
ተሟገት ማንነታዊ የመወራረስ ባህሪን ያልተረዳ ችግር ፈጣሪነት
ቀን: August 18, 2024
በገነት ዓለሙ
ለሕዝብ መረጃ ወይም ዕውቀት ሊሰጡ በመገናኛ ብዙኃንም በኩል ሆነ በአዳራሽ ውስጥ ቀርበው የእንግሊዝኛ ቃላት መደንጎር የሚወዱ ሰዎች ዕውን የሚሠሩትን የሚያውቁ ናቸው? ከውጭ የሚገቡ እንግዳ ዕሳቤዎችንና ነገሮችን (በቀላሉ በሚያዙና በሚለመዱ) አገርኛ መጠሪያዎች ሕዝብ እንዲያውቃቸው አንዳችም ጥረት ሳያደርጉ ከእነ ባዕድ አጠራራቸው ማግበስበስም ደንታ ማጣት ነው፡፡ ሰዎች እየተደናገሩም ባዕድ ቃላትን ከለመዷቸው ወዲያ ‹‹ቋንቋችን በውጭ ቃላት ተወረረ›› ብሎ ለማፅዳት መነሳት ደግሞ የባሰበት የቋንቋዎችን የመወራራስ ባህርይ ያልተረዳ ችግር ፈጣሪነት ነው፡፡ የመጨረሻው ነጥብ ላይ ትንሽ እንቆይ፡፡
ከእነዚህ ‹‹ተቆርቋሪዎች›› ጋር አንድላይ ገጥመን ለማፅዳት ስንነሳ (ለምሳሌ አማርኛን)፣ ‹‹ባዕድ›› ብለን ልናንጓልላቸው የምንችላቸው የቃላት ብዛት በቅርብ ከገቡ የእንግሊዝኛ ቃላት ላያልፉ ይችላሉ፡፡ ስለቋንቋ ተወራራሽነት ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያለው ሰው መጥቶ ቄስ፣ ጳጳስ፣ ባልዲ፣ ጠረጴዛ፣ ቤት፣ ስኳር፣ ከረሜላ፣ እግዚአብሔር፣ ወዘተ የተሰኙትንስ ከምን ትመድቧቸዋላችሁ ቢለን፣ እነሱማ ንፁህ የአማርኛ ቃላት ናቸው ልንል እንችላለን፡፡ ንፁህ አማርኛ መሆናቸውን በምን አወቃችሁ ብንባል የምንሰጠው መልስ ‹‹ናቸዋ!›› ከማለት ያለፈ ላይሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከውጭ መምጣታቸው ላይጎረብጠን ከመልመድ ብዛት የእኛ አድርገናቸዋልና፡፡
በዚሁ መንገድ ከጣሊያንኛ፣ ከፖርቹጋል፣ ከዓረብኛ፣ ከዕብራይስጥ፣ ከግሪክ፣ ከግዕዝ፣ ወዘተ ወደ አማርኛ የገቡ ቃላትን እንለይ ብንል በጣም ‹‹ንፁህ›› ብለን የምናስባቸው እጅግ ብዙ ቃላት የባዕድ ሊሆኑና የአማርኛ የቃላት ጎተራን በእጅጉ ልናራግፈው ነው፡፡ አገር ምድር ሊቃውንት ሰብስበን ከሌላ ቋንቋ ወደ አማርኛ የገቡትን በሙሉ እንለይ ብንል የሚሳካልን ከውጭ መምጣታቸውን ያወቅናቸውን ያህል ብቻ ነው፡፡ ማለትም የፈለገንን ባዕድ ቃላትን ለመለየት ብንሞክር አለማወቅ ገድቦን ከሌላ ቋንቋ መወረሳቸውን ባለማወቃችን የእኛ ናቸው የምንላቸው መኖራቸው አይቀርም፡፡ ከሌላ ቋንቋ መምጣታቸውን ስናውቅ ስናውቅ የእኛ አይደሉም ማለት ሳናውቅ፣ ሳናውቅ የእኛ ናቸው ማለት ደግሞ ትክክለኛ መመዘኛ አይሆንም፡፡ እንዲያውም ከሥረ መሠረት አማርኛ የሆኑትን የመለየት ጉዞችን ቋንቋ ከቋንቋ የሚወላለድበት እውነት ላይ ነው የሚያደርሰን፡፡ እናም ብቻውን የተፈጠረ ቋንቋ ከሌለ፣ የትኛውም ቋንቋ የትውልድ ዘመዶች ካሉት፣ ንፁህና ከሌላ ጋር ያልተነካካ መርጦ ለመያዝ መሞከር በመሠረቱ የተሳሳተና የቋንቋ ባህርይን ያለማወቅ ድርጊት ነው ማለት ነው፡፡
