የፓሪስ ኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች
የምስሉ መግለጫ,በኦሊምፒክ ሁለት የውድድር ስፖርቶች ያሸነፉ አትሌቶች ከሜዳልያ በላይ የሚያገኙት ነገር አለ

ከ 9 ሰአት በፊት

ዘመናዊው ኦሊምፒክ እአአ በ1896 በአቴንስ ሲጀመር ምንም ዓይነት ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ወይም የገንዘብ ሽልማት የማይፈቀድበት አማተር ውድድር ነበር።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ግን በዓመት በመቶ ሚሊዮን ዶላሮችን ከሚያፍሱት እጅግ ባለጸጋ ከሆኑት ስፖርተኞች ጀምሮ በስፖርቱ ለመቀጠል እስከሚንገዳገዱት ድረስ የሚሳተፉበት ሆኗል።

ስፖርተኞቹ ከተለያዩ ምንጮች ገንዘብ ማግኘት ይችላሉ። ከስፖንሰሮች፣ ከየአገሮቻቸው ከሚያገኙት የገንዘብ ሽልማቶች እና ለመጀመሪያ ጊዜም ከኦሊምፒኩ የሽልማት ገንዘብ ያገኛሉ።

በሁሉም ስፖርቶች ግን ገንዘቡ አይገኝም። ይህም ውድድሩ የሚያመነጨውን ሃብት እንዴት በተሻለ ሁኔታ መከፋፈል ይቻላል የሚለውን ጥያቄ ይፈጥራል።

ቦክስ እና አትሌቲክስ

በሴቶች 100 ሜትር ወርቅ ያሸነፈችው ዩሊየን አልፍሬድ
የምስሉ መግለጫ,በሴቶች 100 ሜትር ወርቅ ያሸነፈችው ዩሊየን አልፍሬድ 50 ሺህ ዶላር ታገኛለች

በፓሪስ 2024 ከተደረጉ የኦሊምፒክ 32 የስፖርት ውድድሮች መካከል የገንዘብ ሽልማት የሚሰጠው በአትሌቲክስ እና በቦክስ ብቻ ነው።

የዓለም አትሌቲክስ በፓሪስ 2024 የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎች 50 ሺህ ዶላር እንደሚያገኙ በሚያዝያ ወር አስታውቆ ነበር።

ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ዓለም አቀፉ የቦክስ ማኅበር (አይቢኤ) ለኦሊምፒክ ሻምፒዮናዎች 100 ሺህ ዶላር በሽልማት መልክ እንደሚሰጥ ተናግሯል። ከዚህ ውስጥ አንድ አራተኛው ለስፖርተኞቹ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፤ ሌላው አንድ አራተኛ ገንዘብ ደግሞ ለአሠልጣኞች ይሰጣል።

በሁለቱም የስፖርት ዓይነቶች የብር እና የነሐስ ሜዳልያ አሸናፊዎች አነስተኛ ገንዘብ ያገኛሉ። በቦክስ ውድድር እስከ አምስተኛ የሚወጡ ተወዳዳሪዎች ይሸለማሉ።

የሽልማት ገንዘቡ በቀጥታ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚመጣ ሳይሆን ከሁለቱ ዘርፎች የሚገኝ ነው።

የዓለም አትሌቲክስ ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) የሚያገኘውን የተወሰነ ገንዘብ እየተጠቀመ ነው። ይህ ገንዘብ ቀደም ሲል ስፖርተኞችን ለማፍራት ይውል የነበረ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች የሽልማት ገንዘብ መጀመሩ ትክክለኛ ውሳኔ ስለመሆኑ ጥያቄ አላቸው።

የኮቨንትሪ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ቶም ባሰን “ገንዘቡ ለአሸናፊዎቹ መሰጠቱ ምናልባትም ስም ያላቸው ስፖርተኞች በድንብ እየተከፈላቸው መሆኑን የሚያጠናክር ሊሆን ይችላል” ብለዋል ።

“የወርቅ ሜዳሊያዎችን እያሸነፉ ያሉት ቀድሞውንም ጥሩ የስፖንሰርሺፕ እና የሽልማት ገንዘብ ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።”

ከትችቶቹ አንዱ ይህ ገንዘብ በውድድሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ይልቅ ለታዳጊ ስፖርተኞች ገንዘብ በመስጠት ስፖርተኞችን በመደገፍ በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚለው ነው።

