
ከ 1 ሰአት በፊት
መርየም ሁሴን ለሰባት ዓመታት ያላየችው እና የት እንዳለ የማታውቀውን የበኩር ልጇን መሐመድን ፎቶ እያየች እንደነገሩ በሣር በተሠራቸው ኩሽና ውስጥ ወለል ላይ ተቀምጣለች።
እንባዋ በፊቷ እየፈሰሰ ነው። መሐመድ ወደ አውሮፓ ለመግባት ስላደረገው ተስፋ አስቆራጭ ትግል ትናገራለች። ህልሙ አውሮፓ ገብቶ የቤተሰቡን ሕይወት መለወጥ ነበር።
በሱዳን ምዕራብ ዳርፉር ግዛት ከሚገኘው ቤታቸው ወጥቶ ከባድ በሆነው የሰሃራ በረሃ ለማቋረጥ አደገኛውን ጉዞ ጀምሯል።
“ሊቢያ ሲደርስ ሁለት ጊዜ ታግቷል” የምትለው መርየም፤ የመጀመሪያውን ክፍያ ሲጠየቁ ቤተሰቡ እና ጎረቤቶቻቸው አዋጥተው ከፍለዋል
ከልጇ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተነጋገረችው እአአ ታኅሣሥ 10 ቀን 2017 ነበር።
“በመጨረሻም ወደ አውሮፓ የመሻገር ሙከራውን ከመጀመሩ በፊት በጓደኛው ስልክ ደወለልኝ” በማለት በማግስቱ አውሮፓ ለመግባት ምን ያህል ተስፋ እንደነበረው መርየም ታስታውሳለች።
አሁን ግን በሕይወት መኖሩን ወይም ማለፉን እርግጠኛ አይደለችም።

እአአ ሚያዝያ 2023 በተቀናቃኞቹ የሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነት ተጀመረ። መርየም ከታንሹ ልጇ አሕመድ ጋር ወደ ምሥራቅ ቻድ ተሰደደች።
አሁን መኖሪያቸው 42 ሺህ የሚጠጉ የሱዳን ስደተኞችን በሚያስተናግደው ሰፊው ፋርቻና መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው። ጣቢያው በ2000ዎቹ እና በ2023 የሱዳን ጦርነቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ያስተናግዳል።
በድንጋያማው ጣቢያ ውስጥ እንደነገሩ የተቀለሱት የላስቲክ መጠለያዎች ከአስከፊው ጦርነት ሊያስመልጣቸው ይችላል። ደካማ የኑሮ ሁኔታ፣ በቂ ምግብ አለማግኘት እና ዕድል አለመኖር እንደ አሕመድ ያሉ ወጣቶች ተስፋ አንዲቆርጡ እያደረገ ነው።
በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ መኖር ተስፋ ስላስቆረጠው የወንድሙ የመሐመድን ፈለግ መከተልን ይፈልጋል።
ፋርቻናን ለቅቆ እና ወደ አውሮፓ አደገኛውን ጉዞ ለመሞከር ከጓደኞቹ ጋር በሊቢያ እና በቱኒዚያ በእግር ለመጓዝ ዕቅድ ነድፏል።
“ሱዳን በነበርንበት ጊዜ ዩኒቨርሲቲ ስለገባሁኝ ስለወደፊት ሕይወቴ ህልም ነበረኝ። በጦርነቱ ምክንያት ግን ሁሉንም ነገር አጣሁኝ” ሲል የአስተዳደር ትምህርት መማሩን በማስታወስ ይገልጻል።
- በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ተመድ አስጠነቀቀ5 ሰኔ 2024
- የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው31 ሀምሌ 2024
- የሱዳን ጦርነትን እያባባሱ ያሉት የኢራን እና የኤምሬትስ ድሮኖች12 ሰኔ 2024
የእናት መጥፎ ቅዠት
መርየም እንደ እናት ሰሃራ በረሃ ላይ ሁለት ወንድ ልጆቿን የማጣት አስፈሪ ቅዠት ተጋርጦባታል።
“ሌላኛው ልጄ የደረሰበት ሲጠፋ ስላየሁ እሱም ተመሳሳይ ነገር እንዳይደርስበት ስለሚያስፈራኝ እንዳይሄድ ነገርኩት” ስትል መርየም በጭንቀት ትናገራለች።
አህመድ ግን በቻድ ከቆየ የወደፊት እጣ ፈንታው የጨለመ ስለመሆኑ ቅንጣት አይጠራጠርም።
“አዎ እናቴ እንድሄድ ፈቃደኛ አልሆነችም። ነገር ግን በቻድ መቆየት አልችልም። ትምህርትም ሆነ ሌላ ምንም ነገር የለም” ሲል አሕመድ ተናግሯል።