ሰዎች ብሔረሰቦችን ‹‹ዘር›› አድርገው ሲመለከቱም የዚህ ዓይነት ስህተት ነው የሚፈጽሙት፡፡ የወሎ ወይም የጎጃም አካባቢያዊ አማርኛን ሲናገር ያዩትን ሰው ከአነጋገሩ ተነስተው ‹‹ጥሬ አማራ››፣ ‹‹ንክር ወሎዬ››… ሊሉ ይችላሉ፡፡ ስለዚያ ሰው ቅርብ ዕውቀት ኖሯቸው ምናልባት ሰውየው በአባቱ አማራ፣ በእናቱ ትግሬ ወይም ኦሮሞ ነው ቢባሉ አማራነቱን ግማሽ ያደርጉታል፡፡ ግማሽ ያደረጉትን አማራነት ገባ ብለው አያት ላይ የወሎ ቦረና ኦሮሞ ሆኖ ቢያገኙት በአማርኛ አፉን ስለፈታ እንጂ ከሚል ማብራሪያ ጋር በእናቱም በአባቱም አማራ አይደለም ወደ ማለት ይሄዳሉ፡፡ በዚሁ ዓይነት ጆሮውን ቢቆርጡት ካለ ኦሮሚኛ የማይሰማ ሰው በወላጆቹ/በአያቶቹ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ውጪ መምጣት ምክንያት ኦሮሞነቱ ይቀንስበታል/ይሰረዝበታል፡፡ የኦሮሞነት፣ የአማራነት ወይም የትግሬነት መለያ የምናደርጋቸው ነገሮች ደግሞ እንደ አካል ገጽታችን ከመወለድ የሚገኙ አይደሉም፡፡ ከተወለድን በኋላ ከየባህልና ከየቋንቋ የምናገኛቸው ናቸው፡፡ ባህልንና ቋንቋን ከተወለድን በኋላ የምናገኘው ቢሆንም፣ በየብሔረሰቡ ባህልና ቋንቋ ውስጥ የሚያድገው ሰው ብዙ ጊዜ ከዚያው የበቀለ ነው (ከሌላ አካባቢ መጥቶ የመደባለቅ ነገር አልፎ አልፎ የሚከሰት ነው) ብለን እናስብ ይሆን ይሆናል፡፡
አንዳርጋቸው ጽጌ ‹‹ነፃነት የማያውቅ ነፃ አውጪ›› በተሰኘ መጽሐፉ ውስጥ (ገጽ 146-7) የእኛን አገር ማኅበረሰቦች በጎሳና በብሔረሰብ የዕድገት ደረጃ መሀል ያሉ የዘር (የደም) ትስስሮች አድርጎ በማየት ‹‹ዘውግ›› ይላቸዋል፡፡ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ወዘተ በምንላቸው ውስጥ ያለውን የጎጥ ክፍፍልም ‹‹በደም ለሚዛመዷቸው የቅርብና የሩቅ ወገኖቻቸው… ከሚሰጡት ቅድሚያ የሚመነጭ ነው›› ይለዋል፡፡ የዚህ ዓይነት አመለካከት በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ተወልዶ በኦሮሚኛ አፉን የፈታንና በኦሮሞ ባህል ውስጥ ያደገን ሰው ተወላጅነቱ ከኦሮሞዎች እስካልሆነ ድረስ ኦሮሞ ነኝ እንዳይል የሚከለከል ነው፡፡ ኦሮሞነት፣ ትግሬነት፣ ጉራጌነት፣ ጎንደሬነት፣ ጎጃሜነት፣ ወለጌነት፣ ወዘተ. ሁሉ የዝርያ ቤቶች ተደርገው እንዲታዩ የሚጋብዝ ብቻ ሳይሆን የወላጆችን/የአያት ቅድመ አያት አመጣጥን ተንተርሶ የኦሮሞነትን፣ የአማራነትን፣ የጎጃሜነትን፣ ወዘተ ‹‹የንፅህና ጥራት›› ሙሉ፣ ግማሽና ሩብ እያሉ መለካትን የሚያግዝ ነው፡፡
በሌላ አነጋገር ከአንዱ ማኅበረሰብ ወደ ሌላው በማደጎም ሆነ በጋብቻ መቀላቀልን ‹‹የንፅህና መጉድፍ›› አድርጎ ማንጓለልን የሚያፀድቅ አደገኛ አመለካከት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ማኅበረስብ ውስጥ ‹‹የእርስ በርስ›› (ኦሮሞ ለኦሮሞ፣ ጉራጌ ለጉራጌ፣ ወዘተ) ጋብቻ እንዳለ ሁሉ፣ ትናንትናም ዛሬም ማኅበረሰብ ዘለል ጋብቻዎችም ይፈጸማሉ፣ ይህ ተራ ልብታ ነው፡፡ ዛሬ እንደ ዘር የታዩት ማኅበረሰቦች ዛሬ ያላቸውን ወለላዊ ገጽታዎች አለፍ ብለን የየብሔረሰቦችን አዘማመድ ጀርባ ብንመረምር የምናገኘው ከደም ዝምድና በላይ ማኅበረሰባዊ መዘናነቅና መወራረስን ነው፡፡ ከ76 እስከ 80 ብለን ከምንላቸው የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች ውስጥ በሩቅም ሆነ በቅርብ የታሪክ አዘማማጅነት ከኦሮሞነት ጋር ያልተዛነቀ አንድም ብሔረሰብ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በኦሮሞነትም ሆነ በአማራነት ውስጥ በታሪክ ብሌን ብናጮልቅም የምናየው መላ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችን ተለዋውሶ ኦሮሞ ወይም አማራ በመሆን ገጽታ መከሰትን ነው፡፡ የኦሮሞ እየተባዛ በኢትዮጵያ መሠረጫጨት እንደምን ከሞጋሳ ተነጥሎ ሊታይ ይቻላል!?
የዛሬ ‹‹ንፁህ›› መንዜነትን፣ ‹‹ንፁህ›› ጎጃሜነትንና ‹‹ንፁህ›› ጎንደሬነትን፣ ወዘተ በረዥም ታሪክ ውስጥ ዘልቀን ብናስተውልም የምናገኘው የልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች ቡጭቅጫቂዎች ተዛንቀው አማርኛ ተናገሪ ሆነው መውጣታቸውን ነው፡፡ ዛሬ ባሉን ማኅበረሰቦች የላይ ገጽታ ላይ የምናገኘው ቋንቋ ነክ፣ ዘልማድ ነክ፣ ሙዚቃና ውዝዋዜ ነክ ተዛማጅነትም መወራረሳችንን የሚናገሩ የታሪክ መስታወቶች ናቸው፡፡ ሩቅ ሳንሄድ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ማክተሚያ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የታየውን ኅብረተሰባዊ መተረማመስ ብናስተውል እንኳ ብዙ መደበላለቅ ሁሉም ዘንድ እንደደረሰ መረዳት እንችላለን፡፡
