ዮናስ አማረ

September 1, 2024

ቆይታ

‹‹የእነ ጆን ዳንኤል ጉዳይ የሕፃን ሔቨንን ጉዳይ አስረሳ፡፡ የሕፃን ሔቨን ጉዳይ የአሠልጣኝ ገመዶ ደደፎን ጉዳይ አስረሳ፡፡ የአሠልጣኝ ገመዶ ጉዳይ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ መናርንና የኢኮኖሚ ማሻሻያውን አስረሳ…›› በማለት አንድ የማኅበራዊ ገጽ ዓምደኛ እንደተናገሩት ሁሉ፣ በቅርቡ አገራዊ ትኩረት የሚስቡ አጀንዳዎች አንዱ በሌላው እየተተኩ ሲደራረቡ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ እነዚህ አንዱ ሌላውን እየተከተሉ የተፈጠሩ ወቅታዊ ክስተቶች ደግሞ በሕግና በሞራል እንዴት እንደሚበየኑ የዛሬው የቆይታ አምድ እንግዳ የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ ሰፊ ማብራሪያ ያቀርባሉ፡፡ አቶ አንዷለም በፌደራል ማናቸውም ፍርድ ቤት ጥብቅና ይቆማሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የተመረቁት ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ አንዷለም በፌደራሊዝም ሕግ ማስተርስ ዲግሪ ሠርተዋል፡፡ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በረዳት ዳኝነት ለስድስት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ወደ አሥር ዓመታት ደግሞ በጥብቅና ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የሕግ አስተማሪ ሆነው ለስድስት ዓመታት መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አምና ከመንግሥት ጋር በገባችበት ውዝግብ በፈቃደኝነት በነፃ ለቤተ ክርስቲያኗ ጥብቅና ቆመው ከነበሩ የሕግ ባለሙያዎች አንዱ ናቸው፡፡ ለ40/60 የኮንዶሚኒየም ባለዕድለኞች የቤት ሙግት ጉዳይም ጥብቅና በመቆም ይታወቃሉ፡፡ አቶ አንዷለም ከዚህ በላይ አነጋጋሪ የሕግ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ወደ ሚዲያዎች በመቅረብ ሙያዊ ሐሳባቸውን በማጋራት በሰፊው ይታወቃሉ፡፡ በወቅታዊና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በሚዲያዎች ከሚሰጧቸው አስተያየቶች በተጨማሪ በማኅበራዊ ገጽ ዓምዳቸው በሚያሠፍሯቸው አስተያየቶችም ይጠቀሳሉ፡፡ እኚህን የሕግ ባለሙያ በቅርቡ በኢትዮጵያ ትኩረት የሳቡና ሰፊ የሕዝብ መነጋገሪያን የፈጠሩ የሕግ ጉዳዮችን አስታኮ፣ በሕግና በሞራል ነክ ጉዳዮች ላይ ሪፖርተር በሰፊው አወያይቷቸዋል፡፡ ስለማኅበራዊ ጨዋነት እሴቶች አቶ አንዷለም ሰፊ የሕግ ሐሳቦችን ያነሱበት ከዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- አንድን ጥፋት ወይም የሕግ ጥሰትን ከባድ ነው የሚያስብለው የሕግ አግባብ ምንድነው? አንድ ጥፋት እጅግ ነውረኛ ወይም ፀያፍ የሆነ ከባድ ጥፋት ነው ተብሎ የሚበየነው በምን የሕግ አረዳድ ነው?

አቶ አንዷለም፡- አንድ ዳኛ ጥፋተኝነትን ካረጋገጠ በኋላ ሲወስን ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል ብሎ ሊፈርጀው ይችላል፡፡ በዋነኝነት ከባድ ጥፋት ተብሎ የሚፈረጀው የጥፋት ሁኔታ ሁለት ዓይነት ሊሆን ይችላል፡፡ በልዩ ሁኔታ የሚከብድ አለ፣ እንዲሁም ጠቅላላ ማክበጃ የሚባል አለ፡፡ ጠቅላላ ማክበጃ የሚባለው ከሞራል ነክ ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ ለምሳሌ በከሃዲነት፣ በወስላታነት፣ በወራዳነት የሚሉ የሕግ ቃላትን ይጠቀማል፡፡ መጥፎ አመልን በሚያሳይ፣ በምቀኝነትና ጥላቻን በሚያሳይ፣ እንዲሁም በስግብግብነት ወይም ደግሞ ፍፁም ፈቃደኛ ሆኖ በተለየ ክፋት የወንጀል ድርጊቱ የተፈጸመ እንደሆነ ከባድ ጥፋት እንደሚባል ሕጉ ይዘረዝራል፡፡ እነዚህ ሁሉ መደበኛ ቃላት እንጂ ወንጀልን ማክበጃ ድርጊቶች ናቸው ብሎ ብዙ ሰው ላያውቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕጋችን በቀጥታ አስቀምጧቸዋል፡፡ ሕጉ ወስላታ፣ ወራዳ፣ መጥፎ አመልን የሚያሳይ ምቀኝነት፣ ጥላቻ፣ ስግብግብነት፣ ፍፁም ፍቃደኛ ሆኖ በክፋት ለመፈጸም መነሳትን ወንጀል እንዲከብድ የሚያደርጉ ነገሮች መሆናቸውን አስቀምጧል፡፡ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84 ላይ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ዳኞች አንድ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠ የወንጀል ድርጊት ላይ ውሳኔ ሲሰጡ፣ ከእነዚህ በተጨማሪ ማየት ያለባቸው ሌሎች የወንጀል መሥፈርቶች መኖራቸውም በሕጋችን ተቀምጧል፡፡ ከሰውየው ሰብዕና ጋር አያይዘው መፍረድ እንደሚኖርባቸው ተቀምጧል፡፡ አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊትን ሁለት ሰዎች ቢፈጽሙ ተመሳሳይ ቅጣት ላይጣልባቸው ይችላል፡፡ ሰዎቹ በወስላታነት፣ በወራዳነት፣ በክፋት፣ በምቀኝነት፣ ወዘተ ወንጀሉን መፈጸማቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ውሳኔው ሊለያይ ይችላል፡፡ በግለሰባዊ ማንነቱ አንዳንዱ ሰው ነገረ ሥራው ታይቶ ሊወሰንበት ይችላል፡፡ ይህ ለዳኞች ህሊና የሚተው ቢሆንም ነገር ግን የግለሰቡ ግላዊ ማንነት መጤን አለበት፡፡ ወንጀሉን የፈጸመበት መነሻ ምክንያት መታየት አለበት፡፡ የሐሳቡ ዓላማ መመዘን አለበት፡፡ የግለሰቡ የግል ኑሮ ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ ሁሉ የወንጀሉንም ሆነ የቅጣቱን ክብደት ይወስኑታል፡፡ አንድ ዓይነት ወንጀል በተማረና ባልተማረ ሰው ሲፈጸም አንድ ዓይነት ቅጣት አይጣልም፡፡ እያወቀ ነው ያደረገው ተብሎ ስለሚታመን በተማረ ሰው ላይ ቅጣቱ ሊከብድ ይችላል፡፡ አንድ ዓይነት ወንጀል በሀብታምና በደሃ ሲፈጸም አንድ ዓይነት ቅጣት አይኖረውም፡፡ ኢኮኖሚ ወንጀል የመፈጸም አቅምን ስለሚጨምር የጥፋተኛው ሀብት ቅጣቱን ያከብደዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ወራዳነት፣ ወስላታነት፣ ክፋትና ተንኮል የመሳሰሉ ነገሮች ተሟልተው ከእነዚህ በተጨማሪ የወንጀል ቅጣትን የሚያከብድ ሌላ ነገር ወንጀሉ የተፈጸመበት ዓላማ ነው፡፡ ለምሳሌ መስረቅ እንዳለ ወንጀል ነው፡፡ ሆኖም ስግብግብነት፣ ለታመመ እናት ወይ ቤተሰብ መታከሚያ ወይ መድኃኒት መግዣ መስረቅ በኢትዮጵያ ሕግ የተለያየ ክብደት ያለው የጥፋት ዓይነት ነው፡፡ ከፍ ያለ ስሜት ብሎ ሕጉ የሚያስቀምጠው የወንጀል ገቢር አለ፡፡ ለተከበረ ነገር ወይም በግል ጥቅም ላይ ላልተመሠረተ ነገር እንዲሁም ከፍ ባለ ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ ወይም ሃይማኖታዊ ሐሳብ ተነሳስቶ ወንጀሉን ከፈጸመው ጥፋተኝነቱ ሊቀል እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ለሃይማኖታቸው ባላቸው ቀናዊነት ስላላቸው ትዕዛዝ ላይቀበሉ ይችላሉ፣ ወይ የተሠራ ነገር ሊያፈርሱ ይችላሉ፡፡ ለመስጊዴ ወይም ለቤተ ክርስቲያኔ በማለት የተለያዩ ነገሮች ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ጉዳዩ ወንጀልነቱ ወንጀል ነው፡፡ ሆኖም ቅድም እንደተጠቀስኩት ወራዳና ነውረኛ ድርጊቶች ሳይሆኑ፣ ከፍ ላለ ለተከበረ ነገር የተደረጉ በመሆናቸው የቅጣት ማቅለያ ይኖረዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች የኢትዮጵያ ሕግ ወንጀልን ወይም ጥፋትን የማክበድና የማቅለል ጉዳይን ለዳኞች ነው የሰጠው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበረሰቡን ጨዋነትና ባህል የሚጎዳ፣ ለማኅበረሰቡ ጠንቅ የሆነ ወንጀል ተብሎ የሚገዝፍ የወንጀል ድርጊትም ይታያል፡፡ ይህ በምን መሠረት ነው የሚደረገው?

