እንደምትወዱኝማ አየሁ” ሲል መለሰ፡፡

ተናግሮ ሲጨርስ ልብስ እንዲቀይር ወደ ውስጥ ሲገባ ውጭው በጭፈራ ጦፈ! ለወትሮው ጭፈራ ብዙም የሚያስደስተኝ ባልሆንም በዝናብ ውስጥ ሆኖ የሚጨፍረው የሃገሬ ሰው ድምፅ ለአንዳርጋቸው የመንፈስ ምግብ ስለመሰለኝ ካለሁበት ሆኜ በልቤ አብሬ ጨፈርኩ፡፡ልብሱን ለብሶ ሲወጣ ህዝቡን ፊት ለፊት ማግኘት በመፈለጉ እኛ ደግሞ ደህንነቱ ስላሳሰበን እንዴት አድርገን እንደምናጣጥም ስናስብ “የፎቁ ሰገነት ላይ እናድርገው” የሚል የተባረከ ሃሳብ ከአንዱ የኮሚቴ አባል ተነሳ፡፡ ወደዛው ተጣደፍን፡፡

እንደሚገባው ከፍ ብሎ ቆሞ የሃገሩን ህዝብ ፍቅር በገሃድ ተመለከተ፤ጭብጨባ ሆነ፣ጭፈራው ደራ፣መሬቷ ጠበበች፡፡ የእሱ ስሜት ግን ያው የረጋ ነው፡፡ ወደ ቁምነገሩ ገባ፣ ሃገር ነፃ እስክትወጣ ድረስ ትግሉን እንደማያቆም ተናገረ፣እስር ቤት እያለ ተቆርጦ የተጣለውን ንግግሩን በህዝብ ፊት ተናገረ፡፡ እኔ እንደተያዝኩ “ልቀቁኝ ብየ አልለምናችሁም የፈረዳችሁብኝን የሞት ፍርድ ተግብሩት፣ለህዝብ እየሳቁ መሞትን አሳያችኋለሁ፤ለእኔም እንዲህ ባለ ሃገር ከምኖር ሞቴ ይሻለኛል” ብየ ነበር ሲል መቀስ የቆረጠውን ጣፋጭ እውነት ለህዝቡ ተናገረ፡፡ ቀጠለ “አሁን ባሳሪዎቻችን ፊት የማናወራው ብዙ ነገር አለ፡፡ እኔን መውደድ ብቻ ትግል አይሆንም ሃገር አስሮ የያዘውን መከራ ምክንያት ማጥፋቱ ላይ ነው ማተኮር ያለባችሁ” ሲል እስትንፋሱ እስካለች ድረስ ለህዝብ ከማሰብ፣ለሃገሩ ፖለቲካ ፈውስ ከመልፋት እንደማይመለስ የሚያስመሰክር ንግግር አደረገ፡፡ ህዝቡ በደስታ ሰከረ፡፡ እኔም አምላኬን አመሰገንኩ፡፡ አንዳርጋቸው ያለበት ፖለቲካ ጣዕሙ ታየኝ…….!

ወደ ልጆቹ ሊበር ሰዓታት ሲቀሩት የአቀባበል ኮሚቴ አባቱን ለአስራ አምስት ደቂቃ አግኝቶን ነበር፡፡ በበኩሌ ብዙ ቁም-ነገር ጨብጫለሁ፣ከጎኔ የተቀመጠው ወንድሜ ዳንኤል ሽበሽ ከመጠጋት በላይ ተጠግቶ ሲሰማው አስተውያለሁ፡፡ሆኖም በንግግሩ መሃል ታጋይ አርበኛ መሳፍንትን(ገብርዬ) አንስቶ መናገር ሲጀምር ከሃዘን፣ቁጭት እና ንዴት አልፎ እንባ ሊታገለው ሞከረ፡፡ “እንዴት እኔን አምኖ ትግሉን የተቀላቀለ ልጅ መሰላችሁ?” ብሎ ስሜቱን ዋጥ አድርጎ ወደ ሌላ ጉዳይ ገባ፡፡ ሆኖም ሃዘን ቁጭቱ ተለይቶን እስኪወጣ ድረስ አብሮት እንደነበረ አስተዋልኩ፡፡ የመታመን እዳ ለሚያንገበግበው፣ለተጨማሪ ደቂቃ አብረውት በተቀመጡ ቁጥር ለሚማርክ፣ቢናገሩለት ለማያሳፍር ሰው መቆም የሆነ ስሜት አለው- ኩራት ኩራት የሚል !

በመስከረም አበራ
meskiduye99@gmail.com

የጠ/ሚ አብይ ነገር…. (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

ንግግር አዋቂነት የስኬታማ ፖለቲከኝነት አንድ ግብዓት ነው፡፡የአቶ ሃይለማርያምን ወንበር የተኩት ጠ/ሚ አብይ ከቀዳሚያቸው በተሻለ ንግግር ይጥምላቸዋል፡፡ይሄው ጥዑም ንግግራቸው አድማጫቸው የንግግራቸውን ይዘት ወለፈንዲ ይመረምር ዘንድ ፋታ የሰጠው አይመስልም፡፡ሰውየው የፖለቲካ ፈውሳችን ሊሆኑ የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎችን በተደጋጋሚ አርቆ የጣለብን የኢህአዴግ አባል እንደመሆናቸው መጠን የተናገሩትን በጎውን ከማዳነቅ ጎን ለጎን በመርማሪ ልቦና ማየቱ አትራፊ ያደርግ ነበር፡፡

ጠ/ሚ አብይ በበዓለ ሹመታቸው ቅን ፓርላማ ቀርበው ያደረጉት ንግግር ላይ ላዩን ሲያዩት ድንቅ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን በተመለከተ ያመጧቸው ሃሳቦች የሚወደው ኢትዮጵያዊነቱ ሲበሻቀጥ እንጅ ሲሞካሽ ሰምቶ የማያውቀውን ህዝብን ቀልብ ስቦ ኖሮ የንግግራቸውን ብልት ለመመርመር ፋታ አልተገኘም፡፡በዚህ ላይ ሃገራችንን የመታት የገለልተኛ ተንታኝ ድርቅ ስሜትን በምክንያት ለመተካት አላስቻለም፡፡ ቢቸግረን ወገንተኝነቱን ለአንድ ጎሳ አድርጎ “ካልሆነ ሜንጫ አንሱ” የሚለውን ሁሉ፣የስሜት መረጋጋት የሚያንሰውን፣ የፖለቲካ አቋሙ እንደ ገበቴ ውሃ የሚዋልለውን፣ ዛሬ ያለውን ነገ የማይደግመውን፣ስሜት ምክንያትን አርቆ የጣለበትን፣ጥላቻ እና የተበድየ ተረክ ናላውን ያዞረውን ሳይቀር የፖለቲካ ተንታኝነት ካባ አልብሰናል፡፡የአክቲቪስት እና የተንናኝ ቦታ አደባልቀናል፡፡

ኢህአዴግን የምንወቅስበት ሃቁን ችላ ብሎ የፈለጉትን ብቻ የመስማት አምሮት ኢህአዴግን አምርሮ በሚቃወመው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ጎራም የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሃገራችን በርካታ በሳል ምሁራን ቢኖሯትም አብዛኛው ህዝብ በገና አንስቶ፣ከበሮ አንግቶ የሚዘምርለትን ክስተት ሌላ ገፅታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት ቢነሱ ውግዘት ስለሚከተላቸው እውነታውን ወዲያው ለማሳየት ይቸገራሉ፡፡ ከሰሞኑ በኢሳት ቴሌቭዥን ቀርበው የጠ/ሚ አብይን ነገር ከመነሻው በተለየ ሁኔታ ያዩት እንደነበረ ዘግይተው የተናገሩ ምሁራን ለዚህ ምስክር ናቸው፡፡ ሰዎቹ ጠለቅ ባለ ሁኔታ የነገሩን ብልት ተረድተው እንደነበር ከንግግራቸው ያስታውቃል፡፡ ነገር ግን ይህን የመሰለ ምጡቅ መረዳታቸውን እና ሃሳባቸውን ለጠ/ሚ አብይ ማህሌት በተቆመበት ሰዓት ቢናገሩ ኖሮ “ከህወሃት የባሱ ሴረኞች፣የሴራ ፖለቲካ በሽተኞች” ተብለው ውግዝ ከመዓሪዎስ መባላቸው አስግቷቸው ዝምታን መርጠው ሰንብተዋል፡፡ በዚህ ከቀጠልን ከስህተት መዳኛዋ እውቀት ለስሜት ቦታዋን ለቃ ዳር ሆና ከማየት በቀር ምንም ምርጫ የለም፡፡

ያልበሰለው የሃሳብ ብዝሃነትን የማስተናገድ ልምዳችን ትንታኔን ከሟርት አይለይም፡፡ትንታኔ ሟርት የሚሆነው በበቂ ማስረጃ ካልተደገፈ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የሃሳቡን ባለቤት በደፈናው ለማሸማቀቅ ከመራኮት ይልቅ ደካማ ክርክር ላይ የቆሙ የመሰሉንን ሃሳቦቹን ነቅሶ አውጥቶ የተሻለ የተባለውን ክርክር በማምጣት መሞገቱ መንገድን ለማጥራት ይጠቅማል፡፡በዚህ በኩል ነጮች እጅግ ይበልጡናል፡፡ ከአፍ የወጣ የፖለቲከኞችን ንግግር ቀርቶ የሰውነት መወራጨታቸውን(Gusture) በማጤን የፖለቲካ አቋማቸውን ይተነትናሉ፡፡ በግልፅ ከተባለው የፖለቲከኞቻቸው ንግግር በግልፅ ያልተባለውን (ግን ሊባል የተፈለገውን) ፈልፍለው አውጥተው ህዝባቸውን ያነቃሉ፡፡ ለምን ይህን አሉ ተብሎ ውርጅብኝ የለም! ስለዚህ ከስህተት ይድናሉ፣ፖለቲካቸው ከሞላ ጎደል የተፈወሰ ነው፡፡

በበዓለ ሹመቱ ንግግር ያደረገ መሪ ከሞላ ጎደል የፖለቲካ አቋሙ እና የትኩረት አቅጣጫው እሳት በላሱ ተንታኞች ብልቱ ተፈታቶ ምርቱ ከግርዱ ተለይቶ ይታወቃል፤ የንግግሩ ተዛነፎች ካለው የፖለቲካ ልማድ ጋር ተሰናስሎ ይብጠረጠራል እንጅ “ቀኑ ሲደርስ የሚሆነውን አብረን የምናየው ይሆናል” ማለት የሚያበዛ ተንታኝ የላቸውም፡፡ ቀኑ ሲደርስ ጉዳቱን አብሮ ለማየት ተንታኝ መጥራት ለምን አስፈለገ? በርግጥ ቀኑ ሲደርስ የሚታዩ ፣በፖለቲካ መሪዎች ልብ ብቻ ትክክለኛ ሁኔታቸው የሚታወቁ በጣም ጥቂት ጉዳዮች አሉ፡፡ እዚህ ጥቂት ጉዳዮችም “ሲደርስ እንያቸው” ተብለው ከመታለፍ ይልቅ ካለው እና ከነበረው የፖለቲካ ከባቢ በመነሳት አንዱ ካልሆነ ሌላው የሚሆንበትን አማራጭ የቢሆን አቅጣጫዎችን(scenario) ማሳየት ለሚችሉ በሳል ምሁራን እድል መስጠት እየመላለሱ ከመሳሳት ይታደጋል፡፡

የመሪዎች የበዓለ ሹመት ንግግር ትንታኔ እኛን በአሁን ወቅት እያነታረከ ያለውን ለጠ/ሚ አብይ ምን ያህል ጊዜ እንስጥ ለሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ጥሩ አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ የጠ/ሚው ንግግር አስተዳደራቸው ሊፈታቸው የሚችላቸውን እና የማይችላቸውን፣የእኛ ብርቱ ፍላጎት እና የሰውየው ትኩረት መግጠም አለመግጠሙን፣የሰውየው ስልጣን ምን ያህል ጉበታም ነው የሚለውን፣የሰውየው እውነተኛ ወገንተኝነትስ ለህዝብ ነው ለድርጅታቸው ወዘተ የሚሉ በጣም ጠቃሚ ሃቆችን ለመመርመር ጥሩ ፍንጭ ይሰጣል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ከስሜት እና ወገንተኝነት በፀዳ መንገድ እንመርምረው ከተባለ ብዙ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡ በበኩሌ ከጠ/ሚ ባዕለ-ሹመት ንግግር ውስጥ ስሜት ሰጭ ሆኖ ያገኘሁት ስለ ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ መስተጋብር ያነሱት እና ስለ እናታቸው እና ባለቤታቸው የተናገሩትን ብቻ ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ ስለኢትዮጵያ የተናገሩትን ያዳመጥኩት ከጥያቄ ጋር ነው፡፡ ስለኢትዮጵያዊነት እና ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ልባዊ ዕምነት ያለው ሰው እንዴት ከኢህአዴግ ጋር ተስማምቶ የጠ/ሚነት ማማላይ እስከመድረስ ደረሰ ከሚል ጥያቄ ጋር! የሆነ ሆኖ ንግግሩ ራሱ ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ነገር ስለሆነ በይሁንታ ቢታለፍ ችግር የለው፡፡

የማይታለፉትን ስናነሳ ጠ/ሚው ንግግራቸውን የጀመሩት “ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግስት አስተዳደር ስርዓቷ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በምታከናውንበት በዚህ ታሪካዊ ቀን በተከበረው ምክር ቤት ፊት ቀርቤ ይህንን ንግግር ለማድረግ ስለበቃሁ የተሰማኝን ልዩ ክብር ለመግለጽ እውዳለሁ።…….. የመንግስታዊ ስልጣን ሽግግሩ ያለ እንከን እንዲከናወን ልዩ ሚና ሲጫዋቱ ለቆዩት ሁሉ በመላው ህዝባችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ”(መስመር የእኔ) ብለው ነው፡፡ ቀጠል አድርገው “ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው!” ይላሉ፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ ሃገራችን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እያደረገች እንደሆነ የተቀመጠበት መንገድ ግር ሲያሰኝ ጭራሽ የስልጣን ሽግግሩ የሁለት ካድሬዎች የቦታ መለዋወጥ መሆኑ ቀርቶ መንግስታዊ የስልጣን ሽግግር እንደሆነ መነገሩ አስገራሚ ነው፡፡

መላላክ የደከመው ካድሬ ‘እስኪ አንተ ደግሞ ሞክረው’ ብሎ ከወንበር መነሳቱ የመንግስት ለውጥ ተደርጎ የሚቀርበው ለየትኛው ጥርስ ያላበቀለ ህፃን ነው? ነው ጠ/ሚው የመንግስት ለውጥ ማለት የሰው ብቻ ሳይሆን ፖሊሲ ለውጥ መሆኑን ያጡታል?አብዮታዊ ዲሞክራሲን የመሰለ ችኮ እና አርጄቶ የፖለቲካ መስመር አንግቦ ‘አዲስ መንግስት ነኝ’ ማለት እንዴት ነው? አዲስ መንግስት እና አዲስ ካድሬ ምን አገናኘው? ለዛውስ አብይ አዲስ ካድሬ ናቸው? ይሄንኑን የካድሬ ለውጥ ታሪካዊ ያደረገውስ ምንድን ነው? በኢትዮጵያ ህዝብ የለውጥ ፍላጎት ላይ ተንጠላጥሎ የከረመውን የኦህዴድ የስልጣን ሃራራ ማርካት ታሪክ ተሰራ የሚያስብለው ጥሙ ለረካለት ስልጣን አምላኪ ብቻ እንጅ አብዮታዊ ዲሞክራሲን አንቅሮ ለተፋው የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም፡፡ይህ የስልጣን ሽግግር እንደተካሄደ የማስመሰል ንግግር ህዝብ የሚፈልገው እውነተኛ ለውጥ የመጣ በማስመሰል የህዝብ ጥያቄ ተዳፍኖ እንዲቀር ማድረጊያ ኢህአዴጋዊ ዘዴ ነው፡፡

በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ውስጥ ተሁኖም ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ሰው ካለ በዱላ ቅብብል ተሰናበቱ የተባሉት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ክርስትና አባቶች ምን ተብለው እንደሆነ መልስ በሌለው ሁኔታ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ውስጥ መገኘታቸው፣ ሄድኩኝ ያሉት አቶ በረከት ፖለቲካዊ ህልውና በሃገራች ፖለቲካ ላይ መመለሱን የሚያመላክቱ ነገሮች መኖራቸው፣ሰው ባልጠፋበት ሃገር ዲሞክራሲን አስረው የሚገርፉ ሰዎች የዲሞክራሲ አስተናባሪ ተብለው ለውጥ አመጣለሁ በሚሉት ጠ/ሚ አናት ላይ ጉብ መደረጋቸው፣በፓርላማ ስለነፃነት እየተወራ ባለበት ቅፅበት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መኖራችን፣ ስለ አስተሳሰብ ነፃነት እየተወራ ለኢትዮጵያ ደግ በማሰባቸው ብቻ ነፃነት ቀርቶ የእግዜር ፀሃይ ብርቅ በሆነበት እስርቤት የታጎሩ እንደ አንዳርጋቸው ፅጌን የመሰሉ ብዙዎች መኖራቸው፣ ይህ ንግግር ከተደረገ በኋላ፣ዶ/ር አብይም እውነተኛ ጠ/ሚ ነኝ ካሉ ማግስት እነ ስዩም ተሾመ፣እነ እስክንድር ነጋ ወደ እስር መጋዛቸው ወዘተ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ለውጥን መጠበቅ ህወሃት ስታገል ሞቱብኝ የሚላቸውን ስልሳ ሽህ ሰማዕታት ከሞት ከማስነሳት ጋር ቁርኝት እንዳለው ያመላክታል፡፡ ሰማዕታቱን ከሞት አስነስቶ ለህወሃት የመመለስ “ብቃት” ያለው ብቻ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር እውነተኛ ለውጥ መጠበቅ ይችላል፡፡

ጠ/ሚ አብይ ስለዚሁ “የስልጣን ሽግግር፣የመንግስት ለውጥ” ሲቀጥሉ ይህን ይላሉ “ይህ የሥልጣን ሽግግር ሁለት አበይት እውነታዎችን የሚያመላክት ነው። ክስተቱ፣ በአንድ በኩል በሀገራችን ዘላቂ፤ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ የህገ-መንግሥትታዊ ስርዓት መሰረት ስለመጣላችን ማሳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ሁኔታዎች ጋር እኩል የሚጓዝና በህዝብ ፍላጎት፤ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያገለግል ሥርዓት እየገነባን መሆኑ ያመለክታል። …………. መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመሩን አጥብቆ በመያዝ ሀገራችንን ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ባስተዳደረበት ወቅት በሁሉም መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግሥታዊና ፌዴራላዊ ሥርዓት ገንብቷል። ዓለም በአንድ በኩል በጥሞና፣ በአግራሞትና በጉጉት በሌላ በኩል ደግሞ በስጋት እየተመለከተው ያለ ሀገራዊ ለውጥ ላይ እንገኛለን፡፡” ከላይ የእሳቸውን ወደስልጣን ያመጣው ክስተት እንዴት እንደሆነ ባልገባኝ መንገድ በሃገራችን ዘላቂ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግሰታዊ መሰረት ስለመጣሉ ማስረጃ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የተረጋጋ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የጣለ መንግስት አለም ጉድ እስኪለው ሶስት አመት ባልሞላ ጊዜ ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ ድረስ ማጣፊያ ያጠረው ለምንድን ነው? ወይስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማግተልተልም የመረጋጋት እና ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የመገንባት ምልክት ነው ልንባል ነው? ስምንት መቶ ሽህ ኦሮሞዎችን በቅርቡ ከኢትዮ-ሶማሌ ክልል፣ ማንም ነገሬ ብሎ ያልቆጠራቸውን አማሮች ከመላ ሃገሪቱ ሃያ ሰባት አመት ሙሉ ሲያሰድድ ሲያፈናቅል የኖረውን የጎሳ ፌደራል ስርዓትም በሁሉ መስክ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ህገ-መንግስታዊ ሲሉ አሞካሽተዋል፡፡ ይሄን ሁሉ ህገ-መንግስታዊ መረጋጋት መሪ ድርጅታው ኢህአዴግ እንዳመጣ የነገሩን ሰውየ ወዲያውኑ ዓለም ስጋት እና አድናቆት በተሞላበት ግርታ ያየናል ይላሉ፡፡ አድናቆቱ መጣ ባሉት ድንቅ መረጋጋት ነው ቢባል ስጋቱ በምንድን ነው?

አጋር ድርጅት በሚባል አግላይ አካሄድ ጠ/ሚ አብይ ሃሴት ያደረጉበትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ለመመኘት እንኳን የማይችሉ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ባሉበት ሃገር ‘እኔ መሾሜ ሁሉን አቀፍ ህገመንግስታዊ ስርዓት የመምጣቱ ማሳያ ነው’ ማለት ምን ማለት ነው? ይህን በተመለከተ ጠ/ሚው አቶ ለማን አስከትለው ወደ ኢትዮ-ሱማሌ በተጓዙ ጊዜ አንድ የኢትዮ-ሱማሌ ተሰብሳቢ “የእርስዎ እናት የሃገር መሪ እንደሚሆኑ እንደነገረችዎት የኢትዮ-ሱማሌ እናቶችም ጠ/ሚ ልጅ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ እኮ!” ሲል በነገር አዋዊ ሰው ንግግር ብዙ ያወሩለትን ስርዓት አግላይነት በደንብ ነግሯቸዋል፡፡ ሁሉን አቀፍ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት አመጣ የተባለው ህገ-መንግስት ራሱ የአማራን ህዝብ የሚያክል ብዙ ቁጥር ባለው ህዝብ ላይ በር ተዘግቶ የተፃፈ የቂም-በቀል ዶሴ እንደሆነ ለማን ይጠፋዋል? በሁለተኝነት የተቀመጠው እና አሁን በሃገራችን ያለው ስርዓት ከኢኮኖሚ፣ከፖለቲካ እና ከማህበራዊ ለውጦችን አገናዝቦ እኩል የሚጓዝ ነው ተባለው የተለመደው የካድሬ ስድብ ይመስለኛል፡፡

አገር ኦና እስኪቀር ድረስ ወጣቶቿን በኢኮኖሚ ችግር ሳቢያ እግራቸውን ነቅለው በሚሰደዱባት ሃገር፣ሰው በፖለቲካ አቋሙ ብቻ ታስሮ በሚገረፍባት ሃገር፣ወዳጅ ዘመድ እንዳይጎበኘው ዘመዶቹ በቀላሉ በማያገኙበት እስርቤት በሚወረወርበት፣ ከቤተሰብ ተመርጦ የሰማኒያ አምስት አመት ሽማግሌ ብቻ ስንቅ ያቀብል በሚባልበት የመርገም ሃገር፣ ራሳቸው አዲስ ነኝ ባዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ስራቸውን የጀመሩት ዘመን አመጣሹን ማህበራዊ ድህረ-ገፅ በመርገም መሆኑን እያወቅን ‘ከለውጥ ጋር ተራምዶ ህዝብን አለቃው አድርጎ የሚያረካ ስርዓት መስርተናል’ ማለት የተለመደ ካድሬያዊ ልብ-አውልቅነት ነው፡፡

በሌላው በንግግራቸው ያነሱት ሃሳብ ዲሞክራሲን፣ሰብዓዊ መብትን እና የሃሳብ ልዩነትን በተመለከ ነበር፡፡ ይህን ይላሉ “አሁንም ዲሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም ሀገር በላይ ለኛ የሕልውና ጉዳይ እንደሆነ እናምናለን። ዲሞክራሲ ያለነጻነት አይታሰብም። ነጻነት ከመንግስት ለሕዝብ የሚበረከት ስጦታ አይደለም። ከሰብዓዊ ክብር የሚመነጭ የእያንዳንሱ ሰው የተፈጥሮ ጸጋ እንጂ። ……. መንግሥት የሕዝብ አገልጋይ ነው። ምክንያቱም ገዥ መርሃችን የህዝብ ሉዓላዊነት ነውና። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ውስጥ፣ የመጀመሪያው የመጨረሻውም መርህ፣ በመደማመጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ መሆን አለበት።”

ዲሞክራሲ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተቃዋሚ እግር ሲያወጣ እግሩን፣ምላስ ሲያበዛ ምላሱን እቆርጣለሁ ሲሉ የነበሩት አቶ መለስም የተናገሩት በተግባር የማይታይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊያን የአፍ ማሟሻ ነው፡፡ዲሞክራሲ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ እየተነገረ አምባገነንነቱ እያደር ብሶት በአስቸኳጊዜ አዋጅ የሚመራ ወታደራዊ ቅጥ አስተዳደር ላይ ደርሳለች፡፡ ይህን የሚያወሩት ሰውየም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን ስልጣን ላይ ለመሰየም ከሃይኛው ጋር ተፋልመዋል፡፡ የሴት ልጅ አስር ጥፍር የሚነቅል፣የመነኩሴ ቆብ በድብደባ የሚቀድ፣ወንድ ልጅ የሚያኮላሽ፣የሰውን ልጅ እንደክርስቶስ የሚሰቅል ስርዓት አልጋይ ሆኖ ሩብ ምዕተ አመት የኖረ ሰው ስለ ሰብዓዊ ክብር ለማውራት ቢያንስ ዛሬ ያለሃጢያታቸው የምድር ገሃነም ውስጥ የሚሰቃ የፖለቲካ እስረኞችን ፈቶ ማሳየት አለበት፡፡ ጠ/ሚ አብይ የተቀመጡት በአቶ ኃ/ማርያም ሳይሆን በአቶ መለስ ወንበር ከሆነ፣ስለ ሰብዓዊ/ዲሞክራሲያዊ መብት ሚያወሩት ከልባቸው ከሆነ የፖለቲካ እስረኛ ፈቶ መልቀቀ የግማሽ ቀን ስራ የማይጠይቅ ቀላል ጉዳይ ነው፡፡ይህን ካላደረጉ የተቀመጡት በአቶ ኃ/ማርያም እንጅ በአቶ መለስ ወንበር ላለመሆኑ አስረጅ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ወንበር የተቀመጠ ሰው ደግሞ የስልጣን ጥሙን ከማርካት በቀር አንዳች አይፈይድምና የሚናገረውን ቀነስ አድርጎ ስልጣን ላይ የመወዘት ስሜቱን ማጣጣም ብቻ ነው ያለበት- ንግግር ዕዳ ነዋ!

ስለ ዲያስፖራው በተነናገሩበት ንግግር ይህን ተናግረው ነበር “ኢትዮጵያዊውን ከኢትዮጵያ ታወጡት እንደሆነ ነው እንጂ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊው ልብ ውስጥ አታወጧትም የሚባለውም ለዚህ ነው።…….አንዳንድ ጊዜ ከኢትዮጵያ ያነሰ የተፈጥሮም ሆነ የታሪክ ሀብት ባላቸው ነገር ግን እጅግ በበለጸጉ ሃገራት ውስጥ ራሳችሁን ስታገኙት ስለሃገራችሁ ቁጭት ሳይሰማቹ አይቀርም። ሁላችንም ውስጥ ያ ቁጭት አለ። …..ይሄንንም ሁኔታ ለመለወጥ ለሁላችንም የምትበቃ በዚያው ልክ ግን የሁላችንንም ተሳትፎ የምትፈልግ ሀገር አለችንና እውቀታችሁንና ልምዳችሁን ይዛችሁ ወደ ሃገራችሁ መመለስና ሃገራችሁን አልምታችሁ መልማት ለምትሹ ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላችኋለን።” ኤርሚያስ አመልጋን፣ አቶ ገብረየስ ቤኛን፣የሆላንድ ካርስ ባለቤትን፣ዶ/ር ፍቅሩ ማሩን መጨረሻ ያየ በዚህ ንግግር ላይ ልብ ለመጣል እነዚህ ሰዎች በስም ተጠርተው በይፋ ይቅርታ ተጠይቀው፣ በደላቸውን በግልፅ ተናግረው ወደ ነበሩበት ቢዝነስ ይገቡ ዘንድ መልካም ፈቃዳቸው እንዲሆን መለመን አለባቸው፡፡ በአንፃሩ ኤርሚያስ አመልጋ ማዕከላዊ መንገላታቱ ሳያነስ ለዚህ ሁሉ የዳረገውን ጠመንጃ ታጣቂም፣ ነጋዴም፣ደላላም የሆነ ባለጊዜ ስም ለመጥራት ሲቸገር በጆሯችን ሰምተናል፤ መበለዱ ሳያንስ ልውጣ እያለ የሚተናነቀውን እውነት፣ ውስጡን የሚያብሰለስለውን በደል ለመዘርዘር ድጋሜ የመታሰር ስጋት ሲወረው አይተናል፡፡ እውን ዶ/ር አብይ የሚመሰርቱት ስርዓት ኤርሚያስን ለዚህ ያበቁ ባለጊዜዎችን የመጋፈጥ ጉልበቱ ካላቸው የኤርሚያስ እውነት ተፍረጥርጦ ይውጣ! የሃገራቸውን ህዝብ ለማገልገል ባህር አቋርጠው የመጡትን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም በአስቸኳይ ይፈቱ፡፡ ይህ የመለወጥ ምልክት ሆኖ ሌላውን ሊጠራ ይችላል እንጅ ዝም ብሎ ኑኑ ማንንም አያሳምንም፡፡

“በአገር ውስጥም ሆነ በስደት ከአገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከልባችን ይቅር ተባብለን፣ የትናንትናውን ምእራፍ ዘግተን፣ በብሔራዊ መግባባት ወደ ቀጣይ ብሩህ ሀገራዊ ምእራፍ እንሻገር ዘንድ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡” የሚለው የንግግራቸው ሌላ አንጓ ብረት አንጋች ተቃዋሚ ስደተኛ ወገኖችን ይጨምር አይጨምር ከንግግሩ ፍንጭ ማግኘት አይቻልም፤ ሰውየውን አግኝቶ በጉዳዩላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ለማድረግም በሃገራችን ያለውን የመሸዋወድ፣የማድበስበስ እና የማሞኘት ፖለቲካ ከሚያገለግሉ የመንግስት ሚዲያዎች ሚጠበቅ አይሆንም፡፡ሆነ ሆኖ ዲያስፖራው የኢትዮጵያ መንግስት ከሃገር ልጅ ወገንነቱ ይልቅ ዶላሩን አጥብቆ እንደሚወድ አሳምሮ ያውቃል፡፡ መንግስት የዲያስፖራውን ዶላር የሚወደውን ያህል ዲያስፖራው ደግሞ የሃገሩን ፖለቲካዊ ፈውስ አጥብቆ ይሻል፡፡በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ስደተኛውን ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አፍኖ አምጥቶ አላየሁም ከማለት ጀምሮ በዘመድ ወዳጅ አላስጎበኝም እስከማለት በደረሰ ጭካኔ እና መገመት በማያዳግት የሲኦል ኑሮ ውስጥ ካስቀመጠ ወዲህ የኢትዮጵያን መንግስት አያሳየኝ ብሏል፡፡ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ልጆቻቸውን በትነው፣ሞቀውን ከተማ ለንደንን ደህና ሁኚ ብለው ወደ ትጥቅ ትግል ለመውረድ የወሰኑት ዲያስፖራው በአንድ ስብሰባ ላይ “እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ የምን ትግል ነው የምታወሩት?” ካላቸው ቀን ጀምሮ እንደሆነ በወያኔ እጅ ሳይወድቁ ተናግረዋል፡፡ የትጥቅ ትግል በዞረበት ዞሮ የማያውቅ ይመስል የትጥቅ ትግልን እንደ ሰይጣን ስራ የሚያወግዘው ህወሃት/ኢህአዴግ ታዲያ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በረሃ ያበረረው አላማ ዶላሩን የሚናፍቁት አብዛኛው ዲያስፖራ አማራጭ ከማጣት የተነሳ የሚጋራው መንገድ እንደሆነ ቢያውቅም ማመን አይፈልግም፡፡ ጠ/ሚ አብይም ይህን የህወሃት ሃሳብ እንደሚጋሩ ከሰሞኑ ‘እኛን የሚጠላን ፌስቡክን ብቻ የመረጃ ምንጭ ያደረገው አንድ ፐርሰንቱ ዲያስፖራ ነው’ ባሉት ንግግራቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል እንዲህ ያለውን ነጭ ክህደት እየካዱ በሌላ በኩል ደግሞ ኑ እንግባባ ማለት እንዴት አብሮ ይሄዳል? የውጭ ምንዛሬ ድርቅ የመታው የኢህአዴግ መንግስት ከዲያስፖራው ጋር ለመታረቅ ሳይሆን የጥል ግድግዳን በጣም በመጠኑ ለማቅለል አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን ነገ ዛሬ ሳይል መፍታት አለበት፡፡

የኢህአዴግን መንግስት የሚቃዎሙ ተቃዋሚዎችን እና በአውራ ነኝ ባዩ ኢህአዴግ መካከል ስለሚኖረው መስተጋብር በተመለከተ በሰነዘሩት ንግግርም ይህን ብለዋል “ከኢህአዴግ ውጪ ያሉ ፓርቲዎችን የምናይበት መነጽር እንደተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ፣ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም፣ አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ አገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነው፡፡ ስለዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የተመቻቸና ፍትሃዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲኖር በመንግስት በኩል ጽኑ ፍላጎት ያለ በመሆኑ ስለሰላምና ፍትህ በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ አብሮነታችንንና ሰላማችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንንም አሳልፈው የሚሰጡ የአስተሳሰብ መስመሮችን በአርቆ አስተዋይነትና ሀገራዊ ፍቅር፤ በሰጥቶ መቀበል መርህ የተሻለ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት እንድታግዙ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡” ይሄ ተቃዋሚዎችን እንደ ወንድም እና ባለ አማራጭ ሃሳብ ሃገር ወዳድ እንጅ እንደጠላት አናይም በሚለው ጠ/ሚ አብይ ንግግር የጠረጠርኩት የኢህአደግን መቀየር ሳይሆን የጠ/ሚውንየአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፅንሰሃሳብ ግንዛቤ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተቃራኒው የቆሙትን ቀርቶ አጋር ድርጅት ብሎ በፓርላማ እጃቸውን እያስወጣ የፈለገውን ህግ እንዲተገብር የሚያደርጉትን አጋር ድርጅቶች እንደሌላ አይቶ ከዋነኛ ስልጣን እጣፋንታ የሚከለክል አግላይ ድርጅት ነው፡፡

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተቃዋሚዎችን መጥፋት ያለባቸው እኩዮች አድርጎ ያያል፣በፀረ-ሰላምነት ይከሳል፣በሃገር ካጅነት ይወነጅላል፡፡ የተቃዋሚዎች መኖር በደሜ በላቤ አመጣሁት የሚለው ልማታዊ መንግስት ተረገግቶ የማቱሳላን እድሜ እንዳይገዛ የሚያደርግ ተደርጎ ይታሰባል-በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወግ፡፡ ልማታዊው የኢህአዴግ መንግስት ማንም ሳይረብሸው ከዚህ በኋላ ለሃምሳ አመት ወንበሩላይ ተረጋግቶ ቁጭ ብሎ፣በአንድ ልቡ ልማቱን ማስቀጠል እንደሚፈልግ ከ1997 በኋላ ሳያፍር የሚያወራው የፖለቲካ መስመሩ ነው፡፡ አውራ ፓርቲ እና ልማታዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የሚሉትን ተግተልታይ ቃላት የወለደው ይሄው ረዥም ዘመን ስልጣን ላይ የመሰንበት እቅዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነፍስ ያላቸውን ተቃዋሚዎች መንጥሮ ወንበሩን ለክፉ ከማይሰጡ ፌዘኛ ተቃዋሚ መሰል ቤተ-ዘመዶች ጋር ማዝገሙን መርጧል፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እውነተኛ ማንነት ይህ ሆኖ ሳለ ጠ/ሚ አብይ ይህን ዲስኩር የሚያሰሙት ወይ ራሳቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲን በውል አያውቁትም ወይ ለተቃዋሚዎች ከልክ በላይ የወረደ ግምት አላቸው፡፡ “በልዩ ልዩ መንገድ የምትታገሉ” የምትለዋ ሃረግ ምናልባት የሃገርቤቱንም የውጭ ሃገሩንም ተቃዋሚ የመጥራት አላማ/ተግባር ካላት ነው ኢህአዴግ እውነትም ተቃዋሚን እንደ ባለ አማራጭ ሃይል ወስዷል ማለት የሚቻለው፡፡ ይህ ደግሞ ገና ሃምሳ አመት ስልጣን ላይ ሊወዘት ባሰበ ፓርቲ የሚደረግ ነገር አይመስለኝም!

ተዝካሩ ስለተበላው የሃገራችን የትምህርት ጥራት ጉዳይ እና እንደማይሆን ሆኖ የተበላሸው የፍትህ ስርዓታችንን እንደቀላል ነገር እናስተካክላለን ሲሉ ቃል የገቡበትን ንግግር በተመከተ ፈጣሪ ይርዳዎ ብሎ ከማለፍ በቀር ምንም ማለት አልችልም፡፡ ይልቅስ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሕዝባችንን ብሶት ካጋጋሉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ ሙስና አንዱ ነው።” ወዳሉበት ንግግር ልለፍ፡፡ እውነት ነው ሙስና የሃገራችንን ህዝብ አማሯል ግን ነገሩ የሚጠፋው እሳቸው እንዳሉት የምንችለውን በማድረግ ብቻ አይደለም፡፡ ሙስና የሚሞተው ራሱ የእሳቸው ፓርቲ ሲሞት ብቻ ነው፡፡ የነገሩ ጥልቀት እና ስፋት ከእርሳቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ አቅምም በላይ በሆነ ሁኔታ በጠመንጃ ታግዞ የሚደረግ ሥሩ ጠለቅ፣ አሰራሩ ረቀቅ ያለ ወንጀል ነው፡፡ ሙስናን እናጥፋ ከሚለው ንግግራቸው ጋር ያለው ሌላ ወለፈንዲያዊ ንግግር ይህ ነው “ትናንት የተፈጠረን ሃብት ከሌላው በመቀማት ሂሳብ ለማወራረድ የሚተጋ አገርና ሕዝብ ወደፊት ለመራመድ አይችልም። ገበታው ሰፊ በሆነበት፣ ሁሉም ሰርቶ መበልጸግ በሚችልበት ኢትዮጵያችን አንዱ የሌላውን ለመንጠቅ የሚያስገድድ ይቅቅርና የሚያሳስብ ምንም ምክንያት ይለም። ይልቁንም ወቅቱ የፈጠረልንን ልዩ አጋጣሚና ሀገራዊ አቅማችንን አቀናጅተን የእጥረትና እጦት አስተሳሰብን በማስቀረት ለጋራ ብልጽግና እንትጋ።” ትናንት የተፈጠ ሃብት ማለት የነማን ሃብት ነው?ይህን የሚሉት ለማን ‘የተረጋጉ’ ዋስትና ለመስጠት ነው? በአሁኗ የሃገራችን ሁኔታ ሚበዙቱ ባለሃብቶች ከጤናማ የንግድ ስርዓት በተፋታ የሙስና መንገድ በአንድ ቀን ሰማይ ጠቀስ የሃብት ማማላይ የሚወጡቱ እንጅ በጤናማ የንግድ ስርዓት፣በእውቀት ላይ በተመሰረተ ንግድ ለፍተው ሃብት የሚያከማቹት መጨረሻቸው አይምርም፡፡ እና ‘ትናንት የተፈጠረ ሃብት በመቀማት ሂሳብ ማወራረድ’ ማለት ምን ማለት ነው? ዘርፎ ቱጃር የሆነው ሁሉ በዘረፈው ምስኪን ህዝብ ከሲታ ኢኮኖሚ እያላገጠ ያለተጠያቂነት ይኑር ማለት ነው? “ወቅቱ የፈጠረው ልዩ አጋጣሚ” ያሉትስ ቢሆን እነዚህን ደራሽ ቱጃሮች ያገለግል ይሆናል እንጅ ለሌላው ህዝብ ምን ፈይዶለታል? ራሱ ወቅቱ የፈጠረው ልዩ አጋጣሚ ማለት ምን ማለት ነው? ስለ የቱ አጋጣሚ ነው የሚናገሩት? ‘እንዲህ ስላሉት ሰዎች ብዙ ሳትመራመሩ ያው በገሌ እያላችሁ ኑሩ’ መሰለኝ አባባሉ! እንዲህ ባለው ንግግር እና “አሁን በጀመርነው አዲስ ምዕራፍ፣ ዘረፋን፣ የሀብት ብክነትን እና የተደራጀ ሙስናን፣ መላው ህዝባችንን በሚያሳትፍ እርምጃ ለመመከት ሌት ተቀን እንተጋለን።” ሲሉ በጠቀሱት ሙስናን የመዋጋት ጥሪ መሃከል እንዴት ያለ ግንኙነት አለ? ነው ሞስነው ግን ገና ሃብት ያልመሰረቱት አዲስ ጅቦች ላይ ነው ትኩረታቸው? እንዲህ የማይገናኝ ነገር ከማውራት አቅማቸው የማይፈቅደውን፣ከማይጋፉት ባለጋራ ጋር የሚያላትማቸውን የሙስናን ነገር አለማንሳት ነበር የሚሻለው-ልክ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ትንፍሽ እንዳላሉት!

በመጨረሻም “ዘረኝነትና መከፋፈልን ከአገራችን እናጥፋ! የተማረና በምክንያት የሚከራከር ዜጋ እንፍጠር!” ሲሉ ጥሩ ነገር አምጥተውዋል፡፡ ግን ይህም የተነገረው ኦሮሞነታቸው ወደስልጣን ጎትቶ ባመጣቸው ሰው በመሆኑ የሃሳቡ ሞገስ ይኮሰምናል፡፡ ከምክንያታዊነት ጋር አንዳች ተዛምዶ በሌለው የጎሳ ፓርቲ ውስጥ ተቀምጦ፣ዘርን ብቻ ቆጥሮ ስልጣን ላይ ከተሰየሙ በኋላ ዘረኝነትን ከሃገር እናጥፋ፣ምክንያታዊነትን ከሰማይ እናውርድ ማለት የተናጋሪውን ጤንነት ወይም ቅንነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነገር አለው፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

የኦህዴድ ጉዞ ስንክሳር (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
መጋቢት 24 2010 ዓ.ም.

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

ህወሃት አንጉቶ ከጋገራቸው አጋር እና አባል የብሄር ፓርቲዎቹ ውስጥ እንደ ኦህዴድ አጉረምራሚ የለም፡፡ “የማይገሰስ የማይደፈር” አምባገነንነት ላይ ደርሶ የነበረውን የአቶ መለስ ዜናዊን ጠንካራ ክንድ ለመጀመሪያ ጊዜ “ሃይ” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ከኦህዴድ ወገን ናቸው፡፡መቃለል መናቁ የሰለቻቸው ዶ/ር ነጋሶ ስልጣናቸው ቀርቶ ህይወታቸው ሊገጥመው የሚችለውን አደጋ ለመቀበል ቆርጠው ልክ የመሰላቸውን አድርገዋል፡፡ይህ የመጀመሪያው ኦህዴድ ለህወሃት የላከው የእምቢተኝነት መልዕክት ነው፡፡ ሆኖም ጌታን አንጓጦ በጌታ እልፍኝ መምነሽነሽ አይቻልምና ዶ/ር ነጋሶም ሁሉን ትተው ክብራቸውን ብቻ ይዘው ይኖራሉ፡፡

ከዶ/ር ነጋሶ ሌላ አቶ ሽፈራው ጃርሶ እና አቶ ጁነዲን ሳዶም “ድርጅቱ” እስከመባል ገዝፈው የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ይጠየቁ ዘንድ የማይሿቸውን፣ካድሬ ሁሉ “ውሾን ያነሳ” ብሎ የተዋቸውን እንደ ኢፈርት ጉዳይ ያሉ አይነኬ አጀንዳዎች በህዝብ ዘንድ ምን ያህል እያነጋገሩ እንደሆነ አንስተው አቶ መለስን ቱግ ያደርጉ እንደ ነበር በኮብላይ ካድሬዎች ተፅፎ አንብበናል፡፡ ከምርኮኛ መኳንንት ነፃ የወጣው የአሁኑ ኦህዴድ ደግሞ በኢትዮጵያ ሶማሌ ይኖሩ የነበሩ ኦሮሞ ተወላጆች መፈናቀል በጌታው ህወሃት ላይ ክፉኛ እንዲያመር ሳያደርገው አልቀረም፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስቆጣ ምን ቢክሱት የማይጋርዱት ክፉ ግፍ ነው!

ኦህዴድን ከጭቃ አቡክቶ እስትንፋስ እፍ ያለበት ህወሃት ቢሆንም ታሪክ የመዘገበው የኦሮሞ ብሄርተኝነት እድሜ ከዚህ ዘለግ ያለ ነው፡፡በኢትዮጵያ ውስጥ በብሄር ተደራጅቶ ማህበር አቋቁሞ ስለዘውጉ ለመምከር፣የዘውግ ብሄርተኝነትን መንፈስ ቆሜለታለሁ በሚለው ህዝብ ልቦና ለማስረፅ የኦሮሞው ሜጫ ቱለማ ቀዳሚው ነው፡፡ሜጫ ቱለማ ሄዶ ሄዶ ኦነግን ወለደ፡፡ኦነግ ደግሞ ስሜትን ከእውነት እደባለቀ በተበዳይነት ላይ የቆመ ሆደባሻ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን አጧጧፈ፡፡

በአካል በህወሃት የተነጎተው ኦህዴድም የዚሁ የኦነግ የተበድየ ፖለቲካ መንፈሳዊ ውላጅ ነው፡፡ይህ ነገር ነው አቶ መለስን በአንድ ወቅት “ኦህዴዶች ጀርባችሁ ቢላጥ ኦነግ ናችሁ” እስከ ማለት አድርሷቸው ነበር የሚባለው፡፡ኦህዴድ ብዙ ገንዘብ አፍስሶ የአኖሌን የቂም ሃውልት ያስቆመውም የኦነግ መንፈስ እንጅሌላ አይደለም፡፡ዛሬ ዋናውን የስልጣን እርካብ ለመርገጥ ዳርዳር ሲሉ ኢትዮጵያዊነትን ይሰብኩ የያዙት የኦህዴድ ካድሬዎች እነ ኦቦ ለማ መገርሳም የአኖሌን ሃውልት ከበው ፎቶ ከሚነሱት ወገን ነበሩ፡፡ከሜጫ ቱለማ ጀምሮ ስሩን የተከለው እና እያደገ የመጣውን የኦሮሞ ብሄርተኝትን ማንገቡ ለኦህዴድ ከሌሎች አቻ የኢህአዴግ ፓርቲዎች በተሻለ የብሄር ፖለቲካውን ብልት ለመረዳት ሳይጠቅመው አልቀረም፡፡ይህም በጎሳ ፖለቲካ ደቆንኩ በሚለው ህወሃት ላይ ኦህዴድ ቄስ ለመሆን መሞከርን እንዲደፍር አድርጎታል፡፡

የተሟላ አምባገነንነትን ጨብጠው የነበሩት አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት ኦህዴዶች ከመመኘት በቀር ጮክ ብለው ተናግረውት የማያውቁትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ዛሬ የጌታን ክንድ መዛል ተንተርሰው ከመመኘት አልፈው ጨብጠውታል፡፡ከኦሮሞ የተወለደ ሰው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋና ሆኖ ማየት በኢህአዴግ እልፍኝ ያለውን ኦህዴድም ሆነ በተቃውሞው ጎራ ያሉትን የኦነግ ስብርባሪ ፓርቲዎች፣ ግለሰብ አክቲቪስቶች በጋራ የሚወዘውዝ ብርቱ ናፍቆት ነው፡፡

አሁን የዶ/ር አብይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር መውጣት የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሽው ያለበትን ሁሉ ልብ በደስታ እያዘለለ ነው፡፡የሃሳብ ብልጫ ሳይሆን የዘር ሃረግን ቆጥሮ ፖለቲካን ለሚቀምር ይህ በቂ የደስታ ምክንያት መሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡ወንበሩ ምን አይነት ነው? ምን ሊያሰራ ይችላል? ወደ ስልጣን የመጡት ሰውየስ በምን አይነት ፖለቲካዊ ዳራ የሰነበቱ ናቸው? የሚለውን ለማጤን የብሄር ፖለቲካው የስሜት ፈረስ ፋታ አይሰጥም፡፡ይሄው የስሜት ፈረስ ለውጥን አጥብቆ የመሻቱን ያህል አጥብቆ መስራቱ ወደ ማይሆንለት፣ይልቅስ ለውጥን በቀላሉ እና በአቋራጭ ወደ ሚመኘው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛውንም ሳይጋባ አልቀረምና ምኞትን እና እውነት ያላማጠኑ የሚመስሉ ትንታኔዎችን እንሰማ ይዘናል፡፡

የኦህዴድ የማርሽ ለውጥ

አብዛኛው ለውጥ ፈላጊ ዜጋ የአቶ ለማ መገርሳን ኦህዴድ የለውጥ ተስፋ ማድረግ የጀመረው ኦህዴድ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ የሚታወቅበትን የተበድየ ፖለቲካ ውላጅ የሆነውን የአግላይነት ስብከት ቀየር አድርጎ ድንገት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማቀንቀን በመጀመሩ ነው፡፡ይህ የማርሽ ቅየራ በሚገባ ተሰላስሎ የተደረገ ሳይሆን ፈጣን እና ድንገቴ ሆኖ ይሰማኛልና እንደወረደ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ ጥርጣሬየን የሚያበረታው ደግሞ በአጠቃላይ ለኢህአዴግ አባልም ሆነ አጋር ድርጅት ካድሬዎች የግንዛቤ ደረጃ ያለኝ ግምት ነው፡፡ሁሉም ለማለት በሚያስችል ሁኔታ የኢህአዴግ ካድሬዎች የፖለቲካ እምነታቸውን የሚያነሱትም ሆነ የሚጥሉት በነጠረ ሳይንሳዊ ግንዛቤ ላይ ተመርኩዘው አይመስለኝም፡፡ ይልቅስ የኢህአዴግ ካድሬዎች ‘ምን ብል የበለጠ አተርፋለሁ?’ በሚል ስሌት ይመስለኛል ፖለቲካዊ መንገዳቸውን የሚነድፉት፡፡ይህ በኢህአዴግ ቤት መኖር የሚያመጣው አድርባይነት ወለድ ችግር ነው፡፡አድርባይነት የኢህአዴግ ካድሬዎች ዋና ምልክት ነው፡፡
የኢህአዴግ ካድሬ አድርባይነት ልማድ መጥፎ ገፅታው የአቋም ለውጥ ሲደረግ የአቋም ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት በአጥጋቢ ሁኔታ አያስረዳም፡፡ይህ የሚሆነው አንድም የቀድሞው አቋምም የሆነ ቀን አትራፊ ነገር ይዞ ሊመጣ ስለሚችል እርግፍ አድርጎ ለመተው ስለማይፈልግ ይሆናል ሁለትም ፖለቲካዊ ትርፍን ከማለም ባለፈ የአቋም ለውጡ ያነገበው አንዳች ሳይንሳዊ ግንዛቤ ስለሌለ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት አቋም ቀይረናል ካሉ በኋላም ሳያውቁት የቀድሞው እምነታቸውን በንግግራቸው መሃል ሲደነቅሩ ያጋጥማል፡፡ለምሳሌ አቶ ለማ መገርሳ አዲሱን አቋማቸውን ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው ሲሉ የተናገሩት ከህዝብ ጆሮ ሳይወርድ በሁለት ሳምንቱ በኢህአዴግ ስራ አስፈፀሚ ስብሰባ ላይ መግለጫ በሚሰጡበት አጋጣሚ ደግሞ ‘ኢትዮጵያዊነት የተጫነብን ማንነት ስለሆነ ቀስ እያለ ነው በህዝቡ ውስጥ መስረግ ያለበት’ ብለው ቁጭ አሉ፡፡በምክንያት ለሚያምን ሰው ደግሞ ይህን አይነቱን የመገላበጥ እና ምክንያት አልቦ ስሜት ተከትሎ ለማጨብጨብ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡

የኢህአዴግ አድርባይ ካድሬዎች ሌላው ችግር ቀድሞ ያራምዱት የነበረው አቋም እና እምነት ላስከተለው ችግር ሃላፊነት ወስደው፤ለጥፋታቸው ይቅርታ ሳይጠይቁ ለሰሚ የሚያስደስት የሚመስላቸውን አዲሱን አቋም ልክ አብሯቸው የተወለደ ሃሳብ አስመስለው ማነብነባቸው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬ ላይ ድንገት የኢትዮዮጵያዊ ብሄርተኝነት ሱስ ወረደብኝ የሚለው የነለማ መገርሳ ቡድን ደርሶ አዲስ አቋም ማራመዱ ሃያ ስድስት አመት ሙሉ ከህወሃት ስር ስር እያለ ሲያራምደው የነበረው የጎሳ ፖለቲካ ላስከተው ሃገራዊ ኪሳራ ከህወሃት እኩል ተጠያቂ ከመሆን አያድነውም፡፡ ዛሬ አዲስ አቋም ማራመዱ እሰየው ቢያስብልም ከዚሁ ጎን ለጎን የቀድሞ አቋሙ ያመጣውን ጥፋት አምኖ፣ከህወሃት እኩል ተጠያቂ መሆኑንም አድምቆ አስምሮ ለጥፋቱ ሃላፊነት መውሰድ አለበት፡፡

ለመስማት ደስ የሚለው እነ ኦቦ ለማ መገርሳ ደርሶ ወረሰን የሚሉት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ሱስ በጭራሽ እውነት ሊሆን አይችልም ማለት ባይቻልም እውነት ነው ብሎ መቀበል የሚቻለው በተግባራዊ እርምጃዎች መታጀብ ሲችል እና የማይዋዥቅ የሁልጊዜ አቋም ሲሆን ነው፡፡ የሁልጊዜ አቋም መሆኑን ያተራጠረኝ አንድ መረጃ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ያለው የኦቦ ለማ መገርሳ አንደበት መቼት ቀይሮ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ጭነት ነው ሲል በጆሮየ መስማቴ ነው፡፡ይህ ነገር ከኢህአዴግ ካድሬዎች ተገላባጭ አድርባይነት ጋር ሲደመር የተባለን ሁሉ ዝም ብሎ ከማመንም ጭልጥ አድርጎ ከመጠራጠርም ቆም ብሎ መመርመሩ እንደማይከፋ ያመላክታል፡፡

የኦህዴድ የማርሽ ለውጥ ሌላ መገለጫ በኢትዮጵያ ታሪክ የኦሮሞን ህዝብ ቦታ ወይ የሁልጊዜ ተበዳይነት አለያም የመገለል ብቻ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርበውን ሲደጋገም እውነት የመሰለ የኦነግ ተረክ የሚያናጋ አቋም ማራመዱ ነው፡፡ኦህዴድ በመሰረቱ የኦነግ የመንፈስ ልጅ ቢሆንም ኦነግን እድሜ ብቻ ያደረገው መንገድ እንደማያዋጣ ተረድቶ የኢትዮጵያ ህዝብ በሚፈልገውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን መስመር ገብቶ ጉዞውን ማፋጠን መርጧል፡፡የተሳካለትም ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ህወሃትም ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ ይሄው ተገልጦለት ነው ኢህአዴግ የሚለውን ማዕቀፍ የቀለሰው፡፡ሆኖም ትግራዊነቱ ሲብስበት እንጅ ሲሻለው አላየንም፡፡የህወሃት ንግግር በተግባር ሲፈተሸ ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው በዛው ባደቆነው ትግራዊነቱ ላይ እንደሆነው ሁሉ የኦህዴድ ኢትዮጵያዊነት ሱስም በተግባር የመፈተሻ ዘመን ሊቀመጥለት ይገባል እንጅ በመናገር ብቻ ጠግበን የታሪክ ስህተት ስንደጋግም መኖር የለብንም፡፡

የታሪክን ስህተት ላለመድገም ደግሞ ሁነትን ተከትሎ ከመንጎድ ገታ ብሎ ሁነቱን ያመጣውን እውነት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ እነ አቶ ለማ መገርሳ ከኢህአዴግ ካድሬ ለዛውም ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ መንደር ተሰምተው የማይታወቁ ብቻ ሳይሆን የማይጠበቁ ሁለት አዳዲስ ነገሮችን በአንዴ ሲያዥጎደጉዱ በግሌ የተመለከትኩት በከፍተኛ ጥርጣሬ ነበር፡፡ አንደኛው እና የብዙዎችን ቀልብ የሳበው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ዝንባሌያቸው ሲሆን ሁለተኛው ከባለጠበንጃው ህወሃት ተፅዕኖ ለመላቀቅ እና በራሳቸው ልቦና አስበው በራሳቸው አፍ የሚያወሩ ድርጅታዊ ነፃነት ያላቸው አካላት መስለው የታዩበት ሁኔታ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን የማቀንቀናቸው ነገር ‘ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መቀንጠስ’ አይነት መፍጠኑ ሳያንስ በጣም ጎኖ ሱስ ሆኖ መገለፁ በልቦናቸው ጊዜ ተሰጥቶት ተብሰልስሎ፣በጥልቅ ግንዛቤ ላይ ተምርቶ የተደረገ ተፈጥሯዊ የአቋም ለውጥ አይመስልም፡፡

ይልቅስ የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ህዝባዊ ትግል ከማዶ ማዶ እየተጠራራ ወንድምነቱን አንድነቱን ማስተጋባቱን ተከትሎ በተለመደው ካድሬያዊ አዋጭ መንገድን አፈፍ አድርጎ ትርፍ ለመሰብሰብ ሲባል ህዝብ የሚፈልገውን እየዘመሩ ደጋፊንም አባዝቶ ወደ ስልጣን የመገስገስ አካሄድ ያደላል፡፡ ስለዚህ የኦህዴድ የአሁኑ ኢትዮጵያዊነትን የመስበክ አካሄድ ምንጩ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚወደው ህዝብ ትግል እንጅ የለማ መገርሳ ካቢኔ አይደለም፡፡ የለማ መገርሳ ቡድን ይህን የህዝብ ፍላጎት ከህወሃት ክርን ማምለጫ አምባ አደረገው እንጅ እራሱ ፈጥሮ ለእውንነቱ የሚታገልበት ነገር አይደለም፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ኦህዴድ በማጉረምረም አንዳንዴም በግልፅ እምቢኝ በማለት(ዶ/ር ነጋሶ ያስታውሷል) ለህወሃት የሚያስቸግር ድርጅት ነው፡፡ማስቸገሩ ስረ-ምክንያት ደግሞ የህዝቤን ቁመና የሚያክል ቁመታም ስልጣን ይገባኛል በሚል ቁመት እና ወርድ የሚያንሰውን ህወሃት ወንበር መመኘቱ ነው፡፡ አንድ ቋንቋ የሚናገርን ህዝብ ብዛት ብቻ ተመርኩዞ ለሰው ልጅ የትልቅነት እና ትንሽነት መደብ የሚመድበው የጎሳ ፖለቲከኞች ግንዛቤ እዚህ ድረስ ነውና ኦህዴድ ለምን ይህን አለ ማለት አይቻልም፡፡በዚህ መሰረት ኦህዴድ ለራሱ ረዝሞ የሚታየውን የራሱን ቁመት የሚመጥን ስልጣን ሲመኝ ኖሯል፡፡ ሆኖም የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዙ ህወሃት ይዞ የሚጓዘው የጎሳ ፖለቲካ ተረክ ከማንም በፊት ኦህዴድን ወደሚወደው ስልጣኑ እንደሚጋብዝ አሳምሮ ስለሚያውቅ ጠመንጃውን ከአጠገቡ አያርቅም፡፡ ኦህዴድም የህወሃትን የብሄር ፖለቲካ ተረክ ተቀብሎ ወደስልጣን እንዳይመጣ ደንቃራ የሆነበት ‘አማራ የሚባለው ጭራቅ ትምክህት ነው’ ሲባል አሜን ብሎ ጭራቁን ከፖለቲካው ስዕል በማስወገዱ ለነገ የማይባል ስራ ላይ እጁን ከህወሃት አጣመምሮ ኖሯል፡፡

‘ጭራቁ’ የሚፈለገውን ያህል ከወንበር ርቆ መገፋቱ ከተረጋገጠ በኋላም ግን ኦህዴድ ወንበሩ ላየ ከመቁለጭለጭ በቀር ያገኘው ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ወንበሩን አርቆ የሰቀለበትን ሌላውን ደንቃራ ሲፈልግ ህወሃት ከነጠመንጃው ወንበር ከቦ መቆሙ ዝግ ብሎ ተገለፀለት፡፡ ይሄኛውን ደንቃራ ለመታገል እንደ አልባሌ ነገር ስርቻ ውስጥ የተቀበረውን ክቡሩን ነገር ኢትዮጵያዊነት ጎትቶ ማውጣት ግድ ብሏል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ስም የራሱን የበላይነት ሲጭን ኖሯል እየተባለ ሲብጠለጠል የኖረውን የአማራ ህዝብም ሆነ ይህን ህዝብ ወክሏል የሚባለው ብአዴን አጋርነትም ያስፈልጋል ተብሎ የኦቦ ለማ መገርሳ ቡድን አባይን ይሻገር ዘንድ አስገድዷል፡፡ ‘የመጣነው ስለምታስፈልጉን ነው፤ይህ ደግሞ ለማለት ብቻ ሳይሆን ከልብ የመነጨ አባባል ነው’ ያሉት ኦቦ ለማ መገርሳ ጥዑም ንግግራቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ጨክኖ የማይጨክነውን፣የተደረገበትን በደል እያነሳሳ በማላዘን የማይታወቀውን የአማራን ህዝብ ልብ ለማግኘት አልተቸገረም፡፡በአማራ ክልል መዲና ላይ ቆመው የተናገሩን ይህ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ወገንተኝነት አዲስ ዝንባሌ በተቀረው የሃገሩ አንድነት ጉዳይ የሚያሳስበው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የኦህዴድን ተቀባይነት ጨመረው፡፡ የኦህዴድ በህወሃት ፊት ቆሞ የመከራከር ሞገስ ምንጩም ይሄው ነው፡፡ምክንያቱም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ህወሃት ካነገበው ጠበንጃ የሚበረታው የህዝብ ክንድ አለ፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የሃገሩን አንድነት እንደሚወድ ይታወቃል፡፡ሃያ ሰባት አመት ዘረኝነት ሲያቦካ ኖሮ ከምጣድ አልወጣ ሲለው ኢትዮጵያዊነትን ድንገት ሲዘምር ለተገኘው ኦህዴድ ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ የተዘረጋው የተቀባይነት እጅ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃገሩን ለማዳን ሲሆን የቀደመ በደልን አይቆጥርም፡፡ይህ የህዝብ ወገንተኝነት ኦህዴድ የህወሃትን ጠበንጃ ተገዳድሮ ወደ ስልጣን የሚያዘግምበት አምባ ሆኖታል፡፡ ትልቁ ጥያቄ ግን ወንበሩላይ ተቀምጦ ምን ይፈይዳል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ከዶ/ር አብይ ሹመት ጀርባ ያሉ እውነታዎች

አመዛኙ የኢትዮጵያ ህዝብ የዶ/ር አብይን ሹመት እውን መሆን በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ነበር፡፡ ለሩብ ምዕተ-ዓመት ዘረኝነት ሲነዛባት በነበረችው ሃገራችን የዶ/ር አብይ ጎሳ ዘለል ተቀባይነት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያህል ዘረኝነት እንዳገሸገሸው የሚያሳይ ነው፡፡ወደ ወንበር መምጣቱ እየተፈለገ ያለው ድህረ-አባዱላ/ሙክታር ኦህዴድም ቢሆን ኦሮሞነቱን አስቀድሞ በኦህዴድ ጥላ ስር መሰባሰቡ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የማይጠፋው ጉዳይ ነው፡፡

ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ በጎሳ ከረጢት ያሉትንም፣አጥብቆ በታከተው ኢህአዴግ ጥላስር የተሰለፉተንም ሳይቀር፣የኢትዮጵያን ስም ከሃያ ሰባት አመት በኋላ ትዝ ብሎት ለሚያነሳም ጭምር ኢትዬጵያን የሚታደግ የሚመስል አዝማሚያ እስካሳዩ ድረስ የበዛ ይቅርታ እና ሆደ-ሰፊነት ያለው ህዝብ እንደሆነ ያሳያል፡፡የዚህ ማሰሪያው የኢትዮጵያ ህዝብ የሃገሩ ህልውና እና የአብሮነቱ ማገር ከምንም በላይ አስቀድሞ የሚያሳስበው ጉዳይ እንደሆነ ነው፡፡ይህ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ የሚመለሰው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ነው ለሚሉ፣አማራውን ኦሮሞ ስልጣን ላይ እንዳይወጣ ዘብ ቆሞ የሚያድር ባለጋራ አድርገው ሲሰብኩ ለኖሩ አማራ-ጠል የኦሮሞ ብሄርተኞች የማፈሪያ ሰዓት ነው፡፡

ዶ/ር አብይ እንደተመረጡ በተነገረ ማግስት ተሰናባቹ ጠ/ሚ አቶ ኃ/ማርያም የወጡበት የደቡብ ኢትዮጵያ እምብርት ሃዋሳ ከተማ ምናልባትም ከኦሮሚያዋ አዳማ እኩል በደስታ ሰክራ ነበር፡፡ ከማህፀኗ ወጣው የቀድሞ ጠ/ሚ መሰናበትም ሆነ ሌላው የደቡብ ሰው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኦህዴዱ ዶ/ር አብይ መሸነፍ ኢትዮጵያዊነቱን ለሚያስቀድመው የደቡብ ህዝብ ከቁምነገር የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሚረባ ነገር እስካላየበት ድረስ የወንዜ ልጅ ስለሆነ ብቻ በከፍታ ይቀመጥ የሚልህዝብ ያለመሆኑ ኢትዮጵያ ከዘር ፖለቲካ ተዋጅታ የችሎታ ፖለቲካን ለማራመድ እድል እንዳላት ተስፋ ያጭራል፡፡ ወደ ሌላው የብአዴን እጩ አማራው አቶ ደመቀ ሲኬድ የአማራ ህዝብ ከዶ/ር አብይ ሊያስቀድመው ቀርቶ ብቻውን ቢወዳደር እንኳን ጠ/ሚ እንዳይሆን የሚጸልይበት ሰው ነው፡፡ የአማራ ክልል ህዝብ የለማ/ዶ/ር አብይ ቡድን አዲሱ ፖለቲካዊ መንፈስ ከማተቡ እኩል አንገቱ ላይ አስሮት የኖረውን፣ጦሱ ሲያሳስር ሲያስገድለው የኖረውን መፍቀሬ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ዘግይቶም ቢሆን በማነሳሳቱ ወከልኩህ የሚሉትን ብአዴኖችን አስረስቶ በየመኪናው መስኮት ላይ የኦህዴድ ባለስልጣናትን ፎቶ እስከመለጠፍ እንዳደረሰው አይናቸው ያየ ሰዎች አጫውተውኛል፡፡በግልባጩ በዶ/ር አብይ ቦታ ኦሮሞ ያልሆነ ሰው ቢቀመጥ ኖሮ በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ተመሳሳይ ስሜት ስለመንፀባረቁ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡የሆነ ሆኖ የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ ያስተዋልኩት ደስታ ተጋብቶብኝ ደስታውን ልጋራ ባልችልም አንድ ወሳኝ ነገር ግን ተረድቼበታለሁ-የኢትዮጵያዊነት ዳግም ትንሳኤ እንደቀረበ!!! ምክንያታችን ቢለያይም የሃገሬ አመዛኝ ህዝብ ደስታ እኔንም ሽው እንዲለኝ ያደረገው ይህ እውነት ነው፡፡

የዶ/ር አብይ ሹመት የሚያሳየው ሌላው እውነታ ህወሓት የፈለገውን ብቻ ከማድረግ ወደ መደራደር እንደ ወረደ ነው፡፡እስኪነክስ ማነከስ የሚያውቀው ህወሃት ወትሮም የቆመው መሳሪያውን በደምባደምብ ከልሎ ነውና ለደምባደምብ ተደራደረ ማለት ተሸነፈ ማለት ላይሆን ይችላል፡፡በዋናነት የቆመበት መሳሪያው አብሮት እስካለ ድረስ የህወሓት ክንድ ዛለ ብሎ መደሰት ለመርካት መቻኮል ይመስለኛል፡፡ የሆነ ሆኖ የኦህዴዱ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ህወሃት ሳይቀባው ወደ ስልጣን የመምጣት ጅማሮ ለመሆኑ የተራዘመው የሊቀመንበር ምርጫ፣የዶ/ር አብይን ስም ሲሰሙ እንደዛር የሚያደርጋቸው መፍቀሬ ህወሃት ድህ-ረገጾች ደምፍላት፣የአዲሱን ሊቀመንበር ምርጫ ተከትሎ ኢህአዴግ ባወጣው መግለጫ ዋና ፀሃፊው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ስራውን የሚሰራው ግለሰብ ሳይሆን ድርጅት ነው የሚለው የበዛ ውትወታ አመላካች ነው፡፡

የአቶ ሽፈራው ውትወታ ‘ከዶ/ር አብይ ብዙ አትጠብቁ’ የሚል እውነትነት የማያጣው መልዕክት አለው፡፡ እንደሚታወቀው በኢህአዴግ ቤት “ድርጅት መንግስትን ይመራል”፡፡ሆኖም ግለሰብ(አቶ መለስ) ድርጅቱ የሚባል ስም እስከሚሰጠው ድረስ ድርጅትን ከመምራት አልፎ ራሱ ድርጅት ሆኖ/አክሎ ገዝፎ መንግስትንም ሃገርንም ረግጦ ሲገዛ ኖሯል፤የጦር ስትራቴጅስት፣ስነ-ትምህርት ፖሊሲ ቀያሽ፣ የግብርና ባለሙያ፣የህግ ሊቅ፣አየር ንብረትለውጥ ጉዳይ ቀማሪ፣የውጭ ግንኙነት ቄሰ-ገበዝ፣የሊጉም የክንፉም አሰልጣኝ፣ሴቱም የወንዱም ካድሬ የክርስትና አባት ሆኖ ከሊጡም ከወጡም ሲል ኖሯል! ዛሬ ከህወሃት ወገን ያልሆኑት ዶ/ር አብይ ወደ ወንበር የተጠጉ ሲመስል ደግሞ ግለሰብ ኮስሶ ድርጅት ይጎላ ዘንድ ተደጋግሞ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ማለት ህወሃት ሲፈልግ ድርጅት ተረስቶ ግለሰብ ከመጉላት አልፎ ይመለካል ሳይፈልግ ደግሞ ድርጅት ጎልቶ ግለሰብ ችላ እንዲባል ይደረጋል፡፡ለዚህ ነው ያልተፈለጉት ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ጠጋ ሲሉ “ድርጅት መንግስትን” ይመራል የሚለው ሙዚቃ እየተሞዘቀ ያለው፡፡

የአቶ ሽፈራው ድርጅት እንጅ ግለሰብ ብቻውን ምንም አይፈጥርም የሚለው ንግግር የሚያመላክተው የዶ/ር አብይ ወንበር ከአቶ ኃ/ማርያም ወንበር የተለየ እንደማይሆን ነው፡፡ከአቶ ኃ/ማርያም በመጠኑም ቢሆን የተለየ ማንነት ያላቸው የሚመስሉት ዶ/ር አብይ አቶ ኃ/ማርያምን የማይመስሉ ከሆነ ድርጅታዊ አመራር በሚል ሰበብ የሚቀመጡበት ወንበር አለቃ እና ምንዝሩ የማይለይበት በተግዳሮት የተከበበ እንደሚሆን አመላካች ነው፡፡ይህ ደግሞ በዶ/ር አብይ ወንበር እውነተኝነት ላይ ሃሳቡን ጥሎ የስራ ዝርዝር እስከማውጣት ለደረሰው ለውጥ ፈላጊ ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡ጠቅለል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ነፍስ የሚዘራው ከህወሃት ወገን የሆነ ሲቀመጥበት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ይህን መረዳት ብዙ የሚያስቸግር ባይመስልም እውነታው ግን አብዛኛው ለውጥ ፈላጊ ዶ/ር አብይ ብዙ ማድረግ እንደሚችሉ እያሰበ መገኘቱ፡፡

የኦህዴድ ለስልጣን መቃተት ለምን?!

