
ከ 9 ሰአት በፊት
እርግጥ ነው በኦሊምፒክ ታሪክ ውስጥ ከሚነሱ እጅግ አስደናቂ ታሪኮች አንዱ ተደርጎ ይነሳል። ነገር ግን ለጀርመናዊው ረዥም ርቀት ዝላይ አትሌት ሉዝ ሎንግ ሁኔታው አስፈሪ ሊሆን ይችል ነበር።
ጄሲ ኦውንስ በ1936 ኦሊምፒክ 8 ሜትር ዘሎ ወርቁን ሲወስድ ትልቁ ተቀናቃኙ የሚባለው ግለሰብ አሸዋውን ተሻግሮ ሄዶ አቅፎ እንኳን ደስ አለህ አለው።
በወቅቱ ጀርመንን ያስተዳድር የነበረው የናዚ ፓርቲ እና አለቃው ሂትለር የአርያን ሕዝብ ከሁሉ ይልቃል ብሎ ያምናሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አስርት ዓመታትን የፈጀው የሰብዓዊ መብት ተቃውሞ ፍሬ ከማፍራቱ በፊት ሁለቱ ግለሰቦች ተቃቅፈው ደስታቸውን ገለጹ፤ ጥቁር እና ነጭ እጅ ለእጅ ተያይዘው ስታድየሙ ውስጥ ጨፈሩ።
ነገር ግን ደስታቸውን ሁሉም አልተጋራውም። ከታዳሚዎቹ መካከል አንዱ የጀርመኑ መሪ አዶልፍ ሂትለር። እየሆነ ያለው ነገር ያስደሰተው አይመስልም።
የሜዳሊያ ሽልማት ጊዜው ደርሶ ሉዝ ሎንግ የናዚ ሰላምታ እየሰጠ ኦውንስ ደግሞ በቆዳው ቀለም ምክንያት ገና ያልተቀበለችውን አገር ብሔራዊ መዝሙር በተጠንቀቅ ቆሞ እየዘመረ ነበር። ሁለቱም ምን እንደሚጠብቃቸው አያውቁም።
- አበበ ቢቂላ፡ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት17 ሀምሌ 2024
- በዓለም እና በአፍሪካ የመጀመሪያ የተባሉ የኦሊምፒክ ታሪኮችን ያስመዘገበው ኢትዮጵያዊ20 ሀምሌ 2024
- በኦሊምፒክ የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያውለበለበው እና በጋዛ ጦርነት የሞተው አትሌት27 ሀምሌ 2024
ኦውንስ እና ሎንግ በ1913 ነው የተወለዱት። ሁለቱም የአትሌቲክስ ብቃታቸው ጫፍ የደረሰው በርሊን በተካሄደው ኦሊምፒክ ነው። የሚያመሳስላቸው ይህ ብቻ ነው።
ወደ ስኬት ጫፍ ለመድረስ የተጓዙበት መንገድ እጅግ የተለያየ ነው።
ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ድንቅ ሰዎች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚቆጠረው ኦውንስ በአሜሪካዋ አላባማ ከሚገኝ አንድ ገበሬ ቤተሰብ የተገኘ ሲሆን፣ ከቤቱ 10 ሕፃናት ትንሹ ነው። አያቶቹ በባርነት የተያዙ ነበሩ።
ልጅ ሳለ ከሌሎች እኩዮቹ ጋር በመሆን ጥጥ ይለቅም ነበር። ነገር ግን ዘጠኝ ዓመት ሲሞላው ቤተሰቡ ጠቅልሎ ወደ ክሊቭላንድ ሲያቀና ትምህር ቤት ገባ። ይሄኔ ነው ለአትሌቲክስ ያለው ፍቅር እየተገለጠ የመጣው።
ታዳጊ ሳለ ጄሲ በተሰኘ ቅፅል ስሙ ነበር የሚጠራው። ጄምስ ክሊቭላንድ ከሚለው የመጣ ነው። ነገር ግን አስተማሪው ጄምስ የሚለውን ጄሴ ብለው ሰምተው ስለመዘገቡት ስሙ በጄሴ ፀና።
ኦውንስ ባገኘው ስኮላርሺፕ ምክንያት ወደ ኦሃዮ ስቴት ዪኒቨርሲቲ አቀና። አሠልጣኙ ላሪ ሽናይደርን ያገኛቸው እዚያ ነው። እኒህ ጉምቱ አሠልጣኝ ኦውንስ አስገራሚ የአጭር ርቀት ሯጭ እንዲሆን ረድተውታል።
