የግብፅ ፕ/ት አብዱል ፋታህ አል ሲሲሰ፣ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያ ፕ/ት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ
የምስሉ መግለጫ,የግብፅ ፕ/ት አብዱል ፋታህ አል ሲሲሰ፣ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያ ፕ/ት ሐሰን ሼክ ሙሐመድ

ከ 5 ሰአት በፊት

ግብፅ ጦር ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር የኢትዮጵያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄ ማቅረቧ ይፋ ሆኗል።

የአፍሪካ ኅብረት እንዲሁ ግብፅ ጦር ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር ሥራ ወደ ሶማሊያ ለመላክ ያቀረበችውን ጥያቄ በበጎ እንደሚቀበለው አስታውቋል።

ኅብረቱ ይህን ያለው በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የአፍሪካ የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ (አትሚስ) የሥራ ጊዜው አብቅቶ ከአውሮፓውያኑ 2025 በኋላ በአዲስ ስያሜ [አፍሪካን ዩኒየን ሰፖርት ኤንድ ስታብላይዜሽን ሚሽን ኢን ሶማሊያ] በአዲስ ኃይል እንደሚተካ ባስወቀበት ወቅት ነው።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የደኅንነት ምክር ቤት በቅርቡ ባደረገው ውይይት ግብፅ እና ጂቡቲ በዚህ አዲስ የሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር ጦራቸውን በሶማሊያ ለማሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቋል።

ሁለቱ አገራት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ጦራቸውን የማሰማራት ፍላጎት ያሳዩት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥራ በሶማሊያ ተሰማርቶ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ከአገሪቱ እንዲወጣ በሞቃዲሾ ባለሥልጣናት እየተጠየቀ ባለበት ወቅት ነው።

ይህ የግብፅ ፍላጎት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ አትሚስ ተልዕኮውን በ2024 መጨረሻ ሲያበቃ፤ የግብፅ ጦር 2025 መጀመሪያ ላይ በሶማሊያ ይሰማራል ማለት ነው።

ለመሆኑ አል-ሲሲ ጦራቸውን በምሥራቅ አፍሪካ ማሰማራት ለምን አስፈላጋቸው? የግብፅ ጦር በሶማሊያ መሰማራት ለኢትዮጵያ እና ለቀጠናው ምን ማለት ነው?

ዘግይታ ለመምጣት የፈለገችው ግብፅ

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉት ማት ብራይደን ዋነኛው ጥያቄ መሆን ያለበት ግብፅ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለምን መላክ አስፈለጋት ሳይሆን፤ “ግብፅ ጦሯን ወደ ሶማሊያ አሁን ላይ መላክ ለምን አስፈላጋት?” የሚለው ነው ይላሉ።

ሳህን በተባለው የምርመር ማዕከል የስትራቴጂ አማካሪ የሆኑት ማት ብራይደን ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሶማሊያ ድጋፍ በሚያሻት ሰዓት ግብፅ በሞቃዲሾ ጉዳይ ያገባኛል ስትል አልተመለከትንም ይላሉ።

“አል-ሸባብ በሶማሊያ ጎረቤት በሆኑ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በጂቡቲ ላይ ጥቃቶችን ፈጽሟል። ለዚህም አገራቱ ወታደሮቻቸውን ወደ ሶማሊያ ልከዋል። ይሁን እንጂ አል-ሸባብ ግብፅን ዒላማ አድርጎ አያውቅም” በማለት የግብፅ ፍላጎት ለየት ያለ ሊሆን እንሚችል ይጠቅሳሉ።

ግብፅ ሊጠናቀቅ በተቃረበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ከገባች ከአስር ዓመት በላይ ሆኗታል። ሶማሊያ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በፈጠረችው ግንኙነት ምክንያት ግንኙነታቸው መሻከሩ ይታወቃል።

ነገር ግን የሶማሊያ መንግሥት ራስ ምታት የሆነውን አል ሻባብን በመወጋት በኩል ከየትኛውም አገር በላይ ኢትዮጵያ ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች። ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሠራዊት አሰማርታም የሶማሊያ መንግሥትን እየጠበቀች እና እየደገፈች ነው።

