የአሜሪካ ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)
የምስሉ መግለጫ,ኢራን ትራምፕን ለማስገደል ፍላጎት እንዳላት ጥርጣሬዎች በርክተዋል

ከ 9 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኢራን በትራምፕ ምርጫ እጇን ስለማስገባቷ ለማጣራት የምርመራ ፋይል ከፈተ።

የመረጃ መንታፊዎች ምናልባት በኢራን የሚደገፉ ወይም ኢራናዊያን ሳይሆን እንዳልቀረ ይገመታል።

የዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን የኢራን መረጃ መንታፊዎች በውስጥ የኢሜል ሥርጭት እጃቸውን አስገብተዋል የሚል ክስ ያቀረበው ከትናንት በስቲያ ነበር።

ይህን ተከትሎ ነው የፌዴራል ምርመራ ቢሮ “ነገሩን እየመረመርን ነው” የሚል አጭር መግለጫ የሰጠው። ሆኖም በዚህ መግለጫው ትራምፕንም ሆነ ኢራንን በስም አልጠቀሰም።

የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ቃል አቀባይ “የውስጥ መረጃችን አሜሪካንን በሚጠላ የውጭ ጠላት ተደርሶበታል” የሚል አስተያየት የሰጡት ከሰሞኑ ነበር።

የኢራን ባለሥልጣናት ግን ስለምትሉት ነገር የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥትም ቢሆን ኢራንን በቀጥታ በስም ጠቅሶ ወቀሳ አላቀረበም።

በአሜሪካ የቢቢሲ የሚዲያ አጋር ሲቢኤስ ዜና በበኩሉ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ የትራምፕን ቡድን ቅሬታ ብቻ ሳይሆን ኢራን በጆባይደን-ካማላ ሐሪስ የምረጡኝ ዘመቻ ላይ እጇን ስለማስገባቷም ለማጣራት ምርመራ ከፍቷል።

ማይክሮሶፍት በሰኔ ወር የአንድ የአሜሪካ አጩ ፕሬዝዳንት መረጃ በኢራን ተሰርስሯል የሚል መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ ነበር የትራምፕ ቡድን በኢራን ላይ ወቀሳ ያቀረበው።

ማይክሮሶፍት እንደሚለው ከኢራን እንደሆነ የጠቀሰው የኤሌክትሮኒክ ኢሜይል ሐቀኛ የውስጥ መረጃ ካለው ሰው የተላከ የሚመስል እንደነበረና መረጃ ለመመንተፍ የታለመ እንደሆነ ጠቅሶ ነበር።

ትራምፕ ይህን ተከትሎ መረጃ ሰርሳሪው ያገኘው ነገር “ሕዝብ የሚያውቀውን መረጃ ነው እንጂ አዲስ ነገር አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ በበኩሉ ጃ ባይደን ከዲሞክራቲክ እጩነት ራሳቸውን ባገለሉበት ዕለት ተመሳሳይ ሐቀኛ መሳይ ኤሌክትሮኒክ ደብዳቤ ለሐሪስ-ባይደን የምርጫ ዘመቻ ቡድን ተልኮ ነበር።

ይህን ተከትሎ የዲሞክራቱ እንደራሴ አዳም ሺፍ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ በጉዳዩ ላይ የሚያውቀውን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ሌላኛው እንደራሴ ኤሪክ ስዋልዌል የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

“እርግጥ ነው ትራምፕ ዋይት ሐውስ ለመግባት ብቁ ያልሆነ አስቀያሚ ሰው ነው። አዎ ትራምፕ ከዚህ ቀደምም የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ሲሻ ነበር። ያ ማለት ግን አሜሪካ የውጭ ኃይሎች በውስጥ ጉዳይ ገብተው እንዲፈተፍቱ ትፈቅዳለች ማለት አይደለም” ብለዋል።

ትራምፕ በፈረንጆቹ 2016 በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ሩሲያ የተቀናቃኛቸውን የሒላሪ ክሊንተንን መረጃ እንድትበረብር በይፋ መናገራቸው ይታወሳል። ይህም ለከፍተኛ ወቀሳ ዳርጓቸው ነበር።

የአሜሪካ የደኅንነት ሰዎች ኢራን ትራምፕን ለማስገደል ፍላጎት እንዳላት ፍንጭ ሰጥተው ነበር። ይህ ግን በፔኒሲልቬኒያ ግዛት ባለፈው ወር ከተሞከረባቸው ግድያ ጋር የሚገናኝ አይደለም።

ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አንድ ከኢራን ጋር ግንኙነት አለው ያለውን ፓኪስታናዊ ትራምፕን ጨምሮ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ለመግደል አሲሯል በሚል በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ ከፍቶበታል።