ክሪስቲና ሲማኑስካያ
የምስሉ መግለጫ,ክሪስቲና ሲማኑስካያ

ከ 9 ሰአት በፊት

“በቶኪዮ ኦሊምፒክ የቤላሩስ ብሔራዊ ቡድን አባል ነበርኩ” ትላለች አትሌት ክሪስቲና ሲማኑስካያ። “አሁን ፓሪስ ላይ ደግሞ ፖላንድን እወክላለሁ” ብላለች።

እአአ በ2021 የ27 ዓመቷ አትሌት በትውልድ አገሯ ሊደርስባት የሚችለውን እስራት በመፍራት በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጥገኝነት ከጠየቀች በኋላ ዓለም አቀፍ ትኩረትን አገኘች።

የቤላሩስ ባለሥልጣናት ያለፈቃድዋ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ በ400 ሜትር የዱላ ቅብብል እንድትሳተፍ ማድረጋቸውን ተከትሎ ሐምሌ 2021 ላይ ሲማኑስካያ በኢንስታግራም ገጿ ውሳኔውን ተቸች።

ይህንን በማድረጓም አትሌቷ ወደ ቤላሩስ እንድትመለስ በግዳጅ ወደ ቶኪዮ አየር ማረፊያ እንደተወሰደች ገለጸች።

አውሮፕላን እንዳትሳፈርም በአየር ማረፊያው ያሉ ፖሊሶች ጥበቃ እንዳስፈለጋት ተናግራለች።

ከክስተቱ በኋላ የቤላሩስ ባለሥልጣናት ሲማኑስካያ “በስሜታዊነቷ እና ሥነ ልቦናዊ ሁኔታዋ” ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ ተወግዳለች ሲሉ ገለጹ። እሷ ግን ይህንን አስተባብላለች።

በየካቲት ወር የቤላሩስ ኦሊምፒክ ዋና አሠልጣኝ ዩሪ ሞይሴቪች ሲማኑስካያ ከኦሊምፒኩ መውጣቷን ተከትሎ በነበራቸው ሚና ምክንያት ለአምስት ዓመታት ታገዱ።

አትሌቷ ጥገኝነት መጠየቋ ፈታኝ ውሳኔ ነበር ስትል ገልጻለች። ቤተሰቦቿን እና ጓደኞቿን ካለማግኘት ባለፈ የአትሌቲክስ ሕይወቷን ሊያቋርጠው የሚችልም ጭምር ነበር። ግን ምንም አማራጭ አልነበራትም።

“አያቴ በስልክ ወደ ቤላሩስ ከመመለስ በቀር ማንኛውንም ነገር እንዳደርግ ነገረችኝ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

“የሙያ መጨረሻ ብቻ ሳይሆን መደበኛ ሕይወቴ መጨረሻ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም ምን እንደሚጠብቀኝ አላውቅም ነበር።”

ክሪስቲና ሲማኑስካያ በቶክዮ
የምስሉ መግለጫ,ክሪስቲና ሲማኑስካያ በቶክዮ

ጥገኝነት መጠየቅ

ሲማኑስካያ ከኦሊምፒኩ በፊት የቤላሩስን የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን በመቃወም በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ተሳትፋ እንደነበር ትናግራለች።

የሩሲያ የቅርብ አጋር የሆኑት ፕሬዚደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ማሸነፋቸውን ካወጁ በኋላ በቤላሩስ ተቃውሞ ተቀስቅሷል። በዚህም የተነሳ አንዳንድ የሲማኑስካያ ጓደኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል።

የቤላሩስ ባለሥልጣናት ከውድድሩ በፊት በተደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራት ያውቁ እንደነበር ተናግራለች።

“ስለዚህ ወደ አገሬ ብመለስ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ እንደሚሆን ተረድቻለሁ” ትላለች።

ሲማኑስካያ በቶኪዮ አውሮፕላን ማረፊያ ፖሊስን ካነጋገረች በኋላ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴን (አይኦሲ) እርዳታ ጠየቀች። በኋላም በፖላንድ ጥገኝነት መጠየቅን መረጠች።

ከስፖርታዊ ውድድሮች በኋላ ወደ አገራቸው ሳይመለሱ ከደኅንነት እና ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ወይም የተሻለ ሕይወት ፍለጋ በሚል ጥገኝነት ከሚጠይቁ አትሌቶች መካከል አንዷ ናት።

ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ
የምስሉ መግለጫ,ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ

የተሻለ ሕይወት ፍለጋ

በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ [በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2021 ተራዝሟል] የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሳበችው ሲማኑስካያ ብቻ አልነበረችም።

