የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ
የምስሉ መግለጫ,የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ

ከ 15 ደቂቃዎች በፊት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና እንዲሰጣት ጠየቁ።

በአሁኑ ወቅት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን ያላቸው አምስቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ናቸው።

አምስቱ ቋሚ አባል አገራት አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በቅኝ ገዚዎች ስር በነበሩበት ወቅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የፈጠሩት ስብስብ፤ የዓለም ፍላጎትን የሚወክሉ አይደሉም ተብለው ይተቻሉ።

ጉቴሬዝ “ከ1945 በኋላ ብዙ የዓለም እውነታ ተቀይሯል። ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤት ስብጥር ግን ጉልህ ለውጥ ሳያሳይ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።

ምክር ቤቱ ከቋሚ አምስት አባላቱ በተጨማሪ ተለዋዋጭ የሆኑ 10 አባል አገራት አሉት። እነዚህ ተለዋዋጭ አገራት የተለያዩ የዓለም ቀጣናዎችን የሚወክሉ ቢሆንም ልክ እንደ ቋሚ አባላቱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የላቸውም።

የአፍሪካ ኅብረት ሁለት የአፍሪካ አገራት ቋሚ የምክር ቤት አባል እንዲሆኑ እና ሁልጊዜም ሁለት ተለዋዋጭ አባል አገራት በምክር ቤቱ ወንበር እንዲኖራቸው ሲጠይቅ ቆይቷል።

የፀጥታው ምክር ቤት አገራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን መጣል፣ የሰላም ማስከበር ስምሪቶችን መፍቀድ፣ እንዲሁም ለግጭቶች ተመድ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለበት የሚለውን ይወስናል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንት ዴኒስ ፍራንሲስ እንዲሁ የፀጥታው ምክር ቤት ዳግም መዋቀር አለበት ሲሉ የጉቴሬዝን ሃሳብ ደግፈዋል።

ጉተሬዝ “የዓለም የሰላም እና ደኅንነት አካል ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ሳይወክል እንዲቆይ መፍቀድ የለብንም” ካሉ በኋላ፤ ከአጠቃላይ የድርጅቱ አባል አገራት ዜጎች 28 በመቶ አፍሪካውያን መሆናቸውን ጨምረው አስታውሰዋል።

ጉቴሬዝ አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ሃብት የግጭት ማዕከል አድርጓታል ያሉ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ግማሽ ያክሉ እየተከናወኑ ያሉት በአፍሪካ መሆኑን ገልጸዋል።

ጨምረውም ከዓለም አቀፉ ድርጅት የሰላም አስከባሪዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያ መሆናቸውን ተናግረው የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካን ተሳትፎ የሚመጥን ውክልና የለውም ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሲቋቋም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ላይቤሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነበሩ በምሥረታው የተሳተፉ የአፍሪካ አገራት።