

የኸርት አታክ ኢትዮጵያ ግብረ ሠናይ ድርጅት በአሜሪካ መሥራች ሐኪሞች
ማኅበራዊ የልብ ታማሚዎችን ለመታደግ እየተሰጠ ያለው ነፃ ሕክምና
ቀን: August 28, 2024
በአዲስ አበባ ከተማ በልብ ሕመም የሚሰቃዩ 100 ሕሙማንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የሕክምና አገልግሎት በሁለት ማዕከሎች እየተሰጠ ነው፡፡ 45 ታካሚዎች የአገልግሎት ቀዳሚ ተጠቃሚ ሲሆኑ የቀሩትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተመሳሳይ አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል፣ ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል በተሰጠው ሕክምና 45 ሕሙማን የታከሙ ሲሆን፣ ለ55ቱ የልብ ሕሙማን ደግሞ ተመሳሳይ አገልግሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ሪፈራል ሆስፒታል ከነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት በመከናወን ላይ ነው፡፡
በማዕከሉ ተደራሽ የሆነውንና በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለውን የሕክምና አገልግሎት በነፃ እየተሰጠ ያለው በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ሁለት የልብ ሐኪሞች ያቋቋሙት፣ ‹‹ኸርት አታክ ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ ከ17 በላይ በልብ ሕክምና ዘርፍ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎችን ያሳተፈ ነው፡፡
ድርጅቱ ለልብ ታካሚዎች ከሚሰጠው ነፃ የሕክምና አገልግሎት በተጨማሪ በጣም ውድ የሆኑ፣ ዘመኑን የዋጁና በአገር ውስጥ ገበያ የማይገኙና አራት ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸውንና ለሕክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ለሁለቱም የጤና ተቋማት በነፃ አከፋፍለዋል፡፡
ከመሥራቾቹ አንዱና የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦብስኔት መርዕድ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ኸርት አታክ ኢትዮጵያ›› ከተመሠረተ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሆነው የተቋቋመውም በአሜሪካ አትላንታ ጆርጂያ ነው፡፡
በቦርድ የሚመራው ይህ ድርጅት አሁን ካበረከተው ነፃ አገልግሎት በፊት ባለፈው የካቲት ስድስት የሕክምና ባለሙያዎችን ይዞ ለ32 የልብ ሕመምተኞች ማከሙንም አስታውሰዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጅዋ አባባል ኢትዮጵያ ውስጥ የልብ ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህ ዓይነቱን የጤና እክል በዓመት አንድ ጊዜ እየተመጣ የሚፈታ አይደለም፡፡ ይህም በመሆኑ የአገር ውስጥ ሐኪሞችን ለማጠናከር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለማከናወን ድርጅቱ እየሠራ ነው፡፡
የቡድኑ መሪና የልብ ሐኪም ተስፋዬ ተሊላ (ዶ/ር) የሕክምና ግብዓቶችን አስመልክተው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለተቋማት ከተበረከቱት ግብዓቶች መካከል የደም ቧንቧ፣ ፔስ ሜከር፣ እንዲሁም ለሕይወት አስጊ ለሆነው ሩማቲክ የልብ ሕመም ለተጋለጡት ሕሙማን የሚያስፈልጉ ብዙ ቫልቮች ይገኙበታል፡፡
በዓለም በዓመት 17.9 ሚሊዮን ሰዎች የልብ በሽታ እንደሚሞቱ ከነዚህም ውስጥ 80 በመቶው የሚከሰቱት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ መሆኑን፣ የሚገርመውም የሚሞቱት ብዙዎች ወጣቶች መሆናቸውን ሐኪሙ አስረድተዋል፡፡
‹‹በሽታን መከላከል በጣም ርካሽ ሲሆን ማከም ግን በጣም ውድ ነው›› ያሉት፣ ተስፋዬ ተሊላ (ዶ/ር) በነፃ የተሰጠውንና እየተከናወነ ያለው የሕክምና አገልግሎት የትኩረት አቅጣጫው ደረት ሳይከፈት የሚሠሩ ሕክምናዎች መሆናቸውን፣ በተጨማሪም የልብ ምት ችግር ላለባቸው የልብ ቀዶ ሕክምና እንደሚደረግላቸው አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ማዕከል ዋና ሥራ እስኪያጅ አቶ ሕሩይ ዓሊ ‹ኸርት አታክ ኢትዮጵያ› ካበረከተው የሕክምና አገልግሎት ባሻገር የዕውቀት ሽግግር የልምድ ልውውጥ ማካሄዱን ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በየካቲት 2016 ዓ.ም. የልብ ሕክምና ተልዕኮውን በልብ ማዕከል ኢትዮጵያ ባከናወነበት ወቅት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለውን ሕክምና በነፃ መስጠቱን ዋናው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
