Asnakew Abebe

  · 

የወልቃይት ቃል ኪዳን ጠብቆ የተገመደ ነው!

ይህ የምታዩትን ፎቶ ያነሳሁት ከሶስት አመታት በፊት ነው። የወልቃይት ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው ወፍ አርግፍ ላይ። ይህ ውብ ታዳጊ ጠብ እርግፍ ብለው ምሳ የጋበዙን ወገኖቻችን ውስጥ አንዱ ነው። ከጎንደር ከተማ ተነስተን የትክል ድንጋይን ተዳፋት ወርደን፣ የአርማጭሆን ውብ መልክአ ምድር እያደነቅን ሳንጃ ላይ የውሃ ጥማችንን ቆረጥን ከፍራፍሬውም ተቋደስን። ሰረቋ ከተማዋን ከነወንዟ የሰራችውን ታሪክ በአርምሞ አይተን አልፈን ዳንሻ ላይ ቅልጥ ያለ ግብዣ እናታለም ጎንደር ምግብ ቤት ውስጥ ተጋበዝን። ተጋበዝን ያልኩት ሂሳብ አትከፍሉም የፍቅር ግብዣ ይሁን ብለውን ጭራሽ ብዙ ቀዝቃዛ ውሃ አሸክመውን ጉዞውን ወደ ሑመራ አቅጣጫ አደረግን።

ወደ ሑመራ ከተማ ቀጥተኛውን መንገድ መከተል ብንችልም ሳይታዩ መታለፍ ያሌለባቸውን ስፍራዎች ለማየት ወደ ግራ በኩል ወደ ምድረ ገነት አቅጣጫ አቀናን። የተንዠረከከው ዋርካ ስር ትንፋሽ ወሰድን ቅዝቃዜውን እረካንበት። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወ*ያኔ ስልጣን በእድል እና በማናለብኝነት ስትፈናጠጥ በአስር ሽህዎች ታጣ*ቂዎቿን አስፍራ የነበረችበትን “ዲቪዥን” የተባለውን ስፍራ ቆርጠነው ሄድን። የጦ*ርነቱ ወላፈን እዛ ላይ በግልፅ ይታይ ነበር። ብዙም ሳንቆይ በድሮ የተለምዶ አጠራር “አብደራፊ” በትክክለኛው በምንጠራት “ምድረ ገነት” ከተማ ደረስነ። ምድረ ገነት ለምን እንደተባለች ወዲያውኑ ነበር የገባኝ። ገበሬው ሁሉ ብር በኬሻ የሚይዝባት እንደሆነች አይቻለሁ። ለውሃ ጥም ቀዝቃዛ ቢራ እንደ ጉድ ይጠጣባታል። ሰው የተረጋጋ ነው። ምግብ ቤት ውስጥ ልንከፍል ስንልን በድጋሜ እንግዶች ተብለን እዛው ተጠቃሚዎች ቀድመው እንደከፈሉት ተነግሮን ቢራ ጠጥሉነ ተብለንም ነበር።

ሑመራ ሳይመሽ ለመድረስ ስለጓጓን አመስግነን ከከተማዋ ሰሜን አቅጣጫ ብዙም ሳንርቅ አይደርቄው እና አስደማሚው ታላቁ አንገረብ ወንዝ ሲንጎማለል አገኘነው። ልናልፈው አልፈለግንም። ገባንበት! ዋኘንበት። በጋ ጠራራ ፀሃይ ሙቀት ስለነበር ቀዘቀዝንበት። ኩልል ያለ ውሃ ነበር። የትም ቦታ ላይ ሳይገደብ ወደ ሱዳን ዘልቆ ይፈሳል፣ ጓንግን ተቀላቅሎ ከዛም የተከዜ ተፋሰስ አካል ይሆናል። ቢያንስ ቢያንስ ይህ መደማምር፣ ይህ ሱፍ ውሃ፣ ይህ የአንገረብ ወንዝ እና የጓንግ ወንዝ የሚገናኙበት ስፍራ ነው የኢትዮጵያ ድንበር። አሁን ሱዳን ያንን መደማምር ተሻግሮ እንደልቡ መፍነክነክ ከጀመረ አራተኛ አመቱ ነው።

ሑመራ ለመድረስ ልባችን ቢነሳሳም፤ የሰማእታቱን አሰ*ቃቂ ድርጊት መፈፀሚያ ማይካድራ ከተማን ግን በቅጡ ማየት እና ተጎጅ ወገኖቻችንን ማስተዛዘን በእቅድ የያዝነው ነበር። ከሑመራ ከተማ ወደ ሰላሳ ኪ.ሜ. እርቀት ላይ የምትገኘው ማይካድራ ከተማ ፈዛ እና የሃዘን ጥላ አንዣቦባት ነበር ያገኘናት። አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያየነውን የጅምላ መቃ*ብር እይታ ልባችን ሊቀበለው ልንሸከመው አልቻልንም። እንባችን እየፈሰሰ መንፈሳችን እጅጉን ተረብሾ ግፉን ከሰለባው ተራፊዎች እማኝ ሰማን። ወያ*ኔ በእቅድ፣ ሰነድ አዘጋጅቶ፣ ነፃ እርምጃ የሚወስዱ ታጣ*ቂዎቹን መድቦ፣ 1665 በላይ በስም በእድሜ እና በማንነታቸው የተለዩ የአማራ ብሔር ተወላጆች በአንድ ጀንበር ነበር የተጨ*ፈጨፉት። ከተለያየ የኢትዮጵያ ቦታዎች ለስራ የመጡ ወገኖቻችንም የዚሁ የጥ*ቃቱ ሰላባ ነበሩ። የጅ*ምላ መቃ*ብር ቦታው የዝንብ ጋጋታ እና ክፉ ጠረን የመከራውን ብዛት እንዳትረሱት ተቀርፆ የሚቀር ክፉ ትዝታ ነው።

