
Monday, 12 August 2024 09:04
Written by Administrator

– የህወሓት ሕጋዊነትን የመመለስ ሂደት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጎን ለጎን ሲካሄድ እንደቆየ ገልጸዋል
– በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሁለቱ ፈራሚዎች እርስ በራሳቸው ዕውቅና እንደሚሰጣጡ “ይደነግጋል” ብለዋል
የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል “ህወሓትን እንደአዲስ መመዝገብ ማለት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን ማፍረስ ማለት ነው” ሲሉ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲያቸው የሰጠውን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ነቅፈው ተናግረዋል። ሊቀ መንበሩ ይህንን የተናገሩት ትናንት ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
“ህወሓት ሃምሳ ዓመታትን ያስቆጠረ…እንደአዲስ መመዝገብ የሌለበት አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ነው” ያሉት ደብረጽዮን (ዶ/ር)፣ “የህወሓት ሕጋዊነትን የመመለስ ጉዳይ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት [ሂደት] ጎን ለጎን እንጂ አሁን የተጀመረ አይደለም ” ብለዋል። አያይዘውም፣ “የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሁለቱ ፈራሚዎች እርስ በራሳቸው እውቅና እንደሚሰጣጡ ይደነግጋል” ሲሉ አመልክተዋል።
የህወሓት ህጋዊነትን ለመመለስ የተካሄዱ በርካታ ውይይቶችን ተከትሎ፣ ድርጅቱና ሌሎች ወገኖችን የሚያካትት፤ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የሚመለከት የተሻሻለ ዓዋጅ እስከ መውጣት መደረሱን አብራርተዋል። “የተሻሻለው በአመፅ ድርጊት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መልሶ ስለመመዝገብ የሚመለከተው ዓዋጅ፣ ህወሓት ወደ ቀደመው ዕውቅና ሊመልስ አይችልም ” ብለዋል፣ ደብረፅዮን (ዶ/ር)።
አያይዘውም፣ ሊቀ መንበሩ “ህወሓት ወደ ነባር ዕውቅናው ይመለሳል እንጂ እንደ አዲስ አይመዘገብም ” በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ “ህወሓትን እንደአዲስ መመዝገብ ማለት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማፍረስ ማለት ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች በተገኙበት ነው ህወሓት ወደ ነባሩ ዕውቅና ለመመለስ ስምምነት ላይ የተደረሰው” በማለት ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት “በልዩ ሁኔታ” በማለት የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።