አስተያየት

August 11, 2024

በዓባይነህ ግርማ

አገራችን ከደሃ አገሮች ተርታ የምትሠለፍ ናት ቢባልም፣ የብዙ ሺዎች ባለሚሊዮኖችና ጥቂት የማይባሉ ባለቢሊዮኖች አገር እየሆነችም ነው፡፡ ይህ ጥሩና የሚያስደስት ዕድገት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባለሚሊዮንነቱና ባለቢሊዮንነቱ የተፈጠረው እንዴት ነው የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ በጥረት ወይም በመልካም አጋጣሚ ወይም የሌሎችን በመንጠቅ ወይም በሁሉም መንገዶች በተገኘ ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ በጥረትና መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም በተገኘ ውጤት ከሆነ ይበልጡን ደስና ባለፀጋ የሚያሰኝ ሊሆን ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ግን የሌሎችን መንጠቅ በሚያስብልና በብዝበዛ መንገድ በተገኘ ውጤት ከሆነ የሚያስከፋና የሚያስኮንን ነው፡፡

ሀብት የተገኘበት መንገድ (ተገቢ በሆነ ወይም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከመሆኑ አንፃር) ትልቅ ግምት የሚሰጠው የመሆኑን ያህል ሌላው ሊጠየቅ የሚገባ ጥያቄ አጠቃቀሙና መሣሪያነቱ እንዴት ነው የሚለው ነው፡፡ ይህም እንደ ሁኔታው በበጎ ወይም በመጥፎ ሊታይ ይችላል፡፡ ለአገራዊ ልማት ዓላማና ፍላጎት፣ ለሕዝባዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መሙያ እንዲያግዝና እንዲያገለግል ጭምር ከሆነ ሀብታምነት ይበል ያሰኛል፡፡ በርካታ ሀብታሞች/ባለፀጎች ካላቸው የገንዘብና ሌላ ሀብት ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአካባቢ ልማት ጥበቃ፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለድንገተኛ አደጋ መከላከልና መልሶ መታደግና ለሌሎች በጎ አድራጎት ሥራዎች  ልገሳ በማድረግ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

አንዳንዶች የሚያደርጉት ልገሳና ተሳትፎ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት በማሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም በላቀ አስተሳሰብ የሚሠሩት ወይም የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ ለአገራቸው ሲሉ እንደሆነ ሲመሰክሩ ይደመጣሉ፡፡ እነዚሀ መሰሎቹ ሀብታምነታቸው የገንዘብና የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን፣ የሞራል ልዕልናም ባለፀጎች ናቸውና የሚመሠገኑ ናቸው፡፡ እነዚህን መሰሎች በሚመለከት ኋላ የምመለስበት ሆኖ፣ ከእነዚህ ባንፃሩ ገንዘባቸውንና ሌላ ሀብታቸውን ለላቀ ሀብት ማጋበሻ ወይም ለሥልጣን መግዥያ ወይም ሌሎችን ለማማለል፣ እንዲያም ሲል ለመንጠቅ የሚያውሉትና ከዚያም ባለፈ ለቅንጦትና ለእዩኝ እዩኝና ጤናማ ባልሆነ አኗኗር ለሚደርስ የጤና እክል የሚዳረጉበት ነው፡፡ 

በኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት ስም የሚደረግ አስተዋጽኦና በጎነት የሚጠላ ባይሆንም በእነዚህ መሰል ባለሀብቶች የሚደረግ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነት አስተዋጽኦና ተሳትፎ አግባብነት በሌለው አስከፊ መንገድ የተገኘ ሀብትን ለመሸፈን፣ ወይም ‹‹ለመካስ ወይም ለማካካስ›› ሲባል የሚያደርጉት ከሆነ ደግሞ የባሰውን አስከፊ ይሆናል፡፡ የዚህን አስከፊነት በሚመለከት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቲዎዶር ሩዝቬልት ስለበጎነት (Benevolent Charity) የቀድሞውን ግዙፍ የሮክፌሌር ፋውንዴሽን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንዲህ ብለው ነበር ይባላል፡፡ “No amount of benevolent charities can compensate in any way for the misconduct in acquiring  the huge fortunes from monopoly in oil”. Anand Giriharadas: Winners Take It6 All: the Elite Charade of Changing the World, P.158. 