አቶ አንዷለም፡- ለኅብረተሰቡ ጠንቅ ነው የሚባል ወንጀል አለ፡፡ ዳኞች በሕጉ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በልዩ ሁኔታ ወንጀልን ማክበድ ይችላሉ፡፡ ምክንያታቸውን በመጥቀስ ብቻ ለማኅበረሰብ ጠንቅ ነው የሚሉት ወንጀል ሊኖር ይችላል፡፡ የካሚላት የወንጀል ታሪክን ማስታወስ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የወንጀሉ አፈጻጸም ከዚያ ወዲህ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አክፍቶታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፍርድ ቤቱ የወንጀሉ አፈጻጸም ለሕዝብ እንዳይገለጽ ቢያደርግ ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዚያ ወዲህ ነው አሲድ ሴቶች ላይ መድፋት እየተስፋፋ የመጣው፡፡ የማኅበረሰቡን ስሜት የሚያውክ ወንጀል አለ፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አራት ኪሎ አካባቢ አህያ አርደው ሥጋ ይሸጣሉ የሚል ክስ ሲሰማ ነበር፡፡ በአሰላ አካባቢም እንዲሁ አህያ አርደው ሥጋ የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ ሲባል ሰምተናል፡፡ የአህያ ሥጋ መብላት ለጤና ምንም ዓይነት ጠንቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው መታወክ እጅግ ከባድ ነው፡፡ እምነት እንዳይኖር ያደርጋል፣ ጥርጣሬ ያፈራል፣ ከዚያም አልፎ ረብሻ እስከ መፍጠር ሊያደርስ ይችላል፡፡ ጉዳዩ ምስር አንደኛ ደረጃ ነው ብሎ ወይም ሌላ ዕቃ አታሎ እንደ መሸጥ አይደለም፡፡ ይህን በተለየ ሁኔታ አደገኛነቱን ተመልክቶና አክብዶ ለመፍረድ ዳኞች ይፈቀድላቸዋል፡፡ ለምሳሌ የሰው መግደል ወንጀል ያው ግድያ ነው የሚባለው፡፡ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ሕግ የሃይማኖት አመራር መግደል ከበድ ያለ ቅጣት ነው የሚያስቀጣው፡፡ የሃይማኖት መሪን መግደልና ተራ ሰው መግደል አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ የአገዳደል ዓይነትም የጥፋተኝነት መጠንን እንዲለያይ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ ተፈጸሙ ተብለው የተነገሩ ወንጀሎች ኅብረተሰቡን በተለየ ሁኔታ ሲያውኩት ተመልክተናል፡፡ በቅርቡ ይፋ የሆነው የሕፃን ሔቨን ግድያ ጉዳይ እኔ የማውቃቸው ሰዎችን ባለቤቴን ጨምሮ እንቅልፍ መተኛት ሁሉ ሲከለክላቸው አይቻለሁ፡፡ የደረሰው የግፍ መጠን ብዙዎችን እያለቀሱ እንዲያድሩ ነው ያደረጋቸው፡፡ በርካቶች ድርጊቱን ከሰሙ ወዲህ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤትም ሆነ ወደ ውጭ መላክ ሲከብዳቸው ታይተዋል፡፡ ተገዶ መደፈር ያው የመደፈር ወንጀል ቢሆንም፣ የአንዳንድ ወንጀሎች አፈጻጸም ግን እጅግ ከባድ ሲሆን ይታያል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቶች እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት አስገብተው ቅጣቱን ሊያከብዱት ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ አገራዊ መናወጥ የፈጠሩ የወንጀል ጉዳዮች ተሰምተዋል፡፡ ከሕፃን ሔቨን ጋር የተያያዘው የባህር ዳሩ ጉዳይ በይግባኝ ላይ ያለና ውሳኔ የሚጠባበቅ መሆኑ ቢታወቅም፣ ከዚያ ወዲህ የእነ ጆን ዳንኤል [ቲክቶከሩ] ጉዳይም አገራዊ መነጋጋሪያ ሲፈጥር ታይቷል፡፡ እንደ ወንጀል እንኳን ባይታይ ሽልማት አልቀበልም ያሉት የአትሌቲክስ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ ጉዳይም ከፍተኛ መነጋገሪያ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ምናልባትም ከእነዚህ የገዘፉ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ አንዳንድ ጥፋቶችና ወንጀሎች ልዩ ትኩረት ሲያገኙ ነው የሚታየው፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አልቀው ዝም ሲባል፣ ትንሽ ነገር ተፈጥሮ ደግሞ ከፍተኛ መነጋገሪያን ሲፈጥር ይታያል፡፡ ይህን መሰል ድብልቅ ስሜት የሚፈጥረው ምንድነው? የወንጀሉ ክብደት፣ ዓይነት ወይስ አፈጻጸሙ የኅብረተሰቡን ምላሽ የተዘበራረቀ እንዲሆን የሚያደርገው?

አቶ አንዷለም፡- ይህ በነገራችን ላይ በግሌ እኔም የምገረምበት ጉዳይ ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ጨዋነት የምንለው ሐሳብ አለ፡፡ ሁላችንንም የሚያግባባ አንድ ነገርን ጥሩ፣ ሌላ ነገርን መጥፎ ብለን የምንበይንበት ሐሳብ ነው፡፡ ከባህል ባህል ብንለያይም የምንግባባበት የማኅበረሰባዊ ጨዋነት መሥፈርት አለ፡፡ አንድ አለባበስ ትክክል ነው ለማለት በጃፓን፣ በሶማሊያ፣ በኮሪያና በአፋር አንድ ዓይነት መሥፈርት ላይኖረው ይችላል፡፡ በጊዜ ብዛት የዳበሩ ነገሮችን ትክክልና ትክክል ያልሆኑ ለማለት የሚያስችሉ እሴቶች ግን በሁሉም ዘንድ አሉ፡፡ በጋራ ለመኖር የሚያስችሉ እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች ግን ከጊዜ ብዛት እየተሸረሸሩ ይመጣሉ፡፡ ማኅበረሰባዊ ጨዋነትን የሚሸረሽሩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በዋናነት የሕግ ጥርስ ሲላላ ነው ይህ ችግር የሚጨምረው፡፡ ሕግ መፈጸሙ ሲዳከምና በየጊዜው የሕግ መላላት ሲፈጠር ነው ይህ ችግር የሚጎላው፡፡ ወንጀል የሰው ልጅ ከተፈጠረ ቀን ጀምሮ አለ፡፡ ነገር ግን አስደንጋጭ ወንጀሎችን መስማታችን እየጨመረ የመጣው ከለውጡ ወዲህ ነው፡፡ ዓይነታቸው እየተቀየረ መጥቷል፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ በወንጀሎቹ ሰቅጣጭነት ልክ ሲደነግጥ አይታይም፡፡ ምክንያቱም መለማመድና መደንደን ተፈጥሯል፡፡ የመንግሥት ሕግን የማስፈጸም አቅም ከዕለት ወደ ዕለት እየተዳከመ መምጣት ከዚህ በላይ ወንጀልን እየጨመረ ነው፡፡ በላቲን አሜሪካና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የምንሰማቸው ዓይነቶች ከባባድ ወንጀሎች ወደ እኛም መምጣታቸው አይቀርም፡፡ በአገሪቱ ዋና ዋና በሚባሉ እንደ አማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ግጭት እንደቀጠለ ነው፡፡ የተረጋገጠ ሥርዓተ አልበኝነት በብዙ አካባቢዎች አለ፡፡ ኅብረተሰቡ በሌሎች ነገሮች ተወጥሮ ብቻ ሳይሆን እንዲያው ከሌላው አገር በተሻለ ጨዋነትና ፈሪኃ እግዚአብሔር የተላበሰ፣ አብሮ በሰላም የኖረና ሃይማኖተኛ በመሆኑ እንጂ እንዳለው ሁኔታ ቢሆን ኖሮ ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ነበር፡፡ ለምሳሌ ግጭቱ ከጀመረ ረዥም ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን አንድም ባንክ ተዘረፈ ሲባል አንሰማም፡፡ ይህን መሰሉ ነገር የመጣው በመንግሥት ሕግን የማስፈጸም ጥንካሬ አይደለም፡፡ መንግሥት ዕለት ተዕለት ሕግን የማስፈጸም አቅሙ እየቀነሰ ከሄደ ግን እስካሁን ካየነው የከፋ የወንጀል ድርጊቶች እናያለን፡፡ የሕግ ማስፈጸም አቅም በተዳከመ ቁጥር በጣም ዘግናኝ ወንጀሎች መፈጸማቸው ይቀጥላል ብቻ ሳይሆን፣ ለረዥም ዘመን የተጓዝንባቸው ጥሩና መጥፎን የለየንባቸው የማኅበራዊ ጨዋነት እሴቶቻችንም ተንደው እናገኛቸዋለን፡፡