በትውልድ ሐረግ ከተራ ሰው የሚለየው መሣፍንትንና ከተወሰነ የአካል ገጽታ ጋር ተዛምዶ የቆየው ‹‹የባርያ ዘርነት›› ሰው ሠራሽ እንጂ ‹‹የመስፍን›› እና ‹‹የባርያ›› የተባለ አጥንትና ደም የለም፡፡ በጦርነት መሸነፍ ደርሶ የመሣፍንት ተወላጅ እንደ ተራው ሰው በባርነት የተናደበት ታሪክ በኢትዮጵያ ደርሷል፡፡ ከባርነትም ተመዝዞና የባለሟልነትን መሰላሎች ሽቅብ ወጥቶ መኳንንት መሆንና ከንጉሥ ዘር ጋር መጋባትም ተችሏል፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ የዳር ሕዝቦች ላይ የተካሄደው የባርያ ፍንገላ ታሪክ ብርቱ ይሁን እንጂ በባርነት መነዳት፣ መሸጥና ሎሌነት ያልደረሰው አንድም ብሔረሰብ በኢትዮጵያ የለም፡፡
ተራ ገባር ገበሬ እንኳ ባለባሪያ የመሆን ወግ እስካየበት የ20ኛው ክፍለ ዘመን ዋዜማ ድረስ የትውልድ ሐረግን መቁጠር ቢቻል የሆነ ደረጃ ላይ የቤት ውልድነት ያልነካካው (‹‹ያልቆሸሸ››) ንፁህ ዘር ይገኝ ይሆን!? ቀደም ባሉ ጊዜያት ጋብቻን ከመፍቀድ በፊት የቅርብ ዝምድና እንዳይኖር ከመጠንቀቅ ባሻገር የባሪያ፣ የቀጥቃጭ፣ የሸክላ ሠሪ፣ የፋቂና የቁጢት በጣሽ ዘር በስህተት ዘር እንዳያጎድፍ (እነዚህ ነገሮች ደም ውስጥ ይገቡ ይመስል) የትውልድ ጀርባ ይመረመር ነበር (አሁንም ገጠር አካባቢ ይህ ገና አልተራገፈም)፡፡ የዚህ ዓይነት የዘር ንፅህና ፍለጋና የጠራሁ ነኝ ባይነት ከቅዠትና ከድንቁር ቁጥር ውስጥ ነው፡፡
ከኢትዮጵያውያን ውስጥ በግል ትውልድ ሐረግም ሆነ በማኅበረሰባዊ ጥንቅር ያልተወራረሱ ማግኘት ይቅርና ሰሜን አፍሪካና ዓረቢያ በረሃ ውስጥ ገብተን ንፁህ ዓረብን ለማግኘት ብንሞክር ልፋታችን ከንቱ ነው የሚሆነው፣ የአፍሪካና የኢትዮጵያ ዘርን እየተመገበ ያልተባዛ ዓረብ የለምና፡፡ ዛሬ ከጥቁርና ከነጭ የተከለሰ ሰውን ከነጭነት የሚለይ አንድም ገጽታ ባይታይበትም፣ ከጥቁር ዘር ጋር በመካለሱ ብቻ ከጥቁር እየመደበ የነጭነትን ‹‹ንፅህና›› ለመጠበቅ የሚሞክረው የነጭ ዘረኝነት እንኳ ማድረግ የማይቻለውን አደረግሁ እያለ ራሱን የሚያሞኝ ድንቁርና ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የሰው ልጅ ሁሉ ከአንድ ዘር የተቀዳ››፣ ‹‹የሰው ልጅ መነሻ ምሥራቅ አፍሪካ›› የሚባለውን ትተን፣ የአፍሪካ ዘር ወደ አሜሪካ እየተጋዘ የእርሻ ሠራተኛ ከሆነበት ታሪክ ብንነሳ እንኳ የነጭ ዘር በድብቅና በግልጽ የቤት ውልድነት ሲቆሽሽ የኖረበት እውነት ላይ እንደርሳለን፡፡
