የኢራን ሰንደቅ ዓላማ

ከ 5 ሰአት በፊት

የሐማስ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ በኢራኗ መዲና ቴህራን መኖሪያ ቤት ውስጥ ሳሉ መገደላቸውን ተከትሎ የኢራን ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን በርካቶች እየጠበቁት ይገኛሉ።

የሐማሱን መሪ ግድያ እና ሌሎች ጉዳዮችን ለመወያያት የ57 አገራት ቡድን የሆነው የእስልምና ትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) እንዲሰበሰብ ኢራን ያቀረበችው አስቸኳይ ጥያቄ ተከትሎ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ረቡዕ ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም. ተሰብስበው ነበረ።

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ በአገራቸው ምድር ላይ ለተፈጸመው ግድያ አጻፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ እና እስራኤል “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቃት ዝተዋል።

አያቶላ ኻሜኒ የሃኒያን ግድያ መበቀል የኢራን ግዴታ ነው ሲሉም የተሰሙ ሲሆን፣ ይህም አስቸኳይ ምክክር ኢራን ሃሳቧን እንድታቀርብ ዕድል የከፈተ ነው ተብሏል።

ኢራንም ሆነች ሐማስ የሃኒያ ግድያን የፈጸመችው እስራኤል ናት ብለዋል።

እስራኤል ምንም እንኳን የሐማሱን መሪ ገድያለሁ ባትልም የራሷ እርምጃ ስለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚታመን ሆኗል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ባግሄሪ ካኒ አገራቸው አጸፋዊ ምላሽ ከመስጠት በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌላት ገልጸው፤ ይህም የሚሆነው “በትክክለኛው ወቅት እና በተገቢው መንገድ ነው” ብለዋል።

ካኒ የኢራን ምላሽ “የግዛቷን ሉዓላዊነት እንዲሁም ብሔራዊ ደኅንነት የመከላከል” ብቻ ሳይሆን “የቀጣናውን መረጋጋት እና ደኅንነት ለማስጠበቅ” እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢስማኤል ሃኒያ የተገደሉት በኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለት የእንግዳ ማረፊያ ውስጥ ሳሉ ነበር።

የሐማስ የፖለቲካ መሪ የኢራን ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን በዓለ ሲመት ላይ ለመታደም ተገኝተው ለጦር ዘማቾች በተቋቋመ ልዩ መኖሪያ ቤት ውስጥ መገደላቸው የኢራንን ደኅንነት ያዋረደ ክስተት ነው ተብሏል።

ኢራን ሉዓላዊነቷን የጣሰ ነው ላለችው የሃኒያ ግድያን እንዴት እና መቼ ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል ለማወቅ የምታደርጋቸውን ንግግሮች ወይም መግለጫዎች በርካቶች በጥንቃቄ እየተከታተሉት ይገኛሉ።

ኢራን በእስራኤል ላይ ልትወስደው የምትችለው አጸፋዊ እርምጃ ቀጣናውን ወደሰፋ ጦርነት ሊመራው ይችላል የሚልም ስጋትም እየተነሳ ነው።

ሚኒስትሩ ባግሄሪ ካኒ የኢራን ምላሽ ሊሆን ይችላል በሚለው ላይ ምንም ዓይነት ፍንጭ ያልሰጡ ሲሆን፣ ከምዕራቡ ዓለም የተገደበ የስለላ መረጃ ጋር ተያይዞ የኢራን አጸፋዊ ምላሽን ማወቅ አዳጋች አድርጎታል።

በሚያዝያ ወር በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በሚገኘው የኢራን ዲፕሎማሲያዊ ግቢ ውስጥ በእስራኤል እንደተፈጸመ በሚታመን ጥቃት ስምንት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ መኮንኖች ተገድለዋል።

ኢራን አጸፋዊ እርምጃ እንደምትውስድ ካሳወቀች በኋላ ከ300 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) እና ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፋ ነበር። ሆኖም ሁሉም ማለት በሚቻል ሁኔታ በእስራኤል እና በአሜሪካ በሚመራው ጥምር ኃይል ከሽፈዋል።

ባልተሳካው ጥቃት የደረሰባትን ውድቀት ላለመድገም ስትል ኢራን በአሁኑ ወቅት ሰፋ ላለ ዘመቻ (ኦፕሬሽን) እየተዘጋጀት ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረው ነበር።

በቅርብ ጊዜ የሃኒያን ግድያ አስመልክቶ የወጡ ዝርዝር መረጃዎች እንደጠቆሙት ከውጭ በተፈጸመ የአየር ጥቃት ሳይሆን በቅርብ ርቀት መሆኑ እና ከአገር ውስጥም በተገኘ እርዳታ ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል።

ግድያው ከውጭ በተቃጣ የአየር ጥቃት አለመሆኑ እንዲሁም የአንድም ኢራናዊ ሕይወት አለመጥፋቱ እና የምዕራባውያን እና የአረብ አገራት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ኢራን የምትሰጠውን ምላሽ እንድትመረምር አስገድዷት ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።

የሃንያ የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት
የምስሉ መግለጫ,በኢራን መሪዎች የተፈጸመው የሃንያ የአስክሬን ሽኝት ሥነ ሥርዓት

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢራን ያልተለመደ ጉብኝት አድርገዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማስዑድ ፔዜሽኪያን ጋር ደውለው “አዲስ ወታደራዊ ግጭት መባባስ እንዳይፈጠር ሁሉንም ነገር እንዲያደርጉ” መናገራቸውን የማክሮን ቢሮ አስታውቋል።

