የሩሲያ ኃይል የዩክሬንን ግስጋሴ ለመግታት ወደ ኩርስክ ግዛት ሠራዊት እየላከ ነው
የምስሉ መግለጫ,የሩሲያ ኃይል የዩክሬንን ግስጋሴ ለመግታት ወደ ኩርስክ ግዛት ሠራዊት እየላከ ነው

ከ 8 ሰአት በፊት

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሠራዊታቸው የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ እያጠቃ መሆኑን ለመጀመርያ ጊዜ አመኑ።

ፕሬዝዳንቱ ትናንት ቅዳሜ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር፤ “ሠራዊታችን ጦርነቱን ወደ ወራሪዋ አገር ግዛት እየወሰደው ነው” ብለዋል።

የዩክሬን ሠራዊት ድንገተኛ ጥቃት የከፈተበት የሩሲያ ግዛት ኩርስክ የሚባለው ክልል ነው።

የዩክሬን ኃይል መጠነ ሰፊ ጥቃት ወደ ሩሲያ መሰንዘር የጀመረው ከአምስት ቀናት በፊት ነው። ጥቃቱ የሩሲያ ኃይልን አስደንግጧል ተብሏል።

የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ እና የሱሚ ክልል ዛሬ ንጋት ላይ በሩሲያ አየር ኃይል ድብደባ ደርሶበታል።

በጥቃቱ አንድ የ35 ዓመት አባት እና የ4 ዓመት ልጁ ተገድለዋል።

አንድ የ13 ዓመት ልጅን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ሰዎች ደግሞ በአየር ጥቃቱ ቆስለዋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የዩክሬን ኃይል ወደ ሩሲያ ግዛት 10 ኪሎ ሜትር ዘልቆ መግባት የቻለው ጦርነቱ ከተጀመረ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ምናልባትም በዚሁ ገፍቶ ድል ከቀናው አንዲት የሩሲያ ክልል በቁጥጥሩ ስር ሊያደርግ ይችላል።

የዩክሬን ሠራዊት ገፍቶ መምጣቱን ተከትሎ በኩርስክ ክልል ድንበር 76ሺህ የሩሲያ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጉን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሩሲያ ብሔራዊ የጸረ ሽብር ኮሚቴ አስቸኳይ ጊዜ በክልሉ ያወጀ ሲሆን ይህም የሰዎችንና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ፣ ስልኮችን ለመጥለፍና ሌሎች ገደቦችን ለመጣል ያስችላቸዋል።

ሩሲያ እንዳስታወቀችው ከአንድ ሺህ የሚልቁ የዩክሬን ወታደሮች በታንክና ሌሎች ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች ታግዘው ኩርስክ ክልል ገብተዋል። ‘ይሁንና በተገቢው ሁኔታ እየመከትናቸው ነው’ ይላሉ።

ዩክሬን በበኩሏ በርከት ያሉ ገጠራማ ከተሞችን መቆጣጠሯን፣ ሱድዣ የተሰኘችውን ከተማም ለመያዝ መቃረቧን ተናግራለች።

በማኀበራዊ ሚዲያ የተሰራጨ አንድ ምስል የዩክሬን ወታደሮች በዚሁ ግዛት የሩሲያው ጋዝፕሮም ኩባንያ ንብረት የሆነ የጋስ ማምረቻ ማእከል መቆጣጠራቸውን ያሳያል።

ቢቢሲ በእርግጥም የምስሉን ትክክለኛነት ያረጋገጠ ሲሆን ቦታው በሰሜን ምዕራብ የሱድዣ ከተማ እንደሆነ ደርሶበታል። ይህም ማለት የዩክሬን ወታደሮች ከድንበር 7 ኪሎ ሜትር ዘልቀው መግባታቸውን ያረጋግጣል።

ሩሲያ ግን ይህ ከተማ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር መውደቁን አስተባብላለች።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ የዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቆ የመግባት ሙከራ መደረጉን አምኖ ነገር ግን ‘በተገቢው ሁኔታ መክተናቸዋል፤ ሙትና ቁስለኛ አድርገናቸዋል’ ብሏል።

አሁን ጦርነት በሚደረግበት በኩርስክ ግዛት የሩሲያ ትልቅ ከሚባሉት አንዱ የሆነ የኑክሊየር ኃይል መሠረተ ልማት መኖሩ ያሳሰበው የተባበሩን መንግሥታት ኒክሊየር ኤጀንሲ ሁለቱ አገራት በተቻለ መጠን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ተማጽኗል።