አል ሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር የአካባቢው አገራት የደኅንነት ስጋት በመሆኑ የሶማሊያ ተጎራባች የሆኑት ኢትዮጵያን፣ ኬንያ እና ጂቡቲ ቡድኑን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ማት ብራይደን እንደሚሉትም በመልክዓ ምድር አቀማመጧ ከሶማሊያ ርቃ ለምትገኘው ግብፅ፤ በአል ሻባብ ምክንያት የሞቃዲሾ የሰላም እጦት ለካይሮ ከባድ የራስ ምታት ሊሆን አይችልም።

አክለውም ግብፅ እና ሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት እና የአረብ ሊግ አባላት መሆናቸው እና ይብዛም ይነስ ያላቸው ታሪካዊ ግንኙነት ሊያቀራርባቸው ይችላል ይላሉ።

ነገር ግን “የግብፅ ወደ ሶማሊያ የመግባት ዋነኛ ፍላጎት የሚመነጨው ከጂኦ ፖለቲካዊ ነው” በማለት ካይሮ ከአዲስ አበባ ጋር አባይ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያለችበትን ውጥረት ያወሳሉ።

ሶማሊያ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት እና በእስላማዊው ቡድን አል-ሸባብ ስትታመስ ቆይታለች።

ካርታ
የምስሉ መግለጫ,የየትኞቹ አገራት ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ ተሰማርቶ ይገኛል

ግብፅ አሁን ላይ ለሶማሊያ አጋርነቷን እያሳየች ያለችው ግን “ለራሷ ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል” ይላሉ ማት።

ለዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ካለችበት ውዝግብ በተጨማሪ በሁቲ አማጺያን ጥቃት እና በአል ሻባብ የባሕር ላይ ውንብድና እየተረበሸ ያለውን የቀይ ባሕር የመርከቦች የንግድ መስመር ደኅንነት ጉዳይ ለግብፅ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

በዚህም ሳቢያ ግብፅ ወደ ሶማሊያ ብትገባ ወሳኙን የቀይ ባሕር የመርከብ መስመርን ደኅንነት ለማረጋገጥ ዕድል እንደሚሰጣት ማት ብራይደን ጨምረው ይናገራሉ።

ግብፅ የሜደትራኒያን ባሕርን ከቀይ ባሕር ጋር ከሚያገናኘው የሱዩዝ ካናል መተላለፊት ከፍተኛ ገንዘብ ከማግኘቷ አንጻር የቀይ ባሕር ደኅንነትን መረጋገጥ ለካይሮ የኅልውና ጉዳይ ነው።

ግብፅ ሶማሊያ መግባት ለምን አስፈለጋት?

የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለምግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል።

ይህ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ግዙፍ ሕዝብ እና ምጣኔ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ሚና እንዲኖራት በማድረግ ተጨማሪ ኃይል ወደ መድረኩ ያመጣል።

“የኢትዮጵያ በሶማሊላንድ የባሕር ጠረፍ ላይ የባሕር ኃይል የማቋቋም ፍላጎትን ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚጻረር ጉዳይ አድርጋ ልትመለከተው ትችላለች። ስለዚህ ግብፅ በሶማሊያ መገኘቷ ከኢትዮጵያ ሊመጣ የሚችልባትን ስጋት ለመቀልበስ ይረዳታል” በማለት ማት ሌላ ምክንያት ያስቀምጣሉ።

የዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም የሆነው ቻተም ሐውስ ባልደረባ የሆኑት አቤል አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው ካይሮ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ለምን መላክ አስፈለጋት? የሚለውን ለመመስለ አሁናዊ እና ታሪካዊ ተያያዥ ጉዳዮችን መመልከት አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሠነድ ተከትሎ የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እጅጉን መበላሸቱን አቤል (ዶ/ር) ያስታውሳሉ።

በመግባቢያ ሠነዱ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ለምታገኘው የባሕር በር ምላሽ ይሆን ዘንድ ለሶማሊላንድ የአገር እውቅና ትሰጣለች መባሉ ሶማሊያን እጅጉን አስቆጥቷል።