በግለሰብ ደረጃ የዝርያ ሐረግን እከሌ እከሌን ወለደ እያልን ቤተ ዘሩን በየጋብቻው ሁሉ ተከትለን ብንደረድር ዘሩ በየጋብቻው እየሳሳ ከመሄዱ ሌላ፣ የዝርያ ትውልድን በወንድ በኩል እንደ መቁጠራችን የወንድየው ተወላጆች ሁሌም ከእሱ የተገኙ ስለመሆናቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ የአባትና የእናት መልክ ቁመና ሁሌም በልጅ ላይ መሳ ለመሳ ላይገለጽ ይችላል፡፡ የአባት ባህርይ አይሎ ልጅ ከሞላ ጎደል አባቱን የሚመስልበት ቀዳዳ እንዳለ ሁሉ የእናትም ባህርይ የሚያይልበት ቀዳዳ አለ፡፡ እነዚህ ቀዳዳዎች ከሌላ የተረገዘ ተወላጅን ሳያውቁ የእኔ/የእከሌ ዘር እያሉ ለመቁጠር ያስችላሉ፡፡ በአንድ ሰው የመወላለድ ረዥም ፈለግ ውስጥ ስንት ጊዜ ቆጠራው ሊስት እንደሚችል ግምት ይዛችሁ የቀዳማዊ ምኒልክን ከንጉሥ ሰለሞን የመወለድ አፈ ታሪክን እውነት ብላችሁ ብትቀበሉ እንኳ፣ እነ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዝርያቸውን ከቀዳማዊ ምኒልክ ጋር ማገናኘታቸው ለገዥነት ከመጥቀሙ በቀር፣ እውነተኛ የዝርያ ፈለግን በማሳየት ረገድ ከንቱ ተረት እንደሆነ መገንዘብ ትችላላችሁ፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ አባትም በኩል ሆነ በእናት በኩል ኦሮሟዊ ምንጭ ጋ እንደርሳለን፡፡ አሮሟዊ ሥነ ልቡና፣ ባህልና ቋንቋ ውስጥ የመኖር ፍላጎት ግን የደም ነገር ሆኖ ተፈሪን አላንዘረዘረም፡፡ ጥቁር አሜሪካውያን በዘር አመጣጣቸው አፍሪካዊ ናቸው፡፡ ይህ ዝርያቸው ግን በባህልም በቋንቋም ሳፊ አሜሪካዊ መሆናቸውን አይቀንስም፡፡ አሁን አሁን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ዕርቅ ወዲህ ከሕፃንነት አንስቶ በኤርትራ ትግሬነት ውስጥ ያደጉና ከዕርቁ በኋላ የማያውቋቸውን አማራም ሆነ ኦሮሞ ወላጅ ለማግኘት የሚያፈላልጉ ወጣቶችን ዓይተናል፡፡ በእነዚህ ወጣቶች አስተናነፅ ውስጥ ግማሽ ኦሮሞነትን ወይም አማራነትን እናገኛለን? ጥያቄውን ቀየር ላድርገው፡፡ የዜግነትን ጉዳይ እንተወውና ከእነዚህ ልጆች ከ20 ምናምን ዓመት በፊት የተነጠሉ ወላጆቻቸው ከሌላ ብሔረሰብ በመሆናቸው ምክንያት የልጆቹ ትግሬነት ከኤርትራ ትግሬዎች ከተወለዱ አብሮ አደጎቻቸው በግማሽ ያንሳል?
