August 13, 2024 – Konjit Sitotaw 

በጋምቤላ ክልል በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ57 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተባለ

በጋምቤላ ክልል በዘንድሮ የክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ ሊያጋጥማቸው ይችላል ተብለው ከተለዩ ዘጠኝ ወረዳዎች ከ57 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጋትቤል ሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ።

ባለፈው ቅዳሜ በክልሉ ባሉ አራት ወረዳዎች ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር 17 ሺህ መድረሱንም ኃላፊው ተናግረዋል።

የጎርፍ አደጋው የተከሰተው፤ ከሶስት ቀናት በፊት አርብ ምሽት በጣለው ከባድ ዝናብ የአኮቦ እና ጊሎ ወንዞች ሞልተው ጎግ፣ ላሬ፣ ጆር እና ዋንቱዋ የተባሉት ወረዳዎችን በማጥለቅለቃቸው መሆኑን አቶ ጋትቤል አስረድተዋል።

በአደጋው የሞተ ሰው አለመኖሩን የገለጹት ኃላፊው፤ ሆኖም “በንብረት፣ በሰብል እና ከብቶች ላይ ግን ጉዳት ደርሷል” ብለዋል።

በጎርፍ መጥለቅለቁ ሳቢያ እስከ ትላንት ድረስ 16 ሺህ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን መረጋገጡን የገለጹት ኃላፊው፤ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በትላንትናው ዕለት መጨመሩን አስረድተዋል።

ሁሉም ተፈናቃዮች በየወረዳዎቹ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲጠለሉ መደረጉን አቶ ጋትቤል አመልክተዋል።

ለተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት የሚመገቡትን እያቀረቡላቸው የሚገኙት፤ በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች እንደሆኑ ኃላፊው ጠቁመዋል።