ቤሪ “ቡቸር” ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ
የምስሉ መግለጫ,ቤሪ “ቡቸር” ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ

13 ነሐሴ 2024

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 5/2024 ሁለት አሜሪካዊያን ጠፈርተኞች ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ (አይኤስኤስ) ተጓዙ።

ሐሳባቸው የነበረው ወደ ማዕከሉ ሄደው እዚያም ስምንት ቀናት ቆይተው ለመመለስ ነበር።

ነገር ግን ጉዟቸው እንዳሰቡት አልሄደላቸውም።

በቀናት ጉዳያቸውን እንፈጥማለን ብለው ወደ ሕዋ ያቀኑት ቤሪ “ቡቸር” ዊልሞር እና ሱኒታ ዊሊያምስ ናቸው።

ይኸው ከሄዱ ሁለት ወራት አለፋቸው። እነሱም ከምድር በላይ እየተንሳፈፉ ይገኛሉ።

ሁለቱ ጠፈርተኞች መቼ ምድርን ይረግጣሉ የሚለው አይታወቅም። በቀጣይ ወራት የመመለሳቸው ነገርም አጠያያቂ ሆኗል። ኧረ እንዲያውም መጪው የአውሮፓውያን ገና እና አዲስ ዓመትም ሊያመልጣቸው ይችላል።

የ61 ዓመቱ ዊልሞር እና የ58 ዓመቷ ዊሊያምስ ቦይንግ ስታርላይነር በተሰኘው የጠፈር መንኩራኩር ነው ወደ ሕዋ ጣቢያው ያቀኑት።

አዲሱ መንኩራኩር ከዚህ ቀደም ሰው ሳይጭን መጥቆ ያውቃል። ጠፈርተኞች ተሳፍረውበት ሲሄድ ግን ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

መንኩራኩሩ በመደበኝነት ሰዎችን ማመላለስ ከመጀመሩ በፊት ለመሞከር ነው ሁለቱ ጠፈርተኞችን ይዞ የተላከው።

ነገር ግን ወደ ጣቢያው መቃረብ ሲጀምር ሁኔታው ይወሳሰብ ያዘ። በተለይ ደግሞ ‘ፕሮፐልሽን ሲስተም’ የተሰኘው እሣት የሚተፋው ክፍል ማፍሰስ ጀመረ። ሌሎቹም ክፍሎቹ ችግር ይስተዋልባቸው ነበር።

ምንም እንኳ ሁለቱ ጠፈርተኞች በሰላም ወደ ጣቢያው ቢደርሱም ወደ ምድር ለመመለስ ሌላ የትራንስፖርት መንገድ መፈለግ አለባቸው። ካልሆነ ደግሞ ስታርላይነር ታድሶ ወደ መሬት መመለስ እንደሚችል ሲታወቅ ነው የሚመለሱት።

ባለፈው ረቡዕ መግለጫ የሰጡት የናሳ ባለሥልጣናት ቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው ጥያቄ እስካሁን የረባ ምላሽ የለንም ብለዋል።

“ዋነኛው አማራጫችን ቡች እና ሱኒን በስታርላይነር መመለስ ነው” ብለዋል የናሳ የመንገደኞች በረራ ፕሮግራም ኃላፊ ስቲቭ ስቲች።

“ቢሆንም ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም ዕቅዶች እያወጣን” ነው ሲሉ አክለዋል።

ቦይንግ ስታርላይነር
የምስሉ መግለጫ,የተጓዙበት መንኮራኩር

ናሳ ሁለቱን ጠፈርተኞቹን ለመመለስ ብዙ አማራጮች እየተመለከተ ይገኛል። አንደኛው አማራጭ በሚቀጥለው መስከረም ወደ ሕዋ ተጉዞ በጪው የአውሮፓውያን ዓመት 2025 የካቲት የሚመለስ መንኩራኩር ላይ መጫን ነው።

ይህ ወደ አይኤስኤስ የሚደረገው በረራ የሚካሄደው በስፔስ ኤክስ ክሩው ድራገን መንኩራኩር ነው። ይህ በረራ አራት ሰዎችን ጭኖ መሄድ ነበር ዕቅዱ። ነገር ግን ሁለት ሰዎች መሬት ሊቀሩ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ይህ ማለት ለስምንት ቀናት ወደ ሕዋ ጣቢያ ያቀኑት ሁለቱ ጠፈርተኞች ስምንት ወራት ይቆያሉ ማለት ነው።

