ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል

ከ 8 ሰአት በፊት

ሁለት ዓመት ተኩል ባስቆጠረው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ትልቁን ድንበር ተሻጋሪ ወረራ ያደረገችው ኪዬቭ 100 ሺህ ሄክታር የሚሆን የሩስያ ግዛትን መቆጣጠሯን አንድ የአገሪቱ ከፍተኛ አዛዥ ገለጹ።

ኮማንደር ኦሌክሳንደር ሲርስኪ እንዳሉት ከሆነ ዩክሬን ከሰባት ቀናት በፊት የጀመረችውን “የኩርስክ ግዛት ጥቃት” አጠናክራ መቀጠሏን ነው።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ በሌሎች ላይ ጦርነት እየከፈተች ነበር፤ አሁን ግን ጦርነቱ ወደ ሩሲያ እየተመለሰ ነው ብለዋል።

የሩሲያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ወረራውን “ትልቅ ጸብ አጫሪነት” በማለት የሩሲያ ሃይሎች “ጠላትን ከግዛታችን ጠራርጋችሁ አስወጡ” የሚል ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ በርካታ ነዋሪዎች ከምዕራብ ሩሲያ ግዛት የተፈናቀሉ ሲሆን ተጨማሪ 59 ሺህ ሰዎች ለቀው እንዲወጡ ተነግሯቸዋል።

በአካባቢው የሚገኙ 28 መንደሮች በዩክሬን ኃይሎች እጅ መውደቃቸውን የአከባቢው አስተዳዳሪ ገልጸው 12 ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን እና “ሁኔታው አስቸጋሪ ሆኖ ቀጥሏል” ብለዋል።

የዩክሬን ወታደሮች ባለፈው ማክሰኞ ድንገተኛ ጥቃት በማድረስ 30 ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ድንበር ዘልቀው ገብተዋል።

ጥቃቱ በዩክሬን በኩል መነሳሳት እንዲጨምር አድርጓል ቢባልም፣ ስልቱ በዩክሬን ላይ አዲስ አደጋ ይኖረዋል ሲሉ ተንታኞች ገልጸዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የብሪታኒያ ከፍተኛ ወታደራዊ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሞስኮ በዚህ ወረራ በጣም ስለምትናደድ በዩክሬን ሲቪሎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቷን በእጥፍ ልትጨምር እንደምትችል ስጋት አለ።

ካርታ ቤልጎሮድ ከኩርስክ ቀጥሎ ምልክት ተደርጎበታል።

ፕሬዝዳንት ፑቲን ሰኞ ዕለት በመንግስት ቴሌቪዥን ቀርበው ባስተላለፉት መልዕክት “ከጠላት ግልጽ ግቦች አንዱ ግጭትን መዝራት፣ መቃቃርን፣በነዋሪዎች ላይ ፍርሃት ማሳደር፣ የሩሲያን ማህበረሰብ አንድነትና ትስስር ማፍረስ ነው” ብለዋል።

“ዋና ሥራ የመከላከያ ሚኒስቴር ጠላቶቻችንን ከግዛታችን ማባረሩ ነው” ሲሉ በባለስልጣናቱ ስብሰባ ወቅት ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር 121 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል። በዩክሬን ኃይሎች በተያዙ አካባቢዎች ወደ 2 ሺህ የሚጠጉ የሩሲያ ዜጎች መኖራቸውን ለፑቲን ተነግሯቸዋል።

“ስለ ዕጣ ፈንታቸው የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ አክለዋል።

መስኮት በሌላቸው እና ጠንካራ ግድግዳ ባላቸው ክፍሎች ውስጥ ከሚሳኤሎች ራሳቸውን እንዲከላከሉ አስጠንቅቀዋል።

ከኩርስክ ቀጥሎ ባለው ቤልጎሮድ ክልል ድንበር ላይ የጠላት እንቅስቃሴ አለ ያሉት አስተዳዳሪው ቭኣቼስላቭ ግለድኮቭ፤ ከክራስናያ ያሩጋ አካባቢ 11 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤታቸው እንዲለቁ ተማጽነዋል።

