የዩክሬን ወታደሮች
የምስሉ መግለጫ,በሱሚ ክልል የሚገኝ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በርካታ የዩክሬን ወታደሮች በመኪና ተጭነው ወደ ኩርስክ ሲጓጓዙ ተመልክቷል።

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩክሬን ወታደሮች 30 ኪሜ የሩሲያን ድንበር ተሻግረው ጥቃት መክፈታቸውን ሞስኮ አስታወቀች።

ዩክሬን ጥቃት ከፍታ በዚህን ያህል ርቀት ድንበር አልፋ ስትገባ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር የዩክሬን ኃይልን ግስጋሴ ለማስቆም ቶልፒኖ እና ኦቢቺ ኮሎዶዘ በሚባሉ አካባቢዎች ጦርነት ገጥመዋል።

ዩክሬን በሩሲያ ኩርስክ ክልል የከፈተችው መጠነ ሰፊ ዘመቻ ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ “ኪየቭ ሰላማዊውን የሩሲያ ሕዝብ እያሸበረች ነው” ሲሉ የተከፈተባቸውን ጥቃት አውግዘዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌነስኪ ለመጀመርያ ጊዜ በሩሲያ ግዛት ጥቃት መክፈታቸውን ባመኑበት የቅዳሜው የቴሌቪዥን ንግግራቸው “ በዚህ በበጋ ወቅት ብቻ ከኩርስክ ግዛት 2ሺህ ጥቃቶች ተሰንዝረውብናል፤ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት ስላለብን ዘልቀን ገብተናል” ብለዋል።

አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል በሁለቱም ወገኖች በኩል በርካታ ወታደሮች በጦርነት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በዩክሬን የሚደገፉ ኃይሎች ድንበር አካባቢ መጠነኛ ጥቃቶችን መሰንዘራቸው የተለመደ ቢሆንም ዩክሬን በቀጥታ ሠራዊቷን ወደ ሩሲያ ግዛት ስታስገባ ግን ተሰምቶ አያውቅም።

“የከፈትነው ማጥቃት ነው። ዓላማችን የጠላትን ኃይል ማዳከምና ሠራዊቱ በአንድ ግንባር ሳይወሰን እንዲለጠጥ ማድረግ ነው። በሩሲያ ያለውን ሁኔታ ማተራመስ እንፈልጋለን። ድንበራቸውን መከላከል እንደማይችሉ ማሳየት እንፈልጋለን” ብለዋል እኚሁ ስማቸው ያልተገለጸ የዩክሬን ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣን።

ሩሲያ መጀመርያ አካባቢ በዩክሬን የተከፈተባትን የማጥቃት ዘመቻ አጣጥላ ነበር። “መጠነኛ የጠላት ኃይል ድንበር ላይ በብረት ለበስ ተሽከርካሪ ታግዞ ለመግባት ሙከራ አድርጎ አከርካሪው ተመቷል” በሚል ነበር የገለጸችው።

አሁን የዩክሬንን መግለጫ ተከትሎ ግን “የሩሲያ ኃይል የጠላት ኃይልን በቶልፒኖ እና ኮሎዴዝ አካባቢዎች” መግጠሙን የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል። እነዚህ አካባቢዎች ደግሞ ከድንበር 30 ኪሎ ሜትር ዘልቀው የሚገኙ ናቸው።

የዩክሬን ወታደሮች የተወሰኑ ሰፈሮችን በቁጥጥር ሥር ማድረጋቸውን የገለጹ ሲሆን ጉቮ በሚባል አካባቢ የሩሲያን ባንዲራ አውርደው የዩክሬንን ባንዲራ ሲሰቅሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ይፋ አድርገዋል።

በስቨርዲኮቮ እና ፖሮዝ ደግሞ የአስተዳደር ሕንጻዎችን በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ተለቀዋል።

ኩርስክ ክልልን በሚያዋስነው ሱሚ ክልል የቢቢሲ ሪፖርተር በወታደራዊ ካሚዮኖች የተጫኑ የዩክሬን ወታደሮች በስፋት ወደ ግንባር ሲጓጓዙ ተመልክቷል።

ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው አንድ የሳተላይት ምሥል ሩሲያ አዲስ የመከላከያ ምሽግ ከኩርስክ የኑክሊየር ጣቢያ አቅራቢያ ስትቆፍር ያሳያል።

የኒክሊየር ጣቢያው አሁን የዩክሬን ወታደሮች ካሉበት 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው።

የተባበሩት መንግሥታት የኒክሊየር ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከወዲሁ ስጋቱን የገለጸ ሲሆን ሁለቱም ኃይሎች ኒኩሊየር ጣቢያው አካባቢ ከማንኛውም ጠብ አጫሪነት እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

ሩሲያ እንደምትለው በዚህ የዩክሬን ጥቃት 76ሺህ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሄደዋል።

በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ ታውጇል።

ኦሌክሲ ጎንቻሬንጎ የተባሉ የዩክሬን የፓርላማ አባል አገራቸው በሩሲያ የከፈተችውን ጥቃትን አሞካሽተዋል።

“ሩሲያ በራሷ ግዛት መዋጋት ስትጀምር ያኔ ሕዝቡ ስለ ጦርነቱ ግድ ይሰጠዋል። ይህን ጦርነት ለማቆም ግድ የሚላቸው ያን ጊዜ ነው። ወደ ሩሲያ ዘልቆ ማጥቃት ከመቶ የሰላም ጉባኤዎች የተሻለ ወደ ሰላም ስምምነት ያቀርበናል” ብለዋል።

ይህ የኩርስክ ክልል ጥቃት ሩሲያ በምሥራቅ በኩል ለሳምንታት የዘለቀ ጥቃት ከከፈተችና በርካታ የዩክሬን አካባቢዎች ከተቆጣጠረች በኋላ የመጣ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት ምናልባት ዩክሬን የከፈተችው የኩርስክ ጥቃት ሩሲያ በምሥራቅ በኩል የምታደርገውን ግስጋሴ ይገታል።