የባለሀብቶች ማንነትና በኅብረተሰብ ውስጥ ያላቸው ታዋቂነትና ዝና ባላቸው ከፍተኛ ሀብትና ገንዘብ መጠን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የማንነትን መገለጫ፣ ማለትም መልካም ምግባርንና ተግባርን የሳተ ይሆናል፡፡ የማኅበራዊ ጠበብቶች እንደሚሉት ማጋነን አይሁን እንጂ የአንዳንድ የእነዚህ መሰል ሀብታምነት (ወይም ሀብታሞች) ከሥነ ምግባር አንፃር የሞራል ድህነት ነው (ወይም የሞራል ድሆች ናቸው) ያሰኛል፡፡ አሁንም ቢል ጌትስ ‹‹ሀብትን ማካፈል ሀብትን ከማግኘት የበለጠ ከባድ ሊሆን ይችላል›› አሉ እንደተባለው ሊሆንም ላይሆንም የሚችል ቢሆንም፣ ሀብታምነት የሞራል ልዕልና አያሳጣም የሚባልበት ሁኔታና የዚህ ተምሳሌት የሆኑ ሀብታሞች ወይም ባለፀጎች በየአገሩና በየኅብረተሰቡ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ መሰል ባለሀብቶች ለየአገሮቻቸውና ኅብረተሰባቸው ከመሥራት አልፎ ተርፎ ለሌሎች የሚተርፉና የሚሠሩ ናቸው፡፡ በአገራችን በኢትዮጵያ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማት አጋር፣ የበጎ አድራጎትና የተለያዩ የሰብዓዊ አገልግሎት ለጋሾች በመሆን የሚያደርጉት ተሳትፎ በእኔ ሊገመትና ሊገለጥ የማይችል እጅግ ሰፊና ከፍተኛ ነው፡፡

ከአሜሪካ ብዙ የፊላንትሮፒስት ምሳሌዎችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሊንተን ስለመስጠት በጻፉት ቱጃሩ ዋራን ቡፌት ስለሀብታቸው አጠቃቀም አሉ ያሉትን ለመጥቀስ ያህል፣ ‹‹ዋራን ቡፌት ካላቸው ከፍተኛ ሀብት ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ ያህሉን በፊላንትሮፒ ለመስጠት ያስባሉ፣ ይህንንም ሲያደርጉ ልጆቻቸው ማንኘውንም ለማድረግ ያስችለናል ብለው ለማሰብ የሚያስችላቸውን፣ ነገር ግን ምንም ላለማድረግ የሚያስችላቸውን ያህል በቂ ሀብት ሊተውላቸው ይፈልጋሉ›› ብለዋል፡፡ ‹‹Buffett intends to give away over 95 percent of his fortune, saying he wants to leave his children “enough so they feel they could do anything but not so much they could do nothing››.

‹‹ለመኖር የሚያስፈልገኝን ማንኛውንም ሁሉ ከሀብቴ ከአንድ በመቶ ባልበለጠ ያህል ማሟላትና ማግኘት እችላለሁ›› ማለታቸውም ተጠቅሷል፡፡ ‹‹My gift is nothing; I’m just giving back surplus claims that have no value to me but can do a lot for others››. እንደነ ሮክፌለር፣ ቢል ጌትስ፣ ዜል ክራቨንስኪ የመሳሰሉት ቱጃሮች ለመኖሪያ የሚበቃቸውን ያህል በመተው ያላቸውን ሀብት ከአንድ ሦስተኛ በላይና እስከ ሙሉ በሙሉ ለዕርዳታ የሰጡ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ ቢል ክሊንተን እንደሚሉት እነዚህ ምሳሌዎች የሚያስረዱት ቢሊየነሮች ለመስጠት እስከምን ያህል ሊሄዱ ይችላሉና ሀብት ከተወሰነ ደረጃና መጠን በላይ ካለፈ፣ ለባለቤቱ ተጨማሪ የጠቀሜታ ዋጋ እንደማይኖረው የሚያስረዱ ናቸው፡፡

