
12 ነሐሴ 2024, 15:29 EAT
አሜሪካ ውጥረት ወደተባባሰበት መካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ መሬት ላይ ያሉ ዒላማዎችን ሊመቱ የሚችሉ ሚሳኤሎችን የሚያስወነጭፍ ባሕር ሰርጓጅ መርከቧን ላከች።
ከባሕር ሰርጓጅ መርከቡ ቀድሞ የሚደርስ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ አካባቢው እንደተላከም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ገልጸዋል።
ከፍተኛው የሐማስ መሪና ከፍተኛ የሄዝቦላህ አመራሮች መገደላቸውን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣናዊ ግጭት ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። አሜሪካም ስጋቱን ተከትላ የጦር መርከቦቿን ወደ አካባቢው አሰማርታለች።
አሜሪካ የጦር መሣሪያዎቹን መላኳ እስራኤልን ከኢራን ለመከላከል ቁርጠኛ መሆኗን ያሳያል ሲሉ ሎይድ ኦስተን ተናግረዋል።
“አጋራችንን ለመከላከል ማንኛውንም አማራጭ እንከተላለን” ብለዋል።
ኢራን ለሐማስ ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ግድያ መቼ እና እንዴት አፀፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ እየተጠበቀ ይገኛል።
በሃኒያ ግድያ ኢራን እስራኤልን ተጠያቂ አድርጋለች። እስራኤል ከግድያው ጀርባ እንዳለች በስፋት ቢታመንም ስለ ጉዳዩ ምንም አላለችም።
ዩኤስኤስ ጆርጂያ የተባለውን ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መላኳን ፔንታገን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ኤፍ-32 ሲ ተዋጊ ጄት ተሸካሚ መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲያቀናም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ኢራን ምን እያቀደች እንዳለ ግን ግልጽ አይደለም።
እስራኤል ላይ ጥቃት ሊሰነዝር የሚችለው ሄዝቦላህም ጭምር ነው።
- በህወሓት ጉባኤ መካሄድ ላይ ለሁለት በተከፈሉት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ተካርሯል12 ነሐሴ 2024
- በግዛቷ የተፈጸመውን የሐማሱ መሪ ግድያን ለመበቀል የሚጠበቀው የኢራን አጸፋዊ ምላሽ12 ነሐሴ 2024
- ጦርነት እና ድህንትን በመሸሽ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሰሃራ በረሃ ከባድ መከራን የሚያልፉ ስደተኞች12 ነሐሴ 2024
የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኮማንደር ፉዓድ ሹክር መገደሉን ተከትሎ ሄዝቦላህ አፀፋዊ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
በካታር፣ ጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር መርሀን ካማራቫ እንዳሉት፣ አሜሪካ በይፋ ባሕር ሰርጓጅ መርከቧን ወደ አካባቢው መላኳ “ኢራን እና ሄዝቦላህን ለማስፈራራት” ያለመ ነው።
“ኢራን አንዳች ነገር እያቀደች ነው። ጥቃት መሰንዘሯ አይቀርም” ብለዋል።
ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በርካታ በረራዎች ተሰርዘዋል።
ሉፍታንዛ ወደ ቴል አቪቭ፣ ቤሩት፣ ኤርቢል፣ ቴህራን እና ኦማን እስከ አውሮፓውያኑ ነሐሴ 21 ድረስ በረራ መሰረዙን አስታውቋል።
ኤር ፍራንስም ወደ ቤይሩት የሚያደርገውን በረራ የሰረዘ ሲሆን፣ ስዊዝ ኤር ወደ ቴል አቪቭ እና ቤይሩት በረራ አቋርጧል።
ኤርባልቲክ እና ኢዚጀት አየር መንገዶችም በረራ እንደሚሰርዙ ገልጸዋል።
ከወራት በፊት ሶርያ ውስጥ ያለው የኢራን ቆንስላ ጽህፈት ቤት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ኢራን እስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል።
የጆ ባይደን አስተዳደር በጋዛ የተኩስ አቁም ተደርጎ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ ለማድረግ ንግግሩን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሐማስ በበኩሉ እስራኤል ለድርድር የቀረቡትን ነጥቦች መቀበል እንዳለባት ለአሜሪካ ገልጿል። ሆኖም በንግግር ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን ቡድኑ አክሏል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ንግግሮች ያልተሳኩት በሐማስ ምክንያት ነው ብትልም፣ የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደሚሉት አሜሪካ ቀኝ ዘመም ጥምር ፓርቲ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ስምምነት ባለማድረግ ተጠያቂ ታደርጋለች።
ዋይት ሐውስ ባለፈው ሳምንት በይፋ እስራኤላዊውን የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሊል ስሚትሮች ወቅሷል።
ሚኒስትሩ እስራኤል አሜሪካ ያቀረበችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዳትቀበል ይገፋፋሉ።
የዋይት ሐውስ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሚኒስትሩ “ስህተት ሠርተዋል” ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ይሻሉ።
“ከዚህ በኋላ መዘግየት እንደሌለበት እንስማማለን። መረጋጋት እንዲሰፍን እና ነገሮች እንዳይባባሱ ጥረት እንቀጥላለን” ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።