የፓርቲው መሪዎች

13 ነሐሴ 2024, 13:34 EAT

ተሻሽሏል ከ 2 ሰአት በፊት

ከከፍተኛ አመራሮቹ እና ከአባላቱ እንዲሁም ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገቢውን ሂደት የተከተለ አይደለም የተባለው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ መክፈቻ መቀለ ውስጥ መካሄድ ጀመረ።

በህወሓት ሊቀመንበር እና ምክትል በሚመሩ የድርጅቱ አባላት መካከል ክፍፍልን የፈጠረው ይህ ጉባኤ፤ በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በሚገኘው በሰማዕታት አዳራሽ ውስጥ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በዛሬው ዕለት ማክሰኞ ነሐሴ 7/ 2016 ዓ.ም. ጠዋት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው 14ኛው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ከሰዓት መሸጋገሩን ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ለጠዋት ታስቦ የነበረው የጉበኤው መክፈቻ ለምን ወደ ከሰዓት እንደተሸጋገረ የተገለጸ ነገር የለም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣን “ጠዋት ወደዚህ ለመጣው ጉባኤተኛ ተመለሱ እና ከሰዓት በኋላ 9፡00 ላይ እንድትመጡ ተብለዋል። ከሰዓት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ምን እንደሚካሄድ አይታወቅም” ብለዋል።

ህወሓት በበኩሉ ጠቅላላው ጉባኤ በተያዘለት መርሃ ግብር መሠረት ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ እንደሚካሄድ በፌስ ቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

“ጠዋት ለተሳታፊ ጉባኤተኞች መለያ ካርዶች እና አስፈላጊ ሰነዶች ተሰጥተዋል። ጉባኤው ከሰዓት በኋላ ይጀመራል” ብሏል ህወሓት ያጋራው አጭር መግለጫ።

የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ከኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ጋር ውዝግብ ላይ የሚገኘው ህወሓት የሚጠበቀውን ሂደት ሳይከትል እና ለቦርዱ ሳያሳውቅ የሚያካሂደው ጉባኤ ተቀባይነት የለውም የሚል ደብዳቤ ከምርቻ ቦርጫ እንደተጻፈለት ይታወቃል።

በጉባኤው የሚሳተፉ ከተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የመጡ የህወሓት አባላት እና አመራሮች ስብሰባው ወደሚካሄድበት መቀለ ከተማ ከሰኞ ጀምረው ሲገቡ ነበር።

በሌላ በኩል የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዚህ ጉባኤ እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸው ተገልጿል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፤ “ጉባኤው ትግራይን እና ሕዝቡን አደጋ ውስጥ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም” ብለዋል።

አቶ ጌታቸው የጋራ መግባባት ሳይደረስ አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች ይህን ጉባኤ ለማካሄድ የተነሱት “ይቃወሙናል የሚሏቸውን አመራሮች ለማስወገድ በማለም ነው” ብለዋል።

ህወሓት በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን እንዲሁም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ከቀናት በፊት ያስታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ተቋሙን ሳያውቅ እንዲሁም የቦርዱ ታዛቢዎች ባልተገኙበት ሁኔታ ጠቅላላ ጉባኤው ሊካሄድ እንደማይችል አስታውቋል።

ጠቅላላ ጉባኤው ከቦርዱ ፍቃድ ውጪ ከተካሄደ ለዚህ ጉባኤም ሆነ ለሚወሰኑ ውሳኔዎች ዕውቅና እንደማይሰጥም ከስብሰባው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰኞ ነሐሴ 6/2016 ዓ.ም. ለህወሓት በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።

ፓርቲው የሚተዳደረው የኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ፣ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር ማሻሻያ እንዲሁም በቦርዱ ውሳኔዎችን መሠረት እንደሆነ ገልጾ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጉ ከሦስት ሳምንታት በፊት ማሳወቅ እና ታዛቢዎቹ በዚህ ጉባኤ ላይ መገኘት ግዴታዎቹ ናቸው ብሏል።

በልዩ ሁኔታ መመዝገቡን ያልተቀበለው ህወሓት ያቀረብነው ጥያቄ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስነት መሆኑን እና የተሰጠው መልስ ግን ሌላ መሆኑን ጠቅሷል።

ስብሰባ

ህወሓት፣ ግንቦት መጨረሻ ላይ የጸደቀው የፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ማሻሻያ አዋጅ የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት እንደማይመለስ በመገንዘቡ በጉዳዩ ላይ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የፌደራል መንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገው የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም በአፍሪካ ኅብረት ፓነል ውይይት ላምይ እንዲሁ የፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ከስምምነት ተደርሷል ብሏል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ የተደረሱ መግባባቶችን ወደጎን በመተው ጥያቄውን በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅን ለማሻሻል በወጣ አዋጅ ላይ ተመሥርቶ የሰጠውን ምላሽ አልቀበልም ብሏል።

ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ የፓርቲው ሕገ-ደንብ በሚፈቅድለት መልኩ ተያያዝ ሥራዎችን ያከናውናል ያለ ሲሆ፣ን የፌደራል መንግሥቱም የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው የህወሓት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ማመልከቻ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ የማያውቀው ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ህወሓት የቀድሞው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ለቦርዱ አመልክቶ የነበረ ቢሆንም፣ በጸደቀው ማሻሻያ መሠረት የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነትን መመለስ የሚል ባለመኖሩ ጥያቄው ተቀባይነት አለማግኘቱ ተገልጿል።

በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች መካከል የፓርቲውን ድርጅታዊ ጉባኤ ከማካሄድ እና ከፓርቲው ዳግመኛ ሕጋዊ እውቅና ከማግኘት ሂደት ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ተካረዋል።

ይህን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀ-መንበር ጌታቸው ረዳ እና በፓርቲው ሊቀ-መንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራ ክፍፍል ተፈጥሯል።

በእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) እና ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር የሚመራው ቡድን የትግራይን ጦርነት ተከትሎ የተሰረዘው የፓርቲው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስለት እና ከነገ ማክሰኞ ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. ጀምሮ የፓርቲውን 14ተኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ማድረግ ይፈልጋል።

በሌላ በኩል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ያሉበት ቡድን፤ በአሁኑ ወቅት ድርጅታዊ ጉባኤው እንዲካሄድ ፍላጎት የላቸውም። ፓርቲው፤ ሕጋዊ እውቅናው እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካቀረበው ጥያቄ ጋር የቀረቡ ሰነዶች ሕጋዊነት ላይም ጥያቄ ያነሳሉ።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚመረጡበት ይህ ጉባኤ የሚካሄድ ከሆነ፤ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሊገለሉ ይችላሉ የሚል ግምትም አለ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክትል አስተዳዳሪ እና የክልሉ የፀጥታ ኃላፊ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የሕዝቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ላለልተወሰነ ጊዜ የድጋፍም ይሁን የተቋውሞ ሰልፍ በክልሉ ውስጥ ማድረግ ተከልክሏል ብለዋል።

14ና ዓመት የሚያመለክት ጽሁፍ