ልጠቅሳቸው ወደ ፈለግኳቸው ዋና ምሳሌዎቼ ስመለስ ‹‹የምሠራው ለተጨማሪ ሀብት ሳይሆን ለአገሬ ነው›› በማለት ዓላማቸውን ሲናገሩ ያደመጥኳቸውን የሦስት የቅርብና የሩቅ ምሳሌዎችን በመጥቀስ፣ ሀብታምነት የሞራል ልዕልና የማያሳጣ መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

የሩቁ ምሳሌዬ አንድ አውስትራሊያዊ ቱጃር ወይም ቢሊየነር ናቸው፡፡ እኚህ የንግድ ቱጃርና ባለሀብት አውስትራሊያ ለቻይና የምታቀርበውን የድንጋይ ከሰል ንግድ በበላይነት የሚያካሂድ የንግድ ድርጅት ባለቤት ናቸው ይባላል፡፡ በጣም ሀብታም ከመሆናቸው አንፃር የከሰል ድንጋይ ኤክስፖርቱ ምን ያደርግልዎታል ተብለው ለቀረበላቸው የጋዜጠኛ ጥያቄ የሰጡት መልስ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ ‹‹ለሥራነቱ እሠራዋለሁ፣ ለአገሬ ስል አሠራዋለሁ፣ ለገንዘብ ብዬ አልሠራውም፣ በቀን ሦስት ጊዜ የሚያስፈልገኝን ምግብ ካገኘሁ፣ ምቹ ቤትና አልጋ ካለኝ፣ ዕድለኛ ሆኜ አንድ የዘለዓለም ሚስት ካለችኝ፣ ከሕዝብና ከሕግ ጋር በመልካም ቁመና ላይ ከሆንኩ፣ እናም በእነዚህ ሁሉ የታደልኩ ስለሆንኩም ተጨማሪ ሀብት ለምን እፈልጋለሁ?›› የሚል ነበር፡፡ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሉት ‹‹I do it for work; I do it for the country; I do not do it for money; If I have enough for three decent meals a day, if I have a comfortable home and a comfortable bed, and if I am lucky and have one wife for life, and if I am in good standing with people and the law, which I do, what else do I need more money for?››

በኢትዮጵያም የቅርብ ምሳሌዎቼ በርካታ ሊሆኑ እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም መጥቀስ ባይቻልም ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንዱ ባለሀብት (ስም መጥቀስ ሳያስፈልግ) በንግዱም፣ በኢንዱስትሪውና በግብርናው ማምረቻና ማከፋፈያ፣ በኮንስትራክሽኑና በስቴት ኦፍ አርት የሆቴል አገልግሎት ዘርፎች በስፋት የሚሠሩና በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ፣ የብዙ ድርጅቶች ባላቤትና እንዲሁም ከፍተኛ ግብር ከፋይ ከመሆን ባለፈ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ሰፊና ከፍተኛ የማኅበራዊ በጎ አድራጎት የሚፈጽሙ ሲሆኑ፣ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲሉ ተደምጠው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

