ትዕግስት አሰፋ
የምስሉ መግለጫ,ትዕግስት አሰፋ ከኔዘርላንዷ እና ኬንያዊያን አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር አድርጋለች

ከ 6 ሰአት በፊት

በፓሪስ ኦሊምፒክ መዝጊያ ዕለት በተካሄደው እና ጠንካራ ፉክክር በታየበት የሴቶች ማራቶን ትዕግስት አሰፋ ለኢትዮጵያ ብር አስገኘች።

ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ሲፈን ሐሰን የኦሊምፒክ ሪከርድን በማሻሻል ወርቁን የግሏ አድርጋለች።

በውድድሩ ማብቂያ ላይ ትዕግስት እና ሲፈን ጠንካራ ፉክክር አድርገው ሲፈን 2፡22፡55 በሆነ ሰዓት የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን በማሻሻል ጭምር አሸንፋለች።

እስከ ውድድሩ ፍጻሜ ድረስ ትዕግስት እና ሲፈን ጎን ለጎን ሲሮጡ የነበሩ ሲሆን በመጨረሻው መታጠፊያ ላይ ሲፈን ትግስት አሰፋን ከመንገዷ እንድትወጣ ገፍታት ካለፈች በኋላ ፍጥነቷን በመጨመር ውድድሩን አሸንፋለች።

ሲፈን ሐሰን በዚህ የኦሊምፒክ ውድድር በ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል።

አትሌት አማኔ በሪሶ አምስተኛ ሆና ጨርሳለች።

sifan hassan

በማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ትዕግስት ከሲፈን በሦስት ሰከንዶች ተቀድማ 2፡22፡58 ገብታለች። ኬኒያዊቷ ሄለን ኦቢሲ ደግሞ 2፡23፡10 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ጨርሳለች።

አትሌት ትግስት አሰፋ እና አማኔ በሪሶ ሻንኩሌ ለኔዘርላንድ ከምትሮጠው ሲፈን ሐሰን እና ከኬኒያዊያኑ ሄለን ኦቢሪ እና ሻሮን ሎኬዲ ጋር ጠንካራ ፉክክር ሲያደርጉ ነበር።

አምስቱ ማራቶን ሯጮች እስከ 40ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ሳይለያዩ ሲሮጡ ነበር።

ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ በኢሊምፒክ መድረክ በሴቶች በማራቶን ወርቅ ያገኘችው ከ12 ዓመታት በፊት በ እውሮፓውያኑ 2012 ለንደን ኦሊምፒክ በቲኪ ገላና አማካይነት መሆኑ ይታወቃል።

ትናንት በተደረገ የወንዶች የማራቶን ውድድር አትሌት ታምራት ቶላ በዚህ ውድድር ለአገሩ ወርቅ በማስገኘት የኦሊምፒክ ክብረ ወሰንን አሻሽሏል።

ታማራት ቶላ በፓሪስ ኦሊምፒክ በማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ሲያስገኝ የእነ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴን እና ገዛኽኝ አበራን ታሪክ በመቀላቀል ስሙን ከታላላቆቹ አትሌቶች ጎን እንዲመዘገብ አድርጓል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በፓሪስ ኦሊምፒክ 800 ሜትር በጽጌ ዱጉማ አማካይነት ብር፣ በበሪሁ አረጋዊ በ10ሺህ ሜትር ብር፣ በታምራት ቶላ በማራቶን ወርቅ እንዲሁም በትዕግስት አሰፋ በማራቶን የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።