በ1935 የሚሺጋን ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ውድድር ላይ የተሳተፈው ኦውንስ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሦስት የዓለም ክብረ-ወሰኖች ሰባበረ። 8.13 ሜትር ርዝመት የዘለለው የያዘው ክብረ-ወሰን ከ25 ዓመታት በኋላ ነው የተሰበረው።

ሎንግ ከረዥም ጊዜ ተቀናቃኙ በተቃራኒ ያደገው ነፃነት እና ምቾት በሞላው ቤት ነው። በጀርመኗ ሊፕዚግ ከተማ ያደገው ሎንግ ቤተሰቦች መካከለኛ ገቢ ያላቸው ነበሩ።
አባቱ ካርል መሐል ከተማ የመድኃኒት መደብር ነበራቸው። እናቱ ዮሀና ደግሞ እንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪ ነበሩ። የኦርጋኒክ ኬሚስትሪ አባት የሚባለው ጀስተስ ቮን ሊቢግ ዘመድ ናቸው።
ሙሉ ስሙ ካርል ሉድዊግ ኸርማን ሎንግ ነው። ነገር ግን ሉዝ በተሰኘ አጠር ያለ ስሙ ነው የሚታወቀው። አራት እህት እና ወንድም ያሉት ሉዝ ከከተማ ወጣ ብሎ ነው በሚገኘው መኖሪያ ቤት ነው ያደገው። ቤተሰቡ ደረቱን ባሰጣው ሜዳ ላይ የአትሌቲክስ ውድድር ያዘጋጅ ነበር።
ሎንግ በአውሮፓውያኑ 1928 ሊፕዚግ ስፖርትን ክለብን ተቀላቀለ። አሠልጣኙ ጆርጅ ሪችተር የረዥም ርቀት ዝላይን በደንብ አስተምረውታል። ኦውንስ የአትሌቲክስ ሕይወቱን በሩጫ ሲጀምር ሎንግ ደግሞ በረዥም ርቀት ነው ሀሁ የቆጠረው።
ሎንግ በ1933 በሃያ ዓመቱ የጀርመን ብሔራዊ ሻምፒዮን በመሆን የአገሩን የረዥም ርቀት ዝላይ ክብረ-ወሰንን ሰበረ። የበርሊን ኦሊምፒክ ሊቃረብ ጥቂት ወራት ሲቀሩት በአውሮፓ ረዥም ርቀት ዝላይ ውድድር ላይ ተሳትፎ በ7.28 ሜትር የአህጉሪቱን ክብረ-ወሰን ተቆጣጠረ።

ኦዌንስ እና ሎንግ የነበራቸው ፉክክር የመወዳደሪያ ሜዳ ላይ ብቻ አልነበረም። የፖለቲካው ውጥንቅጥም ቀላል አልነበረም።
የናዚ ጀርመን አይሁዳውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ በበርሊን ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ የለባትም የሚል ጫና እየደረሰባት ነበር።
ኦውንስ መጀመሪያ የበርሊን ኦሊምፒክ ላይ መሳተፍ የለብንም የሚል ሐሳብ ከሚያራምዱ ሰዎች መካከል ነበር። “ጀርመን ውስጥ ያሉ አናሳ ዜጎች በደል እየደረሰባቸው ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ መሳተፍ የለባትም” ሲል በወቅቱ ተናግሯል። ነገር ግን ከአሠልጣኙ እና ከአሜሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቀረበለት ምልጃ መሠረት ለመሳተፍ ተስማማ።
ጀርመን ውስጥ ደግሞ አትሌቶች ከናዚ ጀርመን መንግሥት የሚደርስባቸው ጫና እየረበታ መጥቷል። ሎንግ ብሔራዊው ቡድኑን ተቀላቅሎ ዝና ማካበት የጀመረው በ1933 ነው። አዶልፍ ሂትለር ወደ ሥልጣን የመጣውም በዚያው ዓመት ነበር።
