
Monday, 12 August 2024 06:49
Written by Administrator

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በነገው ዕለት ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እንደሚጀመር ተገልጿል። የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ለህወሓት ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ የኮሚሽኑ አባላት በጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ወይዘሮ ፈትለወርቅ “14ኛው የህወሓት ጉባኤ ነሃሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በመቐለ የሰማዕታት ሐወልት አዳራሽ ይካሄዳል ” በማለት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተው፣ አዘጋጅ ኮሚቴው የጉባዔውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ አስታውቀዋል።
ነገር ግን የደርጅቱ ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ነገ ከሚጀመረው ጉባዔ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። በሌላ በኩል፣ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተካተቱበት፣ ሌሎች 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በጋራ “ማንአለበኝነት የተጠናወተው ጠባብ ቡድን ” ሲሉ በጠሩት አካል በተዘጋጀው ጉባዔ እንደማይሳተፉ ትናንት በጻፉት ደብዳቤ አስታወቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ፣ በትናንትናው ዕለት ሰባት የመቐለ ከተማና ሁለት የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ከፍተኛ የህወሓት ካድሬዎች “ጠባብ ቡድን” በማለት በጠሩት አካል “ተጠራ” ሲሉ በገለጹት የህወሓት ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔ እንደማይሳተፉ ገልጸዋል።
አመራሮቹ በጉባዔው ላለመሳተፍ የገፋቸውን ምክንያት “በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው ጉባዔ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ላለመሳተፍ ወስነናል ” በማለት ገልጸውታል። ይሁንና ጉዳቱ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። አክለውም፣ “ጉባዔውን ተከትሎ ለሚመጣ ነገር እኛ የለንበትም ” ብለዋል።