ታምራት ቶላ
የምስሉ መግለጫ,ታምራት ቶላ ከባዱን ውድድር በክብረ ወሰን ጭምር በማሻሻል ሲያሸንፍ

ከ 9 ሰአት በፊት

ሰኔ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ ኦሊምፒክ የሚወዳደሩ አትሌቶችን የመጨረሻ ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ የታምራት ቶላ ስም በማራቶን በተጠባባቂነት ነበር የተያዘው። ስለዚህም በኦሊምፒክ ላይ የመሳተፉ ነገር እርግጠኛ አልነበረም።

ሲሳይ ለማ፣ ዴሬሳ ገለታ እና ቀነኒሳ በቀለ በወንዶች ማራቶን በኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው ለመወዳደር የተመረጡ ሲሆን፣ ታምራት ቶላ ደግሞ አንዳች ነገር ተፈጥሮ ክፍተት ቢፈጠር በሚል በተጠባባቂነት ነበር የተያዘው።

ይህ የኦሊምፒክ ውድድር የሁሉም አትሌቶች በዘመናቸው ተሳትፈው ካሻነፉ በታሪክ የሚመዘገቡበት ካልሆነም የኦሊምፒክ ስፖርተኛ በመሆን ለሌሎች ውድድሮች የመሳተፍ በር የሚከፍቱበት የታሪካቸው ዋነኛ ውድድር ነው።

ስለዚህም ሦስቱ ቀዳሚ ተመራጭ አትሌቶች ባላቸው አቅም ሁሉ እራሳቸውን ጠብቀው አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ በሚመጣው በታላቁ ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ ስለሚዘጋጁ ተጠባባቂዎች ዕድል የምግኘት ዕድላቸው ጠባብ ነው።

ቀነኒሳ የመጨረሻው ኦሊምፒክ በሚሆነው ፓሪስ ላይ ታላቅ ድል ለማስመዝገብ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ የኦሊምፒክ ማራቶንን በማሸነፍ ታሪክ ለመሥራት ከተዘጋጀው ኬንያዊው ኪፕቾጌ ጋር ይፎካከራል። በጥሩ አቋም ላይ ያሉት ሲሳይ እና ዴሬሳ ደግሞ አዲስ የኦሊምፒክ ታሪክ ለመሥራት ይፈልጋሉ።

በዚህም ምክንያት ታምራት በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያን መሻነፍ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ክብረ ወሰን የማሻሻል ተስፋ አልነበረውም። ነገር ግን ልምምዱን እየሠራ የሚፈጠር አጋጣሚ ካለ መጠበቅ ብቻ ነበር ዕጣ ፈንታው።

ጉልበትን የሚባርከው እግዚያብሔር ነው ሲል ለቢቢሲ የተናገረው ታምራት “እሱ ላይ እምነት ጥዬ ነበር ልምምዴን ጠንክሬ ስሠራ የነበረው” በማለት ተስፋ ሳይቆርጥ እስከ መጨረሻው መጠበቁን ገልጿል።

የሲሳይ ውለታ ለታምራት

በፓሪስ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር አሸናፊ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት ኬንያዊው የሁለት ኦሊምፒኮች አሸናፊ ኢሉድ ኪፕቾጌ፣ አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ቀነኒሳ በቀለ ወይም ሌላው ኬንያዊ ቤንሰን ኪፕሩቶ ነበሩ።

ያልተጠበቁ አትሌቶች ብቅ በሚሉበት የማራቶን ውድደር ኢትዮጵያ ከቀነኒሳ በተጨማሪ ሲሳይን እና ዴሬሳን ይዛ ብትቀርብም፤ ሲሳይ ቀደም ባለ ውድድር ላይ ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ ፓሪስ ላይ አገሩን ለመወከል የሚያስችለው ሁኔታ ላይ አልነበረም።

በውድድሩ ላይ በመሳተፍ ውጤት ሳያመጣ ጉዳቱን ከማባባስ እና የሌላ አትሌት ዕድልን ከመሻማት ይልቅ ቦታውን ለታምራት ቶላ የመልቀቅን ታላቅ ውሳኔን ሲሳይ ወስኖ ከውድድሩ ወጣ። ይህም በውጤት ድርቅ የተመታውን የኢትዮጵያ ቡድንን አንገት ቀና የሚያደርግ ድል እንዲገኝ ምክንያት ሆነ።