የኢራን አጸፋዊ ምላሽ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አዛዡ በእስራኤል ጥቃት የተገደለበት የሄዝቦላህም ጥቃት የሚጠበቅ ይሆናል።

ሃኒያ ከመገደላቸው ከሰዓታት በፊት እስራኤል በቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ በምትገኘው ዳሂያ የአየር ጥቃት በመፈጸም የሄዝቦላህ የከፍተኛ አዛዥን ፉአድ ሽኩርን ገድላለች። ቡድኑ ለዚህ ግድያ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥም ዝቷል።

መስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ እያካሄደች ባለበት ወቅት በቀጣናው የሰፋ ጦርነት ሊካሄድ ይችላል የሚለው ስጋት እንደነገሰ ነው።

የጋዛን ጦርነት ተከትሎ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ያለው ውጥረት የከረረ ሲሆን፣ በሊባኖስ ውስጥ ጦርነት ሊጀመር ይችላል እየተባለም ይገኛል።

ሄዝቦላህ እና እስራኤል እያደረጉት ያለው ግጭት በሊባኖስ እና በእስራኤል ድንበር የተወሰነ ሲሆን፣ ሁለቱም አካላት ሰፋ ያለ ጦርነት ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌላቸው እየገለጹ ነው።

እስካሁን ድረስ ሄዝቦላህ በእስራኤል ላይ እየፈጸማቸው ያሉት ጥቃቶች በአገሪቱ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ቢሆኑም፣ ጥቃቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ እንዲሁም በእስራኤል ውስጥ ዘልቀው የገቡ ዒላማዎችን እየመቱ ነው ተብሏል።

የኢራን ሚሳኤሎች

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስራላህ እስራኤል የገደችለችባቸውን የቡድናቸውን ከፍተኛ አዛዥ ፉአድ ሽኩርን “የትግሉ ቀያሽ አዕምሮ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ “ጠንካራ” እና “ውጤታማ” አጸፋዊ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉም ዝተዋል።

ከዚህ ቀደም ሄዝቦላህ ከፍተኛ የጦር አዛዦቹ በሚገደሉበት ወቅት በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን በማስወንጨፍ አጸፋዊ ምላሽ ይሰጥ ነበር። አሁን ግን በሊባኖስ መዲና እንዲህ ያለ ከፍተኛ አዛዡ መገደሉን ተከትሎ ሄዝቦላህ ተምሳሌታዊ ሊሆን የሚችል ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል።

በአውሮፓውያኑ 2006 በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በተደረገው ጦርነት በሊባኖስ ላይ ያስከተለውን ውድመት ያልረሳው ሕዝቡ አሁንም ዳግም ወደ ጦርነት ልንገባ እንችላለን በሚል ስጋት ውስጥ ነው። ነገር ግን ጦርነት ውስጥ ላይገቡ የሚችሉበት ሌላኛው ዋነኛ ምክንያት ኢራን ሄዝቦላህ እንዲዳከም አለመፈለጓ ነው።

ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖች) እንዲሁም ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ትክክለኛ ዒላማዎችን በመምታት የሚታወቀው ሄዝቦላህ፣ ኢራን እንደ መከላከያ የምታየው ቁልፍ አጋሯ ነው።

እስራኤል የኢራንን የኑክሌር መርሃ ግብር እንደ ህልውና ስጋት ታየዋለች። ምናልባትም እስራኤል በኢራን የኑክሌር ማዕከል ላይ ጥቃት ብትፈጽም ሄዝቦላህ እጁን አጣጥፎ እንደማይመለከት እና ለኢራን ምላሽም ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ይገመታል።

ሄዝቦላህ፣ የየመን ሁቲዎች እና በኢራቅ ውስጥ ያሉ ሚሊሻዎች በኢራን የሚደገፉ ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ የተሰኙ ምዕራባውያንን እና እስራኤልን የሚታገሉ ቡድኖች ናቸው።

በሐማሱ መሪ እና በሄዝቦላህ ከፍተኛ አዛዥ ግድያዎች ኢራን እና አጋሯቿ የተባበረ ምላሽ ይሰጡ ይሆን? የሚለው ባይታወቅም የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሄዝቦላህ በራሱ የመጀመሪያውን አጸፋዊ ምላሽ ይሰጣል እያሉ ነው።

በዚህ ሳምንት የአሜሪካ የማዕከላዊ ዕዝ መሪ ማይክል ኩሪላ የደኅንት ዝግጅቱን ለመገምገም በእስራኤል ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረች አሜሪካ ድጋፏን የምትሰጥ ይሆናል ብለዋል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው “ከየትኛውም አቅጣጫ በእኛ ላይ ለሚሰነዘር ጥቃት” ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ሲሉ ዝተዋል።

ምን ዓይነት ምላሾች ይሰጣሉ የሚለው እየተጠበቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት ወደ እስራኤል እና ሊባኖስ የሚደረጉ በረራዎች እየተሰረዙ እንዲሁም እየታገዱ ይገኛሉ።

አየር መንገዶች በሁለቱም አገራት የአየር ክልል ውስጥ መብረር ያቆሙ ሲሆን፣ የተለያዩ አገራትም ዜጎቻቸው ከአገራቱ ለቀው እንዲወጡ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። አንዳንዶችም ቀጣናው ወደ ጦርነት ሊገባ ይችላል በሚል ፍራቻ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።