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ለገባችበት ውዝግብ መፍትሄ ፍለጋ በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር ከመምከር ይልቅ፤ ፊቷን ወደ ግብፅ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት አዙራለች የሚሉት አቤል (ዶ/ር)፤ “ሶማሊያ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ተጸዕእኖ ማሳነስ እና ማኮሰስ ትፈልጋለች፤ ግብፅ በአንጻሩ በቀጠናው ያላትን ፍላጎት ለማሳካት አብሯት የሚሰራ ኃይል ትፈልጋለች” ሲሉ ያስረዳሉ።

“ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር የተቋሰለችበትን ታሪክ በተወሰነ መልኩ ሊያስተካክል የሚችል ቀጠናዊ አጋር ስትፈልግ ለቆየችው ግብጽ ይህ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል” ይላሉ አቤል (ዶ/ር)።

የግብጽ ጦር
የምስሉ መግለጫ,የግብጽ ጦር

የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ እንዲወጣ አጥብቀው ሲጠይቁ የሚሰሙት የቀድሞው የሶማሊያ ሚኒስትር ሞሐመድ ሙክታር ኢብራሂም፤ ግብፅ ጦሯን በሶማሊያ ለማስፍር መጠየቋ በቀጠናው ጉልህ የሆነ ለውጥ ነው ብለዋል።

የቀድሞው የሶማሊያ ኢነርጂ እና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሩ፤ የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የግብፅን ጣልቃ ገብነት እያደገ ለመጣው የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ተጽእኖ ምላሽ አድርጎ ይመለከተዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

ግብፅ በሶማሊያ ለመሰማራት እንድትወስን ያደረጋት በአገራዊ፣ በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውስብስብ ሁኔታዎች ምክንያት ሊሆን ይችላል ይላሉ።

የግብፅ ጦር መግባት የሚፈጥረው ስጋት

አቤል (ዶ/ር) የግብፅ ጦር በሶማሊያ የሚሰማራ ከሆነ የሚጋሩት ድንበር ስለሌላቸው ለዘመናት በርቀት ፍጥቻ ውስጥ የቆዩትን የኢትዮጵያ እና የግብፅ ወታደሮችን ፊት ለፊት የሚያፋጥጥ ሁኔታ ይፈጠራል ይችላል በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

“ኢትዮጵያ እና ግብፅ ፊት ለፊት የሚገናኙበት ተፈጥሯዊ ድንበር የላቸውም። ይህም በቀጥታ የሚገናኙበትን ዕድል ቀንሶት ቆይቷል። የግብፅ ጦር በሶማሊያ ከተሰማራ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ በሁለቱ አገራት የግጭት ዕድልን የሚያሰፋ ይመስለኛል። ይህን በስጋት ልንመለከተው ይገባናል” ይላሉ።

ማት ብራይደን በበኩላቸው ግብፅ በምን ዓይነት ቁርጠኝነት ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ እንደምትልክ ኢትዮጵያ እያንዳንዱን ጉዳይ በዐይነ ቁራኛ መከታተሏ አይቀርም በማለት ኢትዮጵያም ሁኔታውን ዝም ብላ የምታየው እንደማይሆን ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ የአል-ሸባብ ስጋት አለባት ከዚህ በተጨማሪም ከሶማሊያ ጋር የምትጋራውን ሰፊ የድንበር አካባቢን ደኅንነት ማረጋገጥ ስለምትፈልግ የሠራዊቷ በሶማሊያ የመቆየት ነገር ከደኅንነቷ ጋር ልታያይዘው ከመቻሏ በተጨማሪም አንዳንድ የሶማሊያ ግዛቶችም የኢትዮጵያ ሠራዊትን መቆየትን ይደግፉታል።

“ምንም እንኳ አንዳንድ የሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ እንዲወጣ በይፋ የጠየቁ ቢሆንም፤ በከፊል ራስ ገዝ የሆኑ በርካታ የሶማሊያ ግዛቶች የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ እንዲቆዩ ፍላጎት አላቸው” ይላሉ ማት ብራይደን።

