
የደራርቱ አመራር ያዳከመው ፌዴሬሽን
———————————————–
የስፖርት ጋዜጠኛ አወቀ አብርሃምድክመት አደባባይ ተሰጥቷል
=======================
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የውጤትም ሆነ የአስተዳደር ድክመት አደባባይ ላይ ተሰጥቷል:: በፌዴሬሽኑ ውስጥ ታምቆ የቆየው ውስጣዊ የአሰራር ብልሹነት ፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ፈንድቷል:: አትሌቶች ከውድድሩ በፊትም ከትወዳደሩ በሗላም በአደባባይ ቅሬታቸውን እየገለፁ ነው::
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ውጪው ሲታይ እንዳፈራቸው አትሌቶች ግርማ ሞገሳም ቢመስልም ቀረብ ብሎ ላየው ጥቂት ጀግኖች አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በሚያስመዘግቧቸው ብዙ ድሎች ወጪውንና ገመናውን ሸፍኖ የቆየ የነበሩንንና ያሉንን አትሌቶች አቅምና ክብር የሚመጥን ግልፅና ዘመኑን የዋጀ አሰራር የሌለበት ቤት ነው::
ደራርቱ የሰራችው ታሪክና ያላት ዝና ያስከብራታል እንጂ ተቋማዊ አሰራር የተዘረጋለትንና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች የሚተላለፉበትን ተቋም በግሏ እንደፈለገች እንድትወስን ስልጣን አይሰጣትም::ብሶት የወለደው ብሶት ሲወልድ
========================
ደራርቱ ፌዴሬሽኑ ሮጠው በማያውቁ ሰዎች ስለሚመራ የአትሌቶችን ስሜት የማይረዱ መሪዎች ተነስተው እኛ ሃላፊነቱን ብንይዝ የአትሌቶችን እንባ እንጠርጋለን የሚል ሃሳብ ይዞ በተነሳ የቀድሞ አትሌቶች አብዮት ተሳፍራ ነው ወደ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ የመጣችው::
ከዚህ በፊት የነበረውን እንተውና በፓሪስ ኦሊምፒክ ብቻ በደራርቱ ፌዴሬሽን ተበደልን ካሉ አትሌቶች ዮሚፍ ቀጄልቻ ፍሬወይኒ ሃይሉ ፅጌ ገብረሰላማ ሱቱሜ ታደሰ ሂሩት መሸሻን መጥቀስ ይቻላል:: በአንድ ውድድር ይህን ያህል ቅሬታ የቀረበበትን ጊዜ አላስታውስም::
ጉደፍ ፀጋይ በ3 ርቀቶች ትወዳደር ብላ በራሷ ውሳኔ ያሳለፈችው ደራርቱ ኢትዮጵያ ብዙ አማራጭ አትሌቶች ስላሏት ከሁለት በላይ ርቀት መወዳደር የለባትም የሚል ሃሳብ ከነበረው የፌዴሬሽኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት ገዛኸኝ አበራ ጋር አለመግባባት ውስጥ የገባችው የፍሬወይኒ ሃይሉን የመወዳደር እድል በግል ውሳኔዋ መስዋዕት አድርጋ ነው::
ጉደፍ 3 ርቀት እንድትወዳደር የተፈቀደላት ፍሬወይኒ ሃይሉ መወዳደር የሚያስችል የተሻለ የቅርብ ጊዜ ሰዓት እያላት ነው:: ለጉደፍ ከተፈቀደ ፅጌ ገብረሰላማም ዮሚፍ ቀጄልቻም በ5 ሺህና 10 ሺህ ሊያሳትፋቸው የሚችል ሰዓት ነበራቸው:: ግልፅ የሆነ አሰራር አለመኖር አንዱን ልጅ ሌላውን የእንጀራ ልጅ የሚያስመስል ውሳኔ ሲያሳልፍ አይተናል::ያልቻለችውን የተሸከመችው ደራርቱ
==========================
ደራርቱ ፌዴሬሽኑን መምራት ክብዷታል:: እንዲህ ዓይነት ሃላፊነት ላይ ስላልኖረች በግሏ ተዓምር እንድትፈጥር ባይጠበቅባት እንኳን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን አማክራ ባለሞያዎችን አወያይታ ግልፅ አሰራር ዘርግታ ቅሬታዎች የሌሉበት አልያም ብዙ የማይሰሙበት ተቋም እንድታደርገው ሲጠበቅባት የሆነው ተቃራኒው ነው::
ስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ስሙ ብቻ አለ እንጂ ውሳኔዎችን በራሷ ነው የምትወስነው:: ከሷ ሃሳብ የሚፃረር ሲነሳ የማትቀበል የሷ ሃሳብ ብቻ ትክክል የሚመስላት ፌዴሬሽኑን እንደግል ንብረት እንጂ እንደ ሃገር ሃላፊነት የማታይ ናት ይላሉ አብረዋት የሰሩ::
በደራርቱ የሚመራው ፌዴሬሽን ግልፀኝነት የጎደለው አድሏዊ አሰራር የሚታይበት ጎጠኝነት ተንሰራፍቶበታል ብለው አትሌቶች የሚያለቅሱበት በጥቅም ግንኙነት ሲታማ የኖረ በዘልማድ የሚሰራበት ፌዴሬሽን ነው::
በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚነት አብረዋት ያሉት ሰዎች እንደሷ በስፖርቱ ውስጥ ያለፉ እንዲሁም ከስፖርቱ ውጪ በተለያየ ዘርፍ ልምድ ያላቸው ስለነበሩ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብጥር ደረጃ ጥንካሬ ያለውና ሰርቶ ሊያሰራ የሚችል ነበር::
በፓርላማ የማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ረዥም ዓመት የሰሩት ወ/ሮ አበባ ዮሴፍን የመሰሉ አቅም ያላቸው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ሲመጡ ፌዴሬሽኑ በውይይት የሚወሰንበት ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ራሷን ብቻ በምታዳምጠው ከሷ ሃሳብ ተቃራኒ ሲነሳ በምትበሳጨው ደራርቱ ምክንያት እውን ሳይሆን ቀርቷል::
የፌዴሬሽኑ ፋይናንስ ቦታ በሃላፊነት የሚቀመጡ ሰዎች አላስፈላጊ የመሰላቸውን ወጪ እንዲፈርሙ ሲጠየቁ ይህ አግባብ አይደለም ወይም አላምንበትም የማለት መብት እንኳን የላቸውም:: ለግለሰቦች የሚሰጥ ክፍያ ላይ አላምንበትም ያላትን የፋይናንስ ሃላፊ “ወንድ ከሆንክ ሳትፈርም ስትቀር እናያለን ማንነቴን አያይሃለሁ” የሚል ዛቻ መሰንዘሯን ፌዴሬሽን ውስጥ የሰሩና ለፌዴሬሽኑ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የሚያውቁት ነው::
ሃይሌ ራሱን ከፕሬዚዳንትነቱ ሲያነሳ ቦታውን ከያዘችበት ጊዜ አንስቶ ደራርቱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን እንደሌለ በመቁጠር ማንንም ሳታማክር ውሳኔዎች የምታሳልፍበት የግሏ ቤት አድርጋዋለች::
በተጨማሪም የምታስተዳድረው ፌዴሬሽን ስለሚሰሩት ስራ በቂ እውቀትና አቅም የሌላቸው ሰራተኞች የታጨቁበት መረጃ እንኳን ቢፈለግ ጥርት ባለ ሁኔታ የማይገኝበት ነው:: ሁሉንም እሷ ያልቀጠረቻቸው ሊሆኑ ይችላሉ ግን በ6 ዓመት የሃላፊነት ቆይታዋ ብዙ ክፍተቶችን ማስተካከል የሚያስችል ከበቂ በላይ ጊዜ ነበራት:: እያንዳንዷ ቅንጣት መረጃ በምትተነተንበት ዘመን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ትልልቅ መረጃዎችም ተፈልገው ላይገኙ ይችላሉ::አንድ ቀላል ማሳያ ልጥቀስ
=====================
