ያህያ ሲንዋር

13 ነሐሴ 2024

ሐማስ ከኢስማኤል ሃኒያ ግድያ በኋላ የቡድኑ አጠቃላይ መሪ አድርጎ ያህያ ሲንዋርን ሾሟል።

አቡ ኢብራሂም በሚል በስፋት የሚታወቀው ያህያ ሲንዋር፣ ሐማስ ባለፈው መስከረም መጨረሻ በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ካቀነባበሩ አንዱ ነው።

እስራኤል ያህያን ለመግደል እያሳደደችው ትገኛለች።

በጋዛ ሰርጥ የሐማስ መሪ ነው። አሁን የቡድኑን የፖለቲካ ክንፍ ጠቅልሎ ይመራል።

የያህያ መመረጥ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ባለው ጦርነት ምን ይፈጥራል? በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚካሄደው ድርድር ላይስ ተጽዕኖ አለው? የሚሉትን ጉዳዮች ይህ ዘገባ ይዳስሳል።

ደስታ እና ተስፋ መቁረጥ

ፋታህን ጨምሮ ሌሎችም የፍልስጤም ቡድኖች ሐማስ ያህያን በመምረጡ እንኳን ደስ አለን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፋታህ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፀሐፊ ጂብሪል ራጁብ ውሳኔው “ምክንያታዊ እና የኢስማኤል ሃንያን ግድያን የሚበቀል” ነው ብለዋል።

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ እስራኤል ካትዝ በኤክስ ገጻቸው “የተሰጠው ሹመት እሱን ማጥፋት ግዴታ የሚሆንበት ተጨማሪ ምክንያት ነው” ብለዋል።

የእስራኤል ወታደራዊ ክፍል ኃላፊ ሌተናንት ጄኔራል ኸርዚ ሄልቪ “ስሙን መቀየር እሱን ፈልጎ ከማጥቃት አያስቆመንም” ብለዋል።

ጦርነት የታከታቸው ፍልስጤማውያን ግን ሹመቱ አስግቷቸዋል።

ከጋዛ የተፈናቀለው መሐመድ አል-ሸሪፍ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ በሰጠው ቃል “[ሲንዋር] ተዋጊ ነው። እንዴት ድርድር ሊካሄድ ይችላል?” ብሏል።

እስራኤላውያንም በሹመቱ ደስተኛ አይደሉም።

ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ እስራኤላዊ “ሹመቱ ብዙ ይናገራል። አክራሪ ያልሆነ ሰው መምረጥ አልፈለጉም” ብሏል።

ሦስት መልዕክቶች ከሐማስ ለእስራኤል

ሐማስ በያህያ ሲንዋር ሹመት ለእስራኤል እና ለዓለም ብዙ መልዕክት እያስተላለፈ ነው።

የሐማስ አመራር ኦሳማ ሐምዳን ለቢቢሲ እንደተናገረው ሦስት ዋና መልዕክቶች አሏቸው።

አንደኛው ሐማስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ “ትክክለኛ ውሳኔ ማስተላለፍ” እንደሚችል እና ንቅናቄው “በኅብረት መቆሙን” ማሳየት ነው። ጨምሮም ያህያ የተሾመው “በሙሉ ድምጽ ነው” ይላል።

ሁለተኛው መልዕክት “ንቅናቄው ወደፊት እንደሚቀጥል እና መሪዎች ንቅናቄውን ወደፊት ማስቀጠል እንደሚችሉ” ማሳየት ነው።

ሦስተኛው፣ “ጫናዎች ሐማስን ከአቋሙ እና ከአካሄዱ እንደማያናውጡት” ማሳየት መሆኑን ተናግሯል።

በአል-አህራም ማዕከል ፀሐፊ እና የፖለቲካ ተመራማሪ በሽር አብደል ፈታህ እንደሚለው፣ ሹመቱ “የነገሮችን መጋጋል” የሚያሳይ ነው።

“ለኢራን ቅርበት እንደሆነ እና በፖለቲካም ይሁን በወታደራዊ እንቅስቃሴ እስራኤል ላይ ጠንካራ አቋም እንዳለው የሚታወቅ ወታደራዊ ኃላፊን መሾም፣ ሐማስ ወታደራዊ ትግሉን እንደሚቀጥል እና እየደረሰበት ላለው ጫና እና ጉዳት እንደማይንበረከክ ማሳያ ነው።”