ከዛም ጀንበር ስትዘቀዝቅ ተንደርድረን ሑመራ ከተማ ደረስነ። ቀጥ ብለን ስለት ነበረብን እና ተከዜ ወንዝ ተወርውረን ገባን። ተጠመቅን! ታጠብን! የአርባ አመታት የእብሪት ወረራ አብቅቶ በእርስታችን በቀያችን በወንዛችን ታጠብን! የተከዜ ድልድይ ላይ ወጣን። ተሻገርን። ከማዶ ያሉ የሐማሴን ወገኖቻችን እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለው በፍቅር አስተናገዱን። ከዛም ጀንበሯ ቦታዋን ስትለቅ ወደ ሆቴላችን አመራን። የወልቃይት ጠገዴ ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው እራት አብረውን አመሹ። በጀነሬተር መብራት ብዙ መከርን አወጋን። ቃል ኪዳን አደስን። ምግቡን ከዛ በፊትም ከዛ በኋላም በልቸው የማላውቅ ካርቤቶ የሚባል፣ አሁን በፍልሰታ ለወግ የማይመች ግን እጅ የሚያስቆረጥም በልዩ ሁኔታ ተቀምሞ የተዘጋጀ ጥብስ ከነቅልጥሙ ነበር።

ሑመራ በማለዳው ተነስተን ወደ ቤት ሞሎ ማቅናት ነበረብን እና የከተማዋን ልዩ ቁርስ ልናልፈው አልፈቀድንም። እናም ፉል ቤት አቀናን። በቃ፣ ሌላ ቦታ አታገኙትም። በሰሊጥ ዘይት አብዶ የተሰራ፣ ከደጋማው ወገራ በመጣ ባቄላ ግሩም ሆኖ የተዘጋጀ፣ ኦርጋኒክ አይብ ያለበት ድብን ብሎ የተከሸነ ቁሊት ያሽሞነሞነው የፍየል እንትን ቅርፅ ባለው ባኒ ተመገብን። ቀኑን ሙሉ እህል አያምርም። ከሙዙ፣ ከብርቱካኑ፣ ከሎሚው እና ከሸንኮራው የሚበቃንን ያክል የማለዳ ገቢያው ላይ ከነምርቃቱ ሸመትን።

ከዛማ ቀጥ ባለው መንገድ ለሰአታት በፈጀው አብዛኛው ጥቅጥቅ ደን፣ እንዲያም ሲል እርሻ፣ በየመሀሉ ትንንሽ መንደሮች እና ለቁጥር የማይዘለቅ የቁም እንስሳት መንጋ እያየን ፍፈረስ መጋላቢያን፣ አዲጎሹን አልፈን በትግሬ በኩል ወዳለው የተፈጥሮ ወሰናችን ተከዜ ወንዝ አቅጣጫ ስንጠመዘዝ፤ የመዘጋ ወልቃይት የአማደጋዋን ፈርጥ ቤት ሞሎ ከተማ ደረስንባት። እዛ አቅራቢያ ነው ዝነኛው የጎንደር ዘመን አያናዝጊ የወልቃይት ጥንታዊ ቤተመንግስት የሚገኛው። ምሳ ሰአት አለፍ ብሎ ነበር። ምሳ ግን ይቅርብን ብለን የዋልድባ ገዳማት መነኮሳትን የአክብሮት ሰለምታ እየሰጠን ወደ ተከዜ ወንዝ ለመጠጋት ከጅለን ለአይን የሚያታክተውን የአርማ ደጋ ሰፊ መልክአ ምድር እየቃኘን የእጣን ሙጫ መገኛ ነጫጭ የመቀር ዛፎች በአይናችን ውልብልብ እያሉ ስንገሰግስ፣ ከወንዙ ስንቃረብ ለፀጥታው ብዙም ዋስትና የለምና ተመለሱ ተብለን ወደ ወልቃይት ወረዳ ዋና ከተማ ወፍ አርግፍ ማቅናቱን መረጥን።

የወልቃይት መስተንግዶ በፅሁፌ መነሻ የጠቀስኩትን ጉብል ታዳጊ ጨምሮ ብዙ ጣፋጭ ትዝታ አለን። እዛ ላይ ጀግናው ኮ/ል ደመቀን ጨምሮ ብዙ የከተማው ጉምቶ ባላባቶች ጠብ እርግፍ ብለው አስተናገዱን። ብዙ ብዙ ተባባልነ!

ታሪኩን ልቀጥለው… ግን ለአሁኑ በይደር ያዙልኝ፣

ታሪኩም ቃል ኪዳናችንም ይቀጥላል!

ሙሉነህ ዮሐንስ

May be an image of 1 person and smiling