
ከ 3 ሰአት በፊት
ኬንያ ውስጥ ከ40 በላይ ሴቶችን በመግደል ተጠርጥሮ ተይዞ የነበረው ግለሰብ እና 12 ኤርትራውያን ከእስር ቤት ማምለጣቸውን ተከትሎ ፖሊስ ሰፊ አደን ማካሄድ መጀመሩን አስታወቀ።
ናይሮቢ ውስጥ ከሚገኘው የፖሊስ እስር ቤት ማምለጣቸው ከተነገረው እስረኞች መካከል ሚስቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን ገድሏል ተብሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘው ኮሊንስ ጁማይሲ ኻሉሻ ይገኝበታል።
ከፖሊስ ጣቢያው ያመለጡት ሌሎቹ እስረኞች ደግሞ 12 በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብተዋል ተብለው የተያዙ ስደተኛ ኤርትራውያን መሆናቸው ተገልጿል።
ግለሰቡ በግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘው ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ በናይሮቢ አንድ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ስፍራ የተቆራረጠ የሴቶች አካል በማዳበሪያ ተጥሎ ከተገኘ በኋላ ነበር።
ፖሊስ ኮሊንስ አሰቃቂውን ግድያ መፈጸሙን ማመኑን ከገለጸ በኋላ ተጠርጣሪው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ግን ወንጀሉን አለመፈጸሙን ተናግሯል።
የሴቶቹ አስክሬን መገኝት በአገሪቱ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ባለቤቱን ጨምሮ 42 ሴቶችን መግደሉን ያመነው የ33 ዓመቱ ተጠርጣሪ የተያዘው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ቢያንስ የስምንት ሴቶች አስከሬን ከተገኘ በኋላ ነው።
- የሰባት ዓመቷን ሄቨን ደፍሮ በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ ፍርድ የፈጠረው ቁጣከ 7 ሰአት በፊት
- በታንዛንያ በደቦ የተደፈረችን ሴት ከወሲብ ንግድ ጋር ያያዙት ፖሊስ ከኃላፊነት ተነሱከ 5 ሰአት በፊት
- የሊቢያው ማዕከላዊ ባንክ ባለሥልጣን ከእገታ መለቀቃቸውን ተከትሎ ባንኩ ሥራ ጀመረከ 9 ሰአት በፊት
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ ያለው ኮሊንስ ጁማይሲ ከአውሮፓውያኑ 2022 ጀምሮ ሴቶችን ብቻ እየለየ ሲገድል እንደቆየ ቃሉን መስጠቱን ፖሊስ ቢያስታወቅም፣ ግለሰቡ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የእምነት ቃሉን የሰጠው በፖሊስ በተፈጸመበት ስቃይ ምክንያት መሆኑን ተናግሯል።
በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ከሚገኘው ጊጊሪ ፖሊስ ጣቢያ ያመለጠው ኮሊንስ ብቻ ሳይሆን 12 ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ፖሊስ ያመለጡትን ሰዎች ለመያዝ ፍለጋ ላይ መሆኑን ገልጿል።
እስረኞቹ ታስረው ከነበሩበት ፖሊስ ጣቢያ ያመለጡት ማክሰኞ ሊነጋጋ ሲል መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፣ ማለዳ ቁጥጥር በሚደረግበት ጊዜ 13ቱ ታሳሪዎች ከፖሊስ ጣቢያው እስር ቤት ሾልከው መውጣታቸው መታወቁ ፖሊስ አመልክቷል።
የአገሪቱ የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሞሐመድ አሚን እስረኞቹ ማምለጣቸውን አረጋግጠው፤ ፖሊስ ሁሉንም መልሶ ለመያዝ ፍለጋ ላይ መሠማራቱን ገልጸዋል።
ከ40 በላይ ሴቶችን በመግለደል ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር የነበረው ጁማይሲ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ባለፈው አርብ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተጨማሪ ሰባት የምርመራ ቀናት ለፖሊስ ተፈቅዶ ነበር።
በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ የገቡ ናቸው ተብለው ታስረው የነበሩት እና ማምለጣቸው የተነገረው የአስራ ሁለቱ ኤርትራውያን ስም ዝርዝር የወጣ ሲሆን፣ ሁሉም በጎልማሳ ዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙም ተገልጿል።