አንዳንድ የኦሊምፒክ ሻምፒዮናዎች ጭምር በአስቸጋሪ የፋይናንስ ሁኔታዎች ውስጥ ስለሚገኙ በገንዘብ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በኦሊምፒክ ውድድሮች አራት የወርቅ እና ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን ያገኘችው የሶቪየት ኅብረት የጅምናስቲክስ ተወዳዳሪዋ ኦልጋ ኮርቡት በችግር ምክንያት ሦስት ሜዳሊያዎቿን በ333 ሺህ 500 ዶላር በ2017 ለመሸጥ ተገዳለች።

ለቦክስ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት ምንጭ ብዙም ግልጽ አይደለም። ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ በቅርብ ጊዜ ከአይቢኤ ጋር ያለውን ግንኙነት “የፋይናንስ ግልጽነት እጦት” ሲል በገለጸው ምክንያት አቋርጧል።

“እንደ ሁልጊዜውም የአይቢኤ ገንዘብ ከየት እንደሚመጣ ግልጽ አይደለም” ሲል ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ዶ/ር ባሰን አክለውም “አይቢኤ ይህን የሚያደርገው ራሳቸውን የኦሊምፒክ አካል አድርገው ለማቆየት ለመሞከር ነው” ብለዋል።

ብሔራዊ ኩራት

የሲንጋፖር ተወዳዳሪዎች ከፍተኛ ሽልማት ያገኛሉ
የምስሉ መግለጫ,የሴንጋፖር የኦሊምፒክ ስፖርተኞች ሜዳሊያ ካሸነፉ ከፍተኛ ሽልማት ከአገራቸው መንግሥት ያገኛሉ

ስፖርተኞች በኦሊምፒክ ሜዳልያ በማሸነፋቸው የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙባቸው ሌሎች ብዙ ነባር መንገዶች አሉ።

በርካቶች መድረኩ ላይ ለሚያስመዘግቡት ድል በየአገራቸው ይሸለማሉ።

ሲንጋፖር ለስፖርተኞቿ ፍተኛ ሽልማት የምትሰጥ አገር እንደሆነች ይታመናል። በፓሪስ የወርቅ ሜዳልያ የሚያገኙ ስፖርተኞች 750 ሺህ ዶላር ያገኛሉ።

አስተናጋጇ ፈረንሳይ 80 ሺህ ዩሮ ትሸልማለች። የሞሮኮ ስፖርተኞች ደግሞ ከ200 ሺህ ዶላር ከፍ ያለ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።

አሜሪካ ደግሞ “በዘመቻ ወርቅ” ፈንድ 37 ሺህ 500 ዶላር ትሸልማለች።

እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አንዳንድ አገራት ምንም የገንዘብ ሽልማት አይሰጡም።

እነዚህ ሽልማቶች ግን ትልልቆቹ ስፖርተኞች ከሚያገኙት ገቢ አንጻር ዝቅተኛ ነው።

“ራሳቸውን ለመደገፍ የትርፍ ጊዜ ሥራ ካላቸው ስፖርተኞች ጀምሮ እንደ አሜሪካ የቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ያሉ ከፍተኛ ደሞዝ የሚያገኙ ስፖርተኞች ይሳተፉበታል” ብለዋል ዶ/ር ባሰን።

የኮከቦች ጉልበት

ሌብረን ጄምስ
የምስሉ መግለጫ,የቅርጫት ኳስ ተጫዋቹ ሌብረን ጄምስ በኦሊምፒክ ከተሳተፉ ስፖርተኞች መካከል ከፍተኛው ተከፋዮች መካከል አንዱ ነው

እንደፎርብስ መጽሔት ዓመታዊ ስፖርተኞች ገቢ ዝርዝር ከሆነ ስፔናዊው ጎልፍ ተጫዋች ጆን ራህም በፓሪስ 2024 ከፍተኛ ተከፋይ ሆነ ስፖርተኛ ነው።

ስፖርተኛው ባለፈው ፈረንጆች ዓመት 218 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘ መጽሔቱ ይገምታል። አብዛኛው ገንዘብ የተገኘው ከሳዑዲ አረቢያው አወዛጋቢ የሊቭ ጎልፍ ተሳትፎ ነው።

በማያስደንቅ ሁኔታ ሁለተኛው ከፍተኛ ክፍያ የሚከፈለው የአሜሪካው ቅርጫት ኳስ ኮከብ ተጫዋቾች ሌብረን ጀምስ ነው። በዚህም 128 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘ ይታመናል።

በኦሊምፒክ መወዳደር የሚያገኙት ገቢ ለራህም እና ለጀምስ ባላቸው ሀብት ላይ ምንም ተጽእኖ አያሳድርም።

ነገር ግን ብዙም የማይታወቁ ስፖርተኞች ሜዳልያ ማግኘታቸው የገቢ ጭማሪ እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል።