አቶ ኃ/ማርያምን ያየ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበር ለመቀመጥ መጓጓቱ በግሌ ግራ የሚያባኝ ጉዳይ ነው፡፡ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ስልጣን ነፍስ የሚዘራው የደም መስዕዋትነት ከፍሎ ስልጣን የያዘው፣ዛሬም የህግ ፍፃሜ ሁሉ የአፈሙዝ ባለቤትነት እንደሆነ የሚቆጥረው ህወሓት አባል ሲይዘው ነው፡፡በኢህአዴግ ክንፍ የተኮለኮሉ፣ሁለተኝነታቸውን ያመኑ እህት ተብየ ፓርቲዎች ሁሉ ይህን ከእኛ ከሩቆቹ ይልቅ በደምብ አሳምረው የሚያውቁት የኑረታቸው አካል ነው፡፡

አሁን ብዙ ተስፋ እየተጣለበት ያለው ኦህዴድ የሃገራችንን ፖለቲካ በእጅጉ ከሚዘውረው አፈሙዝ መንደር ራቅ ብለው ከቆሙት ከሁለተኞቹ ወገን የሆነ እንጅ ሌላ ማንነት ያለው ፓርቲ አይደለም፡፡ ስለሆነም በመቀመጡ ብቻ የአቶ ኃይለማርያምን ወንበር ነፍስ ዘርቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ አይሆንም፡፡ሆኖም ኦህዴድ የወንበሩ በድንነት ሳይበግረው ወንበሩ ላየ ለመቀመጥ አይሆኑ ሆኗል፡፡ ነፍስ አልቦው ዙፋን ላይ ለመሰየም እንቅፋት የሆነበትን የደምባደምብ እግድ ለመሸሽ የፓርላማ መቀመጫ የሌላቸው አቶ ለማ መርሳ በዶ/ር አብይ እንዲተኩ ሆኗል፡፡እንዲህ መከራ የሚታይለት ወንበር በአቶ መለስ ዘመን በማወቅ፣ በአቶ ኃ/ማርያም ዘመን ባለማወቅ ብዙ ደም ያለበት ወንበር ነው፡፡ አንድም እንዲህ በተበከለ ሁለትም በድን በሆነ ወንበር ላይ ለመቀመጥ በመሸሽ ፋንታ መሟሟት ትርጉሙ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ግድ ነው፡፡

ከላይ እንደተገለፀው ኦህዴድ በአካል የህወሃት ጥፍጥፍ ቢሆንም በመንፈስ የኦነግ ቁራጭ ነው፡፡ በመሆኑም ኦሮሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ከመሪነት ቦታ ተገልሎ የኖረነው ብሎ ያስባል፡፡ነገሩን ሲያጎነው ኦሮሞ የቁመናውን ያህል በኢትዮጵያ መንግስታዊ ስልጣን ላይ ተንሰራፍቶ ሆኖ አያውቅም ይላል፡፡ ታሪክ ደግሞ ከጥንት እስከዛሬ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኦሮሞ አድራጊ ፈጣሪ ባለስልጣናትን ይዘረዝራል፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኞች ይህ አይዋጥላቸውም፡፡ እነዚህ ታሪክ የፃፋቸው ያለፉት ስርዓት ኦሮሞ ባለስልጣናት ወደስልጣን የመጡት ኦሮሞነታቸውን ለአማራነት ገብረው እንጅ ኦሮሞነታቸውን አስቀድመው ስላልነበር የኦሮሞን የስልጣን ተጋሪነት አያመለክቱም ባዮች ናቸው -የዘመናችን የኦሮሞ ብሄርተኞች፡፡ ለነዚህ ለኦሮሞ ብሄርተኞች ኦሮሞ በቁመናው ልክ ስልጣን አገኘ የሚባለው እንደ ኦነግ ወይም እንደ ኦህዴድ በኦሮሞ ብሄርተኝነት ፓርቲ ውስጥ ታቅፎ ስልጣን ላይ ሲቀመጥ ነው፡፡

ለዚህ ነው ዛሬ በኦህዴድ ታቅፈው ወደ ነፍስ አልቦው ወንበር እያዘገሙ ያሉት የዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትርነት በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው የኦሮሞ ባለስልጣን የታየ ይመስል የሚያስፈነድቅ የሆነላቸው፡፡ ፍንደቃው በተለያየ መስመር ቆምን የሚሉ ኦሮሞ ብሄርተኞችን አንድ ያደረገ ነው፡፡ የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት ኦነግን የሚያስፈነድቀውን ያህል ኦነግን በአሸባሪነት በፈረጀው ኢህአዴግ እቅፍ ያለውን ኦህዴድ በደስታ ያዘልላል፡፡ኦህዴድንም ሆነ ኦነግን አንመሰልም ነገር ግን የኦሮሞን ብሄርተኝነት ፖለቲካ በመዘወሩ፣ለኦሮሞ በመቆርቆሩ የሚያህለን የለም የሚሉ ግለሰብ አክቲቪስቶችንም የአንድ የወንዛቸው ልጅ ወደ ስልጣን መሰል ወንበር መቃረብ አፋቸውን በሳቅ ምላሳቸውን በእልልታ ይሞላል- ማሰሪያው የወንዝ ልጅነት ነውና!ሲጠቃለል ኦህዴድን የልቡን ወደ ማይሰራበት ስልጣን የሚቻኩለው ተነጉቶ የተሰራበት፣ከክርስትና አባቱ ኦነግ የወረሰው የተበድየ ፖለቲካ እንጅ እኛ እንደምንመኘው የህወሃት/ኢህአዴግን ቤተ-መቅደስ የሚያጠራበት ጅራፍ ይዞ ለመግባት፣የምንናፍቀውን የዲሞክራሲ ፀሃይ ለማውጣት የሚያስችል አቅሙም ተፈጥሮውም ኖሮት አይመስለኝም፡፡ኢትዮጵያ የተዘፈቀችበት ችግር በተለይ ህወሃት ከነጠበንጃው ባለበት ማዕቀፍ፣በአጋርም ሆነ በአባል ፓርቲ ካድሬ አቅም እና ግንዛቤ ይፈታል ብየ ለማመን እጅግ ይቸግረኛል፡፡

ነፃ ያልወጣ ነፃ ያወጣል?

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ኦህዴድ የኦሮሞ ብሄርተኝነትን በኢትዮጵየ ብሄርተኝት ለውሶ ለተቀረው ኢትዮጵያዊ ሰሚ እንደሚመች አድርጎ አቅርቦ ወደ ወንበር እየባከነ ይገኛል፡፡በድሮ በሬ ማረስ ምርት እንደማያሳፍስ በደንብ የተረዳ የሚመስለው ኦህዴድ ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ዘይቤ ይዞ ስልጣን ላይ መቀመጡ ቢያንስ ጠላትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ሳይገነዘብ አልቀረም፡፡ሆኖም ይህ የሚገሰግስለት ወንበር ምቹነቱ፣ነፃነቱ እና እውነተኝነቱ አጥብቆ ያጥራጥረኛል፡፡ የጥርጣሬየ መነሾ ደግሞ በኢህአዴግ የቤታቤት ደምብ አድራጊ ፈጣሪው ጠበንጃ እንጅ ሌላ አለመሆኑ፤ጠበንጃውን ያነገተው አካል ደግሞ የፈለገውን ለማድረግ ህግጋትን የማይፈራ መሆኑ ነው፡፡ አሁን ብዙ የለውጥ ተስፋ የተጣለበት ኦህዴድ ደግሞ ዝናር እና መውዜሩን በማጋፈሩ በኩል እጣ ፋንታ ያለውም የሚኖረውም ስለማይመስለኝ ነው፡፡ ይህ የድሮ ዘፈን ነው ዛሬ ባለጠመንጃው ህወሃት ተዳክሟል በሚል የህወሃትን የቀድሞ ጉልበታምነት ለኢህዴድ ሸልሞ በኦህዴድ ላይ ተስፋ የማድረግ ትንታኔዎች በሰፊው አስተውላለሁ፡፡

በርግጥ ኦህዴድ ከቀድሞው በተሻለ በህወሃት ላይ የማጉረምረሙን ድምፀት ማጉላቱን የሚያመላክቱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በኦሮሚያ የኦሮሞ ወጣቶች ህይወትን የሚያጠፉ የፌደራል የፀጥታ ሃይሎችን ድርጊት በድፍረት ከማውገዝ አልፎ ሳንጠራቸው መጥተው ነው ህይወት የሚያጠፉት እስከማለት መድረሳቸው በማዘዝ መታዘዝ በሚታወቀው ኢህአዴግ ቤት የተለመደ አይደለምና ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በተለይ ህወሃት ባልጠበቀበት ሁኔታ የፓርላማ ወንበር ያላቸውን ዶ/ር አብይን በአቶ ለማ መገርሳ ቀይረው ለጠቅላይ ሚንስትርነት ወንበር ፓርቲያቸውን ማዘጋጀታቸው የማይታመን ድፍረት ከመሆኑ የተነሳ ነገሩ በህወሃት ይሁንታ የሆነ ይሆን እስከማስባል ካደረሳቸው ውስጥ ነበርኩ፡፡ ሆኖም ይህን ተከትሎ ኢህዴግ በተራዘመ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስየማ ስብሰባ ላይ መሰንበቱ፣ የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ሰውየውን እንደ ግለሰብ ከማጉላት ይልቅ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ሊያመጣ በሚችለው ለውጥ ላይ መተኮር እንዳለበት በመወትወቱ ላይ እየተሟሟተ ያለው የኢህአዴግ ፅ/ቤት አካሄድ የሰውየውን በኢህአዴግ እውነተኛ ባለቤቶች ዘንደ አለመወደድ ያስመሰክራሉ፡፡
መረሳት የሌለበት ሃቅ ግን ኦህዴድ ህወሃት እምብዛም ያልፈለገውን ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ለማድረግ ተሳካለት ማለት ህወሃት ተዳክሞ በሞት እና በህይወት መሃል ሆነ ለማለት የሚበቃ ምልክት አለመሆኑ ነው፡፡ በግልባጩ ኦህዴድ ህወሃትን ድባቅ መትቶ በቀድሞው የህወሃት የሃያልነት ወንበር ላይ ተንሰራፍቶ ተቀምጧል ለማለትም የሚያበቃ ነገርም አይደለም፡፡ይህ ማለት ህወሃት አስራ ሰባት አመት ጠመንጃ ነክሶ መዋጋቱን እንደ አለፈ ውሃረስቶ፣ወንበሩንም ከነጠመንጃው አስረክቦ ለመሄድ የማያቅማማ ልበ-ቀላል ገራገር ለመሆኑ እርግጠኞች መሆን አለብን፡፡ኢትዮጵያ በተጨባጭ ከህወሃት ጋር ያሳለፈችው ፖለቲካዊ ታሪክ ደግሞ የሚያሳየን ይህን አይደለም፡፡

ይልቅስ ህወሃት ደርግን የጣለበትን ብቃቱን የስኬት ሁሉ ጫፍ፣ የጣለውን ደርግ ደግሞ የሃይለኛ ሁሉ መጨረሻ አድርጎ ራሱን በሁልጊዜ የአሸናፊነት ሰገነት ላይ ያስቀመጠ፣በአደባባይ ‘መበለጥን አልወድም’ የሚል የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ያሰከረው ፓርቲ መሆኑ በዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ጠበንጃው በክንዱ እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ ህወሃት የማይፈልገው ሰው ወደ ስልጣን መምጣት ሃያልነቱን ለማስመስከር ሌላ መንገድ እንዲፈልግ ያደርገው ይሆናል እንጅ መሸነፉን ተቀብሎ ተረኛው ሃያል የሚያደርገውን ለማየት ሸብረክ የሚል አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ትናንት ስለ አቶ መለስ ዜናዊ ልዕለ-ሰብነት ሲያመልክ የኖረው፣ሰውየውን ከሰውነት ደረጃ ከፍ አድርጎ ድርጅቱ ብሎ እስከመጥራት ደርሶ የነበረው የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ጄሌ ካድሬ ሁሉ ዛሬ ከዶ/ር አብይ ግለሰባዊ ማንነት ላይ አይናችንን ነቅለን በድርጅቱ ብቃት ላይ እንድናተኩር ሳይደክማቸው የሚወተውቱን፡፡

ህወሃት የሁልጊዜ አሸናፊ ለመሆን ህግን እና መሳሪያን ከፕሮፖጋንዳ ጋር አሰናስሎ ይጓዛል፤በህግ እና ደምብ ያሸነፈውን በጠመንጃው ያምበረክካል፡፡በጠመንጃው ያምበረከከውን በፕሮፖጋንዳው አንቋሾ የተበዳይ ተወቃሽ አድርጎት ቁጭ ይላል፡፡ይህን ኦህዴድ ራሱም ከህወሃት ስርስር እያለ አብሮ ሲያደርገው የኖረው ጉዳይ ነውና አሳምሮ ያውቀዋል፤ቀዩን መስመር ያለፈ ዕለትም ጠመንጃው ወደራሱም ሊዞርበት እንደሚችል፣የማጉረምረሙ ርቀትም የትድረስ ሊሆን እንደሚችል አሳምሮ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ባለጠመንጃው ጠመንጃ እስኪያነሳ ድረስ የማያደርሰውን ማጉረምረም ብቻ ያጉረመርማል፤የታሰረበትን ገመድ ርዝመት ከእኛ ይልቅ እርሱ ያውቃል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይፀድቅ ዘንድ ለፓርላማ ሲቀርብ ዶ/ር አብይ ፓርላማ ቀርበው ድምፃቸውን ለመስጠት መቸገራቸው ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር ከተቆናጠጡ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሱ በብዙዎች የሚጠበቁት ዶ/ር አብይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ያላቸውን አቋም ከመገመት ባለፈ በገሃድ አይታወቅም፡፡አመዛኙ ገማች ግን ሰውየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አልወደዱትም ስለዚህ ነው መምጣቱን ያልወደዱት የሚል ነው፡፡ የሰውየው በፓርላማ ተገኝተው እውነተኛ ሃሳባቸውን አለማንፀባረቃቸው የሚያሳየው ግልፅ ነገር ግን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቶ እንደ አንድ የፓርላማ አባል ሃሳባቸውን ለማንፀባረቅ እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው በጥብቅ የሚፈሩት አንዳች አካል እንዳለ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የነፃነት ምልክት አይደለም፡፡ የዶ/ር አብይ ከፓርላማ መቅረት ሊያስወቅሳቸው ባይችልም ፓርቲያቸው ኦህዴድ የሰጣቸው የተጋፋጭነት ጉልበት ሊወስዳቸው የሚችለውን ርቀት ያሳያል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አለቀለት አበቃለት እየተባለ ያለው የህወሃት ጉልበት ያለበትን ደረጃ ያመላክታል፡፡

ዶ/ር አብይ እንደ አንድ የፓርላማ አባል ቀርበው ሃሳባቸውን ለመግለፅ ሲያፈገፍጉ ሌሎች ሰማኒያ የኦህዴድ አባላት የመጣውን ለመቀበል ወስነው ፓርላማ ተገኝተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት ዶ/ር አብይ እነዚህ የፓርላማ አባላት ያላቸውን ድፍረት ማጣታቸው በኢህአዴግ ቤት ስልጣን ከፍ ሲል የባርነት ሰንሰለትም ጠበቅ እንደሚል ሊያሳይ ይችላል፡፡በዚህ መሰረት የዶ/ር አብይ ወደ ጠ/ሚነት ወንበር ከፍ ማለት ይዞ የሚመጣው ነፃነታቸውን ይሁን ባርታቸውን መገመት ካባድ አይደለም፡፡ ዶ/ር አብይ በፓርላማ ውሏቸው ደጋግመው ካመሰገኗቸው የኦህዴድ ጓዶቻቸው መራቃቸው እና በምትኩ የጠ/ሚው አማካሪ ተብለው ወንበራቸውን በከበቡ የቀድሞ ታጋዮች መከበባቸው ጉልበታችን የሚያደክም እንጅ የሚያበረታ ነገር አይመስለኝም፡፡

ባርነትን አልቀበልም ካሉ ደግሞ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ እንደሚመስለኝ ዶ/ር አብይ የአቶ ኃ/ማርያምን ያህል የተገሩ አገልጋይ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ይህ ማለት ግን የእሳቸው እምቢ ማለት ብቻ በኢህአዴግ ቤት የተለመደውን የሎሌ ጌታ ግንኙነት ቀይሮ ወንበራቸውን የእውነት ያደርገዋል ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ ሰውየውም እንደ አቶ ኃ/ማርያም መሆንን በጄ ካላሉ አዛዥም ማዘዜን አልተውም ካለ ሊፈጠር የሚችለው ነገር የዶ/ር አብይ መጨረሻም እንደ አቶ ኃ/ማርያም ስልጣናችሁን ውሰዱ ብሎ ውልቅ ማለት ነው፡፡ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን በመጡበት ቀን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ከተሰናባቹ ጠ/ሚ ጎን ተቀምጠው መስህብ የሌለውን የአቶ ኃ/ማርያም መጀመሪያም መጨረሻም አዳንቀው ማውራታቸው የእሳቸው እድልም ከዚሁ እንደማያልፍ ልቦናቸው ነግሯቸው ይሆናል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚስትር የከበባቸው ፈተና ቀላል ያለመሆኑን በመረዳት ሰውየው ታሪክ ያጠራቀመውን የሃገራችንን የፖለቲካ ችግር ሁሉ እንደጉም አብንነው የሚያጠፉ ተደርጎ መታሰብ የለበትም፡፡ ሰውየው ይህን እና ያንን ያድርጉ እየተባለ የሚወጣው መዘርዝርም እውነታውን ያገናዘበ አይመስለኝም፡፡ዶ/ር አብይ የቆሙበት ፖለቲካዊ መሰረት የልባቸውን እዲያደርጉ የማያስችል ሆኖ ሳለ ብዙ እንዲያደርጉ ሲጠበቅ ለሰውየው ደህንነት ማሰብም ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር እንደማንኛውም ሰው በህይወት መኖር የሚፈልጉ፣ የሚወዱት እና የሚወዳቸው ቤተሰብ ያላቸው የሰው ልጅ እንጅ ብረት ለባሽ ፍጡር አይደሉም፡፡ስለዚህ የምንሰጣቸው የቤት ስራ ይህን ሁሉ ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡

ዶ/ር አብይ ስልጣን ሲይዙ ከኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ኦህዴድን ይዘው መውጣቱ አንዱ እድል እንደሆነ ተፅፎ አንብቤያለሁ፡፡ይህ የሚሆን አይመስለኝም እንጅ ቢሆንም የሚጠቅመው ህወሃት/ኢህአዴግን እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብንም ኦህዴድንም አይደለም፡፡ ዶ/ር አብይ ኦህዴድን ከኢህአዴግ ገንጥየ ልውጣ ቢሉ ህወሃት ጠፍጥፎ የሰራውን ኦህዴድን ከነነፍሱ ይዘው ይወጡ ዘንድ ዝምብሎ የሚያያቸው ነፈዝ ስብስብ ሳይሆን አጋጣሚውን በእልልታ ተቀብሎ፣ እሳቸውን እና መሰል ጓዶቻቸውን በአንጀኝነት ከስሶ ፣ወህኒ አውርዶ፣የቀድሞውን ኦህዴድ የሚመልስበትና የራሱን የቀድሞ አዛዥነቱን ከነሙሉ ክብሩ እና ጥቅሙ መልሶ የሚያመጣበት ብልጣብልጥ ድርጅት ነው፡፡ ህወሃት ከኦህዴድ ቀርቶ ከራሱ ፓርቲ አኩራፊ ተገንጣዮች የትየለሌ ያተረፈ ድርጅት ነው፡፡ የእነ አቶ ስየ-ተወልደ ቡድን አኩርፎ መውጣት የህወሃትን ገዥ ነጅነት አጠናከረ እንጅ ያሳጣው ነገር የለም፡፡

የኦህዴድ ውበት!

ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣናቸው በሃገሪቱ ፓርላማ ቡራኬ ባገኘበት ወቅት ከሌሎች የኢህአዴግ ካድሬዎች በተለየ ሁኔታ ያደረጉት ህይወት ያለው ንግግር ከአንድ ፖለቲከኛ የሚጠበቅ ርቱዕ አንደበት እንዳላቸው ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ንግግራቸው ቢያንስ የራሳቸውን አለፍ ሲልም ፓርቲቸው በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ ያለውን ምኞት እንደሚያሳይ ጥልቅ ስሜታቸውን ያጤነ ሁሉ ይረዳዋል፡፡ የሴት ሚና እምብዛም በማይነሳሳበት ሃገር ባለቻቸው አጭር ሰዓት ስለሴቶች ያላቸውን የሰለጠነ እሳቤ ያቀረቡበት መንገድም እናታቸውን እና ባለቤታቸውን አስቀድመው ያደረጉት ነውና የማስመሰል አይመስልም፡፡ በተለይ በተለይ ስለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጉዳይ ያነሱት ፓርቲያቸው ከኖረበት የኦሮሞን ህዝብ ታሪክ የማይመጥን የጎሳ ፖለቲካ ጠባብ ከጢረት እልፍ ማለቱን የሚያሳይ ነው፡፡ በተግባር የሚሆነው ነገር ንግግራቸውን ይምሰል አይምሰል ዋል አደር ብለን የምናየው ሆኖ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ልህቀት፣ጥልቀት፣ውስብስብ ቋጠሮ፣ሩቅነት በተመለከ የተናገሩበት መንገድ እጅግ ግሩም ከመሆኑም በላይ ራሳቸውን ብቸኛ የኦሮሞ ህዝብ ሞግዚት አድርገው የኦሮሞ ህዝብ በጎ ነገር የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ እንደሆነ የሚሰብኩ አፍራሾችን አጓጉል መንገድ አይረቤነት ያሳየ ስለሆነ ለኢትዮጵያ ብሄርተኛው ትልቅ ድል ነው!

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

___
ማስታወሻ: በዚህ ጽሁፍ ላይ የተንጸባረቁ ሳሃቦች የጸሃፊውን እንጂ የድረገጹን አቋም አያንጸባርቁም። ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com ወይንም በ info@borkena.com

የሴት ቀን የወንድ ዓለም (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

ቦርከና
በመስከረም አበራ
መጋቢት 15 2010 ዓ.ም.

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

አላማችን ወደ ምዕራብ ጋደል ብላ እንደምትሽከረከር ከአንደኛ ደረጃ ትምህርቴ ሰምቻለሁ፡፡ አድጌ የአለምን ማህበራዊ መስተጋብር መመርመር ስጀምር ደግሞ ማጋደሏ ወደ ወንዴ ፆታ እንጅ የአንደኛ ደረጃ መምህሬ እንደነገሩኝ ወደ ምዕራብ እንዳልሆነ በየቀኑ፣ በየሠዓቱ፣ በየሰበቡ እገነዘባለሁ፡፡ ማጋደሉ ሲጀመር ወንድነት የመደመጥ ሴትነት የመታየት መንስኤ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በሌላ አባባል ሴቷ ልታሻሽለው በማትችለው፣ወዳ ፈቅዳ ባልሆነችው ገፅታዋ ስትተረጎም ወንዱ ጥሮ ግሮ ሊያሻሽለው በሚችለው የአእምሮው ይዘት፣የኪሱ ክብደት ይመዘናል፡፡በዚህ የተነሳ ሴት ወደ ውበቷ ወንድ ወደ እውቀቱ ይተጋሉ፡፡ሴቷ እጅግም የማታሻሽለውን ገፅታዋን የተሻለ ለማድረግ ስትለፋ፣ በእዛው ላይ ቀልቧን ስትጥል ቁምነገሩ ያልፋታል፤ከእውቀት ማዕድ ትጎድላለች፡፡ሆኖም በመኳኳሏ ትዘለፋለች ትምህርት የማይዘልቃት በመሆኗም ትብጠለጠላለች፡፡በመልኳ ሲመዝናት የኖረው ራሱ ማህበረሰብ መልኳን ለአይኑ እንዲመች ለማድረግ በመልፋቷ መልሶ ይወቅሳታል፤ከሊፒስቲክ እና ቻፕስቲክ በቀር ዓለም የሌላት ድርጎ ሚዛኗን ያቀለዋል፡፡

እድል ቀንቷት ራመድ ካለ ቤተሰብ ተፈጥራ ማህበረሰቡ ከመደበላት የመታየት እጣ ፋንታ አፈንግጣ እውቀትን ከሻተች፣እሱም የተሳካላት እንደሆነም መሰናክል አያጣትም፡፡ከመሰናክሎቿ አንዱ ይካድ ዘንድ የማይቻለውን ስኬቷን አሳንሶ ማየት፣እውቅና አለመስጠት ነው፡፡ ሰለጠንኩ በሚለው ዓለም ጭምር ሴት የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ከወንድ ጓዶቻቸው እኩል እየሰሩ እኩል የማይከፈልበት ሃገር እስከዛሬ አለ፡፡ የፊውዳሉ ስርዓት ከዓለማችን ሲወገድ ሁሉም የሰው ልጆች መሪዎቻቸውን የመምረጥ መብት ይኑራቸው ሲባል የዚህን መብት እፍታ ያጣጣሙት ወንዶች ነበሩ፡፡ሴቶች ከወንድ እኩል መሪዎቻቸውን ለመምረጥ ሌላ ሴታዊ ትግል ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በዚህ በኩል ሃገሬ ኢትዮጵያ አትታማም- ሴትን ምርጫ እንዳትመርጥ የሚከለክል ህግ አልነበረምና! በመንግስት ፔሮልም የሴት እና የወንድ ደሞዝ ብፌ በታሪክ አልተመዘገብ፡፡

ሆኖም በግል አሰሪዎች ዘንድ እንዲህ አይነት የሴት ሰራተኛን ክፍያ የማሳነስ አካሄድ የለም ማለት አይደለም፡፡ በደንብ አለ! ሴቶችን በአምስት ብርም ሆነ በአስር ብር አሳንሶ መክፈል የሚጎዳው ኪስን ሳይሆን አእምሮን ነው፡፡ በተግባር እንደማታንሰው ልቦናው እያወቀ፣የምታበረክተውም ከወንድ ቅጥሮቹ ያነሰ እንዳልሆነ ልቦናው እየነገረው የሴቷን ክፍያ በሽራፊ ሳንቲም አሳንሶ እሱና የጾታ መሰሎቹ እንደሚበልጧት ምስክር ሊያደርግ የሚሞክር አሰሪ ራሴ ገጥሞኝ አይቻለሁ፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ብየ ሙግት መግጠሜ አልቀረም፤ ማን ነገሬ ቢለኝ! ጭራሽ በሰው በምጠላው ገንዘብ ወዳድነት ተከስሼ ቁጭ ….! እንዲህ ያለው የድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ያለው ሰው የአደባባይ ስሙ “የሰብዐዊ መብት ተሟጋች” ሆኖ ስሰማ ከሳቄ ጋር ያታግለኛል!
ሌላው ሴቶችን የማሳነሻ ዘዴ ለስራቸው በከፊል ወይም በሙሉ እውቅናን መንፈግ ነው፡፡ ይህ እንደ ጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር የህግ አንቀፅ ጠቅሰውለት በወንጄል የማይከሱት ወንዳወንዱ አለም የሴቶችን ችሎታ የሚያዳፍንበት ረቂቅ ልማድ ነው፡፡ ይህን የሚያደርጉት ወንዶች ብቻ አይደሉም ሴቶችም ጭምር እንጅ! እንዴውም ሴት ለሴት ያለውን ችግር ቢፅፉትም የሚያልቅ አይመስለኝ፡፡ ወንዶች ሁሉ የሴት ሥራ ያዳፍናሉ ማለትም አይደለም፡፡ ስልጣኔ ከፀጉራቸው እና ከልብስ ጫማቸው አልፎ ልቦናቸውንም የጎበኘው፣ በጥልቅ ያነበቡ፣ ከመጠምጠም እውቀት ያስቀደሙ፣ከማወቃቸው የተነሳ ራመድ ያሉቱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ለጥሩ ስራ ሁሉ እውቅና ይሰጣሉ፡፡የሰራችው ሴት ስትሆን ደግሞ ስንቱን መሰናክል አልፋ እዚህ እንደ ደረሰች ያውቃሉና ለስራው ያላቸው ክብር ይጨምር ይሆናል እንጅ አይቀንስም፡፡ እንዲህ ያሉ በርካታ የሃገሬ ሰዎች እንዳሉ በጣም አውቃለሁ፡፡ እነዚህ ያረጄውን አስተሳሰብ ለማሸነፍ የሞራል ስንቆችም ጭምር ናቸው፡፡

ወደ አዳፋኞቹ ስንመጣ ያልሰለጠነው ጭንቅላታቸው ከሴት የማይጠብቀውን ስኬት ሴት ልጅ ስታስመዘግብ ካዩ የሚያዩዋትን እሷን ትተው ከጀርባዋ ለስራው ባለቤት የሚሆን ስውር ወንድ ይፈልጋሉ – እከሌ ሰርቶላት ነው፣ እንቶኔ አግዟት ነው፣ እንትና አስገብቷት ነው ሲሉ የወንድ ሞግዚትነት ያማትራሉ፡፡ ግፋ ሲልም በግልፅ እንደማትችል ይነገራታል፡፡ በዚህ አንፃር በግሌ የገጠመኝን ሁሉ ባነሳ ወርዶ ያወርደኛልና አንዱን ብቻ እንደማሳያ ላንሳ፡፡ ከሶስት አመት በፊት ስልኬ የማላውቀውን ሰው ስልክ ቁጥር እያመላከተኝ ሲያቃጭል አፈፍ አድርጌ “አቤት” ስል እኔ ወደምኖርበት ከተማ ከጓደኞቹ ጋር መምጣቱን እና ሊያገኙኝ እንደሚፈልጉ አንድ የወንድ ድምፅ ሲነግረኝ “ስልኬን ከየት …” ብየ ሳልጨርስ “ስልክሽን የሰጠን እንትና አጠገባችን ደውሎልሽ ነበር ረሳሽ?” ሲለኝ “እሽ ይቅርታ! አስታዎስኩ በቃ ነገ ይሻላል” ብየ በማግስቱ አገኘሁዋቸው፡፡ ስለሃገራችን ፖለቲካ አውርተን ፣አንዳንዴ የምጫጭራቸውን ነገሮችም እንደሚያነቡ ነግረውኝ፣በርቺ ግን ተጠንቀቂ የሚል የበጎ ሰው ምክር ሰጥተውኝ ተለያየን፡፡

ከአንድ ሁለት አመት በኋላ ከመሃላቸው አንዱን በሆነ አጋጣሚ አግኝቸው ስንጨዋወት እኔ አምደኛ ሆኜ ከምፅፍበት መፅሄት ውስጥ የሚጽፉ ሰዎች እየጠራልኝ የምንስማማባቸውን አብረን ስናደንቅ በማልስማማባቸው ልዩነቴን እየገለፅኩ ስንጫወት ቆየንና በስተመጨረሻ የሁሉንም አምደኞች ፅሁፍ ሲያነብ የኔን ፅሁፍ ነገሬ ብሎ ተመልክቶት እንደማያውቅ ነገረኝ፡፡ እኔም “እኔኮ የምፅፈው እንደ አንተ መርጠው ለማያነቡ፣ ጊዜ ለተረፋቸው አሰሱንም ገሰሱንም ለማያልፉ ነው፡፡አንተማ መቼ አዳርሶህ የእኔን ዝባዝንኬ ታነባለህ” ብየ መከፋቴን ለማየት ፊቴ ላይ የሚሯሯጡ አይኖቹን ደስታ ነፈግኳቸው፡፡ ነገሬ ቀልድ እንዳልሆነ ሁለታችንም ብናውቅም ቀልድ አስመስለን ሳቅንበት እና ወደ ሌላ ጨዋታ አለፍን፡፡ በጨዋታ መሃል “ባለፈው ሳምንት የፃፍሽው ፅሁፍ ግን ሴት የፃፈው አይመስልም” ሲል መልሶ ወደማዳፈን ስራው ገባ:: አሁንስ በዛ ! “ፅሁፌን አንብበህ እንደማታውቅ ነግረኽኝ ነበር፤ነው ያነበበ ነገረህ?” ብየ በነገር ወጋ አደረኩትና “ሴት የፃፈው መልኩ ምን አይነት ነው?!” አልኩት ንቀቴን መደበቅ እያቃተኝ፡፡ እሱ ድንግጥ እኔ ፈርጠም …. ! ሌላ ረዥም ሳቅ ! “አንች አትቻይም ከሚያዋሩሽ ፅሁፍሽን ማንበብ ይሻላል” ሲለኝ፤ የአፉን ሳይጨርስ “አዎ ሲያሳንሱኝ አልወድም!” አልኩኝ ሳቄን አባርሬ እውነተኛ ስሜቴን እየገለፅኩ፡፡በዚሁ ተለያየን፤ከዛ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም፤ ወደፊትም የምንገናኝ አይመስለኝም በኔ በኩል፡፡

ይህ ወዳጄ እንዲህ የሚቸገረው በግሉ ክፉ ሰው ስለሆነ ላይሆን ይችላል፡፡ ይልቅስ እሱ የለመደው የወንድ ቦታ ላይ ሴት የተቀመጠ ስለመሰለው የሆነ “የተዛባ” ነገር ይታየዋል፡፡የተዛባው ነገር እረፍት ነስቶታል፡፡ ይህ ሁሉ የመጣው ደግሞ ከኖርንበት ስርዓት ነው፡፡ የኖርንበት ስርዓት የተገመደው ደግሞ ሴትን ማየት ወንድን መስማት ከመውደድ ነው፡፡ መታየት አለባት ተብላ የምትታሰበዋ ሴት መናገር ከጀመረች መሰማት ያለበትን ወንድ ቦታ ያጣበበች፣ ህግ ያፈረሰች የሚመስለው ብዙ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መፈንቅለ-ፆታ የተደረገበት ይመስለውና በወንበሩ የተቀመጠች ለመሰለችው ሴት በጎ እይታ አይኖረውም፡፡ በቀላሉ የምትወድቅ አይነት ከሆነች በንቀቱ፣በማሳነሱ እና በማዳፈኑ አጣድፎ ሊጥላት መመኘቱም መሞከሩም አይቀርም፡፡ ይህን ስሜት ያልሰለጠኑ ወንዶች ሁሉ ይጋሩታል፡፡ በነገራችን ላይ ያልሰለጠኑ ወንዶች ማለት ዲግሪ ያልደራረቡ ማለት አይደለም፡፡ ተምረው ያልሰለጠኑ በርካታ ናቸው፡፡ ሳይማሩ የሰለጠኑም እንደዛው፡፡ እና ጉዳዩ የመማር ያለመማር ነገር አይደለም፡፡ ያልሰለጠኑ ወንዶች የሴቶችን ስራ ለማዳፈን ሲተጋገዙ ቢጤዎቻቸው ሴቶችም ያግዟቸዋል እንጅ “ነግ በኔ” ብለው ላለመውደቅ ከምትታገለዋ ሴት ጎን አይቆሙም፡፡ይህ ብዙ ያልተወራለት የሴቶች ፈተና ነው!

ጸሃፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል meskiduye99@gmail.com

__
ማስታወሻ: ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በ info@borkena ወይንም
editor@borkena.com ይላኩልን

ልቅናው -የአንዳርጋቸው ፅጌ ….! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

Andargachew

በመስከረም አበራ
ሚያዚያ 28 2010 ዓ ም
የሃገራችን ፖለቲካ ህማሙ ብዙ ነው፡፡የህማሙ ራስ ደግሞ በፖለቲካው ሰፌድ ወደፊት የሚመጡ ፖለቲከኞች የስብዕና ችግር ነው፡፡ ግብዝነት፣ሴረኝነት፣በግልፅ የማይነገር የስልጣን ጥም፣ልታይ ባይነት፣ የእውቀት እጥረት፣ከንባብ መጣላት፣እብሪት፣የፖለቲካ ግብን ጠንቅቆ አለማወቅ፣ስህተትን ያለመቀበል ካፈርኩ አይመልሰኝ ድርቅና፣ቡድንተኝነት፣አድመኝት፣በግልፅም በስውርም የሚንፀባረቅ ዘረኝነት በተቃውሞውም ሆነ ገዥው ጎራ በተሰለፉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ልቦና ያደረ ክፉ ነቀርሳ ነው፡፡ ይህ ክፉ ደዌ የፖለቲካችንን ፈውስ አርቆ ቀብሮብን ከዛሬያችን ትናንታችን የሚሻል ተስፋ ቢሶች አድርጎናል፡፡

ሆኖም በፖለቲካችን ፊተኛ መስመር ብቅ ያሉ መሪዎች የስብዕና እንከን ሁሉንም ፖለቲከኞቻንን አንድስ እንኳን ሳያስቀር የሚያጠቃልል አይደለም፡፡ ይህ ነቀፌታ የማይነካካቸው ትቂት ቢሆኑም ለዘር ለፍሬ የተቀመጡ፣በአደባባይ ካወሩት በላይ በፖለቲካው ጓዳ ውብ ሆነው የሚታዩ አንዳርጋቸው ፅጌን የመሰሉ ከማውራት ቆጠብ ከመስራት በርታ ያሉ ሰዎችም ታድለን ነበር፡፡አሳዛኙ ነገር ሴረኛው ፖለቲካችን እንዲህ ያለ ቅን ማንነት ላላቸው ባለ ከባድ ሚዛን ፖለቲከኞች የማይመች፣ምርትን ከግርድ የመለየት አቅም የሚያጥረው፣ከሁሉም በላይ ደግሞ ድጋፍ ተቃውሞው ተወልጄነት የተጫነው መሆኑ ነው፡፡

ዘመናችን ዘረኝነት እና ስሜታዊነት ምክንያታዊነትን አሳደው አባረው ብቻቸውን የተንሰራፉበት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ አይነት እውነትን ገንዘቡ ያደረገ፣ምክንያት ይዞ የሚመጣ፣ሩቅ የሚወስደውን መንገድ የሚያሳይ፣ባለጥልቅ ግንዛቤ ፖለቲከኛ ጆሮ የሚሰጠው የለም፡፡ከእዛ ይልቅ ምላሱ ላይ ያስቀመጣትን አንዳንድ ጥቅስ ቀራርሞ የሚያነበንብ ካድሬን መድህን ልናደርግ ይቃጣናል፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ሰርተፍኬት ሸማች ካድሬዎች ባለ አእምሮዎችን የሚያስሩ፣እባካችሁ ልቀቁልን ተብለው የሚለመኑ መሆናቸው ነው፡፡

ፖለቲካችን እንዳይሆን ሆኖ የተበላሸ ባይሆን ኖሮ አንዳርጋቸው ፅጌን አስሮ አሳር መከራ የሚያሳይ አገዛዝ መሪ የግንዛቤውን ያህል ስለኢትዮጵያዊነት ሲያወራ፣ስለ ሌብነት አስከፊነት ሲተርክ፣ስለ እኩልነት ባማረ ቃል ሲደሰኩር ልባችን ባልቀለጠ ነበር፡፡አንዳርጋቸው ፅጌ ሃገር አፍራሽ ወንበዴ ተደርጎ፣ዓለምን የሚያክል ወጥመድ ተዘርግቶ ሲታደን ኖሮ በስተመጨረሻው የምድር ሲኦል ውስጥ የተወረወረው የኢትዮጵያን መከራ ማብቂያ መንገድ ያገኘ መስሎት በዛው ሲማስን ነው፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር የሚገልፀው በቀይ ምንጣፍ እየተራመደ፣ቶክሲዶ ለብሶ ሃገር እስኪያልቅ እየዞረ፣ልጆቹን እቅፉ ላይ አድርጎ እየተመፃደቀ፣የገባውም ያልገባውም በሚለቀው የጭብጨባ ጩኽት እየታጀበ አይደለም፡፡ከእባብ ጋር ተኝቶ፣የጉድጓድ ውሃ ጠልቆ ጠጥቶ፣እንጨት ፈልጦ፣በበረሃ ተጠብሶ፣አልባሌ ለብሶ፣እጅ እግሩን እከክ ወርሶት፣የትግል ጓዶቹን ልብስ አጥቦ፣በወንድ ልጅ እጁ እንጀራ ጋግሮ፣ያላደገበትን ተቆራምዶ፣ልጆቹን በትኖ ነው፡፡ይህ ሳያንሰው እሱ ራሱን በጎዳ የተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ለብላቢ ምላስ ችሎ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ፤አላማውን ብቻ አንግቦ እየተጓዘ ነው፡፡አንዳርጋቸው ተጨብጭቦለት አያውቅም!አልተጨበጨበልኝም ብሎም ከመስራት ለግሞ አያውቅም፡፡ ስራ ሰራሁ ብሎ በማንም ላይ አፉን አላቆ አያውቅም፤አንደበቱ ምጥን እና ጨዋ ነው፡፡ እንደ ክርስቶስ ተሰቅየ መድህን ልሆንላችሁ ይህን እና ያንን ሆንኩላችሁ ብሎ ውለታ ማስቆጠርም አይነካካውም፡፡ የሚያደርገውን ሁሉ የእሱ ትውልድ ፖለቲካ ያበላሸውን ለመካስ የተደረገ የእዳ መክፈል ስራ አድርጎ ይቆጥራል እንጅ፡፡ ብዙ ሰርቶ ትንሽ በማውራቱ፣ብዙ ተሸክሞ ግን እዩኝ እዩኝ ባለማለቱ ፣ፊት ፊት ሁን የሚለው የስልጣን ጥም ስለሌለበት ከመታሰሩ በፊት በብዛት አይታወቅም ነበር፡፡

አንዳርጋቸው ሌብነትን፣የሰብአዊ መብት ረገጣን፣አድልኦን ተጠየፍኩ የሚለው በባለጠመንጃ ቤት ሩብ ምዕተ አመት ሲያጋፍር ኖሮ አይደለም፤ሁለት አመት ከመጫኛ ረዝሞበት እንጅ! በዛው የሁለት አመት ቆይታው ታጋይ ነን ባይ ባለስልጣናት በየቤታቸው ሰርክ የሚደግሱት የሆድ ድግስ ሳይቀር ሃገር ይጎዳል ብሎ የሚያስብ፣ ፊት ለፊት የሚሞግት የኢትዮጵያዊ ሁሉ ጠበቃ ነው፡፡ ቅባት የበዛበት የሆድ ድግሳቸው ቢያቅለሸልሸው “የተዋጋችሁት ህዝብ ቀምተው ግብር ያበሉ በነበሩ የፊውዳሉ ዘመን መሳፍንት ቀንታችሁ ነው እውነት ለህዝብ አስባችሁ ነው?” እስከማለት ደርሷል፡፡ አንዳርጋቸው አይልመጠመጥም! እንዲህ እውነትን ለስልጣን የመናገር አቅም እና ድፍረት ያለው ሰው ነው፡፡

የሰው ልጅን ክቡርነት ጠንቅቆ በማወቅ ብቻ ሳይሆን ለመተግበር በመፋተር አንዳርጋቸው ፅጌ ጓደኛ የለውም፡፡ ለዚህ አንድ ቀላል ማሳያ ማሳያ ላንሳ፡፡ስለጀግንነቱ በወንዙ ልጆች ሰርክ የሚወራለት ሜጄር ጀነራል ሃየሎም አርዓያ ከደደቢት ገስግሶ አዲስ አበባን በረገጠ ሰሞን ዘመናዊ መኪናውን በቦሌ ጎዳና እያሽከረከረ ሲያልፉ አህያ የሚነዳ የሃገርቤት ሰው በስፔኪዮ ይመታል፡፡ ምስኪኑ ባለ አህያ በባለጊዜው ታጋይ ነኝ ባይ ጥፋት መመታቱ ሳያንስ፣አቶ የነፃነት ታጋይ ከመኪናው ወርዶ የሃገርቤቱን ሰውየ በጥፊ ይማታና መኪናውን አስነስቶ ይከንፋል፡፡ይህን አንዳርጋቸው የሆነ ካፌ ውስጥ ሆኖ ያያል፤ይበሳጫል! ሃየሎምን አግኝቶ ያደረገውን እንዳየ ነግሮ፣በራሱ ጥፋት ሰውየውን በጥፊ መምታቱ ጥፋት ስለሆነ ሃየሎም በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ላደረገው ነገር ይቅርታ እንዲጠይቅ ይሞግታል፤ ሳይሳቅበት አይቀርም፡፡ አንዳርጋቸው እንዲህ ነው! የመርህ ሰው፣ ያወራውን የሚኖር፣ሊበድል ቀርቶ ሲበደል ማየት የማይፈልግ የፍትህ ሰው፣የሰው ክብር እስከነካ ድረስ ጥፊን እንኳን የማይንቅ ሰብአዊነት ከዳር እስከዳር የገባው አዋቂ፣ በአሮጌ ልብስ ውስጥ ያለ ስብዕናን ማክበር የሚችል ጨዋ!

አንዳርጋቸው ሰውን የበደለ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ሲሞግት ራሱ የራሱን ጥፋት ለማመን እየተቸገረ አይደለም፡፡ የስልሳዎቹ ትውልድ አባል እንደመሆኑ መጠን ይህ ትውልድ ያኛውን ትውልድ የሚወቅስበትን ጥፋት አምኖ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚያስቸግር ትዕቢት የለበትም፡፡ እንደሚታወቀው አንዳርጋቸው በዛ ዘመን እንደማንኛውም ተራ ወጣት ድንጋይ ወርውሮ ይሆናል እንጅ ቀይ ሽብርን ለመመከት ነጭ ሽብርን በማርቀቅ የወንድማማቾችን ደም በማፋሰሱ ፊት አውራሪነት ላይ የተቀመጠ አልነበረም፡፡ ሆኖም መንግስቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ ዋናዎቹ ‘ያደረግነውን ያደረግነው ለሃገር ብለን ነው’ ሲሉ ይቅርታን ይሸሻሉ:: አንድአርጋቸው ግን “አጥፍተናል፤ በማረፊያችን ዘመን ለትግል የምናደርገውን ጥረት እንደ ይቅርታ እጅ መንሻ ቁጠሩል” ብሎ እንደመለሰ በ1997 አካባቢ በአካል ያገኘው የዚህ ዘመን ትውልድ ፅፎ አንብቤያለሁ፡፡

አንዳርጋቸው ልቆ እንዲታየኝ የሚያደርገው ሌላው ስብዕናው የነገሮችን አዝማሚያ ተረድቶ ሚያዋጣውን መንገድ አውቆ ለማሳወቅ የሚለፋ ሰው መሆኑ ነው፡፡አንዳርጋቸው ቆቅ ፖለቲከኛ ነው፡፡ መነሻ እና መድረሻውን፣የፖለቲካ ግቡን፣የትግል መከራከሪያዎቹን ዋና እና ንዑስ ጉዳዮች አሳምሮ የሚያውቅ እንጅ ግማሽ መንገድ ሳይደርስ የደረሰ መስሎት በየመንገዱ ቆሞ የሚነሆልል ተላላ አይደለም፡፡ ወያኔ መራሹ መንግስት ከአባት ገዳይ አምርሮ የሚጠላው ለዚህ ይመስለኛል፡፡የንባቡ ስፋት ለዚህ ሳይረዳው አልቀረም፡፡ከጥልቅ እውቀቱ ቀድቶ ሊያካፍል፣ቀናውን መንገድ ሊመራ ሲያስብ ለማውራት ወደ መድረክ ሳይሆን ለመፃፍ ወደ ወረቀት ያመራል፡፡ከግንዛቤው ጥልቀት የተነሳ ትንታኔዎቹ ሁሉ እንደ ትንቢት የሚቃጣቸው ናቸው፡፡

የፖለቲካ ንፋስን አኳኋዋን አይቶ ቀድሞ መፍትሄ በመጠቆም በኩል በግሌ እንደ አንዳርጋቸው ያለ ፖለቲከኛ አላውቅም፡፡ ሁሌ የሚገርመኝ ይህ ችሎታው በርካታ ቢሆንም ለአሁኑ አንድ ሁለቱን ላንሳ፡፡ የወያኔን ስልጣን ላይ መውጣት ተከትሎ በአማራው ህዝብ ላይ ሊመጣ ያለውን የመከራ ዳመና ተገንዝቦ ስለ አማራ ህዝብ የመደራጀት አስፈላጊነት በወተወተበት በ1985 ዓም የፃፈው “የአማራ ህዝብ ከየት ወደየት?” በሚለው መፅሃፉ ያስቀመጠው ሁሉ (የፊውዳል ዘመን የአማራ መኳንንትን ለብሄርተኝት የነበራቸውን ግንዛቤ ካቀረበበት ነጥብ ላይ ካለኝ ልዩነት በቀር) እየተደመምኩ ያነበብኩት፣አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ሳመሳክረው ደግሞ ትንቢት የሚመስለኝ ነው፤የአንዳርጋቸውጥልቀቱ እንዲገርመኝታየኝ ጥልቀቱ እንዲገርመኝ ካደረጉኝ ብዙ ምክንያቶችም አንዱ ነው፡፡

በዚህ ፅሁፉ ትንታኔው ውስጥ የአንዳርጋቸውን እውነተኛነት፣አንባቢን አክባሪነት ያየሁበት ነው፡፡ በክርክሩ ላይ አንባቢን አላዋቂ አድርጎ አይነሳም፤ይልቅስ አንባቢ ሊያነሳው ይችላል የሚለውን ጠበቅ ያለ ጥያቄ ሁሉ እየመለሰ፣ እንደ እኔ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ልዩነት ያለው አንባቢ ካለም ለእምነቱ እየተወ ብዙ ያስተምራል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ መፀሃፉ ምክንያት ብዙ የአማራ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ከወያኔ እኩል እንደሚጠሉት አውቃለሁ፤ጭራሽ የአማራ ህዝብ ጠላት አድርገውት ቁጭ ይላሉ(በዚህ ጉዳይ ላይ መፅሃፉን ዳስሼ የታየኝን ለማሳየት ከሶስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ የምመለስ ይሆናል)፡፡

ሁለተኛው ትዝብቴ ወያኔ መራሹ መንግስት በምርጫ ስልጣን ለማስረከብ የሚያስችል ቅንነትም ፣ዝግጁነትም፣ተፈጥሮም እንደሌለው ተገንዝቦ ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል ሌላ መልክ መያዝ እንዳለበት መርምሮ የተረዳበት ወቅት ነው፡፡ያኔ ለ1997 ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የወያኔ መንግስት በምርጫ እንደሚወገድ ተስፋ አድርጎ ለዚሁ በሚለፋበት ሰዓት አንዳርጋቸው በመሃል አዲስ አበባ ሁለገብ ትግሉን ለማድረግ የሚያስችል ጥንስስ እየጠነሰሰ እንደ ነበረ “ሰባት ኪሎ” የተባለች መፅሄት “አንዳርጋቸው ያችን ሰዓት”በሚል ርዕስ ስር አስነብባ ነበር፡፡ ይህንኑ ያወቀው የወያኔ መንግስት አንዳርጋቸውን አስሮ ራሱን እስኪስት አስደብድቧል፣በቅንጅቱ ዋና የምርጫ አስተባባሪ የነበሩት ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋንም ‘አንተ የማታውቀው ተንኮል እየተሰራ ነው’ እያሉ ግራ ያጋቡት እንደነበር “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” በሚለው መፅሃፋቸው ገልፀዋል፡፡ አንተ የማታውቀው ተንኮል ማለት እንግዲህ ክሱቱ የአንዳርጋቸው ነገሩ ገብቶት አማራጭ የትግል መንገድ ለማፈላለግ ዳርዳር ማለቱ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ይህን አማራጭ የትግል መስመር ለትግል ጓዶቹ (ፕ/ሮ ብርሃኑን ጨምሮ) ለማስረዳት እና ለማሳመን ብዙ እንደተቸገረ ይህችው ሰባት ኪሎ መፅሄት በጥሩ አቀራረብ አትታ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው እንዲህ ቀስ ብሎ የሚገባን ጥልቅ ፣አንብበን ያልጨረስነው ነገር ግን በአልባሌዎች እጅ አልባሌ ቦታ የተጣለ ሃብታችን ነው፡፡ የዚህን ውድ ሃብታችንን መፈታት የሚጠይቅ ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ እስከ ሮብ የሚቆይ የማህበራዊ ድህረ-ገፅ ዘመቻ ስላለ አንባቢ ዘመቻውን እንዲቀላቀል በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃለሁ !

እምየ አንዳርጋቸው ፅጌ የማን “ዕዳ” ነው?!!! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Andargachew _


(በመስከረም አበራ)
የካቲት 8 2010 ዓ ም

የሃገራችን ፖለቲካ ዕድለ-ቢስ የሚባል አይነት ነው፡፡የፖለቲካችን ሰፌድ እንጉላዩን ወደ ፊት ምርቱን ወደ ታች የሚቀብር ክፉ ልክፍት አለበት፡፡ፖለቲካችን ፈውስ የራቀውም በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም! እንደ እኛ ባለው ተቋማዊነት በራቀው ኋላቀር ፖለቲካ ቀርቶ ተቋማዊነት በበረታበት ስልጡን ፖለቲካዊ ከባቢም ቢሆን የፖለቲካውን ልጓም የያዙ የግለሰቦች ስብዕና ለፖለቲካዊ ፈውስ ሁነኛ ግብዓት ነው፡፡ የሃገራችን ፖለቲካ ብዙም ባይሆኑ የእውነት ለህዝብ አስበው ራሳቸውን ረስተው አደገኛውን ጉዞ የሚያያዙ የእውነት ታጋዮች አላጣም፡፡አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሃገራችን ፖለቲካ አለመፈወስ የእውነት ከሚያሳስባቸው፣ልታይ ባይነት የማይነካካቸው የተግባር ሰዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን ፊተኛው ነው፡፡ አንዳርጋቸው የእርሱ ትውልድ ለመጭ ትውልድ ስራን ሰርቶ፣ጥርጊያን አመቻችቶ ያለመጠበቁ ወንጀል መስሎ ከሚሰማቸው ሰዎች መሃል እንደሆነ የሰጣቸውን ቃለምልልሶች፣የፃፋቸውን ፅሁፎች አንብቦ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ይህ የአንዲ ልዩነቱ ነው!

አብዛኞቹ የአንዳርጋቸው ፅጌ ትውልድ ፖለቲከኞች በዘመናቸው ያጠፉትን ጥፋት ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ተተኪው ትውልድ በዘመናዊ ፖለቲካ ጎዳና ይጓዝ ዘንድ ምን መደላድል ፈጠርን የሚለውም እምብዛም የሚያሳስባቸው አይመስልም፡፡አንዳርጋቸው ፅጌ ግን የእርሱ ትውልድ የተፈወሰ ፖለቲካ ለመጭው ትውልድ ያለማቆየቱ አጥንቱ ውስጥ ገብቶ ይሰማዋል! ‘ይሄ ሁሉ የደም፣የአካል ፣የስነልቦና ድቀት መስዕዋትነት ያስከፈለው የሃገራችን ፖለቲካ እንዲህ እንስሳዊ የጉልበት አካሄድ የተጠናወተው እንዴት ነው?’ ብሎ አጥብቆ እንደሚብሰለሰል በማያመልጡኝ ቃለመጠይቆቹ ለመረዳት ችያለሁ፡፡

ሰውየው የተግባር ሰው ነውና ይህን ህመሙን ይዞ መቀመጥን አልፈለገም! የእርሱን ወደ አረጋዊነት እየተጠጋ ያለ ጉልበት ቀርቶ የጎረምሳን ትክሻ ወደሚፈትን አስቸጋሪ እና አደገኛ ስራ ሰተት ብሎ ገባ፡፡ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ በሚለው መፅሃፉ የገለፀው እና በግሌ አብዝቶ የሚገርመኝን ለፍትህ የመታገል ጉዞውን የጀመረው በህወሃት/ኢህአዴግ ቤት የነበረችው አጭር ቆይታ ከመጫኛ ረዝማበት በቃኝ ብሎ ከወጣ ጊዜ አንስቶ ነው! አንዳርጋቸውን ከኢህአዴግ ቤት ያበረረው ፣በእነሱ ዘንድም ክፉ ጥላቻን የተጠላው የአባቴ ቤት ሲዘረፍ አብሬ አልዘርፍም ማለቱ ነው! አብሮ ሊዘርፍ ቀርቶ ሲዘርፉ ማየት አቅለሽልሾት፣ፍርድ ሲጣመም መመልከት አልሆንልህ ብሎት፣የህውሃታዊያን የዘረኝነት ክርፋት አንገሽግሾት ነው ጥሎ ውልቅ ያለው፡፡ይህ ውሳኔው ሁሌም ልቤን የሚነካኝ፣ግዙፍ ስብዕናውን የሚመሰክርልኝ፣ልዕልናውን የሚያገዝፍብኝ ማንነቱ ነው!

