

ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት
ማኅበራዊ የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳቶችን በባህል ሕክምና ለማዳን መሥራት እስከሞት የሚያደርስ ችግር እንደሚያመጣ ተነገረ
ቀን: August 28, 2024
በአገር አቀፍ ደረጃ ለአጥንትና ለመገጣጠሚያ ጉዳቶች በሚሰጥ የባህል ሕክምና የሚከሰቱ ውስብስብ የጤና ችግሮች፣ ቋሚ የአካል ጉዳትና እስከ ሞት የሚያደርሱ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ የአጥንትና የአደጋ ሕክምና ስፔሻሊስቶች ብሔራዊ ማኅበር አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የአጥንትና የመገጣጠሚያ ጉዳቶች ሲከሰቱ ከሚሰጥ የባህል ሕክምና ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ውስብስብ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ አካሄድኩት ያለውን ጥናት ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት የአጥንትና የአደጋ ሕክምናዎች ስፔሻሊስቶች ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ኤፍሬም ገብረሃና (ዶ/ር) እንደተናገሩት ‹‹በአገራችን ውስጥ በትክክለኛ ሕክምና በቀላሉ መታከምና መስተካከል የሚችል ቀላል የአካል ጉዳት፣ በባህላዊ ሕክምና ምክንያት ለሞትና ለአካል መጉደል ምክንያት እየሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአጥንት ሕክምና በመስፋፋቱ፣ ከባህላዊ አጥንት ሕክምና ጋር ተያይዘው የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮች መቀነስ ሲገባቸው በተቃራኒው እየጨመሩ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በጤና ተቋማት ውስጥ በየዕለቱ በርካታ ታካሚዎች ቀላል የሚባል የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ፣ ወደ ባህላዊ የአጥንት ሕክምና በመሄድ ለተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ተጋልጠው ሲመጡ ማየት የተለመደ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ኤፍሬም (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የአጥንትና የአደጋ ሕክምናዎች ስፔሻሊስቶች ብሔራዊ ማኅበር ላለፉት ሦስት ዓመታት ቦሳድ (Bone Setting Associated Disability) የሚል አገር አቀፍ የጥናትና የምርምር ቡድን በማደራጀት፣ በወጌሻ ሕክምና የተጎዱ ታካሚዎችና የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ አገራዊ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡
ጥናቱ በዋናነት የሚያተኩረው በኢትዮጵያ ከሚከሰቱ የአጥንትና መገጣጠሚያ ጉዳቶች ጋር ተያይዞ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ቅድሚያ አማራጭ ተደርገው ከሚወሰዱት በባህል ሕክምና የሚከሰቱ ውስብስብ የጤና ችግሮችን ለማጥናት ታስቦ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም ጥናቱ ከስድስት የተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ስምንት የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎችን ያካተተና ከመቶ በላይ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት ሐኪሞችና ሬዚደንት ሐኪሞች የተሳተፉበት ነው ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሐኪም፣ እንዲሁም የጀርባ አከርካሪ ቀዶ ሕክምና ሰብ ስፔሻሊስት መንግሥቱ ገብረ ዮሐንስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ጥናቱ በኢትዮጵያ የመጀመሪያና በአገር አቀፍ ደረጃ በአሥር ከተሞች የሚገኙ ከሦስት ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች የተካተቱበትና ችግሩን በጥልቀት ለመፈተሽ የተሞከረበት ነው፡፡
በጥናት ውጤቱም መሠረት ሕፃናትን በተመለከተ ከጤና ተቋም በተሰበሰበ መረጃ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 460 ሕፃናት በጥናቱ የተካተተቱ ሲሆን፣ የጥናቱ ዋና ግኝት እንደሚያሳየው ሕፃናት ከአዋቂዎች የበለጠ ከፍተኛ ለሆኑ ውስብስብ ጉዳቶች የተጋለጡ ናቸው፡፡
ከ76 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአደጋ ዓይነት በሕፃናቶች ላይ የሚይዘው የመውደቅ አደጋ ሲሆን፣ በአንፃሩ በአዋቂዎች ላይ የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛል፡፡
በሕፃናት ላይ ለከፍተኛ ውስብስብ የጤና ችግር አጋላጭ ከሆኑ ተደጋጋሚ ምክንያቶች መካከል በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሕፃናት፣ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ማኅበረሰቦች የተወለዱ ሕፃናት፣ ክፍት የሆነ ስብራት ያላቸው ሕፃናትና ወደ ባህላዊ ሕክምና ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ወደ ጤና ተቋም ደርሰው የተመለሱ ሕፃናት የበለጠ ተጠቂዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደ መንግሥቱ (ዶ/ር)፣ አዋቂዎችን በተመለከተ ከጤና ተቋም በተሰበሰበው መረጃና 783 አዋቂ ታካሚዎችን ባካተተው ጥናት፣ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ታካሚዎች ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ፣ አብዛኞቹም እጅግ በጣም ቀላል የሚባል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ታካሚዎች ወደ ጤና ተቋም ሲመጡ የተመዘገቡ ውስብስብ የጤና ችግሮች ያሉባቸው 77 ከመቶ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 26.7 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ባህላዊ የሕክምና ቦታዎች ከመሄዳቸው በፊት የጤና ተቋማት ደርሰው የተመለሱ ናቸው ብለዋል፡፡ ለውስብስብ የጤና ችግር መከሰት ምክንያት ተብለው ከተለዩ መንስዔዎች መካከልም በገጠር አካባቢ መኖርና ከድህነት ወለል በታች መገኘት የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በሲዳማ ክልል የባህላዊ ሕክምናና ውስብስብ የጤና ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በማኅበረሰብ አቅፍ ጥናቱ ላይ የገጠርና የከተማን በማካተት ጥናት ለማካሄድ ተሞክሯል ያሉት መንግሥቱ (ዶ/ር)፣ ባለፈው አንድ ዓመት አደጋ ከደረሰባቸውና ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 860 ታካሚዎች ውስጥ 68 በመቶ በሚሆኑት ላይ ውስብስብ የጤና ችግሮች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
ውስብስብ ለሆኑ የጤና ችግሮች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከልም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ፣ መሠረታዊ ትምህርት አለመማርና ባህላዊ ሕክምና ተጠቃሽ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአጥንትና መገጣጠሚያ ሕክምና ከአሥር ዓመት በፊት የስፔሻሊስት ትምህርት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ይሰጥ እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አሥር የተለያዩ የአጥንትና መገጣጠሚያ ስፔሻሊስት ትምህርት ማስተማሪያ ተቋማት ውስጥ እየተሰጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