ለምሳሌ የአማራ ክልል ኬዝ ገና ይግባኝ ላይ ቢሆንም ሕጉ እስከሚፈቅደው ድረስ ብንመለከት፣ ወንጀሉ የተፈጸመው ግጭት በአካባቢው በተስፋፋበት ወቅት ነበር፡፡ የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮም ሆነ ፖሊስ የሰጠውን መግለጫ አይቼዋለሁ፡፡ ወንጀሉ የተፈጸመው የፋኖ ኃይሎች አካባቢውን ተቀቆጣጠሩ በተባለ ወቅት ነበር፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. እነሱ ባህር ዳር አካባቢ ገቡ፣ ወንጀሉ የተፈጸመው ደግሞ ሐምሌ 27 ነው፡፡ ሕፃን ሔቨን መደፈሯና መገደሏ በፍርድ ቤት የተበየነ ቢሆንም ይግባኝ ተብሎበታል፡፡ ወንጀሉን ጌትነት ባዬ የሚባለው ሰውዬ ፈጸመውም ሆነ ሌላ አደረገው፣ ወንጀሉ ግን በአካባቢው ግጭት በነበረ ወቅት መፈጸሙ እርግጥ ነው፡፡ ያንን አጋጣሚ ለመጠቀም የፈለገ ሰው መኖሩ አያጠራጥርም፡፡ የከተማውና የአካባቢው በተኩስ መናወጥና ግርግር መኖሩን አይቶ ሌላ ጊዜ ሲያስብበት የቆየውን ወንጀል የፈጸመ አካል አለ ማለት ነው፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት ማኅበራዊ ጨዋነታችን እየቀነሰ ነው የሚለው ድምዳሜ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሃይማኖታዊ እሴትና ፈሪኃ እግዚአብሔር እየተሸረሸረ ነው የሚለው ድምዳሜም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን በየቦታው ያለው ሥርዓተ አልበኝነትና ግጭት ለወንጀሎች መጨመር ተጨማሪ ግብዓት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ልክ በከተማው ሕግ የሌለ ሲመስለው ሕፃን ደፍሮ እስከ መግደል ይታሰባል ማለት ነው፡፡ በእነዚህ መሰል ወቅቶች መዝረፍ እጅግ የቀለለው ጉዳይ እንደሚሆን ከዚህ ተነስቶ መገመት ይቻላል፡፡ የኢኮኖሚ ፍትሕ በሌለበትና እኩል የሀብት ክፍፍል ባልሰፈነበት በልቶ ለማደር ሰዎች የከፋ ነገር ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን በሕግ ተቆጣጥረነው ነው የምንኖረው፣ ነጥቆ ለመብላት ብዙ ሰው ሊፈልግ ይችላል፡፡ በዚያች ሰዓት ለተፈጠረች ግርግር ይህን ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል መፈጸሙን ከሰማን፣ እንዲህ ዓይነቱ ግርግር ለረዥም ጊዜ ቢቆይ ኖሮ ደግሞ ብዙ ነገር ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡ ንብረት መነጣጠቅ፣ መካካድ፣ ልጅም ሆነ ሚስትን መቀማት ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡

አሁን አሁን ስድነት እንደ ባህል እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለአገራዊ ጉዳዮች ሳይቀር ግዴለሽነት እየታየ ነው፡፡ ለመንግሥት፣ ለታላላቆች፣ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለአገር መሪዎች፣ ለታላላቆችና መከበር ለሚገባቸው ክብር የለሽነት ባህሪ ማሳየት እየተለመደ የመጣው በዓለም አቀፍ የባህል ወረርሽኝ ጭምር ነው፡፡ ግሎባላይዜሽኑ ባመጣብን ጣጣ በቲክቶኩና በኢንተርኔቱ ከኢትዮጵያ ባህል ያፈነገጡ ብዙ ነገሮችን እየተለማመድን እንገኛለን፡፡ በቴክኖሎጂ መጠቀማችን እያደገ በመጣ ቁጥር የእኛ ያልሆነ ብዙ ባህልና ልማድ አብሮ መምጣቱ የሚቀጥል ነው፣ ይህን አቻችለን ነው መሄድ የሚኖርብን፡፡ ለምሳሌ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፊት ሁለት ሚሊዮን ብር ሽልማት አይመጥነኝም ለእኔ ስድብ ነው ብሎ እንቢ ማለቱ ብዙ መናወጥ የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ሁኔታ ሻምበል ማሞ ወልዴ ይመስለኛል የማራቶኑ ጀግና በጊዜው አፄ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት እንኳ ቢሰጧችሁ [ከ500 ብር በላይ] ስግብግብ ስለሚሏችሁ በእናንተ አገር እንዳይዋረድ አትቀበሉ ብለው የመከሯቸውን ነገር አስታውሶ፣ በጊዜው አንደኛ ወጥቶ የተሸለመውን የመኪና ሽልማት አልወስድም ብሎ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ መኪና አልፈልግም ብሎ ካሜራ ተሸልሟል፡፡ በጊዜው ውድድሩ ዩጎዝላቪያ ይመስለኛል የተካሄደው፡፡ ማሞ አንደኛ ወጥቶ ሽልማቱ ይበዛብኛል ብሎ መኪናን ትቶ ካሜራ በመሸለሙ የተነሳ በታላቅ ክብር ስሙ እንዲጠራ ተደርጎም ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሙያ ያለ ሰው ሁለት ሚሊዮን ብር ተሸልሞ አልፈልግም፣ አልቀበልም ብሎ በአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ፊት ሽልማት የሚመልስበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ የኢትዮጵያውያን የነበረው ማኅበራዊ እሴት ምን ያክል እንደተሸረሸረ ማሳያ ነው፡፡