ሞሐመድ ሙክታር ኢብራሂም እንዲሁ ግብፅ የአፍሪካ ኅብረት ኃይልን በሚተካው ኃይል ውስጥ ጦሯን በሶማሊያ ብታሰማራ ለሶማሊያ ከሚኖረው ጠቀሜታ ይልቅ በአካባቢው አገራት መካከል የሚፈጥረው ውጥረት ከፍ ያለ ነው ይላሉ።

“የሶማሊያ ቀዳሚ ተግዳሮቶች ከውጫዊ ስጋቶች ይልቅ ከውስጥ ክፍፍል የሚመጡ መሆናቸውን ልብ ማለት ያስፈልጋል” ይላሉ የቀድሞው ሚንስትር።

አቤል (ዶ/ር) የግብጽ ጦር በሶማሊያ ቢሰማራ በቀጠናው ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ሲያስረዱ፤ ካይሮ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ብትልክ የመጀመሪያው ተጎጂ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ነው ይላሉ።

የኢጋድ ዋነኛ ዓላማ በቀጠናው በሚገኙ አገራት መካከል የሰላም እና የደኅንነት ሁኔታዎችን ማስተባበር መሆኑን የሚያስታውሱት አቤል (ዶ/ር)፤ “ከቀጠናው ውጪ ያለ አገር በቀጠናው ሲሰማራ የኢጋዳን ሚና ያሳንሰዋል። ኢጋድ የነበረው አነስተኛ አቅም መንምኖ እንዲታይ ያደርጋል” በማለት ያስረዳሉ።

ግብፅ ከኢትዮጵያ የበለጠ ለሶማሊያ ትጠቅም ይሆን?

የአትሚስ የተልዕኮ ጊዜ ከማብቃቱ ጋር በተያያዘ እንዲሁም አዲሱ ኃይል የገንዘብ ድጋፍ ችግር ገጥሞታል በሚባልበት ወቅት ግብፅ እና ጂቡቲ ጦራቸውን ለማሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸው በአዎንታዊ የሚታይ ጉዳይ ሆኗል።

ሞሐመድ ሙክታር የግብፅ ጦር በሶማሊያ ቢሰማራ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያጠናክራል ይላሉ።

በግብፅ እና ሶማሊያ በኩል የሚፈረም ወታደራዊ መግባቢያ ስምምነት ለፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ካቢኔ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ እንዲሁም በቅርቡ የግብፅ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሹ በረራ መጀመሩ ገና ከአሁኑ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከሩን ያሳያል ይላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ይላሉ ሞሐመድ ሙክታር፤ የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ መሰማራት አል-ሸባብን ለማጥፋት እና የሶማሊያን ሰላም ለማረጋገጥ ለሚደረው ጥረት ትልቅ ልምድ ለሶማሊያ ሠራዊት ማካፈል ይችላሉ ብለዋል።

ሞሐመድ ይህንን ይበሉ እንጂ ወደ 20 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በሶማሊያ ተሰማርቶ የአገሪቱን መንግሥት ሲደግፍ እና አል ሻባብን እየተዋጋ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከየትኛውም አገር ኃይል የላቀ ቁጥር እና ልምድ ያለው መሆኑ ይነገርለታል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ (አትሚስ) ስር ቢያንስ ሦስት ሺህ ሠራዊት ያጀማራች ሲሆን፣ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በተደረሰ የሁለትዮሽ ስምምነት አማካይነት ደግሞ ተጨማሪ ከ5,000 አስከ 7,000 የሚደር ወታደሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሰማርተው እንደሚገኙ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከወራት በፊት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ሠራዊታቸው ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሶማሊያን ግዛት ከአልሻባብ እየጠበቀ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

አዛዡ ጨምረውም የሶማሊያ ባለሥልጣናት ለኢትዮጵያ ሠራዊት ያላቸው አመለካከት መቀየሩን ጠቅሰው ነገር ግን “የሶማሊያ መንግሥት ሞቃዲሾ እንዲቀመጥ ያደረገው የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው” በማለት “ሠራዊቱ ቢወጣ የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ሞቃዲሾ የሚቀመጥ አይመስለኝም” በማለት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ ውስጥ ያለው ሚና ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።