Andargachew 4

“ሩቅ ሆኖ ከመውቀስ እስኪ ጠጋ ብየ ልያቸው የሚረዳ ነገር ካለም ልርዳ” ብሎ ነበር በፍፁም ከማይመጥኑት ሰዎች ጋር ሊሰራ የሞከረው፡፡የሆነ ሆኖ ውሃ ከዘይት ጋር እንደማይገጥም አንዳርጋቸውን የመሰለ ንፁህ ነፍስ እና ምጡቅ ግንዛቤ ያለው ሰው መተኮስ ብቻ ከሚሆንላቸው ከህወሃት/ኢህአዴግ ሰዎች ጋር መስራት እንደማይችል እርግጥ ነው! እሱ በቅርብ እንዳያቸው እነሱም በውል አጢነውት ኖሮ እንደ ተከሰተ ሰይጣን ይፈሩታል፣እንደ አባት ገዳይ ይጠሉታል፡፡በሃሰተኞች መድረክ እውነተኝነቱ፣በሆዳሞች ገበያ የመርህ ሰው መሆኑ፣በበልቼ ልሙት ዘይቤ መጭውን ትውልድ ማሰቡ፣በአላዋቂዎች ማህበር ጥልቅ ግንዛቤው ወንጀል ሆኖበት እንደ ወንበዴ ተቆጠረ! ግንዛቤውን ልቀው ሊያታልሉት እንደማይችሉ፤እሱም እስከመጨረሻው አይቷቸዋልና እንደማይለቃቸው ስለሚያውቁ በጥርሳቸውም በጥፍራቸውም ሊበሉት ቆረጡ፡፡

ስራቸው እርሱን ማሳደድ ሆነ! እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ግዙፍ ተቋም ይቆጥሩታል፡፡ምጡቅ ሃሳቡ፣ጨዋ አንደበቱ፣ማራኪ ስብዕናው፣እውነተኛ ነፍሱ፣ቆራጥ አቋሙ፣ኩሩ ማንነቱ፣የተፈተነ የህዝብ ወገንተኝነቱ እልፎችን የማረከበት ውበቱ እንደሆነ ስለሚያውቁ አጥብቀው ይፈሩታል፡፡ከሚፈሩት በላይ ይጠሉታል!ጠመንጃ አንግበው አዲስ አበባ የመግባታቸውን ገድል አወድሰው የማይጠግቡ የትናንት ሸማቂዎች አማራጭ ሲያጣ የገባበትን የትጥቅ ትግል “ለሰይጣንነቱ” ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ፡፡

እንደዚህ ከአእምሮ በላይ በሆነ ጥላቻ እና ፍራቻ የሚያዩት፣ሊበሉት አሰፍስፈው ሲጠብቁ የኖሩት ሰው በጎደሎ ቀን እጃቸው ሲገባ ምን ሊያደርጉት እንደሚችሉ ማሰብ አልፈልግም! በዛች በእነሱ እጅ በገባባት ዕርጉም ቅፅበት እሱ ምን እንደተሰማው ማሰብም እንዲሁ በሽታ ላይ የሚጥል ነገር ነው!!!! መያዙን ስሰማ የተሰማኝ ስሜት በቃላት ልወክል ይቸግረኛል፤ ከአስራ አምስት ቀን በላይ ሬሳ ቤቱ እንዳስቀመጠ ሰው ክፉ ስሜት ሰንብቶብኛል፤ ጥቅም አልቦነት፣ ደካማነት፣ክፉ የመጠቃት ስሜት፤እድለ-ቢስነት ሳይቀር ተሰምቶኛል!

አንዳርጋቸው ፅጌ በግሌ ልዩ ቦታ የምሰጠው ፖለቲከኛ ነው፤ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ረስቼው አላውቅም፡፡ በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ ብዙ የማከብራቸው ሰዎች ቢኖሩም አንዳርጋቸው በብዙ እጥፍ ልቆ ይታየኛል፡፡ የተግባርም የንድፈ-ሃሳብም ሰው መሆኑ፣ብዙ የሃገራችንን ፖለቲከኞች የሚፈትነው ልታይ ባይነት፣ የወንበር ፍቅር የማይነካካው፣ለፊት ወንበር ከመሮጥ ይልቅ ከኋላ ያለውን ከጉተና የከበደ ሸክም ለመሸከም ትከሻውን የሚያበረታ ትሁት መሆኑ፣ከሚያወራው የሚሰራው መላቁ፣ጥልቅ ግንዛቤው፣ ቆፍጣና ማንነቱ፣እምቦቀቅላ ልጆቹን ጥሎ በስተርጅና ቀንበር ለመሸከም መቅደሙ፣ከለስላሳ አልጋ ወርዶ ሰሌን ላይ ለመተኛት ያስጨከነው የህዝብ ወገንተኝነቱ እጅግ አከብረው ዘንድ ግድ ያሉኝ ልዩነቱ ናቸው! አንዳርጋቸው ፅጌ የእርሱ ትውልድ ያጠራቀመውን የፖለቲካ እዳ በግለሰብ ትከሻው ተሸክሞ የትውልድን እዳ በግለሰብ አቅሙ ሊከፍል ሲማስን ጨቅላ ልጆቹን የማይችሉት ሰቀቀን ውስጥ፣ራሱን ሲኦል የከተተ ጓደኛ አልቦ ሰው ነው!

Andargachew

አንዳርጋቸው የወለደ ሁሉ በሚያውቀው በልጆቹ ፍቅር፣በራሱ ህይወት ላይ የጨከነው ለግል ጥቅሙ ብሎ ወይ ደግሞ ከዚህ ዘውግ ለተወለዳችሁ የወንዜ ልጆች ብሎ ወሰን ከልሎ አይደለም፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ያነገበው ከፍ ሲል ሰብአዊነትን ዝቅ ሲል የኢትዮጵያዊነትን እዳ ነው፡፡ስለዚህ ለአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት መታገል ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መወገን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያስቀድም ሁሉ ለአንዳርጋቸው ፅጌ መቆም አለበት፡፡ እስከ አሁን ባለው መረጃ አንዳርጋቸው ፅጌ ስለመፈታቱ የተባለ ነገር የለም፡፡ከሰው ተለይቶ እንደ መክፋፋቱ እንደ ሌላ ፍጡር የሚታይ ሰው ከመሆኑ አንፃር እንዲህ በቀላሉ እንደማይፈታም መገመት ከባድ አይደለም፡፡እስረኛ ሁሉ ተፈቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ባለቤት እንደሌለው እቃ እስርቤት ከቀረ ሽንፈቱ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እንጅ የሌላ አይደለም፡፡ ጥፋቱ የእኛ እንጅ የህወሃት አይደለም!

በሃገራችን የማይሰማ የለምና በጎሳ ፖለቲከኞች ዘንድ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ባለቤት፣ ህዝባዊ መሰረት (“Constituency”) የሌለው፣“ሲኒ ይሁን ጀበና” የማይታወቅ ነው ነገር ነው ተብሏል፤ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነትም የለም ይባል ተይዟል፡፡ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ክብር ነፍሱን የሰጠውን፣ክብሩን የጣለውን አንዳርጋቸው ፅጌን ባለቤት እንደሌለው ዕቃ ብቻውን እስር ቤት እንዲከረቼምበት ዝም ያልን ቀን ያኔ እውነትም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ባለቤት አልቦ ቅዤት እንደሆነ አስመስክረናል! ስለዚህ አንዳርጋቸው ፅጌን ከእስር ለማስፈታት መታገል ለአሸናፊው ሃሳብ፣ ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን መቆም ነው፡፡

የሰሞኑ የሃገራችን ሁኔታ እንደሚያስረዳው እስረኛ የሚፈታው/የማይፈታው በጀርባው በቆሙት የትግል አጋሮቹ ብርታት/ድክመት ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲከኞች ቤታቸው ድረስ የሚሸኝ መኪና ታክሎላቸው የተፈቱት የወንዛቸው ልጆች ኮስተር ያለ ትግል ስላደረጉ ነው፡፡ማንም እስር ቤት መማቀቅ ስለሌለበት ይህ እሰየው የሚያስብል ነገር ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህ ወቅት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ማንነት፣የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ርዕዮት ብርታት የሚታይበት የፈተና ወቅት ነው፡፡

Andargachew 3

ለሁላችን እንደሰው መቆጠር ነፍሱን ለሰጠ ሰው፣የምንወዳትን ሃገራችንን ለማራመድ ከእባብ ጋር እየተያየ አፈር ላይ እስከመንከባለል ለጨከነ የተግባር ሰው፣ልጆቹን ነገሬ ሳይል፣ ለስላሳ ኑሮ ሳያማልለው ሁሉን ትቶ ሃገሬን ላለ ሰው ምን ብናደርግ ውለታውን ይመጥናል? እንዴት ብንጮህ ከሆነልን ጋር ይመጣጠናል? በአረመኔዎች ቤት እየተጋተ ያለውን መራራ ፅዋ የሚመጥን እንዴት ያለ ካሳ ነው? አንዳርጋቸው ፅጌ አይሆኑ የሆነለት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ነፍስ ዘርቶ ተንቀሳቅሶ ምልክቱ ሆነውን ትልቅ ሰው ማዳን ካልቻለ ሁሉም በየጎሳው ለመወሸቅ ጥሩ ምክንያት ይኖረዋል! በበኩሌ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት ከምንም ምድራዊ ሃይል ገዝፎ፣ ልዕልናው ከምንም ጋር የማይወዳደር እሳቤ ሆኖ ይታየኛል፡፡

በዚሁ መስመር የተሰለፈው ኢትዮጵያዊ የሚከተለው ርዕዮት በምክንያታዊነት ላይ የቆመ ስለሆነ በስሜት ገንፍሎ ሲናድ ስላልታየ እንጅ ትልቅ ጉልበት ያለው ሃይል መሆኑ አያነጋግርም፡፡የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እምነት ከዘውግ ተኮሩ ይልቅ ሩቅ የሚያስኬድ፣ዘመኑን የሚተካከል፣ሰውነትን የሚመጥን እንደሆነ አሌ የማይባል ነገር ነው፡፡ ሆኖም የእሳቤው ልዕልና በራሱ ተነስቶ የሚሰራው ስራ እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡አንድ የፖለቲካ ቡድን የሰለጠነ ሃሳብ ስለያዘ ብቻ አሸንፎ ይወጣል ማለት አይደለም፡፡ የያዘው ሃሳብ ተራማጅነት ከተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር ታጅቦ ስጋ እና ደም ካልለበሰ ሃሳቡ ብቻ የተፈለገውን መከናወን ሊያመጣ አይችልም፡፡ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን የምናቀነቅን ቡድኖች የሚጎድለን ይህ ነው – ተግባራዊ እርምጃ! ይህን ነገር አስመልክቶ ዶ/ር አብርሃም የተባሉ ምሁር በኢሳት ቴሌቪዥን ቀርበው “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛው የፖለቲካ ሃይል የአሸዋ ጭብጦ መሆኑን ማቆም አለበት፤ ሰብሰብ ብሎ አንድ ስራ መስራት አለበት እንጅ እንደአሸዋ ጭብጦ የተበታተነ መሆን የለበትም” ያሉት ትልቅ ንግግር ሃሳቤን ሁሉ የሚያስር አንኳር ነገር ይመስለኛል! ዛሬ ስራ የምንሰራበት፣ ማንነታችን የሚፈተሸበት ትልቅ ፈተና ፊታችን ተደቅኗል- የምልክታችን እምየ አንዳርጋቸው እጣፋንታ በእኛ በምናከብረው ወገኖቹ ተነስቶ መስራት እና አለመስራት ቀጭን ክር ላይ ተንጠልጥላለች! ውድ ነፍሱን የሸጠልን፣ እምቦቀቅላ ልጆቹን በትኖ ሲኦል የወረደው አንዳርጋቸው ፅጌ ንፁህ ነፍስ የምትጠይቀን ቀላል ጥያቄ ጊዜ እና ትኩረት ብቻ ነው! የኮምፒተራችንን ኪቦርድ መነካካትን፣ቀናትን ወስደን ሰላማዊ ሰልፍን የማድረግን ያህል ከሙዝ መላጥ የቀለለ ስራ ነው! በበኩሌ የዚህን ንፁህ ሰው ነፍስ ለመታደግ ውጭ ውየ ባድር፣ እሱ በተንከባለለበት ትቢያ ብንከባለል፣ አመድ ነስንሶ የአለምን ጩኽት ሁሉ ቢጮህ ለውለታው አንሶ እንጅ ከብዶ አይታየኝም፡፡ እሱ ከእስር ወጥቶ በምስሉ ጣኦት ሰርተው እስከማቀፍ ለደረሱ ለጋ ልጆቹ እስኪደርስ ድረስ የሚጠይቀውን ሁሉ ለመክፈል ማመንታት ውለታ ቢስነት ብቻ ሳይሆን ነገ በአንዳርጋቸው ጫማ ገብቶ ቀንበራችንን የሚሸከም የማጣት አደጋም አለው!

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com
__
ማስታወሻ : ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com

“ሱሪ የሰፋቸው” ብአዴኖች

በመስከረም አበራ
ጥር 26 2010 ዓ ም

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

የኢህአዴግ ዕምብርት የሆነው ህወሃት መስራች አባላትን አንድ አሮጌ ሽጉጥ እና አንድ የሽንኩርት መክተፊያ ቢለዋ አስይዞ ደደቢት በረሃ ያስገባቸው ሆን ብሎ የትግራይን ህዝብ የሚበድል አማራ የሚባል “ባለ ሰባት ቀንድ” ጠላት አለን ብለው ማሰባቸው ነው፡፡ ለእነዚህ የነፃነት ታጋይ ነን ባዮች የዘር ጥላቻ(በተለይ የአማራ ጥላቻ) ምትክ የሌለው ሁነኛ የትግል ማፋፋሚያ መንገድ ነበር፡፡የትግል ጥንስሳቸውን በጥላቻ ፖለቲካ መርዝ ለጀመሩት ህወሃታዊያን የትግራይን ሁለንተናዊ ጉስቁልና ያቀነባበረው አማራ የተባለው ባለሰባት ቀንድ ጭራቅ ነው፡፡ለትግራይ ክልል ዝናብ አጠርነት፣ለተራሮቿ ወጣ ገባነት፣ለግራ ካሱ ዳገት ጠመዝማዛነት ሳይቀር አማራን ተጠያቂ ሊያደርግ የሚዳዳው ማኒፌስቶ በቁም ፅሁፍ አዘጋጅተው ሊገድላቸው የማለውን የአማራ ጥላቻ በክታብ አፀኑ፡፡ የሚገርመው ዛሬ ከተሜ ሆነው፣ ኩሽሽ አውልቀው ከረቫት አስረው ሳይቀር ይህንኑ ሊያፍሩበት የሚገባውን በጥላቻ የነተበ አካሄዳቸውን ማሞካሻታቸውን አለመተዋቸው ነው፡፡ የዛሬ ሁለት አመት አቶ አባይ ፀሃይየ “እኛ የተሳካልን ለማታገል ቀላል የሆነውን የብሄር ጥያቄ ይዘን መነሳታችን ነው” ማለታቸው የዚህ አንድ አስረጅ ነው::

የያዙትን ነገር ዳር በማድረስ የማይታሙት ህወሃቶች ጠላታችን ከሚሉት አማራ ህዝብ ቤት እየበሉ እየጠጡ ታግለው አዲስ አበባ መግባታቸው በልጅነታቸው የተላከፋቸውን የአማራ ጥላቻ አላደበዘዘውም፡፡በአይናቸው ያዩት የአማራ ህዝብ ድህነት የአማራን ህዝብ አሻቅቦ የማየት የዝቅተኝነት ስሜታቸውን አላረገበውም፡፡ጭራሽ ባሰባቸው! በመሰረቱት መንግስታቸው እጣ ፋንታ እንዳይኖረው አግልለው መንግስታቸውን አፀኑ፤ ከጠመንጃቸው እኩል አንግበውት አዲስ አበባ የደረሱትን የአማራ ጥላቻ ለሰሚ ሁሉ አደሉት፡፡ አማራን ማንቋሸሽ የአጋር እና አባል ድርጅቶች ካድሬ አፍ ማፍታቻ እና የፖለቲካ እውቀት መለኪያ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ አማራን ከኖረበት ሃገሩ ማፈናቀል ጎፈሬ የሚያስበጥር ጀግንነት ሆነ፤ የአማራ ክልልን መሬት እንደ ሰንበቴ ፃዲቅ ቦድሶ መውሰድ የአማራ ሞቶ መቀበር ማረጋገጫ ተደረገ፤ የአማራ ህዝብ ግንዛቤ ልህቀት ነፀብራቅ የሆነው ተረቱ እና ባህሉ መሳቂያ መሳለቂያ ሆነ፤ አንገት መድፋት የማያውቀው ህዝብ አንገቱን ደፋ!

ይሄኔ ህወሃት ወለድ የጎሳ ፖለቲከኞች “አማራ ሳይዘጋጅ ደረስንበት” በማለት ፅዋቸውን ከፈጣሪያቸው ህወሃት ጋር አጋጩ!የጥቁር አማሮቹ ብአዴንም በፅዋ ማጋጨቱ ውስጥ አለበት፡፡

በበረከት ስምኦን ይመራ የነበረው የጥቁር አማሮች ቡድን ለአማራ ህዝብ ቆሜለሁ እያለ የአማራን ህዝብ በግልፅ የሚሳደብ፣ጀርባ ገልጦ ለህወሃት ቀጥተኛም ሆነ ተዘዋዋሪ ለበቅ የሚያመቻች ይዞ አስገራፊ ሆኖ ብዙ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡አቃፊ መሳይ ገፍታሪው በረከት ስምዖን ህወሃቶች እንደወትሮው ጆሮ አልሰጥ ሲሉት አኩርፎ ከሄደበት አፍታም ሳይቆይ ተመልሻለሁ ያለው አንድም እሱ በሚያደርገው መጠን የአማራን ህዝብ ይዞ ማስገረፉ ለሌሎች ባለመሳካቱ፤ ሁለትም እንደሱ ያሉት “ፎርጅድ” አማሮች ከብአዴን ደጄሰላም መራቃቸው እውነተኛ የአማራ ልጆችን ወደፊት አምጥቶ ለህወሃት ክፉ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አደጋ እንዳለው ታስቦ ነው፡፡

በብአዴን የቤት ደንብ በአማራ ህዝብ ጥላቻ የሰከሩት ጥቁር አማሮች ያልባረኩት የክልሉ ተወላጅ ወደ ስልጣን ይመጣዘንድ አይታሰብም፡፡የስልጣን ጥም ያክለፈለፈው የክልሉ ተወላጅ ሁሉ የቋመጠለትን ወንበር ያገኝ ዘንድ በጥቁር አማሮች ጫማ ስር መንከባለል አሽከራዊ ግዴታው ነው! ከኦህዴድ በባሰ በብአዴን ቤት አሽከርነት የበረታው ለዚሁ ነው፡፡ በአመዛኙ ትውልደ ህወሃት የሆኑት ካልሆነም የአማራን ህዝብ የመጥላቱን ጠበል በደደቢት በረሃ፣ በዋልዋ ተራራ ላይ የተጠመቁት ጥቁር አማሮች ደግሞ እግራቸው ስር የሚንከባለለውን የስልጣን ጥመኛ እነሱን የተጣባቸውን የአማራ ህዝብ ጥላቻ ሳያወርዱበት ከእግራቸው አንስተው ወደ ቋመጠለት ወንበር አይነዱትም፡፡ወንበር ላይ እስካለ ድረስም “ህዝበኝነት” እንዳይጎበኘው ሳያስጠነቅቁ ለወንበር አያበቁትም:: ይህንኑ ዘነፍ ሳያደርግ መከወኑን የሚቆጣጠሩበት ልጓም እንደፈረስ በመንጋጋው ሳያስገቡ የስልጣን ፍርፋሪን ያጣጥም ዘንድ አፉን አያቦዝኑለትም!

እንዲህ በጥቁር አማሮችን እግር ስር ተንከባለው ስልጣን የጨበጡት አማሮች የባህር ዳሩ ወንበር ላይ ተቀምጠው አዲስ አበባ የተቀመጠውን ሿሚ ሸላሚ ጌታቸውን ፈቃድ ይፈፀማሉ:: እንጅ የእነሱ እግርስር ወድቆ የእኩልነት ያለህ፣ የፍትህ ያለህ ፣በልቶ የማደር ያለህ ሚለውን ህዝብ ጩኽት የሚሰሙበት ጆሮ የላቸውም፡፡አእምሯቸውን፣አፋቸውን እና ጆሯቸውን የተከራየው የአዲስ አበባው መንግስት የሚሰማውን ሰምተው የሚናገረውን እንዲናገሩ የአሽከር-ጌትነቱ ውል የታሰረበት ክር ያስገድዳል! ሚገርመው ነገር ግን የብአዴን የላይኛውን አመራር ነፍሰ-ስጋ ተከራይቶ የፈለገውን የሚያናግራቸው ህወሃት ቁልቁል ቢሰቀሉለት እንኳን የማያምናቸው መሆኑ ነው፡፡

የጎሰኝነት አባት የሆኑት ህወሃቶች ራሳቸው የማያደርጉት ስለሆነ ሰው ከሌላ ጋር አብሮ የራሱን ጎሳ ሳያሰልስ ይበድላል ብለው ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አቶ መለስ እያሉ ጭምር ለህዝባቸው ተቆርቋሪነት በማሳየት የሚታወቁትን ኦህዴዶችን ቀርቶ ለአሽከርነታቸው እንከን የማይወጣላቸውን ብአዴኖች(ትውልዳቸው ከአማራ ብሄር የሆኑቱን) አያምኗቸውም፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል ኮሽታ መብዛቱ የብአዴኖች ድጋፍ እንዳለበት አጥብቀው ይጠረጥራሉ፡፡ግፋ ሲልም የድርጅቱን መስመር ለመሳት ዳርዳር በማለት ከዳተኝነት አፍ አውጥተው ይከሷቸዋል፡፡

ኮሎሌል ደመቀ ዘውዱን ለመያዝ ከብአዴን እውቅና ውጭ ከትግራይ ገስግሶ በሌሊት በኮሎኔሉ ቤት የተገኘውን ገዳይ ቡድን ለመተባበር አቶ ገዱ ቸል ማለታቸው የአሽከር ማንጓጠጥ የመጀመሪያ ምልክት ተደርጎ ጥርስ ሳይነከስበት አልቀረም፡፡አቶ ገዱ የተለመደውን ‘አቤት ወዴት!’ ያጓደሉት እውን ለህዝብ አስበው፣ ወይም የወንበራቸውን ሽራፊ ሉአላዊነት አስበው ሳይሆን ጀግናው ኮሎኔል እንደጥጃ አልነዳም ካለ በኋላ የተፈጠረው ቀውጢ ከጌታ ቁጣ የበለጠ አስፈሪ ሆኖ አግኝተውት ይመስለኛል፡፡ሁለትም ተመካክረን ብናደርገው ኖሮ እዚህ ሳይደረስ ሰውየውን ለመያዝ ሌላ ቀላል መንገድ ይገኝ ይሆናል በሚል “የተሻለው ለምን አመለጠን?” ከማለት ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ አጋጣሚ የአቶ ገዱን እና የካቢኔያቸውን ታማኝ ሎሌነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ አጋጣሚ ነው፡፡በበኩሌ የብአዴን የላይኛው አመራር ማንነት ከዚህ የተለየ መስሎ አይታየኝም፡፡

ኢህአዴግ በሚባለው መጋረጃ ውስጥ ህወሃት በሚዘውረው መንግስት/ፓርቲ ውስጥ አጋርም ሆነ አባል ተብለው የተኮለኮሉ ካድሬዎች ሁሉ ሎሌነታቸውን ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ የካድሬ ማጉረምረምም ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያመጣል ብየ አስቤም አላውቅም፡፡ ለዚህ ምክንያቴ ለማመንም ለመክዳትም የአንድ ቀን ተከርቼም ግምገማ የሚበቃው የካድሬ ፖለቲካዊ ግንዛቤ ለውጥን ለማምጣት ቀርቶ ለማሰብም ብቁ መስሎ ስለማይታየኝ ነው፡፡ካድሬ ቢያልም ብሄሩን፣አበሉን፣ፎቁን እንጅ ዲሞክራሲን እንደማይሆን ስለሚገባኝ በየትኛውም የኢህአዴግ ድርጅት ውስጥ ያለ ካድሬ ንግግርም ድርጊትም ቀልቤን አይገዛውም፡፡ የሆነ ሆኖ አበሉን፣ፎቁን፣ዘረፋውን ቸላ ብሎ ወይም ጎን ለጎን እያስኬደም ቢሆን ከዕለታት አንድቀንም ቢሆን ለስልጣን ያበቃውን ጎሳውን ጉዳይ አንስቶ ፈራ ተባ እያለም ቢሆን በጌቶች ፊት ኩርፊያውን እንኳን የሚገልፀው የኦህዴድ ካድሬ እና በአሽከርነቱ ላይ ብቻ በሚበረታው የብአዴን ካድሬ መሃል ልዩነት የለም ማለት አይቻልም፡፡

ብአዴን የአማራ ህዝብ መታረድ፣መፈናቀል፣መሰደብ ታጋይ የህዝብ ልጅ በደሙ በላቡ የፃፈው ደማቅ ታሪክ አንድ ገፅ ይመስለዋል፡፡ ኦህዴድ ደግሞ የህዝቡ ሞት መፈናቀል ያሳስበዋል፤ በቀጥታ ተኩሶ ካፈናቀለው ጋርም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚያስተኩሰው አካል ጋር ቢያንስ በማህበራዊ ድህረገ-ገፅ ሲነታረክ ይታያል፡፡ የተፈናቃዮቹን ፍዳ ቶሎ ማቅለል ባይችልም፣ሃብት ንብረት አፍርተው ለሰው ይተርፉ የነበሩት ተፈናቃዮች በአንድ ጀንበር ምፅዋት ጠያቂ ሆነው ስንት ወር ሙሉ ፀሃይ ቁር ሃሩር ቢፈራረቅባቸውም የኋላ ኋላ በኦሮሚያ ክፍት ቦታዎች እንዲሰፍሩ ለማድረግ እየጣረ ነው፡፡ በዚህ መከፋቱን ቢያንስ በኩሪፊያው ይገልፃል፣ የሚያስተዳድረውን ህዝብ በመትረይስ የሚቆሉ ባለጊዜዎችን አፉን ሞልቶ “ወንጀለኞች ናቸውና ለፍርድ ይቅረቡ” ይላል፡፡በተግባር ለፍርድ እስከ ማቅረብ መጋፋቱ የሎሌነቱ ደረጃ ባይፈቅድም፣ማጉረምረሙም አንድ ነገር ነው፡፡ ብአዴን ደግሞ ገዳይ በሌለበት ሟች የሚኖር ይመስል ስለገዳዮች ትንፍሽ ሳይል “ለሞቱት አዝኛለሁ”ይላል፤ጭራሽ ለቅሶ መድረስም ጀምሯል፤ “ለዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያቱ እኔ ነኝ” እያለ ማንም ጌቶቹን እንዳይጠይቅበት መጋረጃ ይሆናል::

ጥልቅ ተሃድሶው የብአዴንን ሱሪ ያሰፋውን ያህል ኦህዴድን አላደረገውም፡፡ ከጥልቅ ግምገማው ወዲህ፣በረከት ተመለስኩ ካለ በኋላ ብአዴን ሱሪው ሰፍቶት ሰፍቶት ሊወልቅበት እንደ ደረሰ ወልዲያ ላይ የተከሰተውን አሳዛኝ ክስተት ተከትሎ የፓርቲው አመራሮች በሚሰጡት የተውሸከሸከ መግለጫ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ሰው ስለሞተ አዝነናል እያለ ስለሞተ ሰው የአዞ እንባ የሚያነባ ሰው ስለገዳዮች ጭጭ ካለ ከቡከንነት ሌላ ትርጉሙ ምንድን ነው? ሰዎቹን በታቦት ፊት በጥይት እየቆላ በደም የሚነክረው መቼም የአማራ ክልል ፓሊስ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ጦር ሜዳ እንዳሉ ሁሉ ያገኙት ላይ የጠመንጃ ላንቃ የሚከፍቱ ነፍሰ-ገዳዮች እነማን ናቸው? ከበዓሉ ቀደም ብለው ወልዲያ ከተማ ገብተው ሲሰፍሩ ገዱ ያውቅም ነበር? ካወቀ የወንጀሉ ግብረ-አበር ነውና ከተጠያቂነት አይመልጥም፡፡አላውቅም ካለም አስተዳድረዋለሁ ባለው ክልል ነፍሰ-ገዳይ ገብቶ ሲከትም ማወቅ ካልቻለ ስልጣን ላይ ምን ይሰራል? ወይስ ለምን ስልጣኑን በግልፅ ለእውነተኞቹ መሪዎች አስረክቦ ህዝቡም እውነተኛ ጠላቱን እንዲያውቅ አይሆንም? የምን መጋረጃነት ነው! ሲገቡ ያላወቀውን ወይም ተነጋግሮ ያስገባቸው ነፍሰገዳዮች ይወጣሉ ሲል ለህዝብ ቃል ከገባ በኋላ ስንት ሰውነው የገደሉት? ይህን ሁሉ ያደረጉ ነፍሰ-በላዎችን ሳያወግዙ “የአማራ ህዝብ ሰዎችን በማንነታቸው ማጥቃቱ ትክክል አይደለም” ሲል ለገዳይ ሞሻሪዎች ማልቀስ ከአሽከርነት ሌላ ትርጉሙ ምንድን ነው?

ወልቃይት፤ሰማያዊትiii

ከሰማይ በታች ባለ ችግር ላይ ሁሉ ከፓርቲየ ሥራ አስፈፃሚ ጋር ተነጋግሬበታለሁ ያለው ኢህአዴግ የአማራን ህዝብ በእጅጉ እያሳሰበው ያለውን የወልቃይት የአማራ ማንነት ጉዳይ፣ ከአማራ ክልል ወደ ትግራይ ክልል የተዳበሉ ግጨውን የመሰሉ ለም መሬቶችን ጉዳይ በተመለከ ምንን ሳይባል ሲቀር አስጠቂው ብአዴን ነሁልሎ ከመቀመጥያለፈ ነገር አልሰራም፡፡ ከሰማይ በታች ባለ ነገር ላይ ሁሉ የተነጋገረ ስራ አስፈፃሚ በአንገብጋቢው የወልቃይት ጉዳይ ላይ ያልተነጋገረው ወይ የወልቃይት ነገር ከሰማይ በላይ ያለ ጉዳይ ነው አለያም ብአዴን ከምድር በታች ያረፈ አስከሬን ነው ማለት ነው፡፡

እስትንፋስ ያለው ሁሉ እንደሚረዳው የወልቃይት ነገር የአማራን ህዝብ ፀጉር የሚያቆም ጉዳይ እየሆነ ነው፡፡ የወልቃይት ነገር በወሳጁ የትግራይ ክልል ምክርቤት ይፈታ የሚለውን የቀደመ አቅጣጫ ለማስፈፀም መሰለኝ የብአዴን ዝምታ! ጌቶቹን ላለማስቀየም ሲል ዝም ይበል እንጅ የወልቃይት ነገር ለራሱም ለጌቶቹም ወንበር እጅግ ክፉ ውጋት ሊሆን እንደሚችል ለብአዴን አይጠፋውም፡፡ አማራ ነኝ ያለ ወልቃይቴ ከገብሩ አስራት የስልጣን ዘመን ጀምሮም ሆነ ገና ህወሃት ጫካ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ባዶ ስድስት እስርቤት አይሆኑ ሲሆን እንደኖረ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ለብአዴን ምኑም አይደለም! እያለባበሰው መኖርን መርጧል፡፡ አለባብሶ ማረሱ በአረም ለመመለስ እንኳን ፋታ የማይሰጥ መከራ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡

ብአዴን ምን ማድረግ አለበት?

ከአቶ አያሌው ጎበዜ ወደ ስልጣን መምጣት ወዲህ ያለው ብአዴን ከጥቁር አማሮቹ ብአዴን በተሻለ ለህዝብ የመቆም ነገር አለው፣ነገር ግን ፓርቲው በህወሃት ጠንካራ እጅ እና ለህዝብ በማሰብ አጣቢቂኝ ውስጥ ገብቶ የሚንገላታ ነው፡፡ብዙ ትችት ባይበዛበት፤ ይልቅስ በአማራ ልሂቃን አይዞህ ቢባል እንደ ኦህዴድ ለህዝቡ በመቆም ረገድ የተሻለ ስራ ሊሰራ ይችላል የሚሉ ሃሳቦችን የያዙ መልዕክቶች ይደርሱኛል፡፡አንድ ወዳጄ እንደውም “ብአዴን እኮ በማዕከላዊ የእስረኛ ጥፍር እንደሚነቀል አያውቅም፤ አለማወቅ እኮ ነው እንዲህ የሚያደርጋቸው! እባክሽ ተረጃቸው” ብሎ ከሳቄ ጋር አታግሎኛል፡፡ አያውቁም የሚለውን ቀልድ እንተወውና እኔም ያልገባኝ እውነት ያላየሁት አቅጣጫ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ የሚባለውን ለማመን ለብአዴን ድንዛዜ ከስልጣን ጥም፣ከአሽከርነት ልማድ እና የመስዕዋትነት ፍርሃት(የሱሪ መስፋት)የተለየ አጥጋቢ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡እንዲሁ“ተያቸው”የሚለው ነገር ግን ቆምኩልህ የሚሉትን ህዝብ እያስፈጁ ላሉ ሰዎች በርቱ እንደማለት ያለ ነገር ስለሆነ የሚስኬድ አይደለም፡፡ ስለዚህ ብአዴኖች መሰረታዊውን የቤቱን አመል ሳይስቱ፣ ደርሰው አሽከርነታቸውን እናሽቀንጥር ሳይሉ (ቢሉም የሚሆን አይደለምና!) አንዳንድ መሻሻሎችን ካላደረጉ የሚወዱትን የስልጣን ቱርፋት ለማጣጣም እንኳን የማይችሉበት ደረጃ ላይ እንደደረሱ የወሎ ህዝብ ከሰሞኑ በብአዴን ባለስልጣናት እና በቢሮዎቻቸው ላይ የወሰደውን እርምጃ አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከትችት ባሻገር ብአዴኖች ሊያደርጉ የሚገባቸውን እርምጃዎችም ማሳየት ያስፈልጋል የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ስለደረሱኝ በኔእይታ ብአዴን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን እርምጃዎች ልጠቁም፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com
__
ማስታወሻ : ነጻ አስተያየት ወይንም ሃሳብ በዚህ ድረ ገጽ ለማውጣት ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com

የሺፋን ፎቶ ከኢዜአ የተወሰደ

ኢህአዴግ ምን እያለ ነው?! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ)
ታህሳስ 30 2010

Meskerem Abera መስከረም አበራ
መስከረም አበራ

የኢትዮጵያ ህዝብ በከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት ውስጥ መሆኑ ያፈጠጠ ሃቅ ነው፡፡ የለውጥ አምሮቱ የሚንጠው የሃገራችን ፖለቲካ ከዲሞክራሲ ባነሰ ነገር እንደ ማይረጋጋ ሸርተት የማይል ሃቅ ሆኖ ሳለ ይለወጥ ዘንድ የተፈለገውን ስርዓት የሚጋልበው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ፣ከቅን ልቦና የመነጨ ለውጥ ለማምጣት ተፈጥሮውም፣አቅሙም፣ ፍላጎቱም፣ጆሮውም አለው ወይ የሚለው ወሳኝ ነጥብ ነው፡፡ህወሃት የቤቱን ራስ አቶ መለስን ካጣ በኋላ እንደተዳከመ እሙን ቢሆንም ከማንም በላይ የሃገራችንን የወደፊት እጣፋንታ በመወሰኑ በኩል አሁንም የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ እሙን ነው፡፡ በሃገራችን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ውትርናም መስክ ክቡድ ህልውና ያለው ህወሃት ከስልጣኑ አሻግሮ የሃገርን እጣፋንታ በጎ የማድረጊያውን የተሻለ መንገድ የማየት አርቆ አሳቢነት እንዳለው የሚያሳይ ሪኮርድ የለውም፡፡ይልቅስ በማንኛውም መስዕዋትነት ስልጣኑን ማዳን፣በየትኛውም ኪሳራ የበላይነቱን ማረጋገጥ፣ እንደምንም ብሎ የጎሳውን ዘመን ተሻጋሪ ገዥ/ነጅነት ለማረጋገጥ በመፋተር ነው የምናውቀው፡፡

ንፁሃንን ከእስር መፍታት ግዴታ ነው ደግነት?!

ኢህአዴግ ከሰሞኑ ለሃገራዊ መግባባት ስል የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር የሆኑ እስረኞችን ሁሉ እፈታለሁ እያለ ነው፡፡ይህ ውሳኔው በጣም የሚያስደስት ቢሆንም ቅንነት አጥብቆ ከራቀው ህወሃት መራሹ ግንባር የወጣ ነውና ልናየው ሚገባው በጥንቃቄ መሆን አለበት፡፡ እስረኞቹ እስርቤት የሚማቅቁት ቀለላል የሆነውን ለራስ የኖር ዘይቤ ንቀው ብፁዕ እና ከባድ የሆነውን ለሌሎች የመኖርን መልካም ዕጣ ስለመረጡ ነው፡፡ኢህአዴግ አንዴ አሸባሪ ሌላ ጊዜ ፀረ-ሰላም እያለ እንደ ተራ ወንበዴ የሚያበሻቅጣቸው ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ከተዘፈቀበት መከራ መውጫ የተስፋ ጭላንጭል አድርጎ የሚያስባቸው ባለብሩህ አዕምሮዎች ናቸውና እስራቸው እስሩ ነው፡፡በበኩሌ እነዚህን የፖለቲካ እስረኞች ባሰብኩ ቁጥር ከባድ የባለ ዕዳነት ስሜት ይሰማኛል፡፡

ኢህአዴግ እነዚህን ሰዎች ሲያስር ሚሊዮኖችን አብሮ እንዳሰረ፣በሚሊኖች ልብ ውስጥ ክፉ ጥላቻን እየተጠላ እንደሆነ የሚያስብ አይመስለኝም፡፡ እንደውም በተቃራኒው ጉብዝናውን የሚለካው አስሮ በገረፈው ሰው ብዛት ይመስላል፡፡ ደደቢት በረሃ ኖሮ፣ጉና ተራራ ሰንብቶ የመጣ፣ጉብዝናውን በጣለው የወንድሙ ሬሳ ብዛት የሚመዝን፣ጀግንነቱን ባጠነው የባሩድ ሽታ የሚወስን እግረኛ ቀን ቀንቶት ስልጣን ላይ ሲወጣ ያንኑ የጦር ሜዳ የቆረጣ ስነልቦናውን ሊተው አይችልምና በየእስርቤቶቹ የሚያደርገው አውሬያዊ ባህሪ ከለመደው ግዳይ መጣል ጋር ያመሳስለዋል፡፡እናም የቀን ጎዶሎ በክፉ እጁ ላይ የጣላቸውን የህሊና እስረኞች በማይሞላው እስርቤቱ አጉሮ አሳር መከራ ያሳያል፡፡ ማሰባቸው ብቻ ወንጀል ሆኖባቸው የሲኦል ኑሮ መኖራቸው ሳያንስ በደጋፊዎቻቸው እንኳን እንዳይጠየቁ፣ታመው እንዳይታከሙ አድርጎ ‘ጎበዝነቱን’ በክፉነቱ ሲለካ ኖሯል፡፡ እድሜ እየተለመነላቸው ለሃገራቸው ሊሰሩ የሚገባቸውን ሰዎች እስርቤት አጉሮ ምጡቅ አዕምሯቸውን ቦአዝኖ፣ኩሩ ማንነታቸውን አሸማቆ፣ቅስማቸውን ሰብሮ፣ከሰውነት ጎዳና አውጥቶ በምትኩ ሃገርን ለጥራዝ ነጠቅ ካድሬ አስረክቦ ማላገጫ ማድረጉ ለይቅርታ የሚያዳግት የህወሃት/ኢህአዴግ ከተራራ የገዘፈ ጥፋት ነው፡፡

ይህ የሃገርን እርምጃ የማዘግየት ትልቅ ውድመት ድሮም መታሰር የሌለባቸውን ሰዎች በመፍታት ብቻ የሚስተሰረይ ሃጥያት ነው ብሎ ማሰብ የሞኝ ብልጠት ነው፡፡ ንፁሃንን ማሰሩ ራሱ ወንጀል መሆኑ የማያጠያይቅ ስለሆነ እስረኞቹን ከማይገባቸው የሲኦል ኑሮ መፍታቱ በትክክለኛው የፍትህ መንገድ ከታሰበ የመንግስት ግዴታ እንጅ እጅግም አጀብ የሚያስብል የደግነት መገለጫ አይደለም፡፡ማንም የማይጠይቀው አፄ በጉልበቱ ሆኖ ከመኖሩ የተነሳ ሳያጠፉ የታሰሩ የሃገር ሃብቶችን በእስርቤት ሲያሰቃይ ከርሞ ሲፈታልንም ስንደሰት ኖረናልና የዛሬው የእስረኛ እፈታለሁ የኢህአዴግ አዋጅ ከደስታ በላይ እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው፡፡

ሆኖም ከደስታችን ስሜታዊነት ስንመለስ እነዚህ ሰዎች በእስር ያጡትን ነገር ከእስር መፈታት ብቻ እንደማይመልስላቸው እርግጥ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡በእስርቤት የባከነን የጉብዝና ወራት የሚመልሰው ማን ነው? ከገራፊ እጅ ከሚወርደው የዱላ መዓት እኩል ካልተገራ አፍ የሚዘንበውን ቅስም ሰባሪ ስድብ ከዕለታት አንድ ቀን ከእስር መፈታት ይክሰዋል?የልጅን ናፍቆት የቤተሰብን ርሃብ መካሻው ምንድን ነው? ይህ ሁሉ መከራ ሲወርድበት የኖረ ሰው ሃገሩን ሲወድ ከነበረው ውድ እጥፍ ጥላቻ ጠልቶ ከእስር ቢወጣ የሚጠቀመው ማን ነው? ለዚህ ሁሉ መንስዔ የሆነው አስሮ የማይጠግበው መንግስት ታዲያ እስረኛ ስለፈታሁ ይህ ለመለወጤ ምልክት ይሁናችሁና ተነስታችሁ አመስግኑኝ እያለ ነው፡፡ ለዚሁም ማን ተፈትቶ ማን ይቅር የሚለው ገና ጌቶችን እያወዛገበ እንደሆነ ነው የሚወራው፡፡

የመብት ተሟጋቾችን አስሮ ማሰቃየቱ የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ ላይ ካቄመባቸው ብዙ ጥፋቶቹ አንዱ እና ዋነኛው ነው እንጅ ብቸኛው አይደለም፡፡ ስለዚህ እስረኞችን እፈታለሁ ማለቱ አንድ በጎ ነገር ሆኖ ይወሰድ ይሆናል እንጅ የሥራ ሁሉ ፍፃሜ ነው ማለት አይደለም፡፡ኢህአዴግ ሲያጠፋ የኖረው ብዙ ስለሆነ ያለጥፋታቸው የታሰሩ እስረኞችን ከመልቀቁ ባሻገር ሊያርመው የሚገባው የትየለሌ ስህተት አለው፡፡

በሽፍታ ጭካኔ እንጅ በመንግስት ርህራሄ እና ምህረት የማናውቀው ኢህአዴግ ብድግ ብሎ እስረኛ እፈታለሁ ያለበት አካሄድ አላማ ግብ ራሱ በጥልቅ መጤን አለበት፡፡ በሃገራችን የፖለቲካ እስረኛ የለም ሲል የኖረው ገዥው ግንባር ዛሬ ብድግ ብሎ እፈታቸዋለሁ ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች የሚጠራበት ስም አጥቶ “የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች” ይል ይዟል፡፡የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የሚል ስም የተሰጣቸው ሰዎች ከፖለቲካ በቀር የምን እስረኞች ሊባሉ ነው?ደግሞስ መንግስት ሃሳባቸው ከሃሳቡ ጋር ስላልገጠመ ብቻ ያሰራቸው የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ብቻ ነው?ከሆነ እስክንድር ነጋ የየትኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተብሎ ነው የታሰረው? ይሄ ሁሉ መንተፋተፍ ቀድሞ የፖለቲካ እስረኞች በግዛቴ የሉም ሲባል የተኖረውን ለማስተባበል ታስቦ ነው፡፡ነገሩ ግን ከንቱ ድካም ነው፡፡የሚያመላክተውም የኢህአዴግን ከአፈርኩ አይመልሰኝ ገታራነት ዳርቻ፣ስህተቱን ከሚያምን ፍርጥ ብሎ መሞትን የሚመርጥ፣በመለወጡ ተስፋ የማያደርጉበት ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ ይህ እና ሌሎች በኢህአዴግ አባል ፓርቲ ሊቀመንበሮች በተሰጠው መግለጫ ላይ የተሰገሰጉ የማድበስበስ፣ማስቀየስ፣መካድ እና ሃቅን የመሸሽ ሁኔታዎችን ስናስተውል ፓርቲው እስረኞችን እፈታለሁ የማለቱ እርምጃ ራሱ ኢህአዴግ እንደሚያወራው ለሃገራዊ መግባባት ሲል ያደረገው ከራሱ የመነጨ፣የፍፁም መለወጡ ምልክት ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል፡፡

መግለጫው ሲገለጥ

ኢህአዴግ የቀድሞው ተሃድሶየ ጥልቀት ስለጎደለው ተመሼ ወደ አዘቅት ወርጃለሁና ሌላ ግምገማ ያስፈልገኛል ብሎ ለሃያ የተጠጋ ቀን እንደ ኑዛዜ የሚቃጣው ግምገማ አድርጓ ተመልሷል፡፡ ግንባሩን ለአስቸኳይ ሂስ ቀመስ ስብሰባ ያበቃው በአሁኑ ወቅት ሃገራችን ያለችበት አስፈሪ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ይህ ቀውስ የታየው ደግሞ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ብቻ አይደለም፡፡እንደውም ከፍተኛ ቀውስ ላስከተለው የኦሮሞ ህዝቦች ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መፈናቀል ስረ-ምክንያቱ አጋር ፓርቲ በሆነው ኢሶህዴፓ አስተደደር ነው፡፡ነገር ግን ኢሶህዴፓ በሰሞኑ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ አልተካፈለም፤ለማብራሪያም አልተገኘም፡፡ በተመሳሳይ አማሮች በገጀራ እየተመተሩ የተጣሉበትን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን የሚያስተዳድረው ቤጉዴፓም የስብሰባውም ሆነ የመግለጫው አካል አይደሉም፡፡ይህ ከኢህአዴግ የአባል እና አጋር ድርጅቶች ሚስጥራዊ ተፈጥሮ እና ግንኙነት የሚመነጭ እንቆቅልሻዊነት አጋር ድርጅቶች ምን አይነት አካላት እንደሆኑ ይበልጥ እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ነው፡፡ ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንዲፈናቀል፣ክቡር የሰውልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራ እንዲመተር ያደረገን አመራር የግምገማው አካል ያላደረገ የተለውጠናል አዋጅ ለማን ትርጉም ይሰጣል ተብሎ እንደሚወራ ግራ ነው፡፡

እንዲህ አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የተሰየመው ስብሰባ እንደ ተቋጨ ለየት ያለ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ የተላለፈበት እንደሆነ ኢህአዴግ በፀሃፊው በአቶ ሽፈራው ሽጉጤ በኩል አስነገረ፡፡ይህም መግለጫው በጉጉት እንዲጠበቅ አደረገ፡፡ ከዚሁ ግምገማ መልስ ረዘም ያለ መግለጫ ማውጣቱ የማይበቃ ሆኖ የግንባሩ እህት ድርጅቶች ከረዥሙ መግለጫ የረዘመ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ሆኖም የግምገማው መግለጫም ሆነ የእህት ድርጅቶ ማብራሪያ የተጠበቀውን ያህል የኢህአዴግን መለወጥ የሚያመልክት ሆኖ አልተገኘም፡፡ይልቅስ የተለመደው ማድበስበስ፣ አድማጭን ቂል አድርጎ የማየት የሞኝ ብልጠት እና ጭልጥ ያለ ክህደት የታየበት ነው፡፡

ማስቀየስ

በመግለጫውም ሆነ የኢህአዴግ እህት ፓርቲዎች ነን ብለው በቀረቡት የፓርቲ ሊቀመንበሮች የተሰጠው ማብራሪያ የችግርን አናት ከመምታት ይልቅ ማድበስበስ እና ማስቀየስ የበዛበት ነበር፡፡ ኳስ ሜዳ ሳይቀር በዘር የሚጋደሉበት መድረክ የሆነው በጎሳ ፌደራሊዝሙ ሳይሆን በአፈፃፀሙ የተነሳ ነው ይላሉ የተሻለ የተናገሩ የመሰላቸው ኢህአዴጎች፡፡ዘራቸውን መቁጠራቸው ብቻ ባለስልጣን ያደረጋቸው ካድሬዎች የስልጣን ህልውናቸው የሆነውን የጎሳ ፌደራሊዝም በክፉ ባያነሱ አይገርምም፡፡የሚገርመው የሚወቅሱት የጎሳ ፌደራሊዝሙ አፈፃፀምም ቢሆን ከራሳቸው ውጭ ባለቤት እንደሌለው አለማወቃቸው ነው! አፈፃፀሙ አላማረም የሚሉት የጎሳ ፌደራሊዝም በማን እጅ ሆኖ ነው ያላማረው? የአፈፃፀም እንከኑ በስልጣን ላይ ቂጥጥ ካሉት ከእነሱ አላዋቂነት ሌላ በማን ሊመካኝ ነው? ሃያ ምናምን አመት ሙሉ አፈፃፀም አልቻልኩም የሚል አስፈፃሚ ምን ሊያደርግ ስልጣን ላይ ይቀመጣል?

እውን ችግሩ ከጎሳ ፌደራሊዝሙ ሳይሆን ከአፈፃፀሙ ቢሆን ኖሮ በካቢኔ ለውጥ፣በሹም ሽር የሚፈታ ቀላል ነገር ነበር፡፡ ኢህአዴግም በየጊዜው ሹም ሽር ሲያደርግ ኖሮ ጭራሽ የዶክተሮች ካቢኔ አመጣሁ ባለ ማግስት አፈፃፀምን እንደ ብርቱ ችግር እያወራ ነው፡፡ይህ የሚያሳየው የሃገሪቱ የፖለቲካ ችግር ሁሉ የሚቀዳው ከራሱ ከግንባሩ ማንነት እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የሃገር ችግር እንዲፈታ ራሱ ግንባሩ ከነእህትም ሆነ አክስት ድርጅቶቹ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ሲወርድ ነው፡፡ የህዝብ ጥያቄም ያረጀ ያፈጀው ግንባር ከስልጣን ገለል እንዲል እንጅ ለማያርመው ጥፋቱ የተለያየ ስም እያወጣ ሁሌ ማሩኝ እንዲል አይደለም፡፡

መግለጫውም ሆነ የባለስልጣናቱ ማብራሪያ ያስቀመጠው ሌላው ጉዳይ የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች እየተዳደሩ ያሉት በራሳቸው ልጆች ነው የሚለው ባለ መንታ ገፅ ማስቀየሻ ነው፡፡ የዚህ አባባል አንዱ መልዕክት ለሃገሪቱ ችግር ሁሉ ህወሃትን ተቀዳሚ ተወቃሽ አታድርጉ፣ችግር ካለም ችግሩን የፈጠሩት በየክልላችሁ የሚያስተዳሯችሁ የጎሳችሁ ሰዎች ናቸው የሚል ነው:: ይህ በዋነኝነት የሚያነጣጥረው በትግራይ እና በሌሎች ክልሎች መሃከል ፍትሃዊ ያልሆነ እድገት አለ በሚል ጎላ ብሎ በሚነሳው እና ህዝዊ እንቅስቃሴውን በዋናነት ባጎነው ጉዳይ ላይ ነው፡፡
በአይን የሚታየውን የኢፈርትን መንሰራፋት ተጠቅሶ ለሚቀርበው ክርክር ህወሃት መልስ ማድረግ የፈለገው ኢፈርትን ያመጣው የህወሃት አመራሮች ጠንካራነት እንጅ ሌላ እንዳልሆነ፣በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ የፋብሪካዎች መዋለድ እንዲታይ ያላደረገው የእህት ፓርቲዎች መሪዎች ድክመት ስለሆነ እዛው የራሳችሁን መሪዎች ውቀሱ እና ተቻቻሉ እንጅ ነገሩን የህወሃት የበላይነት ያመጣው አድርጋችሁ አትውሰዱ ለማለት ነው፡፡ ይህ ማድበስበስ የማይመልሰው አብይ ጥያቄ ግን ክልሎች ራሳቸውን እያስተዳደሩ ከሆነ በቅርቡ በኦሮሚያ፣በአማራ እና በደቡብ ክልሎች በሚደረጉ የህባዊ አመፆች ላይ ድምፃቸውን የሚያሰሙ ሰልፈኞች የሚያስተዳድሯቸውን ፓርቲ ማለትም ኦህዴድ ወይም ብአዴን ወይም ደኢህዴን ይውረድ ከማለት ይልቅ “ዳውን ዳውን ወያኔ” ሲሉ አሻግረው የህወሃትን ፍፃሜ የሚናፍቁት ለምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡

የዚህ ማስቀየሻ ሌላው መልዕክት የጎሳ ፌደራሊዝሙን የማሞካሼቱ ቅጥያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብ በየቤቱ ልጅ አዋጥቶ ለድል ያበቃው ህወሃት የፈጠረው የጎሳ ፌደራሊዝም ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ያደረገ፣የሃገሪቱ ብሄረሰቦች ፈቅደው የመሰረቱት ብቸኛ እፁብ መንገድ ነው ባይ ነው ህወሃት/ኢህአዴግ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረው የጎሳ ግጭትም የአፈፀፀም እንጅ የሌላ ችግር ስላልሆነ ህወሃት አምጦ የወለደውን፣ዘላለም የበላይ ሆኖ በስልጣን የመኖሩ መሰረት የሆነውን የጎሳ ፌደራሊዝም በዜግነት ፖለቲካ በተቃኜ ሌላ አይነት ፌደራሊዝም ለመቀየር የምታስቡ አደብ ግዙ የሚል ነው፡፡ ይህን አጥብቆ መናገር ስላስፈለገ ከመሄዳቸው መምጣታቸው የቀደመው አቶ በረከት ስምኦንም በየደረሱበት ሲያወሩት ሰንብተዋል፡፡ ይህን ማስረገጥ ያስፈለገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህወሃት አጥብቆ በሚፈልገው የጎሳ ፌደራሊዝሙ ላይ ተስፋ የመቁረጥ አዝማሚያዎች በህዝቡ ዘንድ ስለታዩ ነው፡፡

ማድበስበስ

የእህት ፓርቲ አመራር ነን ብለው የቀረቡት አራት አመራሮች አብዝተው ያድበሰበሱት የህወሃት የበላይነት ጉዳይ ከህወሃት በቀር ሶስቱ ፓርቲዎች ያሉበትን የአሽከርነት ደረጃ ያሳያል፡፡ አቶ ለማ እና አቶ ደመቀ የማይጋረደውን የህወሃት ጌትነት ለመጋረድ የሚያደርጉት መቁነጥነጥ፣የሚናገሩት ሞልቶ ተርፎ በጌታ ምሳር ላለመከተፍ ሲሉ ብቻ ሃቅን ከአፋቸው ለመመለስ የሚታገሉት ትግል፣ቁና ቁና የሚያስተነፍሳቸው የፍርሃት ሰራዊት እነሱን ሳታደርግ ግደለኝ ያስብላል፡፡

የገዥዎች እንጅ የአንድ ብሄር የበላይነት ዛሬም ድሮም እንደሌለ ለማስገንዘብ ታሪክን አጣቅሰው ያስረዱት አቶ ለማ መገርሳ ይህ ማለት እበልጣለሁ ባይ የለም ማለት አይደለም፣በፌደራል መስሪያ ቤቶች የአንድ ወገን ህልውና ጎልቶ አይታይም ማለት አይደለም ሲሉ የጌታን ስም ሳይጠሩ ዳርዳር ብለዋል፡፡የህወሃት አድራጊ ፈጣሪነት የፈጠረባቸው ብሶት ከፊታቸው የሚነበበው አቶ ለማ መገርሳ ህወሃት ከራሱ ፓርቲ አልፎ በእሳቸው ፓርቲ ውስጥ ቡድንተኞችን እያሰለፈ እንደሚያምሳቸው፣የሚሰራ በማይሰራ ተጠልፎ እንዲወድቅ እያደረገ ፈተና እንደሆነባቸው በግልፅ አስቀምጠዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች እህት ፓርቲዎች ድንበር አልፈው በሌላ ፓርቲ ውስጥ ገብቶ በመፈትፈት አልተወቀሱም፡፡ ይህ ራሱ የህወሃትን የበላይነት የማይመሰክረው እንዴት እንደሆነ እህትማማች ነን ባዮቹ ራሳቸው ያውቃሉ!

አቶ ኃ/ማርያም በበኩላቸው የትግራይ የበላይነት ቢኖር ኖሮ ትግረኛ ተናገሩ ተብለን መቸገር ነበረብን፣የትግሬ ባህል እላያችን ላይ ይጫን ነበር ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የአንድ ብሄር የበላይነት አለማለት አንችልም ሲሉ የፖለቲካ ግንዛቤያቸውን ያህል ሲናገሩ በአቶ መለስ አእምሮ ለምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ያሳጫቸውን ምስጢር ገለፁ፡፡ አቶ መለስ ያደረጉት እንዳይቀርባቸው “አንድ አሰፋ የሚባል ሰው ከእናቱ ጋር ሲኖር ሲኖር…” ብለው ለሶስተኛ ክፍል ተማሪዎች እንኳን በሚያዛጋ ተረት አዘል ማብራሪያ የጀመሩት አቶ ኃ/ማርያም ይህን ሲሉ ማንኛውም ካድሬ አፉን የሚፈታበትን የአማራን ጨቋኝነት እና የህወሃትን ከዚህ ጭቆና አውጭ ቤዛነት ማስረገጣቸው ነው፡፡ እግረ መገዳቸውንም እሳቸውን የመሰለ ሰው ጠ/ሚኒስትር ያደረገውን “ድንቅ” ሥርዓት ለመመስረት የትግራይ ህዝብ ከአንድ ቤት ስድስት ሰባት ሰው በመገበር የከፈለውን መስዕዋትነት ገልፀው ከዛው ብሄር የወጡ ግን ደግሞ ለትግሉ ልጅ ያላዋጡ ኪራይ ሰብሳብዎች እንዴት በትግራይ ህዝብ ስም እየነገዱ እንደሆነ ገልፀው አሳርገዋል፡፡በእሳቸው ቤት ኪራይ ሰብሳቢ የተባሉት ትግሬዎች ኪራይ የሚሰበስቡት ከላይ አይዞህ ባይ ጌታ ሳያስቀምጡ እንዲሁ በአየር ላይ ነው፡፡ሰውየው አቶ ኃ/ማርያም ናቸውና ከዚህ በላይ አይጠበቅባቸውም፤የአንድ ወገን የበላይነት የሚገለፅበትን ፈርጄ ብዙ ማመሳከሪያ አገናዝበው እንዲናገሩ መጠበቅ ከእሳቸው መባስ ነው፡፡

መናገሩም መተውም የከበዳቸው የሚመስሉት አቶ ደመቀ ፈራ ተባ እያሉ የህወሃት የበላይነት አለ የሚባለው እንዲሁ ሳይሆን መንጠላጠያዎች ስላሉ ነው ቢሉም መንጠላጠያዎቹ ምን እንደሆኑ ሳያስረዱ አድበስብሰው ትተውት ለህወሃት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ቤተኛ ነኝ ባይ ትግሬዎች የትግራይ የበላይነት ያለ የሚያስመስሉ ስለሆኑ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ጠቁመው አለፉት፡፡የአቶ ደመቀ ንግግር ሲጠቃለል የህወሃት የበላይነት ያለ ይመስላል እንጅ የለም፡፡ ያለ የመሰለው ደግሞ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ስላሉ ስለሆነ እነዚህን መንጠላጠያዎች ለማስወገድ ኢህአዴግ በመወሰኑ ችግሩ ይቀረፋል ሲሉ ሌላው ቢቀር አራቱ ሰዎች በተቀመጡት መድረክ ላይ የሶስቱ ፓርቲዎች መሪዎች ስለ ህወሃት የበላይነት ለመናገርም ለመተውም በሚያዩት አሳር መከራ ሳይቀር የሚገለፀውን የህወሃት የበላይነት አድበስብሰውት አልፈዋል፡፡ አቶ ኃ/ማርያም የህወሃት የበላይነት እንደሌለ የደሰኮሩትን ነገር የማይዋጥለት ብዙ እንደሆነ ጠቆም ማድረጋቸው የሚናገሩት ነገር እውነት ሃሰትነት ለራሳቸውም እንደማይጠፋቸው ያሳብቃል፡፡የህወሃቱ ዶ/ር ደብረፅዮን የህወሃት የበላይነት የሚለወን ነገር ያስጀመረባቸው ደርግ እንደሆነ፣ ያኔ በድርድሩ ወቅትም ከህወሃት እንጅ ከኢህዴን ጋር አልደራደርም ሲል እንደነበረ ይህ ነገር አሁንም የቀጠለው የተመሰረተው ስርዓት የሁሉም እንዳልሆነ ለማስመሰል በሚደረግ ተንኮል እንጅ ሌላ የሚጨበጥ ምክንያት እንደሌለው ሰሚ ካገኙ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ሌላው አናዳጅ ማድበስበስ የኢህአዴግ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያዝን በተመለከተ የተነገረው ይሉኝታ ቢስነትን የጨመረ ሹፈት ነወ፡፡በዚህ ረገድ አራቱም መሪዎች አላግጠዋል፣የምናውቀውን እንደማናውቅ ሊያሞኙን ሞክረዋል፡፡የመንግስታቸው አውሬያዊ አረመኔነት የሚገለፅበትን የህሊና እስረኞች አያያዝ በተመለከተ ያለውን ያፈጠጠ ሃቅ ሊክዱ ከንቱ ደክመዋል፡፡ በፍርድ ቤት ችሎት የተገኘ ሁሉ የሚያነባበትን በተለይ በፖለቲካ እስረኞች ላይ ስለሚፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት ትንፍሽ ሳይሉ ‘እንደተጠበቀው አይደለንም እንጅ ምንም አንልም’ ሲሉ አላገጡ! ማዕከላዊ የሚባለው የሲኦል ቅርንጫፍም የሚዘጋው በደርግ ዘመን የነበረው የስቅይት ቆሌ እየመጣ እያስደነገጠ ስለሆነ እንጅ ዛሬ ግፍ ስለሚሰራበት አይደለም ባይ ናቸው በደህና ቀን ይሉኝታቸውን የጣሉት ጠ/ሚኒስትር ተብየው ሰውየ! አቶ ለማ መገርሳም እስረኞች በምርመራ ጊዜ የሚደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በለሆሳስ አልፈው በፍርድ ስርዓቱ ሂደት እና መዛባት ላይ ማተኮርን መርጠዋል፡፡

ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ደርግ ሰዎችን ሲያሰቃይበት የነበረውን ማዕከላዊ የተባለውን ማጎሪያ ሙዚየም ልናደርገው ነው ሲሉ ማዕከላዊን የሲኦል ቅርንጫፍ በማድረጉ በኩል እሳቸው አቤት ወዴት የሚሉለት ስርዓት የባሰው እንደሆነ እኛ ቂልነታችን የተረጋገጠ ህዝቦች አናውቅም፡፡ ለመሆኑ በዚች ሃገር ሰው የሚሰቃየው ማዕከላዊ ብቻ ነው?የነገሩ ስር ያለውስ በማዕከላዊ ሙዚየም መሆን አለመሆን ነው በስርዓቱ ኢሰብዓዊ ጨካኝ ተፈጥሮ?በደብረዘይት፣ በሸዋሮቢት፣ በቂሊንጦ፣ በዝዋይ ቀርቶ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ሳይቀር ሰው እየታሰረ ቁም ስቅል እንደሚያይ የአይን ምስክሮች አልገለፁም? ጠላቱን በማሰቃየት የሚደሰት ሥርዓት ማዕከላዊ ስለተዘጋ የማሰቃያ መቼት አጥቶ ያነደደውን የበቀል እሳት ሊያጠፋ መሆኑ ነው? ማዕከላዊን ለግፍ ይጠቀምበት የነበረው ደርግ ብቻ ከሆነ ለምን እስካሬ አልዘጉትም? ከሃያ ስድስት አመት በኋላ ምን መጣ? ዛሬ ተቀይረው ነው ብለን በቅንነት እንዳንቀበል እልፍ ማድበስበሳቸው፣ሽህ ማስመሰላቸው ያለመቀየራቸው ምስክር ነው! እንዲህ ባለው ማድበስበስ እና ጨፍኑ ላሙኛችሁ ውስጥ ሃገራዊ መግባባት ቀርቶ ግለሰባዊ መደማመጥ ሊመጣ አይችልም፡፡መለወጥ ከመፀፀት ይጀምራል፡፡ መፀፀት ደግሞ ስህተትን ጠብሰቅ ረገጥ አድርጎ ማመንን ይጠይቃል ፡፡

አቶ ኃ/ማርያም ምናልባት ደርግ ከወደቀ በኋላ ማዕከላዊ ውስጥ የሚመረመር ሰው ለስላሳ ሙዚቃ ተከፍቶለት ነው ተብለው ይህንንም አምነው ይሆናል፡፡ እኛ ግን ስለማዕከላዊ በእዛው የግፍ ጊቢ ውስጥ ፍዳ መከራቸውን ከቆጠሩ፣ዘራቸውን መተካት ቀርቶ ሱሪ መታጠቅ እንዳይችሉ ተደርገው ግልድም አገልድመው ፍርድቤት የቀረቡ፣የበደላቸው ብዛት ሃፍረታቸውን አስረስቷቸው ልብሳቸውን አውልቀው በወንድነታቸው ላይ የደረሰውን በደል ለህዝብ ሲሳዩ አይተን ሰምተናልና በኃ/ማርያም ቀልድ የምንስቅበት ጥርስ የለንም! ማዕከላዊን ለሰይጣናዊ ጭካኔው የሚጠቀምበት ደርግ ብቻ ከሆነ ዛሬ የእነ ንግስት ይርጋን አስር የእግር ጥፍር ነቅሎ በፌስታል እነሆ የሚለው ማነው ነው? ማዕከላዊ ሰው በእግሩ ገብቶ በቃሬዛ የሚወጣበት፣መነኩሴ ቆቡ ወልቆ ቱታ እንዲለብስ የሚገደድበት፣የሰው ልጅ እንደ ክርስቶስ የሚሰቀልበት የዝነኛ አረመኔዎች አምባ መሆኑን አላውቅም የሚል ካለ ሆዱ እና ጭንቅላቱ የተቀያየረበት የስልጣን አምላኪ ብቻ ነው! ይህን ለማድበስበስ መሞከር በራስ ላይ እሳት ማንደድ ነው! ስህተትን ማድበስበስ እና ማስቀየስ ሳይታረሙ የመሞት ምልክቶች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የማንን መጨረሻ እንደሚያከፋ ይታያል፡፡

ሌላው ግልፅ ማድበስበስ ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ለዓመታት ከኖረበት ቀየው በማንነቱ ብቻ ተፈናቅሎ ሜዳላይ የተሰጣበትን ወንጀል ሃላፊነት የሚወስድ ማን እንደሆነ የተቀመጠበት መንገድ ነው፡፡ የዚህን ትልቅ ወንጀል ሃላፊነት የሚወስዱት መናፍስት ይሁኑ ሰው ማይታወቁ ኪራይ ሰብሳቢዎች እና ኮንትሮባንዲስቶች ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ይህን የሚሉት ለህዝብ አሳቢ ተደርገው ድቤ እየተመታላቸው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ መሆናቸው ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የወልቃይት ጉዳይ በዝምታ መታለፉ ደግሞ የብአዴንን የቁም ሞት ብቻ ሳይሆን የህወሃትን የልቡን ሳይሰራ የማይተኛ፣የሁልጊዜ አሸናፊነት ያስገነዝባል፡፡ በዚህ ጉዳይ የሚመጣውን መዘዝ መመለሱ አድበስብሶ እንደማለፉ የሚቀል ከሆነ የምናየው ይሆናል፡፡

ኢህአዴግ በማብራሪያው የተቃውሞ ፖለቲካውን ስላሽመደመደበት እኩይ ስራው ያስቀመጠው ማብራሪያ ከማድበስበስም በላይ ነው፡፡ የተቃውሞ ጎራውን እግር በእግር እየተከታለ ቋንጃውን ሲቆርጥ የኖረው ባለጠመንጃው ኢህአዴግ ‘ለተቃውሞ ፖለቲካው ድጋፍ ባለማድረጌ ፀፅቶኛል፤ ይህንንም ያለ ሃፍረት መክሬበታለሁ’ ሲል የሰራው ስራ አሳፋሪ መሆኑን ልቦናው እንዳወቀ ያሳብቃል፡፡ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች እግር ሲያወጡ ጠብቄ እግር እቆርጣለሁ ከማለት በገንዘባቸው የሆቴል አዳራሽ ተከራይተው እንኳን እንዳይመክሩ እስከማድረግ የደረሰ፣ በመጨረሻም ለመደራደር ስምንት ወር የሚደራደሩ ምንደኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አዝሎ የቀረ እኩያ አልቦ አምባገነን ፓርቲ እንደሆነ ቤት ቀርቶ ጎረቤት ያወቀው ሃቅ ነው፡፡

የተቃውሞውን ጎራ በጠመንጃ እና በእስርቤት ታግዞ ፀጥ ካደረገ በኋላ አውራ ፓርቲ ነኝ ሲል የኖረው ኢህአዴግ ዛሬ ብድግ ብሎ የተቃውሞ ፖለቲካውን ባለማገዜ አዝናለሁ ማለቱ ቀልድ ይሁን ቁምነገር ውሎ አድሮ ይለያል፡፡ ያለምንም ይሉኝታ ምርጫ ቦርድን ሳይቀር ተጠቅሞ፣ፍርድቤቶችን አስከትሎ፣ወታደሩን አሰማርቶ፣ይሁዳዎች አስርጎ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዳልነበረ ማድረግ የተቃውሞ ፖለቲካውን ማውደም ሳይሆን አለማገዝ ብቻ ሆኖ የቀረበበት መንገድ ለነገሩ ቀልድነት ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡

መካድ

ከግምገማው መልስ ሃገራችን የምትገኝበት ችግር ሁሉ መንስኤ በፓርቲችን አባል ፓርቲዎች መሃከል የሚደረገው መርህ አልቦ ግንኑነት ነው እንጅ አስተዳደራችን ለእኩልነት የተመቼ የማንም የበላይነት የሌለው ነው ይላሉ ክህደት መድህን የሚመስላቸው የኢህአዴግ መሪዎች፡፡ የባሰውን ያመጡት አቶ ለማ መገርሳ ደግሞ “የኢትዮጵያ ህዝብ እያለ ያለው ተስተካከሉና እናንተው አስተዳድሩን ነው” ሲሉ ወፍራም ክህደት ይክዳሉ፡፡“ዳውን ዳውን ወያኔ!” የሚለው በየሰላማዊ ሰልፉ የማይጠፋው ጥያቄ እንዴት ሆኖ ተስተካክላችሁ ግዙን ተብሎ እንደተተረጎመ ካድሬ ያልሆነ ሰው ሊገባው አይችልም፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ ወገብ ያጎበጠው የዲሞክራሲ እጦት፣የእኩልነት ጥማት፣ የመተንፈሻ መድረክ ማጣት ቀንበር፣የድህነት መንሰራፋት፣የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ የሙሰኛ ባለስልጣናት በስልጣን መባለግ፣ የፍርሃት ቆፈን ሁሉ ወደጎን ተጣለና ዋኛው የሃገሪቱ ችግር የኢህአዴግ አባል ፓርቲ የላይኛው አመራር ከቀድሞ አሽከርነቱ መጉደሉ ተደርጎ ቀረበ፡፡ ይህ የሚያሳየው ህወሃት ኢህአዴግን ችግር መስሎ የሚታየው የራሱን ስልጣን ሊያሳጣ የሚችል ችግር ብቻ መሆኑን ነው፡፡ እንደ ጉድ የተወራው የግንባሩ አባል ፓርቲዎች የጎንዮሽ ልፊያ ፈፅሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር አይደለም፡፡ችግር ከሆነ ችግር የሚሆነው በአሽከር ካድሬዎች አድሮ ኢትዮጵያን ሲዘውር ለኖረው እና ታማኝ አሽከሮቹ ቀን አይተው ላንጓጠጡት ህወሃት ብቻ ነው፡፡በዚህ ከቀጠልን በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በሌላም መታኮሳችን አይቀርም የሚለው የዶ/ር ደብረፂዮን ንግግር የዚህ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የስርዓት ለውጥ፤የእኩልነት ጥማት፣የሃገር ባለቤትነት፣የሰብዓዊ ክብር አምሮት ነው እንጅ የህወሃት በኦህዴድ ላይ መግነን ወይም የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የቀድሞ ግርማ መሸራረፍ አይደለም፡፡በነዚህ እውነተኛ የህዝብ ጥያቄዎች ዙሪያ ያላጠነጠነ የክህደት መንገድ ለራስ እንጅ ለህዝብ ጥያቄ መልስ አይሆንም!