ያህያ ሲንዋር

ጋዛ ሆኖ መምራት

በጋዛ የሚኖር መሪን ሐማስ ሲመርጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ኢስማኤል ሃኒያ ወደ ኳታር ከመሄዳቸው በፊት ሐማስን ለሁለት ዓመት የመሩት ከጋዛ ነበር።

ኦሳማ ሐምዳን እንዳለው፣ የሐማስ አመራር “ጋዛ ውስጥም ሆነ ከጋዛ ሰርጥ ውጪ ተዳክሞ አያውቅም።”

ያህያ ሲንዋር ከሃኒያ የተለየ ነው።

እስራኤል ያህያን “ለማደን” ዝታለች። ለመስከረም 26/2016 ዓ.ም. ጥቃት ተጠያቂም ታደርገዋለች።

ያህያን ለመያዝ የሚረዳ መረጃ ለሚሰጥ ሰው 400 ሺህ ዶላር ሽልማት እሰጣለሁ ብላለች። ሲንዋት ከመስከረሙ ጥቃት በኋላ በአደባባይ አልታየም።

በአል-ናጃህ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ሐሰን አዩብ “ያህያ የተመረጠው ተግባራዊ መደረግ በሚችል አካሄድ ነው” ይላል።

“እስራኤል ሃኒያን ዒላማ እንዳደረገችው ማንኛውም ከጋዛ ሰርጥ ውጪ ያለ መሪን ዒላማ ልታደርግ ትችላለች። ያህያ ግን ጋዛ ነው። እስራኤል ለረዥም ጊዜ ልትይዘው ሞክራለች” ሲል ያስረዳል።

ያልተጠበቀ ምርጫ

ኢስማኤል ሃኒያ ከተገደሉ በኋላ መሪ በመምረጥ ረገድ ያህያ ዋና ሚና እንደሚኖረው ተንታኞች ገምተዋል። የእሱ ስም ለመሪነት ከታጩት መካከል ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ አልነበረም።

መሪ ሆኖ መመረጡ ሐማስ የሹመት ሂደቱን አጣድፎ ይሆናል የሚል ጥያቄ አስነስቷል። መሪነቱ “ጊዜያዊ” ሊሆን እንደሚችል እና የጋዛ ጦርነት ካከተመ በኋላ በሌላ መሪ ሊተካ እንደሚችል የገመቱ ተንታኞችም አሉ።

የሐማስ አመራር ኦሳማ ሐምዳን በዚህ አይስማማም።

“ጥልቅ ምርመራ ተደርጎ ነው ሁላችንም እሱን ለመምረጥ የወሰነው” ይላል።

የፖለቲካ ፀሐፊ እና አጥኚው በሽር እንደሚለው፣ ሐማስ “የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት መሸፈን እንደሚችል” ማሳየት ይፈልጋል።

ፕሮፌሰር ሐሰን በበኩላቸው፤ የያህያ መመረጥ በወረራ ሥር ላለው ዌስት ባንክ የሚሰጠው ትርጉም አለ።

“ከሁሉም የፍልስጤም ቡድኖች ጋር መነጋገር ይችላል። በፋታህ በሚመራው የፍልስጤም አመራር እና በሐማስ መካከል ያለውን ግንኙነት ማደስ ይችላል” ብሏል።

ያህያ በጋዛ ሰርጥ አመራሩ ወቅት በውስጣዊ እና በቀጠናዊ ኃይሎች መካከል “ምንም ልዩነት” እንደሌለ ሲያሳይ እንደነበር ይገለጻል።

ከግብፅ ጋር ዕርቅ በመፈጸም፣ ለዓመታት የዘለቀውን ከሶሪያ መንግሥት ጋር የነበረውን ልዩነት በማጥበብ እና ሐማስ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር እንዲቀራረብ ለማድረግ በመሞከር ይታወቃል።

በንቅናቄው ውስጥ ያህያ የተሰጠው መሪነት ከፍተኛው ተደርጎ ይወሰዳል።

በየዓመቱ ጠቅላላ ምርጫ ይደረጋል። በምርጫው የሹራ ምክር ቤት ይመረጣል። በዚህም የፖለቲካ ቢሮ አባላት ይመረጣሉ።

አባላቱ የቢሮ ኃላፊ ይመርጣሉ።

መራር አጋጣሚ

እስራኤል ያህያ ሲንዋርን “በጣም ከባድ እና አክራሪ” ስትል ትገልጸዋለች።

የቀድሞ ብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣን ሚካ ኮቢ በአንድ ወቅት ያህያ እስረኛ ሳለ ከ150 ሰዓታት በላይ የምርመራ መጠይቅ አድርጎለታል።

