ቶም ክሩዝ

ከ 4 ሰአት በፊት

የሆሊውድ ኮከቡ ቶም ክሩዝ እሑድ ምሽት በተካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ መዝጊያ ቁልቁል ተመዘግዝጎ በመግባት ታዳሚውን ጉድ አሰኝቷል።

አሜሪካዊው የአክሽን ዘውግ ፈርጥ በስታ ደ ፍራንስ በነበረው መዝገቢያ በገመድ ታስሮ ቁልቁል ሲወርድ ታይቷል።

ሚሽን ኢምፖሲብል በተሰኙ የፊልም ሥራዎቹ የሚታወቀው ቶም ክሩዝ ስታድየሙ ጫፍ ላይ ሲታይ ታዳሚው በጩኸትና ጭብጨባ ደስታውን ገልጧል።

አሜሪካዊቷ አቀናቃኝ ኸር በጊታሯ ታጅባ ሙዚቃ ስትጫወት ሳለ ነው ቶም ክሩዝ የቆዳ ጃኬት እና ጓንት አጥልቆ ታዳሚውን የተቀላቀለው።

ክሩዝ በቀጥታ የቴሌቪዝኝ ስርጭት ይህን ካደረገ በኋላ ከፓሪስ ወደ አሜሪካ ሲጓጓዝ የሚያሳይ ቪድዮ በስታድየሙ ግዙፍ ስክሪን ላይ ታይቷል።

ይህ የሆነው የአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ የኦሊምፒክ አዘጋጅነቱን ክብር ከፓሪስ መቀበሏን ለማመላከት ነው።

አሜሪካዊው ተዋናይ የኦሊምፒክ ባንዲራ ተሸክሞ ከሀገር ሀገር ሲጓጓዝ እንዲሁም በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚገኘው ሆሊውድ የሚለው ግዙፍ ፅሑፍ በኦሊምፒክ ቀለማት ሲደምቅ በቪድዮው ታይቷል።

ፓሪስ በይፋ የዘንድሮውን ኦሊምፒክ አዘጋጅነቷን በማጠናቀቅ ለሎስ አንጀለስ 2028 አስረክባለች።

50 ሜትር ገደማ ወደታች ተወርውሮ መሬት ያረፈው ቶም ክሩዝ ስታየሙ መሐል ሆነው የመዝጊያውን ፕሮግራም ሲከታተሉ በነበሩ አትሌቶች ተከቧል።

ሙዚቀኛዋ ኸር የአሜሪካን ብሔራዊ መዝሙር በሮክ ሙዚቃ ስልት ካዜመች በኋላ ቶም ክሩዝ ተመዘግዝጎ ሲወርድ ደግሞ በኤሌክትሪክ ጊታሯ ተቀብላዋለች።

ክሩዝ የኦሊምፒክ ባንዲራውን በዘንድሮው ውድድር ወርቅ ካመጣችው ታዋቂዋ አሜሪካዊት ጂምናስት ሲሞን ባይልስ ተቀብሎ በሞተር ብስክሌት ተሳፍሮ ሲሄድ ታይቷል።

ቶም ክሩዝ ከዚህ ቀደም በተቀዳ ቪድዮ የኦሊምፒክ ባንዲራውን ተሸክሞ ከፓሪስ ወደ ሎስ አንጀለስ ሲያቀና በሙዚቃ ያጀቡት ሬድ ሆት ቺሊ ፔፐርስ የተባሉት የሙዚቃ ባንድ አባላት ሙዚቃቸውን አቅርበዋል።

ቢሊ አይሊሽን ጨምሮ ስኑፕ ዶግ እና ዶ/ር ድሬን የመሳሰሉ አሜሪካዊያን አቀናቃኞችም በሎስ አንጀለስ ውቅያኖስ ዳርቻ ሙዚቃቸውን ሲያቀርቡ ታይተዋል።

በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲታይ የነበረው አሜሪካዊው ራፐር ስኑፕ ዶግ ሎስ አንጀለስ አንጀለስ ነው ያደገው።

በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በቻይና ስትመራ የነበረችው አሜሪካ እሑድ ከሰዓት በሴቶች ቅርጫት ኳስ አንድ ወርቅ በማምጣቷ በድምር ውጤት ከዓለም አንደኛ ሆና አጠናቃለች።

ከሚሽን ኢምፖሲብል በተጨማሪ ቶፕ ጋን በተሰኘ ተከታታይ የፊልም ሥራው የሚታወቀው ቶም ክሩዝ፤ ፊልሙ ላይ የሚታዩ ድርጊት የተሞለባቸው ድርጊቶችን ራሱ በመፈፀም ይታወቃል።

ከእነዚህ መካከል የግዙፉ ቡርጂ ኻሊፋ ሕንፃን የወረደበት፤ እያኮበከበ ያለ አውሮፕላን ላይ ተንጠልጥሎ የሚታይበት እንዲሁም በሞተር ሳይክል በፍጥነት እየሄደ ከከፍታ ላይ የሚዘልበት ይጠቀሳሉ።

የ62 ዓመቱ አሜሪካዊ ተዋናይ በመዝጊያው ሥነ-ሥርዓት ላይ ሊሳተፍ እንደሚችል በመገናኛ ብዙኃን መነገር የጀመረው ከሰሞኑ በፓሪስ ጎዳናዎች ላይ መታየቱን ተከትሎ ነው።

በተያያዘ ዜና እሑድ ጠዋት በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ከአንድ እስከ ሶስት የወጡት ሲፈን ሐሰን፣ ትዕግስት አሰፋ እና ኦቢሪ በአትሌቶች ፊት ሜዳሊያቸውን ተቀብለዋል።

ኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን እና ኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ በመጨረሻዎቹ ጥቂት መቶ ሜትሮች እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ አድርገው ሲፈን ሐሰን የወርቅ ሜዳሊያውን ማሸነፍ ችላለች።

የዓለም የሴቶች ማራቶን ክብረ-ወሰን ባለቤቷ ትዕግስት አሰፋ እና ሁለቱ ተፎካካሪዎቿ ሜዳሊያ የተሸለሙት የኦሊምፒክ አትሌቶች ሜዳውን ሞልተውት እየተመለከቱ ሳለ ነው።

ኢትዮጵያ በአንድ ወርቅ እና በሶስት ነሐስ በጠቅላላው በአራት ሜዳሊያ 47ኛ ሆና አጠናቃለች።