‹‹እኔ የምሠራው ለአገሬ ነው (አገሬ ሲሉ ኢትዮጵያን ማለታቸው ነው)፣ ድርጅቶቼና ሠራተኞቹ ሁሉ በተሰማሩበት የንግድ፣ የምርትና የአገልግሎት ሥራዎች በትጋትና በተጠያቂነት መሥራት እንዳለባቸውና ይህ ሳይሆን ቢቀር አገራቸውን፣ ሕዝባቸውንና ራሳቸውን እንደ ጎዱ የሚቆጠር ይሆናል›› የሚል ነበር፡፡ ልማታዊ ባለሀብት በመባልም የሚታወቁ ናቸው፡፡ ሌላው ባለሀብትና ኢንቨስተር በሪል ስቴትና መንገድ ኮንስትራክሽን ዘርፎች በመሰማራት በተለይ በሪል ስቴትና ግንባታ ለበርካታ ቤት ፈላጊዎች የብርሃን ዕድል የፈጠሩ፣ እንዲሁም ድርጅታቸው በሚሠራበት የገጠር ኮሙዩኒቲ የሚገኙ የእምነት ተቋማትን በማጠናከርና ለድጋፍ ፈላጊ ትምህርት ቤቶችና ተማሪዎች ሰፊ የስኮላርሺፐ ፕሮግራም የሚያካሂድ ፋውንዴሽን ባለቤት ሲሆኑ፣ የሚሠሯቸው ሥራዎች ሁሉ ለአገርና ለሕዝብ መሆኑን ሲገልጡ የተሰሙ ናቸው፡፡

የተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስለሀብታምነት በመሆኑ እንጂ በምሳሌነት እንደተጠቀሱት የምንሠራው ለአገር ነው ሲሉ ተደመጡም አልተደመጡ፣ ከጥቃቅንና አነስተኛ እስከ ከፍተኛ የንግዱ ማኅበረሰብ አካላት፣ በሩጫ ላባቸው ያፈሩትን ጥሪት በኢኮኖሚና አገልግሎት ሥራዎች ያሰሱ ስፖርተኞች፣ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደመወዝተኛ፣ ከአነስተኛው እስከ ከፍተኛው አርሶ አደር፣ ወዛደርና ሌሎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የሥራ መስክ የተሰማሩ ሁሉ እንደ የገቢ ደረጃቸው ግብር ከፋይ፣ ኢንቨስተር፣ የሥራ ዕድል ፈጣሪ፣ የማኅበራዊ በጎ አድራጊ፣ ወዘተ፣ በመሆን ከራሳቸው አልፈው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የሚሠሩ ዜጎች ሁሉ ሊጠቀሱ የሚገቡ ናቸው፡፡ እነዚህም ሁሉ የሞራል ልዕልና ተገዥዎች መሆናቸውም ይታመናል፡፡

ታዲያ ወደ ጠቀስኳቸው ምሳሌዎች ስመለስ አውስትራሊያዊው ቱጃር በጠቀስኳቸው (ባሏቸው) ነገሮች ብቻ ረክተው ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑም ባለሀብቶች ለአገራቸው በመሥራት ብቻ ይወሰናሉ ባይባልም፣ ቁምነገሩ የአስተሳሰብ ተምሳሌትነታቸው ላይ ነው፡፡ ሀብታምነት የሞራል ድህነት መሆን የለበትም፡፡ እንዲያውም ድህነትን ለመዋጋት ከሀብታምነት የተሻለ መሣሪያ የለምና ሀብታሞች የታደሉ ናቸው፡፡ እንደተጠቀሱት ምሳሌዎች የበጎ አሳቢነትና አድራጊነት ምግባርና ተግባር ካላቸውና ሲኖራቸው ማለት ነው፡፡

ሀብታምነት የሞራል ልዕልና የሚያሳጣ ወይም የሞራል ድህነት አለመሆኑን ለማስመስከር የሚከተሉትን ማሰብና ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ ሀብታምነትና ድህነት በኅብረተሰብ ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የጋራ ጉዳዮች እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ አካል ባለሀብቶች በሚያደርጉት የድህነት ቅነሳ ተልዕኮና ተሳትፎ ድህነት በቀነሰ መጠን፣ እነሱም የበለጠ ሀብታሞች ለመሆን አመቺ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል፡፡ የምርታቸውና የአገልግሎታቸው ተጠቃሚ ይበዛላቸዋል፡፡ ውጤታማም ይሆናሉ፣ ይህ ማለት ጥሩ መሥራት፣ ማትረፍና የበለጠ ሀብት ማፍራት በጎ በማድረግ እንደ ማለት ይሆንላቸዋል (Doing well in business by doing good in social purpose)፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የማኅበረሰብ ድህነት በተንሰራፋበት ኢኮኖሚና ኅብረተሰብ ውስጥ ሀብታምነት ያሰቅቃል፣ ከዚያም በከፋ ያሳማል፣ ያስወነጅላል፡፡ በድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችም ቢሆኑ ከሌሎች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸውንም ጥረት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው ማለትም ነው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች ናቸው ድህነትና ሀብታምነት የጋራ ጉዳዮች ናቸው የሚያስብለው (shared enterprise) and responsibility)፡፡