“ከባድ ሰው” ሲል ያህያን ይገልጸዋል።

ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ “ስሜት አልባ ቢሆንም፣ አእምሮውን የሳተ አይደለም” ሲል ይገልጸዋል።

በአንጻራዊነት ለዘብተኛ የሚባሉት ኢስማኤል ያህያ መገደላቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከያህያ ጋር “የአቻ ለአቻ ግጥሚያ” ውስጥ ገብተዋል።

ያህያ የእስራኤልን አስተሳሰብ ያውቃል።

በእስራኤል ጉዳዮች ጽሑፉ የሚታወቀው ኢልሐብ ጃባሪን “እስራኤል በዚህ ስሌት ፈተና ይገጥማታል” ይላል።

“የእስራኤል ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የጦርነቱ መነሻ ኔታንያሁ እና ያህያ ናቸው ሲሉ ነበር። አሁን ግምታቸው እውን ሆኗል” ሲልም ያስረዳል።

የእስራኤል ብሔራዊ ቴሌቪዢን ጣቢያ የያህያን ሹመት “አስደንጋጭ ነው። በሕይወት እንዳለ እና በጋዛ ያለው የሐማስ አመራር በጥንካሬው እንደሚዘልቅ ለእስራኤል መልዕክት ያስተላልፋል” ሲል ነው የዘገበው።

እአአ በ2011 ያህያ ከእስራኤል እስር ቤት ለመለቀቁ ኔታንያሁን ጥፋተኛ የሚያደርጉ አሉ።

ቤተሰቦቻቸው በጋዛ የታገቱባቸውም በሹመቱ ማዘናቸውን ኢልሐብ ይናገራል።

የመስከረም 26ቱን ጥቃት ተከትሎ ሐማስ 251 እስራኤላውያንን ያገተ ሲሆን፣ 111 የሚሆኑት አሁንም ጋዛ ውስጥ ሲገኙ፣ 39 ሰዎች መሞታቸው በእስራኤል መከላከያ ተገልጿል።

እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ጥቃት ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ ፍልስጤማውያን መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥም አብዛኞቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው።

የተኩስ አቁም ድርድር እንዴት ይካሄዳል?

ኢስማኤል ሃኒያ ከመገደላቸው በፊት በጋዛ የተኩስ አቁም ለማድረግ በሚደረገው ድርድር ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው።

ያህያ ሲንዋርም “ከድርድሮቹ አልራቀም። ዝርዝሩን ያውቀዋል” ሲል ኢልሐብ ይገልጻል።

“ድርድሮች ይቀጥላሉ። መዘግየቱ ያለው ከእስራኤል በኩል ነው” ይላል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት የፈጸመበት ቀን አንደኛ ዓመት እየተቃረበ ሲሆን፣ አሁንም ታጋቾች ጋዛ በመሆናቸው ኔታንያሁ “ፈጥነውም ይሁን ዘግይተው ወደ ድርድር ጠረጴዛ በመመለስ ከያህያ ሲንዋር ጋር መገናኘታቸው አይቀርም” ሲል ያስረዳል።

አሜሪካ ኔታንያሁ ላይ ጫና ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል፣ የሐማስን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ክንፍ ማጥፋት እና ታጋቾችን ማስለቀቅን ጨምሮ ጦርነቱ ግቡን ሳይመታ እንደማታቆም ተናግራለች።

ከጥቂት ወራት በፊት አሜሪካ፣ እስራኤል እና ሐማስ ለተኩስ አቁም መቃረባቸውን አስታውቃ ነበር። ተኩስ አቁሙ እውን ሳይሆን ከቀረ በኋላ ግን ሰፊ ቀጠናዊ ጦርነት እንዳይነሳ ተሰግቷል።

ከዚህ ቀደም ለቀናት የዘለቀ ሰብአዊ ተኩስ አቁም ላይ መድረስ መቻሉ ይታወሳል።

በዚህ ወቅት በሐማስ ከታገቱ መካከል 50 ሴቶች እና ከ19 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎች ነጻ ወጥተዋል። 150 ፍልስጤማውያን ሴቶች እና ታዳጊዎችም ከእስራኤል ከእስር ቤቶች ተለቀዋል።