ባለፈው መጋቢት ወር በቤልግሬድ በተደረገው የዓለም ሃገር አቋራጭ ቻምፒዮና ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች ስለተመረጡበት ውድድር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ የፈለገው ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ መሪ ተቋም ወርልድ አትሌቲክስ የፈለገውን የተሟላ መረጃ ማግኘት አልቻለም::
ስም ዝርዝርና የገቡበትን ሰዓት መረጃ ፈልጎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ቢጠይቅም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች በተመረጡበት የ41ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል ሃገር አቋራጭ ውድድር ላይ አትሌቶች ያጠናቀቁበት ደረጃ እንጂ የገቡበት ሰዓት አልተመዘገምና ከየት ይምጣ:: ይህ ለአንድ ቴክኒክ ዲፓርትመንት አለኝ ለሚል ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን እንደ ሃገርም አሳፋሪ ነው::ይህ ነው እንግዲህ ደራርቱ የምትመራው ፌዴሬሽን::ለአንዱ እናት ለሌላው እንጀራ’ናት
========================
ደራርቱ ውጤታማ አትሌቶች ከያዙ አሰልጣኞች ጋር ጥሩ ቅርበት አላት:: ገመዱ ደደፎ ሃጂ አዴሎና ህሉፍ ይደጎ ዋነኞቹ ናቸው:: እነዚህ አሰልጣኞች ራሳቸው ከያዟቸው አትሌቶች ውጪ ሌሎች እንዳይመረጡ ያደርጋሉ እነሱን ትቶ አሰልጣኝ የሚቀይር አትሌት ካለ በዓለም ቻምፒዮናና ኦሊምፒክ ምርጫዎች ዋጋ ይከፍላል::
አሰልጣኞች ከደራርቱ ጋር ባላቸው የግል ቅርበት እኔን ትታ ሌላ አሰልጣኝ ያዘች የሚሏትን አትሌት እንዳትመረጥ ከማድረግ አንስቶ አንቺ ተመርጠሽ የኔ አትሌት ከወጣች ሰው ይሞታል እስከሚል ማስፈራሪያ የሚሄዱት ከፕሬዚደንቷ ጋር ያላቸውን ጥብቅ ወዳጅነት በሚሰጣቸው ያልተፃፈ ስልጣን ምክንያት ነው ይላሉ ቅሬታ የሚያቀርቡ አትሌቶች::
ሱቱሜ አሰፋ ሃጂ አዲሎና ገመዱ ደደፎ ናቸው ቡድኑ ውስጥ እንድካተት ከተወሰነ በሗላ እንዳልገባ ያደረጉኝ ያለችበት ፍሬወይኒና ፅጌ ገብረሰላማም አሰልጣኝ በመቀየራቸው እንደተጎዱ ይናገራሉ::
በርግጥ ደራርቱ ያላት ተወዳጅነት ከፍተኛ እንደሆነ ስለምታውቅ ሕዝባዊ ተቀባይነቷን ለማሳደግ ጥሩ የሕዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት ላይ አትታማም:: ስልጣኗን የሚያደላድሉ ውጤት የሚያመጡ ነባር አትሌቶችን ከሌሎች በተለየ እንደምትመለከት ብዙ አትሌቶች የሚያነሱት ቅሬታ ነው::
ውድድሮችን ያሸንፉልኛል ያለቻቸውን አትሌቶች ሃዘንም ደስታን በመጋራት በኩል ብርቱ ናት:: ሲወልዱ በግና ዊስኪ ተይዞ የሚጠየቁና የማይጠየቁ ለውጤታማ አትሌቶች ደስታ ሲባል አዳዲስ አትሌቶች መሳተፍ በሚገባቸው ውድድር እንዳይሳተፉ መስዋዕት እየሆኑ ነው:: ያልታደሰ ቤት
=============
ደራርቱ ስራውን እየለመደች ስትሄድ ይቀላታል እንዳይባል እንኳን በፌዴሬሽኑ ሃላፊነት ወንበር ላይ ከተቀመጠች 7 ዓመቷ በዋና ፕሬዚደንትነት መምራት ከጀመረች ደግሞ ወደ ስድስት ዓመት እየተጠጋት ነው:: በነዚህ ዓመታት ደራርቱ ምን አሳካች የሚለው ሲታይ ፌዴሬሽኑ ውስጥ ፀብ ካልሆነ በስተቀር ሊጠቀስ የሚችል ጠብ ያለ ነገር የለም::