እስካኑን የተነጋገርንበትን እንሰብስብ፡፡ ጥቁር፣ ቢጫ፣ ነጭ የምንላቸውንና ዓይነተኛ የገጽታ ልዩነቶች ያሏቸውን ዘሮች ብንወስድ እንኳ ከጥንት ዘመን እስከ ዛሬ ድረስ በነበረና ባለ እንቅስቃሴ ምክንያት አንዳቸውም ከመወራረስ ውጪ አይደሉም፡፡ አንዳቸውም ያልተነካካን ነን ማለት አይችሉም፡፡ መወራረሱ በማንም ሊታገድ የማይችል ሆኖ ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለን ሰዎች በሙሉ በዘር (ሬስ) አንድ ነን — ጥቁር፡፡ በጥቁርነት ውስጥ ደግሞ የአፍሪካና የእስያ መቀያየጥ የበረታብን ነንና ቅይጥ ጥቁር ነን ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ቅይጥነት ከኢትዮጵያ ድንበር ውጭ በአራቱም ማዕዘናት የሚጓዝ ነው፡፡
የዘሮች መቀላቀል በተለያየ ምክንያት በሚካሄድ የሰዎች መጎራበትም ሆነ እንቅስቃሴ፣ ፍልሰትና መዛነቅ የሚመጣ የረዥም ዘመን ሒደት ነው፡፡ ይህ የረዥም ዘመን ሒደት ደግሞ ከተፈጥሯዊ አካባቢ ለውጥ፣ ከሰው ልጅ የሥልጣኔና የመንግሥት ታሪክ ዕድገት ደረጃ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የተፈጥሯዊ አካባቢ ለኑሮ መመቸት ሰውን አንድ አካባቢ እንዲረጋ እንዳገዘ ሁሉ ለመኖር የማያስችል ሥነ ምድራዊ ለውጥም ሰውን አሰድዷል፡፡ ከተፈጥሯዊ ግፊት ሌላ ማኅበራዊ ምክንያቶችም አገፋፍተዋል፣ አጋጭተዋል፡፡ ፍትጊያው ከቀላል ሰፊ ቤተሰቦች ተነስቶ እስከ ግዙፍ ኢምፓየራዊ ጦርነቶችና አስገባሪነት ድረስ ያደገ ባለብዙ መልክና ውስብስብ ጉዞ ነው፡፡
እንደዚያም ሆኖ የፈለገውን ያህል በአየር ፀባይ መቀየርና በጦርነቶች ግፊት የሰው ልጆች ቢፈልሱም አኗኗራቸው በየዕድገት ደረጃው ማኅበራዊ ቅርፅ ነበረው፣ የኑሮ እሽክርክሪቱም በዘላን ኑሮ እንኳ በተወሰነ ሥፍራ የመመላለስ ሁኔታ ነበረው፡፡ ከዛሬ ላይ ተነስተን እጅግ ጥንታዊ ወደ ነበረው የሰው ልጅ ማኅበራዊ የኑሮ ደረጃ በዓይነ ህሊና ብንጓዝ የሰው ልጅ ማኅበረሰቦች ይበልጥ ትንንሽና ንጥልጥል ወደ ነበሩበት፣ ቋንቋዎችም በጣም ብዙ ወደ ነበሩበት ዘመን ነው የምናመራው፡፡ ከጥንቱ ጊዜ ተነስተን ወደ ዛሬው ጊዜ ብንጓዝ ደግሞ የምናገኘው ተቃራኒውን ነው፡፡ የሰዎች ቁጥር እየተባዛ፣ የአካባቢ ይዞታ ሽሚያና መገፋፋት እየጨመረ በመናጠቅ፣ በማብረር፣ በማስገበርና በመዋዋጥ ሒደቶች ውስጥ ማኅበረሰቦችና ቋንቋዎች ቁጥራቸው እያነሰ የሰው ክምችታቸው ግን እየበረከተ ነው የመጣው፡፡ በመወራረስ ምክንያት የማኅበረሰቦችና የቋንቋዎች ቁጥር እያነሰ የመሄድ ዝንባሌ ወደፊትም የሚቀጥል ነው፡፡
ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦችን ‹‹ዘውግ›› አልናቸው ‹‹ብሔር/ ብሔረሰብ›› ሁሉም የአፍሮ-እስያ ቅልቅልነት መገለጫዎች በመሆን አጠቃላይ የዘር ማንነት ውስጥ ያሉ ማኅበረሰባዊ ‹‹ዕድሮች›› ናቸው፡፡ እነዚህ ‹‹ዕድሮች›› ከ70 በላይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከመሆናቸው ባሻገር፣ ከተናጠል ቋንቋ ተናጋሪነት እስከ ደባል ቋንቋዎች ተናጋሪነት በሰፋ መልክ በብዙ ጎጦች የተከታተሩ ናቸው፡፡
