August 13, 2024 – Konjit Sitotaw 

” ይህ ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም ” – አቶ ጌታቸው ረዳ

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ ከደቂቃዎች በፊት መግለጫ አውጥተዋል።

ጉባኤው ” በችኮላና የጋራ መግባባት ሳይደረስበት ፤ በማደናገርና በአቋም አልባነት አሰባስበናቸዋል በሚሉት ኔትወርክ  ‘ ይቃወሙናል ‘ የሚሉዋቸው የተወሰኑ አመራሮች ለማስወገድ በማለም የሚካሄድ ጉባኤ ነው ” ብለውታል።

” ይህ ጉባኤ ትግራይን እና ህዝቡን ወደ አደጋ ከመክተት የዘለለ እርባና የለውም ” ሲሉ ገልጸዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ  ፤ ” የተሻሻለው የፓለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ህወሓት እንደ አዲስ እንደሚዘገብ የሚያደርግ ፣ ወርቃዊው የትግራይ ህዝብ ትግል የሚያጎድፍ በቀጣይ ቅርቃር ውስጥ የሚከት መሆኑን በመገንዘብ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ በማእከላዊ ኮሚቴ አባላት መግባባት ተደርሶ ነበር ” ብለዋል።

” ይሁን እንጂ የተደረሰው መግባባትና መተማመን ወደ ጎን በመተው ‘ ከፌደራል መንግስት ተማምነናል ‘ በሚል ማደናገሪያ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመነጋገር  ከማእከላዊ ኮሚቴ እና ካድሬ በመደበቅ የተሄዴበት ሂደት ወዳልተፈለገ ወጥመድ እንድንገባ ተደርገናል ” ብለዋል።

” በዚህ ምክንያት የሚፈጠር ማንኛውም ጥፋት ተጠያቂው ለጠባብ ቡድናዊ ፍላጎቱ ብቻ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ነው ” ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ጌታቸው ፥ ” የህዝቡ ሰላም እንዳይደፈርስና እንዳይረበሽ ከህዝባችንና ከመላ አባላችን በመሆን እንታገላለን ” ብለዋል።

” ሁሉም የትግራይ አቅሞች በማቀናጀት በተደራጀ ትግል ከፍተኛ ፓለቲካዊ ድርድር በማካሄድ የህወሓት ህጋዊነት በመመለስ ካጠላብን ዙርያ መለስ ፈተና በመውጣት የትግራይ የተሟላ ደህንነትና እድገት እንደሚረጋገጥ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ” ብለዋል።