የመግለጫ/ማብራሪያው አያዎ

ኢህአዴግ ታላላቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አስተላለፍኩበት ሲል ብዙ ያለለት መግለጫም ሆነ ማብራሪያ ልብ ላለው በተቃርኖዎች የተሞላ ነው፡፡ የተቃርኖውን አሃዱ ሲል ኢህአዴግ የመሰረተው ስርዓት ማንንም የበላይ ማንንም የበታች የማያደርግ የእኩልነት ዓለም እንደሆነ በመግለጫው የወተወተው ተረስቶ በኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ አፈና በመኖሩ የተለየ ሃሳብ ማንፀባረቅ ስላልተቻለ በፓርቲው ውስጥ ዲሞክራሲ ሊቀጭጭ ቻለ ሚል ነገር በአራቱም አመራሮች አብዝቶ ተነገረ፡፡ያለ ፍርሃት መናገር ባለመቻሉ ደግሞ በእህት ፓርቲዎች ውስጥ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ነገሰ፤የሰፈነው አለመተማመን እና ጥርጣሬ ደግሞ እስከመታኮስ ሊያደርስ እንደሚችል ነው የተብራራው፡፡እንደተባለው ፓርቲው የበላይ እና የበታች የሌለው የእኩልነት ቤት ከሆነ የተለየ ሃሳብ እንዳይነገር የሚያፍነው ማን ነው? አፈና እና አፋኝ ካለ አፋኙ የበላይ ታፋኙ የበታች መሆኑ ያነጋግራል? አፈና ባለበት እኩልነት ከወዴት ይመጣል?የበላይ የበታች ካልኖረ ማን ማንን ነው የሚፈራው? ምን እንዳይመጣ ነው ጥርጣሬው?

ሌላው አያዎ በአቶ ለማ መገርሳ ተነገረው የኢትዮጵያዊነት ጭነት ጉዳይ ነው፡፡ አባይን ተሻግረው “ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው” ሲሉ የባጁት ኦቦ ለማ ከዶ/ር ደብረፅዮን ጋር በተሰየሙበት መድረክ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት በብሄር ብሄረሰቦች ላይ የተጫነ ጭነት በመሆኑ በጎሳ ፌደራሊዝሙ በኩል ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን ያስተዳድሩ ዘንድ ግድ እንደሆነ ፈርጠም ብለው ይገልፃሉ፡፡ ወዲያው ደግሞ ማንኛውም የግንባራቸው እርምጃ ሃገራዊ አንድነትን ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ፣የሃገርን ህልውና ያስቀደመ መሆን እንደሚገባው ጠንከር አድርገው ይናገራሉ፡፡ በግድ የተጫነ ላሉት ኢትዮጵያዊነት ህልውና ይህን ያህል ማሳሰቢያ ማብዛታቸው ግራ ነው፡፡

ሌላው የአቶ ለማ ግራ አጋቢ ንግግር በስራ አስፈፃሚው ስብሰባ ውጤት መርካታቸውን የገለፁበት ነገር ነው፡፡በአራቱ ድርጅቶች መግለጫ ላይ በተሻለ ድፍረት እውነትን ለመግለፅ ሲጣጣሩ የዋሉት አቶ ለማ ብዙ ጭጋግ በወረሰው የግንባራቸውን የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ውጤት ለመርካት መቸኮላቸው የውድ ይሁን የግድ ራሳቸው ያውቃሉ፡፡አቶ ደመቀ መኮንን ስለ ህወሃት የበላይነት አለመኖር እየተናገሩ ይህን የሚያስጠረጥሩ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ግን መኖራቸውን የደሰኮሩት የአሽከርነት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ነገር ቢሆንም ምንም በሌለበት መንጠላጠያ ከየት መጣ ማስባሉ አይቀርም፡፡ አቶ ደመቀ አንዳንድ መንጠላጠያዎች ሲሉ ሊያሳንሱት የሞከሩት በውትድርናው፣በደህንነቱ፣በውጭግንኙነቱ፣በውጭ ንግዱ፣በኢፈርት ግዝፈት፣በየፌደራል መስሪያቤቱ የአድራጊ ፈጣሪ ስብጥር፣በአዲስ አበባ ሁለመና የሚገለፀውን ለአደግዳጊ ብቻ የማይከሰተውን የገዘፈሃቅ ነው፡፡በዚህ ረገድ አይናቸውን በጨው አጥበው ከተናገሩት አቶ ደመቀ ይልቅ “ህወሃት የበላይ አይደለም የምንለውን ሁሉም ሰሚ እንደማያምነን እናውቃለን” ያሉት አቶ ኃ/ማርያም ይሻላሉ፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በእህት ድርጅቶቹ በኩል ያለውን ችግር በመፍታቱ ለሁሉ መፍትሄ ያመጣ፣በውስጠፓርቲው ቀርቶ ለተቃዋሚዎ ፓርቲዎች የመጫወቻ ሜዳውን በመክፈት ዲሞክራሲን የማስፋት ስራ እንዲሰራና ሃገራዊ መግባባት እንዲመጣ በማድረግ ሃገራችን ላለችበት ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄን የሚያመጣ ተደርጎ ቀርቧል፡፡ይህ በሚነገርበት ወቅት ግን ከፖለቲካዊ መፍትሄ ጋር ግንኙነት በሌለው ሁኔታ መለዮለባሾችን ያጨቀ በአቶ ሲራጅ ፈጌሳ እና በአቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ የሚመራ፣በክልል ፕሬዚደንቶች የታጀበ የብሄራዊ ፀጥታ ምክርቤት ስብሰባ ይከወናል፡፡ ይህ የፀጥታ ምክርቤት ፋኖ በየክልሉ አሰማርቶ የሃገሪቱን ፀጥታ በክላሽ በታጀበ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ግብረሃይል ነው፡፡ ይህ ግብረሃይል ከተዋቀረ አንድ ወር አስቆጥሯል፤ከሰሞኑም የየክልል ፕሬዚደንቶችን ጨምሮ ለስብሰባ ተሰይሟል፡፡በዚህ ውስጥ ጉልበት እንጅ ፖለቲካዊ መፍትሄ አይታይም፡፡ እውን ኢህአዴግ ለሃገራችን ወቅታዊ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ቢሰጥ ኖሮ የክልሎችን ፀጥታ ለማስጠበቅ የክልል ፖሊስ በቂ ነበር፡፡

ብሄራዊ የፀጥታ ምክርቤቱ ፀጥ የማድረግ ስራውን ለመከወን ወደ ክልሎች ሲወርድ የክልሎች የሲቪል አስተዳደር ተሸመድምዶ ለዚሁ ወታደራዊ ጫማ እጅ አለመስጠቱን፣ያልታወጀ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር በሃገሪቱ ስለአለመስፈኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ሃገርን የማረጋጋቱ ስራ በወታደራዊ ጡንቻ ታገዘ ማለት የደህንነት እና ወታደራዊ ክንፉን የሚዘውረው ህወሃት የተለመደ ግዝፍናውን አገኘ ማለት ነው፡፡ይህ ማለት ደግሞ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ምክርቤት ስብሰባ ብዙ የተወራለት የግንባሩ እህት ድርጅቶች ነፃነት፣ራስን በራስ የማስተዳደር ነገር ውሃ በላው ማለት ነው፡፡

“ወደህ በገባህ አትከራከር!”

አስራሰባት አመት መታገሉን የጌትነቱ ሰገነት ያደረገው ህወሃት በኢህአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ አጋርም ሆነ አባል ብሎ የሰየማቸው ፓርቲዎች ውልደት እድገታቸው ህወሃት በደሙ በላቡ በፃፈው “ደማቅ ታሪክ” እንደሆነ አምነው የተጠመቁ፣ይህንኑ የቤቱን ህግ አክብረው ሊኖሩ ወደው የገቡ የድሮ የጠመንጃ ገድል ምርኮኞች ናቸው፡፡ ይህን በተግባርም በቃልም ከማስገንዘብ የማይቦዝነው ህወሃት ከአንድ ትግሬ አባወራ ቤት ስንት ሰው ሞቶ በአጠቃላይ ስልሳ ሽህ ትግሬ ተሰውቶ አዲስ አበባ እንደ ተደረሰ ለወዶ ገቦቹም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለመተረክ ደክሞት አይውቅም፡፡ ህወሃት ስልጣን ላይ ለመቀመጥ ስልሳ ሽህ ምክንያት እንዳለው በቅርቡ በትግራይ ኦንላይን ላይ ተፅፎ አንብበናል፡፡
በኢህአዴግ ቤት ተቀምጦ የህወሃት እበልጣለሁባይት አስቸገረኝ፣ቡድንተኞች አሰማራብኝ፣ዘመዶቹ ይበልጥ ቤተኛ ነን አሉኝ፣ እኔ ሳላውቅ በክልሌ ወታደር ልከው አስተኮሱብኝ የሚለውን ክስ የሚያቀርብ ባለሟል ይሳቅበት ይሆናል እንጅ አይታዘንለትም፡፡የተለመደውን፣ወደው የገቡበትን፣የቤቱን ዋነኛ ደንብ ዛሬ ከሰማይ ዱብ ያለ በደል አድርጎ ማውራት ትርጉም የለውም፡፡

ጥያቄያቸው እና ጥያቄያችን ….

ኢህአዴግ ብዙ ችግሬን አየሁበት መፍትሄም አስቀመጥኩበት ባለበት የሰሞኑ የስራ አሰፈፃሚ ስብሰባው አንገብጋቢ አድርጎ ያነሳው ጉዳይ ሲጠቃለል ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በግንባሩ ውስጥ የቀድሞ ሞገሱን ማጣቱ፣የአባል ፓርቲዎች ቋንቋ መደበላለቅ፣ከቀድሞ አቤት ወዴት ባይነታቸው መጉደል፣የውሰጠ ፓርቲ ደሞክራሲአለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ደግሞ የራሱን የቤት ጣጣ ነው እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ችግር ተደርጎ የቀረበው የግንባሩ ፓርቲዎች የቋንቋ መደበላለቅ፣ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ክንድ መዛል ለኢትዮጵያ ህዝብ ደስታ እንጅ ሃዘን አይደለም፡፡
የኢትየጵያ ህዝብ የሚፈልገው ዲሞክራሲ እነ አቶ ለማ/ደመቀ የሚናፍቁት ከኢህአዴግ ውስጠ ፓርቲ ተነስቶ፣በሊጎች እና ክንፎች ዞሮ ህዝብ ጋ የሚደርስ፣ በዲሚክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተቀፈደደ አይነት ዲሞክራሲ አይደለም፡፡ስለሆነም ኢትየጵያህዝም ጥያቄ ከኦህዴድም ሆነ ከብአዴን ጥያቄ ጋር አይገጥምም፡፡ኢህአዴግ የሚወተውተው የተለውጫለሁ ጋጋታም ከሚፈለገው ለውጥ ርቆ የቆመ ማስመሰሉ የበዛ፣ ይጨብጡት ዘንድ ህልውና የሌለው፣እስረኛ እፈታለሁ ከሚለው በስተቀር ሌላ የሚጨበጥ ቁምነገር የሌለው ነገር ነው፡፡ እስረኛ እፈታለሁ የሚለውም የባቡር ሃዲድ ስለሰራሁ፣አባይን ስለገደብኩ ስልጣ ላይ ልቀመጥ የሚለው የተለመደ ስልጣን ላይ ለመሰንበት የሚጠየቅ የዋስትና ማረጋገጫ ከመሆን አይዘልም፡፡

ለአስተያየት meskiduye99@gmail.com

___
በዚህ ድረ ገጽ ነጻ አስተያየት ወይ ሃሳብ ለማካፈል ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ ይላኩልን editor@borkena.com

ደንጋራው ብአዴን (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
ኅዳር 15 2010 ዓ ም

Meskerem  Abera
መስከረም አበራ

አምባገነንነት የሃገራችን ገዥዎች መለያ እንደሆነው ሁሉ የእርስበርስ መቆራቆስ ደግሞ የተቃውሞውን ፖለቲካ የተጣባ ክፉ ደዌ ነው፡፡ በተቃውሞ ፖለቲካ ጀማሪዎቹ መኢሶን እና ኢህአፓ መሃከል የነበረው የጎንዮሽ ልፊያ የዚህ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡ በኢህአፓ ውስጠ-ፓርቲ ውስጥ የነበረው እርስበርስ መበላላት ትልቁን ዳቦ (ኢህአፓን) ሊጥ አድርጎት የቀረ አሳዛኝ እውነት ነው፡፡ ይህ ደዌ ኢህአፓን ዝንጀሮ እንዳየው ክምር መበታተኑ ብቻ አይደለም ጥፋቱ- የዘር ፖለቲካን ክፉ ደዌ በህብረ-ብሄራዊ ትግል እግር ተክቶ ማለፉ እንጅ፡፡
ለዓለማቀፋዊ ላብአደራዊነት ሲታገሉ የኖሩት ኢህአፓ እና መኢሶን በአመዛኙ በራሳቸው የውስጥ ችግር እንዳልሆነ ከሆኑ በኋላ ነበር በዘመኑ እዚህ ግባ የሚባል ፖለቲካዊ ትኩረት ያልነበረው ህወሃት መለምለም የጀመረው፡፡ በሰዓቱ ‘ህብረ-ብሄራዊ ነኝ’ ይል የነበረው ብአዴንም በእናት ፓርቲው ኢህአፓ መቃብር ላይ ነበር ህልውናውን የጀመረው፡፡በጫካ ቆይታው ህብረ-ብሄራዊው ኢህዴን በብሄር ተኮሩ ህወሃት አይዞህ ባይነት ብቻ ሳይሆን ለሎሌነት በተጠጋ ጥገኝነት ስር እንደነበር አቶ ገብሩ አስራት በመፅሃፋቸው በደንብ አብራርተውታል፡፡ ህብረ-ብሄራዊ ነኝ ሲል የታላቋን ሃገር ሁሉንም ህዝብ ፖለቲካዊ ህይወት ለማሻሻል እታገላለሁ ባዩ ኢህዴን ለአንድ ጎሳ እታገላለሁ በሚለው ህወሃት ጉያ ስር ገብቶ ‘አቤት ወዴት’ ማለቱ የአደናጋሪነቱ ጅማሬ ነው፡፡ ከፅንሰት ውልደቱ ጀምሮ ግራ አጋቢነቱ እየባሰበት የሄደው ብአዴን አትኩሮት ሰጥቶ ለሚከታተለው ብዙ አስገራሚም አደናጋሪም ማንነቶችን የተሸከመ ፓርቲ ነው፡፡

ከፖለቲካዊ ፍዘት ወደ ጎሰኝት መኮማተር

ኢህዴን በጫካ ትግሉ ዘመን የትግራይ ነፃ አውጭ ነኝ ባዩ ህወሃት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግስ የእርሱ ህብረ-ብሄራዊነት ከህወሃት ጎሰኝነት ጋር እንዴት መሰናሰል እንዳለበት ግልፅ አላደረገም፡፡የኢትዮጵያን ህዝብ ወክሎ ሲታገል የትግራይ ህዝብም የኢትዮጵያ ህዝብ ነውና ጥያቄው በኢህዴን ትግል ውስጥ ሊመለስ እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ኢህዴን ስሙን የሚመጥን ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ብርታት አልነበረውምና የህብረ-ብሄራዊነትን ታላቅ ስም ይዞም ለአንድ ጎሳ እታገለላለሁ በሚለው ህወሃት እየተዘወረ በሽፍንፍን አዲስ አበባ ገባ፡፡ ኢህአዴግ የሚለው ማዕቀፍ ከተመሰረተ በኋላም በኢህዴንነቱ ቀጠለ፡፡ ኢህአዴግ የሚለው ማዕቀፍም ሆነ በዚህ ስር ገባ የተባለው ኢህዴን ህብረ-ብሄራዊ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ በሽግግር መንግስቱ ወቅትም ኢህዴን በፓርላማ የተወከለው ኢህአዴግ በሚለው ስም ነበር፡፡ በህወሃት፣በሻዕብያ እና በኦነግ ሲዘወር በነበረው የሽግግር ወቅት ፖለቲካ የኢህዴን ሚና ፈዞ ህወሃት ያለውን ‘አዎ አዎ!’ ማለት ነበር፡፡

ኢህዴን ከዚህ ፖለቲካዊ ፍዘት ወደ ባሰው ጎሰኝነት የተኮማተረው በመአድ መመስረት ምክንያት ነበር፡፡ በታዋቂው ሃኪም ፕ/ሮ አስራት ወልደየስ ዋናነት የተመሰረተው መአድ የመመስረቱ ዋነኛ ምክንያት በሽግግሩ ወቅት በአማራ ህዝብ ላይ የወረደው መቅሰፍት ነበር፡፡ ጊዜ ካለፈ በኋላ ህወሃት በኦነግ፣ ኦነግ ደግሞ በህወሃት የሚያላክኩት ግን ከሁለቱ የማይዘል በአማራ ህዝብ ህልውና ላይ የደረሰው ግፍ አንዳች ሃይል የዚህን ህዝብ ድምፅ ለማሰማት መመስረት እንዳለበት ግድ ብሎ ነበር፡፡ ስለሆነም ፕ/ሮ አስራት ግድ ያለ ውድ በአንድ ብሄር ስም ፓርቲ መስርተው የዚህን ህዝብ መከራ ለማቅለል ደፋ ቀና ይሉ ያዙ፡፡በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን መአድ ወደ ህብረብሄራዊነት እንደሚያድግ፣እርሳቸውም ኢትዮጵያዊነታቸውን እንደሚያስቀድሙ ይናገሩ እንደ ነበር መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

በመሆኑም የመአድ አባላት አማሮች ብቻ አልነበሩም፡፡ ይልቅስ የሰብዐዊ ፍጡርን እንግልት የማይወድ ሁሉ በመአድ ጥላ ስር ተሰባስቦ በየቦታው ለሚገደለው፣ በገደል ለሚወረወረው አማራ ጥብቅና መቆም ጀመረ፡፡ይሄኔ ፕ/ሮ አስራት ጥርስ ውስጥ ገቡ፤ ፓርቲያቸውም ሆነ የአባላቶቹ ህልውና አደጋ ውስጥ ገባ፡፡ ይሄኔ የብልጣብልጡ አቶ መለስ ህወሃት መአድን በብአዴን የማጣፋትን ድንቅ ፖለቲካዊ “ጌም” ይዞ ብቅ አለ፡፡ ወትሮም በፖለቲካዊ ፍዘት ውስጥ የነበረው የነታምራት ላይኔ ብአዴን እሳት እንደነካው ላስቲክ ተጨማዶ ብአዴን ለመሆን አላመነታም፡፡

እዚህ ላይ ልብ መባል ያለበት ነገር ለእያንዳንዱ ብሄረሰብ ቆሜያለው የሚለው የኢህአዴግ አባልም ሆነ አጋር ፓርቲ የህወሃትን ቡራኬ ካላገኘ ስንዝር መራመድ አለመቻሉ ነው፡፡ የአማራን ህዝብ ፍዳ ለማስቆም ከልብ ተነሳስቶ የተመሰረተው መአድ አባላት ቤተክርስቲያን እንደገባች ውሻ ሲታደኑ የነበረው አመሰራረታቸው የህወሃት አሻራ ስለሌለበት ነው፡፡ ከዚህ መገንዘብ የሚቻለው የሃገሪቱ የሽግግር ዘመን ቻርተርም ሆነ በኋላ ህገ-መንግስቱ ስለመደራጀት መብት የሚያስቀምጡት አንቀፅ ምድር ላይ ነፍስ የሚዘራው ህወሃት ይሁን ብሎ እስትንፋስ ሲዘራበት ብቻ መሆኑን ነው፡፡እውነት እንነጋገር ከተባለ የአማራን ህዝብ ቀልብ በመግዛቱ በኩል ከመአድ እና ከብአዴን የቱ የተሳካለት ነበር/ነው? በትቂቱ ፖለቲካዊ ስሌት ብንሄድ እንኳን መአድ የከሰመው ብአዴን ደግሞ የአማራን ህዝብ እየተሳደበም ቢሆን ሁሌ ተመረጥኩ እያለ የሚያስተዳድረው የአማራን ህዝብ ቀልብ የሚስብ ፖለቲካዊ ማንነት ኖሮት ሳይሆን የባለ ጠብመንጃው ህወሃት የትሮይ ፈረስ ስለሆነ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ብአዴን አንድ የተሳካለት ነገር ቢኖር መአድን አጥፍቶ የህወሃት/ኢህአዴግን ልብ ማረጋጋት መቻሉ ነው፡፡

“ስፊኒክሱ” ፓርቲ

የሃገራችን የብሄር ፖለቲካ ስሪት ከክልሎቹ መጠነ ስፋት ጀምሮ በርካታ አስቂኝ እና ግራ አጋቢ እውነቶች ቢኖሩትም እንደ በአዴን አስቂኝነቱ የሚበረታበት የለም፡፡ ጨቋኝ ሲባል የኖረው አማራ መአድን ለማጥፋት ሲባል ብቻ ከመቅፅበት ተጨቋኝ ሆኖ ብአዴን የሚባል ዲሞክራሲ አማጭ ፓርቲ ተነጎተለት፡፡ ከዚህ ይብስ የሚገርመው ክልሉን እንዲያስተዳድር የተነጎተውን ፓርቲ ከቁንጮው ሆነው የሚያስተዳድሩት ሰዎች የአማራ ክልልን በውል የማያውቁ ውልደት እድገታቸው ከአማራ ክልል የራቀ፣በስነልቦና ሆነ በእምነት ከህዝቡ ጋር የማይዛመዱ ሲሆኑ የፓርቲው የታችኛው መዋቅር ደግሞ ግድ ያለውድ አማሮች እንዲሆኑ ሆነ፡፡ ከላይ በኤርትራዊው በረከት፣ “ኦቦ” በሚባለው የኦሮሞ ጎልማሶች መጠሪያ ማዕረግ የሚታወቀው የጭሮው አዲሱ ለገሰ፣ ከየት እንደሆነ በውል በማይታወቀው ታምራት ላይኔ፣በኮረሙ ካሳ ተ/ብርሃን፣ በአዲስ አበባው ህላዌ ዮሴፍ እና ካሳ ጥንቅሹ፣ የአማራ ህዝብን ሙልጭ አድርጎ በሚሳደበው በደቡቡ ተወላጅ ተፈራ ዋልዋ ሲዘወር የኖረው ብአዴን ከስር ከተፎ አማራ ካድሬዎችን አሰልፎ ሲታይ ከአንገቱ በላይ ሌላ ፍጥረት ከአንገቱ በታች ሰው የሚመስለውን ስፊኒክስ ሃውልት መስሎ ተገትሮ ከመታየት ያለፈ ለማንም ምንም ሲያደርግ አልታየም፡፡

ኢህዴን የኢህአዴግ ምንጭ???

‘በጫካ ትግሉ ወቅት ትግራይን የመገንጠል አላማችንን ስህተትነት ወዲያው ተረድተን የመገንጠል ጥያቄችንን ተውን’ የሚሉት ህወሃቶች፤ ‘ለትግራይ ብቻ ከመታገል ወደ ህብረብሄራዊነት አድገን ኢህአዴግን መመስረታችን ሌላው እርምት የወሰድንበት አቅጣጫ ነው’ ባዮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግን ከመሰረቱ ትቂት አመት በኋላ ግን ህብረ-ብሄራዊውን ኢህዴን ወደ ብአዴንነት እንዲያንስ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ ህወሃቶች ኢህዴንን ወደ ብአዴን ሲያሳንሱ በስመ ኢህአዴግ የሃገሪቱን ፖለቲካ በእናት ፓርቲያቸው ህወሃት በኩል የመዘወሩን ረቂቅ ፖለቲካዊ እቅድ ታሳቢ አድርገው እንደነበረ ፈዛዛው ኢህዴን ይግባው አይግባው የሚያውቀው ራሱ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ህወሃት እንደዚህ ባለ ጥበብ ህወሃትነቱን ሳይለቅ ኢትዮጵያን ለመዘወር ደግሞ ኢህአዴግ የሚለውን ካባ ሲለብስ ደንጋራው ኢህዴን ወደ ጎሰኝነት ተኮማትሮም “እልፍ ሆእኛለሁ” እያለ መዘመሩ አልቀረም፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የብአዴንን ይሁን የኢህዴንን 35ኛ አመት በአል ለማክበር በሚደረገው ሽር ጉድ የደኢህዴን እና የኦህዴዶቹ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ እና አቶ አባ ዱላ ገመዳ በኢቢሲ ቀርበው ‘የእኛ ፓርቲዎችም የተመዘዙት ከኢህዴን ስለሆነ የኢህዴን ልደት የእኛ ፓርቲዎችም ልደት ነው’ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እንደውም አቶ ኃ/ማርያም “የብአዴን 35 አመት ለደኢህዴንም ይሰራል” እንደማለት ሲሉ ነበር፡፡ በየጊዜው የሚያመጡት አዲስ ዜማ የማያልቅባቸው የኢህአዴግ ባለስልጣናት እንደሚያወሩት ከሆነ ኢህዴን ከህወሃት በቀር የሁሉም የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እናት ፓርቲ ነው ማለት ነው፡፡ይህ ማለት 37ኛ አመቱን “በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፃፍኩ” እያለ ለራሱ እየዘፈነ የሚያከብረው፣ ኢህዴን ይሁን ብአዴን የማይታወቀው ፓርቲ ተሸንሽኖ ኦህዴድ፣ብአዴን እና ደኢህዴንን ሆኗል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከብአዴን ብቻ ሳይሆን ከደኢህዴንም ከኦህዴድም ስም በፊት ኢህዴን የሚለው ምህፃር መጠቀስ ነበረበት፡፡ በተጨማሪ ከሰሞኑ እየተከበረ ያለው የብአዴን የውልደት በአል ከሆነ ደግሞ በ1985 እንደ መመስረቱ ሰላሳ አምስት አመት የሞላው እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት ሚስጥሩን አቶ ገዱም ሆኑ አቶ ደመቀ የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡

ህዝብ አልቦው ብአዴን

በ1968ቱ ማኒፌስቶው “የአማራ ብሄር ጨቋኝ ናት” ሲል በደፈናው አማራን ሁሉ ፈርጆ ከተነሳው ህወሃት ጋር ግንባር ገጥሞ አዲስ አበባ የገባው ኢህዴን ውሎ አድሮ ‘የአማራ ጭቁን ህዝብ ወኪል ነኝ፤ ስሜም “ብአዴን” ነው’ ብሏል፡፡ ለነገሩ ህወሃትም መጠነኛ ስክነት ሲያገኝ ቢያንስ በቃል ሁሉም አማራ ጨቋኝ አይደለም ማለት ጀምሯል፡፡ ሆኖም የትኛው አማራ ነው ጨቋኙ በሚለው ላይ በህወሃት/ኢህአዴግ መንደር ስክነት የለም፡፡ አቶ መለስ ‘ጨቋኙ የሸዋ አማራ ነው’ ሲሉ እነ አቶ በረከት ደግሞ ‘ጨቋኙ የአማራ ገዥ መደብ ነው’ ይላሉ፡፡ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ውስጥ ገዥ ሆኖ ያልጨቆነ ዘር ይገኝ ይሆን? አገዛዝ እና ጭቆናስ በሃገራችን ዘር ለይተው የሚገናኙ ጉዳዮች ናቸው? ወይስ ስልጣን ሲያገኝ ጫቋኝ የሚሆነው አማራ ብቻ ነው? አማራ ያልሆኑቱ፣በኢትዮጵያ የገዥነት ስልጣን እርከን ላይ የነበሩ ሰዎች ያስተዳድሩ የነበረው ከጭቆና በራቀ ዲሞክራሲያዊ ዘይቤ ነበር? ይህ ማለት የመጨረሻው ዘውዳዊ አገዛዝ ማገር የነበሩት እነ አቶ ይልማ ደረሳ፣ የደርጉ ባለሟሎች እነ ጓድ ተስፋየ ዲንቃ፣ደበላ ዴንሳ፣ጴጥሮስ ገብሬ፣ተስፋየ ወልደስላሴ፣ፍሰሃ ደስታ ወዘተ አማሮች ባለመሆናቸው ከጨቋኝነቱ ማህበር የሉበትም ማለት ነው! ወይስ እነዚህ ሰዎች በገዥው መደብ ውስጥ ተሰግስገው ያሳዩት የጭቆና ማህበርተኝነት ሃጢያት አማራ ባለመሆናቸው ብቻ ይሰረይላቸውና የጨቋኝነቱን መርገም ሁሉ አማራ ጓዶቻቸው ይወስዳሉ? እንደ ባለአእምሮ ለሚያስብ በጨቋኞች ወንበር የተቀመጠ ቀርቶ ጭቆናን እያየ ያልተቃወመ ሁሉ የሞራል ፍርደኛ ነው፡፡ በተቀረ ጭቆናን በዘር የሚተላለፍ መርገም አድርጎ አንድን ዘር ማብጠልጠል የበታችነት ከሚያሰቃየው ልቦና የመነጨ ራስን የማስገመት አካሄድ ነው፡፡

እንዲህ ለፍረጃ በቸኮለ ሁኔታ አማራውን ሰድበው ለተሳዳቢ፣ አድነው ለአዳኝ ወጥመድ ሲሰጡ የኖሩት ህወሃት/ኢህአዴጎች ናቸው እንግዲህ ከእለታት አንድ ቀን ኢህዴን ወደ ብአዴን አንሶ ለጭቁኑ አማራ መቆም አለበት ሲሉ ብአዴንን ያነጎቱት፡፡ የብአዴን ለአማራው ህዝብ እውነት መቆም አለመቆም ተጠየቅ ብዙ የሚያከራክረውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ከዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጉዳይ ለብዙ አመታት በተፃፉ መዛግብት ሳይቀር በጨቋኝነት ሲብጠለጠል የኖረው የአማራ ህዝብ እንዴት ነው ነፃ አውጭ ፓርቲ ያስፈለገው? የሚለው ነው፡፡ይህችን ለማለባበስ ነው በአማራው ህዝብ ላይ ብዙ ግፍ ከተሰራ በኋላ(ከአርባጉጉው እና ከበደኖው ዋይታ በኋላ) ህወሃት/ኢህአዴግ የአማራው አርሶ አደር እና የአማራው ገዥ መደብ ተለያይቶ መታየት አለበት እያለ ያለው፡፡ ይህ አባባሉ ቢረጋለትም ህወሃት/ኢህአዴግ ስህተቱን አረመ ብሎ መቀበል ይቻል ነበር፡፡ ግን ይህም አልሰነበተለትም፡፡እንጀራ ፍለጋ ወደ ሃገሩ ሌላ አካባቢ ሰርቶ ለመኖር የሄደውን ደሃ አርሶ አደር “ሞፈር ዘመት” የሚል ስም ተለጥፎለት እንዲፈናቀል ሲደረግ አይተናልና በኢህአዴግ ዘንድ የአማራ ገዥ መደብ ከአማራ አርሶ አደር ተለይቶ ታይቷል ብንባል እንዴት እናምናለን፡፡

ለአማራ ጭቁን አርሶ አደር ብቻ ቆሜያለሁ የሚለው ብአዴን ይህን በተመለከተ አንዳች ነገር ትንፍሽ ያለማለቱ ተልዕኮው ከሚናገረው የአማራህዝብ ጥብቅና ጋር እንደማይገናኝ ያሳብቃል፡፡ ይብስ ብሎ ‘የቆምኩት በአማራ ክልል ላለ አማራ ብቻ ነው’ ሲል እያደር ማነሱን አስመሰከረ፡፡ በህወሃት/ኢህአዴግ አስተሳሰብ ሎተሪ ሊያዞርም ሆነ የጉልበት ስራ ሊሰራ ከክልሉ የወጣ አማራ ሁሉ ነፍጠኛ ነውና ብአዴን ደግሞ የህወሃት/ኢህአዴግ ምልምል ነውና የቆመው በክልሉ ረግቶ ለተቀመጠው አማራ ነው፤ ይህም ትክክል ነው እንበል፡፡ይህን ብለንም ደንጋራው ብአዴን ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ነገር ይደቅንብናል፡፡ ‘በባዶ እግሩ የሚሄደው አማራ የትምክህት ልሃጩ ሌሎችን ብሄሮች አብሮ አላኖር አለ’ ሲል በር ዘግቶ የተናገረው ባለስልጣን የሚመራው ፓርቲ ለአማራ ህዝብ ጥቅም ቆሜአድራለሁ ቢል ለመቀበል ማሞ ቂሎን መሆን አለብን፡፡

የብአዴን “የአማራ ብሄርተኝነት”

ባለፈው አመት ይሁን ሁለት አመት የኢህዴን በአል ሰሞን “ኢቢሲ” የብአዴን ባስልጣናት ቀደም ሲል ተናገሩትን ንግግር መልሶ ሲያስደምጥ ሰንብቷል፡፡ እነዚህ ባለስልጣናት ከሚናገሩት ንግግር መካከል ስለ አማራ ብሄርተኝነት የተናገሩት ትክክለኛውን የብአዴን ተልዕኮ አመላካች ነው፡፡ ከአንገትም ሆነ ከአንጀት ለበአዴን አመራሮች አሁን ያለው የአማራ ህዝብ ፈለግ ለሁለት ይከፈላል- የአማራ አርሶ አደር እና የአማራ ልሂቃን በሚል፡፡ የአማራ ልሂቃን የተባሉት በአመዛኙ በኢትዮጵያ አንድነት ስም የሌላውን ብሄር ማንነት የመጨፍለቅ አላማ ያላቸው የቀድሞ ስርዓት ናፋቂ ትምክህተኞች ናቸው ፡፡ የአማራው አርሶ አደር ደግሞ እንደሌሎቹ ብሄሮች ተጨቋኝ ነው፡፡ ስለዚህ የአማራው ብሄርተኝነት ትግል መቃኘት ያለበት በተጨቋኙ አርሶ አደር ነው ባይ ናቸው – ብአዴናዊያኑ፡፡ እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡

እንደሚታወቀው የሃገራችን የብሄር ፖለቲካ አጀንዳ የሚቀረፀውም ሆነ የሚዘወረው በየብሄሩ ልሂቃን እንጅ በአርሶ አደሩ አይደለም፡፡ የአማራውን ብሄር ፖለቲካ አጀንዳ ከዚህ ሃቅ የሚለየው ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ የአማራ ልሂቃን የአማራውን ብሄርተኝነት አይቀበሉም የሚለው የብአዴኖች ትንታኔ በሌላ ጎኑ ሲታይ የብአዴን ፖለቲካዊ ማንነት እና የትግል ዘይቤ ለአብዛኞቹ የአማራ ልሂቃን የሚዋጥ አይደለም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ብአዴን አላማውን የሚያነሱ ተተኪ የአማራ ልሂቃንን በበቂ ሁኔታ ማፍራት አልቻለም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከጫካ የመጡት የብአዴን ጉምቱዎች ሲያልፉ በእግራቸው ተተክቶ የፓርቲውን ህልውና ቀጣይ የሚያደርግ ተተኪ እንዲቸግር ያደርጋልና የብአዴንን ቀጣይ ህልውና ፈተና ላይ ይጥለዋል፡፡

የብአዴኖች ትንታኔ ሌላው አንጓ የአማራው የብሄርተኝነት ፖለቲካ መቃኘት ያለበት በአርሶ አደሩ ነው የሚለው ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው የሃገራችንን የብሄር ፖለቲካ የሚዘውሩትም ሆነ ከፖለቲካው ቱርፋት ትርፍ የሚሰበስቡት የየብሄሩ ልሂቃን እንጅ አርሶ አደሩ አይደለም፡፡ እራሳቸው ብአዴንን የሚዘውሩት አማራነን ባዮቹ የብአዴን ልሂቃንም አርሶ አደሮች አይደሉምና በአባባላቸው መሰረት ሙጥኝ ያሉትን ወንበራቸውን ለአርሶአደሩ መልቀቅ ነበረባቸው፡፡ በተግባር ግን ይህን እንደማያደርጉ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ የአማራውን ብሄርተኝነት አርሶ አደሩ ይቃኘው ማለት የማይመስል ትርጉም አልባ ነገር ነው፡፡

ከርካሚው ብአዴን

የኢህአዴግ ፖለቲካ ዋና መዘውር የሆነው የብሄር ፖለቲካ ካልተሳኩለት ነገሮች አንዱ የአማራውን ብሄርተኝነት ማምጣት ነው፡፡ ብአዴን በአማራነት ቀረጢ ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያዊነታቸውን ሁለተኛ የሚያደርጉ የአማራ ልሂቃንን በሰፊው ማየት ይፈልጋል፡፡ አለቃው ህወሃት የቀድሞው ስርዓት የአማራን ሁለተንተናዊ የበላይነት ለማስፈኑ ከውልደት ፍጥረቱ ጀምሮ የሚያቀነቅነውን ዜማ ለአማራ ህዝብ ቆሜያለሁ የሚለው ብአዴንም የሚያስተጋባው ነው፡፡ይህ ህወሃትን ያደቆነው ሃሳብ ብአዴን ከኢህዴን ወደ ብአዴን እንዲኮማተር የፈለገበት የህወሃት ዋና አላማ ነው፡፡ ህወሃት ስለ አማራ ህዝብ የነበረውን አሁንም የለቀቀው የማይመስለውን አቋም ለመገንዘብ 1968ቱን ማኒፌስቶውን ማንበብ ይጠቅማል፡፡

የአማራውን ብሄር የቀድሞ ስርዓት ብቸኛ ማገር አድርጎ የሚያስበው ህወሃት በቀድሞ ስርዓቶች ለተሰሩ ጥፋቶች ሁሉ አማራው ሃላፊነትን እንዲወስድ ይሻል፡፡ ብአዴንም በዚህ ይስማማል፡፡ አማራው ለአለፈው ጥፋት ሁሉ ሃላፊነት ወስዶ፣ሌሎችን ብሄሮች ቅርታ ጠይቆ ባልሰራው ብቻ ሳይሆን ባልነበረበት ዘመን በተሰራ “ጥፋት” እየተሸማቀቀ እንዲኖር የሚያደርገውን አካሄድም ብአዴን እና ህወሃት የዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ድንቅ አብሮ የመኖር ዘይቤ ሲሉ ያሞካሹታል፡፡ ለዚህ ነው አለምነው የአማራ የትምክህት ለሃጭ መራገፍ አለበት ያለው ፣እነ አያሌው ጎበዜ አማራው ከያለበት ሲፈናቀል ጭጭ ያሉት፣ አነ ታምራት ላይኔ የአማራን ህዝብ ሲሳደቡ እና ሲያስገድሉ የኖሩት፡፡

ጠቅለል ሲል የሃገሪቱን ፖለቲካ የሚዘውረው ህወሃት ለረዥም ጊዜ ሲጨቁን ነበር ብሎ የሚያስበውን የአማራ ብሄር ከፍተኛ የስነልቦና የበላይነት የተሸከመ ትምክህተኛ አድርጎ ያስበዋል፡፡ ህወሃት ትምክህት ሲል የሚረዳው በአመዛኙ የአማራውን በአማራ ብሄርተኝነት ቀረጢት ውስጥ ለመግባት ማስቸገርና ለኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማድላቱን ነው፡፡ ይህንን ደግሞ በኢትዮጵያዊነት ሽፋን የቀድሞውን የአማራ የላይነት በሃገሪቱ ለማምጣት የአማራ ልሂቃን የሚያደርጉት ጥረት አድርጎ ይተረጉመዋል – ጠርጣራው ህወሃት፡፡ ስለዚህም አማራው ከኢትዮጵያዊነት የስነልቦና ከፍታ ወደ ተጨቋኝ አማራነት ዝቅ እንዲል ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ነው ህወሃት በብአዴን አድሮ ‘አብዛኛው አማራ እንደሌሎች ብሄረሰቦች በቀድሞው ስርዓት የተጨቆነ ነው’ የሚል አዲስ ዘፈን ያመጣው፡፡ ይህ ከአንጀት እንዳልሆነ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ አማራን ሁሉ በአንድ የጨቋኝነት አይን እንደሚያይ ጭቁን ነው የሚለውን የአማራ ደሃ አርሶ አደር ከነልጆቹ ያለርህራሄ ሲያፈናቅል አረጋግጧል፡፡ የሆነ ሆኖ ህወሃት/ኢህአዴግ በአዴንን የሚፈልገው አማራው ኢትዮጵያዊነኝ ሚለውን የስነልቦና ከፍታውን(በህወሃት አስተሳሰብ የበላይነት ትምክህቱን) ትቶ ወደ ተጨቋኝ አማራነት የጎሳ ጎሬ እንዲገባለት እንዲሰብክለት ነው፡፡ ይህ ግን እንደታሰበው የሄደ አይመስልም፡፡ መገለጫው ደግሞ ብአዴን የአማራ ልሂቃንን ‘ዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን የማይቀበሉ ትምክህተኞች አሉበት’ ሲል መውቀሱ ነው፡፡ ይብስ የሚገርመው ብአዴን ውስጥ ያሉ መካከለኛ እና ዝቅተኛ አመራሮች ራሳቸው ለብአዴን አካሄድ ባዳነት ማሳየታቸው ነው፡፡ የአቶ አለምነውን የቅሌተ ንግግር ቀርፀው ለህዝብ ይፋ ያደረጉት በራሱ በበአዴን ዝግ ስብሰባ የተገኙ ካድሬዎቹ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ በተመሳሳይ አቶ በረከት እና አቶ አዲሱ በብአዴን መካከለኛ እና ዝቅተኛ አመራሮች ላይ ያላቸውን የተመናመነ ተስፋ የተናገሩበት ምሬት የተቀላቀለበት ሚስጥራዊ ንግግር እንድንሰማው ያደረጉት በአዴኖች ናቸው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የአማራውን የበረታ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ወደ ጎሳ ብሄርተኝነት ድንክነት የመከርከም ታላቅ ተልእኮ ያነገበው በአዴን ክርከማው የታሰበውን ያህል እንዳልሰመረለት ነው፡፡

በለማ ሥም የሚመጣ “የተባረከ” ነው?! ( በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
ጥቅምት 30 ፤ 2010 ዓ ም

Meskerem Abera - article -Addis Ababa
Meskerem Abera

ከሁለት አመት ወዲህ የሃገራችን ፖለቲካ ከመቼውም በላይ በሁነት የተሞላ ሆኗል፡፡ይህ ክስተት ተደላድሎ መምራት የለመደውን ህወሃት መራሹን ኢህአዴግ እንደ እንግዳ ዶሮ እያንቦጀቦጀው ይገኛል፡፡ ተጀምሮ እስኪጨረስ አቤት ወዴት ባይ ካድሬዎች የሚመሯቸውን የጎሳ ፓርቲዎች አጋር እና አባል ድርጅቶች ብሎ ከፍሎ የሃገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ በማሳጨድ የተካነው ህወሃት መራሹ አስተዳደር የቅቡልነቱን ማጥበቂያ ገመድ የፈተለው በአፈሙዝ ሃይል መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ጠበንጃውን ከክንዱ ሳያርቅም ሆነ አጋር/አባል ላላቸው ሎሉዎቹ ሳያካፍል እንዲሁ ‘የመንግስቴ ባለእኩል ናችሁ’ እያለ በቀደደው ሲያፈሳቸው ሩብ ምዕተ አመት ተቆጠረ፡፡እነሱም የመንግስቱ ባለእኩልነታቸውን የሚያመሳክሩት ከባለጠግነቱ ከሚያጠግባቸው ስብ ነውና ይሄን ያህል አጥብቀው የሚጠይቁት ነገር የለም፡፡ ወከልነው የሚሉት ህዝብም ነገራ ነገራቸውን እንደ ትርኢት እያየ፣ በየጓዳው እየበገነ ብዙ አመት ከገፋ በኋላ መንሹ የ1997 ምርጫ መጣ፡፡

የተባለው እውነት የመሰለው ህዝብ ምርጫውን አሳወቀ፣ ‘በቃችሁኝ ገለል በሉልኝ’ ሲል ተናገረ፡፡ ማን ቢሰማ?! መሪው ህወሃትም ሆነ ጌታቸውን አምነው ውጭ የሚያድሩት አባል/አጋር ጭፍራዎቹ ያደረጉትን አድርገው ዲሞክራሲን ገድለው በሰልስት ድንኳኑ የልማት ዘፈን ከፍተው ይጨፍሩ ያዙ፡፡ ልማቱ በራሳቸው ህይወት ላይ እንጅ ሌላ ቦታ ተፈልጎ በመታጣቱ ህዝቡ እጁን ከላያቸው ላይ አነሳ! ህዝብ እና መንግስት ሃዘናቸው እንኳን እስከማይገጥም ድረስ ሌላ እና ሌላ ሆኑ፡፡ መንግስትን የሚያስደስተው ጠያቂ፣ ሞጋች፣አሳቢዎችን አስሮ መግረፍ ህዝብን አምርሮ ያሳዝናል፤ መንግስት “አልምቼ ልሞት ነው” ሲል ህዝብ ሌማቱ ደርቆ ሊሞት ሆነ፤ ገዥ “ታድሼ ልገዛ መጣሁ” ሲል ህዝብ “አይንህን የማላይበት የትልሂድ” ይል ያዘ! ቢብሰው የ1997ቱን ጥይት ረስቶ አደባባይ ተገኘ፣ የዓለምን ጩኽት ጮኸ! አሁን በመስማት የማይታማው ህወሃት/ኢህአዴግ መደንገጥ ጀመረ፡፡ ሲደነግጥ እንደሚያደርገው ተኮሰ፣ ገደለ፣ አሰረ፣ ያሰረውን ሲፈታ አሰለጠነ፣ “አይደገምም” አስባለ፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጄ – ለውጥ የለም፡፡ ለውጥ የለም ተብሎ ግን ተኩሶ አስፋልት ላይ የመድፋቱ ፈሊጥ አልቀረም፡፡ ጥይት እስካላለቀ ድረስም ይህ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በመሳሪያ ጉልበት ላይ ብቻ ተንጠላጥሎ ለሚኖር አስተዳደር መተኮስ ማቆም ማለት እንደ ሳምሶም ፀጉርን ተላጭቶ ማስፈራትን ማጣት፣’የጠላት’ መቀለጃ መሆን ነውና ይህ አይሞከርም፡፡

እስኪነክሱ ማነከስ

አሮጌውን አካሄዱን ለመተው ጠመንጃን ሙጥኝ ብሎ የመምጣቱ ተፈጥሮው የማይፈቅድለት አገዛዝ ከዚሁ ጎን ለጎን በጭንቅ ጊዜ የመውጫ መንገድ በመዘየድም አይታማም፡፡ በዋናነት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በተነሱ ህዝባዊ አመጾች ተሰቅዞ የተያዘው አገዛዝ አፈሙዛዊ አቅሙን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው አካሄዶቹ ብቻ የህዝብን ጩኽት እንደማያስቆሙለት፣ተረጋግቶ የመግዛቱን ዘመን እንደማይመልሱለት ሳይረዳ አልቀረም፡፡ በጠመንጃ ፊት ቆመው የሚጮሁ እንጅ የሚሸሹ እግሮች የሌላቸውን ብሶተኛ ሰልፈኞችን ማየቱ ይህን ያስረግጥለታል፡፡ይህ ምልክት እስኪነክስ ማነከስ የማይቸግረውን ህወሃት መራሽ አስተዳደር ለጊዜው ማንከስን እንዲመርጥ አድርጎታል፡፡ ልክ አስገባለሁ ባለበት አፉ የአዲስ አበባ ተቀናጀ ማስተር ፕላን ያልኩትን ትቻለሁ ብሎ ቆየት ብሎ ደግሞ ዞር ዞር አድርጎ የአፈፃፀም ህግ ብሎ ሊያፀድቅ ሲደገስ የሰነበተበት አሁን ደግሞ መልሶ ዝም ዝም ያለበት አካሄድ ህወሃት ማንነቱን የማይቀይር፣ ራስን ብቻ የመስማት፣የራስን ፈላጎት ብቻ የማፅናት ዘላለማዊ ማንነት እንዳለው ልብ ላለው ሁሉ አስረጅ ነው፡፡ እንደ እድል ሆኖ አምባገነኑን ስርዓት ሁለት ነብር እንዳየ ያስደነገጡት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተነሱት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች በተመሳሳይ ወቅት በአንድ ላይ አለመከሰታቸው የአማራው ጋብ ሲል ወደ ኦሮሚያ እየተፈናጠረ ነገሮችን መልክ የማስያዙን እስኪነክስ የማነከሱን አካሄድ ቀላል አድርገውለታል፡፡

ሌላው ቀርቶ ከህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የሚመጣውን ነገር ሁሉ ለውትሮው አብዝቶ የሚጠራጠውን ፣አምርሮ የሚቃወመውን አብዛኛውን ዲያስፖራ ሳይቀር ልብ ለማግኘት የሚያስችል ስራ በመስራቱ ረገድ አገዛዙ እየቀናው እንደሆነ የሚያስረዱ ፍንጮች እየታዩ ነው፡፡ከሰሞኑ ኦቦ ለማ መገርሳ አባይን ተሻግረው እያሰሙት ያሉት ዲስኩር ኦህዴድን ጨምሮ የኦሮሞ ብሄርተኞች ከሚታወቁበት የምሬት ፖለቲካ ለየት ያለ መሆኑ ብቻ አያሌ መርሆችን እግር በራስ ለማድረግ በቂ ሆኖ ተወስዶ ብዙ የፖለቲካ ምርኮ ለህወሃት/ኢህአዴግ ገቢ ማስድረጉን ለመገንዘብ ወደ ማህበራዊ ድህረገፅ ጎራ ማለት በቂ ነው፡፡ ኢሳትን ከፍቶ ላዳመጠም በኦህዴድ አሳብሮ፣በለማ መገርሳ አፈ-ጮማነት ተወስዶ ሳያውቀው ለህወሃት የተማረከው ብዙ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ይህ አስገራሚ ክስተት ህወሃት/ኢህአዴግ ጦረኛ እና ሴረኛ ብቻ ሳይሆን እድለኛም ነው ያስብላል፡፡

ጋሪው እና ፈረሱ!

