August 12, 2024 – Konjit Sitotaw 

” ለሚፈጠረው ችግር እኛ ተጠያቂ አይደለንም ” – የህወሓት ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን

የህወሓት ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ዛሬ ሰኞ ባወጣው ባለ 3 ነጥብ የአቋም መግለጫ ፥ ” ጤናማ ያልሆነ  ሂደት ውጤታማና መልካም ጉባኤ መፍጠር ስለማይችል የሚያስከትለው አደጋ የከፋ ነው ” ብሏል።

” ጤናማነት  ሂደት የሌለው ውጤታማና መልካም ጉባኤ መፍጠር አይችልም ” ብሎ በማመን ከሚካሄደው ጉባኤ ራሱን ማግለሉን አሳውቋል።

” በቡድናዊ ማን አለበኝነት የሚካሄድ ” ብሎ የጠራውን ጉባኤ ተከትሎ በሚፈጠረው ማንኛውም ችግር ተጠያቂ አለመሆኑ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ፤ የህወሓት ህጋዊ እውቅና በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሰረት መመለስ ሲገባው ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የፓለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ እውቅና መሰጠቱ እንደማይቀበለው ገልጿል።

በህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል እና የማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን መግባባት ያልተደረሰበት በእልህ የሚካሄደው ጉባኤን እንደሚቃወምም የገለጸው የቁጥጥር ኮሚሽኑ ፤ ” ጉባኤው ተከትሎ በትግራይ ህዝብና በህወሓት የሚፈጠረው አደጋ ተጠያቂው በማንአለበኝነትና በእኔነት ስሜት በመጓዝ ላይ ያለው ቡድን ነው ” ብሏል።

” በህወሓት የተፈጠረው ችግር መፍትሄው የቡድን ፉክክር ፣ እኔነትና እልህ አይደለም ” ያለው ኮሚሽኑ ” ደርጅቱ የሚድነው በስርአታዊና ተቋማዊ ትግል ነው ” ሲል ገልጿል።

የህወሓት የፅ/ቤት ሃላፊና የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ብሄር ትላንት የህወሓት ማእከላዊ  የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት በጉባኤ እንዲሳተፉ በፃፉት ደብዳቤ ” 14ኛው የህወሓት ጉባኤ ነሃሴ 7/2016 ዓ.ም ከጥዋቱ 3:00  ጀምሮ በመቐለ የሰማእታት ሓወልት አዳራሽ ይካሄዳል ” ብለዋል።

ኮሚሽኑ ግራ ራሱን ከጉባኤው አግልሏል።

ዛሬ ከጥዋት ጀምሮ ደግሞ ህወሓት በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ነገ ለሚጀምረው ጉባኤ ተሳታፊ የሆኑ አባላት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ መቐለ እየተጓዙ እንደሆኑ እያሳወቀ ነው።