ሁለተኛ በጣም ብዙ ወንጀለኞች ብዙ ጥፋት እያጠፉ በተደጋጋሚ ጊዜ ዝም ሲባሉ መቆየታቸው የፈጠረው መለማመድም አለ፡፡ መንግሥት የሚባለው አካል ለውጡን ለማፅናት ወይም የለውጥ ጊዜ ነው በሚል ብዙ ወንጀሎችን ሲታገስ ቆይቷል፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች ከመንግሥት ጋር ትከሻ ሲገፋፉ ዝም የሚባልበት ሁኔታ ነበር፡፡ ለውጥ ሲፈጠር የሚያጋጥም ነው እየተባለ ብዙ ወንጀሎች ዝም እየተባሉ አልፈናል፡፡ ይሁን እንጂ ለውጥ የተባለው አሁን ስድስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡ ሰዎች በፍቅር ቃል ብቻ የሚኖሩ ቢሆን ኖሮ ሕግ አያስፈልግም ነበር፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) መጀመሪያ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ያራምዱ የነበሩት መግደል መሸነፍ ነው፣ በፍቅር መደመር ነው፣ ወዘተ የሚሉ አካሄዶች፣ እንዲሁም ከባባድ ወንጀለኞችን መፍታት የትም እንደማይደርስ ይታወቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ ባህሪ ከዚህ ጋር ስለማይሄድ ነው ሕግና ቅጣት አስፈላጊ የሆነው፡፡ በተቻለ መጠን ወደ ቅጣት ባለመገባቱ በለውጥ እየተሳበበ ብዙ መስዋዕትነት በጊዜው ከፍለናል፡፡ ይህ ደግሞ አሁንም የምናያቸው ነውረኛ ጥፋቶች እንዲፈጸሙ መነሻ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የተፈጠረው ግርግር የዚህ ፍሬ ነው፡፡ እነ ጆን ዳንኤል እኮ አሳዳጊ የበደላቸው ልጆች አይደሉም፡፡ ከእኔና ከአንተ የሚለያቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ሆኖም በቅርብ በምናውቃት ኢትዮጵያ ማንኛውም ዓይነት ከባድና ፀያፍ ወንጀል ከመርህ ውጪ ሲታለፍ ነው የሚታየው፡፡ ይህ ደግሞ ጥፋትና ጥፋተኝነትን ብዙዎች እንዲደፋፈሩ የሚጋብዝና የሚያለማምድ አጋጣሚ ነው፡፡ እነዚህን ልጆች ያለ የሌለ የጥፋት ዓይነት ደራርበን እንቅጣቸው የሚለው ነገር እኔን አያሳምነኝም፡፡ ብዙ ነገሮችን ስንታገስና ስናልፍ ቆይተን ከመሬት ተነስተን ልጆቹ ላይ መረባረቡ አያሳምንም፡፡ በአማራ ክልል ላይ ብዙ ዓይነት ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች ሲሸለሙ ታያለህ፣ በኦሮሚያም እንደዚያው፡፡ አሁን አውሮፕላኑ ላይ ግርግር የፈጠሩ ልጆች እንዴት ተደፋፈሩ በሚለው ነው እንጂ ሰው የተንገበገበው፣ ከዚህ በላይ የሆነ ብዙ ዓይነት ወንጀሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥት አቋቁመናል ያሉ እኮ ነበሩ፡፡ ትጥቅ አንፈታም ብለው በይፋ እስከ መናገር የደረሱ እኮ አሉ፡፡ አዲስ አበባ ጫፍ ድረስ ሰዎች ታግተው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በአዋሽ ባንክ ማስለቀቂያ ሲላክ ምንም ሳይደረግ ይታለፋል፡፡ ይህን ሁሉ መንግሥት ሲታገስ ያዩ ወጣቶች በአየር መንገድ ላይ ግርግር ቢፈጥሩና የአቪዬሽን ሕግ ቢጥሱ ምኑ ነው የሚገርመው?

በአሁኑ ወቅት እኮ መንግሥት አዲስ አበባ ብቻ ነው ሕግ ማስፈጸም እየቻለ ያለው ከአዲስ አበባ በ50 እና በ60 ኪሎ ሜትር ራዲየስ የተደራጀ ቡድን ሰዎችን እያገተ ገንዘብ ይቀበላል፡፡ ይህ እኮ እንደ ብራዚልና ሄይቲ ባሉ አገሮች የምንሰማው የነበረው ነው፡፡ ይህን ያዩ ሰዎች ፕሬዚዳንቷ ፊት ሁለት ሚሊዮን ብር መቀበል ስድብ ስለሆነ አንፈልግም ቢሉ፣ እንዲሁም ከአውሮፕላን ላይ አንወርድም ቢሉ ምን ይገርማል? አንዳንዴ እኛ ኢትዮጵያውያንም ወጥነት ያለው አቋም አናሳይም፡፡ ማኅበራዊ መሠረታችንን የሚያናጋና አብሮነታችንን የሚንድ ከባድ ሁኔታ ተፈጥሮ ዝም እንላለን፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ለትንሽ ነገር በጣም የጋለ ስሜት እናንፀባርቃለን፡፡ የባሰ ነገር ሲፈጸም ዝም ብለን ትንሽ ነገር ስትፈጠር ደግሞ አገር ይያዝ የምንለው ነገር አለ፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ሕግ የማስፈጸም አቅማችን መዳከሙና ሕግ የበላይነት መሸርሸሩ ብዙ ሕገወጥ ነገሮችን እንድንለማመድ በር የከፈተ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሃይማኖት አባቶችና የእምነት ተቋማት ለጽንፈኛ አስተሳሰቦች ስሜታዊ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ፣ ማኅበረሰቡን በሞራል ማነፅና በግብረ ገብ ማረቅ ላይ የሚጠበቅባቸውን ያህል እያበረከቱ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ይህ የእነሱ የሞራል ማረቅ ጣልቃ ገብነት መቀነስ ደግሞ ማኅበራዊ ጨዋነታችን እንዲሸረሸር ተጨማሪ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አሁን አሁን የቤተሰብ ትስስር እየላላ የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኝነት በኅብረተሰባችን ውስጥ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ እነ ጆን ዳንኤልም ሆኑ ሌሎች ቲክቶክ ላይ ያሉ ተናጋሪዎች ብዙ ታዳጊዎችን ከጀርባቸው የሚያሠልፉበት ጊዜ ነው፡፡ እንደ በፊቱ ቤተሰብ ወይም ጎረቤትና የመንደር ሰው ቀጥቶና ገስጾ የሚያሳድገው ታዳጊ እየጠፋ፣ በምትኩ ደግሞ በቲክቶክ አውራዎች የሚዘወር ታዳጊ እየበረከተ ነው፡፡ አንተ ሳትሆን ራሱን ያልቻለ ሌላ ወጣት ነው የአንተን ልጅ እንደፈለገ የሚያሰማራው፡፡ እስከ ጎልማሳና አዋቂ ድረስ ምንም ክብር የሌለው ጎረምሳ ብዙ ወጣቶችን እንደፈለገ የሚጋልብበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡

ለምሳሌ ዳኒ ሮስት የሚባል ቲክቶከር አንድ ትምህርት ቤት ተጠርቶ የክብር እንግዳ ተብሎ ለሌሎች ታዳጊዎች የአድናቆት ፊርማ ሲፈርም አይቻለሁ፡፡ ልጆቼ ይህንን ሰው ሲያዩ አግኝቼ ተቆጥቼ አውቃለሁ፡፡ ዳኒ ሮስት ነኝ ብሎ መሠረታዊ ጉዳዩ ከሰዎች ጋር መሰዳደብ የሆነ ልጅ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊ ባህል አይደለም፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጭምር ተቀምጠው የሚሰዳደቡበት፣ ትልልቅና ዝነኛ የሚባሉ ሰዎች ተሰባስበው በብልግና ቃላት የሚወራረፉበት ልማድ አለ፡፡ እነሱ ያዋጣቸው አያዋጣቸው የራሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ጋ ግን ይህን መሰል ባህል የለም፡፡ እኛጋ በላ ልበልሀ እየተባባሉ በእንካ ሰላንቲያ ክብር በማይነካ መንገድ በግጥምና በቅኔ መወራረፍ የነበረ ባህል ነው፡፡ ነገር ግን አንተ አንተ ምንትስ እየተባባሉ መሰዳደብ ባህላችን አይደለም፡፡ ይህን ሙያዬ ብሎ በቲክቶክ የሚሠራ ልጅ ካቴድራል ይሁን ሌላ ትምህርት ቤት ተገኝቶ የአድናቆት ፊርማ ለሌሎች ወጣቶች ሲፈርም ስታይ ደግሞ ወዴት እየሄድን ነው ያስብላል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ እየወደቅን ነው ማለት ነው፡፡ ይህን መሰል ሰው አርዓያ የሚያደርግ ወጣት የምናፈራ ከሆነ ነገ ተነገ ወዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ፕሬዚዳንቷን፣ የሃይማኖት አባትና ሌላም የተከበረ ሰው የሚያዋርድ ሰው ቢመጣ ምኑ ይገርመናል? ሁለት ሚሊዮኑን አልወስድም ያለውም ሆነ ከአውሮፕላን አንወርድም ያሉ ሰዎች በወያኔ ዘመን ቢሆን ኖሮ አያደርጉትም ነበር፡፡ ይህን መሰሉ ድፍረት በዚያ ዘመን አይታሰብም ነበር፡፡ አሁን ግን ዕለት በዕለት ሥፍር ቁጥር የሌለው ወንጀል እየሰማን እኮ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህ 5,100 ግጭቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መዝግቤያለሁ ብሏል ይህን የሚያጠና አካል፡፡ ይህን ሁሉ ቁጥር ያለው ግጭት ያስተናገድነው ደግሞ ሥርዓተ አልበኝነት ስለነገሠ ነው፡፡ አሁን ከአውሮፕላን አንወርድም የሚል ጥፋት ብንሰማ ወይም ሽልማት አልቀበልም ማለት ብንሰማ ምንም ሊገርመን አይገባም፡፡ የማኅበረሰቡ ሥነ ምግባራዊ እሴቶችና ጨዋነት መሸርሸሩ ጥልቅ ጥናት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን እኔ የምረዳው የሕግ መላላት ነው ለዚህ ያበቃን፡፡ የሙስናና የምዝበራ መስፋፋት፣ በየጊዜው ደግሞ የሚፈጠሩ ንቅዘቶችና የሕግ ጥሰቶችን ተከታትሎ በተገቢው ሁኔታ ምላሽ አለመስጠት ነው ይህን ችግር እያሰፋው የመጣው፡፡