ከሰሞኑ የተጋጋመው ለለማ መገርሳ የማሸብሸቡ ዝንባሌ የተጀመረው ሰውየው የኦሮሚያ ክልልን ወደ ማስተዳደሩ የስልጣን ሰገነት ከመጡ በኋላ በተለይ “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት” የሚለውን ዜማ ከደራሲዎቹ አብልጠው አሳምረው ማዜማቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ይህ ግራቀኝ ከማየት የቀረው የሚመስለኝ ለኦቦ ለማ የማሸብሸብ ዝንባሌ በቅጡ የመረመረው የማይመስለኝ ግን ደግሞ የሁሉ ስር መሰረት እንደሆነ የሚሰማኝ ነገር አቶ ለማ ወደ ስልጣን የመጡበት ምክንያት ነው፡፡እንደሚታወቀው አቶ ለማ መገርሳ ኦሮሚያ ክልልን ወደ ማስተዳደሩ ስልጣን የመጡት ኦሮሚያው ህዝባዊ አመፅ በተቀጣጠለበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ሰውየው በኦሮሚያ ፀጥታ እና ደህንነት ቢሮ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰው ነበሩ፡፡ይህ የስራ ልምዳቸው የሃገሪቱን ወታደራዊ እና ደህንነት ዕዞችን በነሲብ ከተቆጣጠሩት የህወሃት ሰዎች ጋር ቅርርብም እንደሚፈጥርላቸው እሙን ነው፡፡ የሃገሪቱ ፖለቲካ በአያሌው በሚዘወርበት የፀጥታ እና ደህንነት መስሪያቤት በክልላቸው እንዲሰሩ መስኩን በሚዘውሩት ህወሃቶች ይሁን የተባሉት ኦቦ ለማ ለዋናዎቹ ሰዎች የአዘቦት ሰው ስላልሆኑ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ሰውየው በዚህ መስሪያቤት መስራታቸው ከህወሃት ሰዎች ጋር ቅርርብ ብቻ ሳይሆን ታማኝነትንም እንዳገኙበት በቀውጢ ሰዓት ለኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት መሰየማቸው ምስክር ነው፡፡ የለማ መገርሳን ያህል ንግግር ማሳመር የሚቀራቸውን ኦቦ ሙክታር የስልጣን ጊዜያቸውን እንኳን ሳይጨርሱ ከወንበራቸው ያስነሳቸው በክልላቸው ፈልቶ ይንተከተክ የያዘውን ህዝባዊ ማዕበል ፈር በማስያዙ በኩል የጌቶችን እጅ ከመሆን አንፃር የሚቀራቸው ነገር ስለነበረ ነው፡፡ አቶ ሙክታር የኦሮሚያው አመፅ በተነሳ ሰሞን በቴሌቭዥን ብቅ ብለው ሲናገሩ ድንጋጤያቸውን እንኳን ከፊታቸው መደበቅ የማይችሉ ተፈጥሯዊ ቢጤ ነበሩ፡፡በአንፃሩ በደህንነት መስሪያቤት ቆይታቸው ከተፎነታቸው በቅርብ የተጠናው፣በአፈ ጮማነታቸውም የማይታሙት፣ማንን እንዴት አድርገው ፀጥ ማድረግ እንዳለባቸው ከቀድሞው መስሪያቤታቸው ዘዋሪዎች እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩት አቶ ለማ መገርሳ አሁን ኦሮሚያ ያለችበትን ሁኔታ ለራሳቸውም ለበላይ አሳዳሪዎቻቸውም በሚስማማ መልኩ በመለወጡ ረገድ የተሳካላቸው እንደሚሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛው ቦታ በትክክለኛው ሰዓት ለትክክለኛው ሰው ተሰጠ፡፡

ለዘመናት የተጠራቀመው ህዝባዊ ቅሬታ፣ብሶት ያገነፈለው የኦሮሚያ ህዝባዊ አመፅ ኦቦ ለማን ወደ ስልጣን አመጣ እንጅ አሁን እንደሚባው የኦቦ ለማ አልገዛም ባይነት የኦሮሚያን ህዝባዊ ትግልም ሆነ የጨፌ ኦሮሚያ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ካድሬን የጠያቂነት መንፈስ አልፈጠረም፡፡የኦቦ ለማ ወደ ኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት መምጣት በኦሮሚያ የተነሳውን አመፅ ለማርገብ ታስቦ በጌቶች ፈቃድ የተደረገ እንጅ ብዙዎቻችን እንደምናስበው የለማ መገርሳ መምጣት የጨፌ ኦሮሚያን መነቃቃት የፈጠረ፣ ኦሮሚያ ቄሮዎችን ጉልበት ያበረታ እና የህወሃትን እድሜ ለማሳጠር የመጣ ሁነት አይመስለኝም፡፡ በጨፌ ኦሮሚያ የሚገኙ መካከለኛ እና ዝቅተኛ አመራሮች ‘እስከመቼ ታዛዥ ሆነን እንኖራለን?’ የሚለው ጥያቄም ቢሆን ለማ ያመጣው ሳይሆን ከድሮም የነበረ እንደውም ለማ በኢኮኖሚ አብዮት እና ፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል ስም ያቀዘቅዘው ዘንድ ከበላዮቹ የተላከበት የቤት ስራው ነው፡፡ እዚህ ላይ ያቀዳደምነው ፈረስ እና ጋሪ መሰለኝ አሁን በእውር ድንብሩ እየነዳ ለማ መገርሳን መሲህ አድርጎ እያስቆጠረን ያለው፡፡ ሲጠቃለል ለማ መገርሳ ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ከህወሃት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አይደለም፡፡ አቶ ሙክታር የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ፣ ለዛውም በዛ ቀውጢ ሰዓት ኦሮሚያን የማስተዳደሩን በትር የሚጨብጥ ሰው ያለ ህወሃት እውቅና በራሱ እና በካቢኔዎቹ ጉብዝና ወይም በጨፌ ኦሮሚያ ምርጫ ወደ ስልጣን መጥቶ የህወሃትን የበላይነት ግንብ አፈራርሶ፣ የአማራን እና የኦሮሞን “የጠብ ግርግዳ” ሊንድ ባህርዳር ተገኘ ብሎ ጮቤ መርገጥ በአምባገነን ወጥመድ ሰተት ብሎ ገብቶ መጨረሻን ከማክፋት ያለፈ ትርፍ የለውም፡፡

ለለማ ምስጋና ለማምጣት የቸኮለው አብዛኛው ሰው የሚረዳው የለማ ወደስልጣን መምጣት ኦህዴድን እምቢተኛ እንዳደረገው ሲሆን ለዚህ እንደ ሁነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ደግሞ ለማ መገርሳ እና ካቢኔው እንደ አባዱላ እና ኩማ ደመቅሳ የህወሃት የጫካ ምርኮኞች ሆነው የህወሃትን የጫካ ዳቦ አለማነጎታቸው ነው፡፡ምርኮኛ ሆኖ የህወሃትን የጫካ መኖ አለማላቆጥ ብቻውን ዳቦ ካነጎቱት ያነሰ ሎሌ እንደ ማያደርግ ለማሳየት በነአስቴር ማሞ፣ ሙክታር ከድር፣ ሙፈሪያት ፣አለማየሁ አቶምሳ(ነፍስ ይማር)፣አለማየሁ ተገኑን፣አለምነው መኮንንን፣በነዶ/ር ይናገር ደሴን፣ የነ አብዲ ኢሌን ከሁሉ በላይ ደግሞ በነ ሃ/ማርያም ደሳለኝን ታማኝነት ላይ ምርኮኛ ባለመሆናቸው ሳቢያ የመጣ እንከን ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ምርኮኛ ሆኖ ዳቦ ባለማነጎቱ ረገድ ደግሞ በለማ መገርሳ እና በቀደምታቸው በአቶ ሙክታር ከድር መሃከል ልዩነት ስለሌለ ለማ ምርኮኛ ባለመሆናቸው ምክንያት አሳዩት የተባለው የአልገዛም ባይ “አነርነት” በአቶ ሙክታት ላይም መታየት ነበረበት፡፡

ይህን የተውሸለሸለ ክርክር ያመጣው የህወሃት ምርኮኛ የመሆኑ ትክክለኛው ቦታ የት የት እንደሆነ መሳት ይመስለኛል፡፡ህወሃት ታማኝ ሎሎዎችን የሚማርክበት ቦታ ያኔ ድሮ ከደርግ ጋር የተዋጋበት ጦር ሜዳ ብቻ አይደለም፡፡ለምሳሌ የኦህዴድን ካድሬ “የአማራን ጭራቅነት” እንደላሜ ቦራ ተረት በመተረክ፣ ቀጥሎም ከባለጠግነቱ ትቂት በመቆንጠር፣መንትፎ የሰራውን ፎቅ አይቶ እንዳላየ በማለፍ፣በአዲስ አበባ ዙሪያ መሬቶችን ላይ አቁሞ አቤት ወዴት እስካልክ ድረስ እግርህ የረገጠውን ሁሉ ውረስ በማለት ነው፡፡ የህን ያለው ህወሃት ደግሞ “ከአማራ ጭቆናም” ከድህነትም ነፃ አውጭ ጌታ እንደሆነ ተስማምተው መግዛት መንዳቱን እንደተዋረዳቸው ሲቀጥሉ ኖረዋል፡፡

ስብሃት ለለማ መገርሳ የሚያስብለው ሌላው ጉዳይ ሰውየው ገና ወንበሩ ላይ ከመቀመጡ ቀን ጀምሮ ሳያሰልስ የሚዘርፈው “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት” ሚለው ቅኔ ይመስለኛል፡፡የኢኮኖሚ አብዮቱን ስር መሠረት ለማጤን ትኩረት መደረግ ያለበት ቅኔውን “ተቀበል” እየተባለ በሚሞዝቀው ለማ ላይ ሳይሆን የኢኮኖሚ አብዮቱ ሙዚቃ ራሱ በማን? ለምን? እንዴት? እና መቼ? መጣ ሚለውን በመመርመሩ ላይ ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የኦሮሚያው እና የአማራ ክልሉ ህዝባዊ ቁጣ ከሚገለጡባቸው መንገዶች አንዱ የኢፈርት ንብረቶች የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን በማቃጠል እና በማጥቃት ነበር፡፡ ከዚህ ህወሃት የተረዳው ነገር ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በማይዛመድ መልኩ ያመጣውን የኢኮኖሚ የበላይነት ህዝቡ እንዳልወደደው፣ይህ ደግሞ ኢኮኖሚው ረገድ የኢፈርትን የንግድ ዝውውር የመጉዳት መጥፎ ዝንባሌ እንዳለው፤ በፖለቲካው ረገድ ደግሞ የህወሃት የበላይነት አንድ ማሳያ መሆኑን ህዝቡ መረዳቱ አለመረጋጋቱን በማባባስ በኩል አደገኛ ውጤት እንደሚኖረው ተገንዝቧል፡፡ ለወትሮው ኢፈርትን ከዲንሾ እና ጥረት ጋር በማመሳሰል ሲቀለድ የነበረው ቀልድ እንደማያዋጣ በመረዳት ሌላ ‘የኢፈርት መሳ’ የሚመስል ማደናገሪያ በኦሮሚያ መታየት እንዳለበት ታስቧል፡፡ ለዚህ ማስረጃው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት በተባለው እቅድ ውስጥ በአመፁ ሰዓት የድንጋይ በረዶ ሲወርድበት ነበረውን ሰላም ባስን የመሰለ “ኦዳ ትራንስፖርት” የሚባል እንደሚመጣ ሲወራ መባጀቱ ነው፡፡ ሰላም ባስ እንዲደበደብ ያደረገው ተመሳሳዩ የኦህዴድ ንብረት በኦሮሚያ አለመታየቱ ብቻ የመሰላቸው ነገስታት እውን ኦሮሚያን በኢኮኖሚ አብዮት ለማንደድ አምሯቸው ሳይሆን ሰላም ባስ እንደወትሮው እንደልብ ሽር እንዲል፤ሁለትም የለማን ኦህዴድ ከቀደምቶቹ ኦህዴድ የተለየ ለማስመሰል “ለእናንተም እነሆ” እንደማለት ያለ ነገር ነው፡፡ ከነ አቶ አባዱላ ገመዳ የመታዘዝ ማንነት ጋር የተፈተለው የዲንሾ ኩባንያን ነገር ከእነሱው ጋር ገፋ አድርጎ አዲስ ከሚመስሉት አቶ ለማ መገርሳ ጋር አዲስ የኢኮኖሚ አብዮት ሙዚቃን መሞዘቁም ለተአማኒነቱ ይረዳል፡፡የሆነ ሆኖ አቶ ለማ መገርሳም ከ1984 ጀምሮ በኦህዴድ/ኢህአዴግ ቤት ያሉ እና የነበሩ፣የኢኮኖሚ አብዮቱ ሽንገላም የኖረው የማደንዘዣ መውጋት ፖለቲካ ቅጥያ እንጅ በአሮጌው ኢህአዴግ ቤት የተፈጠሩ አዲስ ነገሮች አይደሉም፡፡

የባላጋራን መልክ አለማወቅ…

ኢህዴግ ባላጋራዎቹ ምን ቢበዙ ማንነታቸውን አበጥሮ በማወቅ አይታማም፡፡ በአንፃሩ ኢህአዴግን እንቃወማለን የሚለው ወገን የኢህአዴግን ማንነት በማወቅ በኩል የተካነ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግን ፖለቲካዊ “ማንዋል” በማወቅ የማመሰግነው ኤርሚያስ ለገሰ ሳይቀር ‘ኮካ እና ፋንታ መለየት ያስተማርኳቸው ህወሃቶች ለማ መገርሳን ሃገር እያዞሩ ኢትዮጵያዊነትን በማሰበክ ጊዜ ለማግዛት እስከማሰብ ድረስ በሚደርስ ሴረኝነት መጠርጠር የለባቸውም’ ሲል ገራሞች አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡የሚገርመው ነገር ግን ከዚህ በስንት እጥፍ በበለጠ ኦኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሴራ ኢፈርትን የሚያክል ግዙፍ ድርጅት እንዳቆሙ እሱው ራሱ ፅፎ ያስነበበን መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያለው የኢህአዴግን የቤታቤት ደንብ አለመረዳት ነው በሚገርም ሁኔታ በአቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድ በኩል የህወሃትን ፍፃሜ እያስናፈቀን ያለው፡፡ ይህ አካሄድ ከምክንያታዊነቱ ስሜታዊነቱ በልጦ ይሰማኛል፡፡ ሆኖም በዚህ በኩል የህወሃትን የበላይነት ማብቃት ሚጠብቁ አካላት ሚያቀርቧቸው ምክንያቶችን ማየቱ አይከፋም፡፡

የነዚህ ተከራካሪዎች የንግግር መነሻ ትናንት ዛሬ አይደለም፣ ህወሃትን አጀግነን ማየታችንን እናቁም የሚሉ ናቸው፡፡ እንዲህ ከማለት ባለፈ ግን ትናንት ዛሬ እንዳልሆነም ሆነ ህወሃትን አጀግነን ማየታችንን የምናቆምበት ተጨባጭ ምክንያት ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ መለስ ዜናዊን የመሰለ የተሟላ አምባገነን ያጣው ህወሃት መዳከሙ እርግጥ ነው፡፡ ይህ መዳከም መዳከም የሚባው ህወሃት ከራሱ የቀደመ ብርታት ጋር ሲነፃፀር እንጅ ከኦህዴድ ወይ ከበአዴን ጋር ሲነፃፀር አይደለም፡፡ ንፅፅሩ በህወሃት እና በአባል ድርጅቶቹ መሃል ከሆነ የሚያስገምተው ሊያነፃፅር ያሰበውን ሰው ግንዛቤ ነው፡፡የህወሃት ድካም በሚባለው ጉዳይ ላይ ራሱ መረሳት የሌለበት ጉዳይ መለስ ዜናዊ በሚቀያይረው መልኩ የፖለቲካ ማርሹን የሚያሳልጥ አፈ-ጮሌ በመጥፋቱ በፖለቲካዊ መዋቅሩ በኩል አለመናበብ እና ተወሰነ የፕሮፖጋንዳ/የህዝብ ግንኙነት መፋለሶች ታዩ እንጅ የሃገራችንን ፖለቲካ ለመዘወር እጅግ አስፈላጊ የሆነው ወታደራዊ እና የደህንነት እዙ ከነሙሉ ትጥቁ ዛሬም በህወሃት እጁ ላይ ይገኛል፡፡ ህወሃት ለወትሮው ውልፊት የሚል ሎሌውንም ሆነ በግልፅ የሚቃወመውን አሳቢ ፀጥ የሚያስብለው እንደልቡ በሚያዘው አፈሙዙ፣ በእስርቤቱ፣ በደህንነት መስሪያቤቱን እና በፍርድቤቱ ነው፡፡ ኢህዴግ መዳከም እውን የሚሆነው ቢያንስ ከእነዚህ አንዱን አጥቶ ሲታይ ነው፡፡ ዛሬ ድንገት አነር ሆነ የሚባለው ለማ መገርሳ እውን ህወሃትን የበላይነት ተገዳድሮ ከሆነ፣ከክልል ክልል ሽር የሚለው ነገርም ከጌቶች ፈቃድ ውጭ ቢሆን ኖሮ እነዚህን ተጠቅሞ እሱን እና ካቢኔውን ፀጥ ለማድረግ በህወሃት መንገድ ላይ የሚቆመው ማን ነው?

ጎዳና ላይ እየወጣ ለራሱ ብሶት የሚጮኽው የኦሮሞ ህዝብ ህወሃት ለማን ቢያስር ዝም ስለማይለው ይህን ፈርቶ እጁን ይሰበስባል፣አለያም አሁን ያለው የጨፌ ኦሮሚያ አባል ለማ መገርሳ አንዳች ቢሆን ዝም አይልም የሚል ተከራካሪ አይጠፋም፡፡ ለዚህ ቀላሉ መልስ የኦሮሞ ህዝብ ጩኽቱ የአፈሙዝ ባለቤቶችን ፈቃድ የሚያስቀይር ቢሆን ከሰውነት ደረጃ ወጥተው እንደ ወንበዴ እጃቸውን በካቴና ታስረው ለታዩት ዶ/ር መረራ የሚኽው ጩኽት ይበረታ ነበር፡፡ ግን በሃገራችን ምድር የህግ ፍፃሜ የሚሆነው ባለጠመንጃው ያለው ነገር ነውና ባለጉልበት ያለው ብቻ ይሆናል፡፡ በተሻለ ሁኔታ ጥርስ እያወጣ እንደሆነ ሲነገርለት ዘመናት የተቆጠሩት የጨፌ ኦሮሚያ መካከለኘኛው እና ዝቅተኛው ካድሬም ቢሆን ከሰሞኑ ባደረገው ስብሰባ ከዚህ በላይ መፈራገጥ በህወሃት ጎራዴ መቀንጠስን እንደሚያመጣ አምኖ በነገስታት ፈቃድ ለማደር መለሳለስ ማሳቱን ዋዜማ ሬዲዮ የውስጥ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡

ህወሃት እንደመለስ ያለ አምባገነንነቱ በሙሉድምፅ የተረጋገጠ መሪ ለማግኘት የተቸገረ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም ፓርቲው ተያይዞ አለመቆም ተያይዞ መሞትን እንደሚያመጣ አሳምረው የሚያውቁት የወንዝ ልጆች ድርና ማግ ሆነው የሰሩ መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ “ተዓምረኛው” ለማ መገርሳ ይህንንም ገርስሷል ካልተባለ በቀር! ስለዚህ ህወሃቶች ምን በሃሳብ ቢለያዩ በስንጥቃታቸው ሶስተኛ ወገን ቀርቶ ነፋስ ማስገባት በተለይ በአሁኑ ሰዓት ይዞት የሚመጣውን መዘዝ የማያውቁ ሰዎች አይደሉም፡፡ ‘ለሁለት ተሰነጠቁ ለሶስት ተተረተሩ’ የሚባለው ወሬ መወራት ከጀመረ የሰነበተ ቢሆንም እነሱ ሁለት ሶስት ጊዜ እየተመላለሱ በራቸውን እየዘጉ ተነጋግረው ሲመለሱ ለተመለካች ያው የድሮዎቹ ናቸው፡፡ በተግባርም ቢሆን የሚያነታርካቸው ነገር ‘በየት ዞረን፣በትኛውን የተሻለ ሎሌ ላይ እምነት ጥለን፣በአፉ ተናግረን የበላይነታችንን ዘላለማዊ እናድርግ’ የሚለው ጉዳይ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ጉልበቱን የሚያውቀው ሎሌም ከዚህ ለተለየ ነገር እንደማይፈለግ ያውቀዋል፡፡ ለሎሌ ደግሞ የነገስታትን መንበር ከማፅናት የበለጠ ጉብዝና የለም! በተለይ በኢህአዴግ ቤት ሎሌ የሚለካው በአስቸጋሪ ጊዜ አይኑን በጨው አጥቦ በመቀላመድ ነው፡፡

ሁልጊዜ ህወሃትን አጀግነን አንይ አዳንድቀን ለማን የመሰሉ ሎሌዎችም ሊጀግኑ ይችላሉ የሚሉ ተከራካሪዎች ስሜታዊነታቸው በዝቶ ይሰማኛል፡፡ ህወሃትን ማጀገን የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን ህወሃት ራሱ ያበጃጀው የሃገራችን ፖለቲካ ተፈጥሮ በጠመንጃ የሚያስገድደን ምርጫ አልቦ ነገር ነው፡፡ ብጣብልጡ ህወሃት ራሱ ባበጃጀው ቤት፣መሳሪያውን በእጁ እንደታቀፈ ይሸነፋል ማለት ዘበት ነው፡፡ ህወሃትን ማጀገን እንደሌለብን የሚናገሩ ተከራካሪዎች እነሱ የሚያጀግኗቸውን እነ ለማ መገርሳን ደርሰን ነብር አድርገን እንድናይ የሚያደርግ ተጨባጭ ነገር አያሳዩንም፡፡ ዝምብሎ ኢህአዴግን ማጀኑ መቅረት አለበት ማለት ቂልነቱ ይበዛል፡፡መሳሪያ ብቻ በሚገዛበት ሃገር ባዶ እጆቹን እያወዛወዘ ከክልል ክልል የሚማስነው ለማ መገርሳ ለህወሃት አስቸግሮ፣ከቢጤው ግራ-ገብ ብአዴን ጋር ገጥሞ ህወሃት የነፈገንን ነፃነት የሚያመጣልን በዱኣ ይሁን በወዳጃ ግልፅ አይደለም! ጭራሽ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ባህር ዳር ላይ ተገናኝተው የኢፈርቱን ፋና ስፒከር ደቅነነው የሚያወሩት ወሬ ህወሃትን በአፍጢሙ ለመድፋት እንደሆነ እየታሰበ ነው፡፡ ህወሃት ምን ቢዳከም ኦህዴድ እና ብአዴን ያለ እሱ ፈቃድ ባህር ዳር ላይ ተገናኝተው እሱ ቀድሞ በአእምሮው ፅፎ በአፋቸው ከሚያናግራቸው አጀንዳ ውጭ ያወራሉ ማለት ሶስቱንም ፓርቲዎች አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ሃገርንም አለማወቅ ነው፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ስህተቴን የማርም ፓርቲ መሆኔ ነው ይህን ያህል ያኖረኝ ባይ ነው፡፡ ህወሃት እንደሚለው የሚማር ሳይሆን የተማረ የሚያስመስል ፓርቲ ነው፡፡ ከ1997 ምርጫ ወዲህ ህዝብ ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ እንደሚፈልግ በተግባር ስላሳየው ቀድሞ ፓርቲው ሲያራምደው የኖረው በዘር ሸንሽኖ የመግዛት ዘይቤው እንደማያስኬደው አውቆ ባንዲራን ጨምሮ ሲያናንቃቸው የነበሩትን የኢትዮጵያዊነት ምልክቶችን ቀን ቆርጦ ሳይቀር መዘከር ጀመረ፡፡ለኢትዮጵያዊነት ዘብ መቆሜን ያሳዩልኛል ያለውን ነገር ሁሉ ማድረግ ያዘ፣ተጓዥ የብሄረሰቦች ቀን በአል ማክበሩን ተያያዘው፡፡ በአንድ በኩል እንዲህ ደርሶ የኢትዮጵዊነት ዘበኛ ነኝ እያለ በሌላ ወገን ኢትዮጵያ ሃገራችን ናት ብለው ከትውልድ መንደራቸው ርቀው በጉራፈርዳ የሰፈሩ አማሮችን ጓዛቸውን እንኳን እስኪያዙ ሳይጠብቅ ባዶ እጃቸውን ያፈናቅል ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ ሲባል ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር “ሰዎቹ እኮ ጉራፈርዳን ምዕራብ ጎጃም አስመሰሉት” ነበር መልሳቸው፡፡ በቅርቡ ደግሞ ኦሮሞዎች ዘመናት ከኖሩበት ኢትዮ-ሶማሌ ክልል እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ለማ መገርሳ አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ‘ኦሮሚያ ለስንትስ ሚሊዮን ህዝብ የምትበቃ ስለሆነች ማንንም የማፈናቀልም ስልጣንም ሆነ ፍላጎት የለንም’ እያሉ በሚደሰኩሩበት ወቅት አማሮች በኤሊባቡር በጎራዴ ይቀሉ፣በቆንጨራ ይፈለጡ ፤የኢትዮጵያ ሶማሌዎች በአወዳይ ከተማ በጥይት ይረፈረፉ ነበር፡፡እንዲህም ሆኖ እሳቸውም ሆኑ ጓዶቻቸው ስለኢትዮጵያዊነት መደስኮራቸውን አላቆሙም፤ወሬ ብቻ የሚያጠግበው፣አፍብቻ የሚበቃው ተላላ አድማጭም አላጡም፡፡

ባልተለመደ ሁኔታ ከኦህዴድ መሪ ስለኢትዮጵያዊነት ማህሌት መቆሙን ብቻ በቂ አድርጎ በደስታ ከመስከር ምክንያቱንም መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ባለፈው አመት በጎንደር ተደርጎ በነበረው ሰልፍ የጎንደር ህዝብ ለኦሮሞ ህዝብ በደም የተዋሃድኩ ወንድም ነኝ የሚል አንድምታ ያለው መፈክር ሲያሰማ አፀፋውን ከኦሮሞ ህዝብ ማግኘቱን ያወቀው አጀንዳ በመንጠቅ የተካነው ህወሃት/ኢህአዴግ ይህን የህዝብ ዝንባሌ አፈፍ አድርጎ ኦህዴድን እና በበአዴንን ማስተቃቀፍ ይዟል፡፡ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ መወራቱ ብቻ በስሜት ያሰከረው ፖለቲካውን የሚከታተለው ኢትዮጵያዊ ብአዴን እና ኦህዴድ የሰፊው ህዝብ ወኪል የመሆን ርጋፊ ብቃት እንደሌላቸው እንኳን ዘንግቶ የሁለት ካድሬዎችን እና ጄሌዎቻቸውን ሆያ ሆየ የህወሃት እጅ የሌለበት አድርጎ ሲያሟሙቅ ሰነበተ፡፡በተለይ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አክቲቪስቶች እንደመርገም ጨርቅ ሲቀፋቸው የነበረው ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ ሲነገር ማር ማር ያላቸው ለምን እንደሆነ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለወትሮው እኛ ኢትዮጵያዊያን በደም የተሳሰርን አንድ ህዝቦች ነን ሲባሉ በአንድነት ስም የህዝቦችን ማንነት ለመጨፍለቅ የምታስቡ አማሮች ሴራ ነው ሲሉ የነበሩ እነዚህ አክቲስቶች ዛሬ የለማን መዝሙር ተከትለው የሚያሸበሽቡት ለምድን ነው? ይህ ሃሳባቸውስ አብሯቸው ይኖራል ወይ? ብሎ አለመመርመር ቀና አሳቢነት ሳይሆን ፖለቲካዊ የዋህነት ነው፡፡ እነዚህ ስለኢትዮጵያዊ አብሮነት ሲነሳ እንደዛር ሲያስጎራቸው የነበሩ አክቲቪስት ተብየዎች ኢትዮጵያዊነት በለማ መገርሳ አፍ ሲወራ የጣፈጣቸው የለማ ጉዞ ሄዶ ሄዶ በማንኛውም የወንዛቸው ልጅ እንዲያዝ አጥብቀው በሚመኙት ስልጣን ላይ እንደሚያርፍ ስለተገነዘቡ ነው፡፡ ይህን ያመጣው ለለማ ያላቸው ወዳጅነት ሳይሆን ሊገድላቸው የማለው የዘረኝነት ልክፍታቸው ነው፡፡

“ሃገር አረጋጉ”

ኦህዴድ እና ብአዴን ሳያዳግሙ የሚታዘዙ ሎሌዎች ቢሆኑም አያጉረመርሙም ማለት አይደለም፡፡ ሎሌ የጉልበቱ ዋጋ በውል ያልተከፈለው ሲመስለው ጓዳ ለጓዳ ሊያጉረመርም ይችላል፡፡ እንደውም እንደሎሌ አጉረምራሚ የለም፡፡ ኦህዴድም ከነአሽከርነቱ ሊያጉረመርም ይችላል፡፡ማጉረምረም ብቻውን ሎሌነትን የማሽቀንጠር ምልክት አይደለም፡፡ ሎሌ ብዙ አጉረምርሞ ትቂት ይደመጣል፡፡ ኦህዴድ ማጉረምረም ጀመረ የተባለው በአባዱላ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ብአዴንም በአያሌው ጎበዜ ዘመን፡፡ሆኖም ጉርምርምታቸው እምብዛም ያመጣው ነገር አልነበረም፡፡በተለይ መለስ ክንዳቸውን ሳይንተራሱ፣ህወሃትም እንዲህ እንደዛሬው ከብራቅ በበረታ የህዝብ ጩኽት ግራ ሳትጋባ በፊት የሎሌ ጉርምርምታ ያስገርማት ይሆናል እንጅ ነገሬ ብላ ላታዳምጠው ትችላለች፡፡

ዛሬ የህዝብ ጩኽት ግራ ሲያጋባት ግን አጥብቃ የሎሌዎቿን እርዳታ ፈለገች፡፡ የሚያጉረመርም ሎሌን ለወሳኝ ስራ መላክ ደግሞ እንደማያስተማምን በመረዳቷ “ጩኽታችሁ በፊቴ ነው፣ድምፃችሁን ሰምቻለሁ፣ እውነት ነው በቁመናችሁ ልክ ስልጣን ያስፈልጋችኋል፤ ለእሱ ግድ የለም መጀመሪያ ግን ሃገር አረጋጉ” በማለት የቀደመ ተረጋግቶ የመግዛት ዘመንን ለመመለስ አድርጉ የተባላችሁትን ካደረጋችሁ የማደርግላችሁን አታውቁም ስትል ኦህዴዶችን እንዳረጋጋች፣ ኦህዴዶችም በሰሞንኛ ጉባኤያቸው ከዚህ በላይ ጌታን መጋፋት መከተፍን እንደሚያመጣ ተስማምተው ይሄው “ሃገር ለማረጋገት” አባይን ዋኝተው ጣናን አቋርጠው ወደ ሌላው የባሰበት ሎሌ ግዛት ተጉዘው “ሃገር ማረጋጋቱን” ተያይዘወታል፡፡ይህን የዘገበው ወሳኝ መረጃዎችን ከውስጥ አወቆች አነፍንፎ ሳያዛባ በማቅረብ የታወቀው ዋዜማ ሬዲዮ ነው፡፡

ሱሴ ሱሴ…..!

ሃገር የማረጋጋቱን ስራ በአማራ ክልል የተጀመረው አንደኛው ምክንያት ጌታ ለኦህዴድ ያሰባትን መልካሟን ሃሳብ “ለእኔስ” ለማለቱ ብአዴን ቀዳሚ በመሆኑ ለማ ማለት ኢትዮጵያዊነት እንጅ ኦህዴድነት እንዳልሆነ እንዲታመን በኢትዮጵያዊነት ላይ ጨክኖ በማይጨክነው ህዝብ ምድር ሲቃ እየተናነቀው፣ኢትዮጵያዊነት እንደሱስ እንደሚያዛጋው መቀላመድ ነበረበት፡፡ እነ ቀመር ዩሱፍን የመሰሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችን አግተልትሎ ወደ አማራ ክልል የመንጎዱ ሌላው ምክንያት በሰላማዊ ሰልፉ የታየው ትክክለኛው የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ እውነተኛ የመፈላለግ ዝንባሌ ውስጥ ጥልቅ ብሎ ዋነኛ አገናኝ፣ የፍቅር ሰው ለመምሰል ነው፡፡ ነገሩ ህዝብ ሃያ ምናምን አመት የተሰበከለትን የመነጣጠል ዲስኩር፣ የመባላት ግብዣ የዝሆን ጆሮ ሰጥቶ በፍቅር ሲጠራራ እየተሰማ የተለመደውን የማናከስ ሙዚቃ መክፈት እንደማያስኬድ በመረዳት ግድ ያለውድ የሆነ አካሄድ እንጅ ብዙዎቻችን እንደምናስበው የመነነጣጠል ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞችን የኢትዮጵያዊነት ሱስ አብርሮ ባህርዳር ላይ ጥሏቸው አይደለም፡፡ አንድ ነገር ሱስ የሚሆነው ደጋግመው ሲወስዱት ነው፡፡የጥላቻ ፖለቲካን ሲሰብክ እና ሲሰበክ ከኖረው ኦህዴድ፣የልዩነት ፖለቲካን መኖሪያየ ብሎ ከያዘው ግንባር ኢህአዴግ ወግኖ ጥላቻን ሲምግ የኖረ ሰው እንዴት ብሎ ነው ፍቅር የሆነው ኢትዮጵያዊነት ሱሱ የሆነው? የተላከበትን ነገር አሳምሮ ጨርሶ የተዘጋጀለትን አክሊል ለቀበልም ቢሆን ነገሩን ሱስ ደረጃ ማድረስ ራስን ማስገመት ነው፡፡ከአቶ መለስ ጋር ነፍሱ ከስጋው የተለየችውን የአቶ ኃ/ማርያምን ወንበር ለማግኘት ይሄን ያህል መፋተሩ ካድሬ ሆነው ካላዩት ትርጉሙ አይገባም፡፡

ማለባበስ ይቅር

ወደ ኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳደርነት ከመምጣቱ በፊት በክልሉ የደህንነት መስሪያቤት ውስጥ ሲሰራ የነበረው አቶ ለማ መገርሳ አሁን አሁን ሃጢያቱ ሁሉ የቀረለት ንፁህ መሲህ ተደርጎ እተሞካሸ ይገኛል፡፡ ይህ ትርጉም የሚሰጠው የተሰራ ሃጢያት በቅፅበታዊ የልብ መመለስ ወደ ፅድቅ በሚቀየርበት በመንፈሳዊው ዓለም እንጅ በልብ የተያዘውን በአፍ ከሚወራው ጋር ማመሳከር በማይቻልበት በፖለቲካው ዓለም አይደለም፡፡ በበኩሌ ለለማ መገርሳ ደርሰው ከሚያሸበሽቡት ወገን ለመሰለፍ የምቸገርባቸው ብዙ ነባራዊ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ ሰውየው ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣበት ዘመን ጀምሮ አብረው የመጡ ሰው ከመሆናቸው በተጨማሪ በደህንነት መስሪያቤት በመስራታቸው የእስርቤቱን ቋንቋ ኦሮምኛ በማድረጉ ረገድም ሆነ በአጠቃላይ ፖለቲካችንን ብልሹ በማድረጉ ረገድ ተሳትፎ ያላቸው ሰው ስለሆኑ ድረሶ ለእሳቸው ማሸብሸብ ብዙ መርህ መጠረማመስ መስሎ ይታየኛል፡፡ በየእስርቤቱ ለመስማት እንኳን የሚቀፍ ግፍ ለሚሰራ፣ለህዝብ የቆሙ ንፁሃንን ከልጆቻቸው ነጥሎ፣በቶርቼር ገላቸውን ለሚበጣጥስ፣እናትን በልጅ አስከሬን ላይ አስቀምቶ የሚደበድብ ሥርዓት ማገር ሆኖ ሲገለግል የኖረ/እያገለገለ ያለ ሰው፤ ይህ ጥፋት መስሎ ሳይታየው ጭራሽ ለሌላ ስልጣን ጉብ ቂጥ ለሚል ካድሬ ማሸብሸብ መነሻን እና መድረሻን ያለማያውቅ መርህ አልቦነት ነው፡፡ እንዲህ በመርገም ውስጥ ተዘፍቆ ተመችቶት እየኖረ ያለ ሰው ተቀይሮ ደህና ቀን ያመጣልናል ብሎ ጭራ መቁላት የራስን ስራ ተነስቶ ላለመስራት የሚደረግ የሃሞተ ፈሳሶች ከንቱ ዘፈን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖበት ሊገድለው እንደደረሰ ሲያወራ እልል የሚባልለት ለማ መገርሳ “ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች” የሚለውን የክልሉን ህገ-መንግስት አስፈፅማለሁ ብሎ ስልጣን ላይ ቂጥ እንዳለ ለማሰብ ያልቻለ ፖለቲካ አውቃለሁ ባይ ሃገር የት ያደርሳል? ለማ ከተመረጠ ጀምሮ እንዲሁ ስለኢትዮጵያዊነት እየቀላመደ መስሎኝ ሰዎች ‘ኦሮሞ ሳትሆኑ እንዴት ብትጠግቡ ኦሮሚያ ምድር ተገኛችሁ’ ተብለው በቆንጨራ የተፈለጡት፡፡ ይህን ፈጥኖ ደርሶ ያላስቆመ ለማ መገርሳ፣በሚያስተዳድረው ክልል ኦሮሚያ ላይ ነፍስ ማዳን ያልቻለው ለማ መገርሳ በየት ዞሮ ነው ህወሃትን ለማንጓጠጥ የበቃው? ኤሊባቡር ላይ ሌሎች ናችሁ ተብለው በአሰቃቂ ሁኔታ ነፍሳቸው ባለፈው ዜጎች ደም በምንም ሁኔታ ለማ መገርሳ ከተጠያቂነት አይድንም፡፡ የዚህ ሲገርም የአቶ ለማ ካቢኔ አባል አቶ አዲሱ አረጋ ኮራ ብለው የአስከሬን ዘር ማንዘር ትግሬ ወይ አደሬ መሆን የሚፈይደው ነገር ያለ ይመስል ወለጋ ላይ “የሞቱት ሰዎች ዘር ትግሬ አይደለም” እያለ ነገስታትን አለማስቀየሙን ለማጉላት ብቻ ይፋትራል፡፡ ካድሬ ገርሞኝም ስለማያውቅ የምገረመው በአዲሱ ንግግር ሳይሆን ይህንንም እየሰማ የለማን ካቢኔ ልዩ ብፁዕ ለማድረግ በሚቃጣው ፖለቲካ አዋቂ ነኝ ባይ ነው፡፡

ነገሩን ያደረገው መከረኛው ህወሃት ነው ከተባለም ለማ ህወሃትን አንጓጠጠ የተባለውን ተረት ተረት ፉርሽ ያደርገዋል፡፡ሌላው ካድሬ አዲሱ አረጋ እንዳወራው ድርጊቱን የፈፀሙት ያባረሯቸው የኦህዴድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ቢሆኑም ጀግኖ ሊሞት ነው የተባለው የለማ አስተዳደር በብርሃን ፍጥነት ደርሶ የሰዎችን ነፍስ ማዳን ነበረበት፡፡ይብስ የሚገርመው ለማ መገርሳ በውቢቷ ባህርዳር ተገኝቶ ገዥው ፓርቲ የተለከፈበትን የፕሮፖጋንዳ ጥማት ሲያረካ ኦሮሞ በመሆናቸው ብቻ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ተፈናቅለው መከራቸውን የሚያዩ ዜጎች እባካችሁ አንድ በሉን እያሉ የሰሚ ያለህ ይላሉ፡፡ እውነት ለማ እንደሚያወራው እና እንደሚዘመርለት የአንድነት ሰባኪ፣ የኢትዮጵያዊ አብሮነት ሱሰኛ፣ ለህዝብ አሳቢ፣በራሱ እንጅ በጌቶች ሃሳብ የማይነዳ ቢሆን ቀድሞ ማድረግ ያለበት ኢትዮ-ሶማሌ ተጉዞ የህዝቦችን አንድነት ሰብኮ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው ባህርዳር ሄዶ የአዞ እንባ ማንባት? ይሄ ሁሉ እየሆነም ለማ በኢትዮጵያዊነት ሱስ መለከፉን ለሚያምኑት እያወራ ነው፤ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ህዝብም እየተከተለው ነው፡፡ እውነቱን እድሜ የሰጠው የሚያየው ይሆናል! የማይካደው ሃቅ ግን በዚህ የፖለቲካ ድራማ ውስጥ ህወሃት/ኢህአዴግ በለማ መገርሳ በኩል ባህር ማዶ የተቀመጡ የጥላቻ ፖለቲካ በሽተኞችን እንዳያንሰራሩ አድርጋ መምታቷ ነው፡፡ ይህ የጋራ ድላችን ነው!

ጸሀፊዋን በመስከረም አበራን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል:- meskiduye99@gmail.com

በዚህ ድረገጽ የሚወጡ ሃሳቦች የጸሃፊዋን ወይንም የጸሃፊውን ሃሳብ እንጂ የድረ ገጹን አቋም አያንጸባርቅም ። በዚህ ድረ ገጽ መልስ ፤ መጣጥፍ ወይንም አስተያየት ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ኢሜይል ያድርጉልን። editor@borkena.com
———

ወይ አዲስ አበባ…! – ክፍል ፪ (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

በመስከረም አበራ
ጥቅምት 7 ፤ 2010 ዓ ም

Meskerem Abera - article -Addis Ababa
Meskerem Abera

የሃገራችን ፓርላማ የ2009 ሥራ ዘመኑን ሊያጠናቅቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ስለሚገባው ህገ-መንግስታዊ የልዩ ጥቅም ድንጋጌ ማስፈፀሚያ የሚሆን ዝርዝር አዋጅ እንዲያፀድቅ ቀርቦለት ነበር፡፡ ፓርላማውም አዋጁን ተመልክቶ ለከተማና ቤቶች እና የህግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴዎች መርቶ እረፍቱን አድርጓል፡፡ የአዋጁ ሁለመና ብዙ አነጋጋሪ ጉዳዮችን ይዞ ብቅ ያለ ነው፡፡ተደርጎ በማያውቅ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክርቤት ብቻ የመከረበት፣በፓርላማ ያልፀደቀ ረቂቅ አዋጅ በሃገሪቱ ቴሌቪዥን እንዲነበብ መደረጉ አንዱ አደናጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ፓርላማው ሊያርፍ እየተንደረደረ ባለባቸው የመጨረሻ ቀናት አዋጁን እንዲያይ ማድረጉም ሌላው ግርታ ነው፡፡ የልዩ ጥቅም ድንጋጌው በህገመንግስት ከተቀመጠ ሩብ ምዕተ-አመት ያለፈው ሲሆን ዛሬ ብድግ ብሎ ዝርዝር የአፈፃፀም ህግ ለማውጣት እንዲህ ባለቀ ጊዜ የሚያባክነው ጉዳይም የማያነጋግር አይደለም፡፡

በፓርላማ ያልፀደቀን ዝርዝር ረቂቅ ህግ በቴሌቭዥን ማስነበቡ በተለይ መንግስት በጉዳዩ ላይ በሚያገኘው የፖለቲካ ትርፍ/ኪሳራ ላይ ምን ያህል ትኩረት እንዳረገ ያሳብቃል፡፡ከዕሩብ ምዕተ ዓመት በኋላ ‘ልተገብረው ስለሆነ ዝርዝር የአሰራር ህግ ይውጣለት’ ሲል ለዕረፍት ሊወጣ ጥቂት ቀናት ብቻ ለቀሩት ፓርላማ አቤት ያለው ኢህአዴግ ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ የትግበራ ፍላጎት አድሮበት አይደለም፡፡ ይልቅስ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ንትርክ ተደርጎ ሁልጊዜ ወጥመዱ የማይስታቸውን የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞችን የጎሰኝነት አክራሪ ማንነት አደባባይ አውጥቶ እሱ(ህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት) እንዴት “የተሻለ” አብሮ የመኖር መንገድ እንዳለው ለማሳየት ነው፡፡ ይህ በደንብ ተሳክቶለታል፡፡

በህገ-መንግስቱ ኦሮሚያ የተሰጣት አስዳደራዊ ጉዳዮችን ያማከለ የልዩ ጥቅም መብት ሆኖ ሳለ ‘ኦሮሚያ የሚገባት የአዲስ አበባ ባለቤትነት ነው፤ ከኦሮሞ በቀር ሁሉም እንግዳ ነውና ለባለቤቱ የኦሮሚያ ክልል የመሬት ግብር እየከፈለ፣ፀባዩን አሳምሮ፣የከተማው አስተዳደርም እንደ ማንኛውም የኦሮሚያ ከተማ ተጠሪነቱን ለኦሮሚያ ክልል አድርጎ መኖር አለበት፤አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሞያሌም፣ድሬዳዋም፣ ሐረርም የኦሮሚያ ንብረት መሆን አለባቸው’ ወዘተ የሚል ሃሳብ ይዘው እየተሽቀዳደሙ የሚያውጁ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞችን ያገኘው ኢህአዴግ ‘እሰይ ስለቴ ሰመረ!’ ማለቱ ይቀራል? ፖለቲካዊ ትርፉን በሆዱ የያዘው ኢህአዴግ ህገ-መንግስታዊ ዝርዝር ህጎቹን እንዲያወጣ ያስፈለገው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ እንዲኖራት የተቀመጠው ህገመንግስታዊው የልዩጥቅም ድንጋጌን ለማስፈፀም ያለው አምሮት እንደሆነ ነው በአደባባይ የሚያወራው፡፡ ሆኖም ህገመንግስቱ ራሱ ይህን የልዩ ጥቅም ድንጋጌ እንዲያስቀምጥ የሚያደርግ ከፕሮፖጋንዳ እና ከወቅቱ የተበድየ ሙሾ ባለፈ በቂ እና ተጨባጭ ነባራዊ ሃቅ ነበረው ወይ የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

የልዩ ጥቅሙ ህገመንግስታዊ ድንጋጌ መሰረቱ ምንድን ነው?

በህወሃት/ኢህአዴግ የጠመንጃ ድል ተጠልሎ የአድራጊ ፈጣሪነቱን ቦታ የያዘው የተበድየ ፖለቲካ ታሪክ ያልፃፈውን እያነበበ የሰራው ስህተት የእርምቱን መንገድ ሩቅ አድርጎታል፡፡ የአፄ ዮሃንስ ዘውድ “ተነጥቆ” ሸዋ መግባቱ ሆድ ሆዱን የበላው የትግራይ የተወልጄ ፋኖዎች ቡድን ደደቢት ሲገባ የአባት አያት ዘውድ የመነጠቁን ዘውጋዊ ቅንዓት ሃሰት በሆነው የትግራይ ተበዳይነት የአማራ በዳይነት ሙዚቃ ቀየረው፡፡ የሚያብሰለሰወለውን ዘውድ የመነጠቅ እና የመበለጥ ቁጭት በፈረደበት የአማራ ብሄር ጨቋኝነት እና በዳይነት ልቦለድ አዳፍኖ አዲስ አበባ ሲደርስ በለስ ያልቀናውን የሁልዜ የበደል ፖለቲካ አላዛኝ ቢጤውን (ኦነግን) ጠርቶ፣ የበረሃ ጓዱን/አለቃውን (ሻዕብያን) አክሎ እንደምርኮ ምድር ተንበርክካ ያገኛትን ሃገር በጎሰኝት ቢለዋ ዘነጣጥሎ፣ የብሄረሰቦች የስጋ መደብ አስመሰላት፡፡

በ“ባልንጀራው” ህወሃት ድል አጥብቆ የተማመነው ኦነግ የኢትዮጵያን የብሄር ብልት በማውጣቱ ቀዳሚው ተሰላፊ ነበር፡፡የኦነግን እድሜ አጭርነት ቀድሞ የሚያውቀው፣ ያሰበውን ለማሳካት ደግሞ ማጎንበስን በደንብ የተካነው ህወሃትም የኦነግን ያለቅጥ ፈንጠዝያ ባላወቀ ማለፍን መረጠ፡፡ ህወሃት ስምንቱን አኑሮ አንዱን እንደሚያጫውተው የማያውቀው ኦነግ ያልተፃፈ እያነበበ የማይዘለቅ ማህበሩን በጠጅ ጀመረ፡፡ በውል የተመዘገበ ታሪክ ከሚያስረዳው በተቃራኒ “በሸዋ ነገስታት መስፋፋት የእኛ ህዝብ መብት ተገፏል፣ስለዚህ መብታችን ይመለስ ቢያንስ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ረገድ ኦሮሞ በፊንፊኔ ላይ መብቱ ይጠበቅ እንዲሁም ሃረርም በኦሮሚያ መካከል ስለሆነች በተመሳሳይ የኦሮሞ መብት ይጠበቅ” የሚል ጥያቄ ኦነግ አንስቶ እንደ ነበር የወቅቱ ዝብርቅርቆሽ ፊታውራሪ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሐምሌ 8/2009 ዓ.ም ለወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሲደጋገም እውነት የመሰለ፣ የታሪክን ጉማጅ ይዞ የሚያላዝነውን፣ የኦነግ የተበድየ ተረክ መናነት ባለፈው ዕትም ላይ ለማሳየት ስለሞከርኩ አሁን ወደዛ ጥልቅ ታሪካዊ ጉዳይ መግባት አልፈልግ፡፡ ሆኖም በኋላ የመጣውን እና ከፊተኞቹ የኦሮሞ ተስፋፊዎች አንፃር እዚህ ግባ የማይባለውን የሸዋ ነገስታት ተስፋፊነት በዓለም ላይ ተደርጎ እንደማያውቅ ትልቅ በደል ጠቅሶ፣በማይሆን ሁኔታ አዲስ አበባን በካሳነት ለመቀበል የመከጄሉ ሙከራ የስህተቱ ሁሉ መሰረት ስለሆነ ሳያነሱ ማለፍ አይቻልም፡፡ሲጠቃለል አሁን በስራ ላይ ባለው የሃገራችን ህገመንግስት የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው ስለሚገባው ልዩ ጥቅም የተደነገገው አንቀፅ መሰረት ያደረገው የኦነግን የተበድ ፖለቲካዊ ስነልቦና ሲሆን ይህ እንዲሆን የፈቀደው ደግሞ ህወሃት ከኦነግ በፖለቲካው ሰፌድ መቆየት ማትረፍ የፈለገውን ትርፍ ይሰበስብ ዘንድ ነው፤ እንጅ ነገሩ እንደሚባለው ታሪካዊ መሰረት ኖሮት አይደለም፡፡

በሽግግሩ ወቅት አዲስ አበባ በልዩ ሁኔታ የኦሮሞዎች ልዩ ጥቅም የሚጠበቅባት ምድር እንድትሆን የሚያደርግ በህገ-መንግስታዊ አንቀፅ ይካተትልኝ ሲል የነበረው ኦነግ ታሪካዊ ልቦለድ ለመሆን እንኳን አቅም የሌለው የበደል ድርሰት ጠቅሶነው፡፡ የደገሰውን በደንብ የሚያውቀው ህወሃት ኦነግ የተፈለገበትን የቤት ስራ እስኪከውንለት ድረስ የልደቱን ቀን እንደሚያከብር ህፃን የፈለገውን እንዲሆን የፈቀደለት ወቅት ነበረ፡፡ በመሆኑም ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ የሚያደርገው የኦነግ ተረክ የመጨረሻ እውነት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ በወቅቱ ኦነግ ሰፋ አድርጎ ሃረርንም ቢጠይቅም ያልፈለገውን የማያየው ህወሃት የሃረሯን ጥያቄ ችላ ብሎ ኦነግ ከተባረረ በኋላም የአዲስ አበባውን የልዩ ጥቅም ጉዳይ ብቻ በህገመንግስት አፀና፡፡ የሃረሩ ጉዳይ ተድበስብሶ የቀረበትን ምክንያት “አላውቅም” ይላሉ ‘ህገመንግስቱን ለማርቀቅ ከሄዱት ሁለት የኢህአዴግ ሰዎች አንዱ ነበርኩ፣ ህወሃትም ማንንም ሳይወክል እኔን እና ዳዊት ዮሐንስን የኢህአዴግ ወኪል ሆንን’ የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ቃለምልልሳቸው፡፡

በጋዜጣው ላይ ከዶ/ር ነጋሶ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ጋዜጠኛ “በአዲስ አበባ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ላይ የተለየ አቋም አልነበረም?” ሲል ጥሩ ጥያቄ አስከተለ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በወቅቱ “ንጉስ የወደደው” ኦነግ የፈለገውን መቃወም አዳጋች እንደ ነበረ በገደምዳሜ በሚያስረዳ መልኩ ይህን ይላሉ “በአርቃቂ ኮሚሽኑ በኩልችግር አልነበረም፤ሁሉም የተቀበለው ጉዳይ ነበር፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ በወጣው አዋጅ ላይ ስለነበረና የኦሮሞ ድርጅቶች ዋነኛ ጥያቄም ስለነበረ መከራከሪያ አልቀረበም ነበር”፡፡ የኦሮሞ ድርጅቶች የተባሉት ከአንጋፋው ኦነግ በተጨማሪ የእስላማዊ ኦሮሞ ነፃነት ግንባር እና በአርሲ፣ ባሌ እና ሐረር አካባቢ ይንቀሳቀስ የነበረ “ቶክቹማ” የሚባል ድርጅት እንደሆነ ዶ/ር ነጋሶ በዚሁ ቃለምልልስ ያብራራሉ፡፡

ከዚህ መልስ የምንረዳው ትልቅ ነገር እንደ ፍፁም ህግ ተደርጎ አስር ጊዜ የሚጠቀሰው ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖራት የሚደነግገው ህገመንግስታዊ አንፅ (አንቀፅ 49 ንኡስ አንቀፅ 5) በዋናነት መሰረት ያደረገው የኦነግን ደመነፍሳዊ ፍላጎት እንደሆነ ነው፡፡የኦነግ ደመናፍሳዊ ፍላጎት የሚመነጨው ደግሞ ድርጅቱ ደቁኖ ከቀሰሰበት የተበድየ ፖለቲካዊ ስነልቦናው ነው፡፡ የተበድየ ፖለቲካዊ ስነልቦናው ተረክ ዘፍጥረት ደግሞ አስራስድስተኛውን ክፍለዘመን የአለም መፈጠሪያ የታሪክ መቆጠሪያ ጅማሬ አድርጎ ከሚወስደው እንዳይሆን የሆነ ፣ሸምበቆ የተመረኮዘ ክርክር ነው፡፡

ይህ አይነቱ ኦነግ ወለድ አካሄድ እንደማያዛልቅ የተረዳው ብልጣብልጡ ህወሃት ታዲያ ኦነግ ከሸዋ መኳንንት መስፋፋት ጋር አጣቅሶ ያመጣውን የልዩ ጥቅም ህገመንግስታዊ ድንጋጌ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር ካላት ጉርብትና ጋር ተያይዞ ከሚመጣ መስተጋብር ጋር ብቻ የሚያያዝ አድርጎ በህገመንግስቱ እንዲህ አሰፈረው “የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም ተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፤እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይከበርለታል፡፡ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል”(አንቀፅ 49 ንኡስ አንቀፅ 5)፡፡ የሽግግር ዘመኑ ኦነግ እና የአሁኑ ዘመን የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች በአዲስ አበባ ባለቤትነት/ባለ ልዩ መብትነትን ለማፅናት በሚያነሱት ታሪክ ጠቀስ ክርክር እና በህገመንግስቱ ድንጋጌዎች(ህወሃት በጉዳዩላይ ያለው ፍላጎት ግልባጭ የሆነ) መሃል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡

በስህተት የአሸናፊነት ታሪክ የማይወጣቸው የኦነግ አመራሮች አያት ቅድማያቶቻቸው በመካከለኛው ዘመን ሸዋን ሲገዛ ነበረውን ንጉስ አንበርክከው፣ሸዋን እና ጎጃምን የራሳው አድርገው ሽቅብ ወደትግራይ መገስገሳቸውን እያወቁ አይወሩም፡፡በምትኩ እንዴት ሸዋ ላይ እንደተገኙ ሊናገሩ የማይፈልጓቸው ቀደምቶቻቸው በሸዋ መኳንንት ቁምስቅል ማየታቸውን እያለቃቀሱ አውርተው ካሳውም አዲስ አበባ ለኦሮሞ ሁሉ ልዩ ጥቅም መስጠት ያለባት ምድር ማድረግ እንደሆነ ያስቀምጣሉ፡፡ የነዚሁ የኦነግ ፖለቲከኞች ተከታይ ትውልድ የሆኑት የዘመናችን አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ደግሞ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች ኦሮሞዎች እንደሆኑ ከምድር ተነስተው እርግጠኛ ሆነው ‘አዲስ አበባ ራሷ በኦሮሚያ ክልል ሥር ሆና በኦሮሞ የጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያቤት ካልተቀረጠች ምኑን በደል ተካካሰ’ አይነት ነገር ይሰነዝራሉ፡፡

አዲስ አበባ ላይ ክፉኛ ስር የሰደደው ህወሃት/ኢህአዴግ ደግሞ ማሳረጊያው ከእርሱ ፍላጎት እንደማይወጣ ቢያውቅም አጨራረሱ ባላጋራውን እንዳይነሳ አድርጎ ድባቅ መትቶ እንዲሆን ስለሚፈልግ ለመገመት/ለመጠላት/ለመፈራት የቀረበን ሁሉ እስከጥግ እንዲገመት/እንዲጠላ/እንዲፈራ በቂ ጊዜ ሰጥቶ በዛውም የራሱን የአሸናፊነት መንገድ መጥረጊያ ጊዜም ይገዛል፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ህገመንግስቱ ራሱ ስለዚህ ጉዳይ ያሰፈረው ድንጋጌ በተጨባጭ ታሪካዊ/ፖለቲካዊ ሃቅ ላይ የቆ አይደለም፡፡ ይልቅስ ህወሃት ኦነግን በኦህዴድ እስኪተካ እሹሩሩ ለማለት ሲል ከአንገቱ በላይ የተቀበለው ነገር ነው፡፡ የድሮው ኦነግ እና የዛሬው ኦነግ ደግሞ ለህወሃት እኩል አስፈላጊነትም/ትርጉምም ያላቸውም አይደሉም፡፡ ለህወሃት የዛሬው ኦነነግ ትናንት እንዳይበረግግ ቀስ ብሎ የሚያስተኛው ‘የስለት ልጅ’ ሳይሆን ባጠፋውም ባላጠፋውም የሚረግመው ባላጋራው ነው፡፡ ስለዚህ ብልጣብልጡ ህወሃት በድሮ በሬ ከልቡ ሲያርስ አይገኝምና ዛሬም በኦነግ አንጎበር ውስጥ ያሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች እንደሚመኙት ‘አዲስ አበባን እንካችሁ ብቻ አትቆጡብኝ’ የሚልበት ምክንያት የለውም፡፡

የአስራሰባት አመት የጫካ ትግሉ ሁሉን በአሸናፊነት የሚወጣበት ሁነኛ ቦታ ላይ ያስቀመጠው ህወሃት/ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ፍላጎት ግልፅ ነው፡፡ዋነኛው ግልፅ ነገር የዘመናችን የኦሮሞ አክቲቪስቶች እንደሚፈልጉት አዲስ አበባን በኦሮሚያ ስር አድርጎ ሰዶ ማሳደድ ውስጥ እንደማይገባ ነው፡፡ይህን ለማረጋገጥ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች፤ባለቤት አልባ ከተማ” በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሃፍ ገፅ 240 ላይ እንዳስቀመው ከ1997 አስደንጋጭ የምርጫ ሽንፈቱ በፊት ኢህአዴግ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን ፍላጎት ባሳዩ ኦሮሞዎች ላይ የነበረውን የመረረ አቋም ማስተዋል በቂ ነው፡፡ የሽንፈቱ ድንጋጤ መለስ ሲልለት በተጫጫነው ንዴት ሳቢያ ሃሳቡን በተቃራኒው ቀይሮ አዲስ አበባን የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን ቢፈቅድም በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ መስተጋብር ያለውን እውነተኛ ፍላጎት የሚያሳየው ግን ከንዴቱ በፊት(ከ1997) ያራምድ የነበረው አቋም ነው፡፡

ሁለተኛው ነገር የአዲስ አበባን ወሰን ከዚህ መልስ ብሎ ልማታዊ ባለሃብቶቹ አጥብቀው የሚሹትን የአዲስ አበባ እና የአካባቢውን የመሬት አቅርቦት የማድረቅ ገራገር ውሳኔ እንደማይሞክራት ነው፡፡ ለዚህ አንዱ ማስረገጫ ባለፈው አመት መገባደጃ ለፓርላማ ባቀረበው እና በኢቢሲ ባስነበበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የአዲስ አበባ ከተማን ወሰንን በመከለል ላይ አንዳችም ነገር አለማንሳቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ማሳያ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ኦሮሚያ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቶች ለልማት ከተፈለጉ ለአርሶ አደሮቹ በቂ ካሳ ይከፈላል እንጅ ከቦታቸው መነሳታቸው “የማይቀር የልማት ጥያቄ” እንደሆነ አስረግጦ ማስቀመጡ ነው፡፡

አዲስ አበቤ- የጎጥ ፖለቲካ “የእንጀራ ልጅ”?

በዚህ መሃል ፍላጎቱን እና ጥቅሙን ይተነፍስ ዘንድ መድረክ ያላገኘው የአዲስ አበባ ህዝብ አለ፡፡ ራሱን በጎሳ ማንነት የማይገልፀው የአዲስ አበባ ህዝብ ሁለቱ የጎሳ ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞች(ኦነግ እና ህወሃት/ኢህአዴግ) በከተማዋ ላይ የሚያነሱት ክርክር ከፍላጎቱ ጋር እንደማይገጥም እርግጥ ነው፡፡ ብሄር አልቦው አዲስ አበቤ ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስላለው ጉዳይ ለመምከር የሚያስችል የፌደሬሽን ምክርቤት ውክልና የለውም፡፡ በክልሎች መሃከል የሚነሳ ክርክር የሚሄደው ወደዚሁ የፌደሬሽን ምክርቤት እንደሆነ የሃራችን ህገመንግስት አንቀፅ 62 ንዑስ አንቀፅ 6 ይደነግጋል፡፡ በተመሳሳይ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ ደግሞ በፌደሬሽን ምክርቤት የሚወከሉት የሃገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችን የያዙ ክልሎች እንደሆኑ ያትታል፡፡ ሸገር በፌደሬሽን ምክርቤት ለመወከል ያልበቃችው በብሄር ብሄረሰቦች የማትገለፅ ባለዥጉርጉ ሆድ በመሆኗ ነው፡፡

ስለ ሃገራችን ርዕሰ ከተማ በሚያወራው የህገመንግስቱ ክፍልም አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 4 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ብቻ እንደሚወከሉ ያወሳል እንጅ በፌደሬሽን ምክርቤት ውክልናቸው ጉዳይ አንዳች ነገር አያነሳም፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር እንዲህ እንደ አሁኑ ያለ ወደ ፌደሬሽን ምክርቤት የሚወስድ ጉዳይ ሲገጥመው ምን ማድረግ እንዳለበት ያስቀመጠው ነገርም የለም፡፡ የህግ የበላይነት እንደሰማይ በራቀው የሃገራችን ፖለቲካ በየትኛውም ምክርቤት መወከል ንጉስ የወደደውን ከማድረግ እንደማያስቀር የታወቀ ቢሆንም ከነጭርሱ የፌደሬሽን ምክርቤት ውክልና ማጣቱ ደግሞ የነገስታትን እንደልቡነት ይብስ ያጎላዋል፡፡

ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ጆሮ የተጣገበው የአዲስ አበባ ህዝብ ከወደ መንግስት የሚመጣውን አብዛኛ ህግጋት አማራጭ ስለሌለው ብቻ የባሰ አታምጣ በሚል ዘየ ተቀብሎ ይኖራል፡፡ ወልዶ ከብዶ የኖረባት አዲስ አበባ ቤቱ ስላልሆነች ግብር እየከፈለ መኖር እንዳለበት ህገመንግስታዊ አንቀፅን ጠቅሶ የሚያውጅ ባለቤት ነኝ ባይ ሲመጣበት ደግሞ የባሰ እንደመጣና የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የተሻለ አድርጎ ለመቁጠር መገደዱ አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ የተገመተው ተገምቶ፣የተጠላው አይንህ ላፈር ተብሎ፣ማስፈራሪያ ሊሆን የተፈለገው በገዛ ምላሱ ገላጭነት አስፈሪ ምስሉ ጎልቶ ከወጣ በኋላ የሚፀናው ህወሃት/ኢህአዴግ ይሆን ዘንድ የወደደው እንደሆነ እሙን ነው፡፡

የሚሰራውን በደንብ የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ የፈለገውን ለማፅናት የህጋዊነትን ካባ ደርቦ ከች እንደሚል የታወቀ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ላለው ፍላጎቱ ህጋዊ ከለላ ለመስጠት ደግሞ ገና ድሮ የልቡን እንዲናገር አድርጎ ያበጃጀውን ህገመንግስት ከመጥቀስ የበለጠ አዋጭ መንገድ የለም፡፡ሆኖም ህገመንግስቱን አስር ጊዜ የሚያነሳሳው መንግስት ሚኒስትሮች ምክርቤት መከረበት የተባለው ረቂቅ አዋጅ ራሱ ከህገ-መንግስቱ አንቀፆች ጋር የሚተላለፍበት አካሄድ ቢኖርም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ከሚያነሱት አስገራሚ ጥያቄ አንፃር የመንግስት ረቂቅ አዋጅ በተሻለ ለህገመንግስቱ አንቀፆች ሊቀራረብ ይሞክራል፡፡ እዚህ ላይ የባሰ አለ ለማለት እንጅ ህገመንግስታዊ አንቀፅን መሸራረፍ ለማንም የተቻለ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡

አልተገናኝቶ…!

የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ይገባል ስለተባለው የባለቤትነት/የልዩ ጥቅም ባለመብትነት ጉዳይ ከኦሮሞ የብሄርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞች/ፖለቲከኞች የሚነሳው ጥያቄም ሆነ ረቂቅ አዋጅ ተብሎ በፓርላማ ሊፀድቅ በር ላይ ያለው (የመንግስትን ፍላጎት የሚያሳየው) ረቂቅ መሰረቱን የሚያደርገው ህገ-መንግስቱን ነው ይባል እንጅ ህገመንግስቱን አለመምሰሉ ይበዛል፡፡አዲስ አበባን አስመልክቶ በህገ-መንግስቱ በተቀመጠው አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 1 ላይ በተቀመጠው ቢጀመር አዲስ አበባ የሃገሪቱ ርዕሰ ከተማ እንደሆነች ያስረዳል፡፡አስፈፃሚው የመንግስት ክንፍ ለህግ አውጭው አቀረብኩ ባለው ረቂቅ አዋጅ ላይ ደግሞ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እንደሆነችም ያትታል፡፡ ይህ መሰረት ያደረገው የህወሃት/ኢህአዴግን እና የኦህዴድ/ኢህአዴግን ወቅታዊ የፖለቲካ ፍላጎት ይሆን ይሆናል እንጅ በፍፁም ህገመንግስታዊ መሰረት ያለው ነገር አይደለም፡፡ የሃገሪቱ ህገመንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ህገመንግስት አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ እንደሆነች አይደነግግም፡፡ በ1994 በተሻሻለው የኦሮሚያ ክልላዊ ህገ-መንግስት ላይ “የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ አዳማ ነው” የሚል ድንጋጌ እንደተደነገገ ኤርሚያስ ለገሰ ከላይ በተጠቀሰው መፅሃፉ ገፅ 240 አሰቀምጧል፡፡ በክልላዊም ሆነ በፌደራሉ ህገ-መንግስት ላይ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ከተማዋ የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ እንድትሆን የሚያዝ ረቂቅ አዋጅ ማውጣት ህገመንግስታዊ ድንጋጌን ስለማስፈፀም እያወሩ ህገ-መንግስታዊ ባልሆነ አካሄድ መንጎድ ከመሆን አያልፍም፡፡ በዚህ ውስጥ ማየት የሚቻለው ነገር የሃገራችን ገዥዎች ፖለቲካዊ ጥቅማቸው በምሉዕ ሁኔታ ለማጣጣም ሲሉ ህጋዊ አካሄዶችን ለመደፍጠጥ እንደማያመነቱ ነው፡፡ ይብስ የሚገርመው ደግሞ ህገ-መንግስት ሊተረጉም የተቀመጠው የፌደሬሽን ምክርቤት ተብየው የዘወትር ዝምታ ነው፡፡

የባሰ ሲመጣ ደግሞ ለህግ መከበር ጥብቅና ሊቆሙ የሚገባቸው የህግ ምሁሩ ፀጋየ አራርሳ በ“OMN” ቴሌቭዥን ቀርበው ህገ-መንግስቱ ካለው በተቃራኒ “እንደውም አዲስ አበባን ለኦሮሚያ ትቶ ሌላ ረባዳ መሬት ተፈልጎ አዲስ ዋናከተማ መመስረት ይቻላል’ የሚል አማራጭን ያስቀምጣሉ፡፡ አማራጭ ቦታ ሲጠቁሙ ደግሞ ‘አዲሱን ዋና ከተማ ሌላ የኦሮሚያ ክልል ቦታ ላይም ሊደረግ ይችላል’ ይላሉ፡፡ ነገሩ እንዳይሆን መሆኑ ካልቀረ፣ ‘ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ዋና ከተማ በኦሮሚያ ማየት ስለማንፈልግ ሌላ ክልል ላይ ዋና ከተማችሁን መስርቱ’ ማለት አንድ የለየለት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ሌላ ዋናከተማ መመስረቱ እንደ አማራጭ ሆኖ ከቀረበ ዘንዳ አሁንም በኦሮሚያ ክልል ያለችውን አዲስ አበባን ጥሎ ሌላ ሜዳማ መሬት በዛው በኦሮሚያ ክልል ፈልጎ ሌላ ዋና ከተማ ለመመስረት መባዘኑ ለምን እንዳስፈለገ የሚያውቁት ፀጋየ ብቻ ናቸው፡፡

ሌላው ከህገመንግስታዊ ድንጋጌው ጋር አልተገናኝቶ የሆነው ጉዳይ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ስር መተዳደር አለባት የሚለው የኦሮሞ ፖለቲከኞች/አክቲቪስቶች ክርክር ነው፡፡የህገመንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 2 “የአዲስ አበባ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል፡፡” ሲል ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪ በህገመንግስቱ ተመሳሳይ አንቀፅ ስር ንዑስ አንቀፅ 3 “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ይሆናል” ይላል:: ይህ በግልፅ በተደነገገበት ሁኔታ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ስር ሆና ትተዳደር ማለት ስሜታዊ እንጅ ህገመንግስታዊ መሰረት የሌለው ጥያቄ እንደሆነ የሚያነጋግር ነገር አይደለም፡፡

ይልቅስ የሚያነጋግረው ሌላው ጉዳይ የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን መስተጋብር አስመልክቶ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ረቂቅ አዋጅ አወጣሁ የሚለው የሃገሪቱ መንግስት ዝርዝር አዋጁን ለማውጣት በህገመንግስቱ በአንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ብቻ ብቻ መዟዟርን የመረጠበት ሚስጥር ነው፡፡ ነገሩ እውነት ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ዝርዝር ህግ የማውጣት ጉዳይ ከሆነ በዚሁ አንቀፅ ስር በንዑስ አንቀፅ 2፣ የአዲስ አበባ ክልል መስተዳድር ራሱን በራሱ ስለማስተዳደሩ በተቀመጠው ድንጋጌ ላይ ዝርዝር ህግ እንደሚወጣ ህገመንግስቱ ያዛልና ዝርዝር ህጉ አብሮ መውጣት ነበረበት፡፡ መንግስት ግን ይህን ማድረግ አልፈለገም፡፡

የዚህ ህግ ዝርዝር አለመውጣት የአዲስ አበባን ህዝብ የራሱ ባለቤት እንዳይሆን የሚያግድ፣የመጣው ሁሉ እንደፈለገ እንዲያደርገው የሚያመቻች ትልቅ መሰናክል ነው፡፡መንግስት ይህን ያደረገው የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያን መስተጋብር በተመለከ የሚያነሳቸውን ካርታዎች ጥሎ ላለመጨረስ እንደሆነ ኤርሚያስ ለገሰ “የመለስ ቱርፋቶች” ባለው መፅሃፉ ከገፅ 240- 254 ከትንታኔ ዘለል ብሎ ትንቢት በሚመስል መልኩ በትክክል አስቀምጦታል፤ አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ሁሉ የገዥውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ማንነት አበጥሮ የሚያውቀው ኤርሚያስ እንዳስቀመጠው ነው፡፡

የመልከዓምድራዊ አቀማመጥ ወግ

አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት ነች የሚለው ክርክር ታሪካዊ ቀደምት ነዋሪነትን፣ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችን ከማጣቀሱ ጎንለጎን የሚያነሳው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሃል የመገኘቷን ነገር ነው፡፡ ይህ ክርክር የሚስተው አንድ ወሳኝ ነጥብ የሃገራችን ክልሎች አከላለል በዋናነት ታሳቢ የሚያደርገው መልከዓምድራዊ አቀማመጥን ሳይሆን በአንድ ስፍራ ላይ የሰፈሩ ህዝቦች የሚናገሩትን ቋንቋ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በተለያዩ ክልሎች ልዩ ዞኖች እና ወረዳዎች እንዲኖሩ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ በአማራ ክልል መሃል ላይ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚገኙበት ከሚሴ የተባለው ቦታ በአማራ ክልል የኦሮሚያ ዞን እንዲሆን ተደርጓል፡፡የኦሮሚያ ልዩ ዞን በአማራ ክልል መሃል ላይ በመገኘቱ ብቻ የአማራ ህዝብን ታሪክ እና ማንነት የሚያጎሉ መታሰቢያዎች፣አሻራዎች እንዲቆሙ ላይ ታች ሲባል ግን አልታየም፡፡ በዚህ እሳቤ ወደ አዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ጉዳይ ሲመጣ በከተማዋ ከሚኖረው ህዝብ የሚበዛው የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዳልሆነ የታወቀ ነው፡፡ ይህም ስለሆነ ነው ከተማዋ ራሱን በቻለ መስተዳድር እንድትተዳደር በህገመንግስት ሳይቀር የተደነገገው፡፡

አሁን ወጣ በተባለው ረቂቅ አዋጅም ከተማዋ ሃገር አቀፋዊ ቀርቶ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላት፣ከኒውዮርክ እና ከጄኔቫ ቀጥላ የአለማቀፉ ማህበር ማዕከል እንደሆነች ተወርቷል፡፡ በዚሁ አፍ ደግሞ የከተማዋ አደባባዮች፣ጎዳናዎች፣ሰፈሮች እና የመሳሰሉት ቦታዎች የኦሮሞ ብሄርን መንፈስ እንዲያሳዩ እንዲረዳ በቀድሞው የኦሮሞ ስማቸው እንዲጠሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል፡፡ የሰፈሮቹ የቀድሞ የኦሮሞ ስም እንዴት እንደሚታወቅ ነገሩን ያመጣው አካል የሚያውቅ ቢሆንም ከተማዋ ሃገራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ አላት ማለት እና የከተማዋ ሰፈሮች ስም ተቀይሮ በኦሮምኛ ስሞች እንድትጠራ ማድረግ እንዴት እንደሚገናኝ ብቻ ሳይሆን ለምን እንዳስፈለገ፣ነገሩ ራሱን ከማንኛውም ብሄር ጋር ለማያጋምደው አዲስ አበቤ ምን ትርጉም እንዳለው ግራ ነው፡፡

የአዲስ አበባ መስተዳድር አብዛኛ ነዋሪ ኦሮምኛ ተናጋሪ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ከተማዋ ራሱን በቻለ መስተዳድር ትተዳደራለች ተብሎ በህገመንግስት በግልፅ በተቀመጠበት ሁኔታ በዙሪያዋ የኦሮሞ ብሄር ስላለ መሃሏ የራሷን ሳይሆን የጎረቤቷን ኦሮሚያ ክልልን ታሪካዊ፣ስነልቦናዊ እና ባህላዊ ማንነት ይስበክ ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ይህን ካደረጉ በኋላ አዲስ አበባ ራሱን በቻለ መስተዳድር ትተዳደራለች የሚለው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ወረቀት ላይ መቼክቼክ ምን ይፈይዳል? አራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች እንደሚያስተዳድሯት የሚወራው አዲስ አበባ የኦህዴድን ገፅታ ብቻ እንድታሳይ ሲደረግ ሌሎቹ ፓርቲዎች ጥቅማቸው ምንድን ነው?

