
12 ነሐሴ 2024, 12:54 EAT
የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ውድድር በይፋ ተጠናቋል።
በዚህ ውድድር ከ30 በላይ በሆኑ ስፖርቶች ከ200 በላይ አገራት አትሌቶቻቸውን አሰልፈው ለሜዳሊያ ተፎካክረዋል።
በዚህም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ቻይና እና ጃፓን ቀዳሚዎቹን ሦስት ደረጃዎችን በመያዝ የበላይ ሆነው አጠናቀዋል።
አዘጋጅ አገር ፈረንሳይ አምስተኛ 5ኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን ፈጽማለች።
ፓሪስ ላይ ከአፍሪካ አገራት 12ቱ ብቻ ሜዳሊያ በማግኘት ስማቸው በአሸናፊዎች ዝርዝር ተካቷል።
ኬንያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆናለች። 4 ወርቅ፣ 2 ብር እና 5 ነሐስ ለማግኘት ችላለች። በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 17ኛ ለመሆን በቅታለች።
አልጄሪያ ከአፍሪካ ሁለተኛ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ ሦስተኛ በመሆን አጠናቃለች።
ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሊምፒክ በአንድ ወርቅ እና በሦስት ብር ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ 4ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ 47ኛ ለመሆን ችላለች።
ለኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጤት ከቶኪዮው የተሻለ ቢሆንም፣ ብዙዎች ከዚህም በላይ ጠብቀው ስለነበረ ኢትዮጵያውያን ደስተኛ አልሆኑም።
ለመሆኑ ባለፉት አራት ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ውጤት አስመዘገበች?


ለንደን 2012 ኦሊምፒክ
በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን በተካሄደው የ2012 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሩጫ እና በውሃ ዋና ተሳታፊ ነበረች።
በሩጫ ከ400 ሜትር እስከ ማራቶን በውሃ ዋና ደግሞ በነጻ ቀዘፋ ተሳትፋለች።
ኢትዮጵያ ውጤታማ ከነበረችባቸው ውድድሮችን አንደኛው የለንደን ኦሊምፒክ ነው።
በውድድሩ ላይ ሰባት ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ አንድ ተጨማሪ ሜዳሊያ በአበረታች መድኃኒት ምክንያት በማግኘቷ ቁጥሩ ወደ 8 ደረሰ። በዚህም 3 ወርቅ፣ 2 ብር እና 3 ነሐስ አግኝታለች።
ወርቅ
- ጥሩነሽ ዲባባ – 10 ሺህ ሜትር
- መሠረት ደፋር – 5 ሺህ ሜትር
- ቲኪ ገላና – ማራቶን
ብር
- ሶፊያ አሰፋ – 3 ሺህ መሰናክል
- ደጀን ገ/መስቀል – 5 ሺህ ሜትር
ነሐስ
- ታሪኩ በቀለ – 10 ሺህ ሜትር
- ጥሩነሽ ዲባባ – 5 ሺህ ሜትር
- አበባ አረጋዊ – 1 ሺህ 500 ሜትር

- “የወርቅ ሜዳልያው የራሴ ብቻ ሳይሆን የሲሳይም አደራ ነው” ታምራት ቶላ11 ነሐሴ 2024
- የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ የሜዳሊያ ሠንጠረዥ24 ሀምሌ 2024
- በኦሊምፒክ ሜዳልያ ማሸነፍ ዋጋው ስንት ነው? በኦሊምፒክ ማሸነፍስ ገንዘብ ያስገኛል?11 ነሐሴ 2024