በተመሳሳይ የሚሳኤል ጥቃት ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀው ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ምድር ቤት እንዲጠለሉ መክረዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በምሽት በሚሰጡት ዕለታዊ መልዕክታቸው “ፑቲን ክፉኛ መዋጋት ከፈለገ ሩሲያ ሠላም ለመፍጠር መገደድ አለባት” ሲሉ ጥቃቱ መፈጸሙን አምነዋል።

“ሩሲያ በሌሎች ላይ ጦርነት እያመጣች ነበር አሁን እሷ ቤት እየመጣ ነው። ዩክሬን ሁልጊዜ የምትፈልገው ሰላምን ብቻ ነው። እናም በእርግጠኝነት ሰላምን እናረጋግጣለን “ሲሉ ዜለንስኪ አክለዋል።

የዩክሬን ባለስልጣናት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች በዘመቻው ላይ ተሰማርተዋል ብለዋል። ይህም በሩሲያ ድንበር ጠባቂዎች መጀመሪያ ላይ ከተዘገበው አነስተኛ ወረራ እጅግ የላቀ ነው።

አንድ ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዜና ወኪል እንደተናገሩት ዓላማቸው “ከፍተኛ ኪሳራ ማድረስ እና በሩሲያ ያለውን ሁኔታ ማወክ” ነው።

በኔቶ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ኩርት ቮልከር ለቢቢሲ የኒውስ ሃወር እንደተናገሩት የዩክሬን ወረራ ፕሬዝዳንት ፑቲን በአገር ውስጥ ፖለቲካዊ ኪሳራ ሊያመጣባቸው ይችላል።

ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቃ የገባችው “በፕሬዚዳንት ፑቲን እና ይህን ጦርነት ባካሄደበት መንገድ ነው” ብለዋል።

“ይህ በሩሲያ ባሉ ልሂቃን ዘንድ የሚጠፋ አይደለም። በሕዝቡ ዘንድም የሚጠፋ አይደለም። ፑቲን በራሱ በሩሲያ ግዛት ላይ ጥቃት ቀስቅሷል። ሰዎችም ተፈናቅለዋል።”

የአሜሪካ ሴናተር ሊንዚ ግራሃም ሰኞ ዕለት በኪዬቭ ከዜለንስኪ ጋር ባደረጉት ውይይት የድንበር ተሻጋሪውን ጥቃት “ምርጥ” እና “ድፍረት የተሞላበት” ከማለት ባለፈ የባይደን አስተዳደር ለዩክሬን አስፈላጊውን መሳሪያ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

አንዳንድ ሩሲያውያን ዩክሬን ወደ ኩርስክ ክልል እንዴት ልትገባ እንደቻለች ጠይቀዋል። የሩስያ ጦር ደጋፊ ሆነው ጦማሪው ዩሪ ፖዶሊያካ በበኩሉ ሁኔታውን “አስፈሪ” ብሎታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሃሮቫ በበኩላቸው ከሩሲያ ጦር ኃይሎች “ጊዜ ሳይፈጅ” ጠንከር ያለ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

የሩሲያ አጋር የሆነችው ቤላሩስ በበኩሏ ዩክሬን ወደ አየር ክልሏ በሰው አልባ አውሮፕላኖች ገብታለች ካለች በኋላ በድንበሯ ላይ ያለውን የጦሯን ቁጥር እያጠናከረች ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ሰኞ ረፋድ ላይ በዩክሬን ግዛት በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዛፖሪዥያ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ እሑድ ዕለት በደረሰ ቃጠሎ የማቀዝቀዣ ማማው ላይ የደረሰውን ጉዳት መፈተሹን ቢገልጽም ምክንያቱን ግን ወዲያውኑ ማወቅ አልቻለም።

ዜለንስኪ ግን የዩክሬንን “ጥቃት” ነው ለማስባል በማሰብ ሩሲያ እሳቱን ሆን ብሎ ጀምራለች ሲሉ ከሰዋል። በክሬምሊን የተሾሙት የዛፖሪዥያ ክልል ገዥ ግን በዩክሬን ጥቃት የተከሰተ ነው ብለዋል።