ቶሞ በአቅራቢያው ባሉ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ካሜራዎች ፊት በፍጥነት ይሮጣል።
የምስሉ መግለጫ,ቶሞ በአቅራቢያው ባሉ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ካሜራዎች ፊት በፍጥነት ይሮጣል።

13 ነሐሴ 2024

የኦሊምፒክ ወዳጆችን አዲስ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሚሠራ ቴክኖሎጂ ትኩረታቸውን ስቦታል።

ቴክኖሎጂው ለወደፊት በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ሊያገኙ የሚችሉ ሰዎችን መለየት የሚያስችል ነው።

የዚህ ፈጠራ ባለቤቶች ዓላማቸው የላቀ የስፖርት ሳይንስን በሁሉም የዓለም ጥጎች ማዳረስ ነው።

ቴክኖሎጂውን እየሞከሩ ያሉት ታዳጊ ወንድማማቾች ታክቶ እና ቶሞ ይባላሉ። የሰባት እና የአራት ዓመት ልጆች ሲሆኑ የተለወዱት በጃፓን፣ ዮኮሃማ ነው።

የሰዎችን እንቅስቃሴ እየተከተለ የተለያየ ቀለም የሚያሳየውን የቴክኖሎጂ ውጤት ተጠግቶ ታክቶ ይሮጣል።

ታናሽ ወንድሙ ቶሞ በአቅራቢያው ባሉ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ካሜራዎች ፊት በፍጥነት ይሮጣል።

ቴክኖሎጂው ለሙከራ የቀረበው ከፓሪስ ኦሊምፒክ ስቴድየሞች በአንዱ አቅራቢያ ነው።

ዋና ዓላማው ለወደፊት በኦሊምፒክ ወርቅ ማምጣት የሚችሉ ሰዎችን ቀድሞ ማወቅ ነው።

ከሩጫ፣ ከዝላይ፣ ከጡንቻ ጥንካሬ አና ከሌሎችም የሰውነትን ብቃት የሚፈትሹ አምስት እንቅስቃሴዎች መረጃ ይሰበስባል።

ይህ መረጃ ይብላላና ሰዎች ያላቸው አቅም፣ ጥንካሬ፣ ብቃት፣ የሰዓት አጠቃቀም እና ፍጥነት ይለካል።

ከዚህ የሚገኘው ውጤት ከኦሊምፒክ አትሌቶች ጋር ይነጻጸራል።

የሰዎችን እንቅስቃሴ እየተከተለ የተለያየ ቀለም የሚያሳየውን የቴክኖሎጂ ታክቶ ሞክሮታል።
የምስሉ መግለጫ,የሰዎችን እንቅስቃሴ እየተከተለ የተለያየ ቀለም የሚያሳየውን የቴክኖሎጂ ታክቶ ሞክሮታል።

የኢንቴል ኦሊምፒክ ኤንድ ፓራሊምፒክ ፕሮግራም ኃላፊት ሳራ ቪከርስ እንደምትለው ሥራውን የሚሠሩት ታሪካዊ መረጃ በማከማቸት እና በምሥል ወይም በተንቀሳቃሽ ምሥል ያሉ ሰዎችን እንዲለይ በተሠራው ‘ኮምፒውተር ቪዥን’ አማካይንት ነው።

“አንድ ሰው በቴክኖሎጂው ሙከራ ሲያደርግ ራሱን ከታዋቂ አትሌቶች ጋር ማነጻጸር ይችላል። በየትኛው የስፖርት ዓይነት ጎበዝ እንደሆነም ማወቅ ይችላል” በማለት ታስረዳለች።

ሙከራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሙከራውን ያደረጉ ሰዎች ከአሥር የስፖርት ዓይነቶች መካከል በየትኛው ቢሳተፉ ውጤታማ እንደሚሆኑ ይነገራቸዋል።

ሙከራውን የሚያደርጉ ሰዎች የግል መረጃ በየጊዜው እንደሚጠፋ እና እንደማይከማች የፈጠራው ባለቤቶች ተናግረዋል።

ሙከራውን ያደረገው ታዳጊ ታክቶ “በጣም ነው የወደድኩት። በተለይ የአጭር ርቀት ሩጫ መሞከራችን የበለጠ አስደስቶኛል” ብሏል።

ተንቀሳቃሹ ቴክኖሎጂ

በፓሪስ ኦሊምፒክ የቀረበው ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ በሚችልበት መንገድ ነው የተሠራው።

ይህም አነስተኛ ካሜራ ያለው እና ለማጓጓዝ የተመቸ ነው።

“በስልክ ወይም በላፕቶፕ ከዚህ ቀደም መሄድ ያልተቻለባቸው ቦታዎች መሄድ ይቻላል” ስትል ሳራ ታስረዳለች።

ሰዎችን ሲሮጡ በካሜራ በመከታተል ብቃታቸውን መለካት የሚችል ቴክኖሎጂ ነው።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቴክኖሎጂውን ወደ ሴኔጋል በቅርቡ ወስዶታል። በአምስት መንደሮች በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊዎች የአትሌቲክስ ብቃታቸው ተፈትኗል።

ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቴክኖሎጂውን ወደ ሴኔጋል በቅርቡ ወስዶታል።
የምስሉ መግለጫ,ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቴክኖሎጂውን ወደ ሴኔጋል በቅርቡ ወስዶታል።

ከሴኔጋል የኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር 48 “የታመቀ ችሎታ” ያላቸው ታዳጊዎች እና አንድ “ልዩ ተሰጥኦ” ያለው ታዳጊን ማግኘት ተችሏል።

ታዳጊዎቹ ፍላጎት ካላቸው የስፖርት ፕሮግራም ውስጥ እንዲገቡ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። በዚህም የአትሌቲክስ ችሎታቸውን ምን ያህል ርቀት መውሰድ እንደሚችሉ ይፈተሻል።

የስፖርት ብቃት መመዘኛ አሠራር ባልተዘረጋባቸው አካባቢዎች ይህንን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ችሎታ ያላቸው ሰዎችን መለየት እንደሚቻል ይታመናል።

በሰፎልክ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጆን ብሪወር እንደሚሉት፣ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች በልጅነታቸው ማግኘት “ታላቅ ድል” ነው።

ከዩናይትድ ኪንግደም የእግር ኳስ ማኅበር ጋር በመሆን ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎችን ለማግኘት የሠሩት ፕሮፌሰር ጆን፣ ይህ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሲውል ጥንቃቄም ያስፈልጋል ይላሉ።

ቴክኖሎጂው መመዘን የሚችለው ችሎታ፣ ቴክኒካዊ ብቃት የሚሹ እንደ እግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስ ያሉ ስፖርቶችን ለማካተት እንደማይችል ያስረዳሉ።

ከባርሴሎና ፓሪስ የሄደችው ፍራንቼስካ ቴክኖሎጂውን ሞክራለች።
የምስሉ መግለጫ,ከባርሴሎና ፓሪስ የሄደችው ፍራንቼስካ ቴክኖሎጂውን ሞክራለች።

“በማራቶን ወይም በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ለማሸነፍ ሰውነት የሚይዘው የትፋሽ መጠን እና ትንፋሽን የመቆጣጠር ብቃት ይጠይቃል። ይሄንን በካሜራ ሊታይ አይችልም” ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ይህ ቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው አትሌቶችን ቀድሞ ለማወቅ እንደሚረዳ ግን ያምናሉ።

“በአንድ ስፖርት ሰዎች ያላቸውን ብቃት እና የሰውነት ቅልጥፍና ለመለየት የሚውል ከሆነ የሚበረታታ ቴክኖሎጂ ነው” ይላሉ።

“ከቦታ ቦታ የሚጓጓዝ ከሆነ የቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሌላቸው እና ብቃትን መለካት የማይችሉ አካባቢዎችን መድረስ ይችላል። ይሄም መልካም ነው” በማለትም ያክላሉ።

ሆኖም ግን “ችሎታን መለየት ከሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች አንደኛው ብቻ ነው” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

የመጨረሻ ውጤት

በቴክኖሎጂው በመታገዝ ብቃቱን በፓሪስ የፈተሸው ታዳጊው ታክቶ የአጭር ርቀት ሯጭ ቢሆን እንደሚሳካለት ተነግሮታል።

አሁን የሚወዳቸው ስፖርቶች እግር ኳስ አና ቴኒስ ቢሆኑም ችሎታው በቴክኖሎጂ ተፈትኖ በተሰጠው ውጤት ደስተኛ ነው።

የቀድሞ ዋናተኞቹ ሐንክ እና ብሮክ በቴክኖሎጂው በመታገዝ ብቃታቸውን ፈትነዋል። የአትሌቲክስ ብቃት እያላቸው ሙከራውን ካደረጉ መካከል ናቸው።

የቀድሞ ዋናተኞቹ ሐንክ እና ብሮክ በቴክኖሎጂው በመታገዝ ብቃታቸውን ፈትነዋል።
የምስሉ መግለጫ,የቀድሞ ዋናተኞቹ ሐንክ እና ብሮክ በቴክኖሎጂው በመታገዝ ብቃታቸውን ፈትነዋል።

“የቀድሞ አትሌቶች ነን። ቴክኖሎጂውን መሞከር ያስደስታል” ሲል ሐንክ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ብሮክ በበኩሉ “እኛ ከ15 ዓመታት በፊት ዋና ስንዋኝ እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጂ አልነበረም” ብሏል።

በቴክኖሎጂው ብቃታቸው ከተለካ በኋላ ሐንክ በራግቢ፣ ብሮክ ደግሞ በቅርጫት ኳስ ስኬታማ እንደሚሆኑ ቴክኖሎጂው ተንብይዋል።

ብሮክ “አንድም ቀን ቅርጫት ኳስ ተጫውቼ አላውቅም” ብሏል።

ጓደኛው ሐንክ ግን አንድ ቀን ብሮክ አብሮት ቅርጫት ኳስ እንደተጫወተ አና ጎበዝ ስላልሆነ ከዚያ በኋላ አብሮት በጨዋታው አነዳልገፋበተ ተናግሯል።

ይሄን ውጤት መነሻ አድርጎ መገመት እንደሚቻለው፣ ምናልባትም ቴክኖሎጂ ሁሌም ትክክል ላይሆን ይችላል።