ኡጋንዳዊው ክብደት አንሺ ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ ከጃፓን የቅድመ ኦሊምፒክ ማሠልጠኛ ካምፕ ጠፋ። በኋላም “ቤተሰቡን ለመደገፍ ሥራ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አድርጎ እንደነበር” ገልጿል።

“ኡጋንዳ ውስጥ ምንም ነገር አልነበረኝም። ባለቤቴ ነፍሰ ጡር ነበረች። ገንዘብ የማገኝበት መንገድ አልነበረኝም” ሲል ሴኪቶሌኮ ለቢቢሲ ተናግሯል። “ቤተሰቤን መደገፍ አልችልም ነበር” ብሏል።

የኡጋንዳ ባለሥልጣናት “አገርን አዋርደሃል” በሚል ከኦሊምፒክ እና ከኮመንዌልዝ ውድድሮች አገዱት።

ሴኪቶሌኮ አክሎም “ስለእውነት ለመናገር አእምሮዬ በዚያን ወቅት አይሠራም ነበር” ብሏል።

የ24 ዓመቱ ወጣት በድሃ አገራት እንዳሉት ስፖርተኞች ሁሉ በአትሌቲክስ ሕይወቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ኑሮውን ለማሸነፍ ይቸገር እንደነበር ተናግሯል።

ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ
የምስሉ መግለጫ,ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ

ቶኪዮ በነበረበት ወቅት በመጨረሻው የኦሊምፒክ ተሳታፊ ቡድን ውስጥ አለመካተቱን በዓለም አቀፉ የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ተነገረው። የኡጋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ወደ ኡጋንዳ እንዲመለስ ዝግጅቱን አጠናቀቀ።

የኡጋንዳ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በመጀመሪያ መግለጫቸው ሴኪቶሌኮ ወደ ጃፓን የገባው ለውድድሩ መብቃቱ ከመረጋገጡ በፊት እንደሆነ አስታወቀ።

ይሁን እንጂ ጁሊየስ መወዳደር አለመወዳደሩን ሳያረጋግጡ ወደ ቶኪዮ የወሰዱትን ባለሥልጣኖች ተጠያቂ አድርጓል።

ሴኪቶሌኮ ወደ ቶኪዮ ለሚደረገው ጉዞ ገንዘብ ለማግኘት ለሥራ ይጠቀምበት የነበረውን ሞተር ሳይክሉን እንደሸጠ ተናግሯል። ሆኖም በቶኪዮ ሳይወዳደር እንዲወጣ ተጠየቀ።

ከጠፋ በኋላ በጃፓን ሥራ ፍለጋ ለሦስት ቀናት ሲንከራተት ቆየ። ቦርሳው ውስጥ ከያዘው ትንሽ ምግብ ውጪ ምንም አልያዘም ነበር።

“ከክፍሌ ስወጣ ጥቂት ኬኮችን እና ሙዝ ቦርሳዬ ውስጥ ከተትኩኝ።”

ወደ ኡጋንዳ እንዲመለስም እሱን መፈለግ ተጀመረ።

ሴኪቶሌኮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ቆይቶ ተለቀቀ።

ክብደት አንሺ አህመድ ሳዳም ሁሴንን በመቃወም እና እገደላለሁ በሚል ፍራቻ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠየቀ።

1948 የለንደን ኦሊምፒክ
የምስሉ መግለጫ,የ1948 የለንደን ኦሊምፒክ

የጥገኝነት ጠያቂዎች ታሪክ

እአአ በ1948 በለንደን በተካሄደው ኦሊምፒክ የቼኮዝሎቫኪያ የጂምናስቲክ አሠልጣኝ ማሪ ፕሮቫዝኒኮቫ በአገሯ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉን ተከትሎ በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት ጠየቀች።

እአአ በ2021 የዓለም ዋንጫ የእግር ኳስ ማጣሪያ በምያንማር እና በጃፓን መካከል በቶኪዮ ጨዋታ እንዲደረግ ቀጠሮ ተይዞ ነበር።

የምያንማሩ ግብ ጠባቂ ፒያ ያን አንግ በአገሩ የተደረገውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም ሦስት ጣቶቹን ከፍ አድርጎ አነሳ።

በቀጥታ በቴሌቪዥን የተላለፈው የእጅ ምልክት ቁጣ ቀሰቀሰ።

ከጨዋታው በኋላ አንግ ተመልሶ ወደ አገሩ ቢሄድ ለሕይወቱ በመፍራት በጃፓን ጥገኝነት ጠየቀ። በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ጥገኝነት ተሰጠው።

ብዙ ተመሳሳይ አጋጣሚዎችን መዘርዘር ይቻላል።

እአአ በ2011 ደግሞ ሁሉም የሴኔጋል እግር ኳስ ቡድን አባላት ለወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታ ካቀኑበት የፈረንሳይ ሆቴል ጠፉ።