ኦዌንስ እና ሎንግ በጣም ተጠባቂ የነበረውን ፍልሚያቸውን ሊያካሂዱ ሲዘጋጁ ነው ሂትለር በጀርመን በርሊን ኦሊምፒክ ስታድየም ታዳሚ ሆነው የተገኙት።
ኦውንስ በ7.87 ሜትር እየመራ ቆይቶ ከብዙ ፉክክር በኋላ ሎንግ ተመሳሳይ ርቀት ሲዘል ደጋፊዎች በጩኽት አቀለጡት። ነገር ግን ኦዌንስ 7.94 ሜትር በመዝለል ስታድየሙን ጭጭ አሰኘ።
ይህ ብቻ ሳይሆን በመጨረሻ ሙከራው 8.06 በመዝለል ክብረ-ወሰን ሰበረ። ይሄኔ ነው ሎንግ ሁሉን ነገር ረስቶ ተቀናቃኙን እንኳን ደስ አለህ ለማለት እየዘለለ ሄዶ ያቀፈው። የታዳሚው ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ ነበር።
የሎንግ ስሜታዊነት የጀርመን ባለሥልጣናትን ትኩረት ሳበ። የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተጠናቀቁ በኋላ የሎንግ እናት ከናዚ ምክትል ሊቀ-መንበር ሩዶልፍ ሄስ ማስጠንቀቂያ ደረሳቸው።
እንደ እናቱ ከሆነ ሎንግ “ከዚህ በኋላ ለጥቁር ሰው ክብር ሲሰጥ እንዳይታይ” ይላል ማስጠንቀቂያው። ከናዚ ጀርመን “ስለዘር የነቃ እውቀት የሌለው” ተብሎ ተፈረጀ።
ሎንግ በዓለም ሕዝብ ፊት ያደረገው ነበር የናዚ ጀርመን ፓርቲ አባላትን ማስቆጣቱ ግልፅ ሆነ። በሁለቱ አትሌቶች መካከል የሚፈጠረው ጓደኝነት ከፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ጋር የሚጣረስ ሆኖ ተገኘ።
እነሆ ይህ ከሆነ 90 ዓመታት አለፉ። የበርሊን ኦሊምፒክ ኦውንስ እና ሎንግ የተፎካከሩበት ብቸኛው ውድድር ነበር።
ኦውንስ በዚያው ኦሊምፒክ በ200 ሜትር እንዲሁም በ400 ሜትር ዱላ ቅብብል እንዲሁም በ100 ሜትር ወርቅ ደርቦ በጠቅላላው አራት ሜዳሊያ ይዞ ገባ።
ነገር ግን ከኦሊምፒክ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ስዊድን ማቅናት ሲገባው አሻፈረኝ ብሎ ወደ አሜሪካ በመመለስ የማስታወቂያ ሥራዎች ላይ መሳተፉ ያስቆጣቸው የአሜሪካ አትሌቲክ ማኅበር አባላት ሁለተኛ እንዳይሳተፍ አገዱት። በዚህ ምክንያት የአትሌቲክስ ሕይወቱ በአጭሩ ተቀጨ።
ኦውንስ ወደ አገሩ ሲመለስ የጀግና አቀባበል ቢደረግለትም አገሩ አሁንም ሙሉ ዜጋ አድርጋ ልትቀበለው ዝግጁ አልነበረችም። ምንም እንኳ አገሩን በኦሊምፒክ ቢያስጠራም አንድ ሆቴል ሲገባ ዋናው መግቢያ ለጥቁሮች አይፈቀደም መባሉ አስቆጣው።
![የሎንግ የልጅ ልጅ ጁሊያ ኬልነር ሎንግ [በስግራ] እና የኦዌንስ የልጅ ልጅ ማርሊን ዶርች [በስተቀኝ] በ2009 የበርሊን የዓለም ሻምፒዮና](https://i0.wp.com/ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/8317/live/d1d69920-53db-11ef-b2d2-cdb23d5d7c5b.jpg.webp?w=800&ssl=1)
ሎንግ ከበርሊን ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ባለቤት፣ ብሔራዊ ሻምፒዮን እንዲሁም የአውሮፓ ክብረ-ወሰን ባለቤት ሆኖ ተመለሰ። ነገር ግን ደስታውን ሲገልጥ ባሳየው ድርጊት ምክንያት ከወቀሳ እና እገዳ አልዳነም።