የስፖንሰር ውል ሲፈራረሙ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሲያገኙ ተጨማሪ ጉርሻ እንደሚያገኙ ውላቸው ላይ ይሰፍራል።

እነዚህ ምሥጢራዊ ቢሆኑም እአአ በ2016 በናይኪ እና በኒው ባላንስ መካከል በተፈጠረ የሕግ ክርክር ወቅት አሜሪካዊው ሯጭ ቦሪስ ቤሪያን በኦሊምፒክ ወርቅ ካሸነፈ 150 ሺህ ዶላር ጉርሻ ሊቀበል መዘጋጀቱ ተገልጾ ነበር።

“ብዙ ሰዎች የዩናይትድ ስቴትስ ወይም በአውሮፓ ቡድኖች የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን እያዩ በሳምንት 100 ሺህ፣ 200 ሺህ ዶላር እንደሚያገኙ ያስባሉ። እውነታው ግን ይህ አይደለም” ይላሉ ዶ/ር ባሰን።

“ለመኖር የሚታገሉ ብዙ ስፖርተኞች አሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአውስትራሊያ አንድ ጥናት ተደርጎ ነበር። በጥናቱ መሠረት ለ2032 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሚሰለጥኑ አትሌቶች 40 በመቶ የሚሆኑት የትርፍ ጊዜ ወይም የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዳላቸው አረጋግጧል።”

የዓለማችን ሀብታም ስፖርተኞች መኖሪያ በሆነችው አሜሪካ እንኳን በርካታ ስፖርተኞች በኑሮ ትግል ላይ ናቸው።

የአሜሪካ ኦሊምፒክ እና ፓራሊምፒክ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ጥናት 26.5 በመቶ የሚሆኑት ስፖርተኞች በዓመት ከ15 ሺህ ዶላር በታች ገቢ ያገኛሉ ብሏል።

የፓሪስ መለያ አይፍል ማማ እና የኦሊምፒክ ዓርማ
የምስሉ መግለጫ,የፓሪስ ኦሊምፒክ ሜዳልያዎች ከአይፍል ማማ የተወሰደ ትንሽ መጠን ያለው ብረት ተካቶባቸዋል

ፌደሬሽኖችን ገንዘብ ለታላላቅ ስፖርተኞች በሽልማት መልክ መስጠት አሁንም አከራካሪ ሆኖ ይቀጥላል። ምናልባትም ከአትሌቲክስ እና ከቦክስ ውድድር ባሻገር ሊሰፋ ይችላል።

“በእርግጥ የሽልማት ገንዘብ እንዲከፍሉ ፌዴሬሽኖች ላይ ጫና ይኖራል” ይላሉ ዶ/ር ባሰን።

ነገር ግን ይህ አነስተኛ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ለሚያገኙ ስፖርቶች የሚያገኙት ገቢም ስለሚያንስ ችግር ሊፈጥር ይችላል።

“አትሌቲክስ እና ቦክስ በዓለም ላይ ከፍተኛ ታዋቂነት ካላቸው ስፖርቶች መካከል ናቸው” ብለዋል ዶ/ር ባሰን። “ከስፖንሰርሺፕ እና ድጋፍ ሰጪዎች ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ቀላል ከሆኑት ስፖርቶች መካከል ናቸው።”

“ለምሳሌ እንደ ታንኳ ቀዘፋ ያሉ ሌሎች ስፖርቶች ለስፖርተኞቻቸው ክፍያ እንዲከፍሉ ጫና ከበዛባቸው በቀላሉ መክፈል የመቻላቸው ነገር አጠያያቂ ነው።”

የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ለዚህ ዓመት አሸናፊዎች የሚሰጣቸው የወርቅ ሜዳሊያ በራሱ ሊያጽናናቸው ይችላል።

ሜዳልያዎቹ ይዘት እና ዋጋቸው

የወርቅ ሜዳልያዎች ከአውሮፓውያኑ 1912 ጀምሮ ሙሉ ወርቅ ሆነው አያውቁም፤ የዘንድሮው ወርቅ ሜዳልያ 505 ግራም ብር እና ስድስት ግራም ወርቅ አለው። የገበያ ዋጋቸውም 950 ዶላር ገደማ ነው።

የፓሪስ ኦሊምፒክ አሸናፊዎች ግን ከዚህም በላይ የድል ፌሽታቸው በዋጋ ሊተመን የማይችል እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።

በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ለተወዳደሩ አሸናፊ አትሌቶች በሚሰጡት ሜዳልያዎች ውስጥ ለመታሰቢያነት የፓሪስ መለያ ከሆነው የአይፍል ማማ የተወሰደ ትንሽ መጠን ያለው ብረት እንደተካተተበት ይነገራል።