
ከ 8 ሰአት በፊት
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት እንጂ በምርጫ ቦርድ ዳግም መመዝገብን እንደማይቀበል አስታወቀ።
ፓርቲው ይህን ያለው ከቀናት በፊት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ በቦርዱ በልዩ ሁኔታ መመዝገቡ ብቻ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በዚህ ዓመት ግንቦት መጨረሻ በጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ መሠረት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነትን መመለስ የሚል ባለመኖሩ ጥያቄው ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልጿል።
ህወሓት በበኩሉ ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አቅርቦ የነበረው ጥያቄ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ እንጂ ዳግም መመዝገብ አለመሆኑን በማስታወስ “ጥያቄው ሌላ መልሱ ሌላ” ሲል የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ተቃውሟል።
ዓርብ ዕለት የወጣው የምርጫ ቦርድ መግለጫ፤ የተሻሻለው አዋጅ “በአመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ በመሆኑ ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ አልተቀበለውም” ብሏል።
የትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ሦስት ወራት ገደማ በኋላ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በምርጫ ቦርድ መሰረዙ ይታወሳል።
- “የወርቅ ሜዳልያው የራሴ ብቻ ሳይሆን የሲሳይም አደራ ነው” ታምራት ቶላከ 9 ሰአት በፊት
- በኦሊምፒክ ሜዳልያ ማሸነፍ ዋጋው ስንት ነው? በኦሊምፒክ ማሸነፍስ ገንዘብ ያስገኛል?ከ 9 ሰአት በፊት
- የሂትለርን ዘመን ጥሶ ለዘመናት መሻገር የቻለው፤ የበርሊን ኦሊምፒክስ የወለደው ጓደኝነትከ 9 ሰአት በፊት
ህወሓት፣ ግንቦት መጨረሻ ላይ የጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት እንደማይመለስ በመገንዘቡ በጉዳዩ ላይ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ፓነል ውይይት ላይ እንዲሁ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።
ይሁን እንጂ ቦርዱ የተደረሱ መግባባቶችን ወደጎን በመተው ጥያቄውን በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣ አዋጅ ላይ ተመስርቶ የሰጠውን ምላሽ አልቀበልም ብሏል።
ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ የፓርቲው ሕገ-ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዝ ሥራዎችን ያከናውናል ያለ ሲሆን የፌደራል መንግሥቱም የማስተካከያ እርምጅ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የህወሓት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ይህን ያሉት ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ቦርዱ ፓርቲው ዳግም መመዝገቡን ይፋ ያደረግበትን መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ለቦርዱ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው።

አቶ ጌታቸው “የምዝገባ ጥያቄው” የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው እንደሆነ ገልጸው “እኛ ለዚሁ ምዝገባ ብለን የፈረምነው ምንም ዓይነት ሰነድ ሳይኖር፣ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው ከድርጅቱ አሠራር ውጪ የፈፀሙት ያልተገባ ተግባር መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን” ሲሉ ቅዳሜ ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም. ለምርጫ ቦርድ በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም ምርጫ ቦርዱ የደረሰው ማመልከቻም ሆነ የፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና ፊርማ የያዘው ሰነድ “የምዝገባ ጥያቄ ግለሰቦቹ እኛን ሳያስፈቅዱ የፈፀሙት መሆኑን እየገለጽን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለእነዚህ ግለሰቦች የሰጠው ምዝገባ በተጭበረበረ ማስረጃ መሠረት በመሆኑ መልሶ እንዲመረምረው እንጠይቃለን” ብለዋል።
አቶ ጌታቸው ይህንን ቢሉም የህወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የፈረሙበት የድርጅቱን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት ለመመለስ የሚጠይቅ ደብዳቤ ሐምሌ 19/2016 ዓ.ም. ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገብቶ በቦርዱ ምላሽ ተሰጥቶበታል።