

ማኅበራዊ የጤናው እክል እንደሆኑ የቀጠሉት ተላላፊ በሽታዎች
ቀን: August 14, 2024
በተለያዩ ክልሎች በሚገኙና የኮሌራና ኩፍኝ ወረርሽኞች ከተከሰቱባቸው 596 ወረዳዎች መካከል 531 ያህሉ ከወረርሽኞች ሙሉ ለሙሉ ፀድተዋል፡፡ በቀሩት 65 ወረዳዎች የተንሠራፉትን ተመሳሳይ ወረርሽኞች ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የቅኝት፣ የክትትልና ምላሽ የመስጠት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሯ፣ የኩፍኝ ወረርሽኝ በጥጥር ሥር የዋለው በ422 ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን፣ ከኮሌራ ወረርሽኝ ነፃ የሆኑት ደግሞ 109 ወረዳዎች ናቸወ፡፡ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ እየተካሄደ ያለውም የኩፍኝ ወረርሽኝ ባሉባቸው 22 ወረዳዎችና የኮሌራ ወረርሽኝ በታዩባቸው 43 ወረዳዎች ነው፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው በስምንት ክልሎችና 58 ወረዳዎች ላይ ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አሥር ዓመት ለሆኑ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሕፃናት የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በመስጠትና የማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ ትምህርትና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመከናዋኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከስድስት ወር እስከ አሥር ዓመት የሆናቸው በ43 ወረዳዎች ለሚገኙ 1.6 ሚሊዮን ሕፃናት በመከተብ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡
ልጆችን ከዘጠኝ ወር ጀምሮ ማስከተብ፣ በሕፃናት ላይ ትኩሳት፣ ሳል፣ አፍንጫ አካባቢ ፍሳሽ (የጉንፋን መጀመርያ) እና ሽፍታዎች ሲታይባቸው ወዲያውኑ አቅራቢያቸው ወደሚገኘው ጤና ተቋም መወሰድ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የኮሌራ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ከሚውሉ ዋና ዋና የምላሽ ሥልቶች መካከል አንዱ የሆነው በአፍ የሚሰጥ የኮሌራ ክትባት ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በተመረጡ ክልሎች በተሰጠው ስምንት ዙር የክትባት ዘመቻዎች በጠቅላላ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መከተብ ተችሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በዘጠኝ ዙር ከዓለም አቀፍ አደጋ መከላከል ቡድን የተጠየቀው 1.6 ሚሊዮን የክትባት መጠን ተፈቅዶ ወደ አገር ገብቷል፡፡ ዘመቻ ለማካሄድም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በ222 ወረዳዎች የታየውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የምልከታ፣ የቅኝትና የክትትል ሥራዎች መከናወናቸውንና ይህ ዓይነቱም ክንውን ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው አንድ ወር ብቻ በበሽታው ለተያዙ ከ700,000 በላይ ዜጎች ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉ፣ ከዚህም ሌላ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕሙማንን ማከም የሚያስችል የፀረ ወባ መድኃኒቶች አገር ውስጥ በማስገባት ለየክልሎቹ መሠራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ፈጣን የመመርመርያ ኪቶችና ግብዓቶች እንዲገዙ መደረጉን፣ 1.8 ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ቤቶች ውስጥ ኪሚካል መረጨቱንም ለዚህም የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ለሥርጭት የሚረዱ መሣሪያዎች ለተለያዩ ክልሎች እንዲላክ መደረጉን፣ ዓምና ከሰባት ሚሊዮን በላይ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ 30 ሚሊዮን አጎበሮች ተገዝተው መሠራጨታቸውን፣ ባለፈው ሳምንትም 551,000 አጎበሮች መገዛታቸውን ገልጸዋል፡፡
አንድ አጎበር እስከ ሦስት ዓመት ድረስ እንደሚያገለግል ሆኖም የኅብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀም ከ50 በመቶ በታች እንደሆነና አጎበር በአግባቡ አለመጠቀም ደግሞ በሽታን በመከላከሉና ሕይወት በማትረፍ ሥራ ላይ እንቅፋትና ጫናን እንደሚፈጥር አመልክተዋል፡፡
ለወባ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች አቅራቢያ 56 ሚሊዮን የወባ አጎበሮች ተሠራጭተዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ መድኃኒት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አብዱልቃድር ገልገሎ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወባን መከላከል የሚያስችሉ በመርፌና በኪኒን የሚሰጡ ብዙ ዓይነት መድኃኒቶች አሉ፡፡
በዚህም የተነሳ በኪኒን መልክ የሚወሰዱ 500 ሚሊዮን ብር የሚያመጡና በመርፌ የሚሰጡ 13 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው መድኃኒቶች መሠራጨታቸውንና በየቤቱ ፀረ ወባ መድኃኒት መረጨቱን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ሁለትና ሦስት ወራት ብቻ 748 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወባ ግብዓቶች ለየክልሎቹ መከፍፈሉን፣ 77 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች በውኃና ረግረግማ ቦታዎች ላይ መረጨቱንም አክለዋል፡፡
በወቅቱ ልየታ አለመሥራት፣ የፀጥታ ችግር፣ የክትባት እጥረትና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች በሽታዎቹ እንዲስፋፉ ያደረጉ ምክንያቶች ቢሆኑም፣ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ሲወተውቱ ከርመዋል፡፡
በተለይ ከጂቡቲ እንደገባች የሚነገርላት ወባ በኢትዮጵያ የጤና ሥጋት መደቀኗ የተነገረው ቀድሞ ነው፡፡
መነሻዋን ከጂቡቲ እንዳደረገች የሚነገርላት አዲሷ የወባ አስተላላፊ ትንኝ ወደ ኢትዮጵያ በመግባቷ በሽታውን በፍጥነት ታዛምታለች የሚል ሥጋት መደቀኑን ደግሞ፣ ሪፖርተር ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የወባ በሽታን ለመከላከል ላለፉት 50 ዓመታት ቢሠራም፣ ገዳይነቱን ማስቆም አልተቻለም፡፡ በቅርቡ የተከሰተችው አዲሷ የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኝ ደግሞ ችግሩን አባብሳዋለች፡፡ በተሠራው የቅኝት ሥራም በ52 የኢትዮጵያ ከተሞች ውስጥ ታይታለች፡፡
ትንኟ ከቀድሞዎቹ በሽታ አስተላላፊ የምትለይበት በርካታ ባህሪዎች ያሏት ሲሆን፣ ከእነዚህ በማንኛውም ክፍት ውኃ ውስጥ መራባቷ፣ በከተሞች አካባቢ መራባቷ፣ ቀድመው ከነበሩት ሁለት ዓይነት የወባ በሽታ አስተላላፊ ትንኞች በመውሰድ ማስተላለፍ መቻሏ ይጠቅሳሉ፡፡
ትልቁ ለየት የሚያደርጋት ባህሪዋ ከዚህ ቀደም ለወባ በሽታ ይሰጡ ከነበሩ ሕክምናዎችና የመከላከያ ሥራዎች ሁሉ ማምለጥ መቻሏ ነው፡፡ የማስተላለፍ መጠኗም ቀድሞ ከነበረው የጨመረ ነው፡፡ ከዓመት ዓመትም በየትኛውም የአየር ፀባይ በመራባት በሽታ ማስተላለፍ ትችላለች፡፡
ድሬዳዋን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ ጥናት ከ10 ሺሕ በላይ አዳዲስ የወባ በሽታ ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን፣ የበሽታው በከፍተኛ መጠን መዛመትም አሳሳቢ ነው፡፡