ክሩው ድራገን ወደ ሕዋ ሄዶ ሁለቱን ጠፈርተኞች ይዞ የሚመጣ ከሆነ ስታርላይነር በኮምፒውተር እየተመራ ወደ መሬት የሚመለሰው ባዶውን ነው ማለት ነው።

የናሳ ባለሥልጣናት እንደገለጹት የመጨረሻው ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከሳምንት በላይ ሊፈጅ ይችላል።

የናሳ የሕዋ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር የሆኑት ኬን ባወርሶክስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ስታርላይነር ያለምንም ተሳፋሪ ወደ መሬት የመመለሱ ዕድል እየሰፋ መጥቷል ብለዋል።

ሁለቱ ጠፈርተኞች በስፔስኤክስ መንኩራኩር ወደ ምድር የሚመለሱ ከሆነ ለቦይንግ ትልቅ ኪሳራ ይሆናል። ቦይንግ ለዓመታት ስፔስ ኤክስን ሲፎካከር የቆየ ቢሆንም የተሳካለት አይመስልም።

ከቀናት በፊት ወደ አይኤስኤስ ምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች የላከው የስፔስ ኤክስን ሮኬት ተጠቅሞ ነው። ሮኬቷ ለሁለቱ ጠፈርተኞች የሚሆን ተጨማሪ ልብስ ይዛ ነው ወደ ሕዋ የተተኮሰችው።

ቦይንግ ስታርላይነር
የምስሉ መግለጫ,ምንጭ፡ ቦይንግ

ባለፈው ወር አጠር ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሁለቱ ጠፈርተኞች ስታርላይነር “በጣም አስገራሚ ነው” ብለው ካደነቁት በኋላ ስለመመለሳቸው “በሙሉ ልብ” እንደሚተማመኑ ተናግረዋል።

የአየር ኃይል ሄሊኮፕተር አብራሪ የነበሩት ጡረተኛዋ ዊሊምስ ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ሲሄዱ ለሦሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ የቀድሞ ተዋጊ ጄት አብራሪ የነበሩት ዊልሞርም እንዲሁ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ወደ ሕዋ ተጉዘው ያውቃሉ።

“እዚህ ካሉት የበረራ አባላት ጋር ተደባልቀን ብዙ ሥራ እየሠራን ነው” ሲሉ ዊሊያምስ ከሕዋ ሆነው በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

“ቤቴ እንደመጣሁ ነው የምቆጥረው። መንሳፈፍ ደስ የሚል ነገር ነው። ሕዋ ላይ መሆን ደስ የሚል ነገር አለው። ለዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ መሥራትም ያስደስታል” ብለዋል የቀድሞዋ አብራሪ።

ቦይንግ ወደ ሕዋ የላከው ስታርላይነር ስኬታማ ከሆነ ወደ ጣቢያው የሚደረጉ ተደጋጋሚ በረራዎችን ለማድረግ ዕቅድ ይዞ ነበር። የስፔስ ኤክስ ንብረት የሆነው ክሩው ድራገን ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ ወደ ሕዋ በረራ እንዲያደርግ በናሳ እውቅና ተሰጥቶታል።

ምንም እንኳ ለስምንት ቀናት ብለው ተጉዘው ለወራት ሕዋ ላይ የከረሙት ሁለቱ ጠፈርተኞች መምጫቸው እስካሁን ባይታወቅም እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

በ1990ዎቹ አጋማሽ ሩሲያዊው ቫለሪ ፖሊያኮቭ ወደ ሕዋ አቅንቶ ለ437 ቀናት ከርሞ መምጣቱ የሚታወስ ነው።

ባፈለው ዓመት ደግሞ ፍራንክ ሩቢዮ ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ጣቢያ ተጉዞ 371 ቀናት ቆይቶ መምጣቱ ይታወሳል።

አሁንም ሕዋ ላይ በሚገኘው ጣቢያ ላይ የሚኖረው ሩሲያዊው ኦሌግ ኮኖኔንኮ ከ1000 በላይ ቀናት በማስቆጠር የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

ዊሊያምስ በጋዜጣዊ መግለጫቸው “እኔ እዚህ ለጥቂት ሳምንታት ቆየሁ ብዬ አላማርርም” ብለው ነበር።

ነገር ግን ዕድለኛ ካለሆኑ ከሳምንታት በላይ የመቆየታቸው ነገር የማይቀር ይመስላል።