ሪፖርተር፡- ለብዙ ነገሮች የሕግ ጥበቃ ሊኖር ይገባል፣ የሕግ ከለላ ሊደረግ ይገባል እየተባለ ሲነገር ይሰማል፡፡ የሕግ ጥበቃ ሲባል እስከ ምን ድረስ ነው መሆን ያለበት? ለምሳሌ አንድ ማኅበረሰብ በሕግ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ሲባል እስከምን ድረስ ነው?

አቶ አንዷለም፡- የሕግ አንደኛው ጥቅሙ ለማኅበረሰብ ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ነው፡፡ ሕግ በአመዛኙ ‹‹ሶሻል ኢንጂነሪንግ›› ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ አንድን ማኅበረሰብ እንዲሆን እንደምንፈልገው አድርገን ልንገነባው እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ጃፓኖች ሠርተውበት ነው አሁን ያላቸውን ማኅበረሰባዊ ማንነት የፈጠሩት፡፡ ጨዋነትና አክባሪነት የጃፓን መገለጫ እንዲሆን በመንግሥትም፣ በግለሰብም፣ በፖሊሲም ተሠርቶበት የመጣ ውጤት ነው፡፡ ጃፓን እንደ ምን ሠለጠነች በሚል ርዕስ የቀረበው የቆየው የጋሽ ከበደ ሚካኤል መጽሐፍ ብዙ ቁም ነገር ስለእነሱ ያስተምራል፡፡ በባለሀብቶች ደረጃ ጨዋነትና ትጋት የጃፓናዊያን መገለጫ እንዲሆን ይሠራበታል፡፡ አንድ ጃፓናዊ ባለሀብት ከከሰረ ለጃፓናዊያን አይመጥንምና ታራያሺ በሚሉት ራስን የመግደል ሥርዓት ራሰን እስከ ማጥፋት የደረሰ ውሳኔ እስከ መወሰን ሊሄድ ይችላል፡፡ ከጨዋነት፣ ካለመስረቅ፣ ከታታሪነት አልፈው በብዙ መንገዶች ብዙ ሠርተው ነው አሁን ለደረሱበት አገራዊ ስኬት የበቁት፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ፣ በሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት መሪዎችና በሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ደረጃ ዕለት ተዕለት መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን ግን በተለምዶ እንዲከወን ከማድረግ በተጨማሪ በሕግ አውጥቶ መተግበርም ይጠይቃል፡፡ አንድን ማነወር የተፈለገ ነገር ለምሳሌ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን በሕግ ብትከለክል የሚፈጸምበትን ዕድል እንዲጠብቅ ታደርገዋለህ፡፡ በድብቅና በማይታይ ሁኔታ መፈጸሙን ማስቀረት ባትችል እንኳ፣ ነገር ግን በሕግ ሕገወጥ ነው ብለህ በመፈረጅህ ድርጊቱ እንዳይዛመት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ነው የሚታመነው፡፡ ለምሳሌ ለመንግሥት ክብር እንዲሰጥ ከፈለግን ወይም ለርዕሰ ብሔርና ለመሪ ክብር መኖር አለበት ካልን፣ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ የፈጸሙትን ዓይነት ድርጊት በመቅጣት ማስተማር መቻል አለብን፡፡ ሰውዬው ትፈለጋለህ ተብሎ ተይዞ መውጣቱን ከመስማት በዘለለ ያደረገው ነገር ነውር መሆኑን በሕግ አግባብ ማሳየት አለብን፡፡ ነገ የአፍሪካ ኅብረት መሪ ወይም የሌላ አገር መሪን በአደባባይ የማያዋርድ ትውልድ እንዲኖረን ከፈለግን እንደ ማኅበረሰብ የምንፈልጋቸውን የጨዋነት መሥፈርቶች ማስቀመጥ አለብን፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ነገ ልንደርስበት የምንፈልግበት፣ ኢትዮጵያዊ ሲባል መገለጫዎቹ እንዲሆኑ የምንፈልጋቸው ነገሮች ላይ መሥራት አለብን፡፡ ማሞ ወልዴ ሽልማት አይብዛብኝ ብሎ ኢትዮጵያን እንዳኮራው ሁሉ ኢትዮጵያውያን ስግብግብ አይደሉም፣ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ይወዳሉ፣ ኢትዮጵያውያን መንግሥታቸውን ያከብራሉ፡፡