‘አዲስ አበባን የሚመግባት በዙሪያዋ ያለ የኦሮሞ አርሶ አደር ስለሆነ ደላላ እንዳያታልለው አዲስ አበባ ገብቶ ምርቱን የሚሸጥ የሚለውጥበት የገበያ ሰንሰለት ያጥርለት ዘንድ ኮሚቴ አቋቁማለሁ’ ይላል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አወጣው የተባለው ህግ፡፡ አዋጁን እየተንተገተገ ያነበበው ጋዜጠኛም ንባቡን ሲያጠቃልል ‘ረቂቅ ህጉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንዲጠቅም ታሳቢ የተደረገ እንደሆነ’ አንገቱን ከፍ ዝቅ እያደረገ ተናግሯል፡፡ ሁላችንም ያጎረሱንን ሁሉ የምንውጥ ካድሬዎች አይደለንምና እዚህ ላይ ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ባለ ብዙ ፍጆታዋ አዲስ አበባ ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የምታገኘው የምርት አቅርቦት ብዙ እንደሆነ አሌ ባይባልም ይህ ቦታ የማይመግባት ብዙ ፍጆታ እንዳለም የታወቀ ነው፡፡ ለምሳሌ ሙዝ አናናስ፣ማንጎ፣አቩካዶው፣በርበሬ፣ዝንጅብሉ፣ኮረሪማው፣ቆጮው የሚጫነው ከደቡብ ኢትዮጵያ እንጅ ከአጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች አይደለም፡፡ ማሩ፣ቂቤው ጤፍ ጥራጥሬውም ከጎጃም ሌላ ሌላውም ከተለያየው የሃገራችን ክፍል ወደሸገር ይጎርፋል፡፡ታዲያ አርሶና አፈር አፍሶ ይህን ሁሉ ምርት ለሸገር የሚያጎርሰውን ከኦሮሚያ ውጭ ያለው ገበሬ በደላላ እንዳይበላ “ለሁሉም ያሰበ ነው” በተባለለት ረቂቅ ህግ ያልተወራው ለምንድን ነው? ዘመኑ የዘመናዊ ፈጣን ትራንስፖርት እንጅ በእግር የሚገሰገስበት የሲራራ ንግድ አለመሆኑ እየታወቀ በመልከዓምድር አቀማመጥ የቀረበ አርሶ አደር የበለጠ ምርት ለሸገር እንደሚያስገባ ማሰብ ሌላ አላማ ከሌለለው የለየለት የእውቀት ድርቅ ነው፡፡

እውን ይህን ረቂቅ ህግ ያወጣው ከአራቱ የኢህአዴግ አባል ፓርትዎች የተውጣጣው የኢህአዴግ ስራአስፈፃሚ ከሆነ ፍራፍሬውን ወደ አዲስ አበባ ጉሮሮ በየቀኑ የሚያስገበውን ህዝብ ወከልኩ ያለው ደኢህዴን ነፍስ እና ስጋ ካለው ‘እኔ የወከልኩት አርሶ አደርስ የደላላ ጥሩር አለው ወይ?’ ማለት ነበረበት፡፡ ብአዴንስ ቢሆን ተመሳሳይ ጥያቄ ለማንሳት የማያበቃ ምርት አልቦ አርሶ አደር ወክሏል? ይህ ረቂቅ ህግ ሌሎቹን የሃገራችን አርሶ አደሮች የግብይት ነገር ችላ ብሎ ለአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሞ አርሶ አደሮች የሚያሳየው “እንስፍሳፌ”እውነት ከልብ እና የጤና ነው? ወይስ እንደ ጅብ እስኪነክሱ ማነከስ? ብሎ መጠየቁ እንጅ ብልህነት ‘ሌላው ተረስቶ እኛ የታሰብነው ለማ መገርሳ ጎበዝ ስለሆነ ነው’ ብሎ መደሳሰት ለዶሮ ውሃ የሚሞቀው ለገላዋ መታጠቢያ ነው ብሎ እንደማሰብ ያለ ተላላነት ነው፡፡

ጸሀፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል:: meskiduye99@gmail.com

___
በዚህ ድረ ገጽ መጣጥፍ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ኢሜይል ያድርጉልን። editor@borkena.com

ወይ አዲስ አበባ….! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

ጳጉሜ 2 2009 ዓ ም
በመስከረም አበራ

ቅድመ-ነገር

Meskerem Abera - article -Addis Ababa
Meskerem Abera

ታሪክ የሰው ልጆችን ያለፈ የህይወት ስንክሳር መርምሮ፣ መጭው ትውልድ ካለፈው ድካምም ብርታትም እንዲማርና የተሻለ ዓለም
እንዲፈጥር ማስቻልን ያለመ የጥናት መስክ ነው፡፡የሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ አተናተን ዘይቤ ክፉኛ በታሪክ ላይ የተጣበቀ ነው፡፡
ፖለቲካችን ታሪክን የሙጥኝ ማለቱ በራሱ ጥፋት የለውም፡፡አስቸጋሪ የሚሆነው ታሪካችንን ለወቅታዊ ፖለቲካችን ትንታኔ
በምንጠቀምበት ጊዜ ስነ-ልቦናችንን አብረን ማጋመዳችን ነው፡፡የሃገራችን ፖለቲካ ውቃቤ እንዲርቀው ካደረጉ ነገሮች ዋነኛው
ታሪክን እና ፖለቲካን በየግል ስነ-ልቦናችን ለንቅጠን፣ የስነልቦናችን ደመነፍስ ያቀበለንን የስሜት ግንፍላት በምክንያታዊነት ላይ
አንግሰን መንጎዳችን ይመስለኛል፡፡

ወደ ስሜታዊነት የሚመራን ፖለቲካዊ ስነልቦናችን ምንጩ ሲመረመር ወይ ዝቅተኝነት የሚያንገላታው የ‘ተበድያለሁ’ እዬዬ ነው
ወይ እብሪት የነገሰበት ‘የገዥ ነኝ’ የበላይነት ስሜት ነው፡፡ የዚህ ፖለቲካዊ ስነ-ልቦና ምንጩ ደግሞ ደመነፍሳዊ ማነብነብን
እንደ ሁነኛ የርዕዮት አለም ትጥቅ ይቆጥር የነበረው የስልሳዎቹ ትውልድ ፖለቲካዊ ስነ-ምህዳር ነው፡፡ ይህ ትውልድ ሃገሩ ፀንታቆማ ዘመን የተሻገረችበትን ሃገረሰባዊ አዕማድ፣ፖለቲካዊ መስተጋብር፣ማህበራዊ ቁርኝት፣ኢኮኖሚያዊ ትንቅንቅ ለመመርመር ጊዜ ሳይወስድ በነስታሊን ወጭት የኢትዮጵያን ወጥ ሊወጠውጥ የተነሳ፣ እንደ ቤቱ ሳይሆን እንደ ጎረቤቱ ሊኖር የፋተረ ነበር፡፡በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሶቬት ህብረት ቀድማና ተለይታ በራሷ የታሪክ ዱካ ከመጓዟ የተነሳ የተሰበዘችበትን ፖለቲካዊ ሰበዝ ልዩ ተፈጥሮ ለመመርመር የማርክስ/ሌኒንን ድርሳን ማነብነቡ ፋታ አልሰጠውም ነበር፡፡

የማነብነብ ቱርፋቱ እውቀት የሚያመጣው እርጋታ እና ብስለት አይደለምና ያነብናቢነት እውቀት ያቀበለው የዘረኝነት ክፉ እንክርዳድ
በሃገራችን የፖለቲካ ማሳ ላይ ተዘራ፡፡ ሃገሪቱ የድሆች እስርቤት መሆኗ ቀርቶ “የብሄረሰቦች እስርቤት ነች” ተባለ፡፡ አንድ ብሄር
አሳሪ ሌላው ብሄር ታሳሪ ተደርጎ የአጋች ታቻች፤የበዳይ ተበዳይ ፖለቲካ እንደ ኤርታሌ ድንገት ገንፍሎ ይንተከተክ ያዘ! የኢትዮጵያ
ታሪክ ሁሉ የመበደል መበደል ድራማ ብቻ እስኪመስል ድረስ ተበደልኩ ባይ ሙሾ አውራጁ በዛ፡፡ አንድ ብሄረሰብ በነሲብ በዳይ
ሌላው ብሄረሰብ በጅምላ ተበዳይ ሆኖ የጎሳ ጥላቻ ሰልፍ፣ የመነጣጠል ጎራ፣ የጥርጣሬ መንፈስ በሃገራችን የፖለቲካ አየር ረበበ፡፡
ሁሉም የተሰለፈበት የዝቅተኝነት ወይ የበላይነት ፖለቲካዊ ስነልቦና እንደመራው ብድግ ብሎ ፖለቲካን መተንተን ጀመረ፡፡ ፖለቲካዊ
ስድነት በሃገሪቱ ነገሰ! የገዛ ሃገርን ቅኝ ገዥ ማለት ከአዋቂነት ተፃፈ፡፡ የሃገርን ትውፊት ማቃለል ዘመናዊነት ሆነ፡፡ የእነ
ገብረህይወት ባይከዳኝ ምጡቅ ልቦና ለሃገራችን ችግር ሃገርኛ መንስኤ እና መፍትሄ የጠቆመበትን ድርሳን ትራስ አድርጎ ተኝቶ
የነሌኒንን የጠብ ዶሴ ማገላበጥ፣ውጭ ውጭውን ማለት የምጡቅነት መለዮ ሆነ፡፡

ይህ የማነብነብ ደመነፍስ በጠመንጃ ታግዞ ስልጣን ላይ ለመውጣት በሚፋትርበት ወቅት ያዋጋ ያጋድል የነበረው ደመ-ጠጭ ዛር
በስተመጨረሻ ለህወሃት ቆሞለት ስልጣን ላይ ሰየመው፡፡ ህወሃት ከላይ ከተነሱት ሁለት ፖለቲካዊ ስነልቦናዎች በተበድያለሁ
መስመር የተሰለፈ ነበረና የህወሃት ስልጣን ላይ መውጣት ለተበድያለሁ ፖለቲከኞች ጥሩ የማላዘኛ መድረክ ፈጠረ፡፡ የተበድየ
ፖለቲካው ሰልፍ ፊታውራሪዎቹ ኦነግና ህወሃት ፍቅራቸው ገመሬ ዝንጀሮ እንዳየው ክምር ድራሹ እስኪጠፋ ድረስ ሻዕብያን ሙሾ
አውራጅ አድርገው በተበድየው ሙዚቃ ደረት ሲደቁ ባጁ!

በአንፃሩ የበዳይነት ጦስ የወደቀበት የአማራው ብሄር የሚወረወርበትን የወቀሳ ፍላፃ ለመመከት የሚያስችል መድረክ እንኳን
ተነፈገው፡፡ በሌለበት የፖለቲካ ችሎት ወንጀለኝነቱ ተረጋግጦ የመገለል ክፉ ፍርድ ተፈረደበት፡፡በሃገሩ ሁነኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ
እንዳይሳተፍ በግልፅም በስውርም እግድ ተጣለበት፡፡የሽግግር ቻርተር በማርቀቅ ቢሉ ቻርተሩን ህገመንግስት በማድረጉ ሂደት ይህ ነው
የሚባል ውክልና ተነፈገው፡፡ያለፈው የሃገሪቱ ክፉ ክስተት ሁሉ ተጠያቂ ተደረገ፡፡ታሪክም አማራውን ጭራቅ አድርጎ ለማሳየት
ያስችላል ተብሎ ከተገመተበት ዘመን ይቆጠር ጀመር፡፡ የሉሲ ሃገር ኢትዮጵያም የመቶ አመት ብላቴና ተደርጋ አረፈችው!

የሰው ልጆች ያለፈ ሁለንተናዊ የህይወት ልምድ ታሪክ መባል ያለበት መቼ ነው የሚለው ነገር የሚያከራክረው ከቅርቡ ወደ ሩቁ
ሲቆጠር ነው፡፡ታሪክ እንደ ጥናት መስክ የሩቁን ለማጥናት ይጓጓል እንጅ የቅርቡን በአያሌው የሚወስነውን የሩቁን ታሪክ ጥሎ
የቅርቡን አንጠልጥሎ አይደናበርም፡፡ የሃገራችንን ፖለቲካ ቅጥ አምባር ያሳጣው ይሄው ብዙውን ጥሎ ጥቂቱን አንጠልጥሎ
የመንጎዱ የእብድ እሩጫ ነው፡፡ በደንባራ በቅሎ ቃጭል ሲጨመር ደግሞ በዚህ ላይ ስነልቦናችን ታክሎበት መመለሻችንን
በሚያስናፍቅ የቁልቁሊት ሩጫ ውስጥ ዶሎናል፤ላለመደማመጥ አማምሎናል፤ምክንያታዊነትን ለዘረኝነት አሰውቶ ፖለቲካችንን
የስነ-ልቦና ቀውስ በሽተኞች መድረክ አድርጎታል፡፡

የፊት አውራሪው ህወሃት ወደ ስልጣን መምጣት ገበያ ያደራለት የተበድየ ፖለቲካ በዚሁ ስነ-ልቦና የተጠቁ አባብሉኝ ባይ
ፖለቲከኞችን እያፈላ ይገኛል፡፡ ቀደምት የበደል ፖለቲካ ቄሰ-ገበዞች፣ የህወሃት ባለንጀሮች እነ አቶ ሌንጮ ለታ እና ጓዶቻቸው
ከህወሃትም ተፋተው፣ እድሜ ብቻ ያደረጋቸውን፣ እንደስማቸው የሚታወቁበትን የበደል ትረካ ፖለቲካ ጥቅም ጉዳት መዝነው፣
‘ዛሬ የተለየ መንገድ ይዘናል’ ቢሉም የዘሩት ዘር ግን እነሱ የተቀየሩ ዕለት የሚቀየር አይደምና በዝቶ ተባዝቶ በቦታው አለ፡፡ የነ
ሌንጮ ለታ የበደል እዬዬ ስብከት ዛሬ መምህሩን የሚያስከነዱ የጥላቻ ደቀመዛሙርትን አምርቷል፡፡ በእንዲህ ያለው ደዌ የተለከፉ
በአብዛኛው የምሁርነትንም ካባ የደረቡ ልሂቃን የሚደውሩት የከረረ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ የህመሙን ክፋት ከሚያሳዩ ብዙ
ምልክቶች አንዱ በቅርቡ የተያዘው የሃገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ የአንድ ብሄር/የኦሮሞ ብሄር/ ተቀዳሚ ንብረት ነች
የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

የብቻ አዲስ አበባ?

የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪዎች የኦሮሞዎች ናቸው በሚለው እሳቤ እርግጠኛ ተሁኖ አዲስ አበባም መተዳደር ያለባት በኦሮሚያ
ክልል ስር ነው የሚል ክርክር በቅርቡ ተፋፍሞ ማነጋገሩን ቀጥሏል፡፡ይሄው የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪነት እና ተቀዳሚ ባለቤትነት
ተረክ ሌሎች የዚሁ እሳቤ ውላጅ የሆኑ መብት ጥያቄዎችን ያስከትላል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ ህገመንግስታዊ የልዩ ጥቅም
ባለመብትነት ጉዳይ፣የአዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ መገኘት ኦሮሚያን በአዲስ አበባ ላይ የባለቤት ፀዳል ለማላበስ በቂ ሁኔታ
ነው የሚሉት ክርክሮች መነሻቸው ይሄው የቀደምት ነዋሪነት ጉዳይ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል አዲስ አበባ ላይ ጅኦግራፊያዊ እና ታሪካዊ ባለቤት እንደሆነች የሚወተውተው ክርክር ዋናው መሰረቱ ኦሮሞዎች
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የኖሩ የአዳም ዘሮች ናቸው የሚለው ተረክ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሞዎችን ቀደምት
ነዋሪነት ትርክት ተአማኒ/ኢ-ተአማኒነት ለማስረገጥ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ መካከል ባለው “የባለቤት/ባለ ልዩ መብትነት”
ጉዳይ ለሚነሱ ንትርኮች በታሪካዊ መዛግብት የተደገፈ ማስረጃ ሊቀርብ ያስፈልጋል፡፡ በታሪክ ምስክርነት ሳይታገዝ የሚቀርብ
‘የኔነው የኔነው’ ሽሚያ ያደገን ሰው እንደ ህፃን ልጅ ‘ሁሉን ነገር ለእኔ’ የሚያስብል የስነ-ልቦና ቀውስ ምልክት እንጅ ሌላ ሊሆን
አይችልም!

“ተው ማነህ ተው ማነህ..”!

ባለፈው ሳምንት ONN በተባለው ቴሌቭዥን “አንደበተ ርቱዕ ምሁር” ተብለው የተጋበዙት ፀጋየ ሃራርሳ “በ1800 ዓ.ም መቶ
ፐርሰንቱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ኦሮሞ ነበረ፤አሁን ግን በወራሪዎች ግፍ ተገፍቶ ተገፍቶ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ አስራ ዘጠኝ
ፐርሰንቱ ብቻ ኦሮሞ እንዲሆን ተደርጓል ይላሉ፡፡” የዚህ ክርክራቸውን ታሪካዊ ማስረጃ አብረው አልጠቀሱም፡፡ ሆኖም ክርክሩ አዲስ
አበባ ሰው ማኖር ስትጀምር ለመጀመሪያ ጊዜ የኖሩባት ኦሮሞዎች ናቸው የሚለውን ተረክ ለማጠናከር የተመዘዘ ሃሳብ እንደሆነ
መረዳት አይከብድም፡፡

በ1800 የአዲስ አበባ መቶ ፐርሰንት ነዋሪ ኦሮሞ ብቻ እንደ እንደሆነ ያውም ምሁር በተባለ ሰው አፍ ተሞልቶ ሲነገር ታሳቢ
መደረግ ያለበት ነገር ይህን ያህል አስተማምኖ የሚያናግር የህዝብ ቆጠራ በ1800 ያካሄደው አካል ማን ነው? ድሮ ቀርቶ ዛሬ
የሃገራችን የህዝብ ቆጠራ የትክክለኝነት ደረጃ እከሌ የእንትን ምድር ባለቤት እንቶኔ ደግሞ መፃተኛ የሚያስብል ነው ወይ? ያኔ

ይቅር ዛሬ በኮምፒውተር ዘመን የሃገራችን ህዝብ ቆጠራ ‘በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ የገባበት ጠፋ’ የሚባልበት፣ የበዛው አንሶ
ያነሰው በዝቶ የሚቀርብበት እንደሆነ በደንብ የምናውቀው የቤታችን ጉድ ነው፡፡ታዲያ በ1800 አዲስ አበባ ላይ የታየ የአዳም ዘር
ሁሉ አንድ ሳይቀር ኦሮሞ ነበር ማለት ሊበሉ ያሰቧትን አሞራ ጅግራ የማለት የስነ-ልቦና ቀውስ ካልሆነ ትርጉሙ ምንድን ነው?
ደግሞስ እንዴት ባለ ምትሃት ነው በአንድ ምድር ላይ በስህተት እንኳን አንድ ሰው ሳይደባለቅ ኦሮሞ ብቻ ሊሰፍር የሚችለው? እሽ
ይሄም በሆነ ምትሃታዊ ሃይል ምክንያት ሆነ እንበልና የ1800 አሰፋፈር የአሁኗን አዲስ አበባ የባለቤትነት መብት ሊወስን የበቃው
እንዴት ነው?

ዛሬ ላይ ተቁሞ፣ሁለት ሶስት ምዕተ-ዓመት ወደኋላ ተጉዞ፣ የከተማ ባለቤትነትን መብት መወሰን ከተቻለ በዚሁ ስሌት
ከአስራስምንተኛው ምዕተ አመትም ወደ ኋላ መሄድና የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት ሊቻል ነው ማለት ነው፡፡ ከአስራ ስምንተኛው
ክፍለዘመን ወደ ኋላ ሲኬድ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ቀርቶ መላ ኦሮሚያ ላይም የኦሮሞ ህዝብ እንዲህ በገፍ አልሰፈረም ነበርና
በአሁኗ ኦሮሚያ ላይ ልዩ ጥቅም ሊጠበቅለት የሚገባ ሌላ ቀደምት የመሬት ባለቤት ህዝብ ፍለጋ መኳተን ሊያስፈልግ ነው፡፡ ነፍሱን
ይማርና ጋሼ አሰፋ ጫቦ ‘ተው ማነት ተው ማነህ የተኛው አለ ትቀሰቅሳለህ’ ይል የነበረው እንዲህ ያለውን ነገር ነበር፡፡ዛሬ
ሃብታምነቷ፣ለምለምነቷ፣ስፋቷ፣የህዝብ ብዛቷ እየተጠቀሰ በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ‘ዋ! እንዳንገነጠል’ አይነት
ማስፈራሪያነት የምትውለዋ የኦሮሚያ ምድር ከማንም ዘር ጋር አብራ ያልተወለደች፣ ይልቅስ በፊተኛው ዘመን ሌሎችን ህዝቦችን
ይዛ እንደኖረችው ሁሉ ከጊዜ በኋላ ደግሞ በተፈጥሯዊው የሰው ልጆች የመውረር መወረር አይቀሬ ክስተት ኦሮምኛ ተናጋሪ
ወገኖችንም ተቀብላ ያስተናገደች ምድር እንደሆነች ታሪክ አገላብጦ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
ታሪክ ምን ይላል?

የመካከለኛውን ዘመን የሃገራችን ታሪክ ግልፅ አድርገው ከፃፉ ፀሃፍት አንዱ አቶ ይልማ ደሬሳ ናቸው፡፡ ፀሃፊው “የኢትዮጵያ
ታሪክ፤በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን” በሚል ርዕስ በፃፉት መፅሃፍ ውስጥ ለኦሮሞ ህዝቦች ወደ መሃል እና ሰሜን ኢትዮጵያ
የመስፋፋት ታሪክ የመደቡት ገፅ አነስተኛ ቢሆንም በጥሩ ሁኔታ አቅርበውታል፡፡ እግረመንገዴን ይህን መፅሃፍ ያላነበበ አንባቢ
ቢያነበው እመክራለሁ፡፡ በያዝነው አጀንዳ ላይ በማስረጃ ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ እንዲኖር ስለሚያስፈልግ ሰፋ ተደርጎ የተቀመጠውን
ማስረጃ ከስር መሰረቱ ማቅረብን መርጫለሁ፡፡ አቶ ይልማ የኦሮሞን ህዝብ የመስፋፋት ታሪክ ሲያስረዱ በምስራቅ አፍሪካ
ከታየበት ዘመን ጀምረው እንዲህ ይተርካሉ፡፡

“ኦሮሞዎች ከመቼ ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ መኖር እንደ ጀመሩ፣እነሱ በዛ ስፍራ ከመስፈራቸው በፊት በቦታው የነበሩ ሰዎች
ማንነት በውል ባይታወቅም በ10ኛው ክፍለ ዘመን ሶማሌ የተባለው ነገድ ከታጁራ ሰርጥ አቅጣጫ ባነሳባቸው ተግዳሮት የተነሳ ወደ
ደቡብ እና ምስራቅ በመጓዝ በዋቢ ሸበሌና ጁባ ወንዞች መሃከል ቤናዲር በተባለው ስፍራ እና በቆላማው ባሌ ሰፈሩ፡፡ ኦሮሞዎች
ጥንታዊውን ሃገራቸውን ለቀው ከቤናዲር በቆላው ባሌ ከሰፈሩ በኋላ የፀጥታ ኑሮ ለማግኘት አልቻሉም፡፡ …..ከሰሜን ወደ
ደቡብ በተጓዙ ጊዜ በሰፈሩበት አገር በስተ ደቡብ ባንቱ የሚባሉ አርበኛ ነገድ ጎረቤት ሆኗቸው፡፡ ስለዚህ ከሰሜን
የሱማሌዎች፣ከደቡብ ባንቱዎች የሚያደርባቸው ጦርነት ምንም ጊዜ ሰላም የሰጣቸው አይመስልም፡፡ ስለዚህ ከዚህም ከአዲሱ
ሃገራቸው እንደገና መሰደድ ግዴታ ሆነባቸው፡፡……ጠብ አጫሪ ከሆኑት ከሶማሌዎች እና ከባንቱዎች ለመራቅ ይህ ሰላማዊ
የነበረው ህዝብ ዋቢንና የገናሌን ወንዝ ተከትሎ ወደ ደቡባዊ ኢትዮጵያ ወይናደጋ መሰደድ ጀመረ፡፡…….የኦሮሞ ህዝብ በስጋ
እና በወተት የሚመገብ [አርብቶ አደር] ስለነበረ ድርቅ ከሆነው ከቤናዲር አውራጃ ተጉዞ ወላቡ ወይናደጋ በገባ ጊዜ ይህች ምድር
ማርና ወተት ታፈሳለች እንደተባለችው እንደ ምድረ ከነዓን የምትቆጠር ሁና አገኟት፡፡ ኦሮሞዎች ወላቡ ብለው የሰየሙት አዲሱ
አገራቸው ብዙ ዝናብ የሚዘንብበት፣ ለምለም ምድር በመሆኑ ነድተው ላመጧቸው መንጋዎች ወሰን የሌለው ግጦሽ የሚበቅልበት
ሆኖ ተገኘ፡፡በወረዳውም ውስጥ ለሰውና ለከብት ወሰን የሌለው ውሃ የሚገኝበት ሃገር ነው፡፡……..ከሃገሪቱ ልምላሜ ሌላ
ይህ አውራጃ ጠብ ጫሪ ከሆነው ከሱማሌ ጎሳ፣ ከባንቱዎች ጉርብትና የራቀ በመሆኑ የወላቡ ሰፈር ለኦሮሞ ህዝብ ምድረ-ገነት
ሆኖ በሰላም፣ በምቾት ትዳራቸውን የሚያስፋፉበት ፋታ ሰጣቸው፡፡ ኦሮሞዎች በወላቡ የነበሩበትን ዘመን በማያቋርጥ ናፍቆት
በታሪካዊ ግጥማቸው እና ዝሙራቸው መዝግበውታል፡፡ወደ ደጋው በመሰደድ ምክንያት ከጦረኞች ስለራቁ ወደ ወይና ደጋው ከገቡ
ዘመን አንስቶ እስከ 16ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ ድረስ ጦርነት እና ውጊያ አልነካቸውም” (ይልማ ደሬሳ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ
ገፅ፣ 212-216)

ከዚህ ታሪክ የምንረዳው ኦሮሞዎችም እንደማንኛውም ህዝብ በሰዋዊው የመግፋት መገፋት፣መወረር መውረር፣ ማሰደድ መሰደድ
ማህበራዊ ህግ እየተገዙ የሰፈሩ ህዝቦች እንጁ አሁን ያሉበትን የኦሮሚያ ክልል መሬት ይዘው የተወለዱ ልዩ ፍጡራን እንዳልሆኑ ነው፡፡
በምክንያት ለሚያምን ይህ በራሱ ማንም ሰው የሚኖርበት መሬት ባለቤት የመሆን መብት እንዳለው አስረጅ ነው፡፡ ምክንያቱም
ያኔ ከቤናዲር መገፋት አብርሮ ያመጣው የኦሮሞ ህዝብ የሰፈረበት መሬት ባለቤት ሆኖ እየኖረ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ በሰፈረበት
መሬት ላይ ባለቤት ሆኖ፣ ከመሬቱ ስባት እያረሰ እያረባ ከኖረ ሌላው ህዝብ የሰፈረበት መሬት ባለቤት የማይሆንበት ምክንያት
ምንድን ነው? ኦሮሚያን እንገነጥላለን የሚሉ ፖቲከኞች ደግሞ ጭራሽ የኦሮሞ ህዝብ በሰፈረበት ለም መሬት ማረስ ማርባቱ
ስለማይበቃው መሬቱን ይዞ ይገንጠል ባዮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች የመገንጠሉን ነገር ሲያመቻቹ ኦሮሞ ያልሆነ በተለይ ደግሞ
ኦሮሚያን ወሮ ያዘ የሚሉት አማራው ከኦሮሚያ ምድር መውጣት እንዳለበት ሲያስገድዱ ሰው ወደ ገደል እስከመወርወር በደረሰ
ጭካኔ ነበር፡፡የዛሬው አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት ነች ዜማም የዚሁ ምክንያት አልቦ ተረክ ቅጅ ነው፡፡ ለራሱ ጎሳ ሲሆን ሰፋሪው
ወገን የሰፈረበት መሬት ሙሉ ባለቤትነት አንሶት መሬቱን ጠቅልሎ ይዞ የመገንጠል መብት እንዳለው የሚከራከር አካል ሌላ ሰፋሪ
ለፍቶ ደክሞ ባያቀናው ከተማ ባይትዋር እንዲሆን የሚፈልግ ከሆነ እንዴት መግባባት ይቻላል?

ወደ ታሪኩ ስንመለስ ኦሮሞዎች ቀደም ብለው ያደረጉት መስፋፋት መዳወላቡ እንዳደረሳቸው የሚነግሩን አቶ ይልማ ከቤናዲር በረሃ
ወደ በመዳወላቦ ምድረ-ገነት መጥቶ የሰፈረው የኦሮሞ ህዝብ አሁንም መስፋፋትን ግድ የሚል የህይወት ህግ ስለገጠመው
መስፋፋቱን እንደቀጠለ እንዲህ ከትበዋል፤ “ኦሮሞዎች ከላይ በተመለከትነው አኳኋን በወላቡ ዙሪያ ብዙ ትወልድ
ካሳለፉ በኋላ ከልክ ያለፈ ተራብተው ምድር ጠበባቸው ከደረቁ ቤናዲር ይዘዋቸው ወደ ወይናደጋው ያመጧቸው የቦረና ዘር ላሞች
ግጦሽ ከመላበት ከለምለሙ ወይና ደጋ በደረሱ ጊዜ አለመጠን ረቡላቸው፡፡ ስዚህ ኦሮሞዎች ከወላቡ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት
በግጦሽም መሬት እንደጠበባቸው አይጠረጠርም፡፡ ከዚህ ሌላ በጥንት ዘመን ከቀድሞ መኖሪያቸው ከአፍሪካ ቀንድ ወግቶ
ያስወጣቸው የሶማሌ ህዝብ አስራ አምስተኛው መቶ ሲጋመስ ከወይናደጋው ድረስ እየመጣ አዲሱን አገራቸውን መውረር
ጀመረ፡፡በዚህ አኳኋን የኦሮሞ ህዝብ ለመከላከል እና ለግጦሽ የሚፈልገውን መሬት አስፍቶ ለመያዝ ከሰላማዊ አኗኗር ወደ
አርበኝነት ሃሳቡን መለሰ፡፡….በዚህ ዘመን ኦሮሞዎች ከረዩ፣ቱለማ፣ሜጫ፣ወሎ በሚባል ትልልቅ ነገድ ተከፍለው ይገኙ ነበር፡፡
ስለዚህ ከረዩ የተባለው ነገድ ባሌን ፈጠጋርን ደዋሮን እንዲወር፤ ቱለማ ወደ ሰሜን ተጉዞ ዛሬ የሸዋ ኦሮሞ ምድር የተባለውን
እንዲይዝ ሜጫ በስተምዕራብ እና በስተደቡብ የሚገኘውን የኢናሪያዎችን አገር እንዲወስድና ወሎ የተባለው ነገድ በሸዋ
በስተምስራቅ ተጉዞ ከወሎ አውራጃ እስከ ትግሬ ተዘረጋውን አንጎት የተባለውን አውራጃ እንዲይዝ የተቀየሰው ኦዳ ነቤ በነበሩ ጊዜ
ነው፡፡ ነገዶቹ ሁሉ ወረራውን በአንድ ጊዜ አለመጀመራቸውን ስንመለከት የጦሩ ስልት የታቀደበትን አኳኋን በማስተዋል ስንመረምር
ከወረራው አስቀድሞ ጉዳዩ በስርአት የታሰበበት መሆኑን ልንገነዘብ እንችላለን፡፡” ገፅ፤225-226፡፡ ይህ ታሪክ ወደ ተነሳንበት
የአዲስ አበባ ባለ ልዩ ጥቅም ባለመብትነት/ባለቤትነት ጥያቄ ስረ-ነገር ይመራናል፡፡

ከላይ ያነበብነው ታሪክ በአፍሪካ ደረጃ ሳይቀር በታላቅነቱ የሚነሳው የኦሮሞ ህዝብ ወደ ሰሜን መስፋፋት ብዙ ሰው
እንደሚያስበው በግብታዊነት የተደረገ የግፋኝ ጉዞ ሳይሆን በወቅቱ በሰፊው ኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የነበሩ ጎሳዎች ተከፋፍለው፣
የቀዳሚ ተከታዩ የጊዜ ምጥነት ተደርጎለት፣ ማን በየት አቅጣጫ እንደሚሄድ በጥንቃ ድልድል የተደረገበት መስፋፋት ነበር፡፡በዚህ
ድልድል መሰረት የዚህ ፅሁፍ ስረ-ነገር የሆነው በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በመሃሉ የከተመችበት የሸዋ ኦሮሞ ክልልላዊ ግዛት
የተወረረው ቱለማ በተባለው የኦሮሞ ነገድ እንደሆነ ነው ከላይ ይልማ ደሬሳ የከተቡት ታሪካዊ ድርሳን የሚያስረዳው፡፡ ሌላው የታሪክ
ፀሃፊ ተክለፃዲቅ መኩሪያ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ” በሚል ርዕስ በፃፉት መፅሃፍ ገፅ 94-95
አቶ ይልማ በሰፊው ያቀረቡትን ታሪክ እንዲህ ያጠቃልላሉ “ነገር ግን ኦሮሞዎች እንደ ሱማሌዎች የኢትዮጵያ ሰፊ ግዛት ነው እያልን
በምንመካበት በደቡብ ኢትዮጵያ ከብዙ ዘመን ዠምሮ መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን በየምክንያቱ በመዠመሪያ ጊዜ
በጥቂቱ፤ በአፄ ልብነድንግልና በግራኝ መካከል በተደረገው ጦርነት ጊዜ ግን በየነገዳቸው እየተከፈሉ ኦሮሞዎች ቁጥራቸውን
አበርክተው ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ማኽል ሸዋ ወደ ዳሞት እና ወደ ጎጃም ወደ በጌ ምድር መግባታቸው የታወቀ ነው፡፡” ስለዚህ
የዛሬዋ አዲስ አበባ የተንጣለለችበት ግዛት ከኦሮሞዎች ጋር በመካከለኛው ዘመን (ከ1562 በኋላ) የተዋወቀ እንጅ የዘመናችን
አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች አዳም ሲፈጠር በኤደን ገነት እንደተገኘ እንደዛው ሁሉ በአዲስ አበባ ምድር የሰው ፍጡር ሲታይ ቀድሞ
የታየው ኦሮሞ ነው እንደሚሉት አይነት አይደለም! እንዲህ ታሪክ ተድበስብሶ ነው እንደግዲህ አዲስ አበባ ለኦሮሞ ቤት ለሌላው
የሰው ቤት ነች እየተባለ አስተዛዛቢ ሙግት እየተነገረ ያለው፡፡

አዲስ አበባ የኦሮሞ ንብረት በመሆኗ እንደ ማንኛውም በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኝ ከተማ ትተዳደር የሚለው ክርክር በስረጅነት
የሚጠቅሰው በታሪክ በውል ያልተደገፈው የኦሮሞ ህዝብ ቀደምት የአዲስ አበባ ነዋሪነት ታሪካዊ መብት አለው የሚለው ተረክ
ከላይ በተጠቀሰው፣ሸዋ ራሷ መቼ እና እንዴት በኦሮሞዎች እንደተያዘች በሚያስረዳው ታሪካዊ ማስረጃ ከእውነት የራቀ እንደሆነ
አይተናል፡፡ ሆኖም ለግራቀኙ ክርክር ንፅፅር እና ፍርድ እንዲመች አዲስ አበባ የኦሮሞ ቀደምት ቤት ነች የሚሉ ወገኖችን ማስረጃ
ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ አስረጅ ሲያቀርቡ ያጋጠመኝ የዚህ ክርክር ባለቤቶች “በ18ኛው ክፍለዘመን የአዲስ አበባ ነዋሪ ሁሉ መቶ
ፐርሰንት ኦሮሞ ነበር” የሚል ከላይ የተጠቀሰው የፀጋየ አራርሳ ገራሚ ክርክር ሲሆን ሌላው ዶ/ር ነጋሶ ሃምሌ 8/2009
ከወጣው ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ታሪክ ጠቅሰው ያቀረቡት ክርክር ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጋዜጠኛው “የአዲስ አበባ
እና ኦሮሞዎች በታሪክ ያላቸው ግንኙነት መቼ ነው የሚጀምረው?” ለሚለው ጥሩ ጥያቄ የመለሱት መልስ በአፄ ምኒልክ አባት
እና አያት ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ የተለመደው ታሪክን ከወገቡ የሚጀምር፣ የኦሮሞ እና የትግሬ ብሄርተኞች(ኦነግ እና ህወሃት)
ውሸትን ደጋግሞ እውነት የማስመሰል፣ ከምክንያታዊነቱ ይልቅ ማደናቆሩ የበዛ የብልጣብልጥነት መልስ ነው፡፡ ብዙ የሚዞረው
የዶ/ር ነጋሶ መልስ ነጥብ ያለው እንዲህ በሚለው ማሳረጊያው ላይ ነው “….አፄ ምኒልክ ቤተ-መንግስታቸውን አሁን
ወዳለበት ያመጡት ለፍል ውሃ ቅርብ ለመሆን ነው፤ እንጅ ቦታው ላይ ኦሮሞዎች በ16ኛው ክ/ዘመን ጀምረው ይኖሩበት ነበር፡፡
….. ቦታውን ምኒልክ ሲይዙት ብዙ የጎሳ መሪዎች ተገድለዋል፡፡ ጎሳ መሪዎቹ ተገድለው መሬታቸው ለቤተ-መንግስት
ሰዎች፣ለውጭ ሃገር ዲፕሎመቶች ነው የተከፋፈለው፡፡ በህይዎት የተረፉት ሸሽተዋል፡፡ ሆን ተብሎ በማፈናቀልም ወደ
አርሲ፣ባሌ፣አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረጉ አሉ፡፡ ባህሉና ቋንቋውም በክርስትና መስፋፋት ጠፍቷል፡፡” የዶ/ር ነጋሶ መልስ ከላይ
ለተነሳው የቀደምትነት ጥያቄ ልከኛ ማስረጃ የሚሆነው አለም የተፈጠረው፣ታሪክ የተቆጠረው ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ ቢሆን
ነበር፡፡ እውነታው ግን ያ አይደለም! አፄ ምኒልክ ፍል ውሃውን ከጓሮዋቸው ለማድረግ፣ ለባህር ማዶ ወዳጅ ሃገራት ኢምባሲ
ለመስራት የሃገሬውን ሰው አፈናቅለው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ተፈናቀሉ የሚባሉ ሰዎች ኦሮሞዎች ብቻ ስለመሆናቸው
ምን ማስረጃ ይቀርባል? የተፈናቀሉት ሰዎች ኦሮሞዎች ብቻ ነበሩ የሚለውን ብንቀበልስ ለመላው አዲስ አበባ የኦሮሞ ቀደምት
ርስትነት ማስረገጫ በምኒልክ ዘመን በፍል ውሃ አካባቢ ኦሮሞዎች የነበሩ መሆናቸው እና በምኒልክ መፈናቀላቸውን ብቻ
ማስረጃ አድርጎ ማረብ ማንን ያጠግባል? ዶ/ር ነጋሶ ሲቀጥሉ “….ሰሜን ሸዋ አሁን ላሎ ተብሎ ሚጠራው አካባቢ ለአዲስ
አበባ እጅጉን ቅርብ ነው፤ ስለዚህ አዲስ አበባ አካባቢ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኦሮሞዎች እንደ ነበሩ የሚታወቅ ነው ማለት ነው::”
ዶ/ር ነጋሶ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ላሎ የሚባል ቦታ ላይ ኦሮሞዎች ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ መኖራቸው በምን ስሌት አዲስ
አበባን የኦሮሞ ንብረት ያደርጋታል ብለው እንዳሰቡ ለኔ ግራ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ከ16ኛው ክፍለዘመን ጀምረው የአሁኑን የሸዋ
ኦሮሞን ግዛት እንደያዙ ታሪክም ከዶ/ር ነጋሶ ሃሳብ ጋር ይስማማል፡፡ እዚህ ላይመነሳት ያለበት ጥያቄ ግን 16ኛው ክፍለዘመን
የዘመን ጅማሬ አይደለምና በዚህ ሰዓት የወረረ አካል የሃገር ብቸኛ ባለቤት ነው ከተባለ ከዛ በፊት በቦታው የነበሩ የሰው ዘሮች
ባለቤት የማይሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ነው፡፡ለዚህ ክርክር አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲከኞች ሲያነሱ
የሚያጋጥመኝ መልስ ኦሮሞ በሚስፋፋበት ዘመን የሚይዘው መሬት ሰው ያልሰፈረበት ምድረበዳ እንደሆነ ነው፡፡ ይሄም
የሚያስኬድ አይደለም፡፡ የታሪክ መዛግብትን እንፈትሽ፡፡

የኦሮሞን ታሪክ የፃፉ ሌላው ፀሃፊ አለቃ አፅሜ “የኦሮሞ ታሪክ ክፍል አንድ” በሚለው መፅሃፋቸው ገፅ 171 ላይ ይህን ፅፈዋል
“…ኦሮሞ አማራን አባሮ ፈጅቶ፣ኢትዮጵያን ከትግሬ በቀር ወረሳት፡፡” ይህ ማስረጃ እኛ ከምናውቀው አባራሪ ተባራሪ ምድብ
ያፈነገጠ፤ አባራሪን (ኦሮሞ) ተባራሪን(አማራ) አድርጎ የዘመናችን ፖለቲካ በደመነፍስ ያስቀመጠውን የበዳይ ተበዳይ ድልድልን
ያቀያየረ ነው፡፡ ታሪክን ከወገቡ ጎምዶ የሚያቀርበው ወቅታዊ ፖለቲካችን የሃገራችን ብቸኛ ወራሪ አማራ የዘወትር ተባራሪ ደግሞ
ኦሮሞን አድርጎ ያቀርባል፡፡ ከጎማዳው ታሪክ እልፍ ሲሉ ያለው እውነታ ግን ሌላ ነው፡፡ የኑሮ ስንክሳር፣ የሃይል ሚዛን እንዲያባርር
ያስገደደው ሁሉ ያባርራል፣ ያፈናቅላል፡፡ሁሉም መውረር መወረር፤መስማማት መጣላት የኢኮኖሚ ጥያቄ፣የሃይል ሚዛን ጉዳይ
ነው! ባለበት ተገትሮ የሚቀር ነገር የለምና አባራሪም የተባራሪነት እጣ ይገጥመዋል፡፡ በዚህ ውስጥ ጎሳዊ ቅድስናው
ተባራሪ፣ጎጣዊ እርኩስነቱ አባራሪ የሚያደርገው የሰው ልጅ የለም፡፡ ስለዚህ ሁኔታ አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ በፃፉት እና ዶ/ር
ሥርግው ገላው አርትኦት በሰሩበት “የኢትዮጵያ ታሪክ” የሚል ርዕስ ባለው መፅሃፍ ገፅ 156 ላይ ይህን ፅፈዋል “…ያን ጊዜ
አማራ እና ኦሮሞ ሞጋሳ ተባብለው ቃል ኪዳን ተገባቡ፡፡ አማራ እና ኦሮሞ ከዚያ ወዲህ ተደባለቀ፡፡ያን ጊዜም ለሚመጣው
ለኋለኛው ዘመን ንግር ተነገረ፡፡ንግሩም እንዲህነው፡፡ኦሮሞ አማራን እያሳደደ ግቤን ወንዝ ባሻገረው በአማራ በዘጠነኛው በኦሮሞ
በአስረኛው ትውልድ ሲሆን ግፍ ብድር አይቀርምና ፈንታውን አማራ ኦሮሞን ያሳድደዋል ተብሎ ተነገረ፡፡ይህም ንግር ጊዜው
በደረሰበት ላይ በኋላ ይፃፋል”፡፡ ለማከል ያህል ፕ/ሮ ጌታቸው ኃይሌ “የአባ ባህርይ ድርሰቶች” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሃፍ ገፅ
123 እንዲህ ይላሉ “ኦሮሞዎች ወደ መሃል ኢትዮጵያ ገብተው የያዙት ሃገር ግራኝ ባዶ ያደረገውን ነው የሚሉትን የዛሬ ኦሮሞ ታሪክ
ፀሃፊዎችን የአባ ባህርይ ጥናት አይደግፈውም፡፡ ኦሮሞዎች ሃገር ሲወሩ ነባሩን ህዝብ እያጠፉና ኦሮሞ እያደረጉነበር…” አባ
ባህርይ ለዚህ ያቀረቡትን ነባራዊ አስረጅ እዚህ ለመፃፍ ስለማልችል አንባቢዎቼ መለስ ብለው እንዲያነቡ የተሸለ ነው፡፡ ከላይ
የተጠቃቀሱት ታሪካዊ ማስረጃዎች በኦሮሞዎች መስፋፋት ወቅት በሃገራችን የነበረውን አጠቃላዩን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱ
ናቸው፡፡ የዚህ ፅሁፍ ዋና ጉዳይ የሆነው የአዲስ አበባ እና የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ መስተጋብርን ከዚህ ከትልቁ ምስል የማይወጣ
በመሆኑ አንባቢ ከትልቁ ምስል አንፃር ደግሞ እንዲያየው በማሰብ ያመጣሁት ነው፡፡

የአጠቃላይ ነገሩን ማስረጃ እዚህ ላይ ልግታና የፅሁፉ ልብ የሆነው አዲስ አበባ የምትገኝበት የአሁኑ የሸዋ ኦሮሞ ግዛት በ16
ክ/ዘመን ኦሮሞዎች ሲወረር ባዶ መሬት ነበር/አልነበረም የሚለውን ወደመመርመሩ እንለፍ፡፡ የአቶ ይልማ ደሬሳን መፅሃፍ ገፅ
245 እንመልከት፡፡ “በ1562 ዓ.ም የሐንሩፋ ገዳ 8 አመት ተፈፅሞ ከአርባ አመት በፊት በሙዳና ገዳ ጊዜ ቡታ ያረደው
ትውልድ ልጆች ባለገዳ ለመሆን ደረሱ፡፡ ቡታ ባረዱም ጊዜ ገዳውን ሮበሌ ብለው ሰየሙት፡፡ በዚህ በሮበሌ ገዳ ጊዜ ትልቅ ዘመቻ
ያደረገው የቱለማ ጎሳ ነው፤ እላይ እንደተመለከትነው ሁሉ ከረዩዎች ወደ ምስራቅ፤ መጫዎች ወደ ምዕራብ፤ ወሎዎች ወደ
ምስራቅ ሰሜን መጓዛቸውን ስናትት ቱለማዎችን ኦዳ ነቤ ላይ ተውናቸው፡፡ በ1562 ዓም ቱለማዎች ከኦዳ ነቤ ዙሪያ ተነስተው
ሸዋን ለመውረር በተጓዙ ጊዜ በአዝማች ዘረ ዮሃንስ የተመራ የንጉሠ ነገሥት ጦር መንገድ ላይ ጠብቆ ገጠማቸው፡፡ ከጦርነቱም
ላይ አዝማች ዘረ ዮሐንስ ሞቱ፤ሰራዊቱም ተሸነፈ፡፡ በዚያን ጊዜ ሮበሌ ባለገዳዎች የሸዋና የጎጃም መንገድ እንደተከፈተላቸው
ቆጥረው በግስጋሴ ወደ ፊት ተራምደው ዛሬ የሸዋ ኦሮሞ ምድር ከተባለው አገር ላይ ሰፈሩ፡፡” ከዚህ የምንረዳው ቀላሉ ነገር
ኦሮሞዎች የአሁኑን የሸዋ ኦሮሞ ግዛት ሲወሩ በቦታው ሌሎች ሰፋሪ ህዝቦች እንደነበሩ ነው፡፡ ህዝቦቹ ገዥ ንጉሰ-ነገስት የነበራቸው
ነገር ግን የኦሮሞዎቹ ጉልበት ስለጠናበት ወረራውን መቋቋ የተሳነው በመሆኑ ሳይወድ በግድ መወረሩን የተቀበለ እንደሆነም
እንረዳለን፡፡ ይህ የመውረር መወረር ክስተት ያለና የነበረ በመሆኑ በታሪክ ሁነትነቱ ከመቀበል ሌላ ትርጉም ያለው ነገር የለም፡፡
ኦሮሞዎቹ በሸዋ ምድር ከመስፈራቸው በፊት የነበሩ ህዝቦችን ማንነት የማፈላለግ ስራ-ፈት ጥያቄ አንስቼ፣ የአዲስ አበባ
ባለቤቶች ኦሮሞዎች ሳይሆኑ ከነሱ በፊት በንጉስ እንቶኔ ሲመሩ የነበሩት የእንትን ጎሳ ሰዎች ናቸው የሚል አዋጭ ያልሆነ ክርክር
ውስጥ መግባት አልፈልግምና የታሪክ መዛግብት ምርመራየን እዚህ ላይ ልግታና እስካሁን ያየናቸው የታሪክ መዛግብት
የሚያቀብሉን መረጃ ከወቅታዊው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ጋር ያለውን መስተጋብር ላንሳ፡፡

ይሄን ሁሉ ያነጋገረን ጉዳይ አዲስ አበባ በታሪክ ቀደምት ነዋሪዎቿ ናቸው የተባሉት የኦሮሞዎች ንብረት መሆን እንዳለባት የሚነሳው
ክርክር ነው፡፡ ይህ በታሪክ መነፅር ሲፈተሸ ኦሮሞዎች እና አዲስ አበባ የምትገኝበት ሸዋ የተዋወቁት በ1562፣ ኦሮሞዎች
ቀድሟቸው በአካባቢው ተገኝቶ፣ አገዛዝ መስርቶ የነበረን የንጉሰነገስት ጦር አሸንፈው አካባቢውን በመውረራቸው ሳቢያ እንደሆነ
አረጋግጠናል፡፡ ስለዚህ ኦሮሞ የአዲስ አበባ ቀደምት ነዋሪ ነው በሚለው ከእውነት የራቀ ክርክር ላይ ተቁሞ የሚነሳው ኦሮሞ
ህዝብ የበለጠ የአዲስ አበባ ባለቤትነት መብት ይከበርለት የሚለው ጥያቄ የማያስኬድ ነው ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በግሌ
የቀደምት ነዋሪነት ክርክር ራሱ ሳይንሳዊ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ቀደምት የምንለው ታሪክ ራሱ ሌላ ቀደምት አለውና
ዘመንን ከሚመች ቦታ ጀምሮ ቆጥሮ እኔ ቀደምት ነኝ ሚለው ክርክር ትርጉም የማይሰጥ ነው፡፡የሆነው ሆኖ የቀደምትነቱ ጨዋታ
ቀደምትነትን ከሚመቻቸው ቦታ ለሚቆጥሩ አካላት ሌላ የቀደምትነት አቅርቦት ስላለው እዳው ገብስ ነው፡፡

ከባዱ ነገር የቀደምትነት የታሪክ ልቃቂተ ሲጎለጎል፣የታሪክ ሃቅ ከፈለጉት ቦታ አንስቶ ወዳልፈለጉት ቦታ ሲያስቀምጥም
የቀደምትነቱን ዜማ እንደያዙ መቆየቱ ነው፡፡አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች የቀደምትነት ውሽልሽል ክርክራቸው ላይ
ተመስርተው የአዲስ አበባ ባለቤትነትን ጥያቄ ሲያነሱ የሚወክሉት የራሳቸውን ስስታምነት እና የስነልቦና ቀውስ እንጅ በጉዲፈቻ
ላሳደገው ልጅ ሃብት ንብረቱን ከወለደው ልጅ እኩል የሚያካፍለውን የኦሮሞ ህዝብ ስነልቦና አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች
ቀደምት ነዋሪነትን ጠቅሰው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ይገባናል ካሉ ከአዲስ አበባ ቀድመው መጠየቅ ያለባቸው ታሪክ ሲገለጥ
የኦሮሞ ህዝብ ከአዲስ አበባም ከመዳወላቡም ቀድሞ ይኖርበት የነበረውን በረሃማውን የቤናዲርን ግዛት ነው፡፡ ይህን ግን
አያደርጉም፡፡ ምክንያቱም ያልሆነውን የቀደምትነት ጥያቄ ያስነሳቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የለፋበት የአዲስ አበባ ወቅታዊ
መንቆጥቆጥ እንጅ እነሱ የሚሉት፣ ታሪክ ግን የማያውቀው የቀደምትነትን ነገር አይደለም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች የአዲስ አበባ
ባለቤትነታቸውን ለማስረገጥ የሚጠቅሱት የታሪክን መዝገብ ብቻ ስላልሆነ በህገመንግስታዊ እና መልከ-ዓምድራዊ ማስረጃዎች
ላይ ተመስርተው የሚያነሱትን ሙግቶች ለማጠየቅ ደግሞ ለሚቀጥለው እትም ላሳድረው፡፡

ጸሀፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል:: meskiduye99@gmail.com

___
በዚህ ድረ ገጽ መጣጥፍ ለማውጣት በሚከተለው አድራሻ ኢሜይል ያድርጉልን። editor@borkena.com

ሆድ ያባውን ቻርተር ያወጣዋል (መስከረም አበራ)

ByAdmin

መስከረም አበራ
ነሃሴ 8 2009 ዓ ም

Meskerem Abera - article
መስከረም አበራ

በሃገራችን መንግስዊ ስልጣን ላይ መሰየሙ ለኢህአዴግ ከሰጠው ጥቅም አንዱ የፈለገውን ፖለቲካዊ አጀንዳ ለእርሱ የፖለቲካ ትርፍ የሚጠቅመው በመሰለው ወቅት እና ሁኔታ አንስቶ ወደ ጠረጴዛ ማምጣቱ ነው፡፡ አለቅነቱ ያመጣለትን በጎ ሁኔታ በመጠቀም ኢህአዴግ እሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ወደ መረሳት በተጠጋ መልኩ ሲያድበሰብሰው የኖረውን ለኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የተሰጠ ህገ-መንግስታዊ መብት ጉዳይ ዛሬ ትኩስ አድርጎ እነሳው ይገኛል፡፡ የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ሊኖረው ይገባል ተብሎ በህገ-መንግስት የተሰጠውን መብት አፈፃፀም አስመልክቶ መንግስት ያወጣውን ረቂቅ አዋጅ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡ዶክመንቱ በመንግስት ይፋ ከመደረጉ በፊት ጉዳዩን አስመልክቶ ማን እንዳወጣው ያልታወቀ ዝርዝር አንቀፆችን የያዘ ሰነድ በተለያዩ ድህረገፆች ተለቆ፣ በሰፊው ተነቦ፣ እጅግ ሲያነጋገር ሰንብቶ ነበር፡፡ዶክመንቱ በተለይ በውጭ ሃገር የከተሙ የኦሮሞ ምሁራንን ቀልብ የሳበ የመነጋገሪ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል፡፡

ኢህአዴግ መራሹ የሃገራችን መንግስት ለእሩብ ምዕተ አመት ዝም ብሎት የቆየውን አጀንዳ ዛሬ ለምን ማንሳት ፈለገ? የሚለው ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ እርግጠኛውን መልስ የሚያውቀው መንግስት ራሱ ቢሆንም መላምቶችን መሰንዘር ግን ይቻላል፡፡ መንግስት የአዲስ አበባ መስተዳድርን ከኦሮሚያ አጎራባች ዞኖች ጋር አቀናጅቶ ለማልማት የሚያስችል እቅድ አውጥቼ ተግባራዊ አደርጋለሁ በማለቱ ባለፈው አመት ከኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው “በቃ ትቼዋለሁ” ማለቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከሚታወቅበት ማድረግ የፈለገውን ሳይደርግ እንደቅልፍ ያለመተኛት ባህሪ አንፀር ነገሩን በአፉ እንዳወራው እርግፍ አድርጎ ይተወዋል ማለት ያስቸግራል፡፡ እናም ከአንድ አመት በኋላ ይህን ዶክመንት ይፋ ማድረጉ፣ በዶክመንቱ ውስጥ የተዘረዘሩ ሃሳቦች የኦሮሚያ አጎራባች ዞኖችን ከአዲስ አበባ ጋር በተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለማቆራኘት የታለሙ አንቀፆች ከመኖራቸው፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ወሰን አሁንም በቁርጥ ያልተቀመጠ ከመሆኑ፣የአዲስ አበባ አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖች የሚኖሩ አርሶ አደሮች መሬቱ ለልማት ከተፈለገ ካሳ ይከፈላቸዋል እንጅ መነሳታቸው አይቀርም ከሚለው የአዋጁ ክፍል ጋር ሲጣመር የአፈፃፀም አዋጁ ለረዥም ወራት ተቆጥቶ የነበረው የክልሉ ህዝብ ከአንድ አመት ገዘፍ ያለ እስር፣እጎራና እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካመጠው ድንጋጤ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያለውን ስሜት ለመለካት ያለመ ትልቅ የግመታ ተልዕኮ ያነገበ ይመስላል፡፡

ሌላው መላምት አቶ ጌታቸው ረዳ ‘እሳት እና ጭድ የሆኑ ቡድኖች አንድነት ያሳዩት እኛ ስራችንን ስላልሰራን ነው’ ካሉት ንግግር ጋር ይቆራኛል፡፡ከአመት በፊት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ባልተለመደ ሁኔታ የትብብር ዝንባሌ ማሳየታቸውን ኢህአዴግ በበጎ ጎኑ እንዳልተመለከተው፤ይልቅስ የመንግስቱ ድክመት ያመጣው ክፉ ውጤት አድርጎ እንዳሰበው የአቶ ጌታቸው ንግግር ምስክር ነው፡፡ በዚህ ግንዛቤ ውስጥ የከረመው የኢህአዴግ መንግስት ታዲያ “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” የምትል ከዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ጋር ክፉ ፀብ ያላት ሃረግ ያዘለ አዋጅ አስነግሯል፡፡ “ልዩ ጥቅም” የሚለው ቃል “Privilege” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይወክላል፡፡ ይህ ቃል ደግሞ የዲሞክራሲ ዋና ከሆነው የዜጎች እኩልነት መርህ ጋር በእጅጉ ይጣላል፡፡ዲሞክራሲ በሰፈነበትም ሆነ ወደ ዲሞክራሲ እያመራ ባለ ሃገር የአንድ ወገን ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር ማንሳት ወደ ሰሜን ለመሄድ ተነስቶ ወደ ደቡብ እንደ መንጎድ ያለ አልተገናኝቶ ነገር ነው፡፡ ለኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚያስገኘው አዋጅ መነሾ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት ነው ሲባል የህገ-መንግስቱ ምንጭስ ማን ነው? ወደ ሚለው ወሳኝ ጥያቄ ይመራል፡፡

ህገ-መንግስቱ እርሾ የሆነው የሽግግር ዘመኑ ቻርተር በሻዕብያ፣በህወሃት እና በኦነግ ለተፈጠሩበት አላማ እንዲያገለግል ሆነኖ ተቦክቶ ተሰልቆ ካለቀ በኋላ፤ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ህገመንግስት ይሆን ዘንድ በህገ-መንግስት አርቃቂ ኮሚሽኑ በኩል ለህዝብ ውይይት ይቅረብ የተባለው እንደው ለቡራኬ ያህል ብቻ እንደሆነ በወቅቱ የነበሩ እንደ አቶ አሰፋ ጫቦ ያሉ ፖለቲከኞች ይመሰክሩት የነበረ ሃቅ ነው፡፡ ህወሃት ኦነግ እና ሻዕብያ የሽግግር ዘመኑ አድራጊ ፈጣሪዎች እንደመሆናቸው ህገ-መንግስቱን ባዋለደው በዚህ ወሳኝ ወቅት እነዚህ “ሶስቱ ኃያላን” ያልወደዱት አካል ለምሳሌ የአማራው ብሄር እና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት አቀንቃኝ ዜጎች ሃሳብ ፣እምነት እና ፍላጎት በቅጡ አልተወከለም፡፡ስለዚህ የህገ-መንግስቱ አረቃቅም ሆነ ኢትዮጵያ ከሽግግር መንግስት ወደ ተመራጭ መንግስት ተዘዋወረች የተባለበት ሂደት የኢትዮጵያን ህዝብ ሁሉ የወከለ አካሄድ አልነበረም፡፡ይህን የሂደቱ ዋና ተዋናይ የነበሩት ዶ/ር ነጋሶም ደግመው ደገግመው የሚመሰክሩት ብቻ ሳይሆን የሂደቱ አካል “በመሆኔም እፀፀታለሁ” ያሉበት ነው፡፡

ህገ-መንግስቱ የረቀቀበት መንገድ እንዲህ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ቢሆንም ኢህዴግ ስህተት እንደሌለው መለኮታዊ መዝገብ ቆጥሮት የህገ-መንግስቱን ስም ስንቅ አድርጎ ወሳኝ የፖለቲካ ቁማሮችን በአሸናፊነት ይወጣበታል፡፡ራሱን ህጋዊ ባላንጦቹን ህገ-ወጥ አድርጎ ህግን በመናድ ከሶ ዘብጥያ ያወርድበታል፡፡ ያሰበውን ለማድረግ እንደ እጁ መዳፍ በሚያውቀው ህገ-መንግስት የተፃፈውን መጥቀስ ቀርቶ ከዛም በላይ የሚሄደው ኢህአዴግ በዚህ አዋጅም ያየነው የተለመደውን ማንነቱን ነውና እግዚኦ የሚያስብል ነገር የለውም፡፡የሚገርመው ነገር ያለው ሌላ ቦታ ነው- በአክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ፖለቲከኞች መንደር፡፡