ምንም እንኳን ተጠባባቂ ቢሆንም ታምራት ለማራቶን ውድድር የሚያስፈልገውን ጠንካራውን ልምምድ እየሠራ ነበር። በዚህ ጊዜ አብሮት ልምምድ የሚሠራው ሲሳይ በቦስተን ውድድር ወቅት በእግሩ ላይ አጋጥሞት በነበረው ጉዳት ሳቢያ ፓሪስ ላይ መሳተፍ እንደማይችል እና ታምራትን እንዲተካው መጠየቁን ሰማ።

“ሲሳይ እኔ ይሄ የፓሪስ ውድድር ‘ይቀርብኝ፤ አንተ ብትወዳደር የተሻለ ነው’ ብሎ ነው ቦታውን ለእኔ የለቀቀልኝ” በማለት ለቢቢሲ የተናገረው ታምራት፤ ሲሳይ ይህንን ትልቅ እና አስቸጋሪ ውሳኔ ባይወስን ኖሮ ታምራት በተጠባባቂነቱ ወደ ፓሪስን ላይሄድ ወይም ፓሪስን አይቶ ብቻ ነበር የሚመለሰው።

ቅዳሜ ነሐሴ 4/2016 ዓ.ም. የፓሪሱ ኦሊምፒክ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን ሲቀረው ሁለት የብር ሜዳሊያ ብቻ በማግኘቱ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተተቸ ያለው የአገሪቱ ኦሊምፒክ ቡድንን አንገት ቀና የሚያደርግ ውጤት በታምራት ተመዘገበ።

በአምስት ሺህ እና በ10 ሺህ የሚጠበቁ ውጤቶች ያልተሳኩለት እና በውዝግብ ሲታመስ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን መሪ የሆኑት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኦሊምፒክ ኮሚቴው ላይ ከባድ ውግዘት ሲዘነዘር ቆይቷል። በርካቶችም በውጤቱ አዝነው ተስፋ በቆረጠ ስሜት ነበር የቅዳሜውን ውድድር የተከታተሉት።

የሜዳልያ ሥነ ሥርዓት

ያልተጠበቀው ታምራት

በርካታ ኢትዮጵያውያን በወንዶቹ የማራቶን ውድድር ለራሱም ለአገሩም ታሪክ በመሥራት አንገታቸውን ቀና ያደርግልናል ብለው ተስፋ የጣሉት ቀነኒሳ ላይ ነበር። ከኬንያውያኑ የሚገጥመውን ፉክክር እንዴት የወጣዋል በሚልም ዐይናቸው እሱን ሲከተል ነበር ያረፈደው።

ነገር ግን ያልጠበቁት ኮከብ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ከፊት ሆኖ በመምራት ሌላ ተጨማሪ ተስፋን ከታምራት ቶላ በኩል ለመመልከት ችለዋል።

በዚህ የዓለም ማራቶን ባለክብረ ወሰኑ እና የሁለት ተከታታይ ኦሊምፒኮች አሸናፊውን ኪፕቾጌን ሳይቀር አቋርጦ እንዲወጣ ባስገደደው አስቸጋሪ በተባለው ውድድር ላይ ተፈትኖ ታምራት በመጨረሻ ላይ ድልን ተቀዳጀ።

ይህ ድል ደግሞ ነጠላ ድል አልነበረም ታምራት 42 ኪሎ ሜትሩን በ2 : 06 : 26 በሆነ ጊዜ በማጠናቀቅ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን አሻሽሏል።

ታምራት በ2008 ዓ.ም. ብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ላይ በተካሄደው ኦሊምፒክ ላይ በ10 ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ያሸነፈ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በማራቶን ታላቅ ድል አስመዝግቧል። ለዚህ ደግሞ ጓደኛው ሲሳይ ለማ ባለውለታው መሆኑን ደጋግሞ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“እሱ [ሲሳይ] ይህንን ውሳኔ ባይወስን ኖሮ እኔ በእሱ ተትክቼ ለዚህ ድል መብቃት አልችልም ነበር። በጣም ነው የማመሰግነው እግዚአብሔር ያክብረው፤ ለዚህ እንድበቃ ዕድሉን የከፈተልኝ እሱ ነው።”

በኦሊምፒክ የረጅም ርቀት ሩጫ ውድድሮች ላይ በሴቶች እና በወንዶች የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ይሆናሉ ከሚባሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ናት። ነገር ግን ይህ ግምት ፓሪስ ላይ ዕውን አልሆነም። ቢሆንም ግን የታምራት የማራቶን ድል ለበርካቶች መጽናኛ ሆኗል።