በ2012 የለንደን ኦሊምፒክ 21 አትሌቶች እና አሠልጣኞች ጠፍተዋል።

በ2018 በአውስትራሊያ በተካሄደው የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች 13 አፍሪካውያን አትሌቶች ጠፍተዋል።

ስማኑስካያ
የምስሉ መግለጫ,ክሪስቲና ሲማኑስካያ

የስደተኞች ሕግ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሠረት ጥገኝነት ጠያቂ ማለት ግጭትን ወይም አደጋን ሸሽቶ ድንበሮችን አቋርጦ ደኅንነትን የሚጠይቅ እና ወደ አገሩ መመለስ የማይችል ሰው ነው።

ስደተኛ የሚለው ቃል አዲስ ሕይወት ለመጀመር ወይም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ተስፋን ለመፈለግ በሚል ወደ ሌላ አገር ለመሄድ የሚመርጥ ሰውን ያመለክታል።

የአውስትራሊያ ጥገኝነት ጠያቂዎች ማዕከል ባልደረባው ጃና ፋቬሮ “ስፖርተኞች በአገራቸው የሰብአዊ መብታቸው ከመጣስ እና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከመጠየቅ ነጻ አይደሉም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የ2032 ኦሊምፒክን የምታስተናግደው አውስትራሊያ በተለይ ከ2018 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች በኋላ በርካታ አትሌቶች ጥገኝነት ሲጠይቁ ተመልክታለች።

ፋቬሮ አክለውም ወደ አውስትራሊያ የሚደርሱበት መንገድ ምንም ይሁን ምን ሁሉም ጥገኝነት የመጠየቅ ሕጋዊ መብት እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የአውስትራሊያ የጥገኝነት ጉዳይ አከራካሪ ነው።

የፋቬሮ ድርጅት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ ጥገኝነት የሚሹ አትሌቶችን ረድቷል።

የ2022 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች
የምስሉ መግለጫ,የ2022 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎች

“የማያቋርጥ አስከፊ ዑደት”

በስሪላንካ የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የ2022 የኮመንዌልዝ ጨዋታዎችን ጨምሮ በርካታ ውድድሮች ላይ የአገሪቱ ስፖርተኞች ጠፍተዋል።

የሲሪላንካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር የነበሩት ዶ/ር ፕራቲባ ማሃናማሄዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንድ ሰው ለጥገኝነት ብቁ ባያደርጉትም፤ ብዙ ስፖርተኞች ጠፍተው ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ሕይወት ለመስጠት ተስፋ ያደርጋሉ።

በዚህም ምክንያት ስፖርቱን ለመተው ፈቃደኞች ናቸው ብለዋል።

የሕግ እና የሰብአዊ መብት ባለሙያው እንደሚሉት አንድ ስፖርተኛ አንዴ ከጠፋ በሌላ እንደሚተካ ቢያምኑም እነሱም መጥፋትን ሊመርጥ ይችላል።

አትሌቶች በሚወዳደሩበት ወቅት ለቤተሰቦቻቸው ማኅበራዊ ዋስትና እና ደኅንነት እስኪያገኙ ድረስ ይህ “አስከፊ ዑደት” እንደሚቀጥል ያምናሉ።

ስማኑስካያ ከፖላንድ የቡድን አጋሮቿ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሲማኑስካያ ከፖላንድ የቡድን አጋሮቿ ጋር

“ምርጫ የለም”

ብዙ አትሌቶች የሚያጋጥሟቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ብዙውን ጊዜ በውድድሮቹ ደማቅ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ይደበቃሉ።

ጁሊየስ ሴኪቶሌኮ ወርሃዊ የቤት ኪራይ ለማግኘት እየታገለም ቢሆንም የዘንድሮውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለማየት ወደ ፈረንሳይ ለመጓዝ ተስፋ ነበረው።

ያለፈውን ትቶ አንድ ቀን እራሱን እንደስፖርተኛ እንደሚያሳይ ተስፋ ያደርጋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ስማኑስካያ ደግሞ በዚህ ዓመት ለፖላንድ ለመወዳደር በዝግጅት ላይ ትገኛለች።

ድጋፍ ባታገኝ ወይም የፖላንድ ዜግነት ባይሰጣት ኖሮ ከስፖርቱ ትለያይ እንደነበር ገልጻለች።

“በዓለም ዙሪያ ሰዎችን አንድ የሚያደርገው የኦሊምፒክ ውድድር ነው” ትላለች።

“እንደ እኔ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ። እንደ እኔ ያሉ ስፖርተኞች አንዳንዴ አማራጭ አይኖራቸውም። አንዳንድ ጊዜ ራሳችንን ለማዳን ብቻ ከአገራችን መሸሽ ይኖርብናል” ብላለች።