“ጦርነቱ ህልማችንን ሁሉ አጨልሞታል። ሁልጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ስነጋገር እንስቃለን፣ እንጫወታለን። ነገርግን በቲቪ፣ በፌስቡክ እና በኢንስታግራም የትምህርት ፕሮግራሞችን ስንመለከት ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ሰዎችን እያየን እናዝናለን” ብሏል።
“እራሳችንን ከእነሱ ጋር እያነጻጸርን ልዩነቱን እናያለን … በዚህ መንገድ መጓዝ አልችልም።”
ይህ ሁኔታ አሕመድ እና ጓደኞቹ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ የዓለም ወጣቶች የተለዩ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው። ጦርነቱ በሱዳን ሰላማዊ ዜጎች ላይ ያስከተለውን ጫናም ያመለክታል።

ያልተሳኩ ሙከራዎች
የአሕመድ ተስፋ መቁረጥ ከ28 ዓመቱ ሲዲቅ ጋር ይመሳሰላል። ሲዲቅ በፋርቻና መጠለያ ጣቢያ ለሁለት አስርት ዓመታት የኖረ ሱዳናዊ ስደተኛ ነው።
ከሊቢያ እና ከቱኒዝያ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሦስት ሙከራዎችን አድርጓል።
“እዚህ ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። ምንም የምሠራው ቋሚ ሥራ የለኝም። ለዚህም ነው በሊቢያ ለመጓዝ ብዙ ጊዜ የሞከርኩት” ሲል ተናግሯል።
ገና የሰባት ዓመት ልጅ እያለ ነበር ከቤተሰቡ ጋር ወደ ቻድ የተሰደደው። በችግር ምክንያት ትምህርቱን አቋርጧል። እንደ አህመድ እና ሌሎች በፋርቻና እንዳሉት ስደተኞች ለሁለቱ ልጆቹ የተሻለ ሕይወት ራሱን ለአደጋ ማጋለጡ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል።
“ዕቅዱ በሂደት ላይ ነው። በዚህ መንገድ መኖር ስለማንችል ሙከራችንን አናቆምም” ሲል ገልጿል።
የሰሃራ በረሃ በዓለም ላይ ካሉ በጣም አደገኛ የፍልሰተኞች መንገድ ተደርጎ ይወሰዳል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በ2023 ብቻ 161 ስደተኞች በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ መሞታቸውን ገልጿል።
አይኦኤም እና ዓለም አቀፍ አጋሮቹ በቻድ ለሚገኙ ስደተኞች ሕጋዊ የስደት መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ አድርገዋል።
ከ 2017 እስከ 2019 ድረስ ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞችን ከቻድ ወደ ፈረንሳይ ለማዛዋወር ችለዋል።
በዩኤንኤችሲአር የፋርቻና ጽህፈት ቤት ባልደረባው ዪንግ ሁ እንደሚሉት ከሆነ ያለውን ሀብት ከግምት በማስገባት ተወሰነ የስደተኞችን ማዘዋወር ዕድል አለ።
“እንደ ሰብዓዊ ቪዛ፣ ቤተሰብ መገናኘት፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በውጭ እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ የስኮላርሺፕ ፕሮግራሞች አሉን” ብለዋል።
አብዛኛው የገንዘብ ድጋፍ እየተካሄደ ባለው ውጊያ ለተፈናቀሉ ሰዎች ሕይወት አድን ዕርዳታ እየቀረበበት በመሆኑ፣ ወደ ሌላ ቦታ ለማዛወር ያለው ግብአት ውስን ነው።
እነዚህ ሕጋዊ መንገዶች እስኪገኙ ድረስ ምን ያህል እንደሚጠብቁ እርግጠኛ አለመሆናቸው፤ አሕመድ እና ጓደኞቹ በአደገኛው የሰሃራ መስመር ለመጓዝ እንዲያስቡ አድርጓል።
“እንሄዳለን!” በማለት አስረግጦ ተናግሯል።