ሪዮ 2016 ኦሊምፒክ
ብራዚል ባስተናገደችው የሪዮ 2016 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሦስት ዘርፎች ተሳትፋ ነበር።
በሩጫ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን፣ በጎዳና የብስክሌት እሽቅድድም እና በ100 ሜትር እና በ50 ሜትር የውሃ ዋና ውድድሮች ተወዳዳሪዎችን አሰልፋ ነበር።
እንደ ለንደን ሁሉ በሪዮ ኦሊምፒክም 8 ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ የቻለችው ኢትዮጵያ፤ አብዛኞቹ ግን የነሐስ ሜዳሊያዎች ነበሩ።
ወርቅ
- አልማዝ አያና – 10 ሺህ ሜትር
ብር
- ገንዘቤ ዲባባ 1 ሺህ 500 ሜትር
- ፈይሳ ሌሊሳ – ማራቶን
ነሐስ
- ጥሩነሽ ዲባባ – 10 ሺህ ሜትር
- ታምራት ቶላ – 10 ሺህ ሜትር
- አልማዝ አያና – 5 ሺህ ሜትር
- ማሬ ዲባባ – ማራቶን
- ሃጎስ ገ/ህይወት – 5 ሺህ ሜትር

ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ
ኢትዮጵያ የምትሳተፍባቸውን የውድድር ዘርፎችን በአንድ ከፍ አድርጋ በጃፓን ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ተሳትፋች።
ከሩጫ፣ ከብስክሌት እና ከውሃ ዋና በተጨማሪ በቴኳንዶም ተሳታፊ ሆናለች።
በውድድሩ ላይ ገኘችው የሜዳሊያ ብዛት ደግሞ በግማሽ ቀንሷል። አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ወርቅ
- ሰለሞን ባረጋ – 10 ሺህ ሜትር
ብር
- ለሜቻ ግርማ – 3 ሺህ መሰናክል
ነሐስ
- ጉዳፍ ጸጋይ – 5 ሺህ ሜትር
- ለተሰንበት ግደይ – 10 ሺህ ሜትር

ፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ
ዘንድሮ ፈረንሳይ ፓሪስ ላይ በተካሄደው ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያ በሩጫ እና በውሃ ዋና ስፖርቶች ብቻ ነው የተሳተፈችው።
በቁጥር ረገድ ደግሞ አራት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ከቶኪዮው ኦሊምፒክ ጋር ተመሳሳይ ውጤት አስመዝግባለች።
ዘንድሮ አንድ ወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳሊያዎችን አሳክታለች።
ወርቅ
- ታምራት ቶላ – ማራቶን
ብር
- በሪሁ አረጋዊ – 10 ሺህ ሜትር
- ጽጌ ዱጉማ – 800 ሜትር
- ትዕግስት አሰፋ – ማራቶን
ቅሬታ እና ተቃውሞ
የኢትዮጵያ ቡድን በፓሪስ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ከመጓዙ በፊት በአትሌቶች እና በኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በኦሊምፒክ ኮሚቴው አለመግባባት ተፈጥሮ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ውዝግብ ሲሰማ ነበር።
ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ እና ውጤት የነበራቸው አትሌቶች ከምርጫው ወጥተው ውስን ሯጮች በተደራራቢ እና በተለያዩ ዘርፎች እንዲወዳደሩ መደረጋቸው ቅሬታን ፈጥሮ ነበር።
ይህ ውሳኔም የቡድኑን ውጤት ይጎዳዋል በሚል አስተያየቶች በስፋት ሲሰጡ ከመቆየታቸው የተነሳ የውጤት መጥፋቱ ብዙዎችን አስከፍቷል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውጤት ታገኝባቸዋለች ተብለው በሚጠበቁት የ5 ሺህ እና የ10 ሺህ የውድድር ዘርፎች ሜዳሊያ አለመገኘታቸው የበለጠ ጥያቄ አስነስቷል።
ይህ ሁኔታም ከቅሬታ እና ከጥያቄ ባሻገር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኦሊምፒክ መሪዎች የአገሪቱ ቡድን ለገጠመው ደካማ ውጤት ኃላፊነቱን ወስደው ከቦታቸው እንዲለቁ ግፊት እየተደረገ ነው።