የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች
የምስሉ መግለጫ,የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂካን ፊዳን እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም (ፎቶው ከፋይል የተገኘ)

ከ 5 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው የባሕር በር አጠቃቀም መግባቢያ ስምምነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ በተናጠል የሚያደርጉት ውይይት ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በቱርክ ጋባዥነት ወደ አንካራ ያቀኑት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አህመድ ሞሊም ሁለተኛ ዙር ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይታቸውን ትናንትና ሰኞ ነሐሴ 6/ 2016 ዓ.ም. በአንካራ ጀምረዋል።

የሁለቱ አገራት ልዑካን በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢገኙም ፊት ለፊት አለመገናኘታቸውን ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ የቱርክ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂካን ፊዳን የሁለቱን አገራት ባለሥልጣናት ለየብቻ በማናገር ለውጥረቱ እልባት ለመስጠት እየተሞከሩም ነው ተብሏል።

የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፊዳን ትናንትና ሰኞ የሁለቱን አገራት ሚኒስትሮች ሁለት ጊዜ በማናገር ልዩነታቸው እንዲጠብ ለማድረግ መሞከራቸውን፣ ይህንን የተናጠል ንግግር በቅርበት የሚያውቁ ባለሥልጣንን ዋቢ አድርጎ ቪኦኤ ዘግቧል።

በሁለቱ አገራት መካከል የተነሱት መሠረታዊ ጉዳዮች የመግባባቢያ ስምምነቱ ይሰረዝ እንዲሁም የባሕር በር ተደራሽነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ተገልጿል።

ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ከሰባት ወራት በፊት በተፈረመ የመግባቢያ ሰነድ ምክንያት ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሁለቱ አገራት፣ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ በተናጠል ሲመክሩ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ አንካራ ከማቅናታቸው በፊት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድን ከስምምነት በሚደረስበት ሁኔታ ላይ ነሐሴ 4 እና 5/ 2016 ዓ.ም. አነጋግረዋቸዋል።

በቱርክ እና በሶማሊያ መካከል ያለውን ትብብር አስፈላጊነት አጽንኦት የሰጡት ኤርዶዋን በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ አገራቸው ጥረቷን እንደምትቀጥል መናገራቸውን የቱርክ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኤክስ ገጹ አስፍሯል።

ኤርዶዋን ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት “በሁለተኛው ዙር ድርድር ተጨባጭ ውጤት” እንደሚጠብቁ መናገራቸውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ኢትዮጵያ፣ የሶማሊያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እንዲሁም የግዛት አንድነት ላይ የምታነሳቸውን ስጋቶች የሚሆኑ እርምጃዎችን ከመውሰድ እንድትታቀብ መናገራቸውን በዚሁ መልዕክታቸው ላይ ሰፍሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሁሉም አካላት በሚስማሙበት መንገድ የኢትዮጵያን የባሕር መዳረሻ የማግኘት አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውም ተዘግቧል።

የሶማሊያው አቻቸው በበኩላቸው አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በምጣኔ፣ ሀብት እና በልማት ለመተባበር ዝግጁ መሆኗን ገልጸው ነገር ግን “እንዲህ ያሉ አጋርነቶች የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንቦችን ማክበር አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ የማሸማገሉን ሚና የያዘችው ቱርክ ከዚህ ቀደም የተናጠል ውይይትን በማመቻቸት ለማደራደር ሞክራለች።

የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ አማካይነት ሰኔ መጨረሻ ገደማ የተናጠል ንግግር ያደረጉ ቢሆንም ከስምምነት ሳይደረስ ሌላ ቀጠሮ ይዘው መለያየታቸው ይታወሳል።

ከውይይቱ ማብቃት በኋላ የሁለቱም አገራት ተወካዮች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ መልካም ጉርብትናን እና ቀጠናዊ መረጋጋትን ከግምት በማስገባት መፍትሄዎችን ለማመላከት ያለሙ ምክክሮችን ለመቀጠል መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሐምሌ 27/ 2016 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር እንዲሁም ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ጋር በመምከር ለውጥረቱ እልባት ለማበጀት መሞከራቸው ተዘግቧል።

ውይይቱን ተከትሎ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ከቱርክ አቻቻው ሃካን ፊዳን ጋር በሰጡት መግለጫ “የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጎዳ ማንኛውንም ድርጊት በጽኑ እንቃወማለን” ማለታቸው ተዘግቧል።

የሚኒስትሩ መግለጫ ሶማሊላንድን ያስቆጣ ሲሆን “በሶማሊላንድ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት በተመለከተ የተነገሩት መግለጫዎች የተሳሳቱ እና የሕዝባችንን ሉዓላዊ መብቶች ያላከበሩ ናቸው” ሲል ተችቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ እና በካይሮ ያደረጉትንም ቆይታ ተከትሎ ነሐሴ 3/ 2016 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ የሶማሊያን ሉዓላዊነት መከበርን ትኩረት አድርገውበታል።

“ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ሉዓላዊነት እውቅና በመስጠት በሶማሊያ በኩል የባሕር በር ካገኘች በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት ይረግባል” ብለዋል ፊዳን።

ቱርክ የሶማሊያ የቅርብ አጋር ስትሆን ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን እና መሠረተ ልማቶችን ከመገንባት በተጨማሪ ለበርካታ ሶማሊያውያን የትምህርት ዕድል ትሰጣለች።

ከወራት በፊትም ቱርክ እና ሶማሊያ ጉልህ የሚባል ምጣኔ ሀብታዊ እና ወታደራዊ ስምምነት አድርገው ግዙፍ የቱርክ የጦር መርከብ ወደ ሶማሊያ መላኳ ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ 2017 ቱርክ በሞቃዲሾ ትልቁን የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር ያቋቋመች ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ደግሞ ቱርክ እና ሶማሊያ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ፈርመዋል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።

ከሶማሊያ በኩል ተደጋጋሚ ክሶች እና መግለጫዎች ከመቅረባቸው በተጨማሪም ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።