ከሰሜን ወደ ደቡብ እየተስፋፋ የመጣው አስገባሪነት የእንዘጭ እንቦጭ ጉዞ ባያጠቃው ኖሮና የሚያዳርሳቸውን አካባቢያዊ ገዥዎች ገብሩልኝ ከማለት አልፎ በቀጥታ መዳፉ ውስጥ አስገብቶ የሚሰለቃቅጥ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ወይም ታላቁ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ እንቅስቃሴ ከማኅበራዊ ጎርፍነት የዘለለ ገዥነትን የማስፈን ፈርጅ ኖሮት ቢሆን ኖሮ ብዙ ቋንቋዎችና ባህሎች ለውህድ ገጽታ የሚሰጡትን ሰጥተው ድምጥማጣቸው በጠፋና የዛሬዋ ኢትዮጵያ ከጥቂት ርዝራዦች በተቀረ አንድ ባህልና ቋንቋ የጎለበተባት አገር በሆነች ነበር፡፡ ይህንን የምለው በቢሆን ኖሮ ለመቆጨት ወይም ተርፈናል የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ሳይሆን፣ ባለብዙ ባህል፣ ባለብዙ ቋንቋና ባለ ብዙ ጎጠኝነት የመሆናችን ሚስጥር ሁሉንም የለዋወሰ የአገዛዝ ታሪክ አለመኖሩና የዘመናዊ ኢኮኖሚ አዘማማጅነት መጓደል መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡
ኋላቀርነት ስለከታተራቸው ማኅበረሰቦችና ጎጦች ስናወራ በአብዛኛው እዚያው በዚያው ውስጥ ስለሚሽከረከር ጋብቻና መወላለድ ማውራታችንም ነው፡፡ ይህ መወላለድ ግን በረዥም ዘመን የመቀያየጥ ዓውድ ውስጥ መሆኑና የመደብለቅ ሒደት ሁሌም መኖሩ ሳይዘነጋ ነው፡፡ በአጭሩ በማኅበረሰባዊ ጥንቅሩ ንፁህ ዘውግ/ብሔረሰብ፣ ንፁህ ኦሮሞ፣ ንፁህ ትግሬ፣ ንፁህ ጎጃሜ፣ ወይም ንፁህ ወለጌ፣ ወዘተ ኖሮ አያውቅም፣ አሁንም የለም፡፡ ከተማዊ-ኢንዱስትሪያዊ ሕይወት ብሔረሰባዊና ጎጣዊ ክትርትሮሾችን ሲቀረዳድድ በየኩሬ ውስጥ ሲሽከረከሩ የነበሩ ‹‹የወንዜ ልጅ…፣ የፋሲል ዘር…፣ የበላይ ነኝ…፣ ወዘተ›› ባይነት ሁሉ ብትክትካቸው እየወጣ ኅብር (ኮስሞፖሊታን) ሰብዕናና እኛነት እየደረጀ መሄዱ አይቀርም፡፡ ከከተማ ዕድገት ጋር ብሔረሰባዊ ቅልቅልንና ቅይጥነትን ያሸራረቡት የሐረር-የድሬዳዋ ልጅነት፣ የጅማ ልጅነት፣ የሐዋሳ ልጅነት፣ የአዲስ አበባ ልጅነት፣ ወዘተ የዚሁ የኅብር ሰብዕና ጅምርማሪዎች ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪያዊ ሥልጣኔ ብሔረሰቦችንና ጎጦችን ብቻ አይደለም የሚበረጋግደው፡፡ የአገሮችንም ድንበር እየጣሰ ሰዎችን ይስባል፣ ሕዝብን ከሕዝብ ይበውዛል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱም ማዕዘን የሚደራ የኢኮኖሚ ግስጋሴ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የሶማሊያና የጂቡቲ ሰዎችን ማላላሱና ማገማሸሩ የማይቀር ነው፡፡