ሎንግ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አትሌትነቱን ትቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ጥብቅና ሥራው አመራ። ታናሽ ወንድሙን ሃይንሪሽ በጦርነቱ ያጣው ሎንግ በ1941 ትዳር መሥርቶ የመጀመሪያ ልጁን ሃይንሪሽ ሲል ሰየመው።
በዚህ ጊዜ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት እንዲሳተፍ ትዕዛዝ ተሰጠው። በግዳጁ መሠረት ወደ ጣልያኗ ሲሲሊ ከተማ አቀና። በዚህ ወቅት ሚስቱ ሁለተኛ ልጃቸውን አርግዛ ነበር።
በ1943 ጣልያንን ነፃ ለማውጣት የመጣው የምዕራባውያን ጥምር ኃይል ወደ ሲሲሊ ከተማ በማቅናቱ ከፍተኛ ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህ ጦርነት ሎንግ እግሩን ተመትቶ ወደቀ። ሽሽት ላይ የነበሩት የጀርመን ኃይሎች ጥለውት በመሄዳቸው ብዙ ደም በማጣቱ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ኦውንስ በሁለተኛው ጦርነት ላለመሳተፍ ወሰነ። በግዳጅ እንዲሰማራም ጥሪ አልተደረገለትም። ነገር ግን በአትሌቲክስ እንዳይሳተፍ በመታገዱ፤ ከማስታወቂያ የሚያገኘው ገቢም በመሟጠጡ ምክንያት ቤተሰቡን ለመመገብ አማራጭ መፈለግ ያዘ።
መኖሪያ ቤቱ አካባቢ ያሉ ፈጣን ሯጮችን ይፈልግ እና 10 አሊያም 20 ጫማ ቀድመውት እንዲሮጡ ያደርግና ቀድሟቸው በመግባት ገንዘብ ይቀበላቸው ጀመር። ከሰው ብቻ ሳይሆን ከሞተር ብስክሌት፣ ፈረስ እና ከተሽከርካሪዎችም ጭምር ይወዳደር ነበር።
“ሰዎች አንድ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ባለቤት ከፈረስ ጋር መፎካከሩ አሳፋሪ ነው ይላሉ። እና ምን ላድርግ? አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች አሉኝ። ነገር ግን የወርቅ ሜዳሊያ ምግብ አይሆን” ብሎ ነበር።
ነገር ግን በ1950ዎቹ ሕይወት እየተቃናለት መጣ። በአነቃቂ ንግግሮቹ መታወቅ የጀመረው ኦውንስ ዓለም አቀፍ የስፖርት አምባሳደር ሆኖ በየክፍለ ዓለማቱ ይዘዋወር ጀመር።
በዚህ ምክንያት ወደ ጀርመን ያቀናው ኦውንስ የኦሊምፒክ ጓደኛው ሎንግን ሞት ተረዳ። ነገር ግን ከሚስቱ እና ከሎንግ ወንድ ልጅ ካይ ጋር ተገናኝቶ መጣ።
ኦውንስ በ1976 ከፕሬዝደንቱ የሚሰጠውን ‘ሜዳል ኦፍ ፍሪደም’ የተሰኘ የነፃነት ኒሻን ተሸለመ። ቢሆንም ባደረበት የፀና የካንሰር በሽታ ምክንያት ከአራት ዓመታት በኋላ በ66 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
በ2016 በጊዜው ፕሬዝደንት የነበሩት ባራክ ኦባማ የአውንስን ቤተሰቦች ወደ ዋይት ሐውስ ጋብዘው ኦውንስ እና ሌሎች የ1936 በርሊን ኦሊምፒክ ጥቁር አትሌቶች ያላገኙትን ክብር ሰጧቸው።