በሶሪያ የደረሰው ጥቃት

ከ 8 ሰአት በፊት

የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ወደሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ይስፋፋል ተብሎ ተሰግቷል።

ኢራን እና ሌሎችም የውጭ አካላት በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል።

ሐማስ ያለፈው መስከረም መጨረሻ እስራኤል ላይ በሰነዘረው ጥቃት ውስጥ ኢራን እጇ እንደሌለ ብትገልጽም፣ እስራኤል ላይ ‘አስደንጋጭ የመሬት መንቀጥቀጥ’ የሆነውን ጥቃት እንደምትደግፍ አስታውቃለች።

ኢራን መጀመሪያ ላይ ከእስራኤል ጋር በቀጥታ አልተጋጨችም። ሆኖም ኢራን በቀጥታም በተዘዋዋሪም የምትደግፋቸው እና ራሳቸውን ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ብለው የሚጠሩ ቡድኖች ከእስራኤል ጋር እየተዋጉ ነው።

እነዚህም የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ የየመኑ ሁቲ እና በኢራቅ ያሉ የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ናቸው።

አብዛኞቹን ቡድኖች አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ሌሎችም አገራት ሽብርተኛ ብለው ፈርጀዋቸዋል።

በግጭቱ የሄዝቦላህ ሚና

የጋዛ ጦርነት በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መካከል ያለውን ውጥረት ዳግመኛ ቀስቅሷል።

ሄዝቦላህ ሐማስን በመደገፍ በሰሜናዊ እስራኤል አካባቢዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።

በመስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ጥቃትን ተከትሎ ባለው ቀን በእስራኤል ይዞታ ሥር ባሉት የሼባ እርሻዎች ላይ ሄዝቦላህ ጥቃት ከፍቷል።

እስራኤል በምላሹ በአካባቢው ያሉ የሄዝቦላህ መጠለያ ድንኳኖችን ዒላማ አድርጋ የአጸፋ ጥቃት ፈጽማለች። የሊባኖስ መከላከያ እንዳለው በዚህ ጥቃት ሊባኖሳውያን ተጎድተዋል።

“በቀጠናው ውስጥ እና ውጭ” ካለው የሐማስ አመራር ጋር ግንኙነት እንዳለው ሄዝቦላህ አስታውቋል።

የሁቲዎች ሚና

የጋዛ ጦርነት ተጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ የሁቲ ንቅናቄ እስራኤል ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ሆነ።

ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የሁቲ መሪ አብዱል-ማሊክ አል-ሀውቲ፣ የእስራኤል ድርጅቶች ንብረት የሆኑ መርከቦች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር አስታወቀ።

ከዚያም በተለይም በባብ ኤል-ማንደብ አቅጣጫ በቀይ ባሕር በኩል ወደ እስራኤል የሚጓዙ መርከቦች ዒላማ ሆኑ።

እነዚህ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል። መርከቦች በሺዎች የሚቆጠር ኪሎ ሜትር በደቡብ አፍሪካ በኩል ዞረው እንዲሄዱ አድርገዋል።

በታኅሣሥ ወር ሁለት የእስራኤል መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ሁቲዎች አስታወቁ። ከዚህ በፊት የእስራኤላዊ ነጋዴ መርከብን ይዘዋል።

ሁቲዎች በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የነዳጅ መኪና የሚሳዔል ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ጥር ላይ የመን ውስጥ አሜሪካ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።

በየመን ምዕራባዊ አካባቢ አል ሁዴይዳህ የሚገኘውን ራስ ኢሳ የነዳጅ ቀጠና የአሜሪካ እና ዩኬ የአየር ጥቃት ዒላማ ማድረጉን ሁቲዎች ገልጸዋል።

ቀጠናውን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ኃይሎች ተባብረው ነበር ሁቲዎች ላይ ጥቃት የከፈቱት።

እስራኤል በሊባኖስ የፈጸመችው ግድያ

እስራኤል በሊባኖስ የአየር ጥቃት ስትፈጽም ነገሮች የበለጠ ተካረዋል።

በየካቲት ወር መጨረሳ ላይ እስራኤል በቤይሩት የሺዓዎች መኖሪያ በሆነው ዳህያህ አካባቢ በፈጸመችው ጥቃት የሐማስ ምክትል ኃላፊ እና የዌስት ባንክ ተጠሪ የነበረው አል-አሩሪ ተገደለ።

አል-አሩሪ በሐማስ እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ቁልፍ አገናኝ ነበር ስትል እስራኤል ገልጻለች።

ከቀናት በኋላ ሄዝቦላህ ወደ 40 የሚደርሱ ሮኬቶች ወደ እስራኤል ሜሮን አየር ኃይል ተኩሷል።

ይህንንም በእስራኤል ለተፈጸመው ግድያ “የመጀመሪያ አፀፋዊ ምላሽ ነው” ሲል ነበር ሄዝቦላህ ጥቃቱን የገለጸው።

በጥር መጀመሪያ ላይ ደግሞ በሌላ የእስራኤል የአየር ጥቃት የሄዝቦላህ ራድዋን ኃይል ምክትል ኮማንደር ዊሳም አል-ታዊል ተገለደ።

የቀብር ሥነ ሥርዓት

የኢራቅ ሺዓ በግጭቱ ውስጥ

በጥር ወር መጨረሻ ላይ በሰሜን-ምሥራቅ ዮርዳኖስ በሚገኘው ‘ታወር 22’ በተባለው የአሜሪካ ወታደሮች ሰፈር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ተገደሉ።

በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው አካባቢ በደረሰው ጥቃት 34 ሰዎች ተጎድተዋል።

ጥቃቱ የደረሰው በሶሪያ ግዛት እንጂ በዮርዳኖስ አይደለም ስትል ዮርዳኖስ አቋሟን አስታውቃለች።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጥቃቱን አውግዘዋል። በሶሪያ እና ኢራቅ የሚንቀሳቀሰው አክራሪው ታጣቂ ቡድን የሚደገፈው በኢራን ነው ብለዋል።

አሜሪካ እጃቸው ያለበትን አካላት ተጠያቂ እንደምታደርግም ተናግረዋል።

የኢራቅ ታጣቂ ቡድን ካታይብ ሄዝቦላህ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።

ይህ ቡድን የሚመራው በኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንደሆነ አሜሪካ አስታወቃለች። ነገር ግን ቡድኑ ከኤራን ጋር ምን ያህል ትስስር እንዳለው በግልጽ አይታወቅም።

ኢራን ይህንን ጥቃት የፈጸመውን ቡድን አልደገፍኩም ብላለች።

በእርሻ ቦታ የደረሰው ጥቃት

የኢራን ቀጥተኛ ተሳትፎ

ኢራን ከእስራኤል ጋር ከዚህ ቀደም ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ አልገባችም።

ያለፈው ሚያዝያ ላይ በደማስቆ የሚገኝ የኢራን ቆንጽላ ላይ እስራኤል ጥቃት አድርሳለች። ከተገደሉት መካከል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አባላት ይገኙበታል።

ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መሐመድ ራዛ ዛህዲም በዚህ ጥቃት ተገድለዋል።

በወሩ መጨረሻ ላይ ኢራን በሰው አልባ አውሮፕላን እና በሚሳዔል የመጀመሪያውን ቀጥተኛ ጥቃት እስራኤል ላይ ሰነዘረች።

በበዚህም በኔጌቭ ያለ የእስራኤል አየር ኃይልን ዒላማ ማድረጓን ኢራን አስታውቃለች።

የእስራል ጦር እንዳለው፣ አብዛኞቹ ሚሳዓሎች እስራኤል ከመድረሳቸው በፊት እንዲከሽፉ ተደርጓል።

በኢራን መከላከያ ሥርዓት ላይ የተወሰነ የአየር ጥቃት በመፈጸም አፀፋዊ ምላሽ ቢሰጥም፣ እስራኤል በይፋ ጥቃቱን መፈጸሟን አላመነችም።

ቀጠናዊ ስጋት

ከሰኔ እስከ ሐምሌ ድረስ ባለው ጊዜ በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል ያለው ውጥረት እጅጉን ተባብሷል።

ሄዝቦላህ ጥቃቱን ሲያጠናክር እስራኤል ከፍተኛ አመራሮቹን እየገደለች ነው።

ቡድኑ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ በእስራኤል ደቡባዊ ክፍል እንዲሁም በሜሮን አየር ኃይል ሮኬቶች ተኩሷል።

በጥቃቱ ሳቢያ በእስራኤል ይዞታ ሥር ባለው ጎላን ኮረብታ አካባቢ እግር ኳስ እየተጫወቱ የነበሩ 12 ታዳጊዎች እና ወጣቶች ተገድለዋል።

ሄዝቦላህ ጥቃቱን እንዳልፈጸመ ቢያስታውቅም፣ እስራኤል በምላሹ በሊባኖስ ሰባት የሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

ሐምሌ ላይ በኢራን የሚደገፈው የየመኑ ሁቲ ቡድን በሚቆጣጠረው የቀይ ባሕር አካባቢ የሆነው ሆዴይዳህ ላይ እስራኤል ጥቃት ፈጽማለች።

በጥቃቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ ከ80 በላይ ተጎድተዋል።

ሁቲዎች ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን በፊት በቴል አቪቭ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት አድርሰው አንድ ሰው ሲሞት ስምንት ተጎድተዋል።

የሄዝቦላህ ከፍተኛ ኮማንደር ፉአድ ሹክር በቤይሩት በተፈጸመ የአየር ጥቃት በተገደለ በሰዓታት ውስጥ የሐማስ መሪ ኢስማዔል ሃኒያ በቴህራን አዲሱን የኢራን ፕሬዝዳንት በዓል ሲመት ለመታደም በሄዱበት ተገድለዋል።

ኢራን ለሐማስ መሪ ግድያ እስራኤልን ተጠያቂ ብታደርግም እስራኤል ግን እስካሁን ኃላፊነት አልወሰደችም።

እነዚህ ክስተቶች ተደማምረው በኢራን እና እስራኤል መካከል ቀጥተኛ እና መጠነ ሰፊ ግጭት ይነሳል፣ ቀጠናውንም ያዳርሳል የሚለውን ስጋት አባብሶታል።