በፊት በፊት በኢኮኖሚው የላቁ ሃገራት በ5ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ሜዳሊያ ማግኘት ሲያምራቸው ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን ዜግነት ሰጥተው ገንዘብ ከፍለው ነበር የሚያሳኩት::አሁን ስልጠናውን አሳድገው በራሳቸው ተወላጆች ሜዳልያዎችን እያሳጡን ነው:: የስልጠናውን ማኑዋል አዘጋጅተን አሻሽለን ለዓለም ማስተማር የነበረብን እኛ ግን ሗላ ቀር ስልጠናና አሰልጣኞች ይዘን ባለንበት ተቸንክረን ስንቀር ባለፉት 6 ዓመታት ፌዴሬሽኑን የመራችው ደራርቱ ያመጣችው ለውጥ የለም::ሃላፊነቱ ከማንም በላይ የደራርቱ ነው
===========================
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በማያገባው እየገባ ነገሮችን የማወሳሰብ ችግሩ እንዳለ ሆኖ በአትሌቲክስ ለሚመጣው ውጤት መጥፋት ሙሉ ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ነው:: አትሌትና አሰልጣኝ መምረጥ የፌዴሬሽኑ ሃላፊነት ነው:: እያንዳንዱ አትሌት እያንዳንዱ አሰልጣኝ ተጠሪነቱ ለፌዴሬሽኑ ነው እንጂ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ አይደለም:: ለውድድር ከሚዘጋጁበት አካሄድና ትግበራ አንስቶ አትሌቶችን አላሳትፍም እስከማለት ድረስ ፌዴሬሽኑ ስልጣን ነበረው አለውም:: በመሞዳሞድ ስልጣኑን ለኦሊምፒክ ኮሚቴ አጋራ እንጂ::
አትሌቶቻችን ሲሮጡም ታሪክ ሰርተው ጡረታ ሲወጡም የሃገር ወኪሎቻችን ናቸውና ሊሸለሙም ሊከበሩም ይገባል:: ነገር ግን ታሪክ ስለሰሩ ብቻ ቀጣይ ታሪኮች እንዳይሰሩ የሚያደርግ የአመራር አቅም ማነስ ኖሮባቸስ ሃገርን የሚወክል ትልቅ ተቋም ይዘው ለመውደቅ ሲንገዳገዱ ዝም ሊባሉ አይገባም::
ደራርቱም ይቅርታ ጠይቃ ሃላፊነቷን ለቅቃ በዘመናት ልፋቷ ያፈራችውን ስሟን ጠብቃ ብትኖር ለክብሯም መልካም ነው:: በምትመራው ፌዴሬሽን የተንሰራፋውን አምባገነንነት በደማቅ ፈገግታዋም ሆነ በማራቶን ወርቅ ሜዳሊያ ድል ልትሸፍነው አይቻላትም::
አውቃለሁ ትልቅ ታሪክ ለሃገር የሰሩ አትሌቶችን መተቸት ከባድ ነው:: ይገባኛል እናታዊ ፈገግታን ከትውስታ ከማይጠፉ ድሎች ጋር ያጣመረችውን ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን አጠፋች ብሎ መውቀስ ለብዙዎች ላይዋጥ ይችላል:: ከአትሌቶች ጋር በሃዘናቸው አብራ ስታለቅስ በደስታቸው ስትፈነድቅ የምናውቃት ደራርቱ አምባገነን ሆና ሁሉም እኔ እንዳልኩት ይሁን የምትል የፌዴሬሽን መሪ መሆኗን ማመን ብዙ ሰው እንደሚከብደው::እውነታው ግን ይህ ነው
==================
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የታላቁ የአበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ድልን ተከትሎ የተመሰረተ ለዘመናት ከተሻገሩ ችግሮቹ ጋርም ቢሆን ራሷን ደራርቱን ጨምሮ ከነ ማሞ ወልዴ አንስቶ እስከ አሁኖቹ እነ ታምራት ቶላ ትውልድ ድረስ ድል ላይ ድል የደራረቡ ጀግና አትሌቶችን ያፈራ ቤት ነው:: ከዛ ቤት በላይ የኢትዮጵያን ስም በበጎ ያስጠራ ተቋም አላውቅም::
ይህ ተቋም ደግሞ ክብሩን በጠበቀ መልኩ ሊመራ ይገባል ለዚያ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል::
በኦሊምፒክ ኮሚቴ እመለሳለሁ::
ጋዜጠኛ አወቀ አብርሃም