ኢንዱስትሪያዊ ሕይወት የኢትዮጵያ ሰዎችን እየበወዘ ኅብር ሰብዕና ሲያንፅ (ኦሮሚኛም የፌዴራል መግባቢያ ሆኖ እንደ አማርኛ ብሔረ ብዙ ተነጋሪነቱ እንደሚሰፋ ከወዲሁ ብናስብ)፣ አማርኛና ኦሮሚኛ ብቻም ሆነ ሌላ ተጨማሪ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ግን አማራነትም ሆነ ኦሮሞነት ወይም ሌላ ብሔረሰብነት ውስጥ ራሳቸውን የማይመድቡ ወይም እንዲያ ያለ ምደባ እጅግም ትርጉም የማይሰጣቸው ሰዎች ይበረክታሉ፡፡ በዚያ ዓይነት ደረጃ ላይ የበለጠ ትኩረት የሚያገኙት ሰውነትና ዜግነት ናቸው፡፡ ዜግነትም ቢሆን ዛሬ ከምናውቀው ኢትዮጵያዊነት አልፎ ሊሄድ ይችል ይሆናል፡፡
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ወጣቶችም አዲስ ኃይል እንደ መሆናቸው ራሳቸውን ማስቀመጥ ያለባቸው ዛሬ በሚገኙባቸው የጎጥና የብሔረሰብ ክፍልፋይነት (ፍራክሽናሊዝም) ውስጥ ሳይሆን፣ መጪው ኢንዱስትሪያዊ ኅብረተሰብ በሚፈጥረው ስብጥርና ኅብራዊነት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ማለት የዛሬ ክፍልፋይነት አላፊ መሆናቸውን በማስተዋል ወደ ነገው ኅብራዊነት ማምራት ማለት ነው፡፡ ቀላል ግን ያልተጠበቀ አንድ ምሳሌ ላስታውስ፡፡ በ2010 ዓ.ም. ሐምሌ 20ዎች ውስጥ ሚኖሶታ ውስጥ ተካሂዶ በነበረ ኦሮሞዎችንና የሌላ ሌላ ብሔረሰብ ሰዎችን ባገናኘው ‹‹የዕርቅና የመደመር›› ስብሰባ ውስጥ፣ ከእነ ዓብይ አህመድ መድረስ በፊት በነበረው የዝግጅቱ ክፍለ ጊዜ በአዳራሽ ውስጥ የኢትዮጵያ ልሙጡ ባንዲራና የኦነግ ዓርማ አንድ ላይ ተገጣጥመው ሲያሽቃብጡ ዓይተናል፡፡ መድረኩ የእኛ የሚል መሰሰት ሳይኖር ልዩ ልዩ ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ዘፈኖች ሲስተናገዱ (ምኒልክን ያነሳሳ ዘፈን ጭምር) ሰምተናል፡፡ ሁሉም በሁሉም ዘፈን ከመወዝወዝ በቀር ጉዳይ ያለ አልነበረም፡፡ በአገር ውስጥም መጎነታተልና ብሽሽቅ በተቀነሰበት ግንኙነት ውስጥ የዛሬ የየኩሬ ዓለሞችን ኮሰኮሰኝ ሳይሉ፣ ግን ኩሬዎችን እያፋሰሱ የሚቀላቅሉ ልማቶችን፣ የባህል ዕድገቶችንና የታሪክ ግንዛቤዎችን በማጎልበት ላይ ማተኮር ከቻልን ጉዞ ሰመረ ማለት ነው፡፡
ግራ የሚያጋባው ታዲያ ዛሬ 70/80 ዘሮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉ አድርገው የሚያስቡ፣ ብሔረሰቦችን ‹‹ዘር›› የሚሉ፣ በብሔረሰብ መደራጀትን ‹‹በዘር›› መደራጀት የሚሉ ልሂቃንና ፖለቲከኞች ለዚህ ጉዞ ምን እንደሚጠቅሙት ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ምን ትችት ቢሰነዘርባቸው ከተሬዎች ባልተለየ ደረጃ ግንዛቤያቸውንና የቃላት አጠቃቀማቸውን ለመመርመር አለመሞከራቸው ነው፡፡ ምናልባት ብሔርተኛነትን አስጠልቶ ለማዳከም ዘዴ ብለውት ይሆን ‹‹የዘር›› ፖለቲካ የሚሉት!?
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