በእርግጥ መንግሥትን ሆነ መሪውን መጥላት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሚባለው ሥርዓተ መንግሥት በጋራ መቆምና የአንድነት ስሜት ማሳየት ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡ መንግሥት ማክበር መንግሥቱ ኃይለ ማሪያምን፣ መለስ ዜናዊን ወይም ዓብይ አህመድን መውደድና መጥላት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነትንና አገረ መንግሥቱን መውደድና ማክበር ግን አስፈላጊ ነው፡፡ በእጃችን ላይ ያሉ ሕጎች አንዳንዴ የሚፈጸሙ ጥፋቶችን ላያርቁ ይችላሉ፡፡ ሕግ አንዴ ተጽፎ ሁሌም ይሠራል ማለት አይደለም፡፡ በየጊዜው ከሚመጡ ነገሮች ጋር አብሮ እንዲሄድ መስተካከልና መሻሻል አለበት፡፡ ጥፋት ከተፈጸመ በኋላ በሌለ ሕግ ሰዎችን ዘሎ መቅጣት አይቻልም፡፡ ሕጎቻችንን አገላብጠህ የመቅጫ መንገዶች ካገኘህ ትቀጣለህ፣ አለበለዚያ ግን ያለ ሕግ ልትቀጣ አትችልም፡፡ እንዲህ ዓይነትም የጥፋት ዓይነት ለካ አለ ብለህ ከዚያ አጋጣሚ ተምረህ ሕግ ታወጣና ትቀጣለህ እንጂ፣ በሌለ ሕግ ልትቀጣ አትችልም፡፡ አንዳንዴ ማኅበረሰባችን በጣም ስስ ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ለምሳሌ ዮናስ አማረ ጠንካራ ልትሆን ብትችልም፣ ነገር ግን የሆነ አሰቃቂ ወንጀል ተፈጸመ በተባለ ጊዜ ሲያለቅሱ ከሚያድሩ ብዙ ሰዎች አንዱ ልትሆን ትችላለህ፡፡ የሆነ ነገር ተፈጸመ ሲባል ስሜቱ በጣም የሚጎዳ ብዙ ሰው አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ለማኅበረሰቡ ተገቢ ጥበቃ የሚያደርጉ ሕጎች ምንድናቸው ተብሎ በደንብ ተጠንቶ የሚወጡ ሕጎች ይኖራሉ፡፡ ማኅበረሰቡ የሕግ ከለላ ሊያገኝ ይገባል ሲባል ይህን የሚጨምር ነው፡፡ መንግሥት የታክስና የሌሎች ሕጎች ብቻ አይደለም የሚያወጣው፡፡ ለማኅበረሰቡ እሴቶች መጠበቅ ዋጋ ያላቸው ሕጎችንም ማበጀት ይኖርበታል፡፡ ይህን የሚያነሳ አካል ስለሌለ ግን የታክስና የገቢ ጉዳዮችን የተመለከቱ ሕጎች ብቻ ናቸው ሲወጡ የሚታዩት፡፡ በሌሎች አገሮች እኮ ለዚህ ሁሉ ተጨንቀው ሕግ እስከ ማውጣት ደርሰዋል ብለን እንድንገረም የሚያደርጉ ሕጎች እናያለን፡፡ የእነዚህ ሕጎች ጥቅምና ተፈላጊነት አልፎ አልፎ ቢሆንም፣ ነገር ግን ለብዙ ጉዳዮች አስበውና ተጨንቀው የሕግ ሽፋን የሚሰጡ መንግሥታት አሉ፡፡ የእምነት አባቶችን ቁጭ ብሎ መስደብ ሥራው ያደረገ ወጣት እየተፈጠረ እኮ ነው፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ የሆነ ከባድ ቀውስ ሲፈጠር ከመደንገጥ ለእያንዳንዱ ነውረኛ መግሪያ የሆነ ሕግ አዘጋጅቶ መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ አንዳንዴ ይህንን ብቻ ሥራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱና ጉትጎታ የሚያደርጉ የሲቪክ ማኅበራት ያስፈልጋሉ፡፡ እነሱ ሲኖሩን ነው የሕግ ቀዳዳ ያለባቸውን ጉዳዮች እየተከታተሉ የሕግ ሽፋን መስጠቱ የሚቀለው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕግ ግዑዝ ነገር አይደለም ወይ? እዚህ አገር ሕጉም ኖሮ አስፈጻሚውም ኖሮ ነገር ግን ሥራ ላይ ማዋሉ ስለከበደ አይደለም ወይ ብዙ ችግር እየተፈጠረ ያለው? በአንዳንድ አገሮች እስር ቤትም ፖሊስም ሳይኖር ለመኖር አይቸገሩም፡፡ እዚህ ግን ሕጉም አስፈጻሚውም ኖሮ በተግባር መተርጎም ባለመቻሉ ብዙ ችግሮች ይፈጠራሉ እኮ?

አቶ አንዷለም፡- በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባሉ ሕጎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ትናንት የብሮድካስት አዋጁን ሳገላብጥ አንድ አስገራሚ ከዚህ ቀደም ያላስተዋልኩት ነገር አግኝቻለሁ፡፡ የወሲብና የብልግና ነክ ነገሮችን አንድ ሰው በሚዲያ ማስተላለፍ የሚችለው፣ ለአዋቂ እንጂ ለአቅመ አዳም ላልደረሱ ሰዎች መተላለፍ የማይችል ነገር ቢሠራ ማሠራጨት የሚችለው ከምሽቱ አራት ሰዓት እስከ ለሊቱ 11 ሰዓት ብቻ ነው የሚል ሕግ አለ፡፡ ይህንን ሕግ በኢትዮጵያ እየጠበቀ ያለ ሚዲያ አለ ወይ የሚለው ያጠራጥራል፡፡ ይህንን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣንም ተከታትሎ አያስፈጽምም፡፡ ይህ በሕጉ መኖሩን የሚያውቀውም ውስን ነው፡፡ ሕግ ግዑዝ ነው፡፡ ተከታትሎ ማስፈጸም ያለበት የሚመለከተው አካል ነው፡፡ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ተከታታይ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል፡፡ አንዴ ሕጉ ወጣ ተብሎ መተው የለበትም፡፡ እኔ አስተማሪም ሆኜ ሠርቼያለሁ፣ ብዙ ጊዜ በየፍርድ ቤቱ ሠርቼያለሁ፡፡ ነገር ግን እኔም በየጊዜው የሚወጣውን ሕግ አላውቅም፡፡ የሚወጡ ሕጎችን በተመለከተ ተከታታይ ሥልጠና በደረጃው ያስፈልጋል፡፡ ሕግ ብዙ ጽንሰ ሐሳቦችን የሚይዝ ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ጋ አንድ ሰው እንደ ምንም ብሎ የዛሬ 20 ዓመት የጥብቅና ፈቃድ ያወጣና ለዘመናት በዚያው ይቆማል፡፡ ፖሊሱም ሆነ ዓቃቤ ሕጉ ዘንድ ስትሄድ እንደዚያው ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የሚወጣው ሕግና አዋጅ ብዙ አዳዲስ ሐሳቦችን ይዞ ነው የሚዘጋጀው፡፡ በየጊዜው የሚከሰቱ የሚፈጠሩ ነገሮች የሚጠይቁት ዕውቀትና ሐሳብ እየጨመረ ነው የሚሄደው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 590/2008 የምንለው አለ፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ በ2013 ዓ.ም. የወጣ የብሮድካስት አዋጅ አለ፡፡ እነዚህ አዋጆች ግን አሁን ያለውን የመገናኛ ብዙኃን ዓይነትና አሠራር የሚቃኙ አይደሉም፡፡ አሁን ቲክቶክ የሚባል የመገናኛ ዘዴ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሆኗል፡፡ ቲክቶክ እዚህ ደረጃ እንደሚደርስ አስቀድሞ ቢታወቅ በአዋጁ አስቀድሞ እንዲካተት ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ባለመሆኑ አሁን ያለውን ሁኔታ መሠረት በማድረግ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አዋጅ ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን የለውጥ ዑደት በጣም ፈጣን ነው፡፡ በግሎባላይዜሽንም ሆነ በሌላ ተፅዕኖ በፈጣን ሁኔታ ነገሮች እየተለዋወጡ ነው፡፡ ሕግ የሚያወጡት፣ ሕግን የሚያስፈጽሙትም ሆነ ሕግን የሚተረጉሙት አካላት ከዚህ ተጨባጭ የለውጥ ሁኔታ ጋር አብረው መሄድ መቻል አለባቸው፡፡ ሕጉ በአንድ በኩል በፍጥነት መታደስና መሻሻል አለበት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ሰዎቹም አብረው መሠልጠን መቻል አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ሕጉ ቢኖር እንኳ ትርጉም የሌለው ግዑዝ አካል ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡

ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ውስጥ የሕግ አለመኖር ሳይሆን የማስፈጸም አቅም ነው ችግራችን ይባላል፣ ይህንን ይጋሩታል?

አቶ አንዷለም፡- በደንብ፡፡ ቅድም እንደ ጠቀስኩት ለምሳሌ ጥልቅ ድረስ ገብቶ የብሮድካስት አዋጁ ስለያዛቸው ለአዋቂና ለሕፃናት የሚሠራጩ ነገሮችን የለየበትን መንገድ አንስቼያለሁ፡፡ አሁን ባለው ፈጣን ተለዋዋጭ ሁኔታ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊት ዓይነቶችም ሆኑ የሚከሰቱበት ፍጥነት ለቁጥጥር ከባድ ሆኗል፡፡ ከእነዚህ ጋር በሚስተካከል ሁኔታ ተከታትሎ ሕግ የማውጣት ሥራ እየተሠራ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕግ አብዛኛውን ጊዜ እንደሚታሰበው ዓይነት ዘገምተኛና ከጊዜው ጋር የሚሄድ ሕግ አይደለም ማለት እችላለሁ፡፡ ከፈረንሣይ፣ ከእንግሊዝና ከህንድ የተቀዱ ሕጎች ናቸው ያሉን፡፡ ኮመን ሎውና ሲቪል ሎው የሚባሉ ሕጎችን ነው የተቀበልነው፡፡ ሕጉ አይደለም የቀረን ብዙ የተሠራበት ሕግ ነው የተቀበልነው፡፡ እንደ አገር ብዙ ወደኋላ የቀረ አይደለም የሠለጠነ የሚባል ነው፡፡ ሕጉ ሳይሆን ብዙ ጊዜ አስፈጻሚው አካል ነው ወደኋላ የቀረው፡፡ አዋጁን ገልበጥ አድርጎ የሚያይ አካል እኮ ብዙ የለም፡፡ አሁን አሁን የፍትሕ ሚኒስትሩ እነ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ሁሉም ሕጎች በአንድ ቋት ተቀምጠው የሚገኙበትን መንገድ ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ለባለሙያውም አለፍ አለፍ እያሉ ሥልጠና ሲያዘጋጁ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በቂ የሆነ ተደጋጋሚ ሥልጠና ባለሙያዎች ያገኛሉ ወይ የሚለው ሌላ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም ምክንያት ባለሙያዎች አይቆዩም፡፡ ጥሩ የሚባሉ ዳኞች፣ ጥሩ የሚባሉ ዓቃቢያነ ሕጎች ደመወዙ ስለማይበቃቸው ወደ ጥብቅናው ሙያቸውን ሲቀይሩ ይታያል፡፡ ፐብሊክ ሰርቪሱ የተሻሉ ባለሙያዎችን ማቆየት አይችልም፡፡ እንዲህ ዓይነት የባለሙያዎችን ችግሮች ካልፈታህ ሕግ ብቻ ማውጣቱ ትርጉም አይኖረውም፡፡