ከስራው አንድ አፍታ የማይዘናጋው፣ የሚያተርፍበት የመሰለውን የፖለቲካ ቁማር አጥብቆ በመያዝ የሚታወቀው ኢህአዴግ ለኦሮሚያ ክልል ከሃያ አምስት አመት በፊት የማለላትን በአዲስ አበባ ላይ የልዩ መብት ባለቤት የመሆን ቃል ለመፈፀም አዋጅ አውጥቻለሁ ሲል በገራገርነት ቃሉን ለማክበር አስቦ ብቻ አይመስልም፡፡እንደሚታወቀው መንግስት ይህን ረቂቅ አዋጅ ያወጣው ፓርላማው ለእረፍት በሚዘጋበት ወቅት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት በአዋጁ ዙሪያ ከህዝቡ የሚነሱ አስተያቶችን፣ የፖለቲከኞችን አሰላለፍ በማጤን ራሱን የፖለቲካ ትርፍ በሚያጋብስበት መስመር ለማሰለፍ ነገሮችን የማጤኛ ጊዜ ለማግኘት ይመስለኛል፡፡ይህን ይበልጥ የሚያስረዳው አቶ ለማ መገርሳ ደግመው ደጋግመው አዋጁ ለውይይት ክፍት ነው እንጅ ያለቀለት አይደለም ሲሉ መሰንበታቸው ነው፡፡ በተጨማሪም መንግስት በቴሌቭዥኑ የአፈፃፀም አዋጁን ከማወጁ በፊት ቀደም ብሎ ባለቤቱ ያልታወቀ ዶክመንት በማህበረዊ ድህረገጾች እንዲከላወስ ሲደረግ፣ብዙ ሲያነጋግር መንግስት አለሁበትም የለሁበትምም ሳይል ድምጹን አጥፍቶ የነገሮችን አካሄድ ሲከታተል ሰነበተ፡፡ከርሞ ከርሞ በቴሌቭዥኑ ያስነገረው አዋጅ የወጣበት ጊዜም እንዲሁ በድንገት የተደረገ አይመስለኝም፡፡ በዚሁ ጊዜ ትቂት የማይባሉ የኦሮሞ ብሄር ፖለቲከኞች ሰተት ብለው ወደ ወጥመዱ ውስጥ ሲገቡ በሰነዱ ውስጥ እጅግ የተገለለው፣እንደሌላ ሊቆጠር ምንም ያልቀረው የኢትዮጵያ ብሄርተኝት አቀንቃኙ አካል ዝምታን መርጦ ከኢህአዴግ ጋር ካብ ለካብ መተያየቱን መረጠ፡፡አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ አራማጆች ብቻ ሳይሆን ምሁራን ጭምር ባለቤቱ እንኳን በውል ባልታወቀ ሰነድ ዙሪያ አስደንጋጭ የክርክር ነጥቦች ያዘሉ ረዣዥ ክርክሮች አምጥተው ራሳቸውን ለግምት አደባባይ አሰጡ፡፡ምሁራን ተብየዎቹ በመገናኛ ብዙሃን(በኦ.ኤም.ኤን እና በቪኦኤ) ቀርበው ሲወያዩ በጆሮየ የሰማኋቸውን እና የገረሙኝን ብቻ ላንሳ፡፡

“የባለቤትነት” እና “የልዪ ጥቅም” እሳቤዎች ንትርክ

ባለቤቱ ያልታወቀው ሰነድ የአዲስ አበባ አደባባዮችን ለመጠቀም ሳይቀር የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች በአዲስ አበባ ለሚጠይቁትን ነገር ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል በሚሉ አንቀጾች ተሞላውን ሰነድ እየጠቀሱ ይህ እጅግ ትንሽ ነገር እንደሆነ እና በአዲስ አበባ ላይ ባለቤት የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ እንደ እንግዳ ቆጥሮ በገዛ ቤቱ ሊያስተናግድ እንደሞከረ ደፋር እንግዳ ቆጥረው አብጠልጥለውታል፡፡መሆን ያለበትን ሲያወሱም ከዶክመንቱ ስያሜ ጀምሮ መሆን ያለበት የባለቤትነት አዋጅ እንጅ የልዩ ጥቅም አዋጅ መሆን እንደሌለበት ነው፡፡ተከራካሪዎቹ ሲያክሉም በአዲስ አበባ የሚኖር ማንኛውም ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የሆነ ተቋምም ሆነ ሌላ አካል የሚኖረው በኦሮሚያ ምድር መሆኑን እንዲያስታውስ፣ትንሽም ብትሆን አመታዊ ግብር ለኦሮሚያ ክልል መክፈል አለበት፣ ቀረጥ እና ግብር በሚከፈልባቸው የጉምሩክ ጣቢዎች ላይም በርከት ያሉ ኦሮሞ ተወላጆች ሊታዩ ያስፈልጋል፣ አዲስ አበባ ራሷም መተዳደር ያለባት በኦሮሚያ ክልል ስር እንጅ በፌደራል መንግስቱ ስር መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ሌላው አስገራሚም አስቂኝም የሆነው የክርክር ነጥብ ጭብጥ ደግሞ ይህን ይላል፤ ‘አሁን አዲስ አበባ የሚኖረው አብዛኛው ሰው የከተሜነት ዲሲፕሊን የሚያንሰው፣በሌሎች ዓለማት ያሉ የከተማ ነዋሪዎች የተላበሱት ትህትና የሚጎድለው፤ ለኦሮሞ ባህል እና ማንነት ክብር ለማሳየት የሚለግም ነው፡፡ ይህ ዝንባሌ መስተካከል አለበት፡፡በአዲስ አበባ መኖር የሚቻለው ባለቤቱን የኦሮሞ ህዝብ እስካበሩ ብቻ ነው፡፡ ይህን እስካደረገ ድረስ መኖር ይችላል ካልሆነ ግን አዲስ አበባን ለባለቤቶቿ ለቆ ሌላ ሰፊ ቦታ ፈልጎ አዲስ ዋና ከተማ መመስረት ነው፤አዲስ ሚመሰረተውን ዋና ከተማ ኦሮሚያ ላይ ማድረግም ይቻላል፡፡’ ይሄ ኦነግን አደቁኖ ካቀሰሰው ‘የውጡልኝ ከሃገሬ’ ፖለቲካዊ ፈሊጥ የተቀዳ ነው፡፡ ወንድም ህዝብን ማግለልን እንደ ፖለቲካ ስኬት ዳርቻ የሚቆጥረው የኦነግ መናኛ ፖለቲካዊ አካሄድ ፓርቲውን እድሜ ብቻ አድርጎት እንደቀረ ተረድቶ ራመድ ማለት ፖለቲካዊ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ኦነግ እንኳን ብሎት ብሎት አልሆን ሲለው የተወውን ውራጅ ፖለቲካ ትርክት አንግቦ መንገታገት ራስን የፖለቲካ ማስፈራሪያ ከማድረግ፤ ቆምኩለት የሚሉትን ህዝብም በጥርጣሬ ከማሳየት ያለፈ ጥቅሙ አይታየኝም፡፡

የዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ‘አዲስ አበባ የኦሮሞ ህዝብ የብቻ ታሪካዊ እርስት ነች’ የሚለውን አስገራሚ እሳቤ ብንቀበል እንኳን ቀደምት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው የተባሉት ኦሮሞዎች መኖሪያ የነበረችው አዲስ አበባ እና የአሁኗ አዲስ አበባ የተለየች መሆኗን ማገናዘብ ይህን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ከባዱ ነገር ከላይ ባሉት ተከራካሪዎች መጤ ይሁን ሰፋሪ እየተባሉ ያሉት ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች ላባቸውንም እድሜያቸውንም ጨርሰው ያቀኗትን አዲስ አበባን ጥለው ወደ መድረሻቸው ይድረሱ፤ ወይም ሌላ ረባዳ መሬት ፈልገው የሃገራቸውን ዋና ከተማ ይመስርቱ የሚለው ሃሳብ ይሰምርልኛል ብሎ ወደ አደባባይ ይዞ መቅረቡ ነው፡፡ከሰሞኑ በቪኦኤ ቀርበው የሚከራከሩ ዶ/ር ኃ/መስቀል የተባሉ ሌላ የኦሮሞ ምሁር ደግሞ ሌላ ክርክር ያመጣሉ፡፡ ሰውየው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃረርም፣ በድሬዳዋም፣በሞያሌም ላይ ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሊከበርላት ይገባል ሲሉ በህገ-መንግስቱም ያልተጠቀሰ ሰፋ ያለ ፍላጎት ያለው ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የሰውየው ክርክር መነሾው እነዚህ ከተሞች ኦሮሚያ ክልል መሃል ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ሐምሌ 8/2009 ከወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃል-ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ነጋሶ ሃረርም በኦሮሚያ መሃከል ስለምትገኝ በሚል ኦነግ በሽግግሩ ወቅት የኦሮሚያ ክልል በከተማዋ ላይ ልዩ መብት እንዲኖረው ጥያቄ አቅርቦ ምክንያቱን በማላውቀው ነገር ህገመንግስቱ ውስጥ ሳይካተት ቀርቷል ይላሉ፡፡፣

ከላይ የተነሱት የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች እና ምሁራን የክርክር ነጥቦች ሲጠቃለሉ አሁን ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ያላትን መብት የባለቤትነት እንጅ የልዩ ጥቅም ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡የኦሮሚያን ህገመንግስታዊ ልዩ መብት ለመተግበር ወጣ የተባለው ረቂቅ አዋጅም መቃኘት ያለበት ከዚሁ አንፃር ነው የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተቃራው የቆመው፤ የአዲስ አበባ ነዋሪም ሆነ ከተማዋን እንደ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት አንድያ መገለጫ ምድር አድርጎ የሚያስበው ዜጋ ይህን የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞችን እና ምሁራን ክርክር ትዝብትም፣ጥርጣሬም፣ድንጋጤም ባጠላበት ዝምታ ነው ያስተዋለው፡፡እንደውም ከነዚህ አይነት የኦሮሞ ብሄርተኞች ይልቅ ቢያስ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በአዲስ አበባ እንዲኖር የፈቀደው ኢህአዴግ እጅግ የተሻለ እንደሆነ ቢታሰብ የሚገርም ነገር የለውም፡፡ የኢህአዴግ እቅድም ይኽው ነው – ለመገመት የተዘጋጀን ማስገመት፤ በዚህ ውስጥ ራሱን የተሻለ መድህን አድርጎ ማሳየት! ሲቀጥልም ለአንድ ሰሞን ሲሰማ የነበረውን የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦችን የትብብር ድምፅ በነዚህ የኦሮሞ ምሁራን እና ፖለቲከኞች ድምፅ በመተካት ሃያ አምስት አመት ሲሰበክ የኖረውን የጥርጣሬ እና የመፈራራት መንፈስ መልሶ በቦታው እንዲተካ ማድረግ ነው፡፡አቶ ጌታቸው ረዳ ኢህአዴግ ቸል አለው ያሉት የቤት ስራም ይሄው ሳይሆን አይቀርም፡፡

አንድም አፍታ ከስራው መዘናጋትን የማያውቀው ኢህአዴግ ይህን ቻርተር ይዞ ብቅ ሲል የኦሮሞ ምሁራንም ቻርተሩ ይስመር አይስመር እንኳን በውል ሳያጤኑ ሆዳቸው ያባውን ሁሉ ትዝብትን ሳይፈሩ አውጥውታል፡፡ ጭራሽ የኦሮሞ ህዝብ አንድ አመት ሙሉ ሲሞትለት የኖረው ጥያቄ አዲስ አበባን በባለቤትነት የማስተዳደር ጉዳይ ብቻ እንደሆነ ለማድረግም ይቃጣዋል ክርክራቸው፡፡ባለፈው አመት የኦሮሞ ህዝብ አምርሮ ሲያነሳው የኖረው አንገብጋቢ ጥያቄ ከኖረበት ቀየው በድንገት ባዶ እጁን ወይም እፍኝ በማትሞላ ካሳ መፈናቀሉን በመቃወም እንጅ አዲስ አበባን ለኦሮሞ ቤት ለሌላው የሰው ቤት ለማድረግ አልነበረም፡፡የልሂቃኑ ክርክር እና የአገሬው ኦሮሞ ችግር እና ፍላጎት ይህን ያህል አልተገናኝቶ መሆኑ ግር ያሰኛል፡፡ከሃገር ርቀው እንደመኖራቸው ሃገርቤት ያለውን ኦሮሞ መሰረታዊ ጥያቄ ለማወቅ ይቸገራሉ ቢባል እንኳን ቆምኩለት ከሚሉት” ህዝብ የልብ ርትታ እንዲህ እጅግ መራራቁ ጤናማ አይመስልም፡፡

አክራሪ የኦሮሞ ብሄረተኝነት ፖለቲከኞች ደጋግመው የሚያነሱት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ሊኖራት ይገባል የሚሉት የባለቤትነት መብት ጥያቄ ማስረጃ አድርገው የሚያነሷቸው ነጥቦች ወደ ሶስት ማጠቃለል ይቻላል፡፡ አንደኛው እና ለተቀሩት መከራከሪያ ነጥቦች መሰረት የሚሆነው ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ ቀደምት ህዝቦች ናቸው የሚለው ትርክት ነው፡፡ለዚህ ትርክት ከማለት ባለፈ በበቂ ታሪካዊ መዛግብት የተደገፈ ማስረጃ ከተከራካሪዎች ሲቀርብ አላጋጠመኝም፡፡ ይልቅስ ከዚህ እሳቤ በተቃራኒው የቆሙ ተከራካሪዎች የተሻለ የታሪክ ማስረጃ አቅርበው ይከራከራሉ፡፡ሁለተኛው የሃገራችን ህገ-መንግስት ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ መብት እንዲኖራት ስለሚያዝ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ሶስተኛው የክርክሩ ማስረጃ አዲስ አበባ(ሐረር፣ድሬዳው፣ሞያሌ ጭምር የሚሉ ተከራካሪዎችም አሉ)በኦሮሚያ ክልል መሃል የምትገኝ በመሆኗ ከኦሮሚያ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን ስለምትጠቀም፣ከተማዋ ለውጋጆቿ መዳረሻም አጎራባች የኦሮሚያ ዞኖችን ስለምትጠቀም ኦሮሚያ በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም ያስፈልጋታል የሚል ነው፡፡ እነዚህ የክርክር ማስረጃዎች ተደርገው የቀረቡ እሳቤዎች ራሳቸው ሊጠየቁ የሚገቡ በመሆናቸው በሚቀጥለው እትም እመለስባቸዋለሁ፡፡

ጸሀፊዋን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል:: meskiduye99@gmail.com

Updated: June 19, 2017

የዕብድ ገላጋዩ ሪፖርት (መስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

መስከረም አበራ
meskiduye99@gmail.com
ሚያዚያ 24 2009 ዓ ም

ዲሞክራሲ ባልሰፈነበት ሃገር ሰብዓዊ መብት ይከበራል ማለት ዘበት ነው፡፡ እንዲህ ባለው ስርዓት የዲሞክራሲም ሆነ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ገለልተኝነት ወይም ነፃነት መጠበቅ ከዓለት ላይ ውሃ የማፍለቅን ተዓምር እንደ መሻት ያለ ቀቢፀ-ተስፋ ይሆናል፡፡ሃገራችን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቻርተሮች ፈራሚ እንደመሆኗ የዓለም አቀፍ ህግጋቱን አንቀፆች አሁን በሥራ ላይ ባለው ህገ-መንግስቷ አካታለች፡፡‘ዲሞክራትም ልማታዊም ነኝ’ የሚለው ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ይህን ማድረጉ ብቻ በቂ ስለሚመስለው ወይም እንዲመስለን ስለሚፈልግ ቀደምት ገዥዎች ባላደረጉት ሁኔታ ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት ሰጥቶ የህገመንግስት አካል ማድረጉን ደጋግሞ ሲያወራ አይሰለቸውም፡፡ሆኖም በተግባሩ የሰብዐዊ መብት ጉዳይ በገለልተኛ እና እውነተኛ ተቋም እንዲመራ አይሻም፡፡በማስመሰሉ ዘመን እያቃረውም ቢሆን ይሁን ብሎ ህልውናውን የፈቀደለት ኢ.ሰ.መ.ጉ የተባለውን ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም በህግ፣ በጠመንጃ፣በበጀት ድርቅ ጥምር ጉልበት አዳክሞ እነሆ ዛሬ እልም ስልም በሚል ህልውና ውስጥ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

ኢ.ሰ.መ.ጉን መላወሻ አሳጥቶ ወደ አለመኖር እያንደረደረው ያለው ኢህአዴግ ታዲያ ብዙ ያወራለት “የሰብአዊ መብት ዘበኝነት” ወጉም እንዳይቀርበት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚባል ድርጅት ሰይሞ የልቡን ይናገርለት ዘንድ በፓርላማ ያመላልሰው ይዟል፡፡ኮሚሽኑን የሚመሩት ዶ/ር አዲሱ ገ/ማርያም ቀደም ሲል የሃገሪቱን ምርጫ ቦርድ ይመሩ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ሰውየው ምርጫ ቦርድን በሚመሩበት ጊዜ በኢ.ህ.አ.ዴግ ነገር አንጀታቸው የማይጠና፤ ክፉውን ማውራት የማይወዱ ከመሆናቸውም ባሻገር አንዳንዴ የሚመሩትን ተቋም ገለልተኝነት ዘንግተው ለመንግስት ወገባቸውን ይዘው ለመከራከርም ሲሞክራቸው ያጋጥማል፡፡ በተለይ በምርጫ ሰሞን ተቃዋሚዎች ለሚያቀርቧቸው አቤቱታዎች ሁሉ መረጃው እዳልደረሳቸው፤እንዲህ ያለ ነገር ይፈጠራል ብለው እንደማያስቡም ፈርጠም ብለው ይናገራሉ፡፡በአንፃሩ የተቃዋሚዎችን ድካም ያሳያል ለሚሉት ነገር ሁሉ ከበቂ በላይ በመረጃ ታጥቀው ይመጣሉ፤ስንት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ሲገባቸው ስንተ ጊዜ ብቻ እንዳደረጉ ደንቀፍ ሳይላቸው ይናገራሉ፡፡ ፓርቲዎቹን ከህይወት መዝገብ ለመሰረዝ ባበቃቸውን “ውስጣዊ ሽኩቻ”፣የትኛው አንጃ ህግ ተከትሎ ለምርጫ ቦርድ ታዞ እደሚኖር የትኛው ለምርጫ ቦርድ ታዛዥ እንዳልሆነ አበጥረው ሲናገሩ መረጃ አያጥራቸውም፤ ‘ሰው ይታዘበኝ ይሆን?’ ብለውም አይጨነቁም!

በሚኒስትር ማዕረግ ቢሰየሙም ‘ገለልተኛ ነኝ’ ብለው ምርጫ ቦርድን ይዘውሩ የነበሩት ዶ/ር አዲሱ የምርጫ ቦርድ ወንበራቸውን ለማን አስረክበው እንደመጡ ባይታወቅም የሰብዊ መብት ኮሚሽን ዋና ሰው ሆነው ምርጫ ቦርድ በነበሩበት ጊዜ የሚያባጥሏቸውን ተቃዋሚዎች በሰብዓዊ መብት መጣስ ተጠያቂ የሚያደርግ ሪፖርት ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡ እንደ ዛር በየቦታው ብቅ የሚሉት ዶ/ር አዲሱ የምርጫ ቦርድ ወንበራቸውን ተመልሰው የሚቀመጡበት ከሆነ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚከሷቸውን ፓርቲዎች በለመደ እጃቸው ከህይወት መዝገብ ለመሰረዝ ርቆ የማይርቀው መንገድ ይበልጥ ይቀርባቸዋል፡፡

በህዝባዊ አመፁ ወቅት ለተደረገው የሰብዐዊ መብት ጥሰት ተኩሶ ከገደለው ወገን ይልቅ ተቃዋሚዎችን እና የመገናኛ ብዙሃንን ተጠያቂ ያደረገው የዶ/ር አዲሱ ሪፖርት ኢህአዴግ ሲለው የባጀውን በሪፖርት ተብየው ከማድመቅ ባለፈ፤ህዝብም ኮሚሽኑን የሚያውቅበትን ማነት ይበልጥ ከማጉላት ሌላ የጨመረው ነገር የለም፡፡ኮሚሽኑ ‘ተዘዋውሬ አጣራሁ’ ባለባቸው የሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ለታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በምክንያትነት ያቀረበው መንግስት ሲለው ሲሰልሰው ሲደጋግመው ሰንብቶ ‘ለጥልቅ ተሃድሶ ሱባኤ አስገባኝ’ ያለውን የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በተጨማሪ ምክንያትነት ያነሳው የስራ አጥነት ነገር መንግስት እስኪያቅረን ያልነገረን ነገር አይደለም፡፡ የተጠያቂነቱ ጣት የተቀሰረባቸው እነ ኢሳት፣ኦ.ኤም.ኤን እና ፌስቡክም መንግስት ቀድሞ ተጠያቂ አድርጎ በአስቸኳይ ጊዜ ህጉ እንዳይደመጡ አዋጅ ያስነገረባቸው ናቸው፡፡ ለኦሮሚያ ክልል ኦ.ፌ.ኮ፣ኦነግ ለአማራ ክልል ሰማያዊ ፓርቲ፣ ቤተ-አማራ የችግሩ አባባሽ እንደሆኑም ከመንግስት አፍ ያልሰማነው ነገር አይደለም፡፡ የሪፖርቱ ነገራ ነገር እንደውም የመንግስት እና የኮሚሽኑን አንድነት እና ልዩነት ድንግርግር ከማባባስ ባለፈ ለሰሚ ያመጣው አዲስ ነገርም ሆነ ለችግሩ አፈታት እነሆ ያለው የአዋቂ አስተዋፅኦ አይታየኝም፡፡

ሪፖርቱ መንግስት የችግሩን ዋና መንስኤ ከማጣራት ይልቅ ያልሆነ አካሄድ ለመሄድ እያዘገመ ያበትን አደገኛ አካሄድ ትቶ ወደ ተሻለው መንገድ እንዲሄድ ትክክለኛው የችግሩ ዋና ፈጣሪ የራሱ አምባገነንነት፣ እንደ አፍላ ጎረምሳ ሁሉን በቡጢ የማለት አካሄድ መሆኑን ከመንገር ይልቅ “አባረህ በለውን” እያዜመ እንደ እብድ ገላጋይ ድንጋይ የሚያቀብል ነው፡፡ መንግስት ሊበላቸው ያሰባቸውን ፓርቲዎች የጥፋቱ ሁሉ መነሾ አድርጎ ቁጭ ሲል ‘አዎ ልክነህ’ የሚል ሪፖርት ገለልተኝነቱ እንዴት ነው? ከወራት በፊት መንግስት ቢሮው ቁጭ ብሎ የጥፋቱ ሁሉ መንስኤ ያደረገውን ነገር ሳይጨምር ሳይቀንስ ቦታው ድረስ ሄጄ አጥንቼ ያገኘሁት የችግሩ መንስኤ ነው የሚል አካል ተላላ አድርጎ ያሰበው ማንን ነው?
ሪፖርቱ ጠለቅ ብለው ሲያዩትም በብዙ እንከኖች የተሞላ ነው፡፡ መረጃ ከማሰባሰብ ዘዴው ቢጀመር የመረጃ ምንጭ ተብለው ከቀረቡት አካላት ውስጥ በአካባቢው የሚገኙ የመንግስት ተወካዩች አሉበት፡፡እዚህ የመንግስት ተወካዩች የዲሞክራሲያዊ መንግስት ተወካዩች እንዳልሆኑ ግልፅ በመሆኑ በሰብዐዊ መብት ጥሰቱ የመንግስትን ትክክለኛ ድርሻ ለመናገር ወይ ይፈራሉ አለያም ራሳቸውን የመንግስት አካል አድርገው ስለሚያስቡ ጦሱን ወደሌላ ይጥላሉ እንጅ ለስብዕና ወግነው መንግስታቸውን የሚያጋልጡበት ልቅና ላይ የሚደርሱ አይመስለኝም፡፡

ሌሎቹ የመረጃ ምንጮች ተደርገው የቀረቡት የሃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ናቸው፡፡ የዘመናችን የሃይማኖት አባቶች እንዴት ያሉ ናቸው? ከሰማዩ እና ከምድሩ ንጉስ ይበልጡን ለየትኛው ሲያገለግሉ ነው የምናውቃቸው?እውነት እውነቱን በመናገር እንጠረጥራቸዋለን ወይ? እውነት እንናገር ቢሉስ መንግስት ከሱባኤ ሳይቀር አውጥቶ የሚፈልገውን እንደሚያደርግ አያውቁምና እውነት ሊናገሩ ይሞክራሉ? የሃገር ሽማግሌዎች የተባሉትስ እንደ ፕ/ሮ ኤፍሬም ይስሃቅ እና አትሌት ኃ/ገብረስላሴ አይነት ናቸው ሌላ?የሚለውን ነገር ይዞ መረጃቸውን የማመን ያለማመን የአድጭ ፋንታ ነው፡፡

በሶስተኛ የመረጃ ምንጭነት የቀረቡት የተጎጅ ቤተሰቦች ናቸው፡፡እነዚህ ምንጮች ተጎጅ ዘመዶቻቸው ከመከላከያ ጋር ያደረጉት ግጭት መንስኤ እና የጉዳት ደረጃን በተመለከተ መረጃ ሰጥተዋል ነው የሚለው ሪፖርቱ፡፡ምን ያህሉ የተጎጅ ቤተሰቦች በተለይ ተጎጅ ዘመዶቻቸው በግጭቱ ወቅት የት ነበሩ ተብሎ ነው ለግጭቱ መንስኤ የሆነውን ነገር በትክክል ያስረዳሉ ተብለው የታሰቡት? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ያውቃሉ ቢባል እንኳን የሚያውቁትን እውነት ለመናገር አይፈሩም ለማለት የእነ ዶ/ር አዲሱ ኮሚሽን በህዝብ ዘንድ ባለው የገለልተኝነት ምስል ይወሰናል፡፡ ሌላው የመረጃ ምንጭ የነ ዶ/ር አዲሱ መስሪያ ቤት ሰዎች የምልከታ እና የቪዲዮ ምስሎች ናቸው፡፡ የነሱን ምልከታ እንዴትነት ለአንባቢ እተዋለሁ፡፡

የኦሮሚያን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ የተደረገውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አጣራሁ የሚለው ሪፖርቱ ከኢሬቻው አመፅ በፊት ሃምሌ 30 የተደረገውን እንቅስቃሴ የሰው ህይወት የጠፋበት፣የአካል ጉዳት የደረሰበት እና ህይወት ያልጠፋበት እንቅስቃሴ ብሎ ለሁለት ከመክፈል ባለፈ ስንት ሰዎች በማን ህይወታቸው እንደጠፋ፣ ምን ያህሉ በማን የትኛውን አካላቸውን እንዳጡ ሰይዘረዝር ሾላ በድፍን አድርጎ ፍትህ ቢኖር እንኳን ለፍትህ አሰጣጥ እንደማይመች አድርጎ አልፎታል፡፡ 2.5ሚሊዮን ሰዎች ተገኝተውበታል ባለው የኢሬቻ በዓል ላይ የተነሳ አመፅ በተመለከተ አንድ ወጣቶት በአሉን ከሚያስጀምሩት አባገዳ የድምፅ ማጉያ ነጥቆ መንግስትን የሚያወግዝ እና አመፅን የሚገልፅ መዕክት ማሰማት ሲጀምር፣ሌሎች ወጣቶች የኦነግን አርማ ማውለብለብ እና እጅ ማጣመር ሲጀምሩ የፀጥታ ሃይሎች ነገሩን ላመረጋጋት ሙከራ ሲያደርጉ ወጣቶቹ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር ግብግብ ጀመሩ፤ በዚህ መሃል የፀጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጋዝ ሲተኩሱ ተሳታፊዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ መሯሯጥና መገፋፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ክስተት በአካባቢው በነበረው ገደል በመግባትና በመረጋገጥ 56 ሰዎች ሞቱ ሲል መንግስት ያለውን ሳይጨምር ሳይቀንስ ያቀርባል፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በመልካም አስተዳደር ችግር፣ የመብት ጥሰት፣የስራ ቅጥር በዘመድ መሆን፣ስራ አጥነት፣የኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም አለመከበር ነው ይልና ኦ.ፌ.ኮ.ን፣ኦነግና ኦ.ኤም.ኤንን ደግሞ በአባባሽነት ይከሳል፡፡ የደረሰበት ምሬት ህዝብ በዓልን ሳይቀር ለብሶት መግለጫ እስከማዋል የሚያደርስ የመብት ጥሰት፣ስራ አጥነት ፣የመልካም አስተዳደር ወዘተ ችግር መኖሩ ከታመነ በኋላ ሃገር አስተዳድራለሁ የሚለው መንግስት ይህን ሁሉ ችግር በመፍጠርም ሆነ መፍትሄ ባለመስጠት ሊጠየቅ ሲገባ ዋናውን አስቀምጦ አባባሽ ፈልጎ ጦሱን ወደ ሌላ አካል መጣሉ ምን ማለት እንደሆነ ግራ ነው፡፡ ራሱ አባባሽ ማለት ምን ማለት ነው? የመረረው ህዝብ ወጥቶ ብሶቱን ለመግለፅ ምን አባባሽም ሆነ ጎትጓች ያስፈልገዋል? አመካኝቶ ፓርቲዎቹን ለመብላት ካልሆነ!

ሌላው አስተዛዛቢ ነገር የተተኮውን አስለቃሽ ጭስ አስመልክቶ ሪፖርቱ በለሆሳስ ያለፈው ነገር ነው፡፡ የአስለቃሽ ጭሱ ጉዳይ ሪፖርቱ በዓሉ ወደ አመፅ ሲያመራ የፀጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ ተኮሱ ብሎ ብቻ በሽፍንፍን እንዳለፈው ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አስለቃሽ ጭስ የሚተኮስበት ህጋዊ ሁኔታ እና የሰው መጠን አለ፡፡ አስለቃሽ ጭስ መተኮስ ያለበት በቁጥር ብዙ ያልሆኑ፣ ዘርዘር ብለው ለመሸሽም ሰፋ ባለ መልከዓ-ምድር ላይ ባሉ አማፅያን ላይ እንጅ እንደዚህ መተናፈሻ በሌለው፣ገበቴ በመሰለ ሸለቆ ውስጥ ታፍገው ባሉ ሚሊዮኖች ላይ እንዳልሆነ ለሰብዓዊ መብት ቆምኩ የሚል ድርጅት ግንዛቤ ያጣል ማለት አይቻልም፡፡ የአስለቃሽ ጭስ አላማ ሰዎችን መበተን እንጅ መግደል አይደለም፡፡ የኢሬቻው አስለቃሽ ጭስ ተኩስ ሰዎችን ለመበተን ታስቦ የተደረገ ከሆነ እንደዛ ባለ መልከዓምድር የተሰበሰበ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ በየት ብሎ በሰላም እንዲበተን ታስቦ ድርጊቱ እንደተፈፀመ ተኳሹን አካል መንግስትን ተጠያቂ የማያደርግ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽ አላማው ምንድን ነው?እንዲህ ያለውን በስብዕና ላይ የተቃጣ ወንጀል አድበስብሶ አልፎ ምን ለማትረፍ ነው ባለ መቶ ሰባ ገፅ ሪፖርት የሚፃፈው? ይብስ የሚገርመው ደግሞ የበዓሉ አዘጋጆች ይህ እንዳይፈጠር የቢሾፍቱን ገደሎች መድፈን ነበረበረባቸው የሚለው የሪፖርቱ ቀልድ አይሉት ቁምነገር ነው፡፡ ይህ ነገር ሪፖርቱ አህያውን ሽሽት ምን ያህል ተንጠራርተቶ ዳውላውን እንደሚደበድብ ራሱን ከማስገመት ባለፈ የቢሾፍቱ ገደል ተሞልቶ ያልቃል ብሎ ገምቶ የሚያምን ቂል አገኛለሁ ብሎ አይመስለኝም!

ሌላው ሚገርመው ነገር የኢሬቻው አመፅ ጉዳይ የመንግስት እና የፀጥታ ሃይሎች ቀድመው እያወቁ በዓሉ እንዲካሄድ መደረጉ ህዝባዊ ሃላፊነት የጎደለው ነው የሚለው የሪፖርቱ ፈሊጥ ነው፡፡ ለመሆኑ የህዝብን በዓል በፖለቲካዊ ምክንያት ማስቀረት ለማን ይቻለዋል? በዓሉ ህዝብ በአመት አንዴ ጉጉት ጠብቆ በደስታ የሚያከብረው መሆኑ ተረሳ? ደግሞስ በዓሉን ለዩኒስኮ አስመዘግባለሁ ብሎ መደገሱ በመንግስት በራሱ ብሶ አልነበረምና ነው በዓሉን ማስቀረቱ እንደአማራጭ የቀረበው? በዓሉን ከማስቀረትና ወጣቶች እጃቸውን ሲያጣምሩና የኦነግን ባንዲራ ሲያውለበልቡ በትዕግስት አልፎ በኋላ በህግ ከመጠየቅ የቱ ይቀላል? የዛን ሁሉ ወገን አስከሬን አጋድሞ በዓለም ጉድ ከመባልና የአመፀኞችን የተጣመሩ እጆች እንዳላዩ ከማለፍ የትኛው መንግስትነትን ይመጥናል?

ሪፖርቱ አንድ አበጄ የሚባልለት ነገር ቢኖር በውጭ ሃገር የከተሙ የኦሮሞ አክቲቪስቶች እና መገናኛ ብዙሃን በኢሬቻ በዓል ላይ መንግስት በሄሊኮፕተር የታገዘ ጥቃት ፈፅሞ ከ600 በላይ ሰዎችን ገደለ ብለው ያሰራጩትን ከጤነኛሰው የማይጠበቅ፣ ሃላፊነት የጎደለው፣ ቅንነት የራቀውን አስተዛዛቢ ወሬ በተመለከተ ያቀረበው መረጃ ነው፡፡ በወቅቱ መንግስት እንኳን አደረሳችሁ የሚል መልዕክት የያዘ ወረቀት በሄሊኮፕተር የበተነበትን ሁኔታ በሄሊኮፕተር የተደረገ ወታደራዊ ጥቃት ተደርጎ ማቅረቡ ለማን ይጠቅማል ተብሎ እንደሆነ አይታወቅም፡፡

የአማራ ክልልን በተመለከተ ሃምሌ 4 ቀን የፌደራል ፀረ-ሽብር ግብረሃይል በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ከሌሊቱ 10፡30 ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ሁከትና ብጥብጥ ተከትሏል ፌስቡክና ኢሳት አባብሰዋል ከማት በቀር ከሌሊቱ አስር ሰአት ሰው ቤት መሄድ ከሰብዓዊ መብት አንፃር እንዴት እንደሚታይ በመንግስት ነገር ሆዱ የማይጠናው የዶ/ር አዲሱ ቢሮ ቃል ትንፍሽ አላላም፡፡ ምናልባትም ድርጊቱ ልክ ነው ብለን እንድናስብ ተብሎ ይሆናል ዝምታው፡፡ አመፁ በመሰረተ ልማት ላይና በትግራይ ተወላጆች ላይ ጉዳት አድርሷል ይበል እንጅ በትግራይ ተወላጆች ደረሰ ያለው ጉዳት የአካል ይሁን የህይወት መጥፋት በግልፅ አያስቀምጥም፡፡ በጥቅል 11,678 የትግራይ ተወላጆች ተፈናቅለዋል ያለው ሪፖርቱ ሰዎቹ የተፈናቀሉባቸውን ቦታዎች ልዩ ስም እና ከየአንዳንዱ ቦታ የተፈናቀሉትን ሰዎች ቁጥር አይገልጽም፡፡ ይህን ያህል ሰው ከጎንደር ከተማ ብቻ ተፈናቀለ እያለ ከሆነም ግልፅ አይደለም፡፡ይሄ ሁሉ “ተፈናቃይ” በአሁኑ ጊዜ ያለበትን ሁኔታም አይገልፅም -ሪፖርቱ፡፡ የትግራይ ተወላጆች ደረሰባቸው የተባለውን ጉዳት የአማራ ህዝብ እንደመከተላቸው የሚገልፀው ሪፖርቱ ሶህዴፓ ለትግራይ ተፈናቃዮች የለገሰውን ገንዘብ ጠቅሶ ገለታ ሳያቀርብ አልፎታል፡፡ በአንፃሩ የአማራ ክልልን መንግስትና የወረዳ አስተዳደሮች ተገቢውን የደንንነት ጥበቃ አላደረጉም፣አደጋው ከደረሰ በኋላም ከመከላከል ይልቅ እግሬ አውጭኝ ብለው በመሸሻቸው የጎበዝ አለቆች አካባቢውን እስከ ማስተዳደር እንዲደርሱ አድርገዋል ሲል በአዴኖችን ከላይ እስከታች ይከሳል፡፡ በአማራ ክልል በአጠቃላይ ያለቀውን የህዝብ ቁጥር በመቶዎቹ ብቻ መጥኖ፤በተለመደው ተመጣጣኝ ሃይል የመጠቀምና ያለመጠቀም ቁማር አምታቶ አልፎታል፡፡

የጋሼ አሰፋ ሞቱ፤ለመግባት ከቤቱ…….! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

FacebookTwitterPinterestWhatsAppLinkedin

በመስከረም አበራ
(meskiduye99@gmail.com)
ሚያዚያ 20 ፤ 2009 ዓ ም

Assefa Chabo

ጋሼ አሰፋ ጫቦ የኢትዮጵያን ፍቅር እንደማተብ በአንገቱ አስሮ፤እንደ እንደ መልካም ሽቶ ለሌሎችም ሲረጨው የኖረ ሰው ነው፡፡ ሃገሩን የሚወድበት ውድ የልክፍት አይነት ብርቱ ነበር፡፡ በሰው ሃገር ተኝቶ በኢትዮጵያ ሰማይ ምድር፣ በሃገሩ ወንዛ ወንዝ፣በጋሞ ጭጋጋማ ተራሮች ግርጌ፣ በሰላሌ ሜዳ፣ በጣና ገዳማት፣በሊማሊሞ አቀበት የሚያዞር ህልም የሚያሳልም የሃገሩ ፅኑ ፍቅር የወደቀበት ሰው ነበር፡፡ከህልሙ ነቅቶ ብዕር ሲያነሳ ያለ ሃገሩ እትብት የመጓተት ፖለቲካ ደዌ፣ገዳዳ የፍትህ ስርዓት፣የልመና አቁማዳ የሚያስነግት አዋራጅ ጠኔ፣ወልጋዳ ፕሮፖጋንዳ፤ ሌላ አይታየውምና እሱኑ ያነሳል ይጥላል፤ለሚሰማው የሚሻል የመሰለውን መንገድ ያሳያል፡፡ የጋሼ አሴን የሃገር ፍቅር ተራራ አይጋርደውም! ለዚህ ነው ምቹው የስደት ሃገር ያልተስማማው፤ስንቱ በእግር በፈረስ የሚሞክረው ስደት ለእሱ እንደ ምርግ ከብዶት ከሃገር ከአፈሩ፤ ከወፍ ከዛፉ ያላስማማው፤ባይተዋር ያደረገው፤ሞቱን ሳይቀር በድብቅ ለማድረግ ያስጨከነው!የሃገር ፍቅር ረሃብ በሰው ሃገር መልካም ምግብ አይጠረቃም፡፡ በቅንጡ ሆስፒታልም አይታከምም!

የጋሼ አሰፋ ነፍስ ለስጋዋ በተመቻት ቦታ ትረጋጋ ዘንድ እምቢ ብላ ‘ሃገሬን’ እያለች ስታስጨንቀው የኖረች ይመስለኛል፡፡መላ ስትዘይድም ያልተመቼውን ስጋዋን ገድላ ከሙት በቀር ህያው የማይወዱትን ነገስታት ጠመንጃ በሞት ተከልላ ሃገሯ ለመግባት መርጣ ይመስላል ጋሼ አሰፋን የተነጠቅነው፡፡እሱን የመሰለ ብዕረ-መልካም ሰው መነጠቅ በቀላሉ የሚተኩት ኪሳራ አይደለም፡፡ በወር አንድ ጊዜ እንኳን አንድ ገፅ የብዕሩን ቱፍታ ቢያጋራን ብዙ እናተርፍ ነበር፡፡ በልጅነት በጉልምስና የማያጠፋ የለምና ጥፋት ቢኖረው እንኳን ከጥፋቱ ሳይቀር የሚያስተምርበት ብዕሩን እንድንጠቀም በሚያደርግ መልኩ ሁሉን ማድረግ ይቻል ነበር-የቂም በቀል ክስ ፈብርኮ የማምሻ እድሜውን የሚያስፈጅ የቅጣት ድግስ ከመደገስ፡፡

እንደ መዥገር እላያችን ላይ የተጣበቁት ነገስታት ግን ለመንግስትነት የሚበቃ ምህረትም ሆነ አርቆ አስተዋይነት የላቸውምና እነሱ እጁን ይዘው የማይመሩት ሰው በሃገር አይኖርም፡፡ ይሄው እኩይነታቸው ወርቁን ሰው ጋሼ አሰፋን ከሚወዳት ሃገሩ ብን ብሎ በሰው ሃገር መዳብ ሆኖ ጎኑን ሳይመቸው እንዲኖር አደረገው፡፡ሃገራቸውን ‘ቅኝ ገዥ’ ብለው አነውረው ‘ለሰው ሃገር’ እንሙት የሚሉ፤ ርጋፊ የሃገር ፍቅር ያፈጠረባቸው የባንዳ ልጆች የማይወዷት ሃገር ባለቤት ሆነው ሃገሩን የሚወድ ሰው በስደት ምድር ነፍሱ እንድትራቆት ማድረጋቸው መራር ነው፡፡ ከሰው እንዳልተፈጠረ፣ወገን እንደሌለው፣ ቢያንስ በብዕሩ ለሃገር እንዳልጠቀመ በመጨረሻው ሰዓት ከሞት ጋር ሲተናነቅ እንኳን የኔ የሚለው ሰው በሌለበት እንዲሆን ከማድረግ ሌላ ምን የበቀል ጥግ ሊገኝ? የዚህ ቁጭትስ እንዴት ሆኖ ከወገን ሆድ ይወጣል?!ይህን ሁሉ ክፋት በክንዳቸው ብርታት ያደረጉ ለሚመስላቸው በቀለኛ ነገስታት የኛ በሃዘን ማረር የሃሴት ጊዜያቸው ነው፤አንድ ባለጋራ ወድቆላቸዋልና “ጎፈሬ” ያበጥሩ፤እኛ ብዙ የጎደለብን ደግሞ ብዙ እናልቅስ! ፈልገናቸው “የልባችን ናችሁ” ብለን አልሾምናቸወምና ሃዘናቸው እና ሃዘናችን ገጥሞ አያውቅም፡፡ዘር ቆርጥመው የሚበሉ ናቸውና ዘር እንዳይተርፍልን በክፋታቸው የዋኖቻችንን እድሜ አሳጥረው በታላላቆች መክሊት ሳንጠቀም እንዲሁ ቀረን!

ጋሼ አሰፋ በግል ህይወቱ ባህሪው ምን አይነት እንደሆነ አላውቅም፡፡ሰው ነውና እንከንም አይጠፋበትም፡፡በግል ባህሪው ወደድነው ጠላነው ባለ ወርቅ ብዕር እንደሆነ ግን ማንም አይክደውም፡፡ የብዕሩ ቱፍታ ለዛ የማይጠገብ፤የወርቅ ብዕሩ ክታብ የተጓዘበት ፍኖት ቢሄዱበት የማይሰለች፤ ቢያፈጡበት የማይደክም እንደሆነ በወዳጁም በጠላቱም ፊት የተሰወረ አይደለም፡፡በደልን የሚተው የይቅርታ ሰውነቱም የሚካድ አይደለም፡፡ አስራ አንድ አመት መታሰሩን አሁንም አሁንም እያነሳ የሞኝ ለቅሶ ሲያለቅስ አላየንም፡፡ ይልቅ “ያለፈው አለፈ አሁን የጋራቤታችንን እንዴት ገንብተን በምን እናሙቅ” በማለቱ ላይ ይበረታል:: ስለዚህ ነገሩ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ተገርሞ ‘አንተ ግን እንዴት ነው የአስር አመት እስርህን በመፅሃፍህ ላይ በለሆሳስ ያለፍከው’ ብሎ ጠይቆት ነበር፡፡ ‘አስሬ ባወራው ምን ይጠቅማል፤ደጋግሞ ማውራቱ የሆነን ነገር ከመሆን አይቀንስ አይጨምር ምን ዋጋ አለው፤ ይልቅ ትርፍ ስላለው የወደፊት ነገር ማውራቱ ይበጅ ይመስለኛል’ ሲል ነበር የመለሰው:: ጋሼ አሰፋ የኢትዮጵያ ፍቅር ያመጣበትን ለኢትዮጵያዊነት የመቆም ሙግት ሲያስረዳ ስሜትን ሳይሆን ምክንያትን ተላብሶ እንደሆነም አይካድም፡፡ በዚሁ የሚተቹት “ኢትዮጵያን ካላፈረስን” ባዮች በፊቱ ቆመው ከመሞገት ይልቅ ማዶ ሆነው ሽምግልናውን በማይመጥን ሁኔታ ስድብ የተሞላ አፋቸውን የሚከፍቱበት ምክንያት ስሜታዊነታቸው የምክንያታዊነቱን ጉልበት፤የግንዛቤውን ጥልቀት፤ የንባቡን ስፋት ይቋቋመው ዘንድ ስለማይችል ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ጋሼ አሰፋ የብሄር ፖለቲካን የሙጥኝ ቢል ኖሮ ይህን ሁሉ የስደት ስንክሳር ባላየ ነበር፡፡ እንደማንኛውም የጎሳ ፖለቲከኛ ያኔ አስራ አንድ አመት ሲታሰር የጋሞን ህዝብ ሁሉ ይዞ እስርቤት የገባ አስመስሎ፤ራሱን ህዝብ አሳክሎ ቢያላዝን ተከታይ እንዳይጠፋ ነው?! በጎሳ ፖለቲካ ተፀንሶ ተወልዶ ለዚህ የበቃው ህወሃትም ይህን አይጠላም ነበር፡፡ “በነጋ በጠባ የምበጥስ የምቀጥለው ማተብ የለኝም” የሚለው ጋሼ አሰፋ ግን አለማቀፍ ወዛደራዊነትን በዘመረበት አፉ በጋሞ ሸለቆዎች ብቻ በሚሽሎከሎክ ጥበት ኢትዮጵያዊነቱን ቸል ይል ዘንድ የግንዛቤው ስፋት በጄ አላላውም፡፡ ይልቅስ ጋሞነቱ ከኢትዮጵያዊነቱ ተጣልተውበት ሊያስታርቅ ቁጭ ብሎ እንደማያውቅ በብሩክ ብዕሩ አስነብቦናል፡፡ ነፍሰ-ስጋውን አልተመቼውም እንጅ ያልተበጠሰ ማተቡን በአንገቱ እንዳሰረ ማንቀላፋቱ ተገለባባጭ በበዛበት ምድር አርአያነት ነው፡፡ እኛ ብዕሩን የለመድን ግን ክፉ ጉዳት ተጎዳን!

ስለ ጋሼ አሰፋ የሰማሁት የተስፋየ ገብረአብን ተግተልታይ ማስታወሻዎች በማነብ ሰሞን ነበር፡፡ ሁለተኛውን ማስታወሻውን ካነበብኩ በኋላ ከጓደኞቼ ጋር ሰብሰብ ብለን ስላነበብናቸው መፃህፍት በምናነሳሳበት የማኪያቶ ሰርክል ከተስፋየ ማስታዎሻዎች ውስጥ የሳበኝ ነገር ቢኖር የአማርኛው ውበት እንደሆነ ገለፅኩ፤ ብዙዎች ተስማሙ፡፡ ከመሃላችን አንዱ “በቃ ተስፋየን ተንኮሏን ብቻ አሳቅፋችኋት ቀራችሁ ማለት ነው” ሲል “እንዴት?” አልኩኝ፡፡ “ተስፋየ የአማርኛ ውበቱን የቀዳው አንድ አሰፋ ጫቦ ከሚባል የአርባምንጭ አካባቢ ሰው ብዕር እንደሆነ ራሱ ተስፋየ እንደተናገረ የሆነ ቦታ አንብቤያለሁ” ብሎ ጀምሮ ስለ ጋሼ አሰፋ ብዙ አጫወተን፡፡ “እኛ እንዴት አናውቀውም ታዲያ?” ጥያቄያችን ነበር፡፡ “ተፈጥሮ ምቀኛ ሆነችባችኋ! ወያኔ ሲገባ እያንዳንድሽ ትምህርትቤት ከገባሽ አነሰሽና ነው ጋዜጣ አንባቢ የሆንሽው?” ብሎ ቀልዶ ጋሼ አሴን ያላወቅንበትን ሚስጥር አስረዳን፡፡ “እስኪ የፃፈው ነገር ካለ አውሰኝ” ብየ ለመንኩ፤አባቱ የከዘኑትን የጋሼ አሰፋ በጋዜጣ መፅሄት የተዘራ ምርት፣ የሰጣቸውን አንድ ሁለት ቃለ ምልልሶች አምጥቶ ዘረገፈልኝ፡፡

የጋሼ አሰፋ ብዕር ከሰማሁት በላይ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ብዕሩን ወደድኩት፤ርቱዕ አንደበቱን አደነቅኩ፤ቅልል ጥፍጥ ያለ ቋንቋው በመንፈስ የቅርቤ ሰው አደረገው!!!!! “አሁን ከወዴት አለ?” ብየ ጠየቅኩ ባስቀር የምወደውን የተዋስኩትን ጋዜጣ መፅሄት ስመልስ፡፡ “አሁን ያው ወያኔ የሽብርተኛ ህጉን ሳታወጣ የደበራትን በምትከስበት የሆነ አንቀፅ ተከሶ ድንገት እንደወጣ ቀረ፤ከዛም የገባበት እንደጠፋ አባቴ ነግሮኛል” ሲል አጫወተኝ፡፡ ‘የገባበት ጠፋ’ ውስጥ ሞትም እንዳለ ጠረጠርኩ፤በአሉ ግርማ ትዝ አለኝ፤አለመታደል ተሰማኝ! የዋና እና የመደዴ፤የምርት እና የግርድ ቦታ ያቀያየረችው ሃገሬ መጨረሻ አሳዘነኝ፡፡ “ሞትም ይኖራል በለኛ” አልኩ ቅዝዝ ብየ፡፡ “ከሞተ እንኳን ይሰማ ነበር፤ካለም የበላው ጅብ አንድ ቀን ይጮሃል” ብሎኝ ተለያየን፡፡

የሞቱን ስጋት ሽውታ ችላ ብየ የበላው ጅብ በቶሎ እንዲጮህ ተመኘሁ፡፡ እግዜር ይስጠው ቶሎ ጮኽ! ጭራሽ “የትዝታ ፈለግ”ን እነሆ አለን፤ትልቅ ሆኖ ሳለ ከእኛ ጋር ወርዶ በፌስቡክ ሜዳ ላይ አብሮን ሰነበተ፤የቅርባችን ሆነ፤የሃገሩን ጠረን ሃገርቤት ባለን ወገኖቹ በኩል ማሽተት ጀመረ፤ሃገሩ የገባ ሳይመስለውም አልቀረም፡፡ በዚህ ነፍሱ ደስ እንዳላት በፌስ ቡክ መስኮት አጫውቶኛል፤በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ!ጋሼ አሰፋ ራሱ እንዳጫወተኝ ሃገሩን አደራ የሚላቸው ወጣቶችን በመብራት ይፈልጋል፡፡ብዙ ባዝኖ ሲያገኝ ትቂቷን ጅማሬያቸውን አግዝፎ አይዟችሁ ይላል፡፡ ሞቱን ትከሻው ነግሮታል መሰል የተተኪ አሳቢ አሰላሳይ ነገር እጅግ ያሳስበው እንደነበረ፤አሁን ፌስቡክን ተቀላቅሎ ሲያይ ካሰበው በላይ ሃገሩ ደጀን እንዳላት በመረዳቱ በጣም እንደረካ ያጫውተኝ ነበር፡፡ እኔ ቀደም ብየ ልወቀው እንጅ እሱ ያወቀኝ ከአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ ጋር የነበረኝን ቆይታ አዳምጦ “በርቺ በልልኝ” ሲል ለጋዜጠኛ ካሳሁን ኢሜል አድርጎ ካሳሁን ካደረሰኝ በኋላ ነው፡፡

ጋሼ አሴ እንደ አብዛኞቹ የዘመን አጋሮቹ ያሁኑን ትውልድ በመናቅ በመርገም አይነሳም፡፡ይልቅስ ልጆች ናቸው ብሎ ሳይንቅ ለመራመድ መውተርተራችንን እንደ ትልቅ ቆጥሮ በርቱ ይላል፡፡የራሴን ባወራ ትንሽ ቀላጤ ስፅፍ ከእውቀቱ በላይ የማውቅ ይመስል የሚያበረቱ ቃላት ከሽኖ ይልክልኛል፤ “ፅሁፍሽን ለማውቃቸውም ለማላውቃቸውም ሳጋራ፣እንዲያነቡ ስጋብዝ ሰነበትኩ፤እናንተን በማየቴ ሃገሬ አውላላ ሜዳላይ እንዳልቀረች አስባለሁና ነገ አያስፈራኝም” ይላል የሚወዳትን ሃገሩን በሁነኛ አደራ ተቀባይ መዳፍ ላይ ለማኖር ሲቃትት!

ምን ያደርጋል እንደተመኘው ሃገሩ ሻል ሳይላት እንደታመመች ቁርጧን ሳያይ፤ሰሚ ባልሆነ የፈርኦን ጆሮ ላይ “ኢትዮጵያን ማሯት” ሲል እንደለፈፈ፤ለእናት ምድሩ እንደማለደ፤ሰምቶ የሚመልስ ሳያገኝ ወደ ማይመለስበት ሄደ፡፡ ርቱዕ አንደበቱ ተዘጋ፡፡አይጠገብ ብዕሩ ድንገት ነጠፈ፡፡አቻቻይ ማንነቱ ተነነ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚያዜምበት በገናው ወደቀ፡፡ “የጋራቤታችንን” ማገር የሚያጠብቅበት የመልካም ሽማግሌ ድንቅ ምክሩ ሲያምረን ቀረ! ከእውቀቱ ጥልቅ የምንቀዳው ውሃ፤የምንቋጥረው ስንቅ ጎደለ፡፡የምንሰባሰብበት የኢትዮጵያዊነት አንድ ባንዲራ ወደቀ፡፡ ከእድሜው ድርና ማግ የምንሸምነው የእውቀት ቡልኮ አጠረ፡፡ከመውደቅ መነሳቱ፤ከ‘ትዝታ ፈለጉ’ የምንቀስመው የልምድ ሰፈፍ ተቆረጠ፡፡የሆነው ሆኖ በድኑ የናፈቃት ሃገሩ መጥቶ እንዲያርፍ እየተሞከረ ያለው ነገር ከተሳካ ጥሩ መፅናኛ ነው፡፡ አምላክ የትልቁን ሰው ውብ ነፍስ በአፀደ ገነት እንዲያኖርልን፤ለእኛም መፅናናቱን እንዲሰጠን እየተመኘሁ ገጣሚ ዮሐንስ ሞላ የጋሼ አሴን ሞት አስመልክቶ የገጠማትን ከእንባ ጋር የምታታግል ግጥም አስከትየ ላብቃ!

Assefa Chabo

ናፍቆታል ሃገሩ፣ጥያሜው ጠረኑ
በስጋው ተሳዶ፣ይያት በአስከሬኑ፤

“አሻም!” በሉት ውጡ፣ አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ በትኑ፣አፈሩን ዝገኑ….

የዕድሜ እንቆቅልሹ፣ የዘመን ትብትቡ
የትዝታው ፈለግ፣ፍቅር የሃገር-ሰቡ
ያንድነት ሃሳቡ፤ያብሮነት ረሃቡ…..

ይፈታለት ህልሙ፤
ይውጣለት ህመሙ
ናፍቆት ሰቀቀኑ
ይሁንለት መጥኑ፤

ሃገሩ መድረሱን፣በሰው መከበቡን
ቡና መወቀጡን፣ወጡ መወጥወጡን
ክረምትና በጋ
ቆላ ወይና ደጋ
በሃሴት መውቀጡን ሌሊቱ እስኪነጋ
ሰስቶ መታየት፣ማውጋት ከእንግዳ ጋ፤
ያውቀዋል አየሩን
ይረዳዋል ነፍሱ
ባያይ እንኳን ዐይኑ
ያውቃል ደመነፍሱ
ለመላ ነው ሞቱ
ለመግባት ከቤቱ፤
“አሻም!” በሉት ውጡ፣አበባ ጎንጉኑ
ገላው ላይ አብኑ፣አፈሩን ዝገኑ
ይብረድለት ሱሱ
ቃናዋ ነው ምሱ

ይቁረጥለት ጥሙ
አፈሯን ይቅመሰው
መለስ ይበል ቅስሙ
ቸሰስ ይበል ጅስሙ…

ሃሳቡን ትውረሰው፣
ገላውን ትጉረሰው
አገር ያጊጥበ፣ተጓትቶ ይልበሰው
ከበቀለበት ሰው፣ተሻምቶ ይቅመሰው፡፡

/ግጥም፡ በዮሐንስ ሞላ/

የአማራ ብሄርተኝነት ነገር… (መስከረም አበራ)

ByAdmin

Share

(በመስከረም አበራ; e-mail meskiduye99@gmail.com)
ጥቅምት 2 2009 ዓ ም

ከፅንሰት ውልደቱ ጀምሮ አማራ የሚለውን ቃል በበጎ ማንሳት የማይወደው ህወሃት ከጫካ ወደ ዙፋን በሚያደርገው ጉዞ ሁሉ በኢትዮጵያ ታሪክ የታየውን የታሪክ ዥጉርጉር በተለይ ክፉ ክፉውን ለአማራ ያስረክብ ነበር፡፡ ስልጣን ላይ ተመቻችቶ ከተቀመጠ በኋላም ያልቀየረው ሙዚቃ ይሄው አማራን ማክፋፋት፣ ማጥላላት፣ከሰው መነጠል፣ ማሳደድ፣ ማሸማቀቅ፣መግደሉን ነው፡፡ ‘ከአማራ ክፉ አገዛዝ ነፃ አወጣኋችሁ’ ሲል በየብሄራቸው አደራጅቶ ከባለጠግነቱ ትቂትም ቢሆን የከፈለላቸው የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶችም ይህንኑ ሲያስተጋቡ ኖረዋል፡፡የማፈናቀል መግደሉ ፊታውራሪ የሆኑም በርካታ ናቸው፡፡

‘የብሄር ብሄረሰቦች መሲህ ነኝ ስለነሱ እኩልነት እና ነፃነት ስል አስራ ሰባት አመት በበረሃ አይሆኑ ሆኛለሁ’ ሲል የማይደክመው ህወሃት ስልጣን ከጨበጠ በኋላ ለተቀሩት ብሄር ብሄረሰቦች አለኝ የሚለውን ተቆርቋሪነት የሚያስመሰክረው አማራውን በአደባባይ በማጥላላት፣በማዋረድና የሌለ ክፉ ስም በመጋገር ነው፡፡በህወሃት የእልቅና ዘመን የአማራን ህዝብ በሚዲያ ሳይቀር ማክፋፋት ሁለት ጊዜ የማይታሰብበት ‘መብት’ ብቻ ሳይሆን ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ ያለን ታማኝነት ማሳያ ተደርጎም ይቆጠራል፡፡ይህ ከመንደር ካድሬ እስከ ቁንጮው መለስ ዜናዊ ድረስ የሚደረግ የቤቱ ልማድ ነው፡፡ለዚህ ነው ከአማራ ህዝብ ወጥቻለሁ ብሎ ክልሉን ሊመራ የተቀመጠው አለምነው መኮንን በአንድ ወቅት ያለውን ያለው፤ካለ በኋላም ህዝብ አይንህ ላፈር እያለው አበጀህ ተብሎ በመንበሩ የፀናው፡፡ አማራ ነኝ ባዮቹ ተፈራ ዋልዋ እና በረከት ስምኦን አማራነታቸውን ቀርቶ አዛውንትነታቸውን የማይመጥን ሃላፊነት የጎደው ብዙ ብዙ ንግግር ተናግረዋል፡፡ለስብሃት ነጋ ደግሞ አማራን መወረፍ የእግዚአብሄር ሰላምታ ያህል አስደሳች እና ዘወትራዊ ነው፤አማራ ተመልሶ ስልጣን ላይ መታየት እንደሌለበት በአደባባይ ሲናገር ከአረጋዊነቱ ጋር በማይሄድ ሁኔታ ነገን ሳያስብ ነበር፡፡

ይህ የህወሃት/ኢህአዴግ ክፉ አስተሳሰብ ወደ ተቃውሞው ጎራም ተሻግሮ ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የተሰባሰቡ ታጋዮች የመሰረቱትን ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ ‘የደርግን ስርዓት መልሶ ለማምጣት የተሰባሰቡ አማሮች የመሰረቱት የአማራ ፓርቲ’ በማለት በህዝብ ዘንድ ተቀባነት እንዳይኖረው፣ በፍርሃት እንዲታይ ‘የጅቡ መጣላችሁ’ ፖለቲካውን የማጧጧፍ ልማዱ የአደባባይ ወግ ነው፡፡ ይህ ፈሊጥ ህብረብሄራዊ ነን ሲሉ በህብረ-ብሄራዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ውስጥ አባል እና አመራር በሆኑ ሰዎችም እንደሚቀነቀን አውቃለሁ፡፡ በአንድ ወቅት መድረክ በሚባለው ስብስብ ውስጥ በነበረው የአንድነት ፓርቲ እና በሌሎች ብሄር ተኮር ፓርዎች መሃከል የጦፈ ንትርክ ነበር፡፡ የንትርኩ መነሾ ደግሞ በመድረክ ስብስብ ውስጥ ‘አማሮች ሊገኑ እየሞከሩ ነው’ የሚል አስገራሚ ስጋት ነበር፡፡ ነገሩ በየሚዲያው ‘የነፍጠኛ ልጆች ተጠንቀቁ!’ የሚል አርቲክል እስከመፃፃፍ እና መወራረፍ የደረሰ የእርስ በርስ መጎሻመጥ ድረስ ደርሶ እንደነበር ፀሃይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ሲብስም በቅንጅት ውስጥ ሳይቀር በብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ‘ተቀባይነት እንድናገኝ አማሮችን ሊቀመንበር እና አመራር ባናደርግ’ የሚባል ድርድር ሁሉ እንዳለ ይነገራል፡፡ ይህ ሁሉ ከግራ ከቀኝ የሚወረወር ሃፊነት አልቦ ድርጊት እና ንግግር ተጠራቅሞ አማራውን ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ወደ አማራ ብሄርተኝነት የግድ ነፍስ የማትረፍ፣ክብርን የማስመለስ ጉዞ ነድቶታል፡፡

‘ክፉ ጠሪ ወይ ባዩን ያከፋል’

የጎሳ ብሄርተኝነት ምንጩ ዘውግን ማዕከል ያደረገ በደል ነው፡፡በደል ደግሞ በአንደበት ከማቁሰል በጥይት እስከ መግደል ይደርሳል፡፡ በእኛ ሃገር እና በአማራ ዘውግ ሁኔታ ደግሞ በመሃሉ መገለል እና መፈናቀልም አለ፡፡ከመጀመሪያው ያለ ምንም ቅጥያ በደፈናው አማራን ቀጥሎ ደግሞ የአማራ ገዥ መደብ ጠላቴ ነው እያለ በምድረበዳ ሲሰብክ የኖረው ህወሃት ስልጣን ሲይዝም ይህንኑ ባላንጣነቱን የሚያሳይበት ፈርጅ ብዙ ነው፡፡ በደሉን ሲጀምረው አዋቀርኩ ባለው የሽግግር መንግስት ላይ የአማራን ህዝብ ውክልና አሳጣ፡፡ ከዛ በኋላ ሁሉ ለመጣው በደል መሰረት የጣለበት ስልት ይህ ጅማሬ ይመስለኛል፡፡ምክንያቱም የሽግግሩ ዘመን የሃገሪቱን የፌደራል አወቃቀር ጨምሮ የወደፊት ዋነኛ ፖሊካዊ አቅጣጫ የሚተልሙ ውሳኔዎች የተሰጡበት ነበር፡፡በዚህ ወሳኝ ሰዓት ከሃገሪቱ ህዝብ ብዛት ሁለተኛ ተርታ ላይ የተቀመጠን ህዝብ ማግለል በአጋጣሚ ነው ማለት አይቻልም፤ነገ የተሰነቀውን ሆድ ስለሚያውቅ እንጅ!