ታምራትም ይህ ወርቅ ሜዳልያ ለአገሩ እና ለራሱ ብቻ ሳይሆን በጉዳት በውድድሩ ላይ ያልተሳተፈው የአትሌት ጓደኛው ሲሳይ ለማም ነው ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ህልሜንም አሳክቼበታለሁ። ነገር ግን ያገኘሁት የወርቅ ሜዳልያ የራሴ ብቻ ሳይሆን የሲሳይ አደራ ውጤት ነው። በጣም ነው የማመሰግነው።”

ታምራት ቶላ

አስቸጋሪው ውድድር

በፓሪስ የነበረው ሙቀት እጅግ ከባድ ነበረ። ይህ ደግሞ 42 ኪሎ ሜትሮችን ለሚሮጡት የማራቶን ተወዳዳሪዎች እጅግ ፈታኝ በመሆኑ የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊው ኪፕቾጌ ተናገሯል።

በውድድር ዘመኑ እንደዚህ ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት እንደማያውቅ የገለጸው ኪፕቾጌ፣ የሦስት ተከታታይ ኦሊምፒኮች ማራቶን በማሸነፍ ታሪክ ሊሠራ ይቅር እና ውድድሩን ሳይጨርሱ ካቋረጡ 10 ሯጮች መካከል ለመሆን ተገዷል።

ታምራት ከመጀመሪያው አንስቶ በውድድሩ ላይ የነበረው ጽናት አድናቆትን አስገኝቶለታል። እስከ 35 ኪሎ ሜትር ድረስ ከፊት የመውጣት ሃሳብ ያልነበረው ሲሆን፣ ቀድመው የሚወጡ ሯጮች እንዳያመልጡት ግን እግር በእግር ሲከተላቸው ነበር።

መጀመሪያ ላይ ጣልያናዊው አትሌት ተነጥሎ ሲወጣ “እየራቀ የሚሄድ ከሆነ ሊያመልጥ እና አስቻጋሪ ሊሆን ስለሚችል ልከተለው እና ሌሎች እንዲደርሱ አድርጌ ወደ ኋላ እመለሳለሁ ብዬ ነበር” ይላል ታምራት።

ጣልያናዊውን ሲደርስበት ሌሎችም ተከትለውት ነበረ። ታምራት ወደፊት ብቻውን ተነጥሎ ከመሮጥ ይልቅ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅሎ የሩጫውን ሂደት በጥንቃቄ ሲከታተል አንድ ጃፓናዊ ሯጭ ተነጥሎ ከፊት ሲወጣ እሱንም ተከትሎት ወጣ።

“ዳገት ላይ ስንደርስ እሱ ብዙም መግፋት ስላልቻለ ፈጣሪ ይረዳኛል ብዬ ወስኜ ወደፊት ሄድኩኝ። ዳገቱ ከብዶኝ ነበር፤ ነገር ግን ዳገቱን ስጨርስ ብርታት አግኝቼ ወደ ፊት ገሰገስኩ” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከዚያ በኋላ ከፊት በመሆን አብዛኛውን ኪሎ ሜትር የሮጠው ታምራት “41ኛው ኪሎ ሜት ላይ ስደረስ ነው እንደማሸንፍ የተሰማኝ” በማለት ለድል የበቃበትን ሁኔታ ይገልጻል።

የትራክ እና የጎዳና ላይ የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪ የሆነው ታምራት ቶላ ከስምንት ዓመት በፊት በብራዚል ሪዮ በተደረገው የኦሊምፒክ ውድድር ላይ በ10 ሺህ ሜትር ሦስተኛ ሆኖ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቶ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2022 በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ታምራት በማራቶን የተወዳደረ ሲሆን፣ ዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ላይ በተካሄደው የብር ሜዳሊያ፣ ዩጂን አሜሪካ በተደረገው ደግሞ የውድድሩን ክብረ ወሰን በማሻሻል ወርቅ አሸንፏል።

በተጨማሪም ታምራት በቶኪዮ እና በለንደን የማራቶን ውድድሮች ላይ ሦስተኛ በመሆን የጨረሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት (2023 እአአ) የኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶንን ክብረ ወሰን በመስበር አሸናፊ ሆኗል።