ሪፖርተር፡- ቅጣትን በሚመለከትም ክርክር ይነሳል፡፡ በአገራችን የሚወሰኑ ቅጣቶች ከተፈጸሙ ወንጀሎች ጋር አይመጣጠኑም፣ አስተማሪነት የላቸውም እየተባለ ይተቻል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የሚፈጠረውስ ለምንድነው?

አቶ አንዷለም፡- አንደኛው ሙስናና ምዝበራ መኖሩ ነው፡፡ ሙስና የገባበት ነገር ሁሉ መበላሸቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነገር ግን የቅጣትን ተገቢነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ወንጀሎች የተለያዩ የቅጣት ማቅለያዎችና ማክበጃዎች በሕጉ አላቸው፡፡ አንድ ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሆኖም የተለያዩ ፍርዶች ሊሰጡ እንደሚችሉ ቅድም አንስተናል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ወንጀሎች ላይ የሚጣለው የቅጣት ምጣኔ የተወሰነ የቅጣት እርከኖችን አልፎ የሚለያይ መሆን የለበትም፡፡ ቅጣት የሚወሰነው የሰዎችን የግለሰባዊ ማንነት ጭምር መሠረት በማድረግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንድ ዓይነት ወንጀል ሆኖ ነገር ግን ሌሊትና ቀን ላይ መፈጸሙ የቅጣት መጠኑን ያለያየዋል፡፡ አንድ ዓይነት ወንጀል ሆኖ ነገር ግን በሁለት ሰው ወይም በአንድ ሰው መፈጸሙ ቅጣቱን ያለያየዋል፡፡ አበበና ከበደ በቡድን ሆነው ፈጸሙት ተብሎ ከዚያኛው ሊከብድ ይችላል፡፡ ዱላ መጠቀምና ጩቤ መጠቀም፣ መሣሪያ መጠቀምና በእጅ መጠቀም የወንጀል ድርጊቱ ጥርስ መውለቅ ቢሆንም ነገር ግን ቅጣቱን ያለያየዋል፡፡ ቅድም እንዳልኩት ወንጀሉ የተፈጸመበት መንፈስ ወራዳነት፣ ወስላታነትና ክፋት የመሳሰሉ ነገሮች ሁሉ ስለሚታዩ የቅጣቱም ሁኔታ በዚሁ መነሻ ይለያያል፡፡ አሁን ግን የቅጣት አወሳሰንን በተመለከተ ራሱን የቻለ መመርያና ማኑዋል ስለወጣ በእሱ መሠረት ነው ቅጣት የሚወሰነው፡፡ መመርያ 2006 የሚባል አለ፡፡ ቅጣት አሰጣጥ ራሱን የቻለ እርከን ወጥቶለታል፡፡ ለአንድ የወንጀል ድርጊት ከስንት እስከ ስንት ዓመት ቅጣት እንደሚጣል ወሰኑ በደንብ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የተራራቀ የቅጣት አወሳሰን በተመሳሳይ ወንጀሎች ላይ አይከሰትም ማለት ነው፡፡ አንድ ወንጀል ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚል ከተቀመጠው የቅጣት ወሰን ውስጥ ዳኞቹ አንድም፣ ሁለትም፣ ሦስትም ዓመት ቢወስኑ ልዩነቱ የተጋነነ አይሆንም፡፡ እንደ ድሮው ከሦስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት ተብሎ እጅግ የተጋነነ ልዩነት ያለው ቅጣት መጣል ቀርቷል፡፡

ይህ ብቻም ሳይሆን የዳኞቹ የቅጣት አሰጣት መንገድም ቢሆን የቅጣት አሰጣጡን ሊያለያየው ይችላል፡፡ ዓቃቤ ሕጎችና ዳኞች በምን መንገድ ክሱ ታይቶ ለፍርድ መብቃት እንዳለበት ይወስናሉ፡፡ ለምሳሌ የባህር ዳሩ የሕፃን ሔቨን ጉዳይ በግፍ ግድያና በአስገድዶ መድፈርም ነበር የቀረበው፡፡ ነገር ግን የግፍ ግድያ ሳይሆን አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ብቻ ነው ብይን ያገኘው፡፡ አስገድዶ መድፈር ደግሞ መደበኛ ዕድሜ ላይ ያለ ሰው ከሆነ ከ15 ዓመት ጀምሮ ይባልና የወንጀሉ ሁኔታ ሕፃን ከሆነ እየተባለ እስከ 25 ዓመት ነው ሊያስፈርድ የሚችለው፡፡ አስገድዶ መድፈሩ ሞት ካስከተለ ዕድሜ ይፍታ ይባልና ያው 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ነው የሚቀጣው፡፡ ጉዳዩን የያዙት ሰዎች ልጅቷ እየተደፈረች ነው የሞተችው? ወይስ ከተደፈረች በኋላ ነው የሞተችው? የሚለውን መመርመራቸውም አይቀርም፡፡ ከተደፈረች በኋላ እንዳይታወቅበት ከሆነ የገደላት ግድያው ራሱን በቻለ ሌላ የግድያ ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እየተደፈረች በትንፋሽ እጥረትና በጉዳት ከሆነ የሞተችው ጉዳዩ ተለይቶ፣ በግድያ ወንጀል የሚፈረድበት ሁኔታን ሕጉ አያስቀምጥም፡፡ ይህን የሕግ አሠራር በጥልቀት የመመርመር ጉዳይ ጉዳዩን ለያዙት የሕግ ባለሙያዎች የሚተው ነው፡፡ በፍርድ ቤት ዳኞችም ሆነ ዓቃብያነ ሕጎች ጥፋተኛን ለማስቀጣት የሚሞክሩት የሚመጣላቸውን መረጃና ማስረጃ ተመልክተው ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የቀረቡ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ከሕጉ ጋር አገናዝበው ተገቢ ፍርድ ለመስጠት ካልቻሉ፣ የሚወስኑት ቅጣት አግባብነት ጥያቄ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ አንዳንዴ የምንሰማቸው ወንጀሎች እጅግ የሚሰቀጥጡ ቢሆኑም ነገር ግን ደግሞ ተፈረደ በሚባለው ውሳኔ የሚያከራክር ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ብዙ ሰዎች የባህር ዳሩን ጉዳይ ሲሰሙ ሰውዬው ይገደል እስከ ማለት የደረሰ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኞቹ ብዙ ነገር አገናዝበውና የነበረውን መረጃና ማስረጃ አቀራረብ በጥልቀት መርምረው ውሳኔውን እንደሰጡ መገመት ይቻላል፡፡ ጉዳዩ ለጥቅምት 21 በይግባኝ ላይ ያለ በመሆኑ ብዙ የምንለው ነገር ባይኖርም፣ ሆኖም ዳኞች በዚህም ሆነ በሌሎች ኬዞች ላይ ፍርድ የሚሰጡት የቀረበላቸውን ተጨባጭ ማስረጃና መረጃ አገናዝበው ሕጉንም በጥልቀት ፈትሸው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይህን ሳያሟላ ፍርድ ከሰጡ በቅጣቱ አወሳሰን ላይ ሁሌም ለክርክር የሚጋብዝ ነገር መፈጠሩ አይቀርም፡፡

ሪፖርተር፡- የአውሮፕላኑ አምባጓሮ ወይም የእነ ጆን ዳንኤል ጉዳይ በጣም ተጋኖ መቅረቡን አንዳንዶች ይናገራሉ፡፡ ልጆቹ የፈጸሙት ጥፋት መኖሩን፣ የአቪዬሽን ሕግ መጣሳቸውንም ሆነ ጥፋት መሆኑን ቢስማሙበትም፣ የሽብር ወንጀል ክስ ድረስ ጉዳዩ መሄዱ ግን እያከራከረ ነው፡፡ ስለዚህ ምን ይላሉ?