ሁለተኛው ለአማራ ህዝብ የተሰነዘረ ክፉ ጥሪ ከህወሃት መንጭቶ አማራን ህዝብ ቆምኩልህ ከሚለው ኢህዴን/ብአዴን አንደበት አእንዲሰማው የተደረገው እና እስከዛሬም እየተነገረ ያለው ሃላፊነት የጎደለው ንግግር ነው፡፡ ነገሩን ሁሉ እንዳይሆን ይዞት እንደነበረ የሚነገረው ታምራት ላይኔ ‘ብአዴን የቆመው በአማራ ክልል ለሚኖረው አማራ ብቻ ነው’ ሲል በአደባባይ የሞት አዋጅ እንዳሳወጀ በዘመኑ ፖለቲካን ለመከታተል የደረሱ ሁሉ የሚመሰክሩት ነው፡፡ለራሱ የተቆፈረትን ጉድጓድ ያላወቀው ታምራት ላይኔ ብዙ ንፁሃን አማሮችን ከነነፍሳቸው ወደገደል የማስወርወሩን የአሽከርነት ስራ በደንብ ሰርቷል፡፡ ታምራትን ሳይውል ሳያድር የራሱ ስራ ጠልፎ ጥሎት አሁን ከሁለት ያጣ ሆኖ ማንንም ወደማይጠየፈው አምላክ አምባ የተጠጋ ቢሆንም በምድራዊ የፍርድ አደባባይ እስካልታየ ድረስ ክፉ ስራው ስብዕና ከሚሰመው ኢትዮጵያዊ ልቦና ውስጥ ሁሉ አይጠፋም፡፡

ክልሉ ውጭ ባለ አማራ ጉዳይ አያገባንም የተባለው የአማራ ህዝብ በመላ ሃገሪቱ በብዛት ተበትኖ እንደሚኖር ስለሚታወቅ በሰፊው የልብን ለመስራት ታስቦ ነው፡፡ በተጨማሪ የአማራ ህዝብ ታታሪነት ስለሚታዎቅ በሄደበት ለፍቶ ደክሞ ሃብት ማፍራቱም ግልፅ ነው፡፡ ያፈራውን ሃብት ዘርፎ ማፈናቀሉ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን ሽባ ስለሚየደርገው ህወሃት የማይወደውን በራስ መተማመኑን ለመንጠቅ ያስችላል፤ይሄኔ አስራ ሰባት አመት ተዋደቅንለት የሚባለው የአማራ “ትምክህት” ድል ተደረገ ማለት ነው፡፡ይህ ምኞት ሙሉ በሙሉ አልተሳካም ማለት አይቻልም፡፡ በሃገሪቱ ዳርቻ ውክቢያ የበዛበት የአማራ ህዝብ፣ የለፋበተን የእሳት እራት አድርጎ ያረጀበትን ቀየ በሃያ አራት ሰዓት ለቆ እንዲወጣ የተደረገ ህዝብ በራስ መተማመኑ አብሮት ሊኖር አይችልም፡፡

ህወሃት/ኢህአዴግ ክልልህ ነው ብሎ ከተመነለት ምድር ውጭ የሚኖረው አማራ በስነልቦና፣ በኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ተደራራቢ ቅጣት ሲቀጣ በክልሉ ያለው አማራ ደግሞ ቆምኩልህ የሚለው ፓርቲ መሪዎች ጮክ ብለው እንዲሰድቡት ሲደረግ ራሱን ጠበቃ የሌለው “ወንጀለኛ” አድርጎ ይቆጥራልና ራሱን ቀና የማድረግ ልማዱን ይተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ህወሃት ትምክህት የሚለወን ግን ደግሞ አጥብቆ የሚፈራውና የሚጠላውን የአማራን ህዝብ በራስ መተማመን ለማትነን ተሞክሯል፡፡ ይህም የታሰበውን ያህል ባይሆንም በመጠኑ ተሳክቷል፡፡ ወንድሙ ከሃገር ዳርቻ እግሩን ነቅሎ ሲሰደድ ፣ማግኘቱ አፍታም ሳይቆይ ማጣት ሆኖ ለማኝ ሲሆን ያየ በክልሉ የሚኖር አማራ ወኪልህ ነኝ በሚለው ሰው ሲሰደብ የሚቆምለት መንግስታዊ አካል እንደሌለ ተገንዝቦ በገዛ ሃገሩ የመፃተኛ መንፈስ እንዲዋረሰው ሆኗል፡፡ ይህ ታስቦበት የተሰራ የስነልቦና፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቃት ባህላዊ ገፅታም አለው፡፡

የአንድ ማህበረሰብ ስነ-ቃሎች የማህበረሰቡን የእይታ ምጥቀት፣ የአስተሳሰብ ደረጃ ጥልቀት የሚያስገነዝቡ ምስክሮች ከመሆናቸውም በላይ እንደ ህዝብ የሚደምቅባቸው ጌጦቹ፣ ራሱን የሚገልፅባቸው መተንፈሻዎቹም ናቸው፡፡ እንደ ሃገርም ተጠብቀው ጥናት እና ምርምር እየተደረገባቸው፣ እየተተነተኑ ለመጭው ትውልድ መተላለፍ ያለባቸው የሃገር ሃብቶች ናቸው፡፡ በእኛ ሃገር ሁኔታ ሁሉም ማህበረሰብ ስሜቱን የሚገልፅበት የራሱ የሆኑ ስነ-ቃሎች አሉት፡፡ከዚህ ሳይንሳዊ ሃቅ በተቃራኒው ተረት ያለው የአማራ ህዝብ ብቻ ተደርጎ ሲቀርብ ይህም የኋላቀርነት፣የነገር ወዳድነት እና የስራፈትነት መገለጫ ተደርጎ የሚያኮራው ነገር መሰደቢያ ሆኖ ኖሯል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነትን መንበር የተፈናጠጠው ሟቹ መለስ ‘የአማራ ተረት ነው ወደ ኋላ ያስቀረን’ ሲል ለሱ አንድም ንግግር ማወቅ ነው ሁለትም የሚጠላውን የአማራ ህዝብ ቅስም መስበር ነው፡፡ የአማርኛ ቋንቋ የአማራ ህዝብ ብቻ ንብረት ይመስል ቋንቋው እንደ ክፍለ-ትምህርት ተደራጅቶ ከአማራ ክልል በቀር በአብዛኞቹ የሃገራችን ዩኒቨርሲቲዎች በአብይ(major)ም ሆነ በንኡስ(minor) የጥናት መስክ ሆኖ እንዳይሰጥ መደረጉ በዘፈቀደ የተደረገ ሳይሆን ከላይ የተጠቀሰውን አማራን አኮስሶ “ትምክህቱን” ለማራገፍ ሲባል ወገብ ጠበቅ ተደርጎ የተሰራበት ጉዳይ ነው፡፡

‘አይን አፋሩ’ የአማራ ብሄርተኝነት

ያመነበትን ነገር አጥብቆ መያዝ የሚያውቀው ህወሃት/ኢህአዴግ ከመነሻው በበጎ ጠርቶት የማያውቀውን የአማራ ህዝብ በብዙ ለበቅ እየገረፈም ቢሆን የአማራ ህዝብም ሆነ ልሂቃኑ ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው የቀደመ ፍቅር እንደነበረ ቀጥሏል፡፡ሆኖም ከበደል የአማራ ብሄርተኝነተን ለመትከል ሳይሆን ከደረሰው በደል አንፃር ተሰብስቦ መላ ለማለት ፕሮፌሰር አስራት እና ጓዶቻቸው ህይወታቸውን ያስከፈለ ትግል አድርገው የመጀመሪያውን የአማራ ዘውግ ወገናዊነት ማዕከል ያደረገ ፓርቲ መስርተው ነፍስ የማዳን ትግል ጀመሩ፡፡ ይህን ትግል ሲጀምሩ ፕሮፌሰሩም ሆኑ የትግል አጋሮቻቸው የአማራ ብሄርተኝነትን ለማቀንቀን አይናፋርነት እንደነበራቸው በቅርቡ “አንፀባራቂው ኮከብ” በሚል ርዕስ በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ህይወት ዙሪያ የተፃፈው መፅሃፍ ካሰፈራቸው መረጃዎች መረዳት ይቻላል፡፡የትግላቸው መዳረሻም የአማራ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደሆነ ያስገነዝቡ እንደ ነበርም ያስረዳል መፅሃፉ፡፡

ነፍሳቸውን አስይዘው በአማራ ህዝብ ክፉ ቀናት ለትግል የታጠቁት ፕ/ሮ አስራትም ሆኑ የትግል አጋሮቻቸው በሰዓቱ ተገቢውን ስራ የሰሩ ቢሆንም የሚታይ ተግዳሮት ከብዙ አቅጣጫ ገጥሟቸው ነበር፡፡ህይወትን ጭምር የጠየቀው ተግዳሮት የመጣው ከህወሃት/ኢህአዴግ ቢሆንም ከአማራ ልሂቃንም ቀላል የማይባል እንቅፋት ገጥሟቸው ነበር፡፡ የአማራ ልሂቃን ክርክር በአማራነት መደራጀት አማራው ኢትዮጵያዊነትን ቸል ብሎ ኢህአዴግ ወደ ሰፋለት የዘር ከረጢት ሰተት አድሮጎ የሚያስገባ፣ ኢህአዴግን ድል የሚያስመታ አካሄድ ነው ባይ ነው፡፡ እንደክርክሩ ህወሃት/ኢህአዴግ በአማራ ህዝብ ላይ ያደረገውን ያደረገው የኢትዮጵያዊ ብሄርትነት ትምክህቱን ለማስጣልና ነው ይህ ደግሞ ለአማራው ሽንፈት ብቻ ሳይሆን መኮሰስም ነው፡፡ እነዚህ ተከራካሪዎች የማይመልሱት፣ አዲሱ የአማራ ብሄርተኝነት ፓርቲ (መአድ) የሚያቀርበው ተገቢ ጥያቄ ለሚሞት፣ ለሚሰደድ፣ለሚፈናቀው፣ በሃገሪቱ ዳርቻ ለሚዋከበው አማራ ማን ይቁምለት? እጣፋንታውስ ምን ይሁን ? የሚለው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የሁላችንም የሆነችውን ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ማስጠበቅ ለአማራው ብቻ የሚሰጥ ሃላፊነት አድርጎ የማሰቡ ነገር ልክ ካለመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መለምለም ሲባል አማራው ሲሞት ዝም ብሎ መታየት አለበት ለማለት የሚቃጣው ነው፡፡ ስለዚህ ፕሮፌሰር አስራት የወሰዱት እርምጃ በወቅቱ አማራጭ የሌለው እንደ ነበር ይሰማኛል፡፡

የመአአድ ወደ መኢአድ መቀየር ከመነሻው የታሰበበት በመሆኑ መኢአድ እና ሌሎች ህብረብሄራዊ ሆነን በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ባይ ፓርቲዎች የቀጠለውን የአማራ ህዝብ እንግልት ለማስቆም ለፍተዋል፡፡ ሆኖም ልፋታቸው ከጅብ እንደማያስጥለው የአህያ ባል ያለ ነገር በመሆኑ የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ ፈተና ቀጥሏል፡፡ ከጥፋቱ መማር የማይችለው ህወሃት/ኢህአዴግ በአማራ ህዝብ ላይ ያነሳውን ጨካኝ ክንዱን ማጠፍ ባለመቻሉ ለአማራ ብሄርተኝነት አይናፋር የነበረውን የአማራ ልሂቅ ፈራ ተባ ከማለት በግልፅ አንዳንዴም በከፍተኛ ምሬት እና ፅንፈኝነት የአማራ ብሄርተኝነት እንዲያቀነቅን፤ ግፋ ሲልም ነውጠኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ አመነም አላመነም የህወሃት/ኢህአዴግ እብሪት አይሉት አላዋቂነት የመራው ጥላቻን አደብ ያለማስያዝ ስህተት ውጤት ነው፡፡

“ከትምክህተኝነት” ወደ “ጥበት”?

ሃገር መውደዱ፣ ቅድሚያ ስለሁላችን ኢትዮጵያ ማለቱ ወንጀል ሆኖ በትምክህተኝት አስፈርጆ በድርብ ድርብርብ ለበቅ ሲያስገርፈው የኖረው አማራ ሃያ አምስት አመት ያጠራቀመው ፅዋ ሞልቶ እነሆ ዛሬ የአማራው ብሄረርተኝነት በአስፈሪ ፅንፍ ታጅቦ ድክ ድክ እያለ ነው፡፡ የዚህ ህዝብ ዝምታ እና ፅዋ እስኪሞላ መታገስ በገዥዎች ዘንድ ሞቶ ከመቀበር፣እንደሲጋራ ተረግቶ ከመጣል ተቆጥሮ በደል በላይ በላይ መዝነቡ ትልቁ ስህተት ነበር፡፡ ዛሬ ትናንት አይደለም፡፡ስለ አማራ የፈለጉትን መናገር አይቻልም፡፡ አማራነቱ ሲነገረው ብቻ ትዝ የሚለው የአማራ ልሂቅ ዛሬ ዛሬ የአማራን በክፉ መነሳት መታገስ ተስኖታል፡፡ ‘አማራን አስራ የምትገርፍ እንጀራ እናት ኢትዮጵያ አታስፈልገንም’ የሚል ያለወትሮ የሆነ የመገንጠል ድምፅ ከወጣት አማራ ልሂቃን አቅጣጫ እየተሰማ ነው፡፡ ስም ጋገራ የማይሰለቸው ህወሃት/ኢህአዴግ ለዚህ አዲስ የአማራ ልሂቃን ፅንፈኛ አቋም ምን ስም እንደሚያወጣለት ለመስማት ጉጉ ነኝ፤ መቼም አልሰማም አይባልም፡፡ እንደተባለው የአማራ ብሄርተኝነት ህወሃት/ኢህአዴግን የሚያስደስት ከሆነም መደሰቻው አሁን ነው፡፡

እስከመገንጠል የወጣው የባይተዋርነት እና ፅንፈኝነት አካሄድ ላይ ባልስማማም ለዘብተኛ የአማራ ብሄርተኝነት እንደሚያስፈልግ ግልፅ ይመስለኛል፡፡የሚታየው የአማራ ህዝብ ጠበቃ አልቦነት፣ የረዘመ መከራ፣ ቅጥያጣ የመንኳሰስ በደል፣እንደ ኦሪት ለምፃም ከሃገር ዳርቻ መዋከብ ወዘተ ነው ፅንፈኝነትን አይጋበብዝም ባልልም በኢትዮጵያዊነት ጥላስር ሆኖ የአማራ ህዝቡ በደል የሚያበቃበትን ትግል መታገሉ ተሻይ መስሎ ይታየኛል፡፡

ወደ ትግራይ ሰዎች… (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

(በመስከረም አበራ;e-mail meskiduye99@gmail.com )

‘በደሜ በላቤ ደማቅ ታሪክ ፀፍኩ’ ባዩ ህ.ወ.ሃ.ት ለመንገዴ መቅናት ምክንያቱ የትግራይ ህዝብ አጋርነት ነው ይላል፡፡ ይህ ግማሽ እውነት ነው፡፡በህወሃት ጥላስር ይታገሉ የነበሩት ትግሬዎች ብቻ አልነበሩም፡፡የቀድሞው የህወሃት ታጋይ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እንደሚናገሩት ስሙ አይነሳም እንጅ ከህወሃት መስራቾች አንዱ ጎንደሬ አማራ ነው፤ሰውየው በአሁኑ ወቅት በሽተኛ እና ችግረኛ ሆኖ አንዳንዴ ቤታቸው እየጠሩ እንደሚያስታምሙትና እንደሚያሳክሙት በአንድ ወቅት መስክረው ነበር፡፡በቅርቡ እንደሰማሁት ይህ ሰው በቂ ህክምና እንኳ ሳያገኝ ህይወቱ እንዳለፈ አንብቤያለሁ፡፡

ከደርግ ግፈኛነት የተነሳ ህ.ወ.ሃ.ት የሚለውን ስም እንደከልካይ ሳይቆጥር ትግሬ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም የህወሃት አባል ሆኖ ደርግን ተፋልሞ ነበር፡፡ህ.ወ.ሃ.ቶች ግን ይህን ማንሳት አይፈልጉም፡፡ከዚህ ይልቅ መላው ኢትዮጵያዊ ከደርግ ተፋልሞ ነፃነቱን ላቀዳጀው የትግራይ ህዝብ ባለ እዳ እንደሆነ፣የትግራይን ህዝብ ቤዛነት እና ጀግንነት በአንደበታቸውም በድርጊታቸውምያስተጋባሉ፡፡ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት “ኢንዶውመንት” በሚል የዳቦስም ትግራይን የፋብሪካ መክተቻ ማድረጉን ተያያዙት፡፡ ‘ምነው ይህ በረከት ለሌላው የኢትዮጵያ ምድር ቢደርስ?’ የሚል ከተገኘ መልሱ ‘የትግራይ ህዝብ በጦርነት የተጎዳ ጀግና ህዝብ ስለሆነ ይህ አይበዛበትም፤ተራ ቅናታችሁን ትታችሁ የትግራይን ልማት ሬት ሬት እያላችሁም ትቀበሉታላችሁ’ የሚል ነበር፡፡ይህን የሚሉት ስለ “እውቀት ጢቅነታቸው” በጀሌ ካድሬዎቻቸው ማህሌት የሚቆምላቸው አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ፡፡ የአቶ መለስ ጉድ የተባለ “ጥልቅ እውቀት” ጀግንነት በዘር የሚተላለፍ ቡራኬ አድርጎ ለማቅረብ የማያፍር ነው፡፡ እርሳቸው የወጡበትን ዘውግ ልዩ የሆነ የጀግንነት ቅመም እንዳለው ከአንድም ሁለት ሶስቴ በአፋቸው የተናገሩት አቶ መለስ በተግባራቸው ያደረጉት በአፋቸው ካወሩት እጅግ ዘለግ ያለ ነው፡፡

የኢፈርት እና ደጀና “ኢንዶውመንቶች” ነገር..!

አቶ መለስ የሚመሩትን መንግስት ዋና ዋና ወታደራዊ እና የሲቪል ስልጣን ለወንዛቸው ልጆች ካደሉ በኋላ ለወጡበት ዘውግ ይገባል ያሉትን ሁሉ ከማድረግ እጃቸውን አልሰበሰቡም፡፡ኢፈርት የተባለውን አደናጋሪ እና ሚስጥራዊ የንግድ ኩባንያዎች ባህር አቋቁመው ሚስታቸውን (ያለ አቅሟም ቢሆን)ይህን የፋብሪካ ባህር እንድታስተዳድር ሰየሟት፡፡ወ/ሮ አዜብ ወደ ኢፈርት ቁንጮነት ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አዛውንቱ ስብሃት ነጋና ሌሎች ትግራዊያን ኢፈርትን ዘውረዋል፡፡የኢፈርት ፋብሪካዎች ወደ ሰማኒያ የሚደርሱ ሲሆኑ አንዱም “በስህተት” እንኳን ከትግራይ ውጭ አልተገነባም፤ከትግራይ ባልሆነ ኢትዮጵያዊም ተዳድሮ አያውቅም፡፡በአንፃሩ ፋብሪካዎቹ የሚያመርቱት ሸቀጥ በመላ ሃገሪቱ ይራገፋል፣ወደባህር ማዶም ይሻገራል፡፡የፋብሪካዎቹ በአንድ ቦታ መከማቸት ከትግራይ ክልል የቆዳ ስፋት አንፃር ሲታይ ፋብሪካዎቹ ‘በስኩየር ኪሎሜትር ስንት?’ ተብለው ሊቆጠሩ ምንም ያልቀራቸው ያስመስላል፡፡ የኢፈርት በትግራይ ብቻ መከተም፣በትግራዊ አስተዳዳሪዎች ብቻ መተዳደር ጉዳይ በጣም እያነጋገረ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሌላ ወንድም “ኢንዶውመንት” በእዛው ክልል በቅርቡ ተመስርቷል፡፡የዚህ ምክንያቱ የኢፈርት ኩባንያዎች መበራከት አለቅጥ ሰፍቶ ለአስተዳደር አመች ወደ አለመሆን ግዝፈት በመድረሱ ሌላ ኢንዶውመንት እንዳስፈለገ ወ/ሮአዜብ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር፡፡የኢፈርት ግዝፈት ሊያመጣ የሚችለውን አስተዳደራዊ ውስብስቦሽ ለመታደግ “ደጀና” የተባለ ትግራይ ከታሚ ኢንዶውመንት በዚህ ከሶስት አመት አካባቢ በፊት ተቋቁሞ እነ አበርገሌን አይነት ኩባንያዎች አቅፎ ልማቱን እያሳለጠ እንደሆነ ሰርክ ይወራል፡፡ አዲሱ ደጀና ኢንዶውመንት ከአስር በላይ ኩባንያዎች በስሩ አቅፎ ታላቁን ኢፈርትን ለመፎካከር ድክ ድክ እያለ ነው፡፡

እነዚህ ኢንዶውመንቶች ከትርጉማቸው ጀምሮ ባለቤትነታቸው፣ኦዲት ያለመደረጋቸው ጉዳይ፣ በአንድ ክልል(በትግራይ) ብቻ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ምስጢር ወዘተ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ የሚያስቆጣ ጥያቄ እየሆነ ከመጣ ዋል አደር ብሏል፡፡የቀድሞው የፓርላማ አባል አቶ ተመስገን ዘውዴ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት ወቅት እነዚህ ፋብሪካዎች ኦዲት የማይደረጉበት፣የኦዲት ሪፖርታቸውም የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ለሆነው ፓርላማ የማይቀርብበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ተገቢ ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ ለዚህ የአቶ መለስ መልስ ‘እነሱ እኮ ኢንዶውመንቶች ናቸው ግልፅ ሪፖርት ማቅረብም አይጠበቅብንም’ የሚል የተለመደ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡ አቶ ተመስንም የዋዛ አይደሉምና “ኢንዶውመንት” የሚለውን ቃል ትርጉም በአማርኛ ሆነ በኦሮምኛ በአፋርኛ ሆነ በትግርኛ በፈለጉት ቋንቋ ተርጉመው እንደዚህ አይነኬ የመሆኑን ሚስጥር ያስረዱን” ሲሉ ቢወተውቱም አቶ መለስ በማስቀየስ እንጅ መልስ በመመለስ ስማይታሙ “የአራዳ” መልሳቸውን ሰጥተው አልፈዋል፡፡የሆነው ሆኖ “ኢንዶውመንት” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአብዛኛው የኮርፖሬት ፈንዶችን ለመግለፅ የሚያገለግል ፅንሰሃሳብ ነው፡፡ከሌሎች የንግድ ማህበሮች በተለየ ከኢንዶውመንት ኮርፖሬት ፈንዶች የሚገኝ ትርፍ ተመልሶ ለልማት የሚዉል እንጅ ለባለቤቶች የሚከፋፈል አይደለም፡፡ የአቶ መለስ “ኢፈርት እኮ ኢንዶውመንት ነው” የሚለው መልስም ትርፉ መልሶ ለሌላ ልማት የሚውል ነው ለማለት ይመስለኛል፡፡ ይህ በግልፅ ኦዲት ካለመደረግ ጋር የሚያገናኘው ነገር በበኩሌ አይገባኝም፡፡

የኢንዶውመንቶቹን ባለቤትነት በተመለከተ የኢፈርት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በአንድ ወቅት ‘ኢፈርት በተዘዋዋሪ የትግራይ ህዝብ ነው’ ሲሉ ሰምቻለሁ:: ‘በቀጥታስ ባለቤቱ የማን ነው?’ የሚለው እስከዛሬ ሚስጥር እንደሆነ አለ፡፡ ለጊዜው በግልፅ ወደ ተነገረን ተዘዋዋሪው ባለቤት የትግራይ ህዝብ እና የኢፈርት መስተጋብር ስንሄድ ኢፈርትን የሚያክል የፋብሪካ ባህር በትግራይ ብቻ እንዲንጣለል ያደረገው ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ ማለፍ አይቻልም፡፡ ህወሃት እንደሚለው ኢፈርት እና ደጀና በትግራይ የከተሙት የትግራይ ህዝብ ወኪል የሆነው ህወሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያፈራውን ገንዘብ ለቆመለት ህዝብ ልማት ማዋል ስላለበት ነው፡፡እዚህ ላይ ብዙ ጥያቄ አለ፡፡ አንደኛው ለህዝብ ነፃነት የታገለው ህወሃት ምን ሰርቶ ይህን ያህል ገንዘብ አፈሰ? ጠመንጃ ተሸክሞ መባተልን የሚፈልገው የትጥቅ ትግል ሲራራ ንግድ አይደለምና ጥሪት አስቋጥሮ የኩባንያ ባህር ማቋቋም ያስቻለውስ እንዴት ነው? ገንዘቡ በትጥቅ ትግል ወቅት የተገኘነው ከተባለስ የትጥቅ ትግሉ የተካሄደው በትግራይ ብቻ አልነበረምና ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ኢፈርት ያሉ ባለግዙፍ ኢንዶውመንቶች ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

የትግሬነት እና ህወሃትነት ልዩነት ትርክት ሳንካዎች

በሃገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ እንደ የትግራይ ህዝብ እና የህወሃት መስተጋብር ያለ ግራ አጋቢ፣ ብዙ እንደማነጋገሩ ፈር የያዘ መልስ ያልተገኘለት፣ለትንታኔ አስቸጋሪ ጉዳይ ያለ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ዋነኛው ምክንያት ህወሃት የኢህአዴግ ልብ ሆኖ ሃገሪቱን ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ሲዘውር ከፊት የሚያሰልፋቸው ዋና ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች ከትግራይ የወጡ መሆናቸው ነው፡፡ ይህን ነገር ህወሃት ለሁለት ጥቅም ያውለዋል፡፡ አንደኛው የወንዙን ልጆች በወሳኝ ቦታዎች ኮልኩሎ ከውልደቱ ጀምሮ የተጣባውን የዘረኝነት ዝንባሌ ያፀናበታል፡፡ በሁለተኛ እና በዋነኝነት የትግራይን ህዝብ ደጀን ለማድረግ ልቡን ማግኛ መንገድ አድርጎ ያየዋል፡፡ አሁን ያለውን ሁኔታ ለተመለከተ ለህወሃት ሁለቱም የተሳኩለት ይመስላል፡፡ለዚህ ማሳያው የህወሃት የሃረግ መዘዛ ፖለቲካ ከእርሱ አልፎ በመላ ሃገሪቱ ማርበቡ ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ የመተባበርም ሆነ ያለመተባበር፣ የመተማመንም ሆነ የመጠራጠር ምንጩ ሃረግ መማዘዝ ሆኗል፡፡ይህ በአንድ እናት ሃገር ልጆች መሃከል ከፍተኛ ያለመተማመን አምጥቷል፡፡ ሌላው ህዝብ እርስ በርሱ በጎሪጥ የሚተያይ ተጠራጣሪ ሲሆን የትግራይን ህዝብ ደግሞ የአፋኙ የህወሃት ጠበቃ አድርጎ የመፍራት አዝማሚያ ይታያል፡፡ይሄኔ ከላይ የተጠቀሰው የህወሃት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እና ያው አድሮጎ የማቅረቡ አላማ ይሰምራል፡፡ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ጋር አንድ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ምንጩ የሚታየው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡በላይኛው የውትድርና ማዕረግ ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ከትግራይ የወጡ ሰዎች መያዙ፤ በሲቪሉ ክንፍም ቢሆን ለረዥም ጊዜ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትርነትነት፣የሃገር ደህንነት ኤጀንሲ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣በስመ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመካሪነት የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን ማሾሩ፣ በአዲስ አበባ መስተዳድር ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የሃፊነት ቦታ የትግራይ ተወላጆች መበራከት፣ይህ ደግሞ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሲወገዝ አለመታየት ለተመልካች ትግሬን እና ህ.ወ.ሃ.ትን አንድና ያው አድርጎ ያይ ዘንድ ይገፋዋል፡፡አሁን ሃገራችን በምትመራበት የዘውግ ፌደራሊዝም ሁኔታ ህ.ወ.ሃ.ት ድርና ማግ ሆኖ መምራት የሚችለው የትግራይ ክልልን ብቻ መሆን ሲገባው የህ.ወ.ሃ.ት ሃያል ህልውና በአዲስ አበባም መስተዳድር ቢሮዎችም ሆነ አዲስ አበባ በከተመው የፌደራል መንግስትም ሚታይ የመሆኑ አደገኛ አካሄድ ለህወሃት መራሹ ኢህዴግ የታየው አይመስልም፡፡ባለሃብትነቱም ቢሆን ለሁሉም ባይሆንም ለትግራዊያኑ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ከሆነ ዋል አደር ብሏል፡፡

ከትግራይ የሆኑ ዜጎች በስልጣን እና በሃብት ማማ ላይ በርከት ብሎ መታየት በተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚታይበትን መንገድ በሰፊው ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡መጠኑ ቢለያይም ትግሬ ሁሉ ህወሃትን ይደግፋል፤ትግሬ ሆኖ ከልቡ የህወሃትን ሁለንተናዊ የበላይነት ማብቃት የሚፈልግ ማግኘት አይቻልም የሚለው ሙግት ነው፡፡በዚህኛው ወገን ያሉ አሳቢዎች ክርክራቸውን የሚያጠናክሩት እስከዛሬ በትግራይ ጠንከር ያለ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አለማወቁን ነው፡፡ ተከራካሪዎቹ በተጨማሪ የሚያነሱት ነጥብ ከትግራይ የሚነሱ የህወሃት ተቃዋሚዎችም ሆኑ አክቲቪስቶች እንደ ኢፈርት እና የወልቃይት ጥያቄን የተመለከተ ከህወሃት የተለያ አቋም ለማንፀባረቅ ይቸገራሉ የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል የቆሙ ተከራካሪዎች ህወሃት እና የትግራይ ህዝብ ተለያይተው መታየት እንዳለባቸው አጥብቀው ይሞግታሉ፡፡እነዚህኞቹ ለክርክራቸው ማጥበቂያ የሚያነሱት ሃሳብ የትግራይ ህዝብም የህወሃት ብልሹ አሰራር ሰለባ መሆን፣ሌላ አማራጭ ሃሳብ መነፈግ እና በአንድ ወገን ፕሮፖጋንዳ መጠለፍ፣የአብዛኛውን የትግራይ ህዝብ የድህነት ኑሮ ወዘተ ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ እና የህወሃትን አንድነት ልዩነት በተመለከተ የሚነሱት እነዚህ ጎራዎች በየፊናቸው ቀላል የማይባሉ ደጋፊዎችን አስከትለው ሲያሟግቱ የኖሩ ቢሆኑም ሁለተኛው ማለትም የትግራይን ህዝብ እና ህወሃትን ለይተን እንይ የሚለው ክርክር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው፡፡በበኩሌ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች መመናመን አብሮነታችንን የሚፈትን፣ የትግራይን ህዝብ ስጋት ላይ የሚጥል አሳሳቢ ነገር ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የህወሃትን ጥፋት የትግራይ ህዝብም አድርጎ የማየቱ ነገር በተቻለ ፍጥነት መቀየር ያለበት ነገር ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ዋነኛውን ድርሻ መውሰድ ያለበት ደግሞ ራሱ የትግራይ ህዝብ ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ ምን ይጠበቃል?

ህወሃት እርሱ በስልጣን ሰገነት ላይ ከታጣ ሌላው ኢትዮጵያዊ የትግራይን ህዝብ እሳት ሆኖ እንደሚበላው ያስፈራራል፡፡ ቀላል የማይባለው ትግራዊም ይህን ተቀብሎ የህወሃት ወንበር የተነቃነቀ በመሰለ ቁጥር ስጋት ይወርሰዋል፡፡ይህን የአብዛኛው ትግራዊ ስጋት የሚረዳው ሌላው የሃገራችን ህዝብ ትግራዊያንን የግፈኛው ህወሃት ወንበር ጠበቃ አድርጎ ያስብና የህወሃት የግፉ ማህበርተኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ ያሳያል፡፡ ይህ ህ.ወ.ሃ.ት ታጥቆ የሰራበት እና ስኬታማ የሆነ የሚመስልበት ፈለግ ነው፡፡ ይህ ነገር ግን መቆም አለበት፡፡ ነገሩን ለመቀየር ደግሞ የትግራይ ህዝብ ማሰብ ያለበት የዚህን ሁሉ መነሻ ምክንያት ነው፡፡ መነሻው የህወሃት ‘ከሌለሁ የላችሁም’ ስብከት ነው፡፡ ይህንን መመርመሩም ደግ ነው፡፡ የምርምሩ መነሻ ‘ህወሃት ሳይኖር ትግሬ አልነበረም ወይ?’ ብሎ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ ሲሆን መልሱ ትግሬ ከህወሃት በፊት ነበረ ነው፡፡ ትግሬ ከህወሃት በፊት ከነበረ ዛሬ እኔ ከሌለሁ የላችሁም የሚለው የህወሃት ዜማ እንዴት መጣ የሚለውን ማስከተልም ተገቢ ነው፡፡የዚህ ዜማ መነሻው ብልጣብልጡ ህወሃት በመላው የትግራይ ህዝብ ስም ግን ለጥቂት ትግሬዎች የሰራው/የሚሰራው አድሎ እና ዘረኝነት ነው፡፡እንደ አሸን ፈልተው ትግራይ የከተሙ የኢፈርት እና ደጀና ኢንዲውመንት ፋብሪካዎች፣በሁሉ ቦታ ብቅ የሚሉ የትግሬ ሹማምንት፣የትግሬ ብቻ የጦር ጀኔራሎች፣ቱጃር ለመሆን የሳምንት እድሜ የሚበዛባቸው ትግራዊ ባለሃብቶች መበራከት ወደ ትግራዊያን ያጋደለው የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል ማሳያዎች ናቸው፡፡ባልበላው እዳ ላለመጠየቅ የሚወድ ትግሬ ሁሉ ይህን አምኖ መቀበል ብቻ ሳይሆን ማውገዝም አለበት፡፡

ወደዚህ ልቦና ለመምጣት ሰፊው የትግራይ ህዝብ ራሱን በሌላው ኢትዮጵያዊ ጫማ ማስገባት ይጠበቅበታል፡፡ ‘እኔ ትግሬ ባልሆን ኖሮ ይህን ጉዳይ እንዴት አየው ነበር’ ብሎ ማሰብ ደግ ነው፡፡ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትር መለስ እና ደቀመዛሙርቶቻቸው ትግሬነታቸው ቀርቶ አፋር ቢሆኑና ኢፈርትን እና ደጀናን የመሰሉ የልማት ተቋማት አፋር ብቻ እንዲከቱ አድርገው፤ በአፋር አለቆች እንዲዘወሩ ቢያደርጉ፤ ይህ ሳያንስ ደግሞ የአፋር ህዝብ ለእንዲህ ያለው አስተዳደር እድሜ ሲለምን ባየው የሚሰማኝ ምንድን ነው ማለት ያስፈልጋል፡፡ከስልጣን የማይወርዱ የአፋር የመንደር ልጆች የራሳቸው ስልጣን ላይ ሙጥኝ ማለት ሳያንስ የአፋር ባለሃብቶችን የመፍጠር ፕሮጀክት ቀርፀው ሌላውን ኢትዮጵያዊ በሃገሩ ላይ ባይትዋር ቢያደርጉ ምን ይሰማኝ ነበር? የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ተብለው በፌደራል ወንበር የተቀመጡት ሰውየ የትግራይን ክልል የኢንዱስትሪ ዞን ለማድረግ እቅድ አውጥተው ነበር ተብሎ ከገዛ ባለቤታቸው ሲነገር መስማት ትግራዊ ላልሆነው ሰፊ ህዝብ ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው ወይ? ብሎ መጠየቅ አሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የሚሰማውን ስሜት ለመረዳት ይበጃል፡፡

በግሌ ከትግራዊ ወዳጆቼ እና ጓደኞቼ ጋር ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስንወያይ በአብዛኛው የሚገጥመኝ ክርክር ‘ኢፈርት ትግራይ መከተሙ ለሰፊው ህዝብ ምንም የፈጠረው ነገር የለም፡፡ የፋብሪካዎቹ ባለቤት የህወሃት ባለስልጣኖች እና ዘመድ አዝማዶች ናቸው’ የሚል ነው፡፡ ይህም ግማሽ እውነት ነው፡፡ የእነዚህ ኢንዶውመንቶች ተጠራርቶ ትግራይ ላይ መከተም ለአካባቢው ሰዎች ቢያንስ የስራ እድል መፍጠሩ በሰፊው ትግራዊ መካድ የለበትም፡፡በቀጥታ የስራዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ በተዘዋዋሪ ለከተሞች ማደግ አስተዋፅኦ አለው፡፡ የፋብሪካዎቹ መኖር የመግዛት ሃይል ያለው ተከፋይ ሰራተኛ በከተሞቹ እንዲኖር በማድረግ በቀጥታ በፋብሪካዎቹ ለመቀጠር ላልቻለው ህዝብ የንግድ እድል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ይህ ሁሉ እድል ፋብሪካ በገፍ ላልተተከለለት ሌላው ኢትዮጵያዊ ያልተገኘ ነውና የእድገት ሁኔታ መዛባት ማምጣቱ ሃቅ ነው፡፡ ይህን ክዶ መነሳት የመግባቢያን ሰዓት ከማራቅ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

ሌላው ከትግራይ ወገኖቻችን የሚገጥመኝ ክርክር ‘የህወሃት ብልሹ አሰራር የትግራይን ህዝብም መድረሻ ያሳጣ ነገር ነው’ የሚል ነው፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡የትግራይ ለፍቶ አዳሪ ድሃ ህዝብ በመዋጮ ብዛት ፍዳውን እንደሚያይ ከቦታው ከመጡ ሁሉ የሚነገር ነው፡፡ የሙስናው ነገር፣ሌላ ድምፅ እንዳይሰማ የማድረጉ አፈና ሁሉ በትግራይም ያለ ነው፡፡ ግር የሚያሰኘው ነገር ግን የትግራይ ህዝብ አለበት የሚባለውን ግፍ በግልፅ ሲቃወም አይተን አለማወቃችን ነው፡፡ ለዚህ አፈናው አያሰናዝርም የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በበኩሌ ይህ አያሳምነኝም:: ምክንያቱም ሌላው ኢትዮጵያዊም የደረሰበትን ብልሹ አሰራር የሚያወግዘው መንግስት ምቹ ሁኔታ ስለፈጠረለት ሳይሆን የደረሰበት ግፍ ብዛት አፈናውን ችላ ብሎ ድምፁን እንዲያሰማ ስለገፋው ነው፡፡ ስለዚህ የተበደለ ሁሉ በዳዮች ቀንበራቸውን እንዲያለዝቡ መጠየቁ ተፈፅሯዊ በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ድምፁን አጥፍቶ አስተዳደራዊ በደሉን እንዲጋት ያደረገው ምን እንደሆነ ትክክለኛውን መረጃ ከውስጥ አወቆች ለመስማት ጉጉት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ከትግራይ የሆኑ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ በደንብ ቢያስረዱን የትግራይ ህዝብ ያለበትን ችግር ይበልጥ ለመረዳት ይጠቅመናል፡፡

እንደ ህወሃት አገላለፅ በትግራይ የከተሙት ኢንዶውመንት ተብየዎቹ አላማ ባመጡት ትርፍ ሌላ የልማት ተቋም በትግራይ መመስረት ነው፡፡ ስለዚህ በትግራይ ልማት ልማትን እየወለደ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ለዚህ ምስክሩ በትግራይ የሚዋለዱት የፋብሪካዎች ብዛት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ፅሁፍ ስፅፍ እንኳን በ850 ሚሊዮን ብር ግዙፍ የጠርሙስ እና የብርጭቆ ፋብሪካ በእዛው ትግራይ ሊከትም እንደሆነ ትግራዊያን መኳንንት በቴሌቭዥን መስኮት እያወሩ ነበር፡፡ ከሳምት በፊት ደግሞ የመስፍን ኢንጅነሪንግ አልበቃ ብሎ የምስራቅ አፍሪካን ገበያ ታሳቢ ያደረገ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዛው በትግራይ ስራ ሊጀምር እንደሆን ሰማን፡፡ይህን እያየን “ላለው ይጨመርለታል” ብለን እንድናልፍ ከታሰበ የማይሆን ነው፡፡

በአንፃሩ በሌላው የሃገራችን ክልል የከባድ ፋብሪካዎች ተከላ ወሬ እንደ ሃምሌ ፀሃይ ተናፍቆም አይገኝ፡፡ ይህን እኔ ትግራዊ ሳልሆን ብሰማው ኖሮ ስሜቴ ዛሬ ትግሬ ሆኘ እንደሚሰማኝ ይሆን ነበር ወይ? ይህን የሚሰራው ህወሃት እድሜ ማጠርስ ያሳስበኝ ነበር ወይ?ይህን ጉልህ የተዛባ አሰራር እያዩ ዝም ማለትስ ይቻላል ወይ? የአንድ ሃገር ሰዎች ሆነን ሳለ ይህ ሲሳይ እኛጋ ያልደረሰው ለምንድን ነው ብሎ መሞገት ወንድም የሆነውን የትግራይ ህዝብ መጥላት ነው ወይ? ብሎ መጠየቅ ደግ ነው፡፡ ህወሃቶችስ ይህን የፋብሪካ መንደር በትግራይ ብቻ እንዲከትም ያደረጉት ሊጠቅሙን ነው ሊጠቀሙብን? በዚህ ሁኔታ የምናገኘው ጥቅም ምን ያህል ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው ይሆናል፤ ብሎ መመርመር ከሃዲነት ሳይሆን ብልህነት ነው፡፡

የህወሃት ወንበር ሲነቀነቅ የትግራይን ህዝብ የሚያሳስበውን ያህል የብ.አ.ዴ.ን ህልውና የአማራን ህዝብ፣የኦ.ህ.ዴ.ድ በስልጣን ላይ መሰንበት የኦሮሞን ህዝብ፣የደ.ኢ.ህ.ዴ.ን በስልጣን ላይ መታየት የደቡብ ህዝብን፣የሶ.ህ.ዴ.ፓ እድሜ የሶማሌን ህዝብ ወዘተ ያሳስባል ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡መልሱ ተቃራኒ ነው፡፡አብዛኛውን ትግራዊ የህወሃት ህልውና ክፉኛ ሲያሳስበው ሌላው ኢትዮጵያዊ እነዚህን ቆምንልህ የሚሉትን የገዥው ፓርቲ አባል/አጋር ፓርቲዎች እንደ የባርነት ወኪል አድርጎ ያያል፡፡ የእድሜያቸው ማጠር ከሚያስከፋው የሚያስደስተው በብዙ እጥፍ ይበዛል፡፡ለዚህ ከሰሞኑ በሃገራች ከተሞች ወከለናችኋል የሚሉዋቸውን የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ አባል ፓርቲዎች ለማውገዝ ጎዳና የወጣው ህዝብ ብዛት ማሳያ ነው፡፡የትግራይ ህዝብም እንደሌሎች ወንድሞቹ ቆምኩልህ እያለ ሌት ተቀን የሚሰብክ የሚያስፈራራውን ህወሃት ህፀፆች ለማውገዝ ማመንታት የለበትም፡፡ ‘ከሌሉ የለሁም’ የሚለውን አጓጉል አስተሳሰብ ትቶ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ሆኖ ህወሃትን ታገስ ተመለስ ፣ካልሆነ ለሚችል ልቀቅ መለት አለበት፡፡ ይህንንም በአደባባይ ማሳየት አለበት፡፡ በተጨባጭ የሚታየውግን ሌላ ነው፡፡

ከላይ በትቂቱ ለማሳየት የተሞከረውን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍል አንስቶ በምክንያት የሚሞግት ሰው ከአብዛኛው ትግራዊያን ዘንድ የሚሰጠው ትርጓሜ ‘እንዲህ የሚያስበው ትግሬን ስሚጠላ ነው’ የሚል ሲሆን ያጋጥማል፡፡ ይሄ ደመነፍሳዊነቱ የበዛ፣ ለመሞገት የሚያስችል የእውነት ስንቅ የማጣት የሚያመጣው የሽሽት መልስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሬ ወገኖቹን ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፡፡የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ጀማሪ፣እጅግ ሰው አክባሪ፣እንግዳ ተቀባይ ነውና የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ህዝብ የሚወድበት እንጅ ብድግ ብሎ የሚጠላበት ምክንያት የለውም፡፡ልክ ያልመሰለውን ነገር ሲጠይቅ ደግሞ ‘ይህን ያልከው እኛ ትግሬ ስለሆን’ ነው ማለት የጥላቻን መንገድ መጥረግ እንጅ ሌላ ጥቅም የለውም፡፡አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርቡ ‘የምታዩትን አድሎ እንዳላያችሁ እለፉ፤ያኔ እንደምትወዱን እናውቃለን’ ማለት አብሮነትን የሚፈትን አስቸጋሪ አቋም ይመስለኛል፡፡

ከትግራይ ህዝብ አንፃር ይህ ሁሉ ሲጠበቅ ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለትግራዊ ወንድሞቹ የሚያቀርበውን ጥያቄ የሚሰነዝረው ረጋ ብሎ፣ ጥላቻን አርቆ መሆን አለበት፡፡እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት የሆነውን መዛባት ሁሉ ያመጣው ህወሃት ከትግራይ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ተመካክሮ አይደለም፡፡ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ወደትግራይ የሚተመው ፋብሪካ ሁሉ ሲተከል ሰፊው የትግራይ ህዝብም እንደ እኛው በቴሌቭዥን ይሰማል እንጅ የሚያውቀው የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ‘ሌላውን ረስታችሁ ለእኔ ይህን አድርጉልኝ’ ብሎ አዞ ያስደረገው ነገርም አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ከትግራዊ ወንድሞቻችን ጋር ስንነጋገር ይህን ሁሉ አስበን መሆን አለበት፡፡ ‘ህወሃት የትግራይን ህዝብ አይወክልም’ ከሚለው ሾላ በድፍን የሆነ ዘይቤ ወጥተን ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ በሌሎች ነባራዊ ሃቆች ላይ ተመስርተን አፍረጥርጠን መነጋገር ያለብን ቢሆንም ንግግራችን ‘እኛ እና እነሱ’ የሚል ግድግዳ የተገነባበት መሆን የለበትም፡፡ ከዛ ይልቅ የአንድ እናት ልጆች መሆናችንን እያሰብን፤ እንደቤተሰብ ውይይት ፍቅር እና መተሳሰብ ባልተለየው መንገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አሁን እያነጋገረን ያለው ጉዳይ ረዥም ዘመን ከተጋራነው ወንድማማችነት የሚገዝፍ አይደለም፡፡ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ከስሜታዊነት የራቀ መሆን አለበት፡፡ ከስሜታችን ምክንያታችን መብለጥ አለበት፡፡ ይህ ካሆነ ዛሬ እንደቀልድ ከአንደበታችን የምናወጣው ነገር ነገ የምንፀፀትመበትን ጥፋት ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ስለዚህ ጉዟችን ሁሉ ማስተዋል የተሞላበት መሆን አለበት፡፡ በፍቅር ከመነጋገር እንጅ ከጥላቻ እና ከመጠፋፋት ትርፍ ያገኘ ህዝብ የለምና ንግግራችን ሁሉ ፍቅርን፣እርጋታን እና ምክንያታዊነትን የተሞላ መሆን አለበት፡፡ይህ ካልሆነ ህወሃትን እያገዝነው እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡

የኔታ መስፍን ምን አጠፉ?! (በመስከረም አበራ)

ByAdmin

ሰኔ 2 ፤ 2009 ዓ ም
በመስከረም አበራ (e-mail meskiduye99@gmail.com)

Meskerem Abera - article
Meskerem Abera

የይለፍ የሚወስዱበት ሰልፍ ብቻ ይመስላቸዋልና ዲግሪ በደራረቡ ቁጥር ከትናንት በተሻለ ራሳቸውን ለማገልገል፣ከሰው በልጦ ለመታየት ይታጠቃሉ፡፡ትምህርታቸው ያልሰራውን ቁስ ከየፈረንጁ ሃገር ይሰበስባሉ፡፡ ቁሱን ይበልጥ ለማጋበስ ከግፈኛ መንግስት ጋር ማህበር ይጠጣሉ፡፡ ከደም አፍሳሽ ጋር ግንባር ይገጥማሉ፤ከእናት ሃገር ሆድ ወጥተው የሷኑ ደካማ ጎን ይመታሉ፡፡

ከትናንት በስቲያ እግረኛ ወታደር የነበረ ኩሽሹን በከረባት ቀይሮ ባላዋቂ እጁ ሲያቦካው የኖረው ፖለቲካ እንደ ቂጣ ምጣዱላይ እንክትክት ሲልበት ‘ኑና ስራየ ልክ እንደ ነበረ ዱክትርናችሁን እየጠቀሳችሁ ከሙያ አንፃር አስረዱ ሲላቸው’ ሊያስረዱ ይሽቀዳደማሉ፡፡ በኢቢሲ አንድ ሁለት ቀን ካናዘዛቸው በኋላ አያያዛቸውን አይቶ፣ፍልስፍናቸው እንደ ቅማል “እራስ ደህና” ማለት እንደሆነ አጥንቶ ለሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ያጫቸዋል፡፡ “የዶክተሮች ካቢኔ አቋቋምኩ” ብሎ ከመጠላቱ በላይ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ለነሱ ክብር መስሎ ይታያቸዋልና ሹመቱ ሃሴታቸው፣የሹመቱ ቱርፋት እርካታቸው ይሆናል፡፡

የመማር ዋና አላማው በስብ መጥገብ ከሆነ ዳርቻው ይህ ቢሆን አይስገርምም፡፡ በስብ ለመጥገብ ግን መማር ግድ አልነበረም፡፡ እንደውም ለቁስ ሰቀቀን ፍቱን መድሃኒቱ፣ የቀጥታ መንገዱ ተደራራቢ ዲግሪ የግድ የማይለው የመነገድ ማትረፉ ጎዳና ነው፡፡መማር ግን ቁስ ከማንጋጋት፣ ሆድ ከመቀብተት ያለፈ ተልዕኮ ያለው ነገር ነው፡፡ መማር መንጋው ያላየውን ቀድሞ አይቶ ማሳየትን፣ባልደላው ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ድሎት እንደማይኖር የመገንዘብ ራስ ወዳድነትን የመሰናበት ልዕልና፤ለእውነት እና ለሃቅ ብቻ የመወገን እና ይሄው የሚያመጣውን ቱርፋትም ሆነ ችግር የመቀበል ልቅና ነው፡፡ይህ ልቅና በተለይ በድሃ ሃገር እንደልብ የሚገኝ አዘቦታዊ ገጠመኝ ሳይሆን እንደ ማዕድን በመከራ ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ነገር ነው፡፡

ፕ/ሮ መስፍን ወ/ልደማርያም በግብር መማራቸውን ከሚመስሉ፣ሁሉን ከሚመረምሩ፣ሳይደክሙ ከሚጠይቁ፤የቁስ ምኞት የራስ ድሎት እምብዛም ከማያስጨንቃቸው ብርቆች ወገን ናቸው፡፡ ሰውየው ከጉብዝና እስከ ሽምግልናቸው ወራት ሲፅፉ ሲሞግቱ የኖሩ የሃገር አድባር ናቸው፡፡ እውቀት ልምዳቸውን በወረቀት አስፍረው፣ በቃል ተናግረው አይጠግቡም፡፡ የተናገሩ የፃፉት ለብዙ የፖለቲካችን ህማማት መልስ አለው፡፡ ሆኖም የሚታያቸውን ለማየት፣ የሚሰማቸውን ለመረዳት አቅሙም ልምዱም የሚያጥረን ሰዎች ልንወርፋቸው እንጣደፋለን፤ የምናስበውን እንዲናገሩልን እንሻለንና ብዙ ጊዜ ባልሆኑት እንከሳቸዋለን፡፡ በበኩሌ ሰው ፍፁም ነው ብየ አላምንም፤ይህን መጠበቅም ደግ አይመስለኝም፡፡ ሰው ናቸውና ፕ/ሮ መስፍንም ሊስቱ፣ ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ወይም በእኛ ግንዛቤ ያጠፉ ሊመስለን ይችላል- ሁላችንም የግንዛቤያችን ነፀብራቅ ነንና! ይሄ ጤናማ ነው፡፡

ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

————
መጣጥፍ በዚህ ገጽ ላይ ለማውጣት በ info@borkena.com or editor@borkena.com ይላኩ። መረጃዎችን ለማግኘት የፌስ ቡክ ገጻችንን ላይ ያርጉ።

ያቺ “ባነር”….. ! ከመስከረም አበራ

ByAdmin

የጎንደሩ ጥሎሽ …

ህወሃት ሁለቱን ህዝቦች እርቅ ሊጎበኘው በማይችል የጠላትነት አዘቅት ውስጥ ለመክተት የተጠቀመው መንገድ መገናኛ ብዙሃን፣የራሳቸውን ሃላፊነት አልቦ አንደበት እና ከሁለቱም ብሄር የወጡ ግዙ ባለስልጣን እና ካድሬዎችን ብቻ አይደለም፡፡ የነመለስ ዜናዊ የጥፋት መንገድ እጅግ ረቂቅ ነውና የተስፋየ ገብረአብን ውብ ብዕርም ለዚሁ እንቅልፋቸውን ለሚነሳቸው የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት ማፍረሻ በደንብ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ተስፋየም ሃፍረት እና ይሉኝታ ባለፈበት ያለፈ ሰው ስላልሆነ ‘ነቅተንብሃል’ እየተባለም በልጅነቱ እንደማተብ የታሰረለትን የጥላቻ ክታብ ሊያወልቅ አልቻለም፤ ከቀድሞ አልባሽ አጉራሾቹ ጋር ከተጣላ በኋላም የጥላቻ ብዕሩ መርዝ መትፋቱን አላቆመም፡፡ ህወሃት ይህን ሁሉ ከንቱ ድካም ሲደክም የኖረው በአሽዋ ላይ የቆመ ቤት ለመስራት ነበርና የአንድ ቀን የህዝብ ድምፅ የሃያ አምስት አመት ድካሙን ገደል ከተተው፡፡ ከወደ ጎንደር በፍቅር ብዕር፣ በመተሳሰብ ሸማ ላይ የተከተበች አንድ ባነር ታሪክ ለወጠች፡፡ “በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው” የምትል የአቶ በቀለ ገርባን ምስል የያዘችው ባነር ስንቱ ፊደል ጠገብ አጥብቆ የፈተለውን የጥላቻ ገመድ በጣጠሰች፤በምትኩ ሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች በፍቅር እንባ አራጨች፤ ያች ባነር!!! መብቱን ከማስከበር ጎን ለጎን የጠፋ ወንድማማች/እህትማማችነትን ፍለጋ የወጣው የጎንደር ህዝብ በፍቅር ፊት መቆም የማይችለውን የህወሃት በአሸዋ ላይ የተገነባ የጥላቻ ቤት በፍቅር አውሎ ንፋስ ከስሩ ነቀነቀው፡፡የጥላቻ መንገድ አይቀናም፡፡ የሴራ ወንበር አይፀናምና ይህ የሚጠበቅ ነው፡፡የጥላቻ ሰባኪዎች ግን ይህን ይረዱ ዘንድ ብቁ አይደሉም፡፡ በወርቅ የማይገዛውን የወንድማማችነት ፍቅር “ያልተቀደሰ ጋብቻ” ሲሉ ያልተቀደሰ ጭንቅላታቸው ያቀበላቸውን ዘባረቁ፤ ፍርሃት ያራደው ከንፈራቸው ላይ የሞላውን ስድብ ሁሉ በሰፊው ህዝብ ላይ አወረዱ፡፡

yachin-banner

ኢህአዴጎች ጥሩ የተናገሩ እየመሰላቸው ከአንደበታቸው የሚወረውሯቸው ቃላት እና ሃረጋት በመንግስት መንበር ላይ መሰየማቸውን አይመጥኑም፡፡ ሌሎቹ ቀርተው የአንደበታቸው ርቱዕነት ወፍ ያረግፋል ይባሉ የነበሩት የአቶ መለስ አንደበት እንኳን በግሌ ጨዋነት የጎደለው፣ማናለብኝነት ያሸነፈው፣ አንዳንዴም ግልብ እንደነበረ ይሰማኝ ነበር፡፡በተከበረው ፓርላማ ፊት ‘ጣትህን እቆርጣለሁ፣ ምላስ እዘለዝላለሁ’ ይሉ ነበር፡፡ የሁለት አካላትን ሰላማዊ ግንኙነትም ከዕቁባታዊ ግንኙነት ጋር እየመሰሉ ማስረዳቱ ይቀናቸው ነበር፡፡ በ1997ዓም አላሰናዝር ብለው የነበሩትን አናጎሜዝን በተመለከተ ለአዲስ ዘመን እና ዘኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጦች ኤዲተር በፃፉት ማስታዎሻ “what love has to do with this” የሚለውን የታዋቂዋን ዘፋኝ የቲና ተርነርን ሙዚቃ ግጥም መንግስትነትን በማይመጥን አላስፈላጊ ሁኔታ አስገብተው ነበር፡፡

አሁን የመንግስት አንደበት ተደርገው የተሰየሙት አቶ ጌታቸው ረዳ መሆናቸው ደግሞ በኢህአዴግ መንደር ለአንደበት ጨዋነት ብዙ ቦታ እንደሌለ አሳባቂ ነው፡፡ ብሶት በጠበንጃ ፊት እንደቆመ እንኳን አስረስቶ የሚያጮኽውን የኦሮሞ ህዝብ ከጅኒ ጋር እያነፃፀሩ ሲያስረዱ ለአቶ ጌታቸው በአማርኛ መራቀቅ፤ በሃሳብ መምጠቃቸው ሊሆን ይችላል፡፡ለሰሚ ግን ትርጉሙ ሌላ ነው፡፡ አንድ ሰው በቤቱ የቀረ በማይመስል ሁኔታ ነቅሎ የወጣውን የአማራ ህዝብ ትቂት የሽፍታ ጠበቆች ሲሉ ዘለፉ፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ከተገደሉ ልጆቻቸው እኩል የተሰደቡት ስድብ አስቆጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የማያበቁት አቶ ጌታቸው ‘ሁለት ባላንጣዎች ያተቀደሰ ጋብቻ መስርተዋል’ ሲሉ አከሉ፡፡ እውነት ለመናገር ነገሩ በጋብቻ ሁኔታ ባይገለጽ ደግ ነበር:: ሆኖም ሰው በልቡ የሞላውን በአንደበቱ ይናገራልና አቶ ጌታቸው በልባቸው የሞላውን ገለፁ፡፡ነገሩ የሚገባቸው በጋብቻ ሁኔታ መገለፅ ካለበት የኦሮሞ እና የአማራ ታላላቅ ህዝቦች ቅዱስ ጋብቻ ጎንደር ላይ በቀረበችው የፍቅር ጥሎሽ (ያቺ ባነር)ተጀምሮ ኦሮሚያ ላይ “አማራ የኛ” በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ተፈፅሟል፡፡ይህ ቢመርም ሊቀበሉት የሚያስፈልግ ሃቅ ነው! በምድር ላይ የሚያስተዳድረው ህዝብ መተሳሰብ የሚያናድደው፣ክፉ የሚያናግረው መንግስት ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ “የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ይህን አይነት መፈክር ይዘው መውጣታቸው የእኛን ስራ ለ,ያለመስራት ያመላክታል” አሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ለፋና ሬዲዮ፡፡ ፋይሉ በድህረገፆች ስላለ ዝርዝሩን አንባቢዎቼ ቢያዳምጡ ሙሉ ስዕሉን ለማግኘት ይችላሉ፡፡ይህ ከአእምሮ በላይ ነው!

ቅዱሱ ጋብቻ!

የኢህአዴግን እግር ተከትሎ በሃገራችን የተንሰራፋው እትብት እየተማዘዙ የጎሪጥ የመተያየት አባዜ አሁንም የሃገራችን ፖለቲካ ዋና ነቀርሳ ነው፡፡ ችግሩ የሚመነጨውም ሆነ የሚበረታው ተማርኩ በሚለው የህብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ መማሩ ስነልቦናውን ከታሪክ ጋር እያዋቃ ጥላቻን ብቻ እንዲሰብክ ያደረገው የትየለሌ ነው፡፡እንደ ደህና ነገር ስንት ገፅ መፅሃፍ አሳትሞ በየገፁ ጥላቻን ሳይረሳ የሚሰብክ ምሁር በበዛበት ሃገር፤ኢህአዴግም ይህን በደንብ ሲያሳልጥ ሃያ አምስት አመት ከንቱ ሲደክም ቢኖርም ሰሚው ሰፊ ህዝብ ጥላቻን የሚሰማበት የጆሮ መስኮቱን ዘግቶ ኖሯል፡፡ የጎንደር ህዝብ የጀመረውን የፍቅር ምልክት የኦሮሚያ ህዝብ ወዲያው ማስተጋባቱ ድሮም ኢህአዴግ በሚያራግበውን እና ፅንፈኛ የጎሳ ልሂቃን በሚያንፀባርቁት ደረጃ ህዝቦች በጠላትነት እንደማይፈላለጉ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ሳይውልሳያድር እናንተም የእኛ ናችሁ ሲል መልስ የሰጠው በፍቅር መበለጥን ስላልፈለገ ነው፡፡በፍቅር ላለመበላለጥ መሽቀዳደም ደግሞ የመልካም ልቦና ዝንባሌ ነው፡፡ይህ ብው በሚያደርግ ንዴት ውስጥ የሚከተው ደግሞ ራሱን መመርመር ግድ ይለዋል!

ንደር እና አዳማ አፋፍ ላይ ሆነው “ደምህ ደሜ፣አጥንትህ አጥንቴ” ሲባባሉ ሌሎች ከተሞችም ይህን ሲከተሉ የኮምፒውተር “በተን” በነኩ ቁጥር ህዝብን የመሩ የሚመስላቸው የጥላቻ ሰባኪዎች የወንጀለኝነት ስሜት እንደሚሰማቸው ጥርጥር የለኝም፡፡ ወትሮም ገታራነት የማይጫናቸው የኦሮሞ ምሁራን ይህ የህዝብ መተሳሰብ የኖሩበትን የፖለቲካ አቅጣጫ እንዳስቀየራቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ሁሉም የሚሉት ‘ህዝብ መራን፤ህዝብ በለጠን፤ ህዝብ ቀደመን’ ነው ! የትምህርት ደረጃን ቆጥሮ ብዙሃኑን ህዝብ ሳይንቁ፣ እኔ አውቅልሃለሁ ሳይሉ፣ይልቅ መበለጥን አውቆ አካሄድን ማስተካልም የምሁራኑን ትህትና ያመለክታልና በተለይ የኦሮሞ ምሁራን ለዚህ ትህትናቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ያመኑት ፈረስ …..

ከህወሃት የወቅቱ ዘዋሪዎች አንዱ አይተ ኣባይ ፀሃይየ የፓርቲያቸውን አርባኛ አመት ድል ባለ ድግስ ሲያከብሩ ‘እነ ኢህአፓ ሲንኮታኮቱ እኛ ድል የተቀዳጀነው ህዝብን ለማታገል ቀለል ያለውን የጎሳ ፖለቲካ የሙጥኝ ስላልን ነው’ አይነት ንግግር ሲናገሩ ተገርሜ ነበር ያዳመጥኳቸው፡፡ህዝብን የማታገያ ዘይቤ የሚመረጠው ስለቀለለ ነው ወይስ የህዝብ እውነተኛ ጥያቄ ስለሆነ? ቀላል የተባለው የጎሳ ፖለቲካ ከምክንያት ይልቅ ስሜትን ስለሚፈልግ ብልጣብልጦቹ የህወሃት መኳንንት በጎሳህ ምክንያት የፈረደበት አማራ ቆረጠህ ፈለጠህ እያሉ የብረት ተሸካሚ፣ ወላፈን እሳት ላይ ተማጋጅ ነፍስ ለማግኘት ስለማያስቸግር ነው፡፡ስልጣን ላይ ከተሳፈረ በኋላም ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ከላይ ለመጥቀስ በተሞከረው መልክ በሃገሪቱ የሚገኙ ወንድማማች ህዝቦችን ከአንድነታቸው ይልቅ ልነት ላይ እንዲያተኩሩ ማድረጉን በቀላሉ ስልጣን ላይ ተወዝቶ የመኖሪያ ሁነኛ ዘዴ አድርጎት እንደነበር ነገራ ነገሩ ያስታውቃል፡፡ በዚሁ በጎሳ እና በጥላቻ ፖለቲካ ተፀንሶ፣አድጎ ዙፋን ላይ የተሰየመው ህወሃት/ኢህአዴግ የሚወደውን ዙፋኑን እየነቀነቀው ያለው ከጎሳ ፖለቲካ ጋር በተዛመደ የመረረ ጥያቄ መሆኑ ትልቅ የፖለቲካ አያዎ ነው!

_________
መስከረም አበራን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል : meskiduye99@gmail.com

ሼር ያድርጉ ፤ ቦርከናን በፌስ ቡክ ላይክ ያድርጉ