በሌላ በኩል ድህነትን በጋራ ኃላፊነት ሲባል አብሮ መደህየት ማለት እንዳልሆነና ይልቁንም አብሮ ለመክበር፣ ብዙ ሀብታሞችን ለማፍራት፣ የህሊና ተወቃሽ ላለመሆን ማሰብና መሥራት ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡ ይህን መቀበል ያለበት ባለሀብቱ ብቻ ሳይሆን ከድህነት በመውጣት ሀብታም ለመሆን የሚፈልገው ደሃውም ጭምር መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ ያም ሆኖ በተለይ ሀብታሞች የሚጠበቅባቸው የውዴታ ግዴት እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ተገቢ በሆነም ባልሆነም መንገድ ከተገኝ ሀብት ጥቂቱን ቆርሶ በዘላቂና ትርጉም ባለው የድህነት ቅነሳ ተግባር ላይ እንዲውል በማድረግ፣ እንዲሁም ተገቢ በሆነም ወይም ባልሆነም መንገድ የተገኘ ሀብት በሌሎች ህልውናና ሥነ ልቦና እንዲሁም ሰብዓዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ላይ ጎጂ ተፅዕኖ እንዳያስከትል ጥንቃቄ በማድረግ ይሆናል፡፡

በመጨረሻ በበጎም ይሁን በተቃራኒው በሀብታምነትና በሀብታሞች ላይ የሚደረግ ርብርብ ወይም ጫና ከፍተኛ እንደሆነ ማንም መገንዘብ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በከፋ ሁኔታና ደረጃ የሚታየው ድህነት በከፋበት፣ ተጠያቂነት በጎደለበት፣ መብት ሕግና ደንብ በሚጣሱበት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባልተጠናከረበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡አሁን አሁንማ በአፋኛች ለሚጠየቅ ማስለቀቂያ ጥቃት እየተዳረጉ ነው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በማናኛውም የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ዓውድና ደረጃ ያለውን፣ ሀብት ያለው ወይም ሀብት-የለሽ ሳይባል የማናኛውም ሰው የሞራል ልዕልና ድክመት ወይም ልሽቀት ምክንያትም ውጤትም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ ጠቀስኳቸው ምሳሌዎች ድህነትም የሞራል ልዕልና የሚያሳጣ ሊሆን አይችልም፣ ድሆችም የሞራል ልዕልና አላቸውና፡፡ የህሊና ድሀ አታድርገኝ ይባል የለም፡፡ የሞራል ልዕልና በሀብትና በሀብታምነት የሚለካ አይደለም፣ በምግባርና ተግባር እንጂ፡፡ ስለሆነም ማናችንም በማናቸውም ጉዳይ የሞራል ልዕልናችንን በመልካም ምግባርና ተግባር የመጠበቅ ኃላፊነት የየራሳችን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኅብረተሰቡ የሚመራባቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ሥርዓቶችና ተግባሮቻቸው የሞራል ልዕልናን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ በከፊል በጸሐፊው “ማንነት በምግባርና ተግባር – ትዝብ ለትምህርት” በሚል ርዕስ ከተዘጋጀ መጽሐፍ የተቀነጨበ ሐሳብ ሲኖረው፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው                                  abgirma323@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