አቶ አንዷለም፡- ይህ በግሌ አልተመቸኝም፡፡ በራሴ ማኅበራዊ ገጽ ላይም ይህንኑ አመልክቼያለሁ፡፡ በግሌ አምባገነንነትን ሕግን ለማጥቂያ መሣሪያነት የሚጠቀም ብለን ስናወግዘው የነበረው የቀደመው መንግሥት አካሄድ ዳግም እንዳይከሰት ሥጋት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁሉም ሰው ለመፍረድ በተመቸ ሁኔታ በቀጥታ ሥርጭት በኢንተርኔት እየተሠራጨ የተፈጸመ ወንጀል ነው፡፡ ጉዳዩ ወንጀልነቱ አያጠራጥርም፡፡ ወደ 27 ሺሕ ሰዎች በቀጥታ በሚከታተሉት ቪዲዮ ሲጀመር ጀምሮ ወንጀሉ እንዴት እንደተፈጸመ ሁሉም ተመልክቶታል፡፡ በዓይናችን ያየነውንና ዛሬም መልሰን ማየት የምንችለውን ይህንን የወንጀል ድርጊት መንግሥት ሽብር ነው የሚለን ከሆነ፣ ነገ ትክክለኛው የሽብር ወንጀል መፈጸሙን ቢነግረን አናምነውም ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተመርምሮ ሽብር ካለውና ያላስተዋልነው ነገር ካለ መንግሥት ሊያሳውቀን ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዳየነው ልጆቹ አውሮፕላኑ የአየር ጭጋግ ተፈጥሮ በረራው ይሰረዛል እንደሚባል አያውቁም፡፡ በቪዲዮው ላይ ኧረ እንውረድ ምን ችግር አለው እያሉ ሲያወሩም እኮ ይደመጣሉ፡፡ ራሱ ጆን ዳንኤል የአውሮፕላኑ ችግር አይደለም ሰዎቹ የሚናገሩት ነገር ነው የሚያበሳጨኝ እያለ ሲያወራም ይደመጣል፡፡ ይህን ሁሉ ያየ ፖሊስ ከጥፋት ኃይሎች ተልዕኮ በመቀበልና ምናምን የሚል ከባድ የሽብር ክስ የሚከስ ከሆነ፣ ከቀደመው የኢሕአዴግ ዘመን አካሄድ በምን ተለየ የሚያስብል ነው የሚሆነው፡፡ ድሮ በየዴስኩ የሚገኝ ማስረጃን ይዞ ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድና በሽብር ወንጀል ለመሰማራት የሚል ክስ መመሥረት ተለምዶ ነበር፡፡ ቀንና የሰዎች ስም ብቻ እየተቀያየረ በሽብር መወንጀል አንዱ የፖለቲካ ማሸማቀቂያ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ ሥርጭት የተላለፈ ወንጀልን እንዲህ ብሎ መፈረጁ ትንሽ ያልተጠበቀና የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ የበረራ ሕጎችን በተመለከተ ግን የተፈጸመው ጥፋት በብዙዎቹ ሕጎች ከበድ ያለ ወንጀል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሕጎችን ጨምሮ በወንጀል ሕጉ እንደተመለከተው ጥፋቱ ከበድ ያለ ቅጣት ያለው ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለአንድ ሥራ ኃላፊነት የተሰጠውን ባለሥልጣን አካል አልታዘዝም ማለት ከሰባት እስከ 12 ዓመታት የሚያስቀጣ ጥፋት እንደሆነ በሕጋችን ተቀምጧል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የእነ ጆን ዳንኤል ጉዳይን በተመለከተ ኅብረተሰቡ እየሰጠው ያለው አስተያየትም ሆነ መንግሥት ጉዳዩን የያዘበት መንገድ የተጋነነ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕግ ስለተያዘ ወይም በፍርድ ሒደት ላይ ስላለ አንድ ጉዳይ መገናኛ ብዙኃንም ሆነ ኅብረተሰቡ አስተያየት መስጠት የሚችሉበት መንገድ ምን ድረስ የተገደበ ነው? አንድ ጉዳይ በሕግ የተያዘ ነው ሲባል የመነጋገሪያ ድንበሩ የት ድረስ መሆን አለበት? ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሆነ ነገር በተፈጠረ ቁጥር በማኅበራዊ ሚዲያ መንደር ከፍተኛ የደቦ ፍርድና ቅስቀሳ ሲደረግም ይታያል፡፡ ይህንን እንዴት ነው ማረቅ የሚቻለውስ?

አቶ አንዷለም፡- ይህ ነገር ሁሌም የሚያከራክር ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን የፍርድ ሒደቶችን የመዘገብ መብት አላቸው፡፡ ሲዘግቡ ግን ጥሬ ሀቁን ይዘው እንጂ አስተያየት መስጠት አይችሉም፡፡ በዛሬው ዕለት ይህን መሰል ጉዳይ ቀረበ፣ ፍርድ ቤቱም ይህን ውሳኔ ሰጠ ብሎ መዘገብ መብት ነው፡፡ ሆኖም የሞት ፍርድ ይገባው ነበር ብሎ የግል አስተያየትን ስለሒደቱ መጨመር አይቻልም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ለፕሬስ መሠረት የሆነው የሐሳብ ነፃነት መብት ተደንግጓል፡፡ ይህ መብት በተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ነው ገደብ የሚደረግበት፡፡ ግለሰባዊ መብትን በሚጋፋ መንገድ ስለሰዎች መዘገብ ለምሳሌ አይቻልም፡፡ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን መዘገብ መብት ነው፡፡ የዳኞችን ውሳኔ አሰጣጥ በሚያዛባ መንገድ መዘገብ ግን አይቻልም፡፡ ይህ ከፍርድ ቤት መዳፈር ጋርም ሊያያዝ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ ፍርድ ቤት አንድ ጉዳይን መዘገብ አይቻልም ብሎ መወሰን ይችላል፡፡ በዝግ ሒደቱን ሊከታተል ይችላል፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህም ብቻም አይደለም በተለየ ሁኔታ ዘግቡ ብሎ አንድን ጉዳይ እንዲዘገብ ማስገደድ ይችላሉ፡፡ ኢቲቪን ይህን ዘግብ ለሌላ ሰው ትምህርት እንዲሆን እፈልጋለሁ ብሎ ማስገደድ ይቻላል፡፡ ሰሞኑን በባህር ዳሩ ጉዳይ ያየን እንደሆነ ግን በዳኞቹ፣ በጠበቆቹና በዓቃቤ ሕጎቹ ላይ ወደ ዛቻ የሚያመራ ዘመቻ ጭምር ነው በማኅበራዊ ሚዲያ የተከፈተው፡፡ በግሌ ይግባኙን የሚሰሙት ዳኞች ያሳዝኑኛል፡፡ የፈለገውን ዓይነት ማስረጃ ቢመጣላቸው ሕዝቡ በጣም ጫና ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ሰው ነግ በእኔ የሚለውን ነገር እየረሳ ነው ያለው፡፡ ነገ የእሱ ቤተሰብ ቢደርስበትና ባላደረገው ነገር ቢከሰስ የሚፈጠረውን ነገር ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ አየር መንገድ ተነካ ብለን ሰዎቹ ይቆረጡ ይፈለጡ እያልን ነው፡፡ ይህ እጅግ አስገራሚ ከሰሞኑ እያየን ያለነው ማኅበራዊ ጠባይ ነው፡፡ የመንግሥት ሰዎችና ተቋማትም ይህንኑ ማኅበራዊ መገናኛ የሚመራው ስሜታዊ መስተጋብር እየተከተሉ በሚመስል ሁኔታ ምላሽ መስጠታቸው አዲስ ዓይነት ልምምድ ነው፡፡ ነገሩ ወዴት እየሄድን ነው የሚያሰኝ ነው፡፡